ህገ መንግስታዊ ዲዛይን ምርጫዎቻችን የትኞቹ ናቸው?

ኤፍሬም ማዴቦ (emadebo@gmail.com )

እኛ ኢትዮጵያዊያን እራሳችንን ስንገለጽ የረጂም ግዜ ሥልጣኔና ታሪክ ያለን፣በነጭ ያልተገዛን፣ከ2000 አመት በላይ ተከታታይ የመንግስት ሥርዓት ያለን፣የሦስቱ ዘመን ያስቆጠሩ አብርሃማዊ ሃይማኖቶች አገር ነን እያልን ነው። ነገር ግን ባለፉት ሃምሳ አመታት የተጓዝነው የፖለቲካ መንገድ፣ በተለይ ዛሬን ጨምሮ ባለፉት አራት አመታት አንዳችን ሌላችንን ለማጥፋት የሄድንበት መንገድ፣ የረጂም ዘመን ሥልጣኔ ታሪክ ያለውና የሦስት ትልልቅ ሃይማኖቶች ባለቤት የሆነ ማህበረሰብ ቀርቶ፣ በታሪክ ባርቤሪያን የተባሉ ማህበረሰቦችም እንኳን ሊጓዙበት ጭራሽ ወደኋላ ዞር ብለው ማየት የማይፈልጉት መንገድ ነው። በተለያዩ ማህበራዊ ሜዲያ አውታሮች ላይ የምናያቸው ከሰው ልጅ ባህሪይ ውጭ የሆኑ የጭካኔ ቪዲዮዎች አፍ አውጥተው የሚናገሩት እንደገና የአንድ አገር ህዝብ ላለመባባል መማማላችንን ነው። ውሻና ድመት በአደባባይ የደበደበ ዜጋ ፍርድ ቤት ቀርቦ በሚቀጣበት አለም፣ በዛሬዋ ኢትዮጵያ የገዛ ወንድማቸውን ከብበው በዱላና በድንጋይ ጭንቅላቱን አፍርሰውና አይኑን አውጥተው ገድል እንደፈጸመ ሰው እየዘፈኑ ወደቤታቸው የሚሄዱ የሰው አውሬዎች ግን የሚጠይቃቸው የለም። ትናንት ጥፋት አጥፍቶ “በህግ አምላክ” ሲባል ቀጥ ብሎ ፖሊስ እስኪመጣ ይጠብቅ የነበረ ማህበረሰብ ለምንድነው እንዲህ ባጭር ግዜ ውስጥ እሱም ፖሊሱም ህግ አልባ የሆኑት? ለመሆኑ መቼና እንዴት ነው ከዚህ አይነት ህገወጥነትና ሥርዓት አልባነት ተላቀን፣ ለሁላችንም የሚስማማና ሁላችንንም እኩል የሚያቅፍ የፖለቲካ ሥርዓት የምንገነባው? መቼ ነው እንደ ዱር አውሬ መገዳደሉን ትተን፣የፖለቲካ ልዩነቶቻችንን በጠረቤዛ ዙሪያ ተቀምጠን በውይይት መፍታት የምንጀምረው? መቼ ነው ”እኛ” እና “እነሱ” ከሚል አፍራሽና ኋላቀር አስተሳሰብ ወጥተን “እኛ” መባባል የምንጀምረው?

አገራችን ኢትዮጵያ የብዙ ብሔር ብሔረሰቦች አገር ናት፣ኢትዮጵያ ውስጥ ቁጥራቸው 80 የሚደርስ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ለዘመናት ጎን ለጎን አብረው ኖረዋል፣ ሆኖም በዘመናዊው የኢትዮጵያ ታሪክ እነዚህ የተለያየ ቋንቋ፣ባህልና ሃይማኖት ያላቸው ብሔር ብሔረሰቦች የኔ ነው የሚሉት ቋንቋ፣ባህልና ማንነት ባለመከበሩ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት 75 አመታት ለተነሳው የቋንቋችን፣ ባህላችንና ማንነታችን ይከበር ጥያቄና የራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ መሠረት ሆኗል፣ ከጥያቄም አልፎ የየብሔራችንን መብትና ነጻነት እናስከብራለን የሚሉ የተለያዩ ኃይሎች ጫካ ገብተውና 17 አመት ተዋግተው የኢትዮጵያን የፖለቲካ ሥልጣን መቆጣጠር እንዲችሉ አድርጓል።

ባለፉት ሃምሳ አመታት በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረኮች ላይ በተከታታይ ከተነሱና ብዙ ክርክር ከተደረገባቸው ጥያቄዎች ውስጥ አንዱ ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው ጭቆና የመደብ ነው ወይስ የብሔር ነው የሚል ነው። የዚህ ጽሁፍ ጸሓፊ አገራችን ውስጥ የነበረው ጭቆና የመደብም ይሁን የብሔር፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የተለያዩ ማንነቶች ቋንቋቸው፣ ባህላቸውና ማንነታቸው አልተከበረም የሚል እምነት አለው። ባለፉት ሰላሳ አመታት በዕብሪተኞችና በአላዋቂዎች ተይዞ ዛሬ የሁሉም ነገር መጀመሪያና መጨረሻ ሆነ እንጂ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የብሔር ጥያቄ ሳይዘራ የበቀለ ጥያቄ አይደለም። የብሔር ጥያቄ ኢትዮጵያ ውስጥ ህዝባዊ መሠረት ያለው ትክክለኛ ጥያቄ ነው፣ይህ ጥያቄ በትክክል መመለሱን ማረጋገጥ የሁላችንም ሃላፊነት ነው። የብሔር ጥያቄን እንመልሳለን በሚል የግለሰቦችን መብት መርገጥ፣ዜጎች ገሃዱን አለም በብሔር መነጽር ብቻ እንዲመለከቱ ማስገደድና፣ በነጋ በጠባ እኛና እነሱ እየተባባልን እርስ በርስ እስክንገዳደል ድረስ የብሔር ፖለቲካን ያለልክ መለጠጥ ግን ለብሔር ብሔረሰቦችም ለአገርም አይበጅም። ስለዚህ የቡድን መብት ከግለሰብ መብት ይቀድማል የሚሉ የብሔር ፖለቲካ አቀንቃኞች፣ የቡድን (ብሔር) የመሠረት ድንጋይ (Buildig Blocks) ግለሰቦች መሆናቸውንና ግለሰብ በሌለበት ቦታ የሚከበር የቡድን መብት ሊኖር እንደማይችል ማወቅ አለባቸው። የግለሰብ መበት እስካልተከበረ ድረስ የቡድን መብትም አብሮ ይከበራል የሚሉ የግለሰብ መብት አቀንቃኞችም፣ ይህ አባባል ትክክል አለመሆኑን የብዙ አገሮች ተጨባጭ ሁኔታ በግልጽ ያሳያልና፣ ለቡድን መብት የሚታገሉ ኃይሎችን መብታችሁን ከግለሰብ መብት ውስጥ ፈልጋችሁ አውጡት ከሚል ትዕቢት መላቀቅ አለባቸው።

በህወሓት የተመሩት የብሔር ኃይሎች በ1983 ዓም ደርግን አሸንፈው የኢትዮጵያን የፖለቲካ ሥልጣን ከተቆጣጠሩ በኋላ በጻፉት ህገ መንግስት ውስጥ ብሔር ብሔረሰቦችን የአገር ሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤት አድርገዋቸዋል። ነገር ግን በወቅቱ በተግባር እንዳየነው አንዳንድ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ሉዓላዊ ናችሁ ወይም “ነፃ ወጣችሁ” በተባሉ ማግስት ነፃነት ፍለጋ ጠመንጃ እያነገቡ ጫካ ገብተዋል። ህወሓት/ኢህአዴግ የገነባው የብሔር ፖለቲካ ሥርዓት በየብሔሩ (በተለይ በትላልቆቹ ብሔሮች) ልህቃን ጭንቅላት ውስጥ የፖለቲካ ሥልጣን እጃችን ውስጥ ከገባ ሁሉም ነገር የኛ ነው የሚል እምነት በመፍጠሩ፣ ዛሬ የኢትዮጵያን ህዝብ ሠላም የነሳው ኃይል አለኝ የሚሉ ብሔሮች  አራት ኪሎን ለመቆጣጠር እዚህም እዚያም የሚጭሩት የጦርነት አሳት ነው። እኛ ኢትዮጵያዊያን የተለያየ ቋንቋ ብንናገርም፣ የተለያየ ባህልና ሃይማኖት ቢኖረንም፣አንድ የጋራ ፖለቲካ ሥርዓት ገንብተንና ፖለቲካዊ፣ ኤኮኖሚያዊና ማህበራዊ እሴቶቻችንን “እኩል” ተካፍለን “የኢትዮጵያ ህዝብ” ተብለን በጋራ በሰላም መኖር የማንችለው ለምንድነው? ወይም በሰላም የሚያኖረንን ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት በጋራ ዲዛይን የማናደርገው ለምንድነው?

የፖለቲካ ሳይንስ ጠበብቶች ከሁለት ምዕተ ዓመት በፊት የጠየቋቸውና ዛሬም ድረስ ሁሉንም የሚያረካ መልስ ያላገኙላቸው ሁለት በቅርብ የተቆራኙ ጥያቄዎች አሉ። አንደኛው – ጥያቄ ኢትዮጵያን በመሳሰሉ የተከፋፈሉ ማህበረሰቦች ውስጥ በየቀኑ የሚነሳውን ግጭትና አለመግባባት አስታግሶ ማህበረሰቡን ወደ አገራዊ አንድነት መውሰድ የሚችሉ ዲሞክራሲያዊ ተቋሞችን መገንባት ይቻላል ወይ የሚል ሲሆን፣ ሁለተኛው ጥያቄ ደሞ ጭራሽ በተከፋፈሉ ማህበረሰቦች ውስጥ ዲሞክራሲ መገንባት ይቻላል ወይ የሚል መሰረታዊ ጥያቄ ነው።“Considerations on Representative Government” በሚለው ሥራው እንግሊዛዊው የፍልስፍና ሰው ጆን ስቲዋርት ሚል የውክልና ዲሞክራሲ በተከፋፈለ ማህበረሰብ ውስጥ ይሰምር ይሆን የሚል ጥያቄ ይጠይቅና እሱ እራሱ መልሱን ሲመልስ ህዝባዊ መንግሥት ባለባቸው አገሮች ውስጥ ብዙ ልዩነቶችንና መራራቆችን ማጥበብ ይችላል ብሎ የሚያምንበትን በተመጣጣኝ ውክልና (Proportional Repersentation) ላይ የተመሠረተ ዲሞክራሲም ቢሆን በብሔር በተከፋፈሉ ማህበረሰቦች ውስጥ ተግባራዊ ሊሆን አይችልም ብሎ በአጽንኦት ተናግሯል። ለመሆኑ ይህ ጆን ስቲዋርት ሚል ከ150 ዓመታት በፊት ህብረ-ቋንቋ፣ህብረ-ባህልና ህብረ-ሃይማኖተ በሆኑ ማህበረሰቦች ውስጥ ዲሞክራሲ የማይታሰብ ነው ብሎ የተናገረው ንግግር እውነትነት አለው? የጆን ስቲዋርት አባባል ትክክል ከሆነ፣እኛ ኢትዮጵያውያን ባለፉት 50 አመታት “ዲሞክራሲ አሁኑኑ” እያልን እርስበርስ የተገዳደልነው ለምንድነው? ወይስ የዘመናችን የፖለቲካ ሳይንስ ጠበብቶች እንደሚነግሩን ህገ መንግሥትን፣ ስነ ምርጫንና መንግሥታዊ ተቋሞችን በተጠና መንገድ ነድፎ በመገንባት ኢትዮጵያን በመሳሰሉ በብሔር፣በቋንቋና በሃይማኖት በተከፋፈሉ ማህበረሰቦች ውስጥ ዲሞክራሲን መገንባት ይቻላል?

በዚህ ጽሁፍ ውስጥ በተደጋጋሚ ከሚነሱ ፅንሰ ሐሳቦች ውስጥ አንዱ “የተከፋፈሉ ማህበረሰቦች” (Divided Societies) የሚለው ፅንሰ ሃሳብ ነው። ለመሆኑ ማህበረሰቦች ምን ሲሆኑ ነው “የተከፋፈለ ማህበረሰብ” ተብለው  የሚጠሩት? አንድን ማህበረሰብ የሚከፋፍለውስ ምንድነው? ደግሞስ አንድን ማህበረሰብ የተከፋፈለ ማህበረሰብ ነው የምንለው በአንፃሩ ያልተከፋፈለ ማህበረሰብ ስላለ ነው ወይስ “የተከፋፈለ ማህበረሰብ” የሚለው ፅንሰ ሃሳብ ከምንም ጋር ሳይነፃፀር ብቻውን የቆመ ፅንሰ ሃሳብ ነው? አንድ ማህበረሰብ በተለያዩ ነገሮች ሊከፋፈል ይችላል፣ ለምሳሌ፣ ኃብትና ትምህርት ማህበረሰብን ሀብታምና ደሃ እና የተማረና ያልተማረ በሚል በሁለት ይከፍላሉ። ሆኖም ኃብትና ትምህርት ኅብረተሰብ በኢኮኖሚ ባደገና ትምህርት በተስፋፋ ቁጥር እየጠበቡ የሚሄዱ መለያዎች ናቸው። በዚህ ጽሁፍ ውስጥ የ”ተከፋፈለ ማህበረሰብ” ሲባል ሃይማኖትን፣ ቋንቋን፣ ብሔርን እና ባህልን የሚያጠቃልል ፅንሰ ሃሳብ ነው። አንድ ማህበረሰብ የተከፋፈለ ማህበረሰብ ነው የሚባለው በማህበረሰቡ ውስጥ በብሔር፣ በቋንቋ፣በባህልና በሃይማኖት የሚለያዩ የወል ስብስቦች ስላሉ ብቻ አይደለም። አንድን ማህበረሰብ የተከፋፈል ማህበረሰብ ነው የሚያሰኘው በማህበረሰቡ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ የማንነት ስብስቦች በማንነታቸው ተደራጅተው የፖለቲካ ሥልጣን እስከ መቆጠጠር ድረስ በተደጋጋሚ ግጭት ውስጥ ሲገቡ ነው።

ለምንድነው የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች በብዛት በሚኖሩበት አገር ሥልጣን ተጋርተው በሰላም ከመኖር ይልቅ በብሔር እየተደራጁ የራሳቸውን ብሔር ማስቀደም የሚፈልጉት? ወይም ለምንድነው ሰዎች በብሔር ማንነታቸው ዙሪያ የሚሰባሰቡት? በአንድ አገር ዉስጥ ብሔሮች በብዛት መኖራቸዉ በራሱ የግጭትና የብጥብጥ ምንጭ ነው? በብዙ አገሮች ዉስጥ የተለያዩ የብሔር ማንነቶች የፖለቲካ ሥርዓቱ ተስማምቷቸዉ ጎን ለጎን በሰላም የሚኖሩት ምን ሲያገኙ ነዉ? ችግራቸውን ከሰላማዊ መንገድ ዉጭ በአመጽ ለመፍታት የሚገድዱትስ ምን ሲያጡ ነዉ? የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራንና የፍልስፍና ሰዎች እነዚህ ከላይ የተጠቀሱትን ጥያቄዎች ይመልሳል ብለዉ ያመኑባቸዉን አያሌ ንድፈሃሳቦች በጽሁፍ አቅርበዋል። እያንዳንዱን ንድፈሃሳብ እዚህ ፅሁፍ ላይ ማቅረብ ከፅሁፉ ድባብ በላይ ነዉ። ሆኖም የዚህ ፅሁፍ አቅራቢ አገራችን ዉስጥ ካለዉ የብሔር ፖለቲካ ጋር በቅርብ ይመሳሰላሉ የሚላቸው ሶስት ንድፈ ሃሳቦች እንደሚከተለዉ ይቀርባሉ።

  • ብሔር እንደ ግጭት መነሻነት የሚያየዉ ንድፈሃሳብ(Ethnicity as Conflictual Theory) -የዚህ ንድፈሃሳብ አራማጆች የብሔር ማንነት በተፈጥሮዉ የነዉጥና የብጥብጥ አዝማሚያ አለዉ የሚል ጠንካራ አቋም አላቸዉ። ማንነት እኛ ሰዎች ለራሳችን ካለን ክብር፣ ለእኛነታችን ካለን ትልቅ ግምትና ቦታ፣ የኔ ነዉ በምንለዉ ማንነት ላይ ካለን ኩራት፣ የዚህ ወይም የዚያ ስብስብ አባላት ነን ከሚል ከፍተኛ ስሜት (Strong sense of belonging) ጋር በቅርብ የተገናኘና የተሳሰረ ነዉ። እነዚህ ከማንነታችን ጋር የተያያዙ እሴቶች በአይን የማይታዩና በእጅ የማይዳሰሱ ስለሆኑ ግኑኝነታቸዉ ከቁሳዊዉ አካላችን ጋር ሳይሆን ከስሜት ህዋሳቶቻችን ጋር ነዉ። ደግሞም እነዚህ እሴቶች ከአካባቢያችን ጋር በየቀኑ የምናደርገዉን ግኑኝነት ትርጉም የሚሰጡትና ገሃዱን አለም የምንመለከትበትን እይታችንን የሚያሰፉት እኛ ሰዎች ብቻችንን ስንኖር ሳይሆን፣ የኛ ነዉ ብለን በምንጠራዉ ብሔር ዉስጥ ተሰባስበን ስንኖር ነዉ ብለን እናምናለን። ያኔ ነዉ ”እኛ” እና ”እነሱ”  ማለት የምንጀምረዉና፣ መልካም መልካሙን ሁሉ ከእኛ ቡድን ጋር መጥፎ መጥፎዉን ደግሞ ከኛ ዉጭ ካለ ቡድን ጋር የምናያይዘዉ። እኛ ሰዎች በብሔራችን ስም ለመግደልም ሆነ ለመሞት ፈቃደኞች የምንሆነዉ እነዚህ ከስሜት ህዋሳቶቻችን ጋር ግኑኝነት ያላቸዉ ከላይ የተዘረዘሩት እሴቶች መገለጫ የሆነዉ ቡድናችን (ብሔር) ከዉጭ ኃይሎች ጥቃት ሲደርስበት፣ ከፖለቲካና ኤኮኖሚ ሥርዓቱ ሲገለልና ባጠቃላይ የኛ የምንለዉ ብሔር የተናቀና የተዋረደ ሲመስለን ነዉ። የብሔር ማንነት ከሌሎች ማንነቶች ሁሉ ጠንካራና የአባላቱን ስሜት የመኮርኮርና የማነሳሳት ችሎታ አለዉ የሚባለዉ፣ እኛ ሰዎች የኛ ነዉ የምንለዉ ብሔር የተዋረደና የተናቀ ሲመስልን ዉስጣዊ ስሜታችን እኛ እራሳችን የተዋረድንና የተናቅን እስኪመስለን ድረስ ስለሚጎዳ ነዉ። በብሔራችን ላይ ጥቃት፣ ዉርደትና ንቀት የሚደርሰዉ የመንግስት መዋቅሮችን በተቆጣጠረ ተፎካካሪ ብሔር ከሆነ ደሞ ፍላጎታችን ሁሉ ይህንን ብሔር መበቀልና ማጥፋት ይሆናል።

 

  • ብሔርን እንደ ሁለተኛ ክስተት የሚያየዉ ንድፈሃሳብ(Ethnicity is Epiphenomenal )- የዚህ ንድፈሃሳብ አራማጆች ብሔረተኝነት የብሔር ፖለቲካ አራማጆች በግልጽ የማይናገሩት ወይም የማያሳዩት የሌላ አላማ ማራመጃ መሳሪያ ነዉ እንጂ ብሔረተኝነት በራሱ ግብ አይደለም ወይም ብሔረተኝነት እራሱ በዉስጡ ያዘለዉ እሴት የለም ባዮች ናቸዉ (Ethnicity has no intrinsic value)። የዚህ ንድፈሃሳብ አራማጆች እንደሚሉት ከሆነ በአንድ አገር ዉስጥ የተለያዩ ብሔሮች ጎን ለጎን ስለኖሩ ብቻ አይጣሉም ወይም ግጭት ዉስጥ አይገቡም ማለት ነዉ። የብሔር ልህቃን የራሳቸዉ ግብ አላቸዉ (ሥልጣን፣ ክብር፣ ዝና፣ ኃብት) – የብሔር ፖለቲካ ወይም ብሔረተኝነት የብሔር ልህቃን ወደዚህ ግባቸዉ ለመድረስ የሚጠቀሙበት መሳሪያ ነዉ። የብሔር ግጭት የሚፈጠረዉ የብሔር ልህቃን የፖለቲካ ግባቸውን ለማሳካት የብሔራቸውን አባላት እንደ መሳሪያ መጠቅም ሲጀምሩ ነው እንጂ ሁለት የተለያዩ ብሔሮች ጎን ለጎን ስለሚኖሩ ብቻ ግጭት ዉስጥ አይገቡም። የብሔር ልህቃን የአንድን አገር ኃብት ከሌሎች ወገኖቻቸዉ ጋር ተጋርተዉ በሰላም ከመኖር ይልቅ የራሳቸው ብቻ ለማድረግ ሲጀምሩ እንዲህማ አይሆንም ከሚሉ ሌሎች ተቀናቃኝ ብሔሮች ጋር ግጭት ዉስጥ ይገባሉ። ይህ ግጭት አንዳንዴ በመሳሪያ የታገዘ ግጭት ሊሆን ይችላል። ጠቅለል ባለ መልኩ ሲታይ በአንድ ብዙ ብሔሮች ጎን ለጎን በሚኖሩበት አገር ዉስጥ አንድ ብሔር ብቻዉን የፖለቲካ ሥልጣን ተቆጣጥሮ የሌሎች ብሔሮችን መብትና ነጻነት ለመርገጥ ሲሞክር ወይም ሲረግጥ የፖለቲካ ሥርዓቱ ያገለላቸዉ ብሔሮች በየብሔራቸው ዙሪያ ተደራጅተው ከፖለቲካ ሥርዓቱ ጋር መፋለም ይጀምራሉ። እዚህ ላይ የብሔር ልህቃን የራሳቸዉን ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኤኮኖሚያዊ ፍላጎት ለማርካት በሚያደርጉት ሩጫ ዉስጥ ብዙሃኑ ለምን ይሰማቸዋል ወይም ለምን ይከተላቸዋል የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። የብሔር ልህቃን ሜዲያን የመቆጣጠር አቅም ስላላቸዉ የገደሉህ፣ ጡት የቆረጡ፣ ያዋረዱህና የበዘበዙህ እነሱ ናቸዉ የሚለዉ ስሜት ቀስቃሽ ፕሮፓጋንዳቸዉ የሚከተላቸዉን ብሔር አባላት ያነሳሳል፣ በሌላ በኩል ደግሞ የፖለቲካ ሥልጣንን ለመቆጣጠር በሚደረገዉ የትግል ወቅትና ከዚያም በኋላ እኛም መጠቀም እንችላለን የሚሉ አያሌ የቡድኑ አባላት ከነተከታዮቻቸዉ የብሔር ልህቃኑን ይከተላሉ። መብትህንና ነጻነትህን እናስከብራለን ብለዉ ህዝብን አነሳስተዉና ለአመታት ተዋግተዉ የፖለቲካ ስልጣን ከተቆጣጠሩ በኋላ የአገርን ኃብት እንደ ጠላት ንብረት ዘርፈዉ የዉጭና የአገር ዉስጥ ባንኮችን ያጣበቡ የብሔር ልህቃንን እዚሁ አገራችን ዉስጥ ትናንትም ዛሬም በግልጽ አይተናል።

 

  • የብሔር ማንነት የግኑኝነት ፍለጋ ዉጤት ነዉ የሚለዉ ንድፈሃሳብ(Ethnicity as Relational Theory)- የዚህ ንድፈሃሳብ ዋነኛ መንደርደሪያ ሃሳብ ብሔረተኝነት ስጋት መቀነሻ መሳሪያ ነዉ (Ethnicity is all about uncertainty reduction)፣ የብሔር ፖለቲካ ግን የራስን ጥቅምና ፍላጎት ማሪኪያ መሳሪያ ነዉ የሚል ነዉ። ይህ ንድፈሃሳብ ሁለት ሃሳቦችን ለያይቶ ያያል። አንደኛ- ሰዎች የብሔር ማንነታቸዉን ፈልገዉ እንዲያገኙት የሚያደርጋቸዉ ምንድነዉ? ሁለተኛ- ሰዎች በዚህ ፈልገዉ ባገኙት የብሔር ማንነታቸው የተነሳ በግለሰብና በቡድን ደረጃ በተመሳሳይ መንገድ እንዲያስቡ የሚያደርጋቸው ምንድነው?

ማንነት ሰዎች የሚኖሩበትን ማህበራዊ አለም ለመዘወር የሚጠቀሙበት የማይዳሰስ መሳሪያ ነው። አንድ ሰው በሚኖርበት አካባቢ ከቤተሰቡ፣ ከጎረቤቱ፣ ከመንደሩ ከሌላ መንደርና ከተፈጥሮ ጋር በየቀኑ መስተጋብር ያደርጋል። ይህ መስተጋብር ዕድልም ተግዳሮትም ይዞ ይመጣል። ማንነት እነዚህ የሚታዩና የማይታዩ መስተጋብሮች፣ ግኑኝነቶችና የተለያዩ ባህሪያት ባሉበት ዉስብስብ ማህበራዊ አለም ዉስጥ ግለሰቦች የራሳቸዉን ቦታ አጠገባቸዉ ካሉ ሰዎች ጋር አንጻራዊ በሆነ መልኩ (Relative to others) ፈልገዉ ለማግኘት ማህበራዊዉን አለም የሚቃኙበት ራዳር ወይም ምናባዊ መሳሪያ ነዉ። ግለሰቦች በዚህ በውል በማያዉቁት አለም ዉስጥ ምን እሆናለሁ፣ ቤተሰቦቼን እንዴት በሰላም አኖራለሁ፣ እንዴት ነው እራሴንና ቤተሰቦቼን ከአደጋ የምከላከለዉ ከሚል ስጋት (Uncertainty) ጋር በየቀኑ ይፋጠጣሉ። ግለሰቦች ይህንን ፍጥጫ ብቻቸዉን መጋፈጥ አይፈልጉም ቢጋፈጡም ብቻቸዉን የሚቋቋሙት አይመስላቸዉም። ስለዚህ ይህንን ስጋት የሚጋራቸዉ ሌላ ሰዉ ይፈልጋሉ። ስጋት ከማንነት ጋር በቅርብ የተቆራኘ መሆኑን በሶስት መልኩ ማየት ይቻላል። አንደኛ- ስዎች የሚኖሩበት ማህበራዊ አለም እጅግ በጣም ዉስብስብ የሆነና የትየለሌ ግኑኝነቶችና ባህሪያት የሚገኙበት አለም ነዉ። ሁለተኛ- ይህ ዉስብስብ አለም በውል የማይታወቅ አለም ነው። ሶስተኛ- ሰዎች ፊት ለፊታቸዉ ያለውን የቅርብ የቅርቡን ነው የሚያዩት እንጂ የትናንቱን፣ የዛሬዉንና የነገውን መረጃ ሰብስበው አካባቢያቸውን መቆጣጠር ወደሚያስችላቸው መረጃ የመለወጥ ችሎታቸው ዉስን  ነው። ይህ መረጃ ሰብስቦ የመጠቀም ዉስንነት ከምንኖርበት አለም ዉስብስብነት ጋር ሲደመር ግለሰቦች በገሃዱ አለም ዉስጥ የሚደርስባቸውን ስጋት ለመቀነስ እርዳታ ፍለጋ የግድ ከራሳቸዉ ዉጭ እነሱን የሚመስል ሌላ ሰው ፍለጋ ይሄዳሉ። ሄደው መቀላቀል የሚፈልጉትና በቀላሉ መቀላቀል የሚችሉትም የጸጉሩ አይነት፣ የቇዳ ቀለሙና የፊቱ ገጽታ እነሱን ከሚመስልና የነሱን ቋንቋ ከሚናገር ሰው ጋር ነው። እንግዲህ ሰዎች በብሔር የሚሰባሰቡት ወይም ብሔር ማህበራዊ ስሪት ነዉ (Ethnicty is socially constructed) የሚባለውም ብሔር ግለሰቦች በማህበራዊ ኑሯቸው ዉስጥ የሚገጥማቸዉን ስጋት ለመቀነስ ፈልገው አግኝተው የሚከለሉበት በረጂም ግዜ አብሮ መኖር ሂደት የፈጠሩት ከለላ ስለሆነ ነው።

እነዚህ ከላይ ተራ በተራ ያየናቸዉ ሶስት ንድፈሃሳቦች የሚመሳስልም የሚቃረንም ሃሳብ አላቸው፣ ለምሳሌ መጀመሪያ ላይ ያየነዉ ንድፈሃሳብ ብሔረተኝነት በተፈጥሮው የግጭትና የብጥብጥ አዝማሚያ አለው ሲል፣ ሁለተኛ ላይ ያየነው ንድፈሃሳብ ግን ብሔረተኝነት በራሱ የግጭት መነሻ ሊሆን አይችልም ወይም ብሔረተኝነት የራሱ የሆነ ዉስጣዊ እሴት የለውም ይላል። ሆኖም ሶስቱም ንድፈሃሳቦች የአንድ አገር የፖለቲካ ሥርዓት የብሔርን ጥያቄ አግባብ ባለው መልኩ ካልመለሰና ብሔረተኝነት/Ethnicity በፖለቲካ ሥርዓቱ ዉስጥ ካልታቀፈ አደጋ አለው በሚለው ሃሳብ ላይ ይስማማሉ። በእርግጥም ከአንዳንድ ያፈነገጡ ሁኔታዎች ዉጭ የብሔር ጥያቄ በሚስተናግደበትና ብሔረተኝነት በሚታቀፍበት የፖለቲካ ሥርዓት ዉስጥ ብሔሮች ህገመንግስታዊ ሥርዓትን አክብረዉ በሰላም ይኖራሉ። ደግሞም የብሔረተኝነትና የብሔር ፖለቲካ ጡዘት እየረገበ ይሄዳል፣ እንዲህ ማለት ግን ብሔሮች ይጠፋሉ ማለት አይደለም። በአንፃሩ የብሔርን ጥያቄ በማይመልሱና ብሔሮችን ቋንቋና ባህል በማያከብሩ የፖለቲካ ሥርዓቶች ዉስጥ ብሔሮች መብታቸውን ለማስከበር ሲሉ ህገ መንግስታዊ ያልሆኑ አማራጮችን ጭምር ይከተላሉ።

የሌሎች አገሮች ልምድ ምን ያስተምረናል?

ኢትዮጵያን በመሳሰሉ ብዙ የብሔር፣ የቋንቋ፣ የባህልና የሃይማኖት ስብስቦች ጎን ለጎን በሚኖሩባቸዉ አገሮች ዉስጥ ነውጥ፣ግጭትና የመገንጠል ጥያቄ ተፍጥሮአዊ ነው ብለን የምናስብ ሰዎች ካለን ተሳስተናል። ሩዋንዳ ዉስጥ እርስ በርስ የተላለቁት ሁቱዎችና ቱትሲዎች እንዲሁም የቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ ስትፈርስ እርስ በርስ የተጨፋጨፉት ሰርቢያዎች፣ ክሮሺያዎችና ቦስኒያዎች በጦርነት ከተፈላለጉበት ግዜ ይልቅ በሰላም አብረው የኖሩበት ግዜ እጅግ በጣም ይበልጣል። በ1994 ዓም ጉጅራት በምትባለው የህንድ ግዛት ዉስጥ ሙስሊሞችና ህንዱዎች በግጭት ሲታመሱ፣ ከጉጅራት ተገንጥላ የወጣቸው ሌላዋ የህንድ ግዛት ማሃራሽትራ ዉስጥ የተለያዩ ማህበረሰቦች ጎን ለጎን በሰላም ይኖሩ ነበር፣ ደግሞም የአለማችን ዋና ዋና ሃይማኖቶች ሁሉ የሚገኙባትና፣በሺዎች የሚቆጠሩ ብሔሮች (Ethnic Groups) የሚኖሩባት ህንድ፣ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየው አይነት የብሔር ግጭትና የርስበርስ ጦርነት አይታይባትም። ናይጄሪያ ዉስጥ በ1960ዎቹ አጋማሽ ላይ ኢቦዎችና ሃዉሳዎች በእርስ በርስ ጦርነት ሲተላለቁ ዩርባ ዉስጥ አንጻራዊ ሰላም ነበር። የቀድሞዋ ሶቭየት ህብረት ስትፈራርስ ዩክሬይንና የቦልቲክ ሪፑብሊክ አገሮች ካልተገነጠልን እያሉ የጮሁትን ያክል የማዕከላዊ ኢሲያ ሪፑብሊኮቹ ካዛክስታንና ኪርግስታን የሚያዋጣን አንድነቱ ነዉ እያሉ ይጮሁ ነበር። ታድያ ለምንድነዉ የእነዚህ አገሮች ታሪክ ሲወሳ በሠላም አብረዉ ከኖሩባቸዉ ብዙ አመታት ይልቅ በጦርነትና በግጭት ያሳለፏቸዉ ጥቂት አመታት ጎልተዉ የሚነገሩት?

ጄኔራል ፍራንኮ ስፔንን በአምባገነንነት በመሩባቸዉ 36 አመታት ዉስጥ ካቶሎኖችና (Catalonians) ባስኮች (Basques) ማንነታቸዉ ተጨልቆ በትልቋ ስፔን ዉስጥ እንዲካተቱ ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል። ይህ በፖሊሲና በህግ ተደግፎ የሁለቱን ህዝቦች ማንነት ለመጨፍለቅ የተደረገው የአምባገነኑ ፍራንኮ ሙከራ ስፔን ዉስጥ የካቶሎኖችና የባስኮች ብሔረተኝነት ጎልቶ እንዲወጣና ሁለቱ ቡድኖች አመጽን እንደትግል አማራጭ እንዲወስዱት አደረገ እንጂ የታቀደለትን አላማ አልመታም። ቡልጋሪያና ሩማኒያ ዉስጥም ኮሚኒዚም ፈርሶ ዲሞክራሲ ሲገነባ፣ ቡልጋሪያ ዉስጥ አናሳ ቱርኮችን ሩማኒያ ዉስጥ ደግሞ አናሳ ሃንጋሪዎችን ጨፍልቆ አንድ ወጥ ብሔራዊ ማንነት ለመፍጠር የተደረገዉ ጥረት ሁለቱም አገሮች ዉስጥ ግጭትና ብጥብጥ ፈጥሮ የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሂደቱን ወደኋላ ጎተተው እንጂ ሌላ ምንም የፈየደዉ ፋይዳ የለም። ሰሪላንካ ዉስጥም በተመሳሳይ መልኩ ሲንሃሊሶች ታሚሎችን ለመጨፍለቅ ያደረጉት ሙከራ ታሚሎች የትጥቅ ትግል ዉስጥ እንዲገቡ ከማድረጉና ሰሪላንካን የብጥብጥ መድረክ ከማድረጉ ባሸገር ታሚሎችን አልጨፈለቃቸዉም።

ዛሬ የብሔር ፖለቲካ በፈጠረው ማህበራዊና ፖለቲካዊ ቀውስ የምትታመሰው አገራችን ኢትዮጵያ ከህንድ፣ከስፔን፣ከናይጄሪያ፣ከሩማንያ፣ከቡልጋሪያና ከሰሪላንካ የምትማራቸዉ ብዙ ጠቃሚ ትምህርቶች አሉ። ስፔን ከጄኔራል ፍራንኮ በኋላ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ስትገነባ ካቶሎኖች ከህገ መንግስቱ ድርድር ጀምሮ ስፔን ዲሞክራሲያዊ ሽግግር ባደረገችባቸዉ ሂደቶች ዉስጥ በእያንዳንዱ ምዕራፍ ውስጥ ተሳታፊዎች ነበሩ። ባስኮች ግን እንዲህ አይነቱን ዕድል እነሱን በሚመጥን መልኩ አላገኙም። ይህ አንዱን የማቀፍ ሌላውን የማግለል አባዜ ካቶሎኖች በፖለቲካ ሥርዓቱ ዉስጥ በሰላም እንዲኖሩ ባስኮች ግን አኩርፈው ከማዕከላዊው መንግስት ጋር ጦርነት ውስጥ እንዲገቡ አድርጓቸዋል። ቡልጋሪያና ሩማኒያ ዉስጥ ቱርኮችና ሃንጋሪዎች በህገ አውጭውና በህግ አስፈጻሚው አካል ዉስጥ መወከላቸው እስኪረጋገጥ ድረስ አመጽ የመጀመሪያ ምርጫቸው ነበር። ሰሪላንካ ዉስጥም የታሚሎች ታሪክ ከዚህ የተለየ አይደለም። የተለያዩ የማንነት ስብስቦች አንዱ አገር ውስጥ ከጎናቸው ካለ ሌላ ማንነት ጋር ተከባብረው በሠላም ሲኖሩ፣ ሌላው አገር ውስጥ ግን የፖለቲካ ሥርዓቱን እስከማፍረስ ድረስ ግጭት ዉስጥ የሚገቡት ለምንድነው? አገራችን ኢትዮጵያ ዉስጥ ሠላምና መረጋጋት ሰፍኖና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ተገንብቶ ሙሉ ኃይላችንን ወደ ዕድገትና ብልጽግና ማዞር ከፈለግን ለዚህ ጥያቄ ተቋማዊ መልስ መስጠት አለብን።

አፍጋኒስታንና ሴሪላንካ ዉስጥ የትኛው ቋንቋ ነው ብሔራዊ ቋንቋ መሆን ያለበት የሚል ንትርክ አለ፣ስፔንና ካናዳ ዉስጥ ካቶሎኒያዊያን እና ኩቤኮች እራሳቸውን በራሳቸው ለማስተዳደር ከሌሎች ግዛቶች የተለየና የበለጠ ሥልጣን ይፈልጋሉ (Ayssyemtric Power)፣ኢራቅና ፊጂ ዉስጥ አናሳ የሃይማኖትና የብሔር ቡድኖች በፖለቲካ ሥርዓቱ ዉስጥ ተመጣጣኝ ውክልና ሊኖረን ይገባል የሚል ጥያቄ ሁሌም እንዳነሱ ነው፣ደቡብ ሱዳን ውስጥ ዲንካዎችና ኑዌሮች የአገሪቱን የፖለቲካ ሥልጣን እኩል መጋራት አለብን በሚል ጦር ይማዘዛሉ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ቋንቋችንና ባህላችን እውቅ ይኑረው ወይም “ክልል እንሁን” የሚል ጥያቄ ሁሌም እንደተነሳ ነው። ዛሬ በተለያዩ የአለም አካባቢዎች እየተቀሰቀሱ የብዙ ሰው ህይወት ከሚቀጥፉና ንብረት ከሚያወድሙ ጦርነቶች ውስጥ ከ95% በላይ የሚሆኑት የሚካሄዱት በሉዓላዊ አገሮች መካከል ሳይሆን፣ በተለያዩ ሉዓላዊ አገሮች ዉስጥ በሚገኙ የቋንቋ፣ የባህልና የሃይማኖት ቡድኖች መካከል ነው። ይህ የሚያሳየን የተከፋፈሉ ማህበረሰቦች ምን አይነት ዲሞክራሲ ያስፈልጋቸዋል ወይም በአንድ የፖለቲካ ሥርዓት ዉስጥ የቋንቋ፣ የባህልና የሃይማኖት ብዝሃነትን እንዴት ነው ማስተናገድ የሚቻለው የሚለው ጥያቄ የዘመናችን ቁልፍ ጥያቄ እንደሆነ ነው። ይህ ጥያቄ እኛም አገር ዉስጥ በጥንቃቄ መመለስ ያለበት ቁልፍ ጥያቄ ነው።

    

             ይህንን ቁልፍ ጥያቄዎች የምንመልሰው እንዴት ነው?

ይህንን ጥያቄ ከመመለሳችን በፊት በቅርቡ ጀዋር መሐመድ አዲስ ስታንዳርድ ላይ የሰጠውን ረጂም ቃለመጠይቅና ለዚህ ቃለመጠይቅ መልስ የስጡትን ፕሮፌሰር መሳይ ከበደና አቶ ሞገስ ዘውዱ የሰጡትን መልስ ባጭሩ መቃኘቱ፣ሰፋ ያለውን የአገራችንን የወደፊት አቅጣጫ ለመቃኘት ይረዳናል ብዬ አምናለሁ። ጀዋር መሐመድ በቃለ መጠይቁ ውስጥ ካነሳቸው ብዙ ትልልቅ ሃሳቦች ውስጥ መድበለ-ባህላዊነት(Multiculturalism) እና ህብረ-ብሔራዊፌዴራሊዝም(Multinational Federlaism) ዋና ዋናዎቹ ናቸው። በዚህ ጽሁፍ ውስጥም ለወደፊቷ ኢትዮጵያ እንደ ዲዛይን አማራጭ ከቀረቡ  ሃሳቦች ውስጥ እነዚህ ሁለት የዲዛይን አማራጮች ይገኙበታል። በዚህ ጽሁፍና በጃዋር መሐመድ ሃሳብ መካከል ግን ትልቅ ልዩነት አለ። ጀዋር  መድበለ-ባህላዊነት እና ህብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝም ሁለቱም የየራሳቸው ደካማ ጎን እንዳላቸው ይናገራል እንጂ ግልጽ በሆነ መንገድ ለኢትዮጵያ የሚበጃት የትኛው እንደሆነና በተለይ ከእነዚህ ሁለት አማራጮች ውጭ ሌሎች ብዙ አማራጮች መኖራቸውን ይዘነጋል፣ ወይም ጀዋር በቃለ መጠይቁ ላይ በግልጽ እንዳስቀመጠው ኢትዮጵያን ከመድበለ-ባህላዊነትና በተለይ ከህብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝም ውጭ አይመለከትም። በዚህ ጽሁፍ ጸሐፊ እምነት ጀዋር ካነሳቸው ሁለት አማራጮች በተጨማሪ ኢትዮጵያ ሌሎች ብዙ ህገ መንግስታዊ የዲዛይን አማራጮች አሏት።

“ምን ግዜም” ሜዲያ ላይ የጀዋርን ሃሳብ በተመለከተ ፕሮፌሰር መሳይ ከበደና አቶ ሞገስ ዘውዱ ሰፋ ያለ፣ ብዙ ሃሳብ የሚጭርና በዩቱብ ሜዲያዎች ላይ ባልተለመደ መልኩ በሳልና አስተማሪ(Enlightening) ውይይት አድርገዋል። በውይይቱ ላይ ፕሮፌሰር መሳይ ኢትዮጵያ የሚበጃት የሚስማማትን ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት ነው ሲሉ፣ አቶ ሞገስ ደሞ ከዲሞክራሲ በፊት መጀመሪያ  “ህዝብ” ሊኖረን ይገባል ሲሉ ተደምጠዋል። ይህንን በተመለከተ ምሳሌ ሲሰጡ፣ ህወሓት/ኢህአዴግ የብሔር ፌዴራሊዝሙን ከፈጠረ በኋላ ሙሉ ዲሞክራሲ ሰጥቶን ቢሆን ኖር፣ ተገነጣጥለን ጠፍተን ነበር ብለዋል። በእርግጥ ብሔረተኝነት ጎልቶ በሚታይባቸው አገሮች ውስጥ፣ የብሔር ልህቃን ዲሞክራሲያዊ ሥርዓቱን ተጠቅመው የመገንጠል ጥያቄ ማንሳት ብቻ ሳይሆን ተግባራዊ ማድረግ የሚችሉበትም መንገድ ሊፈጠር ይችላል፣ጉደኛው የኢትዮጵያ ህገ መንግስት ደሞ ጭራሽ መገንጠል ትችላላችሁ ይላል። እንዲህ አይነት ችግሮች የሚፈጠሩት ግን ሥርዓቱ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ስለሆነ ብቻ ሳይሆን፣ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓቱ ዲዛይን የተደረገበት መንገድ ነው። ዲሞክራሲ ምንድነው የምንፈልገው ምንስ ነው የማንፈልገው ተብሎና ብዙ አማራጮች ቀርበው የምንፈልጋቸውን ዋና ዋና ነገሮች ይዞልን እንዲመጣ ተደርጎ ዲዛይን የሚደረግ ተቋም ነው። መኖሪያ ቤታችንን እንደየፍላጎታችን እና እንደ አቅማችን ዲዛይን እንደምናደርግ፣ ዲሞክራሲንም ከአገራችን ፖለቲካዊና ማህበራዊ ሁኔታዎች ጋር አብሮ እንዲሄድ አድርገን ዲዛይን ማድረግ እንችላለን። ዲሞክራሲያዊ ሥርዓታችንን ዲዛይን ስናደርግ ከቅርብም ከሩቁም አገርች ትምህርት መማር አለብን። ብዙ የአፍሪካ አገሮች በ190ዎቹ መጀመሪያ ከቅኝ አገዛዝ ነጻ ሲወጡ፣ ከቅኝ ገዢዎቻቸው እንዳለ የወረሱት ዲሞክራሲ ከአገራቸው ተጨባጭ ሁኔታዎች ጋር አብሮ አልሄድ ብሎ ምን ያክል እንዳስጨነቃቸው በአይናችን አይተናል። በእርግጥ አቶ ሞገስ እንዳሉት ኢትዮጵያ ውስጥ ዲሞክራሲን ለመገንባት በመጀመሪያ “ህዝብ” መኖር አለበት ያሉት አባባል ሁላችንም ገብቶን ከሆነ እጅግ በጣም ትልቅ አባባል ነው። በነገራችን ላይ ዲሞክራሲ  ግሪኮች  “ዴሞስ”  (The  People)  እና  “ክራቲያ”  (Power or Authority) የሚባሉ ሁለት ቃላቶቻቸውን አጣምረው የፈጠሩት ፅንሰ ሐሳብ ነው። ዲሞክራሲ ማለት የፖለቲካ ሥልጣንን ለህዝብ የሚሰጥ የመንግሥት ሥርዓት ማለት ነው። ስለዚህ በአንድ ድንበሮቹ በግልጽ በተሰመሩ የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ የሚኖር ማህበረሰብ የዚህ አገር ህዝብ ወይም የዚያ አገር ህዝብ በሚባል የዲሞክራሲ መሠረት በሆነ ስብስብ በሚገባ ተገልጾ ባልተቀመጠበት አውድ ውስጥ ዲሞክራሲ እገነባለሁ ማለት ሲሚንቶ ሳይኖር ፎቅ ቤት እስራለሁ ማለት ነው።

ባለፉት 30 አመታት ህገ መንግስታዊ ምህንድስና “በተከፋፈሉ ማህበረሰቦች” ዉስጥ ምን መልክ መያዝ አለበት በሚል ሰፊ የጥናትና ምርምር ስራ የሰሩ አረንድ ሊፓርትን፣ ዶናልድ ሆሮዊትዝን፣ ቤንጃሚን ራሊን፣ ፒፓ ኖርስንና ጆቫኒ ሳቶሪን የመሳሰሉ የአለማችን እውቅ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን ብዝሃነትን ለማስተናደግ አመቺ ናቸው የሚሏቸውን የተለያዩ ንድፈ ሃሳቦችንና እስትራቴጂዎችን በጥናትና ምርምር ስራቸው ዳስሰዋል። ይህ ጽሁፍ ወደነዚህ ሰፊ ሃሳቦች ዉስጥ አይገባም። ሆኖም እኛ ኢትዮጵያዊያን ብንመለከታቸው ለወደፊት ለምናስበው አገራዊ ፕሮጀት ይጠቅማሉ ተብሎ የሚታሰብባቸው ሁለት የስትራቴጂ ንደፈ ሃሳቦች ከዚህ ቀጥሎ ተራ በተራ እንመለከታለን።

እነዚህ ሁለት የስትራቴጂ ንደፈ ሃሳቦች ዉህደት (Integration) እና ማስተናገድ/መስተንግዶ (Accommodation) በመባል ይታወቃሉ። እስትራቴጂዎቹ የየራሳቸው ደካማና ጠንካራ ጎን ቢኖራቸውም፣ በተከፋፈሉ ማህበረሰቦች ዉስጥ በየራሳቸው መንገድ ማህበረሰቦችን ያቀራርባሉ ተብሎ የሚታመንባቸው እስትራቴጂዎች ናቸው። እዚህ ላይ ግን አንድ መጠንቀቅ ያለብን ጉዳይ አለ፣ እሱም ስለ እስትራቴጄዎቹ ደካማና ጠንካራ ጎን ስናወራ፣ ለምሳሌ ኢትዮጵያ ዉስጥ ከአንዱ እስትራቴጂ አንድ ጠንካራ ነው ተብሎ የተነገረለትን ተቋም ወስደን ተግባራዊ ብናደርግ፣ይህ ተቋም ኬንያ ወይም ጋና ውስጥ ጭራሽ ላይሰራ ይችላል። ስለዚህ እነዚህን ሁለት እስትራቴጂዎች በተመለከተ ጠንካራና ደካማ ጎን ሲባል አባባሉ ከተለያዩ አገሮች አኳያ በአንጻራዊነት መታየት አለበት።ኢትዮጵያ ዉስጥ ይደረጋል ተብሎ ለሚጠበቀው ብሔራዊ ጉባኤ በጥናታዊ ጽሁፍ ደረጃ ይቀርባሉ ተብለው ከሚጠበቁ የተለያዩ የእስትራቴጂ አማራጮች ወይም ሃሳቦች ውስጥ አንዱ የውህደትና የማስተናገድ/መስተንግዶ እስትራቴጂ ነው። እነዚህን ሁለት እስትራቴጂዎች የተለያዩ ማንነቶችን ከማንነቶቹ ፍላጎት ዉጭ በኃይል ጨፍልቆ ወደ አንድ አገራዊ ማንነት ለመለወጥ ከሚሞክረው ጭፍለቃ/መጨፍለቅ (Assimilation) ከሚባለው እስትራቴጂ ለይቶ ማየት አስፈላጊ ነው። ጭፍለቃ/መጨፍለቅ ማለት ሀ + ለ + ሐ = መ እንደ ማለት ነው። ዉህደት እስትራቴጂ ግን ቀጥለን በስፋት እንደምንመለከተው የማህበረሰቦችን ማንነት አይጨፈልቅም፣ እንዲያውም ዜጎች በግል ህይወታቸው ውስጥ ማንነታቸውን በተለያየ መልኩ እንዲገልጹ ይፈቅዳልም ያበረታታልም። ዉህደት ማለት ሀ + ለ = [(ሀ+ለ) + (ለ +ሀ)] እንደ ማለት ነው። እንዲህ ማለት “ሀ” ማንነቱን ሳይለቅ ከ “ለ” የሚያገኘው ብዙ ነገር አለ፣“ለ” ም ማንነቱን ሳይለቅ ከ“ሀ” የሚያገኘው ብዙ ነገር አለ ማለት ነው።

ዉህደት (Integration)

በእንግሊዝኛ ቋንቋ “Integrate” ማለት አንድን አካል ከሌላ አካል ጋር ማዋሃድ፣ማስተባበር እና አካላቱ ተዋህደው አንድ ላይ እንዲሰሩ ማድረግ ማለት ነው። “Integration’ ሲባል ደግሞ ይህንን ከላይ የተጠቀሰውን ድርጊት የመከወን ሂደት ማለት ነው። የዉህደት እስትራቴጂ ዜጎች የብሔር፣ የቋንቋ፣ የባህልና የሃይማኖት ማንነታቸውን በግል ህይወታቸው ዉስጥ እንዳሰኛቸው የመግለጽ መብታቸውን ያከብራል፣ ነገር ግን በማህበረሰብ ዉስጥ ያሉ የማንነት ልዩነቶች ተቋማዊ መልክ እንዲይዙ ወይም መንግስታዊ ጉዳዮች እንዲሆኑ አይፈቅድም። ይህ እስትራቴጂ የማንነት ልዩነቶች ቦታቸው በግለሰብ ደረጃ (Private Life) ዉስጥ ነው እንጂ በማህበረሰብ ደረጃ (Public life) ዉስጥ መሆን የለበትም የሚል እስትራቴጂ ነው። እንዲያውም የእስትራቴጂው ቁልፍ ግብ ግለሰቦች የየራሳቸውን የተለያዩ ማንነቶች እንደያዙ በጋራ ዜግነት ተሳስረው የጋራ በሆነ የፖለቲካ ማህበረሰብ ውስጥ ጎን ለጎን በሰላምና በእኩልነት አንዱ ሌላውን አክብሮ እንዲኖሩ ማድረግ ነው። የዉህደት እስትራቴጂ አቀንቃኞች በአንድ አገር የፖለቲካ ተቋሞች ዉስጥ ወገናዊነትና የአንድ ቡድን የበላይነት እስካለ ድረስና፣ የአንድን ወገን ሃይማኖት፣ ብሔር፣ ወይም ቋንቋ ብቻ የሚደግፍና አጉልቶ የሚያወጣ መንግስት እስካለ ድረስ፣ በዚያ አገር ውስጥ የፖለቲካ አለመረጋጋትና ግጭት የየዕለቱ ክስተት ይሆናል ጠንካራ እምነት አላቸው።

የዉህደት እስትራቴጂ አቀንቃኞች ማንነት ተኮር ግጭቶችንና አለመረጋጋትን ለማስወገድ የአንድ ቡድን የበላይነትን ማጥፋት አለብን፣ የአንድ ቡድን የበላይነትን ለማጥፋት ደግሞ የዚህ ምንጭ የሆነውን የብሔር ፓለቲካን ማጥፋት አለብን ብለው ይሞግታሉ። ከዚህ በተጨማሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሲቪክ ማህበራት ከዜግነት ውጭ በየትኛውም አይነት ማንነት ዙሪያ መደራጀት የለባቸውም የሚል ጠንካራ አቋም አላቸው። ቁልፍ አገራዊ ተቋማት ግንባታን በተመለከተ ደሞ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች በማንነት ዙሪያ እንዳይደራጁ የሚያበረታቱ የምርጫ ሥርዓቶችና ከብሔር፣ ከሃይማኖትና ከቋንቋ ፍጹም ነጻ ሆኖ የሚደራጅ የህግ አስፈጻሚ አካል ለተከፋፈሉ ማህበረሰቦች እጅግ በጣም አስፈጊዎች ናቸው ብለው ያምናሉ። በተለይ የፖለቲካ ሥልጣን ለመያዝ የሚወዳዳሩ ተወዳዳሪዎች ማሻነፍ ያለባቸው በአገር አቀፍ ደረጃ ከሁሉም የማህበረሰብ ክፍል ድምፅ አግኝተው ቢሆን ለአገር ሰላምና መረጋጋት ትልቅ አስተዋጽኦ አለው ብለው ያምናሉ። ከዚህ በተጨማሪ ለአንድ የብሔር፣የባህል፣ የቋንቋና የሃይማኖት ቡድን ለብቻው የሚሰጥ የአካባቢ አስተዳደርን አጥብቀው ይቃወማሉ። የዉህደት ስትራቲጂ አራማጆች ሪፑብሊካን፣ሊብራል እና ሶሻሊስት ተብለው በሦስት ይከፈላሉ።

ሪፑብሊካን የዉህደት እስትራቴጂ አራማጆች በሲቪክ ብሔረተኝነት ላይ የተመሰረተ መንግስት ዋነኛው ምርጫቸው ነው። ዜጎች ንብረት ማፍራት የሚችሉበት ፍትሃዊ ሥርዓት ካለና፣ በፖለቲካ ሥርዓቱ ውስጥ እኩል መብትና ነጻነት ካላቸው የአምባገነንነት አዝማሚያዎችን አለመቀበል ብቻ ሳይሆን በሙሉ ኃይላቸው ይዋጋሉ። ሪፑብሊካኖች ለሲቪክ በጎነት(Civic Virtue) ትልቅ ቦታ ይሰጣሉ። በነሱ እምነት ሲቪክ በጎነት የጋራ ሥርዓተ ትምህርትና የጋራ ባህል በመገንባት፣ ዜግነትን በመጋራትና ሪፑብሊኩን በወታደራዊነት በማገልገል ይገነባል። እነዚህ እሴቶች ማህበረሰብን አሰባስቦ በሲቪክ ብሔረተኝነት(Civic Nationalism) ላይ የተመሰረተ መንግስት ለመገንባት አይነተኛ መሳሪያዎች ናቸው። ሪፑብሊካን የውህደት እስትራቴጂ አራማጆች ታሪካዊ ኢፍትሃዊነት አለ ወይም ነበረ ብለው ያምናሉ፣ ነገር ግን በቡድን ላይ የተመሰረተ መፍትሄ ከጥቅሙ ጉዳቱ ስለሚበልጥ፣ የዜጎች አገር ፈጥረን ዜጎችን ሁሉ እኩል መመልከትና ዜጎች እራሳቸውን የሚያሳድጉበትን መንገድ ማመቻቸት ይሻላል ባዮች ናቸው። ፈረንሳይ የሪፑብሊካን ዉህደት እስትራቴጂ አይነተኛ ምሳሌ ናት።

የሪፑብሊካን የዉህደት እስትራቴጂ አራማጆች አንዱና ትልቁ መለያ ምናልባትም ከኛ አገር “ፌዴራሊዝም ወይም ሞት” ከሚሉ ኃይሎች ጋር የሚያጋጫቸው ጉዳይ ቢኖር፣ ፌዴራሊዝም አገርን የማፈራርስ አዝማሚያ የሚታይበት የመንግስት አወቃቀር ነው በሚል ፌዴራሊዝምን በፍጹም የማይቀበሉ መሆናቸው ነው። የመንግስት ቅርጽን በተመለከተ፣ ሪፑብሊካኖች የህግ አስፈጻሚው አካል መሪም ሆነ የህግ አውጪው አካላት በአብላጫ (50+1) ድምፅ እስከተመረጡ ድረስ በፕሬዚደንታዊና በፓርላማ ሥርዓቶች መካከል ብዙ ልዩነት አያዩም። በዚህ ጽሁፍ ውስጥ  ሲቪክ ናሺናሊዝም የሚል ቃል በተደጋጋሚ ተጠቅሷል። ሲቪክ ናሺናሊዝም ማለት መሰረቱን ብሔርን ወይም ማንነትን ሳይሆን ዜግነትን፣ነጻነትን፣እኩልነትን እና ከሌሎች ጋር ተከባብሮ፣ተግባብቶና ተቻችሎ መኖርን መሰረቱ ያደረገ ናሺናሊዝም ነው።

ሊብራሎችና ሪፑብሊካን የውህደት እስትራቴጂ አራማጆች በአንድ አገር ውስጥ ብሔርና ፖለቲካ ተጋብተው አንድ ላይ መኖር የለባቸውም የሚል ጠንካራ እምነት አላቸው፣ ደግሞም ሁለቱም መከፋፈልን ይጠላሉ፣ ጠንካራ የአገር አንድነትና ሁሉም ዜጎች የሚጋሩት አገራዊ ማንነት መኖር አለበት ብለውም ያምናሉ። የሁለቱ ካምፖች ትልቁ ልዩነት ሪፑብሊካን ፌዴራል የመንግስት መዋቅርን አይደግፉም። ሊብራሎች ግን የፌዴራሊዝም ደጋፊዎች ናቸው፣ ሆኖም ፌዴራሊዝም በማንነት ላይ ሲመሠረት የብሔር ፖለቲካ አቀንቃኝ ልህቃን የፈለጉትን ለማድረግ የፖለቲካ አቅም ስለሚሰጣቸው፣ የአገር አንድነትና የጋራ ማንነት እየላላ መጥቶ የመበታተን አደጋን ጭምር ይዝ ስለሚመጣ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን አይነትና መሰረቱ ብሔር የሆነውን ፌዴራሊዝም በፍጹም አይቀበሉም። በነሱ እምነት ፌዴራሊዝም በሁሉም መስክ የግለሰቦችን አቅም በማጎልበት የአገር አስተዳደር ዉጤታማና ቀልጣፋ እንዲሆን ማድረግ ነው ያለበት እንጂ አገርን ወደ መከፋፈል፣ ወደ አካባቢያዊ አምባገነንነትና ወደ መገነጣጠል መውሰድ የለበትም። ስለዚህ የሊብራሎች ትልቁ ትኩረት ከብሔር ተኮር ፌዴራሊዝም ይልቅ ብሔራዊ ፌዴራሊዝም፣ ከቡድን መብት ይልቅ የግለሰብ መብት ላይ ነው። እንዲህ ማለት ግን፣ የግለሰብን መብት ከቡድን መብት ያስቀድማሉ ማለት ነው እንጂ የቡድን መብትን አያከብሩም ማለት አይደለም። ባጠቃላይ የሊብራል የዉህደት እስትራቴጂ አቀንቃኞች መንግስት የዜጎችን የቆዳ ቀለም፣ዘር፣ቋንቋ፣ባህልና ሃይማኖት እያየ አንዱን የሚደግፍ ሌላውን የሚያገል ፖሊሲ ማውጣት የለበትም፣ ወይም መንግስት እነዚህን ጉዳዮች በተመለከተ ገለልተኛ መሆን አለበት ይላሉ። የሊብራል ዉህደት እስትራቴጂ አይነተኛ ምሳሌ አሜሪካ ናት።

ሶሻሊስቶች የውህደት እስትራቴጂ አራማጆች ከሪፑሊካንና ከሊብራል የውህደት እስትራቴጂ አራማጆች  የሚቀራረብም በጣም የተለየ ሃሳብም አላቸው። ሶሻሊስቶች የመንግስት መዋዕለነዋይን ከዚህ በፊት ተረስተዋል በሚባሉ አካባቢዎች ማድረስ የሚችልና ለበጎ አድራጎት ቅድሚያ የሚሰጥ መንግስት መኖር አለበት ብለው ያምናሉ (Welfare State)። በሶሻሊስቶች አስተሳሰብ በአንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ ዉስጥ ያሉ ማህበራዊ መደቦች የዚያ ማህበረሰብ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኤኮኖሚያዊ ህይወት መሰረቶች ናቸውና የፖለቲካ ሥርዓቱ ፖሊሲዎች ትኩረት መሆን የሚገባው በማህበረሰቡ ዉስጥ ፍትሃዊ ክፍፍል እንዲኖር ማድረግ ነው (Distributive Justice)። ሶሻሊስቶች የአንድ ማህበረሰብ መሰረቶች ናቸው ብለው የሚያምኑት በፖለቲካ ሥርዓቱ ውስጥ የሚገኙትን ማህበራዊ መደቦች በመሆኑ፣ ፍትሃዊ ክፍፍልን ተግባራዊ ለማድረግ ፖለቲካ ከዘር፣ ከሃይማኖትና ከቋንቋ መሰረቶች ተላቅቆ በዜግነት ላይ መመስረት አለብት ብለው ያምናሉ። ሶሻሊስቶች በማንንነት ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ የሰራተኛውን መደብ የፖለቲካ ባለቤትነት ዋጋ ያሳጣዋል ብለው ያምናሉ። ሶሻሊስት የውህደት እስትራቴጂ የተሞከረባቸው አገሮች ማርክሲዝምን የሚከተሉ አገሮችና አዉሮፓ ውስጥ የሚገኙ ሶሻል ዲሞክራቶች ናቸው።

ማስተናገድ/መስተንግዶ (Accommodation)  በዚህ ጽህፍ ውስጥ በተከፋፈሉ ማህበረሰቦች ዉስጥ ብዝሃነትን ማስተናገድ ይችላሉ ተብሎ ከቀረቡ ሁለት እስትራቴጂዎች ውስጥ አንደኛው እስካሁን የተመለከትነው የውህደት እስትራቴጂ ሲሆን ሁለተኛው ከዚህ ቀጥሎ የምንመለከተው ማስተናገድ/መስተንግዶ (Accommodation) እስትራቴጂ ነው።  የዚህ እስትራቴጂ አራማጆች ኢትዮጵያን በመሳሰሉ የብሔር፣ የቋንቋ፣ የባህልና የሃይማኖት ብዝሃነት ባለባቸው ማህበረሰቦች ዉስጥ፣ ብዝሃነት የዉህደት እስትራቴጂ አራማጆች እንደሚሉት የግለሰብ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን በመንግስት ደረጃም እውቅና ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው ባዮች ናቸው። የዉህደት እስትራቴጂ አራማጆች መንግስታዊ ተቋሞች ከማንነት በላይ መሆን አለባቸው ሲሉ፣ የማስተናገድ/መስተንግዶ እስትራቴጂ አራማጆች ግን እያንዳንዱ የማንነት ቡድን እራሱን ከአብዛኛው ጭቆና ለመከላከልና በአካባቢው እራሱን በራሱ ማስተዳደር እንዲችል እራሱን የሚገልጽበት ህዝባዊና ፖለቲካዊ ምህዳር (Public & Political Space) ሊኖረው ይገባል ብለው አጥብቀው ይሞግታሉ። ባጠቃላይ የማስተናገድ/መስተንግዶ እስትራቴጂ አራማጆች በአንድ አገር ዉስጥ ከአንድ በላይ የብሔር፣ የቋንቋ፣የባህልና የሃይማኖት ስብስብ አለ ብለው ካመኑ፣ እነዚህ ስብስቦች ማንነታቸውን ጠብቀው ከእነሱ ከተለየ ሌላ ስብስብ ጋር አንድ ላይ መኖር የሚችሉበት፣ ለብዝሃነት እውቅና የሚሰጥ፣ ብዝሃነትን የሚንከባከብ ወይም የሚያከብር የፖለቲካ ስርዓት መገንባት አለበት ይላሉ። ይህንን ለማድረግ የሚከተሉትን አራት አማራጭ መንገዶች ያቀርባሉ።

1 ማዕከልተኮር (Centripetalism)- የብሔር ፖለቲካ በተለይ አክራሪ ብሔረተኝነት ባለባቸው  ማህበረሰቦች ዉስጥ ዋና ዋናዎቹን የዲሞክራሲ ተቋማት እንዲደጋገፉ  አድርጎ ዲዛይን በማድረግ ሆድና ጀርባ የሆኑ ቡድኖችን ማቀራረብ ይቻላል የሚል ጽንሰ ሃሳብ ነው። የዚህ ጽንሰ ሃሳብ ዋና ትኩረት የተለያዩ ቡድኖች ተቀራርበው እንዲሰሩ በማድረግ የብሔር አክራሪነትን ወደ ማዕከል ፖለቲካ ማምጣት ነው። በብሔርና በሃይማኖት በተከፋፈሉ ማህበረሰቦች ዉስጥ በመንግስት (ህግ አስፈጻሚ) ውስጥ አለመካተት በፖለቲካ ሥርዓቱ ውስጥ ካለመካተት ወይም ካለመታቀፍ ተነጥሎ አይታይም። ኢትዮጵያን ጨምሮ በሌሎችም በተከፋፈሉ ማህበረሰቦች ዉስጥ በፖለቲካ ሥርዓቱ አለመታቀፍ ማለት ደግሞ ከአንድ አገር ኤኮኖሚያዊና ማህበራዊ ኑሮ ውጭ እንደመሆን ተደርጎ ስለሚቆጠር፣ ይህ ስሜት ባለባቸው አገሮች ውስጥ ሰላምና መረጋጋት አይኖርም። ማዕከል-ተኮር (Centripetlism) በእነዚህ ማህበረሰቦች ውስጥ ይህንን በፖለቲካ ሥርዓቱ ያለመታቀፍ ስሜት ማሻሻል የሚችሉ የፖለቲካ ተቋሞች ግንባታ ዲዛይን ሃሳቦችን የያዘ እስትራቴጂ ነው። ይህ እስትራቴጂ በተቃራኒ ጎራ የቆሙ የፖለቲካ ልህቃን እንዲፈላለጉና አብረው እንዲሰሩ በማድረግ አናሳው በአብዛኛው የውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ላይ የራሱን ተፅዕኖ ማድረግ እንዲችል የሚያደርጉ ተቋሞችን ያቀፈ እስትራቴጂ ነው።

የማዕከል-ተኮር ጽንሰ ሃሳብ ደጋፊዎች የፖለቲካ ባለድርሻዎችን አመለካከት የሚቀይርና ከመራራቅ ይልቅ ተቀራርበው አንድ ላይ እንዲሰሩ የሚያደርጉና ፖለቲካዊ መተባበርንና አብሮ መስራትን የሚሸልሙ የምርጫ ሥርዓቶችን እና የመንግስት ቅርፅን በተጓዳኝ ነድፎ ተግባራዊ በማድረግ የብሔር ፖለቲካ ጡዘት የሚፈጥረውን የፖለቲካ አለመረጋጋት ማርገብ ይቻላል የሚል ጽኑ እምነት አላቸው። ማዕከል ተኮሮች የብሔር ፖለቲከኞችን ከሚሸልሙ ተመጣጣኝ ዉክልና የምርጫ ሥርዓትን ከመሳሰሉ የምርጫ ሥርዓቶች በተለይም ከፓርቲ-ዝርዝር የምርጫ ሥርዓት መራቅ አስፈላጊ ነው ይላሉ። የማዕከል ተኮር እስትራቴጂ ቀንደኛ አቀንቃኝ የሆነው አሜሪካዊው ዶናልድ ሆሮዊትዝ፣ የብሔር ፖለቲካ በጦዘበት አገር ውስጥ ጫፍ ላይ ያሉ ኃይሎችን ወደ ማዕከል ፖለቲካ ለመሳብ አማራጭ ድምፅ የምርጫ ሥርዓትና ፕሬዚደንታዊ የመንግስት ቅርፅ አንድ ላይ ዲዛይን መደረግ አለባቸው የሚል ጽኑ እምነት አለው። ዶናልድ ሆሮዊትዝ የፓርላማ/ምክር ቤት አባላትን ለመምረጥ አማራጭ ድምፅ (Alternate Vote) የምርጫ ሥርዓትን፣ ፕሬዚደንቱን ለመምረጥ ደግሞ በአገር አቀፍ ደረጃ ከሚሰጠው ጠቅላላ ድምፅ ባሻገር በየክልሉ የሚሰጠውን ድምፅ ከግምት ውስጥ የሚያስገቡ የምርጫ ሥርዓቶችን ዲዛይን ማድረግ አስፈላጊ ነው ብሎ ያምናል። ለምሳሌ፣ ናይጄሪያ ዉስጥ አንድ ዕጩ ተወዳዳሪ ፕሬዚደንት ሆኖ ለመመረጥ በተለምዶ ህዝባዊ ድምፅ (Popular Vote) የሚባለውንና በአገር አቀፍ ደረጃ የሚሰጠውን ድምፅ ማሸነፍ ይችላል፣ግን ፕሬዘደንታዊ ምርጫውን ለማሸነፍ ከዚህ በተጨማሪ በጠቅላላ ከተሰጠው ድምፅ አንድ አራተኛውን ከሁለት ሦስተኛዎቹ የናይጄሪያ ግዛቶች ውስጥ ማግኘት አለበት። የዚህ አይነት የምርጫ ሥርዓት ጥቅሙ ዕጩ ተወዳዳሪዎች ወደ እያንዳንዱ የምርጫ ወረዳ ሄደው የምረጡኝ ዘመቻ እንዲያካሄዱ የሚያስገድድ መሆኑና ማሸነፍ የሚፈልጉ ተወዳዳሪዎች የኔ ነው ከሚሉት ብሔር ክልል ወጥተው የሌላ ብሔር አባላትን ምረጡኝ ብለው እንዲማጸኑ ማድረጉ ነው። እንዲህ አይነቱ አስራር ከተለያየ ብሔር የመጡ ዕጩ ተወዳዳሪዎች የምረጡኝ ዘመቻ ሲያካሄዱ ከጠባብ ብሔረተኝነት ተላቅቀው በአካባቢያዊና በአገራዊ አጃንዳዎች ላይ እንዲያተኩሩ ያስገድዳቸዋል። ማዕከል-ተኮሮች ፌዴራል የመንግስት መዋቅር አናሳ ቡድኖች የሚኖሩበትን አካባቢ እንዲያስተዳድሩ ዕድል ስለሚሰጣቸው፣የፖለቲካ ሥልጣንን ከማዕከል ቆርሶ ለአካባቢ በመስጠት አምባገነንነትን ስለሚዋጋና አካባቢያዊ ችግሮችን በአካባቢ ወስኖ ስለሚያስቀራቸው ፌዴራሊዝምን ይወዱታል።

ስምምነት/መግባባት (Consociationalism)  በብሔር፣ በቋንቋ፣  በባህልና በሃይማኖት በተከፋፈሉ ማህበረሰቦች ውስጥ በተለይ የሥልጣን ፉክክርና የርስ በርስ ግጭት በሚገኝባቸው  ማህበረሰቦች ውስጥ፣ የፖለቲካ ልህቃኑ ቁጭ ብለው ተደራድረውና የፖለቲካ ሥልጣን ተጋርተው አገርን ማረጋጋት ይቻላሉ የሚል የፖለቲካ ጽንሰ ሃሳብ ነው። የዚህ ጽንሰ ሃሳብ  አራማጆች ዋና ትኩረት የቡድን ውክልና እና ሥልጣን መጋራት ነው (Power sharing & Representation)

3 መድበለባህላዊነት (Multiculturalism)- መድበለ-ባህላዊነት የተለያየ ባህል፣ቋንቋና ሃይማኖት ያላቸው ስብስቦች ተቋማቂ ጥብቃ ያስፈልጋቸዋል የሚል ከላይ ከተመለከትነው ከስምምነት መግባባት እስትራቴጂ ጋር የሚመሳሰል ንዑስ ስትራቴጂ ነው። ይህ ንዑስ እስትራቴጂ የመንግስት ስራ የአንድን ማህበረሰብ ቋንቋና ባህል ብቻ መርጦ አገርን በዚህ ባህልና ቋንቋ ዙሪያ ከመገንባት ይልቅ ለሁሉም ባህሎችና ቋንቋዎች እውቅና መስጠትና ለቋንቋው ተናጋሪዎች በቋንቋቸው አገልግሎት መስጠት አስፈላጊ ነው የሚል እስትራቴጂ ነው። እንዲህ ማለት ደግሞ አናሳ ቡድኖች በትምህርት ቤቶች ውስጥ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ይማራሉ፣ባህላቸውና ሃይማኖታቸው ይከበራል፣ የማንነት መገለጫ ልብሳቸውን እና ምልክቶቻቸውን ያለምንም ፍራቻ በአደባባይ መልበስና ማሳየት ይችላሉ ማለት ነው።

4-አካባቢያዊ ብዙኃንነት (Territorial Pluralism)- ይህ እስትራቴጂ በውስጣቸው የብሔር ወይም የማንነት መነሳሳት ያለባቸውና በአንድ የጆግራፊ አካባቢ ተከማችተው የሚኖሩ የተለያዩ ቡድኖች ባሉበት አሃዳዊ ወይም ፌዴራል አገር ውስጥ፣ እያንዳንዱ ቡድን እራሱን በራሱ እያስተዳደረ ከሌሎች ማንነቶች ጋር ጎን ለጎን በሰላም እንዲኖሩ በማድረግ ብዝሃነትን ማቀፍ ይቻላል የሚል እስትራቴጂ ነው። ይህ እስትራቴጂ ተግባራዊ መሆን የሚችለው አሜሪካንን በመሰሉ ብሄራዊ ፌዴሬሺኖች ዉስጥ ሳይሆን ለማንነት ቡድኖች የራሳቸውን አካባቢ ሸንሽነው በሚሰጡ ቤልጂምን በመሳሰሉ ህብረብሄራዊ ፌዴሬሺኖች ውስጥ ነው።

የብሔር፣ የቋንቋና የባህል ብዝሃነት ባለባቸው አገሮች ዉስጥ እንዴት ፍትህ፣ነጻነት፣ ዲሞክራሲና እኩልነት ኖሮን በሰላም አንድ ላይ እንኖራለን በሚለው ሃሳብ ላይ አገራዊ ስምምነት ሳይኖር ሲቀር የዚያን አገር ፖለቲካ ጫፍ ወስደው የንትርክ፣ ያለመረጋጋት፣ ያለመግባባትና የግጭት ፖለቲካ የሚያደርጉትም፣ ስምምነት ሲኖር ደግሞ የሰላምና የመግባባት ፖለቲካ የሚያደርጉትም የፖለቲካ ልህቃን ናቸው። ህዝብ ከልህቃኑ ግፊትና ተፅዕኖ ዉጭ በራሱ ተነሳስቶ የፖለቲካ አለመረጋጋትና ግጭት የፈጠረበት አገር የለም። እስካሁን የተመለከትናቸው ሁለት እስትራቴጂዎች ዋና አላማም የፖለቲካ ልህቃኑ በተለይ በተከፋፈለ ማህበረሰብ ውስጥ የሚኖሩ የፖለቲካ ልህቃን ልዩነቶቻቸውን አስወግደው እንዴት አንድ ላይ እንደሚሰሩና እንዴት ሰላማዊና የተረጋጋ የፖለቲካ ማህበረሰብ መገንባት እንደሚችሉ የሚያሳዩ እስትራቴጂዎች ናቸው። እነዚህ ሁለት እስትራቴጂዎች የአንደኛው ደጋፊ ሌላውን እየተቸና የሌሎችም ምሁራን ትችት ተጨምሮበት ለረጂም ግዜ ውይይትና ክርክር እየተደረገባቸው ዛሬ ላይ የደረሱ እስትራቴጂዎች ናቸው። ዉህደትና ማስተናገድ/መስተንግዶ እስትራቴጂዎች ኢትዮጵያን በመሳሰሉ የተከፋፈሉ ማህበረሰቦች ዉስጥ ብዝሃነትን ለማስተናገድ ይበጃል የሚሉት የየራሳቸው የመፍትሄ ሃሳብ አላቸው፣ እነዚህ የመፍትሄ ሃሳቦች አንዳንዶቹ ይመሳሰላሉ አንዳንዶቹ በጣም ይለያያሉ። ይህ የሚያሳየን ብዝሃነትን ለማስተናገድ በስራ ላይ የምናውላቸው ስትራቴጄዎች ምን ያክል ጥንቃቄ እንደሚያስፈልጋቸውና፣ እንደየአገሩ ተጨማጭ ሁኔታ ብቻ ሳይሆን በአንድ አገርም ውስጥ ቢሆን በመሳሪያነት ስንጠቀምባቸው ከተጨባጭ ሁኔታዎች ጋር ሊገናዘቡ እንደሚገባ ነው፣ ወይም እስትራቴጂዎችን የምንጠቀመው ይጠቅማሉ ተብለው ስለቀረቡልን ብቻ ሳይሆን ከችግሮቻችን ጋር እያስተያየን በአገራችን የማንነት ፖለቲካ አውድ ውስጥ ዲዛይን ሊደረጉ ይገባል ማለት ነው።

የማንነት ፖለቲካ ችግሮች እንደየአገሩ ሁኔታ ብቻ ሳይሆን በአንድ አገር ዉስጥም ከአንዱ አካባቢ ወደሌላው ጠባያቸው ይለያያል። ለምሳሌ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ ውስጥ፣ ኦሮሚያ ውስጥ፣ ትግራይ ዉስጥና አማራ ክልል የሚታየው የብሔር አክራሪነት በጣም ይለያያል፣ ችግሩም ያን ያክል ይለያያል። ስለዚህ እንደየቦታው የተለያየ ቅርፅና ይዘት የሚኖረውን የማንነት ፖለቲካ ዉስብስብ ችግሮች “ዉህደት/Integration” እና “ማስተናገድ/መስተንግዶ/Accomodation” በሚል ሁለት የእስትራቴጂ አቅጣጫዎች ብቻ ከመመልከት ከሁለቱ እስትራቴጂዎች ባሻገርም ማሰብ ችግሩን ለመፍታት አመቺ ይሆናል ብለው የሚያስቡ ብዙ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን አሉ። ይህንን ትልቅ ችግር በሁለትዮች የእስትራቴጂ መነጽር ብቻ በመመለከት መፍትሄ ለማግኘት የሚደረገው ጥረት አንዳንዴ ችግሩን ሊያባብሰው ይችላል ብለው የሚያምኑ ምሁራንም አሉ፣ እነዚህ ምሁራን ብዝሃነትን ለማስተናገድ የሚደረገው ጥረት እነዚህን ሁለት እስትራቴጂዎች በጥልቅና በስፋት ከመመልከት ባሻገር ሌሎች አማራጮችንም መመልከትና እስትራቴጂዎቹን አንድ ላይም በተናጠልም መመዘን ይጠቅማል ባዮች ናቸው። የእነዚህ ምሁራን አስተያየት ምን ያክል አግባብ ያለው አስተያየት መሆኑን እስካሁን ያየናቸው ሁለቱ እስትራቴጂዎች ብዝሃነትን ለማስተናገድ ያስቀመጧቸውን አራት መንገዶች በመመርመር መገንዘብ ይቻላል።

ኢትዮጵያን ጨምሮ ምስራቅና መካከለኛው አውሮፓ፣አፍሪካ፣ኢሲያና ደቡብ አሜሪካ ውስጥ ዲሞክራሲያዊ ሽግግር በሚያደርጉ አገሮች ውስጥ ትልቁ ችግርና ፈተና የብሔር፣ የሃይማኖት፣ የቋንቋና የባህል ማንነቶችን ማስተናገድ የሚችሉ ዲሞክራሲያዊ ተቋሞች መገንባት ነው። የአዳዲስ ዲሞክራሲያዊ ተቋማት ዲዛይን እና ግንባታ በአንዳንድ አገሮች ውስጥ የአገረ-መንግስት ግንባታ ሂደት ዉጤት ነው፣በአንዳንድ አገሮች ውስጥ ከረጂም ግዜ ግጭትና ጦርነት በኋላ የሚሆን ነው፣ በአንዳንድ አገሮች ውስጥ ደግሞ የፖለቲካ ሥርዓቱ አግልሎናል የሚሉ ወገኖች የሥልጣን ክፍፍልና በፖለቲካ ሥርዓቱ የመታቀፍ ጥያቄ ሲያነሱ የሚሆን ነው። የዛሬዋ ኢትዮጵያ ዉስጥ ከአመታት በፊት ተጀምሮ ያልተጠናቀቀ የአገረ- መንግስት ግንባታ ሂደት አለ፣ ኢትዮጵያ ተረስተናል፣ተጨቁነናል ወይም ተበድለናል የሚሉ ቡድኖች ክስ የሚሰማባት አገር ናት፣ ኢትዮጵያ አሁንም በጦርነት ውስጥ የምትገኝ አገር ናት። እነዚህ መራራ እውነቶች የሚነግሩን ኢትዮጵያ ውስጥ ብዝሃነትን የሚያቅፉ፣ የፖለቲካ ልዩነቶችን ማስተናገድ የሚችሉ፣ሁሉንም ኢትዮጵያዊ በእኩልነት የሚመለከቱ ፍትሃዊና ዲሞክራሲያዊ ተቋማት ግንባታ ሂደት መጀመር እንዳለበት ነው።

አገራችን ኢትዮጵያ የማንነት ብዝሃነት የሚገኝባት አገር ብቻ ሳትሆን የማንነት ፖለቲካ ከጡዘት አልፎ ህዝብን እርስ በርስ የሚያጋድልባት አገር ናት። እንደ ኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር በ1980ዎቹ አጋማሽ አብሮ አያኖረንምና ይቅርብን እየተባለ የተገነባው የብሔር ፖለቲካ ዛሬ የኢትዮጵያን ህዝብ እርስ በርስ ከማጋደል አልፎ ጭራሽ የአገራችንን ህልውና እየተፈታተነ ነው። ታዲያ እኛ ኢትዮጵያዊያን ምን ብናደርግና ምን አይነት የፖለቲካ ሥርዓት ብንገነባ ነው ይህንን አደጋ ማቆም የምንችለው? ኢትዮጵያ ውስጥ መካሄድ አለበት የምንለው አገራዊ ምክክር ለዚህ ጥያቄ የማያወላዳ መልስ መስጠት አለበት። ብዝሃነትን ያስተናግዳሉ ተብለው በዚህ ጽሁፍ ውስጥ ከተመለከትናቸው ሁለት ስትራቴጄዎች ውስጥ የትኛው ነው የሚያዋጣን? በምን መመዘኛ ነው ከሁለቱ ስትራቴጄዎች አንዱን የምንመርጠው?

ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ብሔር ብሄረሰቦች መኖራቸው ብቻ ሳይሆን ባለፉት ሰላሳ አመታት ኢትዮጵያዊያን እራሳቸውን ከብሔር ማንነት ውጭ እንዳይመለከቱ ተደርገዋል፣ ደግሞም አገራችን ዉስጥ የብሔር ፖለቲካ እየከረረ መጥቶ ዛሬ የአብሮ መኖርና የአገር አንድነት ችግር እየሆነ ነው። ስለዚህ አገራችን ዉስጥ ይህንን ችግር እንዲያቃልሉና በሰላም አብረን እንድንኖር የሚያደርጉንን ተቋሞች ዲዛይን ስናደርግ የውህደትና ማስተናገድ/መስተንግዶ ስትራትጂ አቀንቃኞች ከሚያደርጉት “የኔ ስትራቴጂ የተሻለ ነው” ከሚለው ክርክር ወጥተንና አዕምሯችንን ሰፋ አድርገን ብዙ አማራጮችን መመልከት አለብን። ለምሳሌ፣ የማስተናገድ/መስተንግዶ ስትራቴጂ አባቶች ብዝሃነት ተቋማዊ እውቅና ማግኘት አለበት የሚል ጠንካራ አቋም አላቸው። የዉህደት ስትራቴጂ አባቶች ደግሞ የተለያዩ የብሔር ማንነቶች ተቋማዊ እውቅና ሲያገኙ፣ አንዱ ብሔር እራሱን ከሌላው እየለየ አገርን በራሱ ብሔር መነጽር ብቻ መመልከት ይጀምርና ጠንካራ አገራዊ አንድነት ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት አደጋ ላይ ይወድቃል ይላሉ። የማስተናገድ መስተንግዶ ስትራቴጂ አባቶችም የሚሉት እንደዚሁ ነው፣ የብሔር ማንነትን መኖሩን ተረድተን ለመኖሩ ተቋማዊ እውቅና ካልሰጠን አገር በሰላም መኖር አይችልም ባዮች ናቸው። ይህ የሚነግረን እኛ ኢትዮጵያዊያን ተራችን ደርሶ በህገ መንግስታዊ ዲዛይን ሂደት ዉስጥ ስናልፍ ከማስተናገድ/መስተንግዶ እና ከዉህደት እስትራቴጂዎች የግድ አንዱን መምረጥ እንደሌለብን ነው። የዲሞክራሲ ተቋሞቻችንን ዲዛይን ስናደርግ ከሁለቱ እስትራቴጂዎች የግድ አንዱን መምረጥ የለብንም። ሁለቱ እስትራቴጂዎች እያንዳንዳቸው የተለያዩ ንዕሳን ክፍሎች ስላላቸው ከእነዚህን ንዑሳን ክፍሎች ውስጥ የሚጠቅመንን መምረጥ እንችላለን። ከዚህ በተጨማሪ ከሁለቱ እስትራቲጂዎች ውጭም ሌሎች ብዙ አማራጮች አሉና እነሱን መመልከትና፣ ያሉንን አማራጮች ሁሉ በቅደም ተከተል አስቀምጠን ለችግሮቻችን መፍትሄ ይሆናሉ የምንላቸውንና ከኛ አገር የፖለቲካ ባህል፣ ማህበራዊ አደረጃጀት፣ የእድገት ደረጃና ማህበራዊ ባህል ጋር አብረው የሚሄዱትን መርጠን እንደ ጡብ ድንጋይ እየጠረብን አብሮ የሚኖረንን ዲሞክራሲ ዲዛይን ማድረግ አለብን።

በህገ መንግስታዊ ምህንድስና ሂደት ውስጥ አገራዊ ስምምነት ተደርሶባቸው ዲዛይን መደረግ ያለባቸው ብዙ ተቋሞች አሉ፣ሆኖም የመንግስት ቅርፅ፣ የመንግስት መዋቅር፣  የምርጫ ሥርዓት፣ የህግ አውጪው አካል፣ የህግ አስፈጻሚው አካል፣የፍትህ ተቋሞችና የአካባቢ አስተዳደር አካላት ዋና ዋናዎቹ ናቸው። ይህ ጽሁፍ የመጀመሪያዎቹን ሦስት ተቋሞች በአጭሩ ይዳስሳል። ኢትዮጵያን ውስጥ የብሔር ልህቃን ትልቁ ጥያቄ ብሔራቸው ውክልና ማግኘቱና ማንነታቸው በፖለቲካ ሥርዓቱ እውቅና ማግኘቱ ነው። የብሔር ልህቃን ብሔራቸው በህግ አውጪውና በህግ አስፈጻሚው አካል ውስጥ ውክልና እስካገኘና በፖለቲካ ሥርዓቱ ዉስጥ ከሌሎች ብሔሮች ጋር በእኩልነት እስከታየ ድረስ ብሔራቸውን ለአመጽና  ለግጭት የመቀስቀሻ መንገድ አያገኙም። ኢትዮጵያ ውስጥ ይደረጋል ተብሎ የሚጠበቀው አገራዊ ምክክር አስቦበት፣ ተወያይቶበትና ብዙ አማራጮችን አይቶ በጥንቃቄ ዲዛይን ማድረግ ከሚገባቸው ተቋሞች ውስጥ የመንግስት ቅርፅና የምርጫ ሥርዓት ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

የመንግሥት ቅርፅና የምርጫ ሥርዓትና እጅግ በጣም የተወሳሰቡና እርስ በርስ የተቆላለፉ የዲሞክራሲ ተቋሞች ናቸው፣ ከሁለቱ አንዱን ስንመርጥ ምርጫው በሌላኛው ምርጫዎቻችን  ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያደርጋል። ይህ ማለት ደሞ አንደኛው ምርጫችን ትክክል ሆኖ ሁለተኛው ከተበላሸ ገና ከጅምሩ ሁለቱም የተበላሹ ሊሆኑ ይችላሉ ማለት ነው። ስለዚህ የመንግስት ቅርጽ ዲዛይን ስናደርግ፣ አብሮት የሚሄደውን የምርጫ ሥርዓትም አንድ ላይ ዲዛይን ማድረግ አለብን ማለት ነው።

አገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መሠረት ሲጣል ያሉን  የዲይን አማራጮች ጀዋር መሐመድ እንደነገረን ሁለት ብቻ አይደሉም፣ ብዙ የዲዛይን አማራጮች አሉ። ይህንን ለማወቅ የዉህደት (Integration) እና የማስተናገድ/መስተንግዶ (Accomaodation) ስትራቴጄዎች በውስጣቸው የቃፉትን የተለያዩ ንዑሳን አማራጮች መመልከት ይበቃል። ለምሳሌ፣የማስተናገድ/መስተንግዶ(Accoodation) እስትራቴጂ-ማዕከል-ተኮር (Centripetalism) የሚልና -ስምምነት/መግባባት (Consociationalism)  የሚሉ ሁለት ትልልቅ አማራጮች አሉት። እነዚህ ሁለት አማራጮች ደሞ እያንዳንዳቸው በውስጣቸው ብዙ አማራጮች አሏቸው። ለምሳሌ፣ስምምነት/መግባባት- ግዙፍ ጥምረት (Grand Caoalitation)፣ ተመጣጣኝነት (Proportionality)፣ ድምጽን በድምጽ የመሻር ሥልጣን (Mutual Veto)፣ እና በአካባቢ  እራስን በራስ ማስተዳደር (Segmental Autonomy) የመሳሰሉ የተለያዩ ንዕሳን ክፍሎች አሉት። እንደገና ከእነዚህ አራት አማራጮች ውስጥ ግዙፍ ጥምረት የሚለውን ብንወስድ፣ ይህንን አማራጭ የተለያዩ ሰዎች በተለያየ መልኩ ያስቀምጡታል።

የስምምነት/መግባባት ስትራቴጂ አባት የሆነው አረንድ ሊፓርት በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ የሚገኙ ቡድኖች ሁሉም በግዙፍ ጥምረት መንግስት ውስጥ ውክልና ሊያገኙ ይገባል የሚል ዕምነት አለው።ነገር ግን ከሊፓርት በኋላ የመጡ የራሱ የሊፓርድ ተከታዮች በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ የሚገኙ ቡድኖች የግድ ሁሉም በግዙፍ ጥምረት መንግስት ዉስጥ ውክልና ማግኘት የለባቸውም ይላሉ። ዛሬ ስምምነት/መግባባት ዲሞክራሲን በተመለከተ ሦስት የተለያዩ አስተሳሰቦች አሉ-

  • የተሟላ ስምምነት/መግባባት (Compelte Consociations)-የዚህ ሃሳብ ዋነኛው ጭብጥ፣በግዙፍ ጥምረት መንግስት ውስጥ የሁሉም ቡድኖች ተወካዮች መኖር አለባቸው የሚለው ሃሳብ ነው
  • ተጓዳኝ ስምምነት/መግባባት (Concurrent Consociations)- ይህ አስተሳሰብ በግዙፍ ጥምረት መንግስት ውስጥ ሁሉም ሳይሆኑ አብዛኛ (Majority) የዋና ዋና ቡድኖች ተወካዮች ቦታ ማግኘት አለባቸው የሚል ከላይ በቁጥር አንድ ላይ ከተጠቀሰው አስተሳሰብ የተለየ አስተሳሰብ ነው።
  • ብዙሃነት መስማማት/መግባባት (Plurality Consociations)-ይህ አስተሳሰብ የዋና ዋናዎቹ ቡድኖች ተወካዮች የግድ አብዛኛዎቹ ሳይሆኑ ቢያንስ ብዙ ቁጥር ያላቸው ተወካዮች በግዙፍ ጥምረት መንግስት ውስጥ ቦታ ሊኖራቸው ይገባል የሚል አስተሳሰብ ነው።

ይህ የሚያሳየን እኛ ኢትዮጵያዊያን በህገመንግስታዊ ዲዛይን ሂደት ውስጥ ስናልፍ፣ካሉን ብዙ የዲዛይን አማራጮች ውስጥ አንዱን መምረጥ ሳይሆን ያለብን፣የተለያዩ የዲዛይን አማራጮችን እንደ ጡብ ድንጋይ እየጠረብን መቀላቀልና ለኛ አገር ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኤኮኖሚያዊ ሁኔታ የሚመች አማራጭ ዲዛይን ማድረግ እንዳለብን ነው። ይህ ማለት ግን ዲዛይን የምናደርገው አማራጭ እንከን የለሽ ነው ማለት አይደለም። በህገ መንግስታዊ ምህንድስና ሂደት ውስጥ እንከን የለሽ ዲዛይን ብሎ ነገር የለም፣ ዋናው ቁምነገር ከነእንከኑ መቀበል ያለብን የትኛውን ዲዛይን ነው የሚለው ሃሳብ ነው።

 

ህገ መንግስታዊ ምህንድስና (Constitutional Engineering) ማለት ምን ማለት ነው?

ህገ መንግስታዊ ምህንድስና በአገረ-መንግስት (Nation-Building) ወይም በመንግስት ግንባታ(State-Building) ሂደት ዉስጥ በሚያልፉ አገሮችና፣ ከረጂም ግዜ ግጭትና የርስ በርስ ጦርነት ተላቀው ዲሞክራሲያዊ ሽግግር በሚያደርጉ በተለይ በተከፋፈሉ ማህበረሰቦች ውስጥ የተለያዩ ተቋማትን እንዲደጋገፉ አድርጎ ዲዛይን በማድረግ በብሔር፣ በቋንቋ፣ በባህልና በሃይማኖት ተለያይተው የጎሪጥ የሚተያዩና አንዳንዴም የሚጋጩ ማህበረሰቦችን በማቀራረብ የጋራ አገር መገንባት የሚያስችሉ ተቋማዊ መሳሪያዎች የሚቀርጹበት ሂደት ነው። ይህ ሂደት በውስጡ የተለያዩ ንድፈ ሃሳቦች፣ እስትራቴጂዎች፣ ዘዴዎችንና የተለያዩ የመፍትሄ ሃሳቦችን ያቀፉ ጥቅሎች አሉት።

ኢትዮጵያ የፖርላማ ሥርዓትን የምትከተል አገር ናት። የኢትዮጵያ ፓርላማ የሌሎች አገሮች ፓርላማ ያሉት ተቋማዊ መሳሪያ የሚጎድለውና፣ የህግ አውጪውና የህግ ተርጓሚዉ አካላት በደባልነት የሚኖሩበት ተቋም ነው። ስለዚህ የፓርላማ ሥርዓታችንን በሌላ የመንግስት ቅርፅ እንተካው ወይስ እሱን እራሱን አሻሽለን እንደገና እናዋቅረው? ብዙ  ፓርቲዎች የፓርላማ መቀመጫ ማሸነፍ የሚችሉበትና የጥምር መንግስት መመስረት የሚችሉበት ሥርዓት ነው የሚያስፈለገን ወይስ አንድ ፓርቲ ብቻዉን መንግስት መመስረት የሚችልበት ሥርዓት ነው የሚያስፈልገን? በህግ አውጪውና በህግ አስፈጻሚው አካላት መካከል የሚኖረው ግኑኝነት ምን መምሰል አለበት? ህገ መንግስታዊ ምህንድስና ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ አለው።

የመንግስት ቅርጽና የምርጫ ሥርዓት በተከፋፈሉና ዲሞክራሲያዊ ሽግግር በሚያደርጉ አገሮች ውስጥ እንዲደጋገፉና የፖለቲካ ሥልጣንን እንዲያጋሩ ተደርገው ከተዋቀሩ  ብዝሃ ትን  ማስተናገድ ይቻላል ብለው የሚያምኑ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን አሉ። በእንዲህ አይነት መንገድ የሚገነቡ ተቋማዊ መደጋገፎችን ነው የህገ መንግስት ምህንድስና ጠበብቶች  “ሥልጣን መጋራት” ብለው የሚጠሩት። ለመሆኑ ሥልጣን መጋራት (Power Sharing) ማለት ምን ማለት ነው?

 

ሥልጣን-መጋራት-

በአንድ አገር ውስጥ የህግ አስፈጻሚውን፣ የህግ አውጪውን፣ የህግ ተርጓሚውን፣ የቢሮክራሲውንና  ወታደራዊ ተቋሞችን የተወሰኑ የማህበረሰብ ክፍሎች በተናጠልም ሆነ  ቡድን  በብቸኝነት እንዳይቆጣጠሩ የሚያደርግ

አናሳውም አብዛኛውም በአገሩ የወደፊት ጉዳይ ላይ በተወካዮቹ  አማካይነት የመወሰን ችሎታ እንዲኖረው የሚያደርግ

የአንድ አገር የፖለቲካ ሥርዓት ሁሉንም እኩል አቃፊ እንዲሆን ወይም ከፖለቲካ ሥርዓቱ በመገለሉ የሚያኮርፍ የማህበረሰብ ክፍል እንዳይኖር የሚያደርግ ህገ መንግስታዊ መሳሪያ ነው። ሥልጣን-መጋራት ብዙ ደጋፊዎች ያሉትን ያክል ተቃዋሚዎችም አሉት። ደጋፊዎቹ “ሥልጣን-መጋራት” የሚለውን ቃል “ግዙፍ ጥምር መንግስት” (Grand Coalition) ፣ “አቃፊ የፖለቲካ ሥርዓት”፣ የመግባባት ወሳኔ (Consensus) እና የመንግስት የሃላፊነት ቦታዎችን ተመጣጣኝ በሆነ መልኩ መከፋፈል ከሚሉ ጽንሰ ሃሳቦች ጋር እያቆራኙ ያሞግሱታል። ተቃዋሚዎቹ ደግሞ ማንነትን መሠረት ባደረገ መልኩ በሥልጣን-መጋራት ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ አደረጃጀትን ከመሪ አልባነት፣ ከፖለቲካ ቀውስ፣ ካለመረጋጋት፣ ከውሳኔ አልባነት፣ከጎታታነት፣ ከጭቅጭቅ፣ ከግትርነትና ከችኮነት ጋር እያያዙ ይኮንኑታል። በእርግጥምሥልጣን-መጋራት (Power-Sharing) ከአንድ አገር ችግሮች፣ የፖለቲካ ባህልና ከፖለቲካ ተዋንያኑ ባህሪይ ጋር እንዲዛመድ ተደርጎ በጥንቃቄ ካልተቀረጸ የፖለቲካ ሽባነትን ሊያመጣ ይችላል፣ ወይም ማስወገድ የሚገባውን ችግር ሊያባብሰው ይችላል።ሥልጣን መጋራት የተለያዩ ሞዴሎች አሉት።

ከዚህ ቀጥሎ የኢትዮጵያን የወደፊት የሚወስኑ አካላት መመልከት አለባቸው ብዬ የማምነውን አራት የዲዛይን አማራጮች ይቀርባሉ፣አራቱን አማራጮች ወይም ሞዴሎች  ከመመልከታችን  በፊት የሞዴሎቹ ወይም ባጠቃላይ የሥልጣን መጋራት መሠረት የሆኑትን ሁለት ጽንሰ ሃሳቦች እንደገና ባጭሩ መመልከቱ ጠቃሚ ነው። አራቱ የዲዛይን አማራጮቹ የሚቀርቡበት ቅደም ተከተል ትርጉም የለውም፣ወይም መጀመሪያ ላይ የቀረበው አማራጭ ሁለተኛ፣ሦስተኛ ወይም አራተኛ መሆን ይችል ነበር።

1-ስምምነት/መግባባት Consociationalism በብሔር፣  በቋንቋ፣ በባህልና በሃይማኖት በተከፋፈሉ ማህበረሰቦች ውስጥ በተለይ የሥልጣን ፉክክርና የርስ በርስ ግጭት በሚገኝባቸው ማህበረሰቦች ውስጥ፣ የፖለቲካ ልህቃኑ ቁጭ ብለው ተደራድረውና የፖለቲካ ሥልጣን ተጋርተው አገርን ማረጋጋት ይቻላሉ የሚል የፖለቲካ ጽንሰ ሃሳብ ነው። የዚህ ጽንሰ ሃሳብ አራማጆች ዋና ትኩረት በህግ አውጪው አካል ውስጥ የቡድን ውክልና እንዲኖር በህግ አስፈጻሜው አካል ውስጥ ደግሞ የሥልጣን መጋራት እንዲኖር ማድረግ ነው.። ስምምነት/መግባባት Consociationalism በሚከተሉት አራት እሴቶች ላይ የተመሰረተ ነው።

1- ግዙፍ ጥምረት/Grand Coalation- በፖለቲካ  ሥርዓቱ  ውስጥ የሚገኙትን ዋና ዋና የፖለቲካ ኃዮሎች  ያጠቃለለ  ጥምረት

2- ተመጣጣኝ ውክልና/Proportional Representation- የፖለቲካ ሹመቶችን እና ፋይናንስን በተመጣጣኝ መንገድ መከፋፈልን  እና ምርጫ  ለማካሄድ ተመጣጣኝ የምርጫ  ሥርዓት  መጠቀም

3- አካባቢያዊ አስተዳደር (Territorial and non-territorial autonomy)

4- ድምፅን በድምፅ የመሻር ሥልጣን (አናሳ ኃይሎች በብዙኃኑ እንዳይጨፈለቁ)

2- ማዕከልተኮር (Centripetalism)   የብሔር ፖለቲካ በተለይ አክራሪ ብሔረተኝነት ባለባቸው  ማህበረሰቦች ውስጥ የሚደጋገፉ ተቋማትን ገንብቶ በመጠቀም የተቃቃሩና  ሆድና ጀርባ የሆኑ ቡድኖችን ማቀራረብ ይቻላል የሚል ጽንሰ ሃሳብ ነው። የዚህ ጽንሰ ሃሳብ ዋና ትኩረት የተለያዩ  ቡድኖችን  ተቀራርበው እንዲሰሩ በማድረግ የብሔር  አክራሪነትን  እና የብሔር ፖለቲካን ወደ ማዕከል ፖለቲካ ማምጣት ነው፣   ወይም በተቃራኒ ጎራ የቆሙ የፖለቲካ ልህቃን  እንዲፈላለጉና አብረው እንዲሰሩ በማድረግ አናሳው በአብዛኛው  የውሳኔ አሰጣጥ ሂደት  ላይ የራሱን ተፅዕኖ ማድረግ እንዲችል የሚያደርጉ ተቋሞችን መገንባት ነው፣ ከእነዚህ ተቋሞች ውስጥ አንዱ የምርጫ ሥርዓት ነው፣ ሌላው የመንግስት ቅርፅ ነው።

ሞዴል አንድሊብራል ሥልጣን መጋራት (Liberal Power Sharing)— ሊብራል የሥልጣን መጋራት  ሲባል በተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች  መካከል የሥልጣን ክፍፍል የሚደረገው ወይም የፖለቲካ ኃይሎች ሥልጣን የሚጋሩት አስቀድሞ  በተቀመረ ኮታ ሳይሆን ከህዝብ በምርጫ ባገኙት ድምፅ ወይም ባሸነፉት የምክር ቤት መቀመጫ መጠን ነው ማለት ነው።  ይህ ሞዴል በአንድ በኩል በህግ አስፈጻሚ ደረጃ አቃፊነትን ይዞ ስለሚመጣ፣ በሌላ በኩል ደግሞ አቃፊነቱ የብሔር  ኮታን የማይከተል በመሆኑ፣ ሞዴሉ ቀደም  ሲል የተመለከትናቸውን ሁለት ጽንሰ ሃሳቦች (ስምምነት/መግባባት) እና  ማዕከል ተኮርን ደባልቆ የያዘ ሞዴል ነው። የፖለቲካ ፓርቲዎች ሥልጣን የሚጋሩት  በምርጫ አሸንፈው  ባገኙት  የምክር ቤት መቀመጫ ቁጥር ልክ ነው፣ ወይም ፓርቲዎች በህግ አስፈጻሚው አካል ውስጥ የ ሚያገኙት የካቢኔ ቦታ ቁጥር በህግ አውጪው አካል ውስጥ ከሚያገኙት መቀመጫ ቁጥር ጋር የተመጣጠነ ነው። በዚህ ሞዴል መሠረት ከፍተኛ የፖርላማ መቀመጫ ያሸነፈ ፓርቲ የካቢኔ ቦታዎችን እንዲመርጥ የመጀመሪያው ዕድል ይሰጠዋል። ፓርቲው ካሸነፈው መቀመጫ ቁጥር ጋር ተመጣጣኝ የሆነ የካቢኔ ቦታ ከመረጠ በኋላ የሚቀጥለው  ዕድል  በሁለተኛ ደረጃ ከፍተኛ የፓርላማ መቀመጫ ላሸነፈ ፓርቲ ይሰጣል። ይህ አሰራር ሁሉም የካቢኔ ቦታዎች እስኪያዙ ድረስ ይቀጥላል። እያንዳንዱ ፓርቲ የሚያገኘው የካቢኔ ቦታና ቁጥር ከሱ የሚቀጥለው ፓርቲ ከሚያገኘው የካቢኔ ቦታ በአይነትም በቁጥርም የተሻለ ነው።  በዚህ ሞዴል ውስጥ ያሉት የዲሞክራሲ ተቋሞች ፌዴራል የመንግስት አወቃቀር (ህብረብሔራዊ ፌዴራሊዝም)፣  ፓርላማዊ የመንግስት ቅርፅና አማራጭ ድምፅ የምርጫ  ሥርዓት ናቸው። አማራጭ  ድምፅ  የምርጫ ሥርዓት እያንዳንዱ ድምፅ ሰጪ በምርጫው ካርድ ላይ የቀረቡለትን ተወዳዳሪዎች  በቅደም ተከተል እያስቀመጠ ፍላጎቱን (Prefrence) የሚገልፅበት   የምርጫ ሥርዓት ነው። ይህ የምርጫ ሥርዓት ባለባቸው አገሮች ውስጥ  ምርጫውን የሚያሸንፈው  ተወዳዳሪ በጠቅላላ ከተሰጠው ድምፅ ከግማሽ በላዩን ያገኘው ተወዳዳሪ ነው።

445555tg

                                  Territorial and Non-territorial Autonomy

የሊብራል ሥልጣን መጋራት ሞዴል ጠንካራና ደካማ ጎኖች አሉት። የብሔርና አገራዊ ፓርቲዎችን ያቅፋል፣ ብሔረተኞችን እና የማዕከል ፖለቲካ አራማጆችን ሥልጣን ያጋራል፣ የፓለቲካ ኃይሎችን ያቀራርባል (Moderation)፣ ሥልጣን መጋራትንና እራስን በራስ ማስተዳደርን አንድ ላይ ይዞ ስለሚመጣ ብሔረተኝነትን ያለዝባል። እነዚህ ጠንካራ ጎኖቹ ናቸው። ሞዴሉ በሥልጣን መጋራት ላይ ስለሚያተኩር አማራጭ ድምፅ የምርጫ ሥርዓት መፍጠር የሚገባውን የፖለቲካ መቀራረብ ይቀንሳል፣ይህ የሚሆነው ፓርቲዎች የካቢኔ ቦታ እንደሚሰጣቸው እርግጠኛ ከሆኑ ከተቃራኒያቸው ጋር መቀራረብ ስለማይፈልጉ ነው። በሌላ በኩል ደሞ ብዙ ድምፅ ማግኘት የማይችሉ ፓርቲዎችን የማግለል ባህሪይ ስላለው እነዚህ ፓርቲዎች ከፖለቲካ ሥርዓቱ ይገለላሉ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በዜግነት ፖለቲካና በብሔር ፖለቲከኞች መካከል ያለውን ርቀት በሚፈለገው መጠን አያጠብም።

ሞዴል ሁለት ኮርፖሬት የሥልጣን ክፍፍል (Corporate Power Sharing) – ኮርፖሬት የሥልጣን መጋራት ሲባል በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የሥልጣን ክፍፍል የሚደረገው ወይም ፖርቲዎቹ ሥልጣን የሚጋሩት ለእያንዳንዱ ብሔር አስቀድሞ በተቀመረ ኮታ መሠረት ነው ማለት ነው። ይህ ሞዴል ሥልጣን ክፍፍል ላይ የብሔር ኮታን እና ሊብራል የሥልጣን ክፍፍልን አንድ ላይ የያዘ ሞዴል ነው። ፓርቲዎች (ብሔር/ህብረ-ብሔር) የካቢኔ ቦታ የሚከፋፈሉት ፓርላማ ውስጥ ባላቸው የመቀመጫ ብዛት ልክ ነው። የፓርላማ አባላት የሚመረጡት በተመጣጣኝ የምርጫ ሥርዓት ነው። ፓርቲዎች ፓርላማ ውስጥ ባላቸው የመቀመጫ ብዛት ልክ የካቢኔ ቦታ ይሰጣቸው እንጂ፣ እያንዳንዱ ፓርቲ በካቢኔ ቦታ ላይ የሚያስቀምጣቸው ሰዎች ለብሔር በተሰጠ ኮታ ልክ ነው። ለምሳሌ አንድ ፓርቲ አምስት የካቢኔ ቦታ ቢኖረውና ከምስቱ ሦስቱን በኮታው መሠረት ለብሔር መስጠት ካለበት፣ ፓርቲው ሶስቱን የካቢኔ ቦታዎች የግድ  በተሰጠው ኮታ መሠረት ለሦስት የተለያዩ ብሔሮች መስጠት አለበት። ፓርቲዎች በተሰጣቸው የብሔር ኮታ መሠረት ለብሔር ተወካዮች የካቢኔ ቦታ ካልሰጡ  የካቢኔ ቦታዎቹን ያጣሉ።

ይህ ሞዴል በአንድ በኩል ለፓርቲዎች ባሸነፉት መቀመጫ ልክ የካቢኔ ቦታ ይሰጣል፣ በሌላ በኩል ደግሞ ፓርቲዎች የተሰጣቸውን የብሔር ኮታ ማሟላት አለባቸው። ይህ ማለት ደግሞ የፌዴራል መንግስቱ የሥልጣን ክፍፍል ለብሔረተኞች ያደላ ነው ማለት ነው። ይህንን ለማካካስ የፌዴራል ክልሎች ብሔረተኝነትን ማለዘብ በሚችሉበት መንገድ ይሸነሸናሉ። ለምሳሌ አማራና ኦሮሚያን እያንዳንዳቸውን አራት ወይም አምስት የተለያዩ ክልሎች ማድረግ ማለት ነው። እነዚህ በአዲስ መልክ የተዋቀሩ ክልሎች የየራሳቸውን የስራ ቋንቋ፣ አርማ፣ ህግ መንግስት ወዘተ ይመርጣሉ። በእነዚህ ክልሎች ውስጥ የተለያዩ የቋንቋና የባህል ስብስቦች ቋንቋቸውን፣ ባህላቸውንና ሃይማኖታቸውን በተመለከተ እራሳቸውን በራሳቸው ያስተዳድራሉ (Non-territorial Autonomy)።

ይህ ሞዴል በዛሬው የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ሁለቱን የኢትዮጵያ ተቀናቃኝ ኃይሎች (ብሔረተኞች/ዜግነት) የሚያስደስትም የሚያስቆጣም አስራር አለው። ዛሬ ከኢትዮጵያ ውስጥ ካለው የኃይል አሰላለፍ አኳያ ሲታይ ሞዴሉ በፌዴራል መንግስት ደረጃ ያሉትን የሥልጣን ቦታዎች በብሔር ኮታ ስለሚያከፋፍል የብሔር ኃይሎችን ያስደስታል፣ በሌላ በኩል ደግሞ በክልል ደረጃ ብሔረተኝነትን ለማለዘብ ክልሎች ብዙ ብሔሮችን አቅፈው በአዲስ መልክ እንደገና እንዲዋቀሩ በማድረግ አንድ ክልል የአንድ ብሔር ነው የሚል አስተሳሰብ እንዲጠፋ ያደርጋል። ይህ ደግሞ የዜግነት ፖለቲካ አቀንቃኞችን ያስደስታል። ይህ የሚያሳየን ሁለቱን ኃይሎች በማይፈልጓቸው የሞዴሉ ሃሳቦች ላይ ቁጭ ብለው መደራደር እንዳለባቸው ነው።

በዚህ ሞዴል ውስጥ ያሉት የዲሞክራሲ ተቋሞች ፌዴራል የመንግስት አወቃቀር (ህብረ-ብሔራዊ ፌዴራሊዝም)፣ ፓርላማዊ የመንግስት ቅርፅና ተመጣጣኝ የምርጫ ሥርዓት ናቸው። ተመጣጣኝ የምርጫ ሥርዓት ማለት ከአንድ የምርጫ ወረዳ ከአንድ በላይ ተወካዮች የሚመረጡበትና፣ በህግ የተቀመጠውን ዝቅተኛውን የድምፅ መቶኛ ያገኙ ፓርቲዎች ከህዝብ ካገኙት ድምፅ ጋር ተመጣጣኝ የሆነ የፓርላማ መቀመጫ የሚያገኙበት የምርጫ ሥርዓት ነው። በዚህ ሞዴል ዉስጥ የሚገኘው ህብረ-ብሔራዊ ፌዴራሊዝም ጀዋር ከሚለው ህብረ-ብሔራዊ ፌዴራሊዝም ይለያል። ጀዋር ህብረ-ብሔራዊ ፌዴራሊዝም ሲል እያንዳንዱ ብሔር የኔ ንበረት ነው የሚለው ክልል አለው ማለቱ ነው፣ ወይም የጀዋር ህብረ-ብሔራዊ ፌዴራሊዝም መሬትና ማንነት ተጣብቀው የሚገኙበት ፌዴራልዝም ነው። በዚህ ሞዴል ውስጥ ያለው ህብረ-ብሔራዊ ፌዴራሊዝም ግን በአንድ ክልል ውስጥ የተለያዩ ብሔሮች ለምሳሌ፣ ቦረና፣ቡርጂ፣ኮይራ፣ጉጂና ኮንሶ አንድ ክልል ፈጥረው አንድ ላይ ሊኖሩ ይችላሉ። ከእነዚህ ብሔሮች ውስጥ አንድ ብሔር ብቻውን ክልሉ የኔ ነው ማለት አይችልም። ነገር ግን እያንዳንዱ ብሔር ትምህርት፣ቋንቋና ባህሉን በተመለከተ እራሱን በራሱ የማስተዳደር ሥልጣን ይኖረዋል (Non-Teritorial Autonomy)።

445555tgg

                                                                            

የኮርፖሬት ሥልጣን መጋራት ሞዴል ትልቁ ጥቅም በማዕከላዊው መንግስት ደረጃ ብሔረተኞችን እንዲያቅፍ፣ በአካባቢ አስተዳደር ደረጃ ደግሞ ብሔረተኝነትን ማለዘብ እንዲችል ተደርጎ ዲዛይን የተደረገ ሞዴል መሆኑ ነው። ይህ ሞዴል ኢትዮጵያ ውስጥ የብሔር ፖለቲከኞችና የዜግነት ፖለቲካ አራማጆች ሁለቱም የሚወዱትም አጥብቀው የሚዋጉትም ጎን አለው፣ ስለዚህ ሞዴሉ ዲዛይን ሲደረግ ሁለቱን ወገኖች እንዲያስማማ ተደርጎና በሌሎች የዲዛይን አማራጮችም ተደግፎ መቅረብ አለበት።

ሞዴል ሦስት ፕሬዚደንታዊ ሥርዓት- ፕሬዚደንታዊ ሥርዓት ሁለት በተለያየ መንገድ በህዝብ የሚመረጡ አካላት (ፕሬዚደንቱና ምክር ቤቱ) ያሉትና በሦስቱ የመንግስት አካላት (ህግ አስፈጻሚ፣ ህግ አውጪና ህግ ተርጓሚ) መካከል የተሰመረ ልዩነትና ህገ መንግስታዊ ቁጥጥር ያለበት ሥርዓት ነው። የፕሬዚደንታዊ ሥርዓትን ከፓርላማ ሥርዓት ከሚለዩት ብዙ ባህሪያት ውስጥ አንዱና ዋነኛው የህግ አስፈጻሚው አካል መሪ በቀጥታ በህዝብ የሚመረጥ ሆኖ ርዕሰ ብሔርም የመስተዳድሩ መሪም መሆኑ ነው።  ይህ ከዚህ ቀጥሎ የምንመለከተው ሞዴል  በቀጥታ በህዝብ የሚመረጥ ፕሬዚደንት፣ ፕሬዚደንቱን ለመምረጥ የምንጠቀምበት ሁለት ዙር የምርጫ ሥርዓት፣ የምክር ቤት አባላቱን ለመምረጥ የምንጠቀምበትን አማራጭ ድምፅ የምርጫ ሥርዓትና ህብረ-ብሔር ፌዴራልዝምን አዳብሎ የያዘ ሞዴል ነው። በፕሬዚደንታዊ ሥርዓት ውስጥ የምክር ቤቱን ይሁንታ አግኝቶ ካቢኔውን የሚመሰርተው ፕሬዚደንቱ ስለሆነ፣ በዚህ ሞዴል ውስጥ የምክር ቤት መቀመጫ ባገኙ ፓርቲዎች መካከል የሚደረግ የሥልጣን ክፍፍል የለም። ጥምር መንግስት በሚመሠረትባቸው ፕሬዚደንታዊ ሥርዓቶችም ዉስጥ ቢሆን፣ ከየትኞቹ ፓርቲዎች ጋር እንደሚጣመርና ለየትኞቹ ፓርቲዎች የካቢኔ ቦታ መስጠት እንዳለበት የሚወስነው ፕሬዚደንቱ ወይም የፕሬዚደንቱ ፓርቲ ነው።

ከላይ በተመለከትነው ሞዴል ዉስጥ ክልሎች ሲዋቀሩ ብሔረተኝነትን ማርገብ በሚችሉበት መንገድ ነበር የተዋቀሩት። ይህ እንዲሆን የተደረገው በፌዴራሉ መንግስት ደረጃ የተደረገው የሥልጣን ክፍፍል ለብሔር ፓርቲዎች ያደላ ስለነበር ነው። በዚህ ሞዴል ውስጥ ግን ፕሬዚደንቱ በአገር አቀፍ ደረጃ ስለሚመረጥና የምክርቤቱ አባላት የሚመረጡት በመቀራረብና በማዕከል ፓለቲካ ላይ በሚያተኩረው አማራጭ ድምፅ የምርጫ ሥርዓት ስለሆነ፣ በክልል ደረጃ  በተቻለ መጠን ብሔሮች እራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ ይደረጋል (ህብረ-ብሔራዊ ፌዴራልዝም)። ህብረ-ብሔራዊ ፌዴራሊዝሙ አናሳ ቡድኖች ታሪካቸውን፣ የትምህርት ፖሊሲያቸውን፣ሃይማኖታቸውን፣ ባህላቸውንና ቋንቋቸውን በተመለከተ እራሳቸውን በእራሳቸው የሚያስተዳድሩት አሰራር አለው (Non-territorial Autonomy)። በክልል ደረጃ የሚገኙ ምክር ቤቶችን ለመሙላት የሚደረገው ምርጫ የሚካሄደው በተመጣጣኝ የምርጫ ሥርዓት ነው። የክልል ፕሬዚደንቶች የሚሾሙ ሳይሆን በክልሉ ህዝብ በቀጥታ የሚመረጡ ናቸው (ሁለት ዙር ምርጫ ሥርዓት)

በፕሬዚደንታዊ ሥርዓት ውስጥ ፕሬዚደንቶች ከፍተኛ ሥልጣን አላቸው። ኢትዮጵያን በመሳሰሉ በተከፋፈሉ ማህበረሰቦች ውስጥ የአገሪቱ ከፍተኛው ሥልጣን ወደ አንድ ብሔር እጅ ሲገባ ለተፎካካሪ ብሔሮች የሚዋጥ አይደለም። በተለይ ፕሬዚደንታዊ ምርጫው የሚደረገው አሁን በስራ ላይ ባለው አብላጫ ድምፅ የምርጫ ሥርዓት ከሆነና፣ ፕሬዚደንቱ የተመረጠው አብዛኛውን ድምፅ ከራሱ ብሔር ብቻ አግኝቶ ከሆነ፣ የምርጫው ውጤት ከተፎካካሪ ብሔሮች ብዙ ተቃውሞ ይበዛበታል። ከዚህ በተጨማሪ በፕሬዚደንታዊ ሥርዓት ውስጥ ሥልጣን አንድ ሰው እጅ ላይ ስለሚከማች፣ እንደ ኢትዮጵያ አይነቱ ጠንካራ የዲሞክራሲ ተቋም የሌለው አገር ውስጥ ፕሬዚደንቱ ወደ አምባገነንነት ቢለወጥ የሚያቆመው ተቋም የለም። ይህ ደሞ ፕሬዚደንታዊ ዲሞክራሲን በሚከተሉ ብዙ አገሮች ውስጥ በተደጋጋሚ ታይቷል። ለምሳሌ፣አሜሪካ ውስጥ January 6, 2021 ትራምፕና ደጋፊዎቹ የፈጸሙት የፖለቲካ ሸፍጥ ሊገታ የቻለው አሜሪካ ጠንካራና የረጂም አመት ልምድ ያላቸው ተቋማት ስላሏት ነው። ስለዚህ ኢትዮጵያ ፕሬዚደንታዊ ሥርዓት ምርጫችን ከሆነ ህገ መንግስቱ ሲጻፍና፣ የምርጫ ሥርዓቱና ፕሬዚደንታዊ ሥርዓቱ ዲዛይን ሲደረጉ ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ያስፈልጋል። ደሞም የአንድን ሰው ፍላጎት ለማርካት ሲባል አሁን እንደሚታየው ዘጭፍን ዘልለን ፕሬዚደንታዊ ሥርዓት ዉስጥ ከመግባት፣ ከፍጹም ፕሬዚደንታዊ ሥርዓት ውጭ የሚገኙ ግማሽ-ፕሬዚደንታዊ ሥርዓቶችንም መመልከትና ለአገራችን የሚበጀው የትኛው ነው የሚለውን መልስ ከፖለቲከኞች ወይም ከገዢው ፓርቲ ብቻ ሳይሆን፣ የምሁራኖቻችንን የጥናትና ምርምር ስራም እንደ ግብአት መጠቀም አስፈላጊ ይመስለኛል።

445555tggH

ሞዴል አራት ጠ/ሚኒስትር-ፕሬዚደንት ሥርዓት- ይህ ሞዴል  ተግባራዊ እንዲሆን ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የምርጫ ሥርዓትና የመንግስት ቅርፅ መለወጥ አለባቸው፣ ክልሎችም እንደገና በአዲስ መልክ መዋቀር አለባቸው። እነዚህ ሦስት ትልልቅ ለውጦች የአብዛኛውን ኢትዮጵያዊ ስምምነት የሚፈልጉ ለውጦች ስለሆኑ ሰፊና ጥልቅ ውይይት ሊደረግባቸው ይገባል፣ደግሞም በሰጥቶ መቀበሉ ሂደት ዉስጥ የሞዴሉን መሰረታዊነት የማይለውጡ ነገር ግን የተለያዩ ባለድርሻዎችን ማቀራረብ የሚችሉ ብዙ የዲዛይን አማራጮች ቀርበው መታየት አለባቸው። ይህ ሞዴል በቀጥታ በህዝብ የሚመረጥ ፕሬዚደንት፣በሁለት የተለያዩ የምርጫ ሥርዓቶች በህዝብ የሚመረጡ አባላት ያሉት ምክር ቤትና በፕሬዚደንቱ ቀርቦ በምክር ቤቱ የሚጸድቅ የካቢኔው መሪ (ጠቅላይ ሚኒስትር) አንድ ላይ ያሉበት ሞዴል ነው። ከላይ በተመለከትነው ፕሬዚደንታዊ ሥርዓት ውስጥ ፕሬዚደንቱ ርዕሰ ብሔረም የመስተዳድሩ መሪም ነው፣ በዚህ ሞዴል ግን ፕሬዚደንቱ ርዕሰ ብሔር፣ ጠ/ሚኒስትሩ ደሞ የመስተዳድሩ መሪ ነው።

በዚህ ሞዴል ውስጥ ሦስት የተለያዩ የምርጫ ሥርዓቶች ሊኖሩ ይችላሉ። አንደኛው የምርጫ ሥርዓት ፕሬዚደንቱ የሚመረጥበት ሁለት ዙር የምርጫ ሥርዓት ሲሆን፣ ሁለተኛውና ሦስተኛው የምርጫ ሥርዓቶች የላይኛውና የታችኛው ምክር ቤቶች የሚመረጡባቸው የምርጫ ሥርዓቶች ናቸው። የታችኛው ምክር ቤት (የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት) አባላት በድብልቅ የምርጫ ሥርዓት ይመረጣሉ። ድብልቅ የምርጫ ሥርዓት አብላጫ ድምፅና ተመጣጣኝ የምርጫ ሥርዓቶችን አዳቅሎ የያዘ የምርጫ ሥርዓት ነው። የታችኛው ምክር ቤት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲሆን፣ ይህ ምክር ቤት የሚወክለው በምርጫ ወረዳ ደረጃ የመረጠውን ህዝብ ነው።

የላይኛው ምክር ቤት አባላት የሚመረጡት በየክልሉ ሲሆን ውክልናቸውም ለመረጣቸው ክልል ነው። በዚህ ምርጫ ላይ ፓርቲዎችም የግል ተወዳዳሪዎችም መወዳደር ይችላሉ። የግል ተወዳዳሪዎች ስማቸው የምርጫ ካርድ ላይ እንዲኖር በህግ የተቀመጠውን የማህበረሰብ ድጋፍ ከክልሉ ህዝብ ማግኘት አለባቸው። ይህ ከህዝብ የሚገኘው ድጋፍ ሊረጋገጥ የሚችልና ከተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች የተገኘ ድጋፍ መሆን አለበት። ይህ ምርጫ በሁለት ዙር የምርጫ ሥርዓት ወይም በአማራጭ ድምፅ የምርጫ ሥርዓት ሊካሄድ ይችላል። በሁለቱም የምርጫ ሥርዓቶች የሚመረጡ ተወዳዳሪዎች ከ50% በላይ የህዝብ ድምፅ የሚያገኙ ሲሆን፣ አማራጭ ድምፅ የምርጫ ሥርዓት ደግሞ ከዚህ በተጨማሪ የፖለቲካ ባለድርሻዎችን የማቀራረብና የብሔር ፖለቲካን የማለዘብ ባህሪይ አለው።

በጠ/ሚ-ፕሬዚደንት ሞዴል ዉስጥ ርዕሰ ብሔሩና (ፕሬዚደንቱ) የመስተዳድሩ መሪ (ጠ/ሚኒስትሩ) የህግ አስፈጻሚውን አካል ስራ ህገ መንግስቱ በሚያዘው መሠረት ይጋራሉ። ኢትዮጵያ ዉስጥ እነዚህ ሁለት የህግ አስፈጻሚው አካል አባላት (ፕሬዚደንቱና ጠ/ሚኒስትሩ) የአንድ ብሔር አባላት ባይሆኑ ይመረጣል፣በተለይ የህዝብ ብዛታቸው ከአንደኛ እስከ አምስተኛ ከሆነ ብሔሮች እንዳይሆኑ መደረግ አለበት። በዚህ ሞዴል ውስጥ ፕሬዚደንቱ ምክር ቤቱን፣ ምክር ቤቱ ደግሞ ካቢኔውን መበተን ይችላሉ። ይህ  ፕሬዚደንቱና የህግ አውጪው አካላት ያላቸው ህገ መንግስታዊ መሳሪያ በአንድ ፕሬዚደንት የሥልጣን ዘመን ውስጥ ስንት ግዜ መጠቀም እንደሚቻል በህግ መቀመጥ አለበት።

በጠ/ሚ-ፕሬዚደንት ሞዴል ዉስጥ ክልሎች የሚደራጁበት መንገድ ከላይ ሞዴል 3 ላይ ከተመለከትነው የክልል አደረጃጀት ጋር ተመሳሳይ ነው። አንድ ክልል ሲዋቀር ብዙ መመዘኛዎች ታይተው በተቻለ መጠን ከሁለት በላይ የቋንቋና የባህል ስብስቦችን አቅፎ እንዲዋቀር ይደረጋል። በአንድ ክልል ዉስጥ የሚኖሩ የቋንቋና የባህል ስብስቦች ቋንቋቸውን፣ ታሪካቸውን፣ ባህላቸውንና ልማዳቸውን እራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር እንዲችሉ ይደረጋል (Non-Territorial Autonomy)። ክልሎች የራሳቸውን የምርጫ ሥርዓት ይመርጣሉ። ክልሎች እንዳሁኑ በፕሬዚደንት የሚመሩ ከሆነ ፕሬዚደንቱ በቀጥታ በህዝብ የሚመረጥ ይሆናል።

445555tggHQ

 

የጠ/ሚኒስትር-ፕሬዚደንት ሞዴል የሚከተሉት ጥቅሞች ይኖሩታል፡

  1. የክልሎችን ጥቅምና ፍላጎት የሚወክል በየክልሎቹ የተመረጠና የህግ አዉጪው አካል የሆነ ምክር ቤት አለ፣ በየክልሉ ዉስጥ የሚኖሩ የወል ስብስቦች አናሳ ቡድኖች ቋንቋቸውንና ባህላቸውን በራሳቸው መንገድ የሚያስተዳደሩበት ሥርዓትም አለ። እንዲህ አይነቱ አደረጃጀት ብሐረተኝነትን ስለሚያለዝብ የዜግነት ፖለቲካ አራማጆቹን ይወዱታል፣ የብሔር ብሔረሰቦችን ቋንቋ፣ባህልና ታሪክ እንዲከበር ስለሚያደርግ የብሔር ልህቃንም ይወዱታል።
  2. ፕሬዚደንቱ በአገር አቀፍ ደረጃ ከሚሰጠው ድምፅ ከግማሽ በላዩን አግኝቶ ስለሚመረጥ (ሌላም መጠበቂያ ሊበጅለት ይችላል) በፕሬዚደንቱ ምርጫ ውጤት የሚከፋ አካል አይኖርም። ፕሬዚደንቱ የብሔራዊ አንድነት ምልክት ስለሆነ (National Symbol) በምክር ቤቱ ዉስጥም ሆነ በሌሎች በተለያዩ ብሔራዊ መድረኮች ላይ ጥግ የያዙ የፖለቲካ ኃይሎችን የማቀራረብ ማንዴት አለው
  3. የህግአስፈጻሚው አካል ወይም ከሁለቱ ምክር ቤቶች በአንደኛው ዉስጥ የሚመነጩ የህግ ረቂቆች ህግ ሆነው ለመጽደቅ የሁለቱም ምክር ቤቶችና የፕሬዚደንቱ ድጋፍ ስለሚያስፈልጋቸው፣ የህግ አውጪው አካል የሚያወጣቸው ህጎች የህዝብን ጥቅምና ፍላጎት የሚያንጸባርቁ ይሆናሉ፣ የማይሆኑ ከሆነ ወይም ህዝባዊ ተቀባይነት የሌላቸው ህጎች ጸድቀው ህግ የመሆን ዕድላቸው እጅግ በጣም ዝቅተኛ ነው
  4. ፕሬዚደንቱና ጠ/ሚኒስትሩ የሚያዋቅሩት ካቢኔ የምክር ቤቱን ድጋፍ ማግኘት ስላለበት የህግ አስፈጻሚው አካል ስብጥር ሁሉንም የፖለቲካ ባለድርሻ እኩል ባያስደስትም ሁሉም ባለድርሻ ያከብረዋል
  5. በወረዳደረጃ በሚደረጉ ምርጫዎች ድምፅ ሰጪው ማህበረሰብ ፓርቲዎች ከሚያቀርቧቸው ተወዳዳሪዎች ውስጥ ለሚፈልገው ተወዳዳሪ ድምጹን መስጠት ይችላል፣ በዚህ ደረጃ የሚመረጡ ተወዳዳሪዎች የሚወክሉት የተመረጡበትን ወረዳ ህዝብ ስለሆነ ትኩረታቸው በአካባቢ ጉዳዮች ላይ ነው። በአገር አቀፍ ደረጃ በሚደረገው ምርጫ ህዝብ ድምጹን የሚሰጠው ለግለሰብ ተወዳዳሪዎች ሳይሆን ለፓርቲዎች ነው። ፓርቲዎች የሚወዳደሩትና አሸንፈው የምክር ቤት መቀመጫ የሚይዙት በአገር አቀፍ ደረጃ ስለሆነ፣ ምክር ቤቱ ውስጥ የሚያተኩሩትም በብሔራዊ ጉዳዮች ላይ ነው። ይህ ማለት ደግሞ ድብልቅ የምርጫ ሥርዓት ባለባቸው አገሮች ውስጥ ውክልና አካባቢያዊና ብሔራዊ ገጽታ አለው ማለት ነው። የህግ አውጪው አካል የሚያወጣቸው ህጎች ይዘትም አካባቢያዊና ብሔራዊ ሚዛናቸውን የጠበቁ ይሆናሉ ማለት ነው
  6. ድብልቅ የምርጫ ሥርዓት በአንድ በኩል ዉክልናን (Representation) በሌላ በኩል ደግሞ   ተጠያቂነትን (Accountabilty) አጣምሮ የያዘ የምርጫ ሥርዓት ስለሆነ፣ ትኩረታቸው ዉክልና የሆነ የብሔር ኃይሎችንም ተጠያቂናትና ጠንካራ ማዕከላዊ መንግስት ፈላጊ ኃይሎችንም እንደየጠባያቸውና ፍላጎታቻው ማስደሰት ይችላል
  7. ይህ ሞዴል የፓርላማና የፕሬዚደንት የመንግስት ቅርፅ የተለያዩ ባህሪያትን አጣምሮ የያዘ ስለሆነ ኢትዮጵያ ውስጥ የሁለቱንም የመንግስት ቅርፅ(ፓርላማና ፕሬዚደንት) ደጋፊዎች ማስማማት የሚችል የመንግስት ቅርፅ ነው

 

የጠ/ሚኒስትር-ፕሬዚደንት ሞዴል ደካማ ጎኖች

  1. ምክርቤቱ ዉስጥ የተለያዩ ፓርቲዎች ካሉና የፕሬዚደንቱ ፓርቲ አብላጫ ከሌለው ውሳኔ ማሳለፍ አስቸጋሪ ስለሚሆን አንደኛ የፖለቲካ ሽባነት ይፈጠራል፣ ሁለተኛ- ፕሬዚደንቱ ምክር ቤቱን ወይም ምክር ቤቱ ካቢኔውን መበተን ስለሚችሉ የእነዚህ ኩነቶች መደጋገም የፖለቲካ አለመረጋጋት ስለሚፈጥር፣ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ የተከፋፈሉ ማህበረሰቦችና የዲሞክራሲ ጀማሪዎች ይህ ትልቅ አደጋ አለው
  2. የጠቅላይ ሚኒስትሩና የፕሬዚደንቱ ፓርቲ የተለያየ ሲሆን የህግ አስፈጻሚው አካል የንትርክ ቦታ ሊሆን ይችላል፣ እንደገና የጠቅላይ ሚኒስትሩና የፕሬዚደንቱ ፓርቲ የተለያየ ሆኖ የጠ/ሚኒስትሩ ፓርቲ የምክር ቤቱ አብላጫ ከሆነ፣ በቀጥታ በህዝብ የተመረጠው ፕሬዚደንት ጠ/ሚኒስትሩን መስማት አለበት ካለዚያ አሁንም ከላይ የተመለከትነው አይነት የፖለቲካ ሽባነት ይፈጠራል
  3. የህግአስፈጻሚውን አካል ጠ/ሚ እና ፕሬዚደንቱ ስለሚጋሩት ለተሰሩ ስራዎች፣ መሰራት ሲገባቸው ላልተሰሩና ተሰርተዉ ድክመት ላለባቸው ስራዎች ማን ሃላፊነት እንደሚወስድ በዉል ተለይቶ አይታወቅም።
  4. እንደ ኢትዮጵዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች በብሔር መደራጀት ብቻ ሳይሆን፣የብሔር ፓርቲዎች የምክር ቤት መቀመጫ ማሸነፍ የሚችሉበት አጋጣሚ ሲኖርና በተለይ ምክር ቤቱ ውስጥ 50 + 1 ድምፅ ማግኘት የሚቻለው ከሁለት ፓርቲዎች በላይ ዉሳኔውን ሲደግፉ ከሆነ፣ ምክር ቤቱ የተከፋፈለ (Fragmented) ይሆንና የውይይት ሳይሆን የጫጫታ መድረክ ይሆናል

 

                    ግማሽ ፕሬዚደንታዊ የመንግስት ቅርፅ

ግማሽ ፕሬዚደንታዊ በመባል የሚታወቀው የመንግሥት ቅርፅ ፕሬዚደንታዊና ፓርላማዊ የመንግሥት ቅርጾችን አዳቅሎ የያዘ ድብልቅ የመንግሥት ቅርፅ ነው። ‹‹ድብልቅ›› የመንግሥት ቅርፅ እስካሁን ካየናቸው የመንግሥት ቅርጾች ፍጹም የተለየ አዲስ የመንግሥት ቅርፅ አይደለም። እንድያውም እስካሁን ያየናቸው ሁለቱ (የፓርላማና የፕሬዚደንታዊ)  የመንግሥት ቅርጾች ተደባልቀው የፈጠሩት የመንግሥት ዓይነት ነው። በግማሽ ፕሬዚደንታዊ የመንግስት ቅርፅ ዉስጥ ጠ/ሚኒስትር -ፕሬዚደንት እና ፕሬዚደንት-ፓርላማ በመባል የሚታወቁ ሁለት የተለያዩ የመንግስት ቅርጾች አሉ።

ጠ/ሚኒስትር -ፕሬዚደንት የመንግሥት ቅርፅ ስሙ በግልጽ እንደሚናገረው እንደ ፕሬዚደንታዊ ሥርዓት በቀጥታ በህዝብ የሚመረጥ ፕሬዚደንት አለበት፣ ደግሞም እንደ ፓርላማ ሥርዓት ርዕሰ መስተዳድሩን የሚመራው በቀጥታ በህዝብ የማይመረጥ ጠ/ሚኒስትር አለበት። በጠ/ ሚኒስትር -ፕሬዚደንት ሥርዓት ውስጥ ጠ/ ሚኒስትሩንና የካቢኔ አባላትን የሚመርጠው ፕሬዚደንቱ ነው። ሆኖም የጠ/ሚኒስትሩና የካቢኔው ተጠያቂነት ለምከር ቤቱ ብቻ ነው። ሁለቱንም ከሥልጣናቸው ማሰናበት የሚችለውም ምክር ቤቱ ብቻ ነው። ፕሬዚደንቱ ከመስተዳድሩ ጋር በሚጋራቸው የኃላፊነት ቦታዎች ሁሉ ከጠ/ ሚኒስትሩ ጋር መግባባት ነው ያለበት እንጂ ጠ/ ሚኒስትሩን /መስተዳድሩን ማስገደድ ወይም ህ ገ መንግሥታዊ በሆነ መንገድ በመስተዳድሩ ላይ ተፅዕኖ ማድረግ አይችልም። መስተዳድሩም ቢሆን በአንድ በኩል ከፕሬዚደንቱ ሊመጣ ይችላል ብሎ የሚሰጋው ምንም ዓይነት የፖለቲካ ጫና የለበትም፣ በሌላ በኩል ደግሞ መስተዳድሩ ምክር ቤቱን ሳያማክር ከፕሬዚደንቱ ጋር ተስማምቶ ያሰኘውን ማድረግ አይችልም። በጠ/ ሚኒስትር -ፕሬዚደንት ሥርዓት ውስጥ የፕሬዚደንቱ ፓርቲ በምክር ቤቱ ዉስጥ አብላጫ (Majority) መቀመጫ ከሌለውና፣ በተለይ ደግሞ ፕሬዚደንቱና ጠ/ሚንስትሩ የአንድ ፓርቲ አባላት ካልሆኑ፣ፕሬዚደንቱ የግድ ከምክር ቤቱ ጋር መስማማት አለበት፣ ካለዚያ ምክር ቤቱ ተበትኖ አዲስ ምርጫ መጠራት አለበት፣ ወይም የፕሬዚደንቱ የሥልጣን ዘመን እስኪያልቅ ድረስ የፖለቲካ ሽባነት ይኖራል። ፈረንሳይ፣አልጄሪያ ማሊና ፖላንድ ጠ/ ሚኒስትር-ፕሬዚደንት የመንግስት ቅርፅ ያለባቸው አገሮች ናቸው።

ፕሬዚደንት-ፓርላማ የመንግሥት ቅርፅ በህዝብ የተመረጠ ፕሬዚደንት፣ሃላፊነቱ ለምክር ቤቱና ለፕሬዚደንቱ የሆነ ጠ/ ሚኒስትር፣ ጠ/ ሚኒስትሩ የሚመራው ካቢኔና ምክር ቤት ጎን ለጎን የሚገኙበት የመንግሥት ዓይነት ነው። በዚህ የመንግሥት ዓይነት ውስጥ ጠ/ ሚኒስትር የሚሾመውና የካቢኔውን አባላት የሚመርጠው ፕሬዚደንቱ ቢሆንም የፕሬዚደንቱ ምርጫ የምክር ቤቱን አብላጫ ድጋፍ ማግኘት አለበት። በፕሬዚደንት- ፓርላማ ሥርዓት ውስጥ መስተዳድሩ ለሁለት በህዝብ ለተመረጡ አካላት ተጠያቂነት አለበት (ለፕሬዚደንቱና ለምክር ቤቱ)፣ ደግሞም ህለቱም መስተዳድሩን ከሥልጣን የማባረር ሥልጣን አላቸው። ይህ ማለት ደግሞ በፕሬዚደንት-ፓርላማ ሥርዓት ውስጥ መስተዳድሩ በሥልጣን ላይ ለመቆየት የፕሬዚደንቱንም የምክር ቤቱንም ድጋፍ ይፈልጋል ማለት ነው። ሩሲያ፣ካሜሩን፣ ኦስትሪያና ሴኔጋል ፓርላማ-ፕሬዚደንት የመንግስት ቅርፅ ያለባቸው አገሮች ናቸው።

በፕሬዚደንት-ፓርላማ ሥርዓትና በጠ/ ሚኒስትር -ፕሬዚደንት ሥርዓት መካከል ጉልህ ልዩነቶች አሉ- አንደኛ- በፕሬዚደንት ፓርላማ ሥርዓት ውስጥ ፕሬዚደንቱና ምክር ቤቱ ካቢኔውን ከሥልጣን የማባረር ሥልጣን አላቸው። በ‹‹ጠ/ ሚኒስትር -ፕሬዚደንት›› ሥርዓት ውስጥ ግን ፕሬዚደንቱና ምክር ቤቱ በካቢኔ ምሥረታ ላይ የየራሳቸውን ሚና ይጫወታሉ እንጂ ካቢኔውን ከሥልጣን ማባረር የሚችለው ምክር ቤቱ ብቻ ነው። በፕሬዚደንት-ፓርላማ ሥርዓት ዉስጥ ያለው ፕሬዚደንት በጠ/ ሚኒስትር -ፕሬዚደንት ሥርዓት ውስጥ ካለው ፕሬዚደንት የበለጠ ሥልጣን አለው፣ ይህ ሥልጣን ከፍተኛ ሥልጣን ስልሆነ የፕሬዚደንት-ፓርላማ ሥርዓት ለአምባገነንነት ቅርብ ነው። ለምሳሌ፣ የሩሲያ ፕሬዚደንት በተቋም ደረጃ ሥልጣኑን የሚገድብ ህገ መንግሥታዊ አንቀጽ ባለመኖሩ ዛሬ ሩሲያ  “የምርጫ  ዓምባገነን ”  በመባል  ትታወቃለች።

 

ማጠቃለያ

የዘመናዊው ኢትዮጵያ ታሪክ አብዛኛው ምዕራፍ የጦርነት፣ የግጭትና የርስ በርስ መጠፋፋት ምዕራፍ ነው። ጀብሐ፣ ሻዕቢያ፣ ኢዲህ፣ ህወሓት፣ኢህአፓ፣ኦነግ፣ኦብነግ እነዚህ ሁሉ በአንድ ወቅት ከኢትዮጵያ ማዕላዊ መንግስት ጋር ብቻ ሳይሆን፣ በአንድ በኩል እርስ በርስ፣ በሌላ በኩል ደሞ አንጃ ፈጥረው ከራሳቸው አባላት ጋርም ተዋግተዋል።  በ2010 ዓም ከሥልጣን የተባረረው ህወሓት እኔ የማልገዛት ኢትዮጵያ ትፍረስ ብሎ ሰሜን ኢትዮጵን ለሁለት አመታት አተራምሷል። አሁን ደሞ ይባስ ብሎ የፌዴራሉ መንግስት ፋኖን ትጥቅ ካላስፈታሁ በሚል በከፈተው ጦርነት የአማራ ክልል በሦስት አመት ውስጥ እንደገና ለሁለተኛ ግዜ በጦርነት እየታመሰ ነው።

ከሃምሳ አመት በኋላና ከሦስት መንግስታት መቀያየር በኋላ ዛሬም እኛ ኢትዮጵያዊያን ልዩነቶቻችንን መፍታት የምንሞክረው በጦርነት ነው፣ በመካከላችን ልዩነት በተፈጠረ ቁጥር ማስወገድ የሚቀናን በመካከላችን ያለውን የሃሳብ ልዩነት ሳይሆን በሃሳብ የሚለዩንን ነው። በታሪካችን የፖለቲካ ልዩነቶቻችችንን በሰላማዊ መንገድ የማስወገድ ባህል ስለሌን ነው እንጂ፣ ባለፉት ሃምሳ አመታት እርስ በርስ የተዋጋናቸውን ጦርነቶች በድርድድር ወይም በውይይት ለማስወገድ ሞክረን ቢሆን ኖር ዛሬ እንደ አገር ሁላችንም አሸናፊዎች እንሆን ነበር።

የፊውዳሉ ሥርዓት ሰው በላ ሥርዓት ነው እያለ ቀዳማዊ ኃ/ሥላሤን እየኮነነ ወደ ሥልጣን የመጣው ደርግ፣እሱ እራሱ በሺዎች የሚቆጠሩ ምህራንን እና ወጣቶችን በቁማቸው በልቶ ነው ከሥልጣን የተወገደው። ደርግን ከሥልጣን ያስወገዱ ኃይሎች አዲስ አበባን ሲረግጡ ማደን የጀመሩት ወንጀለኞች ያሏቸውን የደርግ ባለሥልጣኖች ነበር። ከ27 አመት በኃላ እነሱም በተራቸው ከሥልጣን ሲወገዱ የ”ቀን ጅቦች” ተብለዋል። እነሱን የ”ቀን ጅቦች” ያለው ኃይልም ዛሬ ከደርግና ከህወሓት አወዳደቅ መማር አቅቶት፣ የኢትዮጵያን ችግሮች መፍታት የሚሞክረው ከሱ በሃሳብ የሚለዩትን በማፈን፣ በማሰቃየትና በጦርነት ነው።

ኢትዮጵያ ዉስጥ ካሁን በኋላ የሚመሰረተው መንግስት በ1967፣ በ1983 እና በ2010 ዓም ወደ ሥልጣን የመጡ ሦስት ተከታታይ መንግስታት ማድረግ ሲገባቸው ያላደረጉት አጅግ በጣም ቁልፍና ታሪካዊ ስራ ይጠብቀዋል። ወታደራዊው ደርግ ሶሻሊዝምን ከውጭ እንዳለ ተውሶ አምጥቶ ክረምት ከበጋ የሚፈሱ ወንዞች፣ለምልም የእርሻ መሬትና ታታሪ ገበሬ ይዘን እንድንራብ አድርጎናል። ህወሓትም የኢትዮጵያን ፖለቲካ መሠረት በብሔር ላይ በማዋቀር ሃያ ሰባት አመት ሙሉ እርስ በርስ አባልቶናል። ህወሓትን የተካው የብልፅግና መንግስትም ሥልጣን ላይ ከወጣበት ቀን ጀምሮ ኢትዮጵያ ውስጥ የጠመንጃ ድምፅ ሳይሰማ ውሎ አድሮ አያውቅም።

ካሁን በኋላ አራት ኪሎ የሚገባው መንግስት የኢትዮጵያን ህዝብ በዘር፣በቋንቋና በሃይማኖት ሳይለይ አንድ ላይ በሰላም የሚያኖርና፣ሰብዓዊ፣ማህበራዊና ኤኮኖሚያዊ ደህንነታቸውን የሚጠብቅ መንግስት መሆን አለበት፣የብሔር ፖለቲካን በቃ የሚልና ሙሰኝነትን የሚጸየፍ መንግስት መሆን አለበት፣ ሲቪክ ናሺናልዝምን የሚገነባ፣ ለሰላምና መረጋጋት ዋስትና የሚሰጥና ብዝሃነታችንን የሚያስተናግዱ የዲሞክራሲ ተቋሞችን እዚሁ አገራችን ውስጥ ዲዛይን የምናደርግበትን መንገድ የሚያዘጋጅ መንግስት መሆን አለበት።

ኢትዮጵያን እንደ አገር ያዋቀሩ ትልልቅ ዉሳኔዎች በነገስታቱ ዘመን በንጉሶች፣ በደርግ ዘመን በኮሎኔል መንግስቱ፣ በህወሓት ዘመን በመለስ ዜናዊ፣ ዛሬ ደሞ በጠሚ አቢይ አህመድ ነው የተወሰኑት ወይም የሚወሰኑት። ካሁን በኋላ፣በተለይ እርስ በርስ የተገዳደልንባቸውን ያለፈውን ሃምሳ አመት የጨለማ ታሪካችንን በይቅርታ አልፈን ለአዲስ የፖለቲካ ሥርዓት መሰረት ስንጥል የምንወስናቸው ውሳኔዎች አብዛኛውን የአገራችንን ባለድርሻ ማካተት አለባቸው። ይህንን ለማድረግ ደሞ እኛ ኢትዮጵያዊያን በአገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄድ ነጻና ገለልተኛ የውይይት መድረክ ወይም አገራዊ የምክክር ጉባኤ ያስፈልገናል። ይህ  አገራዊ ምክክር ጉባኤ የጨለማውን ዘመን ታሪክ ዘግቶ አዲስ የተስፋ ዘመን መጀመር አለበት፣ይህ ምክክር የረጂም ግዜ ታሪካችንን የሚጣፍጠውንም የሚመረውንም የጋራ ታሪካችን እንደሆነ አስምሮበት፣ ታሪክ በታሪክነቱ ለሚቀጥለው ትውልድ የምናስተላልፈው እንጂ የግድ የምንስማማበት ክስተት አለመሆኑን አትኩሮት መስጠት አለበት፣ ይህ ምክክር በታሪክ የተሰሩ ስህተቶችን ማስተካከል እንደማንችልና የወደፊታችንን ግን ከስህተታችን ተምረን መልካም የማድረጉ ዕድል እጃችን ላይ እንዳለ ለኢትዮጵያ ህዝብ ግልፅ ማድረግ አለበት።ይህ ምክክር ኢትዮጵያ ውስጥ በብሔርና በዜግነት ኃይሎች መካከል ያለውን ልዩነት ማስወገድ አለበት፣ ይህ ምክክር እኛ ኢትዮጵያውያን የተለያየ ብሔር፣ቋንቋ፣ባህልና ሃይማኖት ቢኖረንም የአንድ ቁጭ ብለን ተደራድረን በጋራ የምንፈጥረው ፖለቲካ ማህበረሰብ ዜጎች መሆናችንን ማረጋገጥ አለበት፣ ይህ ምክክር ልጆቿ ሁሉ እናቴ የሚሏት አዲስቷን ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን መሸከም የሚችሉ የዲሞክራሲ፣የፍትህና የደህንነት ተቋሞች የትኞቹ ናቸው የሚለውን ቁልፍ ጥያቄ በመመለስ ኢትዮጵያ ውስጥ ከአንድ ምዕተ አመት በፊት ተጀምሮ በእንጥልጥል የቀረውን የአገረ-መንግስት ግንባታ ሂደት ማጠናቀቅ አለበት።

 

ዋቢ ጽሁፎች

  1. Birnir, Johanna: Ethnicity and Electoral Politics
  2. Constitutional Design for Divided Societies: Integration or Accommodation?  Edited by Sujit Choudhry
  3. Hale, Henry E: The Foundations of Ethnic Politics
  4. Horowitz, Donald L.: The Challenge of Ethnic Conflict- Democracy in Divided Societies
  5. Lijphart, Arendt: Democracy in Plural Societies- A Comparative Exploitation
  6. Semir Yusuf, Constitutional design options for Ethiopia Managing ethnic divisions

 

5 Comments

  1. ወንድም ኤፍሬም ማዴቦ፦
    አንተው ራስህ እኮ “አገራችን ኢትዮጵያ የብዙ ብሔር ብሔረሰቦች አገር ናት፣ኢትዮጵያ ውስጥ ቁጥራቸው 80 የሚደርስ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ለዘመናት ጎን ለጎን አብረው ኖረዋል፣” ካልህ በኋላ፣ አንድነታችንና ሰላማችን እንዴት እንደተመረዘና ለመጋደል እንደበቃን ሳትነግረን ወደ ፈረንጅ ደራስያንና ወደ ሌሎች አገሮች የትርምስ ልምድ ሄድህ ። ይህ የብዙ ምሁራን ያቀራረብ ሥልት ስለሆነ አልፈርድብህም። ግን አንዱና ዋናው የሰላም ማጣታችን ፈጣሪ ተማርሁ ያለው ግልብ አገሩን የማያውቀው አዲሱ ትውልድ ነው።

    በሰላም የሚኖሩ ብሔር ብሔረሰቦቻችንን ምን አውሬ ከመሀላቸው ገብቶ ነው ያበጣበጣቸው ? ያን አውሬ ማስወገድስ እንዴት አቃተን። የቆየውን አኗኗራችንንስ እንዴት ብናደርግ ለሁላችንም እንዲጠቅመን አድርገን አገር በሰላምና በሕብረት ማሳደግ እንችላለን የሚለውን ጥያቄ ምሁራን ነን ባዮች ከ 1960ዎች ጀምሮ ስለሚፈሩት፣ የሚቀልላቸው የፈረንጅ መጻሕፍት ማነብነብ፣ የባዕድ አገሮች አሠራር፣ መጋደሉን ጭምር፣ መገልበጥና ኢትዮጵያን በስምምነት በመገንባት ፈንታ ኢትዮጵያን ሰላም መንሳቱን እንደ ሙያ ይዘውታል። ምሁር ነኝ የሚለውን ኢትዮያዊ ሊያሳስብ የሚገባው ፈረንጅ መጥቀሱ ሳይሆን ያንን ከ50 ዓመት በፊት የነበረንን ሰላም ከዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ጋር እንዴት እንመልሰው የሚለው ነው። የፈረንጅ ድርሰት መጥቀስ የምሁር መለያ መሆኑ ሊቆም ይገባል። ማኦ፣ ሌኒን፣ እስታሊን፣ ማርክስ፣ ኤንገልስ ባገራቸውም አልበጁም።

    “በህወሓት የተመሩት የብሔር ኃይሎች በ1983 ዓም ደርግን አሸንፈው የኢትዮጵያን የፖለቲካ ሥልጣን ከተቆጣጠሩ በኋላ በጻፉት ህገ መንግስት ውስጥ ብሔር ብሔረሰቦችን የአገር ሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤት አድርገዋቸዋል። ነገር ግን በወቅቱ በተግባር እንዳየነው አንዳንድ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ሉዓላዊ ናችሁ ወይም ‘ነፃ ወጣችሁ’ በተባሉ ማግስት ነፃነት ፍለጋ ጠመንጃ እያነገቡ ጫካ ገብተዋል። ህወሓት/ኢህአዴግ የገነባው የብሔር ፖለቲካ ሥርዓት በየብሔሩ (በተለይ በትላልቆቹ ብሔሮች) ልህቃን ጭንቅላት ውስጥ የፖለቲካ ሥልጣን እጃችን ውስጥ ከገባ ሁሉም ነገር የኛ ነው የሚል እምነት በመፍጠሩ፣ ዛሬ የኢትዮጵያን ህዝብ ሠላም የነሳው ኃይል አለኝ የሚሉ ብሔሮች አራት ኪሎን ለመቆጣጠር እዚህም እዚያም የሚጭሩት የጦርነት አሳት ነው። እኛ ኢትዮጵያዊያን የተለያየ ቋንቋ ብንናገርም፣ የተለያየ ባህልና ሃይማኖት ቢኖረንም፣አንድ የጋራ ፖለቲካ ሥርዓት ገንብተንና ፖለቲካዊ፣ ኤኮኖሚያዊና ማህበራዊ እሴቶቻችንን ‘እኩል’ ተካፍለን “የኢትዮጵያ ህዝብ” ተብለን በጋራ በሰላም መኖር የማንችለው ለምንድነው? ወይም በሰላም የሚያኖረንን ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት በጋራ ዲዛይን የማናደርገው ለምንድነው?” ብለህ

    1ኛ/ “ብሔር ብሔረሰቦችን የአገር ሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤት አድርገዋቸዋል።” የተባለው ሐረግህ ውሸት ነው። የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 5፣ አንቀጽ 8 እና አንቀጽ 47 አገናዝበህ ካየህ፣ ስሕተቱን ታየዋለህ ። ለ83 ብሐሄር ብሔረሰቦች 9 ክልል ፈጥሮ፣ የቀሩትን ለዘጠኙ ተገዢ አድርጎ፣ ” ነፃ ናችሁ ” መባሉ ሕዝብ ማታለለ ነው። ታዲያ ይኸ ነፃነት ያጣ ሕዝብ ከዘጠኙ ባለክልል ጎሣዎች እኩል አይደለሁም ብሎ አመልክቶ ሰሚ ሲያጣ ወደ ጫካ ቢገባ ስሕተቱ የት ላይ ነው ?

    2ኛ/ “ኢትዮጵያ የፖርላማ ሥርዓትን የምትከተል አገር ናት። የኢትዮጵያ ፓርላማ የሌሎች አገሮች ፓርላማ ያሉት ተቋማዊ መሳሪያ የሚጎድለውና፣ የህግ አውጪውና የህግ ተርጓሚዉ አካላት በደባልነት የሚኖሩበት ተቋም ነው።” ትላለህ ። ሰለዚህ፣ ኢትዮጳያ ሊዝ ትራስንና ቦሪስ ጆንሰንን እንዳሰናበተው እንደ እንግሊዝ ፓርላማ ሥርዓትም የላትም እያልኸን ነው። ትክክል !!!

    3ኛ/ የፌደራል ሥርዓት እንደሌላትም የቅርቡ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጎንደር ሄዶ ስብሰባ መምራቱ፣ ክልል ርዕሰ መስተዳድር በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መሾምና መሻሩ፣ የፌደሬሽን ም/ቤት ሥራ አስፈጻሚውን ዘርፍ ማዘዙ፣ ሥራ አስፈጻሚው ፓርላማውን ማዘዙ፣ ሕግ ተርጓሚው ዘርፍ በሥራ አስፈጻሚው ሥር መሆኑ፣ ክልሎች ክፌደራል መንግሥት ሥር መሆናቸውና ሌሎችም መንግሥታዊ ሂደተች የፌደራል ሥርዓትም እንደሌለን አመልካች ናቸው። ሕገ መንግሥቱን አንብብ !

    የአገራችን ሥርዓተ መንግሥት ፓርላማዊም፣ ፈደራልም፣ ዲሞክራሲያዊም ባልሆነበት ሁኔታ “ለምንድነው የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች በብዛት በሚኖሩበት አገር ሥልጣን ተጋርተው በሰላም ከመኖር ይልቅ በብሔር እየተደራጁ የራሳቸውን ብሔር ማስቀደም የሚፈልጉት?” ብለህ መጠየቅህ ይገርማል። በጉልበት በሚኖርበት አገር፣ ጉልበቱ ካለህ፣ ለራስህ ሰፊና ለም ክልልና የፈላጭ ቆራጭ ሥልጣን ይኑረኝ ማለቱ የሚጠበቅ ነው።

    ከጠቃቀስሀቸው አገራት ውስጥ የዓለም ብሄር ብሔረሰቦች የሚኖሩባት አሜሪካ ለምን በሰላም እንደምትኖር አልነገርኸንም። ለአያሌ ዘመናት ሲጋደሉ የነበሩ ብዙ ጫካ የገቡ ዜጎች በነበሯት ደቡብ አፍሪቃ፣ ኔልሰን ማንዴላ ከእስር ቤት በ1984 ዓ።ም. ወጥተው ከፕሬዚደንት ደክለርክ ጋር ተባብረው ፣ 26 ፓርቲዎችን አግባብተው፣ የሽግግር መንግሥት በጋራ አቋቁመው፣ በ1986 ዓ.ም. ዲሞክራሲያዊት ፌደራል ደቡብ አፍሪቃን ባንድ ሙከራ ብቻ፣ በሁለት ዓመት የአገር ወዳድ የሽግግር ዝግጅት፣ እንዳዋለዱ ለኢትዮጵያም ሊበጅ የሚችል ስኬት መሆኑም አልታየህም ?

    የብዙሀን ብሔሮች አገር መሆናችን ችግር የለውም። ችግራችን ተማርን የሚሉ ካድሬ-ነጋዴዎች ጎሣን በመመርኮዝ ለግል ጥቅም መሰለፋቸውና አገር ማተራመሳቸው ነው። ሀቀኛ ዲሞክራሲያዊ ፌደራል ሥርዓት ለመፍጠር ፈረንጅ መጋበዝ ወይም የፈረንጅ ጥናት ማቀንቀንም አያሻም። ደቡብ አፍሪቃውያን አንድም የተሳካላቸው አማካሪ ፈረንጅ አንፈልግም በማለታቸው ነው። እንደ ድሮው ተስማምተን ለመኖር፣ ክልልም አያሻንም፣ ክልል ለከብቶች ማገጃ ቢሆን ትክክል ነው። አሜሪካ፣ ጀርመን፣ እንግሊዝ መቼ ክልል አላቸው? ያላቸው ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ብቻ ነው። የዛሬው ችግራችን ምንጭ ሕግ መንግሥታቸን ለውጥ ያስፈልገዋል። ለውጡም በጥቂት የጎሣ አፈ-ጮሌዎች ሳይሆን በሙሉ ሕዝባችን ሀቀኛ ተወካዮች ስምምነት መሠራት አለበት ።

    የጎሣ ካድሬ-ነጋዴዎች ብዙ ጊዜ የሚያነሱት ጫጫታ የምኒልክን ኢትዮጵያን አንድ የማድረጉ ጦርነት ነው። ጣሊያን በጋሪባልዲ ቀይ ሽሚዝ ለባሾች እየደማች መሰባሰቧ፣ ጀርመን በቢስማርክ የብረት ክንድ መሰባሰቧን፣ አሜሪካ ለልዕለ ኃያልነት የበቃችው እኣአ ከ1861 እስከ 1865 ደም እንደጎርፉ በወረደበት የርስ በርስ ጦርነት መሆኑን፣ ደንቆሮ ካድሬዎች ለምን ምኒልክ የፈንጠዝያ ግብዣ አድርገው ኢትዮጵያን አላሰባሰቡም የሚሉ ይመስላል። ታዲያ አስተዋዮች አውሮጳውያንና አሜሪካውያን አንድነት መሥራች አባቶችን ያከብራሉ። ሊንኮልን በአሜሪካ፣ ቢስማርክ በጀርመን፣ ጋሪባልዲም በጣሊያን የተከበሩ ናቸው። ምኒልክ ከማሰባሰባቸው ሌላ፣ የአድዋ ድል ባለቤት ናቸው፣ የባርነት ሥርዓትን ያስቆሙ ናቸው፣ የዘመናዊት ኢትዮጵያ ያበሰበስነው ባቡር፣ መብራት፣ ትምሕርት፣ የቧንቧ ውሀ፣ ጤና አጠባበቅና የሆቴል ሥራና ዘመናዊ መንግሥታዊ ሥር ዓትም ያስጀመሩ ብሩህና አንጀታም ንጉሥ ነበሩ። በምኒልክ አኳያ ያለው ስሕተታችን፣ በሕገ መንግሥቱ ላይ እንደገጠመን፣ ለራሳችንም የሚጠቅመውን መለየትና ማስተዋል አለመቻል ነው።

    እንዲህም ሆኖ፣ ለአግረራችን በቁጭትና በስሜት ከምትጥስፈው በመነሳት፣ ከማከብራቸው ወገኖቼ አንዱ መሆንህን እንድታውቅልኝ እፈልጋለሁ።

  2. አንድነት- እንድ ነገር እርግጠኛ ሆነህ ከመናገርህ በፊት ትንሽም ቢሆን የቤት ስራ መስራት ያለብህ ይመስለኛል። እንተ አላነበብክም ማለት እኔ ስለኢትዮጵያ ዋና ዋና ችግሮች ምንም አላልኩም ማለት አይደለም። እስኪ ይህንን አንብብ

    https://www.linkedin.com/posts/zehabesha_%E1%8B%A8%E1%8B%9B%E1%88%AC%E1%8B%8B-%E1%8A%A2%E1%89%B5%E1%8B%AE%E1%8C%B5%E1%8B%AB-%E1%89%B5%E1%88%8D%E1%89%81-%E1%89%BD%E1%8C%8D%E1%88%AD%E1%88%9D%E1%8A%95%E1%8B%B5%E1%8A%90%E1%8B%8D-%E1%8B%98-%E1%88%90%E1%89%A0%E1%88%BB-ethiopian-activity-7160074645323358208-6vLv

  3. ወንድም ኤፍሬም፦
    የቤት ሥራ መሥራቱን የኖርሁበት ስለሆነ አልፈራውም። ግን የቤት ሥራ ሲሰጥ በጥንቃቄ ነው። እኔ አንተ ስለ ኢትዮጵያ አልጻፍህም አላልሁም። ያልሁት ሕገ መንግሥቱን በጥንቃቄ አንብበው ነው። በጥንቃቄ ብታነብበው ኖሮ፣ ” በህወሓት የተመሩት የብሔር ኃይሎች በ1983 ዓም ደርግን አሸንፈው የኢትዮጵያን የፖለቲካ ሥልጣን ከተቆጣጠሩ በኋላ በጻፉት ህገ መንግስት ውስጥ ብሔር ብሔረሰቦችን የአገር ሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤት አድርገዋቸዋል። ” አትልም ነበር። በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 8 ተወናብደው፣ ሁላችንንም ቢበዛ የዘጠኝ ጎሣ ተገዥ፣ በተግባር ግን የአንድ ጦረኛና ጠባብ ጎሣ ተገዢ ያደረገውን ሕገ መንግሥት ብሔር ብሔረሰቦችን የሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤት አደረገ ብሎ በተለይ ምሁር ማስተማሩ ከፍተኛ ግድፈት ነው። የሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤት ከሆንን፣ ወላይታና ጉራጌ ለምን ክልል ይኑረን አሉ ?

    ሕገ መንግሥቱን ሕወሀትና ኦነግ አርቅቀው ያወጁልን፣ ኢትዮጵያን ለመታደግ ሳይሆን፣ ለመግዛት ስለነበር፣ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ የዲሞክራሲ ሽታ የለበትም። አገር ወዳድ አርበኞች ሕገ መንግሥት አርቅቀው መንግሥት ሲመሠርቱማ፣ ከእሥር ቤት በወጣ በነጋታው ዲሞክራሲያዊት ፌደራል ደቡብ አፍሪቃን የመሠረቱትን ኔልሰን ማንዴላን አይተናል። መለስ፣ ሌንጮና አቢይ ያ የማንዴላ ወርቃማ ዕድል ነበራቸው፤ ግን አልፈለጉትም። የተፈጥሮ ጉዳይ ሆነና፣ በጭፍን ያረቀቁልን ሕገ መንግሥት ለዛሬው አገር አቀፍ ውድቀት አበቃን። ሕገ መንግሥቱ ይህን ውድቀት እንዴት እንዳመጣብን እንድታየው ነው በጥንቃቄ አንብብ ያልሁህ ። በጥንቃቄ ደግሞ አላነበብኸውም።

    ላይ ከጠቀስሁት አስተያየትህ ጋር ቢቆረቁረኝም ያላነሳሁት፣ ግን የተሳሳተ ግንዛቤ ያለበት ሌላ አስተያየት አለ። እሱም ” …. አንዳንድ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ሉዓላዊ ናችሁ ወይም ‘ነፃ ወጣችሁ’ በተባሉ ማግስት ነፃነት ፍለጋ ጠመንጃ እያነገቡ ጫካ ገብተዋል። ህወሓት/ኢህአዴግ የገነባው የብሔር ፖለቲካ ሥርዓት በየብሔሩ (በተለይ በትላልቆቹ ብሔሮች) ልህቃን ጭንቅላት ውስጥ የፖለቲካ ሥልጣን እጃችን ውስጥ ከገባ ሁሉም ነገር የኛ ነው የሚል እምነት በመፍጠሩ፣ ዛሬ የኢትዮጵያን ህዝብ ሠላም የነሳው ኃይል አለኝ የሚሉ ብሔሮች አራት ኪሎን ለመቆጣጠር እዚህም እዚያም የሚጭሩት የጦርነት አሳት ነው።” ይላል።

    እዚህ ላይ ሊገዙን የተነሱ “ነፃ ወጣችሁ ” ስላሉ ብቻ እውነት ባለመሆኑ ምሁራን ሊቀበሉት አይገባም። ታዲያ ምሁርነቱ ለመቼ ነው ? በተጨማሪ ከ1983 ዓ.ም. ጀምሮ የገዙን መጀመሪያ ሕወሀት ሲሆን፣ ትንሽ የሚባል ብሔር ነው። ቀጣዩ የዛሬው ገዢ ኦሮሞ ነው፣ እሱ ትልቅ ከሚባሉት አንዱ ነው። ታዲያ ኦሮሞ እየገዛ ስለሆነ ነፃነት ፍለጋ ጫካ አልገባም። እየገዛ ሳለ ለምን ጫካ ይገባል ?

    ምናልባት “… (በተለይ በትላልቆቹ ብሔሮች) ልህቃን ጭንቅላት ውስጥ የፖለቲካ ሥልጣን እጃችን ውስጥ ከገባ ሁሉም ነገር የኛ ነው የሚል እምነት በመፍጠሩ፣ ዛሬ የኢትዮጵያን ህዝብ ሠላም የነሳው ኃይል አለኝ የሚሉ ብሔሮች አራት ኪሎን ለመቆጣጠር እዚህም እዚያም የሚጭሩት የጦርነት አሳት ነው።” ያልኸው ኦሮሞንና አማራን ለመውቀስ ይመስላል። ኦሮሞን ሥልጣን የሕዝብ ነው ብሎ ያመነ በመምሰል፣ ዲሞክራሲያዊ ሕገ መንግሥት አርቅቄያለሁ ማለቱ ተረስቶ ለምን ሥልጣን ከእጃችን የወጣል ብሎም እየገዛ ሳለ ለምን ጫካ ገባ ለማለት፣ አማራን ደግሞ ሥልጣን ፍለጋ ጦርነት መፍጠሩን ለመጠቆም ይመስላል።

    አማራ ምን ጊዜም ሥልጣን ብቻውን የያዘበት ወቅት የለም። የመንግሥት የሥራ ቋንቋ አማርኛ ስለሆነ፣ አማርኛን የሥራ ቋንቋ ያደረገ መንግሥት ሁሉ አማራ ነው ከተባለ፣ የአፄ ዮሐንስም መንግሥት አማራ ነበር ሊባል ነው። ጅንሆይም እኮ የደጃች ወልደሚካኤል ጊዲሣ የልጅ ልጅ ናቸው። በዚያ ላይ የምኒልክ የጦር መሪዎች ጎበና አባ ዳጮና አባ መላም አማራ ነበሩ ሊባል ነው። የዛሬዎቹም ዶር አቢይ አሕመድና ሽመልስ አብዲሳ አማሮች ናቸው ሊባል ነው። የፈረንሳይኛና የእንግሊዝኛ የሥራ ቋንቋም ያላቸው መንግሥታትም ፈረንሳይ ወይም እንግሊዝ ናቸው ማለቱ የጠባብ ራስ ግንዛቤ ነው።

    ባጭሩ አማራ እንደ ሌላው ኢትዮጵያዊ ፣ ክፉና ደጉን እኩል ከመጋራት ውጭና በተለይ የውጭ ወራሪ፣ የሽፍታና የባንዳ ኢላማ ከመሆንና ከሌሎች ወድሞቹ ኢትዮጵያውያን ጋር ደሙን አፍስሶ አጥንቱን ከስክሶ የኢትዮጵያን አንድነትና ነፃነት ከማስጠበቅ ውጭ ያተረፈው አንድም ነገር የለም። የአማራን ገጠር ዛሬም ዘወር ዘወር ብሎ ማየት ተገኘ ተብሎ በወሬ ስልቻዎች ስለተወራው ትርፍ ተጨባጭ ምስክር ይታያል። በአማራነቱ ሊያተርፍ የፈለገበት የታሪክ ወቅትም የለም። ዛሬም፣ ተደጋግሞ እንደምንሰማውና ወንድም ኢፍሬም ማዴቦም እንዳለው፣ ሥልጣን ካልያዝሁ ጫካ እገባለሁ ሲባል አልሰማንም። የሰነፍ ልሂቃን ፈጠራ ነው። በ21ኛው ክፍለ ዘመን ላይ፣ እንደ ፊውዳሉ ሥርዓቱ ፣ ሥልጣን ለብቻ መያዙም ለዛሬይቱ ኢትዮጵያ ይመጥናል ብሎ አማራ አያምንም። ስለሆነም፣ ወንድም ኤፍሬም በትላልቅ ብሔሮች አኳያ የሰጠኸው የጅምላ አስተያየትም አማራ ለኢትዮጵያ አንድነትና ነፃነት ምንጊዜም ሳያወላልውል ላፈሰሰው ደምና አጥንት አይመጥንም። ምንም ተባለ ምን፣ አማራ ምን ጊዜም፣ እንደ ሌሎች ኢትዮጵያውያን ወንድሞቹ፣ አማራነቱንና ኢትዮጵያዊነቱን አዋህዶ መሄዱን አያቆምም።

    ወንድም ኤፍሬም፣ ለኢትዮጵያና ለሁሉም ምዝብር ዜጎቿ የምታደርገው በጎ ጥረትህ እንዲቀጥል እመኛለሁ።

  4. የህገ መንግስቱን ምዕራፍ ሁለት፣አንቀጽ 8 ንዑስ አንቀጽ 1 አንብብና ምን እንደሚል ንገረኝ . . . . እኔ ሳነበው እንዲህ ይላል
    “የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ብሔረሰቦች፣ ህዝቦች የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤቶች ናቸው”
    የአማራ ሃይሎች ጦርነት ውስጥ የገቡት ስልጣን ፍለጋ ነው የሚል አልወጣኝም፣ በአማራ ክልል የሚደረገው ጦርነት የህልውና ጦርነት ነው፣ ደሞም አማራ ላይ ጦርነት መጣበት እንጂ አማራ ጦርነት አልጀመረም። ይህንን እውነት ኢትዮጵያ ውስጥ ሆኜም ተናግርያለሁ። ያላልኩትን አትበል።

  5. ወንድም ኤፍሬም ማዴቦ፦

    “…. ዛሬ የኢትዮጵያን ህዝብ ሠላም የነሳው ኃይል አለኝ የሚሉ ብሔሮች አራት ኪሎን ለመቆጣጠር እዚህም እዚያም የሚጭሩት የጦርነት አሳት ነው።” ያልኸው በእርግጥ አማራን በቀጥታ አይጠቅስም። ግን ይጠቁማል።

    የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 8 ንዑስ አንቀጽ 1 ብቻውን ሳይሆን “የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ አባላት” ከተባሉት በአንቀጽ 47 ንዑስ አንቀጽ 1 ከተዘረዘሩትና ቢበዛ 9 ጎሣ ብቻ ከነገሠባቸው 9 ክልሎች ጋር መነበብ አለበት ። ይህን መቸ አጣኸው፣ ወንድሜ? የመብትና የሥልጣን ጉዳይ ባይቸግራቸው የወላይታና ጉራጌ ወገኖቻችን እኛም ክልል እንሁን ብለው እስክ መደብደብ፣ ሞትና መታሠር ይደርሱ ነበር ? ሲጀመር ጀምሮ፣ አንቀጽ 8 እንደሚለው፣ ሁሉም ብሔሮች ሉዓላዊ ሥልጣን ከነበራቸው፣ ዛሬ በደቡብ ኢትዮጵያ፣ ሲዳማ ክልልም ጭምር፣ ለምን አዳዲስ ክልሎች በቅርቡ ተፈጠሩ ?

    ወንድም ኢፍሬም፣ ጥሩ ኢትዮጵያዊ እንደሆንህ አልጠራጠርም። እውነቱ ግን ይኸው ነው። አንቀጽ 8 እውነት ቢሆን ኖሮ፣ ዛሬ ኢትዮጵያ ሰላም ትሆን ነበር። በመሠረቱ ግን ኢትዮጵያን ለ 83 ጎሣ ወሰን ለያይቶ ማከፋፈል አይቻልም። አሜሪካ የዓለም ጎሣዎች ስብስብ ናት ? አሜሪካን በጎሣ መከፋፈል ይቻላል? የተቀላቀለ፣ የተጋባ፣ የተዛመድ ሕዝብ ያላትን ኢትዮጵያንም መከፋፈል አይቻልም። ሕወሀትና ኦነግ ይህን አሳምረው ያውቃሉ። አንቀጽ 8 ከአንቀጽ 47 ራቅ ተብላ የተሽጎጠችው ለብዝበዛ የተቀረጸች ማታለያ መሣሪያ ስለሆነች ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ የዋህና ሹም አማኝ በመሆኑ፣ እናታልለው ተብሎ ነው። ግን ማታለል አያዛልቅም። አላዛለቀም !!!!

    ዋናው የሕወሀትና ኦነግ ዓላማ ሰፋፊና ለም አገር ትግሬ ነው ለማለት፣ ሌላውን ለምና ሰፊ አገር ኦሮሞ ነው ብለው ጊዜያዊ ኃይላቸውን መከታ አድርገው ተከፋፍለው፣ የፊውዳል ቅሪት የሆነ ደንቆሮ አስተያየት ላይ ተመሥርተው ረግጠው መግዛትና መዝረፍ ነው የፈለጉት ። በዚህ ዘዴ፣ ሕወሀት ብዙ ቢሊዮኔሮች አፍርታለች ይባላል ። ዛሬ የኦነግ ተከታዮች ያን የእኩይ አስተማሪያቸውን የሕወሀትን ሰይጣናው ልምድ እየተከተሉ እያመሱን ነው። ይህን ኋላ ቀር፣ ጎጠኛና ጠባብ አመለካከት ትተው እንደ ኔልሰን ማንዴላ ሀቀኛ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ኢትዮጵያን ቢመሠርቱማ እነሱ ብቻ ሳይሆኑ ሙሉ ኢትዮጵያዊ ወገናችን ሀብታምና አገራችንም ኃያል ልትሆን እንደምትችል አለማወቃቸው ሳይሆን፣ የሌላ ጎሣ ዕድገት ያምማቸዋል።
    አይዋጥላቸውም። ሁላችንም አንድላይ ብንሰራማ ሰፊ አገር፣ ብዙ የውሀ ሀብት፣ በሚሊዮን የሚቆጠር ጠንካራ ወጣት፣ ሰፊ የማዕድን ሀብት ስላለን ነገ ከማንም አገር እኩል ወይም መብለጥ እንችል ነበር። በተፈጥሮ አቅመ ደካማ፣ ምቀኛ፣ ጠባብና ደንቆሮ ፍጡር ግን በእግሩ ቆሞ ስለማያውቅ፣ ከአፍንጫው አሳልፎ ማየት አይችልም። ለዚህ ነው ሀቀኛ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ኢትዮጵያን ለማክበርና ለማስከበር አሁንም መታገል ያለባቸው።

    አሁንም፣ ተሳትፎህ እንዲቀጥል እመኛለሁ።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

191154
Previous Story

የሸዋ እዝ ድል በመሃል አምባ፣ ናስና ዘንደጉር| ኦሮሚያ ትልቅ ማዕበል ሊነሳ ነው | ከ4ኪሎው ዝግ ስብሰባ ሾልኮ የወጣ | እስክድርም ዘመነ ካሴም ስለ ድርድሩ |

Abiy Ahmed the killer 4
Next Story

የቤተመንግስቱ ሚስጢራዊ ስብሰባ፥ የፋኖ ድሎች በጎጃምና ጎንደር፥ የከሸፈው የህወሀት ጥቃት በጠለምት፥ ጌታቸው ረዳና አብይ አህመድ

Latest from Blog

የፀረ ግፍ አገዛዝ ታጋድሎ እና መልካምና ፈታኝ ሁኔታዎች

June 23, 2024 ጠገናው ጎሹ በአጭር አገላለፅ መልካም ሁኔታ (opportunity)  አንድን  ጉዳይ በአወንታዊነት ወደ ፊት ለማስኬድና ለማሳካት የሚያስችሉ አመች እድሎችን (አጋጣሚዎችን) የሚገልፅ ፅንሰ  ሃሳብ ሲሆን ፈታኝ ሁኔታ (challenge)  ደግሞ በመልካም ሁኔታዎች (አጋጣሚዎች) ላይ  አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ ወይም ሊያሳድሩ የሚችሉ

ደርና ጎጃም እልፍ  ጥይት ከሚጮህ፣አዲስ አበባ የሚባርቅ አንድ ጥይት የብልፅግና መንግሥትን ያንቀጠቅጠዋል!

ሚሊዮን ዘአማኑኤል (ኢት-ኢኮኖሚ /ET- ECONOMY) ይድረስ ለአማራ ፋኖ እዝ፤ጥናታዊ የአማራ ህዝብ የፖለቲካ፣የኢኮኖሚና ማህበራዊ ጉዳይ ዳሰሳ   የፖለቲካ ዳሰሳ ፋኖ ‹‹እሣት ሲያንቀላፋ፣ ገለባ ጎበኘው!!! እሣት ሲያንቀላፋ፣ ገለባ ጎበኘው!!! ፋኖ ሲያንቀላፋ፣ ገለባ ጎበኘው!!!››   ጎንደርና ጎጃም እልፍ

ሱሌማን አብደላን ፍለጋ..

ሱሌማን አብደላን ፍለጋ.. ዲፕሎማቱ #ሱሌማን አብደላ አደጋ ላይ ነው! የአንባሳደሮቹ ወጥመድ ወይስ? “የብሔር ፌደራሊዝምን እደግፋለሁ” ሱሌማን አብደላ | “አዲስ አበባ/መተከል የአማራ ዕርስት ነው እና ወደ ባለቤቱ መመለስ አለበት” Suleiman Abdella

‘ሕይወቴ አደጋ ላይ ነው’ የሚሉት የ‘ጦርነት ይቁም’ ሰልፍ አስተባባሪው ፖለቲከኛ ዳንኤል ሺበሺ ተሰደዱ

24 ሰኔ 2024 በአገሪቱ የሚካሄዱ ግጭቶች እንዲያበቁ እና ለችግሮች ሰላማዊ መፍትሄ ለመጠየቅ በኅዳር ወር ማብቂያ ላይ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ካስተባበሩት ፖለቲከኞች መካከል አንዱ የነበሩት አቶ ዳንኤል ሺበሺ ‘ሕይወቴ አደጋ ላይ ነው በማለት’

አዲስአበባ ተኩስ ተከፈተ “ለመደራደር ዝግጁ ነን” አረጋ ከበደ | አብይ አደገኛውን ካርድ መዘዙ | አዲሱ አዋጅና የቀረበበት ተቃውሞ “የሞተም ሰው ንብረት ይጣራል | ጌታቸው ያጋለጠው ጸብ

አዲስአበባ ተኩስ ተከፈተ “ለመደራደር ዝግጁ ነን” አረጋ ከበደ\  አዲሱ አዋጅና የቀረበበት ተቃውሞ “የሞተም ሰው ንብረት ይጣራል አብይ አደገኛውን ካርድ መዘዙ ጌታቸው ያጋለጠው ጸብ
Go toTop