
መሳይ መኮነን
የሚለው ብሂልም አይገልጸውም። ቢያንስ ሴትየዋ የጠመቀችውን ራሷ ልፋ ብትጨረሰውም ሌላው የጠመቀውን መንትፋ አልጠጣችም። ይህ ሰው ድንኳን ሰባሪ ነው። በሰው ላብ ወዙን የሚወስድ ጩሉሌ። እሱ እንዲህ ዓይነት ፕሮጀክት ለመስራት አእምሮው የሚፈቅድለት አይደለም። ይህቺኑ ብልጭልጭ አምፖልና ዘንባባ ለመትከል የሚያስችለው የአእምሮ ውቅር እንጂ ትውልድ ተሻጋሪ፥ ሰው ተኮር ፕሮጀክት ለመስራት አቅምም ፍላጎትም የለውም። የሰው ታሪክ ቀምቶ፥ ድንኳን ሰብሮ ግን ጩኸቱ ሀገር ምድሩን አቅለጠለጠው። በዚህ ፕሮጀክት ታሪክ የሚያስታውሳቸው መለስ ዜናዊን፥ ኢ/ር ስመኘው በቀለንና ከማንም በላይ የኢትዮጵያን ህዝብ ነው። የሰው ወርቅ አያደምቅም። የሰው ላብ አያወዛም። ድርቅ፥ ምንችክ ማለት ይቻላል። በእርግጥ ድንቁርና ወለድ ድፍረት አይጣል ነው።
ይህ ህዝብ መከራው በዛ። የደረቀ ባዶ ሆዱን በቁራሽ ምግብ የሚሞላለትና የሚያረጥብለት ቢያጣ ወሬ እንዲጠግብ ተፈርዶበታል። በእርግጥም ሆዳችን ተነፋ። በፕሮፖጋንዳ ቅሪላ አክሏል። ሰውዬው ፊቱን በሜካፕ እየወለወለ ቴሌቪዥን መስኮት ላይ መደቀን፥ ቩቩዜላ መልቀቅ የየዕለት ስራው አድርጎታል። እርሙን ቢጠምቅ(እሱ ባይጠምቅም) ራሱ ጠጥቶ ሊጨርሰው ነው። ወሬው ሀገር ያስለቅቃል። አሁንም ወሬ ላጥግባችሁ፥ ስሙኝ ብሎ መጥቷል። ሆዳችንን ሊነፋ ቀጠሮ ይዟል። ጩኸት! የጆሮ አምላክ ይድረስልን።