ሚያዚያ 22 ቀን 2017 ዓ/ም የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት እስረኞች ወደ ማደሪያቸው ከገቡ በኋላ ከምሽቱ 12:00 ሰዓት ቀይ ቦኔት የጫኑ የፌደራል ፖሊሶች ቁልፍ ሰብረው እንዳስወጧቸው እና እስከ ሌሊቱ 7:00 ሰዓት ድረስ ሜዳ ላይ እንዳሳደሯቸው ምንጮቻችን ለመሠረት ሚዲያ ገለፀዋል።
በተመሳሳይ ዶ/ር ወንደሰን አሰፋ ፣ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ ፣ ጋዜጠኛ ዳዊት በጋሻው ፣ ፕሮፌሰር መዓረጉ ቢያበይን እና ሲሳይ አውግቸው (ዶ/ር) ይሄው ድርጊት የተፈፀመባቸው መሆኑን አርብ ሚያዚያ 24 ቀን 2017 ዓ/ም ለፍርድ ቤት አቤቱታ አቅርበዋል።
“ቀይ ቦኔት የጫኑ የፌደራል ፖሊሶች ምሽት 12:00 ሰዓት በሩን በኃይል ከፍተው ከገቡ በኋላ ሁላችንንም እጃችንን ወደ ላይ እንድናደርግ አዘው ሜዳ ላይ በሰልፍ አቁመውን በመሳሪያ ሲያስፈራሩን ነው ያደሩት” ሲሉ ነው ለፍርድ ቤቱ የገለፁት።
“ይህን ድርጊት በቦታው ተገኝተው ያስተባበበሩት የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ የሽብር ወንጀል መከላከል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኢንስፔክተር አዱኛ ረጋሳ እና የፌደራል አቃቢ ሕግ የሽብር እና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ኢዮሲያድ አበጀ ናቸው” ሲሉ ለችሎቱ አስረድተዋል
“እነዚህ ሁለቱ ዳይሬክተሮች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ውስጥ በርካታ የአዲስ አበባ ወጣቶችን ከወቅታዊ የአማራ ክልል የፀጥታ መደፍረስ ጋር በማገናኘት የሽብር ወንጀል ልትፈፅሙ አቅዳችኋል በማለት ኢ- ሰብዓዊ ድርጊት እየፈፀሙ ይገኛሉ” ሲሉ ተከሳሾቹ አቤት ብለዋል።
“ቀደም ሲል በምርመራ ወቅት ድብደባ የፈፀሙብን ሁለቱ የመንግስት ሹማምንት ሲሆኑ ከሁለት ዓመት በኋላ የቂሊንጦ ማረሚያ ቤትን አጥር ጥሰው ፣ የተኛንበትን ቤት በር በኃይል ሰብረው እስከ ሌሊት 7:00 ሰዓት ድረስ ሜዳ ላይ አሰልፈውን አሳድረውናል። ሕይዎታችን አደጋ ላይ መሆኑን ሕዝባችን እንዲያውቅልን” ሲሉ አሳስበዋል።
ዮሐንስ ቧያሌው እና ክርስቲያን ታደለ ከአንድ አመት በፊት በአዋሽ አርባ ወታደራዊ እስር ቤት በነበሩበት ወቅተ የከፋ የጤና መታወክ ገጥሟቸው እንደ ነበር ይታወቃል።
በመሆኑም ጤናቸው ገና ሳያገግም በድጋሜ ሜዳ ላይ ተሰልፈው እንዲያድሩ መደረጉ ለባሰ የጤና እክል ተጋልጠዋል ሲሉ ምንጮቻችን ለመሠረት ሚዲያ ተናግረዋል ።
የፌደራል ፖሊሶች የማረሚያ ቤቱን አጥር ሰብረው ለምን እንደ ገቡ እና በሽብር የተጠረጠሩ እስረኞችን ለምን ከክፍላቸው አስወጥተው ሜዳ ላይ እንዳሳደሯቸው የታወቀ ነገር የለም ።
ESAT