የኢትዮጵያውያን የትብብር መድረክ Ethiopians solidarity forum
የተናጠል ትግል ለሽንፈት የተባበረ ትግል ለድል ያበቃል!
ግንቦት 09 ቀን 2017 ዓም(28 -05-2025
ከሰባት ዓመት በፊት የተቋቋመው ብሔራዊ የትብብር መድረክ በኢትዮጵያ አገራችን ሕዝብ ላይ እንዲሁም በተለያዩ የሙያ ዘርፍ በተሰለፉት ዜጎች ላይ የሚደርሰውን መጠነ ሰፊና የተለያዩ በደልና ጭቆናዎችን ለመከላከል አንዲሁም አደጋ ላይ የወደቀውን የአገር ህልውና ለማስከበር በተናጠል የሚደረገውን ትግል ሰብሰብ ሰድርጎ በአንድ የጋራ መድረክ ለማሰለፍ የተቋቋመ ድርጅት ነው።
እንደአለመታደል ሆኖ ግን ይህንን ለቀና ተግባርና ዓላማ የተቋቋመ ድርጅት በስራቸው ለማድረግ የሞከሩ ድርጅቶችና ዓላማው ያስፈራቸው የአገዛዙ ደጋፊዎች ባደረባቸው ስጋት ድርጅቱ ምንም እንዳይሠራ በሰርጎ ገቦች ገና ከጅምሩ አሽመደመዱት።ያ ውጥን ተሳክቶ ቢሆን ኖሮ አሁን ላይ በያቅጣጫው የሚሰማው እሮሮ ባልተከሰተና በጧቱ በተቀጨ ነበር።
ምንም እንኳን ቢዘገይም አሁንም የጋራ ትግል ከመቸውም በላይ አስፈላጊ ሆኗል።የመምሕራን፣የሓኪሞች፣የአርሶ አደሮች፣የነጋዴዎች፣የአገልግሎት ሰጭ ሰራተኞች፣በሰላማዊ አካባቢና መንደር ተወልዶ ጤናው ተጠብቆለት ለማደግ ዕድሉን የተነፈገው ተስፈኛው ትውልድ በሰላም ተምሮ የመግባት መብቱ ብቻም ሳይሆን አስፈላጊውን የምግብ አቅርቦት ባለማግኘቱ ለብዙ በሽታዎች ተጋልጦ ከስቶና ገርጥቶ ካሉት በታች ከሞቱት በላይ ሆኖ ይታያል።ትምህርቱን ጨርሶ ሥራ ያጣው ወጣት ህይወቱን ለማትረፍ ድንበር ጥሶ ለመውጣት ሲሞክር ያውሬና የወንበዴዎች ሲሳይ ሆኖ ካሰበበት ሳይደርስ በውሃ ጥምና በርሃብ እንዲሁም በወንበዴዎች እጅ ተገሎ ያሞራ ሲሳይ የሆነው ጥቂት አይደለም። በአጠቃላይ የከተማውና የገጠሩ ነዋሪ በኑሮ ውድነት እዬተሰቃዬ፣በሽተኛው የመታከም መብትና አቅም እያጣ ከመሰቃዬቱም በተጨማሪ በማንነቱና በሚከተለው እምነት ተፈርጆ ለብዙ ስቃይ ተዳርጓል። ከዛም በላይ አገሩ ተበታትና አገረቢስ የሚሆንበት ዕድሉ ከመቸውም በላይ ፈጦና ገጦ ይታያል፤ ይህ በምንም ሽፋንና መጋረጃ ሊደብቁት የማይችሉት በገሃድ የሚታይ እውነታ ነው።
ጥቂቶች በሚንደላቀቁባት ብዙዎች የበይ ተመልካች በሆኑባት አገራችን በብዙ መከራ የተተበተበው ሕዝባችን በተለያዩ ጊዜያቶች ትግል ቢያደርግም ብዙ መስዋእትነት ቢከፍልም ከችግሩ ሊላቀቅ አልቻለም።ይበልጥ ሰንሰለቱ እዬጠበቀበት ለትግል እንዳይነሳ በተለያዩ ዘዴዎች አሞቱ እንዲፈስ ሆኗል።ከውስጡ በጥቅም የተደለሉት ወይም በጎሳ ሰልፋቸው የረኩት እያሸበረኩ ላገዛዙ ምሳር እጀታዎች እዬሆኑ አስጠቅተውታል። ይህ ሁሉ ሊሆን የቻለው ትግሉ በተናጠል በመሆኑና በመርህ ሁሉንም አስተባብሮ የሚመራ የጋራ አካል ባለመኖሩ ነው።በመሆኑም ብዙዎች ሲታፈኑና ሲገደሉ ፣የት እንደገቡ ሳይታወቅ ጥቂት የማይባሉትም ለአሰቃቂ እስራት ተዳርገዋል፤ቤተሰባቸው ከመኖሪያ ቤቱ ተፈናቅሎ ሜዳ ላይ እንዲፈስ ለብርድና ለሃሩር እንዲጋለጥ ሆኗል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሃኪሞች አድማ በመካሄድ ላይ ነው።ይዞ የተነሳው ጥያቄ ከራሱ መብት በላይ በተጨማሪ ሌላውንም የሚመለከት የጋራ ጥያቄ የሆነውን የኑሮ ውድነትና የዜጋ መብትን ጭምር ነው።ይህ የሃኪሞች ትግል በነጠላው ከቀረ መኮላሸቱ አይቀሬ ነው።አገዛዙም ትግሉን ለማጨናገፍ ልዩልዩ ዘዴዎችን በመጠቀም ላይ ይገኛል።ስለሆነም ከብረት የጠነከረ አንድነት ከሚያስፈልግበት ወቅት ላይ ደርሰናል።
ይህንን የሃኪሞች የመብት ትግል ሌላውም የህብረተሰብ ክፍል በተለይም የመምህራን፣የተማሪ፣የነጋዴ፣የአርሶአደር፣የከተማው አገልግሎት ሰጭ ማህበረሰብ፣የእምነት ተቋማት፣የአገዛዙ ጋሻ በሆነው ግን ስንቁንም ትጥቁንም ከሰፊው ሕዝብ ግብር ክፍያ የሚያገኘው የወታደሩ ክፍል አባል የሆኑት አገር ወዳድና ለውጥ ፈላጊ አካላት ተባብረው በጋራ በመቆም ዳግማዊ የካቲትን እውን በማድረግ እራሳቸውንና አገራቸውን ሊታደጉ ይገባል።ይህ ወርቃማ ጊዜ ካለፈ ባርነትን ብቻ ሳይሆን አገር አልባነትን ፈቅዶ መቀበል ይሆናል።
ለቀውሱ ሁሉ ምክንያት የሆነውን ለዘመናችን የማይጥምና ዃላቀር የጎሳ ፖለቲካና አስተሳሰቡን ከአገራችን ምድር ነቅሎ ለመጣል በጋራ መታገል ይገባል።ከዚህ ውጭ አማራጭና አቋራጭ መንገድ የለም።የተባበረ ሕዝባዊ ትግል ከተባበረ ጎሰኛና ወንጀለኛ አገዛዝ ሰራዊት የበለጠ ሃይል አለው።
በጫካ ታጥቆ የህይወት ዋጋ የሚከፍለው አገር ወዳዱ ፋኖ አንድነቱን አፅንቶ ለከተማው ሕዝባዊ ትግል መከታና ጋሻ በመሆን እንዲሰለፍ፤በውጭ አገር የሚኖረው አገር ወዳድ በውሃቀጠነ ልዩነቱን ወይም የጎጥና ቡድን አሰላለፉን አሶግዶ በጋራ ተባብሮ ያገርቤቱን ትግል በሚያስፈልገው ሁሉ እንዲያግዝ የኢትዮጵያውያን የትብብር መድረክ ጥሪውን ያቀርባል
ድር ቢያብር አንበሳ ያስር!
የተባበረ ሕዝብ ያሸንፋል!!