‹‹ስሜቴን መግለፅ የምችለው በምሰራው ዜማ ነው›› (ቃለምልልስ ከድምጻዊ ሚካኤል በላይነህ ጋር)


(ቁምነገር መጽሔት /ከኢትዮጵያ)ሚካኤል በላይነህ ‹‹ማለባበስ ይቅር›› በተሰኘው ስለ ማግለል የሚሰብከው ህብረ ዝማሬ ላይ በዜማ ድርሰትና በድምፃዊነት በመሳተፍ ነው ከአድማጭ ጋር የተዋወቀው፡፡ በይበልጥ የሚታወቀው ግን ‹‹የፍቅር ምርጫዬ›› በተሰኘውና የፍቅረኞች ብሔራዊ መዝሙር ሊሆን በተቃረበው ለስላሳ ዜማው ነው፡፡ ‹‹አንተ ጎዳና›› ከተሰኘው ተወዳጅ አልበሙ በፊት ‹‹መለያ ቀለሜ›› የተሰኘ በፒያኖ የታጀበ የመጀመሪያ አልበም የሰራው ሚካኤል በቅርቡም ሶስተኛ አልበሙን እንካችሁ ብሎናል፡፡ ስለ አልበሙና ስለ ግል ህይወቱ ሚኪ እንዲህ ይላል. .
ቁም ነገር፡- ከሰባት ዓመት በኋላ ነው በሙሉ አልበም የመጣኸው?
ሚካኤል፡- ልክ ነህ፡፡
ቁም ነገር፡- 7 ዓመት እንዴት አለፈ?
ሚካኤል፡- በውጣ ውረድ /ሳቅ/ የመጀመሪያ ካሴቴን ያወጣሁት 97 ክረምት ላይ ነው፤ በደንብ የተሰማው ግን 98 ነው፡፡ ከዚያ በ2001 ሁለተኛ አልበሜን ለማውጣት ነበር እቅዴ አልሆነም፤ ከዚያ በኋላ እንደውም ከአንድ ዓመት በላይ በሀዘኑ ምክንያት ሙዚቃ አልሰራሁም፡፡፡
ሚካኤል በላይነህ ‹‹ማለባበስ ይቅር›› በተሰኘው ስለ ማግለል የሚሰብከው ህብረ ዝማሬ ላይ በዜማ ድርሰትና በድምፃዊነት በመሳተፍ ነው ከአድማጭ ጋር የተዋወቀው፡፡ በይበልጥ የሚታወቀው ግን ‹‹የፍቅር ምርጫዬ›› በተሰኘውና የፍቅረኞች ብሔራዊ መዝሙር ሊሆን በተቃረበው ለስላሳ ዜማው ነው፡፡ ‹‹አንተ ጎዳና›› ከተሰኘው ተወዳጅ አልበሙ በፊት ‹‹መለያ ቀለሜ›› የተሰኘ በፒያኖ የታጀበ የመጀመሪያ አልበም የሰራው ሚካኤል በቅርቡም ሶስተኛ አልበሙን እንካችሁ ብሎናል፡፡ ስለ አልበሙና ስለ ግል ህይወቱ ሚኪ እንዲህ ይላል. . .
ቁም ነገር፡- በዚያን ጊዜ አሜሪካ ነበርክ፤ እንዴት አለፈ?
ሚካኤል፡- ለማረፍ ነበር የሄድኩት፡፡ ከባድ ጊዜ ነበር፤ ለሶስት ወር ነበር የሄድኩት ግን ስሜቴን ሳየው ተጨማሪ ጊዜ መቆየት ነበረብኝ፡፡ ለመቆየት ከወሰንኩ በኋላ ደግሞ ቁጭ ከምል ብዬ በኢንተርኔት የሙዚቃ ትምህርት መማር ጀመርኩ፡፡
ቁም ነገር፡- የት?
ሚካኤል፡- በርክሌይ ዩኒቨርሲቲ የሙዚቃ ቲዎሪ ትምህርት ነው ተምሬ የመጣሁት፡፡
ቁም ነገር፡- መድረክ አልሰራህም?
ሚካኤል፡- አልሰራሁም፡፡ ተጠይቄ ነበር፤ ግን ሙዚቃ ለመስራት በሚያስችል ሙድ ላይ አልነበርኩም፡፡ የኛንም የፈረንጆችንም አዲስ ዓመት ያሳለፍኩት እዚያ ነበር፡፡
ቁም ነገር፡- ከሀዘኑ በኋላ ቶሎ ወደ ሙዚቃው ለመመለስ አልተቸገርክም?
ሚካኤል፡- የራሱ የሆነ ተፅዕኖ አለው፤ ግን ከሙዚቃ አልተለየሁም፡፡ አሜሪካ ሀገር እንደሄድኩ እንደውም መጀመሪያ ያደረኩት ነገር ኪቦርድ መግዛት ነበር፡፡ ጥሩ ስሜት ላይ ስሆን አንዳንድ ዜማዎችን እሰራ ነበር፡፡
ቁም ነገር፡- በወቅቱ ለአዲሱ አልበምህ የሰራሃቸው ስራዎች አሉ?
ሚካኤል፡- ብዙዎች ዜማዎች የሰራኋቸው በፊት ነው፡፡ አሜሪካ ሄጄ የሰራኋቸውም አሉ፡፡ የአልበም ስራውን ከጀመርኩ በኋላም የሰራኋቸው ዜማዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ ትመጪ እንደሆን፣ ስንዋደድ፣ ቃል ነበረ፣ ቅርብ ጊዜ የተሰሩ ናቸው፡፡
ቁም ነገር፡- ለመጀመሪያ ጊዜ የሰራኸው ዜማ የቱ ነው?
ሚካኤል፡- ለመጀመሪያ ጊዜ የሰራሁት ‹‹ሙሽራዬ›› የሚለውን ዜማ ነው፡፡
ቁም ነገር፡- እንዴት ሰራኸው፤ በአጋጣሚ ወይስ ሠርግ ነበረብህ?
ሚካኤል፡- ለአንድ ጓደኛዬ ሠርግ ነው የሰራሁት፡፡ ሂልተን ነበር ሠርጉ ከግርማ ይፍራሸዋ ጋር በፒያኖ ነው ዘፈኑን የተጫወትኩት፡፡ ጥሩ ተቀባይነት ነበረው፡፡
ቁም ነገር፡- ዜማ መስራት እንደምትችል አመላክቶሃል ለማለት ቻላል?
ሚካኤል፡- ይቻላል፤ ግን የዚያን ጊዜ እኮ ተወሰኑ ዜማዎችን ሠርቼ ኤልያስ ጋር ነበሩኝ፡፡ ኤልያስ ሰምቶ ጥሩ አስተያየት ስለነበረው ዜማ መስራት እችላለሁ የሚለውን ነገር ውስጤ ነበር፡፡ የፍቅር ምርጫዬ የሚለው ዘፈን ሁሉ እኮ የዚያን ጊዜ ሳልሰራው እቀራለሁ ብለህ ነው?
ቁም ነገር፡- ብዙዎች አርቲስቶች ግጥምም ዜማም ይሰራሉ፤ አንተ ግን ዜማ ብቻ ነው የምትሰራው፤ ግጥም አትሞክርም?
ሚካኤል፡- ግጥም ከልጅነት ጀምሮ እየዳበረ የሚመጣ ነገር ይመስለኛል፡፡ ክህሎት ብቻ ሳይሆን የሥነ ፅሁፍ ልምድም የሚፈልግ ይመስለኛል፡:
፡ የኔ ልምድ ወደ ዜማው ነው፡፡ ስሜቴን መግለፅ የምችለውም በምሰራው ዜማ ነው፤ ግን ግጥምንም እሰማለሁ አደንቃለሁ፡፡
ቁም ነገር፡- ዘፈንን ዘፈን የሚያደርገው ግጥሙ ነው ወይስ ዜማው ነው?
ሚካኤል፡- ዘፈንን ዘፈን የሚያደርገውማ ዜማው ነው፡፡ ዜማ የሌለው ግጥም እኮ መድብል ነው፡፡ ልክ በመፅሐፍ ታትሞ የሚቀርብ ማለት ነው፡፡ ለዘፈን ዜማ አስፈላጊ መሆኑን የምታውቀው የማታውቀውን ቋንቋ ዘፈን ስትሰማ ትወደዋለህ፤ ግጥሙን ሰምተህ አይደለም የምትወደው፡፡ የሚስብህ ዜማው ነው፡፡ ለምሳሌ እኔ ኦሮምኛ ቋንቋ አልችልም ግን የአሊቢራን ዘፈኖች በጣም ነው የምወዳቸው፡፡ የዘፈኑን መልዕክት አውቄው አይደለም፡፡ የወደድኩት ዜማው ነው የሚስበኝ፡፡ ስለዚህ አንድን ዘፈን ዘፈን የሚያደርገው ዜማው ነው፡፡ ግጥሙ በኋላ የሚመጣ ነው፡፡
ቁም ነገር፡- ግጥም ይዘህ ዜማ ትፈጥራህ ወይስ ዜማ ሰርተህ ነው ግጥም የምትፈልገው፤ ሙድህ እንዴት ነው?
ሚካኤል፡- ይሄ ነው የሚል ነገር የለኝም፡፡ ዜማ ሰርቼ ግጥም የምፈልግላቸው ስራዎች አሉ፤ ግጥሙን አይቼም ዜማ የምፈጥርላቸው ሥራዎች አሉ፡፡ እንደሁኔታው ነው፤ የሚገርምህ ግን በአሁኑ አልበሜ ላይ ግጥማቸውን የሰሩልኝ ልጆች በሙሉ ግጥማቸውን የፃፉት የኔን ዜማ ሰምተው አይደለም፡፡ ግጥሙን ሰጥተውኝ አይቼው ነው ዜማ የሰራሁላቸው፡፡
ቁም ነገር፡- ብዙ ሰዎች የመጀመሪያ አልበምህን መለያ ቀለሜ ሳይሆን፤ ‹‹አንተ ጎዳና››ን አድርገው ነው እንዲህ አይነት አስተያየት አላጋጠመህም?
ሚካኤል፡- አዎ የመጀመሪያ ሥራዬ ግን ‹‹መለያ ቀለሜ›› ነው፤ ከግርማ ይፍራሸዋ ጋር በፒያኖ የተጫወትኩት አልበም ነው፡፡ አልበሙ የወጣው በ1995 ዓ.ም ነው፤ ትልቅ ፕሮጀክት ነበር ሰራው እንኳን አንድ ዓመት ወስዶብናል፡፡ ለማስመረቅ ደግሞ ወደ 6 ወር ወስዷል፡፡ በዚህ መሀል አንተ ጎዳና አልበም ሳይወጣ እነ ማለባበስ ይቅርን ነጠላ ዜማ ሰርቼ ከህዝብ ጋር በደንብ የተዋወቅሁት፡፡
ቁም ነገር፡- የዛሬ 8 እና 9 ዓመት ገደማ ትዝ ይልህ ከሆነ ጥሩ ጥሩ ግጥሞችን መርጠህ የግጥም ንባብ መድረክ በቋሚነት ለማዘጋጀት ሀሳብ እንዳለህ አጫውተኸኝ ነበር፤ ያ ሀሳብ ምን ደረሰ?
ሚካኤል፡- ልክ ነህ፤ ያ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም የቢዝነስ ሀሳቦች ነበሩኝ፡፡ በወቅቱ ከመለያ ቀለሜ አልበም በኋላ ሁኔታዎች አስቸጋሪ እንደሆኑ ነው ያየሁት ይሁን እንጂ አሁንም ድረስ የማስባቸው የቢዝነስ ሀሳቦች አሉኝ፡፡ ግን የሙዚቃ ስራ አንድ ጊዜ ከገባህበት ሌላ ቢዝነስ ለመስራት ያስቸግራል፡፡ ሙሉ ጊዜ የሚፈልግ ሙያ ነው፡፡ በውጪው ዓለም ሀሳብ ካለህ አንተ የግድ ስራውን መስራት የለብህም ለሚሰሩ ልትሰጠው ትችላለህ፤ እኛ ሀገር ግን ሀሳብ ብቻውን የመሸጡ ጉዳይ አስተማማኝ ስላልሆነ ይዢያቸው የተቀመጥኩት ሀሳቦች አሁንም አሉኝ፡፡
ቁም ነገር፡- ከአዲስ አልበም በኋላ በየመድረኮች መጋበዝና መዝፈን የተለመደ ነው፤ አንተ ግን ብዙ መድረኮች ላይ አትታይም ለምንድነው?
ሚካኤል፡- በመጀመሪያ ደረጃ መድረኮችን እመርጣለሁ፤ እዛም እዛም በሚዘጋጁ መድረኮች ላይ ስጠራ መዝፈን አልፈልግም፡፡
ቁም ነገር፡- ለምን?
ሚካኤል፡- ምክንያቱም ሙዚቃ በቂ ዝግጅት ይፈልጋል፡፡ ዛሬ ደውዬልህ ነገ ዝፈንልኝ ልልህ አይገባም፡፡ በዚያ ላይ ሁለት ዘፈን ብቻ እኮ ነው የምትዘፍነው ልትባል ትችላለህ፤ የሙዚቃ ስራ የአንድና የሁለት ዘፈን ጉዳይ መሆን የለበትም፡፡ በቂ ዝግጅት በቂ ልምምድ ያስፈልጋል፡፡ ከዚያ በላይ ደግሞ በቂ መሳሪያና ተጫዋቾች ሊኖሩ ይገባል፡፡ ቢያንስ 4 ሙዚቀኞች መኖር አለባቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ አንድ ሊድ ጊታር፣ አንድ ቤዝጊታር ኪቦርድና ሳክስ ያስፈልጋሉ፡፡ እነዚህ በሌሉበት በአንድ ኪቦርድ ብቻ ምን አይነት ሙዚቃ እንዲሰራ እንደሚፈለግ አላውቅም፡፡ በቅርቡ ኮንሰርቶች ይኖሩኛል እዚያ ላይ በሙሉ ባንድ ነው የምንሰራው፡፡
ቁም ነገር፡- ባንድ ነበረህ? ዘመን ባንድ የማነው?
ሚካኤል፡- ከጓደኞቼ ጋር በጋራ የመሰረትነው ባንድ ነበር፡፡ ባንዱ አሁንም አለ፡፡ የዛሬ 4 እና 5 ዓመት ኦሎምፒያ መውጫ ላይ የሚገኘው ቴምፕቴሽን ናይት ክለብን ሪትም ብዬው ማታ ማታ እሰራበት ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ግን እኔ በተለያዩ ስራዎች የተነሳ አብሬ መስራት ስላልቻልኩ አቆምኩኝ፤ ልጆቹ አሁንም ይሰራሉ፡፡ አሁን የምናቀርበውን ኮንሰርትም ከዘመን ባንድ ጋር ነው የምሰራው፡፡
ቁም ነገር፡- መድረክ ላይ በሙሉ ባንድ ለመስራት የመውደድህን ያህል አልበምህን ግን በሙሉ ባንድ አይደለም የተሰራው፤ ለምድነው?
ሚካኤል፡- አልበም በሙሉ ባንድ መስራት እኛ ሀገር ቅንጦት ነው አይደለም በሙሉ ባንድ ከአንድ አቀናባሪ ጋር እንኳን እየተገናኘህ በምታስበው ጊዜ አልበምህን ሰርተህ ለመጨረስ አትችልም፡፡ ከጊዜው ሌላ የውጪ ጥያቄ አለ፤ ሙሉ ባንድ ስታሰራ ባንድ አግኝተህም ደግሞ የስቱዲዮ ችግር አለ፡፡ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ የምታስቀርፅበት ስቱዲዮ ያስፈልግሃል፡፡ እዚህ ሀገር ደግሞ ማን ጋር ነው የምትሄደው፡፡ ያሉት ከሁለትና ሶስት አይበልጡም፡፡ የነሱም ጊዜ አለ፤ ለምሳሌ እኔ በ2004 አልበሜን የግድ ማውጣት አለብኝ ብዬ ወስኜ ስለነበር የግድ መስራት ነበረብኝ፡፡ ስለዚህ ያለው ሌላው አማራጭም የስቱዲዮን ስራ ልክ እንደ ሙሉ ባንድ ሆኖ እንዲሰማ አድርገህ ማሰራት ነው፡፡
ቁም ነገር፡- ግን ይቻላል?
ሚካኤል፡- ይቻላል፤ ለምሳሌ የኔን አልበም የሰሙ ሰዎች በሙሉ ባንድ እንዴት አሰራኸው ብለው የጠየቁኝ አሉ፡፡ ዋናው ነገር በጥሩ ባለሙያ መሰራቱ ነው፡፡
ቁም ነገር፡- የፖለቲካል ሳይንስ ተማሪ ነበርክ፤ ፖለቲካ ተወዳለህ?
ሚካኤል፡- አልጠላም /ሳቅ/ ማንም ሰው እኮ ከፖለቲካ ውጪ መሆን አይችልም፡፡
ቁም ነገር፡- ፖለቲካል ሳይንስ የተማርከው መርጠህ ነው ወይስ በአጋጣሚ?
ሚካኤል፡- መርጨው ነው፤ ከሙዚቃ ውጪ አንድ ሌላ ሙያ እውቀት እንዲኖረኝ አሁንም እፈልጋሁ፤ ስለዚህ በወቅቱ መርጬ ፈልጌው ነው የገባሁት፡፡
ቁም ነገር፡- በአዲሱ አልበምህ ላይ የተጫወትካቸውን ዘፈኖች የፃፉልህ እነ ቴዎድሮስ ፀጋዬ ናቸው፤ በዘፈን ግጥም ፀሐፊነት አይደለም የሚታወቁት፤ አንተ እንዴት ደፈርክ ከነሱ ለመውሰድ?
ሚካኤል፡- ምክንያቱ ግልፅ ነው፤ ጥሩ ግጥም ስለሚፅፉ ነው፡፡ ግጥሞቹን አይተሃቸው ከሆነ ግልፅ ናቸው፡፡ በቀላል ቋንቋ የተፃፉ ናቸው፡፡ አገላለፃቸው ደስ ይላል፡፡ ሀሳቦቹም አዳዲስ ናቸው፡፡ ዘፈን ደግሞ በእኔ እምነት አንድ ጊዜ ሰምተህ የምታስቀምጠው ሳይሆን እየቆዬ ሲሄድ የበሰለ የሚደመጥ ነው፤ ለመደመጥ ደግሞ ግጥሙ ትልቅ ዋጋ ይኖረዋል፡፡
ቁም ነገር፡- ግጥሞቹ ግን ጠንከር ያሉ አይመስልህም?
ሚካኤል፡- አይመስለኝም፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ግጥም ወስጄ ከመዝፈኔ በፊት ሳነበው ገብቶኛል ወይ? የሚለውን ነው የምለካው፡፡ እኔ ካልገባኝ ለአድማጩ ልሰጠው አልችልም፡፡ ለዚህም ነው ግጥም ወስጄ ከመዝፈኔ በፊት ግር ያለኝ ነገር ካለ ከገጣሚዎቹ ጋር ቁጭ ብዬ የምነጋገረው፡፡ ትንሽ ወደ ፍልስፍናዊ ሀሳቦች የሚሄዱ ነገሮች ካሉ ምን ለማለት ፈልገህ ነው እንደዚህ ያልከው እላለሁ፡፡ ሲያስረዳኝ ካልተግባባን በል ቀይረው እኔ ለእያንዳዱ አድማጭ አሁን አንተ እንዳብራራኸው ለማብራራት አልችልም፡፡ የምንገናኘው በካሴት ወይም በሲዲ ነው ብዬ እንዲስተካከል አደርጋለሁ፡፡ ከዚህ አንፃር በአልበሙ ውስጥ ምን ለማለት ፈልጎ ነው እንደዚህ ያለው ብሎ የሚያመራምር ነገር የለም፡፡
ለምሳሌ ‹‹ልምጣ ያልሽ እንደሆን ቀና ነው ጎዳና
ልቤ ተመላልሶ ደልሎታልና›› የሚል ስንኝ አለ፡፡ ይህንን ስትሰማ አገላለፁ ይስብሃል እንጂ ምን ለማለት ፈልጎ ነው አትልም፡፡
ቁም ነገር፡- ግጥሞቹን የዘፈንካቸው ከገጣሚዎቹ ጋር በደንብ ከተነጋገርካቸው በኋላ እንደሆነ ነግረኽኛል፤ ያንተ ዜማዎችስ ተተችተዋል?
ሚካኤል፡- ጥሩ ጥያቄ ነው /ሳቅ/ በሚገባ ተተችተዋልና ያው ቅንብሩን የሚሰሩት ልጆች ተችተዋቸው ነው የሰራኋቸው፡፡ እንደውም አንዳንዶቹ ላይ እዚህ ጋር እንደዚህ ብትለው እያሉኝ በመግባባት ነው የሰራኋቸው፡፡ የሚገርምህ ያህንን አልበም የሰራሁት ከዚህ በፊት አብሬያቸው ካልሰራኋቸው የገጣሚያንና አቀናባሪዎች ጋር ነው፡፡ በዚህ ስራ ተግባብተን ሁላችንም በጥሩ ስሜት ነው የሰራነው፡፡ የጋራ ስራ የሚባለው ለዚህ ነው፡፡
ቁም ነገር፡- የገብረክርስቶስ ደስታን ግጥም ዜማ ሰርተህለት ዘፍነኸዋል፤ የኮፒ ራይት ጉዳዩን ቤተሰቦቹን አግኝተህ ለመጨረስ ሞክረሃል?
ሚካኤል፡- ሞክሬያለሁ፡፡ በመጀመሪያ ስራውን ከሰራሁት በኋላ የሄድኩት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዶ/ር ኤልሳቤጥ ጋር ነበር፡፡ ከዚያ ከሰዓሊ በቀለ መኮንን ጋር አግኝቻቸው ሙዚቃውን አሰማኋቸው፡፡ ከዚያ በቀለ ወደ ጌታ መኮንን ላከኝ፡፡ ጌታ መኮንን ሀጎስ የሚባል የገብረክርስቶስ ደስታ የቅርብ ዘመድ ጋር አገናኘኝ፤ እሱም ወ/ሮ ሙላቷ ከሚባሉ ሌላ ዘመድ ጋር አገናኘኝ፤ ሙዚቃውን አሰማኋቸው በጣም ደስ አላቸው፡፡ ግን የሱን ስራ በተመለከተ ሊፈቅድ የሚችል የቅርብ ቤተሰብ ወይም በስሙ የተቋቋሙ ፋውንዴሽን ስለሌለ ስራውን ለመፍቀድም ለመከልከልም አንችልም ነው ያሉኝ፡፡ ገብረክርስቶስ በስነ ጥበብ ቤተሰቡ ዘንድ ይታወቃል፡፡ በሌላው ህብረተሰብ ዘንድ ግን በዚህ አይነት ግጥሙ ስለማይታወቅ ብዘፍነው ዘመን የመሻገር አጋጣሚው ይጨምራል በሚል እምነት ወስኜ መጫወት ነበረብኝ፤ እንደውም በዚህ አጋጣሚ በስሙ ፋውንዴሽን ተቋቁሞ ከዚህ የተሻለ ስራ ሰርተን ብናጠናክረው ሁሉ የሚል ሀሳብ አለኝ፡፡ የሚፈቅድ አካል ቢኖር እንኳን ለአንድ ግጥም የተወሰነ ክፍያ ከፍሎ መጫወቱ ብዙ አይጠቅመውም፡፡ ዘላቂ የሆነ ነገር ለመስራት ጥሩ መነሻ የሚሆን ነገር መስራት ነው የሚሻለው የሚል እምነት ነው ያለኝ፡፡
ቁም ነገር፡- ግን አሁን የሄድክበት ርቀት በአልበምህ ላይ አልገለፅክም ለምንድነው?
ሚካኤል፡- ልህ ነሀ፤ መግለፅ ነበረብኝ ግን ትንሽ ጥድፊያ ላይ ስለነበርኩ ሳይገባ ቀርቷል፡፡
ቁም ነገር፡- ክሊፕ ስንት ዘፈን ሰራህ?
ሚካኤል፡- አንድ ነው እስካሁን የተሠራው ‹‹ትንታ›› ብቻ ነው፡፡ እሱም ድሬ ቲዩብ ላይ የተለቀቀው ዛሬ /ቅዳሜ/ ነው ገና 24 ሰዓት ሳይሞላው 20ሺህ ሰዎች እንዳዩት ቁጥሩ ያመለክታል፡፡ ዳይሬክተሩ ያሬድ ሹመቴ ነው፤ ሌሎች ሶስት ወይም አራት ዘፈኖችን በቅርቡ እሰራለሁ፡፡
ቁም ነገር፡- አዲካ ነው ያሳተመው፤ እንዴት ተገናኛችሁ?
ሚካኤል፡- አዋድ የመጀመሪያ አልበሜን በጣም ይወደው ነበር፡፡ የዚያን ጊዜ አዲካ ኮሙኒኬሽን ገና አልተቋቋመም ነበር፡፡ በኋላ ግን ድርጅቱ ከተቋቋመ በኋላ የሰራኋቸውን ዘፈኖች አሰማሁት፤ ወደዳቸው ከዚያ ሲያልቅ ወጣ ማለት ነው፡፡
ቁም ነገር፡- የሁለታችሁም ስም ነው አልበሙ ላይ ያለው ኮፒራይቱ የማነው?
ሚካኤል፡- ልክ ነው፤ የሁለታችንም ስም ነው ያለው፤ ግን ለተወሰነ አመት የነሱ ነው ኮፒራይቱ የሚሆነው፡፡
ቁም ነገር፡- በሼር ነው በሽያጭ ነው የታተመው?
ሚካኤል፡- በሽያጭ ነው፡፡
ቁም ነገር፡- በስንት የሚል ጥያቄ ይመችሃል?
ሚካኤል፡- ዋጋውን መናገሩ ሰው ለስራው ያለውን ግምት ክፍያው እንዲለካው ስለማልፈልግ ባልናገር ነው የሚሻለው፡፡ ነገር ግን ለስራዬ የሚገባኝንና ለቀጣይ ስራዬ የሚሆን ነገር አግኝቻለሁ፡፡ በነገራችን ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራም ትልቅ ድጋፍ አድርጎልኛል፡፡ ለፕሮሞሽኑ እጅግ ከፍተኛ ወጪ ነው ያወታው፡፡ አዲካንም ቅዱስ ጊዮርጊስንም ከልብ ነው የማመሰግነው፡፡
ቁም ነገር፡- ጎጆ የወጣኸው በቅርቡ ነው፤ አዲሱ ትዳር እንዴት ነው?
ሚካኤል፡- በጣም ደስ ይላል?
ቁም ነገር፡- ባለቤትህ ሆስተስ ነች ይባላል፤ ልክ ነው?
ሚካኤል፡- ነበረች፡፡ አሁን በግል የማርኬቲንግ ስራ ላይ ነው ያለችው፡፡
ቁም ነገር፡- ሆስተስ ከነበረች አውሮፕላን ላይ ነው የተዋወቁት የሚባለውስ?
ሚካኤል፡- እሱም ልክ አይደለም /ሳቅ/
ቁም ነገር፡- እሺ የት ተዋወቃችሁ?
ሚካኤል፡- ሠርግ ላይ ነው የተዋወቅነው፡፡ አንድ የማውቃት ልጅ ኤደን ገነት መናፈሻ ሠርግ ላይ ሙሽራዬ የሚለውን ዘፈን እየዘፈንኩ ድንገት አየት ሳደርጋት ፈገግታዋ የሚያዛልቅ መስሎ ተሰማኝ /ሳቅ/
ቁም ነገር፡- የዘፈኖችህ አድናቂ ነበረች?
ሚካኤል፡- የኔ ብቻ ሳይሆን ሙዚቃ በጣም ትወዳለች፤ ታዳምጣለች፤ እንደውም ወደ አርቱ የመግባት ፍላጎቱ አላት፤ ትወና ትሞክራች፡፡
ቁም ነገር፡- ከዘሪቱ ከበደ ጋር ችግኝ ተከላ ጀምራችሁ ቆመ፤ ምንድነው?
ሚካኤል፡- የጀመርነው ግሪን ኢንቪቲሺ የሚል ድርጅት አቋቁመን ነበር፡፡ ነገር ግን የማህበራት ምዝገባ ኤጀንሲ ኢንቪቲሺ ብላችሁ መንቀሳቀስ አትችሉም፡፡ የበጎ አድራጎት ማህበር ሆናችሁ ካልተመዘገባችሁ ሲሉን ለጊዜው ቆመ፤ እቅዳችን አዲስ አበባ ላይ አንድ ኮንሰርት ከሰራን በኋላ በየክልሉ እየሰራን ችግኝ ተከላውን ልንሰራ ነበር ግን አልሆነም፡፡ ከዚያ ወደ በጎ አድራጎት ማህበር ለመቀየር እንቅስቃሴ የሚያደርግልን መሀመድ የሚባል ልጅ ነው፤ እየተንቀሳቀስን ነው እንመለስበታለን፡፡
ቁም ነገር፡- ብዙ ሠርጎች ላይ ትጋበዛለህ፤ ራስህን እንደ ሠርግ ዘፋኝ ትቆጥራለህ?
ሚካኤል፡- እኔ ሠርግ ላይ የምጋበዘው የፍቅር ምርጫዬንና ሙሽራዬን ለመዝፈን ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ብዬ የማስበው ብዙዎቹ ሙሽሮች ከመጋባታቸው በፊት ፍቅረኛሞች ሆነው የፍቅር ምርጫዬ ዘፈን ተገባብዘዋል፡፡ እና ሲጋቡ ይህንን ዘፈን ቢዘፈንላቸው ደስ ይላቸዋል፡፡ ለዚህ ይመስለኛል የሚጋብዙኝ፡፡ በፊት በፊት አልዘፍንም እል ነበር፡፡ ነገር ግን የሰዎች ስሜት ሲጎዳ ሳይ ለምን ብዬ ያውም በዋጋ መደራደር ጀመርኩ ማለት ነው /ሳቅ/ አንድ ስራ አንድ ሰው ከሰራው በኋላ የእሱ ብቻ አይደለም የህዝቡም ነው፤ ስለዚህ እንደፍላጎታቸው እዘፍናለሁ፤ ያው የፍቅር ምርጫዬንና ሙሽራዬን ነው የምዘፍነው፡፡ ሙሽራዬን ግን ብዙ ጊዜ መዝፈን የምፈልገው ሙሽሮቹ ኬክ ሲቆርሱ ሳይሆን ከቆረሱ በኋላ ተያይዘው እንዲደንሱበት ነው፡፡ ምክንያቱም ግጥሙን ለእንደዚህ ተብሎ የተሰራ ነው፡፡ ይህንን ሀሳቤን ሳልነግራቸው ቀድመው ከገለፁልኝና ደስ ካለኝ ሠርግ አንዱ የሜድሮክ ኢትዮጵያ ክፍ ኤክስኪዩቲቭ ኦፊሰር የሆኑት ዶ/ር አረጋ ይርዳው ልጃቸውን በቅርቡ ሸራተን ስታገባ እኔ ሳልነግራቸው ሙሽራዬ ከኬኩ በኋላ ብትጫወተው ጥሩ ነው ነበር ያሉኝና ደስ እያለኝ ነበር የተጫወትኩላቸው፡፡
ቁም ነገር፡- የፍቅር ምርጫዬን ያልዘፈንክበት ሠርግ አለ?
ሚካኤል፡- የለም፡፡ ዋናው የምጠራው ለምን ሆነና፡፡
ቁም ነገር፡- አንተ ሠርግ ላይስ?
ሚካኤል፡- አልዘፈንኩም፡፡ የዘፈንኩት የሰይፉ ዮሐንስን በመልክሽ አይደለም ውበትሽን የማውቀው የሚለውን ነው የተጫወትኩት፡፡
ቁም ነገር፡- በመጨረሻስ?
ሚካኤል፡- በመጀመሪያ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፡፡ አድናቂዎቼን የስራዬ ነዳጅ ስለሆኑ አመሰግናቸዋለሁ፡፡ አልበሙን አብረውኝ ሰሩትን ሙያተኞች ሚኪ፣ ኪሩቤል፣ ቴዎድሮስ ፀጋዬ፣ዳዊት ተስፋዬ፣ መስፍን ትንሳኤ፣ አበጋዝ አዲካ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሁሉንም ባለበቴን ጭምር በጣም አመሰግናታለሁ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የሚኒሶታ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማህበር ለ18ኛ ያዘጋጀው የባህል ምሽት የፊታችን ቅዳሜ ይደረጋል
Share