በኤልያስ እሸቱ ውልደቱ በአዲስ አበባ መስካዬሕዙናን መድሐኒያለም ከዛሬ 68 ዓመት ገደማ ነበር። አባታቸው አቶ ለማ እጅግ ሲበዛ ፀሎት የሚወዱ የዓለማዊ ነገር የማይወዱ በቀያቸውና በመንደራቸው አንቱ የተባሉና ሰው አክባሪ አዛውንት ነበሩ ። የሁለተኛ ደርጃ ትምህርቱን በተፈሪ መኮንን አጠናቋል። ለጋሽ ተስፋዬ ስድስት ኪሎ አካባቢ በተለይ የጥምቀት በዓል በጃን ሜዳ የነበሩት ልዩ ልዩ ትይንቶች፣ ጭፈራዎቸ፣ ዘፈኖች ከህሊናው መቼም ቢሆን እንደማይወጣ ያወሳል። ልቡ ወደ ወደደውና ቀልቡ ወደ ጠራው ሞያ ለመቀላቀል እንደ መንደርደሪያ ስሜቱን የሳቡት በተፈሪ መኮንን ከበሮና ትራንፔት የሚጫወቱ በተለይ በዛን ሰዓት በሚያዚያ 7 እና ሀምሌ 16 በዓላት ላይ ቀይ ካባ፣ ሰማያዊ ከረባትና ነጭ ሱሪ ለብሰው የተለያዩ ማራኪ ትይንቶችን የሚያቀርቡ ሰልፈኞችን ሲመለከት እነርሱን መሆን አለብኝ ብሎ ይነሳል። በኋላም በቤት ውስጥ ልጅ ተስፋዬ ጡሩንባ ሲነፋ አባት ያስተውሉና ከመጠን በላይ አዝነው ልጃቸውን ይቀጣሉ። ከቅጣቱ ጋር ተያይዞ በኢትዮጵያ ሪድዮ ጠዋት ፀሎት ከተሰማ በኋላ ልጃቸው ዘፈን እንዳያዳምጥ ይዘጉበት ጀመር። ልጅ ተስፋዬ ግን የጎረቤት አጥር ስር ጆሮውን እየለጠፈ ስሜቱን በከፊል ያስደስት ነበር። በተለይ የክቡር ዘበኛ የሙዚቃ ክፍል፣ የሰልፈኛ ሙዚቃ የሚያሰሙዋቸው ልዩ ልዩ ሙዚቃዎች ልጅ ተስፋዬን በጣም እየማረከው ስለመጣ በየአደባባዩ ከነሱ ጋር እየተከተላቸው አብሮ መንፈሱን ያስደስት ነበር። በዘመኑ በተለይ እነ ጥላሁን ገሰሰ፣ እሳቱ ተሰማ፣ ተፈራ ካሳ እና ተዘራ ሀይለሚካኤል ታይቶ በማይታወቅ መንገድ በሙዚቃቸው የህዝቡን የሙዚቃ ስሜት ለውጠው ነበር። አርቲስት ተስፋዬ ይህን የህዝቡን ስሜት ሲያስተውል የተለያዩ ግጥሞችን መግጠም ራሱን በደንብ ካሰለጠነ በኋላ በኢትዮጵያ ኪነጥበብ ት/ቤት በ1960 ዓ.ም በአርቲስት ተስፋዬ ገሰሰ አማካኝነት ለመጀመሪያ ጊዜ በ50 ብር ደመወዝ ተቀጠረ። በዚያም እያለ በርካታ ሞያተኞችን ከስር ጀምሮ እየኮተኮተ ለፍሬ ለማድረስ በቅቷል። የራስ ቲያትር ስራ አስኪያጅ፣ የአዲስ አበባ የባህል ማዕከል መስራች በመሆን ለብዙ ዓመት አገልግሏል። በተጨማሪም ከመደበኛ ስራው ሌላ ለዶ/ር (አርቲስት) ጥላሁን ገሰሰ ከ10 በላይ ድርሰቶች፣ ለድምፃዊ ማህሙድ አሕመድ፣ ለድምፃዊ መልካሙ ተበጀ፣ በአዲስ አበባ ፣ማዘጋጃ ቤት ለአርቲስት ፋንቱ ማንዶዬ እንዲሁም ለድምፃዊት ሒሩት በቀለ፣ ለድምፃዊት ብዙነሽ በቀለና ለተለያዩ አርቲስቶች ስራዎቹን አበርክቷል። በራስ ቲያትር በነበረበት ወቅት በጣም ዕውቅ የሙዚቃ ሰዎችን ለአብነት ያህል ድምፃዊ ንዋይ ደበበን፣ ፀሐዬ ዮሀንስን፣ ኤልያስ ተባባልን፤ ሻምበል በላይነህንና ሰለሞን ተካልኝን የመሳሰሉትን ዕውቅ ድምፃዊያን አፍርቷል። ይህ አንጋፋ የጥበብ ሰው ለሙያዉ ባለዉ ፍቅርና አክብሮት የበኩሉን አስተዋጾ ሲያደርግ ለራሱ ሳይሆን የኖረው ለባህላችን፣ ለሙዚቃችንና ለቅርሳችን ነው። በዘርፉም ከ45 ዓመት በላይ አገልግሏል። ለዚህ አንጋፋ ሰው የባህላችን አምባሳደር የሚለው መገለጫ እጅግ ያንሰዋል። ዛሬ ጋሽ ተስፋዬ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ታሪክ ላይ የተመሰረተ መጽሐፍ ለማሳተም ደፋ ቀና በሚልበት ወቅት ነው። ይህ አንጋፋ የባህል አምባሳደር በህመም ምክንያት ነርሲንግ ሆም ከገባ 12 ዓመት ነበር።ዛሬ በሞት የተለየንን አርቲስት ተስፋዬ ለማን ለማስታወስ ከ2 ዓመት በፊት ይሁኔ በላይ በዋሽንግተን ዲሲ አካባቢ ከሚያሳትመው ባውዛ ጋዜጣ ያገኘነውን ቃለ ምልልስ እናካፍላችሁ። ቃለ ምልልሱ ስለ ተስፋዬ ለማ ብዙ መረጃዎችን ያቃምስዎታል።
ባውዛ፤- በኪነጥበብ ትያትር ቤት ከተቀጠርህ በኋላ ምን ምን ዋና ዋና ነገሮችን አከናወንክ? ጋሽ ተስፋዬ፤- በገባሁ በጥቂት ጊዜያት ውስጥ በርከት ያሉና አዳዲስ ግጥሞችንና ዜማዎች በመድረስ ለነ ጌታመሳይ አበበ፣ ፀሃይ እንዳለ፣ ዘሪሁን በቀለና ከበደ ወልደማርያም ከዚህ በፊት ተሰምተውና ታይተው የማይታወቁ አዳዲስ ስራዎችን ደርሼ ስሰጥ በጣም እየተደነቅሁና እየተወደድኩ መጣሁ። በኋላም የኦርኬስትራ ኢትዮጵያ ከድሮው የበለጠ በጣም እየተወደደ መጣ። ባውዛ፤- በወቅቱ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በበጀት ማነስ ምክንያት ኦርኬስትራውን ማሰናበቱ ይታወቃል። ከስንብት በኋላስ የኦርኬስትራውና የአባላቱ እጣ ፈንታ ምን ደረሰ? ጋሽ ተስፋዬ፤- የሚገርምህ ሺ ሰማንያ የሚባል አካባቢ በግሌ ቤት ተከራይቼና ለሰላሳ ሰው ደመወዝ እየከፈልኩ ኦርኬስትራውን እያለማመድኩ ልዩ ልዩ የሰርግና የቱሪስት ጥሪዎችንና የተለያዩ ዝግጅቶችን እያዘጋጀን እስከ ደርግ መምጫ ጊዜ አቆየሁት። የደርግ መንግስት እንደመጣ “ይህ የሙዚቃ ቡድን በግሉ ብዙ ጥረት አድርጓል አሁን ተረከቡኝ” ብዬ ጥያቄ አቀረብኩ። በኋላም የወታደራዊው መንግስት ሙዚቀኞቹን ወደ አዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ትያትርና ባህል አዳራሽ ንዲዛወሩ አደረገ። ባውዛ፤- ለሰላሳ ሰዎች ደመወዝ መክፈል አይከብድም ነበር?። ጋሽ ተስፋዬ፤- (ፈገግ) በዛን ሰዓት እድሜዬ 19 ዓመት ነበር። ደመወዝ መክፈል ላልከው። እንኳን የሰላሳ ሰው ደመወዝ ይቅርና አንድ ሰው አንድ ቤተሰብ ለማስተዳደር ቀላል አልነበረም። እኔ ግን በዛን ዘመን ወጣት ብሆንም በወጣትነት የሚደረጉ ማንኛውንም ነገሮች እርግፍ አድርጌ ትቼ ነው እንደሽማግሌ ሆኜ ይህን ሀላፊነት የወሰድኩት። በዛ ሙዚቃ ቡድን ውስጥ የስልሳና የሰባ ዓመት ዕድሜ ያላቸው አዛውንቶች ነበሩ። የነሱ ህይወት ያስጨንቀኝ ነበር። ኑሮአቸው እንዳይበላሽ በሀይል መስራት ይጠበቅብኝ ነበር። እግዚአብሔርም ስለረዳኝ የኔም የሙዚቃ ስራዎች እየተወደዱና እየተደነቁ መምጣታቸው ነው። ችግሩን የተቋቋምኩት። ኦርኬስትራው በዘመኑ በጣም የተወደደ ነበር። አብዛኛው የሰርግ ጥሪ ለኛ የቴአትር ቡድን ነዉ የሚሰጠው። ቱሪስቶች በፈለጉበት ጊዜ የሚያገኙት የኛን የሙዚቃ ቡድን ነው። የቀዳማዊ ሐይለስላሴ ትያትርና የሀገርፍቅር ቲያትር ቤት የመንግስት ስለነበሩ ብዙ ቢሮክራሲ ነበራቸው። የምግብ ችግር አልነበረም። በስምንትና በዘጠኝ ብር በግ ተገዝቶ ቆዳው አምስትና አራት ብር ተመልሶ የሚሸጥበትና ሰውም ተሳስቦ የሚኖርበት፣ ዘመን ነበር ባውዛ፤- የአንተ የሙዚቃ ልምድ ከምን የመነጨ ነበር? የሙዚቃ ትምህርትስ እንዴት ነው ? ጋሽ ተስፋዬ፤- በርግጥ በተፈሪ መኮንን እስከ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ድረስ ተምሬያለሁ። ዋናው እኔ ሙዚቃ የተማርኩት በኦርኬስትራ ኢትዮጵያ አዛወንቶች የጥንቱን ሙዚቃ ከሚያውቁትና በአሜሪካ በኢንዲያና ዩኒቨርስቲ አንድ አመት ተኩል ቆይቻለሁ። የኔ ዋናው ልምዴ ግን ከኢትዮጵያዉያን የመነጨ ነው። የምሰራውም የኢትዮጵያን ሙዚቃን ነው። ዋናው ነገር ሀገር ውስጥ ያሉትን የሙዚቃ ልምዶች በጥልቀት ማወቅና ማጥናት ነበረብኝ። ባውዛ፤- የህዝብ ለህዝብ እንቅስቃሴ ምን ይመስል ነበር? የት የትስ ሀገሮች ተዟዙራችሁ ስራችሁን ለማቅረብ ቻላችሁ ? ምን ያህል ጊዜስ ፈጀባችሁ? ጋሽ ተስፋዬ፤- በምስራቅና በምዕራብ አውሮፓ፣ በካናዳ፣ በአሜሪካም ጭምር ነበር። በርግጥ እኔ እስከ መጨረሻው አብሬያቸው አልነበርኩም። ህዝብ ለህዝብ አሜሪካ ሲደርስ ነው የቀረሁት ጠቅላላ ዝግጅታቸውን አጠናቀው ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ወደ ሁለት ወር ገደማ ሳይፈጅባቸው አልቀረም። ባውዛ፤- አንተ አሜሪካን ስትደርስ እንዴት ልትቀር ቻልክ?
ተስፋዬ፤- እኔ በደርግ መንግስት አመራር የማልስማማ ሰው ነበርኩ። ያን አይነት ፖለቲካ ከኔ ተፈጥሮና ልምድ ጋር የማይሔድ ነው። ያንን መንግስት በመቃወም አንዳንድ የፖለቲካ ሙዚቃዎች ደርሼ ነበር። በዚህም ምክንያት ከአንድም ሁለት ሶስቴ ታስሬ ነበር። እናም ኑሮዬ በሙሉ በስጋትና በመጨነቅ ነበር የምኖረው። በሰላም እኖር ስላልነበር ከፍተኛ ጥላቻ ነበረኝ። በዚህ ምክንያት ነበር የቀረሁት።
ባውዛ፤- የራስ ቴአትር ስራ አስኪያጅ በነበርክበት ወቅት በጣም እውቅ እውቅ የሙዚቃ ሰዎችን አፍርተሀል። ለአብነት ያህል ድምፃዊ ነዋይ ደበበን፣ ድምፃዊ ፀሃዬ ዩሐንስን፣ ድምፃዊ ኤልያስ ተባበልን ድምፃዊ ሻምበል በላይነህን፣ ድምፃዊ ሰለሞን ተካልኝንና ሌሎችንም በማፍራት የተደራጀ ቡድን መፍጠርህ ይታወቃል። በወቅቱ የነበረው የሙዚቃው እንቅስቃሴና እድገት ምን ይመስል ነበር? የምትፈልገውንስ ያህል ተንቀሳቅሰናል በሙሉ ሃይላችን ሰርተናል ብለህ ታምናለህ? ምትፈልጋቸውንስ የሙዚቃ ሰዎች አግኝተሀል? ጋሽ ተስፋዬ፤- በወቅቱ የኔ አላማ በጣም የተለየ ነበር። በዛን ዘመን የባህል ሚኒስቴር የነበሩትን ዶ/ር ኃይሌ ወልደሚካኤልን ሳስፈቅድ በየቤሔረሰቡ በየሀገር ቤታችው ወይም በመንደራቸው ታሪክና ባህል መሰረት የአሰልጣኝ ቡድን ለማፍራት ነበር። ግን የደርግ መንግስት በዛን ዘመን ይፈልግ የነበረው ለፕሮፓጋንዳ ሶሻሊዝምን ለማስፋፋት እንጂ የብሔረሰብን ባህል እንዲጠናከር አይደለም ብሎ አከሸፈብን። ያው እነሱ እንደሚፈልጉት ዝነኛ ድምፃዊያንን ማውጣት ላይ አዘነበልኩ። ባውዛ፤- የግል ህይወትህን በማመቻቸቱ በኩልስ ምን ስራዎች የሰራኸው አለ? ጋሽ ተስፋዬ፤- እኔ ከ19 ዓመቴ ጀምሮ ከሰላሳ በላይ ሰዎች ሀላፊ ሆኜ እላይ እታች የምል ሰው ይህን የሞያ ጉዞዬን እ ን ዳ ያ ደ ና ቀ ፍ ብ ኝ የራሴን ህይወት በማመቻቸቱ በኩል ብዙ አልሰራሁም። ባውዛ፤- በሞያህ ለስንት ዓመት ያህል ለዘርፍ አስትዋፆኦ አድርገሀል ማለት ነው? ጋሽ ተስፋዬ፤- አሁን 65 ዓመቴን ይዣልሁ። እዚህ አሜሪካ ሀገር 20 ዓመት ሆኖኛል። በኢትዮጵያ ከ19 ዓመት እስክ 45 ዓመት ድረስ ሰርቻለሁ። በዚህ በአሜሪካም እስከ ታመምኩበት ጊዜ ድረስ በተለያዩ ዘርፎች ተንቀሳቅሻለሁ። ባውዛ፤- በወቅቱ እነዚህ ነግሮች ተሟልተውልኝ ቢሆን ኖሮ ለዘርፉ እድገት ይበልጥ እሰራ ነበር ብለህ የሚቆጭህ ነገር አለ? ጋሽ ተስፋዬ፤- ወደ ኢትዮጵያ ታሪክ የተመለስን እንደሆነ ከትላንት ወዲያ የንጉስ ዘመን ነበር፣ ትላንት የፋሺስት ዘመን ነበር። በዚህ ጊዜ ውስጥ ብዙ ነገር መጠበቅ አይቻልም። አንድ ሀገር በጣም ትልቅ ነገር የሚፈጥረው በዲሞክራሲና በነፃነት ሲሰራ ነው። ከአርቲስቱም ትልቅ ነገር መጠበቅ አይቻልም። ያለፋት የንጉሱና የደርግ ዘመን ምቹ አልነበሩም። በተገኘው ቀዳዳ የተቻለውን ነገር ከተሰራ በቂ ነው። የደርጉንም የንጉሱንም ዘመን ሁላችንም ያለፍንበትና የምናውቀው ነው። ወደፊት የኢትዮጵያ ህዝብ በዚህ እንደ አሜሪካናሌሎች ሀገሮች እንደሚያድግ ጥርጥር የለኝም። ባውዛ፤- ብዙዎቹ የሙያ ልጆችህ በየአጋጣሚው ስላንተ ተናግረውና አውርተው አይጠግቡም ይህ ከምን የመነጨ ይመስልሀል? ጋሽ ተስፋዬ፤- ብዙ ጊዜ አብሬያቸው ከምሰራቸው በእድሜ ከገፉ አዛውንቶችም ሆነ ወጣቶች ጋር እንደቤተዘመድ ሆነን ነው እንጂ እንደ አሰሪና ሰራተኛ አይደለንም። በተለይ ለወጣቶቹ በጥሩ ስነምግባር እንዲኖሩ የህይወትም ትምህርት ጭምር ነው የምሰጣቸው። ሁሉንም እወዳቸዋለሁ እነሱም ይወዱኛል። ስንለያይም በመነፋፈቅ እንጂ በጥላቻ አይደለም። እኔም ለረጅም ዘመን ካገለገልኩ በሁዋላ ኢትዮጵያ ውስጥ መታሰሩ ስጋቱና ጭንቀቱ ስላስቸገረኝ ከንግዲህ ወዲህ ይህን ወደማላይበት ሀገር መሰደድ አለብኝ ብዬ ነው የወስንኩት። አብሬ የሰራዋቸውም ሆነ ያልሰራዋቸው ስለኔጥሩ እንጂ መጥፎ አስተያየት የላቸውም። እግዛብሔር ይህን ሁሉ ለኔ ስላደረገልኝ በጣም ነው የማመሰግነው። ባውዛ፤- በወጣትነት ዘመን ሙዚቃ መድረስን እንዴት ታየዋልህ? ጋሽ ተስፋዬ፤- (ፈገግ) እኔ የሚገርምህ በዛን ሰዓት ሙዚቃ መድረስ እንደቀላል ጨዋታ ነበር የማየው። አንዳንድ ጊዜ በቀን አራት አምስት ሙዚቃዎችን የምደርስበት ጊዜ ነበር። በተለይ ሰው የሚወደውና የሚደመጥ ሙዚቃ መስራት ለኔ በጣም ቀላል ነበር። አሁን እያረጀሁ ስመጣ እየደከምኩ መጣሁ እንጂ (ሳቅ..) እራሴም የሚገርመኝ በዛን ወቅት የራስ ቲያትር ስራ አስኪያጅ ነበርኩ፣ በዚያ ላይ ሙዚቃው ጥሩ ጥራት እንዲኖረው ድርሰት የምደርሰው እራሴ ነኝ፣ ራሴ ከምሰራበት መስሪያ ቤት አልፌ ለሌሎች መስሪያ ቤት እሰራ ነበር። የአዲስ አበባ የባህል ማዕከልንም መስርቼ የነዛን ሁሉ ድርሰት የምሰጠው እኔ ነበርኩ በአንድ ጊዜ ሶስት አራት ቦታዎችም እሰራ ነበር። ባውዛ፤- ጋሽ ተስፋዬ፤ ሀገርን ጥሎ በሰው ሀገር ስደትን ለምን መረጥክ? ጋሽ ተስፋዬ፤- በኔ ልምድ በቀዳማዊ ሀይለስላሴና በደርግ ጊዜ ኖሪያለሁ እንደ ደርግ ጊዜ መጥፎ ሕይወት ኖሬ አላውቅም። የመሰደዴም ዋና ምክንያት ይህ ነው። በጃንሆይ ጊዜ ታስሬ አላውቅም በደርግ ጊዜ ግን ሶስት ጊዜ ታስሬያለሁ። እኔ ብቻ ሳልሆን በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ሰዎች ተሰደዋል። የዚህ ዋናው ምክንያት አገሪቷ በጥቂት ስልጣን ወዳዶችና ለሀገር ፍቅር በሌላቸው ሰዎች እጅ በመግባቷ ነው። ስደት መለመድ የለበትም። አንድ ህዝብ በሀገሩ በነፃነት በመስራት፣ መኖር፣ መክበርና መጠቀም አለበት እንጂ ሀገሩን ለቆ መሔድ የለበትም። ወደፊት በመጪው ትውልድ ላይ ይህ እንደሚታረም ተስፋ አለኝ። ባውዛ፤- አሜሪካ ከመቼ ጀምረህ ነው የቀረኸው? በዚህ ጊዜ ውስጥ ምን ምን ነገሮችንስ ለመስራት ጥረት ታደርግ ነበር። ጋሽ ተስፋዬ፤- እ ኤ አ 1997 በአራተኛው ወር መጋቢት ውስጥ ነበር። በዋሽንግተንና አካባቢዋ ላለው የኢትዮጵያ ህዝብ እንቁጣጣሽን በዚህም ሀገር መልመድ አለባቸው ብዬ በማሰብ የተለያዩ ሙዚቀኞችን ከኒዮርክና ከሌሎች ሀገሮች በማስመጣት እንቁጣጣሽ በአሜሪካ በሚል ታላቅ የሙዚቃ ድግስ እያዘጋጀሁ ለህብረተሰቡ አስለመድኩ። በተጨማሪም ወደ ኢትዮጵያ በመሔድና በማስመጣት የሽመና፣ የእርሻ እና የሀይማኖት ዕቃዎች እንዲሁም ልዩ ልዩ የቤት ውስጥ መገልገያ ዕቃዎች፣ የተለያዩ አልባሳቶችና የሙዚቃ መሳሪያዎችን የያዘ ሙዜየም በአስራ አምስተኛው ጐዳና ላይ ከፍቼ ነበር። በዚህ በዋሽንግተን ዲሲ እንዲህ እንዲህ እያልኩ ስድስትና ሰባት ዓመት ካንቀሳቀስኩት በኃላ በእኔ መታመም ምክንያት ስራውን ላቋርጠው በቃሁ። እቃውን ወደ ኢትዮጵያ ኤምባሲ በመላክ ለዘጠኝ ዓመታት ተቀምጦ አሁን ቺካጐ የሚግኘው የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ተረክቦ ስራውን እንደገና ጀምረውታል። ሌላው ናይል እንሰምብል የሚባል የሙዚቃ ቡድን ከ164 በላይ ትርኢቶችን በተለያዩ ዩኒቨርስቲና ኮሌጆች ፊስቲቫሎች ላይ ያሳየው የነበረዉ ቡድንም በኔ መታመም ምክንያት ፕሮግራማቸውን አቋረጡ። ባውዛ፤- ይህን ሁሉ ነገር ስትሰራ አሜሪካን ሀገር እንዴት ተቀበልህ? ጋሽ ተስፋዬ፤- በእውነቱ ይህ ሀገር የሰው ልጅ ያሰበውን ሁሉ መፈፀም የሚችልበት ታላቅ ሀገር ነው። በዚህ አጭር ጊዜ ይህን ሁሉ መስራት የቻልኩት፣ በተለይ ሙዜየም ማቋቋም በሀገሬም ቢሆን የማይታሰብ ነው። ሌላው ለምሳሌ እንደህመሜ ከሆነ ኢትዮጵያ ብሆን ኖሮ የዛሬ 20 ዓመት ሞቼ ነበር። በቂ ህክምና የለም ኑሮም ከባድ ነው። እዚህ ሀገር ሁሉ ነገር በተሟላ ሁኔታ በነርሲንግ ሆም ጤንነቴ ምግቤን ሁሉን ነገር ሳይጓደልብኝ እየኖርኩ ነው። ለሀገሬ እና ለኢትዮጵያ ህዝብ የምመኘው እዚህ ሀገር የምናየውን አይነት ሰላም፣ ነፃነትና ዲሞክራሲ አገኝተው እንዲኖሩ ነው። ባውዛ፤- መጽሀፍ ለማሳተም የተለያዩ እንቅስታሴዎችን እያደረክ እንደሆነ ይታወቃል። መጽሀፉ ምን ምን ነገሮች ላይ ያተኩራል? እንዴትስ አሰብከው? ጋሽ ተስፋዬ፤- ሁላችሁም እንደምታውቁት ከዛሬ አስር ዓመት በፊት እንደማንኛውም ሰው የፈለኩበት ቦታ በእግሬም፣ በመኪናም እየነዳሁ እየተዘዋወርኩ እሰራ ነበር። በኋላ ባጋጠመኝ የኩላሊት ህመም ምክንያት ምንም መስራት አልቻልኩም። አሁን ባለሁበት ሁኔታ ምን ልሰራ እችላለሁ ብዬ ራሴን ስጠይቅ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ከ45 ዓመት በላይ ስላሳለፍኩ ያንን ልምዴን ለቀጣዩ ትውልድ ለማበርከት ተነሳሳሁ። መጽሀፍ በአብዛኛው በኢትዬጵያ ሙዚቃ ውስጥ ያለፉትንና በመሰማት ላይ ያሉትን ከአፄ ምኒልክ እስከ ደርግ ጊዜ ድረስ የኢትዬጵያ ሙዚቃ ምን እንደሚመስል የሚያሳይ ታሪክ ያለው መጽሀፍ ለመፃፍ እየሞከርኩ ነው። እንደሚታወቀው በሃይለስላሴ ዘመን ስለነገስታቱና ስለመኳንቱ ነው የሚፃፈው በደርግም ቢሆን ስለሶሻሊዝምና ለመሳሰሉት ነበር የሚፃፍ። በተለይ በዛን ወቅት ስለዘፋኝ እንፃፍ ቢባል ስንት ቁም ነገር እያለ ስለዘፋኝ እንፃፍ ትላላችሁ ነው የሚሉት። እኔ ለማዘጋጀት የማስበው መጽሀፍ ሙዚቀኞችና ድምፃውያን ስላደረጉት አስተዋፆኦ በታሪክ መልክ በዚህም ሀገር፣ በአውሮፓም በተለያዩ ላይብረሪ ውስጥ ተቀምጦ የልጅ ልጆቻችን ታሪካቸውን እንዲያውቁ ብዙ ይጠቅማቸዋል ብዬ አምናለሁ። ባውዛ፤- እንዲህ አይነት ታሪክ ያለው መጽሀፍ ስታዘጋጅ ታሪክ ከሚፃፍለት ህብረተሰብ ምን ምን እገዛዎችን ትፈልጋለህ። ጋሽ ተስፋዬ፤- ይህን መጽሀፍ ከጀመርኩት ሶስት ዓመት አልፎኛል። በዚህ ሀገር የተለያዩ መረጃዎችን ለማግኘት በጣም ቀላል ነው። እኛ ሀገር ግን በቃል እየተጠየቀ፣ የተለያዩ ፎቶግራፎችን መሰብሰብ ስለሆነ የተወሰነ ረዘም ያለ ጊዜ ሊወስድብኝ ይችላል። ወደፊት ስራው ተጠናቆ ወደማተሚያ ቤት ሲሔድ በተለይ ከሙዚቀኞችና ከድምፃዊያኑ እንዲሁም ከጥበብ ወዳጆች በሙሉ ድጋፍ ሊያስፈልገኝ ይችላል። እኔ ከእንግዲህ ወዲህ ከዚህ መጽሀፍ የማገኘው ጥቅም ወይም ዝና የለም። እኔ አብቅቻለሁ። በህይወት የምቆይበትም ጊዜ የተወሰነ ነው። እኔ በአሁኑ ሰዓት ለራሴ ለግሌ የምፈልገው፣ የጐደለብኝ ለምሳሌ የገንዘብ ችግር የለብም። ባውዛ፤- ሙዜየምን ስትከፍት እንቅስቃሴው ምን ይመስል ነበር። ኢትዮጵያውያን ጐብኝዎችን እንደጠበከው ታገኝ ነበር? አሁንስ ሙዜሙ የትደርሰ? ጋሽ ተስፋዬ፤- ከትላንት ወዲያ በንጉስ ትላንት በፋሺስት ስርዓት ውስጥ ሲኖር የዋለ ህብረተሰብ ለምን ሙዜየም መጐብኘት አላዳበርክም ብለን መዉቀስ አያስፈልግም። ፈረንጆችን የወሰድን እንደ ሆነ ከልጅነታችው ጀምረው ልምዱ ስላላቸው ከኛ ማህበረሰብ ይልቅ ፈረንጆቹ መጥተው ይጐበኛሉ። በአሁን ሰዓት በቺካጐ የሚገኝ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ በሃላፊነት ይህን ስራ ለመጀመር ደፋቀና እያለ ነው። ባውዛ፤- ከእለት እለት ህብረተሰባችን በተለያዩ ምክንያቶች ወደዚህ ሀገር በመምጣት ላይ ናቸው። ቁጥራቸው እጅግ እየበዛ መጥቷል። በዛን ዘመን እንኳን ህዝብ ለህዝብን የሚያክል ሀገርንም ህብረተሰብንም በጣም የሚጠቅም እንቅስቃሴ ተደርጐ ነበር። ስለ አሁኑ ትውልድ ምን የምትለው ነገር አለ። ጋሽ ተስፋዬ፤- የዛሬ 50 ዓመት ገደማ ቤተሰቦቼ ጋር ስኖር እነሱ ስላረጁ ያለም መጨረሻ ይመስላቸው ነበር። እኔም ደግሞ አሁን ሳረጅ እንደነሱ ማሰብ የለብኝም ዓለም ትቀጥላለች ከኛ የበላለጡ ታላላቅ ልጆች እንደሚፈጠሩ መገንዘብ አለብን። አንዳንድ ሰዎች እገሌን የሚያክል ሰው አይመጣም እየተባለ ይወራል። ይህ ስህተት ነው እግዚአብሔር አዋቂ ነው ሌላ ብዙ ብዙ ነገሮችን መፍጠር ይችላል። ለምሳሌ ጥላሁን አረፈ። ለኛ ባይሆንም ለአዲሱ ትውልድ የሚያስደስተው ነገር እንደ ድምፃዊ ቴድሮስ ካሳሁንና ሌሎችም አርቲስቶች እየተፈጠሩ ነው። እንዲህ እንዲህ ያለ ትውልድ በትውልድ ይቀጥላል። አዲስ ነገርም ይፈጠራል እንዳልከው በተለያየ መልክ ወደዚህ ሀገር የመጡትና በመምጣት ላይ ያሉት ብዙዎች ናቸው። አሜሪካን ሀገር መምጣት እንደ ስደት መቆጠር የለበትም። አሜሪካን ማለት ከሀገር የተሻለ ሌላ ሀገር እንደማግኘት ነው ላወቀበት። ስደቱ እግዚአብሔር ያመጣው ጥሩ ነገር ነው። ላወቀበትና ለተጠቀመበት ልጆቹን በጥሩ ሁኔታ እያስተማረ ነው። ራሱም በተለያዬ ዕውቀት እየተገነባ ነው። እናም ይህ ትውልድ በዚህ ሀገር ብዙ ነገር መጠቀም መቻል አለበት። በንጉሱ ጊዜ እኮ የመኳንትና የመሳፍንት ልጅ ያልሆነ ወደ ውጭ ሀገር አይመጣም ዛሬ ሙህሩ፣ ተማሪው፣ በግብርና ላይ ያለው የህብረተሰባችን ክፍል ሁሉ ሳይቀር ወደዚህ ሃገር እየመጣ ነው። በዚላይም ወደ ሀገሩ እየተመለሰ ዕውቀቱን፣ ገንዘቡን፣ እያፈሰሰ፣ አሮጌው ምሁር በአዲሱ ምሁር፣ አሮጌው ነጋዴ በአዲሱ ነጋዴ እየተቀየረ አለም የደረሰችበት ደረጃ ላይ ሀገርንም ማድረስ ይቻላል። ሁሉን ነገር በበጐ ነገር እየተረጐምን ትውልዱን መደገፍ ወደ ቀና አቅጣጫ መምራትና ድጋፍ ማድረግ ከኛ ይጠበቃል። ባውዛ፤- እስካሁን ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ። ጋሽ ተስፋዬ፤- እኔም እግዛብሔር ይስጥልኝ።__
ለተስፋዬ ለማ ነብሱን በገነት እንዲያኖራት፤ ለወዳጅ ዘመዶቹም መጽናናትን እንዲሰጣቸው ዘ-ሐበሻ ትመኛለች።