የሀገር ፖለቲካና የሃይማኖት ወይም የእምነት ተቋማት አመራር በመጥፎ እጆች ሲገቡ ምን ሊፈጠር እንደሚችል የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ በማየት መረዳት ይቻላል፡፡ ኢትዮጵያ በሞትና በሕይወት መካከል ሆና እያቃሰተች የምትገኘው ከሰውነት ተራ የወጡና ሆዳቸው ብቻ የሚገዛቸው ሰዎች የሃይማኖቱንም ሆነ የፖለቲካውን የአመራር ቦታዎች ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ ስለተቆጣጠሩ ነው፡፡ የኛው ባሰ እንጂ እንዲህ ዓይነት አስቸጋሪ ወቅቶች በየሀገሩ ይከሰታሉ፤ ግን ደግሞ ነባራዊው የዓለማችን ተጨባጭ ሁኔታ የሚያዝዘው ነውና ጊዜያቸውን ጠብቀው ያልፋሉ፡፡ ጥንቃቄ መደረግ ያለበት ታዲያ የሚያልፍ ነገር የማያልፍ ታሪካዊና ሞራላዊ፣ ባህላዊና ሥነ ልቦናዊ፣ ቁሣዊና ሃይማኖታዊ ጠባሳ ትቶ እንዳያልፍ ነው፡፡
የሶሻል ሚዲያውን በንቃት ለተከታተለ ሰው ለአካላዊና አእምሯዊ ህመም የሚዳርጉ ብዙ ነገሮችን ይመለከታል፡፡ ሌላ ሌላውን ትተን በፋኖና መሰል የነፃነት ታጋዮች ነን ባዮች ዙሪያ በተለይ ላለፉት ሁለት ዓመታት ያህል ሲዘገቡ የነበሩትን ዜናዎች የሚከታተል ሰው ሆዱን በማይጨበጥ የተስፋ ዳቦ እየቆዘረ የኢትዮጵያ ነፃነት በሰዓታት ውስጥ የሚበሠር ያህል እስኪሰማው ድረስ በደስታ የሚያስፈነድቁ የውሸት ወይም እጅጉን የተጋነኑ ሰበር ዜናዎችን ኮምኩሟል፡፡ እነዚህ ሰበር ዜናዎችና መረጃዎች ለጥቂቶች የዕለት እንጀራ ማግኛ ቢሆኑም ለብዙዎች ግን የተስፋ መጨለምና እውነት ቢዘገብ እንኳን እምነት እንዳይኖራቸው ሰበብ ሆነዋል፡፡ ኃላፊነት የጎደላቸው በርካታ ጋዜጠኛ ተብዬዎች ውሸት በመርጨት ሥጋቸውን የተመረዘ እንጀራ መግበው ነፍሳቸውንና ኅሊናቸውን ግን አቆሽሸዋል፡፡ በዚህ ዓይነቱ የሞኞችና የሆዳሞች ድርጊት ብዙዎቻችን እንደተታለልን ደግሞ በበኩሌ እረዳለሁ፡፡ ይሁንና ውሸት ምን ጊዜም ውሸት ነውና ጊዜ ባለፈ ቁጥር መገለጡና መጋለጡ አይቀርም፡፡ ስለሆነም በፋኖ በኩልም ሆነ በሌላ አቅጣጫዎች በየሰዓቱ ይለፈፉ የነበሩ እልፍ አእላፍ ሰበር ዜናዎች አሁን አሁን ትናጋቸው እየተቆለፈ አንዳንዶቹ እያፈሩም ጭምር ዝምታን ሲመርጡ አንዳንዶቹ ግን ነገሩን ለዘብ አድርገው በዚያው ጎዳና እየተመሙ ይገኛሉ፡፡ “አለባብሰው ቢያርሱ ባረም ይመለሱ” ይባላል፡፡ “ሆድን በጎመን ቢደልሉት ጉልበት በዳገት ይለግማል”ም እንላለን፡፡ መሠረተቢስ ሰበር ዜና ሊያታልል የሚችለው ጥቂት ሰዎችንና ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ዋናው ነገር ንግግርንና ተግባርን ማስማማት ነው፡፡ እንደእውነቱ ከሆነ ቃላት የተጠቃሚያቸውን አንደበትና ብዕር ለመቆጣጠር አቅምም መብትም የላቸውም፡፡ የቃላት አጠቃቀም በተናጋሪውና ጸሐፊው ይወሰናል፡፡ አንጎል የሌለው ቀዳዳ ሰው ያሻውን ነገር ይበጠረቅና የዋሃን አድማጮችን ያሞኛል እልፍ ሲልም ገደል ይከታል፡፡ በሀገራችን በሁሉም አቅጣጫ እየተስተዋለ ያለው ይሄው ነው፡፡ አብዛኞቻችን ደግሞ በትምህርት ያልገፋንና በልምድም ያልዳበርን በመሆናችን ለመታለል እጅጉን ፈጣን ነን፡፡ እናሳዝናለን፡፡ ቆም ብለን ማሰብና ማስተዋል ያልፈጠረብን ብዙ ነን፡፡ የመንጋ አስተሳሰብ ተጠቂዎችም እንደዚሁ ቁጥራችን የትለሌ ነው፡፡
በሃይማኖት ተቋማት አንጻር የተመለከትን እንደሆነ ሕዝበ አዳም በቸርች ውስጥ እንደእህል ተከማችቶ ከእህል ባልተናነሰ ማንም ጫኝ አውራጅ ፓስተር ሲጫወትበት እናያለን፡፡ በየዐውደ ምሕረቱም ማንም ወስላታ ባህታዊና መነኩሴ ነኝ ባይ ምዕመናንን ሲቀፍልና ሲቦጠቡጥ እንታዘባለን፡፡ በየቀበሌና ከፍተኛውም ምድረ ካድሬ አገርንና ሕዝብን እንዳሻው ሲመዘብር እንመለከታለን፡፡ በየሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱም በዘር ልክፍት በተሰባሰቡ ሰዎች መካከል ሀገር እንደገና ዳቦ እየተቃረጠች ናት፡፡ ማየት ለሚችል ብዙ ያያል፡፡ ሀገራችን በሰው አምሳል የሚራመድ ግዑዝ ነገር እንጂ ትክክለኛ ሰው መውለድ ያቆመች ትመስላለች፡፡ በቁጥር ካልሆነ በጥራት ከማንኛውም ሀገር ሕዝብ በታች ነን ቢባል ስህተት የለውም፡፡ አንድ ኩንታል ጥቁር ጤፍ 16 ሺህ ብር ገብቶ ጦም አዳሪው በበዛበት ዘመን፣ አሥር ሺህ ብር ይቅርና 50 ሺህ ብር በወር አንድን ሰው በማያኖርበት አስጨናቂ ወቅት “አንድ የህክምና ዶክተር አሥር ሺህ ብርም ይበዛበታል” የሚል ጠ/ሚኒስትር በተፈጠረባት ሀገር ተራው ዜጋ የምን ዓይነት አስተሳሰብ ሰለባ ሊሆን እንደሚችል ማሰቡ ራሱ ለከፍተኛ ራስ ምታት (ማይግራይን ለሚባለው) ይዳርጋል፡፡ እኛ በርሀብ እያለቅን አስጠሊታ መልኳንና በርሜል ሰውነቷን ቅርጽ ለማስያዝ በመቶ ሚሊዮኖች ወጪ አሜሪካና አውሮፓ የምትመላለስ ከንቲባ ሲኖረን ነው እንደሀገር ያበቃልን፡፡ ባለሁለት ዲግሪውና ባለሁለት ሥራው ሰውዬ ምሣየን እንደምንም ብቀምስ አዳሬን ጦሜን ተከንትሬ እየተኛሁ በዘር ወይ በድንቁርና የተመረጠ አንድ ሚኒስትር 5 መኪኖች ሲመደብለት ነው ሀገራዊ ቁም ነገር የተበላሻሸውና ገደል የገባው፡፡ ማይም ወደቤተ መንግሥት ምሁር ወደስደት ሲሄዱ ነው ሀገር የጠፋችው፡፡ የ86 ብሔሮች አገር “ኦሮምኛ ካልተናገራችሁና በገዳ ሥርዓት ካልመራናችሁ እንፈጃችኋለን” ስንባል ነው ያለቀልን፡፡ “አንተ ትግሬ፣ አንተ አማራ …” እየተባባልን ስንጨራረስና ለወል ጠላቶቻችን ምቹ ስንሆን ነው መጥፋታችን ቀድሞ የተረጋገጠው፡፡ አሁንማ ወደን ከተደፋን ቢረግጡን ሊከፋን አይገባም፡፡ አሁንማ በተቆፈረልን ጉድጓድ በደስታ እየዘለልን መግባትና መቀበር እንጂ ማንገራገር ከንቱ ነው፡፡
ስለውሸት ካነሳን ሁለት ሰዎችን እንመልከት፡፡ ሳስባቸው አባትና ልጅ ሳይሆኑ አይቀሩም፡፡ ሰው ይታዘበናል ብሎ ነገር ሲያልፍ አይነካቸውም፡፡ ለኔ እነዚህ “ሰዎች” ሰው አይመስሉኝም፡፡ ተለማማጅ ሣይንቲስት የሠራቸው ሰው መሣይ ሮቦቶች ይመስሉኛል፡፡ እርግጥ ነው እንደሰው ሲስቁና ሲበሉ ሲጠጡ ሰው ይመስላሉ፡፡ እንጂ በማቀርባቸው ማስረጃዎች የተነሣ እነሱን ሰው ብሎ እንደሰው መቁጠር ስህተት ነው፡፡ እነዚህ ማሽኖች አቢይ አህመድና የፋኖው ጩጬው አቢይ – ማርውሸት ፀሐዩ ናቸው፡፡ ማስረጃየን ላቅርብ፡፡ በነገራችን ላይ ፋኖ፣ ፋኖ የሚሆነው ፋኖ ሆኖ ሲገኝ ብቻ ነው፡፡ የምለው የማይገባው ካለ አዝናለሁ፡፡ የጨው ጨውነትም የሚመዘነው ጨው ሆኖ ሲገኝ ብቻ ነው፤ ካልሆነ ከድንጋይ ተለይቶ አይታይም፡፡ ስለዚህ ጨውም ፋኖም ራሳቸውን ማስከበር የሚችሉት ተፈጥሯዊ ንጥረ ነገራቸውን የሚበርዝና የሚከልስ ነገር ሲመጣ ተከላክለው ሲገኙ ነው፡፡ እሽኮለሌና ማባበል ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያመዝን በጊዜ ሂደት ተረድተናል፡፡ (Infatuation, baseless love, doesn’t help at all; it rather hurts so much.)
አቢይን ማንም ያውቀዋል፡፡ ስለርሱ ውሸታምነት ማውራት ጊዜ ማባከን ነው፡፡ ቢሆንም አንድ ሁለት ሦስቱን ላስታውስ፡፡ በቀጣይ አምስት ዓመታት ውስጥ የኢትዮጵያ ገበሬ በየቤቱ ሮቦት ይኖረዋል፡፡ በጎጃምና በሸዋ ዝናብ ያዘነብነው እኛ ነን፡፡ ነዳጅ በቅርቡ አውጥተን ለሽያጭ እናቀርባለን፡፡ ወዘተ.
አነሳሴ ስለውሸት አወሻሽ ማስተማር አይደለም እንጂ ውሸት ስንዋሽ እንዴት መዋሸት እንዳለብን ጥቂት ነጥቦችን ባስቀምጥ በወደድኩ፡፡ በመሠረቱ ውሸት መዋሸት ብዙም ያልተለመደ አይደለም፡፡ ለተለያዬ የተቀደሰና የተኮነነ ዓላማ እንዋሻለን፤ እንወሻሻለን – ከሞላ ጎደል ሁላችንም፡፡ ስንዋሽ ግን የሚታመነውን ውሸት ከማይታመነው መለዬት ካልቻልን እንደአቢይና ማርውሸት ሰው አክ እንትፍ ብሎ ሊተፋን ይችላል፡፡ ስንዋሽ መጠንቀቅ አለብን፡፡ አቢይ ለምሣሌ – “በቀጣይ አምስት ዓመታት የገጠሩን ገበሬ በጫማ እንዲሄድና በባዶ እግር የሚሄድ ሰው እንዳይኖር ጥረት እናደርጋለን፡፡” ወይም እንደመለስ ዜናዊ “በቀጣዮቹ አሥር ዓመታት የኢትዮጵያ ሕዝብ በቀን ሦስቴ እንዲመገብ እንሠራለን፡፡” ቢል የሚያምነው ሰው አይጠፋም – እኔን ሳይጨምር፡፡ ስለሮቦት የተናገረው ግን ማሣቅ እንኳን የማያስችል ያራዳዎች መገልፈጫ ነው የሆነው፡፡ ስለሆነም ውድ አንባቢያን! መዋሸት ሰውኛ ቢሆንም እንደዚያ አባቱ ውሸት ሊያስተምረው ፈልጎ “እዚያ ላይ ተመልከት ልጄ፣ ሰማይ ቤት በነጫጭ በሬዎች ጤፍ እየተወቃ ነው” ቢለው “ውይ አባዬ፣ ዕብቁ ዐይኔ ውስጥ ገባብኝ” ሲለው “አንትንማ ምኑን አስተማርኩህ፤ እኔንም በልጠኸኝ የለም እንዴ?” በተባለው የውሸት ትምህርት የተጠቀሰ ልጅ እንዳንሆን እንጠንቀቅ፡፡ በቃ፣ መዋሸት ካለብን የሚታመን ውሸት እንዋሽ፡፡
ወደአቢይ ልጅ ስንመለስ – የዛሬ ስንት ዓመት ይሁን ስንት ወር እንደተናገረው፡- “ጦርነቱን በሰባት ወር እንጨርሰዋለን፡፡ ባንጨርሰው እንኳን ከብልጽግና የሚቀሩን ብርሃኑ ጁላና አበባው ታደሰ ብቻ ናቸው፡፡” በዚህ አያበቃም ጩጬው አቢይ – ሰሞኑን ደግሞ “ምሥጋና ለአርበኛ ዘመነ ካሤ (ይሁንና)፣ ይሄ ዘሪሁን የሚባለው መሣሪያ በማጥቃት ሥልቱም፣ በአቅሙም ምናልባትም አቢይ የሌለው፣ ፋኖ ብቻ ያለው …” በማለት አንድም ቅሽሽ ሳይለው ከአንድ ጋዜጠኛ ጋር በሚያደርገው ቃለ ምልልስ ሲናገር ይደመጣል፡፡ ምን ማለት ነው? ለውሸቱ ለከት ቢያበጅለት ምን አለ? እኔን አድማጩንስ እስከዚህን ድረስ ለምን ይንቀኛል? አላሳዝነውም? በስንቱስ ልቃጠል? ምንስ ያተርፋል? ወይንስ አቢይና መንጋው እንደናቁን እነሱም ማለቴ ማርውሸት የሚወክላቸው ፋኖዎችም እኛን “ምንም አያመጡም፤ ውሸትን እንደሆነ ከደርግና ከወያኔ በፊትም ጀምረው ተለማምደውታል፤ ግዑዛን ናቸው፤ ምናባታቸውንስ ያመጣሉ?” ብለው ናቁን? ያሳስባል፡፡ ይሄ አካሄድ በፍጥነት መታረም አለበት – ይቅርታም መጠየቅ አለብን፤ ዝም ስላልን ዝምታችን ወደጎን ሄዶ ለውጥ ባያመጣ ወደላይ ሄዶ ከፅርሃ አርያም ሊዘገይ የሚችል ግን የማይቀር መዘዝ ሊያስከትል እንደሚችል መታወቅ አለበት፡፡ ክፋትን ክፋት፣ ድንቁርናን ድንቁርና፣ ዕብሪትንና ትዕቢትን ዕብሪትና ትዕቢት እየተካው ከሄደ ማንም ተጠቃሚ አይሆንም፡፡ ግልጽ እኮ ነው፡፡ የደርግ ትምክህት አልተነፈሰም? የወያኔ ዕብሪት አልሟሸሸም? የዚህኛው ደግሞ ከፊተኞቹም በባሰ ይፈነዳና ጥምባት ክርፋቱ ለአፍሪካም ይተርፋል፡፡
የሁለቱ ሰዎች ልዩነት የዕድሜና የውክልና ብቻ ነው፡፡ አቢይ ፀረ ኢትዮጵያ ኃይሎችን ወክሎ ሀገር እያወደመ ያለ ሲሆን ማርውሸት ደግሞ ኢትዮጵያን ከአጥፊዎቿ እናድናለን ብለው ከሚታገሉ የኔዎችም ናቸው ብዬ በተስፋ ከምጠብቃቸው ወገኖች ይመደባል፡፡ በውሸት ግን አንድና አንድ ናቸው፡፡ ስለዚህ ውሸት ውሸት ነውና እኩል ልንታገላቸው ይገባል፡፡ “የነሱ ውሸታም”፣ “የኔ ውሸታም” የሚባል ነገር ደግሞ መኖር የለበትም፡፡ ሀገር ያጠፋው ይህ ዓይነቱ ሸውራራ አመለካከት ነው፡፡ “የኔ መጥፎ ከነሱ መጥፎ ይሻላል” የሚል ካለ እሱ የለዬለት መጥፎ ነው፡፡ “ያንቺ ልጅ የኔን ልጅ መትቶት ከሆነ ምች ይምታው፤ የኔ ልጅ ያንቺን ልጅ መትቶት ከሆነ ግን መቼም…” አለች የተባለችው ሴት በመንደር ውስጥ እንጂ ይህ ዓይነቱ መድሎ ለአንድ ሕዝብ ቆሜ እታገልለታለሁ ከሚል የ120 ሚሊዮን ሕዝብ ወኪል አይጠበቅምና ይሄ ጎጠኝነትና መንደርተኝነት በአስቸኳይ መቆም አለበት፡፡ ዘመነ የሚገድለው ሰው አቢይ ከሚገድለው ሰው ባነሰ ካሳዘነኝ ችግር አለብኝ፡፡ ትልቁ መሻቴ መሆን ያለበት የፍትኅ ርትዕ ጉዳይ ነው፡፡ አበሻም ይላል – “በፍርድ ከተነዳች በቅሎየ፣ አለፍርድ የተዘገነች ቆሎየ” (ታሳዝነኛለች ለማለት ነው)፡፡ ስለሆነም በየትኛውም ጎራ ያለ እንደሻው ገዳይና ዋሾ ሃይ ሊባል ይገባል፡፡ ገዳይ ገዳይ ነው፤ ዋሾም ዋሾ፡፡ የእውነት መንገድ ቀጭንና እልህ አስጨራሽ ብትሆንም በዚያች ብቻ እንጓዝ፡፡ መግደል ደግሞ የምንም ዓይነት ችግር መፍትሔ አይሆንም፡፡ እኔ ለምሣሌ አቢይ አህመድ እንኳን ቢሆን እንዲገደል አልፈልግም፤ አገኘሁ ተሻገርም እንኳን ቢሆን እንዲገደል አልሻም፡፡ ይሁንና – ለምሣሌ – አቢይ ሰው እንዳይገድል የሚደረግበትን መፍትሔ እደግፋለሁ፡፡ ያ መፍትሔ አማራጭ ጠፍቶ እንትንን ቢያካትት ደግሞ ዐይኔን የማሽ አይመስለኝም፤ ለዚህ ያበቃኝም የርሱ ዕኩይ ሥራ ነው፡፡
ለማጠቃለል ያህል ማንም ይሁን ማን መዋሸት ከፈለገ ሊታመን በሚችል መልኩ ቢዋሸን ለሱ ከሚኖረን ግምት አኳያም መልካም ነውና ወዳጅ ካላቸው እነዚህን ዓይነት ሰዎች ጠጋ ብሎ ይምከራቸው፡፡