ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected])
እንደ አውሮፓ ዘመን አቆጣጠር በ1980ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ ደቡብ አሜሪካና አፍሪካ ውስጥ የሚገኙ ታዳጊ አገሮች ከፍተኛ የውጭ ዕዳ ቀውስ ውስጥ የተዘፈቁበት ግዜ ነበር። ይህ አዝማሚያ አበዳሪዎቹን አገሮች እያሳሰባቸው መምጣቱ ብቻ ሳይሆን በከፍተኛ ደረጃ አስደንግጧቸው ነበር። ስለዚህም ዋና ዋናዎቹ አበዳሪ ምዕራባዊያን አገሮች በተለይም አሜሪካ ይህንን በታዳጊ አገሮች ውስጥ የሚታየውን የብድር ቀውስ (Debt Crisis) ከቁጥጥር ውጭ እንዳይወጣ ማድረግ አለብን ብለው መምከር ጀመሩ። ላቲን አሜሪካና አፍሪካ ውስጥ የሚታየውን የብድር ዕዳ ቀውስ ለመቆጣጠርና ታዳጊ አገሮች ፈጣን የኤኮኖሚና ማህበራዊ ዕድገት እንዲያስመዘግቡ በሚደረገው ጥረት ውስጥ እነዚሁ ምዕራባዊያን አገሮች የሚቆጣጠሯቸው የአለም ባንክና አለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም(IMF) ወሳኝ ሚና መጫወት አለባቸው በሚለው ሃሳብ ዙሪያ ስምምነት ላይ ተደረሰ።
ይህንን ስምምነት የተመለከተውና በወቅቱ በአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስቴር ውስጥ ሁሉን አቀፍ የሆነና ለኤኮኖሚ ዕድገትና መረጋጋት የተመቻቸ ምንዛሪ ዋጋ ሥርዓት ለመዘርጋት በጥናትና ምርምር ስራ ላይ የነበረው እንግሊዛዊው የኤኮኖሚክስ ምሁር ጆን ዊሊያምሰን፣ የአለም ባንክ፣አለም አቀፉ የገንዘብ ተቋምና የአሜሪካ ገንዘብ ሚኒስትር በተግባራዊነታቸው ላይ ቢስማሙ ለአለም አቀፉ የብድር ዕዳ ቀውስ መፍትሄ ይሆናሉ ያላቸውን የፖሊሲ ነጥቦች በማስቀመጥ ስምምነቱን የ“ዋሺንግተን ስምምነት” (The Washington Consensus) በሚል ስያሜ ጠራው። በዚህ ዛሬም ድረስ የ“ዋሺንግተን ስምምነት” በመባል በሚታወቀው ፖሊሲ መሰረት፣ ታዳጊ አገሮች ከገቡበት የብድር ዕዳ ቀውስ ውስጥ ወጥተው ወደ ተሟላ ኤኮኖሚያዊ ልማትና ዕድገት የሚያመሩት እነሱ እራሳቸው በሚቀይሱት የዕድገትና ልማት ቅደም ተከተል ሳይሆን፣ የአለም ባንክና አለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም የሚሰጧቸውን ፖሊሲዎች ተከትለው ነው። በ”ዋሺንግተን ስምምነት” መሰረት ዛሬ የአለም ባንክና አለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም የማበደር ጡንቻቸውን ተጠቅመው በታዳጊ አገሮች ላይ የሚጭኗቸውና ከሰሞኑ የኢትዮጵያ መንግስትም ኢትዮጵያ ላይ እንዲጫን የተስማማባቸው ዋና ዋና የፖሊሲ ሃሳቦች የሚከተሉት ናቸው-
- የበጀት ጉድለትን የሚቀንሱ እርምጃዎች መውሰድ
- የግብር ሥርዓቱን ማሻሻል (Tax Reform)
- ተንሳፋፊ ወይም ዋጋው በገበያ ኃይሎች የሚወሰን የውጭ ምንዛሪ ተመን እንዲኖር ማድረግ (Floating Exchange Rate)
- በንግድ ዘርፍ ላይ የተጣሉ ገደቦችን ማንሳት ወይም መቀነስ
- የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን የሚገድቡ ህጎችንና ደንቦችን መሰረዝ
- የመንግስት ኢንተርፕራይዞችን ወደ ግል ማዞር
- የፋይናንስ ዘርፉን የወለድ ተመን በገበያ ኃይሎች እንዲወሰን ማድረግ በሚችል መልኩ
ነፃ ማድረግ
- ነጻ የገበያ ውድድርን የሚገድቡ ፖሊሲዎችን መሰረዝ
- ለፖለቲካ ፍጆታ ሲባል ለተለያዩ ፕሮጀክቶች የሚወጡ ወጪዎችን ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ትርፍ ወደሚያስገኙ ፕሮጀክቶች ማዛወር
እነዚህ የፖሊሲ ዝርዝሮች ታዳጊ አገሮች ከአለም ባንክና ከአለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ገንዘብ መበደር ከፈለጉ የግድ መቀበል ያለባቸው ፖሊሲዎች ናቸው። ባለፉት ሰላሳ አመታት እነዚህን ፖሊሲዎች ላቲን አሜሪካ፣ አፍሪካና ኢሲያ ውስጥ ብዙ ታዳጊ አገሮች ብድር ለማግኘት ሲሉ ተቀብለው ተግባራዊ ለማድረግ ሞክረዋል። ፖሊሲዎቹ ተግባራዊ መሆን ከጀመሩ ከአመታት በኋላ ታዋቂ የአለማችን ኤኮኖሚስቶች በእነዚህ አገሮች ውስጥ ያደረጉት ጥናት በግልፅ እንደሚያሳየው፣ እነዚህ ፖሊሲዎች አገሮችን ከብድር ዕዳም ከኤኮኖሚ ኋላ ቀርነትም እንዳላላቀቋቸው ነው።
ብዙ የጥናትና ምርምር ስራዎች እንደሚያሳዩት፣የአለም ባንክና የአለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ታዳጊ አገሮች ብድር በፈለጉ ቁጥር ብድሩን ለማግኘት እንደ ዋና መመዘኛ አድርገው የሚደረድሯቸው የፖሊሲ ጫናዎች፣ የተበዳሪ አገሮች መንግስታት የራሳቸውን አገር ኤኮኖሚ ለማሳደግ ያላቸውን ባለቤትነት ወይም ሉዓላዊነት በመቀማታቸው፣በተበዳሪ አገሮች ውስጥ የተጠበቀው የኤኮኖሚ እድገት ሊመጣ አልቻለም። ይልቁንም በአንድ በኩል የመንግስት በጀትን ለመቀነስ የተወሰዱ ዕርምጃዎች ለድሃው የህብረተሰብ ክፍል ዲዛይን የተደረጉ ፕሮግራሞችን በመሰረዝ ድህነት እንዲጨምር አድርገዋል፣ በሌላ በኩል ደሞ ለግብርናው ዘርፍ ይደረግ የነበረው ድጎማ መነሳቱ የታዳጊ አገር ገበሬዎች በአለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ እንዳይሆኑ አድርጓል። የሌሎቹን ትተን የእነዚህ ሁለት ፖሊሲዎች ውጤት ብቻ ስንመለከት የአለም ባንክንና የአለም አቀፉን የገንዘብ ተቋም ፖሊሲዎች ተግባራዊ ባደረጉ በርካታ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ድህነት፣ የስራ አጥነት እና ማህበራዊ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ጨምሯል። እዚህ ላይ የእነዚህ የአለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ለታዳጊ አገሮች ገንዘብ ለማበደር እንደ ቅድመ ሁኔታ የሚጠቀምባቸው ፖሊሲዎች ዋነኛ አጣንጣኝ የሆነችው የአለማችን ኃብታሟ አገር አሜሪካ፣ ለኃብታም ገበሬዎቿ ከፍተኛ ድጎማ የምታደርግ አገር መሆኗ መዘንጋት የለበትም።
ባለፉት 30 አመታት የተደረጉ ተከታታይ ጥናቶች በግልፅ እንደሚያመለክቱት የ”ዋሺንግተን ስምምነት” ፖሊሲዎች የታዳጊ አገሮች መንግስታት በአገራቸው ኤኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ለመወሰን ያላቸውን አቅም ይቀንሳል፣ ወይም ውሳኔዎቹን በተዘዋዋሪ መንገድ ለባዕዳን የውጭ ኃይሎች ይሰጣል። በእርግጥም መረጃዎች እንደሚያሳዩት የአለም ባንክንና የአለም አቀፉን የገንዘብ ተቋም ፖሊሲዎች ተቀብለው ነገር ግን ፖሊሲዎቹን የራሳቸውን አገር የእድገት ቅደም ተለተል እንዲከተሉ አደርገው በተግባር ላይ ያዋሉ አገሮች በተለይ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን ከድህነት-ተኮር ፖሊሲዎች ጋር ማጣመር የቻሉና ባጠቃላይ የኤኮኖሚ እድገቱን ከአገራቸው ተጨባጭ ሁኔታ ጋር እንዲዛመድ አድርገው በራሳቸው መንገድ መምራት የሞከሩ ታዳጊ አገሮች መልካም ውጤት አግኝተዋል።
አገሮች የውጭ ምንዛሪ ተመናቸውን በቀነሱ ቁጥር የውጭ ንግድ ዘርፋቸውን ማሳደግ እንደሚችሉ ኤኮኖሚክስ ሳይንስ በግልጽ ይናገራል፣ ለምሳሌ፣ የኢትዮጵያ ብርና የአሜሪካ ዶላር የምንዛሪ ተመን እኩል ሆኖ ኢትዮጵያ ውስጥ 100 ኪሎ ቡና 500 ብር ከሆነ፣ ስታርባክ የሚባለው የአሜሪካ ኩባኒያ 500 ኪሎ ቡና ከኢትዮጵያ የሚገዛው በ500 ዶላር ይሆናል ማለት ነው። እዚህ ዋጋ ላይ የትራንፓርት፣ የግብርና ሌሎችም የተለያዩ ዋጋዎች ሲጨመሩ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የቡና ዋጋ ለስታርባክ የሚያዋጣ ስላልሆነ ስታርባክ ኢትዮጵያን ትቶ ሌላ ገበያ ይፈልጋል። ስለዚህ የኢትዮጵያ መንግስት ብዙ ቡና መሸጥ ከፈለገ፣ በዶላርና በብር መካከል ያለውን ግኑኝነት መቀየር ወይም የብርን የምንዛሪ ተመን መቀነስ አለበት ማለት ነው። ይህ እርምጃ ለውጭ አገር ገበያ ቡና የሚያቀርቡ ድርጅቶችን እና ቡና አምራቾችን ያበረታታል፣ሌሎችም የካፒታል ዝግጅት ያላቸው ነጋዴዎች ከቡና በተጨማሪ ሌላ የውጪው አለም በብዛት የሚፈልገውን ምርት አገር ቤት በብዛት እንዲያመርቱ ይገፋፋቸዋል፣ እነዚህ ድምር ውጤቶች የውጭ ንግዱን ዘርፍ እያሳደጉት ይሄዳሉ፣ኢትዮጵያም ከውጭ ንግድ የምታገኘው የውጭ ምንዛሪ እያደገ ይሄድና አሁን በውጭ ንግድና በገቢ ንግድ (Import and Export) መካከል የሚታየውን ከፍተኛ ጉድለት ይስተካክላል ማለት ነው። እንደዚህ ሲባል ግን ኢትዮጵያ ወደውጭ ከምትልከው በላይ ከውጭ ብዙ ዕቃዎችን የምትገዛ አገር ናትና የብር ምንዛሪ በቀነሰ ቁጥር ወደውጭ የምንልከው ዕቃ ዋጋ እንደሚቀንስ ሁሉ፣ ከውጭ አገር የምናስገባቸው ዕቃዎች ዋጋም የዚያኑ ያክል እንደሚጨምር መዘንጋት የለብንም። የጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት ወደ ሥልጣን ሲመጣ አንድ የአሜሪካ ዶላር በ27 ብር ነበር የሚመነዘረው፣ ዛሬ እንደ ገበያው ሁኔታ ሊዋዥቅ ቢችልም በ74 ብር ይመነዘራል። ታዲያ የማክሮ መረጋጋት እና የውጭ ንግድ ዘርፍ መስፋፋትን በፈለግን ቁጥር የት ድረስ ነው የብርን ተመን እየቀነስን መጓዝ የምንችለው?
ከሰሞኑ የኢትዮጵያ መንግስት ከአለም አቀፍ የገንዘብ ተቋም የ10.3 ቢሊዮን ዶላር ብድር ለማግኘት ሲል፣ ብዙ ታዳጊ አገሮች ሞክረውት አላዋጣ ያላቸውን የ“ዋሺንግተን ስምምነት” ፖሊሲዎች በመቀበሉ ኢትዮጵያዊያን በያሉበት በጉዳዩ ላይ በስፋት መነጋገር ጀምረዋል። አንዳንድ የመንግስት ከፍተኛ ባለሥልጣኖችና ሜዲያዎች የብዙ ቢሊዮን ዶላር ባለዕዳዋ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ግዜ ብድር የተፈቀደላት ይመስል “እንኳን ደስ ያለን” እስከማለት ደርሰዋል።
የዚህን ጽሁፍ ጸሃፊ ጨምሮ የብዙ ኢትዮጵያዊያን ጥያቄ፣መንግስት ለምን ይበደራል አይደለም፣ለምን ከአለም አቀፍ የገንዘብ ድረጅት ጋር ተስማማም አይደለም። ትልቁ ህዝባዊ ጥያቄ፣ የአገራችን ልማትና ዕድገት ባለቤቶች ለምን እኛው ኢትዮጵያዊያን አንሆንም፣ ለምንድነው በዚህ ትልቅ የኤኮኖሚ ውሳኔ ላይ በአገር ውስጥና በውጭ አገር የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን የኤኮኖሚ ጠበብቶችን ያላማከርነው፣የአለም ባንክና የአለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም የማክሮ ማሻሻያ ፖሊሲዎች በብዙ አገሮች ተግባራዊ ሆነው ችግር ፈጥረዋልና ለምን ከሌሎች አገሮች ልምድ አንማርም፣ የኑሮ ውድነቱና የዋጋ መናር የአብዛኛውን ኢትዮጵያዊ ጀርባ ባጎበጠበት፣ ሰላምና መረጋጋት ጠፍቶ አገራችን የጦርነት አውድማ በሆነችበት ግዜ ይህ አገራችንን ከድጡ ወደማጡ ሊወስድ የሚችል እርምጃ ለምን አስፈለገ የሚል ትክክለኛ ጥያቄ ነው።
እንደ ኢትዮጵያ ድሃና በዕድገት ኋላ ቀር የሆኑ አገሮችን ኤኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች በሚፈለገው መጠን ማቃለል ለመቻላቸው የተረጋገጠላቸውና ሁለንተናዊ ተቀባይነት ያላቸው ፖሊሲዎች የሉም፣ሊኖሩም አይችሉም። ሆኖም የኢትዮጵያ መንግስት የሁላችንም የጋራ በሆነች አገር ዉስጥ የሚወስዳቸውን ሁሉንም እርምጃዎች እኔ ብቻ ነኝ የማውቀው ማለቱን ትቶ ከምሁራን፣ ከዘርፍ ባለሙያዎች፣ ከሲቪል ተቋማትና በተለያዩ መንግስታዊና የግል ድርጅቶች ውስጥ ከሚሰሩ ኤክስፐርቶች ምክር ፍለጋ ቢሄድና ባጠቃላይ እመራዋለሁ የሚለውን ህዝብ ቢሰማ አገራችን በይበልጥ ትጠቀማለችና፣ ከሰሞኑ ተው ለብቻ አይሆንም እኛንም ስማን እየተባለ ሲለመን እምቢ ብሎ ብቻውን የወሰደውን እርምጃ በተመለከተ ከዚህ ቀጥሎ የተቀመጡትን ምክር አዘል ነጥቦች በጥሞና ቢመለከት አገራችንን ከከፍተኛ ችግር ይታደጋል የሚል ከፍተኛ እምነት አለኝ –
- ገበያንያማከለ የፖሊሲ ማሻሻያ ለዕድገት ጠቃሚ ሊሆን ቢችልም፣ እያንዳንዱ የማሻሻያ ፖሊሲ በተቋማዊ አውድ፣ የእድገት መነሻ በሆኑ ተጨባጭ ሁኔታዎች ውስጥና በሶሺዮ ፖለቲካል ማዕቀፍ ውስጥ በከፍተኛ ጥንቃቄ መታየት አለበት
- የኤኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲዎች አጀንዳ ባለቤት የየአገሩ መንግስታት ሲሆኑና ፖሊሲዎቹ የአብዛኛውን ባለድርሻ ተቀባይነት ሲያገኙ፣በአንድ በኩል የማሻሻያ ፖሊሲዎቹ ከፍተኛ ህዝባዊ ድጋፍ ያገኛሉ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ውጤታማ የመሆን ዕድላቸው ከፍተኛ ነው
- ኢትዮጵያን በመሳሰሉ ድሃ አገሮች ውስጥ የኤኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲዎች ተግባራዊ ሲሆኑ ተያይዘው ለሚመጡ ኤኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች ተጋላጭ የሆኑ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች አሉና(Safety Net) ፣እያንዳንዱ የኤኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃ ይህንን የማህበረሰብ ክፍል ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆን አለበት
- የፖሊሲ ማሻሻያዎቹ ትኩረት ኤኮኖሚን ለማሳደግና የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋትን ለማስፈን ቢሆንም፣ይህንን አላማ ለማሳካት ሲባል ትምህርትና ጤናን የመሳሰሉ ማህበራዊ ፍትህን የሚያስፍኑና የወደፊቱን የሰው ኃይል ካፒታል የሚገነቡ ዘርፎች በፍጹም የኤኮኖሚ ዕድገት ጥረት ሰለባ ሊሆኑ አይገባም
- ስለኤኮኖሚ ዕድገት ስናስብ አንድና ወጥ በሆነ መንገድ ችግሮችን ሊፈታ የሚችል አካሄድ የለም፣ ሊኖርም አይችልም። ስለዚህ የኤኮኖሚ ዕድገት ማሻሻያዎች ፖሊሲዎች ተግባራዊ ሲሆኑ ከግትርነት የተላቀቀ አካሄድ፣ ቀጣይነት ያለው ግምገማና የማስተካከያና የማሻሻያ እርምጃዎች የሂደቱ አካል መሆን አለባቸው።
የአለማችን አገሮች የኤኮኖሚ ዕድገት ደረጃ የተለያየ ነው፣በዕድገት ወደፊት የገፉ አገሮች አሉ፣በመካከለኛ የዕድገት ደረጃ ላይ የሚገኙ አገሮች አሉ፣ በዕድገት ወደኋላ የቀሩ አገሮችም አሉ። የአንዳንድ ኃብታም አገሮች ኤኮኖሚ ኤክስፖርት ተኮር ነው፣ እነዚህ አገሮች ወደ ውጭ የሚልኩት ዕቃ ዋጋ በገንዘብ ሲተመን ከውጭ ከሚያስመጡት ዕቃ ዋጋ ይበልጣል (ቻይና፣ጃፓን፣ጀርመን)። አገራችን ኢትዮጵያን ስንመለከት ግን አንደኛ በዕድገት ወደኋላ የቀረች ድሃ አገር ናት፣ በሁለተኛ ደረጃ ደሞ አገራችን ከውጭ ለምታስገባቸው ዕቃዎች የምትከፍለው ገንዘብ ወደ ውጭ ልካ ከምታገኘው ገንዝብ እጅግ በጣም ይበልጣል። ይህ የሚያሳየን ከኢትዮጵያ ይልቅ በገበያ በሚወሰን የውጭ ምንዛሪ ተመን ከፍተኛ ተጠቃሚዎች መሆን የሚችሉት በዕድገት ወደፊት የገፉ አገሮች ናቸው። ይህ ማለት ግን የኢትዮጵያ ብር የምንዛሪ ተመን ዝንተ አለም በነበረበት መንገድ መቀጠል አለበት ማለት አይደለም፣ ይልቁንም ኢትዮጵያ ኤኮኖሚዋን ለማሳደግ ትኩረቷ የውጭ ምኒዛሪዋን በመቀነስ ላይ መሆን የለበትም ማለት ነው። ትኩረታችን ከውጭ ይልቅ ወደ ውስጥ ቢሆንና፣ አላግባብ የሚባክኑና በተለያየ መልኩ በሙስና ወደ ግለሰቦች ኪስ የሚገባውን ከፍተኛ የአገር ኃብት ጥቅም ላይ ማዋል ቢቻልና፣ የዕድገት ቅደም ተከተል አውጥተን በዕቅድ ብንመራ፣ የእርሻና የእንዱስትሪ ዘርፎቻቸን ተደጋግፈው እንዲያድጉ ማድረግ እንችላለን። ይህንን ስራ ከሰራን በኋላና ወደ ውጭ የሚላኩ ሸቀጦችን በብዛት ማምረት ስንጀምር ነው ስለ ብር ምንዛሬ ተመን በጥንቃቄ ማሰብ ያለብን።
ባለፉት 35 አመታት በአለማችን ውስጥ እጅግ በጣም አስገራሚ በሆነ ፍጥነት ያደገቸው ቻይና ዛሬ ያለችበት ከፍተኛ የዕድገት ደረጃ ላይ መድረስ የቻለችው የገንዘቧን የውጭ ምንዛሪ ተመን በገበያ እንዲወሰን በማድረጓ አይደለም፣ ይልቁንም ቻይና ያደገችውና ዛሬ ግንባር ቀደም የኤክስፖርት አገር መሆን የቻለችው የገንዘቧን የውጭ ምንዛሬ ተመን ማዕከላዊ ባንኳ በዕቅድ እንዲቆጣጠረው በማድርጓ ነው። ዛሬ በውጭ ንግድ ብቃታቸው በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱ አገሮች ውስጥ በገበያ የሚተመን የውጭ ምንዛሪ የሌላት አገር ቻይና ናት። ስለዚህ አገራችን ኢትዮጵያ ለፈጣን የኤኮኖሚ ዕድገት ለምታደርገው ጥረት የፖሊሲ ትምህርት መውሰድ ያለባት የኃብታሞቹ ምዕራባዊያን አገሮች ጥቅም አስጠባቂ ከሆኑት ከአለም ባንክና ከአለም አቀፍ የገነዘብ ተቋም ብቻ ሳይሆን ቻይናን ከመሳሰሉ አገሮችም መሆን አለበት።