
ዋዜማ ሬዲዮ
ማሞ ከሃላፊነት የለቀቁት፣ በሌላ የሙያ መስክ ለመሰማራት ስለፈለጉ እንደሆነ ረቡዕ፣ ነሃሴ 28፣ 2017 ዓ፣ም በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባወጡት የስንብት መግለጫ ላይ ገልጸዋል። ማሞ፣ ኢትዮጵያ ካለፈው ዓመት ሐምሌ ጀምሮ ተግባራዊ እያደረገችው ያለችውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብር በመንደፍና የአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብሩን ተፈጻሚ በማድረግ እንዲሁም ብሄራዊ ባንክ በ50 ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ባካሄደው ስር ነቀል ማሻሻያ ሂደት ውስጥ ተሳታፊ በመሆናቸው ክብር እንደሚሰማቸውም ገልጸዋል። ብሄራዊ ባንክ አገሪቱ ወደ ዘመናዊ የገንዘብ ሥርዓት እንድትሸጋገር አስችሏል ያሉት ማሞ፣ ባንኩ ዓላማውን ወደሚመጥን ዘመናዊ ማዕከላዊ ባንክ ለመሸጋገር የሰነቀውን ራዕይ ማሳካት የሚችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል የሚል ጽኑ እምነት እንዳላቸውም ገልጸዋል።
ማሞ በሃላፊነት ላይ በነበሩበት ወቅት፣ በአገሪቱ ማክሮ ኢኮኖሚ ላይ ስር ነቀል ለውጥ ያመጣውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ እና በገበያ ላይ የተመሠረተውን የውጭ ምንዛሬ ፖሊሲዎች የቀረጹ ሲሆን፣ ላለፈው አንድ ዓመትም ፖሊሲዎቹ ተግባራዊ እንዲሆኑ አድርገዋል። ማሞ፣ ዓለማቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ ኤም ኤፍ) ለኢትዮጵያ የ3 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር ብድር ሲያጸድቅ ለመንግሥት ባስቀመጠው ቅድመ ሁኔታ መሠረት፣ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ተቋማዊ ነጻነቱን እንዲያገኝ የሚያስችለውን አዲስ አዋጅ ተዘጋጅቶ ተግባራዊ እንዲሆንና የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍም ለውጭ ባንኮች እንዲከፈት አድርገዋል።
ማሞም በዚሁ የስንብት መግለጫቸው፣ ባንኩ አስተዳደራዊ ነጻነቱን እንዲቀዳጅ አዲስ ሕግ ወጥቶ ተግባራዊ እንዲሆን ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል። ማሞ በሥልጣን ዘመናቸው፣ ለአገሪቱ አካታች የዲጂታል የፋይናንስ ሥርዓት በማዘጋጀት ተግባራዊ ማድረጋቸውንም የጠቀሱ ሲሆን፣ የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ መንግሥት ለአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብሩ ማስፈጸሚያ ከዓለም ባንክ እና ከዓለማቀፉ የገንዘብ ተቋም ባጠቃላይ የ10 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ብድር እንዲያገኝ ብሄራዊ ባንክ አስተዋጽኦ ማድረጉንም አውስተዋል። ማሞ በዚሁ የስንብት መግለጫቸው፣ ብሄራዊ ባንክ ተግባራዊ ያደረጋቸው ማሻሻያዎች፣ የባንኩ የውጭ ምንዛሬ ክምችት መጠን በሦስት እጥፍ እንዲጨምር፣ በሰባት ዓመታት ውስጥ የዋጋ ንረቱ ወደ ዝቅተኛ ደረጃ እንዲወርድ እና የዲጂታል የፋይናንስ ክፍያዎች በአስር እጥፍ እንዲጨምሩ እንዲሁም የፋይናንስ ሥርዓቱ አጠቃላይ ሃብት ወደ 5 ትሪሊዮን ብር እንዲያድግ ማስቻላቸውን ዘርዝረዋል። [ዋዜማ]