June 16, 2024
15 mins read

በትሮይ ፈረስነት የመከራና የውርደት አገዛዝን ማራዘም ይብቃን!!!   

June 16, 2024

ጠገናው ጎሹ

በሥልጣነ መንበር ላይ የሚፈራረቁ ባለጌ፣ ሴረኛ፣ ሸፍጠኛና ጨካኝ ገዥ ቡድኖች መከረኛውን ህዝብ ከአስከፊ ድንቁርና እና ከሁለንተናዊ የመከራና የውርደት ዶፍ ጋር እንዲለማመድ  ከሚያደርጉባቸው እጅግ በጭካኔ  የተሞሉ ዘዴዎቻቸው መካከል ኮሚቲ፣ ቦርድ፣ ኮሚሽን፣ እንባ ጠባቂ (ombdusman)፣ የሴቶች ማህበራት እና የወጣቶች ማህበራት፣ ወዘተ በሚል የሚሰይሟቸው አካላትን በትሮይ ፈረስነት (as Trojan Horses) መጠቀም ነው።

በዚህ እጅግ የአስቀያሚና የአደገኛ ፖለቲካ ጨዋታ ውስጥ  ህሊናን በእጅጉ አስጨናቂና አስፈሪ እየሆነ የመጣው  ጉዳይ ደግሞ ከፈጣሪ የተሰጣቸውን የመልካም እረኝነት ሃላፊነትና ተግባር በአግባቡ ከመወጣት ይልቅ ራሳቸውን ለትሮይ ፈረስነት አሳልፈው እየሰጡ  “አገርና ሃይማኖት ከፍተኛ አደጋ ውስጥ ናቸውና እግዚኦ በሉ” የሚል ድርጊት አልባ አዋጅ የሚያውጁ የሃይማኖት መሪዎች፣ ሊቃውንት ፣ ሰባኪያን፣   መምህራንና ባለ ሌላ ማዕረግ አገልጋዮች ቁጥር ቀላል ያለመሆኑ ግዙፍና መሪር እውነታ ነው።  

ደረጃው ይለያይ እንጅ እንዲህ አይነቱ እያታለሉና እያዘናጉ የመከራንና የውርደትን የቤተ መንግሥት ፖለቲካ (palace politics) የማስቀጠል እኩይ ዓላማና ተግባር ለዘመናት የዘለቀ የመሆኑ እውነታ እንደተ ተጠበቀ ሆኖ የፈጣሪያቸውንና የአሳዳጊያቸውን የህወሃትን ጠርናፊነት አስወግደው የተረኝነቱን ሥልጣንና ተግባር በተቆጣጠሩት ኦህዴዳዊያን/ኦሮሙማዊያን/ ብልፅግናዊያን የስድስት ዓመታት አገዛዝ ወቅት ያየነውና እያየነው ያለው የትሮይ ፈረሶችን (ሽፋን ሰጭ አሻንጉሊቶችን) የመፍጠርና በዘመቻ መልክ የማሠማራቱ ሥራ በአይነትም ሆነ በመጠን በእጅጉ አስከፊ ነው።

ይህ  አስከፊ የኢህአዴግ ውላጅ የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኞች ቡድን በዘመነ ህወሃት/ ኢህአዴግ የተቋቋሙትን የምርጫ ቦርድ ፣ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን እና እንባ ጠባቂ (ombudsman)  ተብለው የሚጠሩ  አካላትን ይበልጥ ሸፍጠኝነት፣ ሴረኝነትና ጨካኝነት በተሞላበት አኳኋን በትሮይ ፈረስነት እየተጠቀመባቸው የመሆኑን ግዙፍና መሪር እውነታ የሚክድ ባለ ቅንና ባለ ሚዛናዊ ህሊና ነፃነትና ፍትህ ፈላጊ የአገሬ ሰው የሚኖር አይመስለኝም።

በፀረ- ህወሃት/ኢህአዴግ ህዝባዊ እንቅስቃሴ ወቅት የነበራቸውን ለነፃነትና ለፍትህ ሥርዓት እውን የመሆን እምነታቸውንና አወንታዊ አስተዋፅኦ በህወሃት ተፅፎ የተሰጣቸውን ያልሠሩትን የወንጀል ድርሰት በመፈረም ታጉረውበት ከነበረው ማጎሪያ ቤት በመውጣት ክፋኛ ያጎሳቆሉትን ብርቱካን መዴቅሳን  እና ዳንኤል በቀለን ከያሉበት ጠርቶና አስጠርቶ የአገዛዙን ወንጀል መሸፈኛ ላደረጋቸው የምርጫ ቦርድ እና የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ተብየዎች  የበላይ ሃላፊነት ሹመት የሰጠበትን ዋነኛ ምክንያት ከስድስት ዓመታት ወዲህ ከሆነውና እየሆነ ካለው ግዙፍና መሪር እውነታ በላይ ማስረጃ የለም።በአንድ በኩል የእኩያን ገዥዎችንና የግብረ በላዎቻቸውን ተውኔተ ፖለቲካ እና በሌላ በኩል ደግሞ መሬት ላይ የሆነውንና እየሆነ ያለውን ግዙፍና መሪር እውነታ ከምር የሚያስተውል የአገሬ ሰው ለዘመናት ከዘለቅንበትና በአሁኑ ወቅት ደግሞ ይበልጥ አስከፊ በሆነ ሁኔታ ተዘፍቀን ከምንገኝበት ፖለቲካ ወለድ መከራና ውርደት ሰብረን ለመውጣት የምናደርገው ትግል በእጅጉ ፈታኝ እንደሆነ እና ይህንኑ የሚመጥን የጋራ ተጋድሎን የግድ የሚል መሆኑን ለመረዳት የሚሳነው አይመስለኝም።

የምርጫ ቦርድ ተብየው የእኩያን ገዥ ቡድኖች የተዋጣለት የትሮይ ፈረስነቱን በማያሻማ ሁኔታ ያረጋገጠው ለስሙ እንኳ የራሱን ህግና ደንብ ያላሟላውን ብልፅግና ተብየ ፓርቲ በምርጫ እንዲሳተፍ እና በተካነበት የማጭበርበርና የመጨፍለቅ ዘዴው በመጠቀም “አሸነፍኩ” ብሎ በተቆጣጠረው ሥልጣነ መንበር ማስፈፀሚያነት መከረኛውን ህዝብ የመከራው ቀንበር  ተሸካሚ አድርጎ እንዲቀጥል የማስቻሉ መሪር እውነታ ነው ።

አብይ አህመድም የዚህ አይነት እጅግ ሴረኛና ጨካኝ የፖለቲካ ተውኔት ውጤት የሆነውን  አገዛዙን ነው “በህዝብ ምርጫ” ያገኘውን ሥልጣነ መንበር መቃብሩ ላይ ካልሆነ በቀር ለሽግግር መንግሥት ባዮች አሳልፎ መስጠት እንደማይሞከር የምክክር ኮሚሽን በሚባለው የትሮይ ፈረሱ “የምሥራች አብሳሪ” ስብሰባ ላይ ተገኝቶ ፍርሃት በተናነቀው አንደበቱ ያረጋገጠልን።

የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ተብየው ለዘመኑ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጅ ምሥጋና ይግባውና ከአገር አልፎ ዓለም በደቂቃዎችና  በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ግልፅና ግልፅ  በሆነ ሁኔታ የሚያውቀውን ግዙፍና መሪር እውነት የገዥውን ቡድን የስሜት መጠንና ግለት እያዳመጠ ወይም እየለካ ሪፖርትና መግለጫ ከማሳወቅ ያለፈ ፋይዳ  ኖሮትም አያውቅም፤ የለውምም። በእውነት ስለ እውነት ከተነጋገርን ይህ ኮሚሽን ተብየ ዋነኛው ተጠያቂ ከላይ ከቤተ መንግሥቱ ፖለቲካ የሚጀምረው ሥርዓት አስተሳሰብና አሠራር  ሆኖ እያለ በደምሳሳው  የመንግሥት አካላት፣ የፀጥታ አካላት፣ ህግ አስከባሪ አካላት፣ ታጣቂዎች ወዘተ፣ የሚል ሪፖርት በማጠናቀር ከማሰማት/ከማሳወቅ ያለፈ ፋይዳ የለውም። ባይኖረውም አይገርምም። ለምን? ቢባል እኩያን ገዥ ቡድኖች እንኳንስ ለአገዛዛቸው የትሮይ ፈረስነት የፈጠሩትንና በቀጥታ የሚቆጣጠሩትን አካል በአንፃራዊነት ከእነርሱ ቀጥተኛ ቁጥጥር ውጭ የሆነን አካልም ፋይዳ ቢስ ያደርጉታልና ነው። ለዚህም ነው የኮሚሽኑ ኮሚሽነር መንግሥት የሚያካሂደውን የህግና የሰላም ማስከበር አስተወፅኦ ማበረታታትና መደገፍ እንዳለብን ምክር ቢጤ ሊሰጠን ሲሞክር የታዘብነውና የምንታዘበው ። ይህንንም  ብሏል  እንዴ? የሚል ሰው ካለ በየጊዜው የሰጣቸውን ቃለ ምልልሶች ቢጎበኝ ጥሩ ነው።

ይበልጥ አስቀያሚ የሆኑ ጉልቾች መለዋወጥ እንጅ የእውነተኛ ለውጥ እሴቶች፣ አስተሳሰቦችና አሠራሮች ፈፅሞ ያልታየበትን ሥርዓት በጠርናፊነት የተቆጣጠረው የኦህዴድ/የብልፅግና ገዥ ቡድን ለዚህ የትሮይ ፈረስነት ወይም ሽፋን ሰጭነት ይጠቅመው ዘንድ በመጀመሪያ ካቋቋሟቸው መ/ቤቶች መካከል አንዱን የሰላም ሚኒስቴር ብሎ በመሰየም በሰላም በራሱ እና ሰላምን በተጠማው መከረኛ ህዝብ ላይ ተሳልቋል።

ይህንን እጅግ አስከፊ ሁኔታ አግባብነት ባለው ይዘትና አቀራረብ በወቅቱ መገዳደር የሚችል የፖለቲካ ሃይል እና ህዝባዊ ንቅናቄ እውን ለማድረግ ባለመቻላችን ለአብይ አህመድና ካምፓኒው (ገዥ ቡድን)  የትሮይ ፈረሶችን የፖለቲካ ጨዋታ እንዲቀጥሉበት እድል ሰጠናቸው።  እናም የወሰንና የማንነት ኮሚሽን (እአአ 2019)  እና የእርቅና የሰላም ኮሚሽን (እአአ 2018) የተሰኙ የትሮይ ፈረሶቹን በአዋጅ እንዳቋቋሙ ነገሩን።

የሁለቱንም መኖር ወይም  አለመኖር ወይም እየኖሩ አለመኖር ሳናውቅ ነበር ብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን (Ethiopian National Dialogue Commission)  ተብየው 1   የፕሮፌሰርነት ማዕረግና የረጅም ዓመታት የሥራ ልምድ ባለቸው ግለሰብ ሰብሳቢነት የሚመራ ሆኖ  4 የዶክትሬት ፣ 4 የሁለተኛ ዲግሪ እና 2 የመጀመሪያ ዲግሪ   የያዙና የየራሳቸው  የሥራ ተሞክሮ ያላቸው በድምሩ 11 የሆኑ ግለሰቦችን እንዲይዝ ተደርጎ ( እ.አ.አ 2021)  በወጣ አዋጅ መቋቋሙ  የተነገረን።

ይህ ኮሚሽን ተብየ ከሂደቱ ጀምሮ የእኩያን ገዥ ቡድኖች የሴራና የሸፍጥ ፖለቲካ ማስፈፀሚያ መሣሪያነቱ (የትሮይ ፈረስነቱ) ግልፅና ግልፅ እንደነበር ቅንና ሚዛናዊ ህሊና ያለው የአገሬ ሰው የሚስተው ሃቅ አይመስለኝም ።  የመማርን፣ የሥራና የእድሜ ተሞክሮን ሰፊና ጥልቅ የሆነ ትርጉም (እሴትነት) በአድርባይነት ደዌ ያጎሳቆሉትና እያጎሳቆሉ ያሉት ኮሚሽነሮች ተብየዎች ከ10 ቀናት በፊት በአ.አ ባካሄዱት እና የእኩያን ገዥ ቡድኖች የሸፍጥና የሴራ ፖለቲካ  ቫይረስ ተሸካሚነታቸውንና አስተላላፊነታቸውን በአብይ አህመድ “የሽግግር ብሎ ነገር አይሞከርም” ዲስኩር አማካኝነት በይፋ አሳውቀውናል። ከሰሞኑ ደግሞ ይባስ ብለው  በህልውናው ላይ ወደ ተዘመተበት  የአማራ ህዝብ (ክልል) በመዝመት ህሊናዎቻቸውና እጆቻቸው በአያሌ ንፁሃን ደምና የቁም ሰቆቃ የተጨማለቁ ገዥ ቡድኖች የትሮይ ፈረስነታቸውን ተልእኮ ለመወጣት እየተዘጋጁ እንደሆነ ያለምንም ሃፍረት ነግረውናል።

ሌሎች አያሌ ድክመቶቻችን እንዳሉ ሆነው ዘመን ጠገብና ሥርዓት ወለድ የሆነውን የመከራና የውርደት ቀንበር  ሰባብረን ለሁሉም ዜጎች የሚበጅ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን  ለማድረግ ከፍተኛ ፈተና ከደቀኑብን ጉዳዮች አንዱ በሥልጣነ መንበር ላይ ለሚፈራረቁ እኩያን ገዥዎች (ቡድኖች) በትሮይ ፈረስነት ወይም በሰው ሥጋ ለባሽ አሻንጉሊትነት የሚያገለግሉ ምሁራን (የተማሩ) ተብየዎች ቁጥር ቀላል ያለመሆኑ መሪር እውነታ ነው።

እንዲህ አይነቱን የሥልጣኔና የሁለንተናዊ እድገት መሠረት በሆነው በሰላም እና  ሰላምን በተነፈገው ህዝብ ስም የመቆመር አስከፊ ደዌ  ዛሬውኑ በቃ ካላልነው በእጅጉ አስከፊ የሆነ ነገና ከነገ ወዲያ ነው የሚጠብቀን።

እናም ልብ ያለው ልብ ይበል!

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

በላይነህ አባተ ([email protected]) መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ምዕራባውያን የኢትዮጵያን ልጆች እያታለሉና እየደለሉ ከእምነታቸው ለመንጠቅ ሲቃጡ በ1951 ዓ ም ባሳተሙት ‘መድሎተ አሚን ወይም የሃማኖት ሚዛን ጥልቅ መጽሐፍ ሽፋን ላይ ሕዝብ ልቡናውን፣ ዓይኑን፣ ጀሮውንና

ሰው ሆይ!

“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።”  መዝሙረ ዳዊት 39:1 ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 15 January 2025 መግቢያ የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን

ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

Go toTop