
በአማራ ህዝብ ላይ የተጋረጠውን የህልወና አደጋ ለመመከት ላለፉት ሁለት ዓመታት ታላቅ ተጋድሎ እየተደረገ መሆኑ የሚታወቅ ነው። በተበታተነ ሁኔታ የሚደረገውን ተጋድሎ ወጥ በሆነ ድርጅታዊ መዋቅር ስር ለማድረግ በተጀመረው ጥረት የአማራ ፋኖ ብሄራዊ ሃይል የተወለደና ትግሉን በተሻለ ቁመና እየመራ የሚገኝ መሆኑ ይታወቃል። በጥቂት ታጋዮች ከኋላ ቀር መሳሪያ የተነሳው የአማራ ፋኖ ትግል በሁለት ዓመት ውስጥ ያስመዘገበው ድልና የገነባው ግዙፍ ወታደራዊ ሃይል የተጀመረውን የህልውና አደጋ ለመመከት በሚያስችል ቁመና ላይ እንዲገኝ አድርጎታል።
ምንም እንኳን ትግሉ ከሚፈልገው አቅምና ብቃት እንዲሁም የአማራ ህዝብ እየደረሰበት ካለው መከራና ስቃይ አንጻር የምንገኝበት ምዕራፍ ገና ብዙ እንደሚቀረን የሚያሳይ ቢሆንም በቁርጥኝነትና በተባበረ ሃይል ከቀጠልን በቅርብ ጊዜ የአገዛዙን የጭቆና ቀንበር በጣጥሰን እንደምንጥል ጥርጣሬ የሚያስፈልገው ጉዳይ አይደለም።
ለዚህም የተጀመረውን የአንድነት ጉዞ ማፋጠንና ወደኋላ የማንመለስበት የፋኖ ወጥ መዋቅር ለመገንባት ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረግን እንገኛለን። የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ኃይል ለዚህ የአንድነት ጉዞ የሚረዳና የተጋረጡብንን ችግሮች በውይይት ለመፍታት የሚያስችል ታላቅ ሲምፖዚየም ማዘጋጀቱን ሲገልጽ በደስታ ነው።
የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ኃይል ( አፋብኃ) ከዚህ አቅሙ የበለጠ ጠንካራ እንዲሆንና የትግሉ ጊዜ ባጠረ መልኩ ለመቋጨት ያስችል ዘንድ እና ለአለማቀፉ ማህበረሰብ የትግሉን ሂደትና ዓላማ ግልፅ ለማድረግ፣ ለማስተዋወቅ እና በጎ ፈቃደኛ ደጋፊዎችን ለመጨመር ያለመውን ይህን ሲምፖዚየም ጷጉሜ 01 እና 02 ቀን 2017 ዓ.ም ወይም በፈረንጆቹ አቆጣጠር September 06,2025 Saturday Starting 12 Noon and September 07,2025 Sunday Starting 12 Noon በቀጥታ ስርጭት የሚያካሂድ መሆኑን ያስታውቃል።
በሲምፖዚየሙ ላይ የአፋብኃ ማዕከላዊ ኮማንድ አመራሮች በጋዜጠኞች ቃለመጠይቅ ይደረግላቸዋል፣ ዝግጅቱም በቴሌቪዥንና በዩቲዩብ፣ ቲክቶክ እና የX (Twitter) ማህበራዊ ሚዲያዎች የቀጥታ ስርጭት ሽፋን ያገኛል።
በዚህ የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ኃይል ( አፋብኃ) ሲምፖዚየም ተሳታፊ በመሆን የአማራ ህዝብ የታወጀበትን እልቂት ለመመከት እየታገለ ያለውን የአማራ ፋኖ በመደገፍ፣ ከአማራም አልፎ በየተራ ሁሉንም ብሄሮች በማጥቃት የጭቆናና የባርነት ስርዓቱን ለማስቀጠል እየሰራ ያለውን “ብልፅግና” የተሰኘውን ጸረ ሕዝብ አገዛዝ እንድንታገልና ሀገርን ከመፍረስ እንድንታደግ ጥሪ እናቀርባለን።
ህልውናችን በተባበረ ክንዳችን!
የአማራ ፋኖ ብሄራዊ ኃይል (አፋብኃ)