January 15, 2025
82 mins read

ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች

“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።” 
መዝሙረ ዳዊት 39:1

Abiy stupid

ወንድሙ መኰንን፣
ኢንግላንድ 15 January 2025

 

መግቢያ

የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን አለበት። ጥሩ ከተናገረ፣ እንደ ኦባማ፣ ታሪካዊ ንግግር ሆኖ ሲወሳለት ይኖራል። ከዘበዘበ መዘባበቻ ይሆናል። አንድ የአገር መሪ ብቃቱ የሚለካው፣ በተግባሩ ብቻ ሳይሆን፣ በምግባሩ፣ በኑሮው፣ በሥነ-ሥርዓቱ፣ በዕውቀቱና በአነጋገሩ ጭምር ነው። እነዚህ ክህሎቶች የሚዳብሩት ደግሞ ከተፈጥሮ ችሎታ ባሻገር፣ በትምህርት፣ በልምድ፣ በዕድሜና፣ እንዲሁም በዙሪያው በከበቡት ችሎታ፣ ዕውቀትና ብስለት ባዳበሩ ባለሙያ አማካሪዎቹ ነው። የበሰለ መሪ፣ የበሰሉትንና አስተዋይ አማካሪዎችን ይሰበስባል። ያልበሰለ መሪ ግን፣ እንደሱ እንጭጮችንና እበላ ባይ አማካሪዎችን ይሰበስባል። ለምሳሌ በመጽሐፍ ቅዱስ፣ ሮብዓም የተባለ እንጭጭ በነገሠ ጊዜ በአባቱ በንጉሥ ሰሎሞን ፊት ይቆሙ የነበሩትን አስተዋይ አዛውንቶችን ትቶ እንደሱ ባሉ ባልበሰሉ ወጠጤ ጎረምሳዎች በመከበቡ እስራኤል ለሁለት የመከፈል አደጋ ደረሰባት (መጽሐፍ-ቅዱስ)። ኢትዮጵያስ ለስንት ትከፈል ይሆን?

በአብዛኛው በአደጉት ታላላቅ አገሮች፣ በሆነ ተአምር ካልሆነ በስተቀር፣ ሁልጊዜም ለአገር መሪነት የሚመረጠው፣ ምራቁን ዋጥ ያደረገ፣ ከጀርባው ብዙ አዎንታዊ ተግባራትን የፈጸመ፣ ለአገሩ በተሰለፈበት መስክ ተጨባጭ ሥራ የሠራ መሆን ይጠበቅበታል። ለምሳሌ፣ አሜሪካን ብንወስድ በዕድሜ የመጨረሻ ትንሹ ፕረዝደንት፣ ሩዝቨልት (Theodore Roosevelt 1909-1913) ሲሆን ፕረደዝንት የሆነው፣ 42 ዓመቱ በአጋጣሚ ነበር። የጦር አመራር ጀግናም ነበር። ለዚህ ከፍተኛ ሹመት የበቃው፣ ፕረዝደንት ዊሊያም ማኪንሌይ (William McKinley 1897-1901) በነፍሰ-ገዳይ ጥይት ሕይወቱ ስላለፈ ምክትሉ መተካት ነበረበት። ታስቦ የነበረው ይኽ የጦር ጀግና ጎልማሳ በምክትልነት ቆይቶ የፕሬዝደንቱ የሥራ ጊዜ ሲያልቅ፣ ሰክኖ፣ ልምድ አካብቶ፣ በራሱ ተወዳድሮ ካሸነፈ ፕረዝደንት ይሆናል ተብሎ ሲጠበቅ ዕድል የራሷን መንገድ ቀይሰችለትና በአቋራጭ ሩዝቨልት ፕረዝደንት ሆነ። ቢሆንም የከበቡት አማካሪዎች ምራቅ የዋጡና አንቱ የሚባሉ ስለነበሩ፣ አንዳችም ከነሱ ምክር ወጥቶየፈጸመው ተግባር አልነበረም። የመጨረሻው ከፍተኛ ዕድሜ የነበረው አሁን ሥልጣን ላይ የሚገኘው ፕርዝደንት ጆ ባይደን ነው (Joe Biden 2021 – incumbent)። ሥልጣን ላይ የወጣው በ78 ዓመቱ ነው። በሚመጣው 20 January 2025 ለሁለተኛ ጊዜ ሥልጣን ላይ ሊቀመጥ የተመረጠው ትራምፕ (Donald Trump) በዓለ ሲመቱ ሲጀምር 78 ዓመት ከ6 ወር ይሞላውና ከባይደን ሊበልጥ ይችላል። በእኛና አፍሪካ አገሮች ግን ያልበሰሉ ጎረምሶች፣ በየጊዜውሥልጣን ላይ እየወጡ፣ አገራቸውን ያምቦጫርቃሉ። ልጅ ያቦካው ለእራት አይበቃም ይባል የለ? ለዚህ ነው የማያልፍልን።

ጠቅላይ ሚኒስትራችን ዳግማዊ ጠቅላይ ሥቃይ ሁኖ ቁጭ ብሏል። ያኔ በወረት መስማት የምንፈልገውን እያወራ ሲመጣ፣ ወያኔ የጫነችብንን የዘረኝነት ቀንበር ይሰብርልናል ብለን ስንጠብቅ፣ የባሰውኑ የኦሮሙማ የጭቆና የገዳ ሥርዓት ቀንበር ደረበብን። ወያኔ በዘር ከፋፈለችን፣ እሱ ደግሞ በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጭንቅላት የሚያስቡትን የኦሮሙማን የበላይነት ቀንበር በህዝቡ ላይ ጫነ። በመግደል፣ በማፈናቀል፣ በማሳደድ፣ በማሠር፣ በማንገላታት ብቻ ሳይሆን፣ አንድ ሰው ጥሮ ግሮ፣ ላቡን አንጠፍጥፎ ሠርቶ ወይም ገዝቶ የኖረበትን ቤት ሳይቀር በላዩ ላይ በማፍረስ፣ ቦታውን ለሚወደው የኦሮሙማ አቀንቃኝ  ሸልሞ፣ ህዝቡን ጎዳና ተዳዳሪ አደረገው። እንደመጣ ኢትዮጵያዊ ሊመስል ሞክሮ ነበር። እየዋለ ሲያድር ግን፣ ከኦነጎችም የከፋ በራሱ ፍቅር የወደቀ ናርሲስት (narcissist) ሁኖት አረፈው።

 

ከአያያዝ ይቀደዳል፣ ከአነጋገር ይፈረዳል።

 

አንድ ብልህ መሪ አብዛኛውን ጊዜ የሚናገረውን፣ መጥነው፣ መዝነው የሚጽፉለት ሊኖሩት ይገባል። ከአያያዝ ይቀደዳል፣ ከአነጋገር ይፈረዳል ይባል የለ? በእንግሊዝኛው “Speech Writers” ይኖሩታል። ትልቅ ሹመት ነው። የአገር መሪ  ሲናገር ፈጽሞ መዘባረቅ የለበትም። ስለዚህ ባለሙያዎች (professionals) ሊቀጠሩለት ይገባል። የራሱን እንኳን ንግግር ማድረግ ሲፈልግ፣ ሊያቀርብ ያሰበውን አሳይቷቸው፣ አስተካክለው ይሰጡታል።  የሌሎችን ሀሳብ እንዴት መጠቀም እንዳለበት ያስተካክሉለታል። አለበለዚያ “ኮራጅ” እየተባለ ጣት ይቀሰርበታል። ለዚህ አልታልደንም። ሰውዬው አመዛዝኖ መናገር አይችልም። አሁን የተናገረውን፣ ከ10 ደቂቃ በኋላ አይደግመውም። በዚህ ምክንያት የሚከተሉትን ለናሙና 10 የተመረጡ ዝብርቅርቅ ንግግሮቹ እንዴት መዘባበቻ እንዳደረጉት እንመልከት። ኩረጃውን ለጊዜው እንርሳ! ማዋረዴ አይደለም። ድንገት ቢታረም ተግሳጽ ነው። ለሚፈልግ፣ የአሥሩም ቪዲዮዎች አሉኝና ጠይቁኝ ላጋራ እችላለሁ።

1) የሕልም እንጀራ!

በሕልም ዓለም ቅዠት፣ እየተጋገረ

ወፋፍራም እንጀራን፣ እንልፈው ጀመር።

 

ድሀ በህልሙ ቅቤ ባይጠጣ እከክ በወረሰው ነበር። ይላል ያገራችን ሰው። ነዳጅ ድፍድፍ ተገኘ ጨፍሩ አሉን። እንኳን ነዳጅ ድፍድፍ ሽታውም አልነበረም። ኢትዮጵያ በስንዴ ምርት እራሷን ቻለች፣ ደንሱ አሉን። ከተመረተ በኋላ፣ ስንዴው ለውጭ አገር ሺያጭ የሚቀርብ ሁኖ ተገኘ። ከተመጽዋችነት ሳንወጣ ቀረን። አንድ ሰሞን ደግሞ፣ አሰብ የኛ ሆነች ተባለና፣ እስክስታ ውረዱ ተባልን። እንደተወራ ቀረ። ከሶማሌ ላንድ ወደብ ተሰጠን ተባልን “ኧረ እሱ ነገር ህጋዊ አይደለም፣ ጣጣ ውስጥ አገሪቱን ይከታል አልን።”የመከላከያ ተሸላሚ የክብር አባላት” ዩትዩበሮች እና ደንገጡሮቻቸው፣ ያዙን ልቀቁን፣ “ወደብ አገኘን፣ ደስ ሲላችሁ ሲገባ እንዴት በአገራችሁ ላይ ትመቀኛላችሁ?” ብለው ድረገጾችን አጣበቧቸው። ትንሽም ሳንቆይ ያልነው ደረሰ። ወፍ የለ፣ ወደብ የለ። በዓለም አቀፍ መድረክ መዘባበቻ ሆን። ጦርነት አንዣበበ፣ ቀኝ ኋላ መዞር መጣ። ይኸ አሳፋሪ ተግባር እንዴት ይሸፈን? የማያፍረው ጠቅላይ ሚኒስትር ታዲያ አሰበበትና በማይመስል ትርክት መጣ። ፊቱን በጨው አጥቦ ያለምንም ማፈር፣ ለአሻንጉሊቶቹ የፓርላማ ኣባላት ጥፋቱን ወደኛ አዙሮ ቁጭ አለ።

ህልም የሌላቸው የሚቃዡ ሰዎች ምን ይላሉ? ይኸውና ቀይ ባህር እናሳካለን ብለው ዓመት ሞላ ሳይሳካ ይላሉ! እኛ እኮ እንኳን በዓመት፣ በሀያ ዓመት ባይሳካም ልጆቻችን ያሳኩታል ነው ያልናቸው። አይሰሙም! ለምን? ህልም አያውቁማ!”

“ቀጣፊ!” ልለው አሰብኩና የአገሬ መሪ መባሉ ትዝ ሲለኝ፣ አፌ ላይ አድርሼ መለስኩት። ምክንያቱም፣ “በኢትዮጵያ እንደኔ የተሰደበ መሪ የለም” ብሎ ስሞታ ሲናገር ሰምቼ አዝኘለት ነዋ! ዝም ባለ አፍ እኮ፣ ዝምብ አይገባበትም!ይባላል። በቃ አልተሳካም ብሎ ዝም ቢልስ! ሆነልኝ ብሎ ታምቡር ካስመታ በኋላ፣ “ከሀያ ዓመት በኋላ ነው ያልኩት”፣ ከሚለን አፉን ዘግቶ፣ እንደልማዱ ወደ ችግኝ ወደ መትከሉ ቢሄድ ያዘናጋን ነበር። ባህር በር ተገኘ አይደል እንዴ የተባልነው። ሾርት ሚሞሪ ነበር ያለን?

ስለጠቅላይ ምንስትሩ ህልም ሳስብ፣ አንድ ሰው የተገጠመው ግጥም ትዝ አለኝ።

ስስምሽ ስላደርኩ፥ ትላንት በህልሜ፣

ዛሬ ቶሎ ተኛሁ፥ ልሰምሽ ደግሜ።

ታዲያ ምን ያደርጋል!

የህልሜ ደራሲ፥ አትታደል ቢለኝ፣

ህልሜን ገለባብጦ፥ ሲስሙሽ አሳየኝ።

 

አንድ ሰው ለማለም መጀመሪያ መተኛት አለበት። አገራችን አደጋ ውስጥ ሁና መች ልንተኛ! ሰው በቁሙ ህልም አያይም። ይኸ ዕውነታ ሊታመን ይገባል። በሕልሙ ሲደሰት አድሮ፥ ሲነቃ በገሀዱ ዓለም አስደሳች ነገር ሳይኖር ይከፋዋል። ለምን ነቃሁ ይላል። ባዶነት ይሰማዋል! እየተበሳጨ መዋል ነው። የአዕምሮ በሽታም ሊያመጣ ይችላል። ይኸ የአገሪቱ መሪ ህዝቡን የህልም እንጀራ ሊመግበው ያምረዋል። የህልም እንጀራ ደሞ አያጠግብም። ክውሸቱ ጭካኔው፣ ከጭካኔው ውሸቱ! 

 

አንዲት ዓይታው ዓይታው ስልችት ያላት ወጣት እንዲህ ስትል አሾፈችበት።

 

ማመስገን የምፈልገው እኔ፣ አባታችን ብላቸው ቅር አይለኝም። አባታችን ዶክተር ዐቢይን … አመሰግናለሁኝ። በተለይ በቃ ሳንጠይቅ የሚያደርጉትን ነገር። አሁን እኛ ስለዳቦ፣ … ዳቦ ራበን ብለን ብንጠይቅ፣ እሳቸው ደሞ፣ የዳቦን አመጣጥ፣ ዳቦ ለምን እንደሚያስፈልግ፣ የአሜሪካው ዳቦ ከኡጋንዳው ዳቦ በምን እንደሚለይ፣ ባንበላ እራሱ፣ ችግር እንደሌለው እያስረዱ ስለሚያጠግቡን እግዚአብሔር ይስጦት እላለሁኝ። እንደአባት ደሞ፣ … እኔ እንደአባት የምለው ደሞ ይቆጣል አይደል? ቤተሰብ ይቆጣናል። እንደአባት ደሞ እናነተ ሾርት ሚሞሪ ያላችሁ  ልጆች እያሉን፣ እየተቆጡን፣ ደንገጥ እንድንል ስለሚያደርጉን፣ እንዲያው ቤተሰብ እንዳለን ስለሚሰማን አመሰግናለሁኝ።

 

የፒተር ፓንን (Peter Pan) ፊልም አይታችኋል? እነዚያ ህጻናት ተሰባስበው የምናብ (imaginary) ምግብ ሲያነክቱ?! በልጆች የዕቃ-ዕቃ ጨዋታ ሊያታልለን ሲሞክር ያናድዳል! ህልም የሚታመን ነገር ሊሆን አይችልም። ህልም ተግባራዊ አይሆንም። ራዕይ ነው ታስቦበት ተግባራዊ የሚሆነው።

2ኛ) ዶሮ አርቢዋ የጤና ባለሙያ

ግራ የሚይጋባ ጉድ እዩ፡

“አንድ የጤና … ሙያተኛ የሆነች ሴት፣ ከሥራዋ በተጓዳኝ፣ 40 ዶሮ፣ 50 ዶሮ፣ በቤቷ ውስጥ በዚያች ትንሽ ቦክስ ቢኖራት፣ በቀን 20፣ 30፣ 40 ዕንቁላል ብታመርት፣ ማሩ ሲጨመር፣ ዓሣው ሲጨመር፣ ወተቱ ሲጨመር፣ በቤት በቂ ምግብ ስላለ፣ በሥራ ከሚገኘው ገንዘብ፣ ተጨማሪ ማጣፈጫ ይሆናል ማለት ነው።”

“ጉድ በል ጎንደር!” አለ ያገሬ ሰው! ይኸን ሰው ሳስበው አንድ ነገር ትዝ ይለኛል። “ቡና የለም እንጂ፣ ከሰል ቢኖር የዶሮ ዓይን የመሰለች ቡና አፈላልህ ነበር” አለች ድኃይቱ! ይኸንን አባባል፣ ሌላ ጊዜ እጠቀምበታለሁ፣ ደግሜ! የጤና ባለሙያዋ፣ የዶሮ ዕርባታ ባለሙያ ስትሆን ይታያችሁ። ትምህርቱንም መውሰድ ነበረባት ማለት ነው? እሷ ዶሮ አርቢ ስትሆን፣ ህክምናውን ማን ሊሸፍንላት ነው? ኧረ እየተስተዋለ! በዚያ ትንሽ ቤት ውስጥ ከዶሮዎቹ ጋር በደባልነት ስትኖር፣ የ40 ዶሮ ኩስ ስትጠርግ ታየችኝ እኮ! ቆዩኝማ! እሺ ዶሮዋንስ አቅፋ በኪራይ ቤት ትደር እንበል፣ ማሩ፣ ዓሣው እና ወተቱ ከሰማይ ቤት እንደመና እየተግተለተለ ሊወርድላት ነው ወይስ ከሥራው በተጓዳኝነት፣ ንብም ታርባ፣ ዓሣም ታስግር፣ ላምም ታርባ ሊለን ፈልጎ ነው? ምነው የሚመስል ወሬ ቢያወራ! አንድ ጊዜ ማን እንዳናደደው አላውቅም “ምን ዓይነቱ ጀዝባ ነው!” ሲል ሰማሁት መሰለኝ። “ጀዝባ” ምን እንደሆነ ባላውቅም፣ በዚህ ላይ ሽንኩርት በየመሥሪያ ቤቱ መመረት እንዳለበት የሰጠውን መመሪያ ስናክልበት፣ “ማነው ጀዝባ?” ያሰኘናል። መሪያችንን ደፈረ እያሉ ደንገጦሮቹ ሲጨፍሩ ታየኝ። እኔ ላይ ከማላዘናችሁ በፊት እሱ ክብሩን ይጠብቅ!

3ኝ) አንድ ዓመት ብትዋጉን አታሸንፉንም!

ሳያስበው በጀብደኝነት ጦሩን ልኮ፣ በአስራ አምስት ቀን ትጥቁን ብቻ ሳይሆን ሱሪውንም አስወልቀዋለሁ ብሎ ዘሎ የገባበት ጦርነት እንዳሰበው፣ እንዳሳመረው ፓርክ ውስጥ መንሸርሸር ያህል ሳይቀለው ሲቀር ዓይኑን በጨው አጥቦ፣ እንዲህ አለን።

ደጋግሜ እንዳነሳሁት፣ በኦሮሚያ ክልል፣ በአማራ ክልል ያሉ፣ ወንድሞቻችን፣ አንድ ዓመት ቢታገሉ ስለማያሸንፉ፣ አንድ ዓመት ቢወድቁ ቢነሱ ለውጥ ስለማያመጡ፣ ያኛውን መንገድ ጥለው ወደ ሰላም እንዲመጡ፣ በዚህ በተከበረ ጉባዔ በድጋሚ ጥሪ አቀርብላቸዋለሁ።

አንድ ቀልድ ትዝ አለኝ። እስቲ እንዝናናበት። አንድ ጠና ያሉ ሀብታም ሰው፣ ቆንጂዬ ኮረዳ አግብተው ይኖሩ ነበር። ብዙ ጊዜ ለሥራ ወጣ ብለው ይመለሳሉ። አንድ ቀን ታማኝነቷን ለማረጋገጥ ሩቅ ቦታ እንደሚኼዱና አድረው እንደሚመለሱ ነግረዋት ተሰናብተዋት ወጡ። ለትንሽ ሰዓታት ከኼዱ በኋላ፣ ተመለሱ። ድምጻቸውን አጥፍተው በጓሮ በር ገቡ። ቤቱ ጸጥ ብሎ ነበርና በቀጥታ ወደ መኝታ ቤታቸው ዘው አሉ። አንድ ጎረምሳና ሚስታቸው ተቃቅፈው እንደተኙ እጅ ከፍንጅ ያዟቸው። ሁለቱ ወንዶች ትግል ገጥመው ተናነቁ። እንግዳው ጎረምሳ ወደማሸነፉ ተቃረበ። አዛውንቱ ዞር ብለው ሲያዩ ከፍቅር ጨዋታቸው በፊት ለምግብና ለመጠጥ ወጥተው የተደረደሩትን በጣም ውድ ውድ የሆኑ ሰሀኖች፣ ሲኒዎች፣ ክርስታል ብርጭቆዎችን አስተዋሉ። ታዲያ፣ሰሀኑን አንሺው! ብርጭቆውን አንሺው፣ ሲኒውን አንሺው!” ይሏት ገቡ። ሚስትየዋ ግራ ተጋብታውይ! በሞቴ! ሊወድቁ ነው?” አለቻቸው። ሰውዬው ንድድ ብሏቸው፣የለም! የለም! አንቺ ባመጣሽው ጣጣ ተገትሬልሽ ላድር ኑሯል!” አሏት ይባላል።

“ይሞታል እንዴ?!” አለች አንዲት የምወዳት እህቴ! ትላንትና ወደ አማራው ሲዘምት እኮ፣ በ15 ቀን ውስጥ ትጥቁን ብቻ ሳይሆን፣ ሱሪውን እናስፈታለን ብሎ ፎክሮ አልነበር የኦህዴድን መከላከያ ያዘመተው? ካልተሳካስ? ምን ችግር አለው እንደ ወደቡ ፍጥጥ ብሎ ማራዘም ነዋ! ምነው አሥራ አምስቱን ቀን ወደ ሺ ዓመት አራዘመው?! ለምን ይሆን “Not in a million years” አለ የተባለው እዚህ ላይ ትዝ ያለኝ? በ15 ቀን ባንጨርሰው፣ ልጆቻችን በሺ ዓመት ያሸንፋሉ ማለት ይችላል። ምን ችግር አለው፣ ሁሉ በእጁ ሁሉ በደጁ! ግን፣ የሱሪዋ ነገር እንዳላየ ታለፈች አይደል? ነገ ረጋፊ መሆኑን ተረሳው።

ይኸ ሰው፣ ህዝቡን ሲገድሉት፣ ሲያስሩት፣ ሲያሳድዱት ቁጭ ብሎ እስኪጨርሱት መጠበቅ አለበት ብሎ ያምናል መሰለኝ።  ግድግዳን ገፍተኸው ገፍተኸው ማለፍ አትችልም ሰውዬ! መልሶ ይገፋሀል! ይኸ የፊዚክስ ሕግ ነው። ጦርነቱም ሆነ ማንኛው በኢትዮጵያ ላይ የሚደርሰው ግፍ እሱ ባመጣው ጣጣ መሆኑን ግን ማን በነገረው? 

ድንቄም ጠቅላይ  ሚኒስትር! ለመሆኑ፣ የትኛው ፕላኔት ላይ ነው የሚኖረው? እኛን “Short memory” አለን እንጂ፣ ከቀን በፊት ያለውን የማያስታውስ ፍጡር ነው። አሳዳጊው ሕወህት/ወያኔ እኮ 17 ዓመት ተዋግቶ ነበር፣ ዝሆን የማያገፋውን ጦር ገዝግዞ ደርግን የጣለው! ህዝብን አታሸንፍም በሉት!! የኢትዮጵያ ህዝብ 27 ዓመታት ታግሎ ነው ወያኔን የተገላገለው። የሦሪያው ፕረዝደንት ባሻር አልአሳድ ዲሰምበር 8 ቀን 2024 በኃይል መገርሰሱን ጆሮውን በጥጥ ደፍኖ አልሰማ ካላለ እንጂ ሁኗል፣ ተፈጽሟል።

የአማራ ጥላቻው ግርም ይለኛል። ልጆቹ እኮ ግማሽ አማራ ናቸው። ወያኔ ሲያሳድደው በቤቱ ደብቆ ያተረፈው እኮ አማራ የሆነ ሰው ነው። ከአሳዳጊው ወያኔ ጋር የገጠመውን ማን ነበር ያሸነፈለት? ከመከላከያ ቀድሞ ምሽግ እየደረመሰ፣ እራሱን እየሰዋ፣ ወያኔን ወደመጣችበት የሰደደለት ማን ነበር? ሾርት ሜሞሪ ማለት ይኸ ነው ወዳጄ! አሁንስ ቆሌው ርቆታል። 

በጣም ከገረመኝ ንግግሩ፣ “በሰላም መታገሉ ነው የሚያዋጣቸው” ማለቱ ነው። በሰላም የታገሉትማ አዋሽ አርባና ቅሊንጦ እሥር ቤት እየማቀቁ ናቸው። እነ ክርስቲያን ታደለ፣ ዮሐንስ ያለው፣ መስክረም አበራ፣ ታዲዮስ ታንቱ፣ ገነት አስማማው፣ በሰላም ታግለው ምን እንዳጋጠማቸው እያየን እኮ ነው። ታየ ዳንዳአን ክፉ ተናገረኝ ብሎ፣ ምን እንደ ገጠመው አይተናል። በጠብመንጃ የተፋለሙትማ፣ እነስብሀት ነጋ በክብር ተሸኝተው በአሜሪካ በኩራት ይንቀባረራሉ። ከፍ ዝቅ እያደረጉ ሲያዋርዱት የነበሩት፣ እኔ ጌታቸው ረዳ ተሹመው ተሸልመው አገር ውስጥ ይንፈላሰሳሉ። ሰሞኑን እንኳን፣ ህዝብን ሲፈጁ የነበሩት እነ ጃል ሰኚና ጓደኞቹ ለሹመት በቅተዋል። በሰላም ኢትዮጵያ ውስጥ መታገል፣ ለአሳር ነው። 

4ኛ) ሳናጣራ አናስርም

ለሥልጣን በበቃ ማግስት፣ በስሜት ቃል የገባውን ሁሉ አንድ በአንድ ክዷል። በኢትዮጵያ ባህል፣ ቃል ማፍረስ ነውር ነው። ሎሪየት ጸጋዬ ገብረመድኅን ስለ ቃል እንዲህ ብለው ነበር። “ቃል የዕምነት ዕዳ ነው እንጂ፣ ያባት እናት እኮ አይደለም።” ይኸኛው ደሞ ቃል ኪዳን ገብቶልን ካፈረሳቸው አንዱ አብረን እንይ።

እንደ ከዚህ በፊቱ፣ አስረን ከምናጣራ፣ አጣርተን ብናስር ብለን ነው። አንድ ንጹህ ሰው ከሚታሰር ለፍትህ ሲባል መቶ ወንጀልኛ መፍታት ይሻላል ይባላል።

ጽድቁ ቀርቶብኝ በቅጡ በኰነነኝ ይባላል። ነገር ማሳመር ሲችልበት! ለመሆኑ በጅምላ እየታፈሱ፣ አዋሽ አርባና ቅሊንጦ እንዲሁም ድብቅ እስር ቤቶች አዲስ አበባ ውስጥ የሚማቅቁ ጋዜጠኞችና ንፁሀን የአማራ ተወላጆች አጣርተን ነው ያሠርነውሊለን እንዳይሆን የበሻሻው አራዳ? ጅምላ እሥሩ እኮ፣ ከኛ ከባለጉዳዮች አልፎ፣ የዓለም አቀፍ ሚዲያዎችንና፣ የዓለም አቀፍ ሰባዓዊ መብት ተሟጎቾችን ሁሉ ያሳሰበ ጉዳይ ሁኗል። November 6, 2024 የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ዘገባ ብቻ ማንበብ ይበቃል (Amnesty, 06 November 2024)። በተግባር የሚሠራውን እያየን “ዓይናችሁን ጨፍኑ ላሞኛችሁ ነው” ማለቱ ነው። ከሰሞኑ፣ እነ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤን (ኢሰመጉ)፣ የሕግ ባለሙያዎች ሰብዓዊ መብቶች፣ የመብቶችና ዲሞክራሲ ዕድገት ማዕከል፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕክል መሣሪያ አንስተው ተዋግተው ነው የታገዱት? ሰው ምን ይለኛል አይልም እንዴ!

5ኛ) “አዲስ አበባ ውስጥ ኦሮሞ ጠል አስተሳሰብ አለ”

ሕዝብን አክብሮ እንጂ፣ አዋርዶ ሰድቦ ለማስተዳደር የደፈረ፣ አንድም መሪ አይቼ አላውቅም። የንጉሡንም አስተዳደር ደርሼበታለሁ አላደረጉትም። ጄኔራል አማን አንዶምም አላደረጉትም። መንግስቱ ኃይለማሪያምም አላደረገውም። ኧረ መለስም፣ ኃይለማርያም ደሳለኝም አላደረጉትም። 

የጉራጌን ህዝብ በጅምላ ሲሰድብ ያየነው፣ ዐቢይ አህመድ አሊ ነው። “የጉራጌ ህዝብ፣ ማንም የሚጭነው፣ የኅዳር አህያ ነው” አለ። ስለእሱ እኛ ተሸማቀቅን። “የኢትዮጵያን ህዝብ ከማስተዳደር ሺ ጉንዳን በጫንቃ ተሸክሞ መሄድ ይቀላል” አለ። አሁን ደግሞ፣ የአዲስ አበባን ህዝብ ሙልጭ አድርጎ እንዲህ ሲል ሰደበው።

“አዲስ አበባ ላይ ከፍተኛ ኦሮሞ ጠል ኃይሎች፣ ኦሮሞን የሚጠሉ፣ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ መኖር የሚያስቡ ሰዎች፣ “ኦሮምኛ ተዘመረ አሉ። የግሪክ ትምህርት ቤት አለ አዲስ አበባ ውስጥ፣ ሊሴ አለ፣ ፈረንሳይ ትምህርት ቤት፣ ጣሊያን ትምህርት ቤት አለ፣ ጀርመን አለ፣ ማሪፍ አለ፣ ኢንተርናሽናል ኮሙዩኒቲ ስኵል አለ። ይኸ ሁሉ በቋንቋው ነው የሚዘምረው። ሊሴ ሲዘምር ያላመመው ኢትዮጵያዊ በኦሮኛ ሲዘመር የሚያመው ኢትዮጵያዊ ምን ኢትዮጵያዊ ይባላል? ኢትዮጵያዊ ነው ይኸ? በዚያ ደረጃ ጥላቻ ጥሩ አይደለም። ኦሮሚያን ለአዲስ አበባ ውሀ አላመጣህም ብለን የምጮህበት፣ ቆሻሻ ሲደፋበት እያየን የተቀበልን፣ ኦሮምኛ ሲሰማ የሚጎረብጠን ከሆነ እንዴት በጋራ እንኖራለን።”

አይባልም! ድንቄም! አስረድቶ ልቡ ውልቅ ብሏል። አንድ በአንድ ቃላቶቹን እንሰንጥቅለት። በመጀመሪያ ደረጃ፣ አንድ የአገር መሪ እንዲህ የወረደ ንግግር ከአፉ ይወጣል ተብሎ አይጠበቅበትም። ነውር ነው! ቀጥሎ የአዲስ አበባ ሕዝብ፣ ዘር ብሎ ነገር አያውቅም። ኦህዴዶች ዘረኝነታቸውን በግድ ልትጭኑበት ሲትነሱ “እምቢዮ” ማለቱ በኦሮሞ ጠቅላይ ሚኒስትር “ከኦሮሞ ጠልነት” ሊያስፈርጀው አይችልም። የአዲስ አበባ ህዝብ ዘረኛን ይጠላል። አይፈረድበትም። ዘረኝነት ውዳቂ አስተሳሰብ ነው። ጥንብ ነው።

ዐቢይ አህመድ አሊ ኦሮሞ መሆኑን ከመጀመሪያው ጀምሮ የአዲስ አበባ ህዝብ ግጥም አድርጎ ያውቃል። ኦሮሞ መሆኑን ስላላወቀ ነበር ያንን ሁሉ ፍቅር ያለ ገደብ የቸረው? የአዲስ አበባ ህዝብ እነዚህ ዘረኞች በጉልበት የአንድ ጎሳ የዘረኝነት መርዝ አትግቱኝም ነው ያለው። አዲስ አበባ ወለጋ አይደለም። ሰውን እንደሰውነት ተቀብሎ ወንድሜ፣ እህቴ እያለ የሚኖር የሜትሮፖሊታን ህዝብ ዘረኝነትን ይጸየፋል።  

እስቲ ሰኔ 10 ቀን 2010 (23 June 2018) እናስታውሰው። ያችን መስቀል አደባባይ በህይወቱ ላይ በራሱ ሰዎች የቦምብ ጥቃቷን ረስቷት ይሆን? የአዲስ አበባ ህዝብ ኦሮሞ ጠሊታ በመሆኑ ነበር እንዴ፣ ሁለት ኗሪዎቿ ህይወታቸው የሰዉለትና 44 ሰዎች ቆስለው ህይወቱን ያተረፉለት?! ምስጋና ቢስ!!! 10/10/10 መሆኑን ልብ በሉ። እሱ ቢረሳው እኛ አንረሳም፡፡ የሚረሳ ቁጥር አይደለም።

የግሪክም ሆነ፣ ሊሴም ሆነ፣ ጣሊያንም ሆነ፣ ጀርመንም ሆነ፣ ማሪፍም ሆነ፣ ኢንተርናሽናል ኮሙዩኒቲ ስኵልም ሆነ በቋንቋቸው በግል ትምርት ቤታቸው ይዘምራሉ። የግል ትምህርት ቤት ነዋ! ወላጆች ፈቅደው ፈልገው፣ ገንዘባቸው ከፍለው ነው እዚያ ትምህርት ቤት ልጆቻቸውን የሚያስተምሩት። የኛዎቹ ባለጊዜዎች ኦሮሞዎቹ እኮ፣ የጋራ በሆነው በየመንግሥት ትምህርት መዝሙራችን ካልተዘመረ፣ ባንዲራችን ካልተሰቀለ ነበር ያሉት። የማንኛውም ብሔረሰብ ህዝባዊ መዝሙር ነው በፌዴራሉ መቀመጫ ከተማ ሲዘመር ያዩት? የአማራ ነው? የአፋሩ ነው? የሱማሌው ነው፣ የሐረሬው ነው፣  የሲዳማው ነው?  የቤኒ ሻንጉል ግሙዙ ነው ወይስ የደቡቡ? እደግመዋለሁ! በፈቃደኝነት ሳይሆን ሊያስገደዱት እኮ ነው የሞከሩት። በኦሮምኛ ብቻ የሚያስተምሩ ትምህርት ቤቶች ካሉ፣ እዚያ ኦሮሙማቸው ያድርጉ። መስመር አትለፉ፣ ዘረኛ አታድርጉን ማለቱ “ኦሮሞ ጠል” ያሰኘዋል? አዲስ አበባን ለመንጠቅ ከታቀደው አንዱ ስግብግብነት፣ የተጠነሰሰች ሴራ መሆኗን የአራዳ ልጅ ያውቀዋል። የአዲስ አበባ ህዝብ ነቅቶበታል። አዲስ አበባ በግድም በወድም ተነጥቃ “ፊንፊኔ ኦሮሚያ” እስካልሆነች ድረስ፣ የማይታሰብ ሙክራ ነው። እስከ መጨረሻው ይፋለማቸዋል። የዐቢይ ድንፋታ የሚያስከትለው፣ እመኑኝ የሥልጣኑ ማብቂያ ደወል ነው። አዲስ አበባ ክሥሩ ተንሸራተተች ማለት፣ የመንበሩ መፈንገል ትንቢታዊ ምልክት ነው።

16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን፣ አንድን ሕብረተሰብ ወረው ካንበረከኩት በኋላ፣ ኦሮሞዎች ያደርጉ የነበሩት ግፍ አለ። እሱም የተሸነፈውን ወገን በኦሮምኛ እንዲዘፍን ያስገድዱት  ነበር። በቋንቋቸው “ሲርባ ጊዲ!” ይሉታል። “የግድ ዘፈን!” ማለት ነው። አሁንም የአዲስ አበባን ህዝብ አስገድደው የዘረኛ መዝሙራቸውን ሊያስዘምሩት ነዋ ህልማቸው! አዲስ አበቤው ታክስ እየከፈለ በሚያስተምርበት የመንግሥት ትምህርት ቤት ውስጥ የሚፈልገውን ይበል፣ በጋራ የመንግሥት ትምህርት ቤት ውስጥ አይታሰብም። ይኸ ዓይነቱ ግፍ በአዲስ አበባ ህዝብ ላይ ሊፈጸም እንዴት ተሞከረ? ደግሞ መዝሙራቸው የጥላቻ መዝሙር እኮ ነው። ሲተረጎም እንዲህ ነው የሚለው!

ኦሮሚያ፣ ኦሮሚያ፣ የትልቅ ታሪክ ባለቤት

የኦሮሞዎች ማዕከል፣ የገዳ ሥርዓት ማህደር

የሕግና ሥርዓት ምድር፣ የጨፌ ኦዳ እናት

የታደለች ለምለሚቷ፣ ሁሉን አብቃይ

የመቶ ዓመት ግፍን፣ በደም አጠብንልሽ 

በውድ መስዋዕትነት፣ ሰንደቅሽን ከፍ አደረግን

ደስ ብሎናል ደስ ይበልሽ፣ ገዳችንን አስመልሰን

ሰላምና ዲሞክራሲ፣ ሰብዓዊ መብት

አስተማማኝ ልማት፣ ፈጣን ዕድገት

ከሌሎች ህዝቦች ጋርም፣ በፍቅርና በአንድነት

ለመኖር ዋስትና፣ ጽኑ ዓላማ አድርገን

በኃይላችን አንድ አድርገን፣ ተነስተናል ተመኚልን

ኦሮሚያ ልምላሜ፣ ብልጽግና ኑሪ!

 

ቁም ነገሩ በኦሮምኛ ዘፈን ስንጨፍር ነው የኖርነው። በውድ እንጂ በግድ ሲጫንማ ወዲያልኝ ወዲያ! በውስጡ ያሉትን መርዝ ማየት ያስፈልጋል። “የመቶ ዓመት ግፍን በደማችን አጠብንልሽ” የሚል ጉድ! የምን ግፍ ነው የሚያወሩት። ባለፉት መቶ ዓመታት ውስጥ ምን ግፍ ተፈጸመባቸው? የምን ደም ነው ዘምሩልን የሚሉት? ላለፉት 50 ዓመታት አንዴ መኢሶን ውስጥ ተሰግስገው፣ አንዴ ደርግ ውስጥ ተሰግሰገው፣ ሌላ ጊዜ ወያኔ በፈጠረላቸው ኦህዴዳቸው፣ አሁን ደግሞ በብልጽግና ያአማራውን፣ የጋሞውን፣ የወላይታውን ደም ሲያፈሱ የነበሩት እነሱ ሁነው፣ የአዞ እምባ ሊረጩብን ተነሱ! “በኃይላችን አንድ አድርገን” የሚልም ቃል ይገኝበታል። በፍቅርማ መኖር ከፈለጉ፣ የዘር ማጽዳት በወለጋና በመሳሰሉት ማጽዳት ዘማቻቸውን ባልፈጸሙ ነበር። ያንን አዲስ አበባ ላይ ሊደግሙት?! ቡና በኦሮሚያ ተገኘ የሚሉትን ትርክት እየሰማን ነው። ክትፎ የኦሮሞ ባህላዊ ምግብ ነው ሲሉም ሰማናቸው። ባዲስ አበባ በፍቅር መኖር ህዝቡን ምን ገዶት! የ16ኛውን የጭካኔ እጃቸውን መልሰው ሊያነሱበት ሲነሱ “ክላ” ቢላቸው ይፈረድበታል? ክፋታቸው መልሶ ባርቆባቸው ነው። የአዲስ አበባ ህዝብ እኮ በየቀኑ የሽመልስ አብዲሳን ንግግር ይከታተላል። ለአዲስ አበባ የደገሰውን እልቂት በተጠንቀቅ እየተጠባበቀ ነው። ሸገር ተብሎ ተቀርፎ የከበበውንም የእሳት ግንብ ይረዳል። “ፊንፊኔ ኬኛ” እየተባለ የሚፎከርበትንም በትዕግስት ያስተውላል። ትላንት ቡራዩ ላይ ጋሞዎችን የጨፈጨፉትንም አልረሳም። ወለጋ ውስጥ የተጨፈጨፉትንም አልረሳም። በገዛ እጃቸው ሀጫሉን ገድለው፣ በሻሸማኔ፣ በዝዋይ፣ ያረዷቸውን ሁሉ የአዲስ አበባ ህዝብ ያውቃል። አሁንም በአዲስ አበባ ቤቱን ሁሉ በላዩ ላይ የሚያፈሱትን የኦህዴድ ባለሥልጣኖች እያየና እየሰማ የግድ አፍቅሩኝ ነው? ክፉን ከወደደ የጠላ ነገደ! 

 

አንድ የኦህዴድ ባልሥልጣን ኢቲቪ  ላይ ቀርቦ ስለሚፈርሱት ቤቶች እንዲህ አለ፡

 

“አሁን፣ የሚገርመው እኮ፣ ከትግበራው በፊት መለየት ሁሉ አለ ስንለይ እራሱ ያውቃሉ። እንወያያለን፣ ከተወያየን በኋላ ማኅበረሰቡ እያለ ያምናል። ሕገወጥ ነው በቃ ብለው ያምናሉ። ከዚያ ካመኑ በኋላ ወደ መለየቱ ይኬዳል። አሁን ቅድም አልፎ አልፎ የሚባለው፣ ይታለፋል ምናምን ነገር አንዳንዴ ጊዜ፣ ኢንዲጂነስ የሆነውን ማኅበርሰብ አናፈርስበትም።” 

https://www.facebook.com/watch/?v=2022652128175165&rdid=nls47Vg4voWrB5d3

 

እንዲህ ነው እንጂ! ኢንዲጂነስ የሚባለው ምርጡ ዘር ኦሮሞ መሆኑ ነው? የሚሉሽን በሰማሽ ገበያ ባልወጣሽ ይባላል። አረብ ፋቂ (Arab-Faqih, 2003) የተባለው የመኒ፣ አህመድ ኢብን ኢብራሂም አል ጋዚ (Ahmad ibn Ibrahim al-Ghazi)፣ በተለምዶ ግራኝ አህመድን ጦር እየተከተለ በዘገበው ዜና መዋዕል መጽሐፉ ላይ፣ በረራ (ያሁኗ አዲስ አበባ) ትግራይ እስኪደረስ፣ አንድም ቦታ “ኦሮሞ” ወይም “ጋላ” የሚል ቃል አታገኙበትም። ኦሮሞ ከኋላው እየተከተለው ስለነበረ አላጋጠሙትማ! የያኔው በረራ የአሁኑ አዲስ አበባ የአጼ ልብነድንግል መናገሻ ከተማ እንደነበረች ማንኛውም የታሪክ ምሑር የሚያውቀው ሐቅ ነው። አጼ ምንሊክና እቴጌ ጣይቱ ናቸው ዳግም አዲስ አበባን ከመቃበር ያነሷት። ምርቱን ለገበያ ለማቅረብ ወደ ንጉሡ ከተማ ዙሪያ የሠፈረው ኋላ-መጥ ኦሮሞ እንዲጂነስ ሁኖ፣ የአያት ቅደመ አያቱ አጽመ ርስት ላይ የሚኖረው “መጤ” ከተባለ በገዛ ዳቦዬ ልብ ልቡን አጣሁት የሚባለው ዓይነት ግፍ ያንገፈፋል። “ሲርባ ጊዲ” ማለት ይኸ እኮ ነው። አስገድዶ ከመድፈር ምን ለየው? ባሰ እንጂ!

 

6ኛ) የአካም ኦልቴ ነገር

 

አሁንም፣ ስለ ኦሮምኛ! ይኸ ሰውዬ፣ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር መሆን አልነበረበትም። ምክንያቱም፣ ኢትዮጵያ ሳትሆን አልፋውና ኦሜጋው፣ ኦሮሚያ ናታ! የኦሮሚያ ነገር ብቻ ነው የሚጨንቀው። እንዲህ አለን።

 

“አማሮች ደፈር ብላችሁ ‘አካም ኦልቴ’ ማለት መጀመር አለባችሁ።”

 

ጉድ ፈላ! ልክ ቀደም ብዬ የነገርኳችሁ “ሲርባ ጊዲ” ተመልሶ መጣ። የአሥራ ስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ግፍ ዓይኑን አፍጥጦ መጣባችሁ አማሮች! እንደዚያ ኦሮሞነቱ ካልበለጠበት ምነው፣ “ዲጎ ቤቴ? በሉ አላለን? “ኬሮ ሆሲቶ” በሉ አላለን? ለምን_”ፈያዲያይ” በሉ አልተባልንም? ለምን “ፈያ ወክሙ” በሉ አልተባልንም? “ኬሬ ሆሲኒ”ም እኮ ከቋንቋችን አንዱ ነው። 86 የኢትዮጵያ ቋንቋዎች እኮ አሉን። አማሮች በሄዱበት የአካባቢውን ቋንቋ በፈቃዳቸው በደስታ ነው ተምረው የሚናገሩት። አስገድዶ አንድም ነገር የሚፈጽም የለም። በግድ? እንዲህ የሚል ህግ በቅርቡ እንጠብቅ። “በብልጽግና ዘመን፣ ሁሉም ብሔረሰቦች እኩል ናቸው። አንዳንድ ብሔረሰቦች ግን ከሁሉም በበለጠ እኩል ናቸው”። 

 

ይኸ ሰው ሊመከር የሚገባው አንድ ነገር ቢኖር፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ፣ አማራው ብቻ ሳይሆን ሌሎች ብሔረሰቦች (ብሔር አላልኩም፣ ልብ በሉ። ብሔር አገር ነው) እንዲህ የሚንገበገብበትን ኦሮምኛን የሚማሩለት የሱን ፍላጎት ለማሟላት ሳይሆን፣ ፈቅደው፣ ፈልገው፣ ወደው ነው መሆን ያለበት። ይኸ ሰውዬ፣ በዚህ ቢያበቃስ! ቀጠለ።

 

7ኛ) “አማሮች ኦሮምኛ መማር አለባቸው”

 

አሁንም ኦሮምኛ ለሦስተኛ ጊዜ። ብሶበታል! እንዴት ነው፣ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ነኝ የሚል ግለሰብ የኦሮሞ ነገር ከምንም በላይ የሚቆጠቁጠው? በኦሮምኛ “አካም ኦልቴ በሉ”፣ ኦሮሚኛ ተማሩ፣ በኦሮሚኛ ዝምሩ …። ካልሆነ ኦሮሞ ጠል ናችሁ ይለናል። ግን ሌሎች ብሔርሰቦች በኦሮምያ ሲጨፈጨፉ፣ ሲፈናቀሉ፣ ሲሰደዱ፣ ቅንጣት ያህል አይሰማውም። አቅጣጫ ለማስቀየር ችግኝ ተከላ ይወጣና፣ ካድሬዎቹን ያንን አስጩሁ የሚል ትዕዛዝ ይሰጠቸዋል። እንዲህ ተባልን፡

 

“በአማራ ክልል የኦሮኛ ትምህርት መጀመር አለበት። አማራ ክልል ኦሮኛ ለማስተማር፣ በፍጥነት ካልወሰነ የሆነ ጊዜ ላይ አንድ መሆን አስቸጋሪ ጉዳይ ነው። ከኦሮሚያ ክልል ቀጥሎ፣ ሰፊ የኦሮሞ ህዝብ ያለው አማራ ክልል ውስጥ ነው። በዞን የተደረጀ አለ፣ ከዚያም በላይ ቅድም እንዳነሳሁት ጎንደር ውስጥ ጎራድ (?) አለ፣ ጎጃም በጣም በርካታ ኦሮሞ አለ፣ ወሎ በርካታ ኦሮሞ አለ፣ ሸዋም እንደዚሁ የተቀላቀለ ነው። ብዙ ኦሮሞው ያለዉም እዚሁ ክልል ነው። አማራ ክልል ኦሮኛ ለማስተማር በፍጥነት ካልወሰነ እዚህም እዚያም  የተለያየ ቋንቋ እየተናገርን፣ የተለያየ ባህል እየገነባን፣ የተለያየ ማንነት እየገነባን የሆነ ግዜ ላይ አንድ ላይ መሆን አስቸጋሪ ነው፣ ጉዳይ ነው።”

 

ለዘመናት ከነበሩት መንግሥታት መሪዎች ተለይቶ፣ ይኽ ድንቅ ምስጢር እንዴት ተገለጠለት ጃል?! በመርዝ የተለውሰ ማር ዓይነት ንግግር ነው። ሁለት እኵይ ዓላማ አለው። አንዱ ልክ ኦሮሚያ ውስጥ ኦሮሞዎች በዘር ፖሊቲካ ተነስተው ከክልላቸው አማራውን ከቤት ንብረቱ  ሲያፈናቅሉት፣ አማራ ክልል የሚኖሩት ኦሮሞዎች በሰላም መኖራቸው ያበሳጨው ይመስላል። ለዚህ ሰው፣ አማራውና ኦሮሞው በሰላምና በፍቅር ከ400 አመታት በላይ የኖረ መሆኑን ማን በነገረው! በአማራው ክልል እንደዚያ ያለ የዱር አውሬ ጭካኔ ባለመተግበሩ አንጀቱ አሯል። አማራ የሞራል የበላይነት ማግኘቱ አንገብግቦታል። የኦሮሞ ደም ደሜ ነው ብሎ ወንድምነቱን ሲገልጽ፣ ለለበጣ አልነበረም። ሸዋን ብትወስዱ የቱ ኦሮሞ፣ የቱ አማራ እንደሆነ አይታውቅም። ወሎም እንደዚያው። ኦሮሚያ ውስጥ ዘረኞች ሲያብዱና አማራውን ሲያሳድዱ፣ አማራ ውስጥ የሚኖሩ ኦሮሞዎች አጸፋው ስላልተወሰደ፣ ያለሥጋት በሰላም መብታቸው ተጠብቆላቸው መኖራቸው፣ የዘረኞችን ትርክት አከሸፈባቸው። አማራ ጨዋ ህዝብ ነው።

 

ሌላው ግን፣ ቋንቋቸውን ከዚያ የማይመች የላቲን ሾርባ ከነቁቤያቸው፣ ልክ አሁን አዲስ አበባ ላይ ለማድረግ እንደሚሞክሩት፣ አማርኛን ለማዳከም የታቀደ ከንቱ መርዝ ነው። ሺመልስ አብዲሳ እኮ በግልጽ የአማርኛን ቋንቋ በ50 ዓመት ውስጥ እናጠፋለን ብሏል። ጠቅላይ ሚኒስትሩን እንዲህ ግብግብ አድርጎ የሚያስለፈልፈው፣ ያንን ዕቅድ አለማሳካቱ ነው። አማርኛ ኦሮሚያ ክልል በደንብ ማስተማር አለበት ብሎ እኮ መመሪያ ቢሰጥ መርዙ ይሸፈንለት ነበር። ለምን ጉራጊኛ፣ ሲዳምኛ፣ ጋሞኛ፣ ወላይትኛ፣ አፋርኛ ካፊኛ፣ አርጎብኛ፣ ሐረሪኛ፣ ሶማሊኛ … አላለም? የሱ መነሻና መድረሻ፣ አልፋና ኦሜጋ ኦሮሞና ኦሮሞ በመሆኑ ነው! ሲያምረው ይቅር። አማራ ኦሮምኛ ፈቅዶ ቢያስተምር፣ በላቲን ቁቤ አይሆንም!

 

በአንድ አገር ውስጥ አንድ ብሔራዊ የሁሉም መግባቢያ ቋንቋ፣ የተለመደ አሠራር ነው። እስካሁን አማርኛ በደንብ አገልግሏል። ሁሉም ብሔረሰብ የሚባል ተሰብስቦ እንደገና ተወያይቶበት አማርኛ አስጠላኝ ብሎ፣ ሌላ ተመራጭ ብሔራዊ ቋንቋ ላይ በድምጽ ብልጫ እስካለወጠው ድረስ፣ ቢመረው ይጋተው፣ አማርኛ ብሔራዊ ቋንቋ ነው። የሚመረጠው ኦሮምኛ ከሆነ፣ ሁሉም ኦሮምኛ ይማራል። ያኔ አማሮችም የግዳቸውን ይማሩታል። አሁን ግን በፈቃደኝነት ካልሆነ ንክችም አያደርጋትም። 

 

ሕንድ ውስጥ ከ2,000 በላይ ብሔርሰቦችና ቋንቋዎች አሉ። ሁሉም የተስማሙበት አንድ ብሔራዊ ቋንቋ ከ1950 ጀምሮ ሒንዲ ነው። ዛሬም በዚያው እየተሠራ ነው። ቻይና ውስጥ 56 ትላልቅና ስፍር ቁጥር የሌላቸው ትናንሽ ድሀጣን ህብረተሰቦች አሉ። ከ1930 ዓ.ም. ጀምሮ ማንደሪን ብሔራዊ ቋንቋቸው ነው። አሜሬካም፣ ቱርኪያም ሌሎችም እንደዚሁ። ኢትዮጵያ የተለየች አገር አይደለችም! ዋጠው!

 

8ኛ) “ደሞዝ የማንከፍላቸው ከቁጥጥራችን ውጪ ሊሆኑ” ነው።

 

በሰላም ታገሉ ይለናል። ጋዜጠኞችን እያደነ ያስራል። ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን፣ ያግዳል። ተመልከቱ!

 

“አሁን የተከበረው ምክር ቤት፣ ብዙ ነገረ ሳላበዛ፣ የሰብዓዊ መብት የሚባል፣ አዋጅ ተቋም አሠራር መፈተሽ ያስፈልጋል። እኛ ደሞዝ የማንከፍለው፣ ሌሎች ኃይሎች የቀጠሩት፣ ለሌሎች ኃይሎች ሪፖርት የሚያቀርብ ተቋም ኢትዮጵያ ውስጥ ከፈቀድን፣ ምን ሌፈጸም እንደሚችል፣ ለእናንተ መተው ነው።”

 

“በነጻ” እንዲንቀሳቀሱ ህጋዊ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ነበሩ። “ሳስበው ታከተኝ፣ አለች ሴትዮዋ! “ከቁጥጥራችን ውጪ በመሆናቸው ጉዳችንን ሊያጋልጡብን ነው” ብሎ ሰጋ። ስለዚህ በተዘዋዋሪ መንገድ እንደፈለገው ደሞዝ እየከፈለ የሚዘውረውን “የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን” የሚባለውን “ጨርግደህ ጨርግደህ ጣልልኝ” እያለ የሥራ አቅጣጫ አሳየ። ይኸን ተከትሎ፣ በትዕዛዙ መሠረት እነ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤን (ኢሰመጉ)፣ የሕግ ባለሙያዎች ሰብዓዊ መብቶችን፣ የመብቶችና ዲሞክራሲ ዕድገት ማዕከል፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕክልን፣ እንዳይንቀሳቀሱ አግዷቸዋል።

 

ይኸ ማለት፣ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ ወርዶ (Editor, 2024)፣ በአሁኑ ሰዓት በተጠባባቂ ኮምሽነር ራኬብ መሰለ፣ የሲቪል ፖሊቲካ ሶሻል-ኢኮኖሚ ኮምሽነር አብዲ ጂብሪል እና የሴቶች፣ ሕጻናት፣ አረጋውያን እና የአካል ጉዳተኞች መብት ኮምሽነር ርግበ ገብረሐዋሪያ የሚመራውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንን፣ “ደሞዛችሁን የምንከፍለው እኛ ነን፣  ቁጥጥራችን ውስጥ ናችሁ፣ የመንግሥትን ገጽታ የሚያበላሽ ሪፖርት ካቀረባችሁ፣ ወየውላችሁ”፣ እያላቸው ነው። ይኸን ጽሑፍ ላኩላቸው።

 

ድመት መንኩሳ፣ አመሏን አትረሳ ይባላል። ወያኔ የፈለፈላቸው ዘረኞች ምንጊዜም መርዘኞች ናቸው። በአንድ አፍ ሁለት ምላስ ይሉታል ይኸ ነው እንግዲህ። ካጠፋን ንገሩን እያለ ሲያማልል የነበረው ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ነጻ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶችን ደሞዝ እኛ አንከፍላቸውምና ከቁጥጥራችን ውጪ ስለሆኑ ገመናችንን እንዳያዝረከርኩብን፣ ይታገዱ ብሎ ፓርላማ ላይ አወጀ። ይኸ ዓይን ያወጣ አምባገነን መሆኑን፣ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። የኢሕአዴግ ልጅ፣ ብልጽግና! 

 

9ኛ) “ኢትዮጵያዊ ሸንኩርት እይበላ ዶሮ በላሁ ይላል።

 

የኢትዮጵያን ባህልና እሴት የሚጠላ፣ የሚንቅ፣  ምን ሲባል ነው፣ እየኢትዮጵያ መሪ የሚሆነው? ኤዲያ!

 

“ኢትዮጵያ ውስጥ ዶሮ እንበላለን? ከዚህ ቀደም፣ ዶሮ ሳይሆን  ሽንኩርት ነው የምንበላው። ሽንኩርቱን ውስጥ ትንሽ ዶሮ ጨምረን፣ ከዚያ ዶሮ በላን እንላለን እንጂ ፕራይመርሊ የሚበላው ሽንኩርቱ ነው። ሽንኩርቱን መብላት ሳይሆን፣ ወደ ዶሮ መብላት መሸጋገር ነው የሚያስፈልገው። ተጠብሶ፣ በጣም ብዙ ዘይት፣ ብዙ ሽንኩርት ሳይኖርበት፣ ዶሮውን ከዳቦ ጋር እያደረግን መብላት እንድንችል ነው፣ ዋናው ፍላጎት።” 

 

“አይ አለማወቅሽ አገርሽ መራቁ!” ይባላል። በመጀመሪያ የዶሮ አሠራራችን ከኢትዮጵያ አልፎ በዓለም ደረጃ የተደነቀ፣ የተወደደ ምግብ ነው። ውጭ አገር፣ ሒልተን ውስጥ ዶሮ ወጥ በአገራችን አሠራር ተቀምሞ ተሠርቶ ፈረንጆቹ ሲወርዱበት ሳይ፣ የተሰማኝን ኩራት ለመግለጽ አልችልም። የዶሮ አሠራር ሁሉም ኢትዮጵያዊ የተራቀቀበት ተወዳጅ የአገሪቱ ምግብ ነው። “ከዘፈን እንደ ትዝታ፣ ከዘፋኝ እንደ ጥላሁን፣ ከምግብ እንደ ዶሮ ወጥ” ተብሎ በአንደኝነት ደረጃ የተቀመጠ ባህላዊ እሴታችን ወይም ፋይዳችን ነው። ይኸ የኦህዴድ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ከኢትይጵያ ባህል ጋር፣ ምን በጠላትነት አቆመው? ባህሏን ከጠላ፣ ማንነቷን ከጠላ፣ ለምን አገሪቱን ለቆልን አይገላግለንም?!

 

ለመሆኑ፣ ዶሮ እኮ ዋጋዋ በአሁኑ ጊዜ የበሬ ዋጋ መሆኑን ማን በነገረው! ይኸ የደላው ሰውዬ፣ “ለምን ኬክ አይበሉም” (“Qu’ils mangent de la brioche“) አለች የተባለችውን የፈረንሳይ ልዕልት ሜሪ አንቷነትን (Marie Antoinette) ያስታውሰናል። እንኳን በዚህ ውድ ዋጋ የተገዛች ዶሮ ይቅርና፣ ድሮም ዶሮ በሀምሳ ሳንቲም ስትገዛ፣ የምትበላው ቢያንስ ቢያንስ እስከ ሰባት የቤተሰብ አባላት ድረስ እንድታዳርስ ተደርጎ ነው። ዶሮ ታርዳ፣ አሥራ ሁለት ቦታ ተቆርጣ፣ ሙልጭ ተደርጎ ልፋጯ ተጠርጎላት፣ በሎሚና ሞቅ ባለ ወሀ ተደጋግሞ ታጥባ ትዘጋጃለች። ንጹህ  ቆዳዋም ቢሆን፣ በነበልባል እሳት ተለብልቦ፣ ፀጉሮቿ ተወግደው፣ በንፅህና ተዘጋጅታ ቁሌቱ ውስጥ ትጨመራለች። ዋናዎቹ ብልቶቹ ሰባት ናቸው፤ እነሱም ሁለት ረዥም እግር፣ ሁለት መላላጫ፣ ፈረሰኛ፣ ሁለት አጭር እግር ሲሆኑ፣ ሁለት ክንፎች፣ መቋደሻ፣ ማቀፊያ፣ አንገት ግን እንደተጨማሪ የሚቆጠሩ ናቸው። ሰውዬው የታየው ሽንኩርቱ እና ዘይቱ ብቻ ነው። “በ12 ቅመም የተሰራች ዶሮ፣ እኔ እሷን ቀምሼ አልተርፍም ዘንድሮ” ተብሎ ቅኔ የተቀኘው እኮ ባህላዊ አሠራሯ ልቅም ብላ፣ ሽንኩርቱም፣ ነጭ ሽንኩርቱም፣ ዝንጅብሉም፣ ኮረሪማውም፣ በሶ ብላውም፣ ድምብላሉም፣ ሌሎቹም ቅመማ ቅመሞች በምጥን በምጥን በባለሙያይቱ በጥንቃቄ ተዘጋጅቶ 12ቱ ብልቶች ተቆራርጠው ተጨምረውባት፣ በልዩ ዘዴ የተነጠረ ቅቤ ተጨምሮባት፣ እንቁላልም ተቀቅሎ ገብቶበት፣ መጨረሻ ላይ መከለሻ ተጨምሮበት ይወጣል። ታዲያ ያ በሞንሟና የጤፍ እንጀራ ከነአይቡ ሲቀርብ “እጅ አያስቆረጥማል” እንላለን፣ ሲጣፍጠን። በዳቦ? የምን ዳቦ አመጣብን? በእንጀራ ነው የሚበላው! የዶሮ ዝግጅት ለየት ያለ በመሆኑና ጥንቃቄ የሚፈልግ በመሆኑ፡ እንዲህም እየተባለ ተዘፍኗል፡

ሀ)ዓሣ አበላሻለሁ፣ ዓባይ ዳር ነው ቤቴ፤

ዶሮ መረቅማ፣ ከወዴት አባቴ

ለ) ተስማሚዬ ሁነህ፣ እንድትዋብልኝ፤

እንደ ዶሮ መረቅ፣ ፍቅርህ ይጣፍጥልኝ።

 

የኢትዮጵያ ዶሮ፣ ከሥጋዋ ሳይሆን ከመረቋ ነው ቁምነገሩ ያለው። ማማሩስ? ማስጎምጀቱስ? እስቲ የሚከተሉትን ፎቶዎች አወዳድሩ። ከዐቢይ ዶሮና ከኢትዮጵያ ዶሮ፣ የትኛው ነው ምራቅ የሚያስውጣችሁ?

 

 

 

 

ሰሞኑን ዝነኛዋ የባህል ዘፈን አቀንቃኝ አርቲስት አምሳል ምትኬ፣ ሰይፉ ፋንታሁን በኢቢኤስ ላይ ቀርባ፣ ከዘፈኗ ባሻገር እሷ የሠራችውን ዶሮ የቀመሰ እንግዳ፣ ዕድሜ ልኩን ጣዕሟን አይረሳትም ብላ ስትፎክር ሰምቼ ፈገግ አሰኘችኝ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የዶሮ አሠራር ባህላዊ መሆኑን ረስቶ፣ ለኮለስትሮ የሚዳርገውን ልፋጯ ሳይወጣ፣ በሎሜ ሳትታጠብ፣ የተጠበሰችውን ዶሮ በዳቦ ብሉ እያለ ሲመክረን፣ ገረመኝ። ዳቦውስ ሲገኝ አይደል? ዳቦ በሙዝም ብሉ ብሎ እኮ መክሮን ነበር። ዳቦዋ ተደጋገመችሳ! ለዚህ ነው ምስኪኗ፣ “ቡና የለም እንጂ፣ ከሰል ቢኖር የዶሮ ዓይን የመሰለች ቡና አፈላልህ ነበር!” ያለችው። እኛ በስደት አገራችን፣ ዶሮ እንደልብ የምትመረትበት ምዕራብያውያን አገር የምንኖርው ኢትዮጵያውን፣ ባይገርመው፣ አሁንም በባህላዊ ዘዴ የተሠራችውን ዶሮ ነው በእንጀራ ጠቅልለን ቅርጥፍ አድርገን የምንበላት፣ በዳቦማ አንነካትም። ዳቦ የፋራ ነው! ኢትዮጵያዊ ዶሮዋን ጠብሰን አንበላም፣ እንጀራችንንም በዳቦ አንቀይርም። ተስፋ ይቁረጥ! አሁን ገና በዓይናችን መጣ።

 

10ኛ) የሆያ ሆዬና የአበባ አየሽ ወይ ግጥሞች መቀየር አለባቸው

 

ሆሆ! ይኸ ሰውዬ አበላላችንን ብቻ ሳይሆን፣ በሌሎች ኢትዮጵያዊ ባህሎችን እና እሴቶች ላይ ነው ዘመቻውን ያጧጧፈው! እስቲ የሚከተለውን አባባሉን እዩልኝማ!

 

“ተረትና ምሳሌዎቻችን፣ ሆያ ሆዬና አበባ አየሽ ወይ ሳይቀሩ፣ ግጥም መቀየር አለበት። እንጨት ለቅሜ፣ እንጀራ እናቴ፣ ምናምን መቆም አለበት። እሱ መጥፎ መርዝ ነው ግጭት ውስጥ የሚገባው። ያ ግጥም ካልተቀየረ ውስጥ ውስጡን እየገባ እየገባ ሂዶ ጥፋት ያመጣል። እና ትርክት ፣ ስንጠይቅም፣ ስንመልስም፣ ስንሠራም፣ ስንኖርም የሚገነባ ነገር ነው። እኛ አንጨርሰው። ተባብረን ግን ልጆቻችን እንደዚህ በሠፈር ሳይባሉ፣ እንዲኖሩ ማድረግ፣ የሚያስችል ነው።”

 

“ለዛው ሙጥጥ” አሉ አባት እናቶቻችን! ሲጀመር በሆያ ሆዬና በአበባ አየሽ ወይ ውስጥ ያሉትን ባህላዊ ግጥሞች ጥልቀት ለመረዳት፣ የዳበረ ጭንቅላት የለውም። በነዚህ ባህላዊ ጭፈራዎች ምክንያት የሠፈር ልጆች ተባሉ ሲባል፣ ገና ከዚህ ሰውዬ ለመጀመሪያ ጊዜ መስማቴ ነው። ከኢትዮጵያ ባህልና ቅርስ ጋር ሰውዬው ሆን ብሎ ሲጣላ ሊኖር ነው? ምን ይሻለዋል? ማስተዋል የሚችል በአካባቢው፣ የሚያምርበትንና የማያምርበትን የሚነግረው አንድ ምራቅ የዋጠ ደፋር ሰው ይጥፋ! መሳቂያ ሆነ እኮ። 

 

ከዚህ ቀደም አንበሳ የኢትዮጵያ አርማ መሆን የለበትም በማለት፣ ካለበት ሁሉ እንዲጠፋ ሀሳብ አቅርቦ ነበር። ከሱ ይልቅ ከኢትዮጵያ ጋር በምንም ዓይነት የማትቆራኘውን የበርማ ወፍ ምልክታችን ለማድረግ ሐውልት ሁሉ እንደ አኖሌ ሳይቀር አቆመላት። በመጀመሪያ ደረጃ የፒኮክና (peacock) ፒኸን (peahen) ልዩነቱንም የሚያውቅ አይመስለኝም። ፒኮክ አውራው ነው። ላባው አምሮ በተለያየ ቀለም የሚምነሰነሰው ፒኮክ ፒኸኗን (ሴቷን) ለማማለል የፍቅር ግብዣ ነው። ይኸ ሰውዬ ያልተረዳው፣ ኢትዮጵያውያን ከሰሜን እስከደቡብ አንበሳን የሚያዩት በልዩ አድናቆት ነው። እሱ ወጣሁበት የሚለው የኦሮሞ ሕብረተሰብ አንበሳን ከመወደዱ የተነሳ፣ ወንድ ልጆቹ ሲጎብዙለት፣ “ያ ሌንጫ ኮ!” እያሉ ያንቆለጳጵሳሉ። ለዚህ ነው ለልጆቻቸው ሌንጮ እያሉ ስም የሚያወጡት። ለምሳሌ፣ ሌንጮ ባቲ አለ፣ ሌንጮ ለታም ከጎኑ አሉለት አይደል?

 

የአንበሳ ጥላቻው በጣም የጠለቀ በመሆኑ፣ በገደምዳሜ፣ በአንበሳ የሚጠሩ ድርጅቶች በሙሉ እንዲጠፉ እየጣረ ነው። አንበሳ ፋርማሲ ማፍረሱን ልብ ብላችኋል? አንበሳ አውቶቡስንም፣ ስሙንና መልኩን ሊቀይሩለት ነው። ሲቲ ባስ ሊባልም ነው። “ሞጋሳ” መሆኑ ነው። ምን አግብቶት ነው አባቶቻችን የሰየሙትን ለመቀየር የዳዳው?

 

“አያገባው ገብቶ፣ ሰው ይዘባርቃል፤

እኔ ስሜን እንጂ፣ ምኞቴን ማን ያውቃል።”

 

ነበር ያለቺው፣ ብዙነሽ በቀለ! ሲጀመር አንደኛ ቅኔ ምን እንደሆነ ምንም የሚያውቀው ነገር የለም። የሚያውቃት አማርኛ፣ ጥራዝ ነጠቅ፣ የጎዳና አማርኛ ናት። ወዳጄ! አማርኛ ከምታስበው በላይ ጥልቅ ነው። አንድ ባለ ቅኔ ያደነቀህ መስሎ ሙልጭ አድርጎ ሰድቦህ ይኼዳል። አንዳንዴ ቶሎ የሚገባ አይደለም። በዚህ የታወቁት፣ አለቃ ገብረሀና የሚባሉ ሊቅ ነበሩ። ታዲያ አንድ ጎረምሳ፣ ከሰድቡት ሊደበድባቸው ዝቶ፣ አህያውን ጭኖ፣ ዱላውን ጨብጦ ከቤቱ ወጣ። መንገድ ላይ ተገናኙ፣ የእግዚአብሔር ሰላምታ ተሰጣጥተው ተላለፉ። ወደ መንደር ገባና፣ “ያ ደብተራ ጸባዩን አሳምሮ አለፈኝ” አለ። ሌላው “ምን ነበር ያሉህ?” ቢለው፣ “ኧረ ምንም! በትህትና እጅ ነስቶ ‘ደህና አደራችሁ” ብሎኝ አለፈ” አለ። “ከማን ጋር ነበርክ?” አለው። “እንድምታየው ብቻየን ነበርኩ። አህያዬን ጭኜ፣ ወደዚህ እየመጣሁ ነበር” አለው። “አዪዪ! በል ተወው! አንተና አህያዋ አንድ ናችሁ ብለውህ ሰድበውህ አለፉ” አለውና አበገነው።

 

ጠቅላይ ምንስትሩ ጨርሶ የግጥሞቹ ጥልቀት ስላልገባው፣ በማያውቀው ገብቶ ዘላበደ። የሆያ ሆዬም ሆነ የአበባ አየሽ ወይ ግጥሞች እሱ ካሰበው በላይ ጥልቅ ትርጉም አላቸው። አማርኛን ጠልቆ ለማወቅ አማራ መሆን ብቻ አይበቃም። መማር፣ መመራመርን ይጠይቃል። አማራ ሳይሆኑ፣ በአማርኛ የረቀቁ ሞልተዋልና! የግጥሞቹን ጥልቀት፣ እኔ እዚህ ከማሰለቻችሁ፣ እንደሱ ከምዘበዝብ፣ አንድ አዋቂ ሰው በአርትስ ቲቪ ላይ፣ በሚከተለው ቪዲዩ በሚገባ መልክ አስረድቶ ነበር። ተጋበዝልኝ አደራ!

 

https://youtu.be/cIW57vXoVEk?si=D5aXNNfqLG0h8dke

 

ስለዚህ፣ የሚሰማችሁ ከሆነ፣ ይኸ ሰው ከመዘባረቁ በፊት የሚናገረውን ብታስተካክሉለት እንደዚህ አዋርዳለሁ ብሎ ከመዋረድ ይተርፋል። ይኸ ወጣቶች በታላቁ ሩጫ ላይ ሲዘፍኑ “ጠቅላይ ሚኒስትራችን ላይ አሾፋችሁ” እየተባለ የሚታፈሱበት ምክንያት ባልኖረ ነበር። እረፍ በሉት። “በአፍ ይጠፉ፣ በለፈለፉ።“አፍ ሲከፈት፣ ጭንቅላት ይታያል” ይባላል። ተረትና ምሳሌ ይጠላ የለ? ቅመስ በሉት!

 

ማጠቃለያ!

 

በአገር ደረጃ የገጠመን፣ ቀላል የሚባል ችግር አይደለም። ከዮዲት ጉዲት ጊዜም የከፋ ነው። ከግራኝ ጀሀዳዊ ጦርነትም ጊዜ የከፋ ነው። ከዘመነ መሳፍንትም ጊዜ የጨቀየ ነው። ከአድዋ ጦርነትም ሆነ፣ ከማይጨው ጦርነትም ጊዜ በበለጠ የሚያሰጋ ነው። እርስ በርስ የመባላት ጊዜ ነው። ሕገ-መንግሥት ቀርጸው፣ ዘረኝነትን ያስተዋወቁንም ህወሀቶች ዙሮባቸው እሳቱ ፈጃቸው። የትግራይንም ህዝብ ለእልቂት ዳርጓል። የ16ኛውን ክፍለ ዘመን ነፍሰ-በላ ኦሮሙማ ሥርዓት ቀንበር ተጭኖብናል። አማራው በአሁኑ ሰዓት በጦርነት ቁም ስቅሉን እያየ  ነው። የኦህዴድ መከላከያ ሠራዊት አማራ ክልል ዘሎ ገብቶ፣ ሕጻናትን፣ ሽማግሌዎችን፣ ሴቶችን ከውጪ ከወረሩን ጠላቶች በበለጠ እየጨፈጨፈን ነው። እንኳን ለአማራውና ሌሎች ብሔረሰቦች ቀርቶ፣ ለራሳቸው ለኦሮሞዎችም የስቃይና የሰቆቃ ዘመን ሆኖባቸዋል። የባሰውን፣ ጠቅላይ ሚኒስትራቸው፣ ከአንድ የአገር መሪ የማይጠበቅ አነጋጋሪ ንግግሮች ከአንደበቱ እያፈለቀ፣ ህብረተሰቡን እያሸማቀቀ ነው። አትኵሬ ፎቶውን ሳስተውል ኢል ዱቼ (IL Duce) እየመሰለኝ መጣ።ሆድ ለባሰው ማጭድ አታውሰውይባላል። አንድ ቀን የከፋው ቆራጥ እርምጃ ይወስድበትና፣ ይገላግለናል። በቅርቡ ነገሮች እንደሚገለባበጡ ነው። ሰከን ቢል ይሻለዋል።

 

የጆርጅ ኦርዌል (George Orwell) “የእንስሳት ግብርና” (Animal Farm) የሚባል መጽሐፍ አንብባችኋል? ካላነበባችሁ አንብቡት። ዐቢይ አህመድ አሊ ማለት ናፖሊዮን (Napoleon) ነው። ለማ መገርሳ ማለት ስኖውቦል (Snowball) ነው። ሙአዘ ኅምዝ ዘልዘሊቱ ዳኒኤል ክብረት ማለት ስኵለር (Squealer) ነው። ኮሬ ነጌኛ ማለት፣ እነዚያ ስኖቦልን ሊዘነጣጥሉት በድበቅ የሰለጠኑ አደገኞቹ ውሾች፣ ናፖሊዮን ገና በቡችልነታቸው ክብሉቤል (Bluebell) እና ጄሲ (Jessie) እንደተወለዱ፣ ዓይናቸውን ሳይከፍቱ ነጥቆ፣ በሰዋራ ቦታ ለአደገኛ ገዳይነት 9 ወራት የደበቃቸው ነፍሰ በላ ናቸው።። ሺመልስ አብዲሳ፣ ኦሮሚያን የሚያስተዳደራት ከሌሎቹ ባለሥልጣናት፣ በአራተኛ ደረጃ ተቀምጦ ነበር። ከስኖቦል መባረር በኋላ፣ ወደ 3 ደረጃ ከፍ ብሏል። ሌሎቹ አሳሞች በየክልሉና ዞኖች ላይ ተሹመው ብልጽግናን የሚያገለግሉ፣ “የእንስሳት ግብርና” ሹሞችን ይመስላሉ። ደመቀ መኰንን ፈረሱ ቦክሰር (Boxer) ነው። የዐቢይን ብልጣብልጥነት ነቅተውበት፣ ግን መኼጃ አጥተው ዝም ብለው የሚያገለግሉት፣ ፈረሷ ክሎቨር (Clover) እና አህያው ቤንጃሚን (Benjamin) ናቸው። የኦህዴድ መከላከያ ያለምንም ጥያቄ ትዕዛዝን ተቀብለው ንጹሓንን የሚጨፈጭፉ፣ ከኤታ ማጆር ሹሙ፣ እስከ አየሩ ኃይሉ፣ ከሎጂስቲክ ጠቅላይ መመሪያ ኃላፊው እስክ እዞቹ አመራር ቁልፍ ቁልፍ ቦታ የያዙ የኦህዴድ ጀኔራሎችና ከፍተኛ መኰንኖች፣ የሰለጠኑ ምርጥ ዘር አሳሞች ናቸው። ዐቢይ ይምራን እያሉ፣ የሚያስተጋቡት ደንገጡሮቹ፣ ናፖሊዮንን የሚያመልኩት ምስኪን በጎች ናቸው። አገር ውስጥ የህዝብ ደህንነት ውስጥ፣ እንዲሁም በአፋቸው ጥሬ የቆሉ ካድሬዎች፣ እንዲሁም በዓለም የተናኙት ልዩ የመከላከያ የክብር አባል ተሸላሚ ሆድ አደር ጋዜጠኞች፣ “የእንስሳት ግብርና” ውስጥ በየዘርፉ የተሰማሩ፣ ማንበብና መጻፍ የተማሩ፣ ሌሎች ምርጥ ዘር አሳሞችና ሙሴ (Moses) የተባለው ለስለላ የሰለጠነ ቁራ ናቸው። 

 

አገራችን ኢትዮጵያ፣ በአሁኑ ሰዓት፣ ቅጣአምባሯ የጠፋ ሆናለች። ዜጎቹ፣ እየተራቡ፣ “ጠግበናል በሉ”፣ የሚበላ የሚቀምስ ጠፍቶ “ሞልቶናል ብሉ”፣ እየተራቆቱ “ለብሰናል በሉ”፣ እየከሱ “ወፍረናል በሉ”፤ እየተረበሹ “ሰላም ነን በሉ”፣ እየደኸዩ “በልፅገናል በሉ”፣ እየታመሙ “ጤናማ ነን” በሉ፣ ተብለው በኦሮሙማ መረብ ተተብትበው፣ በእግዚአብሔር ተአምር ኑሮ ይገፋል። አገራችን፣ በአሳሞቹ መሪዎቿ የምትዘወር፣ ጆርጅ ኦርዌል የደረሳትን መጽሐፍ፣ “የእንስሣት ግብርናን” ትመስላለች።

 

ከአያያዝ ይቀደዳል፣ ከአነጋገር ይፈረዳል ይባላል። ፖለቲካ የውሸት ጥበብ ቢሆንም፣ መሪዎቻችን እየመረጡ ቢዋሹ ይመረጣል። በተላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናገሮ የሚያሳምናቸው ቢኖሩ፣ ደንገጡሮቹን ብቻ ነው። እኛስ እሺ ቀደዳውን ለምደናል፣ እንደ ብርክስ (BRICS), አፍሪካ ሕብረት (African Union), ዩኤንዲፒ (UNDP) ፊት እየወከለን ቀርቦ፣ ስለልማት፣ ስለ ዕድገት፣ ሰለሰላም ባያወራ ሀቁን ግጥም አድርገው ያውቃሉና፣ ባያሳፍረን ይመረጣል።

 

ከተዘራ ያልታረመ አንደበቱን፣ ማን ያስተካክልለት? ከባድ ነው!

References

Amnesty, I. (06 November 2024). Ethiopia: End the month-long arbitrary detention of thousands in Amhara Region. Retrieved December 04, 2024, from https://www.amnesty.org/en/latest/news/2024/11/ethiopia-end-the-month-long-arbitrary-detention-of-thousands-in-amhara-region/

Arab-Faqih. (2003). “Futuh AL-Habasha, The Conquest of Abyssinia (16th Century), 2003, . 

Editor. (2024, July 5). Daniel Bekele Steps Down From His Position As Chief Commissioner Of The Ethiopia Rights Commission. The Habesha. Retrieved January 11, 2025, from https://zehabesha.com/daniel-bekele-steps-down-from-his-position-as-chief-commissioner-of-the-ethiopia-rights-commission/

መጽሐፍቅዱስ. (n.d.). መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ ቁጥር ምዕራፍ 12 ቁጥር 4-15. 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም   January 10, 2025  በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡ ቤተ ሰብ፡ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ያጣችሁ: ልጆቻችሁን የቀበራችሁ፡ አካልችሁን ያጣችሁ፡ የተሰነዘረውን ብትር በመከላከል ላይ ያላችሁ፡ያለፈቃዳችሁ በመንግሥት ተጽእኖ ወደመግደልና

በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛ ተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡

January 10, 2025
Go toTop