November 24, 2024
36 mins read

 የሃይማኖት መሪዎች፣ ምሁራንና ሰባኪዎች የውድቀት ቁልቁለት

November 24, 2024

ጠገናው ጎሹ

በአንድ ትልቅ እምነት ዲኖሚነሽን (ለምሳሌ ክርስቲኒቲ ) ሥር  የሚመደቡና የሃይማኖት መጻሕፍትን በየራሳቸው አተረጓጎም በመተርጎም ለዚሁ መገለጫነት የሚያገለግሉ የተለያዩ ሥርዓቶችን  የሚከተሉም ይሁኑ አንድ አይነት ሃይማኖትና ሥርዓተ ሃይማኖት  እንከተላለን የሚሉ ሃይማኖታዊ ተቋማት የተከታዮቻቸው ብዛትና ብስለት (በስሜት የመነዳት ወይም ያለመነዳት)  እንደ ተቋም የጥንካሬዎቻቸውና የድክመቶቻቸው ስፋትና ጥልቀት  የመሪዎቻቸው/የምሁሮቻቸው/የሰባኪዎቻቸው በተአማኒነት ፣ በፅዕናት ፣ በብቃትና በጥበብ ተልእኳቸውን የመወጣት ወይም ያለመወጣት ፣ ወዘተ  ረገድ የሚኖራቸው ልዩነት  እንደ ተጠበቀ ሆኖ በዘመናችን ከምንገኝበትና ሰብረን ለመውጣት ካልቻልንበት የቀውስና የውድቀት አዙሪት  መሪር እውነታ አንፃር የሃይማኖታዊ እምነት ተልእኳቸውን ባለመወጣታቸው ከሃላፊነትና ከተጠያቂነት ነፃ የሚያደርጋቸው አሳማኝ ምክንያት ግን ፈፅሞ የላቸውም።

አዎ! በእውነት ስለ እውነት ከተነጋገርን የውድቀቱ ስፋትና ጥልቀት ሊለያይ ቢችልም ለዘመናት ከመጣንበት አስከፊ ተሞክሮ በመማር ከስድስት ዓመታት ወዲህ ደግሞ ለማመን ቀርቶ ለማሰብም በሚከብድ ሁኔታ ተባብሶ የቀጠለውን ሁለንተናዊ ሰቆቃ (ፖለቲካ ወለድ የምድር ላይ ሲኦል) ትርጉም ባለውና ትውልድ ተሻጋሪ  በሆነ የሃይማኖታዊ እምነት መርህ ፣ ተልእኮና ሃላፊነት ስሜት  “ክፉ ነገር (ሃጢአት) ነውና በአስቸኳይ ቆሞ ፈጣሪ የሚወደውና የሚባርከው እውነተኛ የነፃነትና የፍትህ ሥርዓት ይመሥረት” ብሎ የመናገር፣  የመነጋገር ፣ የመሟገትና የመቆጣት ውድቀት የዚህኛው ወይም የዚያኛው ሃይማኖት ብቻ ሳይሆን ሁሉም የሚጋሩት  የአስቀያሚ ታሪካችን አካል መሆኑን መካድ የሚያስችል አሳማኝ ምክንያት የለንም።

ለአያሌ ዓመታት የመጣንበትን የውድቀት ቁልቁለት ሰብረን በመውጣት ለሥጋና ለነፍስ  የሚበጅ ሥርዓተ ማህበረሰብ እውን ማድረግ ካለብን በዚህ ልክ ነው መናገርና መነጋገር ያለብን። በእኩያን ገዥ ቡድኖች አገር እየፈረሰ “ስለ ሰላም ብቻ ተናገሩና ሰላምን እሹ” የሚል ድርጊት አልባና አደንዛዥ ስብከት እየሰበክን ፣ በገዛ ራሳችን ልክ የለሽ ውድቀት ምክንያት ሥልጣን ላይ የሚወጡ እኩያን ገዥዎችን ፈጣሪ በራሱ ምክንያት እንዳደረገው አድርገን እየተረክንና ፈጣሪን ጨምረን እየተፈታተን፣  ቆም ብለን ራሳችንን ለመፈተሽ በማያስችል ግልብ ስሜት እየተነዳን፣ ከየትኛውም ትውልድ በከፋ ሁኔታ የወደቅንበትን የውድቀት ቁልቁለት ተረድተን ከፈጣሪ እገዛ ጋር የጋራ መፍትሄ ከመፈለግ ይልቅ በየጎሳችን/በየጎጣችን/ በየሃይማኖታዊ እምነታችን ጓዳ እየተወሸቅን ፣ ወዘተ ጵጵስናችን ፣ ክህነታችን ፣ ሊቅነታችን ፣ ምንኩስናችን ፣ ካርዲናልነታችን፣ ፓስተርነታችን ፣ ነቢይነታችን፣ ሸህነታችንና ኢማምነታችን ፣ ወዘተ መንፈስ ቅዱሳዊ ነው ማለት ፈፅሞ ስሜት አይሰጥም።

ከታላቁ መጽሐፍ (መጽሐፍ ቅዱስ) እና ከሌሎች ሃይማኖታዊ ምንጮች ጥቅሶችን ለራሳችን በሚያመች ሁኔታ እየጠቀስንና እያጣቀስን ስህተትን/ድክመትን ሸፋፍነን ለማለፍ ከመሞከር ይልቅ ከምር በሆነ ንስሃ (ገንቢ ፀፀትና እርምት) ወደ ትክክለኛው መንገድ የመመለሱ ጉዳይ አንገብጋቢነት የሚያጠያይቀን መሆን አልነበረበትም የሚል ፅዕኑ እምነት አለኝ ።

ያለማታደል ወይም የሰይጣን ጉዳይ ሆኖብን ሳይሆን ከየራሳችን ህሊና በሚመነጨው ደካማነት/ስንፍና (መጥፎ መንፈስ -ውስጣዊ ውድቀት) ምክንያት ማጣፊያው ሲያጥረን የሰበብ ድሪቶ እየደረትን ፈጣሪን ጨምረን የውድቀታችን ተባባሪ እያስመሰልን ከመኖር (መኖር ከተባለ) የከፋ የሃይማኖታዊ እምነት መሪነት ፣  ጳጳስነትና ካህንነት፣ ሊቅነትና ሊቀ ሊቃውንትነት፣ ዶክተርነትና ፕሮፌሰርነት፣ ባህታዊነትና መነኩሴነት ፣ሰባኪነትና ዘማሪነት፣ ባለ ቅኔነትና የቅኔ ዘራፊነት፣ ፆመኝነትና ፀሎተኝነት፣ ፓስተርነትና ነብይነት፣ ኢማምነትና ሸህነት፣ ካርዲናልነትና ቄስነት፣ ሐዋርያነትና ወንጌላዊነት፣ ወዘተ ውድቀት የሚኖር አይመስለኝም።

አዎ! ሃይማኖታዊ እምነቱን የምድራዊውም ሆነ ከሞት በኋላ ተስፋ የሚያደርገው ህይወት መዳኛ አድርጎ የሚቆጥር መከረኛ የአገሬ ህዝብ በሥልጣነ መንበር ላይ በሚፈራረቁ እኩያን ገዥ ቡድኖች ለአያሌ ዓመታት መግለፅ በሚያስቸግ ሁለንተናዊ የመከራና የውርደታ ዶፍ ሰለባ ሲሆን በሃይማኖታዊ አርበኝነት ከጎኑ ቆመው “ህዝባችንን ተውት/ልቀቁት” ለማለት አለመድፈራቸው አልበቃ ብሎ ከእኩያንና ጨካኝ የፖለቲካ ቁማርተኞች  ጋር ሲተሻሹና ሲርመጠመጡ መታዘብ እንኳንስ እውነተኛ አማኝ ነኝ ለሚል እንደ ሰው ሞራላዊ ሰብእና አለኝ ለሚል የአገሬ ሰውም በእጅጉ ከባድ ፈተና ነው።

እየተነጋገርን ያለነው ቃልና ተግባር ተዋህደው በፈጣሪ (በአላህ) አምሳል ከማሰቢያ አእምሮና ከብቁ አካል ጋር ተፈጠረ ብለን የምናምንለትን የሰው ልጅ መሠረታዊ ወይም ሰብአዊ መብቶቹን የሚደፈጥጡ እኩያን ገዥዎችን በግልፅ፣ በቀጥታና አግባብነት ባለው ይዘትና አቋም መተቸትና መገሰፅ አነስተኛው የሃይማኖታዊ እምነት ሃላፊነትና ተግባር ስለመሆኑ ነው። ከዚህ መሠረታዊ ተልእኮና ዓላማ ውጭ ተሸክመን የምንዞረው ሊቅነታችን/ልሂቅነታችን ወይም ዶክተርነታችን ወይም ፕሮፌሰርነታችን የዓለማዊ ኑሮ የገቢ ምንጭ ወይም ማሻሻያ ወይም መበልፀጊያ ከመሆን ውጭ ሌላ የመንፈሳዊነት እሴት ጨርሶ የለውም/አይኖረውምም። ለዘመናት ከመጣንበትና ከስድስት ዓመታት ወዲህ ደግሞ እንኳንስ ለማመን ለማሰብም በሚከብድ ሁኔታ ተዘፍቀን ከምንገኝበት ፖለቲካ ወለድ መከራና ውርደት ሰብረን ለመውጣት ካልቻልንባቸው ዋነኛ ምክንያቶች አንዱ ከዚሁ የሃይማኖታዊ እምነት አመራር የውድቀት ቁልቁለት እና ከደርጊት (በመሬት ላይ ካለው መሪር የሰው ልጆች ህይወት) ጋር ለመቆራኘት/ለመዋሃድ ካልቻለው (ከተሳነው) የባዶ ስብከት አስቀያሚ ልማዳችን የሚመነጭ ነው።

በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ይህንን ግልፅና ቀጥተኛ አስተያየቴን የሃጢአት መንገድ አድርጎ በማሰብ የውግዘት ወይም የእርግማን  ናዳ ለማውረድ የሚፈልግ ወገን ብዙ ሊሆን እንደሚችል እረዳለሁ። የሚኖረኝ መልስ ያገጠመንና እያጋጠመን ያለውን የገዛ ራሳችን ስንፍና  እና ውድቀት ከምር በሆነ ንስሃ (ገንቢ ፀፀትና እርምት) አስተካክለን ወደ ፊት መራመድን እንጅ የሰበብ ድሪቶ እየደረትን የውድቀት አዙሪት ሰለባ መሆንን የሚባርክ እውነተኛ አምላክ የለምና ልብ ያለው ልብ ይበል የሚል ነው።

እስኪ ወኔው ይኑረንና ራሳችንን እንጠይቀው፤ እርስ በርሳችንም እንጠያየቅ እና እውነተኛ፣ ገንቢና ዘላቂ የጋራ መልስና መፍትሄ አምጦ በመውለዱ አንገብጋቢ ጉዳይ ላይ እንረባረብ፦

1)   የሃይማኖታዊ እምነት ተቋማት መሪዎች፣ ሊቃውንት፣ ሰባኪያንና ባለ ልዩ ልዩ ማዕረግ አገልጋዮች ያላቸውን (የተሰጣቸውን) እጅግ ታላቅና ክቡር ተልእኮና ሃላፊነት ተጠቅመው ከዘመናት ሁለንተናዊ መከራና ውርደት እንወጣ ዘንድ ትርጉም ያለው አስተዋፅኦ ከማድረግ ይልቅ ወደ ባሰ የውድቀት ቁልቁለት እየወረዱ የመሆኑን መሪር እውነት እየሸሸንና በየአስቀያሚው የሰበብ ጓዳ እየተሸጎጥን ስንቱን የመከራ ጊዜ ነው የመናሳልፈው?

2)   እውን እኛ ማለት እንደዚህ ነበርን እንዴ?  ግማሾቻችን የራሳችንን ዘመን በጎ ታሪክ ሳንሠራ  ቀደምት ትውልዶች በሠሩትና ከእኛ አልፎ ዓለም በሚወቀውና በሚያደንውቀው በጎ ታሪክ ብቻ እየተኩራራን እና ሌሎቻችን ደግሞ በጎ ታሪክ ካለማስመዝገብ አልፎ በጎውን ታሪክ ድምጥማጡን በማጥፋት እኩይ ተግባር ላይ ተሰማርተንና እየተሰማራን ስለ የትኛው የሰላም፣ የፍቅርና የመንፈሳዊነት እሴት ነው የምንሰብከው (የምናስተምረው)?

3)   እንዴትና መቸ ነው በእንዲህ አይነት ሁለንተናዊ (ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ሞራላዊ፣ መንፈሳዊ ፣ ወዘተ) ደዌ የተለከፍነውና በውድቀት ቁልቁለት መንጎድ  የጀመርነውመቸና እንዴትስ ነው ከዚህ ዘመን ጠገብና አስከፊ የውድቀት ቁልቁለት ወጥተን ሃይማኖትን ጨምሮ የሁሉም አይነት ነፃነት የሚረጋገጥበትና የሚከበርበት ሥርዓተ ፖለቲካንና አስተዳደርን እውን የምናደርገው?

4)   የፈጣሪን እገዛ ከሚያስገኝልን በጎ ሃሳብ፧ በጎ ሥራ፣ እና እልህ አስጨራሽ ጥረት ጋር የእርሱን ፈቃድና እገዛ እየጠየቅን ወደ ፊት ከመገስገስ ይልቅ የነበረውን በጎ የጋራ ታሪክ ሁሉ  እንዳልነበር የማድረጋችንንና በማድረግ ላይ የመሆናችንን ብርቱ ደዌ ማን እስኪነግረንና እንስኪያስቆመን ነው የጠበቅነውና እየጠበቅን ያለነው?

5)   የሚያቅበዘብዘንን የገዛ ራሳችንን በሽታ በብዙ ስም በምንጠራው ሰይጣን እያላከክን/እያሳበብን የመጣንበት በእጅጉ የተንሸዋረረ የሃይማኖታዊ እምነት እሳቤንና አረዳድን በእውነተኛ አማኝነት ህሊና/መንፅር ለማየት ወኔው የሚከዳን ለምንድን ነው?  በሌላ አገላለፅ  ከክፉ እሳቤና ድርጊት ለመራቅ የምናደርገውን ጥረት በአምሳሉ እንደፈጠረን የምናምነው እውነተኛ አምላክ እንዲያግዘን ከመጠየቅ ይልቅ  ህሊናችንን በሰይጣን እያስፈራራንና ራሳችንን አቅመ ቢሶችና የስንፍና መናኸሪያዎች እያደረግን ፈጣሪን በእጅጉ የማስቸገራችንን መሪር እውነታ የተሰጣቸውን ታላቅ አምላካዊ ተልእኮና ሃላፊነት ተጠቅመው የሚነግሩንና ከዚሁ ክፉ አዙሪት ሰብረን እንድንወጣ የሚያግዙን  የሃይማኖት መሪዎችንና ባለ ሌላ ማእረግ አገልጋዮችን ለማግኘት ያልቻልንበት እንቆቅልሽ ምድነው?

6)   ከመሪዎቿ በሚመነጭ ድክመት/ስህተት ምክንያት የሚገባትን ያህል ሰላምና ፍቅር  አግኝታ የማታውቅ የመሆኑ መሪር እውነትነት እንደ ተጠበቀ ሆኖ ታላቅና የተከበረች እንደሆነች የመንናገርላት ቤተ ክርስቲያን (ተዋህዶ ኦርቶዶክስ) የዲቁና እና የሙአዘ ጥበባትነት ማዕረግን ያጎናፀፈቻቸው እንደ ዳንኤል ክብረት አይነቶች የዚህ ትውልድ እጅግ አደገኛ እያጎዎች መፈንጫና መጫወቻ ስትሆን ከምር ከመገሰፅ ይልቅ እርሱ ከሚያማክረው እኩይና ጨካኝ የቤተ የመንግሥት ፖለቲካ ጋር የሚተሻሹና የሚርመጠመጡ የሃይማኖት መሪዎችንና ባለ ሌላ ማእረግ አገልጋዮች ነን ባዮችን ከማየት የከፋ የእውነተኛ አማኝነትን ህሊና የሚፈታተን  ጉዳይ (ፈተና) ይኖራል እንዴ?

7)   ንፁሁ ወገንና አማኝ በሥልጣነ መንበር ላይ የወጣ ወንበዴ፣ ዘራፊ፣ ሴረኛ፣ ሸፍጠኛና ጨካኝ ገዥ ቡድን ሁሉ ቀርጥፎ ሲበላው ከባድ መስዋእትነት መክፈል ቀርቶ ከምር ለመገሰፅ ወኔው የሚከዳው የሃይማኖት መሪ፣ አስተማሪ፣ ሊቅ፣ ሰባኪ፣ ፓስተር፣ ካርዲናል፣ ሸህ/ኢማም፣ ነብይ ተብየ፣ ፓትርያርክ፣ ጳጳስ/ሊቀ ጳጳስ፣ ኘሮፌሰር/ዶክተር፣ ባህታዊ ተብየ፣ አባ/መነኩሴ፣ ወዘተ የመከራንና የውርደትን እድሜ  ከሚያራዝሙት ወገኖች መካከል አንዱ ቢሆን ምን ያስገርማል?

8)   ታይቶና ተሰምቶ  በማይታወቅ ፖለቲካ ወለድ ዶፍ በተከበበና ሰለባ በሆነ የቤተ እምነት አውድ ወይም  አዳራሽ ወይም አደባባይ አለባበሱን አሳምሮና ገፅታውን አሰማምሮ “መንፈስ በላዬና በላያችሁ ላይ አርፏልና/አድሯልና እልልልል በሉ” እያለ ስብከት ሳይሆን አደገኛ ቅዠት የሚቃዠውንና የተሟላ ኑሮ ለመኖር በፈጣሪ ስም ሳንቲም የሚሰበስበውን የሃይማኖት ነጋዴ () ከነውረኛነትህ/ከአታላይነትህ ታቀብ (ተቆጠብ) ብሎ በግልፅና በቀጥታ መናገርንና መነጋገርን ሃጢአት የሚያደርግ እውነተኛ አምላክ አለ እንዴ?

9)   የምንፀልየው  ፀሎት፣ የምንሰብከው ስብከት፣ የምናሰማው እግዚኦታ(ምህላ)፣ የምንፆመው ፆም (ለነገሩ የአገሬ ህዝብ እንኳንስ በጦም ሌላም ጊዜም ጦመኛ ነው)፣ የምንዘምረው ዝማሬና የምንቀኘው ቅኔ የምንተነብየው  ትንቢት፣ አጋንንት አባረርንበት የምንለው መንፈስ፣ ወዘተ ለዘመናት ከመጣንበት መከራና ሰቆቃ ለምን አልታደገንም? ብሎ መጠየቅ እና መልሱም ፈጣሪ መከራችን አላይና አልሰማ ብሎ ሳይሆን እንጠቀምበት ዘንድ የሰጠንና ረቂቅ የማሰቢያ አእምሮና የማከናወኛ አካል እየተጠቀምን የእርሱን (የፈጣሪን) እገዛ የምንጠይቅ ሆነን ባለመገኘታችንና ይህም እኛን የፈጠረበትን መሠረታዊ ምክንያትና ዓላማ በእጅጉ ያጎሳቆለ በመሆኑ ነው የሚል ቢሆን ይገርመን ይሆን?

10)        እኩያን ገዥ ቡድኖች  ለእኩይ ዓላማቸው ማስፈፀሚያነት (ሽፋን ሰጭነት) የሚጠቀሙባቸውንና የሰላም ሚኒስቴር፣ የምርጫ ቦርድ፣ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፣ እንባ ጠባቂ፣ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን፣ የሰላም ም/ቤት፣ ወዘተ በሚል የሚጠራቸውን አካላት በማቋቋም በመከረኛው ህዝብ ላይ እንደሚሳለቁ ሁሉ የአገራችን የሃይማኖት ተቋማት መሪዎችም ከዛሬ 14 ዓመታት በፊት መሰረትነው ያሉት የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ም/ቤትም (Ethiopian Inter-Religious Council) አብይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከወጣ ብዙም ሳይቆይ መፈፀም ስለጀመረውና ያላማቋረጥ ስለ ቀጠለው የህዝብ መከራና ሰቆቃ ምንም ያለማለቱ አስደንጋጭ ሁኔታ የሃይማኖት ተቋማት መሪዎችን እጅግ አስከፊ የውድቀት ቁልቁለት ካላሳየን ሌላ ምን?

11) ከሰሞኑ፦ ሀ)   የሩብ ምዕተ ዓመቱ ህወሃት/ ኢህአዴግ ወላጅ የሆነውና ለራሱ ብልፅግና በሚልና   ትክክለኛ (እውነተኛ) ሃይማኖታዊና ዓለማዊ ትርጉሙን  በእጅጉ በሚያጎሳቁል ሴረኝነትና ሸፍጠኝነት በመሰየም  ከስድስት ዓመታት በላይ አገርን ምድረ ሲኦል በማድረግ ላይ ያለውን የገዥ ቡድን በሃይማኖታዊ ሃላፊነት ከምር ለመገሰፅ፣ አሳረኛውን ህዝብ በሃሳብ ለማገዝ፣ የህዝባችን (የወገናችን) መከራ መከራችን ነው በሚል በዓለም ዙሪያ ድምፃቸውን ከሚያሰሙት ጋር ቆመው ለመታየት ፈፅሞ ወኔው ኖሯቸው የማያቁና ነገር ግን  ለቤተ ክርስቲያኗ በቀዳሚነት ከሚሰለፉት መካከል ነን በሚሉ ሁለት ወገኖች {ሊቀ ጳጳስ እና ዶክተር/ፕሮፌሰር/መመህር) መካከል የተካሄደው “ያኛው እንስሳ ይበላል እና ይኸኛው ግን አይበላም” የሚል እጅግ ጉንጭ አልፋ ብቻ ሳይሆን በመከረኛው ህዝብ መከራና ሰቆቃ የመሳለቅ ያህል ሆኖ ያልተሰማው እውነተኛ አማኝና እንደ ሰው ሰው ሆኖና እንደ ዜጋ የአገር ባለቤት ሆኖ ለመኖር የሚፈልገውን የአገሬ ሰው ባያስገርምም በእጅጉ ሳያሳዝን ይቀር ይሆን?

ለ) ለመሆኑ  የአሳማ ወይም የሌላ እንስሳ ሥጋ መመገብ መከረኛው/አሳረኛው ህዝብ በተረኛና ጨካኝ የጎሳ ደምና አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኞች በጅምላና በተናጠል የግፍ አሟሟት እና የቁም ሰቆቃ  ሰለባ ሲሆን ባዶ ስብከት እያነበነቡ ቆሞ ከማየትና ከመስማት  የባሰ ያረክሳል እንዴእንዲህ አይነቱን ወለፈንዲነት (paradox) በግልፅና በአግባቡ መጠየቅንና መተቸትን  ሃጢአት ወይም መርገምት የሚያደርግ እውነተኛ አምላክ ይኖራል እንዴ?

 ሐ) በአንድ ወቅት በዜና አንባቢዎች ለምን ዶክተር/ፕሮፌሰር አልተባልኩም ብሎ ያዙኛና ልቀቁኝ በማለት የአስተሳሰብ ግብዝነቱን በራሱ አንደበት የነገረን መምህር ዘበነ ለማ ወይ አስተምርበታለሁ በሚለው መድረክ ወይም ወገኖቹ ለመከረኛው ህዝብ ድምፃቸውን ለማሰማት አደባባይ በሚወጡበት አጋጣሚ ተገኝቶ ክርስቶስ “ጨካኝ ገዥዎችን ህዝቤን ልቀቁ” እንዳላቸው መላልሶ የሚሰብከንን ስብከት ሆኖና አድርጎ ሳይገኝ የአሳማ ወይም የፈረስ ወይም የሪያ ሥጋ መበላት የሰው ሥጋ እንደመብላት አድርጎ ሊያሳምነን የሄደበት ርቀት የመከረኛውን ህዝብ የመገንዘብ ችሎታ (መሠረታዊ እውቀት) የመናቅ ግብዝነት እንጅ ሌላ ምን ሊባል ይችላል?

መ) መሬት ላይ ያለውን  ግዙፍና መሪር የህዝብ ስቃይና መከራ ፈፅሞ የማያንፀባርቅ/ የማይገልፅ ባዶ ስብከትን በየሳሻል ሚዲያውና በተለይም በተከበረው የቤተ እምነት አውድ ላይ ስሜትን ከሚኮረኩሩ የሃይማኖት መፃሕፍት ጥቅሶች ጋር እያቀናበሩ የአገልግሎታቸውን ክፍያ (ገቢ) ፈፅሞ በማይመጥንና ልክ በሌለው የግልና የቡድን የጥቅም ፈላጊነት የተለከፉ ወገኖች  ወደ ትክክለኛው ሃይማኖታዊ የአገልግሎት መስመር እንዲመለሱ እና ይህ ካልሆነ ግን ተቀባይነታቸው ጥያቄ ውስጥ ሊገባ እንደሚችል ማስገንዘብ ሃይማኖታዊ ስህተት/ህፀፅ ይሆናል እንዴ?  የሃይማኖት መሪነትና ሰባኪነት ተልእኮና ተግባር በአግባቡ የማካሄዱ ጉዳይ/ጥያቄ የመሪዎችና የሰባኪዎች ብቻ ሳይሆን የሃይማኖቱ ተከታዮች ጭምር ካልሆነና ይኸው መስተጋብር በትክክል እንዲካሄድ ለማድረግ ካልተቻለ የእውነተኛ አማኝነታችን ትርጉም/ማንነትና እንዴት ጥያቄ ውስጥ ቢገባ ይገርመን ይሆን?

ሠ) የቀድሞው አባ ወልደ ተንሳይ የአሁኑ አቡነ በርናባስ  ጋዜጠኛ ነኝ ባይ (የእግረኛው ሚዲያ) ስሜት ኮርኳሪ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ለገቢ ምንጭ ማሳለጫነት ያቀረበውን ጥያቄ ህዝብ (አገር) እና ቤተ ክርስቲያን በእጅጉ አስከፊና አስፈሪ በሆነ ሁኔታ ውስጥ እየማቀቁ በእንዲህ አይነቱ ስሜታዊነትን በሚጋብዝና አከራካሪ በሆነ ጉዳይ ላይ መወያየት ትክክል ስለማይሆን በጣም አጭር በሆነ መልስ ማስተናገድ ሲገባቸው አላስፈላጊ ለሆነና ፈፅሞ የስምምነት መቋጫ ለማይገኝለት ክርክር መክፈታቸው አለኝ ለሚሉት እውቀትና ለተሸከሙት ሃላፊነት በፍፁም አይመጥንም ብሎ መተቸት ነውርና ሃጢአት ይሆን?

ረ) አባ በርናባስ ከመጀመሪያውም የሰሩት ስህተት  አልበቃ ብሎ የሲኖዶስ አባላት የገቢ መጠንና አይነትን ሃላፊነታቸውንና ተግባራቸውን ከመወጣት ወይም ካለመወጣት እና ለማመን በሚያስቸግር ሁኔታ ከተጎሳቆለው መከረኛው ህዝብ  ህይወት አንፃር ለማየትና ለመመለስ ከመሞከር ይልቅ እርሳቸው በሚኖሩበት ምድረ አሜሪካ ካሉ ባለ አውሮፕላን ፓስተሮች ጋር ለማነፃፀር የሄዱበት ርቀት የሃይማኖት መሪዎቻችንና ሰባኪዎቻችን የውድቀት ቁልቁለት ያሳያልና ሊያሳስበን ይገባል ብሎ መተቸት አባቶችን ከመዳፈር አልፎ ሃጢአት ይሆን?

በፖለቲካ ወለድ የግፍ አሟሟትና የቁም ሞት ሰለባ እንዲሆን የተፈረደበት ህዝብ በተግባር አልባ እግዚኦታ የትም እንደማይደርስ አውቆ ቢያንስ ከትጥቅ ትግል መለስ ያሉትን መንገዶች በመጠቀም ራሳን በራሱ የፍትህ ሥርዓት ባለቤት ያደርግ ዘንድ ከምር በማስተማርና በመከታተል ተገቢውን እገዛ ማድረግ ከመሠረታዊ የሃይማኖታዊ እምነት ተልኮዎችና ዓላማዎች አንዱ ነውና እውነተኛ አማኝ ነኝ የሚል እና የነፃነትና የፍትህ ወርቃማ እሴት ሥራ ላይ ውሎ ማየት እፈልጋለሁ የሚል የሃይማኖት መሪ፣ ምሁር፣ ሰባኪ ፣ ወዘተ ከየመጽሐፉ እየነቀሰና እየጠቀሰ የሚሰብከው ስብከት መሬት ላይ ካለው  የህዝብ ስቃይና መከራ) ጋር ትርጉም ባለው ሁኔታ መገናኘቱን/መያያዙን ካላረጋገጠ ለዘመናት ከመጣንበት መግለፅ የሚከብድ የውድቀት አዙሪት ፈፅሞ መውጫ የለንም።

እጅግ የተሳሳተ የሃይማኖታዊ እምነት እሳቤና አካሄድ ያስከተለውና  እያስከተለ ያለው አሉታዊ ተፅዕኖ ነገ ሳይሆን ዛሬ ካልታረመ ወይም ካልተስተካከለ በልጆቹ አስተባባሪነትና መሪነት ህልውና፣ ነፃነት፣ ፍትህ፣ ሰላምና የጋራ እድገት እውን የሚሆንበት ሥርዓት ይወለድ ዘንድ  እልህ አስጨራሽ ተጋድሎ በማድረግ ላይ በሚገኘው ህዝብ ላይ የሚያሳድረው የመደንዘዝና የማደንዘዝ ተፅዕኖ በእጅኩ የበረታ ነው የሚሆነው። ለምን? ቢባል ከእኩያን ገዥ ቡድኖች ፖለቲካ ወለድ ወንጀል ጋር በመተሻሸትና በመርመጥመጥ ሃይማኖትን ጨምሮ የትኛውም መሠረታዊ ሰብአዊ መበት ከቶ ሊረጋገጥ አይችልምና ነው።

በሁሉም አይነት ሃይማኖታዊ ተቋሞች ውስጥ አንፃራዊ የሆነ (ፍፁምነት የለምና) የመሪነት፣ የምሁርነት ፣ የሰባኪነት እና የሌላም አገልጋይነት ሰብዕና ጥንካሬ ያላቸው በጣም ጥቂት ወገኖች/ግለሰቦች  የመኖራቸው  እውነትነት እንደተጠበቀ ሆኖ በአብዛኛው ግን የምድራዊውና የሰማያዊው ህይወት ቁርኝት ወይም የቃልና የተግባር ውህደት በእጅጉ የሚጎድለው አለመሆኑን ለመረዳትና ለማስረዳት የሚቻል አይመስለኝም። ባይጎድለውማ ኖሮ መከረኛው ህዝብ በሥልጣነ መንበር ላይ በሚፈራረቁ እኩያን ገዥ ቡድኖች እንኳን ለማመን ለማሰብም በሚከብድ ሁኔታ የማያቋርጥ መከራና ሰቆቃ ሰለባ ሆኖ ባልቀጠለ ነበር።

በእጅጉ የሚያሳዝነው ( ህሊናን የሚያቆስለው) አሁንም በፓትርያርክነት ፣ በጳጳስነትና ሊቀ ጳጳስነት ፣ በመመህርነትና በሰባኪነት ፣ በመነኩሴነት፣ በመጋቢነት፣ በባህታዊነት፣ “በአጋንንት አውጭነት”፣ በካህንነትና ሊቀ ካህናትነት፣ በካርዲናልነትና በቄስነት ፣ በፓስተርነት፣ “በነብይነት” ፣ በኡላማነትና በሸህነት ፣ ወዘተ ስም  ራሱን የሚጠራውና የሚያስጠራው ወገን በመከረኛው ህዝብ ላይ ግዙፍና መሪር የመከራና የሰቆቃ ዶፍ እያወረዱ የቀጠሉትን ሸፍጠኛ፣ ሴረኛ፣ ፈሪና ጨካኝ የጎሳ ደምና አጥንት ስሌት  ፖለቲካ ሥርዓት ጠርናፊዎችን  ከምር በሆነና ትርጉም ባለው ሁኔታ ለመተቸትና ለመገሰፅ ተስኖት ሲንደፋደፍ ወይም በአድርባይነት ሲርመጠመጥ ማየትቱና መስማቱ ነው ።

እናም ከዘመን ጠገቡ እጅግ አሰቃቂ ፖለቲካ ወለድ ወንጀል ግዙፍና መሪር ተሞክሮ በኋላም የዚያው ክፉ የፖለቲካ አስተሳሰብና አካሄድ ውላጆችና ታማኝ አገልጋዮች የነበሩና ከስድስት ዓመታት ወዲህ የመከራውንና የውርደቱን መጠንና አይነት ለማመን በሚያስቸግር ሁኔታ እያስኬዱ ያሉትን ተረኛ ገዥ ቡድኖች ወይ አስገድዶ ወደ የሽግግር ፍትህ ሥርት በማምጣት፣  አንደፈርም ካሉ ግን በተባበረና በተቀነባበረ ህዝባዊ ተጋድሎ በማስወገድ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን የሚሆንበትን የሽግግር ፍትህ ሥርዓት እውን ከማድረግ ውጭ ሃይማኖትን  ጨምሮ እውን የሚሆን መብትና ነፃነት  ፈፅሞ አይኖርምና ልብ ያለው ልብ ይበል!!!


 

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም   January 10, 2025  በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡ ቤተ ሰብ፡ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ያጣችሁ: ልጆቻችሁን የቀበራችሁ፡ አካልችሁን ያጣችሁ፡ የተሰነዘረውን ብትር በመከላከል ላይ ያላችሁ፡ያለፈቃዳችሁ በመንግሥት ተጽእኖ ወደመግደልና

በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛ ተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡

January 10, 2025
Go toTop