August 27, 2024
81 mins read

ከድጡ ወደማጡ፤ ከአንድ ዕዳ ወደ ሌላ ዕዳ! የአዙሪት ጥምጥም ውስጥ የመግባት አባዜ!

ፈቃዱ በቀለ (/)

ነሐሴ 27  2024(ነሐሴ 20 216)    

 

መግቢያ

አንድ ሰሞን እንደዋና መነጋገሪያ ሆኖ የሚናፈሰው ዜና ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት(IMF) የድረስልኝ ጥሪ ካቀረበች በኋላ ከገንዘብ ድርጅቱ የ2.9 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ብድር ለማግኘት ስምምነት ላይ እንደደረሰች ነበር። እዚህ ዐይነቱ ስምምነት ላይ ለመድረስ የገንዘብ ድርጅቱ ተጠሪ የሆኑት ወይዘሮ ሶላኒ ጄን አዲስ አበባ ከጥቅምት 29 ጀምሮ እስከ ህዳር 8፣ 2019 ዓ.ም ድረስ እንደቆዩና ከመንግስቱ ተወካዮች ማለትም፣ የኢኮኖሚና የፋይናንስ ሚኒሰተሩና የሚኒስተር ዲኤታው፣ እንዲሁም ከጠቅላይ ሚኒስተሩ ጋር እንደተስማሙ ተነግሮን ነበር።  እ.ኢ.አ በታህሳስ 5፣ 2012 በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ ታትሞ በወጣው ሀተታ መሰረት ኢትዮጵያ ለዓለም የገንዘብ ድርጅቱ የይድረስልኝ ጥያቄ ያቀረበችው ከማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት ለመላቀቅነው የሚል ነበር።   የገንዘብ ድርጅቱ ኤክስኪዩቲቭ ቦርድ ስምምነቱን በመቀበል የብድሩን መሰጠት ሲያፀድቅ፣ ይህ 2.9 ቢሊዮን ዶላር በአንድ ጊዜ የሚለቀቅ ሳይሆን በሶስት ዐመት ውስጥ ቀሰ በቀስ የሚለቀቅና ዕዳውም ከአስር ዐመት በኋላ የሚከፈል ነው የሚል ነበር። የኢትዮጵያ መንግስት የብድሩን ስምምነት ከፈረመ በኋላ የገንዘብ ድርጅቱ ያኔውኑ 308.4 ቢሊዮን እንድሚለቅ ቃል-ቂዳን ገብቶ ነበር።  እንደተገነገርን ከሆነ ወለዱ ወደ ዜሮ የሚጠጋ ነው።

ሰሞኑን ደግሞ የአገራችንን ኢኮኖሚ በከፍተኛ ደረጃ የሚያናጋ፣ የብድሩን መጠን የሚቆልልና የመክፍል ኃይልንም የሚያዳክም ሌላ የብድር ስምምነት ላይ ተደርሷል። በአቢይ አህመድ የሚመራው አገዛዝና የብሄራዊ ባንኩ የዓለም የገንዘብ ድርጅት(IMF) ያቀረበውን የኢትዮጵያን ብር በገበያ ተዋንያን ወይም በጠያቂና በአቅራቢ እንዲወሰን(Floating Exchange Rate) የማድረጉን ቅድመ-ሁኔታ ከተቀበሉ በኋላ የገንዘብ ድርጅቱ $3.4 ቢሊዮን በብድር መልክ እንደሚሰጥ ሲስማማ፣ የዓለም ባንክ ደግሞ አገር ቤት ውስጥ የሚያድገውን ኢኮኖሚ(Home-Grwon Economy) “የጥገና ለውጥ” ለመደገፍ ሲል $ 500 ሚሊዮን በብድር መልክ ሲሰጥ፣ በሌላ ወገን ደግሞ በዕርዳታ መልክ $1 ቢሊዮን እንደሚሰጥ ስምምነት ላይ ተደርሷል።  የአቢይ አገዛዝና የብሄራዊ ባንኩ የኢትዮጵያ ብር በገበያ ተዋንያን እንዲወሰን የሰጡት ዋናው ምክንያት ከቁጥጥር ውጭ የወጣውን የጥቁር ገበያ ለመዋጋት ነው ሲሉ፣ በተጨማሪም በዚህ ዐይነቱ የገንዘብ ትመና አማካይነት ወደ ውጭ የሚላከው ምርት ሲስፋፋና ጠያቄውም ሲያድግ፣ በዚያው መጠንም ከውጭ የመዋዕለ-ነዋይ አፍሳሾች በመምጣትና በማኑፋከቸሪንግ መስኩ በመሳተፍ ለኢኮኖሚው ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንደሚያድርጉ ነግረውናል። ከዚህም ባሻገር ይህ ዐይነቱ የገንዘብ ትመና የውስጥ አምራቾችን የሚያነቃቃና በኢኮኖሚው ውስጥ እንዲሳተፉ መንገዱን ያመቻቻል የሚል ዕምነት እንዳላቸው አብስረውልናል። ይሁንና ግን ይህ ዐይነቱ “የገንዘብ የጥገና ለውጥና ሌሎችም” በነፃ ገበያ ስም  ህወሃት ስልጣን ከያዘ ጀምሮ፣ በተለይም ከ1993 ዓ.ም ጀምሮ በተከታታይ ተግባራዊ የተደረጉት የጥገና ለውጦች በአገራችን ምድር በተለይም የውስጡን ገበያ ለማስፋፋትና ለማሳደግ የሚችሉ መሰረታዊ ለውጥን እንዳላመጡ ለማረጋጋጥ ይችላል። የማኑፋክቸሪንግ መስኩ በተለይም ለመሰረታዊ ለውጥና ለውስጥ ገበያ መስፋፋት የሚያመቸውና እንደ ጀርባ አጥንት በመሆን ሊያገለግል የሚችለው የማሽን ኢንዱስትሪ አልተስፋፋም። በህወሃት የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ መሆን የተነሳ በተለይም የቀድሞው ዐይነት የማባዛት ኃይሉ በጣም ደካማ የሆነ እንደስኳር ፋብሪካና የመጠጥ ፋብሪካዎች ነው የተስፋፉት። ከዚህም በሻገር እንደሆቴል ቤቶች የመሳሰሉት በመስራትና በመስፋፋት በተለይም የአገልግሎት መስኩ በከፍተኛ ደረጃ እንዲያድግ ነው የተደረገው። ይህ ዐይነቱ ውስጠ-ኃይሉ በጣም ደካማ የሆነ የአገልግሎት መስክ ደግሞ የዋጋ ግሽበትን በከፍተኛ ደረጃ እንዲናር ከማድረግ በሻገር፣ የስራ መስክ ለሚፈልገው በተለይም ለወጣቱ መክፈት ያልቻለ ነው። ሰለሆነም በህውሃት ዘመን አደገ የሚባለው ኢኮኖሚ ዋናው መሰረቱ ማኑፋክቸሪንግ፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሳይሆኑ የአገልግሎት መስኩ ብቻ ነበር ማለት ይቻላል። በዚህም ምክንያት ነው ህውሃት ስልጣን ላይ ከወጣ ጊዜ ጀምሮ ተግባራዊ የተደረገው የተቋም ማስተካካያ ፖሊሲና(Structural Adjustment Programs) አቢይ አህመድ ስልጣንን ከያዘ ወዲህ ከዛሬ ስድስት ዓመት በፊትና በኋላ “አገር ውስጥ የሚያድግ ኢኮኖሚ የጥገና ለውጥ” (Home-Grown Economy Reforms) በሚል ስም የተካሄደው  “ የጥገና ለውጥ” የአገራችንን መሰረታዊ ችግሮች፣ በተለይም ኋላ-ቀርነትንና ድህነትን ለመቅረፍ ያልቻሉት።

ስለሆነም ሰሞኑን የኢትዮጵያን ብር በገበያ ተዋንያን እንዲተመን ማድረጉ ያለውን የውስጥ የተቋም ችግር(Structural Problems) የሚያባብሰው እንጂ መሰረታዊና አስተማማኝ ለውጥ ለማምጣት በፍጹም አይችልም። ይህ ዐይነቱ የኢትዮያን ብር በገበያ ተዋንያን እንዲተመን ማድረጉ የብሄራዊ ባንኩን መሰረታዊ ደንብና ኃላፊነትን የሚጥስ ነው። እንደሚታወቀው የአንድ አገር የብሄራዊ ባንክ ዋና ኃላፊነትና ተግባር የአገሩን ብር እንዲጠነክር አስፈላጊውን እርምጃዎች መውሰድ ሲሆን፣ ከዚህም በላይ ኢኮኖሚው በሚፈልገውና በሚሸከመው መሰረት በንግድና በሌሎች ባንኮች አማካይነት ኢኮኖሚውን ለማንቀሳቀስ የሚያስችል ገንዘብ አትሞ ማቅረብ ነው። የአንድ አገር ገንዘብ ጥንካሬ ሊወሰን የሚችለው ደግሞ ብሄራዊ ባንኩ በሚወስደው የተለያዩ የገንዘብ ፖሊሲዎች፣ ለምሳሌ ወለድን ከፍ በማድረግ ሲሆን፣ ከዚህም በላይ መንግስት ጠቅላላውን ኢኮኖሚ ለማጠንከርና ለማሳደግ፣ እንዲሁም የውስጡን ገበያ ለማስፋፋት ተግባራዊ በሚያደርገው ፖሊሲ አማካይነት የሚወሰን ነው። ከዚህም በላይ የህዝቡን የተለያዩ ፍላጎቶች ለማሟላት ሲባልና ትርፍም ለማትረፍና በተከታታይ ኢንቬስት ለማድረግ እንዲቻል የግዴታ በግል መስኩ የሚሰማሩ የአገር ውስጥ ካፒታሊስቶች በስራ-ክፍፍል መሰረት የተለያዩ ምርቶችን ማምረትና ለበላተኛው ማቅረብ የገንዘብን በፍጥነት መሽከርከከርና መጠንከር እንደዋና የኢኮኖሚ መሰረተ-ሃሳቦች ሆነው ሊወሰዱና በተግባርም መዋል ያለባቸው የኢኮኖሚ መሰረታዊ ሃሳቦች ናቸው። ከዚህ መሰረታዊ የኢኮኖሚ ጉዳይ ስንነሳ የአቢይ አገዛዝና የብሄራዊ ባንኩ ከዓለም የገንዘብ ድርጅት ትዕዛዝ በመቀበልና በመስማማት ተግባራዊ የሚያደርጉት በአቅራቢና በጠያቂ የሚደነገግ የገንዘብ ትመና ፖሊሲ የብሄራዊ ባንኩን የአሰራር ደንብና ኃላፊነትን የሚጥስና በህግም የሚያስጠይቅ ነው። ነገሩን ጠጋ ብለን ስንመለከት የአቢይ አህመድ አገዛዝና ብሄራዊ ባንኩ የወሰዱትና ተግባራዊ ያደረጉትና የሚያደርጉትም “የፖሊሲ ዕርምጃ” የካፒታሊስት አገሮችን፣ በተለይም የአሜሪካንን ትላልቅ ባንኮችና፣ እንደብላክ ሮክ የመሳሰሉትን የአሜሪካንን ከበርቴዎች፣ እንደ ቢል ጌትና፣ ሰከር በርግ፣ እንዲሁም ቤዞዝን የመሳሰሉትን በገንዘብ የናጠጡ ባለሀብቶችን ገንዘብ የሚያስተዳድሩትን ጥቅም የሚያስጠብቅ ነው። ምክንያቱም የዓለም የገንዘብ ድርጅቱም ሆነ የዓለም ባንክ በቀጥታ ሆነ በተዘዋዋሪ በጥቅም ከትላልቅ የአሜሪካን ባንኮችና እንደነ ብላክ ሮክ ከመሳሰሉት የገነዘብ አስተዳዳሪዎች ጋር የተሳሰሩ በመሆናቸው ነው።  ሰለሆነም አቢይ አህመድና የብሄራዊ ባንኩ የወሰዱት በማክሮ ኢኮኖሚ ስም ተግባራዊ የሆነውና የሚሆነው ፖሊሲ ኋላ-ቀርነትንና ድህነትን የሚያጠነክርና ተበዝባዥም የሚያደርገን ነው ማለት ይቻላል።  በሌላ አነጋገር በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ሰፋ ያለ የውስጥ ገበያ ለማዳበር በፍጹም አይችልም ማለተ ነው።

ይህንን ዐይነት ስምምነትና ኢትዮጵያም በስምምነቱ መሰረት ከላይ የተጠቀሰውን  የገንዘብ መጠን በብድር  መልክ ማግኘት በአንዳንድ የኢትዮጵያ  የኢኮኖሚ ባለሙያተኞች አመለካከት  አገሪቱን  እስትንፋስ  እንደሚሰጣትና  ኢኮኖሚውም ወደ ትክክልኛው አቅጣጫ  እንደሚጓዝ አመልክተዋል።  ከዚህ በተጭማሪ „አንድ አፍታ “ ተብሎ በሚታወቀው የዩቱብ ቻናል ላይ ይህንን ጉዳይ አስመልክቶ ለዶ/ር ቆስጠንጢኖስ በረኸተስፋ ከጋዜጠኛው ስለቀረበለት ጥያቄ ሲመልስ፣ የብድሩን አስፈላጊነት ሲያጠናክር፣ በተጨማሪም ምንም ጊዜ ቢሆን ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅቱ ትከሻ ለመላቀቅ እንደማንችል ምከአራት ዓመት በፊት አረጋግጦ ነበር። ከብድሩ መሰጠት ጋር የሚቀርቡ ሁኔታዎችን አሉታዊ ጎናቸውን፣ለምሳሌ እንደገንዘብ ቅነሳ የመሳሰሉት የአገሪቱን የንግድ ሚዛን ለማሻሻል አለመቻል ቢናገርምና፣ አገሪቱ ያላትን ፖቴንሽያል አለመጠቀም የቱን ያህል እንደጎዳን ቢያመለክትም- በተለይም በጊዜው ስለቻይናና ጃፓን የተናገው ግን ትክክል አልነበረም፤ አይደለምም። ቻይና እ.አ.አ በ1978 ዓ.ም  የገበያ ኢኮኖሚ የጥገና ለውጥ ለማድረግ ከጀመረችበት ጊዜ ድረስ ከዓለም የገንዘብ ድርጅትም ሆነ ከዓለም ባንክ ብድር ወስዳ አታውቅም። ይሁንና ግና በአሁኑ ወቅት የሶስት ትሪሊዮን ዶላር የገንዘብ ክምችት እያላት፣ እንደዚሁም ደግሞ አንድ ቲሪሊዮን ያህል ገንዝብ አፍሳ የአሜሪካንን የመንግስት ቦንድ ብትገዛና፣ ለብዙ የአፍሪካ አግሮችም ብድር ብትሰጠም፣ ከኢኮኖሚ ሎጂክ አንፃር ለመግለጽ በሚያስቸግር መንገድ ለአንዳንድ ፕሮጀክቶች ከዓለም ባንክ ብድር ትወስዳለች። የጃፓንን ጉዳይ ስንመለት ደግሞ ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ እንዳለው ሳይሆን፣ እ.አ.አ በ2008 ዓ.ም በብዙ የካፒታሊስት አገሮች የፋይናንስ ቀውስ በተከሰተበት ውቅት የካፒታሊስት አገሮች ለዓለም የገንዘብ ድርጅቱ ማስተላለፍ የነበረባቸውን የገንዘብ ድርሻ መክፍል ያቅታቸዋል። በዚህ ጊዜ የገንዘብ ድርጅቱ(IMF) ከጃፓን መንግስት $ 100 ቢሊዮን  እንደተበደረ መረጃዎች ያረጋግጣሉ።

ያም ሆነ ይህ ቻይና፣ ጃፓንና ደቡብ ኮሪያ  የራሳቸውን የኢኮኖሚ ፖሊሲ በመቀየስ ነው ውጤታማ ለመሆን የበቁት። በተለይም ጃፓንና ደቡብ ኮሪያ ከሁለቱ እህትማማች ድርጅቶች የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚ የጥገና ለውጥ እንዲያደርጉ ግፊት ቢደረግባቸውም ሃሳባቸውን አሽቀንጥረው በመጣል በማኑፋክችሪንግ ላይ የተመሰረተና ወደ ውስጥ ያተኮረ የኢኮኖሚ ግንባታ በመከተልነው አመርቂ ውጤት ለማግኘት የቻሉት። በቃለ ጥያቄ ምልልሱ ላይ ይህንን ጉዳይ አስመልክቶ ጋዜጠኛው ታዲያ እነዚህ አገሮች እንዴትና በምን ዐይነት የኢኮኖሚ ፖሊሲ ነው ውጤታማና የተስተካከለ የኢኮኖሚ ዕድገት ለማምጣት የቻሉት? ብሎ አልጠየቀም። ዶከተሩም ይህንን ጉዳይ ሳይብራራ የብድርን አስፈላጊነት ብቻ ነው አስምሮበት ያለፈው። ይህ ዐይነት በደንብ ያልተብራራ ጥያቄና መልስ ብዙ አድማጮችን ሳያደናግር እንደማይቀር በእርግጥ መናገር ይቻላል። በተለይም ደግሞ የእነዚህን ድርጅቶች ሚና በደንብ ላልተከታተለና ዕውነተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት ምን መምሰል እንዳለበት  ለማይረዳና ላላጠና ሰው የዶክተር ቆስጠንጢኖስ አባባልን አምኖ ሊቀበለው ይችላል። በተለይም   ከዓለም የገንዘብ ድርጅትና ከዓለም ባንክ ትክሻ ላይ መላቀቅ አንችልም”  የሚለው አባባል አሳሳችና በራሳችን ላይ እንዳንተማመን የሚያደርግ ነው። የዶክተሩ አገላለጽ በሳይንስና በቲዎሪ የተደገፈ ሳይሆን የገንዘብ ድርጅቱን (IMF) መንፈስን የሚያዳክም ቅስቀሳና ግፊት የሚያጠናክር ነው። ትችታዊ አመለካከት(Critical thinking) የጎደለውና በምድር ላይ የሚታዩ ተጨባጭ ሁኔታዎችን ለምን በዚህ መልክ ሊገለጹ ይችላሉ? የችግሩስ ምክንያት ምንድነው? በማለት የእነ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅቱን ኢ-ሳይንሳዊ ኢኮኖሚክ ፖሊሲ አደገኛነት ለመመርመር የሚቃጣ አይደለም።

ለማንኛውም በህወሃት መሪነት ኢሃዴግ የሚባለው አገዛዝ እ.አ.አ በ1991 ዓ.ም አገራችንን ከተቆጣጠረ በኋላ ኢኮኖሚውን ወደ ነፃ ገበያ  ለማሸጋገርና ተወዳዳሪ በመሆን መዛባትን የሚያስወግድ ኢኮኖሚያዊ አወቃቀር እንደሚዘረጋ እ.አ.አ ከ1992 ዓ.ም ጀምሮ ሰፋ ያለ ያለ የመዋቅር ማስተካከያ ፖሊሲ ተግባራዊ እንዳደረገ ይታወቃል። ይሁንና ግን ከ28 ዐመት የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ሙከራ በኋላ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ከድሮው በባሰ መልክ እንደተዛባና፣  በተለይም ደግሞ ከፍተኛ የስራ አጥነትና በቀላሉ ሊቀረፍ የማይችል ስር የሰደደ ድህነት በአገራችን ምድር እንደተስፋፋ እናያለን። በሌላው ወገን ደግሞ በጣም ጥቂት ሰዎች የናጠጠ ሀብታም በመሆን እዚህ አውሮፓ ውስጥ ማንም ገዝቶ ሊነዳው የማይችል መኪና ሲነዱና በኑሮ ሲንደላቀቁ ይታያል። ይህም ማለት እንደተነገረንና አምነንም እንድንቀበል በተደረገው መሰረት ተግባራዊ የሆነው ነፃ የገበያ ኢኮኖሚ ጥገናዊ ለውጥ በወያኔ የ27 ዓመት የአገዛዝ ዘመንና  በኋላም ላይ  ብሄራዊና ውስጣዊ ኃይል ያለው፣ እንዲሁም  ደግሞ እያደገና እየተስፋፋ በመሄድ አገሪቱንና ህዝባችን በፀና መሰረት ላይ እንዲቆሙ የሚያደርጋቸው ኢኮኖሚ ለመዘርጋት እንዳልተቻለ ነው። ይህንን ሁኔታ ለመረዳት በመጀመሪያው ወቅት የተደረገውን ጥገናዊ ለውጥና የዕዳውን ዕድገትና፣ ለምንስ ከውጭ በሚመጣ ብድር የአገራችንን ኢኮኖሚ ማሳደግ እንደማይቻል ለማሳየት እወዳለሁ። በተለይም የዕዳው ዕድገትና የኢኮኖሚው መዛባትና ድህነት መስፋፋት ከዚህ ዐይነቱ ኢ-ሳይንሳዊና ኢ-ብሄራዊ ከሆነ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ጋር በጥብቅ የተያያዘ እንደሆነ ለማረጋገጥ እሞክራለሁ።

የመጀመሪያው የገበያ ኢኮኖሚ የጥገና ለውጥ!

ወያኔ ስልጣን ከመያዙ በፊትም ሆነ ስልጣን ከያዘ በኋላም የዓለም ኮሙኒቲውን፣ በተለይም ደግሞ የአሜሪካንን ዕርዳታና ድጋፍ ለማግኘት ከፈለገ የግዴታ ከዓለም የገንዘብ ድርጅትና(IMF) ከዓለም  ባንክ ጋር መስራት እንዳለበት ነው። ሁለቱ ድርጅቶችም የሚያቅርቡለትን ቅድመ-ሁኔታዎች ከተቀበለና ተግባራዊ ማድረግ ሲችል ብቻ ነው ዕርዳታና ድጋፍ እንደሚሰጠው የተነገረው።  እንደሚታወቀውና  በምዕራቡ ዓለም፣ በተለይም በአሜሪካንና፣ ባጭሩ የዓለም ኮሙኒቲው ተብሎ በሚታወቀው አመለካከት የደርግ አገዛዝ እስከወደቀ ጊዜ ድረስ በአገራችን ምድር ተግባራዊ የሆነው የኢኮኖሚ ፖሊሲ “የሶሻሊስት ወይም የዕዝ ኢኮኖሚ “ ነው የሚል ነበር። ይህ ዐይነቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ በተለይም ከ1945 ዓ.ም በኋላ በአሜሪካን የበላይነት የሚመራውንና በእሱ አቀነባባሪነት እ.አ.አ በ1944 ዓ.ም በብሬተን ውድስ ላይ የፈለቀውንና እንደመመሪያ የሆነውን  የኢኮኖሚ ፖሊሲ የሚፃረር እንደመሆኑ መጠን መዋጋትና፣ በሌላ ለአሜሪካንና ለግብረ አበሮቿ በሚስማማውና የእነሱንም ጥቅም በሚያስጠብቀው ተፈጥሮአዊ በሆነው የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ፖሊሲ የግዴታ መተካት ያስፈልጋል ተብሎ የተደረሰበት ስምምነት ነው።  በተለይም ወደ ሶቭየት ህብረትና ወደ ግብረአበሮቿ እየተጠጋ የመጣው የደርግ አገዛዝ የአሜሪካንን   የጄኦ ፖለቲካ ስትራቴጂያዊ ጥቅምና   አገሮችን የማከረባበት ወይም በዘለዓለማዊ ውዝግብ ውስጥ እንዲወድቁ የሚያደርገውን ሴራ የሚቀናቀን ስለሆነ በደርግ የሚመራው የሶሻሊስቱ ስርዓት ወድቆ የአሜሪካኖች አምላኪ፣ ጀርመኖች ደግሞ የእነሱ ጓደኛ(friendly) ብለው በሚጠሩት  መንግስት መተካት  እንዳለበት አብዮቱ ከፈነዳ ጀምሮ አጥብቀው የሰሩበት ሁኔታ ነው።  ይህ ግባቸው እንዲሳካላቸው የተለያየ ስም ያነገቡ የግራም ሆነ የቀኝ አዝማሚያ ያላቸውን የውስጥ ኃይሎችን በማስታጠቅና በገንዘብ በመደጎም በአገራችን ላይ ከፍተኛ ዘመቻ አድርገዋል፤ ጦርነትም ከፍተዋል።

በዚህም መሰረት በተለይም እ.አ.አ ከ1980 ዓ.ም በፕሬዚደንት ሬገን አስተዳደርና በወይዘሮ ቴቸር አጋዝኘነት የዋሽንግተን ስምምነት(The Washington Consensus) የሚባለው፣  በተለይም የአፍሪካን አገሮችንና ሌሎችም የሶስተኛው ዓለም ተብለው የሚጠሩ አገሮች እንዲቀበሉት የተዘጋጀው የመዋቅር ማስተካከያ ፕሮግራም”(Structural Adjustment Programs) ወይም የኒዎ-ሊበራል አጀንዳ ተብሎ የሚጠራው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ህወሃት ስልጣን ላይ ሲወጣ እንደ ቅድመ-ሁኔታና የአገሪቱ  የኢኮኖሚ ፖሊሲ መመሪያ ሆኖ ቀረበለት። ፖሊሲው ከፀደቀ በኋላ ቀደም ብሎ እ.አ.አ በ1980 ዓ.ም ጋና፣ ቀጥሎ ደግሞ ናይጄሪያና ሌሎች የአፍሪካ አገሮች ተራ በተራ ተግባራዊ የተደረገ ፖሊሲ ነው። ፖሊሲው ጋና ውስጥ ተግባራዊ ከተደረገ ከጥቂት ዐመታት በኋላ ኢኮኖሚዋ እየተሻሻለና ወደ ውስጥ የማምረት ኃይሏ እያደገና የስራ መስክ እየከፈተ የመጣ ሳይሆን ይባስ ብሎ የስራ-አጥ ቁጥሩ እየጨመረና፣ በዚያው መጠንም የውጭው ንግድ እየተዛባና ዕዳውም እያደገ እንደመጣ ኢምፔሪካል ጥናቶች ያረጋግጣሉ። ስለሆነም የጋና ኢኮኖሚ የባሰውኑ በካካኦ ምርት ላይ ብቻ እንዲመካ በማድረግ ይህ ምርት እየተስፋፋ  ሊመጣ ችሏል። ጋናም ወደ ውስጥ ያተኮረና አስተማማኝ ወደ ሆነ የውስጥ ገበያ አላመራችም። ለውስጥ ገበያ ማደግ እንደ ዋና መሰረት ወደሆነው የማኑፋክቸሪንግ፣ በተለይም ደግሞ በማሺን ኢንዱስትሪ ላይ ለማትኮር ባለመቻሏ ልዩ ልዪ ለኢንዱስትሪ ተከላ የሚያገለግሉ ማሺኖችን መስራት አልቻለችም።

እ.አ.አ በ1989 ዓ.ም በሶቭየት ህብረት የሚመራው የሶሻሊስቱ ግንባር ሲፈራርስ ለአሜሪካንና ለግብረ አበሮቿ ይህን  የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተቀባይነት እንዲኖረው  ማድረግና አገሮችንም በእነሱ ቁጥጥር ስር በማምጣት በቀላሉ መበወዝ የሚቻልበት ሁኔታ ሊፈጠር እንደቻለ የጊዜው ሁኔታ ያረጋግጣል። በተለይም በፍራንሲስ ፉኩያማ የርዕዮተ-ዓለም ፍጻሜ ተብሎ የተደረሰው መጽሀፍ የሚያረጋግጠው የአሜሪካንን የበላይነት የአፀደቀ እንጂ የኋላ ኋላና ዛሬም እንደምናየው በዓለም አቀፍ ደረጃ የሊበራል ዲሞክራሲን ተግባራዊ ያደረገና፣ በተለይም ኋላ-ቀሩ የሚባሉ አገሮችን ወደ ብልጽግና እንዲያመሩ ያደረገና፣ የካፒታሊዝምን ስልተ-ምርት በተሟላ መልኩ ተግባራዊ እንዲያደርጉ የረዳቸው ፖሊሲ አይደለም። በአንፃሩ ይህ የኒዎ-ሊበራል ፖሊሲ ኢንፎርማል ሴክተር በመባል የሚታወቀውን የተዘበራረቀ ኢኮኖሚ መስክ እንዲፈጠር በማድረግ ግልጽነት ያለው የገበያ ኢኮኖሚና በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የሚመካ የካፒታሊስት ኢኮኖሚ እንዲያድግና ህብረተሰቡን እንዲያስተሳስር የሚያስችል የኢኮኖሚ ስርዓት እንዳይገነባ ያገደና የሚያግድ ነው።

ወደ አገራችን ተጨባጩ ሁኔታ ስንመጣ፣ ወያኔ የተቋም ማስተካከያ ወይም የኒዎ-ሊበራል ፖሊሲውን አሜን ብሎ ከተቀበለ በኋላ በዓለም የገንዘብ ድርጅቱ  „ፍልስፍና“ መሰረት  ለነፃ ገበያ ኢኮኖሚ  ፖሊሲ ተግባራዊነት የሚያመቹና ፍቱን  መፍትሄም ሊያመጡ ይችላሉ የተባሉት ዝርዝር መሰረታዊ ነገሮች ተግባራዊ ይሆኗሉ። ይህንን ጉዳይ በተለያዩ ጊዜያት እየደጋገምኩ ባቀርብም በአብዛኛዎቹ ዘንድ ይህን ያህልም ግንዛቤ ውስጥ የገባና፣ ዛሬ አገራችን ለምትገኝበት ውድቀትና ለህዝባችን ድህነት ተጠያቂ ለመሆኑ በጭንቅላት ውስጥ የተቀረፀ ሃሳብ ለመሆኑ እጠራጠራለሁ። የሁላችንም አስተሳሰብ ወያኔን በመጥላትና እሱን በማስወገድ ላይ ብቻ ያተኮረ ስለነበርና አሁንም ስለሆነ ከበስተጀርባው ሆኖ የአገራችንን የእኮኖሚ ፖሊሲ ማን እንደሚያወጣና ተግባራዊም እንዲሆን የሚገፋፋው የዓለም ኮሙኒቲው በሚለው ላይ ይህን ያህልም ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ አይደለም። ዛሬም ቢሆን አቢይ አህመድንና አገዛዙን በመጥላት ላይ ያተኮረ እንጂ አቢይ አህመድ የአሜሪካንን ትዕዛዝ በመቀበልና በዓለም የገንዘብ ድርጅትና በዓለም ባንክ በመመክር ድህነትንና ኋላ-ቀርነትን እንደሚያስፋፋ ይህንን ያህልም ግንዛቤ የለንም። በተለይም በዚያው ሰሞን በዶ/ር አክሎግ ቢራራ ዕዳን ወይም ብድርን አስመልክቶ በተለያዩ ድህረ-ገጾች ላይ የቀረበው ጽሁፍ፣  ጸሀፊው ወያኔ ስልጣንን ላይ ከወጣ ጀምሮ ተግባራዊ ያደረገውን የኒዎ-ሊበራል  የኢኮኖሚ ፖሊሲና ያመጣውን ጠንቅና፣ የዕዳው መቆለል የመዋቅር  ማስተካከያ ፖሊሲው ተግባራዊ ከመሆን ጋር የተያያዘ መሆኑን አንዳችም ቦታ ላይ በፍጹም አያመለክትም። በእሱ አመለካከትና ዕምነት የኢኮኖሚ ዕድገት እንዳለ ሲያምን፣ ይህ ዐይነቱ ዕድገት ምን ዐይነትና ብሄራዊ ባህርይ ይኑረው አይኑረው፣ በሰፊና በፀና መሰረት ላይ የተመረኮዘና ተከታታይነት ያለው ወይም የሌለው ኢኮኖሚ ዕድገት ለመሆኑ ለማሳየት አልጣረም። በተጨማሪም ለዛሬው በአገራችን ምድር ተንሰራፍቶ ለሚገኘው ድህነትና ያልተስተካከለ ዕድገት፣ እንዲሁም በብዙ ከተማዎችና መንደሮች የማዕከለኛው ዘመን ዐይነት አኗኗር ዘዴ መስፈን ከዚህ ዐይነቱ ሳይንሳዊ መሰረት ከሌለውና ከአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት ሳይሆን የዓለም ኮሙኒቲውን ለመጥቀምና በዓለም አቀፍ ደረጃ የጥቂት የካፒታሊስት አገሮችን የባሰውኑ በሀብት ለማዳበር ከተነደፈው የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ጋር በጥብቅ የተያያዘ መሆኑን ለማሳየት ወይም ለማብራራት አልጣረም።

ለማንኛውም በመዋቅር ማስተካከያው ቅድመ-ሁኔታ መሰረት፣ 1ኛ) የኢትዮጵያ ገንዘብ ከዶላር ጋር ሲወዳደር መቀነስ (devalue) አለበት። በዓለም የገንዘብ ድርጅት ዕምነት መሰረት የገንዘቡ  መቀነስ የጠቅላላውን ኢኮኖሚ ሁኔታ የሚያንፀንባርቅ ሲሆን፣ ኢትዮጵያም ወደ ውጭ የምትልከውን ምርት በቀላሉ ለመሽጥና ተወዳዳሪ በመሆን የውጭ ምንዛሬ በብዛት ታገኛለች። ይህ በራሱ ደግሞ የውጭ ንግድ ሚዛኑን ጤናማ ያደርገዋል ይለናል። 2ኛ)  በመንግስት ቁጥጥር ስር ያሉ ኩባንያዎችና የንግድ ዘርፎችን ወደ ግል ማዘዋወር። ይህ በራሱ ወደ ውስጥ የአገር ውስጥ ከበርቴ ተሳትፎን ከፍ ሲያደርገው፣ በዚያው መጠንም ውድድር ይጦፋል። ስለሆነም ኢኮኖሚው በማደግ የስራ መስክም ሊከፈት ይችላል። 3ኛ) ገበያውን በገበያ ህግ መሰረት፣ ማለትም በአቅራቢና በጠያቂ ህግ መሰረት የዕቃዎች ዋጋ እንዲደነገግ  ማድረግ፣ 4ኛ) ስለሆነም መንግስት እንደማህበራዊ በመሳሰሉና፣ አገልግሎቶችና ሌሎች ቁሳቁሶች ላይ የሚሰጠውን ድጎማ ማንሳት አለበት። ወደዚያ የሚፈሰው ገንዘብ ሲነሳ ገንዘቡ ምርታማ ለሆኑ ሀብታሞች ይለቀቃል። 5ኛ) የውጭው ንግድ ልቅ  መሆን አለበት። የውጭውን ንግድ ክፍት ወይም ሊበራላይዝ ማደረግ የውጭ ከበርቴዎችን ለመሳብና በአገራችን ምድር መዋዕለ-ነዋይ እንዲያፈሱ ያበረታታቸዋል። በዚህ መልክ ለብዙ መቶ ሺህ ሰዎች የስራ ዕድል ይከፈታል ይሉናል። ስለሆነም እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩት ነገሮች ቀስ በቀስ ተግባራዊ ከተደረጉ-ተደርገዋልም- የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ያድጋል፤ ኢትዮጵያም የሰለጠነው ዓለም አካል ትሆናለች፤ ህዝባችንም በደስታ ይፈነድቃል፤ ድህነትም ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜ በማክተም የታሪክ ትዝታ ሆኖ ይቀራል ይሉናል። ከዚህ ስንነሳ በህወሃት የ28 ዓመታት አገዛዝ ዘመን ይህ ዐይነቱ የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ አልሆነም  የሚል ካለ በግልጽ ወጥቶ መከራከር ይችላል። ለማንኛውም ከላይ የተጠቀሱት የፖሊሲ ዝርዝሮች ተግባራዊ ከሆኑ በኋላ እንደታቀደውና እንደታለመው የአገራችን ኢኮኖሚ አደገ ወይ? ህዝባችንም ከድህነት ተላቀቀ ወይ? አብዛኛውስ ህዝብ የስራ ዕድል አገኘ ወይ? የውጭውስ ንግድ ጤናማ ሆነ ወይ? ዕዳችንም እየቀነሰ ወይም እየጨመረ መጣ ወይ? እነዚህን ነገሮች ታች በዝርዝርዝር እንመልከት።

የተቋም ማስተካከያው ወይም የኒዎሊበራል ኢኮኖሚ ፖሊሲ ውጤት!

በመጀመሪያ የገንዘብ መቀነስን እንመልከት። የካፒታሊስት አገሮችን የኢኮኖሚና የአገር ግንባታ ታሪክ ለተከታተለና ላጠና አንዳቸውም የካፒታሊስት አገር ገንዘቡን ከሌላው አገር ጋር በማወዳደር የቀነሰበት(devalue)ጊዜ የለም። ይህ ዐይነቱ ቅነሳ እነ ዓለም የገንዘብ ድርጅት የአፍሪካንና የተቀሩትን የሶሰተኛውን ዓለም አገር ኢኮኖሚዎች ለማዳከም ያወጡት ስትራቴጂ ነው። ድርጅቱ በ1944 ዓ.ም ሲመሰረት ዋናው ዓላማው በየአገሮች ውስጥ  እየገቡ በመፈትፈት ኢኮኖሚያቸውን ማዳከም ሳይሆን ለአባል አገሮች አጠቃላዩ የውጭ(BOP) ክፍያቸው ወይም ንግዳቸው ሲናጋ ካለምንም ቅድመ-ሁኔታ የመሸጋገሪያ ብድር መስጠት ብቻ ነው።

ለማንኛውም አንድ አገር የአገሯን ከረንሲ ወይም ገንዘብ ከዶላር ጋር ሲወዳደር ብትቀንስ ወደ ውጭ የምትልከው ምርት በብዛት ይሸጣል የሚለው የተረት ተረት ነው። በመጀመሪያ ደረጃ የዓለም ገበያ ከሚፈልገው ምርት በላይ አይወስድም፤ አይገዛም። ይህ ዐይነቱ የገንዘብ ቅነሳ ሊሰራ የሚችለው አንድ አገር የኢንዱስትሪ ምርቶችን ወይንም ማሺኖችን ለዓለም ገበያ የምታቀርብ ከሆነ ብቻ ነው። ይህ ከሆነ ደግሞ እንደዚህ ዐይነት ጠንካራ ኢኮኖሚ ያላት አገር ገንዘቧን መቀነስ አያስፈልጋትም። አውቶማቲክ ዲቫሊዬሽን የሚሉት ነገር አለ። ይህም ማለት፣ ለምሳሌ በተለያየ ምክንያት፣ ፖለቲካንና ጦርነትን እንዲሁም የኢኮኖሚ ጉዳይን አስመልክቶ፣ ወይም ደግሞ በአሜሪካን የማዕከላዊ ባንክ ወለዱ ከፍ ሲል ዶላር በዓለም ገበያ ላይ ተጠያቂነቱ ከፍ ይላል። በዚህ ጊዜ ዶላር ከኦይሮ ወይም ከጃፓኑ ገንዘብ ጋር ሲወዳደር የልውውጥ  ዋጋው ይወደዳል።  በዚህ ምክንያት የተነሳ በኦይሮ ክልል ውስጥ ያሉ እንደጀርመን የመሳሰሉ ኢኮኖሚዎች ማሺኖቻቸውንና ሌሎች የኢንዱስትሪ ምርቶቻቸውን፣ ለምሳሌ እንደመኪና የመሳሰሉትን በዚህ ዐይነቱ የገንዘብ ልውውጥ  መቀነስ የተነሳ በዓለም ገበያ ላይ ሊሸጡ ይችላሉ።  በሌላ ወገን ደግሞ የጀርመንም ሆን የአንዳንድ ኢንዱስትሪ አገሮች የኢንዱስትሪ ምርት ውጤቶች የጠሩና ተወዳጅም ስለሆኑ ለምሳሌ የኦይሮ የልውውጥ ዋጋ ቢጨምርም አስመጪዎች ዐይናቸውን የግዴታ ወደ ሌላ አገር አያዞሩም።

ወደ ጥሬ-ሀብትና የእርሻ ምርት አምራች አገሮች ስንመጣ ግን ሁኔታው የተለየ ነው። እነዚህ ምርቶች በኢንዱስትሪ ውስጥ ስለማይፈበረኩ በተለያየ ደረጃ የሚወጣውን ወጪ ለመተመን አስቸጋሪ ነው። በተጨማሪም የእነዚህ ምርቶች ዋጋ በትላልቅ ኩባንያዎች ወይም ካርቴሎች ተብለው በሚጠሩ ስለሚተመኑ የሚያመርተው ገበሬም ሆነ ነጋዴው የቡናንም ሆነ የሌሎች የጥሬ-ሀብቶችን ዋጋ መተመን አይችልም። በዚህ መልክ ሳይፈበረክና ወደ መጨረሻ ተጠቃሚነት(End product) ሳይለወጥ ወደ ውጭ የሚወጣ የጥሬ-ሀብት የግዴታ ከዐመት ዐመት የንግድ ሚዛኑ እንዲዛባ ማድረጉ ብቻ ሳይሆን፣ ወደ ውስጥ ደግሞ የአገር ውስጥ ገበያ(Home Market) እንዳያድግ ያግዳል። ይህ ከሆነ ደግሞ አብዛኛው ህዝብ፣ በተለይም ቡና የሚያመርተው ገበሬና በጥሬ-ሀብት ማውጣት ላይ የሚሰማራው ሰራተኛ ከሰላሳና ከአርባ ዐመታት በላይ ቢሰራም ከጎጆ ቤት ኑሮው ለመላቀቅ አይችልም፤ ጥሩ ምግብም መመገብ በፍጹም አይችልም። በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የትናንሽ ቡና አምራቾችን የኑሮ ሁኔታ ለተመለከተ ይህ ፖሊሲ ተግባራዊ ከመሆኑ በፊትም ሆነ በኋላ ከ30ና ከአርባ ዐመታት በላይ ቡና እያመረቱ ቢሽጡም አዲስና የተሻለ ህይወት መምራት አልቻሉም። በወያኔ ዘመን የዎል ስትሪት ተጠሪ የሆነችውና ብዙ የአፍሪካ የፖለቲካ ኤሊቶችን የምታሳስተውና በነፃ ገበያ ስም እየማለች በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ዕውነተኛ ዕድገት እንዳይመጣ እዚህና እዚያ የምትሯሯጠው  በዶ/ር  ኤሌኒ ገብረመድህን ዋና ተዋናይነት የኮሞዲቲ ገበያ ቢቋቋም የገበሬዎች ገቢ አላደገም፤ ኑራቸውም አልተሻሻለም። ገንዘብ ለማግኘት ሲሉ ብቻ በቡና ተከላ ምርት ላይ እንዲሰማሩ በመደረጋቸው ሌሎች ለምግብ የሚያሰፈልጋቸውን ምርቶች እንዳያመርቱ ተገደዋል። ይህ በራሱ በገበሬው ዘንድ ድህነት እንዲስፋፋና በድብቅ ረሃብ እንዲስቃዩ ለማድረግ በቅቷል። የዚህ ዐይነቱ የኮሞዲቲ ገበያ ተጠቃሚዎች  የወያኔ ካድሬዎችና ጥቂት ባለሀብታም የቡና ነጋዴዎች ብቻ  ነበሩ።

ወደ ሌሎች በመንግስት ቁጥጥር ስር ያሉ ሀብቶችን ወደ ግል ማዘዋወር ስንመለከት በመሰረቱ እንደ ኢትዮጵያ በመሳሰሉ አገሮች ውስጥ የተተከሉት ኢንዱስትሪዎች የማደግና የመባዛት ባህርይ የላቸውም። በተጨማሪም አብዛኛዎቹ የአገልግሎት መስጫዎች ስለሆኑ ለውድድርና ለቴክኖሎጂ ምጥቅት ይህን ያህልም አስተዋፅዖ አያደርጉም። እ.አ..አ ከ1980 ዓ.ም  ጀምሮ በተቋም ማስተካከያ ስም በብዙ  የሶስተኛው  ዓለም  አገሮችና በራሽያና በሌሎች ከሶቭየት ህብረት ግዛት የተላቀቁ አገሮች ውስጥ ተግባራዊ የተደረገውን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ስንመለከት የመንግስት ሀብቶች በቀላሉ ከባንኮች ብድር ለማግኘት ለሚችሉ ግለሰቦችና ከመንግስት መኪና ጋር ግኑኝነት ያላቸው ሰዎች እጅ ነው የተላለፉት።

ወደ አገራችን ስንመጣ ኢንዱስትሪዎች፣ የእርሻ ማሳዎች፣ የዕቃዎች ላኪና አስመጪ ኩባንያዎችና ሆቴል ቤቶች ለወያኔ ካድሬዎችና ለአላሙዲን በርካሽ የተሸጡ ናቸው። በተለይም በጊዜው የወያኔ ካድሬዎች ወደ ሶስት ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ከባንክ ተበድረው ኩባንያዎችን ከገዙ በኋላ ብድሩን አልከፈሉም። ባጭሩ እንደ ኢትዮጵያ በመሳሰሉት አገሮች ውስጥ በዚህ መልክ ከመንግሰት ወደ ግል የተላለፉት ኩባንያዎች በመሰረቱ የሀብት ዘረፋ የሚካሄድባቸው እንጂ የቴክኖሎጂ ምጥቅት የሚታይባቸው አይደሉም። የወያኔ ካድሬዎችና አላሙዲን የመንግስት ሀብቶችን በርካሽ ዋጋ ከገዙ በኋላ በአጭር ዓመታት ውስጥ የናጠጡ ሀብታሞች ለመሆን በቅተዋል።  ለማንኛውም የወያኔ ካድሬዎችና አላሙዲን  በቴክኖሎጂ ላይ የተደገፈና  የመባዛት ባህርይ ያለው ኢንዱስትሪና የውስጡን ገበያ ለማሳደግ በሚችል ማዕከለኛና ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች ላይ በመሰማራት ተወዳዳሪና የስራ-መስክ ፈጣሪዎች ሊሆኑ በፍጹም አልቻሉም። በአንፃሩ ወደ ውጭ የሚላኩ ስትራትጂክ ምርቶችን በመቆጣጠርና፣ አላሙዲን ደግሞ በበኩሉ ወርቅ በማውጣትና ወደ ውጭ በመላክ የሀብት ዘረፋ ላይ ነው የተሰማሩት። ይህ ዐይነቱ የሀብት ቅብብሎሽና ዘረፋ በአገሪቱ ውስጥ ማፊያዊ ዐይነት የሆነ የአሰራር ዘዴ እንዲስፋፋ ማድረጉ ብቻ ሳይሆን፣ ሙስናና የብልግና ኢንዱስትሪውም በመስፋፋት የህዝቡ፣ በተለይም የወጣቱ ሞራል በከፍተኛ ደረጃ እንዲበላሽ ለመደረግ በቅቷል። በጥቂት ስዎች እጅ ገንዘብ በከፍተኛ ደረጃ በመከማቸቱና፣ ይህ ገንዘብ ለምርት ክንውን ሳይሆን ለፍጆታ ዕቃ እንዲውል በመደረጉ በሰው ዘንድ የሚኖረውን ጤናማና በሞራል ላይ የተገነባውን ህብረተሰብአዊና የቤተሰብ ግኑኝነት ሊበጣጥሰውና የሰው የርስ በርስ ግኑኝነት በገንዘብ እንዲለካ ሊደረግ በቅቷል።፡ በዚህ መልክ ወያኔና ካድሬዎቹ እንዲሁም እንደ አላሙዲን የመሳሰሉት ዘራፊ ነጋዴዎች የአገራችንን እሴት በማበላሸታቸውና የብልግና እንዱስትሪ በማስፋፋታቸው በህግ መጠየቅ የሚገባቸው ነበሩ።

ሌሎች ጉዳዮች ከዚህ የባሱ እንጂ ለአገራችን የኢኮኖሚ ዕድገት ይህንን ያህልም አስተዋፅዖ ያበረከቱ አይደሉም። በተለይም የውጭው ገበያ ልቅ ከመሆኑ የተነሳና ወደ ውስጥ በተፈጠረው አዲስ ዐይነት የፍጆታ  አጠቃቀም የተነሳ ከዚህ በፊት ታይተው የማይታወቁ ዕቃዎች በብዛት በመግባት ለንግድ ሚዛኑ መባዛት ከፍተኛ አስተዋፅዖ አበርክተዋል። ህወሃት ስልጣን ላይ በነበረበት 28 ዐመታት ያህል በአገራችን  ምድር  የተፈጠረው ልዩ ዐይነት የህብረተሰብ ኃይል በሀብታምና በደሃ መሀከል ያለውን ልዩነት በከፍተኛ ደረጃ አሳድጎታል። ይህ የህብረተሰብ ክፍል ልዩ ዐይነት የፍጆታ አጠቃቀም( Consumption pattern)  ከመልመዱ የተነሳ የእሱን የፍጆታ ፍላጎት ለማርካት ሲባል ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እየፈሰሰባቸው የቅንጦት ዕቃዎች በመግባት የንግድ ሚዛኑ እንዲዛባ ለማድረግ በቅተዋል። ይህ ብቻ ሳይሆን፣  ውሃ በተትረፈረፈበት አገር ሃይላንድ ወተር የሚባል በፕላስቲክ የታሸገ ውሃ በማስገባት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እንዲባክን እየተደረገ ነው።  ከዚህ በተጨማሪ አገሪቱ ከምትፈልገውና ከምትችለው በላይ አዲስ የፍጆታ አጠቃቀም የለመደውን የህብረተሰብ ክፍልና ከውጭ የሚመጣውን ዲፕሎማትና አንዳንድ ጎብኝዎችን ለማርካት ሲባል ባለአራትና ባለአምስት ኮከብ ሆቴል ቤቶች ተሰርተዋል። ሼራተንና ስካይላይት፣ እንዲሁም ራማዳ የሚባሉት ሆቴል ቤቶች በአደጉ የካፒታሊስት አገሮች እንኳ የማይታዩ ናቸው። እነዚህን የመሳሰሉ የቅንጦትና የመባለጊያ ሆቴል ቤቶችን ለመስራት ከውጭ ልዩ ልዩ ዕቃዎች፣ በተለይም ፊኒሺንግ ማቴሪያልስ ይገባሉ። እነዚህና ምንም ጥራት ሳይኖራቸው ከቻይናና ከሌሎች አገሮች የሚገቡት አላስፈላጊ ዕቃዎች የአገሪቱን የውጭ ምንዛሪ በከፍተኛ ደረጃ ለመጋራት በቅተዋል። ማሽኖችን ለማስመጣትና ኢንዱስትሪዎችን ለመትከል ጠቀሜታ ላይ ሊውል ይችል የነበረው የውጭ ከረንሲ በዚህ መልክ በቅንጦት የፍጆታ ዕቃዎች ላይ እንዲውል ያደርጋል።

ከዚህም በላይ የህዝብ ፍላጎትን ለማሟላትና የአገሪቱን የውስጥ ገበያ ለማሳደግ ሳይሆን የካፒታሊስት አገሮችን፣ በተለይም የአውሮፓን አንድነት ፍላጎት ለማሟላት ሲባል ወደ አስር የሚጠጉ የስኳር ፋብሪካዎች ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ፈሶባቸው ተተክለዋል። የስኳር ፋብሪካዎች ን ቢያንስ 16 ሰዓት ያህል በ70% ካፓሲቲ እንዲያመርቱ ለማድረግ የግዴታ በብዙ ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የሽንኮራ አገዳ መተከል አለበት። እንደሚታወቀው የሽንኮራ አገዳ ተከላ በብዛት ከመሬት ውስጥ ውሃን ስለሚመጥ በአካባቢው ላይ ድርቀትን ሊያስከትልም እንደሚችል ጥናቶች ያረጋግጣሉ። የስኳር ፋብሪካዎችን ለመትከል የእኮኖሚክ ኮሚሽን ፎር አፍሪካ እንደተሳተፈበት በዋና ኢኮኖሚስትነት ተቀጥሮ አዲስ አበባ ውስጥ ለብዙ ዐመታት ሲሰራ የነበረ ጀርመናዊ ነግሮኛል። ከሰውየም ጋር ብዙ ሰዐታት ተጨቃጭቀናል። ይህ ዐይነቱ ምክር አሳሳችና እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮችን የባስውኑ የደሃ ደሃ እንደሚያደርጋቸው ነግሬዋለሁ። በመሰረቱ ከስኳር ምርት በፊት የሰፊው ህዝብ ፍላጎት መሟላት ያለበት ብቻ ሳይሆን ጤናማ አስተሳሰብ ያለው ምሁር ወይም ኢኮኖሚስት አንድን መንግስት መምከር ያለበት ለአገር ዕድገት በሚያመቹ ዘርፎች ላይ እንዲሰማራ ነው መገፋፋት ያለበት በማለት አመለካከቱንና አሳሳች አስተሳሰቡን ነግሬዋለሁ። በዚህ መልክ እሱን የመሳሰሉ ኤክስፐርት ነን ባዮች በህወሃት 28 የአገዛዝ ዘመን የአገራችንን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ኤሊት ለመቆጣጠርና ተፅዕኖ ሊያሳድሩበት ችለውል። እንደነፃ ሰው ትክክል ነው ብሎ በሚያምነው አስተሳሰብ እንዳይመራና በምድር ላይ የሚታዩ ነገሮችን ማንበብና መተንተን እንዳይችል አድርገውታል። በዓለም አቀፍ የአገዛዝ ሂራርኪ ውስጥ እንዲካተት በማድረግ ተንሳፎና ሰውን እየናቀ እንዲኖር  ለመደረግ በቅቷል። ስለሆነም እነዚህንና ሌሎች የማባዛት ባህርይ የሌላቸው እንደኮካላና የቢራ ፋብሪካ ተከላዎችና ገብስም ከውጭ ለማምጣት የሚፈሰው የውጭ ከረንሲ፣ በአንድ በኩል የውጭ ንግድ ሚዛኑን ሲያዛቡ፣ በሌላ ወገን ደግሞ የውጭ ዕዳን ለመክፈል የሚያስችሉ የምርት ክንዋኔዎች እንዳይስፋፉ መሰናክል ለመሆን በቅተዋል። ከዚህ በተጨማሪ $500 ሚሊዮን የሚገመት ስንዴ በዐመት ከውጭ ይመጣል። ሰሊጥና ኑግ እንዲሁም ተልባና ሌሎች ለዘይት ጭመቃ የሚያገለግሉ የቅባት እህሎች በሚመረትበት አገር አገሪቱ በዐመት የምግብ ዘይት ከውጭ ለማስመጣት ቢያንስ $ 400 ሚሊዮን ታወጣለች። ከውጭ የሚመጣው የፓልም ዘይት ደግሞ የቱን ያህል በሰው ህይወት ላይ የጤንነት ቀውስ እንዳስከተለ የሚታወቅ ጉዳይ ነው። በወያኔ የአገዛዝ ዘመን ከውጭ በሚመጣ ምግብና ዘይት የተነሳ  የብዙ ሺህ ሰዎች  ጤንነት ለመቃወስ ችሏል። የስኳርና የኩላሊት በሽታዎች መስፋፋት፣ ነቀርሳና ሌሎች ከምግብ ለውጥ ጋር የተያያዙ በሽታዎች ከዚህ ዐይነቱ ልቅ የሆነ የውጭ ንግድ ጋር የተያያዙ ናቸው። ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ አባል ከሆነች ደግሞ ሁኔታው ከዚህ ይብሳል እንጂ የሚሻሻል አይደለም። አገራችን የዓለም ንግድ አባል እንድትሆን መንግስትና ተወካዮቹ ሌት ተቀን እንዲሚሰሩ ነግረውናል። ለማንኛውም ወያኔ የመንግስቱን መኪና በሚቆጣጠርበት ዘመን የስንዴውንም ሆነ የዘይቱን ገበያ የሚቆጣጠረውና የትርፍ ትርፍ የሚያካብትበት መንገድ ነበር።

ከዚህ ስንነሳና የአገራችንን የውጭ ንግድ መዛባትና የዕዳውን መቆለል ስንመለከት ይህንን ያህልም ሊደንቀን በፍጹም አይችልም። የውጭ ዕዳውን ዕድገት ስንመለከት እ.አ.አ በ1981 ዓ.ም  1.6 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ነበር። ይህ ዕዳ እ.አ.አ በ1995 ዓ.ም ወደ 9.8 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ያድጋል። እ.አ.አ በ2008 ዓ.ም በጂ ስምንት ስብሰባ ላይ በተደረገው ስምምነት መሰረት በከፍተኛ ዕዳ ለተጠቁ አገሮች የዕዳ ቅነሳ ሲደረግ ይህ ዕድል ለኢትዮጵያም ይደርሳታል። በዚህ መሰረት የዕዳው መጠን ወደ 2.9 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ይቀንሳል። ይሁንና ግን ይህ ዕዳ በ2014 ዓ.ም ወደ 15.9 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ይተኮሳል። በአሁኑ ወቅት ዕዳው አንዳንዶች  ጥናቶች እንደሚያመለክቱት $ 30 ቢሊዮን ደርሷል ሲሉ፣ ሌሎች ደግሞ ወደ $50 ቢሊዮን ያስጠጉታል። የዕዳን ጉዳይ አስመልክቶ  ሯጩ ኃይለ ገብረስላሴ በአንድ የሰላምና የመግባባት ስብሰባ ላይ ንግግር ሲያደርግ የአገራችን ኢኮኖሚ ዕድገት በውጭ ብድር የተደገፈና ሀብታችንም በአራጣነት እንደተያዘ ለታዳሚው ሰው በቀላልና በሚገባ መልክ አስቀምጦታል።

ያም ሆነ ይህ እዚህ ላይ መነሳት ያለበት ጉዳይ ኢትዮጵያ የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚ ፖሊሲውን እንድትቀበልና ተግባራዊ እንድታደርግ  ጫና ሲደረግባት ኢኮኖሚውን ከመዛባት ለማዳንና ወደ ሚዛናዊነት ደረጃ ለማምጣት ነው የሚል ነበር። ይህ መሆኑ ቀርቱ ከ28 ዓመታት የወያኔ አገዛዝ ዘመን በኋላ የባሰውኑ ተዛብቶና በቀላሉ ሊቀረፍ የማይችል የባህል፣ የስነ-ልቦናና የማህበራዊ ቀውስ አስከትሎ የገዢ መደቡን ጭንቅላት እንኳን ሊያደበዝዘው በቅቷል።  ይሁንና ግን ለእዚህ ዐይነቱ ውድቀትና አገር መከስከስ ምክንያቱ ምንድነው? ማንስ ነው ተጠያቂው? ብሎ የሚጠይቅ አንዳችም የተገለፀለት ኃይል የለም። ጥያቄ ማንሳትና መከራከር እንደወንጀል በሚቆጠርበት አገር ውስጥ ስልጣን ላይ የተቀመጡትና አማካሪዎቻቸውም፣ እንዲሁም ደግሞ የውጭ አማካሪዎች ተብዬዎች አንድን አገር በቀላሉ የማትወጣው ማጥ ውስጥ ይከቷታል። ከብርሃን ይልቅ ጨለማ፣ ከኑሮ መሻሻልና የተስተካከለና አገርን ከሚያስከብር ዕድገት ይልቅ ኋላ-ቀርነትና ድህነት የዚህ ዐይነቱ ኢ-ሳይንሳዊና ፍልስፍና አልባ የሆነ ፖሊሲ ውጤቶች ናቸው።

ወደ አሁኑ የብድር ጉዳይ እንምጣ። የዓለም የገንዘብ ድርጅቱ ልዑካን ብድሩን ለመስጠት ያቀረቡት አምስት ቅድመ-ሁኔታዎች ናቸው። አምስቱንም ቅድመ-ሁኔታዎች ለተመለከተና የሶይሎጂና የኢኮኖሚ ታሪክን ላጠና ምሁር አምስቱም-ቅድመ ሁኔታዎች በምንም መልካቸው የኢትዮጵያን ሁኔታ የሚያንፀባርቁ አይደሉም። የቴክኖክራቶች ውጥንቅጦች እንጂ ከአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳትና በዐይን የሚታየውን፣ በአዲስ አበባም ሆነ በአገር አቀፍ ደረጃ እየተዘዋወሩ በማየትና በቲዎሪ ደረጃ በመተንተንና ምክንያቶቻቸውን በማወቅ የተነደፈ ፖሊሲ አይደለም። ባጭሩ የሚሉን የገንዘብ ልውውጡ ጉዳይ በጠያቂና በአቅራቢ እንዲወሰን፣ በመንግስት ቁጥጥር ስር ያሉ ኢንዱስትሪዎችም ሆነ የአገልግሎት መስጫዎች አሁንም ወደ ግል መዘዋወር አለባቸው፤ የፋይናንስ ገበያውን ልቅ ማድረግና የውጭ ከበርቴዎች መጥተው እንደፈለጋቸው ይዋኙ የሚሉ ናቸው። ለምሳሌ የገንዘቡ ልውውጥ ለገበያው ቢለቀቅ የባሰ የዋጋ ግሽበትን ያስከትላል። አንዳንድ የውጭ ኤክስፐርቶች እንደሚሉን ከሆነ የኢትዮጵያ ብር አሁንም ቢሆን ቢያንስ 25% ከሚገባው በላይ የተተመነ ሰልሆነ ይህን ያህል መቀነስ አለበት ይላሉ። ከዚህ በተረፈ የፋይናንስ ገበያውን ለውጭ ከበርቴዎች ልቅ ማድረግ ኢትዮጵያ ያለባትን ውስጣዊ የተቋም ችግርና(structural crisis) በአጠቃላይ ሲታይ ድህነትንና ኋላ-ቀርነትን በፍጹም ሊቀርፍ የሚችል አይደለም። በዶ/ር ቆስጠንጢኖስ ዕምነት የፋይናንስ ገበያው መሻሻል እንደ ሆንግኮንግና ዱባይ በኢኮኖሚ ያሳድገናል። በእኔ ዕምነት ግን የውጭ ከበርቴ ወደ አንድ አገር ሄዶ ኢንቬስት ለማድረግ ሲፈልግ የአንድን አገር ኢኮኖሚ ለማሳደግና የማህበራዊ ሁኔታውን ለማሻሻል ሳይሆን ትርፍ ለማግኘት እችላለሁ ብሎ በማስላት ብቻ ነው። ለምሳሌ የሆንግኮንግን ሁኔታ ስንመለከት የፋይናንስ ኢንዱስትሪው በከፍተኛ ደረጃ የተስፋፋበትና አብዛኛው ህዝብ ደግሞ ወደ ድህነት የተገፈተረበትን ሁኔታ እንመለከታለን። አንድ ተራ ሰው በሚያገኘው መጠነኛ ገቢ ቤት ተከራይቶ ለመኖር የማይችልበት አገር ነው። አብዛኛዎቹ የአሜሪካንና የቻይና የገንዘብ ኩባንያዎች ሆንግኮንግና ከአንዳንድ አገሮች ውስጥ በመሆን የብዙ አፍሪካ አገሮችን የጥሬ ሀብቶች የሚቆጣጠሩባቸው መሳሪያዎች እንጂ በየአገሩ ለተስተካከለ ዕድገት፣ ለቴክኖሎጂና ለሳይንስ ምጥቀትና ለስራ መስክ መከፍት ይህን ያህልም አስተዋፅዖ የሚያበረክቱ አይደሉም። ይልቁንስ በሀብታምና በደሃ መሀከል ያለው ልዩነት እንዲሰፋ ማድረጋቸው ብቻ ሳይሆን፣ ኢ-ምሁራዊ፣ ኢ-ሳይንሳዊና ፍልስፍና-አልባ ስርዓት በማስፋፋት  ልዩ ዐይነት ያልታቀደ የህብረተሰብና የማህበራዊ ቀውስ እንዲፈጠር የሚያደርጉ ናቸው። ይህ ጉዳይ በእነዚህ አገሮች ብቻ ሳይሆን በእነ ብላክ ሮክ- አንደኛውና ትልቁ የአሜሪካ ፋይናንስ ኢንዱስትሪና የብዙ አገሮችን ኢኮኖሚ በመቆጣጠር ችግር የሚፈጥር ነው። ይህን የመሰለ ችግር አሜሪካ ውስጥም በጉልህ የሚታይና በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች መኖሪያ ቤት አጥተው በብርድና በሃሩር ውጭ የሚያድሩበትንና የሚኖሩበትን ሁኔታ እንመለከታለን።

ከዚህ ስንነሳ የአቢይ አህመድ አገዛዝ ያገኘው ብድርና ቅድመ-ሁኔታዎችን ተግባራዊ ማድረጉ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ አንድም እርምጃ ወደፊት ፈቀቅ አያደርገውም። አገራችንም በኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ  ፖሊሲ አማካይነት ወደ ብልጽግና ለመሸጋገር በፍጹም አትችልም። በአንፃሩ ድህነቱና ማህበራዊ ቀውሱ ይሰፋል። በህወሃትና አሁን ደግሞ በአቢይ አህመድ የአገዛዝ ዘመን ተግባራዊ የሆነውንና የሚሆነውን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ስንመለከት በዛሬው ወቅት በአገራችን ምድር በጉልህ የሚታዩት የማህበራዊና የስነ-ልቦና ቀውሶች የፖሊሲው ውጤቶች ናቸው። የሌብነት መብዛት፣ የሙስና መስፋፋት፣ በምግብ ነክ ነገሮች ላይ ለጤንነት ጠንቅ የሆኑ ነገሮችን ማስገባት፣ የሴተኛ አዳሪነት መስፋፋት፣ የጨአት መቃምና የሌሎች ዕፆች ሱሰኛ መሆን፣ ማጅራች መችነት መስፋፋት፣ ህብረተሰብአዊ እሴቶች መበጣጠስና፣ ሀብታም ነኝ የሚለውና አገዛዙ ርህራሄ አልባ መሆንና፣ አገሪቱ ወዴት እንደምትጓዝ ማየት አለመቻል… ወዘተ. እነዚህ ሁሉ የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚ ፖሊሲው ውጤቶች ናቸው። ምክንያቱም እደዚህ ዐይነት የኢኮኖሚ ፖሊሲዎችና ተግባራዊነታቸው በሰው አዕምሮ ወይንም መንፈስ ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተፅዕኖ ስለሚኖራቸውና፣ የግዴታ ልዩ ዐይነት የህብረተሰብ አሰላለፍን ስለሚፈጥሩ ነው። ከላይ የተጠቀሱት ህብረተሰብአዊ ቀውሶችና መመሰቃቀሎች በብዙ የላቲንና የማዕከለኛው አሜሪካና የአፍሪካ አገሮች በጉልህ የሚታዩና አገዛዞችን የሚያተራምሱና፣ በሌላ ወገን ደግሞ ራሳቸው አገዛዞች በደነደነ ልብ በህዝብ ላይ ጦርነት በማወጅ ህዝብና አገዛዞች ፍጥጫ ውስጥ የገቡበትን ሁኔታ እንመለከታለን። በዚህም ምክንያት የተነሳ የየአገሩ አገዛዞች የህዝብ አለኝታና ዕውነተኛና ለሰፊው ህዝብ የሚጠቅምን የተስተካከለ ዕድገት የሚያመጡ ኃይሎች ከመሆን ይልቅ ወደ ዘራፊ መንግስታትነት በመለወጥ ህዝቦቻቸውን መቀመጫና መላወሻ ያሳጡበትን ሁኔታ እንመለከታለን። ፈላስፋዎች እንደሚሉን አንድ ነገር ካለ አንዳች ምክንያት እንደማይፈጠር ሁሉ፣ ዛሬ በአገራችን ምድር ያለው የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ፣ የባህልና የስነ-ልቦና ቀውስ የዚህ ዐይነቱ ኢ-ሳይንሳዊና ፍልስፍናዊ አልባ ፖሊሲ ውጤት ነው። ከዚህ ውጭ ማሰብ አንድ ህብረተሰብ በምን ዐይነት ህጎች እንደሚተዳደርና እንደሚገዛ አለማወቅ ነው። ይህንን ትተን በብዙ የሶስተኛው ዓለም አገሮች ውስጥ ያለውን ትርምስ ለመረዳት ዕዳ ከግሎባል ካፒታሊዝም ጋር እንዴት እንደተቆላለፈ እንመልከት።

ይቀጥላል…

fekadubekele@gmx.de

ማሳሰቢያ፤  በተለይም አጠቃላይ የውጭ ንግድ ሚዛን ችግር ያለባቸው አገሮችና  ድህነትን ለመቅረፍ የሚያስችል ብድር ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት ተጨማሪ ብድር ካስፈለጋቸው(Extended Credit Facility) የገንዘብ ድርጅቱ ያስቀመጠውን ልዩ ልዩ ቅድመ-ሁኔታዎችን  ማሟላት አለባቸው።  ስለሆነም ኢትዮጵያም ከዚህ ውስጥ የምትደመር እንደመሆኗ መጠን ተጨማሪና ልዩ ብድር ለማግኘት ከፈለገች ሰሞኑን የዓለም የገንዘብ ድርጅቱ ለአቢይ አገዛዝ ያስተላለፈውን ቅድመ-ሁኔታዎችን የግድ ማሟላት አለባት። በተለይም ቀደም ብለው የሰፈሩትን ቅድመ-.ሁኔታዎች በተከታታይ ተግባራዊ ማድረግ ሲገባት፣ በተጨማሪም አሁን በዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅቱ የቀረበውን ተጨማሪ ቅድመ-ሁኔታዎችንም ማሟላት አለባት። 1ኛ) የኢትዮጵያ አገዛዝ ወደ ውጭ ማስተላለፍ ወይም መክፈል ያለበትን ገንዝብ ማቆም የለበትም። በተከታታይ ማስተላለፍ አለበት። በሌላ አነጋገር፣ ማገድ ወይም ደግሞ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ማስፈር የለበትም። 2ኛ) በአገሪቱ ውስጥ ከኢትዮጵያ ብር በተጨማሪ በወረዳዎች ወይም በየክልሎች ሌላ የገንዘብ ዐይነት መሽከርከር የለበትም። ይህ በአንዳንድ አገሮች ውስጥ በሎካል ደረጃ ከብሄራዊ ገንዘብ ባሻገር ሌሎች ተጨማሪ ገንዘቦች ተግባራዊ እንደሚሆኑ የታወቀ ሲሆን፣ በተለይም ብራዚል ውስጥ በህግ የተፈቀደ ተጨማሪ ገንዘብ በአንዳድ ፌዴራል መንግስት ውስጥ ይሽከረከራል። በታወቁ የገንዘብ ቲውሪና በባንክ ዓለም ውስጥ ከሰላሳ ዓመታት በሰሩ የኢኮኖሚና የባንክ ተመራማሪዎች  ዘንድ ይህ ዐይነቱ በአንድ አገር ውስጥ በብሄራዊ ደረጃ ከሚሽከረከረው ገንዘብ ባሻገር ተጨማሪ ገንዘብ(Parallel Currency) ቢሽከረከር በየሎካል ያሉትን ችግሮች ለመቅረፍ እንደሚቻል ያረጋግጣሉ።  3ኛ) በሁለት አገሮች መሀከል የሚደረገውን የመክፈል ስምምነት ኢትዮጵያ ማድረግ የለባትም። ይህ የዓለምን የገንዘብ ድርጅት በአንቀጽ  ስምንት ላይ የሰፈረውን የገንዘብ ድርጅቱን ደንብ የሚጥስ ነው። የዓለም የገንዘብ ድርጅቱ ይህንን አንቀጽ ሲያስቀምጥ ምን ማለቱ እንደሆነ ግልጽ አይደለም። ኢትዮጵያ ከሌላ አገር የመበደር መብትና ብድሩንም መልሳ የመክፈል መብት የላትም ማለቱ ነው? ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት በስተቀር ክሌላ አካልና አገር ብድር የመበደር መብት የላትም ማለቱ ነው? ነገሩ ግልጽ አይደለም። 4ኛ) የውጭ ንግድ ሚዛኑን ለማስተካከል ወይም በዚህ ችግር ምክንያት የተነሳ የኢትዮጵያ መንግስት ከውጭ ወደ ውስጥ የሚገቡ ዕቃዎች ላይ ገደብ መጣል ወይም መቀነስ የለበትም ይላል።  ይህም ማለት ኢትዮጵያ አጠቃላይ የሆነ የውጭ ንግድ ሚዛን ችግር ቢኖርባትም ይህንን እንደምክንያት በመውሰድ ከውጭ የምታስመጣውን ዕቃ መቀነስ የለባትም ይላል። በሌላ አነጋገር፣ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ከሚሸከመውና ህዝቡም ከሚፈልገው በላይ ማንኛውንም ዕቃ ከውጭ ማግበስበስ አለባት እንደማለት ነው። ይህንን መቀበል ደግሞ በአገር የኢኮኖሚ ፖሊሲ ውስጥ ጣልቃ እንደመግባት ይቆጠራል። ባጭሩ የዓለም የገንዘብ ድርጅቱ(IMF) የሚለን የኢትዮጵያ መንግስት በራሱ ተነሳሽነት የውስጡን ኢኮኖሚ ለማሻሻል እርምጃ መውሰድ የለበትም። በማንኛውም ፖሊሲ ነክ ነገሮች ላይ ለዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅቱ ማሳወቅና ምክር መጠየቅ ያስፈልጋል ነው የሚለን። በአገራችሁ ውስጥ ገብቼ እንደልቤ መፈትፈት አለብኝ ነው የሚለን። ብሄራዊ ነፃነታችሁም የተገደበና ካለኛ ፈቃድ ውጭ ምንም ነገር ማድረግ አትችሉም ነው የሚለን። ይህንን ዐይነቱን ድፍረት ማንኛውም አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ መታገል አለበት። ይህም ዐይነት አስረራና የገንዘብ ድርጅቱ አካሄድ ተፈጥሮአዊ ስላልሆነ አጥብቆ መቃወም ያስፈልጋል።

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop

Don't Miss

ዋለልኝ መኮንን

ዋለልኝ መኮንን ዳግም ሞቷል! – ሙሉዓለም ገ/ መድህን

“ዋለልኝ መኮንን” የሚለው ሥም በኢትዮጵያ (የቅርቡ) የሃምሳ ዐመት ፖለቲካዊ ትርክት