የጥላቻ ንግግር ማሰራጨት እና ግጭት መቀስቀስ ወንጀል የተከሰሱትን አቶ ታዲዮስ ታንቱ በ6 ዓመት ከ3 ወራት ጽኑ እስራትና በገንዘብ ተቀጡ።
የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ የህገ-¬መንግስትና ህገመንግስታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት አቶ ታዲዮስ ታንቱን በተከሰሱበትና ጥፋተኝነት በተባሉባቸው 3 ክሶች ነው የጽኑ እስራትና የገንዘብ ቅጣት የጣለባቸው።
አቶ ታዲዮስ ታንቱ በሰኔ 20 ቀን 2014 ዓ.ም የጥላቻ ንግግር በማሰራጨት እና የእርስ በርስ ግጭት መቀስቀስ ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው በፍትህ ሚኒስቴር በተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች ዐቃቤ ሕግ በኩል ተደራራቢ አራት ክሶች ቀርቦባቸው እንደነበር ይታወሳል።
ዐቃቤ ሕግ ባቀረበው አንደኛው ክስ ላይ እንዳመላክተው በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 32/(1)ሀ እና አንቀጽ 257/ሀ ስር የተደነገገውን በመተላለፍ በግንቦት 11 ቀን እና በመጋቢት 22 ቀን 2014 ዓ.ም እና በተለያዩ የዩቲዩብ ቻናሎች ህዝባዊ አመጽ መቀስቀስ ወንጀል የሚል ነው።
በ2ኛ ክስ በተመለከተ ደግሞ የጥላቻ ንግግርንና ሀሰተኛ መረጃን ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁ 1185/2012 አንቀጽ 4 እና 7/4 በመተላለፍ በታሳስ 3 ቀን 2014 ዓ.ም በአንድ የዩቱዩብ ቻናል ሀሰተኛ መረጃ አሰራጭተዋል የሚል ክስ በዐቃቤ ሕግ ክስ ቀርቦባቸው ነበር።
በ3ኛ ክስ ደግሞ የወንጀል ህግ ከንቀጽ 32 /1ሀ ና አንቀጽ 337 በመተላለፍ የመከላከያ ሰራዊትን እቅስቃሴን ለማሰናከልና የመከላከል አደጋ እንዲደርስ ለማድረግ በማሰብ ሀሰተኛ ወሬ በመንዛት ቅስቀሳ ማድረግ ወንጀል ተከሰዋል።
በታሪክ አዱኛ