የታወቁት የአሜሪካ ፈላስፋና ደራሲ ኖአም ቾምስኪ ስለ አሜሪካ ህብርተሰብ የቁልቁለት ጉዞ መሰረት መዋቅራዊና ተቋማዊ መሆን አብሰረው ሲናገሩ ትዝ ያለኝ እኛ ኢትዮጵያዊያንም በሃሰት ጭምብል ተሸፍነን የኢትዮጵያን ማህበረሰባዊ ኢኮኖሚ ውድቀት ሃቁን እንዳናስተናግድ፤ ለፍትህ፤ ለሚያዋጣና ትርጉም ላለው መሰረታዊ ለውጥ እንዳንቆምና በጋራ እንዳንታገል ያደረገን፤ ከፋፍሎ የሚያጋድለንና የሚያደማን የገዢው መንግሥት መሪዎችና ካድሬዎች የሚያስተጋቡት መርህ እና ትርክት መሆኑን አለመገንዘባችንን ነው፡፡ ሃስት፤ አስመሳይነት እና አድርባይነት ነግሷል፡፡ የሞራል ልእልና ደቋል፡፡
የአሜሪካ ሕዝብ በራሱ ላይ የሚካሄደውን ጥልቀት ያለው ሴራ የተገነዘበው መሆኑን የሚያሳዩ ልዩ ልዩ ምልክቶች አሉ፡፡ ቾምስኪም የሚያረጋግጡት ይህንኑ ነው፡፡ በየቀኑ ሰላማዊ ሰልፍ ይካሄዳል፡፡
የአማራውን መዋቅራዊና ተቋማዊ ተግዳሮቶች ከተገነዘቡና የአማራ ፋኖን እንቅስቃሴ ከሚያደንቁ ባለድርሻዎች መካከል አንዱ ነኝ፡፡
እኔ በተከታታይ ስመራመረው የአማራው ዋና ችግር መስረትና መንስኤው የአማራው ለአንድ ዐላማ ተባብሮ አለመነሳት ነው፡፡ ይህ ተግዳሮትና መሰናክል ከተማሪው እንቅስቃሴ ጀሞሮ ያየሁት ክስተት ነው፡፡ ይህ ክስተት ለአማራ ጠላቶች ወንፊትና መሳሪያ ሆኗል ብል አልሳሳትም፡፡ ይህንን ችግር ካላጤንነው የእርስ በእርስ ግድያውንና የገመድ ጉተታውን ልንፈታው አንችልም፡፡
የአማራው ሕዝብ ዘርፈ ብዙ ችግሮችና ተግዳሮቶች እንደተደቀኑበት የሚካከራክር አይደለም፡፡ በፖለቲካው እንዳይሳተፍ፤ በኢኮኖሚው እንዲዳክም፤ እንዲማክንና እንዲራብ፤ በእምነቱ እንዲሳቀቅ፤ እንዲሰደብና እንዲሳደድ፤ በባህሉ እንዲሸመቀቅ፤ በመሬቱ እንዳይጠቀም እንዲያውም ከመሬቱ እንዲፈናቀል እንዲሰደድ፤ በስነልቦናው መጤ ነህ፤ ጨቋኝ ነህ፤ ትምክህተኛ ነህ ወዘተ ተብሎ እንዲፈረድበት፤ በባህሉ በራሱ እንዳይተማመንና ፈርቶ እንዲኖር፤ በውጭ ግንኙነት እንዲጠላና ወዳጅ እንዳይኖረው ወዘተ የተደረገና የተፈረደበት ሕዝብ ነው፡፡ የአማራውን ብሶት ከሌላው የሚለየው አማራው በመሰረታት አገር የፖለቲካ ሥልጣን ቀርቶ ምንም አይነት ሚና የለህም፡፡ መሬቱ፤ ባህሉ፤ ሌላው ቀርት እምነቱ፤ ታሪኩ፤ ተቋማቱ፤ ቋንቋው ወዘተ ላንተ አይገባህም፡፡ መወገድ አለብህ ተብሎ ከአምሳ ዓመታት በላይ ስር የሰደደ፤ ተቋማዊ፤ መዋቅራዊና መ
ንግሥታዊ ግፍና በደል የሚካሄድበት ሕዝብ ነው አማራው፡፡
የአማራው የሞት የሺረት ትግል የህልውና ትግል ብየ የምቀበለው ይህንኑ ነው፡፡ ማንንምና ምንንም የማይምር ጭካኔ የተሞላበት እልቂትና ውድመት ነው የአማራው የህልውናው ትግል፡፡ አማራው ታግሎ ከማሸነፍ ውጭ ሌላ አማራጭ የለውም፡፡ ህወሃትም ሆነ የኦህዴድ መሪዎች የሚተገብሩት ይህንን አጀንዳ ነው፡፡ የሥልጣን ግብግብ ቢያሳዩም በአማራው ሁለ ገብ ጥቃት ላይ ይስማማሉ፡፡
ይህ በሁሉም መልኩ ግፍና በደል የሚካሄድበት የማራ ሕዝብ ያለው አማራጭ አንድ ብቻ ነው የምለው ለዚህ ነው፡፡ ራሱን ከዚህ መከራና አጣብቂኝ በአንድነት ታግሎ ጠላቱን ማሸነፍ የአማራው ህልውና መሰረት ነው፡፡ ማንም በአማራነቱ መለያ የሚያምንና ለሠብአዊ ፍጥረት ደንታ ያለው ሰው ይህንን እያየ ለስልጣንና የግል ዝና የሚታገል ፋኖ መሪ ሊኖር አይችልም፡፡ በውጭ ተሰዶ የሚኖረው አማራም ከዚህ የተለየ አቋም ሊኖረው አይችልም፡፡ አማራው ካልተደራጀ፤ አማራው አንድ ወጥ የፋኖ ድርጅት፤ አንድ ወጥ የፖለቲካ፤ የሚሊታሪ፤ የዲፕሎማሲ ወዘተ መዋቅር ካልመስረተ ይህንን ዘርፈ ብዙ ተግዳሮት ሊወጣው አይችልም፡፡
በጦር እያሸነፉ ማፍረስና ተቋም አለመመስረት ዋጋ ያስከፍላል፡፡
የአማራ ፋኖ ባጭር ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ ተጋድሎና ጀብዱ ማሳየቱ በምንም ሊካድ አይችልም፡፡ ይህ ጀብዱ የሚካሄደው ባራቱም የአማራ ክፍለ ሃገሮች፟–በሸዋ፤ በወሎ፤ በጎጃምና በጎንደር መሆኑ እስካሁን ጠቅሞታል፡፡ ደጀኑ ሕዝቡ መሆኑን አስምስክሯል፡፡
የአማራ ፋኖ ግዴታው ለመላው የአማራ ሕዝብ ታዛዥ መሆን ነው፡፡ ሕዝብ የሚደግፈው ሃይል ደግሞ በምንም አይሸነፍም፡፡ ለማሸነፍና የፖለቲካ ሥልጣን ለመያዝግ ግን ጉዞው ውሥስብና ጊዜ የሚወስድ መሆኑን መቀበል ያስፈልጋል፡፡
አንድ ይቅር ልለው የማልችለው ተደጋጋሚ ክስተት አለ፡፡ ይኼውም የአማራ ፋኖ መሪዎችና ደጋፊዎች መጠየቅ ያለባችው መሰረታዊ ጉዳይ እንዲህ የሚል ነው፡፡ በአማራ ፋኖ እርስ በእርስ መናከስ፤ መገዳደል (በቅርቡ በጎንደርና ሸዋ)፤ መነታረክ፤ የገመድ ጉተታ ተጠቃሚው ማነው? አንጠራጠር፤ ተጠቃሚዎቹ ህወሃት፤ ሻብያ፤ የኦህዴድ መንግሥት፤ አረቦች፤ የደም ነጋዴዎች ናቸው፡፡ አንድ አንድ ሜድያዎች ይህንን ሁኔታ አባብሰውታል፡፡ ይህ አሉታዊ ጎኑ ነው፡፡
በአወንታዊ ጎኑ ስገምግመው፤ ሜድያዎች የሚዘግቡትን መረጃ ሳዳምጥ በተከታታይ የድል ዜና ስሰማ፤ በውትድርናው በኩል የአማራው ፋኖ የዐብይን ጦር በማሸነፍ ላይ ይታያል፡፡ ለዚህ ዋናው ምሳሌ ፋኖ የታጠቀው መሳሪያ የተገኘው ከምርኮው ነው፡፡ ሆኖም፤ የፖለቲካውን አጀንዳ ገና አልቀየሰውም፡፡ የአማራ ፋኖ በአንድነት፤ በጋራ አመራር ለመስራት ያልቻለበት መሰረታዊ ምክንያት አልገባኝም፡፡ ይህንን ስኬታማ ማድረግ ለህልውናው ትግል ወሳኝ ነው፡፡
የአማራው ሕዝብ ብዙ ዋጋ እየከፈለ ግለስቦችና ስብስቦች ወደ ገመድ ጉተታ መግባታቸው በታሪክ ያስጠይቃቸዋል፡፡ ሁልጌዜ ይለፈፋል እንጅ አንድነት ስትራተጂክ መርህ መሆኑ፤ የተደጋጋፈና የወል አመራር ዘመናዊ መሆኑ፤ የጋራ ዓላማ፤ የጠራ ራእይ፤ የሚያዋጣ ግብና የጊዜ ገደብ ማስተናገድና መተግበር ለውህልውናው ትግል ሲስተናገድ ቢቻል ወሳኝ መሆኑን አስመርበታለሁ፡፡ ለምን አልተቻለም? በተጨማሪ እኔ የአማራ ፋኖ ኢትዮጵያን ወደ የት እንደሚመራት አላውቅም፡፡ የዳበሳ ጉዞ እየሆነብኝ ነው፡፡
የአማራ ፋኖ በአንድነት ከሰራ ጦርነቱን ከአማራው ክልል ለማውጣት ይቻላል፡፡ ከቆየ ግን የአማራው ሕዝብ ይሰለቻል፡፡ ከፋኖ ሊሸሺ ይችላል፡፡ ትግሉ ሰፋ ብሎና ከአማራው ክልል መጥቆ ወጥቶ፤ ሌሎችንም ተቃዋሚ ሃይሎች እንዲደግፉት አመቻችቶ የሚወጣበት ወቅት ለነገ የሚባል አይደለም፡፡ ይህ ወሳኝ ሂደት ነው፡፡
ይህ ባይሆን ምን ይከሰታል?
ሕዝብ እየሰለቸና ተስፋ እየቆረጠ ይሄዳል፡፡ የአማራ ፋኖ መጥቆ ወደ ከፍተኛ ደረጃ ሊሸጋገር የሚችለው አንድ መላውን የአማራ ሕዝብ የሚወክል ተቋም ወይንም ድርጅት ሲኖረው፤ ሁለት፤ መላውን የአማራ ሕዝብ የሚመራ የሚሊታሪ፤ የፖለቲካ፤ የውጭና የሕዝብ ግንኙነት አመራር ሲመሰርት ሶስት፤ ለአማራ ፋኖ የሚሰበሰበው ድጋፍ በአንድ ቋት ሲደረግና በጥንቃቄ ሲሰራጭ፤ አራት፤ በውጭ ዲፕሎማሲ ያለው ድጋፍ በመናበብ ሲሰራ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡
የአማራ ፋኖ ብሄራዊ ሀይልና የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት ስትራተጂክ የሆነ የዓላማና የመስመር ልዩነት የላቸውም እየተባለ ይነገራል፡፡ ልዩነት ከሌላቸው አንድ ወጥ ድርጅት፤ አንድ ወጥ የሃይል አሰላለፍ፤ አንድ ወጥ አመራር የመመስረት ግዴታ አለባቸው፡፡ ትግሉ የግሰሰብ ጉዳይ አይደለም፡፡ ትግሉ የአንድ አካባቢ ጉዳይ አይደለም፡፡ ትግሉ የዲያስፖራ ጉዳይ ብቻ አየይድደለም፡፡ እኔ ማንም ይሁን ማን ይምራው፤ ብቃት እስካለው ድረስ ይምራ እላለሁ፡፡ በተራም እየተፈራረቁ ሊሰሩ ይችላሉ፡፡ እያንዳንዱ የፋኖ መሪ ሚና ሊኖረው የሚችልበት እድል አለ፡፡
እኔን የሚያሳስበኝ አሁን በአንድ ላይ ለምስራት ካልቻሉ ሥልጣን ቢይዙ ምን ሊየደርጉ ነው? የሚለው የአማራ ሕዝብ ብዙ መሆኑ ነው፡፡
በአማራው ሕዝብ ላይ የሚካሄደው ግፍና በደል መዋቅራዊ እና ተቋማዊ ይዘት ያለው ነው፡፡ አማራ በህይዎት ሊኖርባት የሚቻልባትን ኢትዮጵያ ለመመስረት የሚቻለው በአንድነት እንጅ በመለያየትና በገመድ ጉተታ ሊሆን አይችልም፡፡ የአብይ አገዛዝ ከፋፋይ መሆኑን ስንቀበል፤ በፋኖ በኩል ሚጠየቀው አስገዳጅ መርህ የተለየ መሆን ይኖርበታል፡፡ ፍትሃዊ፤ በህግ የበላይነት የተመስረተ፤ በስነምግባር እንከን የሌለው፤ የዜጎችን መብት የሚያስከብር፤ እውነተኛ የሕዝብ እኩልነትን መሠረት ያደረገ፤ የፖለቲካ ኢኮኖሚው መርህ ሕዝብን ያማከለ፤ ሕዝቡ የሥልጣኑ ባለቤት መሆኑን የሚያመለክት፤ ምርጫ የዲሞክራሲ መሰረት መሆኑን የሚያበስር፤ በኢትዮጵያ ብሄራዊና ግዛታዊ አንድነት ላይ የማያሻማ አቋም ያለው፤ በጠቅላላው ከአሁኑ በዘውግ እና በቋንቋ ከተመሰረተ ስርኣት የተለየ መሆን አለበት፡፡ የሽግግር መንግሥት የሚያስፈልገው ይህንን ስኬታማ ለማድረግ ነው፡፡ የሽግግር መንግሥት ሁሉን ባለድርሻዎች ማሳተፍ ይኖርበታል፡፡
የአማራው ሕዝብ ታሪክ የሚያስተምረኝ ይህ ታላቅ ሕዝብ ጀግንነቱን፤ አገር ወዳድነቱን፤ ያስመስከረ፤ በእኩልትና በአብሮነት የሚያምን፤ ለፍትህ/ርትእ፤ ለክብር ቀናኢ የሆነ፤ ለአገሩ ግዛታዊ አንድነት ቆራጥ የሆነ መሆኑን ወዘተ ነው፡፡ ይህ ሕዝብ አድልዎን፤ አግላይነትን፤ ዘረኛነትን፤ መሰሪነትን፤ ሙሰኛነትን፤ አጎብዳጅነትን ይጠላል፡፡
የአማራ ሕዝብ ሌላውን ጨቁኖ እኔ ብቻ በድሎት ልኑር ብሎ አያውቅም፡፡፡ ከሌላው ጋር ተጋብቷል፤ ተዋልዷል፡፡
የአማራ ፋኖነት ምንድን ነው?
የአማራ ፋኖ ዘላቂ መርህ ከእነዚህ እሴቶች ጋር የሚጣመር እንጅ የተለየ ሊሆን አይችልም፡፡ ለዚህ ነው፤ የአማራ ፋኖ ትግል ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ፋይዳ አለው ብየ የምከራከረው፡፡
ፋኖ ማለት የኔ ትውልድ ባርነትን አይቀበልም፤ የእህቴን፤ የናቴን፤ የአክስቴን መደፈር አልቀበልም፤ የአማራውንም ሆነ የሌላውን እልቂት አልቀበልም፤ የአማራው ወጣት ከትምህርት ገበታ እንዲወጣ ያደረገውን መርህ አልቀበልም፤ የወገኖቸን ከቀያቸው በገፍ መባረር አልቀበልም፤ የወገኖቸን በገፍ መታሰር አልቀበልም፤ የወገኖቸን በረሃብ መሰቃየት አልቀበልም፤ ይህንንና ሌላውን ግፍ ሁሉ አወግዛለሁ፤ ተዋግቸ አዲስ ምእራፍ እከፍታለሁ የሚል ሃይል ነው፡፡
ፋኖ ማለት ቃሌን አከብራለሁ፤ ሕዝቤን በቅንነት አገለግላለሁ፤ የአማራውን የህልውና ትግል መርህ አደርጋለሁ፤ ለራሲ ዝና ሳይሆን ለህዝቤ ክብር እስዋለሁ የሚል ሃይል ነው፡፡
ፋኖ ማለት ለግል ጥቅም፤ ለግል ዝና፤ ለግል ጉራ፤ ለግል ስልጣን አልሻማም፤ ጎጠኛነትን እጠየፋለሁ፤ የዓላማ አንድነትን አከብራለሁ የሚል ሃይል ነው፡፡
ፋኖ ማለት ተንኮልንና ሴራን እጠየፋለሁ፤ ሰርጎ ገቦችን እየለየሁ አዋጋለሁ፤ በወንድሜ ላይ አልተኩስም፤ ኢላማየ ዘግናኙ ስርዐት እንጅ ተራው የኦሮሞ ሆነ የትግራይ ወዘተ ሕዝብ አለመሆኑን አውቃለሁ የሚል ሃይል ነው፡፡
ፋኖ ማለት የህወሃት፤ የኦነግ/ኦህዴድ፤ የብልጽግና ፍንተ ካርታና መርህ አምካኝና ከፋፋይ መርህ አይወክለኝም የሚል ለብሩህና ፈር ቀዳጅ አማራጭ የሚታገል ሃይል ነው፡፡
ፋኖ ማለተ ሃይማኖት፤ ሃብት፤ እድሜ፤ አገር ውስጥና ከአገር ውጭ እና ሌላ መለያ የኔን የፍትህ ትግል አንድነት አይበክለውም በሚል መርህ የሚያምን ሃይል ነው፡፡
ፋን ካለፈው ስህተት የሚማርና ዘላቂ መፍትሄ ለማቅረብ ችሎታ ያላቸውን ምሁራንና ልሂቃን በመሰብሰብ የሚገኝ ታጋይ ሃይል ነው፡፡
ፋኖ ማለት ለህይዎቱ የማይሳሳ፤ ለፍትህ እሞታለሁ ብሎ ቆርጥ የተነሳ፤ የአማራውን የህልውና ትግል ግብ ለማድረስ የሚችል የአማራ ጀግና እንቅስቃሴ ማለት ነው፡፡
ፋኖ ማለት ለሆዳምነት አልገዛም፤ በማንም ሃይል የገንዘብ ፈሰስ አልታለልም፤ ከአላማየ ውጭ አላስብም፤ አልሰራም የሚል ሃይል ነው፡፡
ይህ እንዳለ ሆኖ፤ በመጨረሻ፤ ማለትም ፋኖ ካሸነፈ በኋላ የፋኖ ራእይ፤ ተልኮና አላማ ምንድን ነው? የሚለው መስረታዊ ጥያቄ ለውይይት መቅረብ አለበት፡፡
እኔ የሚካተቱን በከፊል ላቅርብ፤
የአስተሳሰብ ለውጥ ወሳኝ ስለሆነ የአማራ ፋኖ የሚተካው ስርአት ካለፈውና ከአሁኑ የተለየ እንዲሆን እመክራለሁ፡፡ ፋኖ ያገኘውን ከፍተኛ እድል በብልሃት እንዲጠቀምበት እመክራለሁ፡፡
የአማራ ፋኖ ባስቸኳይ አንድ ወጥ የፖለቲካ ፍኖተ ካርታ መቀየስ፤፤ አንድ ወጥ የአማራ ፋኖ ድርጅት ወይንም ተቋም መመስረት፤ አንድ ወጥ አመራር የመመሰየም ግዴታ አለበት፤ ለዚህ ደግሞ ቃል ኪዳን መግባት አለበት፡፡
የአማራ ፋኖ ከሌሎች ተቃዋሚ ሃይሎች ጋር ከአሁኑ ጀምሮ ውይይትና ድርድር መጀመር አለበት፡፡
የወደፊቷ ኢትዮጵያ ሁሉም ዜጎቿ የመሬቷ፤ የወግና የማእረጓ፤ የልማቷ ተከፋይ እንዲሆኑ ማድረግ ግድ ይላል፤ ይህንን መለያችን ለመላው ዓለም የማስታወቅ ግዴታ አለብን፡፡
የወደፊቷ ኢትዮጵያ ማንም ዜጋዋ ረሃብተኛና ስደተኛ እንዳይሆን የፖለቲካ ኢኮኖሚውን መርህ ሕዝብ ያማከለ ማድረግ ግድ ይላል፤ ድህነትን ሙሉ በሙሉ መቅረፍን መርህ ማድረግ ግድ ይላል፡፡ የአማራ ፋኖ ይህንን ግብ ስኬታማ ለማድረግ ቢወስን ይመረጣል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ፤ የወደፊቷ ኢትዮጵያ ለወጣቱ ትውልድ የስራ እድል መፍጠር ይኖርባታል፡፡ ተምሮ መሰደድ መቆም አለበት የሚል ፖሊሲ እንዲካተት እመክራለሁ፡፡
የወደፊቷ ኢትዮጵያ ጥቂቶች በድሎት የሚኖሩባት አብዛኛው የለት ምግብ ለማግኘት የሚባክንባት መሆን የለባትም የሚል አቋም መውሰድ ያስፈልጋል፡፡
የአሁኑን ከፋፍለህ ግዛውና ብላው ሕገ መንግሥትና የአስተዳደር ስርአት ቀይሮ ሕዝቡ የፖለቲካ ስልጣኑ ባለቤት እንዲሆን ማድረግ ግድ ይላል፡፡
ኢትዮጵያዊያን በሙሉ፤ በተለይ ምሁራንና ልሂቃን፤ ፋኖን ጨምሮ በሚያለያዩን ሁኔታዎች ላይ ከማተኮር ይልቅ፤ ከምናጋራቸው፤ ለምሳሌ በዜግነት ሁላችንም ሰብአዊ ፍጥረትና ኢትዮጵያዊ ነን በሚል ላይ ብናተኩር ይመረጣል የሚለውን ምክረ ሃስብ አቀርባለሁ፡፡
በመጨረሻ፤ በውጭ የምንኖር የአማራ ባለድርሻዎች በመሰረታዊ ፖሊሲዎች ላይ ውይይት አድርገን አቋም እንድንወስድ እመክራለሁ፡፡
ድር ቢያብር!!
July 15, 2025