ከቴዎድሮስ ሃይሌ
“ታላላቅ ሰዎች ከመላዕክት ጋር እራሳቸውን የሚያቆራኙት ትልልቅ መስዋዕትነት በመክፈል ነው:: እርካሽ ሰዎች ደግሞ ለትንሽ እርካታ ሲሉ በገሃነብ እሳት መቃጠላቸውን እያወቁት ወደ እዛ ያመራሉ::” (ማርያ ፑዞ)
እርዕሱ እንዴት ያለ ድፍረት ነው ቢያስብልም አያስገርምም:: እንዴት ሕልውናዬ አደጋ ውስጥ ወድቋል ብሎ ትግል የጀመረ ሕዝብ የመጥፉቱ ምክንያት እራሱ ሊሆን ይችላል? አደጋውስ እንዴት ያለ ነው? ምን አይነት መንገድ ቢከተልስ ነው? የሚሉ በርካታ ጥያቄዎችን ማስነሳቱ አይቀሬ ነው:: የወገኔ ጉዳይ ያሳስበኛል የሚል ወገን በጽሞና ሌያጤነው የሚገባ ወቅታዊና ወሳኝ ነጥብ ነው:: የአማራ ሕዝብ ያለበት የትግል የአደረጃጀትና የፖለቲካ ቅራኔ የደረሰበት ቀውስ አሳሳቢ የሆነ ደረጃ ላይ ደርሷል:: የፉኖ ሃይሎች የእርስ በእርስ ሽኩቻ ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ ሁሉንም ሃይሎች ያለአድሎ በጥንቃቄ መገምገም ነገ ሊመጣ የሚችልን ችግር ለመቅረፍ ያግዛል::
የሰሞኑ የፉኖ አደረጃጀቶች የተካረረ መግለጫ የሃገርና የወገኑ ጉዳይ የሚያሳስበው ሁሉ አስደንግጧል:: የፉኖ ሃይሎች ከመካሰስ አልፈው ወደ ለየለት ጦርነት ለመሸጋገር ያላቸውን አስተዋይነት የጎደለው አካሄድ ተው የሚል ድምጽ ሊበረክት ይገባል:: በዚህ የሕልውና ትልግ ከፍተኛ ዋጋ እየከፈለ በስቃይና በመከራ ውስጥ ያለው የአማራ ሕዝብ ሊታዝንለት ይገባል:: የፉኖ አደረጃጀቶችና መሪዎቻቸው ከሚያራምዱት አጉራ ዘለል እርምጃ እንዲታቀቡ ማስገንዘብና ጫና መፍጥር የሁሉም አማራ ተወላጅ ቅድሚያና አፉጣኝ ተግባር መሆን ይኖርበታል:: እናት ልጇን መርቃ አባት አይዞህ ብሎ ለዘመቻ የላከው ልጅ ሕዝቡን ሊታደግ እንጂ የጥቂት መሪዎችን የስልጣን ቅዠት ለማሳካት አይደለም:: ሕዝቡ ደጀን ሆኖ ያለውን አካፍሎ ትግሉን እያገዘ ያለው የጎበዝ አለቆች እንዲጫወቱበት አይደለም:: አማራ ኢኮኖሚው ደቆ ልጆቹ ከትምህርት ቤት ቀርተው በተኛበት በድሮንና በከባድ መሳሪያ እየተፈጀ ባለበት በዚህ ወቅት የሃሳብና የአካሄድ ልዩነትን በሰለጠነ መንገድ ፈቶ ጠላቶቹን ከቅዪው ማራቅ ይገባው የነበረው ሁሉም የፉኖ አደረጃጀት ጫካ ውስጥ መሽጎ የእርስ በእርስ ግጭት የሚያባብስ መግለጫ መለዋወጡ ከየትኛውም የፉኖ አመራርና ተቋም አይጠበቅም::
እንደ አማራ ባለፉት 17 ወራት በፉኖ ተጋድሎ ኮርተናል:: ጀግንነቱን ለሕልውናው መዋደቁ ጥንካሬና ብርታቱ አስደስቶናል:: በአንጻሩ በመሪዎቹ ግለኝነት ቅራኔዎችን የመፍታት ብቃት ማጣት ለሚስጥራቸው መዝረክረክ መከፉፈላቸው እና መናቆራቸው አሸማቆናል:: የፉኖ ደጋፊ ነን በሚሉ የደም ነጋዴ ሚድያዎች የቲክቶክና የዩቱብ ጥገኛ ምናምቴዎች ከፉኖ መሪዎች ጋር ያላቸው ቁርኝት አሳፍሮናል:: የስድቡና የአሉባልታው መዐበል አንገታችንን እንድንደፉ አድርጎናል:: ታላቁን ትግል ይመሩ ዘንድ በታሪክ አጋጣሚ መሪ ሆነው የወጡት የፉኖ አንዳንድ መሪዎች ለስልጣን ያላቸው ጥማት ብቁና የተሻለ ሰውን ወደፊት ላለማምጣት ያላቸው ፍላጎት በግል ኢጎ ማበጥና የአቅም ማጣትን እያየን አዝነናል:: የመሪዎቹ ብቃት ማጣትም ሕዝባዊ ትግሉ ለአደጋ የተጋለጠ እንዲሆን አድርጎታል::
በግራም በቀኝም ከላይም ከታችም የተነሱ የአማራ ጠላቶችን ያስበረገገው አስደናቂና መብረቃዊው የፉኖ ፈጣን ወታደራው ምላሽ ከአስደናቂነቱ በላይ ሰንቆት የነበረው ስር ነቀል ሃገራዊ ተስፉ ከፍተኛ ነበር:: በታሪክ ከተመዘገቡ የትጥቅ ትግሎች በአስደንቂነቱ መመዝገብ የቻለው የፉኖ ትግል በአጭር ግዜ ውስጥ ከባዶ እጅ ተነስቶ አመት ባልሞላ ግዜ ውስጥ ከጠላቱ በማረከው ትጥቅና ሎጀስቲክ ከጋንታ አደረጃጀት ወደ ክፍለጦር እና እዝ ያሳየው እመርታ እጅግ እስደኒቂና አኩሪ ሆኖ ተመዝግቧል::
ይህን በወታደራዊ አካሄድ የተገኘውን እመርታ በፖለቲካ አደረጃጀት አጠናክሮ ወደ ወሳኝ ግቡ ይሸጋገራል : ከሌሎች ሃገራዊ ሃይሎች ጋር ትብብርና ቅንጅት ፈጥሮ ሰው በላውን የአብይ አህመድ አገዛዝ በአጭር ግዜ ደምስሶ የስርዐት ለውጥ ያመጣል ተብሎም ተጠብቆ ነበር:: እየመጡ ነው የሚል ተስፉን የሰነቀ ዜማ ከመተማ እስከ ቦረና ከደንበጫ እስከ ወጨጫ የተዜመው ፉኖ ሕዝባዊና ሃገራዊ ተልዕኮ የመሸከም አቅም ያላቸው ትግሉን በድል መምራት የሚችሉ መሪዎች አሉት በሚል ግምት ነበር:: እየሆነ ያለውና የምናየው ሁኔታ ካልተለወጠ የአማራን ሕልውና ማዳኑ ቀርቶ የበለጠ የሚያጠፉው እንዳይሆን ስጋትን ወደ መፍጠር ተሸግግሯል:: አማራ እንደ ሕዝብ ትግል በጀመረበት በዚህ ወሳኝ ወቅት የገጠሙትን ፈተናዎች በጥበብና በዘዴ ፈቶ ወደ ፊት እንዳይራመድ ከባድ ያደረገው የችግሩ ደንቃራ ሌላ ማንም ሳይሆን የእራሱ የአማራው ልሂቅ ፖለቲከኛ ነኝ ባዩ እና በግንባር ሆነው ትግሉን እየመሩ ያሉት የፉኖ መሪዎች መሆኑ ዛሬ ላይ የአደባባይ እውነታ ሆኗል::
አማራ ከሃገራቸው አልፈው ለአለም አሻራቸውን ያኖሩ ታላላቅ ሰዎችን ያፈራ:: ለኢትዮጵያ አንድነት ለነጻነቷ መስፈሪያ የለሽ ዋጋ የከፈለ ባለታሪክ:: ለእድገትና ስልጣኔ ፈር ቀዳጅ በመሆን ብዙ ያዋጣ ለአፍሪካውያን ነጻነት ተምሳሌቶችን ያፈለቀ ሕዝብ: : የአመራር ጥበብ የአስተዳደር ክህሎት የቅራኔ አፈታት ስልቶችን ያኖረ የደመቀ ባህል ባለቤት ነበር::ስልጣኔ ሊሸረው ያልቻለ የሽምግልና ተቋማዊ እሴትና ዘመናዊነት ሊደመስሰው ያልቻለ የራሱ የሆነ የኑሮ ዘይቤና ወግ ያለው ሕዝብ ነው::
ይህ ታላቅ ባለታሪክ ሕዝብ የታሪክ መጋጠሚያ ላይ ደርሷል:: ከወግና ባህሉ ያፈነገጠ ነውረኛ ትውልድ እንደ አረም በቅሎበታል ::ባንዳነት ክብሩ : የገዛ ወገኑን መሸጥ ንግዱ ያደርገ በዝቶበታል:: ልሂቁ ትግል ለመጥለፍ የሚሰማራ ታጋዮችን የሚያባላ ተማርኩ የሚል መሃይም ሰለጠንኩ የሚል ሰይጣን የፉኖን ትግል ወሮታል:: “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል እንዳለችው አህያ” እኔ የሌለሁበት ድርጅት ይጥፉ የኔ ቡድን ከፍ እንዲል ሌላው ይውደም የሚል ጨካኝ የበዛበት ነው:: ውይይት እርቅና መነጋገር ይኑር ብሎ ከመሞገት ይልቅ እርስ በእርስ እንዲዋጉ በደሃ ወገኖቹ ላይ መከራ የሚያውጅ አረመኔ የዲያስፖራ መንጋም እንዳለ አብረን ሆነን እለት እለት የምናየው አሳዛኝ ትራጄዲ ነው::
አማራ በዚህ አይነት ሁኔታ ከቀጠለ ለከፉ እልቂት የሚዳርግ ቀበቶ እናስፈታለን ብለው ጦርነት የጀመሩበት ጠላቶቹ ሱሪውን አስወልቀው መዘበቻና መጫወቻ ቢያደርጉት ተጠያቂው የፉኖ አመራር እና በዲያስፖራ ያለንው ይሆናል:: ለአማራ ሽንፈት መበተንን : ከእሴትና : ባህሉ : ከወጉ እና ከማንነቱ ተነጥሎ መጥፉትን ማስከተሉ ሊሰመርበት ይገባል:: አማራ በዚህ ከባድ የሕልውና አደጋ በተከበበት ጠላቶቹ ጥርሳቸውን አግጠው ሊውጡት ባሰፈሰፉበት የመከራ ወቅት ምን አዙሪት ቢኖርብን ምን ያህል የከፉ ድንቁርናስ ቢጫነን ነው እርስ በእርስ ለመጠፉፉት ጠመንጃችንን የምወለውለው::
ያ ሃገር ያቆየ አማራ የቅራኔ ፈቺ ዘመን ተሻጋሪ የአመራር ጥበብ እና የሽምግልና ወግና ስርዐት ያለው ሕዝብ አብራክ ወጥተን ምን ነካን በዚህ ያህል ደረጃ የወረድንው ::ይህ ዛሬ ላይ እጅ ለእጅ ተያይዘን ልንሻገርበት ይገባ የነበረውን ፉኖአዊ የአንድነት መርከብ እንዴት እራሳችን እንሸነቁራለን:: ከመርከቡስ ስንቶቻችን እንተርፉለን:: ይህ የመከራ ውቅያኖስ ሁሉንም የሚያሰምጥ በክፉት እና ደካማነታችን ሁላችንንም ጠራርጎ አንጦሪጦስ ነው የሚጥለን:: መተባበር ቢያቅተን መከባበር እንዴት ያቅተናል:: እንዴት በአደጋ በተከበበ ቀጠና ውስጥ ሆነን በጋለሞታ እንደሚጣላ የመንደር ጎረምሳ በነውር ቃላት እንሰዳደባለን:: አረ ጎበዝ እናስተውል:: መሪ ተብየዎቹንም አደብ ግዙ እንበል:
አማራ እንደ ሕዝብ ኢትዮጵያ እንደ ሃገር መዝቀጥ ከጀመሩበት ከ66ቱ ንቅናቄ ጀምሮ ቁልቁል እየወረድን የመጨረሻው ጠርዝ ላይ ደርሰናል:: አብዮታዊያኑ በተቀላወጠ የግራ ርዕዮተ ዓለም በተዛባ የሃሰት ተረክ እና በኑፉቂያዊ አስተሳሰብ ተመርዘው የብሄረሰቦች እኩልነትን በኩታና ጋቢ ልክ መዝነው የገዢና ተገዢ ትንተናን በማቀንቀን ዛሬ አማራ የሚታረድበትን ቢላ አቀብለዋል:: የነዋለልኝ የተንበርካኪነት ሌጋሲ ወራሽ የሆኑ ሕዝባቸውን ለአራጆች አሳልፈው የሰጡ ብአዴን ከሚባሉ ጉግማንጉግ ሰው በላዎች እስከ እነ በለጠ ሞላ አብን የጭራቅ አጫዋቾች ብዙ መርገምቶች ከአማራው ሕዝብ አብራክ መገኘታቸው ሕዝቡን ማሳፈር ብቻ ሳይሆን ለሰቆቃው መክበድ ዋና ምክንያት ሆነዋል::
አማራ ከትልንት እስከ ዛሬ ከአብራኩ በወጡ የእንግዴ ልጆች ለጠላቶቹ አሳልፈው ሲሰጡት ቆይቷል:: ዛሬም ያው ቀጥሏል በተለይ በውጭ ሃገር የሚኖረው የአማራ ፖለቲከኛ ተብዬ በማህበራት ስም ቀውስን አክትቪስት ተብዬው መለያይየትን በሚድያ ያለው መርገምቱን ልሂቅ ነኝ ባዩ ልዩነትን በማቀጣጠልና በማራገብ ሲቆሰቆስ የቆየው እሳት ሕዝብና ትውልድን ሊበላ ተቃርቧል:: የፉኖ ጥቂት መሪዎች አርቀው ማሰብ ተስኗቸው በዲያስፖራው ክፉት እና ፉኖን መስለው በተጠጉ ቅጥረኞች ወደ ውድቀት መንገድ እየተገፉ ነው:: የግብ የአላማና ይህ ነው የሚባል የርዕዮተ ዓለም ልዩነት ሳይኖር በጥቂት የፉኖ መሪዎች ኢጎ ሕዝባችን ወደ ጨለማው ሳይገባ ትኩሳቱን ለማብረድ መረባረብ የወገኑ ጉዳይ የሚያሳስበው ሁሉ ድምጹን ሊያሰማ ይገባል::
የአማራ ሕልውና ይመለከተኛል የሚል ቀና ወገን ሁሉ የፉኖ ትግል ካለበት የአመራር ቅርቃር እና ከእርስ በዕርስ ግጭት እንዲወጣ ዘመኑን የሚዋጅ ከአሮጌ ፖለቲካ ባህል የተፉታ ከመንጋ አስተሳሰብ የራቀ በምክንያት በሂስና ግለሂስ የሚዘወር ፖለቲካ ባህልን የተላበሰ አቋምና መፍትሄን መመልከት ይኖርብናል:: በተለይ በውጭ ሃገር ያለንው “በሮማ ስትኖር እንደ እሮማዊ ሁን” አዋቂዎች እንዲሉ : የሃሳብ ብዝሃነት ዋልታ የረገጡ ጽንፍ አስተሳሰቦች በውይይትና በንግግር በሚፈታበት በምዕራቡ ሊበራል አለም ውስጥ እየኖርን የዛገና የወየበ የስብስቴ ዘመንን የሚያስንቅ የዘለፉና የአሉባልታ ባህል ውስጥ ፖለቲካችን የማውጣት ሃላፊነት አለብን:: ሁሉን በእኩል ማየት የማይችል አመለካከት ማስወገድ አለብን:: መንጋነት ለከብት እንጂ ለሰው ልጅ ስብዕና የሚስማማ አይደለም:: ውይይታችን ምልከታና አቋማችን ያለው ተቃርኖ በሰለጠነ ውይይት ልንፈታው ይገባል:: አለያ በየጏዳውና በየድብኝቱ አድፍጦ በሃሳብ የተለየንን ማጠልሸት መስደብ ተራ የባልቴት ተግባር በመሆኑ የዚህ ባህል ቁራኛ የሆነው ፖለቲካችን መፈወስ ይኖርበታል:: ጎበዝ አለም የተለወጠችው በክርክር በውይይት አዳዲስ ባህልና በጎ ልማድን በማጎልበት እንጂ ንጉስ አይከሰስ ሰማይ አይታረስ በሚል እንደ ጋሪ ፈረስ በአንድ አቅጣጫ ካልተጏዝኩኝ በሚል መንጋነት አይደለም:: በአማራ የሕልውና ትግል ውስጥ: ትግሉም ታጋዩም ድርጅቱም ክፍለጦሩም ሻለቃ ይሁን ብርጌድ የአማራን አንድነት እስካላረጋገጠ ድረስ የትም አይደርስም:: አንዱን ጥሎ አንዱን አንጠልጥሎ ወንዝ መሻገርም አይቻልም:;አንዱን አጀግኖ ሌላውን ተሳድቦ ፈጽሞ ውርደትን እንጂ እንደ ሕዝብ ወደ ክብር አያሸጋግረንም::
አባቶቻችን ደማችውን አፍስሰው አጥንታቸውን ከስክሰው እጅግ ከባድ የሕይወት ዋጋ ከፍለው ያወረሱንን ሃገርና ታሪክ : በርካሽ ስብዕና በከንቱ ውዳሴና በባዶ ኢጎ አብጠን በአሉባልታ ወሬ ሰክረን ወደ ሲዖል እንዳንወርድ ከጀመርንው የእርስ በርስ የመካሰስ የጭለማ መንገድ ወጥተን ወደ አብሮነት የብርሃን ተራራ እንወጣ ዘንድ ፈጣሪ ማስተዋሉን ያድለን::
ድል ለጭቁኑ የአማራ ሕዝብ!!!
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!!