ዳግማዊ ጉዱ ካሣ
ይሄ ሰውዬ አራት ኪሎን እስኪለቅ የማንሰማውና የማናየው ጉድ ላይኖር ነው፡፡ ምሉዕ በኩልሄ ሊባል የሚችል የመርገምት ፍርጃ ማለት እንዲህ ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያና እንደ ኢትዮጵያውያን አሁን በምንገኝበት የዕብድ አገዛዝ ያለፈ ሕዝብና ሀገር ሊኖር እንደማይችል በአሥር ጣቴ እፈርማለሁ፡፡ እኛም አቢይ አህመድም እንገርማለን፡፡ ታሪክና ቀሪው ዓለም እንዴት አንደሚታዘቡን ስገምት ደግሞ በዚህ ሁሉ ሕዝብ ድንቁርናና ከነባራዊው ዓለም ወጥቶ በራሱ ዓለም እየተንገራገጨ መኖር እደነቃለሁ፡፡ አንድን ዕብድ ተባብሮ ማስወገድ ሲቻል ሁሉም ተራ በተራ ሲያብድና ሲቀውስ ማየት በእጅጉ ያሳዝናል፡፡ ትናንት አመሻሽ አካባቢ ከቤቴ ወጥቼ ቁልቁለቱን ስወርድ አንዲት የማውቃት ሴት ለይቶላት አብዳ አየሁ፤ ጨርቋን ገና አልጣለችም፡፡ ልታናግረኝ ስትጠጋኝ ፈርቼ ሸሸሁ፡፡ ገና ሁልሽም ታብጃለሽ፡፡ ምን ታዬና!
ስለአቢይ መጻፍም ሆነ መናገር ከመሰልቸቴ የተነሣ ለመጻፍ ፍላጎቱ አልነበረኝም፡፡ ነገር ግን ወደጠፈር ሊሄድ ነው መባሉን ተከትሎ የሚናፈሰውን ወሬ ሳነብ ይህችን ማስታወሻ መክተብ ወደድኩ፡፡
በተረቱም “ዕብድና ዘበናይ የልቡን ይናገራል” ይባላል፡፡ ተረቱን “ዕብድና ዘበናይ የልቡን ያደርጋል” ብንለውም እምብዝም አንሳሳትም፡፡ የልቡን የሚናገር ዕድሉን ካገኘው የልቡን ከማድረግ አይመለስምና፡፡ እናም ይህ አቢይ የሚባል ዘበናይ ዕብድ ቤተ መንግሥታችንን የሙጥኝ ብሎ እስከቆዬ ድረስ የማናየውና የማንሰማው ሣጥናዔላዊ ተዓምር እንደማይኖር ይህ የጠፈር ጉብኝቱ አንዱ ምሥክር ነው፡፡ ነገረ ሥራችን “ትለብሰው የላት ትከናነበው አማራት” እንደሚባለው ነው፡፡ 86 ሚሊዮን ሕዝብ ከድህነት ወለል በታች ወርዶ ይልሰውንና ይቀምሰውን በማጣት በርሀብ ላይ እያለ ይሄ ጉደኛ ሰው ጠፈርን በመጎብኘት ከዓለም ይሁን ከአፍሪካ መሪዎች የመጀመሪያው ሊሆን ነው አሉ፡፡ እንደዴቪስ ቲቶ ያሉ ቢሊዮነሮች የጎበኙትን ጠፈር የበሻሻው ቁማጫም ድሃ በኢትዮጵያውያን የደም ገንዘብ መጎብኘቱ ለምን ይቅርበት? ለነገሩ እሱ ምን ያድርግ – እኛን የመሰለ በስቃያችን ሌሎችን የምናንደላቅቅ ሕዝብ አግኝቷል፡፡ እኛም ወደፈጣሪ እስካልተመለስን ድረስ በሚገጥመን ሲዖላዊ የመርገምት ፍሬ ሁሉ ማንንም ልንወቅስ አይገባንም፡፡ በተለይ ባለፉት 50 እና 60 ዓመታት ውስጥ የተፈጠርን ኢትዮጵያውያን ከምን ንጥረ ነገር እንደተሠራን መመርመርና ህክምናም ካስፈለገን እንድናገኝ ቢደረግ ጥሩ ነው፡፡ ሳጤነው ሰው ሁሉ ከቀልቡ አይደለም፡፡
ይህ ሰው የቤታችንን ቀለምና የመብራት ዓይነት እንዲሁም የበርና የመስኮት መጋረጃ ከመወሰን አልፎ የቁርስና የምሣ ሰዓታችንንም ገድቦ ከዚያ ውጪ ሻይም ሆነ ቡና ብንቀምስ ቅጣት ሊጥልብን እንደሆነ እየተነገረ ነው፡፡ ውስጣችን በስብሶ ሳለ አጥራችንን በግምብና በመንግሥት የቀለም ምርጫ እንድናስውብ እየተገደድን ነው፡፡ ትያትሩ ተነግሮ አያልቅም፡፡ አዲስ አበባን ለማን መኖሪያነት እያዘጋጃት እንደሆነ ግራ ገብቶን ቆመን እያዬነው እንገኛለን፡፡ ይህች የአፍሪካ ኩራት የነበረች ውብ ከተማ በአሁኑ ጊዜ ከነዋሪዎቿ በግምት 50 እና 60 መቶኛው ተባሯል፡፡ ይህን ለመረዳት የከተማዋን ውስጠኛ ክፍል እየተዟዟሩ መጎብኘት ነው፡፡ ከተማዋ ሰው አልባ ሆናለች፡፡ ቤቶች ፈርሰው ሣር የተተከለበት ባዶ ቦታና የታጠረ ባዶ ሥፍራ ከተማዋን አጥለቅልቋል፡፡ የነዋሪዎቿ ቤት እየፈረሰ ለመኪና ማቆሚያነት አስፋልት ለብሶ እዚህም እዚያም ይታያል፡፡ ነገረ ሥራቸው ሁሉ ከተማን የማስዋብ ሳይሆን ዓላማቸው አንድን ማኅበረሰብ ከአዲስ አበባ በማፈናቀል የማጥፋት ትልም ስለመሆኑ ጡት ያልጣለ ሕጻንም ይረዳዋል፡፡
ይሄ አቢይ እንደፈለገ የሚፈነጭባት ኢትዮጵያ አሁን ደግሞ 55 ሚሊዮን ዶላር ከፍላ ዕብድ ልጇን ማርስን ልታስጎበኝ ቦርሣዋን እያሟሟቀች እንደሆነ እየሰማን ነው፡፡ አያደርግም ደግሞ አይባልም፡፡ እሱ ትዝ አይበለው እንጂ ትዝ ካለው ከፀሐይ በታች የማያደርገው ነገር የለም፡፡ ይህ ገንዘብ ይታያችሁ እንግዲህ!
ሀኪሞች አሸር ባሸር የሆነ ምግብ እንኳን አግኝተው ሕይወታቸውን አውሎ ማሳደር አቅቷቸው የደሞዝ ጥያቄ ቢያቀርቡም መልሱ “በርሀብ ዕለቁ እንጂ ምንም ማድረግ አንችልም፤ ይልቁንስ ያቆማችሁትን ሥራ ጀምሩ – ለዚያውም መንግሥትን ይቅርታ ጠይቃችሁ” ነው፡፡ ደመወዝ ማስተካከልን ጨምሮ ይሄ 55 ሚሊዮን ዶላር ስንትና ስንት ሀገራዊ ችግር ሊፈታ እንደሚችል አስቡት፡፡ ቤተ መንግሥቱን እየገነባበት ያለው በአሁኑ የዋጋ ንረት ከሁለት ትሪሊዮን የሚበልጥ ብር ስንትና ስንት ሀገራዊ የልማት ሥራ ሊሠራ እንደሚችልም መገመት አይከብድም፡፡ ሰውዬው የተከበበው እንደሱ ባሉ ዕብዶችና ንኮች እንዲሁም ከሆድ በስተቀር ጭንቅላት ብሎ ነገር ያልፈጠረባቸው በመሆናቸው ልጁን “ሃይ” የሚለው የለም፡፡ በዙሪያው የተከማቸው ከብትና ጅብ እንዲሁም ዓሣማ ሆዱ ከሞላ ሕዝብ ተበደለ፣ ተራበ፣ ተሰደደ ብሎ ማሰብ አይችልም፡፡ ዕብዱን ጠ/ሚኒስትርም ለማስወገድ ምንም ጥረት አያደርግም፡፡ ከሦስተኛና አራተኛ ክፍል ያልዘለለ ትምህርት ያለው ምድረ ጄኔራልና ኮሎኔል ደግሞ ሆዱ አይጉደል እንጂ የሕዝብና የሀገር መጥፋት ደንታው አይደለም፡፡ በዚያ ላይ በዘረኝነት መሥፈርት ከየጉራንጉሩና ከየጠላና አረቂ ቤቱ ተመልምሎ ለዚህ ትልቅ ማዕረግ የበቃ የሠፈር አውደልዳይ ካድሬ የአቢይ ተንኮልና ሀገር የማፈረስ ሤራ ገብቶት እርሱን ይገዳደራል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው፡፡ አቢይስ ምኑ ሞኝ – የተማረን ሲጀመር አያስጠጋም፤ በስህተት ካስጠጋም ያባርረዋል ወይም ይቀነድሸዋል፡፡ ኢትዮጵያ በአቢይ ያጣቻቸው የክፉ ቀን ልጆቿ ብዙ ናቸው – ጄኔራል አሣምነው ፅጌ አንዱ ነው፤ ዶክተር አምባቸው ሌላኛው፡፡ ስለሆነም አቢይ ማርስን ብቻ አይደለም ዘጠኙንም ፕላኔቶች ቢጎበኝ ይሄ አጋሰስ ኮልኮሌ ጉዳዩ አይደለም፡፡ ቦርጩ ብቻ አይጉደልበት፡፡ ለዚህ ነው ሀገር የጭንቅ ምጥ ላይ እያለች አንድም መካሪ የሌለው ይህ ዕብድ ልጅ የሀገርን ውሱን ሀብት በክብሪት ለኩሶ የማቃጠል ያህል ጠፈርን ካልጎበኘሁ ሞቼ እገኛለሁ የሚለው፡፡
የኛ ኑሮስ?
እኛ በሥነ ልቦናም በሉት በአካል፣ በኢኮኖሚም በሉት በሌላ ማናቸውም ማኅበራዊ ሕይወት ከሞቱት በላይ ከቆሙት በታች ነን፤ ቅስማችን ተሰብሮ ሥነ ልቦናችንም ተጎድቶ ለመኖር ያህል ብቻ ነው የምንኖረው፤ ሀብታሙም ድሃውም አንድ ሆኗል ከዚህ አኳያ፡፡ በገጠር ሕይወት የለም፡፡ በድሮንና በመድፍ ሰው እያለቀ፣ ንብረትም እየወደመ ነው፡፡ ትምህርት መማርና የዕለት ከዕለት ሥራን ማከናወን ቅንጦት የሆነባቸው አካባቢዎች ብዙ ናቸው፡፡ ከተሞችንም ጨምሮ በብዙ ቦታዎች የጤና፣ የትምህርት፣ የእርሻ፣ የኢንዱስትሪና መሰል የልማት ዝርጋታዎች እንደዱሮው መከናወናቸው ይቅርና ያሉትንም የማፈራረስ ሤራ በስፋትና በግልጽ እየታዬ ነው፡፡ ዘረኝነት ጥምባት ነው የሚባለው ለዚህ ነው፡፡ አማራው ሲወድም ኦሮሞው የሚደሰት ከሆነ የኦሮሞ ባለሥልጣን የአማራን አካባቢ ማውደሙ ያረካዋልና እየታዬ ያለው አሳዛኝ ክስተት ይሄው ነው፡፡ የሆኖ ሆኖ ልማቱና ዕድገቱ ቀርቶበት “በድሮን ዒላማ ውስጥ ገባሁ ወይንስ በመከላከያ የታንክና ዲሽቃ ዒላማ ውስጥ ገባሁ” በሚል ጭንቀት የተወጠረው ሕዝብ እጅግ ብዙ ነው፡፡ የኑሮ ውድነቱም በዚያ ጭንቀት ላይ ተደርቦ ሕዝብን ከመኖር ይልቅ መሞትን እያስመረጠው ይገኛል፡፡
የከተሞችም ከዚህ የሚተናነስ አይደለም፡፡ መቅበጥ የሚዳዳው ሰው ዘመድ ለመጠየቅ ወይም በሀዘን ምክንያት ወደ ክፍለ ሀገር መሄድ ከፈለገ ለአጋቾች የሚሆን በትንሹ አንድ ሚሊዮን ብር ዘመድ ዘንድ ማስቀመጥ አለበት፡፡ የአቢይና ሽመልስ ሸኔዎች አማራን በየአቅጣጫው ወጥረው መተንፈሻ አሳጥተውታል፤ አማራም ምቹ ሆኖ ተገኝቶላቸዋል፡፡ ከአጥፊዎቹ ጋር የሚሞዳሞድ ፍጡር ማየት ደግሞ እጅጉን የሚደንቅ ነው፡፡ ተባብሮ ጠላትን ማስወገድ እየተቻለ ተለያይቶና በፍርፋሪ ተገዝቶ በራሱ ላይ የዘር ፍጅት (ጄኖሣይድ) ያወጀን የለዬለት ጠላት መተባበር በርግጥም መረገም ነው፡፡ ኢትዮጵያ በሕይወት ያለች የምትመስል ግን አፈር ያልተመለሰባት አስከሬን ሆናለች፡፡ “አገር መምራት አቅቷችኋል ይሉናል ደግሞ” ሲል ባለፈው እየገለፈጠ በልግጫ መልክ የተናገረው አቢይ ይህችን የመሰለች ማስጠሎ ኢትዮጵያ “መምራቱ” ደረቱን አስነፍቶት ነው፡፡ መርቶ ልቡ ውልቅ ብሏል፡፡ ለማንኛውም በከተሞች የሚታዬው የኑሮ ውድነት እንዲህ በቀላሉ በነባር ቃላት ብቻ ሊገለጽ አይችልም፡፡ አዳዲስ ቃላት መፈጠር አለባቸው፡፡ የአቢይ ተፈጥሮ ልዩ እንደመሆኑ ነባር ቃላት ባይገልጹት አይገርምም፡፡ ለምሣሌ አቢይን በተራ ቋንቋ “ውሸታም” ብትለው አይገልጠውም፡፡ የአቢይ ውሸት ከተራራና ከቋጥኝም በእጅጉ ይገዝፋልና፡፡
ወደ ኑሯችን ልመለስ፡፡ ተጣርቶ አሥራ አምስት ሺህ ብር የሚከፈለው አንድ ሰው በዚህ ብር ብቻ ከአራት የቤተሰብ አባላቱ ጋር ይኑር ከተባለ በአራተኛው ወይም በአምስተኛው ቀን ጨርቁን ጥሎ ያብዳል፡፡ ይህ ሰው በዚህ የደሞዝ መጠን ካበደ ሁለትና ሦስት ወይም አራትና አምስት ሺህ የሚከፈለው አብዛኛው የመንግሥትና የግል ድርጅት ተቀጣሪ እንዴት ሊኖር እንደሚችል ማሰብ ከባድ አይደለም፡፡ ይህ የሆነው የገንዘቡ የመግዛት አቅም ከቀን ወደ ቀን እያሽቆለቆለ መጥቶ አሁን አሁን አንድ መቶ ብር የደርግን አንድ ብር እንኳን መሆን እያቃተው ብሩ ዜሮ በመሆኑ ነው፡፡ በዚህ የኑሮ ውድነት ሰው እንዴት እየኖረና ከቅዳሜ ወደ እሁድ እንደሚሻገር ሲያስቡት ይደንቃል፡፡ አንዳንዴ ሳስበው ኢትዮጵያ ዕንቆቅልሽ ትሆንብኛለች፡፡
ዝርዝር ውስጥ መግባት አያስፈልግም፡፡ የራሴን የወጪ ሰነድ ልንገርህና ተገርመህ ንባብህን ጨርስ፡፡
ከቤቴ መ/ቤቴ ለደርሶ መልስ ትራንስፖርት በቀን 150 አወጣለሁ፡፡ 150 ሲባዛ በ26 ይሆናል 3900፡፡ ምሣ እይዛለሁ – በ100 ግምት ይያዝልኝ – ወጪ አለዋ! 100 ሲባዛ በ30 ይሆናል 3000፡፡ ከጓደኞች ጋር ምሣ ሰዓት ላይ ቡና እንጠጣለን – 25 ሲባዛ 26 ይሆናል 650፡፡ ቁርስ በቀላል ግምት 50 ብርና እራትም እንዲሁ በቀላል ግምት 100 ብር ይሁኑ – ድምራቸው 4500፡፡ ቤት ኪራይ አለ፡፡ በ12 ሽህ ይያዝልኝ፡፡ አልፎ አልፎ ቢባል በሚያንሰው ሁኔታ ማታ ማታ ከቢጤዎቼ ጋር አመሻለሁ – በቀላል ግምት 5000 ይያዝልኝ፤ በዚህ መልክ መንግሥትን ካላማህ ጭንቀቱ ሊገልህም ይችላል እኮ፡፡ ገና ዝርዝሩ ሳይጀመር የእስካሁኑ ብቻ 29050 (ሃያ ዘጠኝ ሽህ ሃምሣ ብር) ሆነ፡፡ በዚህ ከቀጠልኩ መቶ ሽህም አይጠቅመኝምና ልተወው ….፡፡ እኔ እንግዲህ አንድ ድሃ መምህር ነኝ፡፡ ድህነቴን ደግሞ ከሙስናና ምዝበራ ውጪ ደመወዝ ሲያልፍ በማይነካቸው ማይማን መንጋ የሚዘወረው መንግሥት የጫነብኝ እንጂ ወድጄና ፈቅጄ ራሴ ያመጣሁት አይደለም፡፡ ከኢትዮጵያ ውጪ የማንኛውም ሌላ ሀገር ዜጋ ብሆን ኖሮ 37 ዓመታትን በዲግሪ ደረጃ ሠርቼ ወደ ማርስ ልሂድ ብዬ አልቀናጣ እንጂ መሠረታዊ ፍላጎቶቼን ማሟላት በጣም ተራ ነገር ነው፡፡ መሪ በሌላት ሀገር ውስጥ በመኖሬ ግን እነሱ የኔን ኑሮ እየኖሩ እኔ ደግሞ የነሱ ድንቁርና በነሱን መሰል ደናቁርት ላይ ሊፈጥረው የሚችለውን የሰቆቃ ሕይወት ስለነሱ እንደነሱ ሆኜ እንድገፋ ተገድጃለሁ – መሪው ተመሪ፤ ተመሪው መሪ ሲሆን የሚታየው ትርዒት ይሄ ነው፡፡ ጥሩ መሪዎች ያሏቸው ሀገሮች ቤት አልባን ባለቤት ሲያደርጉ መጥፎ መሪዎች ያሏቸው ሀገሮች ደግሞ ባለቤትን ቤቱን አፈራርሰው ጎዳና ተዳዳሪ ያደርጋሉ፡፡ ኢትዮጵያ የጉዶች ሀገር ሆናለች፡፡
የኔውስ ቀላል ነው፡፡ ከውስጥም ከውጪም በተለይ በበዓላት ሰሞን የሚደግፈኝ አላጣም፡፡ ከዚህ ልዩ ነጥብ ጋር በተገናኘ እዚህ ላይ መጥቀስ አያስፈልገኝም እንጂ በጎሣና በነገድ ጭራሽ የማንገናኝ በኢትዮጵያዊነትና በሰውነት ግን የምንዋደድ አንድ ወዳጄን ባነሳ ደስታየ ወሰን ባልነበረው፡፡ እዚህ ላይ ማስታወስ የምሻው ዋና ነገር ቋንቋም ሆነ ትምህርትና ሀብት ከተወለዱ በኋላ የሚገኙና ሲሞቱ ተከትለው የማይሄዱ መሆናቸውን ነው፤ ሰው ሆኖ መገኘት ነው ትልቁ ፀጋና በረከት፡፡ ከኑሮ አኳያ ከገለጽኩት ዘግናኝ ሁኔታ አንጻር የኔን የመሰለ ዕድል የማያገኙ ዜጎች እንዴት እየተሰቃዩ እንደሚኖሩ አውቃለሁ፡፡ ሰሞነኛው የሀኪሞቹ የሥራ ማቆም አድማም ከዚህ የመነጨ ነው፡፡ የነዚህን ወገኖቼን ብርታት በዚህ አጋጣሚ ሳልጠቅስና ሳላደንቅ ማለፍ አልፈልግም፡፡ የኔን ብሶት ነው ይዘው የተነሱት፡፡ የኔን ዕንባ ሊያብሱ ነው እየተሰቃዩ ያሉት፡፡ አንዴ ለሚኖርባት ምድር እንዲህ እየተሰቃዩ ከሚኖሩ ደግሞ በአድማቸው ቀጥለው ሌላው ተበዳይ ወገንም አድማውን ተቀላቅሎ ይህን የአቢይ የአጋንንት መንጋ በአፋጣኝ ማስወገድ ነው፡፡ አቢይ ትንሽ የሥልጣን ዕድሜ ካለው ገና ሬሣችንንም በጨረታ ከመሸጥ አይመለስም፡፡ በያላችሁበት ሰላም ሁኑልኝ፡፡