ሰኔ 2017 ዓ/ም
አምስት አመት ሊሞላኝ ትንሽ ሲቀረኝ መመለሴ ነው፡፡ ከተማዋን ያየኋት እንደ ብኩኑ ያገሬ አውቃለሁ ባይ፣ ስግብግብ፣ ጉረኛ፣ አስመሳይ፣ ራስ-ወዳድ ፈሪና ሆድ-አደር የሕብረተሰብ ክፍል (ልሂቅ፣ ምሁር፣ ዳያሰፖራ ወዘተ…) የተብለጨለጨውን ብቻ እያየሁ በመፍነክነክ አይደለም፡፡ ሁኔታዎችን በቅጡ ሳላጤን ጥቅሜን፣ ምቾቴንና ደስታዬን ብቻ በመፈለግ ራሴን አስንፌና ጭንቅላቴን ደፍኜ የወገኖቼ ሰቆቃና የሃገሬ ጉዳት አያገባኝም፣ እኔን አይመለከተኝም በማለትም አይደለም፡፡ ሥጋዊ ፍላጎቴን ለማርካት በመቅለብለብና በየመሸታ ቤቱ እየተራወጥኩ ቀፈቴን በመሙላት ለድሃው ያረረበትን እንጀራ ከአቅሜ በላይ በመጎስጎስና ሃገሪቱ ከድሃ ሕዝብ አፍ እየነጠቀች በውጭ ምንዛሪ በምታባክነው የአልኮል መጠጥና ሌላም ሌላም ጭንቅላቴን በማናወዝም አይደለም፡፡ ሳይለፉ በዘረፉት ያገር ሃብትና ከድሃው ሕዝብ በሚሰርቁት ገንዘብ ሕሊናቸው ናውዞ የበሉትን አስኪያሰመልሱ የሚዝናኑትን ጉዶች አሳፋሪ ትዕይንት ለዘመኑ ሰዎች ትቼ ከተማዋና ነዋሪዎቿ የሚገኙበትን አጠቃላይ ሁኔታ በአንክሮ ለማስተዋል ራሴን አንቅቼ ህሊናዬን ለሃቅ ተገዥ በማደረግና ስለ እውነት ለመመስከር ራሴን በማዘጋጀት ነው፡፡
አይኑን ለጨፈነና የሌላው ሰቆቃ ለማይሰማው ብኩን፣ ሆዳም፣ ዘረኛና አድር ባይ ይህች የብዙሃን ምስኪን ድሆች ከተማ ለማየት የሚፈልገውንና ለእሱ እንድትሆንለት የሚመኘውን ለመስጠት አትቦዝንም፡፡ ዶላሩን ይመንዝር እንጂ በሚፈልገው ሁኔታ ለማስተናገድ ወደ ኋላ አትልም፡፡ ከድሃ ሕዝብ የተመነተፈው ብርና አየተሰረቀ የተገኘው ዶላር እንደ ቅጠል ይነስነስ እንጂ ምግቡም፣ መጠጡም፣ ሌላ ሌላውም በገፍ ይቀርባል፡፡ ሕዝብ እየተበደለ! ሕዝብ መፈናፈኛ እያጣ! ሕዝብ በቁሙ አየሞተ! ሕዝብ መሠረታዊ ፍላጎቱን ማሟላት ተስኖት የሞት የሽረት ኑሮ እየኖረ! መዝናኛውም፣ ጭፈራውም፣ መጠጡም፣ ዝሙቱም፣ ጉራ የመንዛት እድሉም፣ ገንዘብና ስልጣን ካለ በተፈለገው መጠንና አይነት ይቸበቸባል፡፡ ልታይ ልታይ የሚያስብለውና ጉራ የሚያስነዛው፣ አይንን ጨፍኖ ከጥሩ በስተቀር መጥፎ አላየሁም የሚያስብለው የማዘናጊያና የማደናገሪያ ብልጭልጩ፣ ሁካታውና አስረሽ ምቺው አጓጊ ነው፡፡ ለደከመ፣ ለደነዘ፣ ለተስገበገበ፣ ተምሮ ላልተማረ ጭንቅላት!!!
ከተማዋ ውስጥ በጎ ጎኑና ለነዋሪው ሕዝብ ጠቃሚነቱ አሳማኝ ባልሆነ፣ በሚያጠራጥርና ስርዐት ባልተከለ ሁኔታ በተያዘው ‹‹የኮሪዶር ልማት›› መርሃ ግብር ግልጽ ለውጥ ይታያል፡፡ ነባር ሰፈሮች ያለ በቂ ጥናትና ውይይት እንዲሁም ሕዝባዊ ስምምነት፤ ያልተገደበ ማይምነት በፈጠረው እብሪት፣ ጥላቻና የበታችነት ስሜት እንዲፈርሱና ነዋሪዎቻቸውም እንዲፈናቀሉ እየተደረጉ ነው፡፡ ሥልጣን ልቡን ባሳበጠው አመራር ግብታዊ ውሳኔ እየተደመሰሱ በፓርኮች፣ በሳር፣ በልዩ ልዩ እፅዋትና በአንዳንድ ዘመናዊ ሕንፃዎች እየተተኩ ነው፡፡ የነዋሪዎችን ሰብዓዊና የዜግነት መብት ያላከበረ፣ ታሪክን ቅርስንና የሕብረተሰቡን የአኗኗር ዘይቤ ያላገናዘበ ውሳኔ የሕዝብን ድምፅ በማፈን ጭካኔና ቂም በቀል በተሞላው እብሪት እየተከናወነ ይገኛል፡፡ በተደመሰሱት ነባር ሰፈሮች ምትክ ከአብዛኛው የከተማዋ ሕዝብ ኑሮና የገቢ አቅም ጋር የማይመጣጠኑ ትላልቅ ቅንጡ ፕሮጀክቶች በየቦታው እንደኪንታሮት ብቅ ብቅ ብለው ይታያሉ፡፡ ድሆችና ነባር ነዋሪዎች ወደ ከተማዋ ዳርቻዎች ተወርውረው የድህነት ኑሯቸው ከፍቶ ሕይወታቸው ተመሰቃቅሏል፡፡
አንዳንድ አውራ ጎዳናዎች ከሚገባቸው በላይ ተለጥጠው ነባርና ታሪካዊ መንደሮችን እየደመሰሱ በመጓዝ ከሌሎች ሰፋፊ መንገዶች ጋር በተንጣለሉ፣ በተንቦረቀቁና አሽከርካሪዎችንና እግረኞችን ለማደናገር ሆነ ተብለው የተቀየሱ በሚመስሉ አደባባዮች አማካኝነት ይቀላቀላሉ፡፡ አሠራራቸው የሕብረተሰቡን የመጓጓዣና የመገናኛ ፍላጎቶችን ለሕዝቡ የአኗኗርና የአሰፋፈር ሁኔታ በሚያመች ሁኔታ ለማሟላት ሳይሆን አገሪቱን የሚመሩት ግለሰቦች የግል ፍላጎታቸውን ለማርካትና የዝቅተኝነት ስሜታቸውን ለማርገብ፣ ያበጠ ልባቸውን ለማኮፈስ የተጠነሰሱ ለመሆናቸው በተገልጋዩ ሕብረተሰብ ዘንድ ከሚታየው መደነባበር፣ የኑሮ መመሰቃቀል፣ መጨናነቅና አጠቃላይ ሥርዓት ያጣ የተሸከርካሪና የእግረኛ መተራመስ መገንዘብ ይቻላል፡፡ አብዛኛው የከተማዋ ነዋሪ እግረኛ በሆነበት ሁኔታ ለመኪናዎችና ለአሽከርካሪዎቻቸው እየተሰጠ ያለው ትኩረት በማይምናንና በቁንጽል እውቀት በሰከሩ እብሪተኞች እጅ የሕዝብ ንብረት በማይገባና ለሕዝብ በማይጠቅም፣ ዘለቄታነት በሌለው ሁኔታ እየባከነ እንደሆነ የሚያመላክት ነው፡፡
አዳዲሶቹ አውራ ጎዳናዎች በሰፊው ተቀይሰው፣ ከሚያስፈልገው በላይ ተንቦርቅቀው መልክዐ ምድሩን እንደጠባሳ እያበላሹና አየቀደዱ ድሆችንና አቅመ ደካሞችን እያፈናቀሉና መድረሻ እያሳጡ ወደሚቀጥለው መገናኛ ያመራሉ፡፡ በጥሩ ሁኔታ ፀድቀውና አድገው ጥላ ይሰጡ የነበሩ ነባር ዛፎችና እፅዋት እየተነቀሉና አየተቆረጡ እንዳንድ ቦታዎች ላይ በአበቦችና በመጤ ዘንባባዎች ሲተኩ፣ እንዳንድ ቦታዎች ላይ ደግሞ በሲሚንቶ በአስፋልትና በድንጋይ ተጠርዘው ለአይን የሚያታክቱና ለእግረኛ ተጠቃሚዎች ዝውውር ችግር እየፈጠሩ አቅመ ደካሞችን፣ ሕፃናትንና አካል የጎደላቸውን ግለሰቦች ሲያጉላሉ ይታያሉ፡፡ አቅመ ደካሞች፣ አካል ጉዳተኞችና ሕፃናት እነዚህን ጎዳናዎች ለማቋረጥ ችግር ሲገጥማቸው ማየት የተለመደ ነው፡፡ ትኩረቱ ማብለጭለጩ ላይ ስለሆነ ይህ ሁኔታ የሚያሳስበው አመራር እንደሌለ ከመተላለፊያዎቹ አሰራር ቅጥ ማጣትና መንቦርቀቅ እንዲሁም የሁሉንም ተገልጋዮች ፍላጎት ያላገናዘበ እቅድ አወጣጥ መረዳት ይቻላል፡፡
ባንፃሩ በትርኪ ምርኪ ማብለጭለጫዎች አሸብርቀውና ተንቆጥቁጠው ከፍተኛ ወጪ እየወጣባቸው የሚሠሩ አዳዲስ የተንጣለሉ አውራ ጎዳናዎች በያቅጣጫው በጥድፊያና መሠረታዊ ጥራትን ሳይጠብቁ የመሠራታቸውን ያህል፣ ነባር የውስጥ ለውስጥ መንገዶችና አገናኝ መተላለፊያዎች በጎርፍ የተነሳ እንዲሁም ወቅታዊ አድሳትና ጥገና በማጣታቸው ፈራርሰውና ተቦርቡረው ከጥቅም ውጭ ሆነው አገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እያወጣች የምታስገባቸው የግልም ሆኑ የመንግሥት እንዲሁም የድርጅት ተሸከርካሪዎች ያለጊዜያቸው እንዲሰበሩ ምክንያት ሲሆኑ ይታያል፡፡ ተገልጋዩን ሕብረተሰብም ለከፍተኛ መጉላላትና ለጊዜ መባከን ሲዳርጉ ይሰተዋላሉ፡፡ ከተማዋን አያለማን ነን የሚሉት ብኩን መሪ ነን ባዮች ግን ይህ ችግር የሚያሳስባቸው አይመስሉም፡፡ የነሱ ትኩረት ትልልቅ አውራ ጎዳናዎችን፣ ከሕዝቡ ኑሮ ጋር የማይመጣጠኑ ሰማይ ጠቀስ ሕንፃዎችንና አደባባዮችን ገንብተዋል መባልን እንጂ የሕዝብን መሠረታዊ ፍላጎት አሟልተው የኑሮን ጫና አቃልለዋል መባልን አይደለምና! በነሱ ደካማ አመለካከት እድገትና ስልጣኔ ቀፎ ፎቆች መደርደርና አውራ ጎዳናዎችን ማብለጭጭ ስለሚመስላቸው!!!
እንደ ታዘብኩት ከሆነ የሃገሪቱ መሪዎች በቅድሚያ ሃገሪቱና ሕዝቧ የሚያስፈልጓቸው ነገሮች ምንድናቸው ለሚለው ጥያቄ ደንታ ያላቸው አይመስሉም፡፡ ሕዝቡን አለቅጥ ንቀውታል፡፡ በዝቅተኝነትና በበቀል ስሜት ተገፋፍተው፣ ያንድን ብሔረሰብ ልሂቃን የቅዠት አላማ ለማሳካት ከእኛ ይለያል ብለው የሚያስቡትን የህብረተሰብ ክፍል በማሽማቀቅና በመናቅ ሲኮፈሱና ሲውተረተሩ ይታያሉ፡፡ የታሪክ አጋጣሚ የሰጣቸውን ኢትዮጵያን በቅንነት የመምራት እድል ሁሉንም በሚጠቅም መንፈስ ለመፈፀም የወደዱ አይመስሉም፡፡ ያለፉትን አስተዳደሮች እየወቀሱ በዝቅተኝነት፣ በበቀል ስሜትና በእብሪት ተገፋፍተው የዘመናዊ አስተዳደርን ቅደም ተከተሎችና ቅን ባለሙያዎችን ያሳተፉ የአሠራር ስልቶች ሳይከተሉ፣ ሕዝብንና ተጠቃሚውን ሳያማክሩ በግብታዊነት በሚወስኗቸው ውሳኔዎች ሃገርን ለእዳ ሲዳርጉ ሕዝብን ቁም ስቅል የሚያሳዩ ውሳኔዎችን ሲወስኑ ይስተዋላሉ፡፡ እነዚህ ክፉ መሪ ነን ባዮች የሰነፍና የምቀኛ ሥራ እየሠሩ ዘልቀዋል፡፡ የጥፋት ዘመቻቸውንም፣ ሊገዳደራቸው የሚገባው ልሂቅ ሳይማር ያስተማረውን ህዝብ እያዘናጋ ራሱ ሰንፎ አገር ስላሰነፈ ያለምንም ስጋት በእብሪት ቀጥለውበታል፡፡
ተማረ የሚባለው የሕብረተሰብ ክፍል የሁኔታውን ኢፍትሐዊነትና አጥፊነት አያየ በተራ ዱሩዬነት የሰለጠኑ አታላዮች አገሩን ሲያተራምሱት በቃ በማለት ፋንታ እነሱ ሙያ እናስተምርህ ሲሉት እየተንገላጀጀ ያዳምጣል፡፡ አገሪቱ የተማረ ሰው የሌላት ይመስል ልሂቁ በማይምነት የተወጠሩ መሪ ነን ባዮች እንደ ከብት ሲነዱት ያለምንም ጥያቄ ይነዳል፡፡ አይጠይቅም፣ አያጉረመርምም፣ አይንቀሳቀስም፡፡ ይህን በብልጽግናና በልማት ስም የተገነዘን የጥፋት ዘመቻ ለተመለከተ የሃገሪቱ ልሂቅ ነኝ ባይ ሕብረተሰብ የቱን ያህል ደነዝ እንደሆነና ምንም ሳያውቁ አወቅን የሚሉ አታላዮች እንደፈለጉ የሚያላጉት ግዑዝ የሕብረተሰብ ክፍል እንደሆነ ያሳያል፡፡ በሙያው ትክክል ያልሆነ ሥራ ሲሠራ አያየ ይህ ትክክል አይደለም ለማለት የሽኮረመማል፡፡ ሌሎች ራሳቸውን ሰውተው ነፃ እንዲያወጡት ይጠብቃል፡፡ ባለሙያ ሆነው ለጥቅም፣ ለስልጣንና ለሙገሳ ራሳቸውን የሸጡ በርካታ ጉዶችን የምታስተናግድ አገር ናት ኢትዮጵያ ባሁኑ ሰዓት፡፡ አገር ውሰጥም ሆነ ውጭ አገር ተምረው የቀሰሙትን እውቀት ወደ ሥራ ለመተርጎም አቅም ያነሳቸው የመሆናቸው ምልክት አጠቃላይ የእቅድ፣ የንድፍና የአፈፃፀም ጉድለት በግልፅ የሚታይባቸው ፕሮጅክቶች በርካታ መሆናቸው ነው፡፡ የአንድን ፐሮጀክት ጥራት ሊቀንሱ የሚችሉ ሁኔታዎችን በቅጡ ለይቶ ለማገናዘብ ያልተዘጋጀ ሕብረተሰብ በለብ-ለብ ስራ ለተብለጨለጨ ነገር አድናቆቱን ቢሰጥ ካለማወቅ ነው ይባላል፡፡ እያወቁ መሠረታዊ መመዘኛዎችን ሳያሟሉ ጥራት ለኛ አይነት አገር ቅድሚያ የሚሰጠው ነገር አይደለም በሚል እብሪት በርካታ ፕሮጀክቶችን በተርመጠመጠ ሁኔታ የሚያስፈፅሙት አድር ባይ ምሁራን ግን አሳዛኝና አሳፋሪ ፍጡሮች ናቸው፡፡
ካዛንችስን እንደምሳሌ እንውሰድ፡፡ በዚህ አካባቢ በጣሊያን ወረራ ዘመን የተሠሩ ጥራታቸውን ጠብቀው የዘመናዊ ሕንፃ አሰራር ቅድመ ሁኔታዎችን በሚገባ አሟልተው የተሠሩ ሕንፃዎች ተደምስሰው በተንቦረቀቁ አውራ ጎዳናዎች፣ ፓርኮችና ከቦታዎቹ ጋር የማይመጣጠኑ አዳዲስ ግንባታዎች ተተክተው ቀደም ሲል ሞቅ ያለ ሕይወት ይታይባቸው የነበሩ መንደሮች አካባቢዎች ሰው አልባ ሆነው ይታያሉ፡፡ እነዚህን ሕንፃዎች ማፍረስ ለምን እስፈለገ? የማፍረሱ ውሳኔስ እንዴት ተወሰነ? ጥቅሙና ጉዳቱ ተጠንቷል ወይ? እነዚህንና ሌሎችም ጥያቄዎች መጠየቅ ሲገባው ልሂቁ የሥነ ሕንፃ፣ የምሕንድስና፣ የውሃና ፍሻስ፣ የእቅድና ንድፍ፣ የመገናኛ ወዘተ….ባለሙያው ለአምባገነን መሪዎች እንዳላችሁ አድርጉ እያለ ባገሩ ላይ ከጠላት የከፋ ባንዳ ሲቀልድበት አይቶ እንዳላየ ራሱን ሲደብቅ ይታያል፡፡
እስኪ እንተንትነው፡፡ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ጥራትን በጠበቀ ሁኔታ ተገንብተው ለኑሮም ሆነ ለተለያዩ ሥራዎች የሚያስፈልጉ አገልግሎቶችን በተገቢው መንገድ ለማሟላት የሚችሉ ሕንፃዎች በጣም ጥቂት ናቸው፡፡ ከነዚህ ጥቂት ሕንፃዎች ውስጥ በጣሊያን ዘመን የተሰሩት ሕንፃዎች ቀዳሚውን ቦታ የሚይዙ ነበሩ፡፡ ያሰራራቸው ጥራት፣ ጥንካሬያቸው፣ የሥነ ሕንፃ፣ የመሠረት አሰራር፣ የውሃ ልክ አጠባበቅ፣ የውሃና ፍሳሽ አጠቃቀም ስልታቸው፣ ለተገልጋይ አመቺነታቸው፣ ለከባቢው አየር ተስማሚነታቸው ወዘተ… በተለያዩ መመዘኛዎች ብቁ የሆኑ ቢጠበቁና በቅጡ ቢታደሱ ሃገሪቱንም ከተማዋንም ከከፍተኛ ወጪ ሊያድኑ የሚችሉ ሕንፃዎች ነበሩ፡፡ ለከተማዋ የተለየ ውበት ለማጎናፀፍ የሚችል የሰለጠነ የሥነሕንፃ የጥበብ ብቃት የሚታይባቸው ታሪካዊ ሕንፃዎች ነበሩ፡፡ ከድንጋይ አጠራረብ ጀምሮ፣ መሠረት አጣጣላቸው፣ ቅርፃቸው ወዘተ… ከማፍረስ ይልቅ ወጣቱን ትውልድ ለማስተማር ልንጠቀምባቸው ይገባ ነበር፡፡ እነሱን ጠብቆ ተጨማሪ ዘመናዊ ሕንፃዎችን መገንባት ሊታሰብበት የሚገባ አማራጭ ነበር፡፡ የእቅድና ንድፍ ባለሙያዎች በጥሩ ሁኔታ እነዚህን ሕንፃዎች ያሁኑን ዘመን በሚመጥን መንገድ አዋሕደው ለተጠቃሚውም ለተመልካቹም የሚማርኩ አቅዶችን ማውጣት ይጠበቅባቸው ነበር፡፡
ከጥልቅ ድህነት የወጡና በእጃቸው ጥራት ያለው ነገር ሠርተውና አንፀው የማያውቁ ጉዶች ሌላው ተጨንቆና ተጠቦ የሠራውን ለማፍረስ ሲሽቀዳደሙ አውቃለሁ፣ ተምሪያለሁ የሚለው የህብረተሰብ ክፍል ልክ አለመሆናቸውን እያየ በድንዛዝ ይመለከታቸዋል ፡፡ የሚያደርሱት ጥፋት በተለይ ከምቀኝነት፣ ከዘረኝነትና ከጥላቻ ጋር ተዋህዶ ያንድን ሕብረተሰብ ማንነት ለመሰረዝ በሚደረግ ጥረት ሲተገበር ደግሞ የሚያደርሰው ውድመት ከፍተኛ ስለሆነ ሊወገዝና በቃ ሊባል ይገባው ነበር፡፡ ጊዜ የሠጣቸው ተራ መሃይሞች የራሳቸውን አሻራ ለማድመቅ ሌሎች የሠሩትን በማውደም ሲረኩ እውነት ይች አገር ሰው አላት ወይ የሚያስብል ነው፡፡ ባለሙያ ነን ባዮች ጥቅምና ጉዳቱን በማመዛዘን በማይችሉ፣ ጊዜያዊ ፍላጎታቸውን ለማርካት እየተቅለበለቡ ጥላቻን የሕይወታቸው መመሪያ ባደረጉ ጉዶች እየተመሩ የጥፋት ተባባሪ ሲሆኑ ማየት ያስገርማል፣ ያሳዝናል፡፡ እነዚህን ሕንፃዎች አፍርሶ ካልጠፋ ቦታ በፓርክ መተካት ወይንም ለዘመኑ ቱጃሮች መሬቱን መሸጥ ከእንከፍነት ሌላ ምን መገለጫ ይኖረዋል፡፡ የመንፈስ ድሕነት፣ የአእብሪትና፣ የደካማ ጭንቅላት ውጤት እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ይህን በማየት የኮሪደር ልማቱ ዓላማ ሕዝብን ማፈናቀል እንደሆነ አለመረዳትና ይህን የክፋት ዘመቻ አለማውግዝ ትልቅ ደካማነት ነው፡፡
እርጉሞቹ መሪ ነን ባዮች ሰው በጥራት የሠራውን እያፈረሱ በተበላሹ፣ የነዋሪውን ፍላጎት ያላገናዘቡና አገሪቱንም ሆነ ከባቢያቸውን በማይመጠኑ ሕንፃዎች ይተኩታል፡፡ በድህነት ያደጉ ጉረኞች ከአቅማቸው በላይ በመንጠራራት ሰማይ ጠቀስ ፎቆችን አየተመኙ ዓላማቸውን ለማሳካት አገር ያተራምሳሉ፡፡ ለሥነ ጥበብ፣ ለሥነ ሕንፃ፣ ለግንባታ ጥበብና ለመሳሰሉት የእውቀት ዘርፎች የተዘጋጀ አእምሮ አልፈጠረባቸውም፡፡ አጠገባቸው የሚገኙት ልሂቅ ነን ባይ አማካሪ ነን ባዮችም እንደቀን ሠራተኛ ሙያቸውን አከራይተው እርስዎ እንዳሉ ከማለት ሌላ ሃሳባቸውን የማካፈል፣ ግፋ ሲልም ይህ አሠራር ትክክል አይደለም ብለው ለዕውቀትና ለእውነት የመቆም ሀሞት አልታየባቸውም፡፡
ከተማዋ ውስጥ በቅርቡ ከተጠናቀቁት ሕንፃዎች ውስጥ ከጥቂቱ በስተቀር አብዛኞቹ ውሃ ልክ እንኳን በቅጡ ጠብቀው ያልተሰሩ፣ የተንጋደዱ፣ የተጣመሙ፣ ሥርዓትን በጠበቀ መልክ ሰለማይታቀዱና ስለማይነደፉ አስፈላጊውን የዘመናዊ ሕንፃ ቅድመ ሁኔታዎች ለማሟላት የማይችሉ ናቸው፡፡ የውሃና፣ የፍሳሽና የአሌክትሪክ አገልገሎታቸው ያልተሟላ፣ ክፍሎቻቸው ማዕዘን ያልጠበቁ፣ ሽንት ቤቶቻቸው ዉሃ ስለማይደርሳቸው የጠነቡ የቀበሌ ህንፃዎችንና የወረዳ ክፍለ ከተማ ሕንፃዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ የኮንዶሚኒየሞችም የሥራ ጥራት ድክመት የነዋሪዎቻቸውን የኑሮ ሁኔታ ያወሳሰቡና ለባለቤቶቻቸውና ለተከራዮቻቸው ከፍተኛ እዳ ያስከተሉ መሆናቸውን ሥራዬ ብሎ የታዘባቸው ያውቀዋል፡፡ ከተማዋ ውስጥ በግለሰቦች የሚገነቡት ሕንፃዎችም አሰራራቸው ከሲሚንቶ፣ ከሸክላና ከድንጋይ ቢሆንም ወጪ ለመቀነስ በጉቦ ጥራታቸውን ሳይጠብቁ እየተሠሩ ለተጠቃሚዎቻቸው መስጠት የሚገባቸውን አገልግሎት ሳይሰጡ እየፈራረሱና አእየተበላሹ ሕዝብን ለምሬትና ለተጨማሪ ወጪ ሲዳርጉ ይታያሉ፡፡
በማንኛውም መመዘኛ አሁን ከሚሰሩት ሕንፃዎች የበለጠ ጥራት፣ ውበትና ጥንካሬ ያላቸውን ሕንፃዎች እያፈረሱ ነባር ሰፈሮችን ሰው አልባ ማድረግ፣ ቤተ እምነቶችን ከምዕመናን መለየት፣ ሕብረተሰቡን ከማሕበራዊና ሕብረተሰባዊ ግንኙነት መነጠልና የተወረሱ ቦታዎችን በዶላር መቸብቸብ አላማው በኮሪደር ልማት ስም የማይፈልጉትን ሕዝብ ማፈናቀል እንደሆነ ግልጽ ሊሆን ይገባል፡፡ ስለሆነም፣ እነዚህን ህሊና ቢስ መሪ ነን ባዮች ማስወገድ ጊዜ ሊሰጠው የማይገባው ጉዳይ መሆኑን ተረድተው ያገሪቱ ልሂቃን ከእንቅልፋቸው መንቃት ይጠበቅባቸዋል፡፡