ነፃነት ዘገዬ
ለግፉኣን ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት ሰምላታየ በያላችሁበት ይድረስ፡፡ አሁን ከኢምግሬሽን አካባቢ ስመጣ ጥቁር አንበሣና ሊሴ ገ/ማርያም ትምህርት ቤቶች ሊደርስ ምንም ባልቀረው ሠልፍ ውስጥ የነበራችሁ ህጋዊ ስደተኞችም በዚህ አጋጣሚ ሰላም ልበላችሁ፤ ከሀገር ውስጥ ስደት የውጪውን ስደት መምረጣችሁን ታዘብኩ፡፡ ከ40 ደቂቃዎች በፊት አሜሪካን ኤምባሲ አካባቢ ያየኋችሁ በብዙ መቶዎች የምትቆጠሩ ቪዛ ፈላጊ ባለመኪናዎችም ይቅናችሁ፡፡ በጀርመን ኤምባሲ በኩል ሳልፍ በወንዝ ዳር ልማት ስም ድምጥማጣችሁ ጠፍቶ በነበራችሁባቸው ቤቶች ምትክ ሣር የተተከለባቸውና ወደመዝናኛነት የተለወጡ ግን አንድም ሰው ዝር ሲልባቸው ባላየሁባቸው ባዶ ቦታዎች ትኖሩ የነበራችሁ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችም የት እንዳላችሁ ባላውቅም በያላችሁበት ሰላም ለእናንተ ይሁን፡፡ የሀገሬ ሰው ለዚያውም ዕድል ከቀናው በ20 እና በ40 ካሬ ሜትር ኮንዶምንየም ከነሰባት ቤተሰቡ ተደራርቦ እየተኛ ከዚህ በባሰም በድልድይ ሥርና በበረንዳ ሌሊቱን እያሳለፈ እንግሊዝንና አሜሪካንን የመሳሰሉ ዘመናዊ ቅኝ ገዢዎች የጂቡቲን የመሬት ስፋት ሊያክል ምንም ያልቀረው ግቢ በኤምባሲ ስም አጥረው የያዙ ቅምጦሎችም ሰላምታየ አይቅርባቸው፡፡ የሀበሾች ምድር ውስጧ ለቄስ የሆነች የትንግርት ሀገር ሆናለች፡፡
ኢትዮጵያ ከያዛት የካንሰር ደዌ ልትድን ከተፈለገ ከሰው ምንም አልጠብቅም፤ ጠብቄ ጠብቄ ሰለቸኝና ተስፋ ቆረጥኩ፡፡ በበረሃም በከተማም ያሉት ሁሉ ከተስፋ ሰጪነታቸው ይልቅ ተስፋ አስቆራጭነታቸው ጎልቶ ታየኝ፤ አሁን ብቸኛው የምጠብቀው መድኅን ከሰማይ ሆኗል፡፡ ተዓምር፡፡ ተዓምር ብቻ ኢትዮጵያን ያድናታል፡፡ ከዚያ ውጪ ልፋት ነው፡፡ ሰው የለም፡፡ ሰው በዘረኝነት ልክፍት፣ በጥቅምና ፍላጎት መለያየት፣ በቋንቋና በዘር፣ በሃይማኖትና በሀብት ልዩነት፣ በማይምነትና በእበላ-ባይነት፣ በባንዳነትና በአንፋሽ አጎንባሽነት … ተመርዞ ነገን ሣይሆን ዛሬን ውሎ ማደርን በመምረጡ ምክንያት ስለሀገር መጨነቅ፣ ስለጋራ ነፃነት ማሰብ ዕርም የሆነበት ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡ ሕዝብ የለም፤ መብላት እንጂ ማሰብ የማንችል በሰው አምሣል የተፈጠርን ሮቦቶች ሆነናል፤ እንደኛ የሚያሣዝንና በቁሙ የሞተ አለ ብዬ ማመን ይቸግረኛል፡፡ በሕዝብ ቁጥር ከአፍሪካ አንደኝነቱን ናይጄሪያ ብትወስድብንም ሁለተኝነትን የሚቀማን የለም፡፡ ይህን ሁሉ ሕዝብ የያዘች ሀገር ግን የአንድ ኩታራ መጫወቻ ሆነች፡፡ እርሱ ራሱ እንዴት እንደሚታዘበን አላውቅም፡፡ ፈሪዎች ነን፡፡ ሌሎች በሠሩት ታሪክ የምንኮፈስ የራሣችን ታሪክ የሌለን የ8ኛው ሺህ ቦቅቧቆች ለመሆናችን የጫካውን የርስ በርስ ትርምስ ትተን የከተማውን በኮሪደር ልማትና በከተማ ውበት ስም በሚሊዮኖች ስንፈናቀል ፀጥ ረጭ ማለታችን አንዱ ኅያው ምሥክር ነው፡፡ ይሄ ሁሉ ሚሊዮን ሕዝብ አንድ ሮጦ ያልጠገበ ጮርቃ በሚያሰማራው ደምብ አስከባሪ ተብዬ ቤት አፍራሽና የጉሊት ገበያ በታኝ ሕይወቱ ሲመሰቃቀል ማየት በርግጥም ተዓምር ነው፡፡ ቤትን ያህል ነገር በግሬደር ሊያፈርስ የሚመጣን ኃይል በጋራ ሆኖ እንደመጋፈጥ ገመድ ይዞ ወደሚርብ ዛፍ መሮጥ የሚቀናን ፍርሀታችን ራሣችንን የሚያጠፋን የፈሪ ፈሪ ነን፡፡ እውነትን መካድ አይገባም፡፡ “ጀግና አይውጣብሽ” ተብላ በተረገመች ሀገር ውስጥ መኖር ከባድ መረገም ነው፡፡ ሰው ሁሉ እንደመልካም አማራጭ የወሰደው በባህርና በየብስ እየተሰደደ የዐውሬ ሲሳይና የልብና ኩላሊት ሻጮች የገንዘብ ምንጭ መሆንን ነው፡፡ በአንድ ወር ውስጥ በዚህ መልክ የሚሰደደው ብቻ አንድ የጦር ግምባር ቢፈጥር ስንትና ስንት ለውጥ በሀገራችን ባዬን ነበር፡፡ ለዚያ ግን አልታደልም – ስደት ብቻ፡፡ በዚያ ላይ አፍራሹና ተላላኪው የመንግሥት ታጣቂ ሁሉ ከዕለት ጉርስ የዘለለ ገቢ የሌለው መናጢ ድሃ ሆኖ ሳለ የታዘዘውን ሁሉ ካለ አንዳች ማንገራገር የሚፈጽምብን መሆኑን ስንረዳ የተጣለብን የመርገምት ልብስ በምንም ዓይነት እንዶድ ቢታጠብ የማይጸዳ መሆኑ ቁልጭ ብሎ ይታየናል፡፡ ይህም በራሱ ሊጸለይበት የሚገባ ትልቅ መቅሰፍት ነው፡፡
አዲስ አበባን ተዟዙሬ አየኋት፡፡ እኔ የማውቃት አዲስ አበባ የለችም፡፡ ሞታለች ወይም ጣር ላይ ናት፡፡
የቱን አንስቼ የቱን እንደምጥል ግራ ገባኝ፡፡ አፌ ያመጣልኝ ልናገር፡፡ ማንንም ለማስቀየም ግን አይደለም፡፡ እውነቱንና እውነቱን ብቻ ለመናገር ነው ዓላማየና አነሳሴ፡፡ አሁንና በዚህ ዘመን ኢትዮጵያዊ አለመሆን መታደል ነው፡፡ ቡርኪናቤ ሆኜ ብሆን ኖሮ እንደገና የተፈጠርኩ ያህል በተሰማኝ፤ እነሱ ታድለዋል፡፡ ሲያስቀኑ!! እነሱ የ34 ዓመት ዕድሜ ቅን አሳቢ መሪ አገኙ፤ እኛ ደግሞ የ43 ዓመት ዕድሜ ከሲዖል ያመለጠ ጂኒ ተላከብን፡፡
አብዛኞቹ አማሮች ወደውና ፈቅደው ባልተወለዱበት የዘር ሐረግ ምክንያት ከአዲስ አበባና ሸገር ከሚባለው ቦታ ተጠራርገው ወጥተዋል፡፡ ሰሞኑን በሄድኩባቸው ቦታዎች ሁሉ የታዘብኩት ይህንን ነው፡፡ ቀደም ሲል እነሽመልስና አቢይ ቃል በገቡት መሠረት አማራን ሲቻል በግድያ ያ ሳይቻል ሲቀር በማፈናቀል ከአዲስ አበባ አስወጥተው የዴሞግራፊ ለውጥ ሥራ መጀመራቸውንና በአጭር ጊዜ ውስጥ አመርቂ ውጤት ለማምጣት ቆርጠው መነሣታቸውን በማንአለብኝነት ድፍረት አሰምተውን ነበር፡፡ የእነሱ “ጨዋነት” ዋና መለኪያ ደግሞ የሚያደርጉትን አንድም ሳያስቀሩ አስቀድመው ለሚወዱት ሕዝባቸውና ለቄሯቸው ይፋ ማድረጋቸው ነው፡፡ አሁን አዲስ አበባ ስትታይ ሰው ሰው በማይሸት የመንገዶችና የተክሎች፣ የፏፏቴዎችና የሣሮች እንዲሁም የጫካ ፕሮጀክት የተባለ የአንድ ዕብድ ቤተ መንግሥት መመለኪያ አድባር ሆና ባዶ ቀርታለች፡፡ አብዛኛው ሕዝብም ፈዝዞና ደንግዞ ይልሰውንና ይቀምሰውንም አጥቶ በየመንገዱ ሲነሆልል ይታያል፡፡ የመንግሥቱ ለማ ግጥም ትክክለኛ ጊዜ አሁን ነው፡- “ምን ቢረዝም ሕንጻው ቢንጣለል አስፋልቱ፤ ሰው ሰው ካልሸተተ የታለ ውበቱ፡፡” በአፄ ቴዎድሮስ ዘመን ተገጠመ የተባለው የአንዲት አዝማሪ ግጥም ትክክለኛ ወቅትም አሁን፡- “አንድ እግር በርበሬ መንቀል አቅቷችሁ፤ አቃጥሎ ለብልቦ አንድዶ ፈጃችሁ፡፡” እውነት ነው፡፡
ሀኪሞች አድማ ቢመቱ፣ የተወሰኑ መምህራን ሥራ ቢያቆሙ … የተናጠል ትግል የትም አያደርስምና ብልጡ የዲያቢሎስ ወኪል አቢይ አህመድ ሁሉንም ግን በየተራ እርሱ የተላከበትን የጨለማውን መንግሥት ወራሽ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ነው – ለጊዜው አልተሣካለትም አንልም፡፡ አንድ እዚህ ግባ የማይባል ጭባ በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብና ታላቅ የምትባል ታሪካዊት ሀገር በሰባት ዓመታት ውስጥ ብቻ እንዲህ ጃርት የበላት ዱባ ማስመሰሉ ለክፋት ሽልማት የለውም እንጂ ቢኖረው ኖሮ ብዙ የኖቤል ሽልማቶችን ባገኘበት ነበር፡፡ የአንድ ሀኪም ደመወዝ ለወር የቤት ኪራይ እንኳን አይሆንም፡፡ ግልጽ ነው፡፡ የአንድ መምህር ደመወዝ የወር የትራንስፖርት ወጪ ከመሆን ብዙም አይዘልም፡፡ ይህም ግልጽ ነው፡፡ የአንድ መለዮ ለባሽ (ፖሊስ፣ መከላከያ፣ ደምብ አስከባሪ፣…) ደመወዝ ከአንድ ሸሚዝና ከአንድ ጫማ አያልፍም፡፡ ማንም ያውቀዋል፡፡ የአንድ ተራ የመንግሥት ሠራተኛ ደመወዝ በቀን ሦስት ቆቆር ወይንም ጮርናቄ በሻይ ካበላ እሰዬው ነው፡፡ በሦስት ሽህ ብር ጡረታ የሚተዳደር ሰው በወር የሚመጣበት የመብራትና ውኃ ሒሣብ በትንሹ 3000 ብር ነው፡፡ ይህም ግልጽ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ የኑሮ ውድነቱንና የገንዘብ ግሽበቱን እንዲሁም የመንግሥት ተብዬውን ማጅራት መቺነት ልግለጽ ብል አውሎ ያሳድራል፡፡ ይህ ሁሉ እየሆነ ግን ሕዝብ አለ ይባላል፤ መንግሥትም አለ ይባላል – በአስቂኟ ኢትዮጵያ ውስጥ፡፡ ሀፍረትን ሁሉም አሽቀንጥሮ ጥሏል፡፡ ከአጠቃላዩ ሕዝብ አምስት ግፋ ቢል አሥር መቶኛው ተንደላቅቆ ስለኖረ፣ በሌቦችና በአጭበርባሪዎች፣ በሙሰኞችና በዘመድ አዝማድ ተረጂዎች፣ በመያዶች ውስጥ በመቀጠርና በልዩ ልዩ ገቢዎች ምክንያት ደህና ኑሮ የሚኖሩ የሚመስሉ ሰዎች በሚያሽከረክሯቸው መኪኖች አዲስ አበባን ጨምሮ አንዳንድ ከተማዎች ስለተወረሩ፣ ሕንጻዎች ስለተገተሩና የመንገድ መብራቶች በግዳጅ ጭምር ስለበሩ ኢትዮጵያ ያለች የሚመስላቸው በተለይ የውጭ ዜጎች አይጠፉም፡፡ እንጂ እንደውነቱ በቁም ሞተናል፡፡ የሰው አባባል ልዋስና – አልሞትንም ብለን እንዳንዋሽ አደራችሁን!! ለፈዋሽ በሚያስቸግር ሁኔታ ሞተናል፡፡
የዛሬን አያድርገውና አቢይን በጣም እንቀው ነበር፡፡ በማጭበርበር ከተሸከመው የስም ዶክተርነት ባለፈ የረባ ትምህርት የለውም፤ የዚህ ዋና ምልክቱ ደግሞ እንግሊዝኛ ባለፈበት መንገድ አለማለፉ ነው፤ ዕድሜው ልጅ ነው፤ በተሞክሮና በልምድ አልበሰለም፤ ሰውን ይንቃል፤ ራሱን የሁሉም ሙያዎች ባለቤት ያደርጋል፤ ፓይለትን ስለአውሮፕላን ማብረር፣ ሀኪምን ስለመርፌ አወጋግ፣ የጦር ጄኔራልን ስለጦር አመራር፣ ወታደርን ስለአተኳኮስ፣ ቀጭን ፈታይን ስለእንዝርት አያያዝ፣ ገበሬንና የግብርና ባለሙያን ስለአስተራረስ፣ ነፍሰ ጡርን ስለምጥ፣ የተራበን ስለአመጋገብ፣ … በማስረዳትና ሥልጠና በመስጠት ራሱን በራሱ የሚያረካ ወፈፌ፣ አባርሰኛ፣ ራሱ የማያምንበትን ዘረኝነት እንደመከፋፈያና መግዣ መሣሪያ የሚጠቀም ዋሾና አስመሳይ ነው፤ በዚያ ላይ በጭካኔው ወደር አይገኝለትም፡፡ በነዚህና በሌሎችም ምክንያቶች የተነሣ ክፉኛ እንቀውና እጠየፈውም ነበር፡፡ እንደሰውም አልቆጥረውም – ከዚህ ነጥብ አንጻር አሁንም ጭምር፡፡
በኋላ ላይ ሳጠናው ግን እኛና ኢትዮጵያ በመረረ አኳኋን መቀጣት ካለብን የዚህ ዓይነት ሰው ነው ሊላክብን የሚገባው፡፡ ማሰብ የሚችል ቢላክ ቅጣታችን ሊቀል ነው፡፡ ሩህሩህ ሰው ቢላክ ሀገር ልትለማና ሕዝብ ሊመነደግ ነው፡፡ ያ ደግሞ አልተፈቀደልንምና ሌላው ቀርቶ ጥሩ አምባገነን መሪ እንኳን የማግኘት አማራጭ አንዳንዶቻችን በህልማችን የምንዝናናበት ምናባዊ ዕሤት ሆኖ ቀረ፡፡ መቀጣት ከነበረብን፣ ታሪካዊ የምናወራርደው ዕዳ ከነበረብን መላክ የነበረበት እንደአቢይ ዓይነት ዐረመኔና ጭራቅ ነው – ሲዋሽ ለነገ የማይልና ምን ይሉኝን አንቅሮ የተፋ፡፡ “ይሄ ተልእኮስ ይቅርብኝ” ብሎ እርሱ ራሱ እምቢ ቢል እንኳን አይችልም – ዕዝ ነዋ፡፡ ስለሆነም ከሁሉም መልካም ነገሮች የራቀ፣ አመዛዛኝ ስብዕናን የተነጠቀ፣ ዐውሬያዊ ባሕርይና አጋንንታዊ መንፈስን የተዋረሰ ሣጥናኤልን የሚያስንቅ ጉግማንጉግ ሊመጣብን የግድ ነበር ማለት ነው፡፡ ሲታዘዝ እንዲህ ነው ወገኖቼ፡፡
ይህ አቢይ ነው እንግዲህ አንድም እንከን በሌለበት ሁኔታ ጥንቅቅ ያለ ተንኮለኛና ሤረኛ፣ ገዳይና አስገዳይ፣ ሰላይና አሰላይ… ሆኖ በልዩ ሰይጣናዊ ጥበቡና ይህ ቀረሽ የማይባል አጋንንታዊ ዕውቀቱ መተትንና ጥንቆላን ጨምሮ ባገኘው ጥልምያኮሣዊ የሸርና የተንኮል ዘዴ ሁሉ ኢትዮጵያን እያጠፋ፣ አፍሪካውያንን ሳይቀር እያሞኘ ወደመንግሥቱ ማለቂያ የተቃረበው፡፡ ይህ ሁሉ ጥረቱ ሜዳ ላይ ወድቆ አልቀረም፡፡ የላኩትን ወገኖች እጅግ አስደስቷል፡፡ ኢሉሚናቲዎች በኢትዮጵያ መፈራረስ ጮቤ እየረገጡ ነው፡፡ አማራንና አጠቃላይ ሰሜኑን ከነሃይማኖቱ መሬት ላይ ጥሎ ስለደቆሰላቸው፣ ካህኑንም ጳጳሱንም ሽንት ቤት ከትቶ በዓለማዊ ቆሻሻ ጭቃ ስላርመጠመጠላቸው ኅቡዓን የሉሲፈር ድርጅቶች አሁን ደስታቸው ወደር አልተገኘለትም፡፡ ግን ይህችም ቀን ታልፍና ኢትዮጵያ ዳግም ልደቷን ትጎናጸፋለች፡፡ ቃሌን ያዝ፡፡ ሰይጣን ጥሩ አጥቂ እንጂ ጥሩ አሸናፊ ሆኖ አያውቅም፡፡ በተጨማሪ ሰዓትም ይሁን በሪጎሪ ኢትዮጵያ በመጨረሻው ፊሽካ የአሸናፊነቷ የምሥራች ይበሰራል፡፡ በሰው ደግሞ አንመን፤ ሰው ሰው ነው – ተሰባሪና ተንሸራታች፡፡ ሰውን ማመን ጉም እንደመዝገን ነው፡፡ ለጊዜው ግና አቶ አቢይ አህመድ ምንም እንኳን ነፍሱን አስይዞ ትልቅ ዋጋ ከፍሎበት ቢሆንም የሠራውና እየሠራ ያለው ሀገርን የማፈራረስና አንድን ሕዝብ የመበታተን ተልእኮ በሚገባ እየተወጣ ነው፡፡ እናጨብጭብለት አይባል ነገር፡፡…
ከፍ ሲል አንድ ነገር ጀምሬ ነበር፡፡ በርሱ ልደምድም፡፡ ኢትዮጵያ ስትወለድ ማለትም የማይቀር ትንሣኤዋ እውን ሲሆን በአመራር ቦታ የምትቀመጡ ወገኖች ብዙ ዕዳ አለባችሁ፡፡ በጣም ብዙ፡፡ አንደኛው በውጭ ሀገራት የተያዙ ሰፋፊ መሬቶችን ከየኤምባሲው በህጋዊ አግባብ እየወሰዳችሁ በገዛ ሀገሩ ባይተዋር የሆነ ሕዝባችሁን ማስፈር ነው፡፡ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ምን ያህል የቤትና የግቢ ስፋት እንዳላቸው አላውቅም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታዬው ገሃድ የወጣ እውነታ ግን የሚገርም ነው፡፡ እንግሊዝ፣ ፈረንሣይ፣ ጀርመን፣ አሜሪካ፣ ጣሊያን ያላየኋቸውና የማላውቃቸው ሌሎች ባለብዙ ስፋት ግቢ ኤምባሲዎች ተደምረውበት የምናገኘው ስፋት በእርግጠኝነት በመሬት ልኬቷ ከአፍሪካ ትንሹዋ የምትባለውን የሲሼልሽን የቆዳ ስፋት መፎካከሩ አይቀርም፡፡ ይህ በጅሎች ዘመን እንደልብ የተረጨ መሬት ወደሕዝቡ መመለስ ይገባዋል፡፡ የቪዛ ማኅተም ለማስመታትና የዲፕሎማሲ ግንኙነት ለማከናወን አንድ አገር መሬት አያስፈልግም፡፡ ዘመኑ የቴክኖሎጂ ነው፤ በአንድ ቢሮ ውስጥ ብዙ ነገር መሥራት በሚቻልበት ዘመን አንድ ከተማ የሚያህል ግቢ ይዞ ዜጎችን ቤት አልባ ማድረግ ወቅቱ የሚፈቅደው አሠራር አይደለም፡፡ በግቢያቸው ፈረስ የሚጋልቡ የኤምባሲ ሠራተኞች ከከተማ ወጣ እያሉ ይጋልቡ፡፡ ሕዝብ በረንዳ አዳሪ ሆኖ፣ ያገሬው ዜጋ መኖሪያ ቤት አጥቶ እንዲህ ያለ ቅንጦት ማየት በርግጥም ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር መቁረጥ ነው፡፡ ይህም በልባሞች ልብ ውስጥ ይመዝገብልኝ፡፡ ለነገሩ “ዱቢን ሃቡልቱ” ይላሉና የሀገሬ ሰዎች እኔም በዚሁ ግሩም አባባል ልሰናበት፡፡
አሃ! ይህን ጦማር ከላክሁ በኋላ ትዝ ያለኝ አንድ ትዝብት አለ – ስዞር የገጠመኝ፡፡ ብዙዎቹ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ከዘበኛ እስከ ዋና የበላይ ሹም ኦሮሞ ነው፡፡ ለማስመሰል ያህል በሚመስል ሁኔታ ሌሎችም አሉ በርግጥ፡፡ ሚዛን የሚደፉት ግን ኦሮሞዎች ናቸው፡፡ ይህ በአጋጣሚ ቢሆን ችግር የለውም፤ በብቃትና በውድድር ቢሆን ደግሞ ይበልጥ ቆንጆ ነው፡፡ ግን አይመስለኝም፡፡ ይህም በጣም ካሳዘኑኝና ከተከፋሁባቸው ክስተቶች እንደ አንዱ ይመዝገብልኝ፡፡ ባንክ ሄድሽ፣ ሚኒስትር መ/ቤት ሄድሽ፣ የትም ሂጂ … የሚያስተናግድሽ በአብዛኛው የኦሮሞ ተወላጅ ነው፡፡ በሌላ መልክ አትውሰዱብኝ ታዲያ፡፡ ፍትኃዊ የቅጥር መሥፈርት ይኑር ለማለት ነው፡፡ አማራ በትምህርት ደረጃና በሌላ ሌላ በልጦ ከተገኘና እርሱን መቅጠር ባይፈለግ ኢትዮጵያ የወላድ መካን አይደለችምና ከ85ቱ ሌሎች “ቤርቤረሰቦች” መቅጠር ይቻላል፡፡ ነገ ለሚያልፍ ነገር በዚህ ደረጃ እስከዚህ መውረድ የኦሮሞን ታሪክ ማጠየም ነውና ጥሩ ጥሩ ኦሮሞዎች እባካችሁን ስሞታየን ሰምታችሁ ጣልቃ ግቡ – እነሱ ደንቁረዋልና የሚሰሙት ሲሞቱ ብቻ ነው፡፡ ትናንት ዛሬ አይደለም፤ ነገም ዛሬን አይሆንም፡፡ ዛሬ ማለፉን የምገልጽላችሁ ግን የበላሁትን ቁርስ ምንነት የማውቀውን ያህል እርግጠኛ ሆኜ ነው፤ ዛሬ በሌላ ዛሬ ነገን ሆኖ ተተክቶ ይጠብቀናልና ስለነገም እንጨነቅ ወንድሞቼ፡፡ የምለው ሁሉ ከአድራጊዎቹ ይልቅ ስለተናገርኩት ብቻ እኔን ይበልጥ እያሣፈረኝ መሆኑን ደግሞ ሳልጠቁም መቅረት አልፈልግም፡፡ እነሱማ እንደቀዳሚዎቻው ሀፍረትንና ይሉኝታን ሸጠው በልተዋልና በሚሠሩት ሁሉ ከመኩራት ባለፈ ቅንጣት ሀፍረት አይሰማቸውም፡፡