ዳግማዊ ጉዱ ካሣ
ሕወሓት በሕይወት ሳለ በርካታ ልሣኖች ነበሩት – በጋዜጣም በሬዲዮና በቲቪም፡፡ ከነዚያ ልሣናቱ አንዱ “ወይን” የሚባለው ጋዜጣ ነበር፡፡ “ይ” ጠበቅ ትበል ታዲያ የመጠጡ እንዳይመስል፡፡ ለምን ትዝ አለኝ አሁን?
ብዙዎቻችን እንቅልፍ ክዶናል መቼም፡፡ እናልህ ወደ ሚያዝያ 1/2017 ዓ.ም በምንሻገርባት የማክሰኞ ለረቡዕ ሌሊት ዶሮ መጮኺያ አካባቢ አዘውትሬ የምከታተለውንና ከነቅሬታየ የምወደውን ዳግማዊ “እፎይታ” ማለትም “ወይን” የሕወሓት የዩቲዩብ ልሣን ኢትዮፎረምን ማዳመጥ ጀመርኩ፡፡ ዝግጅቱ የሚያጠነጥነው ስለጌታቸው ረዳ ነው፡፡ “ጌታቸው ውሎዎቹና ገጠመኞቹ፤ ያልተሰሙ መረጃዎችና ታሪኮች” በሚል ርዕስ ይህ የሣልሣይ ወያኔ ደቀ መዝሙር ባቀረበው ዝግጅት ጌታቸውን ከመላእክት በጣም ከፍ፣ ከእግዚአብሔር ደግሞ ትንሽዬ ዝቅ አድርጎ አድማጩ እንዲረዳ ያላደረገው ጥረት የለም፡፡ እየገረመኝ፣ እየተደነቅሁና የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ መለዋወጥ እያስደመመኝ ያን ዝክረ ጌታቸው በተመስጦ ተከታተልኩ፡፡ ከተነሱት ነጥቦች የማረኩኝን እዚህ መጥቀስ ስለፈለግሁ ነው በደረቅ ሌሊት ሞባይሌን ያስቸገርኳት፡
ለወያኔ ስስ አንጀት ያለው አማራ ጠሉ ወንድሜ ያዬሰው ሽመልስ ለጌታቸው ካለው ፍቅር የተነሣ በትግራይና በኦህዲድ ጦርነት ማገባደጃ አካባቢ ጌታቸው ረዳ አቢይን እንዴት እንዳጥረገረገውና ዞሮ ደሞ እንዴትና በምን ሞራል የአቢይ ተላላኪ አሽከር ሊሆን እንደቻለ ትንፍሽ አላለም፡፡ ምክንያቱም ያቺን በአንድ የቤት ታዛ ሥር ሆኖ ጌታቸው የተናገራትን አቢይን በትክክል የምትገልጽ ንግግር ቢያስደምጥ ለአቢይ ዱላ እንደማቀበልና ለጌታቸው ደንቃራ እንደመፍጠር ሊሆን ነው፡፡ እንኳን አልተናገረ፤ እኔም ነገር ያሳመርኩ መስሎኝ እንጂ መናገር እንዳልነበረብኝ አውቃለሁ፡፡ ለነገሩ አህያ ለአህያ ቢራገጥ ጥርስ አይሳበርም፡፡ አንድ ናቸው፡፡
ነገር ግን “ትግራይ ግዛቷ ተወስዶባታል፤ ተፈናቃዮቿም ወደነዚያ ግዛቶቿ መመለስ አለመቻላቸው ነው ችግሯ…” በሚለውና በመሰል ሌሎች አነጋገሩ ትልቅ ተቃውሞ አለኝ፡፡ በነገራችን ላይ ወያኔ ምን ዓይነት ድግምት እንደሚያዞርባቸው አላውቅም ብዙ አማራ ነን ባዮችን ወደ አክራሪ ትግሬነት እየለወጠ ከትግሬ በላይ ትግሬ የማድረግ የቆዬ ልማድ አለው – ከጳጳሱ በላይ የሚኮተልክን የካቶሊክ ምዕመን ያስቧል፡፡ የሚደንቅ መተት ነው፡፡ አሮጊቷ ገነት ዘውዴ በመለስ ዜናዊ ፎንቃ ተጠልፋ ወድቃ ፓርላማ ውስጥ ሳይቀር በዕንባ ባሕር ትነፈርቅ ነበር፡፡ ክፍሌ ወዳጆ የሚባል ነፈዝ ሕግ አርቃቂያቸው ነበር፡፡ ጌታቸው ሴኩቱሬ እስከሞት በደረሰ የወያኔ ፍቅር ተመርዞ ትግራይ ውስጥ “ተሰውቷል”፡፡ ሙሉጌታ አሥራተ ካሣ አንደኛው የወያኔ አለቅላቂ ነበር፡፡ አንዳርጋቸው ጽጌም … እሱን እንኳን እዚህ አላንሳው፡፡ እ… ከጥበቃና ከኩሊነት የወሰዷቸው እነተመስገን ጥሩነህና አገኘሁ ተሻገርም አይዘነጉም፡፡ ምን አለፋችሁ – አማራን መቅ የከተተው በአብዛኛው ባንዳውና ሆዳሙ እንዲሁም የማይሠራበትን ልቅምቃሚ ሥልጣን ፈላጊው አማራ እንጂ አክራሪ ትግሬና ኦሮሞ ብቻ አይደሉም፡፡ የሚደንቀው ጥቂት የማይባሉ ሃቀኛ ትግሬዎችና ኦሮሞዎች እንዲሁም ደቡቦች ከአማራ እውነተኛ ልጆች ጋር አብረው ለአማራ ነፃነት ሲታገሉና ለመብቱ ሲከራከሩ የነዚህ አማሮች መበላሸትና የዘር ሐረጋቸውን ለዕልቂት መዳረጋቸው ሲሆን ይህም አሳዛኝ ክስተት ፍቺ የሌለው ዕንቆቅልሽ መሆኑ ተሰምሮበት በታሪክ ተመዝግቦ የሚቀመጥ የባንዳዎች ጥቁር ድርሣን ይሆናል፡፡ አሁን ደግሞ ዕድሜና ተሞክሮ የማያስተምረው ያዬሰው ሽመልስ የተባለ ጎበዝ ጋዜጠኛ ያለውን ዕውቀት በተጣመመ አኳኋን በመጠቀም አማራን ተሳዳጅ አድርጎ ለማጥፋት ከአማራ ጠላቶች ጋር ወግኖ የተቻለውን ሁሉ ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡ በ”ምዕራብ ትግራይ” እና በመለስ የሙት መንፈስ ፍቅር ተነድፎ ፍዳውን እያዬ ነው፡፡ አለመለከፍ ነው ጓዶች፡፡
የአማራን መከራና ስቃይ እያበዛውና የነፃነትንም ቀን እያዘገዬ የሚገኘው ከአማራ ማሕጸን ወጣሁ የሚለው ወገን ስለመሆኑ ብለነው ብለነው የጨረስነው ጉዳይ ነው፡፡ ክርስቶስንም በመሣም አሳልፎ የሸጠው እኮ የራሱ ደቀ መዝሙር ነው፡- ሊያውም ሳይበላው ታንቆ ለሞተበት የወቅቱ 30 አላድ፡፡ ስለዚህም የነዳንኤል ክብረት ለኦሮሙማ ማፈንደድና የነያዬሰው ለሕወሓት መነጠፍም አያስደንቅም፡፡ እኛም ድህነትን መርጠን ድኅነትን ለማግኘት ብለን የተደበቅነው እግዚአብሔር አምልጡ ቢለን እንጂ ይሄኔ አደባባይ ብንወጣ ኖሮ “ኮሎኔል ዶክተር ፊልድ ማርሻል ሼህ አቢይ አህመድ ገና የኢትዮጵያን ስም ሲሰሙ ዕንባቸው ይቀድማል፤ አንጀታቸው ይንሰፈሰፋል፡፡ ሰሞኑንማ የሌት ከቀን ህልማቸው ልክ እንደቡርኪና ፋሶው ኢብራሂም ትራኦሬ መኖሪያ ቤት ሠርተው ከቀለብና ልብስ ጋር ቤት ለሌላቸው አማሮች ማለትም ዜጎች በነፃ ሊያድሉ ነው፡፡…” ከማለት የሚያግደን አልነበረም፡፡
ብሂሉም እንዲህ ሲል ይደግፈናል፤
ደግሞ ለውሸት አለው ወይ ድካ፤
አምሣ ሰው ገዳይ ባንድ አማሪካ፡፡
(አማሪካ እሚባል የጥይት ስም ነበረ ዱሮ)
እንግዲህ የኛ ነገር እንዲህ ሆኖ አረፈው፡፡ እኔማ በቲያትር ዓለም የምኖር እየመሠለኝ ክፉኛ ተቸግሬያለሁ፡፡ በኔ ዕድሜ ኢትዮጵያ በዚህ መልክ ምድራዊ ሲዖል ትሆናለች ብዬ በእውን ቀርቶ በህልምም አስቤው አላውቅም፡፡ በተለይ አቢይን የመሠለ በክፋትና በተንኮል፣ በሤራና በሸር፣ በጭካኔና በዕብለት ሰይጣንን ዕጥፍ ድርብ የሚያስከነዳ ዕብድ መሪ አያለሁ ብዬ አልጠበቅሁም፡፡ በወያኔው ያዬሰው ሽመልስም እንደተጠቀሰው አቢይ ሰሞኑን ተጋሩን ሲያሿሹም ምን አለ መሰለህ – “ተጋሩ እንደሌሎች ወንድሞቻቸው በሰላም ወጥተው እንዲገቡ ለታደሰ ወረደ ሁለት ዐይኖች ከፌዴራል የዐይን ባንክ አውጥተን ሰጥተናል፡፡” እዚህ ፍቼና ጎሃ ጽዮን በየሣምንቱ አማራ እየታገተና እየተገደለ፣ ሬሣ ለማስለቀቅም በሚሊዮኖች እየተጠየቀ በሰላም ወጥተው የሚገቡ ትግሬዎችን በተቃራኒው የኛን ወደነሱ ይገለብጣል – የበለጥሻቸው አድባር ይገልብጠውና፡፡ በሀሰተኛ ንግግር ዲግሪ ቢሰጥ አቢይ አህመድ በሺዎች የሚቆጠሩ PhDs ይኖሩት ነበር፡፡ የዚህ ሰው ሥነ ተፈጥሮማ መመርመር አለበት – ሬሣውም ቢሆን፡፡
ባልጀመርኩበት ጉዳይ ለማጠቃለል ያህል – የሕዝቡ የዝምታ ጩኸት እጅግ ያስፈራል፤ ያስደነግጣልም፡፡ የዝምታው ጩኸት መላውን ዓለምን እስኪያደነቁር ድረስ ጎልቶ ይሰማል፡፡ የሕዝቡ ዝምታና የዐውሬው ጭካኔ መሳ ለመሳ ሆኗል፡፡ ዐውሬው ኦሮሙማ በየቀኑ ቀያጅና ርሀብን አስፋፊ መመርያና ደምብ ሲያወጣ አንድም የሚቃወም ድምፅ የለም፡፡ ይህም ፀጥታ የልብ ልብ እየሰጣቸው አዲስ አበባን ከሞላ ጎደል አፍርሰው ጨርሰው ወደክልሎች ገብተዋል፡፡ በነገራችን ላይ አብነት የሚባለው አካባቢም በቅርቡ እንደሚፈርስ ለኗሪዎቹ ተነግሯቸው ሽብር ውስጥ ገብተዋል፡፡ አሁን ጋብ ያለ የሚመስለው የቤት ፈረሳና የሕዝብ መፈናቀል ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ግልጽ ነው – አሁን በግልጽ እንደምናስተውለው ገንዘብ ጠፍቶ አንድም መሠረታዊ ልማት ማካሄድ ቢቸግራቸውም ለማፍረስ የሚሆን ቡልዶዘር መግዛትና አፍራሽ ግብረ ኃይል ወደየሠፈሩ ማሰማራት ግን አያቅታቸውም – የተሟላ መረገም ማለት እንዲህ ነው – እነሱም እኛም፡፡ ለምን ብትል የኦሮሙማ መጨረሻ ከሕወሓትም የበለጠ ሰቅጣጭ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነውና፡፡ በቂም በቀል ተነሳስተህ፣ በጥላቻም ታውረህ ወዳጅህን ለመጉዳት አትሞክር፤ አጸፌታውን አትችለውምና – ከላይ ወይም ከታች የሚመጣብህ መቅሰፍት መኖሩን አስቀድመህ ተረዳ ወንድሜ፡፡ አቢይ ከአሁን በኋላ አንድ ወይ ሁለት ዓመት ካገኘ በአዲስ አበባና በዙሪያዋ አንድም አማራ አይኖርም – ቆርጦ የተነሳበት ዓላማው ነው፡፡ አማራ ግን ምን እንዳደደበው አላውቅም በፀጥታው ጸንቷል፡፡ “ተው እንዳታስጨርሰን፤ የኔን እግር እየቆረጠመ ነው” የሚለውን የፈሪዎች ታሪክ በሚያስታውስ መልኩ አማራው በየተራ ግን ሁሉም በሚያልቅበት የውድመት ወረፋ ላይ ይገኛል፡፡ አምላክ ይድረስለት ከማለት ውጪ የምለው የለም – ለጊዜው፡፡ እነእንቶኔም ወገቡን እንደተመታ እባብ እዛው እየተልሞሰሞሱ ችግሩን ከማባስ በዘለለ በእስካሁኑ ሁኔታ ለአማራው ስቃይ መቀነስና መጥፋት የፈየዱለት ነገር የለም – መስዋዕትነታቸውን አደንቃለሁ፤ ዘር ይውጣላቸው፡፡ እዚያ አካባቢ የሠረገው የአጋንንት መንጋ ግን በጸሎትም ይሁን በዱላ ካልጸዳ በስተቀር ነፃነት ባትቀርም መዘግየቷ ግን በገሃድ እየታዬ ነው፡፡ አንድ ነገር በዘገዬ ቁጥር ደግሞ ተስፋ መቁረጥ ይንሠራፋና ዜጎች ወደዞምቤነት የመለወጥ መጥፎ ዕድላቸው ያመዝናል፡፡ በአንድ ማይም ዕብድ ሕጻን እንዲህ መሆናችን በበኩሌ የእግር እሳት ነው የሆነብኝ፡፡ በዘርና በጎሣ፣ በሀብትና በቋንቋ፣ በጎጥና በሸጥ የመከፋፈል አባዜ ለዚህ ዓይነቱ ችግር ይዳርጋል፡፡ በዚያም ላይ ለጨለማው ንጉሥ የሚገዙ የሃይማኖት አባቶች ሀገር ምድሩን ተቆጣጥረውት ሲታዩ የገጠመን ችግር ቀላል እንዳልሆነ መገመት አይከብድም፡፡ ከቤተ መንግሥት ጀምሮ የፍቅርሲዝሙ ዓይነት ነቢይ ደምሣሽና ምድረ አጭበርባሪ የቸርች ኮልኮሌ በዝቶ ሲታይ ደግሞ አሳራችን ቀላል እንዳልሆነ ይገባናል፡፡ አጥማቂ ነኝ ባዩ ራሱን በእግዜር ቦታ ተክቶ በተገዛ የአጋንንት መንፈስ ምሥኪኑን ሕዝብ እያስጮኸ ፍራንክ የሚለቅመው “መነኩሴ”ና “ባህታዊ” ደግሞ ሌላ ጉድ ነው፡፡ በእውነት እኮ የኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ ከማሳበድም በላይ ነው፡፡ አሁን በእውነቱ በኢዩ ጩፋና በማነው ዳንሣ የሚታለል በሰው አምሣል የተፈጠረ ሰው መኖር ነበረበት? ሰውን ምን ነካው? ምን ገባብን? ወይንስ ይሄ የምዘረዝረው ሁሉ ለኔ ብቻ ይሆን የታየኝ?
ለማንኛውም እስካሁን የጦማችሁ ማብቂያው ላይ ስትደርሱ እንዳትሽሩ አደራችሁን ተጠንቀቁ፡፡ ፋሲካ እየተቃረበ ነው፡፡ “ሰው ጠባቂና ጦም ጧሚ አንድ ነው…” እንደሚባለው እንዳትሆኑ የጦማችሁትን ጦማችሁ በመጨረሻው ጉድ እንዳትሆኑ አጥብቃችሁ ጸልዩ፡፡ ተበልቶ እዳሪ ለሚሆን፣ ተጠጥቶ ሽንት ለሚሆን፣ ተገንብቶ በሞት ለሚታጣ ሕንጻ፣ ተለብሶ ለሚያልቅ ኮትና ሱሪ፣ አሁን ታይቶ አፍታ ለማይቆይ … ኃላፊና ጠፊ ምድራዊ ቁስ ብለን እናታችንን እንዳንከዳ፤ ይህን በዕንባና በደም ተለውሶ ወደፈጣሪው እየጮኸ የሚገኝን ሕዝብም እንዳንረሣና እንደአብን እንዳንበን – (ወይ የሞሌ ልጅ! ወይ የመርሻ ዲቃላ!)፡፡ አቤት ቅኔ! እንደጉድ እቀኘው የለ እንዴ፡፡ (ስለጦሙ ያልኩት ድርብ ነገር ታይቶኝ ነው – ወደሰሙነ ህማማት ልንገባም አይደል? ለዚያ ነው፡፡)
መሰነባበቻ፦
“በመጨረሻው መጨረሻ ዘመን ታጣቂው ይበዛል፡፡ በሽምብራ ዛፍ ሥር ተቀምጦ የተጣመመ ፍርድ የሚሰጠው እረኛ ዳኛም እንደዚሁ ይበዛል፡፡ ዐዋቂዎችና ዕውቀት ከሀገር ይሰደዳሉ፡፡ በሞትና በስደት ሕዝብ ይሰቃያል፡፡ መግደል የሚያዝናናበት፣ ማሰቃየት የሚያሾምበት ዘመን ይብታል፡፡ ቤተ መንግሥቱን ቁንጫና ትኋን ይወረዋል፡፡ በጠቢባንና አስተዋዮች ላይ ሞት ይበረታል፡፡ ሁሉም እየተነሣ ‘እኔ እበልጥ,፥ እኔ እበልጥ’ ይላል፡፡ እህልን ከሚያመርተው እርስ በርስ የሚዋጋው በጥፍ ድርብ ይበልጣል፡፡ አቅለቢስነት ነግሦ ጭካኔ በመላ ሀገሪቱ ይናኛል፡፡ ሃይማኖትና መልካም ሥነ ምግባር ይጠፋሉ፡፡ ይህ ሁሉ ያልፍና ትንሣኤ ይበሠራል፡፡ ለትንሣኤው የሚበቁ ግን እጅግ ጥቂቶች ናቸው፡፡ ምክንያቱም አብዛኞቹ የክፋትና የጭካኔ ንጉሥ ለሆነው የሣጥናኤል መንግሥት ተንበርካኪ ነበሩና፡፡ የሚተርፈው ግን ከየት መጣ በማይባል ደገኛ ንጉሥ እየተመራ በአባቶቹ ዘመን ተነጥቆ የነበረውን ክብርና ሞገስ ያገኛል፤ ያኔም ‘ስደት ወደ ኢትዮጵያ ይሆናል’ የተባለው ቀዳሚና ዘመን የማይሽረው ትንቢት እውን ይሆናል፡፡ ይህ የማይናወጥና የማይለወጥ ቃለ ትንቢት እውን ሲሆን ኢትዮጵያ ወደቀድሞው የክብር ማማዋ ትመለሳለች፡፡” – አቤቱ ጌታ ሆይ! የዚያ ዘመን ሰው እንድታደርገን በጭንቅ አማላጇ በሰዓሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም እንለምንሃለን!!!
“ዕብድና ዘበናይ የልቡን ይናገራል” የሚል ሰው እንደማይኖር ተስፋ አለኝ፡፡ ነግቶ ያገናኘን ለማንኛውም፡፡