እንግዳ ታደሰ / ኖርዌይ
ሲፈልግ ሸክፎህ – ሲያሻውም መትሮህ
እንደዘንቢል ጭኖህ-እንደንፍሮ ዘግኖህ
እንደ አጋሰስ ጋልቦህ- እንደ አህያ ገርፎህ
ቀንበር አሸክሞህ – ፉርሽካውን ጭኖህ
ሆድህ ካሸነፈህ – ሰውነትክን ካጣህ
እዛው ማገዶ ሁን – መቸም ፋንድያ ነህ ፡፡
አማራ ነን ብለው አማራውን ለሚያስጨፈጭፉ ብአዴኖች
የት እንደሆነ አላስታውስም ግን አንብቤአለሁ ፡፡ << አማራው እርስ በራሱ የሚጣፋ ፍራክሽን ነው >> የሚል ኃይለ ቃልን የያዘ ቁጭት ወይም ሹፈት ፡፡ ኃይለ ቃሉ ! ለሚቆጩት እራሳቸውን እንዲመረምሩ ፣ ለሚያላግጡበት ደግሞ ፣ሁኔታው ወደ አልተፈለገ ፍጥጫ ወስዶ ! የማን ቤት ለምቶ ! የማን ይጠፋ ? ወደሚል አደጋ ውስጥ እንዳይወስደን እሰጋለሁ ፡፡
በኢትዮጵያዊነት ፍቅርና ማተብ ላደገ ዜጋ ምናልባት አማራነቱን እንዲያውቅ በታሪክ የተገደደበት ዘመን ቢኖር በወያኔ የአገዛዝ ዘመን ብቻ ነው ፡፡ ወያኔ የከፋፍለህ ግዛ የአገዛዝ መዋቅሩን በአገሪቱ ካሰፈነበት ጊዜ ጀምሮ ፣ ኢትዮጵያዊ ነው ዜግነቴ ብሎ ፈርጥሞ የሚናገረውን ዜጋ ! በትምክህተኝነትና በነፍጠኝነት ድሪቶ በማስደረት አንገቱን እንዲደፋ ለማድረግ የተኛበት ጊዜ አንድም ቀን አልነበረም ፡፡ ይህን እኩይ ሥራውን ለማካሄድ የአቶ መለስ መንግሥት ፣ ከቤተ መንግሥቱ ከሚደላ ፍራሽ ይልቅ ፣ የዛፍ ላይ እንቅልፍን መርጧል አሁንም ይመርጣል ፡፡
ኢትዮጵያዊ ነኝ ያለ ዜጋ መታወቂያ እንዳይሰጠው አድርጓል ፡፡ በተለያዩ መንግሥታዊም ሆነ የግል ንግድ እንቅስቃሴ ላይ የዜግነትን መብት የሚያጎናጽፈውን ብሄራዊ መብቱን እንዲያጣ ደንግጓል ፡፡ ይህን የብሄረሰብ ማንነትን የሚያሳይ መታወቂያ የያዘ ዜጋም ቢሆን በነርሱ አጠራር አምሀራ፟ ከሆነ ከመገፍተር አላዳነውም ፡፡ እንዲያውም ክፉ ዘመን ሲመጣ በቀላሉ ተነጥሎ እንዲመታ አድርጎታል ፡፡ በደኖን ፥ ዎተርን ፥ ጉርዳፈርዳን እንዲሁም በቅርቡ በቤኒሻንጉልና ጉሙዝ ክልል እያየን ነው ፡፡ መታወቂያው ላይ ያለው ብሄር- አማራ የሚለው ታፔላ ከሌሎች ወገኖቹ ኢትዮጵያውያን በመልክና በቁመና ባይለይም ወያኔ ሠራሽ በሆነው መታወቂያ ተለይቷል ፡፡ የወያኔ ወንጭፍ ሳያንቀላፋ በየጊዜው እንደ አሜባ ቅርጹን እየለዋወጠ እንደ ተውሳክ አማራውን ማጥቃት ይችላል ፡፡
አማራውን አሳጥቶ ለማስመታት ወያኔ ያልፈነቀለው ድንጋይ የለም ፡፡ ወደ ደቡብ ብንወርድ ፣ አማራና ፍየል እየተረገሙ ይረባሉ የሚል ብሂል ሞቅ ተደርጎ እንዲጮህ አድርጓል ፡፡ወደ ሱማሌ ክልል ብንሄድ ፣ ኢትዮጵያዊውን ሱማሌ የሂሳብ ትምህርት ሲሰጠው ፣ አምስት ፍየል ቢኖርህና ማታ ሲመሻሽ ወደጉሮኗቸው ሶስቱ ብቻ ቢመለሱ ሁለቱን ፍየሎች ማን የበላቸው ይመስልሃል ? ብሎ ሲጠይቅ ተማሪው ነብር ቢሆን መልሱ ተሳስታችኋል ፣ የበላቸው አምሃራ ነው ብሎ ያስተምራል ፡፡ በቅርቡም በዘመነኛው ፓልቶክ ተብሎ በሚጠራው የውይይት መድረክ ፣ እቶን የምትተፋው የገዛ ተጋሩ የትግራይ ሴት ካድሬ የአማራውን ህዝብ ልሂቃን popcorn politician ብላቸዋለች ፡፡ የሚንጣጡ ፈንድሻዎች ! ጧጧ ብቻ በማለት ተሳልቃባችዋለች ፡፡
በቅርቡ ከወደ ትግራይ አንድ አርቆ አሳቢና መጪው ጊዜ አደገኛ እንደሆነ በተገኘው አጋጣሚ የሚጽፍልን ወጣት አብርሃ ደስታ ያለውን ማስተዋል ይገባል ፡፡ በትግራይ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች በነበርንበት ወቅት ፣ የደርግን ክፉነት በጨቅላ ዓይምሮአችን እንዲቀረጽ ለማድረግ ፣ ደርግ አማራ ነው የሚል ትምህርት ተሰጥቶን ነው ያደግነው ብሏል፡፡ ቢያንስ ይህ ወጣት በትግራይ ህዝብ ስም የሚነግዱትን ወገኖቹን ክርስቶስ ለስጋው አደላ በሚለው ብሂል ቀባብቶ አላለፋቸውም ፡፡ ቢያንስ የትግራይ ህዝብ በአማራው ክልል ውስጥ ወልዶና ተዋልዶ ይገኛልና ነግ በኔ እንዳይሆን ብሎ በኢትዮጵያዊነት ጨዋነት ወያኔዎች አዙረው እንዲያዩ አድርጓል ፡፡
ሚሚ ስብሃቱ ! የአማራውን መባረር ከዛፍ ጨፍጫፊነቱ የተነሳ የተወሰደበት ርምጃ ነው ብላ ሰሞኑን እንደረገመችው ይህ ወጣት የትግራይ ልጅ በአምሃራ ጥላቻነት እንዲማር ቢገደድም – በአማራው ህዝብ ላይ አልተሳለቀበትም ፡፡ አይጋ በሰሞኑ የሆድ አደሩን የተስፋዬን ሃቢሶ የአማራውን መርገምት ጽሁፍ ለተባረሩት አማሮች ምክንያት ነው ብሎ እንደለጠፈው የዘረኝነት ዝብዝንኬ ጽሁፍ ፣ ይህ የትግራይ አርቆ አስተዋይ ወጣት ወርዶ የአማራውን ህዝብ አልሰደበም ፡፡ ተዉ የትግራይ ህዝብ አማራው ውስጥ አለ እየኖረም ነው ብሎ ነው የመከረው ፡፡
ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ ታሪካዊ ቦታዎች ጉዞ
ጡጦውን ላመጣ ከጓዳ ገብቼ
የወተቱን ሙቀት ስለካ ቆይቼ
ስመለስ ሳሎኑን ትበረብራለች
የመኪናውን ቁልፍ የት ነው ያደረግሽው ? ብላ ፊቴ ቆመች
ዓይኔ ዓይኗ ላይ ሆኖ ጊዜን ተሟገትኩት
በምንኛ ፍጥነት ከቅፌ ፈልቅቀህ ልጄን ወሰድክ አልኩት ፡፡
-ግጥም ዝነኛዋ ጸሃፊ ዓለም ፀሃይ ወዳጆ
ከባለቤቴ ጋር በመሆን አገራችንን ሳናውቃት በስደት የተለየናትን የሰሜን ኢትዮጵያ ታሪካዊ ቦታ ለመጎብኝት የዛሬ 12 ዓመት ግድም ጉዟአችንን ከአክሱም ለመጀመር ፣ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ተገኝተናል ፡፡ከተሰቀለው የጉዞ ማሳያ ሰሌዳው ላይ አክሱም የሚል ባለመለጠፉ ፣ ከባለቤቴ ጋር ስንጠያየቅ ፣ አንዲት ከጀርባዋ ላይ አንስተኛ ቦርሳ የሸከፈች ወጣት ሴት ልጅ ለካስ ታዳምጠን ኖሮ ! ወደ አክሱም ነው የምትሄዱት ብላ በኢትዮጵያዊ ጨዋነት ትጠይቀናለች ፡፡መልሳችን አዎ! ስለነበር ፣ እኔም ወደዚያ ስለሆነ ሰልፉ እዚህ ነው አብረን እንሄዳለን አለች ፡፡ ተረጋግተን ሰልፋችንን ይዘን ስንጠባበቅ የመብረሪያ ሰዓታችን ደረሰና ወደ ጢያራዋ ውስጥ ዘልቀን ገባን ፡፡ ይህች ወጣት ልጅ የመጣችው ከካናዳ እንደሆነ ፣ በትውልድ ቀዬዋ ከዛው አክሱም እንደሆነች ነግራን እኛም ከየትኛው የውጭ አገር እንደመጣን ጠየቀችን ፡፡ ከሰሜን አውሮፓ ከስካንድኔቪያ እንደመጣን አወጋናት ፡፡
አውሮፕላኗ ውስጥ አቀማመጣችን እርሷ ከፊት ፣ እኔና ባለቤቴ ደግሞ ከርሷ ኋላ የተቀመጥን ሲሆን ፣ ከኛ ኋላ ደግሞ ሁለት ሴቶችና አንድ ወንድ ሆነው በጋራ ሞቅ ያለ ወሬ ተያይዘው ነበር ፡፡ ብዙ ጊዜ ጭውውታቸው በአማርኛና እንግሊዘኛ ጉራማይሌ ቋንቋ ፥ አልፎ አልፎ ደግሞ በትግርኛ እያወሩ ጉዞአችንን ወደ አክሱም ተያይዘነዋል ፡፡ እነኝህ ከኋላችን የተቀመጡት ዲያስፖራዎች ፣ የመጡት ከእንግሊዝ አገር ነበር ፡፡በትግርኛ የሚያወሩትን ንግግር ምን እንደሆነ ባናውቀውም ፣ ከፊት ለፊታችን የተቀመጠችው ከካናዳ የመጣችውና የአክሱም ልጅ የሆነችው ልጅ ግን ታደምጣቸው ነበር ፡፡ አክሱም ደርሰን ከአውሮፕላኗ ስንወርድ፣ጭሥስ ያለችው የአክሱም ልጅ ፣ ከናንተ ኋላ የተቀመጡት ሶስት ሰዎች የሚያወሩትን አድምጣችኋል በማለት ትጠይቀናለች ? በአማርኛና በንግሊዘኛ የሚሉትን ሰምተናቸዋል ፡፡ በትግርኛ የተናገሩትን ግን አልገባንም ብለን መለስንላት ፡፡
ምናሉ መሰላችሁ ? የአውሮፕላኗ አፍንጫ ወደ አክሱም ስታዘቀዝቅ አረንጓዴ ምድር ሲያዩ ! እዪ አድዋን ! እዪ አድዋን እያሉ ይኩራራሉ ፡፡ አውሮፕላኗ እኮ የነበረቸው አክሱም ክልል ነው ብላ በመናደድ ትነግረናለች ፡፡ ግራ የተጋባነው እኔና ባለቤቴ ፣ አድዋ ከዚህ ምን ያህል ይርቃል ብለን ስንጠይቃት ወደ 20 ኪሎሜትር ግድም እንደሆነ ስትነግረን ትንሽ ግራ እንጋባለን ፡፡ እንዴት በሃያ ኪሎሜትር ርቀት የሰው አመለካከት ይለያያል ብለን ግራ ተጋባን ፡፡ ኧንዲያውም የሃያ ኪሎሜት ርቀት ላይ ካለንማ በትራንስፖርት ሄደን አድዋን ማየት አለብን ታሪካዊ አገራችን አይደለች ብዬ እንዳልኩ ፣ የተናደደቸው የአክሱም ወጣት ምን አለ ብላችሁ ነው ? ባዶ ተራራ ነው ብላ ሃሳቤን አጣጣለችው ፡፡
ይህ በዚህ እያለ ሆቴል የት እንደያዝን ትጠይቀናለች ? ገና ሆቴል እንዳልያዝን ግን ጥሩ ሆቴል የቱ እንደሆነ ብትጠቁምን ደስ እንደሚለን ስንነግራት ፣ ጥሩ ሆቴል አስይዛችኋለሁ ፣ ከዚያ በፊት ግን እቤት ገብታችሁ ፥ ምሳ በልታችሁና ቡና ጠጥታችሁ ዕረፍት ካደረጋችሁ በኋላ ነው በማለት በግድ ወደ ቤተሰቦቿ ቤት ትወስደናለች ፡፡ የግቢውን በር እንደቆረቆረች ፣ የልጃቸውን መምጣት የሚጠባበቁት እናት የውጭው በር ድረስ መጥተው አብረው ስመው ተቀበሉን ፡፡ አማርኛ መናገር ትንሽ ቢያዳግታቸውም በልጃቸው አስተርጓሚነት ምሳ በልተን ፣ ቡና እየጠጣን ብዙ ወግ እናትየዋ አወጉን ፡፡አማርኛ ተናጋሪ በመሆናችን እኝህ አዛውንት እናት አልጎረበጣቸውም ፡፡ የሆዳቸውን አወጉን ፡፡
ወያኔ ወንዶች ልጆቻቸውን ልቅም አድርጋ ወስዳ በህይወት እንዳልተመለሱ ፣ አንድም የቀራቸውን ወንድ ልጅ ፣ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት ሊወስዱት ሲሉ ፣ ወደ አዲስ አበባ አሽሽተው ከዚያም ኬንያ እንዳስገቡትና ካናዳ ያሉት እህቶቹ እየረዱት ኬንያ እንደሚገኝ በማዘን ነገሩን ፡፡ለወያኔ ያላቸውንም ጥላቻ ሳይደብቁ ነገሩን ፡፡ ጭውውታችን ሲያልቅ ፣ እባካችሁ በቂ መኖርያ ክፍል አለን ፥ ሻወርም አለን አትሂዱ እዚሁ እደሩ ብለው ተማጸኑን ፡፡ የለም ጠዋት ስለሆነ ወደ ቀጣዩ የላሊበላ ጉዞ የምናደርገው በጠዋት አንቀሰቅሳችሁም እግዜር ይስጥልን ብለን ፣ በእንግዳ ተቀባይነታቸው አክብረንና እጅ ነስተን ወደ መረጡልን ራሃዋ የሚባል ሆቴል ይመስለኛል ወደዚያ አመራን ፡፡
ላሊበላ አንድ ቀን ቆይተን ቀጣዩ ጉዟችን ጎንደር ነበር ፡፡ ላሊበላ ሳለን አንድ ወጣት ልጅ ያረፍንበት ሆቴል ውስጥ እንተዋወቃለን ፡፡ የተዋወቅነው ወጣት ዲያስፖራ ሳይሆን ላሜ ቦራ ነበርና ፣ ጎንደር ጥሩ ሆቴል የቱ እንደሆነ ስንጠይቀው ፣ ሰርክል የሚባል ሆቴል እጅግ ጥሩ ሆቴል ነው እዚያ ያዙ ይለናል ፡፡ ልጁ በነገረን መሰረት ጎንደር እንደደረስን አውሮፕላን ጣቢያ ያገኘነውን ታክሲ ይዘን ሰርክል ሆቴል አድርሰን እንለዋለን ፡፡
ባለታክሲው ምን እንደሆንን ሳያውቅ ፣ለምን ሰርክል ሆቴል ትይዛላችሁ ? ለናንተ ጥሩ ሆቴል እኔ አስይዛችኋለሁ ብሎ ያግባባናል፡፡ የለም እኛ እዚያ ነው መያዝ የምንፈልገው ብለን ድርቅ እንላለን ፡፡ እሽ ካላችሁ ነገ ግን አድራችሁ ሳገኛችሁ አዝናችሁ አገኛችኋለሁ ብሎን ሆቴል ከመግባታችሁ በፊት ጎንደር ከተማን አንዴ አዟዙሬ ላሳያችሁ በማለት ከተማዋን ሲያሳየን በመጀመርያ ወስዶ ያሳየን ፣ ዳሽን ቢራ ፋብሪካውን ነበር ፡፡ ይኽውላችሁ ይህ ፋብሪካ ሲሠራ አጥሩን የሚያጥር ግንበኛና ወዛደር የመጣው ልክ ቻይኖች የራሳቸውን ሰዎች እንደሚያመጡት ከትግራይ ነበር ፡፡ ጎንደር ባገሩ የቀን ሥራ እንኳ ተከልክሎ ከትግራይ ! እያለ ይቆጭ ጀመር ፡፡ ጭራሽ ስትዝናኑ ቡና ቤት ስትገቡ ዳሽን ቢራ እንዳትጠጡ ፡፡ ዳሽን ከጠጣችሁ የጎንደር ህዝብ የወያኔ ደጋፊዎች ናችሁ ብሎ ፣ ይጠረጥራችኋል ይለናል ፡፡ባለቤቴን ምንም አይነት አስተያየት እንዳትሰጥ ቆንጠጥ አድርጌያት ታክሲ ነጂውን መጠርጠር ያዝኩ ፡፡ አናግሮ አናጋሪ በሚል ፍራቻ ፡፡ ሆቴላችን አድርሶን የሚገኝበትን ስልክ ቁጥር ሰጥቶን ይሄዳል ፡፡
በማግስቱ በጠዋት ሆቴላችን ድረስ መጥቶ አዳራችን እንዴት እንደነበረ ይጠይቀናል ? ከፊታችን ላይ ደስታ እንዳልነበረን የተረዳው ታክሲ ነጂ አልነገርኳችሁም ?አልሰማ ብላችሁ እኮ ነው ይለናል ፡፡ በቂ እንቅልፍ እንዳልተኛን ሌሊቱን ሙሉ የትግርኛ ሙዚቃና ከበሮ ብቻ ሲዘፈን እንዳደረ እና እንደረበሸን ነገርነው ፡፡ ድሮስ ! አልሰማ ብላችሁኝ እኮ ነው ብሎ በወያኔ ላይ ያለውን ጥላቻ በግልጽ ነግሮን ወደ ኤርፖርት መልሶ አደረሰን ፡፡ በዚያች ምድር ወያኔ በሚሠራው የዘረኝነት መርዝ ምን ያህል የትግራይ ህዝብ እንደተጠላ ተረዳን ፡፡ ይህ ታክሲ ነጂ ፣ ሰሞኑን የአቶ በረከት ሰምኦን እናት በወታደራዊ ሠልፍና ማርሽ ጎንደር ጸጥ ብላ ሲቀበሩ ምን ተሰምቶት ይሆን ? በህይወት ካለ ፡፡
ባህር ዳር
ከጎንደር ባህርዳር ባደረግነው ቆይታ ብዙ ነገር ለመታዘብ ችያለሁ ፡፡ ቢያንስ ጎንደር ከተማዋ በነጻ ጋዜጦች ሽያጭ የማትታማ ፣ ሁሉኑም ጋዜጦች ማግኘት የሚቻልባት ፣ በአንጻራዊነትም የጎንደር ህዝብ በግልጽ ለወያኔ ያለውን ጥላቻ ከማሳየት የማይታቀብበት ከተማ ስትሆን ፣ የአማራው ክልል ዋና ከተማ የተባለው ባህርዳር ግን ዝም እርጭ ያለ፣ ምንም አይነት ነጻ ጋዜጣ የሚባል የማይታይበት ከተማ ነበር ፡፡ ባህርዳር ከተማ ውስጥ ያላየነውን የወያኔ ተቃውሞ ምልክቶች ማጣት ግን ጢስ አባይን ጎብኝተን በታንኳ ጎርጎራ የሚባለውን ጎንደርንና ጎጃምን የሚያውስነውን ወንዝ ለማየት ስንሄድ፣ የገጠመን አስደንጋጭ ንግግር ግን ይህች አገር ወዴት እንደምትሄድ የሚያሳይ ጠቋሚ አደጋ ነበረ ፡፡ ግፋ ቢል እድሜያቸው ከአስር እስከ አስራ ሁለት አመት የሚጠጋቸው ልጆች በአሽዋ ውስጥ የተቀበረ አንቧውሃ ይዘው ጋሽዬ ! ክኔ ግዙ ! ጋሽዬ ከኔ ግዙ፡! እያሉ ይሻማሉ ፡፡ ከሁሉም መግዛት ባንችልም እጃችን ወደ ወሰደን እና ቀደም ብሎ ከተማጸነን ካንደኛው ልጅ ላይ ልንገዛ ስንል ! አንቱ ጋሽዬ ! ከሱ ልጅ አትግዙ ብለው ሁሉም ህጻናት ጮሁ ፡፡
ለምን እሱ ነው ከቅድም ጀምሮ ግዙኝ እያለ የለመነን አልኳቸው ፡፡ አይ ! የሱ አባት ትግሬ ስለሆነ አትግዙት ጋሽዬ አሉን አንድ ላይ በመጮህ ፡፡ ባለቤቴና እኔ ተያየን ፡፡ በአድማ እንዳይሸጥ የተጮኸበት ልጅ አንገቱን ደፋ ፡፡ አዘንን ፡፡ለማስተባበል ሞከረ በማዘን ፡፡ አይዞህ ምንም አይደል እንገዛሃለን አልነው ፡፡ የተሰበረ ልቡን ለመጠገን ስንል ፡፡ ይህ ልጅ መርጦ አልተወለደም ፡፡ የአቶ መለስ መንግሥት በዘራው የዘረኝነት መርዝ ይህ ጎንደርና ጎጃም ድንበር ላይ ጎርጎራ የተወለደው ልጅ የርሱ እኩዮች በሆኑ ልጆች ጥርስ ውስጥ ገብቷል ፡፡ ዘረኝነት ምን ያህል አስከፊ እንደሆነ እንኳን በአዋቂዎች በልጆች ውስጥም መዝምዞ እንደገባ ያሳየናል ፡፡ ዓለም ጸሃይ በግጥሟ እንዳለችው ፣
ጡጦዋን ላመጣ ከጓዳ ገብቼ
የወተቱን ሙቀት ስለካ ቆይቼ
በምንኛ ፍጥነት ከቅፌ ፈልቅቀህ ልጄን ውስድክ አሉት ? ማለት ይህ ነው ፡፡
ህወሃት በአማራው ህዝብ ላይ የጣለውን ዘር የማጥፋት ርምጃ ፣ እንዲያስፈጽሙለት ፣ የአማራውን ህዝብ በወልድ አግድ እንዲያስተዳድረው የመደበለት የአማርኛ ተናጋሪ የትግርኛ ክፍል ፣ የአማራውን ብሄር በቁጥር ከሁለት ሚልዮን ተኩል በላይ በህዝብ ቆጠራ ወቅት የት እንደደረሰ ጠፍቶ ባለበት ጊዜ እንኳ አለመጠየቁ ሲደንቀን ፣ አቶ መለስና የማፍያ ቡድናቸው ግን አየር በአየር ስለሸጡት ብዙ ሺህ ቶን ቡና ከፍተኛ ቦታ ተሰጥቶት ሲነገር ፣ አማራው ግን ከቁጥር ሳይገባ ለጠቅላይ ሚንስትሩ ቢሮ ቡና ጠፋ ተብሎ ሪፖርት ሲደረግ፣ አማራ ግን ቁጥሩ ለምን እንዲቀንስ ተደረገ ብሎ የጠየቀ አካል አልነበረም ፡፡ ብአዴን የተባለው አማራውን በወልድ አገድ የያዘ የትግርኛ ተናጋሪ የአማራ ክፍል ከቤኒሻንጉልና ጉሙዝ ለተባረሩት አማሮች መብት ባይቆም የሚደንቀን ለምንድነው ?
አማራው አዲስ አበባ አካባቢ ከሌሎች ጎሳዎች በላይ በቁጥር በልጦ መታየቱ እንቅልፍ የነሳው ህወሃት፣ በዘዴና በኮንዶሚኒዬም ሰፈራ ዘዴ ጥንታዊውን ነዋሪ ከለመደው ቀዬ በማፈናቀል ፣ አንዱን ጉለሌ ፣ሌላውን ገርጂ በመበታተን እንዲሁም ጥንታዊዎቹን እድሮች በማፈራረስ ሰዉ ባይተዋር እንዲሆን በማድረግም ፋሽስታዊ አካሄዶችን ተግብሯል ፡፡ ብዙ ጊዜ እያጠቃን ያለው እና እንዳልዛይመር ህመም ሁሉን የመርሳት ችግር እየገጠመን ፣ በፎቅና መንገድ መሽቆጥቆጥ ጥንታዊው ነዋሪ የት ሰፈረ ? እድሮችስ የት ሰመጡ ? ብለን አለመጠየቃችን ፣ አራዳ ነኝ ለሚለው ወያኔ ! እኛ ወረዳ ሆነንለታል ፡፡ ወያኔ ብዙ የሚጫወትባቸውን ካርታዎች ገና ከእጁ አልጣለም፡፡ አሁንም አልዛይመር ካልያዘን የምርጫ 97 ን ምርጫ ወቅት አለመርሳት ነው ፡፡ ቅንጅት አዲስ አበባን አሸንፎ ዶክተር ብርሃኑ ከንቲባ ሆነ ሲባል ፣ አይንህን ከፊንፊኔ እንዳላየው ብሎ ናዝሬት ያባረረውን ኦህዴድን ወዲያው ከናዝሬት ጽህፈት ቤቱን አስነቅሎ ያስመጣውን መርሳት የለብንም ፡፡ ምን ግዜም በ 110 ካሬ ሜትር ቦታ እንደ ኤሳው በጭብጦ ምስር ቤት አለኝ ብሎ አንገቱን የሚደፋለት ዲያስፖራ ፣ ነገ ያንተ ክልል አይደለምና ውጣ ተብሎ እንደሚባረር አልገባውም ፡፡በተለይ ጥቁር ልብስና ወይባ የለበሱት እንዲሁም ዲያቆናት አስተማሪዎች ነን ብለው ከአዲስ አበባ ዋሽንግቶን ዲሲ በተጨማሪም አውሮፓ ለአገልግሎት ሲመጡ ከነሚስቶቻቸው የሚጋበዙት ሰባኪዎቻችን ፣ከሰማዩ ቤታቸው ይልቅ ወያኔ ለሚሰጣቸው 110 ካሬ ሜትር ቦታ ሲሉ ፥ ለሰማዩ ቤታቸው የመግቢያ ቪዛ ሳይሆን ፣ ወያኔ ለሚሰጣቸው የመግቢያ ቪዛ ሲሉ ፣ ተራው አማኝ የማያውቃቸውን አስፈሪ ጥቅሶች እየጠቀሱ ፣ ህዝቡን ፖለቲካ አትስማ በማለት እያስተኙ የሚያስጨፈጭፉንን ፈሪሳውያን ቀሳውስትና ዲያቆናት .. ህዝባችሁ ሲጋዝ ምነው ድምጻችሁ የት ጠፋ ? ካላልናቸው አብረው ከወያኔ ጋር እንደነገዱብን ይቀጥላሉ ፡፡
በውጭ ያለው አማኝ ይህ ሁሉ የአገሪቱ ዜጋ ሲፈናቀል ቤተክርስቲያኖቻችንን በተለይ ገለልተኛ ነን የሚሉትን ምነው የጸሎት ጊዜ አላወጃችሁም ብሎ መጠየቅ ይገባዋል ፡፡ ከአዲስ አበባ የውሃ መንገድ የሆነላቸውን ብልጣ ብልጥ ዲያቆናትን ከንግዲህ የአውሮፕላን ትኬት አንገዛም ፣ እዚያ አገራችን ያለውን የተፈናቀለ ህዝባችንን በጸሎትም ሆነ ከጎኑ ሆናችሁ አጽናኑ ማለት አለብን ፡፡ ቤተ ክህነት ውስጥ ሆነው ፣ ከስድስት ኪሎ አራት ኪሎ የተደረገውን አልሰማንም የሚሉ ጥቁር ለባሽ ጳጳሳትን እየሰማን ባለንበት አገር ቤንሻጉሉና ጉሙዝማ እጅግ ሩቅ ነው ፡፡ በብአዴን የተጠረነፉ ፈሪሳውያን ወንጌላውያንም ቢሆኑ አማራውን በወልድ አግድ በምድር ገዝተው ያሰሩት ጭምር ናቸው ፡፡
እግዚአብሄር የግፉሃንን እንባ ያብሳል !
ኢትዮጵያ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር