በአሁኑ ጊዜ ሁለት የፋኖ አሰላለፎች አሉ:: መኖር ያልነበረበት:: አንከር ሜዲያ ከሁለቱም አሰላለፎች፣ ሁለት ፋኖ መሪዎች ጋር ቃለ ምልልስ አድርጋለች፡፡ ሁለቱን አደመጥኩ፡፡ በሰማሁት ነገር ተደስቻለሁ:: ትልቅ ተስፋ እንድሰንቅም አድርጎኛል:: የአማራ ህዝባዊ ድርጅት የፖለቲካ ዘርፍ ሃላፊ ነው መስለኝ፣ ከተሳሳትኩ አርሙኝ፣ ረዳት ፕሮፌሰር ጌታ አስራደ፣ ከአማራ ፋኖ በጎንደር አመራር አንዱ ሲሆን፣ ሌላው የአማራ ፋኖ በጎጃም ምክትል ሰብሳቢና የፖለቲካ ዘርፍ ሃላፊ ፋኖ ጠበቃ አስረስ ማረ ዳምጤ ነበር፡፡
እነዚህ ሁለት የፋኖ መሪዎች አንድ አይነት ነገር ነው የተናገሩት:: የአንድነትን አስፈላጊነት ነው በአፅንዎት የገለፁት::
“የአማራ ህዝብ ካለው አቅም አጻንር፣ የፋኖ ሓይል ካለው አቅም አኳያ ከዚህ በላይ መስራት እንችላለን፣ ይገባናል” ያለው አስረስ ማረ ዳምጤ፣ የዓላማ የግብ የአካሄድ የስትራቴጂ የታክቲክ ልዩነት በምንም ተዓምር በፋኖ መካከል እንደሌለና፣ ፋኖ ከታች ወደ ላይ እያደረገ የመጣ እንደመሆኑ ፣ አሁን በቅርጽ በአደረጃጀት ጉዳይ መስተካከል ያለባቸው ጉዳዮች እንዳሉ አምኗል፡፡ ከሌሎች የፋኖ አደረጃጀቶች ጋር ውይይቶች፣ ንግግሮች እየተደረጉ እንደሆነ የተናገረው አስረስ፣ የ”ችርቻሮ ድል” ብሎ ከጠራቸው ከታክቲካል ድሎች ወደ ወሳኝ፣ ጦርነት በአሸናፊነት ወደ ሚያጠናቅቁ ስትራቴጂክ ድሎች መሸጋገር የግድ እንደሆነ አሳስቧል፡፡ በአንድነት እንነሳ ሲል ጥሪ አቅርቧል፡፡
ፋኖ ጌታ አስራደም በበኩሉ፣ ከሌሎች ወንድሞቻችን ጋር ውይይቶች እያደረግን ነው፣ በቅርቡም አንድ ሆነን መልካሙን ዜና ለህዝብ እናበስራለን ሲል ትልቅ ተስፋ ሰጥቷል፡፡ የአማራ ፋኖ አንድነት ድርጅት ውስጥ ያለን፣ ከሌሎች ጋር ተነጋግረን፣ ሁሉንም አሸናፊ፣ አንዱ የበላይ ሌላው የበታች ያልሆነበት አሰራር ለመዘርጋት አበክረው እንደሚሰሩ ገልጿል፡፡
ፋኖ ጌታ አስራደም ሆነ ፋኖ አስረስ፣ የሰጡትን አስተያየቶች ላዳመጠ ሰው፣ ከዘመነ ካሴና ከ እስክንድር ነጋ በተጨማሪ፣ ፋኖ ተዋጊዎች ብቻ ሳይሆን እጅግ በጣም ብዙ የፖለቲካ ብቃት ያላቸው፣ ብዙ ወገኖች ውስጡ እንዳሉትም በግልጽ ያመላከተ ነው፡፡
ወደ አንድነት እስከመጡ ወይም ወደ አንድነት ለመምጣት እየሰሩ እስከሆነ ድረስ፣ ሁሉንም ልናግዝ፣ ልናበረታት እንጂ ወደ ማበላለጥ መሄድ የለብንም፡፡ ማንም ይሁን ማንም፣ ለህዝብ የሚጠቅም ነገር ከሰሩ መደገፍ አለብን፡፡ ፋኖ ጌታ አስራደ የተናገረው ነገር አንዷም ነገር ጠብ የምትል አይደለችም፡፡ አስረስም የተናገረው እንደዚሁ፡፡ ጎራ ይዘን አስረስን እያሳነስን ጌታ አስረዳን ማሞገስ፣ ጌታ አስራደን እያሳነስን አስረስን ማወደስ ነውር ብቻ ሳይሆን ጸረ ፋኖነት ነው፡፡ ፋኖዎች እንድ እንዳይሆኑ የማድረግ ተግባር ላይ እንደመሰማራት ነው፡፡
ይህን ስል የፋኖ መሪዎች ስህተት ሲሰሩ መተቸት፣ ጥሩ ሲሰሩ መመስገን የለባቸውም ማለቴ አይደለም፡፡ ከዚህ በፊት አስረስን ተችቼ ጽፊያለሁ፡፡ ከዚህ በፊት ከነ ጌታ አስራደ ጋር ያለን ፋኖ እያሱን ተችቼ ጽፊያለሁ፡፡ ከሁለቱም አሰላለፎች፡፡ አሁንም ደግሞ ከሁለቱም ጥሩ ነገር ስሰማ፣ ደስታዬ ገልዣለሁ፡፡ ሁለቱም ጥሩ እያደረጉ፣ አንዱን አሞግሶ ለሌላ ዝም ማለት ግን ትክክል አይደለም፡፡