ይች ምድር ፍርደ ገምድሏ ነገር ዓለሟ ውሎዋ ከመጠን በላይ የከፋ፣
ሰዶሞች ተቤተ መንግስት ቁጭ ብለው የጥፋት ወሀ ደረስ በጎፋ፡፡
እንደ እፍኝት ልጆች ተራራው ድንጋዩ አሽዋው ሳሩ ቅጠሉ ከዳና፣
ህፃን ጎልማሳው አዛውንት ባልቴቱን ሁሉ አፈር ተጫነው በጎፋ!
ጭራቆች ዘርን ለማጥፋት ድሮን በዶላር ከቱርክ ከዱባይ ሲገዙ፣
ጎፋዎች አካፋ እንኳ አጥተው አፈር በእጃቸው በርቅሰው እሬሳ መዘው አወጡ፡፡
ስስት ያከነፋቸው ጆፌዎች ይሉኝታን ጥለው በጀት እሮቢላዎች ሲበሩ፣
ለፍቶ አዳሪዎች ገባሮች ጎፋዎች ለጥርጊያ መንገድ እንኳን ያልበቁ፣
ገደሉ ሲናድ ፈጥኖ የሚደርስ እንኳንስ የዓለም የአገር አጋዥ እንኳ አጡ!
የአገርን አጥንት ሥጋ በቋንቋ ካራ ቆራርጠው ክትፍትፍ አርገው የበሉ፣
ትውከት ተቅማጡ ሲያማቸው ለህክምና ወደ ውጭ አገር ሲበሩ፣
ጎፋዎች ናዳው መቷቸው አጥንት ስጋቸው ተጎድቶ ደም እንደ ጅረት ሲያፈሱ፣
የቁስል መጥረጊያ ፋሻና የአጥንት ስብራት ማሰሪያም ጀሶ አጡ፡፡
የሚገብሩትን ግብር ላፍ አርገው የቅንጦት ኑሮ የሚኖሩቱ ሌቦቹ፣
መንገድ ክሊኒክ በመስራት ፋንታ የዘር መጥረጊያ ታንክ የሚገዙቱ፣
ዛሬ ዓለም ሲሳለቅ አፈር ውጧቸው ጎፋዎች አፈር በእጃቸ ሲዝቁ፣
እንደ አዛኝ ቅቤ አንጓች የሶስት ቀን ሐዘን አዋጅ አውጥተው ቢሰብኩ፤
እንኳንስ ተእግዜር ተሕዝብም አንጀት ጠብ አይል ተታሪክ ተጠያቂነት አይድኑ፡፡
እንደ ሌባ ገዥዎች ተራራው ጋራው ወቅትን ተጠቅሞ ሙልጭ አድርጎ የከዳህ፣
የጎፋ ሕዝብ ሆይ እግዚአብሔር እንባህን ያብስ ጥናቱን ባያሌው ይስጥህ፣
እንደ ጋሞዎች የምትወዳት የኢትዮጵያ አምላክ ሐዘን ልቅሶህን ያዳምጥህ፣
ከወጎኖችህ እሬሳ የአፈር ተራራ በእጆችህ ከመዛቅ የሚያድን መንግስት ያምጣልህ፡፡
በላይነህ አባተ ([email protected])
ሐምሌ ሁለት ሺ አስራ ስድስት ዓ.ም.