አርበኛ ዘመነ ካሤ
ዳግማዊ ጉዱ ካሣ (ma74085@gmail.com)
በዩቲዩብ የሚታዩ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ከሚታዩት ውስጥ ጠቃሚ የመኖራቸውን ያህል እርባናቢሶችና ወቅትን ያልጠበቁ፣ ዘመኑን ያልዋጁ ምናልባትም በጠላት የተሸረቡ ተንኮሎችና ሤራዎችም እየተዛነቁ በዚሁ ሶሾል ሚዲያ ይተላለፋሉ፡፡ እንደኔ ዕይታ ጎጂ ናቸው ብዬ ከማምንባቸው የሶሻል ሚዲያ ልጥፎች ውስጥ አንዱና ምናልባትም ዋናው ከፍ ሲል በርዕሴ የገለጥኩት ነው፡፡
ዘመነ ካሤ በአማራ ፋኖ የነፃነት ትግል እያበረከተ ያለው አስተዋፅዖ እጅግ ከፍተኛ ነው፤ ከልፋቱ አንጻር የአንድ ዘመን ብቻም ሣይሆን የበርካታ ዘመናት ንግሥና ይገባዋል፡፡ ከልጅነት ዕድሜው ጀምሮ ለአማራ ነፃነት እያደረገ ያለው ትግልና አመራር ሰጪነት በታሪክ ሲዘከር የሚኖር ለመሆኑ ከኤርትራ በረሃ ጀምሮ እያስመዘገበ የሚገኘው የትግል ተሣትፎ ጉልኅ የታሪክ ሥፍራ የሚይዝ ቋሚ ምሥክሩ ነው፡፡ መስሎትና በጊዜው አምኖበት ከኢትዮጵያና በተለይም ከአማራ ጠላቶች ከነብርሃኑ ነጋ ጋር (ይሄ ነጋ የሚሉት ስም ልክ እንደ ተሾመ ሁሉ አሁንስ ሊያቅረኝ ደረሰ!) በኤርትራ ብዙ ደክሟል፡፡ እየቆየና ሁኔታዎች እየጠሩ ሲመጡ ግን በአሁኑ ወቅት በገዛ ቀየው ትግሉን አፋፍሞ በሁሉም የአማራ ግዛቶች ጨፍጫፊውን ኦነግሸኔን ከሚታገሉ ጓደኞቹ ጋር የነፃነት ትግሉን ወደመጨረሻው ምዕራፍ እያስጠጉ ይመስላል፡፡ ሆኖም ቢሆን ገና ብዙ አስቸጋሪ ዳገቶች መኖራቸው ግልጽ ነው፡፡ የተናበበና የተሟላ ልባዊ አንድነት ካልተፈጠረ ትግሉ አድሮ ቃሪያ እንደሚሆን ካሳለፍነው መሪር ተሞክሮ መገንዘብ ይቻላል፡፡ የተናጠል ጉዞ ማንንም የትም ሊያደርስ እንደማይችል ብዙ መስዋዕትነትን የከፈልንባቸው ያለፉት 20 ምናምን ወራት ጠቋሚ ናቸው፡፡ ይህን የሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ ጉዳይ ዕልባት ካላገኘንለት ውኃ ቢወቅጡ እምቦጭ ከመሆን አይዘልም፡፡ አማራን የጎዳው ከባንዳው በተጓዳኝ በየጎጥ ሸንተረር ተከፋፍሎ መታገሉ ነው፡፡ መከፋፈሉ የተወሰነ ሥልታዊ ጥቅም እንዳለው ቢታመንም አንድ መሆኑ ደግሞ በአመዛኝ ትልቅ ጥቅም አለው – በቁራኛ የሚታይና በጥንቃቄ የሚመራ አንድነት ወሳኝ ነው፡፡ እንጂ አሥር የአማራ የትግል ሰልፍ አዲስ አበባ ቢገባ ጣጣው ብዙ ነው፡፡ አእምሮን ማሳደግ ከመሣሪያ አነጣጥሮ መተኮስ የበለጠ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ የተኩስ ዕውቀትና የአእምሮ አስተዋይነት ወይም ጥበብ ለዬቅል ናቸው፡፡ የተሟላ ስብዕና ባለቤት ለመሆን ደግሞ ጸሎትና ንባብ ወሳኝ ናቸውና ፋኖዎች በዚህ ዙሪያ ብትጥሩ ደግ ነው፡፡
አንዱ ዳገት በርዕሴ የጠቀስኩት ጉዳይ ነው፡፡ ማን እንደሚለጥፈው አላውቅም “ዘመነ ተነስቷል ዙፋኑን ሊረከብ” በሚል የሙዚቃና የትርክት ዝግጅት በዩቲዩብ ገጽ አያለሁ፡፡ ይህን መልእክት ዘመነ ራሱ የፈቀደውና የሚፈቅደው አይመስለኝም፡፡ ያለንበት ዘመን የ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ዘመነ መሣፍንት ሳይሆን የ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነው፡፡ በዚህ ዘመን ደግሞ ንጉሥና ንጉሠ ነገሥት፣ መሣፍንትና መኳንንት፣ አልጋ ወራሽና የእልፍኝ አስከልካይ፣ ደጃዝማችና ፊታውራሪ ወይንም ባላምባራስና አፈ ንጉሥ የሚባሉ የቀደምት ባህላዊ የሹመት እርከኖች የሉም፡፡ ዘመናችን በክህሎትና በዴሞክራሲ፣ በትምህርትና በምርጫ ሥልጣንና ኃላፊነት የሚያዝበት እንጂ ገና ከአሁኑ ትግሉ ከጫካ ወጥቶ መናገሻ ከተማ ሳይገባ በታጋዮች መካከል እንዲህ ያለ ሸፍጥ የተሞላበት የሚመስል ተንኮልና ጎጥ አዘል ሸር በሚዲያ ማስተላለፍ ከእውነተኛ የአማራ ትግል ጎራ አይወጣም፤ ከፋፋይና ጎጠኝነትን የሚያበረታታ ሸረኛ አካሄድ ነው፡፡ የሚገርመው ኮሜንት እንኳን እንዳይሰጥበት ዝግ ነው፤ አይቻልም፡፡ ይህን መሰሉን የአማራን ትግል ቀርቶ ዘመነን ራሱን የማይጠቅም ስሜት-ወለድ ልጥፍ ማሰራጨት መከልከል አለበት፡፡ የጎጃም ፋኖ በዚህ ላይ ውይይት አድርጎ ሊቃወመውና ሊጠየፈውም ይገባል፡፡ ዘመነ ካሤ አንዱ የትግሉ ሰበዝ እንጂ በዚህ መልክ ገና ከአሁኑ የሥልጣን ሽሚያ ውስጥ ሊገባ የሚተጋም አይመስለኝም – እንደመሳጭ ንግግሩ፡፡ እርግጥ ነው የንግግር ማማርና የተግባር ነገር በሀገራችን የሚለያዩ መሆናቸው ግልጽ ነው፡፡ ቢሆንም እኔ የማውቀው ዘመነ በዚህ መልክ ስሙ ሲጠፋ ዝም የሚል ከሆነ ስህተት ነው፡፡ ይህን መሰሉን አጉራ ዘለል ቅስቀሳ እያወቀ ዝም ብሎ ከሆነ መቼም አማካሪዎች ይኖሩታልና ከዚህ ዓይነቱ ሕዝብን የሚያስከፋ አካሄድ ራሱን ነፃ እንዲያወጣ ይምከሩት፡፡ አቢይ መከራውን የሚበላውና የወጣትነት ዕድሜውን በከንቱ የሚያባክነው በተለከፈበት ተለክፎ ነው፡፡ አሁን ይሄኔ በሱም የሚቀና ይኖራል፡፡ እናም በአጠቃላይ የፋኖ አመራሮች ኅሊናቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ ይሁን፡፡ ከጭብጨባ ይራቁ፡፡ ጭብጨባ ገደል የሚከት የ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ወረርሽኝ ነው፡፡ በስሜት ወበቅ እያነሆለለ ወደዕብሪት የሚነዳን የጓደኛ ምክርንም ሆነ የዘመድ አዝማድና የመታች አስመታች አጓጉል ሰው መራቅ አለባቸው፡፡ ጉድ እየሠራን ያለው ይሄ የሥልጣን አራራና የታዋቂነት አባዜ ነውና ፋኖ ከነዚህን መሰል መሰናክሎች ራሱን ይጠብቅ፡፡ በጥቅሉ “ፋኖ ንጉሡ፣ ፋኖ ጅግናው፣ ፋኖ ሣተናው …” እየተባለ ቢዘመር ክፋት የለውም፡፡ በግለሰብ ደረጃ ከሆነ ግን ስንጥቃትን ስለሚፈጥርና ጎጠኝነትን ስለሚያፋፋ ይቅር፡፡ አንደኛ አማራ አማራ ነው – የትም ቢወለድ፡፡ ስለዚህ በጎጥና በሸጥ መከፋፈሉ አስቂኝ ብቻ ሣይሆን ዕብደትም ነው፡፡ ሁለተኛ ፋኖ እየታገለ ያለው አማራንና ኢትዮጵያን ከነዚህ ዐረመኔ ጅቦች ነፃ በማውጣት ለሁሉም ዜጋ እኩልና ምቹ የሆነች ሀገር ለመፍጠር እንጂ በአንድ ጎሣ የምትዘወር ሌላ አዙሪታዊት ሀገር ለመመሥረት አይደለም፡፡ ስለሆነም ፋኖ መጠንቀቅ የሚገባውና ካለፉት ሁለት ዘረኛ ሥርዓቶች ትምህርት መቅሰም የሚገደድበት ብዙ ነገር አለ፡፡
እዚህ ላይ የታወሰኝ አንድ ራስ ምታቴን ልግለጽ – በራስ ምታት መሞቴ ነው ወገኖቼ፡፡ በየመሥሪያ ቤቱና በየእምነት ቤቱ ስሄድ የሚገጥመኝ ነገር የኦሮሞው ሠራተኛ ብዛት፣ የኦሮሞው ኃላፊ/ባለሥልጣን ብዛት(ደግሞ እኮ ሲንቀባረሩ!ፐ!)፣ የሙስናው ብዛት፣ የማይምነቱ ብዛት፣ የኢሞራሊቲው አሳሳቢነት፣ የባለሥልጣናቱ በትምህርት አለመግፋትና ምግባረ-ብልሹነት፣ የሃይማኖት መላላት፣ እንደሚወራውም የፎርጂዱ ዓይነትና ብዛት ወዘተ. ነው፡፡ የተማረና በትክክል የሚያገለግል ኦነግሸኔ በየባንኩም ሆነ በሌላው ቢመደብ ሃሳቡ አይበላኝም፡፡ ግን የጋራ ቋንቋውን ጨምሮ የሥራ ኃላፊነቱን ያልተረዳና እጅ እጅህን የሚያይ ኦሮሞ ነው አዲስ አበባን የሞላት፡፡ ችግር ነው፡፡ ባጭሩ ሀገር ፈርሳለች፡፡ አሁን የሚያስጨንቀኝ ታዲያ – ይህች አገር ነገ ነፃ ብትወጣ በአንጻራዊነት ቀደም ሲል ወደነበራት አቋም ሊመልሳት የሚችል ኃይል ከየት ሊመጣ ነው? እውነቴን ነው እኮ፡፡ አሁን በታዘብኩት ሁኔታ ሁላችንም እንደዚህ ከበከትን ህገ እግዚአብሔርን የሚጠብቅ ቄስና ካህን ከየት ሊመጣ ነው? ፈጣሪን የሚፈራ የሃይማኖት አባትና በጎችን ጠባቂ እረኛ ከየት እናገኛለን? ህግ አስከባሪ ፖሊስና የፍትኅ አካል ከየት ልናገኝ ነው? በፍትኅ የሚያስተዳድሩ አመራሮች ከየት ይመጣሉ? ከሰማይ ሊወርዱ ወይንስ ከመሬት ሊፈልቁ? ካለ ጉቦ የሚያስተናግድህ የትራፊክ ፖሊስ፣ የፍርድ ቤት ዳኛ፣ የቀበሌ ዘበኛ፣ የክፍለ ከተማ የመሬት ይዞታ ሠራተኛ፣ የሚኒስትር መ/ቤት ሹም፣ ወዘተ. ወዘተ. ወዘተ. ከየት ሊገኝ ነው? በእውነት ከዛሬው የነገው ይበልጥ ያስጨንቃል፡፡
ወደዘመነዋ ልመለስ፡፡ ስለዘመነ ቀደም ሲል ያልኩትንና ቀጥሎ የምለውን ስል ዘመነ ሥልጣን አይገባውም ወይም ይበዛበታል/ያንስበታል የሚል ክርክር ውስጥ ልገባ ፈልጌ አይደለም – ከፍ ሲል እንደገለጽኩት ዝንተ ዓለሙን ቢነግሥ ግዴለኝም ብቻ ሣይሆን ደስ ይለኛል፡፡ ነገር ግን ዘመኑን ባላገናዘበ መልክ እየተንሸራሸረ ያለው ነገር ደስ አይልም፡፡ “በጊዜ የጮኸ ጅብ አያሳድረኝም” ይባላልና ዘመነን ለማስጠመድ በእግረ መንገድም የፋኖን ትግል ለመከፋፈል የሚንቀሳቀሱ ወገኖች አደብ ይግዙ፡፡ እሱን የጠቀሙ ወይም በርሱ የተወደዱ መስለው በዚህ መልክ ቆዳቸውን ለማዋደድ የሚፈልጉ ካሉ ወይም እርሱን ተገን አድርገው የአማራን ትግል አቧራ ለማልበስ የሚፍጨረጨሩ ቢኖሩ የሚያስከትሉት ጉዳት ሊናቅ አይገባውምና ሃይ ሊባሉ ይገባል፡፡ በበኩሌ ዘመነ ነገሠ፣ ምሬ ነገሠ፣ ተፈራ ነገሠ፣ ደሳለኝ ነገሠ፣ ሀብቴ ነገሠ … ደቻሣ ነገሠ፣ ሐጎስ ነገሠ፣ አብደላና ገ/ወልድ ነገሡ …. ምኔም አይደለም፡፡ ነጋሹ ቁስሌን ያክምልኝና ወደነበርኩበት የሰውነት ደረጃ ይመልሰኝ እንጂ እንኳንስ ሰው ዝንጀሮም ይንገሥ፡፡ ሁሌም እንደምንለው ወንበሩ የሚይዘው አንድ ሰው እንጂ 130 ወይም 60 እና 70 ሚሊዮን አይደለም፡፡ ደግሞም ቀድሞ የመቀመጫየን ብላለችና ዝንጀሮዋ ወጡ ሳይወጠወጥ ስለነጋሾች አሁን ማውራት የአውሪውን ግለሰብ ፍላጎትና ምናልባትም ያልተገባ ፍላጎት እንደመጠቆም ይቆጠራል፡፡
ስለሆነም እነዘመነና ሌሎችም የፋኖ ትግል መሪዎች በተጠመደላችሁ ፈንጂ አትረማመዱ፡፡ ስለሥልጣን በጭራሽ አታስቡ፡፡ አቢይን አላወቃችሁትም ማለት ነው፡፡ አቢይ ከታችኛው ዓለም የተላከ ከባድ ሚዛን የሚደፋ የአጋንንት ኃይል ነው፡፡ መላ ሀገራችንን በሰይጣናዊ መንጋጋው እያላመጣት በሚገኝበት በአሁኑ ሰዓት ስለሥልጣን ማውራት በርግጥም ጫካውና ቤተ መንግሥቱ በአንድ ዓይነት መንፈስ ስለመያዛቸው የሚያስጠረጥር ነው፡፡ የጦርነት ዕልቂቱ እንዳለ ሆኖ፣ የአማራው ቤት ፈረሳና መፈናቀል እንዳለ ሆኖ፣ የአማራ ግድያና ብርቱካናዊ ደፈራው እንዳለ ሆኖ፣ የአማራ መራብ መጠማቱ እንዳለ ሆኖ፣ አማራ በያለበት እንዲጠፋ መፈረዱ እንዳለ ሆኖ፣ …. በአሁኑ ወቅት ኑሮው ሰማየ ሰማያትን አልፎ አንድ ኪሎ ቡና 1100 እየተሸጠ ስለሕይወት መቀጠል ማውራት ሲገባ ስለሥልጣን ማውራት በርግጥም ህመም ነውና እባካችሁን የደላችሁ ሰዎች ዘወር ብላችሁ እኛ የምንለውንም ስሙ፡፡ በቃ፡፡ የምን መተፋፈር ነው፡፡ እኔ ስለራሴና ቤተሰቤ አድሮ ወይም ውሎ መገኘት እየተጨነቅሁ የደላው ስለንግሥና ይዘፍናል፡፡ ምን ዓይነት የአስተሳሰብ ዝቅጠት ነው!! በምታምኑበት ይሁንባችሁ ወደዬቀልባችን ባፋጣኝ እንመለስ፡፡
ጊዜውንም እንረዳ፡፡