አንዱ ዓለም ተፈራ
ሰኞ ነሐሴ ፳ ፮ ቀን ፳ ፻ ፲ ፯ ዓ. ም.
ይህ የምሁር፣ የምርምር ጥናት ውጤት አይደለም። በአንጻሩ ደግሞ፤ የአንድ ድርጅት የመቀስቀሻ ምናብ አይደለም። የአንድ ኢትዮጵያዊ አገር ወዳድና ለነገ ተጨናቂ፣ የዐማራ ህልውና ትግል አካል የሆነ ግለሰብ፤ የግል አስተያየት ነው። አዎ! ከወዲሁ ላሳውቅና፤ ወገንተኛ ነኝ። ለማስታረቅ ወይንም ለነገዋ ኢትዮጵያ መፍትሔ ለማቅረብ አይደለም፤ ይሄን የጻፍኩ። ስለኢትዮጵያዊነቴ ወይንም ስለኢትዮጵያ እንደሌሎቻችሁ ሁሉ እጨነቃለሁ። በመሠረቱ፤ ለአንድ ዐማራ፤ ስለ ኢትዮጵያም ሆነ ስለኢትዮጵያዊነት ሊሰብክ የሚሞክር፤ ራሱን የማያውቅ ነው። ዐማራ በልሂቃን ኦሮሞ ግለሰቦችና በመላ ኦሮሞ ሕዝብ መካከል ይለውን ልዩነት ጠንቅቆ ያውቃል። ከዚያ አልፎ ተርፎ፤ በኦሮሞ ልሂቃንና በገዢው የብልፅግና ፓርቲ መካከል ያለውንም ልዩነት በትክክል ይረዳል። ዐማራ፤ ኢትዮጵያን፣ ከአሁኑ ወቅት ገዢዎች ጋር በፍጹም አያቆራኛትም። እናም ከዚህ ዕይታ ተነስቼ፤ ይሄንን ጽሑፍ አቀርባለሁ።
እያንዳንዳችን በያለንበት ስለ ነገዋ ኢትዮጵያ እንጨነቃለን። አገር ነገ ትኖረናለች ወይ! የምንል ብዙዎች ነን። ይሄ የዐማራ ተወላጅን ብቻ ሳይሆን፤ መላ ኢትዮጵያዊያንን በያሉበት ኡአስጨነቀ ያለ እውነታ ነው። ችግሩ ያለው፤ መፍትሔው ምንድን ነው? የሚለውን የምናይበት መነፅር ነው። የኦሮሞ ልሂቃንና የዐማራ ልሂቃን፤ በአስራ አምስተኛውና አስራ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን የሆነውን በትክክል በአንድነት የሚረዱበት ግንዛቤ ሳይኖር፤ ሁሉም በየበኩላቸው እንዲስማማቸው እያሽከረከሩ፤ አንድ የሆነ መፍትሔ ላይ ይደርሳሉ ማለት፤ ከምኞት ያለፈ ተጨባጭነት የለውም። ይሄን የምለው፤ የነበረ ታሪክ፤ አሁን ባሉ ሰዎች ፍላጎትና ዓላማ የሚሽከረከር ባለመሆኑ ነው። የነበረው አንድና አንድ ጉዳይ ነው። ይሄንን የለም እንዲህ ነበር! የለም እንዲያ ነበር! ብሎ መከራከር አያዋስኬድም። ሁሉም ይሄንን የማያውቅ ሆኖ አይደለም። ነገር ግን፤ አሁን ለፈለግነው ዓላማ እንዲጠቅመን፤ ታሪክን በየበኩላችን ስለምንጠመዝዘው፤ ከዚያ ተነስተን ትክክለኛ መፍትሔ ልናመጣ አንችልም። ከታሪክ መማር እንጂ፤ ታሪክን መቀየር አይቻልም።
በኦሮሞ ልሂቃን በኩል፤ በነሱ ግንዛቤ የተመሠረተውና እየቀረበ ያለው፤ በኛም አገር ሆነ በዓለም ዙሪያ አገርን ለመገንባት የተሄደውን ክንውን፤ መኮነንና ያንን መውቀስ ብቻ ሳይሆን፤ ያንን ለማረም ወደኋላ ሄደን እንዝመት! የሚል ነው። ይሄ አገር ለመገንባት የተደረገውን ሂደት እናፍርስ! አዲስ አገር ግንባታ እንፍጠር! የነበረን ታሪክ እንሻርና አዲስ ታሪክ እንፍጠር! የሚል አካሄድ ነው። ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት ሁኔታ የደረሰችው፤ እኛ ጠላነውም ወደድነውም፤ ኢትዮጵያዊያን ከፍተኛ ተጋድሎ አድርገው ነው። ይህች አገር፤ የነገሥታቱ ብቻ አልነበረችም! ይህች አገር፤ የዐማራ ብቻ አልነበረችም! ይህች አገር፤ የመላ ኢትዮጵያዊያን፤ የተለያዩ ሃይማኖቶችን የተከተሉ፤ ከተለያዩ የትውልድ ሐረግ የሚመዙ፣ የተለያዬ ቋንቋዎችን የሚናገሩ የገነቧት ነች። አሁን ሀቁ፤ ዐማራ እንዲጠፋ በያለበት እየተዘመተበት መሆኑ ነው። ይሄ የአሁን የማይካድ ሀቅ ነው። ይሄንን የሚክድ፤ ኦሮሞም ይሁን ዐማራ፣ ትግሬም ይሁን ሌላ፣ ስለኢትዮጵያም ሆነ ስለ ኢትዮጵያዊነት ሊናገር አይችልም።
መንግሥት ሲባል፤ የመላ የአገሪቱ ሕዝብ አስተዳዳሪ ነው። የትግራይ ህዝብ ነፃ አውጪ ግንባር ኢትዮጵያን ሲገዛ የነበረው፤ ኢትዮጵያዊ ሆኖ ሳይሆን፤ የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር ሆኖ ነበር። እናም ትግሬነቱና የትግራይ መንግሥትነቱ ለጥያቄ የሚገባ አልነበረም። አሁንም ይሄ ቡድን እየታገለ ያለው የትግሬዎች መንግሥት እንዲመለስ ነው። በአንጻሩ፤ አሁን በኢትዮጵያ ያለው፤ የኦሮሞ መንግሥት ነው። ተረኛዎች እኛ ነን! ከማለት ጀምሮ፤ ማንኛውንም መንግሥታዊ መዋቅር ይዞ የሚገኘው የአክራሪው ኦሮሞ ገዢ ቡድን ነው። ይሄን፤ ሁላችንም መቀበል አለብን። አንድን የኦሮሞ ክፍል ጎዳ አልጎዳ፤ ለማንነቱ ተንባይ አይደለም። ይሄው የልሂቃን ስብስብ፤ ምን ያህል የመገዘዝ አርሶ አደር፣ የስሜን አርሶ አደር፣ የአላማጣ አርሶ አደር፣ የመተከል አርሶ አደር ይኖር እንደነበር ትንሺም ለመረዳት ጥረት ሳያደርግ፤ የንጉሠ ነገሥቱ ዘመን፤ የዐማራ መንግሥት ነበር እያለ አውጇል። የዐማራ ጠላት ሆኖ አንድ ትውልድን የጨረሰውን የደርጋማው የመንግሥቱ ኃይለማርያም መንግሥት፤ የዐማራ መንግሥት ነበር ይላል። አሁን በሱ ሲመጣበት፤ የኦሮሞ መንግሥት አይደለም! የኦሮሞ መንግሥት አትበሉ! እያለ ይሰብካል። የኦሮሞ መንግሥት የማይባልበት ምክንያት ምንድን ነው? ያለውን ሀቅ መካድ አይቻልም!
መጀመሪያ ካስቀመጥኩት የታሪክ ግንዛቤ ልዩነት ቀጥሎ የተቀመጠው፤ አሁን ያለውን መንግሥት አስመክቶ፤ በኦሮም ልሂቃንና በዐማራ ልሂቃን መካከል የተለያዬ ግንዛቤ መኖሩ ነው። ይሄ ሁለተኛው ነጥብ ነው። በነበረውና ባለው ሀቅ ላይ ስምምነት በሌለበት ሁኔታ፤ ሁሉን ያቀፈ መፍትሔ ሊገኝ አይችልም። ሁኔታውን በትክክል ሳንገነዘብ፤ እንኳንስ የተለያዬ ግብ ያላቸው አካላት ይቅርና፤ በአንድ ላይ የቆሙትም ሊስማሙ አይችሉም።
ወደ ዐማራ የህልውና ትግል ልመለስ። የዐማራ የህልውና ትግል የተጀመረው፤ የአክራሪ ኦሮሞ ገዢ ክፍል ሥልጣኑን ከመያዙ በፊት ነው። አሁን ያለው የአክራሪው ኦርሞ ገዢ ቡድን፤ በትውልድ ሐረግ የተመሠረተውን ዘረኛ አገዛዝ አልጀመረውም። ለዚህ ተጠያቂው፤ ራሱን የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር ብሎ የሚጠራው ቡድን ነው። እንደገና፤ ዐማራ፤ በትግራይ ሕዝብና በትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር መካከል ያለውን ልዩነት አጣርቶ ያውቃል። በተጨማሪም፤ አዲስ ትርክት ፈጣሪዎችን እና ከኢትዮጵያ ይልቅ ለምን የፋሺስት ጣሊያን አትገዛንም ነበር! የሚለውን የትግራይ ልሂቅ፤ ከትግራይ ሕዝብ ለይቶ ያውቃል። እኒህ ሁለት አክራሪ፤ የትግራይና የኦሮሞ ዘረኛ ክፍሎች፤ አንድ የሚያስማማቸው ጉዳይ አለ። ይሄም፤ ለዐማራ ያላቸው ጥላቻ ነው። ይሄን ያላመነ፤ በመፍትሔው በኩል ትክክለኛ መረዳት ሊኖርው አይችልም። ለምን ለሚለው፤ እያንዳንዳቸው መልስ አላቸው። በትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ በኩል፤ ሲነሳ፤ “በዐማራ መቃብር የትግራይን ሩፑብሊክ እመሠርታለሁ!” ብሎ ስለተነሳ፤ ሌላ መግለጫ ማቅረብ አይጠበቅብኝም። በኦሮሞ አክራሪ ገዢ ቡድን ደግሞ፤ ከላይ እንደጠቆምኩት፤ “ምናለ እኛ ብንገዛ! ተረኞቹ እኛ ነን!” ያለው በቂ ነው። የአክራሪ ኦሮም ገዢ ቡድን፤ ባይፈጥረውም፤ በትውልድ ሐረግ የተመሠረተውን ዘረኛ አገዛዝ፤ የኔ ብሎ ተቀብሎ ጥብቅና ቆሞለታል። እናም ወራሽ ብቻ ሳይሆን፤ አሳዳጊና አስፋፊ ነው።
ዋናው ጉዳይ፤ አገርና ሕዝብ መሠረታዊ የሆነው ትስስራቸው፤ የአገሩ ዜጋ መሆናቸው ነው። ያ በሌለበት ቦታ፤ አገር ሊኖር አይችልም። ኢትዮጵያ አገሬ ናት ስል፤ የኢትዮጵያ ዜጋ ነኝ! ኢትዮጵያዊ ነኝ! እያልኩ ነው። በኢትዮጵያ ሙሉ ባለቤት ነኝ! የትም መኖር አችላለሁ! የፈለግሁትን አመለካከት ልይዝ እችላለሁ! በኢትዮጵያ ውስጥ የትም መንቀሳቀስ እችላለሁ! እያልኩ ነው። ያን ስነፈግ፤ ኢትዮጵያዊ አይደለህም! እየተባልኩ ነው። አሁን ዐማራ፤ እዚህ አትኖርም! በምትኖርበትም ቦታ፣ እኛ ስንፈቅድልህና እና የምንፈልገውን ስታደርግ ነው! እየተባለ፤ አገሬ ሊል አይችልም። በአንጻሩ፤ ይሄን ባዩ የኦሮሞ ብልፅግና ፓርቲ፤ የኢትዮጵያ ብቸኛ ባለቤት እንዳልሆነ፤ ዐማራ ጠንቅቆ ስለሚረዳ፤ የሚያደርገው የህልውና ትግል፤ ራሱን አድኖ ኢትዮጵያን ለማዳን ነው። አሁን ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት አደጋ ላይ ናቸው። ይሄን የማይረዳ፤ ትክክለኛ መፍትሔ ሊያቀርብ አይችልም። በትክክል ለኢትዮጵያ መፍትሔ አቅርቦ ወደፊት ለመሄድ፣ ለዐማራ የህልውና ትግል ስኬት፣ መጀመሪያ የዐማራ ህልውና ትግል ደጋፊዎች በአንድ ላይ መሰባሰብ ይኖርብናል። ይህ ጉልበት አግኝቶ ከጠነከረ፤ በውስጥ በትግሉ የተጠመዱት እኛን ሊያዳምጡን የሚችሉበት ዕድል ይሰፋል። እናም ለነሱ የመተባበር ሂደት ልንረዳ እንችላለን።
ከዚህ እውነታ ዘለን፤ ስለነገ ኢትዮጵያ በዐማራና በኦሮሞ ግለሰቦች መካከል ስምምነት ይደረስ ቢባል፤ ትርጉሙ ያስቸግረኛል። ስለነገ ስንነጋገር፤ አሁን ስላለው ስምምነት መኖር አለበት። ስለአሁን ስንነጋገር፤ ትናንት ስለነበረው ስምምነት ሊኖር ይገባል። ለነገው መፍትሔ ማቅረቡ ይቅርና፤ በምሁር ደረጃ ለመነጋገር ሀቁን በየፈለግንበት ማስኬድ አንችልም። ስምምነት ሀቁን መቀበልን ግድ ይላል። ሀቅ ደግሞ እያንዳንዳችን የምንፈጥረው ሳይሆን፤ በተጨባጭ በአገራችን ያለው እውነታ ነው።
በኦሮሞ ልሂቃን በኩል፤ እኔ እንዲህ አድርጉ ወይንም አታድርጉ ማለት አልችልም። ነገር ግን፤ በኢትዮጵያዊነታችን እና አንዲት ኢትዮጵያን በመውደዳችን ምክንያት፤ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ፤ የሚከተለውን አቀርባለሁ። ታሪክ መማሪያ እንጂ መጣያ መሆን የለበትም። ታሪክን አድበስብሶ ወይንም ለራስ ግብ ጠምዝዞ፤ የሚያቀራረብ መንገድ መፍጠር አይቻልም። እኔ የማውቀው ታሪክ ብቻ ነው እውነቱ! እያልኩ አይደለም። እኔም የተረዳሁት፣ እናንተም የተረዳችሁት፤ የሚያጣላን አይደለም። እሺ! በተረዳችሁበት መንገድ ልሂድ። የዛሬ የፖለቲካ ሂደት፤ የሚሽከረከረው በዛሬ ተጨባጭ ሀቅ ነው። እናም፤ ትናንትን በዚህ ወይንም በዚያ ተረዱ አልልም። በፈለጋችሁት ተረዱ። የዛሬን እውነታ ደግሞ አብረን እያየነው ስለሆነ፤ ሀቁን አብረን በትክክል እንገንዘብ። አሁን ከላይ ባስቀመጥኩት መንገድ፤ የአክራሪ ኦሮሞ ገዢ ቡድን፤ ዐማራን ለማጥፋት ዘመቻ ላይ ነው። ይሄ ዘመቻ ኦሮሞዎችን እየጎዳና የማይጠቅም መሆኑን አብሬያችሁ እረዳለሁ። የታሪክ ሀቅ የሚነግረን፤ በአንድ አገር ውስጥ፤ የትርክቱ ሂደት የሚነገረው፤ ጎልቶ በአንደኝነት በተቀመጠው አጀንዳ ነው። በአሁኗ ኢትዮጵያ ይሄ አጀንዳ ደግሞ፤ ዐማራን ለማጥፋት፤ ገዢው የኦሮሞ አክራሪ ቡድን መዝመቱ ነው። ይሄን ተከላክለን በአንድነት የሚቀጥለውን መንግሥት ሂደት አስመልክቶ መነጋገር እንችላለን። በርግጥ በልሂቅ ጉንጭ አልፋ መንገድ መነጋገር፤ ችግር የለውም። መፍትሔ ሆኖ አገር እንዲያድን ግን፤ ትክክለኛ ተወካዮች፣ ትክክለኛ አጀንዳ፣ እውነተኛ ፍላጎትና ሌሎችን ለመረዳት ፈቃደኝነትን ይጠይቃል። በዚህ መንገድ መቀራረብና ለነገ ማሰብ ትርጉም ይኖረዋል።