December 27, 2024
84 mins read

ሁለ-ገብ ለሆነ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ዕድገት መሰረት የሚጥል ህግ፣ ወይስ የኢትዮጵያን ሀብት የሚያዘርፍና ህዝብን አቅመ-ቢስ የሚያደርግ አዲስ የባንክ ህግ- ከኒዎ-ሊበራሊዝም ወደ ባሰ ኒዎ-ሊበራሊዝም የዝቅጠት ጉዞ!

ፈቃዱ በቀለ (ዶ/ር)

(ታህሳስ 19 2017) December 28, 2024

መግቢያ

እንደተነገርን ኢትዮጵያን “ከዕዝ ወይም ከሶሻሊስታዊ” ኢኮኖሚ አላቆ ወደ “ ነፃ ገበያ ኢኮኖሚ” እንድትሸጋገር ከተደረገ ይኸው ከ31 ዓመት በላይ ሊያስቆጥር ነው። በጊዜው ስልጣንን የተቆናጠጠው የህወሃት አገዛዝ በህዝብና የአገር ጉዳይ ያገባናል በሚሉ ኢኮኖሚስቶች ዘንድ ምንም ዐይነት ውይይት ሳይካሄድ ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት(IMF) ጋር በ1993 ዓ.ም በመስማማት ተግባራዊ ያደረገው የተቋም ማስተካከያ መርሀ-ግብር(Structural Adjustment Programms) ሰፋ ያለና ሰፊውን ህዝብ ከድህነት ሊያላቅቅ የሚያስችል በማኑፋክቸሪንግ ላይ የተመሰረተ የገበያ ኢኮኖሚ ተግባራዊ ማድረግ አልተቻለም። በጊዜው በዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅትና በአጠቃላይ የዓለም አቀፍ ኮሙኒቲው ዕምነት እንደሌሎች የአፍሪካ አገሮችም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዋናው ችግር ከፍተኛ የሆነ የመንግስት ጣልቃ-ገብነት ስላለበት፣ በዚህም ምክንያት የተነሳ የገበያ ኢኮኖሚው ሊያድግ አልቻለም። ስለሆነም የዕዝ ኢኮኖሚ ተግባራዊ በመሆኑ የተነሳ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከፍተኛ የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት ይታይበታል ብለዋል። በዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት ዕምነት ወይም ጥናት የማክሮ ኢኮኖሚው መዛባት የሚገለጸው በውጭ ንግድ ሚዛን መዛባት፣ በሌላ አነጋገር አገሪቱ ወደ ውጭ ከምትልከው ይልቅ ወደ አገር ውስጥ የምታስገባው የፍጆታና ልዩ ልዩ ዕቃዎች መጠን ከፍ ያለ ነው፤ በዚህም ምክንያት የተነሳ የውጭው ንግድ ሚዛን የተዛባ ነው የሚል ነው። ከዚህም በላይ፣ የማክሮ ኢኮኖሚው መዛባት በመንግስት በጀት መዛባት፣ ማለትም መንግስት ለማህበራዊ መስክ የሚያወጣው ወጭ ከፍ ያለ ነው፤ በዚህም ምክንያት የተነሳ ምርታማ ለሆነው መስክ ሊውል የሚችለው ገንዘብ ምርታማ ወዳልሆነው የማህበራዊ መስክ ላይ ይውላል። ይህም ለገበያ ኢኮኖሚ ዕድገት እንቅፋት ነው የሚል ነው። ሌላው የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት ደግሞ በመንግስት ቁጥጥር ስር ያሉ ኢንዱስትሪዎችና ልዩ ልዩ የኢኮኖሚ  አውታሮች ናቸው። በዚህም ምክንያት የተነሳ በረቀቀው እጅ አማካይነት ሊተገበር የሚችለው የገበያ ኢኮኖሚ ሊጨናገፍ ችሏል። ከዚህ ጋር ተጨምሮ የውጭው ገበያ ቁጥጥር ስላለበት ለውጭ ኢንቬስተሮች ልቅ መሆን አለበት፤ ይህ ከሆነ ደግሞ የውጭ ኢንቬስተሮች ተንጋግተው በመምጣትና ኢንዱስትሪዎቻቸውን በመትከል የስራ መስክ ይከፍታሉ፤ በዚያውም ኢኮኖሚው ያድጋል የሚል ግምት ነበራቸው። ሌላው የማክሮ ኢኮኖሚው መዛባት የሚገለጸው በገበያው ላይ የሚሽከረከረው የፍጆታ ዕቃ ዋጋው በጠያቂና በአቅራቢ ህግ የሚደነገግ አይደለም፤ ስለሆነም ገበያ ከመንግስት ቁጥጥር ውጭ መሆን አለበት። እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩት የዓለም የገንዘብ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ምክሮች ተግባራዊ ከሆኑ አገሪቱ በአንድ ዕምርታ ወደ ገበያ ኢኮኖሚ ትሸጋገራለች የሚል ዕምነት አለ። ከዚህ በላይ በእነ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት ዕምነት የኢትዮጵያ ገንዘብ ከፍ ተብሎ ወይም ከኢኮኖሚ መሰረትና፣ ኢትዮጵያም በዓለም ገበያ ላይ ተሳትፎ ካላት ጋር በማነፃፀር የተተመነ ገንዘብ ስላለሆነ የኢትዮጵያ ገንዘብ ከዶላር ጋር ሲነፃፀር ዝቅ ተብሎ ቢተመን(Devaluation) ኢትዮጵያ ወደ ውጭ የምትልከው የጥሬ-ሀብት፣ እንደ ቡና፣ ሰሊጥና ሌሎችም የቅባት እህሎች ከፍተኛ ጠያቂ ሊያገኙ ይችላሉ ብለው ይገምታሉ። በዚህም ምክንያት የተነሳ በተለይም የውጭው ንግድ ሚዛኑ ጤናማ ይሆናል የሚል  በካፒታሊስት የኢኮኖሚ ግንባታ ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ፖሊሲ ተግባራዊ እንዲሆን በጊዜው ስልጣን ላይ በነበረው የህውሃት አገዛዝ ላይ ጫና ለማድረግ ችለዋል። ታዲያ ይህ ዐይነቱ የእነ ዓለም የገንዘብ ድርጅት የተቋም ማሻሻያ መርሀ-ግብር ተግባራዊ ከሆነ ጀምሮ በኢትዮጵያ ምድር ሙሉ በሙሉ የገበያ ኢኮኖሚ ተግባራዊ መሆን ችሏል ወይ? የስራ መስክ የሚፈልገውና ሊሰራ የሚችለው ህዝብ ተቀጥሮ የመስራት ዕድል አጋጥሞታል ወይ? ሰፊው ህዝብስ ከድህነት ተላቋል ወይ? የማክሮ ኢኮኖሚዉ ማሻሻያ ተግባራዊ ከሆነ ወዲህ በደርግ ዘመን ይታይ የነበረው የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት ሊሻሻል ችሏል ወይ? ወይስ እየተባባሰ መጥቷል?

እንደሚታወቀው የመጀመሪያው የማክሮ ኢኮኖሚው ማሻሻያ በዚህ ሳያቆም የኢትዮጵያ ብር ከዶላር ጋር ሲነፃፀር ዝቅ እንዲል ከተደረገ በኋላ በህወሃት ዘመን ከሁለትና ከሶስት ጊዜ በላይ ዝቅ እንዲል ተደርጓል። የአቢይ አህመድ አገዛዝ ስልጣንን ከተቀዳጀ ጀምሮ ወዲህ እንደዚሁ ዝቅ ተብሎ እንዲተመን ሲደረግ፣ ከሁለት ወር በፊት ይህ አይበቃም፣ የገንዘቡ የመግዛት አቅም እንዲያውም በአቅራቢና በጠያቂ ህግ መሰረት(Free Floating) መተመን አለበት ተብሎ ተግባራዊ ሆኗል። ሰሞኑን ደግሞ የአገር ውስጥ የባንኩ መስክ ለውጭ ባንኮች ክፍት መሆን አለበት በሚል  የህብረተሰብና የኢኮኖሚ ህግ በማይገባቸው ፓርሊያሜንት ውስጥ በተዘፈዘፉ ሰዎች አማካይነት አዲስ ህግ ፀድቋል። ይህም አዲስ ህግ አንዳንድ ኢኮኖሚስቶች ነን የሚሉ የካፒታሊስት አገሮች፣ በተለይም የፊናንስ ኦሊጋርኪው ታዛዥ የሆኑትን እንደ ዘመዴነህ ንጋቱንና ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ በረኸተስፋ የመሳሰሉትን የአፍሪካን የጥሬ-ሀብት አዘራፊዎች እንዲፈነድቁ አድርጓቸዋል።

ለማንኛውም ይህ ሁሉ እርምጃ የሚወሰደው አገሪቱን ወደ ገበያ ኢኮኖሚ ለማሸጋገር በሚል ቅዠት ነው። ይህ ዐይነቱ የእነ ዓለም የገንዘብ ድርጅትና የሌሎች የዓለም አቀፍ ተዋንያን የኢኮኖሚ ፖሊሲ የሳይንስንና የህብረተሰብን ህግ መሰረታዊ በሆነ መልክ እንደሚፃፀረና አንድን አገር ከድህነት ሊያላቅቃትና በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ  የተመሰረተ ሰፋ ያለ የውስጥ ገበያ መገንባት እንደማትችል፣ እንዲያውም ይባስ ብሎ ድህነትንና ኋላ-ቀርነትን እንሚያመጣ ለማሳየት እሞክራለሁ። ይህን መሰረታዊ ጉዳይ ለመረዳት አንዳንድ ከሰው ልጅና ከህብረተሰብ ጋር የሚያያዙ፣ ወይም መያያዝ ያለባቸውን ነገሮች ጠጋ ብሎ መመልከት ያስፈልጋል።

የስራክፍፍል(Division of Labor) ጉዳይ!

እነ አዳም ስሚዝ የነፃ ገበያን፣ በተለይም ለገበያ ማደግ መሰረት የሚሆነውን የስራ-ክፍፍልን ከመጻፋቸው በፊት የግሪክ ፈላሳፋዎች ሶክራተስና ፕሌቶን በጊዜው የነበረውን በዐይን ያዩትን በስራ-ክፍፍል አማካይነት የነበረውን የንግድ ልውውጥ በአንድ አገር ውስጥ የሚኖርን ህዝብ እንደ ማህበረሰብ ወይም ህብረተሰብ ሊያያዘውና፣ የውስጥ ኃይሉን ወይም የመፍጠር ችሎታውን ሊያዳብር እንደሚችል በሚገባ ጽፈዋል። የሰው ልጅ ውስጣዊ ኃይል ያለው ብቻ ሳይሆን፣ የመፍጠር ችሎታም ስላለው አዳዲስ መሳሪያዎችን በመስራትና የፍጆታ ዕቃዎችን በማምረት ከነበረበት ዝቅተኛ የሆነ የአኗኗር ስልት ወደ ተሻለ እንደሚሸጋገር አመልክተዋል። አዳም ስሚዝም ይህንን መሰረት በማድረግና የግሪክ ፈላስፋዎች የጻፉትን ጠጋ ብሎ በማጥናትና፣ እሱ በሚኖርበት በ18ኛው ክፍለ-ዘመን የነበረውን የእንግሊዝን ሁኔታ ከተመለከተ በኋላ ለገበያ ኢኮኖሚ ማደግ የግዴታ የስራ-ክፍፍል ማደግና መዳበር እንዳለበት አመልክቷል። በእሱ ዕምነት ሰፋ ያለ የስራ-ክፍፍል ሲዳብርና የንግድ ልውውጥም ሲኖር ብቻ ነው ህዝባዊ ሀብት(National-Wealth) ሊፈጠር የሚችለው። ከዚህም በላይ በአዳም ስሚዝ ዕምነት የገበያ ኢኮኖሚ በአንድ አካባቢ ብቻ ተውስኖ መቅረት ያለበት ሳይሆን፣ እንዲያድግና በአንድ አገር ውስጥ የሚኖርን ህዝብ እንዲያካትት ከተፈለገ የግዴታ የገበያው ስፋት ማደግ አለበት። ከዚህም በላይ የኢኮኖሚው መሰረት ማኑፋክቸሪንግ መሆን አለበት። በተጨማሪም፣ በአዳም ስሚዝ ዕምነት ነፃ የሆነ የገበያ ኢኮኖሚ ሊያድግ የሚችለው በረቀቀው እጅ(Invisible Hand) አማካይነት ነው።

እነ አዳም ስሚዝና ሌሎችም የእንግሊዝ ክላሲካል ኢኮኖሚስቶች ይህንን ሃሳብ ሲያዳብሩ ሌሎች ነገሮችን እንደተሰጡ ወይም እንዳሉ (as given) አድርገው በመውሰድ ነው እንጂ አስፈላጊ መሆናችውን በማስመር አይደለም። ለምሳሌ ዲሞክራሲያዊ የመንግስትና የተቋማት አገነባብ ጉዳይ፣ ወይም መኖር። ምክንያቱም በአንድ አገር ውስጥ የሰለጠነ አገዛዝ ከሌለና የሰውንም ሆነ የጥሬ-ሀብት ሊያንቀሳቅስ የሚችል የተቀላጠፈ ተቋማት ከሌለ የገበያ ኢኮኖሚ በፍጹም ሊያድግ አይችልም። ሌላው ለገበያ ኢኮኖሚ ማደግ የግዴታ ከተማዎችና መንደሮች ስርዓት ባለው መንገድ መገንባት አለባቸው፤ ወይም ተዘጋጅተው ሲኖሩ ብቻ ነው የገበያን ኢኮኖሚ ተግባራዊ ማድረግ የሚቻለው። ምክንያቱም ግልጽነት ያለውና የህዝብን ሃሳብ መሰብሰብና ስርዓትም እንዲኖረው ማድረግ የሚቻለው በደንብና ጥበባዊ የሆኑ ከተማዎች ሲኖሩ ብቻ ነው። ከዚህም በተጨማሪ፣ አንድን ዕቃ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ለማሸጋገርና ሰውንም ለማመላለስ የግዴታ የመመላለሻና የመገናኛ መስመሮችና የባቡር ሃዲዶች መዘርጋት አለባቸው። ይህ ሲሆን ብቻ ነው የገበያ ኢኮኖሚ ከመንደር  በመላቀቅ አገራዊና ብሄራዊ ሊሆን የሚችለው። በዚህም አማካይነት ብቻ ነው በአንድ አገር ውስጥ የሚኖር ህዝብ የመፍጠር ችሎታውን ማዳበርና ልዩ ልዩ የፍጆታ ዕቃዎችንና መሳሪያዎችን በማምረትና በመስራት ለገበያ ኢኮኖሚ መዳበር ዕምርታን የሚሰጠው።

በመሰረቱ በተለይም መርከንታሊስት የሚባሉ የኢኮኖሚስቶችን አስተሳብና፣ ከዚህ ጋር ተያይዞ የመንግስትን ጣልቃ-ገብነት የሚቃወመው አዳም ስሚዝና ተከታዮቹ ሊገነዘቡ ያልቻሉት በምዕራብ አውሮፓ ውስጥ፣ እንግሊዝን ጨምሮ የገበያ ኢኮኖሚ ሊያድግና ብሄራዊ መንግስት(Nation-State) ሊጠነክር የቻለው በመንግስት የዕውቅና የኢኮኖሚና የዕገዳ ፖሊሲ አማካይነት ብቻ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ በጊዜው የነበሩት የፍጹም ሞናርኪዎች(Absolutist Monarchies) የሚባሉት አገዛዞች ዕውቀት እንዲስፋፋ ዩኒቨርሲቲዎችን አቋቁመዋል፤ ቤተመጻህፍቶችም ዘርግተዋል። በየመጻህፍትቤቶችም ውስጥ ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ ዕድገት የሚጠቅሙ መጻህፍቶች ከግሪክ ቋንቋ ወደ ላቲን እየተተረጎሙ ተደርድረዋል። በዚህም አማካይነት ነው የተለያዩ ዕውቀቶች፣ በተለይም የተፈጥሮ ሳይንስና የኢኮኖሚክስና የኋላ ኋላ ላይ ደግሞ እንደሶስዮሎጂ የመሳሰሉት በመዳበር በአጠቃላይ ሲታይ የተወሰነውን የህብረተሰብ ክፍል አርቆ አሳቢ በማድረግ ፈጣሪ ማድረግ የተቻለው።

ባጭሩ በአንድ አገር ውስጥ ለገበያ ኢኮኖሚ ዕድገት የስራ-ክፍፍል መኖር ብቻውን በቂ አይደለም። ከላይ ከተዘረዘሩት መሰረታዊ ነገሮች ባሻገር የዕውቀት መዳበርና መሻሻል፣ እንዲሁም ክርክር መኖር አንድን ህብረተሰብ አቅጣጫ እንዲኖረውና፣ እስከተወሰነም ደራጃ ድረስ እያንዳንዱ ገለሰብ ከየት እንደመጣ፣ ለምን በዚህች ዓለም እንደሚኖርና፣ ወዴትስ እንደሚጓዝ እንዲያስብ ያደርገዋል። በተለይም የጀርመን ፈላስፋዎች፣ ሁለ-ገብ የሆነ የኢኮኖሚ ዕድገት አስተሳሰብ አፍላቂዎችና የተፈጥሮ ሳይንስ ተመራማሪዎች አንድ አገርና በአንድ አገር ውስጥ የሚኖር ህዝብ ወደ ንጹህ ገበያ ኢኮኖሚ ብቻ ተቀንሶ መታየት እንደሌለበት አጥብቀው በማንሳት፣ እያንዳንዱ ሰውና ህብረተሰብ ሁለንታዊ በሆነ መልክ መታይት እንዳለበት በትክክል አስተምረዋል። ይህ ሲሆን ብቻና በአንድ አገር ውስጥ የሰለጠነ አገዛዝ ካለና አስፈላጊውን ለህብረተሰብ ዕድገት የሚሆኑ መሰረቶችን የሚጥልና የሚያሻሽል ከሆነ አንድ ማህበረሰብ ከሞላ ጎደል ሚዛኑኑ ጠብቆ ሊጓዝ ይችላል የሚል ዕምነት አለ። በጀርመን ፈላስፋዎች፣ ሳይንቲስቶች ዕምነት፣ የሁለ-ገብ ኢኮኖሚ መምህራን፣ ኢንጂነሮችና የከተማ ዕቅድ አውጭዎች ዕምነት የገበያ ኢኮኖሚ እንደ ዓለማ መወሰድ የለበትም። ምክንያቱም አንድ ማህበረሰብ ወይም ህብረተሰብ ከገበያ ኢኮኖሚ በላይ ስለሆነ አንድን ማህበረሰብ ከሁለንታዊ አንፃር በመመልክት ተከታታይነት እንዲኖረው ቀስ በቀስ መገንባት ያስፈልጋል። አንድ ማህበረሰብ በየጊዜው መመርመርና መኮትኮት አለበት። ይህ ሲሆን ብቻ ጤናማና ብዙም አደጋ የማይታይበት ማህበረሰብ ወይም ህብረተሰብ ሊመሰረት እንደሚችል ያስተምሩናል።

የገንዘብና የገበያ ኢኮኖሚ ጉዳይ!

በአገራችንና በተቀሩት የአፍሪካና በሌሎችም የሶስተኛው ዓለም ተብለው በሚጠሩ አገሮች ውስጥ አንድን ህብረተሰብ በሚመለከት ሰፋ ያለ ውይይትና ክርክር ማካሄድ አለመቻል ነው። ስለሆነም በነፃ ገበያ ላይ ከፍተኛ የሆነ የተሳሳተ አመለካከት ያለውን ያህል በገንዘብ(Money) ከፍተኛ የሆነ አለመግባባት አለ። ለዚህ ዋናው ምክንያት ደግሞ በአገራችንም ሆነ በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ያሉ በኢኮኖሚ ሰለጠን የሚሉ ኤክስፐርቶች፣ ጥቂቶች ካልሆኑ በስተቀር፣ አብዛኛው በኒዎ-ክላሲካል ወይም በኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ትምህርት  የሰለጠኑ ናቸው። በመሆኑም እንደነዚህ ዐይነት ጥራዝ-ነጠቅ ኢኮኖሚስቶች የገበያ ኢኮኖሚን ሁለ-ገብ በሆነ መልክ አይረዱም። በተለይም የሳይንስንና የቴክኖሎጂን፣ እንዲሁም የማኑፋክቸሪንግንና ሌሎችንም ከላይ የተዘረዘሩትን መሰረታዊ ነገሮች አስፈላጊነት አይረዱም። በዚህ መልክ በጥራዝ-ነጠቅ የኢኮኖሚ ትምህርት የሰለጠኑ ኤክስፐርቶች መሰረታዊ ነገሮች እንዳሉ(as given፣ ለምሳሌ የሰለጠነና ዲሞክራሲያዊ የሆነ መንግስት መኖር፣ የተቀላጠፉ ተቋማት መኖርና፣ ከዚህም በላይ ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ ዕድገት አስፈላጊ የሆነው ዕውቀት እንዳሉ አድርገው በመውስድ አንድ አገዛዝ እነ ዓለም የገንዘብ ድርጅት የደነገጉትን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ በማድረግ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደገበያ ኢኮኖሚ ለመሸጋገር ይችላል የሚል ዕምነት አላቸው። በሌላው ወገን ግን፣ የእነ ዓለም የገንዘብ ድርጅት የተቋም ማስተካከያ ብለው የሚጠሩት ፖሊሲ በተለያዩ የአፍሪካ አገሮችና በአገራችንም ጭምር ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ጀምሮ´ አርባ ዓመት ያህል ቢያስቆጥርም የገበያ ኢኮኖሚ የውሃ ሽታ ለመሆን እንደቻለ በፍጹም ለመረዳት አይችሉም።

ወደ መሰረተ-ሃሳቡ ልምጣ። በህብረተሰብ ግንባታ ታሪክ ውስጥ የስራ-ክፍፍል ከመዳበሩ በፊት ገንዘብ አልነበረም። በሌላ አነጋገር፣ የስራ-ክፍፍል መዳበር ሲጀምርና ቀስ በቀስም የዐይነት በዐይነት የንግድ ልውውጥ ሲቀር ነው የሁሉም ዕቃዎች አማካይ የሆነ ገንዘብ የሚባለው ነገር ሊፈጠር የቻለው። በታሪክ ውስጥ ገንዘብ ልዩ ልዩ ቅርጾችን በመውሰድ፣ የኋላ ኋላ ላይ የካፒታሊስት ወይም የገበያ ኢኮኖሚ መዳበር ሲጀምር በጊዜው እንደገንዘብ የሚያገለግሉት የቀለጡ የወርቅና  የብር ሳንቲሞች ወይም ገንዘቦች  በጊዜው እያደገ ከመጣው ምርትና የንግድ ልውውጥ ጋር መጓዝ ስላልቻለ የግዴታ በወርቅ የተደገፈ ገንዘብ ማተም አስፈለገ። በዚያው መጠንም እዚህና እዚያ ገንዘብ ያትሙና ያሽከረክሩ የነበሩ ተቋማት ታግደው አንድ ማዕከላዊ ባንክ በማቋቋም፣  ልዩ አገልግሎቶችን የሚሰጡ ባንኮች ሊስፋፉ ቻሉ። የኋላ ኋላ ላይ ወርቅ ከአንድ አገር ወደሌላ አገር መፍስስ ሲጀምርና በዚያው ሲቀር፣ በተለይም እንደ እንግሊዝ የመሳሰሉት አገዛዞች በወርቅ ላይ ያልተደገፈ ገንዘብ በማተም በገበያው ላይ እንዲሽከረከር ማድረግ ተቻለ። የገበያ ኢኮኖሚም ካለገንዘብ መዳበርና መስፋፋት እንደማይችል ግንዛቤ ውስጥ ተገባ። በሌላ አነጋገር፣ ተጠቃሚውንና አምራቹን ብቻ ሳይሆን፣ የተለያዩ ምርቶችን በሚያመርቱ አምራቾችም መሀከል ግኑኝነትን የሚፈጥርና፣ ኢኮኖሚው እንዲተሳሰርና የውስጥ ኃይልም እንዲዳብር  ገንዘብ ከፍተኛ ሚናን ብቻ ሳይሆን የአንድ አገር ኢኮኖሚው ሞተር በመሆን ለማንቀሳቀስ እንደሚችል መረዳት ተቻለ። ይሁንና ግን ይህ ሁሉ በገበያ ኢኮኖሚ የሚገለጽ ዕድገትና የገንዘብ ማደግና በፍጥነት መሽከርከር በነፃ ገበያ አማካይነት፣ ወይም ካለመንንግስት ጣልቃ-ገብነት ነው የሚል ካለ ከፍተኛ ወንጀል የሚፈጽም ነው። በሌላ አነጋገር፣ የአንድ አገር ኢኮኖሚ በተናጠል፣ ወይም በግለሰቦችም ታታሪነት ብቻ የሚሰራና የሚያድግ አይደለም።  የግዴታ የመንግስት ጣልቃ ገብነትና ቁጥጥር ለገበያ ኢኮኖሚ ማደግ በጣም አስፈላጊ ናቸው። መንግስት እንደ እየአስፈላጊነቱ በኢኮኖሚው ውስጥ ጣልቃ በሚገባበት ጊዜ ይህንን እንደ ዕዝ ወይም እንደሻሊስታዊ ኢኮኖሚ ድንጋጌ መተርጎም ትልቅ ስህተት ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን ራሳቸው ካፒታሊስቶችም ቢሆኑ በመዋዕለ-ነዋይ ክንዋኔ ውስጥ በሚካፈሉበት ጊዜ በአቦሰጡኝ አይሰሩም፤ ወይም ገበያው ራሱን በራሱ ማረም ይችላል ብለው ተዝናንተው አይቀመጡም።

ሰለሆነም እያንዳንዱ ካፒታሊስት ወይም የግለሰብ አምራች ከመጀመሪያውኑ ጀምሮ አንድ ነገር ለማምረት ምን ምን ነገሮች እንደሚያስፈልጉት፣ የተለያየ የዕውቀት ደረጃ ያላቸውንና ለምርት ክንውን የሚያስፈልጉና፣ ሌሎችም በአገልግሎት መስክ ተቀጥረው የሚሰሩና፤ አንድን ምርት ለማምረት ምን ምን ዐይነት የጥሬ ሀብቶች እንደሚያስፈልጉና የትስ እንደሚገኙና ዋጋቸውስ የቱን ያህል እንደሆነ፣ እነዚህ ሁሉ ነገሮች መሰላትና መታቀድ አለባቸው። በሌላ አነጋገር፣ ካለ ዕቅድ የሚሰራ የካፒታሊስት ኢኮኖሚ የለም። እንደዚሁም የካፒታሊስት መንግስታት በኢኮኖሚስቶች፣ በአሁኑ ጊዜ በኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚስቶች እየተመከሩ ነው የኢኮኖሚ ፖሊሲዎቻቸውን የሚያወጡና ተግባራዊ የሚያደርጉት። ይሁንና የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚስቶች የበልያነትን መያዝና መንግስታትን ማማከር እንደሚባለው በየአገሮች ውስጥ በተለይም የህብት-ክፍፍል በሚመለከት ሚዛናዊነት እንዲፈጠር አላደረገም። የኒው-ሊበራሊዝም አስተሳሰብ የበላይነትን ከተጎናፀፈበት፣ ወይም የኬይንስን አሰትሳሰብ እንዲገፋ ካደረገበት ካለፈው አርባ ዓመት በላይ በካፒታሊስት አገሮችም  ሆነ በአተቃላይ ሲታይ ሀብታሙ የባሰ ሀብታም ሲሆን ደሀው ደግሞ የባሰ ደሃ እንደመጣ ጥናቶች ያረጋግጣሉ።

እንደገና ወደ ገንዘብ ጉዳይ ስንመጣ ገንዘብ የመገበያያ መሳሪያ ብቻ ሳይሆን፣ የአንድ ዕቃን መተለሚያ መሳሪያ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ ገንዘብ  የሀብት ማከማቻ መሳሪያና፣ በተጨማሪም በቂና ትርፍ ገንዘብ ያለው አክሲዮን በመግዛት በአክሲዮን ዋጋ ከፍና ዝቅ ማለት የተነሳ ያለውን ሁኔታ በመከታተል ሀብት ትርፍ  ማካበቺያ ዘዴ ነው። ይሁንና ግን ገንዘብ ውስጣዊ ዋጋ(Intrinsic Value) የሌለው ስለሆነ በመተማመን ላይ የሚሰራና፣ ተቀባይነትም እንዲኖረው በመንግስት ወይም በብሄራዊ ባንኩ የተደነገገ ነው። ከዚህም በላይ፣ በአንድ አገር ውስጥ የሚሽከረከር ገንዘብ ህጋዊ ስለሆነ የመገበያያ መሳሪያ እንደመሆኑ መጠን አምራቹም ሆነ ነጋዴው አንቅበለም ሊሉ አይችሉም። ለማንኛውም፣ የአንድ አገር የገንዘብ ጥንካሬ የሚወሰነው የዳበረና እያደገ የሚመጣ የስራ-ክፍፍል ሲኖር ብቻ ነው። ከዚህም በላይ ሰፊው ህዝብ በማኑፋክቸሪንግና በልዩ ልዩ የአገልግሎት መስጫ መስሪያ ቤቶችና መደብሮች ውስጥ ተቀጥሮ የመስራት ዕድል ካለው ተከታታይ ገቢ ይኖረዋል ማለት ነው። በሚያገኘውም ገቢ በገበያ ላይ የሚቀርቡትን የፍጆታና ልዩ ልዩ ዕቃዎች ገዝቶ የመጠቀም ዕድል እንዲኖረው ያስፈልጋል። በዚህ አማካይነት፣ በአንድ በኩል በአማራቹና በተጠቃሚው መሀከል በገንዘብና በንግድ አማካይነት ግኑኝነት ካለ የገንዘቡ የመሽከርከርና(The Velocity of Money) የመጠንከር ኃይል ከፍ ይላል። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ በአምራቾችም መሀከል በገንዘብ አማካይነት መተሳሰር አለ። ብዙ አምራች ኃይሎችም ራሳቸው ከትርፍ በሚያገኙት ገንዘብ ብቻ ስለማይመኩና በቂ ስለማይሆን፣ የምርት ሁኔታዎቻቸውን ለማሻሻልና አዳዲስ የማምረቻ መሳሪያዎችን ገዝቶ ለመትከል የግዴታ ከባንኮች ብድር ይወስዳሉ። በዚህም አማካይነት አምራቾች ብቻ ሳይሆኑ፣ በደሞዝ የሚተዳደረውም ህዝብ አስፈላጊ ሆኖ ካገኘውና ከባንክ በመበደር የሚፈልገውን ዕቃ፣ ለምሳሌ መኪና በመግዛት ተጠቃሚ ይሆናል። ስለሆነም ገንዘብ ዛሬና ነገን፣ እንዲሁም በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና በተቋማት መሀከል ግኑኙነት ወይም መተሳሰር እንዲኖር የሚያደርግ የረቀቀ መሳሪያ ነው። ይህና በአጠቃላይ ሲታይ የአንድ አገር ኢኮኖሚ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ ተደግፎ የምርት እንቅስቃሴ ሲካሄድ ገንዘብ ልዩ ጥንካሬን ያገኛል። ከዚህ አጠቃላይ ሁኔታ ስንነሳ የብድርንም አስፈላጊነትና የኢኮኖሚው አንቀሳቃሽ ኃይል መሆኑን መገንዘብ ከባድ አይሆንም። በሌላ አነጋገር፣ የአንድ አገር ኢኮኖሚ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ ከተመሰረተና፣ የውስጥ ገበያም ሰፋ ካለ አንድ አገር ከዓለም ተቋማት ከሚባሉት ጋር በየጊዜው እየተበደረችና የገንዘቧን የመግዛት ኃይል እየቀነሰች ወደድህነትና ወደባስ ኋላ-ቀርነት ልትገፈተር አትችልም። ይህንን ለመረዳት የማይችሉ ጥራዝ ነጠቅና ኋላ-ቀር የሆኑ፣ ወይም ያልተገለፀላቸው የኢኮኖሚ ኤክስፐርቶች ነን የሚሉ ናቸው የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት አጎብዳጅ በመሆን አንድን ህዝብ ወደ ዘለዓለማዊ ባርነትና ድህነት የሚጥሉት። በዚያው መሰረትም ብሄራዊ ነፃነትን በማስገፈፍ አንድ ህዝብ የራሱን ታሪክ እንዳይሰራና ተሸማቆም እንዳኖር ለማድረግ የሚበቁት። ስለሆነም እንደነዚህ ዐይነት በኤክስፐርት ስም ለዓለም አቀፍ ኮሙኒትዊ የሚያጎበድዱና ትዕዛዝ የሚቀበሉ ኢኮኖሚስት ነን ባዮችን ካለምንም ርህራሄ መዋጋትና ርቃናቸውንም ማስቀረት ያፈልጋል።

ነገሩን ይበልጥ ለመረዳት የአንድ አገር ኢኮኖሚ ሊዳብርና መልክም ሊይዝ የሚችለው የግዴታ የስራ-ክፍፍል ሲኖር ብቻ ነው። በስራ-ክፍፍልም አማካይነት ብቻ ነው ብሄራዊ ሀብት መፈጠር የሚቻለው። ለዚህ ደግሞ በአጠቃላይ ሲታይ ኢኮኖሚው ከሌሎች ነገሮች ጋር በመያያዝ መታቀድና ብሄራዊ ባህርይ እንዲኖረው ማድረግ ያስፈልጋል። ዞሮ ዞሮ የአንድን አገር ኢኮኖሚ በጠንካራ መሰረት ላይ ለመገንባትና ብሄራዊ ነፃነትን ለማስከበርና፣ እያንዳንዱም ዜጋ በራሱ ላይ ዕምነት እንዲኖረው የሰለጠነና የተገለጸለት መንግስት ወይም አገዛዝ መኖር አለበት። በሌላ አነጋገር፣ በአንድ አገር ውስጥ አፋኝ የሆነና የሚለፈልፍ፣ እንዲሁም ማጅራች መቺዎችንም በማስማራት እራሱ ህዝብን የሚያሸማቅቅ አገዛዝ ነኝ ባይ ስልጣን ላይ እስካለ ድረስ አንድ ህዝብ ጠንካራ ኢኮኖሚ ሊገነባ አይችልም። እንደዚህ ዐይነት መንግስትም የሁለ-ገብ ዕድገትና የሰላም ፀር ስለሆነ በማያወላግድ መንገድ ከስልጣን መወገድ አለበት። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ በመንግስትም ሆነ በልዩ ልዩ ተቋማት ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩ ግለሰቦች አገርንና ህዝብን አገልጋይ መሆን አለባቸው። በየጊዜው መመርመር አለባቸው። ከውጭ ኃይሎች ጋር በመተባበር መሰሪህ ስራዎችን የሚሰሩ ለፍርድ መቅረብ አለባቸው። እንደነዚህ ኃይሎችም በምንም ዐይነት ስልጣን አካባቢ እንዳይደርሱ ማድረግ አስፈላጊና በሄራዊ ግዴታ ነው። ይህ ሲሆን ብቻ ነው በአንድ አገር ውስጥ ሰፋ ያለ ኢኮኖሚ መገንባትና የሰለጠነ ስራ መስራት የሚቻለው። በአንፃሩ ብልግና በተስፋፋበት አገር ውስጥና ኢኮኖሚውም ወደ ተራ ሸቀጣ ሸቀጥ ማራገፊያነት የሚለወጥና ኢኮኖሚ በዚህ መልክ የሚተረጎም ከሆነ አንድ አገር በዐይነትም ሆነ ሰፋ ባለ መልክ ልትዳብርና ወደ ተከታታዩ ትውልድ ልትሸጋገር አትችልም።

ገንዘብ፣ ብድርና የባንክ ሚና!

በኢኮኖሚ ዕድገት ታሪክ ውስጥ የስራ-ክፍፍል ማደግና መዳበር፣ እንዲሁም የገበያ ኢኮኖሚ በዐይነትም ሆነ በስፋት መጠንከርና፣ ገንዘብም በተለያየ መልክ መገለጽና የባንኮችም መቋቋም ርስ በርሳቸው የተያያዙ ነገሮች ናቸው። ከስራ-ክፍፍል መዳበር በፊት የገበያ ኢኮኖሚ ያልነበረውንና ያላደገውን ያህል፣ ከላስ- ክፍፍል መዳበር የገንዘብን ሚና መረዳት በፍጹም አይቻልም። የባንክም መቋቋምና፣ ገንዘብ በባንኮች አማካይነት ወደ ብድርነት(Kredit) መለወጥ  ሎጂካዊ የሆነ የካፒታሊዝም ዕድገት ገጽታ ነው ማለት ይቻላል።

በአውሮፖ ውስጥ ኢኮኖሚው ከኢንዱስትሪ አብዮት በፊት ከነበረው ቀደም ካለው የፍጆታ-አመራረት ማነቆነት(Proto-Industrialization or Industrailazation before Industrilaization) እየተላቀቀ ሲመጣ የኢንዱስትሪ አብዮትም ሲካሄድ የባንኮች ሚና እየታወቀና እያደገ ሊመጣ ቻለ። በአውሮፓ የፊዩዳል ስርዓት ውስጥ የአራጣ ብድርነት(Usury) የተስፋፋ ቢሆንም፣ በዚህ መልክ ገንዘብን በከፍተኛ ወለድ ማበደርና ትርፍ ማትረፍ በካቶሊክ ሃይማኖት ዕምነት የተወገዘ ነበር። በዚህም ምክንያትና በነበረው ደካማ ኢኮኖሚ የተነሳ የባንክ ስርዓትና የክሬዲት ስይስተም የተስፋፉ አልነበሩም።  የባንክ ስርዓት ሊስፋፋ የቻለውና ገንዘብም በብድር አማካይነት በመጠነኛ ወለድ ለኢንዱስትሪ መትከያና ለንግድ እንቅስቃሴ እንዲውል የተደረገው በታወቁ ኢኮኖሚስቶች፣ በአዳም ስሚዝና በሁም አማካይነት ክርክርና ማስተማሪያ መሳሪያዎች ሲስፋፋ ነው። በአዳም ስሚዝም ሆነ በሁም ዕምነት፣ ትክክልም ነው ብድር በማበደር ከፍተኛ ወለድ መጠየቅ የኢንዱስትሪ ዕድገትንና የንግድ እንቅስቃሴን ሊገታው ይችላል፤ ስለሆነም ወለድ ከተወሰነ መጠን ወይም ፐርሰንት በላይ መብለጥ የለበትም የሚል ነበር። ይህም ትክክል ነው። ምክንያቱም የአንድ የኢንዱስትሪ ባለቤት አምርቶ ለገበያ ከሚያቀርበውና ከሚያገኘው ትርፍ አብዛኛውን ለወለድ የሚከፍል ከሆነ ኢንዱስትሪውን ለማስፋፋትና ለማሳደግ አይችልም። ስለሆነም የባንክ ብድር በመጠነኛ ወለድ አማካይነት የኢኮኖሚው አንቀሳቃሽ ኃይል እንዲሆን ማድረግ የማዕከላዊ ባንኩ ኃላፊነት ነው። ምክንያቱም የንግድ ባንኮች ማዕከላዊ ባንኩ አትሞ በወለድ አማካይነት በሚያቀርብላቸው የብድር መጠን ተመርኩዘው ነው የራሳቸውን ወለድ ለመወሰን የሚችሉት። ስለሆነም የኢንዱስትሪ ዕድገትና የንግድ እንቅስቃሴ እንዳይገታ የግዴታ የወለዱ መጠን ከተወሰነ ጣራ በላይ ማለፍ የለበትም የሚል ስምምነት አለ።

ካፒታሊዝም እያደገ ሲመጣና አብዛኛውም ህዝብ ተቀጥሮ የመስራት ዕድል ሲያገኝ ደሞዝ በባንኮች አማካይነት ለሰራተኛው የሚተላለፍ ሆነ። አብዛኛውም  ሰራተኛ በየወሩ በባንክ አማካይነት የሚተላለፍለትን ደሞዙን እንዳለ በማውጣት ልዩ ልዩ ነገሮችን ለመግዛት አይጠቀምበትም። የተወሰነውን ገንዘብ በቁጠባ መልክ ባንክ ውስጥ በማስቀመጥ በየዓመቱ ወለድ ማግኘት እንደሚችል ስለተረዳ፣ ይህ በራሱ ለባንኮች ብድር ለሚፈልጉ የብድር መስጫ መሰረት ሆነላቸው። ምክንያቱም በቁጠባ መልክ የተቀመጠው ገንዘብ በብድር አማካይነት ለአማራቾችና ልዩ ልዩ የፍጆታ ዕቃዎች ለመግዛት ለሚፈልጉ ሲሰጥ ብቻ ነው ራሳቸው ተጨማሪ ወለድ በመቀበል ገንዘቡን በቁጠባ መልክ ላስቀመጠው ሰራተኛ የተወሰነ ወለድ መክፈል የሚችሉት። ከዚህ አጠር መጠን ያለ ሁኔታ ስንነሳ ገንዘብ ወደ ብድርና ከዚያም በኋላ ወደ ፋይናንስ ካፒታል መለወጥ ለካፒታሊዝም ዕድገት ከፍተኛ ዕምርታን ሊሰጠው ችሏል ማለት ይቻላል። በዚህ መልክ የገንዘብ መሽከርከር ሲጨምርና ወደ ብድርነትና ወደ ፋይናንስ ካፒታል ሲለወጥ ካፒታሊስቶች እንደየሁኔታው ከባንኮች በመበደርና የተሻለ ቴክኖሎጂ በመትከልና ምርትንም በዐይነትና በጥራት ሲያመርቱ የተለያዩ ምርቶችም ገበያ ላይ ወጥተው የመሽጥ ዕድል ማግኘት ይችላሉ። በዚህም መልክ ጠቅላላው ኢኮኖሚ እንደደም ዝውውር በመንቀሳቀስ ልዩ ዐይነት ኃል በማግኘት የተለያዩ የኢኮኖሚ መስኮችን ማያያዝ ወይም ማስተሳሰር ተቻለ። በዚህም መልክ የሚሰራው የካፒታሊስት ኢኮኖሚ ወደ ተራ የሸቀጣ ሸቀጥ ምርት ወይም የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ በፍጹም ሊቀነስ አይችልም።  ባለፉት ሰባ ዓመታት ብድር በተለይም የትናንሽና የማዕከለኛ ኢንዱስትሪዎች የፋይናንስ ምንጭ ቢሆንም፣ በዚያው መጠንም ኢንዱስትሪዎችን ፋይናንስ ለማድረግ ሲባል ልዩ ልዩ ዐይነቶች የፋይናንስ መሳሪያዎች ተፈጥረዋል። ብዙ ገንዘብ ያላቸው በቀጥታ ወይም በኢንዱስትሪዎች ውስጥ ድርሻ በመግዛት የኢንዱስትሪና የምርትን መስፋፋት ላይ አዎንታዊ ሚና ተጫተዋል። በሌላው ወገን ደግሞ ኢንቬስትሜንት ባንክና ፈንድ አስተዳዳሪዎች የሚባሉና የትላልቅ ኩባንያዎችን ገንዘብ፣ ለምሳሌ ኤለን መስክን፣ የቤዞንን፣ የቢልጌትን፣ የሰከር በርግንና የሌሎች ሀብታሞችን ገንዘብ የሚያስተዳደሩ ለየት ያለ ሚና ያላቸው የፋይናንስ ተቋማት አሉ። የእነዚህ ዋና ሚናና ዓላማ ደግሞ በተጨባጭ ሲታይ በየአገሮች ውስጥ የስራ መስክ በሚከፍቱና የተስተካከለ ዕድገት በሚያመጡ የኢንዱስትሪ ተከላዎች ላይ መሳተፍ ሳይሆን፣ በየአገሩ ያሉ የጥሬ-ሀብቶችን በመግዛትና የእርሻ መሬት በመቀራመትና ተመርተው ወደ ውጭ በሚወጡ የእርሻ ሰብሎች ላይ በመሳተፍ በተለይም እንደ ኢትዮጵያ በመሳሰሉትና በሌሎች የአፍሪካ አገሮች ጤናማና የተስተካካለ፣ እንዲሁም ተከታታይነት የሚኖረው ሁለ-ገብ የሆነ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊና የባህል ዕድገት እንዳይዳብር ማድረግ ነው። በተለይም የፖለቲካ፣ የሚሊታሪ፣ የፀጥታ፣ የኢኮኖሚ ኤሊቱንና፣ በአጠቃላይ ሲታይ ቢሮክራቶችንና ቴክኖክራቶችን በገንዘብ በመግዛት የፖለቲካ ነቃተ-ህሊና እንዳይዳብር ማድረግ ነው። ይህም የሚያረጋግጠው በግሎባል ካፒታሊዝም በነፃ የገበያ ኢኮኖሚና ንግድ አሳቦ ባለፉት ሰባ ዓመታት የሚካሄደው ዘመቻ ዋና ዓላማው የአፍሪካንና የተቀሩትን የሶስተኛው ዓለም አገሮች ንጹህ በንጹህ የጥሬና ለኤክስፖርት የሚሆን ሰብሎችንና ፍራ-ፍሬዎችን በማምረትና ወደካፒታሊስት አገሮች እንዲተላላፉ በማድረግ በዚያው መጠንም የየአገሩ ህዝብ በድህነት ተሸማቆ እንዲኖር ማድረግ ነው። ይህም በተጨማሪ የሚያረጋግጠው ግሎባል ካፒታሊዝም የዲሞክራሲ፣ የነፃነትና የተሟላ ዕድገት ተልዕኮ እንደሌለው ነው።

ለማንኛውም በታሪክ ውስጥ የምዕራብ አውሮፓ አገሮችም ሆነ አሜሪካ የኢንዱስትሪ አብዮትን ማካሄድ የቻሉት የባንኪንግ ስይስተምና፣ በተለይም ደግሞ ኋላ ላይ የተነሱት እንደጀርመንና አሜሪካ የመሳሰሉት ለማኑፋክቸሪንግ መስፋፋት የሚሆን በመንግስት የሚደገፍ ልዩ ዐይነት የክሬዲት ሲይስተም በማቋቋም ነው። በጊዜው እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ ኋላ ላይ ደግሞ አሜሪካና ጀርመን የየራሳቸውን ገንዘብ በማተምና ከዕድገትና ከከተማ ግንባታ ጋር በማያያዝ ብቻ ነው የኢንዱስትሪ አብዮትን ማካሄድ የቻሉት። አሜሪካን በጊዜው የፊናንስ ሚኒስተር በነበሩት በሃሚልተን የተቋቋመው የክሬዲት ስይስተም የሚያረጋግጠው በተለይም እንግሊዝ በአሜሪካን ላይ የምታደርገውን ግፊት ወይም ጫና ለመቋቋምና ከውስጥ በማኑፋክቸሪንግ ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚ ለመገንባት በማሰብ ነው። እንግሊዝ አሜሪካን ራሷን እንዳትችል በጥሬ-ሀብት አምራችነት ላይ ብቻ ተመስርታ እንድትቀር በማሰቧ ይህንን የተረዱት እንደ ሃሚልተን የመሳሰሉት የተገለጸላቸው ምሁራን የክሬዲት ስይስተም በማቋቋም ነው በአጭር ጊዜ ውስጥ በማኑፋክቸሪንግ ላይ የተመሰረተ የአገር ውስጥ ገበያ ማስፋፋት የቻሉት። ወደ ጀርመን ስንመጣ ደግሞ እንደ ፍሪድሪሽ ሊስት የመሳሰሉት የተገለጸላቸውና ሁለ-ገብ ዕውቀት ያላቸው ኢኮኖሚስቶች የእንግሊዝን የበላይነትና የነፃ ገበያ ዶክትሪን በመቃወምና፣ በተለይም የእንግሊዝን ግፊት ለመቋቋም እነ ቢስማርክን ይመክሩ የነበረው አንድ አገር ኢኮኖሚዋን በማኑፋክቸሪንግ ላይ መስርታ ለመገንባት የማትችል ከሆነ በውጭ ኃይል እንደምትጠቃና ህዝቡም በባህል ለማደግ እንደማይችል ነው ማስረዳት የጀመሩት። በሌላ አነጋገር፣ እነ ሃሚልተንም ሆነ እነ ፍሪድሪሽ ሊስት ስለማኑፋክቸሪንግ በሚያውሩበትና በሚያስተምሩበት ጊዜ ንጹህ በንጹህ ከኢኮኖሚ አንፃር ብቻ ሳይሆን ከጠቅላላው የህብረተሰብ አገነባብና ከባህል ዕድገት ጋር በማያያዝ ነው። ምክንያቱም በማኑፋክቸሪንግ ላይ የተመሰረተ የኢንዱስትሪ አብዮትና የንግድ እንቅስቃሴ ለሌላ የፈጠራ ስራዎች በሩን ስለሚከፍት ነው።  በጊዜው በዓለም አቀፍ ደረጃ “ተቀባይነት” ያለው ዓለም አቀፍ ተቋማት ስላልነበረም እነዚህ አገሮች በሙሉና፣ ኋላ ላይ ጃፓንና ኮሪያ የየራሳቸውን የገንዘብ፣ የባንኪንግና የክሬዲት ሲይስተም በማቋቋምና በማስፋፋት ነው ወደ ውስጥ ያተኮረና ህዝቡን ሊያስተሳስር የሚችል የውስጥ ገበያ ለመገንባት የቻሉት።

ከዚህ ሁኔታ ስንነሳ  እንደ ዓለም አቀፍ የንዘብ ድርጅትና (IMF)የዓለም ባንክ(World Bank) የመሳሰሉት መቋቋምና የሶስተኛውን ዓለም ኢኮኖሚ መቆጣጠር መቻል ከፍተኛ የዕድገት መሰናከል ለመሆን ነው የበቁት ማለት ይቻላል። በተለይም ዶላር የዓለም አቀፍ የንግድ መገበያያና የሪዘርብ ከረንሲ መሆን ለተስተካከለ ዕድገት ፀር፣  በእየአገሮች ውስጥ ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ ዕድገት ማነቆ በመሆን በተለይም የአፍሪካ አገሮችን የጥሬ-ሀብት አምራች እንዲሆኑና፣  በአጠቃላይ ሲታይም ኢ-ሳይንሳዊ የሆነ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ እንዲያደርጉ በማስገደድ ስር የሰደደ ኋላ-ቀርነት እንዲስፋፋ ለማድረግ ችለዋል። በተለይም በሚሊተሪ፣ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በፀጥታው ኃይል  አብዛኛውን የአፍሪካ አገሮች ወጥሮ ስለያዘና የየራሱንም ሰዎች እየሰገሰገ በማስገባት በአገራችንም ሆነ በተቀሩት የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ዘራፊና(Predatory State) ፋሽሽታዊ አገዛዞች ሊመሰረቱና ሊፈረጥሙም ችለዋል። ከዚህም በላይ የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ በተደጋጋሚ ተግባራዊ ሲሆን የየአገሩን ህዝብ ከድህነት የሚያላቅቀውና መንፈሳዊ ጥንካሬ የሚሰጠው ሳይሆን የተቃራኒውን ነው የሚፈጠረው። ሰፊው ህዝብ የባሰውኑ ደሃና አቅመ-ቢስ፣ ኑሮው የተዝረከረከና በራሱም እንዳይተማመን የሚያደርግ እጅግ አደገኛ አካሄድ ነው። በተለይም ከዓለም ኮሙኒቲው ጋር የተቆላለፉና ስማርት የሚመስሉ በኢኮኖሚ ኤክስፐርትነት ስም የሚነግዱ ራሳቸውን የነጭ ኦሊጋርኪው መደብ ተላላኪ በማድረግና ህዝባቸውን በመናቅ ወደ ውስጥ ያተኮረና ሰፊውን ህዝብ ከድህነትና ከኋላ-ቀርነት ሊያላቅቅ የሚያስችለውን ሁለ-ገብ ዕድገት ተግባራዊ እንዳይደረገ ከፍተኛ መሰናክል ለመሆን በቅተዋል። እነዚህ ዐይነት ምሁራን ነን ባዮች ልዩ ዐይነት የአኗኗር ስልት(Life Style) በማዳበር ቴክኖሎጂ ፈጣሪዎችና ሰፋ ያለ ሀብት ማዳበር የሚችሉ ሳይሆን ገበሬውና ሰራተኛው በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥት እያመረተ የሚያቀርበውን በመጠቀም ሀብት አውዳሚዎች ለመሆን የበቁ ናቸው።  ይህንን አሻጥርና የተወሳሰብ ሁኔታ የማይረዱ ኢኮኖሚስት ነን ባዮች የዓለም የገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክ አገልጋይ በመሆን ህዝቦቻቸውን የባሰ ደሃና አቅመ-ቢስ እያደረጉ ናቸው።

ያም ሆነ ይህ አንድ አገር ከውጭ በመበደርና በዕዳ በመተብተብ ወደ ውስጥ ያተኮረ፣ በማኑፋክቸሪንግ ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ኢኮኖሚ የገነባችበት ዘመን በታሪክ ውስጥ ታይቶ አይታወቅም። በዓለም አቀፍ ደረጃ በብድር መልክ የሚሸከረከረው ዶላር እንደኛ የመሰሉ አገሮችን በዕዳ ከመተብተብ ባሻገር ልዩ ልዩ ሀብትና የወለድ ወለድ(Compound Interest) ከፋይ በማድረግ ወደ አሜሪካና ወደ ተቀረው የካፒታሊስት አገሮች ማፍሰሻ ዘዴ ነው።  ዶላር ፌክ ወይም የውሸት ገንዘብ የሆነና በምንም ነገር፣ ለምሳሌ በወርቅ ያልተደገፈ ነው። ይሁንና አብዛኛዎችን ሰዎች፣ በተለይም ኢኮኖሚስት ነን የሚሉትንና የሚዘባነኑትን በማታለልና ጭንቅላታቸውን በመጋረድ ከ90% በላይ የሚሆኑ በኢኮኖሚ ኤክስፐርትነት ስም የሚነግዱ ከፍተኛ ወንጀል እየሰሩ ነው። ስለዚህ ያለው አማራጭ ጠንካራ፣ አገር ወዳድ የሆነና በሁለ-ገብ ዕውቀት የተካነ አገዛዝና የምሁር ትውልድ ሲፈጠርና ሲኮተኮት ብቻ ነው አንድን አገር በጠንካራ መሰረት መገንባትና ብሄራዊ-ነፃነትንም ማስከበር የሚቻለው። እስከዚያ ጊዜ ድረስ ግን ጠንክሮ መስራትና ኋላ-ቀር ወይም የሳይንስና የቴክኖሎጂ ፀር የሆኑ ኃይሎችን መዋጋት የጊዜው አንገብጋቢ ጥያቄ ነው። በተለይም ከሌሎች የኢኮኖሚ ቲዎሪዎች ጋር መተዋወቅና፣ በኢኮኖሚ፣ በሳይንስና በቴክኖሎጂ፣ በገንዘብ ማደግና በገበያ መስፋፋት፣ እንዲሁም በተለያዩ ዕውቀቶች መሀከል ያለውን መተሳሰር ወይም የጠበቀ ግኑኝነት መረዳት ያስፈልጋል። ኢኮኖሚስት ነን እያሉ የሚመፃደቁትን መዋጋት የሚቻለው በተለይም ሰፋ ያለና የጠለቀ የፍልስፍና ዕውቀት ሲኖር ብቻ ነው።

የውጭ ባንኮች ወደ አገራችን መግባት በረከት ወይስ እርግማን!

የውጭ ባንኮችን ወደ አገራችን ገበያ ውስጥ ገብተው እንዲሳተፉ የሚያደርገው ህግ የተለያዩ መንገዶችን የሚይዝ ነው። አንደኛው፣ የውጭ ባንኮች አገር ውስጥ ባሉ ባንኮች ውስጥ ድርሻ በመግዛት ይካፈላሉ። ሁለተኛ፣ በኢትዮጵያ ገበያ ውስጥ ለመግባት የሚፈልግ ባንክ ቅርንጫፍ መክፈት ይችላል። ሶስተኛ ፣ ወደ ውስጥ የሚገባው ባንክ በቀጥታ ቅርንጫፍ ሳይከፍት፣ የተወካይ ቢሮ በመክፈት ይሳተፋል። ለመሆኑ እንደዚህ ዐይነት ህግ ሲወጣ ምን ታስቦ ነው?

ወያኔ ስልጣን ላይ ከወጣ ጀምሮ ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት ጋር በመስማማት ተግባራዊ  ያደረገውን የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ወያኔዎችና የኢኮኖሚክ ኤሊቱ ከምን አንፃር በመነሳት እንደተቀበሉት፣ ተግባራዊ እንዳደረጉትና እንዳወደሱትም ለማሳየት ሞክሬያለሁ። እኔ ብቻ ሳልሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ላይ የግሎባል ካፒታሊዝምን እንቅስቃሴ፣ በአፍሪካና በሶስተኛው ዓለም ያለውን የንግድ ግኑኝነትና ሌሎችንም ስምምነቶች አስመልክቶ በጥብቅ የተከታተሉ ኢትጵያውያን ቅሬታዎቻቸውን አሰምተዋል። በሌላው ወገን ደግሞ በጊዜው የህወሃት አገዛዝ የእነ ዓለም የገንዘብ ድርጅትን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ሲቀበልና ተግባራዊ ሲያደርግ ከብሄራዊ የኢኮኖሚ ግንባታ አንፃር በመነሳት ወይስ ራሱንና የተወሰነውን የህብረተሰብ ክፍል ለመጥቀም ብቻ እንደሆነ ግልጽ አልነበረም። ይሁንና ቀደም ብለው የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ ያደረጉ እንደ ጋና፣ ናይጀሪያና ዚምባብዌ የመሳሰሉ የአፍሪካ አገሮች ወደ ውስጥ ያተኮረና በማኑፋክቸሪንግ ላይ የተመሰረተ የአገር ውስጥ ገበያን(Home Market)  መገንባት እንዳልቻሉ ብዙ ጥናቶች ያረጋግጣሉ። እንዲያውም በዕዳ እንደተበተቡና፣ በኢኮኖሚው ፖሊሲው አማካይነትም በመንግስት መስሪያ ቤት ውስጥና በአንዳንድ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩ ሰራተኞች ከዋጋ አንፃር በማስላት ከስራ መስካቸው እንደተባረሩ ይታወቃል። ከዚያም ባሻገር ጋናም ሆነ ይህንን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ ያደረጉ ሌሎች የአፍሪካ አገሮች በዕዳ እንደተበተቡና የውጭ ሚዛናቸውም እየተናጋ እንደመጣ እንደዚሁ ብዙ ጥናቶች ያረጋግጣሉ። በጊዜው የህወሃት አገዛዝ ይህ ዐይነቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ በተደረገባቸው አገሮች ውስጥ ያስከተለውን አሉታዊ ውጤት ሳያጠና ነው በአገራችን ምድር የእነ ዓለም የገንዘብ ደርጅትን ምክር በመቀበል የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲን በጭፍን ተግባራዊ ያደረገው። ይሁንና ከራሱ ከወያኔ ባህርይና አነሳሱንም ስንመለከት ወያኔና ካድሬዎች በቂ ዕውቀት የሌላቸው ብቻ ሳይሆኑ፣ በምንም ዐይነት ብሄራዊና የአገር ወዳድነት ስሜት አልነበራቸውም። የኢኮኖሚ ፖሊሲውም ወደ ተግባር ሲመነዘር የወያኔን ካድሬዎች ነው በአጭር ጊዜ ውስጥ ያደለበው። በዚያው መጠንም የኢኮኖሚው ፖሊሲ የባህልና የአካባቢ ውድመትን ነው ያስከተለው። ወደ ገጠር ውስጥ ደግሞ በአንዳንድ አካባቢዎች የፕላንቴሽን ኢኮኖሚ እንዲስፋፋ ነው ሁኔታዎችን ያመቻቸው። ባጭሩ በእነ ዓለም የገንዘብ ድርጅትና በእነ ዓለም ባንክ የሚወደሰውና ተቀባይነትም እንዲኖረው የተደረገው የኢኮኖሚ ፖሊሲ በአገራችን ምድር ወደ ውስጥ ያተኮረና ነፃ ኢኮኖሚ እንድንገነባ አላስቻለንም።

አሁን ደግሞ የውጭ ባንኮች በአገራችን ገበያ ላይ መጥተው እንዲሳተፉ ሲደረግ አሁንም ያለው ግምት ልክ ኢኮኖሚውን ማሳደግ እንደሚቻል ነው። ይሁንና ግን የኢኮኖሚ ዕድገት ሲባል ምን ማለትና፣ ማንንስ እንደሚጠቅምና፣ የአገር ውስጥ ገበያን ያስፋፋ አያስፋፋ ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ ዕድገት አመቺ ሁኔታዎችን ይፍጠር አይፍጠር የተጠናና የታሰበም ነገር አይደለም። ዝም ብሎ ብቻ የአገራችን የውስጥ የፋይናንስ መስኩ ለውጭ ገበያ የተዘጋ ስለሆነ ቢነሳ የውጭ ባንኮች ገንዘባቸውን፣ ዶላርም ሆነ ኦይሮ አምጥተው ማፍሰስ እንደሚችሉ ነው ግምት ውስጥ የተገባው። ይህ ደግሞ በፍጹም ሊሆን እንደማይችል የውጭ ባንኮች በተሳተፉባቸውና አሁንም በሚሳተፉባቸው በሌሎችች የአፍሪካ አገሮች ውስጥ የተረጋገጠ ጉዳይ ነው።

ቀደም ብዬ ላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት የአንድ አገር ሁኔታ ሎጂካዊ በሆነ መንገድ ካልታየና፣ በነገሮች መሀከል መተሳሰር እንዳለ ግንዛቤ ውስጥ እስካልተገባ ድረስ ኢ-ሳይንሳዊ በሆነ የኢኮኖሚ ፖሊሲና በተበላሸ መልክ በተዋቀረው ፖለቲካዊ መዋቅር የተነሳ እየተከማቸው የመጣው የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ፣ የኢኮሎጂና የባህል ውስብስባዊ ችግሮች በፍጹም ሊቀረፉ አይችሉም። በእርግጥም እንደተረጋጋጠው ተመሳሳይ የሆነ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ ሲሆንና፣ በተለይም የኢትዮጵያን ብር ከዶላር ጋር ሲነፃፀር ዝቅ ማድረግ፣ የመጨረሻ መጨረሻም በጠያቂና በአቅራቢ ህግ የመግዛት ኃይሉ እንዲሰላ ማድረግ የባሰውኑ መቀመቅ ውስጥ ነው አገራችንን የከተታት። ሰፊውንም ህዝብ በዋጋ ግሽበት የተነሳ በጣም አማሮታል። በዚህ ዐይነቱ ጽሰረ-ዕድገትና አገር አፍራሽ የኢኮኖሚ ፖሊስ የተነሳ ሰፊው ህዝባችንና በደሞዝ የሚተዳደረው ሰራተኛ ለድብቅ ረሃብ ተጋልጠዋል።  የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲው 5% የሚሆነውን የህብረተሰብ ክፍል ብቻ ነው ተጠቃሚ ያደረገው። በዚህ ዐይነቱ የተበላሸ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተጠቃሚ የሆነው የህብረተሰብ ክፍል ደግሞ ፈጣሪ መንፈስን(Pioneer Spirit) ያደበረና ለታዳጊው የህብረተሰብ ክፍል ጥሩ ምሳሌ የሆነ ሳይሆን  መጥፎ መጥፎ ነገሮችን ያስተማረና የሚያስተምርም ነው።

የውጭ ባንኮችን በአገራችን ውስጥ የመሳተፍና ሊያስከትል የሚችለውን አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ ለመረዳት ቀደም ብዬ ስለገበያ ኢኮኖሚ አስተዳደግና መስፋፋት አጠር መጠን ባለመልክ ያስቀመጥኩትን መረዳት ያስፈልጋል። በመጀመሪያ ደረጃ ስለኢኮኖሚ በሚወራበት ጊዜ ከሰው ህይወትና ከህብረተሰብ ዕድገት ውጭ ማየት በጣም ስህተት ነው። በሌላ አነጋገር፣ ስለኢኮኖሚ በሚወራበት ጊዜ የሰውን ልጅ ፍላጎት ከማሟላት ውጭ ማሰብ በጣም ስህተት ነው። የገበያን ኢኮኖሚንም እንደ ዓላማ ወይም መድረሻ ግብ አድርጎ መውሰድ ትልቅ ስህተት ነው። ገበያና በገበያ ላይ መገበያየት ታሪካዊ ግዴታና የስው ልጅም በታሪኩ ውስጥ የፈጠረው ነገር ሲሆን፣ ዋናው ተግባሩም ህብረተሰብአዊና ባህላዊ ተቋም በመሆን የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማቀራረብ ውስጣዊ ኃይላቸውን ከፍ ማድረግ ነው። ይሁንና በኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚስቶችና በዓለም አቀፍ ድርጅቶች የሚሰበከውና ተግባራዊም የሚሆነው የኢኮኖሚ ፖሊሲ በጣም ጥቂቱን የህብረተሰብ ክፍል የሚጠቅምና አብዛኛውን ህዝብ ደግሞ እያገለለ እንደሚመጣ የብዙ አገሮች የኢኮኖሚና የማህበራዊ ሁኔታ ያረጋግጣል። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚ ፖሊሲ አምባገነናዊ አገዛዞችን የሚያፈረጥምና ሀብትንም የሚያዘርፍ በመሆን በተለያዩ የሶስተኛው ዓለም አገሮች ውስጥ የውንብድና ስራ እንዲስፋፋ አመቺ ሁኔታን ፈጥሯል።  በዚህም ምክንያት የተነሳ በተለይም ደካማው የህብረተሰብ ክፍልና ወጣት ሴቶች ተጠቂዎች ለመሆን በቅተዋል።

ከዚህ ሁኔታ ስንነሳ  መቶ በመቶ መናገር እንደሚቻለውና፣ ወደፊትም እንደሚረጋገጠው የውጭ ባንኮች በአገራችን የፋይናንስ መስክ ውስጥ ሲሳተፉ እንደሚገመተው ዶላርንና ኦይሮን ይዘው በመምጣት መበደር ለሚፈልገው ህዝብ አያቀርቡም። በመሰረቱ አንድ አገር ዶላርንና ኦይሮን የምትፈልገው በአገሯ ኢኮኖሚ ውስጥ ለማሽከርከር ሳይሆን፣ ራሷ ማምረት የማትችላቸውን ማሺኖች፣ የህክምና መሳሪያዎች፣ መድሃኒቶችና፣ ሲያስፈልግም እህል ለማስመጣት ነው። ከዚህ ውጭ ዶላርና እይሮ ሌላ ሚና የላቸውም። በሌላ አነጋገር፣ የአንድን አገር ኢኮኖሚ ሊያንቀሳቅስ የሚችለው የየአገሩ ገንዘብ ብቻ ነው። የየአገሮችም የባንክ ህግ እንደሚያረጋግጠው ሌጋል ቴንደር በመባል በየአገሮች ውስጥ የሚሸከረከረው ገንዘብ ዶላር ሳይሆን፣ የየአገሩ ገንዘብ ብቻ ነው። በአገራችን ደግሞ ብር ነው። ብርም ነው ባንክ ውስጥ ሲከማች ወደ ብድርና ወደ ልዩ ልዩ የፋይናንስ መሳሪያዎች በመቀየር ኢኮኖሚውን ማንቀሳቀስ የሚችለው። የአገራችን ብር ደግሞ የፋይናንስ ሚናውን እንዲጫውትና ወደ ካፒታል እንዲቀየር ከተፈለገ መሰረታዊ በሆነ መንገድ የአመራረት ዘዴውን መቀየርና፣ በስራ-ክፍፍል ላይ የተመሰረት ሰፊ የኢኮኖሚ መዋቅር መዘርጋት ያስፈልጋል። ይህ ከመሆኑ በፊት የገንዘብን ዋጋ መቀነስ፣ ወይም ደግሞ የውጭ ባንኮች ገብተው ተዋንያን እንዲሆኑ ማድረግ በአገራችን ምድር የሰፈነውን መሰረታዊ ችግር በፍጹም ሊቀርፈው አይችልም። ኢኮኖሚውም ጠንካራ ከሆነና በሳይንስና በቴክኖሎጂም የሚደገፍ ከሆነ የገንዘብን የመግዛት ኃይል በጉልበትና አርቲፊሻል በሆነ መንግድ በፍጹም መቀነስ አያስፈልግም።

ለማንኛውም የውጭ ባንኮች በአገራችን ይፋይናንስ መስክ ውስጥ እንዲሳተፉ ሲደረግ በማኑፋክቸሪንግ ላይ የተመሰረተ የውስጥ ገበያን ለማሳደግ አይደለም። የማሽን ኢንዱስትሪንም ለማስፋፋት አይደለም። እንደሚታወቀውና የካፒታሊስት አገሮች የኢኮኖሚ ዕድገትም ታሪክ እንደሚያስተምረን የአንድ አገር ኢኮኖሚ በጥራትም ሆነ በብዛት ሊያድግ የሚችለው የግዴታ የማሽን ኢንዱስትሪ ሲኖርና፣ ይህ ዐይነቱ ኢንዱስትሪ ደግሞ በመንግስት በሚደገፍ ተቋማት በየጊዜው በምርምርና በዕድገት(Research & Development) ሲደገፍ ብቻ ነው። ካለበለዚያ በአንድ አገር ውስጥ ሁለ-ገብ የሆነና ሰፊውን ህዝብ ሊያካትት የሚችል የኢኮኖሚ ዕድገት ሊመጣ በፍጹም አይችልም። ከዚህ ሀቅ ስንነሳ የውጭ ባንኮች በአንድ አገር ውስት ሲሳተፉ በርካሽ ብድር አማካይነት ትናንሽ፣ ማዕከለኛና ትላልቅ ኢንዱስትሪዎችን በማበደር ሁለ-ገብ የሆነና ርስ በርሱ የተሳሰረ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ዕድገት እንዲመጣ የማድረግ ኃይልና ፍላጎትም የላቸውም። ተሳትፎአቸውም ትርፍ አትርፎ ትርፉን ወደ ውጭ ለማስወጣትና የእናት ባንኮቻቸውን የባሰውኑ በሀብት ለማደለብ ስለሚሆን የሚሰማሩበት መስክ የተወሰነ፣ በተለይም ስትራቴጂክ በሆነ የጥሬ.-ሀብቶችና ወደ ውጭ ሊወጡ በሚችሉ የእህል ሰብሎችና ፍራፍሬዎች ላይ መሰማራት ነው ዋቅና ዓላማቸው። ባጭሩ የውጭ ባንኮች በአገራችን ውስጥ መሳተፍ መሰረታዊ የሆነውን የአገራችንና የህዝባችንን ችግር የሚቀርፈው አይሆንም፤ ከግሎባል ካፒታሊዝምም ሎጂክ አንጽሳር በፍጹም ሊሆን የሚችል አይደለም። ወደ አገራችንንም የሚገቡት ባንኮች የትላልቅ ኢንቬስትሜንት ባንኮች አካሎች ስለሆኑ ዋና ዓላማቸውም የአንድን አገር ኢኮኖሚ መገንባት ሳይሆን የጥሬ-ሀብትን በመዝረፍ አጠቃላይ የሆነ ድህነትን ማስፋፋት ነው። ይህ ዐይነቱ አካሄድም በተለይም የታዳጊውን ትውልድ አስተሳሰብ በማዛነፍ በቀላሉ ሊሰሩ የሚችሉ ነገሮችን እንዳይሰሩ የሚያደርግ ነው።

ሰልሆነም ሁኔታውን ሎጂካዊ በሆነ መልክ መመልከትና መተንተን ያስፈልጋል። በመጀመሪያ ደረጃ፣ የውጭ ባንኮች ወደ አገራችን ውስጥ መግባት በፖለቲካ መስክ የሚካሄደውን ትግል እንድንዘነጋው ያደርጋል። እንደሚታወቀው በአገራችን ምድር ፋሺሽታዊ አገዛዝና ለወጭ ኃይሎች የሚሰራ ኤሊት ስላለ ይህ ዐይነቱ አገዛዝ እስካልተወገደ ድረሰ ጤናማና የተሰተካከለ ማህበረስብ እንዳንገነባ ያደርገናል። በሁለተኛ ደረጃ፣ በአገራችንም ሆነ በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ያለው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግር የሚመነጨውና መነሻውም ከፖለቲካው አውቃቀርና ስልጣንን ከያዘው አገዛዝ ስለሆነ ይህ ቁልፍ ችግር መፈታት አለበት። እንደዚህ ዐይነቱ አገዛዝ ደግሞ ከኢምፔሪያሊስት አገሮችና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚንቀሳቀሱ ኤሊቶች ጋር በጥቅም የተቆላለፋና ታዛዥም ስለሆነ ይህ ዐይነቱ ፋሺሽታዊ ኃይል ሲወገድ ብቻ ነው የተሟላ ሰላምን ማስፈንና ከታች ወደ ላይ ሊያድግ የሚችል የአገር ግንባታ ማካሄድ የሚቻለው። በሶስተኛ፣ ደረጃ አንድን አገር ለመገንባት ከተፈለገ ሰፊውን ህዝብ ማስተማር፣ ማንቃትና በአገር ግንባታ ውስጥ ማሳተፍ በጣም ወሳኝ ነው፡፡ በሌላ ወገን ግን የውጭ ባንኮች በአገራችን የፋይናንስ መስክ ውስጥ መሳተፍ ይህንን ዐይነቱን የተቀደስና ህዝብን የሚያሳትፍ ስራ እንዳንሰራ ያግደናል።  ባጭሩ የውጭ ባንኮች በአገራችን የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ መሳተፍ አሁን አገራችን ለገባችበት ውስብስብ ሁኔታ እንደ መፍትሄ ሊሆን በፍጹም አይችልም። ይህ ዐይነቱ ተሳትፎ  የአቢይ አህመድን የፋሽሽት አገዛዝ ዘመን በማራዘም ህዝባችንን የባሰ ጭቆና ውስጥ የሚከት ነው። ከአውሮፓው፣ በተለይም ከጀርመኑ የኢንላይተንሜንት እንቅስቃሴ ታሪክ ስንነሳ እስካሁን ድረስ በኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነት ተግባራዊ የሆኑት ፖሊሲዎች በሙሉ ወደ ባሰ ጨለማ ውስጥ ነው የከተቱን። በሌላ አነጋገር፣ ተራ የገበያ የኢኮኖሚ ፖሊሲ የሚሉት ነገር አንድን ህዝብና አገር የተሟላ ነፃነት በፍጹም ሊያጎናጽፋቸው አይችልም፤ ሁለ-ገብ የሆነ ዲሞክራሲያዊ ስርዓትም ለመገንባት የሚያስችል አይደለም። መልካም ግንዛቤ!!

fekadubekele@gmx.de

www.fekadubekele.com

https://www.youtube.com/watch?v=HZ3j4hHMO5E

Literature

Arie Arnon; Monetary Theory and Policy From Hume and  Smith to

Wicksell: Money, Credit and the Economy, New York, 2011

Bernard Lietaer and Cristian Arnsperger; Money and Sustainability, Vienna and

Berlin, 2013

Binyamin Appelbaum; The Economists᾽ Hour: False Prophets, Free Market, And

The Fracture of Society, New York & Boston, 2019

Christoph Pfluger, The Next Money: The Ten commen Errors about Money, and

How we can Erradicate it, Darmstadt, 2025

Helmut Creutz;    The Money Syndrom: The way to a crisis Free Market Economy,

Berlin, 1995

Walter Otto Ötsch; Myth Market, Myth Neoclassical Ecconomics-The bankruptcy

of Market Fundamentalism,  Marburg, 2019

 

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop