ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)
ሚያዚያ 14፣ 2017( April 22, 2025)
መግቢያ
ይኸው በፖለቲካ የትግል ዓለም ውስጥ ከገባሁና በተከታታይም መጻፍ ከጀመርኩ ከሰላሳ ዓመት በላይ አስቆጠርኩኝ። ባለፉት ሰላሳ ዓመታት በተከታታይ ስጽፍ ዝምብዬ ከመጻፍ፣ ወይንም ደግሞ የፖለቲካንና የህብረተሰብ ትርጉም እንዲሁም የህብረተሰብን ውስጣዊ ህጎች የተወሰኑ ዘዴዎችን(School of Thought) በመከተል ከመጻፍና ዕውቀቴንም ለሌሎች ለማስተላለፍና ለማስተማር ከማሰብ በስተቀር ለማንና ለምን ህብረተሰብ እንደምታገል ራሴን የጠየኩበት ጊዜ አልነበረም። ለምንስ ስንትና ስንት ገንዘብ ማግኘት የምችልበትን ሌላ ስራዎች በማቋረጥ በጽሁፍና በፖለቲካ ስራ በመጠመድ “ወርቃማ ጊዜዬን” እንዳሳለፍኩ ራሴን ስጠይቅ ለእኔም ሆነ ሌላውን የሚጠቅም ስራ የሰራሁት ነገር የለም። አንዳንዶችም አንዳንድ ጊዜ ስንገናኝ የሚጠይቁኝና የሚነግሩኝ፣ “ለመሆኑ ማን ይሰማኛል ብለህ ነው እንደዚህ ጊዜህን እያጠፋህ የምትጽፈው? ሰው እንደ እብድ ነው የሚቆጥርህ “ እያሉ ነው የነገሩኛና የሚነግሩኝ። በሌላ ወገን ግን መጻፍና ለፖለቲካ መታገል ድረግ ካላጨሰ ወይም ካልወሰደ መንቀሳቀስ ወይም ማሰብ እንደማይችል ሰው መጻፍና ስለፖለቲካ ማስብ እንደሱስ ሆነውብኛል ብል ራሴን ከፍ እድርጌ እንደማልገምት ግንዛቤ ውስጥ እንዲገባልኝ አንባቢዎቼን አሳስባለሁ። ይህ ብቻ ሳይሆን ስለፖለቲካም ሆነ ስለሌሎች የህብረተሰብ ጥያቄዎች በምጽፍበት ጊዜ ከሳይንሳዊና ከፍልስፍናዊ ዕምነት በመነሳት ብቻ ነው። አንድ ሰው በፖለቲካ ትግል ውስጥ ገብቶ በሚሳተፍበት ጊዜ የተወሰነ ሳይንሳዊ አመለካከትና የአሰራር ስልትም እንዲኖረው ያስፈልጋል። ይህን መሰረታዊ አስተሳሰብ ከደሜ ጋር በማዋሃዴ ያሰብኩትንና ትክክልም ነው ብዬ የማምንበትን ከመፃፍ እንዳቅልቆጠብ አድርጎኛል። ይሁንና ግን እኔ ትክክል ነው ብዬ የማምንበት የአፃፃፍና የግንዛቤ ስልት ህዝባችንን ወደሚፈልገው የነፃነት፣ በሰላም የመኖርና አንዳች ዐይነት የሆነ ዕድገት ያጎናጽፈው አያጎናጽፈው መናገር በጣም አስቸጋሪ ነው። በተለይም በአሁኑ በግሎባልያዜሽን ዘመን ብዙ ነገሮች ተዘበራርቀውና የዓለም ህዝብም መላወሻ ባጠበትና አቅጣጫውም በጠፋበት ዘመን ስልጣን ላይ ሊወጡ የሚችሉ ኃይሎች አመፀኖች፣ መንፈሳቸው በዝቅተኛ አስተሳሰብ የተጠመደ፣ ልታይ ልታይ በማለት በራሳቸው ኤጎ የተጠመዱና የሚሰሩትን የማያውቁ ስለሆነ የአንድን ህብረተሰብ የወደፊት ዕድል መገመት በጣም ያስቸግራል።
ለዚህ ጽሁፍ መነሻ የሆነኝ አንድ ጉዳኛዬ በኋትሳፕ መለዕክቱ “መረዳት፣ መግለጽ፣ መተንበይ፣ ራስን መቆጣጠር” በሚል ከአንድ ፌስቡክ ያገኘውን ከላከልኝ በኋላ ይህ የግዴታ ከጭንቅላት ወይም ከሳይኮሎጂ ጋር የተያያዘ መሆኑን በመረዳት፣ በመሰለኝ መልክ መልስ ስጽፍ ትዝ ያለኝ ነገር ወደ ሁለት ትውልድ የሚያሰጠጋ እስካሁን ድረስ በአገራችን ምድር በፖለቲካና በነፃነት ስም የተደረገው ትግል ለምንና ለማን እንደሆነ፣ ስልቱና የቲዎሪ መሰረቱ ወይም ሳይንሳዊ ዘዴው እንዳልታወቀና እንደማይታወቅ ወዲያውኑ ብልጭ አለብኝ። ከዚህ ቀደምም ጥልቅነት በሌለው መንገድ አለፍ አለፍ አድርጌ ብጽፍም ውድ ወዳጄ የላከልኝ የኋትስአፕ መልዕክት ግን በነገሩ ላይ ጠለቅ ብዬ እንድተነትነው አስገደደኝ።
በእርግጥም አብዮቱ ከፈነዳ በኋላና እንደዚያ ዐይነት ምስቅልቅል ያለ ሁኔታ መፈጠሩን አስመልክቶ ከማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት ጎን ሳልወግንና ይኸኛው ነው ትክክል፣ ያኛው ነው ጥፋተኛው በማለት አንድ ወጥ አቋም የወሰድኩብት ጊዜ አልነበረም። ዕውቀቱና ብስለትም ስላልነበረኝ ይኸኛው ድርጅት ነው ትክክል፣ ያኛው ድርጅት ነው ስህተተኛ ብሎ ለመፍረድ የምችል ሰው አልነበርኩም። በፖለቲካ ዓለም ውስጥ ከገባሁና አንዳንድ ከኔ የተሻለ ግንዛቤ የነበራቸው፣ በተለይም ከማርክሲስት ስራዎች ጋር ካስተዋወቁኝ በኋላና፣ ቀስ በቀስም ከአውሮፓው የውጣ ውረድ የህብረተሰብ አገነባብ ታሪክ ጋር ለመተዋወቅ ዕድል ስላጋጠመኝ ሚዛናዊ ፍርድ የመስጠት ዕድል ለማግኘት ችያለሁ ብል የምሳሳት አይመስለኝም። ባለፉት ሰላሳ ዓመታት በተከታታይ ያወጣኋቸውን ጽሁፎቼን ለተከታተለ የሚረዳው የአጻጻፌ ስልትና ፍልስፍናዊ መሰረት ከማንኛውም ድርጅት ጋር የማይጣጣም፣ ወይም ደግሞ ወገናዊ ያልሆነ ነው። ይሁንና ራሴን እንደ አርቆ አሳቢ በምቆጥረበት ጊዜ ደግሞ የትኛዎቹ የአብዮት ተዋናይ ኃይሎች በደመ-ነፍስ በመመራት ለእንደዚያ ዐይነቱ እልቂትና ምስቅልቅል ሁኔታ መፈጠር ተጠያቂ እንደሚሆኑ የማወቅ ችግር አልነበረብኝም፤ የለኝም። በአገራችን ምድር እንደዱብ ዕዳ የወረደው አብዮት የሚሉት ነገር ሲፈነዳ እንደዚያ በብዙ ድሮች ባልተሳሰረና የኢኮኖሚ መሰረቱም በተዝረከረክ መልክ በሚገኝበት አገር ውስጥ ጥራዝ-ነጠቅነትና አርቆ ያለማሰብ እንደሚከሰቱ መረዳቱ ያህንን ያህልም አስቸጋሪ አይደለም። ይሁንና ግን አንድ ነገር መጠኑን ሲስት ዋናውን ምክንያት ለመረዳት ደግሞ በጣም ከባድ እንደሚሆን መገመት ይቻላል። ምክንያቱም በዕልቂቱና በምስቅልቅል ሁኔታዎች ውስጥ እንደዚያ ያለ የብዙ ሺሆች ወጣቶችን ህይወት የቀጠፈ አላስፈላጊ መጠፋፋት በአንዳንድ የድርጅት መሪዎች አማካይነት ቢተለኮስም ሁኔታው በመቀጣጠል የአብዮቱ ተዋናይ የነበረውን አብዛኛውን ሲያካትትና እነሱም በተቀጣጠለው እሳት ላይ ቤንዚን ሲያርከፈክፉበት ምክንያቱን ለመረዳት በጣም ከባድ ይሆናል። በተለይም ደግሞ በተዘዋዋሪ የተቀጣጠለው እሳት የባሰ እንዲባባስ ከበስተጀርባ ሆነው የሚገፋፉና በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በግድያና ባሻጥር ስራ ውስጥ የተሳተፉትን የውጭ ኃሎችና በነፃነት ስም እንታገላለን የሚሉት እንደ ሻቢያና ህወሃት የመሳሰሉትን በቀይና በነጭ ሽብር ድርጊት የተሳተፉትን እነዚህን ሁሉ እየተከታተለ ለመለየትና ለማወቅ በጣም አስቸጋሪ ነበር። ለማንኛውም ራሳቸውም የዚኸኛው ወይም የዚያኛው ድርጅት አባል የነበሩና በማዕከላዊ ኮሚቴ ውስጥ የነበሩ ግለሰቦች የሚመሰክሩት፣ በቃለ-መጠይቅ ምልልስና የሚያመረቃ መጽሀፍ በመጻፍ ያረጋገጡት ጉዳይ ያ ዐይነቱ ሁኔታ ሊከሰት የቻለው በአንዳንድ የድርጅት አመራር አባሎች ስህተትና አርቆ-ካለማሰብ እንደተነሳ መገመቱ ከባድ አይሆንም። ስለሆነም ከራሳቸው ከድርጅት ሰዎች ከነበሩት የወጡትንና የተጻፉትን መልዕክቶች በጥብቅ ለተከታተለና፣ በድርጅቶች ውስጥም የነበረውን ከአርባ በላይ የሚቆጠር በዩቱቭ መልክ የቀረበ ትንተና ለተከታተለ ሰው የተወሰነ ሚዛናዊ ፍርድ ለመስጠት ይችላል የሚል ዕምነት አለኝ።
የዚህ ጽሁፍ ዋና ዓላማ ይህንን ወይም ያኛውን ድርጅት ለመወንጀል፣ ሌላውን ደግሞ ትክክል ነበር ብሎ ለማወደስ የተጻፈ ሀተታ ሳይሆን ከላይ አርዕስቱ ላይ ለማሳየት እንደሞኮርኩት ለማን፣ ለምንና በምንስ ዐይነት ዘዴ ነው የምንታገል የነበረው? አሁንስ የምንታገለው ብዬ ራሴን ስጠይቅ ከሃምሳ ዓመት በላይ በፈጀ የፖለቲካ ትግል ውስጥ እስካሁን ድረስ ራሳችንን ለመጠየቅ አለመቻላችን ነው። ለመሆኑስ ድርጅት መስርቻለሁ፣ የፖለቲካ ትግል አካሂዳለሁ፣ ብሄረሰቤን ወይም ደግሞ ህብረተሰቤን ነፃ አወጣለሁ የሚል ግለሰብም ሆነ ድርጅት ካለ በቂ ቲዎሪ፣ የሳይንሳዊና የፍልስፍና ስልት ወይም ዘዴ ሊታገል ይችላል ወይ? በዚህስ መልክ በሌሎች አገሮች ትግል ተካሂዷል ወይ? በመጠፋፋትና አንደኛው በሌላው ላይ ጣቱን በመቀሰር፣ ወይም ደግሞ ስልጣን ላይ ስወጣ አሳይሃለሁ በማለት የተገነባ ማህበረሰብ አለ ወይ? ብዬ ራሴን ስጠይቅ ቢያንስ ከሞላ ጎደል ተሳካላቸው የሚባሉ ህብረተሰቦችን ስመረምር የምገነዘበው ነገር ለፖለቲካ ነፃነት እንታገላለን ብለው ድርጅት የመሰረቱና የውጣ ውረድ ትግል ያካሄዱት ኃይሎች አነሰም በዛም የህብረተሰባቸውን ችግር በትክክል በማንበባቸውና ትክክለኛ ስትራቴጂም በመቀየሳቸውና በመከተላቸው እስከተወሰነ ደረጃ ድረስ ስኬታማ ለመሆን በቅተዋል፤ ከሞላ ጎደል ህዝባቸውን በማሰባሰብና ህብረተሰብ በመመስረት ለመከበር በቅተዋል። ሌላው ደግሞ በአነሳሳቸው የተገነዘቡት ነገር ከህዝብ ጎን ሊቆም የሚችለውን ኃይል በመሰብሰብ፣ ወይም ደግሞ በተቻለ መጠን ክፍፍል እንዳይኖር በማድረጋቸውና በመተባበራቸው፣ እንዲሁም በአንድ ደርጅት ጥላ ስር በመደራጀታቸው የመጨረሻ መጨረሻ የፈለጉትን ዓላማ አሳክተዋል፤ታላቅ አገርም ለመገንባት ችለዋል። ወደ እኛ አገር ስንመጣ ግን አንድ ዐይነት ርዕይ አለን የሚሉት ሁሉ ሳይቀሩ እንደ ጠላት በመተያየት የመጨረሻ መጨረሻ ወደ መጠፋፋት ነው ያመሩት። በመተባበርና ኃይልን በማጣመርና እንዲሁም በአንድ ርዕይ ስር በመሰለፍ አገራችንን ከመገንባት ይልቅ በተናጠል ውር ውር በማለትና ”የእኔን ሃሳብ የተቀበለ ወዳጄ ነው፣ ያልተቀበለ ደግሞ ጠላቴ ነው” የሚለውን የህብረተሰብንና የተፈጥሮን ህግ የሚጥስ የትግል ዘዴ ብለው የሚጠሩትን በመከተላቸው አገራችንና ህዝባችንን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንዲወድቁ በማድረግ የመጨረሻ መጨረሻ መንገዱን ለገነጣጣይና ለኢምፔሪያሊስት ኃይሎች ላደሩ አፈጋንጭ ኃይሎች አመቻችተው ሄደዋል።
ከዚህ አጭር ሀተታ ስንነሳ ብሄራዊ አጀንዳ አለን የሚሉትም ሆነ ብሄረሰባችንን ነፃ እናወጣለን ብለው አላስፈላጊ ግብግብ ውስጥ የገቡት የብሄረሰብ ድርጅቶች በሙሉ የትግል ስልት የሚሆናቸው የቲዎሪ፣ የሳይንስና የፍልስፍና መሰረት እንዳልነበራቸውና እንደሌላቸው እንገነዘባለን። ይኸው እንደምናየው ከመጠፋፋትና አገርን ከመበታተንና፣ የመጨረሻ መጨረሻ ላይ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ አቅጣጫውና የኑሮ ትርጉም ጠፍቶበት ልክ ድረግ እንደወሰደ ሰው እየተደናበረና ራሱን ሳያውቅ እንዲኖር ለማድረግ በቅተዋል። ይህ ሁሉ ወንጀል የተፈጸመውና የሚፈጸመው በቂ የፖለቲካ ቲዎሪና፣ የፍልስፍና እንዲሁም የህብረተሰብ ህግ ግንዛቤና የውጣ ውረድ ጉዞ ባልገባቸው አሁንም በህይወት አለን እያሉ በሚያወናብዱ ኃይሎች አማካይነት ነው።
ከሃምሳ ዓመታት በላይ ባስቆጠረ የፖለቲካ ትግል በሚሉት፣ ግን ደግሞ ስልትና የቲዎሪ መሰረት የሌለውን የትግል ሂደት ስንጠይቅ አብዛኛው ታጋይ ነኝ ባይና የፖለቲካ ድርጅትም መስርቶ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወገኖቻችንን ያስጨረሰው ለመሆኑ የህበረተሰባችንን ሁኔታና አወቃቀር በበቂው ተረድቷል ወይ? የህብረተሰባችንን አወቃቀር ለመረዳት ብቻ ሳይሆን የህዝባችን የአኗኗር ሁኔታ ለምን በዚያ መልክ፣ ለምሳሌ በድህነትና በኋላ-ቀርነት ይገለጽና እንደሚገለጽ ለመረዳት የተወሰነ ሳይንሳዊ የአሰራር ዘዴን ይከተል ነበር ወይ? ድርጅት መስርተን ነበር በሚሉት ውስጥም የቲዎሪና በፍልስፍና ላይ የተመሰረተ ክርክር ይካሄድ ነበር ወይ? ብለን ስንጠይቅ የምናገኘው መልስና ከውጤቱም እንደምንገነዘበው በቂ ክርክር ወይም ምንም ዐይነት ክርክር ይካሄድ እንዳልነበረ፣ መካሄድ ሲጀምር ደግሞ ክሪቲካል አመለካከት የነበራቸው እንዲወገዱ ወይም በአንዳች ነገር እንዲሰወሩ እንደተደረገ ለመገንዘብ ችለናል።
ከዚህ ዐይነቱ ዓላማ ቢስ የትግል ዘዴ ስንነሳ በአንዳንድ አገሮች ውስጥ፣ በተለይም በአውሮፓ ምድር ለውጥ ለማምጣት የጭንቅላት ትግል ሲጀመር ይነሳ የነበረው ጥያቄ ለምድን ነው አንድ ህብረተሰብ በውዝግብ ዓለም ውስጥ የሚኖረው? ለምንድን ነው ስልጣንን የጨበጡ ሰዎች ከራሳቸው በማለፍ ለሌላው ማሰብ የማይችሉት? አንድ ማህበረሰብስ ራሱን በራሱ ሳያገኝ እንደ እንስሳ እዚህና እዚያ እየዘለለ መኖሩ የተፈጥሮ ህግ ነው ወይ? የሰው ልጅ ከእንስሳ የሚለይ ከሆነ ለምንድነው ስርዓት ያለው ማህበረሰብ ለመመስረት የማይችለው? ስርዓት ያለው ማህበረሰብ ለመመስረት ደግሞ ምን ምን ነገሮች ናቸው የሚያስፈልጉት ወይስ መሟላት ያለባቸው? አንድንስ ህብረተሰብ ለመለወጥ የግዴታ የጠበንጃ ትግል አስፈላጊ ነው ወይ? ወይስ ደግሞ በመጀመሪያ ደረጃ የጭንቅላት ስራ መሰራት አለበት ወይ? አንድን ህብረተሰብ መለወጥ የሚቻለው የጠቅላላውን ህብረተሰብ የንቃተ-ህሊና ደረጃ በማሳደግ ላይ በሚሉ ነጥቦች ላይ ነበር የሚደረገው ውይይት። በተለይም በጀርመን ምድር በፈረንሳይ አብዮት ዘመን 1789 ዓ.ም የተካሄደውን የሰብአዊ መብት መከበርን፣ የፊውዳሎችን ጥቅም የሚያስከብረውን ህግ ማንሳትና ሬፑብሊካዊ የሆነ አገዛዝና የነፃነት ጥያቄና የተቀሰቀስውን አብዮታዊ እንቅስቃሴ አስመልክቶ የጥያቄው አነሳስ ትክክል ቢሆንምና ለሌሎች የአውሮፓ አገሮችም እንደምሳሌ ቢታይም ከዚያ በኋላ በንጉሳውያን ቤተሰብ ላይ የተፈፀመውን አሰቃቂ ድርጊት የተከታተሉ የጀርመን ፈላስፋዎችች የደረሱበት ድምደማ በአንድ አገር ውስጥ ለውጥ በዚህ መልክ መምጣት እንደሌለበት ነው። ስለሆነም የጀርመን አይዲያሊስት ተብለው የሚጠሩት ፈላስፋዎች ያተኮሩት በጭንቅላት ስራ ላይ ነው። ይህም ማለት የአርቆ-አሳቢነትን ትርጉም ማስተማርና አገዛዞችም ሆነ ተራው ህዝብ በዚህ መንፈስ እንዲመሩ ማድረግ የሚል ነበር። ምክንያቱም ማንኛውም መጥፎም ሆነ ጥሩ ድርጊት በጭንቅላት የሚታሰብ ስለሆነና አካላችንም በጭንቅላታችን ስለሚታዘዝና ድርጊቱን ስለሚፈጽም ነው። ወደ እኛ አገር ስንመጣ ግን ፋታ ባለመገኘቱ አንድ ጊዜ እሳቱ ሲቀጣጠል አርቆ የሚያስብ ምሁራዊ እንቅስቃሴ ስላልነበረ የተወሰነው የአብዮቱ ተዋናይ ነኝ የሚለው ኃይል በደመ-ነፍስ በመመራት እስከተወሰነ ደረጃ ድረስ የአገሪቱን የተወሳሰቡ ችግሮች ሊፈታ ይችል የነበረው አብዮት መስመሩን እንዲስት ለመደረግ በቃ። የአብዮቱ ተዋናይ፣ በተለይም በመሪነት ደረጃ ላይ የነበሩት በአብዮቱ እንቅስቃሴ በከፍተኛ ደረጃ የተሳከሩ በመሆናቸውና ስልጣንንም ለመያዝ በጣም የቋመጡ ስለነበር እነዚህን ኃይሎች ከውስጥ ደፍሮ ሊያስቆማቸው የሚችል ኃይል አልነበረም። የሚደፍር ካለ ደግሞ እንዲጠፋ ይደረግ ነበር።
የአንድን ህብረተሰብ የውጣ ውረድ ጉዞና ስልጣንን የጨበጡ ኃይሎች የንቃተ-ህሊና የዕድገት ደረጃ የመረዳት ችግር!
በፍልስፍና ወይም በሳይንስ የአሰራርና የአመራር ስልት ውስጥ አንድን ነገር ከመጀመር በፊት ያ ሁኔታ ለምን በዚያ መልክ እንደሚገለጽ፣ ለምን በሌላ መልክ ለመገለጽ እንዳልቻለ መረዳቱ ስህተት ወይም ወንጀል ከመስራት እንደሚያግድ ፈላስፋዎች ይናገራሉ። አስቸጋሪው ነገር የአንድን የህብረተሰብ አወቃቀር ጠጋ ብሎ በመመርመር ለመረዳት የሚችል ሰው በጣት በሚቆጠርበት አገር ውስጥ ወይም ደግሞ ምንም በሌለበት አገር ውስጥ የሚጀመረው ትግል ነገሮችን ሳይረዱና ዓላማውስ ምን እንደሆን ሳይታወቅ ነው። አብዛኛዎቻችን በተለይም ከአውሮፓው የህብረተሰብ አወቃቀርና የህብረ-ብሄር ምስረታና ግንባታ ጋር ያልተዋወቅን ስላልነበርንና ስላልሆንም- ይህንን አፌን ሞልቼ መናገር እችላለሁ፣ ትላንትም ሆነ ዛሬ ያለ ችግር ነው- በጊዜው በአገራችን ምድር የነበረውን ሁኔታ እንዲያው በጭፍኑ በጥቁርና በነጭ በመሳል ብቻ ነው ትግል የሚባለውን ፈሊጥ አንዳንዶች የጀመሩትና ያስፋፉት። ከዚህም በላይ አብዛኛዎቹ ታጋይ ነን ይሉ የነበሩትና የአብዮቱ መሪዎች የህብረተሰባችንን የውጣ ውረድ ጉዙ ለመረዳት በጣም ጥራዝ ነጠቅ በሆነ መልክ ከተጻፈው መጻሀፍ፣ በተለይም በጊዜው ሶብየትህብረት በተዘጋጀው Fundamental of Marxsim and Lenisim ከሚለው መጽሀፍ ውጭና፣ ሌኒን ካሳተማቸው ለምሳሌ What ist to be done? ና One Step Forward and two Steps Backward ከሚለው አልፈው ያነበቡት መጽሀፍ አልነበረም። ለምሳሌ የማርክስን ቀደም ብለው የነበሩ ስራዎችንና የኋላ ላይ መሰረታዊ ስራውንና ዳስ ካፒታልን በመወስድና በማጥናት የካፒታሊዝምን አፀናነስና በተወሳሰበ መልክ ማደግ ያነበበና ያጠና እንዳልነበረ የሚታወቅ ጉዳይ ነው። በሌላ ወገን ደግሞ የማርክስ ስራዎች ብቅ ከማለተቻው በፊትም ሆነ በኋላ በሌላ መልክ የፍስልፍና፣ የተፈጥሮ ሳይንስ፣ የኢኮኖሚክስ ቲዎሪና የሶስዮሎጂ መጽሀፎች በሚገባ መልክ ተጽፈው እንደሚገኙ የሚታወቅ የነበረና ያለ ሀቅ ነው። ይሁንና ግን የጊዜው ትሬንድ ስለነበር የተማሪው እንቅስቃሴ ያዘነበለው በቁንጽል መልክ በተጻፈው የማርክሲዝም ሌኒንዝም ቲዎሪ ላይ ነው። እንደነዚህ ዐይነት መጽሀፎች ደግሞ በጣም በቁጥብ መልክ እስካልሆነ ድረስ የተለያዩ ህብረተሰቦችን በመውሰድና በመተንተን ውስጣዊ ህጋቸውን ለመረዳት የሚያስችሉ አይደሉም። በአንድ አገር ውስጥ ለውጥ መምጣት አለበት፣ የህዝቡም ኑሮ መሻሻል አለበት ብለን በምንነሳበት ጊዜ ቀደም ብሎ ግሪክ ውስጥ፣ የኋላ ላይ ደግሞ አውሮፓ ውስጥ ከፈለቁት የቲዎሪና የሳይንስ መጽሀፎች ለማምለጥ ባንችልም፣ የሚነሳው ጥያቄ እንዴት አድርገን ነው ጨምቀን በማውጣት ለአገራችንና ለህዝባችን ለለውጥ የሚበጅ ዘዴ መንደፍ የሚቻለው? የሚለው ጥያቄ ከፍተኛ የጭንቅላት ስራን ብቻ ሳይሆን የብዙ ምሁራንንም ተሳትፎ የሚጠይቅ ነው። በሌላ ወገን ደግሞ ካለን ልምድ ስንነሳ ረጋ ብሎ ጊዜ በመውሰድና የተወሳሰቡ ነገሮችን በማጥናት አንድ ወጤታማና ለሁለ-ገብ ዕድገት የሚሆን ሃሳብ ለመንደፍ የሚፈልግ በጣም ጥቂት ነው ማለት ይቻላል፤ ወይም ደግሞ የለም ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል።
ለማንኛውም ከሃምሳ ዓመት ልምድና የቲዎሪ ጥናትና ምርምር በኋላና በብዛት ተተርጉመው ከሚገኙ መጽሀፎች ስንነሳ ማንኛውም አገር እንደማህበረሰ እንዲገነባና አነሰም በዛም ተከታታይነት እንዲኖረው ከተፈለገ፣ የተወሰነና የተሻለ ዘመናዊ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ፣ የባህልና የተቋማት ተሃድሶ እንደሚያስፈልገው ግልጽ መሆን አለበት። ማንኛውም ህብረተሰብ ከአንዳች ርዕዮተ-ዓለም ባሻገር እንደማህበረሰብ ለመቆየትና ለተከታታዩም ትውልድ እንዲተላለፍ ከተፈለገ የግዴታ መሻሻል፣ በየጊዜው መታደስና እርማት ማድረግ አለበት። ይህ ሲሆንና ከፍተኛ የጭንቅላት ስራ ሲሰራና የተወሰነ መስዋዕትነትም ሲከፈል ብቻ ነው አንድን ህዝብና አገር መገንባት የሚቻለው።
ትላንትናም ሆነ ዛሬ በእኛ አገር፣ በተለይም ምሁራንና የፖለቲካ ተዋናይ ነን በሚሉት ዘንድ ያለው ትልቁ ችግር የአንድን ህብረተሰብ ውስጣዊ ህግ ያለመረዳት ችግር ነው። እንደሚታወቀው በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ የሚፈጠሩት ነገሮች በሙሉና የኋላ ኋላ ላይ እንደማህረሰብ ለመኖር የሚያገለግሉት መሰረቶች በሙሉ በዕውቀት አማካይነት ወይም በክፍተኛ ምርምር አይደለም። በተለይም ሰፋ ያለ፣ በጥልቀት የሚያስብ ምሁራዊ ኃይል በሌለበት አገር ውስጥ አብዛኛው ነገር በዘልማድ የሚካሄድ ወይም ደግሞ ብዙም ሳያወጡና ሳያወድርዱ ነው። በግብታዊ ወይም ካለብዙ ውጣ ውረድ ራስን ሳይስጨንቁ (Intuition) የሚፈጠሩና ለጠቀሜታ የሚውሉ ነገሮች ሳይንሳዊ ባህርይ እንዲኖራቸውና በሰፊው ተመርተው ለሰፊው ህዝብ ሊዳረሱ የሚችሉት ጥቂት ኃይሎች ተመራምረው አዳዲስ መሳሪያዎችን ሲፈጥሩና ለሁለ-ገብ የሚሆን የዕድገት አቅጣጫ ሲያሳዩ ብቻ ነው። ለዚህ ዐይነቱ ዕድገት ቀድሞውኑ አመቺ ሁኔታዎች መፈጠር አለባቸው። እነዚሁም በስርዓት የተገነቡ ከተማዎችና መንደሮች መኖርና፣ እንዲያም ሲል የዕደ-ጥበብ ስራዎች ማበብና የንግድ እንቅስቃሴ መስፋፋት ለአዳዲስ ነገሮችና ግኝቶች ወይም ፈጠራዎች አመቺ መሰረቶች እንደሚጥሉ የአንዳንድ አገሮችን የህብረተሰብ የታሪክ ግንባታ ሂደት ለተከታተለ በቀላሉ ሊረዳ ይችላል። ለዚህም ነው የተፈጥሮ ሳይንስና የማቲማቲክስ ሰዎች፣ በኋላ ላይ ደግሞ የቴክኖሎጂ ተመራማሪ ሰዎች ብቅ ማለት የቻሉት።
ወደ አገራችን ስንመጣ በተለያየ ጊዜ ለማስረዳት እንደሞከርኩት እነዚህ ነገሮች በአገራችን ምድር ሊፈጠሩ አልቻሉም። ያልቻሉበትም ምክንያት ስልጣን የያዙት ሰዎች ስላልፈለጉ ሳይሆን ንቃተ-ህሊናቸው ስለማይፈቅድና ቀስ በቀስም እያለ ለዕድገት ተቀናቃኝ የሆኑ ኃይሎችን ሊገፋና ሊተካ የሚችል አዳዲስ አስተሳሰብና ይህንን ለማራመድ የሚችል ምሁራዊ ኃይል ሊፈጠር ባለመቻሉ ብቻ ነው። አዳዲስ ሁኔታዎችና የአኗኗር ስልቶች ቢፈጠሩ ኖሮ ራሳቸው ስልጣንን የጨበጡ ሰዎችም በአዲሱ ሁኔታ በመማረክ ሳይወዱ በግድ ኑሮአቸውን ይለውጣሉ።
አብዮቱ ከመፈንዳቱ በፊት የነበረውና በኋላ ላይም የተፈጠረው አስተሳሰብ ህብረተሰብአችንን በጨቋኝና በተጨቋኝ፣ ወይም ደግሞ በበዝባዥና በተበዝባዥ በመተርጎም ጨቋኝና በዝባዥ ኃይሎች ሲወገዱ ወይም በአንዳች ኃይል ሲጠፉ ሁሉም ነገር መስመር ሊይዝ ይችላል የሚል ግምት ነበር። ከዚህ ሁኔታ ስንነሳ የተማሪው እንቅስቃሴ በተለይም በአገራችን ምድር ላይ ቀስ በቀስ እያለ ከብዙ ዓመታት ጀምሮ የተፈጠሪውን የህብረተሰብ አወቃቀርና(Social Formation) የህሊና ጉዳይ፣ እንደዚሁም በዚህ ዐይነቱ የህብረተሰብ አወቃቀር ውስጥ የተፈጠሩትንና፣ በአንድ አካባቢም ሆነ በአንድ አገር ውስጥ የሚኖሩትን ሰዎች ርስ በርስ የሚያገናኙትን ባህላዊ ነገሮች፣ ለምሳሌ እንደ ሃይማኖት፣ የአማርኛ ቋንቋ ዕድገትና መስፋፋት፣ የእርሻ ስራ መዳበር፣ ልዩ ልዩ ባህላዊ ምግቦች መፈጠርና ሰፊው ህዝብ ቀስ በቀስ እየተለማመደው መምጣት፣ የልብስ ስራዎችና ሌሎች በእንደዚያ ኋላ-ቀር በሚባል ማህበረሰብ ውስጥ የተፈጠሩት ነገሮች በሙሉ በትንተና ውስጥ መካተት የነበረባቸው ነገሮች ነበሩ። በሌላ አነጋገር፣ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ቢገኝም፣ እዚያው በዚያው ደግሞ የራሱ የሆነ ውስጣዊ ኃይል((Dynamism) ነበረው ማለት ይችላል። የምሁራንም ተግባር ይህንን ዐይነት ሁኔታ በማጥናት ሊሻሻል የሚችልበትን መንገድ ማሳየት ነበር፤ ነውም። ከዚህ ሁኔታ ስንነሳ በአገራችን ምድር የተፈጠሩትንና ህዝባችንን የሚያስተሳስሩት ባህላዊ ነገሮች በሙሉ በተራው ህዝብ፣ በገበሬው፣ በእናቶች፣ በሸማኔውና በአንጥረኛው ብቻ የተፈጠሩና ለጥቅም የዋሉ ናቸው ብሎ መናገር ይቻላል። የኋላ ኋላ ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ዘመናዊነት የሚባለው ነገር ሲገባ ይህንን የተወሰነ የዕድገት መሰረት እንዲስፋፋ ሊያደርገው ቢችልም በሌላው ወገን ግን ከውጭ የገባው ዘመናዊነት የሚባለው ፈሊጥ ከፍተኛ ዕምርታን አልሰጠውም። አዳዲስ ሳይንቲስቶችና ፈለስፋዎች፣ እንዲሁም የቴክኖሎጂ ሰዎች ለመፈጠር ባለመቻላቸው ዘመናዊነት ጥበባዊ እንዲሆንና ለሰፊው ህዝብ እንዲዳረስም የማድረግ ኃይል ስላልነበረው በአጠቃላይ ሲታይ የተኮላሸ ዘመናዊነትና ኋላ-ቀርነት እዚያው በዚያው አብረው የሚሄዱ ነበሩ።
ይህም ማለት የዘመናዊነቱ ውስጣዊ ኃይል በጣም ደካማ ስለነበረ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች እንዲፈጠሩ በማድረግ የኢትዮጵያን ህዝብ ኑሮ መሰረታዊ በሆነ መንገድ ሊለውጠው አልቻለም፤ የኢትዮጵያንም ህዝብ መንፈሳዊ ጥንካሬ ሊሰጠው አልቻለም። ይህ ዐይነቱ ክስተት በእኛ አገር ብቻ ሳይሆን በአብዛኛዎቹ የአፍሪካ፣ የማዕከለኛውና የደቡብ አሜሪካ አገሮች የሚታይና የሚሊታሪውን፣ የፀጥታውንና የቢሮክራሲውንም መዋቅር በማጠንከርና በህብረተሰቡ ውስጥ የሚመረተውን ምርት በመምጠጥ እዚያው በዚያው ለሁለ-ገብ ዕድገት ተቀናቃኝ እንደሆነ ለመገንዘብ እንችላለን። በሌላ አነጋገር፣ ከውጭ የመጣው የተቆነፀለ የካፒታሊዝም አስተሳሰብ በተለይም በስልጣን አካባቢ የነበረውን ኃይል የለውጥ አንቀሳቃሽ ኃይል ሊያደርገው አልቻለም። በዚያው መጠንም በፈጠራ ስራ ላይ ሊሰማራ የሚችልና ለካፒታሊዝም ዕድገት አንቀሳቃሽ ኃይል የሚሆንና የፈጠራ መንፈስ(Pioneer Spirit) ያለው ከበርቴያዊ መደብ ሊፈጠር ባለመቻሉ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ አላላውስም ብለው በያዙት በብዙ ቅራኔዎች የተወጠረና የኖርንም ትርጉም እንዳይረዳ የተደረገ ነው። በተለይም ከሃምሳኛው ዓመተ ምህረት ጀምሮ ካፒታሊዝም በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲስፋፋ ይበልጥ ይገለጽ የነበረው በፍጆታ አጠቃቀምና ብልጭልጭ መስለው በሚታዩ ነገሮች ላይ ብቻ ያተኮረ ስለነብር ልዩ ልዩ ምርቶችን በበቂውና በጥራት እያመረተ ሊያቀርብ የሚችል ምርታማ የማምረቻ መስክ ሊዳብር አልቻለም፤ ሰፊው ህዝባችንም ለህይወቱ የሚያስፈልጉ በቂ ግልጋሎቶችን ለማግኘት አልቻለም። ምክንያቱም ልዩ ልዩ ነገሮችን የማምረት ኃይላችን በጣም ዝቅተኛ ስለነበር አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመፍጠር ለሰፊው ህዝብ የሚሆኑ በቂና ጠቃሚ ግልጋሎቶችን(Services) ማቅረብ አልተቻለም። ይህም የሚያረጋግጠው በአገራችንም ሆነ በተቀሩት የሶስተኛው ዓለም አገሮች የካፒታሊዝም መስፋፋት ዕውነተኛ ነፃነትን(Emancipation) አምጭና ሰፋ ያለ በተቋማት ግንባታ የሚገለጽ ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን ለማስፋፋት የሚያመች ኃይል አልነበረውም፤ ለሳይንስና ለቴክኖሎጂም ዕድገትና መስፋፋት የሚያመች አልነበረም። ይባስ ብሎ አዲስ ዐይነት ህብረተሰብአዊ ቅራኔ በመፍጠር፣ በተለይም በሃይማኖትና በጎሳ የሚገለጹና ይህንን ተገን አድርገው የሚታገሉ ኃይሎች ብቅ እንዲሉ አመቺ ሁኔታን በመፍጠር፣ በተለይም ኤሊት ነኝ ባዩና የፖለቲካ ነገርም ያገባኛል የሚለው ኃይል በሳይንስና በቴክኖሎጂ፣ በአጭሩ ሁለ-ገብ ዕድገትን ሊያመጣ በሚችል ዕውቀት ላይ ከመረባረብ ይልቅ የጎሳን ጥያቄ የትግሉ አጀንዳ በማድረግ አገራችንና ህዝባችንን ፍዳ ውስጥ ከተታቸው። ወያኔም ስልጣን ላይ ከወጣ በኋላ የጎሳ ፌዴራሊዝም የሚለውን የከፋፍለህ ግዛው ፖሊሲ ተግባራዊ በማድረግ የስልጣኔው መንገድ እንዲጨልም አደረገ። ኤሊቱና የዚኸኛው ወይም የዚያኛው ጎሳ አካል የሆነው ኃይል ከመሰረታዊ ፍላጎቶች(Basic Needs) መሟላት ይልቅ የጎሳን ጥያቄ በማስቀደሙና ማንነቴም ታወቀልኝ ብሎ በመደሰቱ ሰፋ ላለና ለሁለ-ገብ ዕድገት የሚያመቸውን ሳይንሳዊውን መንገድ እንዲዘነገጋ ተደረገ። ወያኔና ግብረአበሮቹም በዚህ ድርጊታቸው ያሳኩት የኢምፔሪያሊስት ኃይሎችን ወይም የምዕራብ ካፒታሊስት አገሮችን ህልም ነው። ምክንያቱም ኢምፔሪያሊዝም ወይም ዓለም አቀፋዊ ካፒታሊዝም በሳይንስና በቴክኖሎጂ የሚገለጽ ሁለ-ገብና የተሟላ ዕድገት እንደኛ ባለው አገር ውስጥ እንዳይመጣ ስለሚፈልግና አጥብቆም ስለሚሰራ ነው። በአጠቃላይ ሲታይ የጎሳ አቀንቃኝ ኃይሎች ብቻ ሳይሆኑ ራሱ ብሄራዊ ባህርይ አለኝ የሚለው ኢትዮጵያዊ ኃይልም ከአሜሪካንና ከግብረአበሮቹ ቁጥጥር ውጭ የሆነ ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜ ድህነትንና ኋላ-ቀርነትን ሊቀርፍና ሊያወድም የሚችል በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተደገፈ አጠቃላይ ዕድገት እንዳይመጣ የሚታገል ነው፤ መንፈሱም ለሁለ-ገብ ዕድገት የታነፀ ስላለሆነ በትናንሽ ነገሮች ላይ ብቻ በመደሰት የራሱን ኑሮ ለመግፋት የሚፈልግ ነው።
ባጭሩ ከአብዮቱ ጊዜ ጀምሮ በአገራችን ምድር በደመ-ነፍስ ወይም ካለብዙ ጥናትና ምርምር. ወይም ከትክክለኛ ዕውቀት ማነስ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና፣ በተጨማሪም የጎሳ ፌዴራሊዝምን የማዕከላዊ መንግስቱ ዋና ተግባር አድርጎ መቁጠርና፣ ይህንና የኢኮኖሚ ፖሊሲን አስመልክቶ ወደ ውስጥ ያተኮረና ድህነት ቀራፊና ለመጨረሻም ጊዜ አውዳሚ የሆነና ህዝባዊ ሀብት ሊፈጥር የሚችል ሁለ-ገብ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ከመከተል ይልቅ በዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅትና(IMF) በዓለም ባንክ በመመከርና በመደገፍ ተግባራዊ የሆነው የኒዎ-ሊበራሊዝም የኢኮኖሚ ፖሊሲ የአገራችንን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ፣ የባህልና የስነ-ልቦና ሁኔታ ውስብስብ ነው ያደረገው። ችግርን ከመፍታት ይልቅ የነበሩት ችግሮች ተግባራዊ ከሆኑት ጋር በመጣመርና ውስብስብ በመሆን ወደፊት ግልጽነትና በስራ-ክፍፍልና ሀብትን ፈጣሪ የሆነ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ እንዳይሆኑ ነው እንቅፋት ለመሆን የበቁት። በዚህ ላይ ባለፉት ሰላሳና አርባ ዓመታት አዋቂ ነን በማለት የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሜዳውን የሚቆጣጠሩት በአገር ቤት ውስጥና በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን ኃይሎች አመለካከታቸውን አንድ ወጥ በማድረግ ለሌላና አማራጭ ለሆነ የፖለቲካና የኢኮኖሚ፣ እንዲሁም የማህበራዊ ጥያቄ ምሁራዊ ክርክር እንዳይደረግ በሩን ለመዝጋት ችለዋል። እነዚህ ኃይሎች አገር ቤት ውስጥ በተፈጠረው ውስብስብ ሁኔታ ራሳቸው ተጠቃሚ በመሆናቸው የህዝብና የአገር ጉዳይ የሚያሳስባቸው አይደለም። ስለሆነም አዳዲስና የተሻለ አስተሳሰብ እንዲነሳ አይፈልጉም። ጭንቅላታቸው ውስጥ ከቋጠሩት ቀኖናዊ አስተሳሰብ ውጭ የሚነሳ ነገር በሙሉ ሰይጣናዊ ወይም ኮሙኒስታዊ አስተሳሰብ ነው የሚመስላቸው። ይህም የሚያረጋግጠው እነዚህ ኃይሎች በሙሉ ባለፉት ሁለትና ሶስት ሺህ ዓመታት፣ በተለይም ደግሞ ከሬናሳንስ ጀምሮ በአውሮፓ ምድር ውስጥ የተፈጠረውንና የልዩ ልዩ ዕውቀቶች መስረት የሆነውን የኢንላተንሜንት ምሁራዊ እንቅስቃሴ አጀማመርና መዳበር ያልተከታተሉ መሆናቸውን ነው። እነዚህ ኃይሎች የመሰላቸውና የሚመስላቸው የአውሮፓው ካፒታሊዝም ሊያድግ የቻለው በገበያ ኢኮኖሚ ወይም በአቅራቢና በጠያቂ፣ እንዲሁም በሊበራል ዲሞክራሲ አማካይነት ብቻ ነው። በሌላ ወገን ግን የገበያ ኢኮኖሚና የሊበራል ዲሞክራሲ እንዴትስ ለተሟላና በብዙ መልክ ለሚገለጽ ማህብረሰብ የዕድገት መሰረቶች ሊሆኑ እንደቻሉ ሲነግሩንና ሲያስተምሩን አይታይም።
ወደዋናው ንዑስ አርዕስት ጋ እንምጣና አንድ አገርና ማህበረሰብ ተዘጋጅተው በተፈጠሩ ወይም ከሰማይ ዱብ ባሉ ነገሮች አማካይነት ዕድገትን አልተጎናፀፈም፤ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤትም ሊሆን አልቻለም። አንድ ህዝብ ከጨለማ ወጥቶ ብርሃንን ለማየትና ስለማዊ ኑሮ ለመኖር ብዙ ውጣ ውረድና እልክ የሚያስጨርሱ መንገዶችን ማለፍ አለበት። በአንድ አገር ውስጥ የሚኖር ህዝብ በሙሉ የሚኖርበትን ሁኔታ የመረዳት ኃይል ስለሌውና ለምንስ በዚያ ዐይነት ሁኔታ ውስጥ ለመኖር እንደሚገደድ ጥያቄ ስለማያነሳ በጣም የተገለፀለቻው ኃይሎች ከሰማይ ልክ እግዚአብሄር የላካቸው ይመስል ዱብ በማለት ነው ያለውን ሁኔታ በመጋፈጥና ምርምር በማድረግ የዕድገቱን ፈለግ ለማሳየት የሚችሉት። ይሁንና እነዚህ የተገለፀላቸው ኃይሎች ቀድሞውኑ ከተዘጋጀና ሀብትንና ስልጣንን ከሚቆጣጠረው ጋር ስለሚጋጩ እንደሰይጣን በመታየት ክትትል ይደረግባቸዋል፤ በአንዳች ነገርም ደብዛቸው እንዲጠፋ ይደረጋል። ስለሆነም የተቀጣጠለው እሳት በመዳፈን ሰፊው ህዝብ እንደገና በጨለማ ዓለም ውስጥ እንዲኖር ይገደዳል።
ወደ አገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ስንመጣ በፍልስፍና፣ በሳይንስና በጥበብ የሚገለጽ ስፋ ያለ ምሁራዊ እንቅስቃሴ ተከስቶ አልነበረም፤ የለምም። ስለሆነም በተለያየ ጊዜያት ስልጣንን የጨበጡ ኃይሎች ከበስተጀርባቸው ሆኖ የሚገፋቸው ወይም ደግሞ ከፊት ሆኖ የሚጋፈጣቸው ምሁራዊ ኃይል ስላልነበረና አሁንም ስለሌለ አገራችንና ህዝባችንን በተደራጀና ስልት ባለው መንገድ ሳይሆን ያስተዳድሩት የነበረውና ያለው ዝም ብለው በአቦሰጡኝ ነው ማለት ይቻላል። ይህ ዐይነቱ የጭፍን አገዛዝ ደግም የግዴታ በችግር ላይ ችግር በመፍጠር የገዢ መደቦችም ሆነ ሰፊው ህዝብ ለምን በዚህ ዐይነት ቅራኔ በተሞላበት ሁኔታ ውስጥ እንደሚኖሩ ጥያቄ ስለማይጠቁና መልስም ለማግኘት ስለማይጥሩ የኑሮው ፍልስፍና እየተደነባበሩ መኖር ይሆናል። ባጭሩ የአንድን ህብረተሰብ ውስጣዊ ቅራኔ፣ የውጣ ውረድ ጉዞና በስልጣን ላይ የነበሩትንና ያሉትን ኃይሎች የንቃተ-ህሊና ደረጃና ዕውቀት መረዳቱ ከተደናበረና ስልተ-አልባ ከሆነ ትግል ሊያድነን ይችላል የሚሎ ዕምነት አለኝ።
ችግርን ለይቶ የማወቅና ፍቱን መፍትሄ የመፈለግና የማቅረብ አስፈላጊነት ጉዳይ!
“ All errors in politics and ethics have sprung from false ideas which are closely connected with errors in physics and ignorance of the laws of nature.”(Seneca)
ከላይ ከዘረዘርኩት ሀተታ ስነሳ አንድን በብዙ ችግሮች የተበተበን ማህብረሰብ ነፃ ለማውጣት፣ አቅጣጫ ለማሲያዝና ምርታማ የሆነና ለተሟላ ግንባታ የሚያገለግል ስራ እንዲሰራ ሰፊውን ህዝብ ለማንቀሳቀስ እንዲቻል ማነቆ የሆነ ችግሮችን(Problem Identification) ለይቶ ማስቀመጥ ያስፈልጋል። በእርግጥ ይህ ዐይነቱ ጥያቄ ሲነሳ ሁሉም ሰው መልስ የሚመጣለት የፖለቲካው ችግር ከተፈታ ሁሉም ነገር የሚፈታ ነው የሚመስለው። በተለይም አንድ ግለሰብ ቢነሳና በሌላ ቢተካ፣ ወይም አንድ ስልጣንን የያዘ ኃይል ቢነሳና በሌላ ቢተካ ሌሎች ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉ የሚመስለን ጥቂቶች አይደለንም። ጠለቅ ብሎ ላሰበሰው ግን ችግሩ ውስብስብ ነው።
በታሪክ ውስጥ ለውጥ መጣባቸው፣ ከሞላም ጎደልም በጠነከረ መሰረት ላይ ማህበረስባቸውን ለመገንባት ችለዋል የሚባሉ አገሮችን ሁኔታ ስንመለከት እነዚህ አገሮች የተወሰነና ለየት ያለ ባህላዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴ ነበራቸው። ለስራም የሚገፋፋ፣ በተለይም በተደራጀ መልክ ሰፊውን ህዝብ ሊያንቀሳቅስ የሚችል ባህላዊ ልምድና ተቋም ነበራቸው። ስለሆነም እነዚህ አገሮች ያንን መሰረት በማድረግና “ከሌሎች የምናንስበት ምክንያት የለም፤ በተለይም ሰፋ ያለና ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት የማንችል ከሆነ ብሄራዊ ነፃነታችን ይደፈራል፣ ብሄራዊ ነፃነቱ የሚደፈር አገር ደግሞ የባህል ውድመት ይደርስበታል በማለት “ ተፍ ተፍ በማለትና ህዝቦቻቸውን በማሰባሰብ ነው ጠንካራ አገር መገንባት የቻሉት። ወደኛ አገር ስንመጣ ግን በመጀመሪይ ደረጃ ሁሉም በየፊናው ስልጣን ላይ ለመውጣት ከማሰብና ራሱን አጉልቶ ለማሳየት ከመፈለግ በስተቀር ብሄራዊና ህዝባዊ አጀንዳ ያለው አንዳችም የተገለፀለት እንቅስቃሴ የለም። በአገራችን ምድር በየጊዜው የተከሰቱትንና የሚከሰቱትን ችግሮች የሚላከኩት በአንድ ግለሰብ ላይ ብቻ፣ ወይም በድፍኑ ፖለቲካ በሚባለው ነገር ላይ ነው። በሌላ ወገን ግን የመንግስት መኪና ጉዳይ፣ የመንግስት መኪና ኋላ-ቀር አስተሳሰብ ባላቸውና ለዕድገት እንቅፋት በሆኑ ሰዎች የመያዙ ጉዳይ፣ በጠቅላላው የፖለቲካው አወቃቀር፣ የመንግስቱ መኪናና የመንግስቱን መኪና የሚቆጣጠሩትና ህዝባዊ ባህርይ እንዳይኖረው የሚያደርጉት ቴክኖክራቶችና ቢሮክራቶች፣ በተለይም ደግሞ የኢኮኖሚ ፖሊሲ አውጭዎች፣ እነዚህ ሁሉ የህዛባቸውን ችግር ለመፍታት፣ ድህነትን ለመቅረፍ፣ አገራችንና ህዝባችን የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት በመሆን ሰፋ ያለ ህዝባዊ ሀብት እንዲፈጠር ተፍ ተፍ እያሉ በንቃትና በአገር ወዳድነት የሚሰሩ ሳይሆኑ ተልዕኮአቸው የውጭን ኃይል አጀንዳ፣ በተለይም የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምን ጥቅም ማስጠበቅና ህዝባችንም ለዝንተ-ዓለም አቅመ-ቢስ ሆኖና ለማኝ ሆኖ እንዲቀር ማድረግ ነው። ይህንን ጉዳይ በሚመለከት ጠለቅ ያለ ጥናት ለማጥናት የሚፈልግ የለም። የመንግስቱ መኪናና የመንግስቱን መኪና የሚቆጣጠሩት ምኒስተሮች፣ ቴክኖክራቶችና ቢሮክራቶች፣ እንዲሁም የሚሊተሪውና የፀጥታው ኃይሎች ንቃተ-ህሊናቸው በጣም ደካማ ከመሆኑ የተነሳ ለምን ስልጣን ላይ እንደተቀመጡ የማይረዱ ናቸው፤ ንቃተ-ህሊና ስሌላቸውና ኢ-ሳይንሳዊና ኢ-ፍልስፍናዊ በሆነ ዕውቀትም የሰለጠኑ በመሆናቸው ህዝባቸውን ይንቃሉ፤ ስልጣን ላይም የተቀመጡት የውጭ ኃይሎችን ትዕዛዝ በመቀበል የእነሱን ጥቅም ለማስጠበቅ እንደተቀመጡ ነው የሚገነዘቡት። በአጠቃላይ ሲታይ ከላይ የተዘረዘሩት ኃይሎች በሙሉ ሳይንሳዊና የፍልስፍና ዕውቀት ስለሌላቸው ንቃተ-ህሊናቸው ከዜሮ በታች ነው ማለት ይቻላል። ንቃተ-ህሊናው በጣም ደካማ የሆነ አገዛዝና ጠቅላላው ቢሮክራት በመሰረቱ ባህርያቸው አረመኔ ነው። ለወገናቸው የማያስቡና የማይፀፀቱና የአንድንም ህዝብ በነፃነት መኖርና ዲሞክራሲያው ስርዓር የመገንባት ውስጣዊ ፍላጎት አይረዱም። ይህ ዐይነቱ አስተሳሰብ በአብዛኛዎቹ የሶስተኛው ዓለም አገሮች በገዢ መደቦች ዘንድ ያለ አስተሳሰብ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅትም እንደ አሜሪካ፣ ፈረንሳይና እንግሊዝ የመሳሰሉት አገዛዞች የኋሊት-ጉዞ እንዲጓዙ አድርጓቸዋል። በአሁኑ ወቅት በዶናልድ ትረምፕ የሚገዛው የአሜሪካን መንግስት ወደ ልዩ ዐይነት ፋሺዝም እየተጓዘ እንደሆነ ለመረዳት እንችላለን። የአሜሪካን ጠቅላላው የመንግስት መኪና አወቃቀርም ለልዩ ዐይነት የፋሺሽዝም ርዕዮተ-ዓለም መዳበርና መስፋፋት የሚያመች ነው።
ሰለሆነም ወደ አገራችን ስንመጣ ያለው ችግር በአንድ ግለሰብ ብቻ የሚሳበብ ሳይሆን አገዛዙን ወይም አንድን ግለሰብ አቅፈው ደግፈው የያዙትና፣ ካለምንም ጥያቄ አንድን ሰው የሚያመልኩትንና የእሱንም አገር አውዳሚ አጀንዳ የሚያስፈጽሙትን ሁሉ የግዴታ በትንተና ውስጥ ማካተትና ለአገራችን ውድቀት ተጠያቂ መሆናቸውን ማወቅ ያስፈልጋል። በተለይም በአለፉት 34 ዓመታት፣ ሀወሃት ስልጣን ላይ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮና እስካሁን ድረስ ያለውንና፣ በኋላ ላይ ተገዶ ስልጣኑን ለአቢይ አህመድና ለግብረአበሮቹ እስካስረከበበት ጊዜ ድረስ ያለውንና፣ የዛሬውንም አፍጦ አግጦ ያለውን ሁኔታ ስንመረምር ሁለቱም አገዛዞች በአነሳሳቸውና በድርጊታቸው የውጭን ኃይል አጀንዳ የሚያስፈጽሙና ልታይ ልታይም የሚሉ ናቸው። ከስራቸው የሚገኙትም ኃይሎች ታዛዥ በመሆን በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የእነሱንና የበላይ አዛዦቻቸውን ህዝብን የማደኽየትና የአገርን አውዳሚነት ሚና የሚያስፈጽሙ ናቸው። በሌላ አነጋገር፣ ለፖለቲካ ትግል የሚደረገው ትግል አንድን አገዛዝና ቁንጮውን ብቻ በማስወገድ የተሟላ ነፃነትን እንደማያስገኝ ከሌሎች አገሮችም ሆነ በአገራችንም ምድር የተረጋገጠ ነው። ይህም ማለት ከዚህ ዘልቀን በመሄድ ሰፋ ያለና ምሁራዊ ኃይል የሚፈጠርበትን ሁኔታ ማዘጋጀት በጣም አስፈላጊ ነው።
አስቸጋሪው ነገር ግን በዚህ መልክ ከሚታየው የፖለቲካ ችግር ባሻገር ያለውና ሌላው ውስብስብና የረቀቀው አስቸጋሪው ሁኔታ እዚህና እዚያ በፖለቲካ ስም እንቀሳቀሳለን የሚሉና፣ የተለያዩ የዩትቭ ቻናሎችን በመክፈት በጋዜጠኝነት ስም የሚያወናብዱትን ስንመለከት እነዚህም በራሳቸው የችግሩ አንድ አካል ናቸው ብል እንደስህተት አይቆጠርብኝም። እነዚህ ኃይሎች ሁልጊዜ ተመሳሳይ ሰዎችን በተደጋጋሚ በመጋበዝና የራሳቸውን ኢ-ሳይንሳዊ ትንታኔ ከመስጠት ባሻገር ቀድሞም ሆነ በዛሬው ወቅት በአገራችን ምድር የተፈጠረው ውስብስብ ሁኔታ ማነው እንዲፈጠር ያደረገው? ምክንያቱስ ምንድነው? እንዴትስ ይፈታል? ጠንካራና አስተማማኝ የሆነ ህብረተሰብስ እንዴት መገንባት ይቻላል? ለዚህ ደግሞ ዋናው መሰረት ምንድነው? እያሉ ጥያቄዎችን በማንሳትና የተገለፀላቸውን ሰዎች በመጋበዝ ሰፋ ያለ ግንዛቤ እንዳይደረግ የሚሰሩ ናቸው። በእርግጠኝነት ማለት የሚቻለው እነዚህ ጋዜጠኛ ነን የሚሉና የሚጋብዟቸውም ሰዎች ያልተገለፀላቸው፣ አብዛኛዎችም ከፊዩዳላዊ ወይም ኋላ-ቀር አስተሳሰብ ያልተላቀቁና በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የበላይነት የሚያምኑ ናቸው። ይህም ማለት ስልጣንን የጨበጠው ኃይል፣ ከስር አቅፎ ደግፎ የያዘው በጥቅም የተሳሰረ ኃይልና እነዚህ ከውጭ ሆነው አለሁ አለሁ የሚሉ ኃይሎች በሙሉ አገራችንና ህዝባችን በተሟላ መልክ ከድህነት በመላቀቅ ነፃነትን እንዳያገኝ የሚሰሩ ናቸው ብል እንደተራ ውንጀላ አይቆጠርብኝም።
ከዚህ ወጣ ብለን ስንሄድ እንደማነቆ ወይም እንደ ነቀርሳ የያዘን ትልቁ በሽታ ብሄረሰብአችንን ነፃ ማውጣት አለብን ብለው የሚንቀሳቀሱት በተለይም የኦሮሞ ኤሊቶችና የትግራይ ኤሊቶች ጉዳይ ነው። ከሁለቱም ብሄረሰብ የተውጣጣን ነን የሚሉት ኤሊቶች ደግሞ አስተሳሰባቸውና ድርጊታቸው በሙሉ የህብረተሰብንና የተፈጥሮን ህግ የሚፃረር ነው። ብሄረሰብ የሚባለው ነገርም በህብረተሰብ ሂደት ውስጥ፣ ራሱን በራሱ ማግኘት ያልቻለና፣ በስራ-ክፍፍል፣ በንግድ፣ በከተማዎችና በመንደሮች ግንባታ የማይገለጽ በጣም ዝቅተኛ የህብረተሰብ አካል መሆኑን በፍጹም አይረዱም። በሌላ ወገን ደግሞ ከተለያዩ አገሮችና ከአገራችንም ሁኔታ ስንነሳ ብሄረሰብ የሚለው አነጋገር ባይሎጂካል ሳይሆን ያልተሟላ ማህበረሰብ(Nation-State) ነፀብራቅ የሆነና(Social Construction)፣ በተለይም ባልተስተካከለ ዕድገት (Unequal Development) ወይም ኢ-ሳይንሳዊ በሆነ የኢኮኖሚ ፖሊሲና በተሳሳተ የፖለቲካ ግንዛቤ ወይም አስተዳደር የሚከስትና ልዩ ዕምርታን የሚያገኝ ነው። ይህም ማለት በአንድ አገር ውስጥ ጠቅላላውን ህዝብ ከድህነትና ከኋላ-ቀርነት ሊያላቅቀው የማይችል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ በሚሆንበት ጊዜና የሰለጠኑ ተቋማትም በሰፊው ባልተዘረጉበት አገር ውስጥ የዚኸኛውን ወይም የዚያኛውን ብሄረሰብ ጥቅም እናስጠብቃለን የሚሉ የየብሄረሰቡ ኤሊቶች፣ በመሰረቱ በውጭ ኃይሎች በመታገዝና የእነሱን የከፋፍለህ ግዛው አጀንዳ ተግባራዊ ለማድረግ የሚንቀሳቀሱ መከሰታቸው የማይቀር የህብረተሰብ ህግ የሚመስል ጉዳይ ነው። መመሪያቸውም ሳይንስ፣ ፍልስፍናና ሰፋ ያለ ቲዎሪ ሳይሆን፣ ትግላቸውም “ተጨቁነናል፣ መብታችን ተገፏል፣ ስለዚህም ያለን አማራጭ መገንጠል ነው” የሚለውን አጀንዳ በማንገብና በማረማድ ነው። ይህንን ዐይነቱን ኢ-ሳይንሳዊ አስተሳሰብ ሲያራምዱና ቅስቀሳ ሲያደርጉ ስልጣን ላይ የነበረው ኃይል ለአንድ ብሄረሰብ ያደላ ነበር፤ በተለያዩ ነገሮች የሚገለፀው ዕድገት የሚባለው ነገር በአንድ አካባቢና አንድን ብሄረሰብ ብቻ ለመጥቀም ነበር የተዘረጋው ብለው ለማረጋገጥ በፍጹም አይችሉም። በሌላው ወገን ደግሞ ተጨቁነዋል ከሚባለው ብሄረሰብ ውስጥ የተውጣጡ ኤሊቶች የአገዛዙ አካል የነበሩና በራሳቸውም ለተሟላ ዕድገት እንቅፋት እንደነበሩ ሊገነዘቡ አይችልም። በህብረተሰብ ግንባታ ውስጥ፣ በተለይም ኢትዮጵያ እንደ ህብረ-ብሄር(Nation-State) የመገንባት ዕድል ካጋጠማት ከ19ኛው ክፍለ-ዘመን መጨረሻ ጀምሮና በአፄ ኃይለስላሴ የአገዛዝ ዘመን ያለውን ሁኔታ ስንመለከት ከአንድ ብሄረሰብ ብቻ የተውጣጣ ኤሊት ኢትዮጵያን ያስተዳደረበት ወቅት አልነበረም። አፄ ኃይለስላሴና የአገዛዛቸው መዋቅርና አሪስቶክራሲው በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የጥቂት ሰዎችን ጥቅም የሚያስጠብቁ ነበሩ። ስለዚህም ነው ከ1950ዎቹ መጀመሪያ ተግባራዊ የሆነውን ኢ-ሳይንሳዊ የኢኮኖሚ ፖሊሲ በምንመረምርበት ጊዜ ያልተስተካከለ ዕድገትን ያመጣና፣ በተለይም የአማራውን ክልልና የትግራይንም ጭምር በከፍተኛ ደረጃ የበደለ ነበር። በየክፍለ-አገራቱም የተመደቡት የንጉሱ እንደራሴዎች አካባቢዎቻቸውን የማልማት ዕውቀት የሌላቸው ስለነበሩ የተሟላና ድህነትን የሚቀርፍ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ሊከተሉ የሚችሉ አልነበሩም። ስለሆነም ይህንን ጉዳይ ለመረዳት የማይፈልጉ የትግራይና የኦሮሞ ኤሊቶች ችግሩን በጥቁርና በነጭ ብቻ በመጻፍ ሳይንሳዊ ክርክርና ጥናት እንዳይካሄድ ለማድረግ በቅተዋል፤ አሁንም እያደረጉ ነው።
ከዚህ ውስጥ በጣም አሳሳቢና አደገኛ የሆነው ነገር የትግራይ ኤሊት አስተሳሰብና በጭፍን የሚመራው የትግራይ ህዝብ ጉዳይ ነው። ህወሃት የሚባለው ከትግራይ ብሄረሰብ የተወለደ ጭንቅላቱ የደነዘዘ፣ ሎጂክና ሳይንስ የማይገባው ኃይል ራሱንና እወክለዋለሁ የሚለውን ብሄረሰብ እንደልዩ ፍጡር በማየት ላለፉት ሃምሳ ዓመታት በቀላሉ መፍትሄ የማይገኝለት የተወሳሰበ ችግር በአገራችን ምድር እንዲፈጠር አድርጓል። ቀማኝነትና መዝረፍን እንዲሁም ተንኮል መሸረብን አስተምሯል። በጎሳ ፌዴራሊዚም አማካይነት አንደኛው ጎሳ በሌላው ላይ ጥርጣሬ እንዲያድርበት ለማድረግ በቅቷል። በአጭሩ ሰፊው ህዝባችን በጋራ ተነሳስቶ አገሩን እንዳገነባና ከተወሳሰቡ ችግሮችም እንዳላቃቅ አድርጓል። እወክለዋለሁ የሚለውንም ህዝብ የማይወጣው ማጥ ውስጥ በመክተት ጭንቅላቱን ጋርዶታል። እየተራበ፣ እየተጠማ፣ በድህነት ዓለም ውስት እየኖረና፣ ልጆቹም ህወሃትን ብቻ ስልጣን ላይ ለማቆየት ሲባል በጦርነት እየተማገዱና የጥይት እራት ሲሆኑ፣ አካላቸውንም ሲያጡ ጥያቄ የመጠየቅና የማየትም ኃይል ተስኖታል። የሚታዩና የሚሰሩትን ነገሮች ለማገናዘብ የማይችል የበደነ ኃይል ለመሆን በቅቷል። ተገዶም ሆነ ሳይገደድ ሰፊው የትግራይ ህዝብና ውጭም ያለው አቀንቃኝ ኃይል እጅግ ኋላ-ቀር በሆነው ህወሃት የሚያምኑ ናቸው። አንዳንድ ምሁራን ነን የሚሉና የፕሮፌሰርነት ማዕረግም የተከናነቡና ከአርባ ዓመት በላይ አሜሪካ አገር ውስጥ እየኖሩ ህወሃትን ነው የሚያመልኩት። እስካሁን ድረስ የመሰለኝ በሳይንስና በቴክኖሎጂ የሚገለጽ የካፒታሊስት ህብረተሰብ ውስጥ አርባ ዓመት ያህል የኖረ ሰው የሚገለፀለትና ተራማጅ አስተሳሰብ የሚያራምድ ነበር የሚመስለኝ። የእነዚህ የህወሃት አምላኪዎች ምሁራን አመለካከት አስተሳሰቤንና ግምቴን ፉርሽ አደረገብኝ። ሳይንስና ቴክኖሎጂ በራሳቸው አንድን ጭንቅላቱ የደነደነን ሰው መንፈሱን በማደስ ጤናማ አስተሳሰብ እንዲኖረው ለማድረግ እንደማይችሉ አዲስ ትምህርት የመቅሰም ዕድል አገኘሁ።
ህወሃት ስንትናት ስንት ችግር እንደፈጠረበት፣ ለጦርነት እንደዳረገውና፣ በብዙ ሺሆች የሚቆጠሩ ወጣቶችን አካለ-ስንኩላን እንዲሆኑ ያደረገን ኃይል አሁንም እንደመሪና የትግራይን ብሄረሰብ ጥቅም አስጠባቂ እንደሆነ ማመንና በእሱም መመራት የትግራይን ህዝብም ሆነ ምሁር ነኝ የሚለው ኃይል የቱን ያህል ጭንቅላታቸው የተጋረደና ነገሮችን ማገናዘብ እንደማይችሉ ነው ሁኔታው የሚያረጋግጠው። ህወሃት የሚባለው ዘራፊና የወንበዴ ድርጅት፣ የአሜሪካንና የተቀረው ኢምፔሪያሊስት ኃይሎች ተላላኪ የሆነው ኃይል አሁንም ኃይል አለኝ በማለት ህዝባችንን፣ በተለይም አማራውን እያስፈራራ የሚኖር ነው። ህወሃት የሚባለው የዘራፊዎች ቡድን መንፈሰ-አልባ የሆነ እንደመሆኑ መጠን የተሟላ ዕድገት፣ የዲሞክራሲያዊ ስርዓትና የዘላቂ ሰላም ጠንቅ የሆነ ኃይል ነው። ህዝባችንም በሰላም እንዳይኖር የማይሸርበው ሴራ ይህ ነው የማይባል ነው። ስለሆነም ህወሃት የሚባለው ዘራፊ ቡድንና ከትግራይ የተውጣጡ ኤሊቶች በምንም ዐይነት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ዓለም ውስጥ መሳተፍ የለባቸውም። በአገራችን ምድር ዘላቂና አስተማማች ስላም እንዲሰፍን ከተፈለገ፣ ሁለ-ገብ የሆነ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ አገርን በተሟላ መልክ ሊያስገነባ የሚችል ሁለ-ገብ የሆነ የኢኮኖሚ ፖሊሲ እንዲተገበር ከተፈለገ ህወሃት የሚባለው ኃይልና ግብረ-አበሮቹ ከኢትዮጵያ ምድር መጥፋት አለባቸው። ´የለም ይህ አይቻልም የሚባል ከሆነ ትግራይ ራሱን የቻለ ነፃ አገር መመስረት ይችላል። ይህ ከሆነ ደግሞ ከተቀረው የኢትዮጵያ ግዛት ጋር ምንም ዐይነት ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ግኑኝነት እንዳይኖረው ማድረግ ያስፈልጋል። ምክንያቱም ነቀርሳ በሽታ ይዘህ ለዘለዓለም ልትኖር በፍጹም አትችልም። አይ ነቀርሳው አንድ ቀን ያጠፋሃል፣ ከተቻለ ደግሞ ከነቀርሳ በሽታ ለመፈውስና እንደጤናማ ሰው ለመኖር ከፍተኛ የሆነ ስውነትንና መንፈስን የሚፈውስ ከኮኖቬንሽናል ህክምና ባሻገር ፍቱን የሆነ መድሃኒት በመፈለግና የአመጋገብንም ሁኔታ በመለውጥ ራስን ማዳን ያስፈልጋል። ባጭሩ ይህ ነቀርሳ ኃይልና ግብረአበሮቹ ሲወገዱ ብቻ ነው በአገራችን ምድር ስላምና የተሟላ ዕድገት ሊመጡ የሚችሉት።
ከዚህ ቀደም ብሎ መሰራት ያለብት ጉዳይ ግን በዛሬው ወቅት ስልጣንን የተቆናጠጠውን በአብይ አህመድ የሚመራውንና የውጭ ኃይሎች ተላላኪ የሆነውን አገር አውዳሚና ፈሺሽታዊ ኃይል ማስወገድ ወሳኝ ጉዳይ ነው። ይህ ኃይል ሲወገድና ከፍተኛ የሆነ የንቃተ-ህሊና መዳበርና የድርጅት ስራ ሲሰራ ብቻ ብዙ ችግሮችን መፍታት ይቻላል የሚል ዕምነት አለኝ። በተለይም በአገራችን ምድር መወገድ ያለብት መጥፎ አስተሳሰብ ቡድናዊ አስተሳሰብና በጥራዝ ነጠቅ ዕውቀት መመራትንና ህዝብን ማሳሳት ነው። በአገራችን ምድር ያለው የተወሳሰበ ችግር እዚህና እዚያ በሚሯሯጡ ፖለቲከኞች ነን ባዮች፣ ይሁንና ባልተገለፀላቸው ኃይሎችና ቡድኖች የሚፈታ አይደለም። ንቃተ-ህሊናን በማዳበር ከራስ ጥቅም ባሻገር ለህዝብና ለአገር በመቆም ታሪካዊ ስራን መስራት የጊዜው አንገብጋቢ ጥያቄ ነው። ያለውም ችግር የተገለፀለት፣ ሁለ-ገብ በሆነ መልክና ክራሱ ጥቅም ባሻገር ለማሰብ የሚችል፣ ወይም የአገርንና የህዝብን ጥያቄና ዕድል የሚያስቀድም ኃይል እንዴት መፍጠርና ማግኘት ይቻላል? የሚለው ጥያቄ ነው የሚያስቸግረው።
የሰውን ልጅ መሰረታዊ ፍላጎቶች የመረዳትና እንዴትስ መፈታት እንዳለባቸው
የማወቅ ጉዳይ!
በአገራችንም ሆነ በአብዛኛዎቹ የሶስተኛው ዓለም አገሮች፣ በተለይም በአፍሪካ አገሮች ውስጥ ያለው ትልቁ ችግር ለማንና ለምንስ ዐይነት ማህበረሰብ እንደሚታገሉና አንድ ህብረተሰብስ በምን በምን መሰረቶች ላይ ከታች ወደላይ ኦርጋኒካሊ እንደሚገነባ አለማወቃቸው ነው። ከዚህም ባሻገር ስልጣን ላይ በሚወጡበት ጊዜ በመጀመሪያ ደረጃ ተግባራዊ ማድረግ ያለባቸውን ነገሮች በፍጹም አይረዱም። በተለይም ስልጣን ላይ ያሉትና ስልጣንም ላይ ለመውጣት የሚታገሉ ኃይሎች በየአገሮቻቸው ውስጥ ሰዎች እንደሚኖሩና፣ ለመኖርም ሲሉ የግዴታ መሰረታዊ ፍላጎታቸውን ማሟላት እንዳለባቸው በፍጹም አይረዱም። ሰለሆነም የመንግስትን መኪና የተቆናጠጡትና በአጠቃላይ ሲታይ ኤሊት የሚባለው ኃይል ሰፊው ህዝብ በላ አልበላ፣ የሚጠጣው ንፁህ ውሃ አገኘ አላገኘ፣ የሚኖርበት መጠለያ ቤት ይኑረው አይኑረው፣ ተቀጥሮ ይስራ አይስራ፣ ራሱንና ቤተሰቡን ለማሸነፍ ሲል ተከታታይ ገቢ ይኑረው አይኑረው ደንታቸው አይደለም። የአፍሪካ መንግስታት፣ የአገራችንንም ጨምሮ በውጭ ኤክስፐርቶች ነን በሚሉ እየተመከሩ በተለያዩ ጊዜያት ተግባራዊ የሚያደርጓቸው የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች በሙሉ በየአገሩ ያለውን ሰፊ ህዝብ መሰረታዊ ፍላጎቶች ሊያሟሉ የሚችሉ አይደሉም። በነፃ የገበያ ስም የተለያየ ስምን ይዘው ተግባራዊ የሚሆኑት የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች በሙሉ የነፃ ገበያን እንዲመሰረትና እንዲዳብር የሚያደርጉ ሳይሆን ለጥሬ-ሀብት ዘረፋ የሚያመቹና ጥቂቱንም የህብረተሰብ ክፍል የሚያደልቡ ናቸው። ከዚህም ባሻገር ካለብዙ ግንዛቤና ስሌት፣ እንዲሁም ደግሞ ሰፋ ላለ የገበያ ኢኮኖሚ መዳበር አስፈላጊነቱ በደንብ ሳይጠና ከእነ ዓለም የገንዘብ ድርጅትና ከሌሎች የፊናንስ ተቋማት የሚወሰደው ብድር ዕዳውን እንዲቆለል ከማድረግ በስተቀር በየአገሮች ውስጥ ለሰፊው ህዝብ አስተማማኝ የሆነ ሰፋ ያለ የስራ መስክ የሚከፍት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ሲዳብር አይታይም። አብዛኛዎቹ የአፍሪካ መንግስታትና የኢኮኖሚና የፖለቲካ ኤሊቱ ስለሰው ልጅ ያላቸው ግንዛቤ ደካማ ስለሆነና፣ አንድስ ህብረተሰብ በምን በምን መሰረቶች ላይ ቢገነባ ነው ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ባህላዊ ቀውሶች የማይከሰቱት ብለው ስለማይጠይቁ በጭፍን ተግባራዊ የሚያደርጓቸው ፖሊሲዎች በሙሉ አስፈሪ የሆኑ፣ በተለይም ደካማውን የህብረተሰብ ክፍል ሊጎዱ የሚችሉ እንደማጅራት መቺዎች፣ ኪስ አውላቂዎች፣ አፋኝ ቡዱኖችና ሌሎች አደገኛ ኃይሎች እየተፈጠሩ ስርዓተ-አልባኝነት እንዲስፋፉ ለማድረግ ተችሏል።
ግልጽ እንዲሆንልንና ይህ ዐይነቱ ሁኔታ እንዴት ሊፈጠር እንደቻለ ወደ ኋላ ዞር ብለን በህብረተሰብ ግንባታ ውስጥ የተሰሩ ስህተቶችን እንቃኝ። ምክንያቱም በዛሬው ወቅት በአገራችን ምድር አፍጦ አግጦ የሚታየው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ባህላዊና ሌሎችም የህብረተሰብ ቀውሶች በሙሉ ተያይዘው የመጡ ስለሆነ፣ በመጀመሪያ ላይ በተሰራ ፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ ስህተት የተነሳ የተገለፀለትና ብሄራዊ ባህርይ ያለው የፖለቲካ ኃይል ሊፈጠር አልቻለም። ይህንን ለመረዳት ከአፄ ኃይለስላሴ የአገዛዝ ዘመን ጀምሮ የተፈጠረውን ሁኔታ አጠር አጠር ባለመልክ እንቃኘው። በአፄ ኃይለስላሴ ዘመን አርቆ ካለማሰብ በተሰራ የፖለቲካ ስህተት የተነሳ ሰፋ ያለና በሁሉም አቅጣጫ አገሪቱን ሊያስተዳደርና ዘመናዊነትን ሊያስፋፋ የሚችል ምሁራዊ ኃይል ሊፈጠር አልቻለም። አፄ ኃይለስላሴና አሪስቶክራሲው ይከተሉ የነበረው ፊውዳላዊ ለበስ ፖለቲካ፣ በመሰረቱ ኢ-ሳይንሳዊ የሆነና ፍልስፍናዊ-አልባ ፖለቲካ ስለነበር አገዛዛቸው ከራሳቸው የስልጣን ዘመን ባሻገር ስትራቴጂያዊ በሆነ መል ማሰብ የሚችል አልነበረም። ስለሆነም አብዛኛው ነገር፣ በተለይም የኢኮኖሚ ፖሊሲው በአቦሰጡኝ ተግባራዊ የሆነ ስለነበር በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ሰፋ ያለና አገሪቱንና ህዝቡን ሊያስተሳስር የሚችል ኢኮኖሚ መገንባት በፍጹም አልተቻለም። የአፄ ኃይለስላሴ አገዛዝ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ በሆነ መልክ ማሰብ የሚችል ስላልነበር በተሳሳተ ግንዛቤ ካለምንም ውይይትና ክርክር ተግባራዊ የሆነው ዘመናዊ የሚባለው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ወይም በእንግሊዘኛው አጠራር የምትክ ኢንዱስትሪ ተከላ(Import-Substitution Industrialization) በመባል የሚታወቀው ተግባራዊ ከሆነ በኋላ ሰፊውን ህዝብና አገሪቱን እንዳለ ሊያዳርስ የሚችል ስላልነበረ ይህ ዐይነቱ በውጭ አገር አማካሪዎች ተግባራዊ የሆነው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ያልተስተካካለ ዕድገት እንዲፈጠር አደረገ። በዚህም ምክንያት የተነሳ በተለይም በአዲስ አበባና በተቀሩት ከተሞቹና በገጠሪቱ ኢትዮጵያ መሀከል ከፍተኛ የሆነ የአኗኗር ሁኔታና የባህል ልዩነት እንዲታይ አደረገ።
በአብዮቱ ወቅት በተፈጠረው የተመሰቃቀለ ሁኔታና ርስበርስ መጨራረስ የተነሳ በተለይም በአፄ ኃይለስላሴ የአገዛዝ ዘመን ተግባራዊ የሆነውን የኢኮኖሚ ፖሊሲ አስመልክቶ ምሁራዊ ውይይት ማካሄድ በፍጹም አልተቻለም። የአብዛኛው ታጋይ ነኝ ባይም አትኩሮ እንደምንም ስልጣን ላይ ለመውጣት ስለነበር በተለይም የኢኮኖሚና የማህበራዊ ጥያቄዎችን አትኩሮ ሊሰጣቸው አልቻለም። የመኢሶንና የኢህአፓን ልሳን ለተከታተለ የሚገነዘበው ነገር አንዳችም ቦታ ላይ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ጥያቄዎችን በማንሳት በጊዜው አፍጦ አግጦ የነበረው ርሃብና ድህነት፣ እንዲሁም የስራአጥ ጉዳይ እንዴት እንደሚፈቱና ለዚህ ዐይነቱ ቀውስም ዋናው ምክንያት ምን እንደነበር ክርክርና ውይይት አይደረግም ነበር። የፖለቲካ ስልጣንም የጨበጠው ደርግ ፖለቲካዊ ግንዛቤ ያልነበረው በመሆኑና፣ ስለተለያዩ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች የሚያውቀው ነገርም ስላልነበር በራሱ ተነሳሽነት ለነበረው የኢኮኖሚና የማህበራዊ ቀውስ ሳይንሳዊ ትንተናና ፍቱን መፍትሄ ሊሰጥ የሚችል አልነበረም። ማንኛውንም የህብረተሰብ ጥያቄዎችና፣ የብሄረሰብ ጥያቄ የሚባለውንም ጭምር ሊፈታ የሞከረው በጉልበት ወይም በጦርነት ብቻ ስለነበር የግዴታ ይህ ዐይነቱ አስተሳሰብና አካሄድ የነበረውን ቀውስ ውስብስብ ሊያደርገው በቃ። ስለሆነም ይህና በውጭ ኃይሎች በተሸረበው ሴራና የስለላ መዋቅሩም ከውጭ ሆኖ በሚሸረብ ሴራ የተቦረበረ ስለነበር የደርግ አገዛዝ እንዲወድቅ ተገደደ።
ወያኔ ስልጣንን ሲጨብት ካለምንም ምሁራዊ ውይይትና ግንዛቤ፣ ድህነትን ይቀርፍ ወይም አይቀርፍ እንደሆነ፣ ሰፋ ያለ ህዝባዊ ሀብት ይፈጥር ወይም አይፈጥር እንደሆነ ሳያወጣና ሳያወርድ ነው የዓለም የገንዘብን ድርጅትና(IMF) በአጠቃላይ አነጋገር የዓለም አቀፍ ኮሙኒቲ የሚባለውን ሃሳብ በመቀበል የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲን ተግባራዊ ያደረገው። በተለያዩ ጊዜያት ባወጣኋቸው ጽሁፎቼ ውስጥ ለማሳየት እንደሞከርኩት ይህ ዐይነቱ በእነ የዓለም የገንዘብ ድርጅትና፣ በአጠቃላይ ሲታይ በዓለም ኮሙኒቲው የሚደገፍ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ብለው የሚጠሩት በመሰረቱ ጥቂቶችን የሚያበለጽግ፣ ለዘረፋ የሚያመችና በዚያው መጠንም ሰፊውን ህዝብ ወደ ድህነት ዓለም በመገፍተር በአገራችን ውስጥ ያልተስተካከለ ዕድገት(Unequal Develeopment) እንደሚያመጣ ነው፤ በተግባርም የታየው ይህ ነው።
የአቢይ አህመድ አገዛዝም ይህንኑ በመከተል ነው የቀጠለበት። ከሶስት ዓመት በፊት በአገር ውስጥ የሚያድግ ኢኮኖሚ(Home Grown Economy) የገንዘብ ምኒስተር፣ የምኒስተር ድዔታው በዶ/ር ዕዮብ አማካይነት የወጣና ለዓለም አቀፍ ኮሙኒቲው ያስተዋወቀ ቢሆንም ይህ አገር ውስጥ ይበቅላል፣ ያድጋልም የተባለው ኢኮኖሚ የውሃ ሽታ ሆኖ ሊቀር ችሏል። ከዚያም በኋላ የኢትዮጵያ ገንዘብ በተደጋጋሚ ከዶላር ጋር ሲነፃፀር እንዲቀንስ በመደረግ የኢትዮጵያን ህዝብ የችግር ችግር ውስጥ ከትቶታል። በተለይም የኢትዮጵያ ብር የመግዛት ኃይሉ “በአቅራቢና በጠያቂ ህግ” እንዲደነገግ ከተደረገ በኋላ የብሩ የመግዛት ኃይል በከፍተኛ ደረጃ ቀንሷል። የኢትዮጵያ ህዝብም በኑሮ ውድነት እየተማረረ ይገኛል። ይህ ዐይነቱ ኢ-ሳይንሳዊ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ የሚደረገውና ህዝባችንም ፍዳውን የሚያየው በአገራችን ውስጥ ሊበቅሉ፣ ሊዘሩና ሊተክሉ የሚችሉ፣ በሌሎች አገሮችም የማይገኙ የሰብል ዐይነቶች፣ የጥራጥሬ ዐይነቶች፣ ለዘይት ጭማቂ የሚሆኑ እንደ ተልባና ኑግ የመሳሰሉ በሚገኙበት፣ የተለያዩ የፍራፍሬ ዐይነቶች በሚበቅሉበት አገር ውስጥ ነው። ይህም የሚያረጋግጠው አገራችን ነፃ እንዳልሆነችና በዓለም አቀፍ ኮሙኒቲው ዶላር እየተከፈላቸው ህዝባችንን ለዝንተ-ዓለም በድህነት ዓለም ውስጥ እንዲቆዩ ዘመናዊ በሚመስሉ፣ በመሰረቱ የፈረንጅ ተላላኪ በሆኑ ተማርን በሚሉ ኢትዮጵያውያን ኃይሎች አማካይነት እንደምትተዳደር ነው።
እስካሁን ድረስ በአገራችንና በሌሎች የሶስተኛው ዓለም ተብለው በሚጠሩት አገሮች ውስጥ ያለው ትልቁ ችግር በፖለቲካና በሁለ-ገብ የኢኮኖሚ ዕድገት መሀከል ያለውን ዲያሌክቲካዊ ግኑኝነት አለመረዳት ነው። በተለይም መንግስት ሰፋ ባለ የኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ የሚኖረውን ሚና አለመረዳትና ስልጣን ላይም የሚወጡት ኃይሎች የዓለም አቀፍ ኮሙኒቴው ወይም የፈረንጆች አሽከር ስለሆኑ ፖለቲካንና የመንግስትን መኪና የሀብት መፍጠሪያና ድህነትን አስወጋጅ መሳሪያ ከማድረግ ይልቅ ወደ መጨቆኛ መሳሪያነት ይለውጧቸዋል። የመንግስትም መኪና የግል ሀብት ይመስል በጥቂት ሰዎች አማካይነት ወደ የጥሬ-ህበት መዝረፊያነት(Predatory State) ይለወጣል። በመንግስት መኪና ውስጥ የሚሰገሰጉት ኃይሎችና ከበላይም ያለው በምሁራዊ እንቅስቃሴ ከታች ወደ ላይ እየተኮተኮቱ ያላደጉ ስለሆነና፣ በየጊዜውም ስለማያነቡና ስለማይመራመሩ የራሳቸውን ስልጣን ካማጠናከርና የውጭ ኃይሎች አሽከር ከመሆን አልፈው ብሄራዊ ኢኮኖሚ እንዲገነባ የማድረግ አቅም ወይም ችሎታ የላቸውም። ስለሆነም በሚከተሉት ኢ-ሳይንሳዊና ፍልስፍና አልባ የሆነ የኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነት ድህነትና ኋላ-ቀርነት እንዲፈለፈሉና እንዲፈረጥሙ ለማድረግ በቅተዋል፤ እያደረጉም ነው።
ከዚህ አጠር መጠን ያለ ሁኔታ ስንነሳ በተለይም የሰፊውን ህዝብ መሰረታዊ ፍላጎት ለማሟላትና እንደሰውም እንዲኖር፣ እንዲያስብና አጠቃላይ ወደሆነ የአገር ግንባታ ውስጥ እንዲሳተፍ ከተፈለገ የግዴታ የመንግስቱ መኪና ከቆሻሻና ዝቅተኛ አስተሳሰብ ካላቸው ኃይሎች መጽዳት አለበት። መሰረታዊ ለውጥም ሲባል የሚጀምረው ከመንግስቱ መኪና ነው። በተለያዩ ጊዜያት በተለይም በአገራችን ምድር ስልጣንን የጨበጡ ኃይሎች ምሁራዊና ሞራላዊ ብቃት ስለሌላቸው፣ እንዲሁም ደግሞ መንፈሳቸው ዝቅተኛ ከመሆኑ የተነሳ ለኢምፔሪያሊስት ኃይሎች ታዛዥ በመሆን አገር አፍራሽና ብሄራዊ ነፃነትን አስደፋሪ የሆነ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ ስላደረጉና ስለሚያደርጉም፣ ከዚህም በላይ ፖለቲካዊ ግንዛቤ ስለሌላቸው እነዚህ ኃይሎች በመንግስት መኪና ውስጥ መካተትና በፖለቲካ ዓለም ውስጥም መሳተፍ የለባቸውም። ስለሆነም በአገራችን ምድር የሰፊው ህዝብ መሰረታዊ ፍላጎቶች እንዲመለሱ ከተፈለገ፣ እንደሰው እንዲኖር ከታሰበ፣ ትናንሽና ትላልቅ መንደሮች፣ እንዲሁም ትላልቅ ከተማዎች መንፈስን በሚያድስ መልክ እንዲገነቡ ከተፈለገ፣ የኢኮኖሚና የንግድ እንቅስቃሴም እንዲዳብሩ ከተፈለገ የግዴታ የመንፈስ ተሃድሶን ሊያመጣ የሚችልና ለውጭ ታዛዥ የማይሆን በልዩ ልዩ ሙያዎች የሰለጠነ ምሁራዊ ኃይል ስልጣኑን መረከብ አለበት። ይህ ዐይነቱ አዲስ አገዛዝ የቢሮክራቶችና የቴክኖክራቶች ስብስብ ሳይሆን የተገለፀለትና በሁለ-ገብ ዕውቀት የሰለጠነና አገሩንም በፀና መሰረት ለመገንባት የሚችል መሆን አለበት። ይህ ሲሆን ብቻ ነው ኢትዮጵያን እንደ አገር መገንባት የሚቻለው፤ ከ90% በላይ ለሆነው ህዝብም አስተማማኝ ሁኔታን መፍጠር የሚቻለው።
ከዚህ ሁኔታ ስንነሳ በፖለቲካ ትግል ውስጥ እሳተፋለሁ የሚል ሰውና በድርጅትም የተደራጀ ካለ በመጀመሪያ መገንዘብ ያለብት ነገር ሰለአገር በሚወራበት ጊዜ በዚያ አገር ውስጥ ስለሚኖር ህዝብ ብቻ ነው። አንድን አገር አገር የሚያሰኘው ህዝቡና የአኗኗር ስልቱ፣ እንዲሁም ራሱን ለማሽሻል ሲል የሚያደርገው መሯሯጥ ነው። ለዚህ ደግሞ በመንግስትና ፖለቲከኛ ነን ባዮች አመቺ ሁኔታዎች መፈጠር አለባቸው። ከዚህ ባሻገር በተለይም እንድ ኢትዮጵያ ባለ አገር ውስጥ የፖለቲካው ሁኔታ መስመር ከያዘ ወይም አሁን ካለው ፋሽሽታዊ አገዛዝ ከተላቀቀ በኋላ ህዝቡን ሊያሳትፍ የሚችል ሰፋ ያለ ዲሞክራሲያዊ የአገር ግንባታ መካሄድ አለበት። ከዚህም በመነሳት ደረጃ በደረጃ የህዝቡ መሰረታዊ ፍላጎቶች(Basic Needs) መፈታት አለባቸው። የመንግስትም ዋና ሚና በዚህ ላይ መረባረብና ድህነትና ረሃብ ከአገራችን ምድር ለአንዴም ለመጨረሻ ጊዜ እንዲወገዱ ወደ ውስጥ ያተኮረ ስራ መስራት ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ በተለይም ምግብ ለስራ የሚባል ልዩና ሰፋ ያለ ፕሮጀክት በአገሪቱ ምድር በማዘጋጀትና ልዩ ዐይነት ፎንድ በመሰብሰብ መንደሮችንና ከተማዎችን ጥበባዊና ዘላቂነት ባለው መልክ እንዲገነቡ ማድረግ። ከዚህም ባሻገር ትናንሽና ማዕከለኛ ኢንዱስትሪዎች፣ እንዲሁም የዕደ-ጥበብ ስራዎች ሊያብቡ የሚችሉበትን ሁኔታ መፍጠርና በልዩ ዐይነት የብድር ሲይስተም መደገፍ ኢኮኖሚው ቀሰ በቀስ ግን ደግሞ በጠንካራ መሰረት ላይ እንዲገነባ ማድረግ ትክክለኛውና ሳይንሳዊ መንገድ ነው። የአንድ አገር የኢኮኖሚ ዕድገትም በትላልቅ ህንፃዎችና በአውሮፕላና ጣቢያዎች፣ በትላልቅ የገበያ አዳራሾች የሚለካ ሳይሆን በሰፊው ሁዝብ የኑሮ መሻሻልና የፈጠራ ስራ ነው። ለዚህ ምሳሌ የሚሆኑ በአሁኑ ወቅት እንደቡርኪና ፋሶ የመሳሰሉ አገሮች በቆራጥ ወጣት መሪያቸው አማካይነት በአጭር ጊዜ ውስጥ ተዓምር ሲሰሩ እናያለን። ከዚህም በላይና ጥበባዊ በሆነ መልክ በአገራችን ምድር ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ከማህበራዊ የኑሮ መሻሻል፣ ከባህል ዕምርታና ከሌሎችም ህዝባችንን ከሚያስተሳስሩ ነገሮች ጋር በማያያዝ የተሻለ ማህበረሰብ ወይም ህብረተሰብ የማንገነባበት ምክንያት የለም። ስለሆነም በራስ መተማመንና የራስን የጥሬ-ሀብትና ሌሎች ሀብቶችንም በራሳችን ቁጥጥር ስር በማድረግ ጤናማ ማህበረሰብና ህብረተሰብ መገንባቱ የማንኛውም ምሁርና የፖለቲካ ተንቀሳቃሽ ኃይል ዓላማ መሆን አለበት። ይህ ሲሆን ብቻና ተከታትያነት ባለው መልክ ሲሰራ ነው አንድን አገር በሁሉም አቅጣጫ መገንባት የሚቻለው። ስለሆነም ዋናው ዓላማችን ህዝባችንን ከድህነት ማላቀቅ፣ ረሀብን ማስወገድ፣ ኋላ-ቀርነትን በሳይንስና በቴክኖሎጂ አማካይነት ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜ በማጥፋት የተከበረችና የሰለጠነች አገር መገንባት መሆን አለበት። የፖለቲካ ትግሉም ከዚህ በታች መሆን የለበትም። መልካም ግንዛቤ!!
fekadubekele@gmx.de
www.fekadubekele.com
Litrature
Albrecht Dihle; The Theory of Will in Classical Antiquity, London, 1982
Alex Battler; Society: Progress and Force, Moscow, 2009
Alexander S. Kohanski; The Greek Mode of Thought in Western Phislosophy,
London & Toronoto, 1983
Alfred Korzybski; Manhood of Humanity: The Science and Art of
Human Engineering, New York, 2021
A.V. Miller; Hegel`s Phenomenology of Spirit, New York & Toronto, 1977
Basil Blackwell; The Rise and Decline of Western Liberalism, New York 1984
Bryan Magee; Philosophy and the Real World: An Introduction to Karl Popper,
London, 1973
Franci Hutcheson; An Inquiry into the Original of our Ideas of Beauty and Virtu,
New York, 1971
J.B.Burry; The Idea of Progress: An Inquiry into its Origin and Growth, London, 1928
Johann Gottlieb Fichte; The Science of Knowledge, London, 1981
J:R. Mailey; The Anatomy of the Resource Curse: Predatory Investment in Africa`s Extractive
Industries, Washington, 2015
Karl R. Popper; Objective Knowledge: An Evolutionary Process, Oxford, 1979
Karl R. Popper; The Open Society and Its Enemies, London & New York, 2002
Nicholas Rescher; Process Metaphysics: An Introduction to Process Philosophy,
New York, 1996
Richard Tarnas; The Passion of the Western Mind: Understanding the Ideas that
have shaped our World View, New York, 1991
T.K.Seung; Plato Rediscovered: Human Value and Social Order, London, 1996
https://www.youtube.com/watch?v=6rXBBqMmIP8
https://www.youtube.com/watch?v=N8PZHZ7K6qQ
https://www.youtube.com/watch?v=o9ASpJsuuT8
https://www.youtube.com/watch?v=_hOQTWrtU7k&t=1635s
https://www.youtube.com/watch?v=m7GESv6Zahg
https://www.youtube.com/watch?v=oO7iCv_NsPE&t=315s