June 2, 2024
ጠገናው ጎሹ
ይህንን ግልፅና ቀጥተኛ አስተያየቴን ድርድር የሚባል ነገር ጨርሶ አያስፈልግም እንደ ማለት አድርገው የሚያላዝኑ ካድሬዎችና የአድርባይነት ልክፍተኞች ቢኖሩ ፈፅሞ አይገርመኝም።
ለማነኛውም የአስተያየቴ መነሻና ማጠንጠኛ ሰላማዊ መፍትሄ (ድርድር) አያስፈልግም ሳይሆን በዘመን ጠገብና እጅግ አስከፊ በሆነ ፖለቲካ ወለድ ወንጀል የተጨማለቀውንና ይበልጥ እየተጨማለቀ በመሄድ ላይ ያለውን የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ሥርዓት እንደ ሥርዓት የሚቀበል ድርድር ይበልጥ አስከፊ የሆነ የመከራና የውርደት ዘመንን የሚያራዝም ነውና ከዚህ ክፉ አዙሪት ብቸኛው መውጫ መንገድ ማን ምን አጠፋ? ማን ንፁህ ወይም ወንጀለኛ ነው? የሚለው በሽግግር ፍትህ የሚታይ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ገዥዎችን ጨሞሮ የሚያሳትፍ የሥርዓት ለውጥ ድርድር ሂደትና ውጤት ነው የሚል ነው ። ከዚህ ያነሰ የድርድር ሂደትና ውጤት ከምር በሆነ ፀፀት፣ ገንቢ በሆነ ቁጭት፣ ብሩህ በሆነ ባለራዕይነት ፣ ፅዕኑ በሆነ የመከባበርና የመቻቻል እኛነት ፣ ወዘተ ወደ ፊት ለመገስገስ ፈፅሞ አያስችለንም።
ሲፈልጉ እየተስማሙ እና ሲያሻቸው ደግሞ ልክ የሌለው የሥልጣን አፍቃሪነታቸው በሚያስገኝላቸው የፍላጎትና የጥቅም ግብስብስ ህሊናቸውን እየሳቱ በሚያካሂዱት እጅግ አሰቃቂ ጦርነትና የመንደር ለመንደር ግጭት አገር ምድሩን በንፁሃን የደም ጎርፍና የቁም ሰቆቃ እያጥለቀለቁ ህግ የማስከበርና አገርን የማዳን ታላቅና ታሪካዊ ተልእኮ እየተወጡ እንደሆነ አድርገው ሊያሳምኑን ሲሞክሩ ህሊናቸውን ፈፅሞ የማይኮሰኩሳቸው ገዥ ቡድኖች ህልውና፣ ነፃነት፣ ፍትህ፣ እኩልነት፣ ሰላምና የጋራ እድገት የሚረጋገጥበት የሥርዓት ለውጥን ተገደው ሳይሆን ወደው ይቀበላሉ ብሎ ማመን እውነትን አዛብቶ የመረዳትና ራስን የማታለል ችግር (the problem of delusion and self-deception) እንጅ ሌላ ሊሆን አይችልም።
ራሳችንን ማታለል ካልፈለግን በስተቀር ለመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ የሚደረገው ሁለገብ ትግል ቆሞ እነርሱ (እኩያን ገዥዎች) በሚያዘጋጁትና በሚቆጣጠሩት ቅድመ ሁኔታ መሠረት “የርካሽ ምክክርና ድርድር ተውኔታቸው” ተሳታፊ ይሆን ዘንድ ጥሪ በማድረግ በመከረኛው ህዝብ ላይ እጅግ የበሰበሰና የከረፋ የፖለቲካ ቅርሻታቸውን እያቀረሹበት ቀጥለዋል። ይህንን ዘመን ጠገብ የሆነና አገርን ለመግለፅ በሚያስቸግር ሁኔታ ምድረ ሲኦል ያደረገ የጎሳ አጥንት ስሌት የፖለቲካ ሥርዓት እንደ ሥርዓት እንዲቀጥል በሚፈቅድ “ድርድር” ለመሳተፍ ፈቃደኛ መሆን ለነፃነትና ለፍትህ ሲሉ በተዋደቁና በወደቁ ወገኖች ደምና አፅም መሳለቅ ነው የሚሆነው።
እናም የሁሉም ዜጎቿ ነፃነት፣ ፍትህ፧ ሰላምና እድገት የሚረጋገጥባትን አገር ከምር እየፈለግን ከሆነ እጅግ ደምሳሳ ከሆነና የአርበኝነት ወኔ ከሚጎድለው የድርድርና የሰላም ስብከት ወጥተን ከሦስት አሥርተ ዓመታት በላይ ሥር የሰደደውንና በትውልድ ላይ ሁለንተናዊ (ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ፣ ሞራላዊ፣ ሥነ ልቦናዊ፣ መንፈሳዊ ፣ ወዘተ) ቀውስ ያስከተለውን ኢህአዴጋዊ/ብልፅግናዊ ሥርዓተ ፖለቲካ መሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ የሥርዓት ለውጥን መሠረት በሚያደርግ የድርድር ይዘትና አቀራረብ እውን ሊያስደርገን የሚችልን የትግል ግንባር ይበልጥ ማጠናከር ይኖርብናል።
አዎ ከሩብ ምዕተ ዓመት በላይ የዘለቀውን የእኩያን ህወሃት የፖለቲካ ልሂቃን ተብየዎች የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ መርዝ እየተጋቱ በአሻንጉሊትነት ሲያገለግሉ የኖሩት የኦሮሞ የፖለቲካ ልሂቃን ተብየዎች አገልጋይነትና ወራዳነት ከማይሰለቻቸው ብአዴኖች ጋር በመተባበር የቤተ መንግሥቱን ፖለቲካ በጠርናፊነት በመቆጣጠር ይኸውና ከስድስት ዓመታት በላይ አገርን ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ ሁኔታ ምድረ ሲኦል እያደረጉ ቀጥለዋል። በእኩያን የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኛ ገዥ ቡድኖች እና በህዝብ መካከል ያለው ዘመን ጠገብና እጅግ አስከፊ ልዩነት ከሥርዓት ለውጥ መለስ ባሉ የድርድር አጀንዳዎች ይፈታል ብሎ ማመንና መቀበል የባርነት ቀንበር ቀጣይነትን ከመቀበል የተለየ ትርጉምና ውጤት ፈፅሞ የለውም ።
አጠቃላይና አጭር በሆነ አገላለፅ ድርድር (negotiation) በባለ ጉዳዮች መካከል ሊነሳ የሚችልን የፍላጎት ወይም የጥቅም ግጭት ከተቻለ ከቁጥጥር ውጭ ሆኖ ጉዳት ከማድረሱ በፊት በተገቢና በወቅታዊ የጋራ መፍትሄ የማስቀረት እና ይህ ሳይሳካ በመቅረቱ ከቁጥጥር ውጭ ሆኖ ጉዳት በማድረስ ላይ ያለን የፍላጎትና የጥቅም ግጭት ደግሞ በእጅጉ አስከፊና መልሶ ለማገገምና ለመገንባት የሚያስቸግር ጉዳት እንደሚያስከትል በመረዳት ተገቢውንና ዘላቂውን የጋራ መፍትሄ ለማበጀት የሚደረግ እና እጅግ ከፍተኛ ሃላፊነትንና ተጠያቂነትን ለመሸከም ፈቃደኝነትንና ዝግጁነትን የሚጠይቅ ሂደትንና ተግባርን የሚገልፅ ፅንሰ ሃሳብ ነው።
ከዘመን ጠገቡ ተሞክሮና ከዘመን ጉዞ ጋር የተሻለ ከመሆን ይልቅ እንኳንስ ኢትዮጵያዊነትን ሰብአዊ ፍጡርነትን በእጅጉ በሚፈታተን ሁኔታ ውስጥ ለምንገኝበት መሪርና ግዙፍ እኛነት ዋነኛ ተጠያቂዎች የሆኑት ገዥ ቡድኖችና ግብረ በላዎቻቸው መሪ ተዋናዮች በሚሆኑበት የጠረጴዛ ዙሪያ ታዳሚ በመሆን በፖለቲካ ወለድ ወንጀል የበሰበሰውንና የከረፋውን ሥርዓት ወደ ጤናማ ሥርዓት መለወጥ ይቻላል ብሎ ከማመንና ከመቀበል የከፋ ድንቁርና እና ከመከራና ከውርደት ጋር የመለማመድ ክፉ ልክፍት ፈፅሞ የለም።
የጦርነትን አስከፊነትና የሰላምን ዋጋ ለመገንዘብ እንኳንስ እንደ እኛ አይነት ግማሽ ምእተ ዓመት ሙሉ በመስማት ወይም በማንበብ ወይም ካዳር ሆኖ በመታዘብ ሳይሆን በመኖር ለሚያውቀው ህዝብ ለማነኛውም ባለ ጤናማ ህሊና ሰው ከቶ የሚከብድ አይደለም።
መከረኛው የአገሬ ህዝብ የፖለቲካ ወለድ መከራና ውርደት ዶፍ ሰለባ ከሆነበት መሪር እውነታ ለመገላገል ከጦርነት ይልቅ ሰላማዊ መፍትሄ (እውነተኛ ድርድርና ምክክር) ቢሰምርለት ኖሮ ምንኛ በታደለ ነበር። ይህ ግን በፖለቲካ ሥልጣን ዙፋን ላይ የሚፈራረቁ ገዥ ቡድኖች ፖለቲካን የብልግናቸውና ዘርፎ የመኖር (መኖር ከተባለ) ዋስትና መሣሪያቸው በማድረጋቸው እና ይኸው ዋስትናቸው ሥጋት ላይ የወደቀ በመሰላቸው ቁጥር በጨካኝ ሰይፋቸው አገርን በንፁሃን ደምና የቁም ሰቆቃ በሚያጥለቀልቁበት መሪር እውነታ ውስጥ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግርንና ምሥረታን ጥያቄ መሠረት የማያደርግ ድርድር ድርድር ሳይሆን አሳዛኝ የውድቀት አዙሪት ነው የሚሆነው።
እናም ህሊናዎቻቸውና እጆቻቸው በንፁሃን ደምና የቁም ሰቆቃ በተጨማለቁ እኩያን ገዥ ቡድኖች ከርሰ መቃብር ላይ ለህዝብ፣ ከህዝብና በህዝብ የሆነን ሥርዓት እውን የሚያደርግ የድርድርና የምክክር ይዘትና አቀራረብ እውን ለማድረግ ከተሳነን ለመከራውና ለውርደቱ መቀጠል ተጠያቂዎች እንደ ዜጋ ፣ እንደ ድርጅት ፣እንደ ማህበረሰብ ወይም እንደ ህዝብ እኛው ጭምር እንጅ እኩይነታቸው ግልፅና ግልፅ የሆነው እነርሱ ብቻ አይሆኑም።
መቸም እኩያን ገዥዎች ካለማመዱን እጅግ አስቀያሚ ድክመቶቻችን አንዱ የገዛ ራሳችንን መሪር ሃቅ መጋፈጥ ሲያቅተን በስንካላ ሰበብ ዙሪያ መዞሩ ስለሚቀናን ነው እንጅ የእውነተኛ ድርድርን ምንነት፣ ለምንነትና እንዴትነት በህወሃት ጠርናፊነት ለሩብ ምዕተ ዓመት በዘለቀው የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ሥርዓት እና በቅርቡ ስድስተኛ ዓመቱን ባስቆጠረውና የዚሁ ሥርዓት ውላጅ በሆነው የኦህዴድ/የኦሮሙማ ጠርናፊነት እና አረጋ ከበደን በመሰሉ ወራዳ ግለሰቦች አሽከርነት ለመግለፅ በሚያስቸግር የመከራና የውርደት ዶፍ ህይወቱ ከተመሰቃቀለበትና እየተመሰቃቀለበት ካለው የኢትዮጵያ ህዝብ መሪር እውነታ አንፃር ተረድተን መሠረታዊ የሥርዓት ለውጥን እውን ለማድረግ በሚያስችል ሁኔታ ለማስኬድ ካልቻልን በእጅጉ አስከፊ እየሆነ ከመጣው ፖለቲካ ወለድ ሁለንተናዊ የቀውስና የመከራ አዙሪት ፈፅሞ መውጫ የለንም።
በመንበረ ሥልጣን ላይ በሚፈራረቁ እኩያን ገዥ ቡድኖች ምክንያት በአስከፊ ሁኔታ ሥር የሰደደውንና በትውልድ የተጋድሎ ቅብብሎሽ ተጠብቃና ተከብራ የኖረችን አገር ህልውና ከፍተኛ አደጋ ላይ እንዲወድቅ እያደረገ ያለውን የፖለቲካ ሥርዓት እንደ ሥርዓት አስወግዶ ለሁሉም ዜጎች የሚበጅ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን ከማድረግ ይልቅ ጠቅላይ ሚኒስትርን ጨምሮ የተወሰኑ ባለሥልጣናትንና ካድሬዎችን ዒላማ ያደረገ ድርድር ከቆሻሻ ግባና ቆሻሻ ውጣ (garbage in and garbage out) የፖለቲካ ተውኔት ፈፅሞ አያልፍም።
ራሳችንን እየደለልንና ፖለቲካ ወለድ መከራን ይበልጥ እየተለማመድን መቀጠል ካልፈለግን በስተቀር በጊዜ ርዝማኔ ሥር በሰደደ ፣ በእጅጉ በተስፋፋ እና ለማመን በሚያስቸግር ሁኔታ አደገኛ በሆነ ፖለቲካ ወለድ ካንሰር የተመረዘውን (የተበከለውን) ግዙፍና መሪር አገራዊ እውነታ ለመለወጥ በማይችልና በማያስችል (የሥርዓት ለውጥን አምጦ መውለድ በማይችል) ድርድር ዘላቂ ሰላምንና አመርቂ እድገትን እውን አደርጋለሁ ብሎ ራስን ከማታለል የከፋ የፖለቲካ ድንቁርና እና የሞራል ዝቅጠት የለም።
ለዘመናት በዘለቀ የንፁሃን ደም እና የቁም ሰቆቃ ለጨቀዩ ህሊናዎቻቸውና እጆቻቸው ሃላፊነትን ወስደው የመፀፀትና ይቅርታ የመጠየቅ ሰብአዊ፣ ሞራላዊና ፖለቲካዊ ወኔ ጨርሶ የሌላቸው ገዥ ቡድኖችን ሥርዓት በሽግግር ፍትህ አማካኝነት ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማሸጋገር የማይችልና የማያስችል ድርድር “አረጋ ከበደ ለሚባል ታላቅ መሪ” እጅ በመስጠትና የፍርፋሪው ምፅዋተኛ በመሆን ማቆሚያ በሌለው ባርነት ሥር መኖር እንጅ ፈፅሞ ሌላ ሊሆን አይችልም።
እንደ እኛ አይነቱን በጎሳ ደምና አጥንት ስሌት ላይ ተመሥርቶ አገርን ያህል ነገር የንፁሃን ዜጎች ምድረ ሲኦል ያደረገንና እያደረገ የቀጠለን የፖለቲካ ሥርዓት ድርድር ለምን? እንዴት? ለማን? በነማን? መቸ? ከየት ወደ የት? ወዘተ የሚሉ እጅግ መሠረታዊ ጥያቄዎችን እየሸሸን ደምሳሳነት በሚያጠቃው እና ከምኞት በማያልፍ የሰላም ስብከት ወይም ዲስኩር ወይም የትንታኔ ድሪቶ መጠመድ ፖለቲካ ወለድ መከራንና ውርደትን ከማራዘም ያለፈ ፋይዳ አይኖረውም። ህልውና ፣ ነፃነት ነፃነት፣ ፍትህ ፣ እኩልነት፣ ሰላምና የእድገት ግሥጋሴ ለሚረጋገጥበት ሥርዓተ ፖለቲካ የሚደረግን ትክክለኛ ተጋድሎ እንደ የሰላም ፀር በመቁጠር “ትጥቅህን እያስቀመጥህና የጨካኔ ሰይፌን ሃያልነት እያመንክ ባዘጋጀሁልህ የተውኔት አዳራሽ ታድመህ ባላገኝህ አንተን አያርገኝ” ከሚል ፍፁም ባለጌና ጨካኝ ገዥ ቡድን ጋር ምን አይነት ገንቢና ዘላቂ የድርድር ውጤት እንደሚጠበቅ ለመረዳትና ለማስረዳት የሚቻል አይመስለኝም።
የሥርዓት ለውጥን ሊያስከትል የሚችል ድርድር ሲባል ሁሉን ነገር እየደመሰሱ ከዜሮ የመጀመር ጉዳይ ሳይሆን ጎጅውን እያስወገዱና ጠቃሚውን የምሥረታውና የግንባታው አካል እያደረጉ በሽግግር ፍትህ አግባብ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እየመሸጋገር ጉዳይ ነው ።
ይህ ግን ለአያሌ ዓመታት ለንፁሃን ዜጎች የግፍ ግድያና የቁም ሰቆቃ ዋነኛ ተጠያቂ የሆነው የገዥ ቡድን ሥርዓት በሚፈቅደው፣ በሚያዘጋጀው፣ በሚመራው (በሚቆጣጠረው) እና ካልፈለገም በሚያፈርሰው ርካሽና አደገኛ የድርድር ጨዋታ ፈፅሞ ሊሆን አይገባውም።
የድርድር ፅንሰ ሃሳብን እንደ የዘወትር ፀሎት ከመደጋገምና ከመስበክ አልፈን መሬት ላይ ከሆነውና እየሆነ ካለው እጅግ ለመግለፅ የሚያስቸግር የእኩያን ገዥዎች ፖለቲካ ወለድ መከራና ውርደት አንፃር ከምር ካልተረዳነው እና በተባበረ የነፃነትና የፍትህ ተጋድሎ ግቡን እንዲመታ ካላደረግነው የአብይ አህመድና የካምፓኒው (ፓርቲው) እና የግብረ በላዎቹ ወጥመድ ሰለባዎች እንሆንና ተመልሰን ለመነሳት ወደ የማንችልበት የውድቀት አዙሪት የ የመውረዳችን መሪር ሃቅ መቀበል ይኖርብናል ።
በሦስቱ የመንግሥት አካሎች (ህግ አውጭ ተብየው፣ ህግ ተርጓሚ ተብየውና ህግ አስፈፃሚ ተብየው) እና እንዲሁም በገዠው ፓርቲ መካከል ያለው የሥልጣንና የተግባር ድርሻና ድንበር በስም (በወረቀት ላይ) ካልሆነ በስተቀር ፈፅሞ በማይታወቀውበት መሪር እውነታ ውስጥ የፖለቲካ ሥርዓት ለውጥ ሊያስከትል የሚችል ድርድርን እንደ ቅድመ ሁኔታ አለማቅረብ ፈፅሞ ስሜት የሚሰጥ የፖለቲካ አቋምና ቁመና አይደለም።
ለዚህ ነው የአማራ ፋኖ እና ዓላማውንና ግቡን የሚጋሩ የነፃነትና የፍትህ ታጋይ ወገኖች የባለጌ፣ የሸፍጠኛ፣ የሴረኛ፣ የዘራፊና የጨካኝ ገዥ ቡድኖችን ርካሽና አደገኛ የድርድር ተውኔት በፅዕናት መክተውና ብሎም አሸንፈው ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ የድል አበስሪነት ይበቁ ዘንድ ግልፅና አሳማኝ (clear and justifiable) የሆነ የድርድር አቋምንና ቁመናን ከምር ሊወስዱትና ሊያስቡበት የሚገባው።