
“ካለፉት ድክመቶች በመማር መደጋፍና መተባበር ለቀጣይ ጉዟችን ወሳኝ ነው” የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጀነራል ታደሰ ወረደ
ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ተቋማዊ ነፃነቱን አስከብሮ እንደ ጊዜያዊ አስተዳደር አካል በመሆን፤ የአስተዳደሩን ተልዕኮ ለማሳካት በጋራ እንደሚሰራ የድርጅቱ ሊቀመንበር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) አስታውቀዋል።
የአዲሱ የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር ፕሬዜዳንት ሌተናል ጀነራል ታደሰ ወረደ በይፋ ሥራቸውን የጀመሩ ሲሆን፤ ከነባሩ ካቢኔና ከደብረፅዮን (ዶ/ር) ህወሓት ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል።
ፕሬዝዳንቱ እንደ አዲስ ካቤኔያቸውን መልሰው እንደሚያደራጁ ያስታወቁ ሲሆን፤ ከዚህም ጎን ለጎን የሦስት ወር እቅድ እንዲዘጋጅ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።
በዚህም ዋንኛው ትኩረታቸው የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ሙሉ ለሙሉ መተግበር ላይ መሆኑን የገለጹ ሲሆን፤ የሕዝብ ሰላምና ደህንነት በአስተማማኝነት መጠበቅ፣ የክልሉ ኢኮኖሚ ማነቃቃት እንዲሁን የአስተዳደር መዋቅሩን ማስተካከል የትኩረት አቅጣዎች መሆናቸው አስታውቀዋል።
አክለውም፤ የተፈጠረውን የፓለቲካ ልዩነት በማጥበብ የትግራይ ሕዝብ ቀጣይ እጣ ፈንታ ማቃናት እንደሚገባ በመግለጽ፤ “አሸናፊና ተሸናፊ ከሚል መገፋፋት በመውጣት በአብሮነት በመደጋገፍ በጋራ መስራት አለብን” ሲሉ ማሳሳበቸውን ከህወሓት የማህበራዊ የትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።