October 19, 2024
ጠገናው ጎሹ
በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ስንነጋገር ሃይማኖት ከፖለቲካ አላስፈላጊ ጣልቃ ገብነትና አሉታዊ ተፅዕኖ በፍፁምነት (in absolute terms) ነፃ የሆነበት ጊዜና ሁኔታ ነበር ወይም ይኖራል ከሚልና ከገሃዱ ዓለም እውነታ ውጭ ከሆነ ቀቢፀ ተስፋነት አይደለም። አዎ! ተሳክቶልን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን እውን ለማድረግ ብንችል እንኳ በፍፁምነት ችግር የማይኖርበት የፖለቲካና የሃይማኖት ግንኙነት አይኖርም። ኖሮም እንደማያውቅ ሁሉ።
ርዕሰ ጉዳዬ ፈፅሞ ማነነፃፃሪያና ማወዳደሪያ የሌለውን ፣ ዘመናትን ያስቆጠረውንና ከስድስት ዓመታት ወዲህ ደግሞ ለመግለፅና ለመረዳት በሚያስቸግር አኳኋን እየቀጠለ ያለውን የባለጌና ጨካኝ የጎሳ ደምና አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኞች ሥርዓት ወደ አስከፊ የታሪክ መማሪያነት ለውጠን ትክክለኛውንና ዘላቂውን የነፃነትና የፍትህ ሥርዓት እውን ለማድረግ ብቸኛው፣ ትክክለኛውና ዘላቂው መፍትሄ ምንድን ነው? መፍትሄውን አምጦ የሚወልደው እና አጎልብቶና አይበገሬ አድርጎ ለድል የሚያበቃውስ ማን ነው? ከሚል መሠረታዊ ጥያቄ የሚነሳ እንጅ ፍፁም እንከን አልባ ከሆነ የሃይማኖትና የፖለቲካ (የመንግሥት) ግንኙነት ናፋቂነት የሚነሳ አይደለም።
ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንደ ሥርዓት በህዝብ ፈቃድ፣ ፍላጎት ፣ ተሳትፎ ፣ የማይሸራረፍ (ሉአላዊ) ሥልጣንና መብት መረጋገጥ ላይ የሚመሠረት በመሆኑ በሃይማኖትና በፖለቲካ መደባለቅ ምክንያት የሚያጋጥሙ አሉታዊ/አፍራሽ ባህሪያትንና ተግባራትን አስቀድሞ በመከላከል እና ከተፈጠሩም በኋላ የከፋ ጉዳት ከማስከተላቸው በፊት ፈጣንና ውጤታማ በሆነ የክትትልና የህግ ሥርዓት መሠረት አስፈላጊውን እርምጃ/እርምት ለመውሰድ ያስችላል እንጅ በመንግሥታዊ እና በሃይማኖታዊ ተቋማት ውስጥ በሚገኙ ግለሰቦች የእከክልኝ እንዳክልህ እና የአድርባይነት ባህሪያት ምክንያት አሉታዊ ኩነቶችን በፍፁምነት (in absolute terms) ማስወገድ የሚቻል ግን አይሆንም ።
እናም ስለ ዘመን ጠገቡና ሊያጋጥም ከሚችል አላስፈላጊ/አሉታዊ ፈታኝ ሁኔታ አልፎ በህዝብ ላይ ለመግለፅ የሚያስቸግር መከራና ውርደት ስላስከተለውና ከስድስት ዓመታት ወዲህ ደግሞ እጅግ አስከፊ፣ አሳፋሪና አስፈሪ ሆኖ ስለቀጠለው በእኩያን ገዥ ቡድኖች እና ከላይ ጀምሮ በየደረጃው በሚገኙ የሃይማኖት መሪዎችና ሰባኪዎች መካከል በግልፅ ስለሚታየው የመተሻሸት/የመላላስ ግንኙነት ግልፅነትን፣ ቀጥተኝነትን፣ ገንቢነትን፣ ትውልድ ተሻጋሪነትን ፣ ወዘተ በተላበሰ ይዘትና አቀራረብ የመናገርና የመነጋገር አስፈላጊነት/ጠቃሚነት የሚያወዛግበን አይመስለኝም ። ይህ አይነት የፖለቲካ፣ የሞራል ፣ የሥነ ልቦና እና የሃይማኖታዊ እምነት መስተጋብራዊ ማንነት፣ ምንነት፣ እንዴትና ወዴትነት ብቻ ነው ከምንገኝበት ክፉ አዙሪት አውጥቶ እጅግ ወርቃማ የሆኑ የሰብአዊና የዜግነት መብቶቻችን የሚረጋገጡበትንና የሚከበሩበትን ሥርዓተ ፖለቲካና አስተዳደር እውን ለማድረግ የሚያስችለን።
መንግሥትን (ፖለቲካን) እና ሃይማኖትን ከሚያገናኟቸው ዋነኛ ጉዳዮች መካከል የእምነት ነፃነት የመከበርን ወይም ያለመከበርን ፣ የሥነ ምግባርና የሞራል ውድቀትን ወይም ልዕልናን ፣ መሠረታዊ የሰው ልጅ መብቶች የመረጋገጥን ወይም ያለመረጋገጥን ፣ የፍትሃዊነት ወይም የኢፍትሃዊነት ጥያቄን እና በአጠቃላይ የአገርን (የህዝብን) ዘላቂ ሰላምና ደህንነት በአግባቡ የማስተናገድን ወይም ያለማስተናገድን ጥያቄዎች/ጉዳዮች በማሳያነት መጥቀስ ይቻላል። ለዚህም ነው የሃይማኖት ተቋማት መሪዎዎችና በየደረጃው የሚገኙ አገልጋዮች ሃላፊነታቸውን መወጣታቸውን ወይም አለመወጣታቸውን በንቃት መከታተልና አስፈላጊም ሲሆን ትክክል አይደላችሁምና (ተሳስታችኋልና) አስፈላጊውን እርምት አድርጉ ብሎ በግልፅ፣ በቀጥታና በአክብሮት ማስገንዘብ/ማሳወቅ የትክክለኛ አማኝነት እንጅ ፈፅሞ የሃጢአት/የመርገምት መንገድ የማይሆነው። “የነውር ወይም የሃጢአት መንገድ ነው” የሚል ካለ ከረቂቅ የማሰቢያ አእምሮና ከብቁ የማከናወኛ አካል ጋር በፈጣሪ አምሳል የተፈጠረበትን ዓላማ ለማወቅ የተሳነው ወይም እያወቀ “በፈጣሪ ያውቃል” ስም ራሱን አቅመ ቢስ በማድረግ ከራሱ አልፎ ፈጣሪውንም የስንፍናውና የፍርሃቱ ተባባሪ ለማድረግ የሚቃጣው ወይም የአድርባይ የሃይማኖት መሪዎችና ሰባኪዎች ሰለባ የሆነ ሰው መሆን አለበት።
በእውነት ስለ እውነት (በእውነተኛው አምላክ ስም) ከተነጋገርን ሲፈልጉ ሃይማኖትንና ፖለቲካን እየቀላቀሉ እና ሲያሻቸው ደግሞ ሃይማኖትና ፖለቲካ/መንግሥት የተለያዩ ናቸው የሚለውን በደምሳሳውና በሸፍጠኝነት( with ambiguity and hypocrisy) እያነበነቡ/እየሰበኩ የህዝብን መከራና ውርደት የሚያራዝሙ እኩያን ፖለቲከኞችን፣ ሃይማኖትን ወደ አትራፊ ንግድነት እየለወጡ ያሉ የሃይማኖት መሪዎችን/ሰባኪዎችን፣ የአድርባይነት ደዌ ልክፍተኛ ምሁራንን፣ የልዩ ልዩ ሙያ ባለሙያነታቸውን የርካሽ ፖለቲካ ፖለቲከኞች መሣሪያ በማድረግ ያረከሱ/የሚያረክሱ ወገኖችን ፣በመንበረ ሥልጣን ላይ ከሚፈራረቁ እኩያን ገዥዎች ጋር በሚፈጥሩት እኩይ ግንኙነት ባለሃብቶች/ኢንቨስተሮች ነን ባዮችን ፣ የእድሜ ባለፀጋነታቸውን በአግባቡ ያልተወጡ/የማይወጡ ኮስማና እድሜ ጠገብ ወገኖችን፣ በጎሳ ደምና አጥንት ስሌት የፖለቲካ እሳቤ ናላቸው የዞረ ልጆቻቸው ፣ ዘመዶቻቸው፣ በማህበረሰባቸው ውስጥ የበቀሉና ያደጉ ግለሰቦች በገዛ ወገናቸው ላይ ታይቶና ተሰምቶ በማያውቅ ሁኔታ ግፍ ሲፈፅሙ ከምር የማይቆጡና የማይገስፁ ወላጆች ተብየዎችን መሠረታዊ የሰብዕና ሃላፊነትን ስታችኋልና ተመለሱ ማለት የሚገደን ከሆን ስለ ምን አይነት ነፃነት፣ ፍትህና ሰላም እንደምንሰብክ/እንደምንደሰኩር ለመረዳት ያስቸግራል።
ክርቶስን (አምላክን) የምንከተለውና የምናመልከው የሰው ልጅ ራሱ ከፈጠረውና ከገባበት እጅግ የትበላሸና አደገኛ አስተሳሰብ እና ባህሪ ሰብሮ በመውጣት የነፃነት፣ የፍትህ፣ የርትዕ፣ የፍቅር፣ የሰላም ፣የመከባበር፣ የመተባበር ፣ የጋራ ብልፅግና (የተሳካ ህይወት) ወርቃማ እሴቶች ተጠቃሚ ለመሆን ይችል ዘንድ እስከ ህይወት መስዋእትነት የሚያደርስ ተጋድሎን የግድ እንደሚለን ሆኖና አድርጎ ስላሳየንና በመጨረሻም የግፈኞችን የስቅላት ሞት ድል የማድረጉን ሃያልነት ስላረጋገጠልን እንጅ እርሱ ተስቅሎ መነሳቱን ብቻ በባዶ (በድርጊት አልባ) የእናምናለን መነባንብና እግዚኦታ ስላስተጋባን እንዳልሆነ ለመገንዘብ የቲዎሎጅም ሆነ የዓለማዊ ፍልስፍና ሊቅነትን ወይም ሊቀ ሊቃውንትነትን ፈፅሞ አይጠይቅም። የእውቀትና ምርምር አስፈላጊነት እንደተጠበቀ ሆኖ።
ከዚህ እጅግ ግዙፍና ሃያል እውነታ አንፃር እኛ ምን አደረግን? ካደረግንስ ውጤቱን ምን ዋጠው? ካላደረግንስ ለምን? አለማድረጋችን አውቀንና አምነን በመቀበል ሆነንና አድርገን ለመገኘት ፈቃደኞችና ዝግጁዎች ነን ወይ? ለመሆኑ ሆነንና አድርገን ባልተገኘንበት እኛነት ውስጥ እውነተኛውን አምላክ ና ውረድ ማለት ምን ማለት ነው? ኧረ ለመሆኑ የዘመናት ፖለቲካ ወለድ ወንጀለኞችን እውነተኛ የሃይማኖት አርበኝነቱ ቢያጥራቸው እንኳ በአግባቡ ለመቆጣት (ለመገሰፅ) የተሳናቸው የሃይማኖት መሪዎችና ሰባኪዎች ስለ የትኛው የነገ የነፍስና የሥጋ ድነት (ስኬታማነት) ነው የሚሰብኩን?
ህሊናችንን የሚያስጨንቁና ሊያስጨንቁ የሚገባቸው ጥያቄዎች እጅግ አያሌዎች ናቸው። ለምን? ቢባል ነገረ ሥራችን (ዲስኩራችን/ስብከታችን) እና የኖርንበትና እየኖርንበት ያለው እጅግ ግዙፍና መሪር እውነታ ተለያይተው መውደቃቸውን ዘወርና ቆም ብለን እንኳ ለማየትና ለመጋፈጥ ወኔው የለንምና።
የመለኮታዊው/የሃይማኖታዊው ዶግማ እንደተጠበቀ ሆነ በሃይማኖት ተቋማት መሪዎችና በባለ ልዩ ልዩ ማእረግ አባላት ስለሚፈፀሙት ግዙፍና አስቀያሚ ስህተቶች ምንነት፣ ለምንነት፣ እንዴትነት እና ከየት ወደ የትነት ግልፅነትን፣ ቀጥተኛነትን፣ ተአማኒነትን፣ መከባበርንና ገንቢነትን በተላበሰ ሁኔታ መናገርና መነጋገር ነውርና ሃጢአት ሳይሆን ለምድራዊውም ሆነ ተስፋ ለምናደርገው ከሞት በኋላ ህይወት ስኬታማነት ጠቃሚነቱ የማያጠያይቅ ስለሆነ “የፈጣሪ እንጅ የእኔ/የእኛ ጉዳይ አይደለም” በሚል የራስን ልክ የለሽ ድክመት ለመሸፈን መሞከር አድርባይነት ወይም ልክ የለሽ ፍርሃት እንጅ ሌላ ሊሆን አይችልም። ሰውን ከረቂቅ የማሰቢያ አእምሮና ከብቁ የማከናወኛ አካላ ጋር ለታላቅ ዓላማ የፈጠረበትን ምክንያት በአግባቡ ባለመጠቀም ራስን አቅመ ቢስ/ፋይዳ ቢስ በማድረግ የሚገኝ ምድራዊ ነፃነት፣ ፍትህና ሰላም ወይም ሰማያዊ ህይወት ፈፅሞ የለም።
ንፁሃን የአገር ልጆች (ዜጎች) በእኩያን ዥዎች ፖለቲካ ወለድ ወንጀል ምክንያት በገዛ ሃገራቸው የምድራዊ ሲኦል ሰለባዎች በሆኑበትና እየሆኑ ባሉበት እጅግ ግዙፍና መሪር እውነታ ውስጥ የገዳይና የአስገዳይ ገዥ ቡድኖች ጠርናፊ (አለቃ/አዛዥ) የሆነውን አብይ አህመድን ለማወደስ ቃላት የሚያጥራቸውን የጵጵስና ማእረግ የተሸከሙ ካድሬዎችንና ያንን አይነት እጅግ ጨካኝና አሳፋሪ ውዳሴ አዳምጠው ወዲያውም ሆነ ዘግይተው ከምር ነውር ነው ለማለት ያልደፈሩ ፓትርያክና ጳጳሳት ሃይማኖትንና አማኞችን እንዴትና መቸ ሊታደጉ እንደሚችሉ ለመረዳት፣ ለማስረዳትና ለማሳመን የሚችል ቅን፣ ሚዛናዊና ተቆርቋሪ የሆነ ህሊና ያለው የአገሬ ሰው የሚኖር አይመስለኝም። በፍፁም!!
እናም ፖለቲካ ወለድ ወንጀልንና ሃይማኖታዊ እምነትን ያለ አግባብ እየደበላለቁ የመከረኛውን ህዝበ ሰቆቃና ውርደት ያራዘሙና በማራዘም ላይ የሚገኙ ወገኖችን ገንቢና የምር በሆነ አቋምና ቁመና በቃችሁ በማለት ከቻሉ የሁሉም አይነት ነፃነት የሚከበርበትን ሥርዓት እውን ለማድረግ የሚደረግን ተጋድሎ በሚያግዝ ምንነትና ማንነት ላይ እንዲገኙ ፣ ይህን ሆነውና አድርገው ለመገኘት ወኔው የማይኖራቸው ከሆነ ግን ቢያንስ ከባለጌ፣ ከሸፍጠኛ፣ ከሴረኛና ከጨካኝ ገዥ ቡድኖች ጋር በአድርባይነት እየተሻሹ የህዝብን መከራና ውርደት ከማራዘም እንዲታቀቡ (እንዲቆጠቡ) ሊነገራቸው ይገባል። አዎ! ይህንን ያህልና በዚህ ደረጃ ካልተቆጣንና ካላመረርን ዘመን ጠገብ ከሆነውና ከስድስት ዓመታት ወዲህ ደግሞ እንኳስ ለማመን ለማሰብም በሚከብድ ሁኔታ ወደ መቀመቅ ( ወደ ጥልቅና ውስብስብ አዘገቅት) ይዞን በመውረድ ላይ ያለውን የጎሳ ደምና አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኞች ሥርዓት ተቋቁመንና ድል ነስተን የሚበጀንን ሥርዓት እውን ማድረግ ፈፅሞ አይቻለንም።
አዎ! በእውነት ስለ እውነት ከተነጋገርን የሃይማኖትና የፖለቲካ መስተጋብር (የሁለትዮሽ ግንኙነት ) ትክክለኛ፣ ጤናማ ፣ገንቢና ውጤታማ ሊሆን የሚችለው ለዘመናት የመጣንበትና ከስድስት ዓመታት ወዲህ ደግሞ ለማመን በሚከብድ ሁኔታ ተዘፍቀን የምንገኝበት የጎሳ ደምና አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኞች እና ሃይማኖትን ለግልና ለቡድን ጥቅማቸው የገቢ ምንጭነት ከመጠቀም አስቀያሚ ባህሪና ተግባር አልፈው የፖለቲካ ወለድ ወንጀል ምርኮኛ/ሰለባ ያደረጉና በማድረግ ላይ የሚገኙ የሃይማኖት መሪዎች (አባቶች) ተብየዎች በሚተሻሹበትና በሚተቃቀፉበት መሪር ሁኔታ ውስጥ ሳይሆን ፅዕኑነትና ዘላቂነት ባለው የተባበረ ተጋድሎ እውን በሚሆን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አማካኝነት ብቻ ነው።
መቸም የገዛ ራሳችንን ግዙፍና መሪር እውነታ በመጋፈጥ የሰብአዊ ፍጡርነታችንንና የዜግነት መብታችንን አውቆና ተቀብሎ በፍቅር፣ በመከባበርና በመተባበር የሚያስተናግደንን ሥርዓተ ዴሞክራሲ እውን ለማድረግ ወኔው ሲያጥረን ሰንካላ የሰበብ ድሪቶ መደረት ክፉ አባዜ ሆኖብን ነው እንጅ ነፃነት፣ ፍትህ፣ ርትዕ፣ ሰላም፣ ፍቅር፣ አብሮነት፣ እኩልነት፣ ወዘተ የክርስቶስ (የሃይማኖታዊ እምነት) መገለጫወች መሆናቸውንና ለተግባራዊነታቸውም አስፈላጊውን ዋጋ መክፈል ለምድሩም ሆነ ከሞት በኋላ ተስፋ ለምናደርገው ህይወት ታላቅ ግብአት እንደሆነ በሰላ አንደበቱ የሚሰብክ የሃይማኖት መሪ ወይም ባለሌላ ማእረግ አገልጋይ አማኞቹን ጨመሮ እጅግ አያሌ ንፁሃን ወገኖች የግፍ አሟሟትና የቁም ሰቆቃ ሰለባዎቻቸው ያደረጉ ባለጌና ጨካኝ ገዥ ቡድኖችን በደፋርነት/በቁርጠኝነት አለመገሰፁ አልበቃ ብሎ በየሰበብ አስባቡ ሲያመሰግን፣ ሲያወድስ፣ ሲቀኝ፣ እና በአጠቃላይ ተዋርዶ ሲያዋርድ ከመታዘብ የከፋ የሃይማኖትና የሞራል ውድቀት ፈፅሞ የለም።
አዎ! በእውነት ስለ እውነት ከተናገርንና ከተነጋገርን የሩብ ምዕተ ዓመቱ የህወሃት/ ኢህአዴግ የጎሳ ደምና አጥንት ስሌት ፖለቲካ ሰለባ ሆኖ የቆየውን ሃይማኖታዊ እምነት ህዝብ በህወሃት ላይ የነበረውን ጥላቻ ተጠቅመው ሥልጣነ መንበሩን የተቆጣጠሩት ህወሃት ወለድ ኦህዴድ/ብልፅግናዎች ይበልጥ አስከፊና አደገኛ በሆነ ሁኔታ ከሸፍጥ፣ ከሴራና ከጭካኔ አገዛዛቸው ጋር እያደባለቁ የቀጠሉበትን ፖለቲካ ወለድ ግዙፍና መሪር እውነታ ከምር ተረድተን ከዚህ ለመውጣትና ለዜጎቿ ሁሉ የምትመች ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የሚደረገውን ተጋድሎ ከግብ ከማድረስ ውጭ ሌላ አማራጭ ፈፅሞ የለም! አይኖርምም!
በአድርባይነት (መስሎና አስመስሎ በማደር) ክፉ ደዌ ልክፍተኝነት ከፖለቲካ ወለድ ወንጀል ማምረቻና ማከፋፈያ ቤተ መንግሥት ጋር የሚተሻሹና የሚርመጠመጡ የሃይማኖት መሪዎች ፣ ጳጳሳት ፣ ሊቀ ጳጳሳት ፣ ሊቀ ሊቃውንት ፣ ሊቀ ጠበብት፣ ዲያቆናት፣ ሊቀ ዲያቆናት፣ አባ ተብየዎች ፣ ሸሆች፣ ግራንድ ኢማሞችና ሙፍቲዎች ፣ ካርዲናሎች ፣ነብያት ተብየዎች ፣ ፓስተሮች፣ ሰባኪያን በሚተራመሱበት ግዙፍና መሪር እውነታ ውስጥ ሃላፊነትንና ተጠያቂነትን ከእኩያን ገዥ ቡድኖች ብቻ መጠበቅ መሠረታዊ የሆነ የፖለቲካ ድንቁርና ፣የሃይማኖታዊ እምነት ህፀፅ እና የሞራል ጉስቁልና ካልሆነ ሌላ ምን? በዚህ ልክ ካልተናገርንና ካልተነጋገርን እና በተገቢው/በክክለኛው ፍኖተ ህልውና ፣ ነፃነት፣ ፍትህ፣ ርትዕ፣ እኩልነት፣ ፍቅር፣ ሰላምና የጋራ እድገት ላይ ተሰባስብን ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትና ዴሞክራሲያዊት አገር ምሥረታ ካልገሰገስን አሁን ከምንገኝበት አስከፊና አደገኛ የፖለቲካና የሃይማኖት መደበላለቅ ቀውስ ሌላ መውጫ መንገድ ፈፅሞ የለም። ሊኖር የሚችለው ከሰሞኑ እንዳየነው አይነት የሥርዓቱ ጉልቾች መለዋወጥን/የቆሻሻ ግባና ቆሻሻ ውጣ ( garbage in , garbage out ) ፖለቲካን እየተከተሉ በአድርባይነት በመርመጥመጥና የአዞ እንባ በማንባት በህዝብ የነፃነትና የፍትህ ተጋድሎ ላይ ቀዝቃዛ ውሃ የሚቸልሱ የሃይማኖት መሪዎችንና ሰባኪዎችን ተሽክሞ መቀጠል ነው ። ምርጫችን መጀመሪያው እንጅ ለዘመናት የመጣንበት ሁለተኛው እንደማይሆን ተስፋ አደርጋለሁ።
እናም የርዕሰ ጉዳዬ መነሻና ማጠንጠኛ ለዘመናት ለመጣንበትና አሁንም እጅግ አስከፊ ሆኖ ለቀጠለው የሃይማኖትና የእኩያን ፖለቲካ ሥርዓት መደባለቅ ( ያልተቀደሰ/የተረገመ ግንኙነት) ለሁለንተናዊው ቀውሳችን/ውድቀታችን ከዋነኛ ምክንያቶች አንዱ መሆኑን እየመረረንም ቢሆን አምነንና ተቀብለን ፈፅሞ ወደ ኋላ ለማይመለስ የነፃነትና የፍትህ ተጋድሎ የምንችለውን ሁሉ ማድረግ የነገ ሳይሆን የዛሬ ታሪካዊ ተልእኳችን መሆን አለበት ነው።
ለዚህ እውን መሆን ደግሞ በትጥቅ ትግል የፖለቲካ ታሪካችን በመነሻ ምክንያትም (justified cause) ይሁን መሬት ላይ በሚታየው በእጅጉ አበረታች የሆነ የአርበኝነት ውሎና የተገራ ዲስፕሊን ( truly encouraging operational discipline and disciplinary actions) በመካሄድ ላይ ያለውን የአማራ ፋኖ እና የሌሎች ዓላማውንና ግቡን የሚጋሩ የነፃነትና የፍትህ ታጋይ ወገኖችን ተጋድሎ ሂሳዊ በሆነ ሁለገብ ድጋፍ/ተሳትፎ የማገዙ ጉዳይ በፍፁም ለነገ ሊባል የሚገባው ጉዳይ መሆን የለበትም ።
እናም ልብ ያለው ልብ ይበል!