ኤፍሬም ማዴቦ (emadebo@gmail.com)
ባለፉት ስድስት ምዕተ አመታት ኢትዮጵያን የህግ የበላይነት የሚከበርባትና የፖለቲካ ሥልጣን በምርጫ ብቻ የሚያዝበት አገር ለማድረግ ብዙ ሙከራዎች ተደርገዋል፣ ሆኖም ለዲሞክራሲ ያልታደለችው አገራችን ኢትዮጵያ ዛሬም አንድን አምባገነናዊ ሥርዓት በሌላ አምባገነናዊ ሥርዓት ከመቀየር ባህል አልተላቀቀምች። ባለፉት ሃምሳ አመታት ህዝባዊ እንቅስቃሴ ወደ ሥልጣን ያመጣቸው መንግስታት ሁሉ አራት ኪሎን ሲቆጣጠሩ ለህዝብ ቃል የሚገቡት፣ መንግስታችን ነጻነት፣እኩልነትና የዜጎችን ሰብዓዊ መብቶች የሚያከብር መንግስት ይሆናል እያሉ ነው። እየዋለ ሲያድር ግን ዛሬ በሥልጣን ላይ ያለውን የጠሚ አቢይ አህመድን መንግስት ጨምሮ ሁሉም መንግስታት ለህዝብ የገቡትን ቃል ክደው ህዝብን መርገጥ ይጀምራሉ።
ከ27 አመት የህወሓት አምባገነንነት በኋላ በ2010 ዓ.ም. ጠሚ አቢይ አህመድ ወደ ኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ብቅ ሲሉና፣ በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ፓርላማ ውስጥ ያደረጉትን የመጀመሪያ ንግግርና ከዚያም ቀጥሎ በተከታታይ ያደረጓቸውን ንግግሮች የሰማ አገር ውስጥም በውጭ አገሮችም የሚኖር አብዛኛው ኢትዮጵያዊ የአዲስቱ ኢትዮጵያ መሰረት የተጣለ መስሎት ነበር። ጠሚ አቢይም ወደ ሥልጣን ሲመጡ ከሳቸው በፊት ከነበሩት መሪዎች በተለየ መንገድ የተናገሯቸውና “እናደርጋለን” ወይም “አናደርግም” ብለው ለህዝብ ቃል የገቧቸው ተስፋዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዘመናዊ ኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ህዝባዊ ድጋፍ እንዲያገኙ አድርጓቸዋል።
ይህ ጠሚ አቢይ አህመድ የነበራቸው ህዝባዊ ድጋፍ እየተሸረሸረም ቢሆን እስከ 2013ቱ ምርጫ ድረስ ዘልቆ ጠ/ሚ አቢይ ለብልፅግና ፓርቲ አሸንፎ ሥልጣን መያዝ ዋነኛው ምክንያት ነበር። አገር ውስጥ በየግዜው በሚከሰቱ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ችግሮች የተነሳ የኢትዮጵያ ህዝብ በጠ/ሚ አቢይ አህመድ መንግስት ላይ ያለው እምነት እየተሸረሸረ ለመሄዱ ብዙ ምክንያቶች አሉ። ወለጋ ውስጥ ያለምንም ከልካይ በተከታታይ የተካሄደውና አሁንም የሚካሄደው የአማራዎች መገደልና መንግስት ሆን ብሎ የተከተለው የዝምታ መንገድ፣ በአዲስ አበባ ከተማ ላይ የተነሳው የባለቤትነት ጥያቄ፣አንዱ ሆዱን ቋጥሮ ያሰራውን ኮንደሚኒየም ነጥቆ ላልሰራው የመስጠት አባዜ፣አንዱ አዲስ አበባ ውስጥ ያየውን መሬት አጥሮ የራሱ እንዲያደርግ መንገድ ማመቻቸት፣ሌላውን አዲስ አበባ አትገባም ብሎ መከልከልና የአንዳንድ ባለስልጣኖች መረን የለቀቀ የዕብሪት ንግግር የጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት ህዝብ የሰጠውን በታሪካችን ታይቶ የማይታወቅ ደጋፍ እንዲሸረሸር ካደረጉ ኩነቶች ውስጥ ዋና ዋናዎቹ ናቸው።
እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩት የተለያዩ ፀረ-ህዝብ፣ፀረ-አገርና ፀረ-አብሮነት ድርጊቶች ብልጭ ድርግም እያሉ በቀጠሉ ቁጥር፣ አንዴ መጀመሪያ ከህወሓት ጋር የተጀመረው ጦርነት በድል መጠናቀቅ አለበት ሲባል፣አንዴ እነዚህ ድርጊቶች ከጠሚሩ እውቅና ውጭ የሚሰሩ ድርጊቶች ናቸው ሲባል፣አንዳንዴ ደሞ ጠሚሩ እራሳቸውን የከበቡት የሳቸውን ራዕይ በማይጋሩ ሰዎች ነው ሲባል፣ የጠሚ አቢይ አህመድ ፓርቲ ምርጫውን አሸንፎ አዲስ መንግስት ከተመሰረተ በኋላ ድርጊቶቹ ጭራሽ ተቋማዊ መልክ ይዘው የኢትዮጵያን ህዝብ የደም እምባ ማስለቀስ ጀመሩ እንጂ አልቆሙም።
ኢትዮጵያ ዉስጥ ግልፅ፣አካታችና ከየትኛውም የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ ባለድርሻ ነጻ የሆነ የሽግግር መንግስት አቋቁመን፣በአገራዊ ምክክርና በሽግግር ፍትህ ሂደቶች ዉስጥ አልፈን የፖለቲካ ሥልጣን በነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ብቻ የሚገኝበት የፖለቲካ ሥርዓት እስካልፈጠርን ድረስ፣ምርጫ ብሎ ነገር በሥልጣን ላይ ያለውን ገዢ ፓርቲ መልሶ መላልሶ የሚያመጣ ዑደት መሆኑን በደርግና በህወሓት ዘመን ከነበረው ምርጫና፣በ2013 ደሞ የህወሓት ልጆች ካካሄዱት ምርጫ የተማርን ይመስለኛል። ቅቤ ምላሱ አቢይ አህመድ በተከታታይ “እናንተ በምርጫ አሸንፉን እንጂ እኛ ሥልጣን ለማስረከብ ዝግጁ ነን” ይበል እንጂ፣ ይህ ሰው በሥልጣን ላይ እስካለ ድረስ በምንም አይነት የሱ ፓርቲ የሚሸነፍበት ብቻ ሳይሆን፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ትርጉም ባለው መልኩ የፓርላማ መቀመጫ የሚያሸንፉበት ምርጫ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲካሄድ አይፈቅድም። ይህንን ደሞ በአንድ በኩል በ2013ቱ ምርጫ ኦሮሚያ ክልል እና አዲስ አበባ ውስጥ የተካሄደው ምርጫ በግልፅ አሳይቶናል፣በሌላ በኩል ደሞ ሽመልስ አብዲሳ ብልፅግና ፓርቲ የተፈጠረው ለምን እንደሆነ በግልጽ በአደባባይ ተናግሯል። ይህ ማለት ግን የጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት በምርጫ የማይወገድ መንግስት ነው ማለት አይደለም፣ እዚህ ላይ ዋናው መልዕክት እኛ ኢትዮጵያዊያን ዲሞክራሲ የናፈቀውን የኢትዮጵያን ህዝብ ከጎናችን አሰልፈን የጠሚ አቢይ አህመድን መንግስት ካላስገደድን በቀር ብልጽግና ፓርቲ የሚሸነፍበት ምርጫ ኢትዮጵያ ዉስጥ አይኖርም የሚል ነው። ስለዚህ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች ካሁን በኋላ ብልፅግና ፓርቲ አምስት አመት እየጠበቀ እራሱን በሚሾምበት ምርጫ አጃቢዎች የሚሆኑበት ምንም ምክንያት የለም። ኢትዮጵያ ዉስጥ ምርጫ አምባገነኖች አስቀያሚ ፊታቸውን የሚሸፍኑበት ማስክ መሆኑ በተከታታይ ታይቷል፣ይህንን ማስክ ላንዴና ለመጨረሻ ግዜ አውልቀን መጣልና፣ኢትዮጵያ ዉስጥ በምርጫ የተሸነፈ መሪና አሸናፊው ተቃቅፈውና ተጨባብጠው ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር የሚያደርጉበት ሥርዓት እንዲፈጠር የመሰረት ዲንጋይ ማኖር አለብን።
የ2018ቱ ምርጫ ከመካሄዱ በፊት የጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት ብዙ ቆሻሻ ፉቱን የሚሸፍኑ ስራዎችን ሊሰራ ይችላል፣ ለምሳሌ፣ አለም አቀፉን ማህበረሰብ ለማስደሰት ምርጫው ነጻና ፍትሃዊ መሆኑን የውጭ ታዛቢዎች መጥተው መከታተል ይችላሉ ሊል ይችላል፣ ነገር ግን ምርጫ 2013 በግልፅ እንዳሳየን፣ አቢይ አህመድ የምርጫውን ዉጤት የሚወስኑ ዋና ዋና ስራዎችን የሚሰራው በምርጫው ዋዜማ፣በምርጫው ቀን ወይም ምርጫው ተካሂዶ ድምፅ ሲቆጠር ሳይሆን ምርጫው ከመካሄዱ ከወራት በፊት ነው። ይህ ታንኩንም ባንኩንም የሚቆጣጠረው መንግስት የውጭ ታዛቢዎችን የሚጋብዘው ድምጽ ሰጪው ማህበረሰብ ብልፅግናን ካልመረጠ ከፍተኛ ፖለቲካዊና ኤኮኖሚያዊ ዋጋ እንዲከፍል የሚያደርጉ ስራዎችን ከሰራና ምርጫውን ብልፅግና ፓርቲ ቢያንስ 90% እንደሚያሸንፍ ካረጋገጠ በኋላ ነው። የጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት ይህንን ለማድረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ የፌዴራልና የክልል መንግስታት የፖሊስና የደህንነት ተቋሞችን፣አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶችን፣የቀበሌና የክፍለ ከተማ ጽ/ቤቶችን፣ዕድሮችንና እንደ ሴፍቲኔት የመሳሰሉ የዕርዳታ መረቦችን ሁሉ ይጠቀማል። ከዚህ በተጨማሪ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን የምረጡኝ ዘመቻ እንቅስቃሴዎች ባለው አቅሙ ሁሉ ይገድባል፣ህዝብ የሚወዳቸውን የተቃዋሚ ፓርቲ ተወዳዳሪዎች ያስራል፣ይደበድባል እንዳንዴም ይገድላል።
ኢትዮጵያ ዉስጥ ዛሬ ካለው የፓርቲ ሥርዓትና የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥንካሬ አኳያ ሲታይ፣ ከ547 የፓርላማ መቀመጫ ዉስጥ 274ቱን አሸንፎ መንግስት መመስረት የሚችል አንድም ተቃዋሚ ፓርቲ የለም፣የሚያሳዝነው ይህ ብቻ አይደለም፣ በተቃዋሚ ፓለቲካ ፓርቲዎች መካከል ያለውን ይህ ነው የማይባል እርስ በርስ መናበብ፣መተባበርና ጥምረት የመፍጠር ፍላጎት ስንመለከት፣በዛሬዋ ኢትዮጵያ ዉስጥ ብልፅግና ፓርቲ የሌለበትና ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ብቻ ያቀፈ የጥምር መንግስትም ሊመሰረት አይችልም። ኢትዮጵያ ዉስጥ የምርጫ ቦርድ እውቅና ያላቸው ከ45 በላይ ፓርቲዎች እንዳሉ ይነገራል፣ሆኖም እነዚህ በተቋቋሙበት መሰረታዊ አላማም ሆነ በድርጅታዊ አቅማቸው ደካማ የሆኑ ፓርቲዎች መኖራቸው የሚታወቀው ቁጥራቸው በሜዲያ ሲነገር ነው እንጂ በሚሰሩት ስራ አይደለም። በዚህ ጽሁፍ ዉስጥ የተጠቀሱት ግዙፍ የአገራችን እውነቶች በግልፅ የሚነገሩን ነገር ቢኖር ለምርጫ 2018 እንዴት እንደምንዘጋጅ ሳይሆን፣ዋናውና ትልቁ ስራችን የምርጫ 2018 ሂደት ከመጀመሩ በፊት፣ አንደኛ- ምርጫው ለሁሉም ተወዳዳሪዎች እኩል ዕድል የሚሰጥ ምርጫ መሆኑን፣ሁለተኛ- በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች ምርጫ ለማካሄድ ምቹ ሁኔታ መኖሩን፣ሦስተኛ-ተቃዋሚ ፓርቲዎች በጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት ላይ ጫና ማሳደር በሚችሉበት ደረጃ ጥምረት መፍጠራቸውን ማረጋገጥ ነው። የሰው ልጅ አንዴ ይሳሳታል፣ምናልባት ለሁለተኛ ግዜም ሊሳሳት ይችላል፣ ነገር ግን በምንም አይነት የሚያስብ አዕምሮ ያለውና በተለይ ዛሬ በመረጃ ቴኮኖሎጂ ዘመን የሚኖር ሰው በተከታታይ አንድ አይነት ስህተት አይሰራም።
ምርጫ 2013
ምርጫ ቦርድ በአዲስ መልክ መዋቀሩና አዲስ አመራር ማግኘቱ፣ አዲሱ የምርጫ ቦርድ አመራር ወዲያውኑ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በመነጋገር የምርጫ ህግና የፓርቲዎች መተዳደሪያ ህግ ማሻሻያ ማድረጉ፣አዳዲስ አገር አቀፍ ፓርቲዎች መፈጠራቸውና ኢህአዴግ የተባለውና የኢትዮጵያን ፖለቲካ ለ27 አመት የተቆጣጠረው የአራት ብሔር ድርጅቶች ግንባር ፈርሶ ብልፅግና የሚባል አንድ ወጥ ፓርቲ መፈጠሩ የ2013ቱን ምርጫ ብዙዎች በጉጉት እንዲጠብቁት አድርጎ ነበር። በእርግጥም ብልፅግና፣ ኦፌኮ፣ ኦነግና ሌሎችም የኦሮሞ ፓርቲዎች ኦሮሚያ ውስጥ፣ብልፅግና እና ኢዜማ ደቡብ ክልል ውስጥ፣ ብልፅግና፣አብንና፣እናት አማራ ክልል ውስጥ በተለይ ደሞ ኢዜማ፣ እናት፣ባልደራስ፣ብልፅግና፣ህብር ኢትዮጵያና ነጻነትና እኩልነት ፓርቲዎች አዲስ አበባ ውስጥ የሚያደርጉትን የምርጫ ፉክክር ለማየት ከፍተኛ ህብዝዊ ጉጉት ነበር። ነገር ግን ሦስት የተለያዩ ክስተቶች የ2013ቱ ምርጫ በኢትዮጵያ የምርጫ ታሪክ ውስጥ መጫወት የነበረበትን ሚና እንዳይጫወት አደርገዋል። ሁለቱ ክስተቶች በቀጥታ ከጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት ጋር የተያያዙ ሲሆን አንደኛው ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር የተያያዘ ነው።
ኦሮሚያ ክልልና አዲስ አበባ በ2013ቱ ምርጫ ዘመቻ ከፍተኛ ፉክክር ይታይባቸዋል ተብሎ ከሚጠበቁ ቦታዎች ቀዳሚዎቹ ነበሩ። አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ትኩሳት መለኪያ መሆኗ፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የኔ ናት የሚላት ከተማ መሆኗ፣አገራዊ ማንነት ጎልቶ የሚታይባት ከተማ መሆኗና፣ የባለቤትነት ጥያቄ በተደጋጋሚ የተነሳባት ከተማ መሆኗ፣ ከምርጫው በኋላ አዲስ አበባን ማን ያስተዳድራል የሚለው ጥያቄ የብዙ ኢትዮጵያዊያንን ቀልብ የሳበ ጥያቄ ነበር። ደሞም አዲስ አበባ ውስጥ ለምርጫ ይቀርባሉ ተብለው ይጠበቁ የነበሩት ባልደራስ፣ እናት፣ ኢዜማ፣ኦነግ፣ ኦፌኮና ብልጽግናን የመሳሰሉ ፓርቲዎች መሆናቸው ከእነዚህ ፓርቲዎች ማን ያሸንፋል ወይም አዲስ አበባ ውስጥ የጥምር አስተዳደር ይፈጠራል ወይ የሚለው ጥያቄ የብዙ ኢትዮጵያዊያን ልብ ሰቅዞ የያዘ ጥያቄ ነበር። ኦፌኮ፣ ኦነግና ብልጽግና ከፍተኛ ውድድር ያደርጉበታል ተብሎ ይጠበቅ የነበረው የኦሮሚያ ክልል ምርጫም ብዙዎች በጉጉት የሚጠብቁት ምርጫ ነበር፣ በተለይ ጀዋር መሐመድ ኦፌኮን ከተቀላቀለ በኋላ የነበረውን የኦሮሚያ ክልል የምርጫ ካርታ ለተመለከተ ሰው ኦሮሚያ ውስጥ ማን እሸንፎ ክልሉን ይመራል የሚለውን ጥያቄ በቀላሉ መመለስ አለመቻሉ የኦሮሚያ ክልል ምርጫ ብዙዎች በግጉት የሚጠብቁት ምርጫ ሆኖ ነበር።
ሆኖም የረባ የምርጫ ውድድር ካልታየባቸውና የምርጫው ውጤት ወደ አንድ ወገን ያጋደለ እንዲሆን ምርጫው ከመካሄዱ በፊት ከፍተኛ መንግስታዊ ሴራ የተሰራባቸው ሁለት ቦታዎች ቢኖሩ አዲስ አበባና ኦሮሚያ ክልል ነበሩ። ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ከብልፅግና ፓርቲ ውጭ ሌሎች ፓርቲዎች እንዳይወዳደሩ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትን የማሰር፣የማስፈራራትና ከዚህ አካባቢ ካልጠፋህ እንገለሃለን የሚል ማስጠንቀቂያ ሁሉ ነበር። ለምሳሌ፣የኦፌኮና የኦነግ መሪዎች ታስረዋል፣ ቢሾፍቱ ውስጥ የኢዜማውን ግርማ ሞገስን እንደግልሃለን ብለው ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ሰጥተው ገድለውታል። አዲስ አበባ ውስጥም ህዝብ ከብልፅግና ውጭ ሌሎች ፓርቲዎችን እንዳይመርጥ የብልፅግና ካድሬዎች ከቤት ቤት እየዞሩ ድርጅታዊ ስራ ሰርተዋል፣ ሴፊቲኔት የሚባለውን የምግብ ለስራ ፕሮግራም በመጠቀም ደሃውን ማህበረሰብ በሆዱ መጥተውበት ብልፅግናን እንዲመርጥ አድርገውታል። ለብልፅግና ታማኝ የሆኑ ሰዎች የትም ይኑሩ የት በቀላሉ ተመዝግበው ብልፅግናን እንዲመርጡ ተደርገዋል፣ በተለይ የኦሮሚያ ክልል አጎራባች በሆኑ የአዲስ አበባ ክፍለ ከተማዎች ውስጥ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ያልሆኑ ዜጎች በከፍተኛ ቁጥር የምርጫ ካርድ እንዲያገኙ ተደርገው ብልፅግናን እንዲመርጡ ተደርጓል። ኦሮሚያ ክልልና አዲስ አበባ ውስጥ የምርጫ ተወዳዳሪዎችና የመራጮች ምዝግባ ሲካሄድ የተከሰቱ አንዳንድ ክስተቶችና ባጠቃላይ የምርጫ የምዝግባው ሂደት ለምርጫ ቦርድ ጭምር ፈታኝ እራስ ምታቶች ነበሩ።
ዛሬ በስራ ላይ ያሉትን የአማራ፣የኦሮሚያ፣የደቡብ ክልል፣የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና የፌዴራሉን ፓርላማ የመቀመጫ ስብጥር ስንመለከት 100% የብልፅግና ተወካዮች ያሉት አዲስ አበባ ምክር ቤትና ጨፌ ኦሮሚያ ዉስጥ ሲሆን በአገራዊ ፓርላማው ውስጥም 100% የብልፅግና ተወካዮች የመጡት ከእነዚሁ ሁለት አስተዳደሮች ነው። አማራ ክልልና ደቡብ ክልል ቁጥራቸው አናሳ ቢሆንም የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት በፌዴራልና በክልል ፓርላማዎች ውስጥ መቀመጫ ማግኘት ችለዋል። ይህ የሚያሳየን ብልፅግና ፓርቲ ኦሮሚያና አዲስ አበባ ውስጥ የሰራቸው ቅድመ ምርጫ የውንብድና ስራዎች ምርጫውን ለማሸነፍ ብቻ ሳይሆን፣ አዲስ አበባና ኦሮሚያ ውስጥ አንድም የተቃዋሚ ፓርቲ ተወዳዳሪ እንዳያሸንፍ ለማድረግ መሆኑን ነው።
ሌላው ምርጫ 2013 በኢትዮጵያ የምርጫ ታሪክ ውስጥ በተለይ በዲሞክራሲ ጅምራችን የመጀመሪያ ምዕራፍ ላይ ትልቅ አሻራ ጥሎ እንዳያልፍ በማድረግም ባለማድረግም አፍራሽ ሚና የተጫወቱት የፖለቲካ ፓርቲዎች ናቸው። በሚያራምዱት የፖለቲካ አጀንዳ፣በአላማና ግብ የማይለያዩ ኢዜማን፣ባልደራስን፣እናት ፓርቲንና ህብር ኢትዮጵያን የመሳሰሉ ፓርቲዎች የ2013ቱን ምርጫ እንዴት ግንባር ፈጥረው መጋፈጥ እንደሚገባቸው ባለማወቃቸው፣ ባለመፈለጋቸውና፣ ስትራቴጂያዊ አጋርንና ገዢውን ፓርቲ ብልፅግናን ለይተው ማየት ባለመቻላቸው እርስ በርስ ሲነታረኩና ሲጠላለፉ አዲስ አበባን ለብልፅግና ፓርቲ አሳልፈው ሰጥተዋል።
በ2013ቱ ምርጫ መንግስት መመስረት የሚያስችለውን የፓርላማ መቀመጫ ብቻውን ማሸነፍ የሚችል ተቃዋሚ ፓርቲ አልነበረም፣ ነገር ግን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ትናንት ላይ ሆነው ዛሬን ተመልክተውና ከማያዋጣቸው መጠላለፍና የተናጠል ሩጫ ተላቅቀው ተባብረው በጋራ ቢሰሩ ኖሮ ዛሬ አዲስ አበባን የሚያስተዳድረው ከብልጽግና ውጭ የሆነ ፓርቲ ወይም የፓርቲዎች ጥምረት መሆን የሚችልበት መልካም አጋጣሚ ነበር። በአገር አቀፍ ደረጃም ቢሆን ተቃዋሚ ፓርቲዎች አሸንፈው መንግስት የመመስረት አቅም ባይኖራቸውም ለ2018ቱ ምርጫ ጠንካራ ተወዳዳሪዎች መሆን የሚችሉበትን ሁኔታ መፍጠር ይችሉ ነበር። ለምሳሌ፣ ባልደራስ፣ኢዜማ፣ እናት፣ህብር ኢትዮጵያና ነጻነትና እኩልነት ፓርቲዎች ስትራቴጂያዊ ጥምረት ፈጥረው የ2013ቱን ምርጫ በጋራ ተጋፍጠው ቢሆን ኖሮ ዛሬ በስራ ላይ ያለው የኢትዮጵያ ፓርላማ ገዢውን ፓርቲ ተጠያቂ ማድረግ የሚችልና የህዝብን ቀልብ የሚስቡ ክርክሮች የሚታዩበት የተቃውሞ ፓለቲካ መድረክ መሆን ይችል ነበር፣ ይህ ደሞ ህዝብ በሚቀጥለው ምርጫ የገዢው ፓርቲ ጫና ቢኖርበትም፣ልክ እንድ ምርጫ 97 ጫናውን ተቋቁሞ ድምጹን ለተቃዋሚ ፓርቲዎች ሊሰጥ የሚችልበት ድፍረት ይፈጠር ነበር።
ባለፉት ሶስትና አራት አመታት የጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት የሚቀጥለውን ምርጫ ብቻ ሳይሆን ባጠቃላይ ምንም አይነት የተቃውሞ ፖለቲካ እንቅስቃሴዎችን መቆጣጠር የሚያስችለውን የተለያዩ ህጋዊና ተቋማዊ እርምጃዎች ወስዷል፣ በተለይ በቅርቡ የምርጫ ቦርድን አዋጅ ለማሻሻል ለፓርላማው የቀረበው የህግ ረቂቅ፣ጠሚ አቢይ አህመድ እንደ እናት፣ኢህአፓና ህብር ኢትዮጵያን የመሳሰሉ በገዢው ፓርቲ ላይ ጠንካራ መግለጫ የሚያወጡ ፓርቲዎችን ማክሰም እንዲችል ሆኖ የረቀቀ ህግ ነው። ባጠቃላይ ከምርጫ 2013 በኋላ ኢትዮጵያ ዉስጥ ብዙ ነገሮች ተለዋውጠዋል፣እነዚህ የተለወጡ ነገሮች ብዙዎቹ ኢትዮጵያ ዉስጥ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓትን የሚያዳክሙና አውራ ፓርቲ ሥርዓትን የሚያጠናክሩ ናቸው። ከዚህ ቀጥሎ የቀረቡት አራት ጉዳዮች የጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ዉስጥ ብቸኛ ተዋናይ ለመሆን የወሰዳቸው እርምጃዎች ናቸው፣ እነዚህ እርምጃዎች የኢትዮጵያ ህዝብ በምርጫም ሆነ በፓርቲዎች ሰላማዊ ትግል መንግሥት ይቀየራል የሚል እምነት እንዳይኖረው አድርገዋል።
- በ2013 ምርጫ ላይ ከፍተኛ ልምድ ያካባቱ የምርጫ ቦርድ መሪዎችና የተለያዩ የክፍል ሃላፊዎች አሁን ላይ ለብልፅግና ታማኝ በሆኑ ሰዎች በመተካታቸው መጪው ምርጫ ምን እንደሚመስል ካሁኑ መገመት ሳይሆን እንድናውቅ አድርጎናል
- በቅርቡየምርጫ ቦርድን አዋጅ ለማሻሻል ለፓርላማው የቀረበው የህግ ረቂቅ በግልጽ እንደሚያሳየው ብልፅግና ፓርቲ ከሱ ፍላጎት ውጭ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎችን ህገ ወጥ ለማድረግ ዝግጅቱን የጨረሰ ይመስላል
- የጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት በቀጥታ የሚቆጣጠራቸውን የፍትህ ተቋማት ብቻ ሳይሆን ከዚህ ቀደም አንጻራዊ በሆነ መልኩ መንግስትን ተጠያቂ ለማድረግ የሞክሩ የሰብዓዊ መብት ተቋማትን ጭምር የገዢው ፓርቲ አገልጋዮች እንዲሆኑ አድርጏል፣ ከእነዚህ ተቋሞች ውስጥ አንዱ ኢሰመኮ ነው
- ብልፅግና ፓርቲ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን አብረን እንስራ የሚል ጥሪ በማቅረብ ህዝብ በከፍተኛ ደረጃ የሚጠብቃቸውን ፓርቲዎች የቤት ውስጥ አገልጋይ በማድረግ በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል መተማመንና ህብረት እንዳይኖር አድርጓል
የኢትዮጵያን ፖለቲካ ያለፉት ሰባት አመታት ለተከታተለ ሰው ብልፅግና የ2013ቱን ምርጫ ለማሸነፍ የሄደበት መንገድ ብዙ ሊያሳስበው የሚገባው አይመስለኝም፣ እሱ አልፏል! እኛን ኢትዮጵያዊያንን ሊያሳስበን የሚገባው እንደ ምሁር፣ እንደ ልህቅ፣ እንደ ፖለቲካ ፓርቲና ባጠቃላይ እንደማህበረሰብ ከ6ኛው አገራዊ ምርጫ ተምረን በ2018 ዓ.ም. ለሚደረገው 7ኛው አገራዊ ምርጫ የምናደርገው ምንም ዝግጅት አለመኖሩ ነው። በኔ እምነት እኛ ኢትዮጵያዊያን በተለይ የፖለቲካ ፓርቲዎቻችና ውጭና አገር ዉስጥ የሚገኙ ሜዲያዎች፣ ገዢውን ፓርቲ ብልፅግናን የማይረሳ ትምህርት ማስተማር የምንችልበት መልካም አጋጣሚ ፊት ለፊታችን ላይ እየጠበቀን ነው።
ይህንን አጋጣሚ በሚገባ ካልተጠቀምን፣ በ2013ቱ ምርጫ ኦሮሚያና አዲስ አበባ ውስጥ ያየነው የምርጫ ቅርጫ በ2018ቱ ምርጫ ወደ ብዙ አካባቢዎች ሊዛመት እንደሚችልና ኢትዮጵያ የአንድ አውራ ፓርቲ መፈንጪያ አገር ሆና ለረጂም ግዜ እንደምትቆይ ምንም ጥርጥር የለውም። በእርግጥም ዛሬ የኦሮሚያን ክልል መንግስትና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን ተቋማዊ ድጋፍ እያገኘ አገር የሚያምሰውን የጠሚ አቢይ አህመድን መንግስት አደብ ካላስገዛንና፣ የ2018ቱ ምርጫ ሂደት ከመጀመሩ በፊት መስራት ያለብንን ትልልቅ ስራዎች ነገ ዛሬ ሳንል ካሁኑ ካልጀመርን፣ የዲሞክራሲ ጅምራችን መኮላሸቱ ብቻ ሳይሆን የአገራችንን አንድነትም አደጋ ላይ ይወድቃል።
ህወሓት/ኢህአዴግ ኢትዮጵያ ውስጥ ከተከላቸውና ብልፅግና ፓርቲ በኩራት ከወረሳቸው ብልሹ ባህሎች ውስጥ አንዱ በፓርቲና በመንግስት መካከል ምንም ልዩነት አለመኖር ነው። በዛሬዋ ኢትዮጵያ ከትግራይ ክልል ውጭ በክልልም በማዕከልም የፖለቲካ ሥልጣንን የሚቆጣጠረው ብልፅግና ፓርቲ ነው፣ይህ ማለት ደሞ በፓርቲና በመንግስት መካከል ምንም ልዩነት በሌለባት ኢትዮጵያ ውስጥ በክልልም በፌዴራል ደረጃም የሚገኙ የህዝብ ተቋም፣ ንብረትና ፋይናንስ በሙሉ የብልጽግና ፓርቲ የግል እሴቶች ናቸው ማለት ነው። በ2013ቱ ምርጫ ላይ በግልጽ እንደታየው፣ብልፅግና ፓርቲ እንዳሰኘው በሚጠቀምባቸው የመሰብስቢያ አዳራሾች ውስጥ ተቃዋሚ ፓርቲዎች መሰብስብ አይችሉም ነበር። ተቃዋሚ ፓርቲዎች የምርጫ ዘመቻ ሲያደርጉ የሚንቀሳቀሱት መኪና ተከራይተው ሲሆን ብልጽግና ፓርቲ ግን የህዝብ ንብረት በሆነ መኪና እንዳሰኘው ይንቀሳቀሳል። በወረዳ ደረጃ የሚገኙ የብልጽግና ካድሬዎች የተቃዋሚ ፓርቲ ተወዳዳሪዎችንና ደጋፊዎችን ያስፈራራሉ፣ ያስራሉ፣ ይደበድባሉ። ብልፅግና ፓርቲ በግብር ከፋዩ ህዝብ የሚተዳደሩትን ሜዲያዎች እንዳሰኘው ይጠቀማል፣ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዲህ አይነቱን ዕድል አያገኙም። ስለዚህ እኛ ኢትዮጵያዊያን ስለ 2018ቱ ምርጫ ማውራት ያለብን እነዚህና ሌሎችም ጉዳዮች መልክ ከያዙ ብቻ ነው።
ምርጫ 2018 ለጠሚ አቢይ አህመድ መንግስትና ለወደፊትም የአምባገነንነት ሃሳብ ላላቸው ሰዎችና ቡድኖች፣ ለተቃዋሚ ፓርቲዎችና ባጠቃላይ ለኢትዮጵያ ህዝብ የማይረሳ ትምህርት አስተምሮ ማለፍ አለበት። ምርጫ 2018 በኢትዮጵያ የመድበል ፓርቲ ሥርዓትና ባጠቃላይ በዲሞክራሲ ግንባታ ሂደታችን ውስጥ እንደ ዶጋሌና እንደ ካራማራ ድል ሁሌም የሚዘከር ክስተተ መሆን አለበት፣ ይህ እንዲሆን ምህሩ፣ወጣቱ፣ሲቪክ ማህበራት፣የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሜዲያው እጅና ጓንት ሆነው መስራት አለባቸው። የእነዚህ ባለድርሻዎች ትልቁ ስራ ኢትዮጵያ ዉስጥ ገዢ ፓርቲዎች በምርጫ ተሸንፈው ሥልጣን በሰላማዊ መንገድ ለአሸናፊው ፓርቲ የሚያስረክቡበት ሥርዓት እንዲፈጠር መንግስትን ማስገደድ ነው።
ኢትዮጵያ ዉስጥ መስከረም ጠባ ሊባል ከ75 ቀን ያነስ ግዜ ነው የቀረው፣ አዲሱ አመት 2018 ደሞ የምርጫ አመት ነው። እኛ ኢትዮጵያዊያን በ2018 መዘጋጀት ያለብን በምርጫው ለመሳተፍ ሳይሆን፣ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ እንዲኖር መሟላት ያለባቸውን ቅድመሁኔታዎች አዘጋጅተን የጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት እንዲያውቃቸው ማድረግ ነው። የ2018 ምርጫ ሂደት ከመጀመሩ በፊት የጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት ማሟላት ያለበትን የተለያዩ ቅድመ ሁኔታዎችን በተመለከተ ድምፅ ሰጪው ማህበረሰብ፣ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ሜዲያ በተናበበና በተቀነባበረ መልኩ የየራሳቸውን ሚና መጫወት አለባቸው፣በተለይ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ሜዲያው ህዝብን ማሳወቅ፣መቀስቀስና ማስተባበር አለባቸው።
ድምፅ ሰጪው ማህበረሰብ
እኛ ኢትዮጵያዊያን ስንተባበርና አንድ ላይ ስንቆም፣ሳይወድ በግዱ ድምጻችንን የሚሰማ እንጂ ሊያሸንፈን ወይም ሊያንበረክከን የሚችል ምንም አይነት ኃይል እንደሌለ ከጎረቤታችን ከኬንያ መማር ያለብን ይመስለኛል። የኬንያ መንግስት ከአለም አቀፉ የገንዝበ ተቋም( IMF) ጋር ተስማምቶ ግብር ለመጨመርና ማህበራዊ ወጪዎችን ለመቀነስ ያደረገውን ሙከራ የኬንያ ህዝብ በነቂስ ወጥቶ በመቃወም የስምምነቱ ዋና ክፍል እንዲሰረዝ አድርጓል። እዚያው ኬንያ ዉስጥ በቅርቡ አንድ ማህበራዊ አንቂ በፖሊስ ምርመራ ላይ እያለ መሞቱ ሲሰማ ኬንያውያን ምድር አንቀጥቅጥ የተቃውሞ ሰልፍ በማድረግ መንግስትን ኮንነዋል። እኛ አገር ከIMF ጋር የተደረገው ስምምነት የምንጎርሰውና የምንቀምሰውን አሳጥቶናል፣ ማህበራዊ አንቂዎችን ብቻ ሳይሆን ባጠቃላይ ዜጎችን እንደ በግ እየጎተቱ ማሰር፣ማፈንና መደብደብ የተለመደ ድርጊት ነው፣ ግን ምንም አይነት ህዝባዊ ተቃውሞ ስናደርግ ወይም ለማድረግ ስንሞክር አንታይም። ይህ ድህነት፣መከራና በደል በነጋ በጠባ እላያችን ላይ ሲጫን እጅ አጣጥፎ ዝም የማለት አባዜ መቆም አለበት። የኢትዮጵያ ህዝብ አድርግ ያሉትን ሁሉ አሜን ብሎ መቀበል ብቻ ሳይሆን፣ ሊደረግልኝ ይገባል ብሎ የጠየቀው ጥያቄ እስካልተመለሰለት ድረስ፣እሱም አድርግ የተባለውን አላደርግም ማለት መጀመር አለበት። በከተማና በገጠር የሚኖረው እያንዳንዱ ድምፅ ሰጪ ኢትዮጵያዊ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በመናበብ፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከምርጫው በፊት መሟላት አለባቸው ብለው ለመንግስት የሚያቀርቧቸው ቅድመ ሁኔታዎች አግባብ ያለው መልስ እስካላገኙ ድረስ፣ ለምርጫ አልመዘገብም ወይም በምርጫው ላይ አልሳተፍም ማለት አለበት። ምርጫ 2018 የኢትዮጵያ ህዝብ በምርጫ ስም የሚመጣ አምባገነን ሥርዓትን አልቀበልም የማለት ጡንቻውን የሚያሳይበት ትዕይንት መሆን አለበት።
ፖለቲካ ፓርቲዎች
ኢትዮጵያ ዉስጥ ትክክለኛ የመድበለ-ፓርቲ ዲሞክራሲ እንዲዳብርና ሁሉም ፓርቲዎች በነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ተወዳድረው ማሸነፍ የሚችሉበት ከገዢው ፓርቲ ቁጥጥር ነጻ የሆነ ምህዳር እንዲፈጠር የሚፈልጉ የፖለቲካ ፓርቲዎች መተባበር፣መናበብ፣መረዳዳትና አንድ ላይ መስራት ያለባቸው ግዜ ቢኖር ከአሁኑ ሰአት ጀምሮ የምርጫ 2018 ዝግጅት ሂደት እስኪጀምር ያለው ግዜ ነው። ከአሁን ጀምሮ እስክ ግንቦት 2018 ያለው ግዜ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፓርቲዎች መንግስትን በተናጠል ሳይሆን እንደ ቡድን በጋራ የሚያናግሩበት ግዜ መሆን አለበት። የ2018ቱን ምርጫ በተመለከተ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ትልቁ ጥያቄ መሆን ያለበት እንዴት ብልፅግናን አሸንፈን ሥልጣን እንይዛለን የሚል ሳይሆን፣ ምርጫ 2018 ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ እንዲሆን መንግስትን ለማስገደድ የምንችለው ምን ብናደርግ ነው የሚል ጥያቄ መሆን አለበት። ይህንን ለማድረግ ደሞ የፖለቲካ ፓርቲዎቻችን ካሁን ጀምረው 7ኛው ዙር የምርጫ ሂደት ከመጀመሩ በፊት መመለስ ያለባቸውን የሚከተሉትን ቅድመሁኔታዎች ለመንግስትን ማቅረብ አለባቸው፣ መንግስት እነዚህን ቅድመሁኔታዎች የማያሟላ ከሆነ፣ የፓርቲዎች ህብረት በምርጫው አንሳተፍም የሚል ውሳኔ በማሳለፍ፣ውሳኔውን ለኢትዮጵያ ህዝብ፣አገር ውስጥ ለሚገኘው የዲፕሎማሲ ማህበረሰብና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ማሳወቅ አለበት። ይህ እጅግ በጣም አስፈላጊ ስራ መሰራት ያለበት የምርጫ ዘመቻው ከመጀመሩ ከታህሳስ 2018 በፊት መሆን አለበት። ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ቅድመ ሁኔታዎች ከምርጫው በፊት ካልተሟሉ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ አንሳተፍም የሚል የጋራ ውሳኔ ማሳለፍ ብቻ ሳይሆን፣የሚቀጥለው አቅጣጫ ምን መሆን እንዳለበት ካሁኑ ተዘጋጅተው ህዝብንም ለሚቀጥለው ምዕራፍ ማዘጋጀት ይኖርባቸዋል።
- አማራ ክልል የሚካሄደው ጦርነት በአስቸኳይ ቆሞ መንግስት ከታጣቂዎች ጋር ዘላቂ ሰላም መፍጠር አለበት
- ትግራይ ክልል የ2013ቱ ምርጫ አልተካሄደም፣ ትግራይ ዉስጥ አሁንም ለምርጫ አመቺ የሆነ ሁኔታ የለም፣ስለዚህ መንግስት ከምርጫው በፊት ከትግራይ ኃይሎች ጋር የፕሪቶሪያውን ስምምነት በግልፅ ያካተተ ስምምነት በማድረግ የትግራይን ሰላምና መረጋጋት ማረጋገጥ አለበት
- ኦሮሚያ ክልል ዝርፊያ፣አፈና፣ግድያና ማለቂያ የሌለው የትጥቅ ትግል የሚካሄድበት ክልል ነው፣ይህ ክልል ሰላምና መረጋጋት የሰፈነበት ክልል መሆኑ ከምርጫው በፊት መረጋገጥ አለበት
- የምርጫ ቦርድ ከመንግስት ተፅዕኖ ነጻ በሆኑ መሪዎች መመራቱ መረጋገጥ አለበት
- ምርጫ 2018 ከመጀመሩ በፊት ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ብልፅግና ፓርቲ እኩል የምርጫ ውድድር ማድረግ የሚችሉበት ምህዳር መፈጠሩ መረጋገጥ አለበት
- ብልፅግና ፓርቲ ካሁን በኋላ የመንግስትን ተቋም፣ፋይናንስና ንብረት ለምርጫ ዘመቻ መጠቀም አለመቻሉ በምርጫ ቦርድና በሌሎችም ተቋሞች መረጋገጥ አለበት
- የምርጫ ቦርድ እውቅና ኖሯቸው በምርጫ የሚወዳደሩ ፓርቲዎች ሁሉ በፌዴራል መንግስትና በክልል መንግስታት ቁጥጥር ስር ባሉ ሜዲያዎች፣ አዳራሾችና አደባባዮች ላይ እኩል የምርጫ ዘመቻ ማካሄድ መቻላቸው መረጋገጥ አለበት
- የምርጫ ዘመቻው ተጀምሮ እስኪያልቅ ድረስ በሆነ ባልሆነው የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችን፣የምርጫ ተወዳዳሪዎችንና የፓርቲ አባላትን ማሰርና ማንገላታት መንግስትን በህግ የሚያስጠይቅ መሆኑ መረጋገጥ አለበት
የፖለቲካ ፓርቲዎች እነዚህ ቅደመ ሁኔታዎች እንዲሟሉ መንግስትን ከመጠየቅ ባሻገር፣ቅድመ ሁኔታዎቹን በተከታታይ ለህዝብ ማሳወቅና፣ ህዝብ የእያንዳንዱን ቅደመ ሁኔታ ዝርዝር እንዲያውቅ ማድረግ አለባቸው። የፖለቲካ ፓርቲዎች ያላቸው ብቸኛ ኃይል ህዝብ ነውና፣ ይህንን ኃይል እንዴትና መቼ መጠቀም እንዳለባቸው ማወቅ አለባቸው። ይህ በእንዲህ እንዳለ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጠንካራ ድርጅታዊ ተቋም እንዲኖራቸው፣በፋይናንስና በሌሎችም አስፈላጊ ግብአቶች እራሳቸውን ችለው መንቀሳቀስ እንዲችሉና፣ በፖለቲካ ፕሮግራማቸውና ባላቸው የፖሊሲ አማራጭ ከገዢው ፓርቲ የተሻሉ መሆናቸውን ህዝብ እንዲያውቀው ማድረግ አለባቸው፣ይህንን ለማድረግ ደሞ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የመሰባሰብና እራሳቸውን ወደ ትልልቅ አገራዊ ፓርቲ የመቀየር ስራ ካሁን መስራት መጀመር አለባቸው። በገዢው ፓርቲና በመንግስት መካከል ምንም ልዩነት በሌለባት ኢትዮጵያ ዉስጥ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሁሉንም ነገር ከሚቆጣጠረው ከብልፅግና ፓርቲ ጋር መወዳደር የሚችሉት በቁጥር ብዛት ስላላቸው ሳይሆን በቁጥር አንሰው ድርጅታዊ ጥንካሬና ህዝባዊ መሰረት ሲኖራቸው ነው። ዛሬ ኢትዮጵያ ዉስጥ ያለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ብዛት ለራሳቸው ለፖለቲካ ፓርቲዎቹ፣ለሥርዓተ ፓርቲ ዕድገታችንና ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ጥረታችን እንቅፋት ከመሆን ውጭ ሌላ ምንም ጥቅም የለውም። ስለዚህ የወደፊቱን ኢትዮጵያ በተመለከተ ተመሳሳይ አመለካከት ያለቸውና በርዕዮተ አለም የሚቀራረቡ ፓርቲዎች ተገናኝተው በመነጋገር ወደ ሶስትና አራት አገራዊ ፓርቲነት መቀየር አለባቸው።
ሜዲያ
ምርጫ 2018ን ፈር በማስያዙ ሂደት ዉስጥ ሜዲያዎች የሚጫወቱት ሚና ብዙ ነው፣ በአንድ በኩል ድምፅ ሰጪው ማህበረሰብ ሚናውን እንዲያውቅና ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር እንዲናበብ የቅስቀሳ ስራ ይሰራሉ፣ በሌላ በኩል ደሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች መንግስት እንዲያሟላ የጠየቁትን ቅድመ ሁኔታዎች ለህዝብ በተከታታይ ከማሳወቅ ባሻገር፣ መንግስት ለቅድመ ሁኔታዎቹ ምን አይነት ምላሽ እየሰጠ መሆኑን በተከታታይ መዘገብ አለባቸው። የፖለቲካ ፓርቲዎች ባስቀመጡት የግዜ ሰሌዳ ውስጥ መንግስት ቅደመ ሁኔታዎቹን የማያሟላ ከሆነ፣ህዝብ ምን ማድረግ እንዳለበት ተከታታይ አቅጣጫ የማሳየት ስራዎች መስራት አለባቸው። ባጠቃላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለመንግስት ቅድመ ሁኔታዎችን ካቀረቡበት ቀን ጀምሮ ቅድመ ሁኔታዎቹ ምላሽ እስኪያገኙ ድረስ፣ውጭና አገር ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ሜዲያዎች፣ በፓርቲዎችና በመንግስት መካከል ለሚደረገው ለእያንዳንዱ የግኑኝነት ምዕራፍ ድምፅ ሰጪው ማህበረሰብ መረዳት በሚችልበት መልኩ አውድ እየሰጡና እየተነተኑ በተከታታይ መዘገብ አለባቸው።
ባዶ ጫጫታ የማይሰለቸው ብልፅግና ፓርቲ በሚቀጥሉት ሦስትና አራት ወራት ምርጫ፣ ምርጫ እያለ ማላዘኑ አይቀርም፣ ሆኖም ካሁን ጀምሮ እስከ ታህሳስ 2018 ድረስ ባሉት ግዜያት፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ከተቃዋሚ ኃሎችና ከሜዲያው ማድመጥ ያለበት ግን ስለ 2018 ምርጫ ዝግጅት ሳይሆን፣ የ2018ቱን ምርጫ ለማካሄድ መሟላት ስላለባቸው ቅደመ ሁኔታዎችና ቅድመ ሁኔታዎቹ ካልተሟሉ መወሰድ ስለሚገባቸው እርምጃዎች መሆን አለበት። ምርጫ የኢትዮጵያ ህዝብ ፖለቲካዊ፣ኤኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጥቅሜን ያስጠብቁልኛል ብሎ የሚተማመንባቸውን ፓርቲዎች የሚመርጥበት ዲሞክራሲያዊ ተቋም ነው እንጂ፣ ሁሌም አንድ ፓርቲ ብቻ እየተመረጠ ያለምንም ከልካይ ህዝብን የሚረግጥበት መሳሪያ አለመሆኑን የፖለቲካ ፓርቲዎች በተከታታይ ለህዝብ ማሳወቅ አለባቸው። ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ሜዲያውና ድምፅ ሰጪው ማህበረሰብ እጅና ጓንት ሆነው መስራት የሚገባቸውን ሰርተው በጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት ላይ ጫና ማሳደር ከቻሉና፣ከላይ የተጠቀሱት ቅድመ ሁኔታዎች አጥጋቢ ምላሽ ካገኙ፣የኢትዮጵያ ህዝብ ከምርጫ 2018 ባሻገር፣አምባገነንነትን ላንዴና ለመጨረሻ ግዜ ከኢትዮጵያ ምድር ነቅሎ ለመጣል የሚያስችለውን ድርጅታዊ ቁመና ለመላበሱ ቅንጣት ታክል ጥርጥር የለኝም!!!