May 20, 2024
315 mins read

ነፃነት፣ ዲሞክራሲ ፣ የብሄረሰብ ጥያቄና የኢኮኖሚ ዕድገት! -እንዴትና ለማን እንዲሁም ምን ዐይነት የኢኮኖሚ ዕድገት፟

ፈቃዱ በቀለ (/)

        ግንቦት 12 2016 (ግንቦት 20 2024)

“Enlightenment is man’s release from his self-incurred tutelage. Tutelage is man’s inability to make use of his understanding without direction from another. Self-incurred is this tutelage when its cause lies not in lack of reason but in lack of resolution and courage to use it without direction from another. Sapere aude! ‘Have courage to use your own reason!’- that is the motto of enlightenment.”  Immanuel Kant

 መግቢያ

እንደምንከታተለው የአብዛኛዎቹ የሶስተኛው ዓለም አገሮች፣ በተለይም ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ አገሮች ዕጣ፣ እንደህብረተሰብና እንደ አገር የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ እጅግ አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል። አብዛኛዎች አገዛዞችና መሪዎቻቸው የአገርና የህዝቦቻቸው ጉዳይ የሚያሳስባቸው አይመስልም። የፖለቲካ አርቆ-አስተዋይነት የጎደላቸውና፣ ህብረተሰብአዊ ኃላፊነት የማይሰማቸው መሪዎች ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ከማደለብ አልፈው የአገርን ሀብት ወደ ውጭ በማሸሽ እዚያ የውጭ ባንኮችና ኢንዱስትሪ አገሮች መጠቀሚያ በማድረግና የሀብት ክምችት አመቻች በመሆን፣ በአንፃሩ ደግሞ ህዝቦቻቸውን እያደኸዩ ነው። በተጨማሪም የአገሮቻቸውን የጥሬ-ሀብትና የእርሻ መሬት ለውጭ ኢንቬስተሮች፣ በመሰረቱ ዘራፊዎች አሳልፈው በመስጠት ከሀብት ዝርፊያ ባሻገር ህብረተሰብአዊ፣ ባህላዊ፣ የህሊናና የአካባቢ ቀውስ እንዲፈጠር እያደረጉ ነው። የፖለቲካ ቀውስ እንዲፈጠር አመቺ ሁኔታዎችን መፍጠራቸው ብቻ ሳይሆን፣ የነቃና አርቆ-አሳቢ የሆነ የህብረተስብ ክፍልም እንዳይፈጠር ሁኔታዎችን እያዘበራረቁ ነው። በዚያው መጠንም የአብዛኛዎቹ አፍሪካ አገዛዞች የመንግስት መኪናዎች በከፍተኛ ደረጃ በጭቆና መሳሪያ በመደለብና በመጠናከር የህዝቦቻቸው አለኝታ መሆናቸው ቀርቶ የዓለም አቀፍ ካፒታሊዝም ታዛዦች መሆናቸውን እያረገጋጡ ነው። በመሆኑም አገዛዞች ከህዝብ የሚነሳን ተቃዎሞን፣ የመብትና የነፃነት ጥያቄን ለማብረድ የሚፈልጉት በውይይትና በሰላማዊ መንገድ ሳይሆን በጠብመንጃ በመታገዝ ሰላማዊ ህዝብ ላይ በመተኮስና በመግደል ነው።

አቢይ ስልጣን ላይ ከወጣ ጀምሮ፣ በተለይም አንድ ዓመት ያህል የሚያስቆጥር፣ በተለይም በአማራው ወገናችን ላይ በአማራው ክልል የሚካሄደውን የዘር ማጥፋት ለተመለከተ አቢይ አህመድና የኦሮሞ ኤሊት ነን ባዮች የሚያካሂዱት ጦርነት በቀጥታ የውክልና ጦርነት ነው። ይህም ማለት ጦርነቱ በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም በተለይና፣  በአጠቃላይ ደግሞ በግሎባል ካፒታሊዝም የሚደገፍና ለሀብት ዘረፋ የሚያመች ነው። ጦርነትም በተከታታይ ሲካሄድ የህዝብ ዕልቂትን ስለሚያስከትል፣ በዚያው መጠንም የህዝብ ቁጥር ይቀንሳል የሚል ስሌት አለ። ስለሆነም አገራችንና ህዝባችን በዚህ ዐይነቱ በቀላሉ መቋጫ ሊያገኝ በማይችል ጦርነት በመጠመድ ዋና ተግባራቸው አገራቸውን መገንባትና ከድህነት መላቀቅ ሳይሆን ጦርነት ማካሄድን እንደተፈጥሮአዊ ህግና ግዴታ በመውሰድ ጦርነትን እየተለማመዱና እየኖሩበት በዚያው መግፋት አለባቸው።  በዚህ መልክ በአገራችን ምድር የሚካሄደው ጦርነት  ከዓለም አቀፍ ካፒታሊዝም የሀብት ምዝበራ ጋር የተያያዘ ሲሆን፣ ብዙ ማስረጃዎችም እንደሚያረጋግጡት የአቢይ አህመድ አገዛዝ በአማራ እህቶቻችን፣ ወንድሞቻችን፣ ልጆቻችን፣ እናቶቻችንና አባቶቻችን ላይ የሚያካሂደው የዘር ማጥፋት ዘመቻ ከአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ስትራቴጂያዊ ስሌት ውጭ በፍጹም ሊታይ የሚችል አይደለም። የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ወያኔን ስልጣን ላይ በማውጣትና ለእሱ የሚስማማውን የከፋፍለህ ግዛው ፖለቲካና የሰፊውን ህዝብ የሚያደኸየውንና አገርን ወደብልግና መድረክ የሚለውጠውን የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ እንዲያደርግ 27 ዓመት ያህል ከተጠቀመበትና እንደሎሚ መጥቶ ከጣለው በኋላ በሌላ ጭራቅ አገዛዝ መተካት ነበረበት። ወያኔ ተግባራዊ ያደረገው የከፋፍለህ ግዛው ፖለቲካና የኢኮኖሚ ፖሊሲ በሌላ መልክ መቀጠልና ጥልቀትም ማግኘት አለበት። ለዚህ የሚስማማ ደግሞ አቢይ አህመድ የሚባል በራሱ በሲአይኤ የተመለመለና የሰለጠነ ሰው ነው።

የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ኮሙኒዝምን እዋጋለሁ በማለት በብራዚል፣ በቺሌና በአርጀንቲና በስድሳኛውና በሰባኛው ዐመተ ምህረት አምባገነናዊና ፋሺሽታዊ አገዛዞችን አስታጥቆ ለስልጣን እንዳበቃና የዲሞክራሲንና የነፃነት ጥያቄን እንዳኮላሸ ሁሉ፣ በአገራችን ምድር ደግሞ ሃያ ሰባት ዓመታት ያህል የወያኔን አገዛዝ በመደገፍና ታዛዡ በማድረግ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንዳያብብ ለማድረግ በቅቷል። በዚህም የተነሳ አዲስና የተገለጸለት እንዲሁም ተፎካካሪ ሊሆን የሚችል የህብረተሰብ ኃይል ብቅ ሊል አልቻለም። ሰፋ ያለ ምሁራዊ እንቅስቅሴም ሊዳብር አልቻለም። የዛሬ ስድስት ዓመት ወያኔ ሳይወድ በግድ ከስልጣን ላይ ከተወገደ በኋላ ህዝባችን እፎይ እንዳይልና የዲሞክራሲንና የነጻነትን ጭላንጭል እንዳያይ ጦርነቱ በሌላ መልክ መቀጠል ነበረበት። በሌላ ወገን በስድሳኛውና በሰባኛው ዓመተ ምህረታት በብራዚል፣ በቺሌና በአርጀንቲና በህዝብ የተመረጡ አገዛዞች በአሜሪካ ታግዘው የመንግስት ግልበጣ ሲካሄድባቸውና ፋሺሽታዊ አገዛዞች ስልጣኑን ሲወስዱ፣ በአገራችን ምድር ግን „ህጋዊ በሆነ„  መንገድ የተካሄደ ቀስ በቀስ ወደ ፋሺሽታዊ አገዛዝነት የተለወጠ የስልጣን ሽግግር ነው በሁለት ተፈራራቂ ኃይሎች ተግባራዊ መሆን የጀመረው።። ለዚህ ደግሞ የጸጥታውን መስክ ከማጠናከር በሻገር፣ በነፃ ገበያ ስም የተካሄደው የኢኮኖሚ ፖሊሲ የወያኔንም ሆነ የአቢይ አህመድን አገዛዝ በጥሬ-ሀብት ዘረፋ እንዲሰማሩ በማድረግ የተወሰነውን ደግሞ ወደ ውጭ እንዲያሸሹ ለማድረግ አስችሏቸዋል። በዚያው መጠንም በውጭ ኃይሎች ጉያ ስር በመውደቅ ታዛዦችና አገርን አውዳሚዎች በመሆን ህዝባችንን አቅመቢስ እንዲሆን አድርገውታል፤ የኑሮንንም ትርጉም እንዳይረዳ ለማድረግ በቅተዋል። ስለሆነም በወያኔ የአገዛዝ ዘመን እንደ ስኳር የመሳሰሉ ፕሮጀክቶችና የመሬት መቀራመት ጉዳይ፣ እንዲሁም እንደሰሊጥ የመሳሰሉትን የቅባት እህሎች በመቆጣጠርና ወደ ውጭ ማጋዝ፣ በመንግስት ቁጥጥር ስር የነበሩ ኩባንያዎችን ከአገዛዙ ጋር ለተቆላልፉ ሰዎች በርካሽ ዋጋ መሸጥና በአጭር ጊዜ ውስጥም የናጠጡ ሀብታሞች እንዲሆኑ ማድረግ ተግባራዊ በሆነው የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ የተደገፈና አዲስ ኦሊጋርኪክ መደብ ብቅ እንዲል ያመቻቸ ነው። ይህ ዐይነቱ ድርጊትም አገሮችን ለዝንተ-ዓለም አደኽይቶ ለማቆየት ከታቀደው ከዓለም አቀፋዊ የካፒታሊዝም ስትራቴጂ ውጭ  ተነጥሎ ሊታይ የሚችል አይደለም። በሌላ አነጋገር፣ የወያኔ አገዛዝ ሙሉ በሙሉ በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና በተቀረው የካፒታሊስቱ ዓለም ይደገፍ የነበረ ሲሆን፣ ዋናው አላማውም የኢትዮጵያ ህዝብ ቀስ በቀስ አገሩን በጸና መሰረት ላይ ገንብቶ የነፃነትና የዕውነተኛ ስልጣኔ ባለቤት እንዳይሆን ማድረግ ነው። ይህም ከሞላ ጎደል ተሳክቷል ማለት ይቻላል። የአቢይ አህመድ አገዛዝም በዚሁ በመቀጠልና፣ በተለይም በወርቅ ዘረፋ ላይ በመሰማራትና ወደውጭ በማሸሽ ድህነትንና ሽፍጠኝነትን በከፍተኛ ፍጥነትና ጥልቀት ያስፋፋ አገዛዝ ለመሆን በቅቷል።

ወያኔ ስልጣን ላይ በነበረበት ዘመን በህዝባችን ላይ ያካሂድ የነበረውን የጭቆና አገዛዝና ጭፍጨፋ፣ እንዲሁም የሀብት ዘረፋ፣ አቢይ አህመድ ደግሞ ስልጣን ላይ ከወጣ ጀምሮ የሚያካሂደውን የዘር ማጥፋት ዘመቻና የሀብት ዘረፋ አስመልክቶ በተለይም ተቃዋሚ ነኝ ከሚለውና፣ እዚህና እዚያ በተናጠልም ሆነ በቡድን ውር ውር ከሚለው በሃሳብ ደረጃ ለውይይት ቀርቦ ጥናት ሲካሄድ አይታይም። በአብዛኛዎችም ዕምነት የዲሞክራሲ፣ የነፃነትና የኢኮኖሚ ዕድገት ጉዳይ ከውጭው ሁኔታ ጋር የሚያያዙ ሳይሆኑ የውስጥ ጉዳይ ብቻ ነው የሚል አመለካከትና ግንዛቤ ሰፍኗል። ችግሩ ከአገራችን የተበላሸ አገዛዝ የመነጨ እንጂ የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት አገዛዞቹ በሚያካሄዱት ጭፍጨፋና ድህነት መስፋፋት ላይ ምንም ዐይነት ተጽዕኖ የላቸውም፤ የኛን ችግር በውጭው ላይ ማሳበቡ አላዋቂነት ብቻ ሳይሆን፣ አክራሪነትም ነው ይሉናል። ስለሆነም ይላሉ፣ እነዚህ በአንድ በኩል የወያኔን አገዛዝ ይጠሉ የነበሩና እንታገላለን የሚሉ ኃይሎች፣ በአሁኑ ወቅትም የአቢይ አህመድን አገዛዝ እንታገላለን የሚሉና በተለይም በውጭው ዓለም ተሰደው የሚኖሩና በስራ ላይም ተሰማርተው የሚገኙ፣ በሌላ ወገን  ደግሞ የምዕራቡ ጣልቃ-ገብነት ሲነሳባቸው የሚያንገሸግሻቸው የምዕራቡን ጥቅም የማይቀናቀን አገዛዝ ስልጣን ላይ ከወጣ ዕርዳታውም ይጎርፍልናል፤ በደስታም እንድንኖር ያደርጉናል በማለት የእቅጩን ይነግሩናል። በመሆኑም ይሉናል፣ የኛ ትግል የነሱን ጥቅም የሚቀናቀን መሆን የለበትም። ብሄራዊ ጥቅማቸውን እስካልነካን ድረስ ሊረዱን ይችላሉ በማለት ከህብረተሰብ ዕድገትና ከሳይንስ ውጭ የሆነ ክርክር ያቀርባሉ። በሌላ ወገን ግን የምዕራቡ ዓለም ብሄራዊ ጥቅም ምን እንደሆን እይነግሩንም። ዕቃቸውን እንዲያራግፉና ጦርነትም እንድናካሂድላቸው፣ በዚያውም መጠንም የህዝባችንን የድህነት ዘመን እንድናራዝምላቸው ይፈልጉ አይፈልጉ እንደሆን እነዚህ ለዲሞክራሲ እንታገላለን የሚሉ እህቶቻችንና ወንድሞቻቸን በግልጽ ሊነግሩን አይችሉም። በተጨማሪም የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት በማድረግ ጠንካራና የተከበረች አገር ለመገንባት ያግዙን እንደሆነ ውድ እህቶቻችንና ወንድሞቻችን አያብራሩልንም። እንዲያውም ይሉናል እሱማ አያስፈልገንም፤ የኛ ተግባር ቀድሞ የወያኔ አገዛዝ ከስልጣን ላይ ማውረድ ነበር፣ በአሁኑ ወቅት ደግሞ የአቢይ አህመድን አገዛዝ ማስወገድ ብቻ ሲሆን፣ ከዚያ በኋላ የሚመጣውን እግዚአብሄር ያውቃዋል በማለት ከሳይንስና ከፍልስፍና እንዲሁም ከቲዎሪ ውጭ የሆነ ክርክር ይገጥማሉ።  ያም ሆነ ይህ በታሪክ እንደታየውና እንደተረጋገጠው፣ ከቀድሞው ሶቭየት ህብረት፣ ቻይናና ከጃፓን የምንማረው ሀቅ የውጭ ኃይሎች በርቀት እስካልታዩና ማንነታቸው ተገልጾ ውይይት እስካልተደረገበትና፣ ወደ ውስጥ ያተኮረ ሁለ-ገብ የህብረተሰብ ግንባታ እስካልተካሄደ ድረስ አንድ ህዝብ ዕውነተኛ ነፃነቱን ሊቀዳጅ እንደማይችል ነው። በተጨማሪም ከእነዚህና በመጠኑም ነፃነትን ከተቀዳጁ አገሮች የምንማረው ሀቅ አንድ ህዝብ በራሱ ኃይልና ዕውቀት ተማምኖ አገሩን ለመገንባት እስካልተነሳሳ ድረስ የዕውነተኛ ነፃነት ባለቤት ሊሆን እንደማይችል ነው። በመሆኑም የኢምፔሪያሊስት ኃይሎች በማንኛውም ረገድ የህዝባችን ተቆርቋሪና የነፃነት አጋዥ ሊሆኑ በፍጹም አይችሉም። ከዚህ ሀቅ ስነነሳ የነፃነትንና የኢኮኖሚ ዕድገትን ጉዳይ ጠለቅ ብለን መወያየት ያለብን ይመስለኛል።

እንደሚታወቀው ክርክርና ሰፋ ያለ የጭንቅላት ስራ በአውሮፓ የህብረተሰብ ታሪክ ወስጥ የተለመደውን ያህል እንደኛ ባሉ በኢኮኖሚና በህብረተሰብ አወቃቀር ወደ ኋላ በቀሩ አገሮች ውስጥ የህብረተሰብን ችግርና የወደፊት ዕድል አስመልክቶ መከራከር የተለመደ ጉዳይ አይደለም። በተለይም ከ50ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ጀምሮ የሶስተኛውን ዓለም አገሮች በኢኮኖሚ አለማደግን ወይም ኋላ-ቀርነትን አስመልክቶ በጣም ጥቂት ምሁራን ካልሆኑ በስተቀር አብዛኛው ክርክር ይካሄድ የነበረው ይህንን ወይም ያንን ርዕዮተ-ዓለም እናካሄዳለን በሚሉ በአውሮፓና በአሜሪካን ምሁራን ዘንድ ነበር። ለሶስተኛው ዓለም ተቆርቋሪ ሆነው የሚታገሉ ኃይሎች አብዛኛውን ጊዜ ከካፒታሊስት አገሮች የወጡና የተገለጸላቸው ኃይሎች እንጂ፣ የዕድገትና የፀረ-ዕድገት ጉዳይ በእኛ ምሁራን ዘንድ ተንስቶ ክርክርና ጥናት የተደረገበት ጊዜ አልነበረም።  በመሆኑም የኢኮኖሚ ፖሊሲ በውጭ ኃይሎች ተረቆ ሲቀርብ እሱን እንደቡራኬ ከመቀበልና ተግባራዊ ከማድረግ በስተቀር ፖሊሲው ዕውነተኛ የኢኮኖሚ ዕድገትን ያምጣ አያምጣ ለውይይት አይቀርብም።  በሁለትና በሶስት ወራት ወይም ሳምንታት ቆይታና ከዚያ በኋላ ደግሞ ይህንን ወይም ያንን መጽሀፍም ሆነ መጽሄት እያገላበጡ ከዚያ በመነሳት ፖሊሲ አውጥቶ ተግባራዊ እንዲሆን ማድረግ እንደምናየው የኛንም ሆነ የሌሎችን አፍሪካ አገሮችን ሁኔታ የባሰውኑ አባባሰው እንጂ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ሁለ-ገብ የሆነ ኢኮኖሚ እንዲገነቡ አላስቻላቸውም። በተለይም የአፍሪካ አገሮች የፖለቲካ ነጻነታቸውን ከተቀዳጁ በኋላ በተከታታይ ተግባራዊ ያደረጓቸው የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች በሙሉ ወደ ውስጥ ያተኮረ ርስ በርሱ የተያያዘ የውስጥ ገበያ እንዲገነቡ አላደረጋቸውም። በተከታታይ ተግባራዊ የሆኑት የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች በሙሉ ቀድሞ የነበረውን ግኑኝነት ሲያጠናክሩ፣ በዚያው መጠንም በዕዳ እንዲተበተቡና የውጭ ንግድ ሚዛናቸውም እየተዛባ ሊመጣ ችሏል።    የብዙ አፍሪካ አገሮችን ሁኔታ ስንመለከት ከ1950ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ በአወቅሁኝ ባይነት በራሳቸው ላይ እንዲቀመጡ የተደረጉ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች በሙሉ የበሳውኑ መቀመቅ ውስጥ ነው የከተቷቸው። የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት በመሆን ህብረተሰቦቻቸውን በስርዓት እንዲገነቡና እንዲያደራጁ አይደለም የረዷቸው።

ከዚህ ስንነሳ በኛ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ከእንካስላንቲሃ በስተቀር የህብረተሰብአችንን የባህል፣ የኢኮኖሚና የፖለቲካ እንዲሁም ሌሎች ችግሮችን እያነሱ መከራከር የተለመደ አይደለም። እንዲያውም የህብረተሰብአችን ዕጣና የወደፊት ዕድል ለዓለም አቀፍ ኮሙኒቲው እየተባለ ለሚጠራው የተጣለ ይመስላል። ሁሉም አድፍጦ ተቀምጧል። ስልጣን ለመያዝ ጊዜን የሚጠባበቅ እንጂ ብሄራዊ ፕሮጀክት እንዳለው ሰፊ ጥናት በማቅረብ እንድንወያይ የሚያደርገን ኃይል ያለ አይመስልም። የአገርን ህልውናና በትክክለኛ ፖሊሲ መሰረተ-ሃሳብ የመገንባቱ ጉዳይ በመሰረቱ ተራማጅ አስተሳሰብ ካለው ኃይል የሚጠበቅ ጉዳይ ነበር። እንደምከታተለው ከሆነ የተራማጅ ወይንም የተገለጸለት አስተሳሰብ ያለው ምሁራዊ እንቅስቃሴ ስለሌለና፣ አንድ ሰሞን ተራማጅ ነኝ የሚለው ኃይል ተሟጦ ከአለቀ በኋላ በአሁኑ ወቅት የሊበራል ነፃ ገበያ እናካሂዳለን የሚሉት ዋናው ተዋናይና ግንባር ቀደም በመሆን ሜዳውን አጣበውታል። ድሮ ተራማጅ ነኝ ይል ከነበረው ኃይል ትንሽ ተሟጦ የቀረው ደግሞ ሹክክ ከማለት በስተቀር የሚፈልገውን ነገር ወደ ውጭ አወጥቶ ለመናገር የሚደፍር አይደለም። በዚህም በዚያም ብሎ ሌሎችን ተገን አድርጎ ወደ ስልጣን ሊመጣ የሚፈልግ ነው የሚመስለው እንጂ ለአገር የሚበጅ በፍልስፍና፣ በሳይንስና በቲዎሪ የተመሰረተና የተረጋገጠ ብሄራዊ ፕሮጀክት አለኝ ብሎ ወደ ውጭ ወጥቶ ሲያሰተምርና ሲከራከር አይታይም። ይህ ዐይነቱ የተድበሰበሰ አካሄድ እስካለ ድረስ የፈለገውን ያህል ዲሞክራሲ ያስፈልጋል እየተባለ ቢጮህም ህዝባችን ዕውነተኛ ነፃነቱን ሊቀዳጅ በፍጹም አይችልም። ከዚህ አስቸጋሪና አደናጋሪ ሁኔታ በመነሳት  ስለ ነፃነት ሊኖረን የሚገባንን ግንዛቤና መደረግ ያለበትንም ትግል እኔ በምረዳው መልክ ከታች ለመተንተን እሞክራለህ።  የነፃነትና የዲሞክራሲ ትርጉሞች ግልጽ ሲሆኑ ብቻ ነው የኢኮኖሚ ዕድገትና የህብረተሰብ ግንባታም መልክ ሊይዙ የሚችሉት።

የነፃነት ትርጉምና ለነፃነት የተደረገው ትግል!

ለመሆኑ ነፃነት ማለት ምን ማለት ነው ?   ኢማኑኤል ካንት የሚባለው የጀርመኑ ታላቅ ፈላስፋ ከሩሶ ስራ ጋር ከመተዋወቄ ወይም ጽሁፎቹን ከማንበቤ በፊት አምን የነበረው በሰው ልጅ አርቆ አሳቢነትና ዕውቀት(Reason and Knowledge)ነበር። ስለዚህም ስለሰው ልጅም የነበረኝ አስተሳሰብ ለየት ያለ ነበር። ያልተማረውን ወይም ደንቆሮውን የምንቅና የተማረውን ብቻ የማከብር ነበር። የሩሶን መጽሀፎች ካነበብኩኝ በኋላ ግን ሁሉንም ነገር በነፃ ፍላጎት (Free Will) ስር መሆናቸውን ተገነዘብኩኝ። ስለዚህም በሩሶና በአይሳቅ ኒውተን መሀከል ያለውን ልዩነት በመገንዘብ፣ የነፃነት ዓለም(The World of Freedom) ከተፈጥሮአዊ ዓለም (The World of Nature) የበለጠና ወርቃማ እንደሆነ ተማርኩኝ“ ይላል። በመቀጠልም፣“ሩሶ የነፃነትን የተደበቀ ምስጢር ለሰው ልጅ ሲያሰተምር፣ ኒውተን ግን የተፈጥሮን ህግ እንድንረዳ መንገዱን ከፈተልን። ሩሶ ኒውተናዊ የሰው ልጅ ሞራላዊ አባት ሲሆን፣ ውዥንብር በሰፈነበት ዘመን ስርዓት እንዲሰፍን ያደረገ ነው።“  በማለት የሰው ልጅ የግዴታ በነፃነት ዓለም ውስጥ መኖር እንዳለበት ያሳስበናል። በሌላ አነጋገር፣ የሰው ልጅ ነፃ ሆኖ የተፈጠረና በራሱ ነፃ አስተሳሰብ መገዛት አለበት። ይህን ሲገነዘብ ብቻ የራሱን ነፃነት ከማስከበር አልፎ ለሌላው ላልተገነዘበውም ጠበቃ ሆኖ ይታገላል። ነፃነት በአንድ አገዛዝ ወይም ኃይል የሚሰጥ ሳይሆን አንድ ህዝብ በራሱ ተነሳሽነት ማንነቱን ተገንዝቦ የሚቀዳጀው፣ ለፈጠራ ስራና ለሁለ-ገብ የአገር ግንባታ የሚያስፈልገው ቅድመ-ሁኔታ ነው። በአውሮፓ የህብረተሰብ ታሪክ ውስጥም የተረጋገጠው፣ በተወሳሰበ መልክ የተካሄደውና በብዙ መልክ የሚገለጸው ነፃነት ተግባራዊ ሲሆን ብቻ ነው ቀስ በቀስ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ የኢኮኖሚ ዕድገት ሊታይ የቻለው።

ይህ ብቻ ሳይሆን፣ በካንት ዕምነት ሩሶ እንደሚለው የሰው ልጅ ህይወት ዕውነተኛ ትርጉም በነፃነት ዓለም ሲኖር ብቻ ነው። ምክንያቱም ክብርና ነፃነት ለሰው ልጅ እጅግ አስፈላጊ ስለሆኑ ማንኛውም የሰው ልጅ የሌላ ሰው ፍላጎት ተገዥና በሱ እየታዘዘ መኖር የለበትም። በሌላው ፍላጎት መኖርና ማጎብደድ የራስን የኑሮ ትርጉም አለመረዳት ብቻ ሳይሆን፣ ራስን እንዳልነበረ አድርጎ መሰረዝና ማዋራድ ነው። ስለዚህም ይላል ካንት፣  “በዚህ ዓለም ላይ እጅግ የሚያስከፋው ነገር በራስ ፍላጎት አለመመራት ወይም የሌላው ተገዢ መሆን ነው“፣ በማለት ነፃ ፍላጎት የቱን ያህል የሰውን ልጅ የመኖርና ያለመኖር፣ አንድ ህብረተሰብ በስነ-ስርዓት መገንባት መቻሉንና አለመቻሉን የሚረዳን ነው ይላል። ካንት ፍሪ ዊል ወይም ነፃ ፍላጎት ሲል አናርኪ ይፈጠር ማለቱ አይደለም። ወይም አንዱ ሌላውን አያክብር ማለቱም አይደለም። ካንት ስለ ሰው ልጅ ነፃነትና ዕውነተኛ ፍላጎት ሲያስተምር የሰው ልጅ ዕውነተኛ ነፃነት ሲሰማው የመፍጠር ኃይሉም ይዳብራል። ራሱንና የሌላውን ሰው ማንነት  በመረዳት የበለጠ ከተፈጥሮ ጋር ያለውን ግኑኝነት ይገነዘባል። በካንት ዕምነት፣ ኒውተን እንደሚለው ተፈጥሮ በድን አይደለችም ወይም ህይወት የሌላት ነገር አይደለችም። የሰው ልጅም የተፈጥሮና የማይታየው ወይም የረቀቀው መንፈስ አካል ነው። ድርጊቱ ሁሉ የተፈጥሮን ህግ በመረዳት የሚካሄድ ነው። በካንት ዕምነት የነፃነት አስተሳሰብ በብዙ ቅራኔዎች የተወጠረ ነው። ይህም የሆነበት ምክንያት የሰው ልጅ ጭንቅላት ውስጥ ገብተው የሚብላሉ ብዙ ነገሮች ስላሉ አስተሳሰቡ በመወሰንና ባለመወሰን፣ እንዲሁም በነፃነትና ነፃ ባለመሆን መሀከል ይዋልላል። ከዚህ የአዕምሮ ጭንቀትና የአስተሳሰብ ቅራኔ ለመውጣት ተግባራዊ በሚሆን የአርቆ አስተዋይነት ወይም አሳቢነት ነው የመዋለሉ ጉዳይ መስመር ሊይዝ የሚችለው።  ይህም ማለት እያንዳንዱ ግለሰብ ለራሱ የሚሆን የአርቆ አስተሳሰብ መመዘኛ ያወጣል። ይህ መመዘኛው ራሱን የሚጠቅም እንጂ  የሚጎዳው መሆን የለበትም። ስለሆነም ይህ ለራሱ ብሎ የደነገገው ሞራላዊ መለኪያ ለሌላውም የሚያገለግል መሆን አለበት። በሌላ አነጋገር፣ መጽሀፍ ቅዱሱ እንደሚለን፣ „በራስህ ላይ ሊደረግ የማትፈለገውን መጥፎ ድርጊት ለሌላውም ሰው አትመኝ፣ ወይም አትፈፅምበት የሚለውንም አስተሳስበ ካንት በመቀበል የሰው ልጅ የግዴታ በአርቆ-አሳቢነት መመራት እንዳለበት ያስተምረናል። ካንት ካቴጎሪካል ኢምፔራቲቭ(Categorical Imperative) በሚለው ስለሌላው ሰው ማሰብና መሰማት በሚያስተምረው አዌርነስ(Awarness) በሚለው ብዙ መሰረተ-ሃሳቦችን በያዘው ፍልስፍናው ውስጥ ነው ይህንን ወርቅ መመሪያ ያሰፈረው።  የካንት አቀራረብ የእንግሊዞቹን የሆበስን፣ የሎክንና የሁምን አመለካከት የሚጻረር ነው። በእንግሊዞች የኢምፔርሲስት ፈላስፋዎች ዕምነት የሰው ልጅ የፍላጎቱ ተገዢ ነው። አርቆ-አሳቢነቱም ከፍላጎቱ በታች የሚገኝ ነው። ስለዚህም ድርጊቱ ሁሉ አንድን ጥቅም ከማግኘት ጋር የተያያዘ ነው። በተለይም በሁም ዕምነት አርቆ-አሳቢነት የፍቅር ስሜት(Passion) ባርያ ነች። ከዚህም በመነሳት እያንዳንዱ ግለሰብ በዚህ ሎጂክ የሚመራ ነው። በሰው ልጅ አስተሳሰብ ውስጥ ግብረ-ገብነትና(Morality) ስነ-ምግባር(Ethiccs) ቦታ የላቸውም። ግብረ-ገብነት ከአርቆ-አሳቢነት ውጭ የሚገኝና፣ በራሱ ህግ የሚተዳደር ነው። በመሆኑም በኢምፔሪሲስታዊ የሳይንስ አመለካከት ውስጥ ግብረ-ገብነትና ስነ-ምግባር ቦታ የላቸውም።

ካንት ከሩሶ የተማረው የነፃነት ዓለም በግሪኩ ስልጣኔ ዘመን ሌላ ትርጉም ነበረው። እንደሚታወቀው በግሪኩ ስልጣኔ ዘመን በእነ ሶክራተስና በፕሌቶን ዕምነት የሰው ልጅ ችግር ሁሉ አርቆ አለማሰብ ወይም የዕውቀት ችግር ነው። በእነሱ ዕምነት በጊዜው ይታይ የነበረው ችግር፣ ረሃብ፣ ድህነት፣ ጦርነትና በውዥንብር ዓለም ውስጥ መኖር የዚህ ሁሉ ዋናው ምንጭ ዕውነተኛ ዕውቀት አለመኖርና አለመዳበር ሲሆን፣ የሰው ልጅም የራሱን ምንነት ለመረዳት አለመቻል ነው። ስለዚህም አርቆ አሳቢነትን ከትክክለኛ ዕውቀት ጋር በማዋሃድ የሰው ልጅ ነፃነቱን እንዲቀዳጅ ማድረግ ይቻላል ይሉናል። በጥንት የግሪክ ፈላስፋዎች በአንድ በኩልና፣ በሌላ ወገን ደግሞ በሩሶና በካንት መሀከል ተቃራኒ አስተሳሰብ ያለ ቢመስልም ሁለቱም አስተሳሰቦች የሚደጋገፉ ናቸው። ይሁንና ግን በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ ያሉ የገዢ መደቦች፣ ወይም ደግሞ የተሻለ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ሁኔታ ያላቸው የህበረተሰብ ክፍሎች የተቀረው የህብረተሰብ ክፍል ለዘለዓለም ተገዢ ሆኖ እንዲቀርላቸው ዕውቀት የሚባለውን ነገር እነሱ በፈለጉት መልክ እየቀረጹ በማውጣትና በማስተማር ተቀባይነት እንዲኖረው ያደርጋሉ። በመሆኑም እነሶክራተስና ፕሌቶ ሶፊስቶችን ሲዋጉ ያመለክቱ የነበረው የተሳሳተ ዕውቀት የሰው ልጅ ሚናውን እንዳይረዳ ማድረጉ ብቻ ሳይሆን፣ በዕውነትና በውሸት መሀከል ያለውን ልዩነት እንዳይገነዘብ ያደርገዋል። በመሆኑም የገዢ መደቦችና አፈቀላጤዎቻቸው የአንድን ህብረተሰብ ሂደትና አኗኗር ራሳቸው በፈለጉት መልክ በመተርጎምና በማጣመም ሰፊው ህዝብ ነፃ አስተሳሰብንና ዕውነተኛ ዕውቀትን እንዳይጎናፀፍ ያደርጉታል። ስልጣናቸውንም ለማራዘም ሲሉ በህብረተሰብ ውስጥ የሀብት ሽግሽግ በማድረግና ለጦርነት በመዘጋጀት አንድ ህዝብ ተስማምቶ እንዳይኖርና ታሪካዊ ስራዎችን እንዳይሰራ እንቅፋት ይሆኑበታል። በዚያውም መልክ እኩልነትና(justice) ጥበባዊ ስራዎች እንዲሁም ስምምነት ትርጉም አጥተው ጥቂቱ የህብረተሰብ ክፍል ብቻ የሚጎናፀፋቸውና የሚደሰትባቸው ይሆናሉ።  ይህ በራሱ ደግሞ የግዴታ ካንት የሚለውን ነፃ ፍላጎት(Free Will) እንዳይዳብር ያግዳል። በእኔ ዕምነትም ሆነ የካንትን ተከታታይ ስራዎችን ላነበበ በትክክለኛ ዕውቀትና በነፃ ፍላጎት መሀከል ተቃራኒ አስተሳሰብ የለም።  ሁለቱም የሚደጋገፉ ናቸው።

ካንት መገለጽ ማለት ምን ማለት ነው? (What is Enlightenment?) በሚባለው ግሩም ጽሁፉ ውስጥ በጊዜው የነበረውን በዲስፖቲያዊ ወይም በፊይዳላዊ አገዛዝ ይሰቃይ የነበረውን ህዝብ ችግር በማሳየት፣ አንድ ህዝብ ከተተበተበበት፣ ነፃ አስተሳሰብን ከሚያፍን ስርዓት የግዴታ መላቀቅ እንዳለበት ያመልከታል። በሱም አባባል መገለጽ ማለት እያንዳንዱ ግለሰብ በራሱ ድክመት የተነሳ ከተተበተበት ሃሳብን ከሚያፍን ስርዓት ለመላቀቅ የሚያደርገው የመጀመሪያው እንቅስቃሴ ነው። የሰው ልጅ በመሰረቱ ሰነፍ ስለሆነ የማሰብ ኃይሉን አይጠቀምም። አንድ ስርዓት ሲያሰቃየው እሱን እንደ ተፈጥሮ ህግ አድርጎ በመውሰድ የድንቁርናው ወይም የማሰብ ኃይል ድክመቱ ተገዢ በመሆን እሱን በሚመስለው በሌላ ሰው መብቱ ይረገጣል። ካንት እንደሚለን ማንኛውም ሰው በተፈጥሮ የተሰጠው የማሰብ ኃይል ሲኖረው፣ ይህንን ውስጣዊ ኃይሉን በራሱ ጥረት ከፍ ማድረግና  ጥያቄዎችን በመጠየቅ ከተተበተበት የጭቆና ስንሰለት መላቀቅ አለበት።  በጊዜው ዲስፖቲያዊ አገዛዝ ከሃይማኖት ጋር በመጣመር በተለይም ሰፊውን የጀርመን ህዝብ ማንነቱን እንዳያውቅና የህይወቱ ባለቤት እንዳይሆን አፍኖ ስለያዘው ካንት ብቻ ሳይሆን፣  ከካንት በፊትም የነበሩ ሌሎች ምሁራንና፣ በኋላ ደግሞ ሌሎች አዳዲስ የተገለጸላቸው ምሁራን እንደ አሸን በመፍለቅና የመገለጽን ምንነት በማስፋፋት በጊዜው ከነበረው ሃሳብን አፋኝ ስርዓት ጋር መጋፈጥ ጀመሩ። በዚህ መልክ የተቀጣጠለው እሳት በመስፋፋትና አፋኙን ስርዓት መፈናፈኛ በማሳጣት  ጀርመንን የገጣሚዎችና የአሳቢዎች ወይም የፈጣሪዎች አገር ማድረግ ተቻለ።

ከዚህ ስንነሳ የነፃነትን ትርጉም ለማያውቁ ወይም ደግሞ ስልጣን ላይ ቁጥጥ ብለው ሌላውን አምሳያቸውን እንደፈለጋቸው ልናሽከረክረው እንችላለን ለሚሉ፣ ነፃነት የሚለው አስተሳሰብ በመጽሀፍ ቅዱስም በቀጥታም ባይሆን በተዘዋዋሪ መንገድ ሰፍሯል። የብሉ ኪዳይ ሞሰስ ምዕራፍ ዘጠኝ ላይ፣ እግዚአብሔር የሰውን ልጅ በአምሳሌ ፈጠርኩት ይላል። ይህም ማለት ማንኛውም የሰው ልጅ በእግዚአብሄር ፊት እኩል ነው ማለት ነው። በሌላ አነጋገር፣ መጽሀፍ ቅዱሱ የሚለን አንደኛው ሌላውን የመግዛትና እንደፈለገው የማድረግ መብት የለውም። የሰው ልጅ የነፃነት ደረጃ ይለያይ እንጂ የመጨረሻ መጨረሻ ነፃነት የህይወት ትርጉም ነው። የነፃነት ደረጃ ስል አንድ ከእናቱ ማህፀን ያልወጣ ወይም ገና ያልተወለደ እዚያው ውስጥ ለማደግ ሙሉ በሙሉ ጥገኝነቱ በእናቱ ነው። ሲወለድና የመጀመሪያውን ብርሃን ሲያገኝ የተወሰነ ነፃነት አገኘ ማለት ነው። በመቀጠልም መዳህ ሲጀምር የተሻለ ነፃነት ያገኛል። እንደዚያ እያልን ስንሄድ አንድ ልጅ ለአቅመ-አዳም ሲደርስ ሙሉ ነፃነቱን ተቀዳጀ ማለት እንችላለን። ይህ ግን ከአካል አንፃር ስናየውና ከዚህ ቀደም ራሱ ማድረግ የማይችላቸውን መፈፀም ሲችል ነው። ይህ ዐይነቱ የአካል ነፃነት ግን ከጭንቅላት ነፃነት ጋር የማይጣጣምበት ሁኔታ አለ። የአንድ ልጅ የአእምሮ ነፃነት በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ በዳበረና ስር በሰደደ ኋላ-ቀር የአኗናር ስልትና ለፈጠራ ወይንም ራስን በደንብ ለመግለጽ በማይቻልበት መልክ ሊወሰን ይችላል። በሌላ አነጋገር፣ በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ የሚገኝ የማቴሪያልና የአስተሳሰብ ሁኔታ የአንድን ልጅ በአዕምሮ መዳበርና አለመዳበር ይወስናል። ለምሳሌ በዘልማድና በባህል በተጠመደ ህብረተሰብና በሌላ በሰለጠነ ህብረተሰብ ውስጥ ተወልዶ ባደገ ልጅ ወይም ሰው መሀከል ነፃ አስተሳሰብና ፍላጎት የዕድገት ደረጃቸው አንድ አይደሉም። በኢኮኖሚም ሆነ በባህል ወደ ኋላ በቀረ ህብረተሰብ፣ ወይም ነፃ አስተሳሰብ እንደልብ በማይሽከረከርበት ህብረተሰብ ውስጥ ተወልዶ የሚያድግ ልጅ ሳያውቀው የግዴታ በህብረተሰብ ውስጥ የተነጠፉ አስተሳሰቦችን፣ የራስን ፍላጎት ወደ ውጭ አውጥቶ አለመናገር፣ ጥያቄ አለመጠየቅ፣ ለመከራከር አለመድፈር፣ አጎብድዶ ወይም አጎንብሶ መጥፎም ነገር ቢሆን እሺ ብሎ ተቀብሎ መሄድ እንደተፈጥሮአዊ ህግ ተደርጎ የሚወሰድበት ሁኔታ አለ። በተለይም በአገራችን ምድር አሁንም ቢሆን ከላይ የተዘረዘሩ የኢትዮጵያውያን ጨዋ ባህል እየተባሉ የሚወራላቸው የሰውን አስተሳሰብ እንደወጠሩት ነው። ስለዚህም እንደዚህ ዐይነት ህብረተሰብ ውስጥ ጥቂት እናውቃለን የሚሉና ስልጣን የጨበጡ ወይም ተማርን የሚሉ ህብረተሰቡን አፉን እንደሚያሲዙትና አጎብድዶም የነሱን አሰተሳሰብ ብቻ እንዲቀበል የማድረግ ኃይላቸው ከፍ ያለ ነው። ከዚህም በላይ እነዚህ ኃይሎች ከውጭው ኃይል ጋር በመቆላለፍና የርዕዮተ-ዓለምና የጥቅም ሰለባ በመሆን አንድ ህዝብና ታዳጊ ወጣት ልጅ አጎብዳጅ ሆነው እንዲቀሩ ያደርጋሉ። በዚያው መጠንም የድህነቱ ዘመን እየተራዘመ በመሄድ፣ አንድ ህዝብ በማቴሪያል ዕጦት ብቻ ሳይሆን ራቁቱን የሚቀረው የአስተሳሰብ ድህነትም ቁራኛ በመሆን ራሱን እንዳይችል ይደረጋል።

በመሆኑም ከጥንቱ የግሪክ ስልጣኔ ታሪክ ጀምሮ እስከ አውሮፓው የህብረተሰብ ግንባታ ድረስ ለዕውነተኛ ዕውቀትና ነፃነት የተደረገውን ትግል ስንመለከት ልማዳዊና ባህላዊ የሚባሉ አኗኗሮች የቱን ያህል የሰውን ልጅ የተፈጥሮ ተገዢ ብቻ ሳይሆኑ፣ በስልጣን ላይ የተቀመጠው ኃይል ተገዢም በመሆን እግዚአብሄር የሰጣቸውን ዕውነተኛ ነፃነት እንዳይጠቀሙና ችግራቸውን ፈቺ እንዳይሆኑ በመረዳት ነው አዕምሮን ነፃ ለማውጣት ትግል የተደረገው። የግሪኩ ስልጣኔም አነሳስ የሰውን ልጅ መሰረታዊ ቦታ በመረዳት የተደረገ እንቅስቃሴ ነው። የመጀመሪያው ታለስ የተባለው የግሪኩ ፈላስፋ 1)  እግዚአብሔርን የማመሰግነው እንስሳ አድርጎኝ አለመፍጠሩ፣ 2) አረመኔ ሳልሆን የሰለጠንኩ በመሆኔ ነው ይላል። በዚያን ዘመን ግሪኮች ራሳቸውን ከሌሎች ህዝቦች ጋር በማወዳደር እነሱ ብቻ የሰለጠኑ መሆናቸውን ያምኑ ነበር። አንዳንድ የፍልስፍና አስተሳሰቦችን በተለይም ከግብፅም ሆነ ከህንድ ቢወስዱም፣ ለፍልስፍና መልክ የሰጡትና የዕውቀት ሁሉ አባቶች እንዲሆን ያደረጉት የግሪክ ፈላስፎች ናቸው። በተለይም ፍልስፍናን ወደ ውጭ አውጥቶ በገበያ ላይ መከራከሪያ ማድረግና ሌላውን መጋፈጥ፣ ወይም በጥያቄ ማፋጠጥና መልስም እንዲያገኝ ማድረግ በግሪክ ፈላስፋዎች የተስፋፋና ለዕውነተኛ ዕድገትና ነፃ አስተሳሰብ መዳበር አስፈላጊ መሆኑን ግንዛቤ የተደረሰበት ነው።  በተለያዩ የግሪክ ፈላስፎች የዳበሩትን ዕውቀቶች ስናገላብጥ፣ የሰው ልጅ ዕድል ቀደም ብሎ እንደሚታመንበት በአምላኮች የሚደነገግ አልነበረም። የጥፋቱም ሆነ የጥሩ ዕድሉ ወሳኝ ራሱ የሰው ልጅ ብቻ ነው።  ይህም ማለት የሰው ልጅ የማሰብ ኃይሉን መጠቀም ከቻለ ኑሮውን ለማሻሻል ሲል የግዴታ መሳሪያም የሚፈጥርና እስከተወሰነ ደረጃም ድረስ ተፈጥሮ የምታደርስበትን አደጋ በመቋቋም ወደፊት መራመድ ይችላል። ከዚያም በመቀጠልም ስርዓትና የተረጋጋ ህብረተሰብ በመፍጠር ለተከታዩ ትውልድ ማስተላለፍ ይችላል። የሰውን ልጅ የስልጣኔ ታሪክ ካለብዙ ጭንቀት ስንመረምር የበለጠ ነፃ በሆነ ቁጥር የማሰብ ኃይሉ ይዳብራል። የመፍጠር ኃይሉም ይጨምራል። ስርዓትና ስምምነትን ከጭንቅላቱ ጋር በማዋሃድ የተሻለ ኑሮን ይመሰርታል። ነፃነት በሌለበት ቦታ ደግሞ የሰው ልጅ የተፈጥሮ አደጋ ሰለባ ይሆናል። ለበሽታና ለረሃብ ይጋለጣል። ተፈጥሮን የመቆጣጠርና ልዩ ልዩ ነገሮችን እያመረተ ለመጠቀም ያለው ኃይል ይዳከማል። ይህ ሁኔታ በተለይም በአውሮፓ ምድር ውስጥ የካቶሊክ ሃይማኖት ባየለበት ከክርስቶ ልደት በኋላ ከሰድሰተኛው ክፍለ-ዘመን እስከ አስራአምስተኛው ክፍለ-ዘመን ድረስ የአውሮፓ ህዝብ በጨለማ ዓለም ውስጥ እንዲኖር አድርጎታል። ይህ የጨለማ ዘመን ሊደመሰስ የቻለው በሪናሳንስ እንቅስቃሴ፣ ቀጥሎ ደግሞ በሪፎርሚሽን፣  በሳይንስና በቴክኖሎጂ ግኝት አማካይነት ነው። ያረጀውና ህብረተሰቡን ተብትቦ የያዘው ስርዓት በአዲስ ዕውቀት ሲፈተንና ግፊት ሲገጥመው ለአዲሱ ቦታውን በመልቀቅ የአውሮፓ ህዝብ፣ ዕደ-ጥበብን፣ ንግድን ማስፋፋት፣ ከተማዎችን መገንባትና ሌሎች ተዓምር የሆኑ ስራዎችን መስራት ቻለ። ይህ ሁሉ የተገኘው ከላይ በተወረወረ ወይም በገዢዎች ቡራኬ ሳይሆን የዕውነተኛ ነፃነትን ትርጉም በተረዱና ራሳቸውን ለመሰዋት በተዘጋጁ ኃይሎች አማካይነት ነው። የነፃነት ትግል አልፎ እልፎ ካልሆነ በስተቀር የተጀመረውና መስመርም መያዝ የቻለው በግለሰብ ታታሪዎች አማካይነት ነው። ይህ ዐይነቱ ትግል በተገለጸላቸው ቄሶች፣ ፈላስፋዎችና ሳይንቲስቶች፣ እንዲሁም የልዩ ልዩ ጥበብ አዋቂዎች የተቀነባበረ የጭንቅላት ትግልና ተግባራዊም የሆነ ነው። ስለዚህም ከጥንት ዘመን ጀምሮ ለነፃነት የተደረገው ትግል ቁንጽል ሳይሆን ሁለንታዊና የሰውን ልጅ ብቁ(Perfect)እንዲሆን ከማድረግ ጋር የተያያዘ ነው። ካንት እንደሚለው የሰው ልጅ ማቴሪያላዊ ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊም ነው። የመንፈስ ደስታውን የሚጎናፀፈው የግዴታ በሚያገኘው ገቢ ብቻ ሳይሆን መንፈሱ የሚያድስለትን ነገርም የተጎናፀፈ እንደሆን ብቻ ነው። መንፈሳዊ ደስታዎች በልዩ ልዩ ነገሮች ነገር ግን ደግሞ በረቁቁም ሆነ በቀጥታ በሚታዩና  ርካታን በሚሰጡ የሚገለጹ ናቸው። የተለያዩ ሰዎች አንድ ዐይነት ስሜት ስለማይኖራቸው የሚረኩበት የመንፈስ ደስታም ይለያያል። እንዲሁም የንቃተ-ህሊናቸው ደረጃ የመንፈስ ርካታቸውን ሁኔታ ሊወስነው ይችላል።

አብዛኛውን ጊዜ ስለነፃነት የሚጽፉ ኢትዮጵያውያንም ሆነ አንዳንድ በኒዎ-ክላሲካል ወይም ኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚክስ ትምህርት የተካኑ የአውሮፓ ምሁራን የነፃነትን ትርጉም ከገበያ ኢኮኖሚ ጋር ነው ለማያያዝ የሚሞክሩት። ይህ ዐይነቱ አቀራረብ የታሪክን ሂደት የሚያጣምም ብቻ ሳይሆን፣ ነፃነት የሚለውን ትርጉምም እጅግ በጠባቡ እንድንረዳና የንግድ ሰዎች ብቻ እንድንሆን የሚያደርገን ነው። ስለዚህም ነው ከአስራሰባተኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ በጀርመንና በእንግሊዝ ፈላስፋዎች መሀከል የጦፈ ትግል የተካሄደው። የጀርመን ፈላስፋዎችና ሳይንቲስቶች መንገድ የበለጠ ነገሮችን ወደ ውስጥ ጠለቅ ብሎ እንድንመረምር የሚያስችለን ሲሆን፣ የእንግሊዞቹ ደግሞ በቀጥታ በምናየው ላይ ብቻ  ያተኮረና የአንድን ነገር ርስ በርሱ መያያዝና ውስጣዊ ኃይል እንዳለው እንድንገነዘብ የሚያደርገን አይደለም። ለምሳሌ የአዳም ስሚዝን የኢኮኖሚክስ ትምህርት ስንወስድ በኒውተን አስተሳሰብ ላይ የተመሰረተ ነው። በኒውተን ዕምነት ተፈጥሮና ህዋ ርስ በራሳቸው የተያያዙ አይደሉም። ማንኛውም ነገር ወደ ጥቃቅን ነገር፣ ለምሳሌ እንደ አቶም ተበጣጥሶ የሚቀነሰና የሚታይ ነው። እነዚህ ተበጣጥሰውና ተሰበጣጥረው የሚገኙ ነገሮች በተፈጥሮ ውስጥ በሚገኝ ህግ የሚተዳደሩ ስለሆነ፣ እግዚአብሔር ከውጭ ሆኖ ድርጊታቸውንና እንቅስቃሴያቸውን የሚመለከት ነው። ጣልቃ አይገባም። ተፈጥሮም ስርዓት ያላትና በተወሰነ የአርቆ አስተሳሰብ ሎጂክ ስለምትዳደር፣ የሰው ልጅ ይህንን የተፈጥሮን ህግ የመረዳት ኃይል ይኖረዋል። የስው ልጅ እየረቀቀና እያሰበ ሲሂድ በማቲማቲክስ ፎርሙላ አማካይነት አንድን ነገር መረዳት ይቻላል። ልምምድና ነገሮችን ጠጋ ብሎ መመልከትና መመርመር ቦታ የላቸውም። ይህ አሰተሳሰብ ወደ ኢኮኖሚክስ ሲተረጎም በአንድ ህበረተሰብ ውስጥ የሚኖር እያንዳንዱ ግለሰብ በራሱ ዓለም ብቻ የሚሽከረከር ነው። ለራሱ ጥቅም በሚያደርገው እሽቅድምድሞሽና በማይታየው ወይም በረቀቀው እጁ(Invisible Hand) አማካይነት በህብረተሰብ ውስጥ የሚፈጠሩ መዛባቶችን ወደ ሚዛናዊነት እንዲመጡ ያደርጋቸዋል። ከፍ ብለን ስንሄድ ደግሞ በዛሬው የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚክስ ቲዎሪ መሰረት፣ እግዚአብሄር በፈጠረው ተፈጥሮ ላይ ጣልቃ የማይገባውን ያህል፣ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ በሚከሰትበትና ብዙ ህዝብን በሚያሰቃይበት ጊዜ መንግስታት ጣልቃ መግባት የለባቸውም፤ በገበያው ውስጥ ያሉ ኃይሎች በራሳቸው ኃይል ቀውሱን ስለሚያርሙ  መንግስታት ዝም ብለው ነው መመልከት ያለባቸው። ኢኮኖሚውን ከገባበት ቀውስ ለማውጣት ጥረት ማድረግ የለባቸውም። ወደ አዳም ስሚዙ ስንመጣ ደግሞ የሰው ልጅ ወደ ምርትና ወደ ፍጆታ(Homo Economicus) ተቀንሶ የሚታይ ነው እንጂ ሌሎች መንፈሱን የሚያድሱ ፍላጎቶች የሉትም።

ከዚህ ጋር በተያያዘና እንዲሁም ደግሞ የነፃ ንግድንም ሆነ ነፃ ገበያን በህብረተሰብ ግንባታ ውስጥ ያለውን ቦታ በሚመለከት እንደዚሁ የጦፈ ትግል ተካሂዷል። በሌላ አነጋገር፣ የጀርመን ክላሲኮች የገበያን ኢኮኖሚ ባይቃወሙም ከህብረተሰብና ከአገር ግንባታ ውጭ ተነጥሎ መታየት እንደሌለበት ያስተምራሉ፤ ያሳስባሉ። ምክንያቱም በአንድ አገር ውስጥ የሚኖር ዜጋ በስራ-ክፍፍል ቢለያይምና በገበያ አማካይነት የሚገናኝና የሚተሳሰር ቢሆንም፣ ይህ ዐይነቱ ግኑኝትና የስራ-ክፍፍል ጠንካራ አገርንና ህብረተሰብን ከመመስረት ተነጥሎ መታየት የለበትም። ማንኛውም ግለሰብም በመነጣጠል ሳይሆን ዕውነተኛ ነፃነቱን የሚቀዳጀውና ኢኮኖሚውንም በጠንካራ መሰረት ላይ ገንብቶ ተጠቃሚ ሊሆን የሚችለው፣  በአንድ ባንዲራ ስርና ለአንድ ዓላማ የቆመ እንደሆነ ብቻ ነው። በተለይም ህብረ-ብሄሮች እየተመሰረቱና አንዳንድ አገሮች ጠንካራ ኢኮኖሚ እየገነቡ ሲመጡ፣ በብዙ መሳፍንቶች ተከፋፍላ የምትገዛውና የውጭ ወራሪዎች ሰለባ የሆነችው ጀርመን በኢኮኖሚ ዕድገት ወደ ፊት መግፋት አልቻለችም። በፈላስፋዎችና በሌሎች ምሁራን ዕምነት ትናንሽ አገሮች እዚያው በዚያው ተከፋፍለው የሚኖሩ ከሆነ ህዝቦቻቸው በፍጹም ዕውነተኛ ነፃነትንና ዕድገትን እንደማይጎናጸፉ፣ ስለሆነም ይህ ዐይነቱ ክልላዊ አስተዳደር ቆሞ ጀርመን በአንድ አገዛዝ ስር መተዳደር እንዳለባትና፣ የጉምሩክ ኬላዎችም መጥፋት እንዳለባቸው ስምምነት ላይ ደረሱ።  በዚህም አማካይነት ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ብቻ ሳይሆን ግለሰብአዊ ነፃነትም ቀስ በቀስ ተግባራዊ እንደሚሆን ግልጽ ነበር። ምክንያቱም ማቴሪያላዊ ዕድገት በሌለበትና፣ አንድ አገር በተለያዩ የመገናኛ መስመሮች እስካለተያያዘና፣ ህዝቡም ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ መንቀሳቀስ እስካልቻለ ድረስ ዕውነተኛ ነፃነትን በፍጹም ሊቀዳጅ አይችልምና።  በመሆኑም ግለሰብአዊና ህብረተሰብአዊ ፍላጎቶች ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉትና አንድም ህዝብ ዕውነተኛ ነፃነቱን ሊጎናጸፍ የሚችለው ከክልሉ ወጣ ብሎ ማሰብ ሲችልና፣ ከሌላው ጋር በተለያዩ መልኮች ግኑኝነቱን ሲያጠናክር ብቻ ነው። በተጨማሪም ግለሰብአዊ ፍላጎቶች ሊሟሉና እያደጉ ሊሄዱ የሚችሉት አንድ አገር በቴክኖሎጂ እየመነጠቀች ስትሄድ ብቻ ነው። ይህ ዐይነቱ ሂደት ግለሰብአዊ ነፃነትን የሚፃረር ቢመስልም፣ ማንኛውም ግለሰብ ዕውነተኛ ፍላጎቱን ሊያረካ የሚችለው እንደ ሮቢንሰን ክሩሶ በደሴት ላይ ብቻ በመኖርና በመታገል ሳይሆን፣ በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ በተቀናጀ፣ ይሁንና ደግሞ ነፃነትን በማያፍን ህብረተሰብ ውስጥ ነው። ከዚህ አንፃር ነው እነ ላይብኒዝ ሲያስጠነቅቁ የነበረው። በኢምፔሪሲዝምና በነፃ ገበያ ስም ተሳቦ የሚሰበከው ነፃነት የመጨረሻ መጨረሻ ግለሰቦችን ወደ ርስ በርስ ጦርነት እንዲያመሩ የሚያደርግ፣ ወይም ደግሞ ዛሬ እንድምናየው ዓለም ጥቂት ኃይሎች የራሴ ጥቅም ተደፈረብን በማለት አገር የሚያተራምሱበት ሁኔታ ይፈጠራል ብለው በመስጋት ነው የእንግሊዝ ፈላስፎችን አስተሳሰብ አጥብቀው ይዋጉ የነበረው።  የእነ አዳም ስሚዙ የነፃ ገበያ አሰተሳሰብና የነፃነት ትርጉም  በጥቂት ኃይሎችና ፍላጎት በፎርማል ደረጃ የሚታይና የሚገለጽ ሲሆን፣ በመሰረቱ የሩሶንና የካንትን የነፃነት ትርጉም ወይም አስተሳሰብ የሚቃወም ነው። ምክንያቱም በግል ሀብት አማካይነት የናጠጡ ኃይሎች ከመንግስት መኪና ጋር በመቆላለፍ በነፃነት ስም ሌላውን የነሱ ተገዢና በነሱ ፈቃድ ብቻ እንዲተዳደሩ ስለሚያደርጉ ነው። እዚህ ላይ የግል ሀብትን ለመቃውም ሳይሆን፣ ቁጥጥር የማይደረግበት የሀብት ማጋፈፍ የግዴታ ስላምን ያሳጣል። በሀብት የናጠጡ ለሌላው ደንታ ስለማይኖራቸው ጦርነትን ይናፍቃሉ። መንፈሳቸው ባካበቱት ኃይል ስለሚሸፈን ጦርነት ቢቀሰቀስ እነሱ ከጦርነት የሚድኑ ይመስላቸዋል። ስለዚህም ነው የጀርመኑ ሰብአዊነት ከተደመሰሰ በኋላ በአስራስምንተኛውና በአስራዘጠናኛው ክፍለ-ዘመን መጀመሪያ ላይ ብቅ ያሉት አዳዲስ የጀርመን ምሁራን የእንግሊዙን ልቅ የነፃ ገበያ ስልት በመቃወም ህብረተሰብአዊና ማህበረሰብአዊ ኃላፊነት ያለው ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ተግባራዊ መሆን እንዳለበት አጥብቀው ይታገሉና ያሳስቡ የነበረው።

የነፃ ገበያና የነፃ ንግድ አስተሳሰብ በአሸናፊነት ከወጣ ከ18ኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ በዚያው መጠንም የኃይል አሰላለፍ ይለወጣል። የሀብት ቁጥጥርና ክፍፍልም ልዩ መልክ እየያዘ ይመጣል። በካፒታሊስት ህብረተሰብ ውስጥ ሁሉም በዕኩልነት ደረጃ ሀብት መቆጣጠር የማይችሉበት ሁኔታ ይፈጠራል። ስለዚህም ህግና የህግ የበላይነት ከዚህ አዲሱ የህብረተሰብ ግኑኝነት አንፃር የሚነደፉ ሆኑ። ቀስ በቀስ የተገነባውን የኃይል አሰላለፍ የሚያረጋግጡ ናቸው ማለት ነው። የገበያ ኢኮኖሚና የነፃ ንግድ ደግሞ የርዕዮተ-ዓለም ተቀባይነት እንዲኖራቸው የሚሰበክባቸው መሳሪያዎች ወደ መሆን አመሩ። ማንኛውም ግለሰብ በነፃ ገበያ አማካይነት ብቻ ዕውነተኛው ነፃነቱን የሚቀዳጅ ነው በሚል በከፍተኛ ደረጃ መሰበክ ተጀመረ። ይሁንና ይህ ዐይነቱ የነፃ ገበያ በጥቂት ካፒታሊስቶች ቁጥጥር ስር ያለና፣ ማንኛውም ግለሰብ የራሱንም ቢሆን ጥቂት መጦሪያ እንኳ እንዳያዳብር የሚያግድ ነው። በተለይም የፊናንስ ካፒታሊዝም እያደገ ሲመጣ፣  ጥቂቱ ብቻ የብድር ዕድል በማግኘት አብዛኛውን የህዝብ ሀብት የሚቆጣጠርበት ሁኔታ መፈጠር ቻለ። እንደመሬት የመሳሰሉትም የተፈጥሮ  ሀብቶች ወደ ሸቀጣ ሸቀጥነት በመለወጥ ጥቂት ግለሰቦች፣ ባንኮችና የኢንሹራንስ ኩባንያዎች የሚቆጣጠሩበት ሁኔታ ተመቻቸ። እንደዚህ ዐይነቱን የግል-ሀብት ዘረፋና ድህነትን የሚያስፋፋ ፖሊሲን የሚቃወም በክፉ ዐይን የሚታይና ለክፉ አደጋ የሚጋለጥ ሆነ።  በዚህ መልክ የነፃነት ትርጉም በካፒታሊዝም የቴክኖሎጂና የሳይንስ ዕድገት፣ እንዲሁም የሀብት ክምችት ዘዴ በመጣመም፣ ሰፊው ህዝብ ዕውነተኛ ነፃነቱን ሊቀዳጅ የማይችልበት ሁኔታ ተፈጠረ።

ካፒታሊዝም ለመጨረሻ ጊዜ የበላይነትን ከተቀዳጀ ከ19ኛው ክፍለዝ-ዘመን ጀምሮ በነፃ ገበያ ስም የተሰበከው ነፃነትን መቀዳጀት ተግባራዊ እንዳልሆነ በዘመኑ የተደረገውን ካፒታሊዝምን የሚጻረር ትግል መመልከቱ ይበቃል። በኢንዱስትሪ አብዮት አማካይነት ከእርሻ መሬት እየተፈናቀለ ስራ ለመፈለግ ሲል ወደ ዋና ከተማዎች እንዲፈልስ የተደረገው ጉልበቱን ከመሽጥ በስተቀር ሌላ ነፃነት እንዳልነበረው በዚህ አካባቢ የተጻፉ አያሌ መጽሀፎች ያረጋግጣሉ። ሰፊው ስራ ፈላጊ ህዝብ እንደ ቆሻሻ የሚታይና በየመንገዱ ላይ የሚያድርና፣ ከመንገድ ላይ ምግብን እየፈለገ የሚመገብ ነበር። በየፋብሪካው ተቀጥሮ የሚሰራው ሰራተኛ ደግሞ ለአሰሪው ታዛዥ ከመሆን በስተቀር በሙያ ማሀበር የመደራጀት መብት እለነበረውም። እጅግ በሚያሰለች መልክ ከማሽን ጋር እየታገለ ከማምረት በስተቀር ብሶቱንና ፍላጎቱን የመግለጽ መብት አልነበረውም። እንደዚህ ዐይነቱ ሁኔታ ሰፍኖ ይገኝ የነበረው ከሶስት መቶ ዐመት በኋላ የሰውን ጭንቅላት የሚያድስ የባህል አብዮት ከተካሄደና፣ በተከታዩ ደግሞ ኤላይንተሜንት የተባለው በሞናርኪዎች ፍጹም አገዛዝ ላይ የተነሳው ምሁራዊ እንቅስቃሴ ብዙ የአውሮፓ አገሮችን ካዳረሰ በኋላ ነው።

በ20ኛው ክፍለ-ዘመን ካፒታሊዝም  በማያወላውል መልክ የበላይነትነትን ሲቀዳጅ የሰው ልጅ ነፃነት በፍጆታ ግዢና ጥቅምን ከማሳደግ አንፃር ብቻ የሚታይ ሆነ። ማንኛውም ግለሰብ በገበያ ፊት ቢያንስ በፎርማል ደረጃ ነፃ ሆኖ የሚታይ ሆነ። ይህም ማለት ነፃንቱ ሊወሰን የሚችለው ባለው የመግዛት ኃይል(Buying Power) ብቻ ነው። በሌላ አነጋገር፣ የነፃ ገበያ እዚያው በዚያው የማግለል ባህርይም አለው ማለት ነው።  በዚህ መልክ ካፒታሊዝም በአገር ደረጃ መወሰኑን ሲያቆምና ዓለም አቀፋዊ ባህርይ ሲወስድ በትምህርት ደረጃ የኢኮኖሚክስ ትምህርት የሰውን ልጅ የነፃነት ትርጉም በዚህ የአስተሳሰብ ክልል ብቻ እንዲወድቅ አደረገ። በንግድ አማካይነት ሁሉም አገሮች የሚተሳሰሩበት ሁኔታ ተፈጠረ። በማምረት አማካይነት ሳይሆን አንድ ህብረተሰብ የሚሻሻለው በንግድ አማካይነት ከሌላው ዓለም ጋር የተሳሰረ እንደሆነ ነው የሚለው በሰፊው መሰበክ ተጀመረ። በአስራሰባተኛውና በአስራስምንተኛው ክፍለ-ዘመን ብቅ ያሉት የእንግሊዝ ፈላስፎችና የነፃ ንግድና የነፃ ገበያ አራማጆች እዚያ በዚያው የቅኝ ግዛት አራማጆች የነበሩ ያዋቀሩት እንደ ኢስት- ኢንዲያን ካምፓኒ(East Indian Company)  የመሳሰሉት አዲስ በተፈጠረው ዓለም አቀፋዊ ግኑኝነት ልዩ አወቃቀር በመያዝ ዛሬ የሶስተኛው ዓለም ተብለው የሚጠሩ አገሮችን ወደ ተራ ጥሬ-ሀብት አምራችነት መለወጥ ቻሉ። የነፃነት ትርጉምም በዚህ የንግድ እንቅስቃሴ ክልል ውስጥ የሚታይ ሆነ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ነው በብዙ የሶስተኛው ዓለም አገሮች ቀደም ብለው የተዋቀሩ የስራ-ክፍፍሎችና የህብረተሰብ አወቃቀሮች እንዲጨናገፉ በመደረግ ቀስ በቀስ እያለ በማደግ ላይ ባለው ግሎባል ካፒታሊዝም መዳፍ ስር እንዲወድቁ የተደረገው። ልክ ሩሶና ካንት እንዳስተማሩን አንድ ሰው የሌላው ጥገኛና ታዛዥ ከሆነ ነፃነቱን ተገፈፈ ማለት ነው ብለው እንዳስተማሩን፣ በግሎባል ካፒታሊዝም ስር የተዋቀረው ዓለም አቀፋዊ ንግድ በብዙ ሚሊዮን የሚጠጉ የሶስተኛውን ዓለም አገር ህዝቦችን ወደ ባርነት ለወጣቸው። ይህም ማለት አንድ ሰው ወደ ተራ አምራችነት ከተለወጠ እግዚአብሔር የሰጠውን የመፍጠር ኃይል ተነጠቀ ማለት ነው። ባርያ ሆነ ማለት ነው። በማሰብ ኃይሉ ልዩ ልዩ ነገሮችን በመፍጠርና በማምረት ፍላጎቱን አሟልቶ ወደ ህብረተሰብ ኃይል ሊሸጋገር አይቸልም። ነፃ አገር ሊመሰርት አይችልም። ከዚህ በመነሳት ነው በእኛና በተቀሩት የሶስተኛው ዓለም አገሮች ሊኖር የሚገባውን  የነፃነት ትርጉም ምንነት መረዳት የምንችለው። በሌላ አነጋገር፣  አገዛዞች ቢለዋወጡም አንኳ፣ ይህ ዐይነቱ ዕውነተኛ ነፃነትን የሚያፍን የስራ-ክፍፍልና የነፃ ንግድ የሚለው አስተሳሰብ እስካለተናጋና መሰረታዊ የአስተሳሰብና የአመራረት ለውጥ እስካልተካሄደና ተግባራዊ እስካልሆነ ድረስ፣ ነፃነት ያስፈልጋል የሚለው አባባል ለአብዛኛው ህዝብ ትርጉም አይኖረውም ማለት ነው።

ያም ሆነ ይህ ለግለሰብአዊም ሆነ ለህብረተሰብአዊ ነፃነት የተደረገው ትግል በተወሰኑ ነገሮች ላይ ብቻ ያተኮረ ሳይሆን ከአጠቃላዩ የህብረተሰብ አወቃቀር ጋር የተያያዘ ነው። ይህም ማለት በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ የተዋቀረው መንግስታዊ መኪና፣ የምርት ግኑኝነት፣ ባህላዊና ርዕዮተ-ዓለማዊ ጉዳዮች፣ የጠቅላላው የህዝቡ አኗኗር ጉዳይ፣ መንግስትና አገዛዙ ዕድገትንና ስልጣኔን በሚመለከት ያላቸውን አሉታዊ ተፅዕኖ፣  … ወዘተ.፣  እነዚህና ሌሎችንም፣ ለአንድ ግለሰብም ሆነ ለጠቅላላው ህብረተሰብ ዕድገት እንቅፋት የሆኑ ነገሮችን  የመመርመሩና እነዚህን የመታገሉ ጉዳይ የነፃነት ትግል መሰረታዊ ሃሳቦች ናቸው። በሌላ ወገን ደግሞ ለነፃነትና ለነፃ ሃሳብ እንታገላለን የሚሉ ግለሰቦችም ሆነ ቡድኖች ከአንድ ህብረተሰብ ውስጥ የሚፈልቁ ሲሆኑ፣  ከነበረው ለዕድገትና ለስልጣኔ ከማያመች ሁኔታ ቀድመው የሄዱና፣ የአንድም ህብረተሰብ ዕድል በእንደዚህ ባለ የጨለማና የተዝረከረከ ኑሮ መወሰን እንደሌለበት የተረዱ ናቸው።  ይህም ማለት ጭንቅላታቸውን ሙሉ በሙሉ ከፊዩዳላዊ ወይም ከኋላ-ቀር አስተሳሰብ ያጸዱ ሲሆን፣ የነፃነትን መሰረታዊ ሃሳብ በፍልስፍናና በቲዎሪ መሳሪያ በሰፊው እያብራሩ ማስተማር የሚችሉ ናቸው። በአውሮፓ የህብረተሰብ ታሪክ ውስጥ ለግለሰብአዊና ለህብረተሰብአዊ ነፃነት የተደረገውን ትግል ስንመለከት በመጀመሪያ ደረጃ በጠብመንጃና በመጋፈጥ የተደረገ ትግል ሳይሆን በከፍተኛ የጭንቅላት ምርምር፣ አርቆ-አስተዋይነትን(Rationality)፣ ህብረተሰብአዊ ኃላፊነትን(Awareness)፣ የሌላውን ሰው የኑሮ ሁኔታ መሰማትንና(Feeling) ሌሎችንም ነገሮችን ያካተተ የትግል ዘዴ ነው። እንደዚህ ዐይነቱ የትግል ዘዴ በየኤፖኩ መልኩን ይለዋውጥ እንጂ፣ የመጨረሻ መጨረሻ ዋናው ዓላማው አንድን ህብረተሰብ ወይም ህዝብ የማንም ተገዢ እንዳልሆነና፣  ማንኛውም ግለሰብ የራሱን ዕድል በራሱ መወሰን እንዳለበት ለማስጨበት ሲሆን፣ በዚህም አማካይነት ታሪክን ሰርቶ በስምምነትና በሰላም እንዲኖር ለማድረግ ነው። እንደዛሬው በጊዜው የነበረው ግንዛቤ የሰላምና የነፃነት ጠንቅ የሚሆኑ ስልጣንን የጨበጡና በሀብታቸው የሚመኩ ናቸው። አብዛኛውን ጊዜ እነዚህ ኃይሎች የማሰብ ኃይላቸውን መጠቀም ስለማይችሉና ሀብት ካላቸው ጋር በጥቅም ስለሚተሳሰሩ አንድ ህዝብ ነፃነቱን እንዳያገኝ የተለያየ ዘዴ በመፍጠር ፍዳውን ያሳዩታል። በዚህም ምክንያት የተነሳ የዕድገት እንቅፋት በመሆን አንድ ህዝብ በዘለዓለማዊ ድህነት ውስጥ እንዲኖር ያደርጋሉ። በአንድ አገር ውስጥ የተትረፈረፈ የተፈጥሮ ሀብት ቢኖርም እንኳ ሰፊው ህዝብ እነሱን በስነስርዓት አውጥቶ ቅርጽ በመሰጠትና በመለወጥ አዲስ ህይወት እንዳይገነባ ያግዱታል። ኑሮው ሁሉ እንዲጨልም ያደርጋሉ።  ስለሆነም ነው በአውሮፓ ምድር ውስጥ በፍልስፋናና በሳይንስ አማካይነት ህብረተሰቡን ነፃ ለማውጣት እልክ ያስጨረሰ ትግል የተካሄደው። ትግሉን የጀመሩት ደግሞ ተራ ሰዎች ወይም ቃልን በመወርወር በሚዝናኑ ሰዎች ሳይሆን፣ ልክ ከእግዚአብሄር የተላኩ ይመስል የራሳቸውን ህይወት በመሰዋት አንድን ህዝብ ከጨለማ ኑሮ ማውጣት አለብን ብለው ቆርጠው በተነሱ ሰዎች ነው። ሶክራትስን እግዚአብሄር ከሰማይ ዱብ አድርጎ የላከው ፍጡር ነው ማለት ይቻላል። ሌሎችም እንደ ፕሌቶንና አርስቴቶለስ፣ እንዲሁም አያሌ የግሪክ ፈላስፋዎች፣ የሳይንስና የድራማ ስዎች እንደዚሁ ልዩ ፍጡሮች ናቸው። የኋላ ኋላም ብቅ ያሉት፣ እንደ ቄስ ኩዛኑስ፣ ዳንቴ፣ ዳቪንቺ፣ ጋሊልዮ፣ ኬፕለር፣ ላይብኒዚ፣ ሺለርና ካንት፣ እንዲሁም ሌሎችም እነሱን የመሳሰሉት የጀርመን አይዲያሊስቶች ዕንቁ ጭንቅላት የነበራቸውና ከተንኮል አስተሳሰብም የጸዱ ሲሆን፣ ዕውቀታቸውም ዓለም አቀፋዊና ዘለዓለማዊ ባህርይ ያለው ነው። ስለሆነም ነው የአውሮፓ ህዝብ ብቻ ሳይሆን የዓለም ህዝብ በጠቅላላው ከጨለማ በመላቀቅ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመፍጠር እርስ በርሱ መገናኘት የቻለው።

ከዚህ ዐይነቱ የተወሳሰበና ከፍተኛ የጭንቅላት ምርምርን ከሚጠይቅ ትግል የምንገነዘበው ሀቅ፣ አንድ ሰው ነፃነት የሚለውን ጽንሰ-ሃሳብ ከመወርወሩ በፊት የቱን ያህል መንፈሳዊ ነፃነትን እንደተቀዳጀና  በነፃስ ማሰብ እንደሚችል ራሱን መጠየቅ አለበት። በሌላ አነጋገር፣ ጭንቅላቱ ከማንኛውም እቡይ አስተሳሰቦች የጸዳና፣  የአንድን ህብረተሰብ አስቸጋሪ ሂደት የተረዳና፣ ይህንንም በጥሩ የቲዎሪና የፍልስፍና መነጽር መመርመር የሚችል መሆን አለበት።  በበሁለተኛ ደረጃ፣ ዕውነተኛ ነፃነት በጉልበት ወይም በጠብመንጃ የማይገኝ መሆኑን የተገነዘበ መሆን አለበት። ይሁንና ግን አንድ አገዛዝ አረመኔ ከሆነና ከፍተኛ በደልም የሚፈጽም ከሆነ ለዚህ ጸሀፊ አመጻዊ ትግል አስፈላጊ እንደሆነ ይገነዘባል። አንድ አገዛዝ በማንኛውም ጊዜ ቢሆን በብዙ መቶ የሚቆጠሩ ስዎችን ቀርቶ አንድን ሰው እንኳ የመግደል መብት የለውም። ከዚህም በላይ አንድ አገዛዝ ቆርጦ በመነሳት ዕድገትን የሚቀናቀን ከሆነ የግዴታ አመጻዊ ትግል ከፍልስፍናና ከቴዎሪ ጋር እየተጋዘ ተግባራዊ መሆን አለበት።  በሶስተኛ ደረጃ፣ ለነፃነት የሚደረገው ትግል የመጨረሻ መጨረሻ አንድን ህዝብ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት የሚያደርገው መሆን አለበት። በዚህም አማካይነት አንድ ህዝብ ጥበባዊ አገር ለመመስረት ወይም ለመገንባት የሚችል መሆን አለበት።  በሌላ አነጋገር፣ የአንድ አገር ህዝብ ኑሮ በቆንጆ ከተማዎችና፣ በቆንጆ መንደሮች የሚገለጽ መሆን አለበት። በባህላዊ ዕድገት የሚታይ መሆን አለበት። አንድ ህዝብ ከልማዳዊ ኑሮ ተላቆ ህይወቱን በአዲስ መልክ ማደራጀት መቻል አለበት። በአራተኛ ደረጃ፣ ዕውነተኛ ነፃነት አንድን ህዝብ የስልጣን ባለቤት(Empower) የሚያደርገው መሆን አለበት። ይህ ሲሆን ብቻና፣ በየጊዜው እየነቃ ሲሄድ አንድ ህዝብ በእርግጥም ዕውነተኛ ነፃነቱን ሊቀዳጅ ይችላል።

ወደ አገራችን ስንመጣ እስካሁን ድረስ ለነፃነት የተደረገው ትግል ግቡን መምታት ያልቻለው ከላይ የተዘረዘሩትን መሰረተ-ሃሳቦች ማሟላት ባለመቻሉ ነው። እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ህብረተሰብ በአጠቃላይና፣ ብሄረሰቦች በተናጠል በሳይንስ፣ በፍልስፍና፣ በስዕል፣ በድራማ፣ በአርክቴከቸርና በከተማ ግንባታ፣ በዕደ-ጥበብ ሙያና በንግድ እንቅስቃሴ የሚገለጽ ምሁራዊ እንቅስቃሴ አልነበራቸውም፤ ዛሬም የላቸውም። ህብረተሰባችንም የተገለጻለቸው ምሁሮችን የማፍራት ዕድል አልነበረውም። በዚህም ምክንያት የተነሳ አገዛዞችንና ልማዳዊ የአኗኗር ስልትን የሚጋፈጥና ሌላ የዕድገት አቅጣጫን ሊያሳይ የሚችል ወይንም አዲስ የህይወት ብርሃንን ሊያፈናጥቅ የሚችል ኃይል ሊፈጠር አልቻለም። ስለሆነም ህዝባችን  የተፈጥሮን ምንነት ተገንዝቦ ወደ ተወሳሰበ የህብረተሰብ ግንባታ ለመጓዝ የሚያስችል መንፈሳዊ ኃይልን ሊቀዳጅና ኑሮውን በአዲስ መልክ ሊያደራጅ አልቻለም። የጠቅላላው ህዝብ ኑሮ ተደጋጋሚና የዘልማዳዊ ኑሮ በመሆኑ ለፈጠራ አያመችም ነበር። በዚህም ምክንያትና በሌሎች አያሌ ምክንያቶች የተነሳ የነፃነትን ትርጉም ተረድቶ በከፍተኛ እምርታ ሊታገል የሚችል ኃይል ብቅ ሊል አልቻለም።  አብዛኛውን ጊዜ ባለማወቅ የተነሳ የተዋቀረው ጠቅላላው ስርዓትና ከዚህ የፈለቀው አስተሳሰብ በራሳቸው የነፃነት ተቀናቃኝ በመሆናቸው በቴክኖሎጂና በልዩ ልዩ ነገሮች ሊገለጽ የሚችል ዕድገት ሊመጣ አልቻለም።

በአለፉት ሃምሳ ዐመታት ለዲሞክራሲና ለነፃነት የተደረገውን ትግል ስንመለከት፣ ይደረግ የነበረው ትግል ጠቅላላውን ህብረተሰብአዊ አወቃቀርና የህዝቡን የአስተሳሰብ መነሻ አድርጎ ከመመርመር ይልቅ በተወሰኑ ነገሮች ላይ ብቻ በማትኮር ነበር። በአገራችን የተለመደ አንድ አነጋገር አለ። ለዕድገት ጠንቅ የሆኑት አገዛዙና ስርዓቱ ናቸው የሚል ተራ አባባል አለ። በሌላ በኩል ግን ለምን አገዛዙና ስርዓቱ ለዕድገት ጠንቅ ሆኑ? ተብሎ ጥያቄ አይቀርብም።  በማወቅ ወይስ ባለማወቅ? የዕድገት እንቅፋት ሊሆኑ ቻሉ ብሎ ነገሩን ዘርዘር አድርጎ ለመጠየቅ ሙከራ አይደረገም። እንደሚታወቀው አብዛኛውን ጊዜ እንደዚህ ያሉ ለዕድገት ጠንቅ የሆኑ ፊዩዳላዊ ስርዓትን የመሳሰሉትና ዛሬም በሌላ መልክ የሚገለጹት ይሁንና የነዑስ ከበርቴው ፋሺዝም የሰፈነበት ስርዓት የሚዋቀሩት በማወቅ አይደለም። ህብረተሰቦች በጨቅላ ዘመን በሚገኙበት ወቅት እንደዚህ ዐይነት ዕድገትንና ስልጣኔን የሚቀናቀኑ በተለያየ መልክ የሚገለጹ የአሰራርና የአመራረት ስልቶች መፈጠራቸው እንደተፈጥሮአዊ ሆነው የሚታዩ ናቸው። ጭቆናዎች ሲበዙና የህዝቡም ኑሮ ባለበት የረጋ ከሆነ ይህ ዐይነቱ ሂደት ትክክል ሆኖ የማይታያቸው ምሁራን ከመቅጽበት ብቅ የሚሉበት ጊዜና ቀስ በቀስም አስተሳሰባቸውን በማዳበርና በማስፋፋት ስርዓቱን የሚጋፈጡበት ጊዜ አለ። ይህ ዐይነቱ የመመራመርና የመጋፈጥ ባህል ወይም ልምድ ወይም ደግሞ ደቀ-መዝሙሮችን የማፍራት ባህል ባልተለመደበት አገር ህብረተሰቦች ባሉበት ረግጠው እንዲቀሩ ይገደዳሉ። በዚህም ምክንያት ነው የኢትዮጵያው ፊዩዳላዊ ስርዓት በተለይም በሰሜኑ የኢትዮጵያ ግዛት ለስምንት መቶ ዐመታት ያህል ተንሰራፍቶ መቆየት የቻለው። በሌላ ወገን ግን የምዕራብ አውሮፓን የዕድገት ታሪክ፣ የፍልስፍናንና የተፈጥሮ ሳይንስን ምርምር ስንመለከት በአብዛኛዎቹ የምዕራብ አውሮፓ አገሮች ውስጥ ከአስራአምስተኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ ዩኒቨርሲቲዎች በብዙ ከተማዎች ውስጥ ተቋቁመዋል። ለምርምርና ለፈጠራ  የሚያገለግሉ ቤተመጻህፍትም ተስፋፍተዋል። በተለይም ጀርመናዊ ጉተንበርግ የማተሚያ ማሺንን ከፈጠረ በኋላ የግሪክን ዕውቀት ወደ ላቲንና የኋላ ኋላ ደግሞ በየአገሩ ቋንቋ እየተረጎሙና ከጊዜው ጋር እንዲሄድ እያሻሻሉ ማስፋፈት የተለመደ ነበር። ለዚህ ነው ከሬናሳንስ እንቅስቃሴ ጀምሮ፣ በተለይም ከኢንላይተንሜንት እንቅስቃሴ በኋላ አያሌ መጽሀፎች እንደ አሸን  ሊፈልቁና ሊስፋፉ የቻሉት። የትርጉም ስራዎችና አዳዲስ ዕውቀቶችንም ማዳበር የየግለሰቦች ጥረት ነበር። ማንም ኃይል ይህንን ጻፍ፣ ይህንን ተርጉም እያለ ያስገደዳቸው አልነበረም።  የጊዜውም አዝማሚያ በዕውቀትና መንፈስን በማደስ ላይ ያተኮረ ሰለበር የምሁራንን መንፈስ የሚያዘበራርቅና ባልባሌ ነገሮች ላይ እንዲያተኩሩ የሚያስገድዳቸው ሁኔታ አልነበረም። እንደዛሬው ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ በባቡር፣ በመኪናና በአውሮፕላን የመጓጓዛ ዕድል አልነበረም። አንድ ምሁርም ሆነ የገዢ መደቦች ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ  ይጓዙ የነበረው በጋሪ ነበር። ለምሳሌ ላይብኒዝ የተባለው የአስራሰባተኛው ክፍለ-ዘመን ሳይንቲስትና ፈላስፋ ከበርሊን ወደ ሞስኮው፣ ፓሪስና ለንደን ይጓዝ የነበረው በጋሪ ነበር። በዚህም አማካይነት ነበር ከመስል ፈላስፋዎችና የተፈጥሮ ሳይንስ ተመራማሪዎች ጋር በመገኛኘት ሃሳብ ለሃሳብ ይለዋወጥ የነበረው። ወደ አገራችን ስንመጣ ግን አብዛኛዎቻችን “ዘመናዊ ዕውቀት” ከሚባለው ጋር መተዋወቅ የጀመርነው ከ1940ዎቹ መጨረሻ ዐመታት ጀምሮ ነው። ይህም ዘመናዊ ዕውቀት የሚባለው የተበላሸና መንፈስን የሚያድስና በጥሩ ዕውቀት የሚቀርጽ አልነበረም። ጥራዝ ነጠቅና አመጸኛ የሚያደረግ ዕውቀት የሚመስል ነበር ከ1950 ዓ.ም መጀመሪያ ጀምሮ መስፋፋት የጀመረው። ለማንኝውም የዕውቀትን መስፋፋትና ዕድገትን ሁኔታ ስንመለከት በአውሮፓና በኢትዮጵያ መሀከል የ500 ዓመት ልዩነት አለ ማለት ነው። ስለሆነም ዛሬ በዚህ ዐይነት የተመሰቃቀለና የዘቀጠ ሁኔታ ውስጥ መገኘታችን ሊደንቀን በፍጹም አይገባም።

የተማሪው እንቅስቃሴ የፊዩዳሉ ስርዓት፣ የኋላ ኋላ ደግሞ ከቢሮክራሲ ካፒታሊዝምና ከኢምፔሪያሊዝም ጋር በመቆላለፍ ለዕድገት ተቀናቃኝ ነው ብሎ ውሳኔ ላይ ሲደርስ፣ በእኔ ዕምነት በተለይም ስርዓቱ ለምን እንደ አውሮፓው ፊዩዳሊዝም ውስጣዊ ኃይል በማግኘትና አዳዲስ ኃይሎችን በማፍለቅ በምሁራዊ ኃይል ሊጋፈጠው አልቻለም? ብሎ ጠለቅ አድርጎ በመመራመር በሰፊ ምሁራዊ እንቅስቃሴ ሊጋፈጠው አልቻለም። ስርዓቱን ሊቀናቀን የሚችል ውስጣዊ-ኃይል ሊፈልቅና ሊዳብር የሚችለው እንደሚታወቀው እያደገ ሊሄድ የሚችል የስራ-ክፍፍልና የንግድ እንቅስቃሴ ሲኖር ብቻ ነው። በተጨማሪም ከተማዎችና መንደሮች ሲቆረቆሩና ህብረተሰብአዊ እንቅስቃሴዎች ሲኖሩ(Social Mobility) ስርዓቱን የሚቀናቁኑ የተገለጸላቸው አዳዲስ ኃይሎች ብቅ ይላሉ። እንደሚታወቀውና ማርክስም እንደሚተነትነው ካፒታሊዝም ከማደጉና የበላይነትን ከመቀዳጀቱ በፊት ቅድመ-ሁኔታዎች የተጣሉት በፊዩዳላዊ ስርዓት ውስጥ ነው።  በእኔ ዕምነት የተማሪው እንቅስቃሴ ይህንን ያልተገነዘበ ብቻ ሳይሆን፣ በአውሮፓ ምድር ውስጥ በሬናሳንስ፣ በሪፍርሜሽን፣ በኢንላይተንሜንትና፣ የኋላ ኋላ ደግሞ በትራንፎርሜሽን ዙሪያና በዘመናዊነት አካባቢ የተደረገውን ሰፋ ያለ ክርክር ጋር በበቂው የተለማመደ ባለመሆኑ የኢትዮጵያን ህዝብ ሰፋ ያለውን የዕድገትና የስልጣኔ ጥያቄ ቀነስ አድርጎ እንዲመለከተው ተገደደ። በመሆኑም ሶስት መፈክሮች ይዞ ሲነሳ በዚህ አማካይነት ብቻ ህብረተሰብአዊ ለውጥን እንደሚያመጣ ነበር የተገነዘበው።  ይህ ብቻ ሳይሆን፣ የተማሪው እንቅስቃሴ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ውጤት በመሆኑኗ፣  በተለያየ መልክ በሚገለጽ ሰፋ ያለ ምሁራዊ እንቅስቃሴ ጋር የተለማመደ ስላልነበር የግዴታ አመለካከቱ ውስን ሊሆን በቃ፤ ወደ ውስጥ ጠለቅ ብሎ የሚያይ መሆን አልቻለም።  እየተከማቸ የመጣውን ችግር  አገዛዙ መፍታት ሳይችልና፣ እንደመሬትና የብሄረሰብ የመሳሰሉት ጥያቄዎች እንደ መሰረታዊ አጀንዳዎች ሆነው ሲታዩ፣ በተለይም በአመራር ደረጃ ያለው የበለጠ ራዲካል እየሆነ መጣ። ይህ ኃይል የደመደመው አገዛዙን በመሳሪያ ታግዞ ከመጣል በስተቀር ሌላ አማራጭ እንደሌለ ነበር የታየው። በሌላ ወገን ደግሞ የአገራችንም ሆነ በተለይም በዓለም አቀፍ ደረጃ የቅኝ አገዛዝንም ሆነ ቀጥተኛ ወረራን ለመዋጋት የጦፈ ትግል ይካሄድ ስለነበር ሁኔታዎቹ ሰፋ ካለ ምሁራዊ እንቅስቃሴ ይልቅ ለመሳሪያ ትግል የሚጋብዙ ነበሩ። መስረታዊ ችግር ይህ ቢሆንም፣  አብዮቱ ከፈነዳ በኋላ የተፈጠረው የዚህ ዐይነቱ ግልጽ ያልሆነና ተወዳዳሪ ያጣው የተማሪው እንቅስቃሴ ያስከተለው እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታ ኃይልን አስተባብሮ በጋራ ለመታገል አንዳይቻል ሁኔታውን አበላሸው። በመሆኑም ሰፋ ባለ የጭንቅላት ተሃድሶ ጉዞ ውስጥ ማለፍ ያልቻለው ወይም ዕድል ያላገኘው የተማሪው እንቅስቃሴ እንደሶቭየት ህብረትና ቻይና፣ በኋላ ደግሞ እንደ ቬትናም ቢያንስ ኃይሉን በማስተባበርና የአስተሳሰብ ጥራት በማዳበር አዲስ አገርና ህብረተሰብ መገንባት አልቻለም። ከብሄራዊና ከስልጣኔ አጀንዳ ይልቅ ስልጣንን ለመጨበጥ በመሽቀዳደሙ አገሪቱን በቀላሉ ሊፈታ የማይችል ችግር ውስጥ ከትቶ አለፈ። የኋላ ኋላም ቶሎ ብሎ የዕርማት እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ እልክ ውስጥ በመግባት የፖለቲካውን ሁኔታ ብቻ ሳይሆን፣ ጠቅላላው የአገሪቱ ሁኔታ እንዲበላሽ የበኩሉን አስተዋፅዖ  አደረገ።

ነገሩን ይበልጥ ግልጽ ለማድረግ፣ በ1917 ዓ.ም እ.አ ሶቭየትህብረት ውስጥ በቦልሺቪኮች የሚመራ ማርክሲስታዊ ሌኒናዊ ኃይል ስልጣንን ከመቀዳጀቱ በፊት፣ ቀደም ብሎ በታልቁ ፔተርና በታላቋ ካታሪኒ ራሺያ ውስጥ ሰፋ ያለ የዘመናዊነት ፖሊሲ ተካሂዷል። ከተማዎች ተገንብተዋል። በራሽያ ውስጥ ካፒታሊዝም ቀስ በቀስ እያለ ሊዳብር ችሏል። ይህ ዐይነቱ መጠነኛ የሆነ የኢንላይንትሜንት ክንዋኔ በራሺያ ምድር የበሰሉ፣ በተለያየ መልክ ሊገለጹ የሚችሉ ምሁራን ብቅ እንዲሉ አመቺ ሁኔታ ፈጥሮላቸዋል። እነ ቶልስቶይና ማክሲም ጎርኪና ዶስቶቮይስኪይ የዚህ ዐይነቱ ሰፋ ያለ የጥገና ለውጥ ውጤቶች ናቸው። በዚያን ዘመን ነው  በራሺያ ውስጥ  የክላሲካል ሙዚቃ መዳበር የቻለው። እነ ሌኒንና ሌሎችም ጠለቅ ያለ የማርክሲስት ኢኮኖሚክስ ዕውቀት ያላቸው እንደ ቡሃሪንና ትሮትስኪ የመሳሰሉት ምሁራን የዚህ ዐይነቱ ከበርቴያዊ የጥገና ለውጥ ውጤቶች ናቸው። ስለሆነም እነ ሌኒን በ1917 ዓ.ም ስልጣን ሲጨብጡ የጀርመን ወረራ ካደረሰባቸው ኢኮኖሚያዊ መንኮታኮትና የህዝብ ዕልቂት በመላቀቅ ቀስ በቀስ ወደ ኢንዱስትሪ ፖለቲካ ለመራመድ የቻሉት የተወሰነ መሰረት ስለነበራቸው ነው። ስታሊን የሰራውን ትልቅ ወንጀል ወደ ኋላ ትተን፣  ከፍተኛ የሆነ የእንዱስትሪ ተከላና እንቅስቅቃሴ መታየት የጀመረው በ1930ዎች ገደማ ነው። ስለሆነም ሂትለር ሶቭየትህብረትን ከወረረና ብዙ ጉዳት ካደረሰ በኋላ በሺዎች የሚቆጠሩ አዳዲስ ታንኮች በማምረትና በማሰማራት የሂትለርን ወራሪ ጦር መደመሰስ ተቻለ።  ይህም የሚያሳየው፣ 1ኛ፟) የዕውቀትን ሁኔታ ነው፣ 2ኛ) የአደረጃጀትን ጉዳይ ነው። 3ኛ) የዲሲፕሊን ጉዳይ ነው። 4ኛ) የመተባበርንና ለአንድ ዓላማ ቆርጦ መነሳትን ነው። እነስታሊን ከጦርነቱ በድል ከወጡ በኋላ ትላልቅ ከተማዎችን መልሰው መገንባት የቻሉት ባላቸው ዕውቀትና ዲሲፕሊን የተነሳ ነው። ከዚያም በኋላ ሶቭየትህብረት የአቶም ኃይል መሆን የቻለችውና ከአሜሪካ ቀድማ ሰውን ወደ ህዋ መላክ የቻለችው ባላት ምሁራዊ ኃይልና ቆራጥነት ነው። ወደእኛ አገር ስንመጣ ግን ነገሩ ሁሉ የተገላቢጦሽ በመሆን በአንድ አገር ውስጥ ከአስር በላይ የሚሆኑ የጦር እንቅስቃሴዎችና የከተማ የደፈጣ ተዋጊዮች በመፈጠር ህብረተሰቡን ማዋከብ ጀመሩ። በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ወጣቶችና ምሁራኖችን እንዲገደሉ አደረጉ። ይህም የሚያመለክተው በጊዜው የነበረውን የተማሪውን እንቅስቃሴ ከፍተኛ የማሰብ ኃይል ድክመት ነው። ሁኔታዎችን አለማጤን፣ የሃሳብ ጥራት አለማዳበር፣ በዲሲፒሊን አለመገዛት፣ ለመተባበር አለመዘጋጀት፣ ሁሉም በየፊናው በመሆን ለስልጣን መታገልና፣ የሚቀናቀነውን መግደል፣ ሰፋ ባለ ዕውቀት ላይ በመመርኮዝ ጠንካራ ድርጅትን አለመመስረት፣ ለግልጽ ዓላማ ከመታገል ይልቅ በህቡዕ በመታገል አስቸጋሪ ሁኔታዎችን መፍጠር፣  ዲሞክራሲያዊ ቶለራንስን ከማስቀደም ይልቅ፣ ከሚቀድመኝ በፊት ልቅደመው በማለት ሁኔታዎችን የባሰውኑ ማዘበራረቅ፣ … ወዘተ. እነዚህና አያሌ ምክንያቶች ተደራርበው በታሪክ ውስጥ ያልታየ የደም መፋሰስና እስከዛሬ ድረስ አልላቀቅ ያለ የቂም በቀል ቁስል በጭንቅላት ውስጥ በመትከል ህዝባችንን ፍዳውን እንዲያይ የተደረገው የህብረተሰብን ህግና በጊዜው የነበረውን አስተሳሰብ ካለመገንዘብ የተነሳ ነው። በአርቆ-አሳቢነትና በምርምር ከመመራት ይልቅ በስሜት ብቻ በመመራቱ በቀላሉ ሊፋቅ የማይችል ቁስል ተጥሎ ታለፈ።  ይህንን የማትተው የተማሪውን እንቅስቃሴ ለመወንጀል ሳይሆን ምሁራዊ እንቅስቃሴን ባልተለመደብትና የመንፈስ ተሃድሶን ባለተጎናጸፈ ህብረተሰብ ውስጥ የተፈጠረን ችግር ለማሳየት ብቻ ነው። ይሁንና ግን አሁንም ቢሆን አስቸጋሪው ጉዳያችን ይህንን ድክመታችንና የተሰራውን ከፈተኛ ስህተት አለመገንዘቡ ወደፊት እንዳንጓዝ አድርጎናል ማለት ይቻላል።

ወደ ቻይናም ስንመጣ ልክ እንደ ራሺያ ቮልሺቪኮች ስልጣናን ከመያዛቸው በፊት የዘመናዊነት ፖሊሲ ተግባራዊ ባይሆንም የነበራቸው ተከታታይ ባህል ራሳቸውን ችለው እንዲንቀሳቀሱ ረድቷቸዋል።  የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ አድሃሪዎች ናቸው ከሚላቸው ኃይሎች ጋር በመተባበር የጃፓንን ኢምፔሪያሊዝም ካባረረ በኋላ በጊዜው አምስት መቶ ሚሊዮን የሚጠጋን ህዝብ በማደራጀት ነው ወደ አገር ግንባታ ማምራት የቻለው። ቻይና እንደ ሰቭየትህብረት ዘመናዊነት የሚባለው ፖሊሲ (Modernization) የተካሄደባት አገር ባትሆንም ለብዙ ሺህ ዓመታት የዳበረው ድርጅታዊና ቢሮክራሲያዊ አገዛዝ፣ እንዲሁም ደግሞ የቻይና በቴክኖሎጂ መዳበርና ለመንፈስ መበልፀግ የሚያግዝ የራሷ የሆነ ፍልስፍና ስለነበረባት ስልጣን ከተያዘ በኋላ ህዝቡን አደራጅቶ አገርን መገንባት ከባድ አልነበረም። ይህም የሚያመለከተው አንድ የሚሰማና በዲስፖሊን የታነፀና እንዲሁም ለመተባበርና ለመቻቻል ዝግጁ የሚሆን የህብረተሰብ ክፍል ስለነበር አገርን መገንባቱ ከባድ አይሆንም ማለት ነው። ለዚህ ደግሞ የግዴታ በራሱ የሚተማንና ለምን ዓላማ እንደተነሳ የሚያውቅና በዲስፕሊንና በሞራል የታነፀ አመራር ዋናው ቅድመ-ሁኔታ ነው። ከዚህ ሁኔታ ስንነሳ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ የታደለም አይደለም። ህብረተሰቡ ተንኮለኞችንና አመፀኞችን እንዲሁም አገር አፍራሾችን የሚያመርት ነው የሚመስለው። እዚያ በዚያው ደግሞ ኩራትና አጉል ጉራ የተወሰነው የህብረተሰብ ክፍል መለዮዎች በመሆን ለፈጠራ ስራና ለአገር ግንባታ እንቅፋት ለመሆን በቅተዋል።

ስለሆነም ሰልነፃነት በሚወራበት ጊዜ ብዙ የማንወጣቸውና የምናወርዳቸው ነገሮች አሉ ማለት ነው። ራሳችንንም መጠየቁ በጣም አስፈላጊ ነው። አንዱ በሌላው ላይ ለማላከክ የሚፈልግ ከሆነና፣ በግልጽ ለመወያየት ዝግጁ እስካልተሆነ ድረስና፣ ትችትንም መሰንዘር እንደ ስድብ ተቆጠሮ የሚታይ ከሆነ በፍጹም አንድ እርምጃ እንኳ መራመድ አይቻልም። ትችት እንደ ንጹህ አየር ወይም እንደ ጥሩ ምግብ መታየት ያለበት ጉዳይ ነው። ትችት ወደ ስድብ የሚቆጥር ሳይሆን፣ ትችት ተፈጥሮአዊ ግዴታና ለአንድ ህብረተሰብ ዕድገት አስፈላጊ ሆኖ መወሰድ ያለበት ጉዳይ ነው። ስለሆነም ትችት የቲዎሪ፣ የፍልስፍናና የሳይንስ አካል ነው። በዚህም ምክንያት ነው በአውሮፓ ምድር ውስጥ ዕውቀት ሊስፋፋ የቻለው። አያሌ ሊትሬቸሮችን ላገላበጠ የሚረዳው አንደኛው ምሁር ተፈጥሮንና የተፈጥሮን ምንነት በአንድ ዐይነት ሊገልጽ ሲሞክር፣ ሌላው ደግሞ በዚህ መልክ ሊገለጽ አይችልም በማለት የሱን አሰተያየት ያዳብራል። በዚህ ዐይነት ትችታዊ አመለካከትና ነገሮችን መረዳት ነው ህብረተሰብአዊ  ዕድገት ሊመጣ የቻለው። ህብረተሰብአዊ ትችት እንደ ጦር በሚፈራበት አገርና፣ አንድ ምሁር እንደ እግዚአብሄር በሚመለክበት አገር ውስጥ  ዕድገትና ስልጣኔ በምንም ዐይነት ሊመጡ አይችሉም።

አብዮት ተካሂዱል በሚባልበት አገር አሁንም ቢሆን እንዲያውም ከፊዩዳሉ ኢትዮጵያ በባሰ ሁኔታ ዛሬ ሃሳብ እንዳይዳብር ሁሉ ነገር ተቆልፎ ተይዟል።  ትችታዊ ሃሳብን ማዳበር አስቸጋሪ እየሆነ መጥቷል። አገዛዙ ብቻ ሳይሆን ተቃዋሚ ነን የሚሉ ግለሰቦችም አምባገነናዊ ባህርይን ያሳያሉ። ለነሱ የመደንገግ መብት የተሰጣቸውው ይመስል አንድ አዲስ ሃሳብ ሲሰነዘር ቶሎ ብሎ ለማፈን ይሞክራል። ሌላው ደግሞ ለመማታት ይቃጣል። አንዳንዱ ደግሞ ወደ መናቅ ያመራል። እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለነው ማለት ነው። ከዚህ ዐይነቱ በሽታ ለመላቀቅ የግዴታ የጭንቅላት ጅምናስቲክ መስራትና ቴራፒ ማድረግ የሚያስፈልግ ይመስለኛል። ልክ ሰውነታችንን ሲያመን ለመመርመርና ለመታከም ወደ ሃኪም ቤት እንደምንሄድ ሁሉ ጭንቅላታችንም መመርመር  ያስፈልገዋል። የጭንቅላታችን በሽታ ግን ሰውነታችን ላይ እንደሚታየው ወይንም ቁርጠት ሲይዘን እንደሚያጎራብጠንና አላስቀምጠን እንደሚለው ዐይነት የሚገለጽ ሳይሆን፣ የጭንቅላት በሽታ የማይታይ፣ የማይዳሰሰና የማይጨበጥ ነው። ሊታወቅ የሚችለው ግን አንድ ህዝብም ሆነ የህብረተሰብ ክፍል ያለበትን ሁኔታ ማየት ሳይችል ሲቀርና ዝም ብሎ አልፎ ሲሄድ የሚገለጽ በሽታ ነው። ይህንን ውድ ወንድማችን ዶ/ር ምህረት ደበበ „የተቆለፈበት ቁልፍና ሌላ ሰው“ በሚለው ግሩም መጽሀፎቹ ውስጥ አብራርቷል። ከዚህም በላይ የጭንቅላት በሽታ በችኮነት፣ በቂም በቀልነት፣ ተንኮል በመስራት፣ የሰውን ስም በማጥፋት፣ ለትችት ዝግጁ ባለመሆን፣  ለመደባደብ በመነሳት፣ ኃላፊነትን ባለመሰማት፣ በዲሲፕሊን እጦት፣ ለሆነው ላልሆነው በመገዛት አገር ለማጥፋት መዘጋጀት፣ ለስልጣንና ለሀብት መስገብገብ፣  ወንጀል ሰርቶ አልሰራሁም ብሎ መዋሸት፣ የራስን ጥፋት በሌላ ሰው ላይ ማላከክ… ወዘተ. የሚገለጽ የረቀቀ በሽታ ነው። ይህ ሁኔታ ነው ለጦርነት መፈጠር፣ ለሰላም እጦትና ለዕድገት ጠንቅ የሚሆንና፣ ስልጣኔዎችና ታሪክ እንዲፈራርስ የሚያደርገው። ስለዚህም ነው እያንዳንዱ ሰው ራሱን ነፃ ካላወጣ ወይም የጭንቅላት ተሃድሶ(Self Emancipation) እስካላደረገ ድረስ አንድ ህዝብ ዕውነተኛ ነፃነትን ሊጎናጸፍና ራሱን በራሱ ማግኘት አይቻልም የሚባለው።

የብሄረሰብና የነፃነት ጥያቄ !!

በአውሮፓው  የሶስት ሺህ ዓመታት ታሪክ ውስጥ የሰውን ልጅ ከጨለማ አውጥቶ እያንዳንዱ ግለሰብ የራሱን ዕድል ራሱ ወሳኝ ለማድረግ ትግል ሲጀመር ፍልስፍና፣ የኋላ ኋላ ደግሞ የተፈጥሮ ሳይንስ ነበሩ ነፃነትን አጎናጻፊ መሳሪያዎች ሆነው የታመነባቸውና፣ እንዲዳብሩና እንዲስፋፉም ርብርቦሽ የተደረገባቸው። በፍልስፍና መሰረተ-ሃሳብ መሰረት፣ ማንኛውም ግለሰብ ከሃይማኖት ወይም ከብሄረሰብ ዕምነት ጋር በመያያዝ የሚወለድ ሳይሆን፣ እንደግለሰብና በእግዚአብሄር አምሳል የሚፈጠር ነው። በተወለደበት አካባቢ ሲያድግ በዚያ ያለውን ከትውልድ ወደ ትውልድ የተላለፉ ኖርሞችንና ባህሎችን በመወሰድ ሳያውቀው ይኖርበታል፣ ይለማመደዋል፤ በመንፈሱም እንዲቀርፅ ይገደዳል ይሁንና ማንኛውም ግለሰብ  በአስተሳሰቡ ሊያድግና በተወሳሰበ መልክ በማሰብ ፈጣሪ በመሆን ነፃነት የሚሰማው ከተተበተበበት የባህል ሰንሰለት ሲላቀቅ ብቻ ነው። እንደየሁኔታው ባህል ጎታችም ነው፤ ለዕድገትም የሚያመች ነው። አዳዲስ ዕውቀቶች በማይስፋፉበት፣ የስራ-ክፍፍል በማይዳብርበትና፣ አንደኛው የማህበረሰብ ክፍል ከሌላው ጋር በማይገናኝበት ቦታ ከትውልድ ወደትውልድ የሚተላለፉ ባህል-ነክ ነገሮች ውስጣዊ-ኃይላቸው በጣም ደካማ ነው። የሰውን የማሰብ ኃይል በማፈን እያንዳንዱ ግለሰብ የማሰብ ኃይሉን በመጠቀም የራሱን ዕድልና ህይወት ወሳኝ እንዳይሆን ያደርጉታል። በአጠቃላይ ሲታይ ግን ባህል ራሱ ውስጠ-ኃይላዊ ክንዋኔ(Dynamic Process) ነው። እስከተወሰነ ደረጃ እስካልሆነ ድረሰ ማንኛውም ማህበረሰብ የራሴን ባህል መጠበቅ አለብኝ ብሎ የሙጥኝ ብሎ እሱን ጠብቆ ሊኖር አይችልም።  እንዲዚህ የሚያደረግ ግለሰብም ሆነ ማህበረሰብ የስልጣኔን ብርሃን ሳይጎናፀፍ ያልፋል። በሌላ ወገን ግን በአሁኑ በግሎባል ካፒታሊዝም ዘመን ቀርቶ የሰው ልጅ በስራ-ክፍፍልና በንግድ ልውውጥ አማካይነት መገናኘት ከጀመረ ጀምሮ እየተሳሰረና እየተዳቀለ መጥቷል። በተለይም በአሁኑ በግሎባል ካፒታሊዝም ዘመን ሁላችንም በቴክኖሎጂ አማካይነት በመደገፍ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ በመንቀሳቀስ ኑሮአችንን ሌላ አገር በመመስረት፣ የአኗኗርና የአስተሳሰብ ለውጥ አምጥተናል። አስተሳሰባችን ክልላዊና አገራዊ መሆኑ ቀርቶ ኮስሞፖሊታን ወይም ዓለም አቀፋዊ ሆኗል። በጋብቻም ከተለያዩ የውጭ አገር ሴቶችም ሆነ ወንዶች ጋር በመጋባት ተቀላቅለናል። ከዚህ ስንነሳ ህይወታችን በክንፈት ዓለም ውስጥ የሚኖር ነው። በአንድ በኩል በአንድ ቦታ ረግተን የምንኖር ብንመስልም ገና ያልተጠናቀቁ ወይም ተግባራዊ ያልሆኑ ህልሞች ስላሉን በሃሳብ ምናልባትም አገራችን ውስጥ ወይም ከመጣንበት ብሄረሰብ ውስጥ ገብተን በሃሳብ እንዋኛለን።  ህይወታችን በቅራኔ ዓለም ውስጥ የሚገኝ ነው ማለት ነው። ስለሆነም፣ በአንድ በኩል በሰለጠነ ዓለም ውስጥ እየኖርን፣ በሌላው ወገን ደግሞ ወደ ኋላ ስንትና ስንት ሺህ ዘመን ተመልሰን የድሮውን ባህል ለመመለስ የምንፈልግ አለን።  በአሁኑ ዓለም አቀፋዊ ተጨባጭ ሁኔታ ደግሞ የኋሊት ጉዞ የማያዋጣ ብቻ ሳይሆን፣  አደገኛም ነው።

ይህ አንደኛው ሲሆን፣ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ በግለሰብ ደረጃም ሆነ በግሩፕ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ እንቅስቃሴ ሲኖር በዚህ አማካይነትም ሆነ፣  በየብሄረሰብ ውስጥ በሚኖረው ውሰጠ-ኃይል አማካይነት ብሄረሰቦች በመጀመሪያው ወቅት የነበራቸውን „የጋርዮሽ መለያ“(Collective Identity) በማጣት እየተሰበጣጠሩና እየተለያዩ(Social Differentiation) ይመጣሉ። በተለይም በአንድ ብሄረሰብ ውስጥ በሚፈጠረው የስራ-ክፍፍል አማካይነትና፣ በዚህም የተነሳ ከሌላው የብሄረሰብ ክፍል ጋር በሚደረገው ግኑኝነት የግሩፕ መለያ እየጠፋ የበለጠ የራስን ጥቅም ማሳደድ በሚለው ላይ አትኩሮ ይደረጋል። በዚህም ምክንያት የተነሳ በአንድ አካባቢ ብቻ ሳይሆን፣ በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ በሚፈጠረው የስራ-ክፍፍልና ህብረተሰብአዊ እንቅስቃሴና የንግድ ግኑኝነት አማካይነት አንዳንድ ግለሰቦች ህይወታቸውን ለማሸነፍ ሲሉ የተወለዱበትንና ያደጉበትን አካባቢ በመተው ወደ ሌላ ቦታ በመሄድ እዚያ ስራ ካገኙ ተቀጥረው በመስራት አዲስ ህይወት መገንባት ይጀምራሉ። በዚህ መልክ ባህርያቸውና የአኗኗር ስልታቸው ይቀየራል።  አንዳንዱ በፋብሪካ ወስጥ ተቀጥሮ ሲሰራ፣ እዚያ ውስጥ ከመሰሉ ጋር በሚያደርገው የቀን ተቀን ግኑኝነት ቀስ በቀስ እያለ ባህርይው ይለወጣል። በዚያው መጠንም አዳዲስ የአነጋገር፣ የአረማመድ፣ የፍጆታ አጠቃቀም ባህርይ በማዳበር ገጠር ውስጥ ካለው ከተመሳሳዩ ብሄረሰብ በተለያዩ ነገሮች እየተለያየ ይመጣል።  ስለሆነም ከአንድ ብሄረሰብ የተውጣጡ፣ ከፊሉ አራሽ ሆኖ ሲቀር፣ የተቀረው ደግሞ አንጠረኛ፣ የፋብሪካ ሰራተኛ፣ ነጋዴና ሀብታም፣ እንዲሁም የመንግስት ሰራተኛ በመሆን በጥንት ዘመን የነበራቸውን „ኮሌክቲቭ አይደንቲቲ“ ያጣሉ። በተለይም በህሊና አወቃቀራቸው የተለያዩ ስለሚሆኑ የማይግባቡብት ሁኔታ ይፈጠራል። እንደዚሁም አውሮፓና አሜሪካ ተሰዶ የሚኖረው ከዚህና ከዚያኛው ብሄረሰብ የተውጣጣ ግለሰብ በአስተሳሰቡ እየተለየ ይመጣል። በመሆኑም ይህንን ተፈጥሮአዊ የሰው ልጅ ሂደትና መሰበጣጠር፣ እንዲሁም የአኗኗር ስልት ቀልብሶ አዲስ መለያ(Identity) ለመስጠት መሞከር ብሄረሰቡን ወደ ኋላ ተጓዝ እንደማለት ይቆጠራል። አንተ ከሌላው የተለየህ ስለሆንክ እዚያው ያለህበት ቦታ በመቅረት መብትህን አስጠብቅ፣ ሀብትህንም ተቆጣጠር ማለት ዕድገትና መሸሻል አያስፈልግህም እንደማለት ነው።

ይህንን ትተን ወደ ሌላ ጉዳይ ላይ ስንመጣ አንድን ብሄረሰብ በጥቅሉ ወስደን መለያይ ይህ ነው፣ በአንድነት ተነስተህ ለመብትህ ታገል ማለት አይቻልም። ለምሳሌ የኦሮሞ ብሄረሰብን ብንወሰድ በአገራችን በየቦታው ተሰብጣጥረው የሚኖሩና የህሊና አወቃቀራቸውም እንደተሰማሩበት የሙያ ሁኔታና በንግድና በተለያዩ የማህበረሰብ ነክ ጉዳዮች ላይ ባላቸው ግኑኝነት የሚለያይ ነው። የባሌው ኦሮሞ ምናልባት በቋንቋ ካልሆነ በስተቀር ከወለጋው ኦሮሞ በብዙ መንገዶች የሚለያዩበት ሁኔታ አለ። ለምሳሌ በወለጋ ውስጥ ቁጥራቸው ጥቂት የማይባል ኦሮሞዎች የፕሮቴስታንት ሃይማኖት ተከታዮች ሲሆኑ፣ የባሌው ኦሮሞ እስላምም የኦርቶዶክስ ሃይማኖትም ተከታይ አለ። ወደ ሸዋ ስንመጣ ደግሞ በዚያ የሚኖረው ኦሮሞ አብዛኛው የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ዕምነት ተከታይ ነው። ወደ ጅማና አካባቢው ስንመጣ አብዛኛው እስላም ሲሆን፣ በህሊና አወቃቀሩ ከወለጋውም ሆነ ከኢሉባቦሩ ኦሮሞ በብዙ ነገሮች ይለያል። እንደዚሁም ከባላባቱ መደብ የወጡ ኦሮሞዎች፣ በተለይም ከአባጅፋር ጋር የዘመድ ግንድ አለን የሚሉ ኦሮሞዎችና ዘመናዊ ትምህርት የቀመሱ በአኗኗራቸው ከገበሬው ወይም ከነጋዴው ኦሮሞ በብዙ መልኩ የሚለዩ ናቸው። ይህ ዐይነቱ የባህርይና የአመለካከት፣ እንዲሁም የአኗኗር ስልት ልዩነት አማራ ተብሎ በሚጠራው ብሄረሰብም ውስጥ ያለ ጉዳይ ነው። ለምሳሌ ጎንደርና ጎጃም አዋሳኝ ሆነው፣ ኑዋሪዎቹ በአነጋገርም ሆነ በአኗኗር ስልት ይለያያሉ። የዘፈናቸውም ቅኝታ ወይም አዘፋፈን ይለያያል። ከዚህ ስንነሳ በተላለየ አካባቢ የሚኖሩና፣  በተለያየ ሙያ እየሰሩ የሚተዳደሩ ግለሰቦችን በአንድ መለያ ለማጠቃለል መሞከር ከሶስዮሎጂ ወይም ከማህበራዊ ሳይንስ አንፃር ትክክል አለመሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ አርቲፊሻል መለያ በመፍጠር አንደኛው ብሄረሰብ በሌላው ላይ እንዲነሳ በማድረግ የስልጣኔውን በር መዝጋት ብቻ ሳይሆን፣ ዘለዓለማችንን እርስ በራሳችን እየተበጣበጥን እንድንኖር ለሚፈልጉና የኛን በዘለዓለማዊ ድህነት እንድንኖር ለሚመኙ አመቺ ሁኔታን መፍጠር ነው። ስለሆነም አርቲፊሻል መለያ መፍጠርና መረጋጋት እንዳይኖር ማድረግ አገርን በጋራ ለመገንባት እንንዳንችል ያደርገናል። ይህ ዐይነቱ ልዩነትም የውጭ ኃይሎች ገብተው በመሀከላችን እንዲፈተፍቱና ርስ በርሳችን እየተበጣበጥን እንድንኖር አመቺ ሁኔታ ይፈጥራል። የሚያሳዝነው ነገር ይህ ጉዳይ  ግልጽ ከሆነ ለምን ከዚኸኛው ወይም ከዚያኛው  ብሄረሰብ የተውጣጡ ኤሊት ነን ባዮች የውጭ ኃይሎች መሳሪያ በመሆን የድህነት ዘመናችንን እንደሚያራዝሙት ነው።

በእኛ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ያለው ትልቁ ችግር፣ ይህንን አስቸጋሪ ጥያቄ ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም ነገሮች ከሳይንስ አኳያ እያነሳን ማጥናትና መከራከር የተለመደ ሳለልሆነ ሌሎችን ላለማስቆጣት ሲባል ብቻ አንዳንድ አስፈላጊ ነገሮች ክርክር ሳይደረግባቸው ተቀብረው እንዲቀሩ ይደረጋሉ። በዚህም የተነሳ በየጊዜው አዳዲስ ሁኔታ ሲፈጠር ሁሉም በየፊናው የፖለቲካ ተዋናይ በመሆን የራሱን አጀንዳ ይዞ በመቅረብና እንደ አዋቂ በመሆን ሌላውን የዋሁን በማሳሳት የስልጣኔና የዕድገት መንገዱን ያጨልምበታል። ትግሉ ለዕውነተኛ ነፃነት መሆኑ ቀርቶ የፖለቲካ መነገጃና እሮሮ ማሰሚያ ይሆናል።  ችግራችንን ውስጥ ለውስጥ በሳይንሳዊ መንገድ እየተወያየን ከመፍታት ይልቅ ፈረንጆች ጋ እየሄድን እሮሮ በማሰማትና ባለን መጠነኛ ቅራኔ ውስጥ ሰርገው እንዲገቡብን በማድረግ ተከፋፍለን እንድንቀር እናደርጋለን። ስለዚህም ከእንደዚህ ዐይነቱ አካሄድ ተላቀን ከዚህም ሆነ ወይም ከዚያኛው ብሄረሰብ እንደመጣን ሳይሆን እንደግለሰብ በአመለካከትና በርዕይ ደረጃ ብንቀራረብና ብንወያይ ችግሩን የበለጠ መረዳት ብቻ ሳይሆን መፍትሄም ለመፈልግ ያስችለናል። ከዚህ በመነሳት ነው የጥያቄውን አነሳስ  መመርመርና፣ የተፈጠረውን ውዥንብር በመጠኑም ቢሆን መረዳት የሚቻለው።

በእኔ ዕምነት የተማሪው እንቅስቃሴ የብሄረሰብን ጥያቄ እንደ አንገብጋቢ ጥያቄ አድርጎ ሲያነሳ በጊዜው ያላያቸውና ያልተገለጹለት ነገሮች ነበሩ። በመጀመሪያ ደረጃ፣ አንዳንድ ግዛቶች ወይም አብዛኛዎቹ ማለት ይቻላል በአንድ ማዕከላዊ ግዛት ውስጥ እንዲጠቃለሉ ሙከራ ሲደረግ ኃይል ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ነው። የታሪክን ማህደር ላገላበጠ በህብረተሰብ ታሪክ ግንባታ ውስጥ ኃይል ወሳኝ ሚናን ተጫውቷል። አንዱ አገር ሌላውን ገባር ለማድረግ ሲል ባህርና ውቅያኖስን በማለፍ አንዳንድ አገሮችን በቁጥጥሩ ስር በማድረግ ሲያስገብራቸውና ዕድገታቸውን ሲወስን ኖሯል። የሮማውያንና የፐርሽያኖች ወረራና ግዛትን ማስፋፋት የተመዘገበና የብዙ አገሮችን ህይወትና ሂደታቸውን የወሰነ ነው። ሮማውያን ያልረገጡብት አንድም የአውሮፓ አገር የለም። በገዙበት ቦታ ሁሉ መሰረት ጥለው አልፈዋል። በባሪያ አገዛዝና በቅኝ ግዛት ዘመንም የተካሄደው አገሮችን ለማስገበርና የነሱ ቅኝ ግዛት አድርጎ ለማስቀረት ነው። ዛሬ ታላቅ የሚባለው አሜሪካንም የጥንት ኗሪ ህዝቦችን በመጨረስና፣ ጥቁሩን ባርያ አድርጎ በመዝበርና በማሰቃየት፣ እንዲሁም ደግሞ በከፍተኛ የዘርኝነት ስሜት በመወጠርና ዝቅ አድርጎ በማየት በመብዝበዝ የተገነባ አገር ነው። ዛሬም ቢሆን ኢንስቲቱሽናላይዝድ የሆነ ዘረኝነት በመስፈን ጥቁር አሜሪካኑ እንደሁለተኛ ዜጋ የሚታይበት አገር ነው። ያውም ወርቅ የመሰለ ህገ-መንግስት እያለና፣ በየአራት ዐመቱም የፕሬዚደንትና የኮንግረስ ምርጫ በሚካሄድበት አገር ዘረኝነት ሰፍኖ ሰፊው ጥቁር ህዝብ ፍዳውን ያያል። ወደ ኮሌጅና ወደ ዩኒቭርሲቲም ለመግባት የሚችለው በጣም ጥቂቱ ጥቁር ብቻ ነው። ይህ ዐይነቱ አካሄድ የማይደገፍ ቢሆንም በታሪክ ውስጥ የታየና አንዳንድ አገሮችም ያለፉበት ሁኔታ ነው።

ወደ አገራችን ተጨባጩ ሁኔታ ስንመጣ በኢትዮጵያዉያን ምሁራን ዘንድ ተነስቶ ያልተብላላ የጭቆና ጉዳይ አለ። ቀደም ብሎም ሆነ በኋላ በአፄ ኃለስላሴ ዘመን አጠቃላይ ጭቆናን በሚመለከት በህብረተሰቡ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በቤተሰብ ውስጥም የነበረ ነው። ጭቆናው ተጨቆኑ የሚባሉ ብሄረሰቦችን የሚመለከት ብቻ ስይሆን፣ ፊዩዳላዊ ስርዓት በሰፈነበት ህብረተሰብ ውስጥ ራሳቸው የፊዩዳል ልጆችም ይጨቆኑ እንደነበር ግልጽ ነው። የፊዩዳል ልጅ ሆኖ ካለዕድሜው ብዙ ከባድ ከባድ ስራዎችን የሚሰራና፣ ቤት ውስጥም ጭቆና የሚደርስበት ልጅ እንደነበር ይታወቃል። እነዚህ ጭቆናዎች በተለያዩ መልኮች የሚገለጹና የአንድን ልጅ ጤናማና ጤናማ ባለሆነ መልክ እንዲያድግ  የሚወስኑ ሲሆኑ፣ አብዛኛውን ጊዜም በማወቅ የሚደረጉ አልነበሩም። ወደ አማራው ክልል ስንመጣም እስካሁንም ድረስ ለአቅመአዳም ከመድረሳቸው በፊት ልጃገረዶች እንዲያገቡ ይገደዳሉ። ከዚህ ስንነሳ በብሄረሰቦች ላይ ሰፍኗል ይባል የነበረውን ጭቆና ከአጠቃላዩ የፊዩዳላዊ አኗኗር ስልትና ከዕውቀት ማነስ ጋር የተያያዘ መሆኑን ብንረዳ መፍትሄም ለመፈለግ አመቺ ይሆናል። በሌላ አነጋገር፣ አንድ ህብረተሰብ ከትውልድ ወደ ትውልድ የተላለፉ የአኗኗር ስልቶችን ይዞ የሚኖር ከሆነና፣ በሌላ በተገለጸለት አስተሳሰብ እስካለተጋፈጠ ድረስ ጠቅላላው ህብረተሰብ የዚህ ዐይነቱ የዕድገት ጠንቅ አኗኗር ሰላባ በመሆን አስተሳሰቡ ውስን መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ አኗኗሩም እንደ ተፈጥሮአዊ ተደርጎ በመወሰድ ድህነት ዘለዓለማዊ መልዮው ይሆናል። በእንደዚህ ሁኔታ ውስጥ የምሁራን ተግባርና ተልዕኮ ችግሩን ከሁለንታዊ አንፃር በመመርመር ሳይንሳዊ መፍትሄ መስጠት መሞከር እንጂ የማይሆኑ መፈክሮችን በማንሳት አንድ ህዝብ በቀላሉ ሊወጣው የማይችል ችግር ውስጥ መክተቱ ከፍተኛ ስህተት እንደመስራት የሚቆጠር ነው። ይህንን አልፈን ወደ ህብረ-ብሄረ መንግስት ምስረታ ጉዳይ እንምጣ።

በአንዳንድ አካባቢ የሚገኙ የተሰበጣጠሩ በመሳፍንት ይተዳደሩ የነበሩ ግዛቶችን ሁኔታ ስንመለከት፣ የታሪክ ግዴታ ሆኖ ትናንሽ ግዛቶች በዚያው ሁኔታቸው ለመኖር አይችሉም ነበር። በተለይም በአስራሰባተኛውና በአስራስምንተኛው ክፍለ-ዘመን የጠነከሩ መንግስታት ደከም ብለው ይገኙ የነበሩ እንደ ጀርመን የመሳሰሉ፣ ገና በአንድ ማዕከላዊ አገዛዝ ጥላ ስር የማይተዳደሩ አገሮችን እየወረሩና እያጠቁ ስላስቸገሩ የግዴታ ጀርመን እንደ አንድ ማዕከላዊ አገዛዝ መዋቀር ነበረባት። በጊዜው ጠንከር ብሎና በባህል ዕድገት ተሽሎ የሚገኘው የፕረሺያው አገዛዝ አልገበርም ያሉትን በሙሉ በጦርነት በመውረርና በማጠቃለል ጀርመን አንድ ለመሆን ስትቃረብ፣ ኃይል በማግኘት ከፈረንሳይና ከአውስትሪያ የተሰነዘረባትን ጦርነት መክታ በመመለስ በ1871 ዓ.ም እ.አ የመጀመሪያው በአንድ ባንዲራ ስር የተጠቃለለ አገዛዝ ተመሰረተ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ጀርመን ለዕድገት እንቅፋት የሆኑ ነገሮችን ሁሉ በማስወገድ በአጭር ጊዜ ውስጥ የኢንዱስትሪና የቴክኖሎጂ ባለቤት በመሆን እንግሊዝንና ፈረንሳይን በአንድ ትውልድ ጊዜ ውስጥ ቀድማ መሄድ ቻለች። በፕረሽያ አገዛዝ ጊዜ ተግባራዊ የሆነው አጠቃላይ የትምህርት የጥገና ለውጥ የኋላ ኋላ በጀርመን ምድር ሳይንቲስቶች እንደ አሸን እንዲፈልቁ አገዘ። ለመጀመሪያ ጊዜ በሃያኛው ክፍለ-ዘመን መጀመሪያ ላይ ሁለት ሶስተኛው የሚሆነው የኖቭል ሽልማት አሸናፊ የሆኑ ሳይንቲስቶች ከጀርመን ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ ነበሩ። ይህ ሁሉ የማዕከላዊ አገዛዝና ልዩ ዐይነት የዕውቀት ውጤት ነው። በሌላ አነጋገር ጀርመኖች ተሰበጣጥረው ቢኖሩ ኖሮ ዕድሜያቸውን በሙሉ በውጭ ኃይሎች በመጠቃት የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባላቤት መሆን ባልቻሉ ነበር።

ወደ አገራችን ስንመጣ በተለይም አፄ ምኒልክ ወደ ደቡቡ የአገራችን ክፍል ያደረጉትን መስፋፋት አስመልክቶ ድርጊቱ ሲኮነንና፣ ጨለማን እንዳመጡ ተደርጎ ይታያል። አንዳንዶቹ እንደሚሉን ከሆነ፣ አፄ ምኒልክ ወደ ደቡብ ግዛታቸውን ከማስፋፋተቸው በፊት ህዝቡ የሰለጠነና፣ የራሱ ቴክኖሎጂና ሳይንስ የነበረው፣ እንዲሁም ደግሞ ከተማዎችን ገንብቶ በስራ-ክፍፍልና በንግድ አማካይነት በመገናኘት ተዝናንቶ ይኖር የነበረ ነው ብለው ሊያሳምኑን ይሞክራሉ።  ሀቁ ግን አነሰም በዛም ሁሉም ግዛቶች ተመሳሳይ ሁኔታ ነበራቸው።  የአማራውም ሆነ ሌላው በኋላ በአንድ ማዕከላዊ አገዛዝ ስር የተጠቃለለው ክፍል በስራ-ክፍፍልም ሆነ በንግድ አማካይነት የዳበሩ አልነበሩም። በመሆኑም በቴክኖሎጂ የሚገለጽ ዕድገት አልነበራቸውም።  ይህ በራሱና ማዕከላዊ አገዛዙ በነበረው ውስጣዊ ድክመት የተነሳ ኢትዮጵያን ሙሉ በሙሉ እንደ አንድ ማህበረሰብ፣ ህብረተሰብና ህብረ-ብሄር በማዋቀር በሳይንስና በቴክኖሎጂ የተመሰረተ ስርዓት  አጠናቆ መገንባት አልተቻለም። በሌላ አነጋገርር፣ ኢትዮጵያ በአፄ ምኒልክ ዘመን፣  የኋላ ኋላ ደግሞ በፄ ኃይለስላሴ ዘመን ወደ ማዕከላዊ መንግስትነት ብትቀየርም፣ ለአንድ አገር እንደ አገር መኖር የሚያስፈልጓት መሰረተ-ሃሳቦች ይጎድሏት ነበር፤ ዛሬም ይጎድሏታል። እነዚህም፣ 1ኛ) የዳበረና የተስፋፋ የስራ-ክፍፍል፣ 2ኛ) ሰፋ ያለ የውስጥ ገበያ፣ 3ኛ) በስነስርዓትና በዕቅድ የተገነቡ ከተማዎችና መንደሮች፣ 4ኛ) ብቃት ያላቸው ኢንስቲቱሽኖች፣ 5ኛ) መንገድና ድልድዮች፣ እንዲሁም የባቡር ሃዲድ፣ 6ኛ) ለአንድ አገር ዕድገትና መሻሻል የሚያስፈልጉ ሳይንስና ቴክኖሎጂዎች፣ 6ኛ) ሰፋ ያለ የዕውቀት መገብያ ኮሌጆች፣ የዕደ-ጠበባ ማሰልጠኛ ተቋሞች… ወዘተ. 7ኛ) የሳይንስ አካዳሚ፣ 8ኛ፟) የቲያትርና የሴኒማ ቤቶች፣ 9ኛ) የስፖርት ተቋሞች፣ 10ኛ) ለሲቪል ሶሳይቲ ማበብ የሚረዱ የሙያ ማህበሮች፣ እነዚህ ሁሉ በጊዜው ደረጃ በደረጃ ታስቦባቸው ለመቋቋም ስላልቻሉ በውስጣዊ ድክመት የተነሳ፣ በአንድ በኩል አገራችን እንደ አንድ ህብረተሰብና ህብረ-ብሄር ልትዋቀር አልቻለችም፤ በሌላ ወገን ደግሞ እንደዚህ ዐይነቱ ክፍተት የተሳሳተ አጀንዳ ላላቸውና አንድ ህዝብ ተስማምቶ ለጋራ ዓላማ እንዳይነሳ ለሚታገሉ ኃይሎች ቀዳዳ በመስጠት እስከዛሬ ድረስ  ራስ ምታት ሆኖብን ሲያሰቃየን ይኖራል። ይሁንና ግን በኢትዮጵያ ምድር ዕድገት አለመታየቱ ሁሉንም ክፍለ-ሀገሮችና ብሄረሰቦች የሚመለከት እንጂ አንዱን ብሄረሰብ ጠቅሞ ሌላውን ለመጉዳት ሲባል አፄ ምኒልክም ሆነ አፄ ኃይለስላሴ በዕውቅ የወሰዱት ጎጂ ፖሊሲ አልነበረም።  እኔ እስከማውቀው ድረስ ኢትዮጵያ ውስጥ የፀረ-ዕድገት ዘመቻ ተካሂዷል ከተባለ ይበልጥ የተጎዳው የአማራው ግዛት ነው። ቡና ወደሚመረትባቸው ክፍለ-ሀገራት ወይም በዛሬው አጠራር ክልሎች የሚሰደደውና ቡና ለቃሚ የሆነው፣ የጎንደሬው፣ የጎጃሜው፣ የወለዬውና የትግሬው ሰው ነው። ስለዚህም ስለበደልና ስለብሄረሰብ ጭቆና ሲወራ ነገሩን ካለማውቅና ሰፋ ያለ የዕድገትን አስፈላጊነት ካለመገንዘብ ጋር ማያያዝ ያስፈልጋል እንጂ፣ ኢትዮጵያ የጨለመችና አስቀያሚ ታሪክ የነበራት አገር ናት እያሉ ማውራትና ማስፋፋት ኢ-ሳይንሳዊ፣ ኢ-ምሁራዊ፣ ኢ-ፍልስፍናዊና ኢ-ጥበባዊ አስተሳሰብ ነው። የህብረተሰብን ዕድገት ታሪክ የሚፃረር አባባል ነው። አንድ ግለሰብም ሆነ ህዝብ ሶሻላይዝድ በመሆን ራሱን በራሱ እሲኪያገኝ ድረስና ታሪክን ይሰራ ዘንድ ብዙ ውጣ ውረድ ያለባቸውን መንገዶች መጓዝ ያለበትን ሁኔታ ካለመረዳት የተነሳ ቀደም ብለው የነበሩ አገዛዞችን አረመኔዎች አድርጎ በመሳልና አገራችንም ጨለማ እንደነበረች ማውራቱ በመሰረቱ ይህ ዐይነቱ አስተሳሰብ በቲዎሪም ሆነ በኢምፔሪካል ደረጃ የሚረጋገጥ ጉዳይ አይደለም።  በተለይም ጭቁን የሚባሉት ብሄረሰቦች ከፍተኛ በደል ይደርስባቸው እንደነበር ይወሳል። አንዳንድ ግለሰቦችና ድርጅቶች ነገሩን ለማሳመር ወይም የሰውን ልብ ለመንካት ሲሉ የሚሆን የማይሆን፣ የህብረተሰብን ህግና ሳይንስን የሚጥስ ነገር ሲናገሩ ይታያል። በተለይም በአሁኑ ዘመን ፕሮፌሽናል ፖለቲከኞች በጠፉበት ዘመንና፣ በተለይም የፖለቲካ ሳይንስ ትርጉም ተጣሞ በሚቀርብበት ዘመን፣ ፍልስፍና፣ ሶስዮሎጂ፣ አንትሮፖሊጂና ሳይኮሎጂ እንደመመሪያ መሳሪያዎች ተደረገው በማይወሰዱበት አገር  ፖለቲካ  መተንተኛና ሳይንሳዊ መሳሪያ መሆኑ ቀርቶ ወደ ስሜታዊነት በመለወጥ የአንድ ህዝብ ታሪክ እንዲጣመም ይደረጋል። በተለይም፣  ፖለቲካን ወደ መነገጂያና መኖሪያ የለወጡ ግለሶቦች አስቸጋሪ ሁኔታንና የታሪክ አጋጣሚን በመጠቀም፣ እንዲሁም ከአንዳንድ ሚዲያዎች አላስፈላጊ ቦታ እንዲያገኙ በማድረግ በሚቀጣጠለው እሳት ላይ ቤንዚን እያርከፈከፉ የባሳውኑ እንዲጋይ ያደርጋሉ። እነዚህ ግለሰቦችም ሆነ ለእነዚህ ግለሰቦች ሁኔታውን የሚያመቻቹላቸው ሚዲያዎች ማወቅ ያለባቸው ነገር ድርጊታቸው ፀረ-ህዝብ ብቻ ሳይሆን በጠቅላላው ጥቁር ህዝብ ላይ እንደተሰዘነረ መረዳት አለባቸው። ወሬን ከማራገብና ሁኔታውን አመቻችቶ ከመስጠት ይልቅ ድርጊታቸውን ከሁሉም አንፃር መመርመሩ እጅግ ጠቃሚ ነው። ለዚህ ደግሞ የሚዲያና የፖለቲካ አማካሪዎችን ድጋፍ ቢጠይቁ ስራቸውን ሊያቃልልላቸው ይችላል። ከስህተትም ሊቆጠቡ ይችላሉ። ስለሆነም የሚላክላቸውን ጽሁፎች በደንብ መመርመር አለባቸው። ቃለ-መጠይቅ የሚጠይቁ ሚዲያዎችም ኮታን ለማሟላት ሲሉ መጠየቅ የሌላበቸውን ሁሉ በመጠየቅ ችግራችንን የባሰውኑ ውስብስብ ማድረግ የለባቸውም። ይሁንና ግን ማንኛውም ሚዲያ የራሱ መብት ስላለው እንደፈለገው ጽሁፎችን ማስተናገድ ይችላል። ለማለት የሞከርኩት ሁላችንም ሰላምንና ብልጽግናን የምንሻ ከሆነ የባሰውኑ ውዝግብ ውስጥ የሚከተን ሁኔታ ውስጥ እንዳንገባ መጠንቀቅ አለብን ለማለት ብቻ ነው።

እንደዚህ ስል ግን በአንዳንድ ብሄረሰቦች ላይ በደል አልነበረም፤ ውይም የለምም ለማለት አይደለም። በኮሎኮንታው፣ በወላይታውና እንዲሁም በከፍቾው ብሄረሰቦች ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ላይ መባል የማይገባቸው ነገሮች ይባሉ ነበር። እነደዚህ ዐይነቱ አባባልና የተወሰነውን የህብረተሰብ ክፍል ማግለልና ለመጥፎ ነገሮች ተጠያቂ ማድረግ በተለይም በአውሮፓ ምድርም ውስጥ በማዕከለኛው ክፍለ-ዘመንና እስከ ኋለኛው ማዕከለኛው ክፍለ-ዘመን ድረስ የተስፋፋ ነበር። በተለይም ካለምንም ምክንያት ይሁዲዎች የሚናቁና የሚጠሉ፣ እንደውሻም የሚታዩ ነበሩ። ስለሆነም ይሁዲዎች የተስቦና የኮሌራ እንዲሁም የልዩ ልዩ በሽታዎች ምንጮት ተደርገው በመቆጠር ከሌላ የህብረተሰብ ክፍል ጋር መጋባት አይፈቀድላቸውም ነበር። ይሁንና ግን ይሁዲዎች ይህንን ሁሉ ከመጤፍ ሳይቆጥሩ፣ ቀስ በቀስ በመማርና በንግድ በመሰማራት የአገሬውን ሰው እየበለጡ ይሄዳሉ። ፈላስፋዎች፣ የሙዚቃና የሊትሬቸር ሊቆች፣ በኋላ ደግሞ ሳይንቲስቶችና የቴክኖሎጂ  አፍላቂዎች በመሆን በተለይም ለጀርመን ዕድገት ልዩ ዕምርታን መስጠት ችለዋል። ዕውቀታቸውም ዓለም አቀፋዊ ለመሆን በቅቷል።  ተሰደብን፣ ተናቅን፣ ተዋረድን ብለው ወደ ጫካ በመግባትና ጠብመንጃ በማንሳት ጦርነት አላወጁም። የሚንቃቸውን በዕውቀት አማካይነት ማሸነፍ እንደሚችሉ ነው ያረጋገጡት። ይሁንና ግን የተሻልን ነን ብለው በመዝናናት ቂም በቀል መወጣት አልጀመሩም። ቀስ በቀስ በመጋባትና በመዋለድ እንዲሁም ዕውቀታቸውን በማስፋፋት ነው ለህብረተሰቡ ልዩ ዕምርታን መስጠት የቻሉት። የሴቶችንንም ጭቆና ስንመለከት በማዕከለኛው ክፍለ-ዘመንና እስከሃያኛው ክፈለ-ዘመን መግቢያ ድረስ በከፍተኛ ደረጃ የሚጨቆኑ ነበሩ። በማዕከለኛው ክፍለ-ዘመን እዚህ አውሮፓ ውስጥ እንደጭራቅ የሚቆጠሩና አንዳንዶችም እስከነነፍሳቸው ይቃጠሉ ነበር። ይህ ዐይነቱ አፀያፊ ተግባር በአገራችንም ሆነ በሌሎች የአፍሪቃ አገሮች የተለመደ አልነበረም።

ሌላው በአገራችን ያለው ትልቁ ችግር የህብረተሰብን ዕድገት ታሪክ ብቻ ሳይሆን፣ የራሳቸውን ብሄረሰብ የመንፈስና የማቴሪያል ዕድገት ሁኔታ በደንብ ያላጠኑ ግለሰቦችም ሆነ ድርጅቶች ነገሩን ሁሉ በመጠምዘዝ የአማራው ብሄረሰብ እንደዚህ አደረገ፣ እንደዚያ ፈጠረ በማለት በየዋሁ ህዝብ ላይ ጦርነት በመክፈት በብዙ ሺሆች የሚቆጠሩ ሰዎች በማያውቁት ነገር ህይወታቸው እንዲጠፋ ለመደረግ በቅተዋል። ራሳቸው ማርክሲስት ነን ይሉ የነበሩ ግለሰቦች ሁሉ ሳይቀሩ አማራውን በነፍጠኝነት በመወንጀል አሳቃይተውታል፤ ገድለውታልም።  ይህ ሁሉ ድርጊት ከታሪክ ጋር ሳይገናዘብ በተለይም ፊደል ቆጥረናል፣ ዩኒቨርሲቲም ገብተን ተምረናል በማለት በሚዝናኑ አንዳንድ ግለሰቦችና በድርጅት ደረጃ የተወሰዱ አላስፈላጊ እርምጃዎች ናቸው።

ያም ተባለ ይህ ፣ ሬኔ ዴካ የሚባለው የፈረንሳዩ ፈላስፋ በአንድ ወቅት የተደረገን ድርጊት ሙሉ በሙሉ ማረጋጋጥ ስለማይቻል እንደሳይንስ ሊወሰድ አይቻልም። ሳይንስ የተፈጥሮ መነጋገሪያና መመርመሪያ፣ እንዲሁም የህብረተሰብ ማደራጃ መሳሪያ ነው። ስለዚህም የዛሬውን ችግር በታሪክ መነጽር ወይም መሳሪያ መፍታት አይቻልም። ያለፈ ነገር ያለቀለትና የደቀቀለት ነው።  ስላለፈው ነገር እየደጋገሙ ማውራት፣ „ውሃ ቢውቅጡት እምቦጭ“ እንደሚሉት አባባል ነው። ስለዚህም ላይብኒዝ እንደሚለን፣ የአዲሱ ትውልድ ተግባር ዛሬ አፍጠው አገጠው የሚታዩ ችግሮችን በሳይንስና በፍልስፍና መሳሪያ መፍታትና ለመጭው ትውልድ ታሪክን ሰርቶ ማለፍ ብቻ ነው።

ከዚህ ስንነሳ የብሄረሰቦች ችግር መብታቸውን በማወቅ ብቻ ሊፈታ ይችላል ወይ? መብትስ ሲባል ምንድ ነው? በራስ ቋንቋ መነጋገር፣ ወይም ደግሞ የራሴ ባህል የሚሉትን መጠበቅ? ሌላው ደግሞ ሀብትን ወይም ሬሶርስን የመቆጣጠር ጉዳይ፣ ሌሎችን አባሮ ሁሉንም የራሴ ብሎ መቆጣጠርና መዝናናት? ለመሆኑ እነዚህ በመታወቃቸው እያንዳንዱ ብሄረሰብ ያለበትን መሰረታዊ ችግር፣ ለምሳሌ እንደ ንጹህ ውሃ ማግኘት፣ ተመጣጣኝ የሆነ ምግብ በጥራትም ሆነ በብዛት ማግኘት፣ መብራትና የምግብ መቀቀያ ጉዳይ፣ ቤትና የትምህርት ቤት ጉዳይ፣ እንዲሁም ህክምና… ወዘተ. እነዚህ መሰረታዊ የማንኛውም ሰው ፍላጎቶች የላይኛዎቹ መብቶች በመታወቅ ብቻ ሊፈቱ ይችላሉ ወይ? ወይስ ዋናው ነገር የመብት ማዋቅን ጉዳይ መፍታትት ነው? ሌሎች ነገሮች አያስፈልጉንም  ለማለት ነው ወይ የሚፈለገው?  ከዚህም ባሻገር አንድ ብሄረሰብም ሆነ ማህበረሰብ ወይም ህብረተሰብ ተከታታይነት ያለውን ጤናማ ኑሮ ለመኖር ከፈለገ የግዴታ ሳይንስና ቴክኖሎጂን ማዳበር ያስፈልገዋል። የቴክኖሎጂንና የሳይንስን ዕድገት የተመለከትን እንደሆን በክልል ወይም በብሄረሰብ ደረጃ ሊያድጉ ወይም ሊዳብሩ፣ ወይም ሊፈጠሩ የሚችሉ አይደሉም። በአንድ አገር ውስጥ የሚኖር የተለያየ ጎሳ በጋብቻ ሲቀላቀልና፣ በስራ-ክፍፍልና በንግድ አማካይነት ግኑኝነቱን ሲያጠናክር የመፍጠር ኃይሉም ያድጋል። የቴክኖሎጂና የሳይንስ ባለቤትም ይሆናል። ይሁንና ግን በአጠቃላይ ሲታይ የቴክኖሎጂ ዕድገት ዓለም አቀፋዊ ጉኑኝነትንና፣ በዘዴ ቴክኖሎጂዎችንም መስረቀንና ማዳበርን ይሻል። በዚህ አማካይነት ብቻ ነው አንድ ህዝብም ሆነ ግለሰብ ኑሮውን ማሻሻል የሚችለው። ራሱን አገልሎ የሚኖር ማህበረሰብም ሆነ ብሄረሰብ በሃሳብ ይቀጭጫል። ዕድገትን ማየት አይችልም። ያለውንም ሬሶርሱን ወይም ሀብቱን በስነስርዓት መጠቀም አይችልም። በእኔ ዕምነት እንደዚህ ዐይነቱን ችግር ለመፍታት በመጀመሪያ ደረጃ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ማቋቋም ያስፈልጋል። አዲሲቱን ኢትዮጵያ ለማስተዳደር የሚችሉ ከሁሉም ብሄረሰብ በችሎታ ተመርጠው ሊስለጥኑ የሚችሉበት ሁሉኑም ዕውቀት ያካተተ ልዩ ዐይነት የኤሊቶች ዩኑቨርሲቲ ማቋቋም ያስፈልጋል።  ይህ ዐይነቱ ልዩ የኤሊቶች ኢንስቲቱት በየክፍለ-ሀገሩ ወይም በየክልሉ የሚቋቋም ሲሆን፣ ፍልስፍናን፣ ታሪክን፣ ሊትሬቸርን፣ የተፈጥሮ ሳይንስን፣ ሜካኒካልና ኤልክትሮቴክኒክ ኢንጂነሪንግን፣ ጥበብና ሙዚቃን፣ የፖለቲካ ሳይንስና የሶስይሎጂ ዕውቀቶችን፣ አርክቴክቸርን… ወዘተ.፣ የሚያጠቃላል መሆን አለበት። በተጨማሪም በየክፍለ-አገሩ በዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ ሁሉንም ዐይነት መጽሀፎች ያጠቃለሉ ቤተ-መጻህፍቶች መቋቋም አለባቸው። አገሪቱ እያደገች ስትመጣ ደግሞ በየቀበሌው የህዝብ መማሪያ ትምህርትቤቶች ቢቋቋሙ ህዝቡ የመማር ዕድልና ከዕደ-ጥበብ ሙያ ጋር የመተዋወቅ ባህልን ያዳብራል። ይህ በራሱ በአጭር ጊዜ ውስጥ እምርታን በማሳየት በህዝቡ ዘንደ ያለውን በማያስፈልግ መልክ የተሰራጨውን አሉባልታ በማስወገድ ህዝባችን በመከባበርና በሰላም እንዲኖር ይረዳዋል። ስለሆነም ስለነፃነትና ስለመብት በምንናገርበት ወይም በምንጽፍበት ጊዜ ነገሩን ሰፋ ባለመልክ መመልከቱ የሚጠቅም ይመስለኛል። ከዚህ ውጭ የሚደረግ ዘመቻና የመብት ጥያቄ እንዲያውም የተገላቢጦሹን ነው የሚያመጣው። ድህነትን ፈላፋይ ነው የሚሆነው። የሳይንስና የቴክኖሎጂን ዕድገት አፋኝ ነው የሚሆነው። ጥበብ እንዳይስፋፋ፣ የሰዎች የመፍጠር ችሎታ እንዳይዳብር አፍኖ ይይዛል። በተጨማሪም መብት ወይም ነፃነት የሚከፈል ወይም እየተከፋፈለ የሚሰጥ ጉዳይ ሳይሆን፣ የሁሉም ሰው ጥያቄ ነው። አብዛኛውን ጊዜ መብትና ነፃነት ግለሰብአዊ ባህርይ ሲኖራቸው፣ በሌላ ወገን ደግሞ ከስራና ከሙያ ጋር በተያያዘ አንድ ፈብሪካ ውስጥ ተቀጥረው ወይም በሌላ የሙያ ማሀበር ተደራጅተው የጋርዮሽ ጥቅማቸው እንዲጠበቅላቸው የሚነሳ ጉዳይ እንጂ በብሄረሰብ ደረጃ የሚታይ ነገር አይደለም።  ሳይንሳዊም ሊሆን አይችልም። ከዚህ ሳይንሳዊ አስተሳሰብና ሀተታ ስንነሳ በአገራችን ምድር የየብሄረሰባቸውን ጥቅም እናስጠብቃለን በማለት የተደራጁ በተለይም የትግራይና የኦሮሞ ኤሊቶች ለነፃት፣ ለዲሞክራሲና ለሁለ-ገብ የኢኮኖሚ ዕድገትና የአገር ግንባታ የሚደረገውን ትግል አጨናግፈዋል። በተሳሳተ ትረካ በመመራት በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ዕውነተኛ ነፃነትን የሚሹ በተለይም ተከታያቸው የሆኑ ወጣቶችን አሳስተዋል፤ እያሳስቱም ነው። የትግራይና የኦሮሞ ኤሊቶች ነን ባዮች ምንም ዐይነት የሳይንስና የቲዎሪ መሰረት የላቸውም። መንፋሳቸው አልባ ከመሆኑ የተነሳ አገርን ከማመሳቀቅልና ድህነትን ከማስፋፋት በስተቀር ይህ ነው ለአገራችን መፍትሄ የሚሆነው ፖሊሲ ብለው የሚያቀርቡት ነገር የለም። የሚፈልጉት ነገር በውጭ ኃይሎች በመታገዝና ስልጣን ላይ በመውጣትና በዘረፋ በመሰማራት ህዝባችን ለዝንተ-ዓለም በድህነት እየማቀቀ እንዲኖር ማድረግ ነው። ባጭሩ እነዚህ ኃይሎች ከጥፋት በስተቀር አገራዊ ስምምነትንና ሁለ-ገብ ዕድገትን ሊያመጡ የሚችሉ አይደሉም። እነዚህ ሁለት ኃይሎች፣ የትግራይና የኦሮሞ ኤሊቶች ለኢትዮጵያ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ለጠቅላላው ጥቁር አፍሪካ ህዝብ ጠንቅ መሆናቸው መታወቅ አለበት።

ዓለም አቀፋዊ ካፒታሊዝምና የነፃነት ትግል አስቸጋሪ ሁኔታ!

ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ የተዋቀረው ዓለም አቀፋዊ የፖለቲካ፣ የሚሊታሪና የኢኮኖሚ ስርዓት የአብዛኛዎችን የሶስተኛውን ዓለም አገሮች፣ በተለይም የአፍሪካን አገሮች፣ የኛንም ጨምሮ የዕድገታችንን አቅጣጫ ለመወሰን ችሏል። በተለይም ከ1950ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ ዘመናዊነት(Modernization) በመባል የሚታወቀው የኢኮኖሚ ፖሊሲ በኛና፣ የኋላ ኋላ ደግሞ ከቅኝ ግዛትነት ከተላቀቁ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ በኋላ በኛም ሆነ በእነዚህ አገሮች ውስጥ አዲስ ህብረተሰብአዊ ግኑኝነት፣ የፍጆታ አጠቃቀምና፣ ለየት ያለ የህሊና አወቃቀር ሊፈጠር ችሏል። ከዚህም ባሻገር የየመንግስታቱ መኪና በአዲስ መልክ በመዋቀርና በመጠናከር አዲስ የተፈጠረውን ህብረተሰአብዊ ግኑኝንት ሊያጠናክረው ችሏል። በሌላ ወገን ግን ይህ ዐይነቱ የዘመናዊነት ፖሊሲ ውስጠ-ኃይሉ ደካማ ከመሆኑ የተነሳ አዳዲስ ህብረተሰብአዊ ችግሮችን ከመፍጠርና ውስብስብ ከማድረግ በስተቀር ሰፊውን የአገራችንንም  ህዝብ ሆነ የተቀሩትን የአፍሪካ ህዝቦች ከድህነት በማላቀቅ አዲስ ህይወት ሊያጎናጽፋቸው አልቻለም፤ ትክክለኛውን የስልጣኔ መንገድ ሊያሳየቸውና በራሳቸው እንዲተማመኑ አላደረጋቸውም።

የምትክ ኢንዱስትሪ ተከላ፣ (Import Substitution Industrialization) ወይም ደግሞ በአጠቃላይ ዘመናዊነት በመባል የሚታወቀው የኢኮኖሚ ፖሊስ በውጭ አማካሪዎች ግፊት ተግባራዊ ሲሆን፣ ዓላማው በዚህ ዐይነቱ ፖሊሲ አማካይነት ዕድገቱ ቀስ በቀስ ወደ ሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎችም በመዳረስ(Trickle–down effect) ኋላ-ቀርነት ተወግዶ ሁሉም አገሮች አነሰም በዛም የምዕራቡ የዕድገት ደረጃ ላይ ይደርሳሉ የሚል ግምት ነበር። ይሁንና ግን የኢኮኖሚ ፖሊሲው ባለው ውስጣዊ ድክመት የተነሳ እንደታሰበው የእኛና የተቀሩትn የአፍሪካ አገሮች ዕድገት ወደፊት ሊያራመድ አልቻለም። በተለይም የየመንግስታቱ መኪና በመጠናከርና፣ የነበረውን ስርዓት እዚያው አፍኖ በመያዝ አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ሊታይና የህብረተሰቡም ፈጠራ ከፍ ሊል አልቻለም። በዚህም ምክንያት የተነሳ አዲስ ውስጠ-ኃይሉ ከፍ ያለና ህብረተሰብአዊ ኃላፊነትን ሊሸከም የሚችል የከበርቴው መደብ ብቅ ሊል አልቻለም። በሌላ ወገን ደግሞ ከታች ወደ ላይ ከኢኮኖሚው ዕድገትና ከህብረተሰቡ የማሰብ ኃይል ጋር እየተቀናጀ ያልተገነባው የመንግስት መኪና የባሰውኑ ጨቋኝ በመሆንና ከህብረተሰቡ በመራቅ ተጠሪነቱ ይበልጥ የውጭ ኃይሎች በመሆን፣ ወደ ውስጥ ደግሞ ሁለ-ገብ የሆነ የኢኮኖሚና የህብረተሰብ ዕድገት እንዳይመጣ እንቅፋት ሆነ።

በ1950ዎቹ መጀመሪያ ላይ ተግባራዊ የሆነው የኢኮኖሚ ፖሊሲ የተጠበቀውን ውጤት ሳያመጣ ሲቀር፣ እንደዚሁ በውጭ አማካሪዎች በስም የሚለያዩ፣ ይዘታቸው ግን ተመሳሳይ የሆነ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ተግባራዊ በመሆን ሁለ-ገብ የኢኮኖሚ ዕድገትን ከማምጣት ይልቅ ሁኔታውን የባስውኑ አዘበራረቀው።  በመሆኑም እርስ በርሳቸው ያልተያያዙ የኢኮኖሚ ክንዋኔዎች በመፈጠር፣ ዘመናዊ በሚባለው የኢኮኖሚ መስክና በእነዚህ ለካፒታሊዝም ዕድገት በማያመቹ የተሰበጣጠሩ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች መሀከል ከፍተኛ ቅራኔ መታየት ቻለ። በአንድ በኩል የዘመናዊ የኢኮኖሚ መስክ ተጠቃሚ የሆነው  ክፍልና፣ በሌላ ወገን ደግሞ በተለያዩ ግን ደግሞ ጥሩ ገቢን በማያስገኙ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች(Informal Sector) በተሰማራው የህብረተሰብ ክፍል መሀከል „የባህል ልዩነት“ መታየት ጀመረ። በጊዜው የነበረው የአፄው አገዛዝ ይህንን ህብረተሰብአዊ ቅራኔ ለመፍታት የሚያስችል ፖሊሲ ስላልነበረው፣ እየተከማቸ በመጣው ቀውስ የተነሳ ቀስ በቀስ እያለ ከስልጣን የሚወገድበተን መንገድ አዘጋጀ። ይህ ሁኔታና፣ በጊዜው የነበረው ዓለም አቀፋዊ የኢኮኖሚ ቀውስ ተደራርበው ለየካቲቱ አብዮት ምክንያት ሆኑ። አብዮቱ ከፈነዳ በኋላ የተወሰዱት እርምጃዎች ከሞላ ጎደል ትክክል ቢሆኑም፣ በነበረው ትርምስ የተነሳ ግልጽ የሆነ ለካፒታል ክምችት የሚያመችና ለሰፊው ህዝብ የስራ መስክ ሊከፍት የሚያስችል የኢኮኖሚ ፖሊስ መንደፍ አልተቻለም።  የወታደሩ አገዛዝ ከስልጣን ከተባረረ በኋላ በውጭ ኃይሎች ግፊት ተግባራዊ የሆነው የነፃ የገበያ የኢኮኖሚ ፖሊሲ በመሰረቱ የአገራችንን የተወሳሰበ ችግር ለመፍታት ሳይሆን አዲስ የህብረተሰብ ኃይል በመፍጠርና በማጠናከር፣ በዚያውም መጠንም ድህነትን አስፋፍቶ ሰፊውን ህዝብ አቅመ ቢስ የሚያድርገው ሆነ።

በተለይም የግሎባል ካፒታሊዝም ባለፉት ሰለሳ ዓመታት የብዙ አፍሪካ አገሮችን ዕድል ወሳኝ በመሆኑ፣ በዚያው መጠንም የየመንግስታቱን መኪና በማጠናከርና ከሰፊው ህዝብ በመገለል፣ የየአገሮቹ መንግስታትና ህዝቦች ሆድና ጀርባ ለመሆን በቅተዋል። በዚህ መልክ የዓለም አቀፍ ካፒታሊዝም በየአገሮች መንግስታት መኪና ውስጥ ሰርጎ በመግባት፣ መንግስታቶች የህዝባቸው አለኝታ እንዳይሆኑ ቆልፎ በመያዝ፣ በአንድ በኩል ህዝባዊ ጭቆና፣ በሌላ ወገን ደግሞ ሸበርተኝነትን መዋጋት ያስፈልጋል በማለት የጎሳና የሃይማኖት ግጭት እንዲስፋፋ ተደረገ። ስለሆነም በዚህም መልክ የየመንግስታቱ ተግባር በመጨናገፍና ሀብት ያልአግባብ  ምርታማ ባልሆነ ቦታ በመፍሰስ የአፍሪካ መንግስታት፣ የአገራችንም ጭምር ከውጭው ኃይል ጋር እጂና ጓንቲ በመሆን ህዝቦችን መፈናፈኛ እንዳያገኙ ለማድረግ ችለዋል። በዚህም ምክንያት የተነሳ በተለያዩ ዘርፎች መልክ የሚደርሱና  የሚከሰቱ መዛባቶችና በደሎችን ሊዋጋ የሚችል ብቃትነት ያለው የሲቪል ህብረተሰብ ሊፈጠር አልቻለም። ይህ ሁኔታ ደግሞ በራሱ የዕርዳታ ሰጭ ድርጅቶች ለሚባሉት መስፋፋትና የተወሰነውን የህብረተሰብ ክፍል በማበላሸት፣ የኛም ሆነ የብዙ አፍሪካ አገሮች ህዝቦች በራሳቸው ላይ ዕምነት እንዳይኖራቸው ሊደረጉ በቃ። በዕርዳታ ስምና ከላይ በተዘረዘረው መልክ ሰርጎ የገባው ኢምፔሪያሊዝም የእኛንም ሆነ የተቀሩትን የአፍሪካ ህዝቦች የነፃነት ጥማቸውን ወይም ፍላጎታቸውን አኮላሸባቸው።  የማሰብ ኃይላቸውን ተጠቅመው አዳዲስ መሳሪያዎችን በመፍጠር የዕድላቸው ወሳኝ እንዳይሆኑ ተደረጉ። በዚህም ምክንያት የተነሳ የእኛና የተቀረው የአፍሪካ ህዝብ ዕውነተኛ ነፃነቱን እንዳይጎናፀፉና የዲሞክራሲ ስርዓት እንዳይገነባ ከሁሉም አቅጣጫ ከፍተኛ እንቅፋት ተደቀነበት። የአፍሪካ መንግስታትም ኢክስፐርት ነን ከሚባሉት በሚሰጣቸው የተሳሰተ መረጃዎች የኢኮኖሚ ፖሊሲ የተነሳ ወደ ውስጥ ያተኮረ የኢኮኖሚ ግንባታ ማካሄድ አልተቻለም። ይበልጥ ለኤክስፖርት መስኩ አትኩሮ በመስጠትና ዕዳን ከፋይ በመሆን ለገንዘብ እንቅስቃሴና ለምርት ክንውን ይህ በራሱ እንቅፋት ሆነ። በግሎባል ካፒታሊዝም ግፊት የተነሳ የብዙ አፍሪካ አገሮች የማምረት ኃይል ሲዳከም፣ በዚያው መጠንም የቆሻሻ መጠያ ሆኑ። ሰከንድ ሃንድ ምርቶች የሚራገፉባቸው በመሆን፣ ይህ ዐይነቱ እንቅስቃሴ በተለይም የዋና ከተሞች ገጽታ ሊሆን በቃ። ይህ አጠቃላይ ሁኔታ በሰፊው ህዝብ የማሰብ ኃይል ላይ ከፈተኛ የሆነ አሉታዊ የህሊና ተፅዕኖ በማድረግ ለዲሞክራሲና ለነፃነት የሚደረገውን ትግል ይበልጥ አዘበራረቀው።

ይህንን የተወሳሰበ ዓለም አቀፋዊ ካፒታሊዝም በአገራችንም ሆነ በሌሎችም አፍሪካ አገሮች ሰርጎ መግባትን አስመልክቶ በተለይም ባለፉት 40 ዓመታት በእኛ ዘንድ ምንም ጥናት አልተካሄደም። በአገራችን ምድር ስልጣን የጨበጠውን ኃይል ከውጭው ዓለም ጋር ምንም ግኑኝነት የሌለው ይመሰል እስካሁን ድረስ የሚደረገው ትግል የተሟላ ሳይሆን እጅግ የሚያሳስትና ለዕውነተኛ ነፃነት የሚደረገውን ትግል በማጨናገፍ ላይ ነው። በተለይም ወጣቱ ትውልድ አስተሳሰቡ የሾለና የበሰለ እንዳይሆን እስከዛሬ ድረስ በአገራችን የደረሰው በደልና ኋላ-ቀርነት የውጭው ኃይል ተጠያቂ ሊሆን አይችልም፤ እነሱንም ማስቆጣቱ ተገቢ አይደለም እየተባለ የትግሉን አቅጣጫ ለማዛነፍ ጥረት ይደረጋል። ሳይንሳዊ ጥናት እንዳይካሄድ መንገዱን በመዝጋት ለዕውነተኛ ነፃነትና በሳይንስና በቴክኖሎጂ ለተመሰረተ የኢኮኖሚ ግንባታ የሚደረገው ሁለ-ገብ የነፃነት ትግል መልክ እንዳይዝ  የሚሆን የማይሆን ፊዩዳላዊ አሉባልታ በማውራት የድህነቱ ዘመን እንዲራዘም  እየተደረገ ነው።

በእኛ በኢትዮጵያውያን ምሁራን፣ በተለይም ደግሞ ለስልጣን በሚታገሉ ኃይሎች ዘንድ ያለው የተሳሳተ ግንዛቤ በብዙ የሶስተኛው ዓለም ተብለው በሚጠሩ አገሮችና፣ የእኛንም ጨምሮ በግሎባል ካፒታሊዝም ወይም ይህንን በሚወክሉ መንግስታትና በእኛዎች ፖለቲከኛ ነን ባዮች ዘንድ ምንም ዐይነት ግኑኝነትና የጥቅም መተሳሰር የለም። ለምሳሌ ባለፉት 36 ዐመታት በአገራችን ምድር ሲካሄድ የነበረው ፖለቲካና ተግባራዊ የሆነው የኢኮኖሚ ፖሊሲ በወያኔ አገዛዝ  ዕውቀትና ኃይል፤ በአሁኑ ወቅት ደግሞ በአቢይ አህመድ አገዛዝ ዕውቀትና ኃይል ብቻ የተካሄዱና የሚካሄዱ ናቸው የሚል የተሳሳተ ዕምነት አለ። የውጭ ኃይሎች፣ በተለይም እንደ ቅዱስ የሚታየው ታላቁ አሜሪካን እንደ እግዚአብሔር ከውጭ ሆኖ የወያኔንም ሆነ የአቢይ አህመድን አገዛዝ የሚሰሩትን የሚያይ እንጂ ምንም ዐይነት ተፅዕኖ እንደማያደርግ ነው። በተጨማሪም እነ ዓለም የገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክ ብድር ሲጠየቁ ከማበደር በሰተቀር በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ፖሊሲ  ውስጥ ምንም ዐይነት ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ ተፅዕኖ የላቸውም። ከዚህ በመነሳት የሚካሄደውም ትግል ለስልጣን የሚደረግና ቀድሞ የወያኔን፣ በአሁኑ ወቅት ደግሞ የአቢይ አህመደን አገዛዝ  የማስወገድ ትግል ብቻ ነው። የነፃነቱም ትግልና ዕውነተኛ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን የመቀዳጀቱ ጉዳይ ቀድሞ ወያኔን፣ በአሁኑ ወቅት ደግሞ የአቢይ አህመድን አገዛዝ ከማስወገድ ውጭ ሊታሰብ አይችልም።  ስለሆነም ወያኔ ከስልጥን ስለተወገደ እሱን እሳቤ ውስጥ ሳናስገባ፣ አቢይ አህመድ ከስልጣኑ ከተወገደ በኋላ ከውጭ ኃይሎች ጋር በሚፈጠረው መልካም መቀራረብ ህዝባችን ዕውነተኛውን ነፃነት ሊቀዳጅ ይችላል የሚል አስተሳሰብ ተስፋፍቷል፤ ተቀባይነትም አግኝቷል። ይህም ማለት እስከአሁን ድረስ የወያኔ አገዛዝም ሆነ በአሁኑ ወቅት ደግሞ የአቢይ አህመድ አገዛዝ ቢያንስ በኢኮኖሚ ፖሊሲና በርዕዮተ-ዓለም ደረጃ ከእነ ዓለም የገንዘብ ድርጅት ጋር በመሆን የኢትዮጵያን ህብረተሰብ ያወላገዱበትንና ያዘበራረቁትን ሁኔታ በትክክለኛው የቲዎሪ መነፅር እየተመለከትን መዋጋት የለብንም ማለት ነው። በሌላ አነጋገር፣ የዓለም ኮሙኒቲ የሚባለው በብዙ ሚሊዮን ህጎች የተበተባቸው ስምምነቶችና አገሮችን በእሱ ቁጥጥር ስር የማድረጉን ልዩ ልዩ ሴራዎች ሁሉ አምነን መቀበል አለብን። ይህም ማለት ለነፃነት የሚደረገው ትግል የተወሰኑ ኤሊቶች በተረጎሙትና የዓለም አቀፍ ኮሙኒቲው በሚደነግገው መልክ ብቻ የሚካሄድ ነው።  በዚህም መልክ የሚተረጎም ነፃነትና  እንደገና ለውዝግብና ለሌላ የማያቋርጥ ትግል የሚጋብዘን ይሆናል። ልክ የደቡቡ አፍሪቃ ሁኔታ በእኛው አገርም ይደገማል። ናኦሚ ክላይን ዘ ሾክ ዶክትሪን(The Shock Doctrine) በሚለው መጽሃፏ ውስጥ የሌሎችን አገሮች ሁኔታ ስታስረዳ እንደገለጸችውና፣ በተከበሩት ኔልሰን ማንዴላ የሚመራው አዲሱ የደቡብ አፍሪቃ መንግስትም ተገዶ ተግባራዊ እንዳደረገው የኢኮኖሚ ፖሊሲና ህብረተሰቡን ለድህነት የዳረገው ዐይነትም መመሪያ፣ በእኛው አገርም በአዲሱ ሁኔታና በአዲሱ መንግስት ተግባራዊ ይሆናል ማለት ነው። የደቡብ አፍሪካ ህዝብ ከአፓርታይድ ስርዓት ከተላቀቀ ከሰላሳ ኣመታት በኋላ በደሃውና ጥቂት ሀብታም በሚባለው የህብረተሰብክፍል መሀከል ከፍተኛ ልዩነት እንዳለ የሚወጡት ዘገባዎች ያረጋግጣሉ። በዚህም የተነሳ ከፍተኛ መዛባት የተስፋፋበት ደቡብ አፍሪካ(The most unequal society in the world) በመባል ይታወቃል። ይህንን ዐይነቱንም ከፍተኛ የዕድገት መዛባትና የድህነትን መስፋፋት ከነፃነት ጋር ለማያያዝ ይሞከራል። ከዚህ ስንነሳ በአንዳንድ ኢትዮጵያውያን እንደ መጽሀፍ ቅዱስ የሚደገመውን የአማርታያ ሴንን የነፃነትንና የመንግስትን አተረጓጎም ሁኔታ ጠጋ ብለን እንመልከት።

በትክክል አማርታያ ሴንን ካነበብኩትና ከተረዳሁት አንደኛውና ዋናው የነፃነት እንቅፋት የሚመነጨው ከመንግስታት የጭቆና አወቃቀር ጋር የተያያዘ ነው። የአለፉት ስድሳ ዐመታት የሶስተኛው ዓለም አገሮችን የየመንግስታቱን ኢኮኖሚ ፖሊሲና፣ እንዲሁም ደግሞ የኢንዱስትሪ አገሮችን መንግስታት ፖሊሲ ስንመለከት ሴን የሚለው ትክክል ነው።  ይሁንና ግን እንደዚህ ዐይነቱ በብዙ የሶስተኛው ዓለም አገሮችና፣ በአገራችንም የተገነቡት የመጨቆኛ መሳሪያዎች የቱን ያህል ከውጭው ኃይል ጋር በጥቅም እንደተሳሰሩና እንደተዋቀሩ ከአማርታያ ሴን መጽሀፍ ውስጥ ፈልጌ ላገኝ አልቻልኩም።  አማርታያ ሴን ለማሳየት እንደሚሞክረው የሶስተኛው ዓለም መንግስታት በራሳቸው የቆሙና በራሳቸው ፍላጎት ብቻ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎችን እንደሚያወጡ አድርጎ ነው። በተለይም የአፍሪካ መንግስታት እንደዚህ ዐይነቱ ሁኔታ ውስጥ እንደወደቁና፣ ኃላፊነት ያለው አገዛዝ ለመመስረት እንዳልቻሉ የአፍሪካን መንግስታት አወቃቀር ችግሮችና የአገዛዞችን ፖሊሲ የመረመረ አይደለም። ከዚህም ባሻገር በአብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች የኢኮኖሚ ፖሊሲንና የማህበራዊ ሁኔታን ጉዳይ አስመልክቶ የመከራከር ልምድ አለመኖርና፣ መንግስታትም ከውጭ የሚመጣባቸውን ግፊት ለመቋቋም የሚችሉበት ምሁራዊ መሳሪያና ኃይል ይኑራቸው አይኑራቸው አማርታያ ሴን የመረመረ አይመስለኝም። በመሆኑም አገራችንም ሆነች ሌሎች የአፍሪካ አገሮች በዓለም አቀፍ የግሎባል ካፒታሊዝም ሎጂክና በጭቆና ሰንሰለት ስር የተዋቀሩ መሆናቸውንና፣ ድህነትን እንደሚያስፋፉና ነፃነትንም እንዲሚገፉ ለማሳየት አልሞከረም።  ከመንግስቱ ቢሮክራሲ፣ ከወታደር፣ ከጸጥታና እስከፖሊስ ኃይል ድረስ ያሉት አወቃቀሮች ቀድሞውኑ በታሰቡትና በተዋቀሩት የጎሎባል ካፒታሊዝም ሎጂክ አወቃቀር ስልት የተዋቀሩ እንጂ ከየአገሮች የኢኮኖሚ ዕድገት ጋር የተያያዙ በመሆን የየአገሮችን ደህንነት ለመጠበቅ ተብለው አይደለም የተመሰረቱትና እንዲደልቡ የተደረገው። ይህም ማለት አብዛኛዎቹ የሶስተኛው ዓለም የመንግስታት መኪናዎች ከታች ወደ ላይ ከማቴሪያላዊ ፍላጎትና ከረጅም ጊዜ የህብረተሰብ ዕድገት ጋር እየተሻሻሉ የተዋቀሩ ሳይሆን፣ በየአገሩ የሰፈኑትን ገዢዎች ጥቅም ለማሰጠብቅና ወደ ውጭ ደግሞ ታዛዥ በመሆን አገርን  ማመሰቃቀል ነው። በዚያው መጠንም አገዛዞችና የመንግስት መኪናዎች በግሎባል ካፒታሊዝም ሎጂክ ውስጥ በመውደቅ ወደ ውስጥ አጠቃላይ የሀብት ክምችት እንዲዳብርና እንዲስፋፋ የሚያደርጉ ሳይሆን፣ እንዲያውም ዕድገትን የሚቀናቀኑና፣ እንዲሁም ድህነትን የሚያስፋፉና የሚያጠናክሩ ናቸው። ምንም ዐይነት ጭንቅላትን የሚያድስ ምሁራዊ እንቅስቃሴ በሌለበትና፣ የኃይል አሰላለፉም ውስን በሆነባቸው አገሮች ስልጣን ላይ ቁጥጥ የሚሉ ኃይሎች የራሳቸውን ጥቅም ከማስጠበቅና የውጭ ኃይሎችን ፍላጎት ተግባራዊ ከማድረግ በስተቀር አልፈው ሊሄዱ የሚችሉ አይደሉም።  ስለሆነም  አንድ አዲስ አገዛዝ ከፍተኛ ንቃተ-ህሊና እስከሌለው ድረስና፣ በዲስፕሊንና በስርዓት የታነፀ እስካልሆነ ድረስ፣ በተለይም ደግሞ የስልጣኔና የዕድገትን ትርጉም የተረዳ እስካልሆነ ድረስ፣ በዲሞክራሲና በነፃነት ስም ምሎ ተገዝቶ ስልጣን ላይ የሚወጣ ኃይል ቀድሞውን የተገነባውን የመንግስት መኪና እንደገና በማዋቀርና የመጨቆኛ መሳሪያ በማድረግና ከውጭ ኃይሎች ጋር በመመሰጣጠር የድህነቱን ዘመን እንደሚያራዝም በብዙ የሶስተኛው ዓለም ተብለው በሚጠሩ አገሮች የታየ ጉዳይ ነው። በብዙ የሶስተኛው ዓለም አገሮች፣ አገራችንንም ጨምሮ አብዮት የተካሄደበትን፣ ወይም የአስተዳደር ለውጥ የተደረገበትን ሁኔታ ስንመለከት አብዮቶች ወይም የአገዛዝ ለውጦች ተጨናግፈው የሚቀሩት ይህንን የሚቀናቀን ወይም የሚገታ ኃይል ከመጀመሪያውኑ ስለሌለ ነው። ለምሳሌ በኢትዮጵያ አብዮት ወቅት ህዝባዊ ድርጅቶች በየቦታው ተቋቋመው ነበር። ይህ ዐይነቱ  ዱዋል ፓወር በጣም ጥሩ ጅምርና፣ ቢሮክራሲውን የሚተካና የሚቆጣጠር ኃይል ሆኖ የታቀደ ቢሆንም፣ የራሳቸን ጥቅም ተነካብን የሚሉ ኃይሎች ከውጭው ዓለም ጋር በመቆላለፋ፣ በተጨማሪም ውስጥ በተፈጠረው ጨቅላ አስተሳሰብና አላስፈላጊ ትግል ይህ ዐይነቱ የመጀመሪያው የዲሞክራሲ ፅንስስ በእንጭጩ እንዲቀጭ ተደረገ።። ወደ ሌሎች አገሮችም ስንመጣ ደግሞ በተጨባጭ ሲታይ እንደ አውሮፓው የምሁር እንቅስቃሴ ህብረተሰብን በሚመለከቱ ማንኛውም ጥያቄዎች ላይ ውይይትና ክርክር ስለማይደረግ በአንዳች አጋጣሚ ስልጣን ላይ የሚወጡ ኃይሎች ስልጣናቸው የህዝብን ፍላጎት ማሟያና ዲሞክራሲያዊ ስርዓት መገንቢያ ከማድረግ ይልቅ የራሳቸው ጥቅም መሳሪያ በማድረግ ወደ ጨቋኝነት ይለውጧቸዋል። የአንጎላንና የዚምባብዌን እንዲሁም የደቡብ አፍሪካን ሁኔታ መመልከቱ ይበቃል። አንዳንድ አገዛዞች ደግሞ አሻፈረኝ ሲሉና የራሳቸውን መንገድ መከተል ሲጀምሩ እንዲገደሉ ይደረጋል። የቶማስ ሳንካራን ሙከራና አከሻሸፍ መመልከቱ ብቻ በቂ ነው። የቶማስ ሳንካራ ጓደኛ ከፈረንሳዩ  የሶሻሊስት መንግስት ነኝ ባዩ የስለላ ኃይል ጋር በመመሰጣጠርና ድጋፍ በማግኘት ቶማስ ሳንካራ እንዲገደል  ተደረገ።  በተለይም የፈርንሳይ ፓርቲዎች፣ ሶሻሊስቶች ሆኑ ወግ-አጥባቂዎች ምንም ዐይነት ለውጥና የኑሮ መሻሻል እንዳይመጣ በድሮ ቅኝ ግዛቶቻቸው ላይ የሚፈጽሙት ወንጀል በሰፊው ተመዝግቧል። ስለሆነም የካፒታሊስት አገሮች የአፍሪካ አገሮች እንዳያድጉ፣ በሳይንስና በቴክኖሎጂ እንዳይበለጽጉ አንድ አገዛዝ ለየት ያለ መስመር  የሚከተል ከሆነ የተለያየ ምክንያት በመፈልግ ብጥብጥ እንዲነሳ ወይም የመንግስት ግልበጣ እንዲካሄድ ያደርጋሉ። ምክንያቱም አገሮች ሁልጊዜ እየተዋከቡ መኖር አለባቸው። እርስ በርሳቸው ሲፋጠጡና ወደ ጦርነት ሲያመሩ ህብረተሰብአዊ መዛባት በመፈጠር የህዝቦች ዋናው ተግባር ጦርነት ይሆናል። ዕድገትና ስልጣኔ የአፍሪካ አገሮች ዋናው የትግል መመሪያ መሆናቸው ቀርቶ የሰው ትግል ወደ ውንብድነት ይቀየራል።  በዚህ መልክ ባለፉት ሃምሳ ዓመታት በአፍሪካ ምድር ከስድሳ የማያንሱ የመንግስት ግልበጣ ሙከራዎች ተካሄደው ተሳክተዋል። እነዚህ ሁሉ የመንግስት ግልበጣዎች የተካሄዱት ልዩ የክርስትናንና የሊበራሊዝም እሴት አለኝ በሚለው የምዕራቡ ካፒታሊዝም፣ በተለይም በእንግሊዝ፣ በፈረንሳይና በአሜሪካን መንግስታት አማካይነት ነው። ለሶት መቶ ሺህ ምሁራን ዕልቂት ተጠያቂው የሆነው ኢዲ አሚን በእንግሊዝና በእስራኤል የስለላ ድርጅት ነው ፕሬዚደንት ሚልተን ኦቦቴን አስዎግዶ የግድያ ዘመቻውን የከፈተው።

እንደገና ወደ አገራችን ስንመጣ በደርግ ዘመን የተዋቀረው የጭቆና ስርዓት ቢፈራርስም የወያኔ አገዛዝ የአሰራር ስልቱን በመውሰድ የጭቆና ሰንሰለቱን በእዲስ መልክ መዘርጋት ችሏል፤ አቢይ አህመድም በዚያ በመቀጠል ጭቆናውንና ግድያውን አባብሶታል። ይሁንና ደግሞ ይህንን የጭቆናና የከፋፍለህ ግዛ አጋዛዙን ለማጠናከር የምዕራቡ ዓለም፣ በተለይም እንግሊዝና አሜሪካ እንደተባበሯቸው ግልጽ ነው። ሸበረተኝነትን መዋጋት ያስፈልጋል የሚለው ፈሊጥ ሌላው የትግል መፈክር በሆነበት ዘመን በመሀከላቸው ያለው መተሳሰርና ወደ ውስጥ ደግሞ ጭቆናን አስፍኖ ነፃነትን መግፈፍና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እንዳይመጣ ማድረግ ዋናው የትግል ስትራቴጂ መሆኑን የእኔ ትንተና ብቻ ሳይሆን፣ ብዙ ጥናቶችም ያረጋግጣሉ። በተለይም እንደኛ ባለው ከፍተኛ የሆነ የአስተሳሰብ ድክመት በሰፈነበትና፣ ተማርኩኝ የሚለው አንዳንዱ ዝም ብሎ ሁኔታውን በሚያይበት አገርና፣ ለስልጣን የሚሯሯጠው ደግሞ የሚታየውን ነገር ለማየትና ለመተንተን በማይፈለግበት አገር ለነፃነትና ለዕውነተኛ ዲሞክራሲ የሚደረገው ትግል እጅግ አድካሚ ይሆናል። ስለሆነም የየካቲቱ አብዮትና በኋላ ደግሞ የምርጫ 97 ውጤት ሊከስሽፉ የቻሉት በመዘናጋት፣ የውጭ ኃይሎችን በመተማመንና ለስልጣን በመስገብገብ የተነሳ ነው። ብሄራዊ አጀንዳን ከማስቀደም ይልቅ የራስን የአጭር ጊዜ ህልም ተግባራዊ ለማድረግ ሲባል ነው እጅ ውስጥ ሊገባ የነበረው ስልጣን እንዲነጠቅ የተደረገውና ህዝባችንም እስከዛሬ ድረስ ፍዳውን እንዲያይ የተፈረደበት። ስለሆነም ከምርጫ 97 በኋላ በውጭ ኃይሎችና በወያኔ አገዛዝ መሀከል ያለው የእከክልኝ ልከክልህ ግኑኝነት የባሰውኑ እየተጠናከረ እንደመጣ እንመለከታለን። ለዚህ ደግሞ የአግአዚ ጦር በቂ ማረጋገጫ ነው። በአሁኑ በአቢይ አህመድ የአገዛዝ ዘመንም የአሜሪካ አሉታዊ ተፅዕኖ ከፍተኛ ነው። የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ከእሱ ቁጥጥር ውጭ የሆነ የአገዛዝ ለውጥ እንዲፈልግ አይፈልግም። በተለይም በአሁኑ ወቅት የራሱን ሰዎች በመጠቀም የፋኖን የጥርነት ትግል ለማኮላሸት የማያደርገው ጥረት የለም። ለማንኛውም ይህንን ሀቅ የአሜሪካንና የግበረአበሮቹን የተወሳሰበ ሴራ ለመቀበል የማይፈልጉ ተቃውሚ ነን የሚሉ ኃይሎች አሉ። ታዲያ በዚህ ዐይነት ሁኔታ ውስጥ ምን ዐይነት የነፃነት ትግል ነው ሊካሄድ የሚችለው? ምንስ ዐይነት ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለማምጣት ነው የሚካሄደው ትግል?

ታጋይ ነን የሚሉ ኃይሎች በሙሉ በእርግጥም ለነፃነት እንታገላለን የሚሉ ከሆነ፣ 1ኛ) የመንግስትን መኪና አወቃቀር ከቲዎሪ አንፃር በሰፊው በማጥናትና በመገምገም ውይይት እንዲደረግበት ማድረግ አለባቸው። የመንግስትን ምንነትና ተግባርን አስመልክቶ  ከፕሌቶን ጀምሮ እስከነ ሺለሩ ጥበባዊ መንግስት ድረስ ሰፊ ውይይትና ክርክር ተካሂዷል። የማርክሲስት ምሁራንም፣ በተለይም እነ ፖላንትዛስ የካፒታሊዝምን መንግስት ምንነትና የሀብት ክምችት አጋዥነት በሰፊው አጥንተው በመጽሀፍ መልክ ለንባብ አቅርበዋል። በተጨማሪም ሌሎች የሶስተኛው ዓለም አገሮችና አንዳንድ የአውሮፓ ምሁራን  እንደዚሁ በሶስተኛው ዓለምና በካፒታሊስት አገሮች መሀከል ስላለው መተሳሰርና የዕድገት ማነቆነት በበቂው አትተዋል። ጆን ጋልቱን የሚባለው የስዊድሹ የሶስዮሎጂና የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር፣ እንደዚሁ ኢምፔሪያሊዝምና የኃይል አወቃቀር“(Imperialism and Structural Power) በሚለው ግሩም መጽሀፉ፣ በኢምፔሪያሊዝም አማካይነት በሶስተኛው ዓለም አገሮች ህዝቦች ላይ የሚደርሰውን ጭቆናና በኢምፔሪያሊስት ኃይሎችና በአፍሪካ መንግስታትመሀክል ያለውን የጥቅም መተሳሰረና የዕድገት ማነቆነት ሳይንሳዊ በሆነ መልክ አትቷል።  ከዚህም በሻገር በተለይም የፋይናንስ ካፒታሊዝም አይሎ በመወጣበት ባሁኑ ወቅት የብዙ ካፒታሊስት አገሮች የመንግስት መኪና በፊናንስ ካፒታሊዝም ቁጥጥር ስር እየዋለና የስለላ መዋቅሩንም እያጠናከረ በመምጣት ነፃነትን አፋኝ እየሆነ መጥቷል። በመሆኑም ይህ ጉዳይ በሶስተኛው ዓለም አገሮች በመስፋፋት መንግስታቱን ተቀጣይና ትዕዛዝ ተቀባይ አድርጓቸዋል። በተለይም ይህ ዐይነቱ ነፃነትን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ማፈኑና ህዝብን መቆጣጠሩ በአሜሪካን ምድር የተስፋፋ ነው። ሳልማድ ሩድሺን ስድሳ አስምስተኛ ዕድሜውን ሲያከብር ባደረገው ንግግር የነፃነት ትርጉም በተለይም በአሜሪካ ምድር እየታፈነ እንደመጣና፣ ማን ምን ዐይነት መጽሀፍን እንደሚያነብ እንደሚመዘገብ በንግግሩ ላይ ጠቅሷል። 2ኛ) የአገራችንን የመንግስት አወቃቀር ከታሪክ አንፃር ማጥናትና፣ ለምንስና እንዴት ለኢኮኖሚ ዕድገት ጠንቅ እንደሆነ ማማልከቱ የምሁራን ተግባር ነው። ከዚህ ስንነሳ ከ40ዎቹ መጨረሻ ጀምሮ በአገራችን ምድር የተዋቀረው መንግስታዊ መኪና ከውጭው ኃይል ጋር የተሳሰረ እንደነበረ ማጥናትና ለውይይት ማቅረብ የሚያስፈልግ ይመስለኛል። ይህ ጥያቄ በሰፊው ሳይጠናና ለክርክር ሳይቀርብ ወደ ስልጣን የሚደረግ ጉዞ የመጨረሻ መጨረሻ የነፃነቱንና የዕድገቱን ዘመን ያጨልመዋል። 3ኛ) ኢትዮጵያ ከውጭው ዓለም ጋር ግኑኝነቷን ካጠናከረች በኋላ በርዕዮተ-ዓለምና በአመለካከት ደረጃ፣ እንዲሁም ደግሞ በፍጆታ አጠቃቀም ያገኘችውንም ጥቅም ሆነ የደረሰባትን ጉዳት አንስቶ መወያየቱ ለነፃነት የሚደረገውን ትግል ግልጽ ያደርገዋል። በተለይም በባህል ላይ የሚደርሰው ወረራና ወጣቱን ማዘናጋቱ የቱን ያህል ራሳችንን እንዳናውቅና የነፃነቱንም ትግል አስቸጋሪ እንዳደረገው መወያየቱ ጠቃሚ ይመስለኛል።  ከዚህም በመነሳት የዓለም ኮሙኒቲ የሚባለው የሚለፍፈውን የህግ-የበላይነትና የገበያ ወይም ነፃ ንግድ ኢኮኖሚ ውስንነት መመርመርና እኛ ከምናልመውና ከምንታገልለት ነፃነትና ዕድገት ጋር ይጣጣም ወይም አይጣጣም እንደሆን መወያዩቱ እጅግ አስፈላጊ ነው። የህግ የበላይነት ዛሬ ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነት ያገኘ ኖርም ነው ብሎ ማተቱ ብቻ የሚበቃ አይመስለኝም። የህግ የበላይነት ከጥቂት ግለሰቦች በሀብት መደለብ ጋር የተያያዘና፣  ይሁንና ግን ሁሉም በህግ ፊት እኩል ነው የሚለውን የተዛባ አመለካከት የሚያንፀባርቅ መሆኑን ማሳየት ያስፈልጋል። በተጨማሪም በዛሬው ዓለም ብዙ አገዛዞችና ኢንስቲቱሽኖች በሎቢይስቶች በሚደገፉበትና በተሰገሰጉበት ዘመን የህግ የበላይነትና ተራ ምርጫ የሚባሉት ቦታ እንደሌላቸው መረዳት ያስፈልጋል። የፈለገውን ያህል ህዝባዊ ተቃውሞ ቢደርስም  በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠሩ ፊርማዎች ለአገዛዞችና ለህዝብ ተጠሪዎች ቢቀርቡም፣ መንግስታት በሎቢስቶች ግፊት የተነሳ የህዝብን እርሮና ጩኸት እንደማይሰሙ እንከታተላለን። በአሜሪካንና በአውሮፓ አንድነት የተካሄደውን የነፃ ንግድ ስምምነት(TTIP) ለተከታተለው የምንገነዘበው ድርድሩ በተዘጋ መልክ የሚካሄድና ህዝብም እንዲያውቀው የሚደረግ አይደለም። ራሳቸው የህዝብ ተጠሪዎች ነን የሚሉ ፓርሊሜንቴሪያን እንኳ የስምምነቱን ውልና አካሄድ ምስጢር ማንበብ አይፈቀድላቸውም። እስከዚህ ድረስ ነው የዘመኑ ካፒታሊዝም የህዝቦችን ነፃነት መግፈፍ የቻለው። በምንመገበው ምግብ ውስጥ ያሉትን ንጥረ-ነገሮች እንኳ የማወቅ መብት የለንም። መታወቅ ወይም በፓኬቱ ላይ በዝርዝር መቀመጥ የለባቸውም። ምክንያቱም ይህ ዐይነቱ ግልጽነት የነፃ ገበያን መሰረተ-ሃሳብ ይፃረራል የሚል ነው። ከዚህ ስንነሳ እኛ ኢትዮጵያውያን በነፃነትና በኢኮኖሚ ዕድገት መሀከል ያለውን ዲያሌክቲካዊ ግኑኝነት በአንድ በኩል፣ በሌላ ወገን ደግሞ በዓለም አቀፋዊው ካፒታሊዝምና በመንግስታችን መሀከል ያለውን መተሳሰርና መደጋገፍ፣ ከዚህም በመነሳት ይህ ዐይነቱ የእከክልኝ ልከክልህ መደጋገፍና መተሳሰር የቱን ያህል ለኢኮኖሚ ዕድገትና ለነፃነት፣ እንዲሁም ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት  መገንባት እንቅፋት እንደሚሆን መወያየቱ እጅግ አስፈላጊ ነው።

      ዲሞክራሲና የዲሞክራሲ ትርጉም!

በጥንታዊቱ ግሪክ ዘመን ዲሞክራሲ የሚለው ጽንሰ-ሃሳብ ከህዝብ አገዛዝ ጋር የተያያዘ ሲሆን፣ ተግባራዊነቱ በሶስት ኢንስቲቱሽኖች የሚወሰን ነበር። በ507 ዓ.ም ከክርስቶስ ልደት በፊት ሲሌይስቴነስ የሚባለው መሪ ፖለቲካዊ የጥገና ለውጥ ያደርጋል። በጥገና ለውጡ መሰረት የውስጡን ፖለቲካና የውጭውን ፖሊሲ የሚያስተዳድር አካል ይመርጣል። ይህ አካል ህግን የሚያወጣና ተግባራዊ የሚያደርግ ሲሆን፣ በሁለተኛ ደረጃ፣ ከተለያዩ የአቴን ጎሳዎች የተውጣጡ ተወካዮች የሚሳተፉበት መድረክ ይቋቋማል። በሶስተኛ ደረጃ፣ ህዝቡ ብሶቱን ወይም ቅሬታውን የሚያቀርብበት ፍርድቤት ይቋቋማል። ይህ ዐይነቱ ዲሞክራሲ ከዚህ ቀደም ብሎ በአሪስቶክራሲውና በተራው ህዝብ መሀከል የነበረውን ልዩነት ከሞላ ጎደል የሰበረ በመሆኑ እስከተወሰነ ደረጃ ድረስ ህዝቡ ከህግ ፊት እኩል ነበር። በሌላ ወገን ግን እንደዚህ ዐይነቱ ዲሞክራሲ የተወሰነውን የአቴንን ዜጋ የሚመለከትና ሴቶችንም ያገለለ ነበር። ይሁንና ከጊዜው የህብረተሰብ ዕድገት አንፃርና በጎሳዎች መሀከል ከሚደረገው ሽኩቻ ሁኔታ ስንነሳ ይህ በአቴኑ መሪ ለመጀመሪያ ጊዜ ተግባራዊ የሆነው የዲሞክራሲ ጽንሰ-ሃሳብ አንድ እርምጃና ከዚያ በኋላ ለተነሳው የአውሮፓ የዲሞክራሲ ትግልና አስተሳሰብ መሰረት የጣለ ነው ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል።  በመሆኑም በአቴኑ ዘመን ተግባራዊ የሆነው የዲሞክራሲ  አስተሳሰብ  ከጎሳ ፖለቲካ ጋር የተያያዘ ሳይሆን ቀስ በቀስ ለሲቪል ሊበሪትና ለግለሰብአዊ ነፃነት በሩን የከፈተ ነው ማለት ይቻላል። እንደዚሁ ከክርስቶስ ልድት በኋላ በ594 ዓ.ም ስልጣንን የተረከበው ሶሎን የሚባለው መሪ አዲስና የተሻሻለ የጥገና ለውጥና ህገ-መንግስት እንዲወጣ ያደርጋል። በጥገና ለውጡም መሰረት ህዝቡ ተጠሪዎችን በመምረጥ በፖለቲካ አወቃቀሩ ላይ ተሳትፎ እንዲኖረው ይደረጋል። በዚህም መሰረት አዲስ የተመረጠው የህዝብ ተጠሪ ሶስት ተግባሮች እንዲኖሩት ይደረጋል። ኦርጋኑም ህግን የሚያወጣ፣ የመንግስት ሰራተኞችን የሚመርጥና ጦርነት መካሄዱንና አለመካሄዱን የሚወስን ይሆናል። ይሁንና ግን በዚህ ዐይነቱ ፖለቲካዊ የጥገና ለውጥ ሴቶች፣ አገልጋዮችና የውጭ ሰዎች የመመረጥ መብት አልነበራቸውም። በህገ-መንግስቱ መሰረት፣ በእርጋኑ ውስጥ ተሳትፎ የነበራቸው የመሬት ከበርቴዎች፣ ሀብታም ነጋዴዎች፣ የተለያየ ደረጃ ያላቸው አንጥረኞችና ገበሪዎች ነበሩ። በዚህ መልክ በሶሎን አማካይነት የተዋቀረው አዲሱ ዲሞክራሲያዊና ሚዛናዊ አገዛዝ በዕዳ የተተበተበውንና  በባላባቱ ስር ጥገኛ የሆነውን ገበሬ ነፃ በማድረግ ለመጀመሪያ ጊዜ ሰፋ ያለ የስልጣኔ መሰረት ለመጣል ረዳ። በእርግጥ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ነው ፍልስፍናም ሆነ ማቲማቲክስ፣ እንዲሁም ጥበብና አርክቴክቸር ቀጥሎም ድራማ የበለጠ በሰው የመፍጠር ኃይል ተግባራዊ ሊሆኑ የቻሉት። ሶሎን ራሱ ፈላስፋና፣ በከፍተኛ ደረጃም የተገለጸለት መሪ ስለነበር የዲሞክራሲን ሰፊ ትርጉም በመረዳት በልዩ ልዩ መልኮች ሊገለጹ የሚችሉበትን ሁኔታ ማዘጋጀት ቻለ። ይህ ሁኔታ በግሪክ ምድር ውስጥ በተለይም በአቴንና በአካባቢው ለስራ ክፍፍል መዳበርና ለንግድ ልውውጥ አመቺ ሁኔታን ይፈጥራል። በዚህ መልክ ቀደም ብሎ በልዩ ልዩ ጎሳዎች ይደረግ የነበረው ውጊያና ፍጥጫ ቆሞ ጠቅላላው ህዝብ ለስራና ለንግድ ታጥቆ ይነሳል። ይሁንና ግን ሶሎን ስልጣኑን ከለቀቀ በኋላ ይህ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ፈተና ይደርስበታል። ሶፊስቶች የመንግስቱን መኪና ወይም አገዛዙን በመክበብና ለራሳቸው መጠቀሚያ በማድረግ የጦርነት ምንጭ ያደርጉታል።  የኋላ ኋላም የግሪኩ ስልጣኔ በሮማውያን ወራሪዎች ቀስ በቀስ ድምጥማጡ ይጠፋል። ታላቁ አሊክሳንደር አልገበርም ያሉትን ሁሉ ካሸነፈ በኋላ ከግብጽ፣ በሱ ስም ከተጠራው አሊክሳንደሪያ ከተማ በመነሳት በአካባቢው ስልጣኔን ለማስፋፋት ያደረገው ሙከራ በሮማውያን ወራሪዎች ይከሽፋል። ወደ ሰባት መቶ ሺህ የሚጠጉ መጽሀፎችን ሁለት ጊዜ ካቃጠሉና፣ ከግብጽም ሀብት ከዘረፉ በኋላ የግሪክ ስልጣኔ ሲደመሰስ በሱ ምትክ ወደ ሰባት መቶ ዓመታት የሚጠጋ የጨለማ ስርዓት ይዘረጋል። የሮማውያን ወረራና ሌሎችን ገባር አድርጎ መግዛት ቀስ በቀስ እየተዳከመ ይመጣል። በየቦታው የተስፋፋው የሮማውያን ኃይሉ እየተሟጠጠ ይመጣል። የመጨረሻ መጨረሻም  በጀርመን ወራሪዎች በመደምሰስ ለፊዩዳሉ ስርዓት በሩን ይከፍታል።  በካቶሊክ ቄሶችና በአሪስቶክራሲው የአውሮፓ ህዝብ መሰቃየት ይጀምራል። ይህ ሁኔታ ግን የኋላ ኋላ በተገለጸላቸው ኃይሎች፣ በተለይም በተፈጥሮ ሳይንስ አማካይነት መጋፈጥ ሲጀምር፣ አዳዲስ ኃይሎች በመፈጠር የድሮው አገዛዝ በአረጀው መልኩ ሊቀጥል እንደማይችል ግልጽ ይሆናል ።

ከኢንላይተሜንት ጀምሮ የተደረገውን በፍጹም ሞናርኪዎችን አገዛዝ ላይ ይካሄድ የነበረውን የተቃውሞ ትግል ስንመለከት ሪፑብሊክን መመስረትና ገበሬውን ከአርስቶክራቲውና ከፊዩዳሉ መደብ ለማላቀቅ የተደረገ ትግል ዲሞክራሲያዊ ትግል ነው ማለት ይቻላል። በተለይም በካቶሊክ ሃይማኖት ተከታዮችና በፕሮቴስታንት የሃይማኖት መሪዎች መሀከል የነበረው ትግል በአልተገለጸላቸውና በተገለጸላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች መሀከል የተደረገ የመረረ ትግል ነበር። ሁለቱ የሃይማኖት ተከታይ መሪዎች በከፈቱት ጦርነት በአንዳንድ ቦታዎች ሁለት ሶስተኛው የሚሆነው ህዝብ እንዳለቀ የታሪክ ማስረጃዎች ያረጋግጣሉ። ከዚህ ውጣ ውረድና የርስ በርስ መተላለቅ በኋላ ነው ጥቂት የተገለጸላቸው ምሁራን ጣልቃ በመግባት መረጋጋት ሊፈጥሩና፣ በፊዩዳሉ አገዛዝ የተሰቃዩ አገዛዞች በፍጹም ሞናርኪያዊ አገዛዝ በመጠቃለል ብዙ የአውሮፓ አገሮች ወደ ህብረ-ብሄር ግንባታ መሸጋገር የቻሉት። ከዚህ የምንረዳው ለዲሞክራሲና ለነጻነት የሚደረገው ትግል በጣም አስቸጋሪና፣ የግዴታም የተገጸላቸው፣ ሰፋና የጠለቀ ዕውቀት ያላቸው ሳይንቲስቶችና ፈላስፋዎች ጣልቃ ገብነት የቱን ያህል ወሳኝ ሚናን እንደሚጫወት ነው። ምክንያቱም በጊዜው የነበሩት አገዛዞች በጣም አክራሪዎች ስለነበሩና፣ ህዝቡም በበሽታና በድህነት ይሰቃይ ስለነበር ከዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለመውጣት እንዴት አድርጎ አገዛዞችን የጥቅማቸው ሳይሆን የመንፈሳቸው ተገዢዎች ማድረግ ይቻላል? የሚለው አስተሳሰብ ነበር ምሁራንን ያስጨንቃቸው የነበረው። ምክንያቱም ከድጡ ወደ ማጡ እንዲሉ፣ የባሰ ችግር ውስጥ ላለመግባት ሲባል የተደረሰበት ውሳኔ ከፍተኛ የጭንቅላት ሰራ መስራትና የምሁራኑን መሰረት ማስፋት ነበር። ይህ ዐይነቱ አካሄድ በአውሮፓ ምድር ውስጥ በልዩ ልዩ መልክ ሊገለጽ የሚችል ምሁራዊ እንቅስቃሴ እንዲስፋፋና እንዲዳብር በማድረግ የዲሞክራሲን ጥያቄና አፈታት የበለጠ እምርታና መልክ ሰጠው።

በሌላ ወገን ካፒታሊዝም እያደገ ሲመጣ የወዝ አደሩ መደብም አዳዲስ ጥያቄዎች ማንሳት ጀመረ። በሙያ ማህበር መደራጀት፣ የስራ ሰዓት መቀነስና ከምርት ዕድገት ጋር ሊሄድ የሚችል ጥያቄዎች በመነሳት የከበርቴውን መደብ ማፋጠጥ ቻለ። ቀስ በቀስም የማርክስ ስራዎች ሲስፋፉ የተወሰነው የሰራተኛው መደብ ራሱን በኮሙኒስት ወይም በሶሻሊስታዊ አመለካከት ማደራጀት ቻለ። በየጊዜው ለሚነሳው የኢኮኖሚ ቀውስና ጥልቀት ያለው ብዝበዛ የካርል ማርክስና የፍሪድሪሽ ኤንግልስ ስራዎች እንደመመሪያ በመሆን አማራጭ የህብረተሰብ ማደራጃ ዘዴ ሆነ። ከካፒታሊዝም የኢኮኖሚና የህብረተሰብ አደረጃጀት ባሻገርም ሌላም ስርዓት መፍጠር እንደሚቻል ቲዎሪው እንደ አማራጭ ሆኖ ቀረበ። የማርክስ ስራዎች በጊዜው የነበረውን የካፒታሊዝም ዕድገት ነፀብራቆች ወይንም ውጤቶች ናቸው ማለት ይቻላል። የጊዜው መንፈስ(Zeitgeist) የወለደው ሲሆን፣ ዝም ብሎ ከሰማይ ዱብ ያለ ሳይሆን፣ ማርክስ ከሃያና ከሰላሳ ዐመታት ጥናትና ምርምር በኋላ ቀስ በቀስ ያዳበረው ነው። የማርክስ ስራዎችም የሚያረጋግጡት አንድን ህብረተሰብ፣ በተለይም የካፒታሊዝምን ስርዓት እነ አዳም ስሚዝና ሌሎቹ የጥንት ኢኮኖሚስቶቸ(Classical Economists) በመባል በሚታወቁት በተረጎሙት መልክ ሳይሆን በሌላ መልክም መተርጎም እንደሚቻልና፣ በማርክስ አባባል ይኸኛው ሳይንሳዊ የህብረተሰብ መተንተኛ ዘዴ  መሆኑን ነው ለማሳየት የተሞከረው። በዚህ መልክ አዳዲስ ቲዎሪዎች ሲፈልቁና ሲስፋፉ የምሁሩም አስተሳሰብ በተወሰነ አመለካከት ብቻ የሚሽከረከር ሳይሆን፣ የነገሮችን ሂደት ከሌላም አኳያ መመርመር እንደሚቻል ግንዛቤ ተደረሰበት። ስለሆነም እየተስፋፋ የመጣው ቲዎሪና የሰራተኛው መደብ በሙያ ማህበሩ መደራጀት በኢንዱስትሪ ውስጥና ከዚያ ውጭ ከከበርቴው መደብ ጋር በተጠሪዎቹ አማካይነት ቁጭ ብሎ ለመደራደር የሚቻልበት ሁኔታ ተፈጠረ።  ይህ የሚያሳየው ምንድነው ? አንድ ህብረተሰብ መስመሩን እንዳይስት፣ ወይም ደግሞ የጥቂቶች መጨፈሪያ እንዳይሆን ከተፈለገ የግዴታ ሁሉንም አስተሳሰቦች ሊያስተናግድ የሚችል ምሁራዊና ዲሞክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች እጅግ አስፈላጊ መሆናቸውን ነው።

በዘመናችን የዲሞክራሲን ትርጉምንና ተግባራዊነት ስንመለከት፣ ተግባራዊነቱ ተወካይን በመምረጥና በመመረጥ የሚገለጽ ቢሆንም፣ ይህ ዐይነቱ ሂደት ሊገለጽ የሚችለው በሶስት ኦርጋኖች መሀከል ባለው የስራ-ክፍፍል ነው። ይህም ማለት ኤክስኪዩቲቭ፣ የህግ አውጭና ህግ አስፈጻሚ። ሌሎች ዲሞክራሲያዊ ኢንስቲቱሽኖች በሙሉ በዚህ ስር ሲጠቃለሉ፣ በተለይም ከ1980ዎች ጀምሮ እያየለ የመጣው መንግስትንና ፓርላሜንትን የሚቆጣጠር ሰፋ ያለ የሲቪክ ማህበራት አለ። ስለሆነም በነፃ መደራጀት፣ ሃሳብን መግለጽ፣ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግና ህዝብንና አካባቢን የሚጎዱ ነገሮች እንዲቆሙ ማድረግ በትግል የተገኙ ብቻ ሳይሆኑ፣ የጠቅላላው የህብረተሰብ ጉዞና ዕድገት አጋዥ እንደሆኑ ማየት የተቻለው ከብዙ ውጣ ውረድና በከፍተኛ ምሁራዊ ተሳትፎ አማካይነት ነው። እዚህ ላይ አስቸጋሪ የሚሆነው የዲሞክራሲ አነሳሰና ትግል፣ የጥያቄው አቀራረብ በጣም ስፊና ውስብስብ ስለሆነ በማቲማቲካል ሞዴሎች ማቅረብ አይቻልም። ይህ ዐይነቱ አቀራረብ እጅግ አሳሳች ከመሆኑም የተነሳ ወደ ማይሆን አቅጣጫ እንድናመራ በማድረግ ለዕውነተኛ ነፃነት የሚደረግውን ትግል እንድንዘነጋ ያደርገናል። በሌላ አነጋገር፣ ዲሞክራሲ የሚጨበጥና የሚዳሰስ አይደለም፤ የምንለማመድበት፤ የምንኖርበት፣ ስሜታችንንና ቅሬታችንን የምንገልጽበት፣ የሚያሳስበንና የሚያስጨንቀንን ወደ ውጭ አውጥተን ለመወያየት የሚያስችለን መሳሪያ  ነው። ስለዚህ ነው ዲሞክራሲን አታየውም፣ ትኖርበታለህ፣ ትለማመድበታለህ፣ የህይወትህ አንደኛው አካል እንዲሆን ታደርገዋለህ የሚባለው። ስለሆነም የዲሞክራሲ ምንነት በቁጥር የሚለካ ወይም በማቲማቴካል ሞዴል የሚረጋገጥ አይደለም። ከዚህ ስንነሳ የዲሞክራሲ ጥያቄ፣ ሶሻል ጀስቲስንና የኢኮኖሚ ጀስቲስን፣ እንዲሁም የፖለቲካ ጀስቲስኝ የሚያካትት ሲሆን፣ እነዚህ ነገሮች ደግሞ የግዴታ ዲሞክራሲያዊ ሆነው ከተዋቀሩ ኢንስቲቱሽኖች ጋር መያያዝ አለባቸው። ይሁንና ግን የካፒታሊዝም ዕድገትና መስፋፋት የሰው ጭንቅላት ከሚሸከመው በላይ በመሆኑ፣ አብዛኛው ህዝብ አቅመ-ቢስ እየሆነ እንደመጣ እንመለከታለን። በተለይም ጊዜ ወስዶ ምሁራዊ ጥናት የሚያደርገው በጣም ጥቂቱ ስለሆነ፣ ሰፊው ህዝብ በቴክኖከራቲክ ጽንሰ-ሃሳብና የአሰራር ዘዴ  እየተደናበረና ግራ እየተጋባ ነው።  ከዚህ በሻገር የመንግስት መኪናዎች ይበልጥ በኤክስክቲቩ የሚመሩ ስለሆነና፣ የሚሊታሪ ኢንደስትሪያል ትስስር(Military Industrail Complex) ስር እየሰደደና እየተጠናከረ በመምጣቱ፣ የፓርሊሜንታሪ ዲሞክራሲን እያዳከመው፣ ተጠሪዎች የህዝብ ተወካዮች መሆናቸው ቀርቶ የራሳቸውን ህይወት ማራዘሚያ መድረክ አድርገውታል ማለት ይቻላል። ስለሆነም ስልጣንን የጨበጡ ፓርቲዎችና ፕሬዜደንቶች ወይም ጠቅላይ ሚኒስተሮች የአንድ አገር ተጠሪ ቢመስሉም፣ በቀጥታ የሚያንፀባርቁት የኢንዱስትሪና የሚሊተሪ ትስስርን ጥቅምና፣ በፀጥታ ኃይሎች አማካይነት የተሳሳተ ኢንፎርሜሽን እየተሰጣቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ ጦርነትን የሚያስፋፉና ደካማ መንግስታትንና አገሮችን የሚያወድሙ ሆነዋል። የከበርቴው የሊበራል ዲሞክራሲ እሴትና የክርስቲያን ቫልዩ የሚባለው አብዛኛው የምዕራብ አውሮፖና የአሜሪካ የሚኩራሩበት፣ በመሰረቱ ባዶ አነጋገር ሆኗል።  ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነት ያገኘ ቢመስልም ከቅርብ ዓመታት ጀምሮ በጥርጣሬ ዐይን እየታየ ነው። ለአንዳንድ አገሮች ሰላምንና ዲሞክራሲን፣ እንዲሁም ብልጽግናን አምጭ ከመሆኑ ይልቅ የጦርነትና  የራስን ጥቅም ማሳደጃ ዘዴ መሆኑ እየተገለጸላቸው መጥቷል።፡በዚህ መልክ ለሁላችንም የማይታይ ቀስ በቀስ ስር የሰደደ የመንግስት ግልበጣ በአብዛኛዎች የሶስተኛው ዓለም አገሮች፣ በተለይም በአፍሪቃ አገሮች ውስጥ ተካሂዷል ማለት ይቻላል።  ያም ሆኖ ግን ይህንን የሚያጋልጡና የሚዋጉ  ኃይሎችና ድርጅቶች እንደ እንጉዳይ ፈልተዋል። ስለሆነም ለዕውነተኛ ዲሞክራሲና ነፃነት የሚደረገው ትግል ያለቀለት ሳይሆን፣ ገና በአዲስ መልክ የሚቀጥል መሆኑን እንገነዘባለን።

ወደ አገራችን ስንመጣ ለዲሞክራሲ ያለን ግንዛቤ አስቸጋሪ የሚሆነው፣ የዲሞክራሲና የነፃነት ጥያቄን ስልጣን ላይ ያሉ ኃይሎች  በቀላሉ ስልጣን ለመስጠት ወይም ለመልቀቅ ፈቃደኛ አለመሆናቸው ለመገንዘብ ዝግጁ አለመሆናችን ነው። በዚህም ምክንያት የዲሞክራሲና የነፃነት ጥያቄ የረጅም ጊዜ ምሁራዊ ትግልን እንደሚጠይቁና፣ ለዚህ ደግሞ ከፍተኛ መስዋዕትነት መከፈል እንዳለበት አለመገንዘባችን በምን መልክ ትግሉን ማካሄድ አንዳለበን ለመወያየት ዝግጁ ባለመሆናችን ትግሉን ውስብስብ እያደረገው መጥቷል። ከዚህም በላይ የስልጣን ጥያቄ ከስልጣኔና ከዕውነተኛ የዲሞክራሲ ፕሮጀክት ጋር ሊያያዝ ባለመቻሉ ትግሉ ለስልጣን ብቻ የሚደረግ ትግል እንጂ ለመሰረታዊ ለውጥ እንዳይደለ ሁኔታዎችን ለተከታተለ ሊገነዘብ ይችላል።  በሌላ ወገን ግን በአብዛኞቻቸን የተደረሰበት ድምዳሜ አንድን አገዛዝ በኃይል አስወግዶ ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን ማስፈን ይቻላል የሚለው አደገኛ ግንዛቤ ነው። ምክንያቱም እነዚህ በአጭር መንገድ፣ ይሁንና የዲሞክራሲን አፈታት የባሰውኑ የተወሳሰበና አድካሚ የሚያደርገውን ትግል የሚያካሂዱት እኛ የተሻለ የዲሞክራሲ ግንዛቤ አለን ከሚለው አስተሳሰብ የመነጨ አጉል ስሌት ነው። ይህ እንደማይሆን ደግሞ በብዙ የሶስተኛው ዓለም አገሮችና በአገራችንም ጭምር ተረጋግጧል። ምክንያቱም እነዚህ በአጭር መንገድ ስልጣን ለመያዝ የሚታገሉ ኃይሎች ራሳቸውም የዚያው ያልተገለጸለት ህብረተሰብ ውጤት በመሆናቸው  አጭሩን መንገድ እንመርጣለን ብለው ሲነሱ የባሰውኑ ትግሉን ውስብስብ በማድረግ ሁላችንም በቀላሉ ልንወጣው የማንችለው ችግር ውስጥ ይከቱናሎ። በተጨማሪም እነዚህ የተሻለ የዲሞክራሲ ግንዛቤ አለን የሚሉ ኃይሎች ለግልጽ ውይይትና ክርክር የተዘጋጁ አይደሉም። የአገራችንን ያለፉትን አርባና ሃምሳ ዓመታት ትግል ስንመረምር፣  ለዲሞክራሲና ለመብታችን እንታገላለን ብለው የሚነሱ ድርጅቶች ወይም ግለሰቦች ስልጣን ከጨበጡ በኋላ የባሰውኑ አፋኘና ገዳይ እንደሚሆኑ ነው። ህብረተሰብን ከማዘበራረቅና የድህነቱን ዘመን ከማራዘም በስተቀር ሌላ የሚታያቸው ነገር የለም። በዚህም የተነሳ ስንትና ስንት መቶ ዓመታት የተገነቡ እሴቶችንና ባህሎች እንዲበጣጠሱ በማድረግ ህዝቡ በውዥንብር ዓለም ውስጥ እንዲኖር ያደርጉታል። በኤርትራ ምድር የሰፈነው ፋሺሽታዊ አገዛዝና፣ ወደ ፋሽሺዝም የሚያመራው የአገራችን አመራር ከተሳሳተ የትግልና የዲሞክራሲ አስተሳሰብ የመነጨ አጉል አካሄድ ነው።  ህዝቡን በዘለዓለማዊ ፍጥጫና መፈራራት ውስጥ በመክተት ሰብአዊ መብቱ ተገፎ ፍዳውን እንዲያይ የተደረገው መጀመሪያውኑ የዲሞክራሲ ጥያቄ ከዕውነተኛ የጭንቅላት ወይም የመንፈስ ተሃድሶ ጋር ሊያያዝ ባለመቻሉ ነው።  የዲሞክራሲና የነፃነት ጥያቄ ከጭንቅላት ምርምርና ተሃድሶ ሳይሆን በጠብመንጃ ኃይል ይገኛል ተብሎ ውሳኔ ስለተደረሰበት፣ ይህ በራሱ ከረጅም ጊዜ አንፃር ሌላ የጭቆና አገዛዝ ምንጭ ሊሆን በቃ።

በአገራችን ምድር በስልጣን ላይ የሚወጡ ኃይሎች ስለዲሞክራሲ ሲነሳ የሚያስፈራቸው ነገር የዲሞክራሲን አስፈላጊነት አለመገንዘባቸው ብቻ ሳይሆን፣ ዲሞክራሲያዊ መብት ተፈጥሮአዊ መብትም መሆኑን ለመረዳት ባለመቻላቸው ነው። በዚህም የተነሳ የወታደሩ አገዛዝ ስልጣን ከጨበጠ በኋላ በዲሞራሴ ጥያቄ ላይ እንዴት እንዳንገራገረና፣ የኋላ ኋላ ደግሞ የባሰውኑ ወደ አፋኝና ወደ ጨፍጫፊነት እንዳመራ እንገነዘባለን። ህዝቡ እየነቃ ሲመጣና ህዝባዊ ድርጅቶች እንደ አሸን መፍለቅ ሲጀመሩ እሱ ብቻ ሳይሆን ቢሮክራሲውም ጭምር መርበድበድ ጀመሩ። ተራማጅ ነን በሚሉ ኃይሎች ዘንድ የተደረገውን መገዳደል ትተን፣ ወርቃማ ጎኑን ስንመለከት ለመጀመሪያ ጊዜ ህዝባዊ ድርጅቶች እንደ አሸን የፈለቁበትና፣ እንዲሁም የዕደ-ጥበብ ሙያዎችና የልዩ ልዩ ብሄረሰብ-ባህሎች የዳበሩበት ዘመን የዲሞክራሲ ጭላንጭል በሚታይበት በአጭር ጊዜ ውስጥ ነበር። ውስጥ ባለው የአገዛዝ ቅራኔና፣ በተለይም ደግሞ ተራማጅ ነኝ በሚለው ኃይል መሀከል ከወረቀት ትግል ይልቅ የጠብመንጃ ትግል ነው የሚያዋጣው በማለት የትግሉን አቃጣጫ ለመቀየር ሙከራ ባይደረግ ኖሮ፣  የዲሞክራሲው ጥያቄ ሌላ መስመርን ይዞ ይጓዝ ነበር። ብዙ ምክንያቶች ተደራርበው፣ በተለይም ደግሞ ተራማጅ ነኝ ይል የነበረው ኃይል ኃሉን አስተባብሮ በቀና መንፈሰ በዕውቀትና በሃሳብ ዙሪያ በመሰባሰብ ቢታገል ኖሮ የወታደሩን አገዛዝም መቆጣጠር ይቻል ነበር።  ይህም ሊሆን ባለመቻሉ ቀስ በቀስ ሁኔታው ከቁጥጥር ውጭ ሲወጣ የዲሞክራሲ ጥያቄ የባሰውኑ መታፈን ጀመረ። በመጀመሪያ አገርን ማዳን በሚለው ስር በተለይም አድርባዩ ሁሉ በመሰባሰብና ቢሮክራሲው ጉያ ስር በመውደቅ ከቀይ ሽብርና ከነጭ ሽብር በተረፉት ላይ ዘመቻውን በማካሄድ አገሪቱን የምሁር አልባ ለማድረግ በቃ። በተለይም ከሶስት የማይበልጡ የኢሃፓ መሪዎች በቁጭት በመነሳት አንዳንድ የመኢሶኖንን መሪዎዎች በጠራራ ፀሀይ ላይ ሲገድሉና በተለይም የከተማ ውስጥ ውጊያ ሲጀምሩ ሊያስከትል የሚደርስውን አደጋ በፍጹም አልተገነዘቡም። ይህንን የከተማ ውጊያና ተራማጅ ኃይሎችን እያነጣጠሩ መግደልን የተቃወሙ አንዳንድ የኢሃፓ መሪዎች ራሳቸው በጥቂት የኢሃፓ መሬዎች ነን በሚሉ በአሰቃቂ ሁኔታ እንዲገደሉ ለመደረግ በቅተዋል።  በሌላ ወገን ደግሞ መኢሶንና ደርግ የነጭ ሽብርን በቀይ ሽብር መመከት አለብን በሚለው አስተሳሰብ በመነሳት ቁጥራቸው የማይታወቅ የኢሃአፓ ካድሬዎች እየታደኑ ሊገደሉ በቅተዋል። አብዛኛዎቹም ለምን ዓላማ ኢሃአፓ እንደሚታገል የሚያውቁት ጉዳይ አልነበረም። ለማንኛውም በዚህ ዐይነቱ የርስ በርስ መተላልቅ የተነሳ ለአገር ዕድገትና ሰፋ ላለ ምሁራዊ እንቅስቃሴ የሚጠቅሙ ምሁራን እንዲያልቁ ተደረጉ። አገራችን የምሁራን አልባ ለመሆን በቃች።  ደርግም ሆነ የተቀሩት ለደርግ ያደሩ የማርክሲስት ሌኒንስት ድርጅቶች ነን ባዮች አባሎች የተረፈውን ምሁር እየጠቆሙ ሲያስገድሉ በኋላ አገሪቱ በምን ኃይል ለመገንባት እንደሚችሉ አለመረዳታቸው ነው። እነ ኮለኔል መንግስቱም ቀሪውን የተማረ ኃይልና ጂኔራሎችን ሲገድሉ ምን ታይቷቸው ነው? ለመሆኑ አንድን አገር ባልተማረ ኃይል መገንባት ይቻላል ወይ?  እሲከዚህ ድረስ ምርር አድርጎ ርስ በርስ የሚያጫርስ ነገር ምንድነው? በየትስ አገር ነው የታየው? የሚገርመውና የሚያሳዝነው ነገር ሁሉም ኃይሎች በማርክሲዝም ሌኒኒዝም እየማሉ ነበር ግድያውን ያጧጥፊት የነበረው። ያም ሆነ ይህ፣ ይህ የመረረ ሁነታ ያለፈ ቢመስልም፣ ዛሬም ቢሆን ከቂም በቀላቸው ያልተላቀቁ ኃይሎች እንዳሉ መገንዘብ ይቻላል። እነዚህ ኃይሎ አብዮቱ ተቀለበሰ ከተባለ በኋላ ተቀምጠው ጊዜ ውስደው ለምን ያህ ሁሉ ጭፍጨፋ እንደተካሄደና ታሪክ እንደወደመ ጥያቄ ለመጠየቅና ግልጽ ውይይት ለማድረግ ስላልቻሉ የጭንቅላት ተሃድሶ ሊያገኙ አልቻሉም። አንዳንዶቹ አሁንም ቢሆን በድሮው ዓለም ውስጥ በመዋኘት ለቀና ውይይትና ለግልጽነት በሩን ሁሉ ዘግተዋል። በዚህ ዐይነት ሁኔታ ውስጥ የፈለገውን ያህል ለአገሬ ነው የምታገለው ቢባልም እያንዳንዱ ለሰራው ስራ ተጠያቂ መሆኑን እስካላመነ ድረስና፣ የመጥፎም ሆነ የጥሩ ድርጊቱ ተካፋይ መሆኑን እስካለተገነዘበ ድረሰና ራሱን ለመጠየቅ ዝግጁ እስካልሆነ ድረስ ይህ ዐይነቱ ግትርነት ሊዲሞክራሲና ለነፃነት የሚደረገውን ትግል ያጨናግፋል።  አገርም ባላፈበት የትግል ዘዴ፣ -ትግል ካልነው፟- ሊገነባ አይችልም።  ስለዚህም ዛሬ አዲስና ሌላ ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ የወደቅን መሆናችንን በመገንዘብና ከድሮው ህልም በመላቀቅ አስተሳሰባችንን በመለወጥ ለአዲስ ህልምና ለአዲስ ዓላማ መነሳት ያለብን ይመስለኛል። አይ ያልተወራረደ ሂሳብ ስላለብን እሱን ካላጠናቀቅን ወደፊት ማምራት አንችልም የምንል ከሆነ  ትርጉም ለሌለው ለራሳችን ጥቅም ወይም ዓላማ ነው የምንታገለው ማለት ነው። ይህ ደግሞ በጠቅላላው ኢትዮጵያ ላይ እንደመዝመት ይቆጠራል። ቀናውን መንገድ እንከተላለን የምንል ከሆነ ደግሞ ቂም በቀልን ብቻ ሳይሆን፣ ከገባንበት የድርጅት አምልኮ መላቀቅ አለብን። ራሳችንን ከድርጅት አምልኮ ስናላቅቅ ብቻ ነው ዕውነተኛ ነፃነትንና፣ ካንት የሚለውን ፍሪ ዊል ማዳባር የምንችለው። ይህን ካልኩኝ በኋላ  ለ27 ዓመት በአገራችን ምድር ጭቆናን በማስፈን፣ የከፋፍለህ ግዛው ፖሊሲን ተግባራዊ በማድረግ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንዳይፈጠር ከፍተኛ እንቅፋት ጥሎ የሄደውን የወያኔን የትግል ስልትና ስለዲሞክራሲ የነበረውን የተበላሽ ግንዛቤ በመተኑም ቢሆን እንመልከት።

የወያኔ አገዛዝ ስለ ዲሞክራሲና ስለ ኢኮኖሚ ዕድገት የነበረው የተበላሸ ግንዛቤ  ስልጣን ላይ ከወጣ ጀምሮ የተፈተረ ሳይሆን የድርጅቱ ባህርይ ሆኖ ተቆራኝቶት ያደገበት ነው። ከመንፈሱ ጋር የተዋሃደና በፖለቲካዊ ዲስኮርስ ሳይሆን በጉልበት ብቻ የሚያምን ነበር። ራሱ በብሄረሰብ ደረጃ መደራጀትና ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ የጥገና ለውጦች ላይ መዝመቱ የሚያረጋግጠው ወያኔ የቱን ያህል ፀረ-ዲሞክራሲና ፀረ-ዕድገት ኃይል መሆኑን ነው። በሌላ ወገን ደግሞ ከእንደዚህ ዐይነቱ በብሄረሰብ ደረጀ ከተደራጀ ቡድን ዲሞክራሲያዊ መብቶችን መለመኑ ወይም መጠበቁ እጅግ የዋህነት ነው። በመጀመሪያ ደረጃ ድርጅቱ በምሁራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ በማለፍ የዲሞክራሲን ምንነት በመረዳት ወደ ውጭ ወጥቶ ለህዝብ ያስተማረና ለጋራ ትግል እጁን የዘረጋ እልነበረም።  ከሌሎች ፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎች ጋር በመተባበር ወታደራዊው አገዛዝን ሲዋጋ፣ የትግል አጋሮቹን የስልጣን መወጣጫና መጠቀሚያ ለማድረግ እንጂ በመሰረቱ እነሱን እንደ ትግል አጋሮቹ በማየት አብሮ በእኩልነት ለመግዛት አልነበረም። በመሆኑም እንደ ብሄረሰብ የመሳሰሉት ጥያቄዎች ለስልጣን መወጣጫ ያገለገሉትና የኋላ ኋላ ደግሞ ለከፋፍለህ ግዛው እንዲያመቸው እሱ በሚፈልገው መልክ ተግባራዊ ያደረጋቸው ናቸው። በመሆኑም የክልል አስተዳዳሪዎች ቢያንስ የራሳቸውን ውስን መብት በማግኘት አካባቢያቸውን ለማስተዳደር እንዳይችሉ ተደርገው ነበር። በሌላው ወገን ደግሞ ራሳቸው የክልል ተወካዮች በምሁር ደረጃ የዳበሩና በራሳቸው የሚተማመኑ ስላይደሉ አገዛዙ ጋር በእኩል ደረጃ በመደራደር መብታቸውን በማስከበር የክልላቸውን ሀብት በማንቀሳቀስ ለየብሄረሰባቸው የኑሮ መሻሻልን ሊያመጡ የሚችሉ አልነበሩም፤ ዛሬም አይደሉም።  የክልል አስተዳዳሪዎች በሀብት ሲደልቡና በቪላ ቤት ሲኖሩ፣ እንወክለዋለን የሚሉት ብሄረሰባቸው  መሰረታዊ ነገሮችን ማግኘት አቅቶት ሲሰቃይ ይታይ  ነበር፤ አሁንም ይታያል። የየመንደሮችንና የከተማዎችን ሁኔታ ለተመለከተ በብሄረሰብ ነፃነት ስም አገራችን የቱን ያህል የኋሊት ጉዞ እንደምታደርግ መረዳቱ ቀላል አይደለም።  ስለሆነም በወያኔ የአገዛዝ ዘመን በክልል ፌዴራሊዝም ስም ለየብሄረሰቡ ዕውነተኛ ነፃነትና ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ሊተገበሩ ያልቻሉት በወያኔ ፀረ-ዲሞክራሲያዊ አስተሳሰብ የተነሳና የየክልሉ አስተዳዳሪዎች ንቃተ-ህሊናቸው በጣም ዝቅ ያለ ከመሆኑ የተነሳ ነው። በአሁኑ የአቢይ አህመድ አገዛዝ ዘመንም የምንመለከተው ሀቅ ሁሉንም ክልሎች የመዋጥ ወይም የመጨፍለቅ ሂደት ነው እንጅ በሲቪሊ ነፃነት ላይ የተመሰረተን ዕውነተኛ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ማስፈን አይደለም። አቢይ አህመድና ግብረ-አበሮቹ ባለፉት ስድስት ዓመታት ያረጋገጡት ነገር በብዙ ሚሊዮን ማይሎች ከዲሞክራሲና ከነፃነት ሃሳብ ርቀው እንደሚገኙ ነው። ስለዲሞክራሲና ስለነፃነትም ያላቸው አስተሳሰብ አልቦ ነው ማለት ይቻላል። ስለሆነም በወያኔ የአገዛዝ ዘመን ዲሞክራሲያዊ ስርዓትና ነፃነት ተግባራዊ ሊሆኑ ያልቻሉትን ያህል አቢይና ግብረ-አበሮቹ ስልጣን ላይ እስካሉ ድረስ ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ ጉዳዮች አይደሉም።

የወደፊቱ የዲሞክራሲ ፕሮጀክት ጋ ስንመጣ እንዲያው የዓለም አቀፍ  ኮሙኒቲው የተቀበለው የህግ የበላይነት ብቻ  ነው ሊሰራ የሚችለው ብለን ነገሩን አደፋፍነን መሄድ አንችልም። በመጀመሪያ ደረጃ ይህ የዓለም ኮሙኒቲ የሚባለው ማን ነው?  ብለን መጠየቅ አለበን። ስምንት ቢሊዮን ህዝብ፣ ይህንን እወክላለሁ የሚለው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ ወይም ሰለጠንኩኝ የሚለው የምዕራቡ ዓለም?  ይህ ጉዳይ በግልጽ መቀመጥ አለበት። በየአገሮች እንደታየው፣ በተለይም ደግሞ እንደ አገራችን ባለ በብዙ ሽህ ችግሮች በተተበተበ አገር ውስጥ ተራ ዲሞክራሲና ምርጫ እንዲሁም መደብለ ፓርቲ የሚባሉት ፈሊጦች አንድ እርምጃ እንኳ ፈቀቅ ሊያደርጉን የሚችሉ አይደሉም። እነዚህ አባባሎች ወይም መፈክሮች በመሰረቱ የኢሊት መፈክሮች ወይም ህልሞች በመሆናቸው ሰፊውን ህዝብ ሙሉ በሙሉ የስልጣን ባለቤት ሊያደርጉት አይችሉም። ማንነቱን እንዲረዳና ፈጣሪ እንዲሆን አያግዙትም። ስለዚህም ህዝባችንን የስልጣን ባለቤት ወደሚያደርገው ዲሞክራሲያዊ ስርዓት መሸጋገር መቻል አለበን። ይህ ማለት ግን ፓርሊሜንተሪ ዲሞክራሲ አይስፈልግም ለማለት ሳይሆን፣ በዛሬው ወቅት ፓርቲዎች በርዕይና በፖሊሲ ደረጃ በደንብ ተደራጅተው በማይታገሉበት አገርና፣ ከፍተኛ ምህራዊ ክፍተት በሚታይበት አገር ውስጥ የመደብለ ፓርቲን ስርዓት ለመፍጠር እጅግ አስቸጋሪ ነው። በሌላ አነጋገር፣  የአገራችንን የተወሳሰበ ችግር ለመፍታት በመጀመሪያ ደረጃ የተሰበጣጠረውን ኃይል ሊያሰባስብ የሚችል መድረክ በመፍጠር ለሚቀጥሉት ሃምሳ ዓመታት አገሪቱን በጸና መሰረት ላይ ለመገንባት የሚያስችል ሁለ-ገብ ፕሮግራም መንደፍ አማራጭ የሌለው ሂደት ነው ብዬ እገምታለሁ። የተወሳሰበው ችግራችን በመደብለ ፓርቲና በምርጫ ሊፈታ የሚችል አይደለም። ወይም አንዱን ድርጅት ወይም ግለሰብ ውክልና በመስጠት ሊቀርፍ የሚችል አይደለም። የአገራችንን የተወሳሰቡ ችግሮችና የመጭውን ትውልድ ዕድል ከራሳችን ጥቅምና ዝና ባሻገር ማየት ያለብን ይመስለኛል። ስለሆነም ሁለ-ገብና የሰፊውን ህዝብ የማሰብ ኃይሉን አዳብሮ ነፃነት እንዲሰማው የሚያደርገውን የዲሞክራሲ ስርዓት መዘርጋት የሚያስፈልግ ይመስለኛል። ይህ ዐይነቱ የተቀደሰ  ዓላማ ወይም ህልም ተግባራዊ ሊሆን የሚችለው ከዛሬው አገዛዝ ባሻገር ብቻ ነው። ለዚህ ደግሞ የሬናሳንስ እንቅስቃሴ ወይም በሁሉም መልክ የሚገለጽ ምህራዊ እንቅስቃሴ መፈጠር አለበት። በተለይም ይህ ዐይነቱ እንቅስቃሴና ለዲሞክራሲና ለነፃነት የሚደረገው ትግል ለፖለቲካ ስልጣን እንታገላለን በሚሉ ኃይሎች የሚካሄድ ሳይሆን ከፖለቲካ ውጭ ያሉ በተለያዩ ሙያ በሰለጠኑ አማካይነት ብቻ ነው። በህብረተሰብ ታሪክ ግንባታም የተረጋገጠው ይህ ነው። ለፖለቲካ ስልጣን እንታገላለን የሚሉ ሰፊውን ህዝብ በቀን ተቀን የአገር ግንባታ ውስጥ ማሳተፍ የቻሉና የሚያስችሉ ስላይደለ ይህ ዐይነቱ የነፃነት ትግል መስመር ሊይዝ የሚችለው በተገለጸላቸው ምሁራን አማካይነት ብቻ ነው። የብዙዎች አገሮች ዲሞክራሲያዊ ምርጫዎች የኒዎ-ሊበራል አጀንዳዎች ስለሆኑ አንድን ህዝብ የስልጣንና የስልጣኔ ባለቤት ሊያደርጉት በፍጹም አይችሉም። በረቀቀ መንገድ ነፃነትን የሚያሰገፍፉና፣ ሀብት እንዲበዘበዝ የሚያደርጉ ናቸው።  ስለሆነም ከኤሊት ዲሞክራሲ ወደ ህዝብ አሳታፊ ዲሞክራሲ የምናመራበት ዘዴ ለውይይትና ለጥናት መቅረብ አለበት።

 

ምን ዐይነት የኢኮኖሚ ዕድገትና ለማን!

ስለ ኢኮኖሚ ዕድገት የተጻፉ ሊትሬቸሮች ሺህ በሺህ የሚቆጠሩ ናቸው። ቁጥራቸውም ከመብዛቱ የተነሳ ትክክለኛውን ሃሳብ ለመጨበጥ በጣም ያስቸግራል። በሌላ ወገን ግን ሰለ ኢኮኖሚ ዕድገት በሚወራበት ወይም በሚጻፍበት ጊዜ ከተወሰነ ርዕዮተ-ዓለም ክልልና የኃይል አሰላለፍ ውጭ ነጥሎ ማየት አይቻልም። ምክንያቱም በአውሮፓ ህብረተሰብ ታሪክ ውስጥ በየጊዜው አዳዲስ ኃይሎች ብቅ ሲሉ አዲስ ከተፈጠረው የኃይል አሰላለፍ ጋር ለማቀናጀት ሲባልና፣ አንዳንድ ምሁራን የዚኸኛውን ወይም የዚያኛውን መደብ ወይም የህብረተሰብ ክፍል ጥቅም እናስጠብቃለን ብለው ስለሚታገሉ፣ ኢኮኖሚክስም በርዕዮተ-ዓለም ትግል ክልል ውስጥ በመካተቱ የአንድን ህብረተሰብ የኢኮኖሚ ሁኔታ በዚህኛው ወይም በዚያኛው የቲዎሪ መነጽር ማየት አስገደደ። ስለሆነም፣ በተለይም ኢኮኖሚክስ ከሌሎች የትምህርት ዐይነቶች እየተነጠለ ሲወጣ የባሰውኑ በርዕዮተ-ዓለም መነፅር መታየት ጀመረ።  ኢኮኖሚክስም ሆነ ሌሎች የሶሻል ሳይንስ ትምህርቶች እሴተ-አልባ(Value-free) መሆናችው ቀርቶ ተጣመው በመቀርብ ለዕውነተኛ ነፃነት የሚደረገው ትግል አስቸጋሪ እየሆነ ሊመጣ ቻለ።

በህብረተሰብ ታሪክ ውስጥ የህብረተሰብ ግንባታንም ሆነ የኢኮኖሚ ዕድገትን ታሪክ ለተመለከተ ዕድገት የሚባለው ነገር ስልጣን ላይ ባለው ኃይልና ከሱ ጋር በጥቅም ከተቆላለፉ ኃይሎች ጋር የተያያዘ ነው። ለዚህም ነው ከጥንታዊቱ የግሪክ ስልጣኔ ጀምሮ ዕኩልነትና(Justice) ሚዛናዊነት ለአንድ ህብረተሰብ መረጋጋትና በሰላም መኖር አስፈላጊ ናቸው እየተባለ ትግል የተጀመረው። ምክንያቱም ስልጣን ላይ የሚወጡ ኃይሎች አብዛኛውን ጊዜ በፍልስፍናና በሳይንሳዊ ህግ ስለማይመሩ የተወሰነ የኢኮኖሚ ፖሊሲን በመከተልና የራሳቸውን ጥቅም ስለሚያስቀድሙ የግዴታ ለድህነት መፈልፈል በአንድ በኩል፣ በሌላ ወገን ደግሞ ጥቂቱ ሀብት በመቆጣጠር የጠቅላላውን ህዝብ የመኖርና ያለመኖር ዕድል እንዲወስን መንገዱን ያመቻቻሉ።  የኢኮኖሚ ታሪክን መጽሀፎች ላገላበጠ በዚህ ዙሪያ የተደረገውን ዕልክ አስጨራሽ ትግል መመልከት ይቻላል።

ወደ  ቲዎሪ ጥያቄ ስንመጣ ደግሞ፣ አንድ አገር ሀብት መፍጠር የምትችለው እንዴት ነው? በሚለው ዙሪያ የተለያዩ አስተሳሰቦች ይስፋፉ ነበር። በፊዚዮክራቶች፣ የመጀመሪያው የነፃ ገበያ ፍልስፍና አፍላቂዎች ወይም ላሴዝ-ፌር (Laissez faire) አሳቢዎች አመለካከት የአንድ አገር ሀብት ምንጭ እርሻ ነው የሚል ነው። ከገበሬው በስተቀር ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ምርታማ(Unproductive) ያልሆኑና፣ ከእርሻ የሚመጣው ትርፋማ ምርት(Surplus product) ለተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተከፋፍሎ የተቀረው እንደገና ለመዋዕለ-ነዋይ በመዋል በዚህ አማካይነት ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ይመጣል ይሉናል። በመርከንታሊስቶች ዕምነት ደግሞ የአንድ አገር ሀብት ዋናው ምንጭ ከውጭ ንግድ የሚመጣ ወርቅና የወርቅ ክምችት ሲሆን፣ ተፈጥሮና ምድርንም ጨምሮ የሰው ጉልበት የሀብት(Wealth) ማመንጫ ዘዴዎች ናቸው ይሉናል። የሰው ጉልበት ወይም ኃይል ወይም ስራ ከተፈጥሮ ውስጥ ቆፍሮ የሚያወጣውን ንጥረ-ነገር በኃይል አማካይነት ወደ ፍጆታ ጠቀሜታ ከለወጠውና፣ የተወሰነው ደግሞ ለመዋዕለ-ነዋይ ከዋለ በዚህ አማካይነት ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ይመጣል ይላሉ። በኋላ ብቅ ያሉት የመርከንታሊስት ኢኮኖሚስቶች ነገሩን በማስፋፋት፣ አንድ ህብረተሰብ በኢኮኖሚ ዕድገት አማካይነት እንዲተሳሰር ከተፈለገ የማኑፋክቸር አብዮት ማካሄድ እንደሚያስፈልግ ያረጋግጣሉ። ምክንያቱም ከእርሻ ይልቅ የማኑፋክቸር መስክ የሚስፋፋና የሚያድግ እንዲሁም የማባዛት ኃይል ስላለው ዕውነተኛ የስራ-ክፍፍልና የኢኮኖሚ ዕድገት በዚህ አማካይነት ብቻ ነው ሊፈጠር የሚችለው ብለው ይነግሩናል። በተግባርም የታየው ይህ ነው። የከተማዎች ግንባታ፣ የንግድና የዕደ-ጥበብ መስፋፋት፣ እንዲሁም የከበርቴው መደብ ማደግና ቀስ በቀስም ብሄራዊ ባህርይ እንዲወሰድ መደረጉ፣ አንድ አገር በመገናኛ መንገድ በመተሳሰር ሰፋ ያለ ገበያ መዳበር የቻለው በመርከንታሊስት የኢኮኖሚ ፍልስፍና ወይም ፖሊሲ አማካይነት ነው። ከዚህም ጊዜ ጀምሮ ነው የኢኮኖሚ ዕድገት መልክ እያየዘ መምጣት የቻለውና፣ ቀስ በቀስም ህብረተሰብአዊ ሀብት(National or Social Wealth) ሊፈጠር የቻለው።

ከቲዎሪ አልፈን ተግባራዊ የሆኑ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎችን  ስንመለከት፣ ከአስራሰባተኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ ተግባራዊ እየሆነ የመጣው የመርከንታሊስቶች የኢኮኖሚ ፖሊሲ ነው ለካፒታሊዝም ዕድገትና መስፋፋት መንገድ የቀደደው። በጊዜው ቢያንስ ማደግ ለሚፈልጉ ኃይሎች መንገዱ ክፍት ነበር። እንደ አገራችን ሁኔታ በጎሳ የተገደበና አፋኝ አልነበረም። እንዲያውም ንቁ የሚባሉ ኃይሎችን(Active forces) በተለያየ መንገድ መርዳትና፣ የውስጥን ገበያ ደግሞ ከውጭ በሚመጣ ዕቃ እንዳይጥለቀለቅ አስፈላጊ የጉምሩክ ፖሊሲ ተግባራዊ ማድረግ የፖሊሲውና የሀብት ክምችቱ አንዱ ዘዴ ነበር። ይህ ዐይነቱ በብዙዎቹ የምዕራብ አውሮፓ አገሮች ተግባራዊ የሆነ ፖሊሲ ነው ለካፒታሊዝም ዕድገት ዕምርታ በመስጠት ህበረተሰቡን ማስተሳሰር የተቻለውና ክልላዊና ሌሎች ገደቦችን በማስወገድ ብሄራዊ አንድነት እንዲፈጠር የተደረገው። ከዚህን ጊዜ ጀምሮ ነው ግለሰቦችም የመፍጠር ችሎታቸውን ማዳበር የቻሉትና፣ አገሮችም እንደ አገር ብቻ ሳይሆን፣ እንደ ህብረተሰብና ነፃነት እንዳላቸው ግንዛቤ የተገባበት። ከዚህን ጊዜ ጀምሮ ነው ብሄራዊ ነፃነት(National Sovereignty) የሚባለው እንደ መሰረተ-ሃሳብ በመወሰድ ማንኛውም አገር በሌላኛው አገር ጣልቃ መግባት እንደማይችል የተደረሰበትና፣ አገዛዞችም የራሳቸውን ነፃነት መጠበቅና መከላከል እንዳለባቸው ስምምነት የተደረሰበት። የብሄራዊ ኢኮኖሚ ቀስ በቀስ እያለ ከተገነባና ህብረተሰብአዊ መተሳሰርና የፈጠራ ስራዎች እየተጠናከሩና እየዳበሩ ሲመጡ  የእነ አዳም ስሚዙ የነፃ ገበያና ንግድ ፖሊሲ መስፋፋት  ጀመሩ።  የራስን ጥቅም ማሳደድ የሚለው ሃሳብ በመስፋፋት፣ ይህ ዋነኛው የሰው ልጅ ውስጣዊ ባህርይ ወይም አብሮት የተፈጠረ ነው በማለት ኢምፔሪሲስታዊ አመለካከት ያላቸው ፈላስፋዎች ይህንን ውስን አመለካከት በማስፋፋት ዋናው የኢኮኖሚ ዕድገት አንቀሳቃሽ ኃይል አድርገው መስበክ ጀመሩ።  ስለሆነም የነፃ ገበያና የነፃ ንግድ በሃሳብና በርዕዮተ-ዓለም ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈለቁትና መዳበር የጀመሩት በእንግሊዝ አገር ነው።  በአዲሱ የዩሊታሪያን አስተሳሰብ መሰረት ህብረተሰብአዊ ሀብትን ለመፍጠር ወይም አንድን ምርት ለማምረት ሶስት ነገሮች መጣመር አለባቸው። ይኸውም፣ የሰው ኃይል፣ ካፒታልና መሬት ናቸው። በተጨማሪም የረቀቀው የሰው እጅ (Invisible Hand) ለኢኮኖሚ ዕድገት ወሳኝ እንደሆነ አዳም ስሚዝ ያትታል። ይህን እንዳለ በመወሰድ የትምህርትቤት ኢኮኖሚክስ በዚህ መልክ ረቀቀ። ሁላችንም በዚህ መልክ ሰለጠን።

ወደ ማርክስ ቲዎሪ ስንመጣ ደግሞ፣ የመርከንታሊሲቶችን ሃሳብ በመቀበልና፣ የአዳሚ ስሚዝንም የቫልዩ ቲዎሪ በማስፋፋት፣ የስራ ኃይል ወይም የሰው ጉልበት ዋናው የዋጋና፣ ተከታታይ የካፒታሊዝም ዕድገት መሰረት እንደሆነ ያብራራል። ከዚህ ጋር በማያያዝ፣ የካፒታሊዝምን አፀናነስና ዕድገት፣ ደረጃ በደረጃ ካተተ በኋላ ውድድር(Competition) የካፒታሊዝም ዋናው የዕድገት አንቀሳቃሽ ኃይል መሆኑን ያመለክታል። በዚህም አማካይነት የምርት ኃይሎች ወይም የማምረቻ መሳሪያዎች በየጊዜው እየተሻሻሉ በመምጣት ለካፒታሊዝም ዕድገት ምጥቀትና መስፋፋት ይሰጡታል። የደሞዝ ዕድገትና፣ የኑሮ መሻሻል፣ እንዲሁም የፍጆታ ማምረቻ ዋጋ መቀነስ ከማምረት ወይም ከማሺኖች ምርታማነት ጋር የተያያዙ መሆናቸው መገንዘቡ ከባድ አይሆንም ። በተጨማሪም ፋይናንስ ካፒታል ወይም ብድር ለካፒታሊዝም ዕድገት አንቀሳቃሽ ኃይል በመሆን፣ ካፒታሊዝም ከዝቅተኛ የምርት ክንዋኔ ወደ ከፍተኛና ወደ ተወሳሰበ ደረጃ መድረስ እንደቻለ እንመለከታለን። የፊናንስ ካፒታል በምርት ክንዋኔና በአዳዲስ መዋዕለ-ነዋይ ላይ ብቻ ሳይወሰን፣ ተጠቃሚውንም በማካተት የካፒታሊዝምን ዕድገት ማፋጠን እንደቻለ ግልጽ ነው።

ለመሆኑ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ካለሳይንስና ካለቴክኖሎጂ ተግባራዊ ሊሆን ይችላል ወይ? አብዛኛውን ጊዜ ስለሶስተኛው ዓለም የኢኮኖሚ ዕድገት ችግር የሚጽፉ ኤክስፐርቶች የሚዘነጉት ነገር ሳይንስና ቲኮኖሎጂ በኢኮኖሚ ዕድገት ውስ|ጥ ያላቸውን ሚና ከቁጥር ውስጥ ባለማስገባት ነው። በተለይም የኒዎ-ክላሲካል ኢኮኖሚስቶች ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ ቦታ አይሰጡትም። ለማንኛውም ብዙ ሳናወጣና ሳናወርድ፣ ወይም በትንሹ ስናሰብ የሰው ልጅ ዕድገት ከቲክኖሎጂ ጋር የተያያዘ ነው።  የተሻሉ የምርት መሳሪያዎች መጠቀም ሲጀምር የበለጠና በብዛት ማምረት ይችላል። ስራውንም ያቃልላል። በዚህም ምክንያት ሳይንስና ቴክኖሎጂ ተግባራዊ መሆን ከጀመሩ ከ18ኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ የምርት መሳሪያዎች መብዛት ብቻ ሳይሆን በጥራትም እየመጠቁም መምጣት ችለዋል። በዚያውም መጠንም የዛሬ ሁለት መቶ ዐመት መመረት የማይችሉ ምርቶች፣ የተለያዩ የሰብልና የፍራፍሬና እንዲሁም የቅጠላ ቅጠል ዐይነቶች ተስፋፋተው ይገኛሉ። ይህም የሚያረጋግጠው በቴክኖሎጂዎች መስፋፋት የሰው ልጅም የማሰብና የማምረት ኃይል ሊያድግ እንደቻለ ነው። ከዚህ ስንነሳ ኋላ-ቀርነትና የረሃብን ምክንያት መገንዘቡ ቀላይ አይደለም። 1ኛ) ዕውነትኛ ዕውቀት ባልተስፋፋበት አገር ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሊፈጠሩና ህብረተሰብአዊ ባህርይ ሊወስዱ አይችሉም። 2ኛ) ሰፊው ህዝብ ካልተማረ ራሱ ምርትን በተለያየ ዐይነት ማምረት ብቻ ሳይሆን አንድንም ምርት በብዛት ማምረት ያቅተዋል። ኢምፔሪካል ጥናቶች እንደሚያረጋግጡት የሰው ልጅ ዕድገት በቁጥር መቀነስና ረሃብና ድህነት መወገድ፣ ከሰፊው ህዝብ የመማርና የማሰብ ኃይል ጋር የተያያዙ እንደሆነ ነው። ስለሆነም ሰፋ ያለና ዕውነተኛ ዕውቀት ዋናው የስልጣኔ ቁልፎች ናቸው። በሁሉም መልክ የሚገለጽ ዕውቀትና በአንድ ክልል ብቻ ያልተገደበ ዕውቀት ነው አንድን ህዝብ ሀብት ፈጣሪ የሚያደርገውና ከድህነትና ከረሃብም ሊያላቅቀው የሚችለው።

ወደ ሌሎች ቲዎሪዎች ስንመጣ፣ የአንድ አገር ሀብት(Wealth) የሚወሰነው ወይም የሚመነጨው በሶስት ነገሮች አማካይነት ነው። 1ኛ) ኃይል(Energy)፣ 2ኛ) ቴክኖሎጂና  3ኛ) ፈጠራ፣ እነዚህ አንድ ላይ ሲጋጠሙ ወይም ሲጣመሩ አንድ አገር ተከታታይነት ያለው ሀብት መፍጠር ይችላል። በተለይም የዚህ ቲዎሪ አራማጅ የስኮቲሹ ተወላጅና በኬሚስትሪ የኖቭል ዋጋ ተሸላሚ የነበሩት ፕሮፌሰር ፍሪድሪሽ ሶዲ ናቸው። ፕሮፌሰር ሶዲ ስለ ኃይል(Energy) በኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ያለውን ሚና በማስመር፣ ኃይልን መቆጠብና ኃይልን በመለወጥ መሀከል ያለውን ዲያሌክታዊ ግኑኝነት በማያያዝ፣ የአንድ አገር ዕድገት ሊወሰን የሚችለው በኃይል አማካይነት ብቻ እንደሆነ በግሩም መልክ ያብራራሉ። በመሆኑም ፀሀይ የኦርጋኒክና ኦርጋኒክ ያልሆኑ ነገሮች አንቀሳቃሽ ኃይልና ለዋጭ በመሆን የሰውን ልጅ ዕድገትና የተፈጥሮን ምንነት ወሳኝ ነች። በፀሀይ ኃይል ወይም ሙቀት አማካይነት ነው ፍሬ ሊሰጡ የሚችሉና ፍሬ ሊያበቅሉ የማይችሉ ዛፎች ሊያድጉና ሊያብቡ፣ እንዲሁም ፍሬ ሊሰጡ የሚችሉት።  በምድር ውስጥ የተከማቹት እንደዲንጋይ ከሰልና ዘይት የመሳሰሉት የጥሬ ሀብቶችና ሊሎችም ንጥረ-ነገሮች የብዙ መቶ ዐመታት የፀሀይ ክምችት ውጤቶች ናቸው።  ከዚህ በመነሳት የአንድ አገር ዋናው እንቅፋት ይህንን የተፈጠሮ ህግ አለመረዳት ሲሆን፣ የጭንቅላት ወይም የአዕምሮ ድህነት ያለባቸው አገሮች ፍዳቸውን የሚያዩት የተሳሳሰተ የኢኮኖሚ ፖሊሲ በመከተላቸው  እንደሆነ ያስተምሩናል። ምክንያቱም በተፈጥሮ ውስጥ ያሉትን ፀሀይንም ሆነ ውሃ፣ እንዲሁም ልዩ ልዩ ንጥረ-ነገሮችን መጠቀም ያለመቻል አንድን አገር ወደ ዘለዓለማዊ ድህነት እንደሚያመራው  ነው። ፕሮፊሰር እሪክ ራይነትም በሌላ መልክ ለአንድ አገር ዕድገት ጥሬ-ሀብት ተትረፍርፎ መገኘቱ ሳይሆን፣ የሰው ልጅ የማሰብ ኃይልና፣ ለስራ ወይም ለስልጣኔ ያለው ፍላጎት ወሳኝ ሚናን እንደሚጫወቱ  ነው የሚያስተምሩን።

ከላይ አጠር ብሎ ከተዘረዘረው አስተሳሰብ ስንነሳ በመጀመሪያ ደረጃ ስለ ኢኮኖሚ ዕድገት በምናወራበት ጊዜ ግልጽ ማድረግ ያለብን ነገሮች አሉ ማለት ነው። በደፈናው የኢኮኖሚ ዕድገት ብሎ ነገር የለም። ከዚህ ጋር መያያዝ ያለበት ጉዳይ፣ ኢኮኖሚ ዕድገት ለምንና ለማን? ብለን መጠየቅ አለብን። ኢኮኖሚ ዕድገት ለዕድገት ሲባል፣ ወይስ ኢኮኖሚ ዕድገት የሰውን የማቴሪያል ፍላጎት አሟልቶ በአስተሳሰብም ደረጃ እንዲያጎለምሰውና ፈጣሪም እንዲያደርገው? ይህንን በሚመለከት የትምህርትቤት ኢኮኖሚክስ የሚለው ወይም የሚሰጠን መልስ የለም። እንዲያው በደፈናው ሁሉም ነገር በገበያ አማካይነት ብቻ ሊወሰን እንደሚችል ለማረጋገጥ ይሞክራል። ለምሳሌ በትምህርት ቤት ኢኮኖሚክስ ማንኛውም ህብረተሰብ በመጀመሪያ ደረጃ፣ ምግብ፣ ንፁህ ውሃና መጠለያ ማሟላት እንዳለበትና፣ ከዚያ በመነሳት አንድን አገር መገንባት እንዳለበት አያሰተምርም። በሁለተኛ ደረጃ፣ በትምህርት ቤት ኢኮኖሚክስ፣ ከተማ ምን እንደሆነ አይታወቀም። የሚታወቀው ገበያ ብቻ ነው። ማለትም ገበያ ካለ ቦታና ጊዜ(Space and Time) የሚካሄድ ነው። በሶስተኛ ደረጃ፣ የትምህርት ቤት ኢኮኖሚክስ ህብረተሰብ ማለት ምን ማለት ነው? እንዴትስ ነው የሚተሳሰረው? እንዴትስ ነው የስራ-ክፍፍል የሚቀናጀውና የሚዳብረው?  የሚለውን መሰረታዊ ጥያቄ አያቀርብም፤ አይመልስም። ከዚህ ስንነሳ የኢኮኖሚ ዕድገት በራሱ ብቻ እንደሚጓዝ አድርገን መመልከቱ ከፍተኛ ስህተት ነው። ፕሌቶን እንደሚያስተምረን፣ አንዱ የወረውረውን ማስተጋባት ሳይሆን፣ መመርምርና መፈተን ያስፈልጋል። ከዚያ በመነሳት የራስን ውሳኔ መስጠት ሳይንሳዊው መንገድ ነው።

እስቲ ከቲዎሪ ተላቀን ወደ ተግባራዊ ነው ወደምንለው ነገር እንመጣ። ባለፉት 36 ዐመታት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እያደገ የመጣ ነው ወይ?  ይህንን ጥያቄ መመለስ የምንችለው፣ ከየትኛው ሁኔታ በመነሳት ነው? የምንገመግመው ወይም የምንለካው? የሚለውን ጥያቄ ካስቀመጥንና ለመመለስ የቻልን እንደሆን ብቻ ነው። ሌሎች እጅግ አብስትራክት የሆኑ የጂዲፕ አሰላልና የምርት ጭማሮና ከውጭ የመጣን ልዩ ልዩ ወደ ምርት ውስጥ የሚገቡ በግማሽ የተፈበረኩና የጥሬ-ሀብት ጉዳዮችን ትተን እንዲያው በደፈናው ስንመለከት ከተወሰነ የህብረተሰብ ክፍል አንጻር፣ ምናልባት 1% ለሚጠጋው የህብረተሰብ ክፍል „የኢኮኖሚ ዕድገት“ መጥቶለታል ማለት ይቻላል። ይህ ዕድገት በትላልቅ ህንጻዎች፣ በሆቴል ቤቶች ስራና ጋጋታ፣ በመንገድ ስራ፣ የስኳርና የቢራ ፋብሪካ የሚገለጽ ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ ከመንግስት ጋር በሺህ ድሮች የተቆላለፉ አየር በአየር ንግድ ውስጥ በመሰማራት፣ የውስጥን ጥሬ-ሀብት በመሸጥ የገቢያቸው መጠን በፍጥነት የተተኮሰ የህብረተሰብ ክፍሎች አሉ። ከዚህ ጋር በተያያዘ የነዚህ ህብረተሰብ ክፍሎች የፍጆታ አጠቃቀም በከፍተኛ ደረጃ አድጓል። ከውጭ የሚመጣው የቅንጦት ዕቃ የማህበራዊ ስታተሳቸውን ከፍ አድርጎታል። ይህንና ከዚህ ጋር የተቆላለፈውን ሀብት ጨራሽ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ነው ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ተብሎ የሚወደስልን። ይህንን ዐይነቱን የኢኮኖሚ ዕድገት በመርከንታሊስቶችም ሆነ በፕሮፌሰር ፍሪድርሽ ሶዲና ፕሮፌሰር ኢሪክ ራይነርት የኢኮኖሚ ቲዎሪ መነፅር ስንመረመረው አዲስ ሀብት የፈጠረ አይደለም። ቲክኖሎጂያዊ ምጥቀትን ያመጣ አይደለም። የውስጥ ገበያ እንዲስፋፋና እንዲዳብር ያደረገና የሚያደርግም አይደለም። ለስራ ፈላጊው ሰፊ ህዝብ የስራ መስክ የከፈተና የሚከፍት አይደለም። የባሰ ጥገኝነትንና፣ ኢኮኖሚያዊ መዝረክረክን ያስከተለና የሚያስከትል ነው። ሀብትን የሚያባክን ነው። በተፈጥሮና በሰው ልጅ ላይ ዘመቻ የከፈተ „የኢኮኖሚ ዕድገት“ ነው። ይህንን ዐይነቱን ዕድገት ጥፋት እንለዋለን። የተወሰነውን የህብረተሰብ ክፍል በማባለግ፣ በዚያው መጠንም ሰፊውን ህዝብ በማድኸየት አቅመ-ቢስ ያደረገ ነው። እንደሚታወቀው አንድ አገር እንደ አገር የምትከበረው ከሁሉም አንፃር ማደግ ስትችል ነው። ግርማ ሞገስ ያላቸው ከተማዎችና የመኖሪያ ቤቶች ሲሰሩና ለሰፊው ህዝብ ሲዳረሱ ነው። ህዝቡ የመፍጠር ችሎታው ሲዳብር ነው። እንደ አንድ ዜጋ ሲታይና ጠንካራ ህብረተሰብ ለመመስረት ሲችል በእርግጥም ኢኮኖሚያዊ ዕድገት አለ ማለት ይቻላል። ልዩ ልዩ መናፈሻ ቦታዎችና ሲዘጋጁለትና የኬነትና ቤተ-መጻህፍቶች  ሲቋቋሙለት ኢኮኖሚው ማደጉ ብቻ ሳይሆን፣ ህዝቡም አዲስ አስተሳሰብ ማዳበር ይችላል። የሰው ልጅ በዳቦ ብቻ አይኖርም፤ ፍቅርና ልዩ ልዩ መንፈሱን የሚያረኩ ነገሮችም ያስፈልጉታል። ከማያስፈልጉ ነገሮች እንዲቆጠብና ውድ ወንድሙን ወይም እህቱን እንደሰው እንዲያይ ከተፈለገ በሳይንስ የተጠና ባህልም መዳበር ከኢኮኖሚው ዕድገት ጋር መያያዝ ያለበት ጉዳይ ነው። 27 ዓመት ያህል በወያኔ የአገዛዝ ዘመን በኒዎ-ሊበራል ኤክስፐርቶችና አማካሪዎቹ ተግባራዊ የሆነው የኢኮኖሚ ፖሊሲ በመሰረቱ ማጅራት መቺዎችንና ማፊያ መሳዮችን የፈለፈለና ድህነትን ያስፋፋ ነው። የአቢይ አህመድ አገዛዝም ስልጣንን ከጨበጠ ጀምሮ የሚከተለው የኢኮኖሚ ፖሊሲ በእነ አይኤምኤፍና በሌሎች የኒዎ ሊበራል ኢኮኖሚስቶች ረቆ የመጣውን ቁንጽል የሆነ ኢ-ሳይንሳዊ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ በማድረግ ነው። አቢይ አህመድ ስልጣን ከጨበጠ ጀምሮ አገርን ከማፈራረስና ሀብት ከመዝረፍ ውጭ ይህ ነው የሚባል ድህነትን ለአንዴም ለመጨረሻ ጊዜ የሚቀርፍ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተደገፈ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ ሲያደርግ አይታይም። ለሰፊው ስራ ፈላጊ ወጣትም የሙያ ማሰልጠኛ ትምህርትቤቶች አለመስፋፋታቸው ብቻ ሳይሆን ሰፋ ያለ የስራ መስክም ለመክፍት አልቻለም። ከዚህም በላይ የኢትዮጵያ ብር ከዶላር ጋር ሲነፃፀር በተደጋጋሚ እንዲቀንስ በመደረጉ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ይታያል። የሰፊው ህዝብ ገቢም እያደገ ለመምጣት ባለመቻሉ በገበያ ላይ የሚቀርበውን ምርት ገዝቶ ለመጠቀም የሚችለው በጣም ጥቂቱ የህብረተሰብ ክፍል ነው። በሌላ ወገን ደግሞ በከፍተኛ ደረጃ ለሰፊው ህዝብ የሚቀርቡ እንደ ጤፍ፣ በርበሬ፣ ስጋ፣ ቅማቅመሞች፣ አትክልቶችና ሌሎች ሰብሎችን የሚጋሩ ትላልቅ ሁቴልቤቶች በመስፋፋታቸው ለዋጋው ንረት ከፍተኛ አስተዋፅዖ ለማበርከት ችለዋል። ሆቴልቤቶችም የሚሰሩትና የሚስፋፉት ለቱሪስቶች ተብለው ስለሆነ ምናልባት በዚህ አማካይነት የውጭ ምንዛሪን ለማሳደግ ስለሆነ ከአጠቃላይ የኢኮኖሚ ዕድገት አንፃር ምንም ዐይነት አስተዋፅዖ የላቸውም። የአንድ አገር ኢኮኖሚ ዕድገትም ሊወሰን የሚችለው ሆቴልቤቶችን በመስራትና በማንጋጋት ሳይሆን በማኑፋክቸሪንግ፣ በሳይንስና በቴክኖሎጂ አማካይነት ብቻ ነው። ስለሆነም ሳይንሰ-አልባ የሆነና በቴክኖሎጂና በማኑፋክቸሪንግ ላይ ያልተመሰረተ ኢኮኖሚያው እንቅስቃሴ ባህልን ከማውደም በስተቀር ለአገራችን የኢኮኖሚ ዕድገት ምንም ዐይነት ትርጉም ሊኖረው በፍጹም አይችልም። ከዚህም በላይ በአሁኑ ውቅት በህዝባችን ላይ፣ በተለይም በአማራው ላይ የተከፈተው ጦርነት ለኢኮኖሚ እንቅስቃሴ፣ ለፈጠራ ስራና ለአጠቃላይ ዕድገት ከፍተኛ እንቅፋት ለመሆን በቅቷል። በጭሩ ስለአም ባልሰፈነበት፣ አንድ አገዛዝ ወደ ተራ ወንበዴነት በተለወጠበትና አገዛዙ ከህዝብ ጋር እልክ በተጋባበት አገር ውስጥና ስልጣን ላይ ያለው ኤሊት ወደ ምዝበራ በተመሰራበት ሁኔታ ውስጥ ስለ ኢኮኖሚ ዕድገት ማውራት በፍጹም አይቻልም።

ከዚህ በመነሳት እኛ ኢትዮጵያውያን ምሁር ሆን አልሆን ለምን ዐይነት ሀብረተሰብና ለምን ዐይነት አኮኖሚ ነው? የምንታገለው ብለን መከራከር አለብን። እኛን የሚያሳሰብን የዚህኛው ወይም የዚያኛው ብሄረ-ሰብ ነፃ መውጣትና አለመውጣት አይደለም። እኛን የሚያሳስበን ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚለው የአርሞው፣ የአማራው፣ የትግሬው፣ የወላይታው፣ የጉራጌው… ወዘተ የኑሮ ሁኔታ ነው። እኛን የሚያሳስበንና አንጀታችንን የሚያቃጥለን ሺህ በሺህ ለአረብ አገሮች በመንግስት የሚሸጡት ልጆቻችንና እህቶቻችን ህይወት ነው። የሚያሳስብን በመንገድ ላይ የሚያድረው፣ ከቆሻሻ እየለቀመ የሚበላው፣ የዕፅ ሱሰኛ እንዲሆን የተገደደው ልጃችን ህይወት ነው። እኛን የሚያስጨንቀን የህዝባችን ኑሮ መጨለሙ ነው።  እኛን የሚያሳስበን የአገራችን ውድመትና መቸብቸብ ነው። ህዝቡ እንደ አንድ ዜጋ እንዳይተሳሰር መደረጉ ነው። እኛን የሚያሳስበን ህዝባችን ዕውነተኛ ነፃነቱን እንዳይጎናፀፍና ዕድሉን ወሳኝ እንዳይሆን መደረጉ ነው። በዚህ ዐይነቱ ውጥቅንጡ የወጣ ስርዓት ግለሰብአዊ መብቶች መጣሳቸው ነው የሚያስጨንቀን። ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ መሪ የሌለው መደረጉ ነው ሌት ከቀን እንቅልፍ የነሳን። የሚያሳስበን ያረጀ የብሄረ-ሰብ  ጥያቄ ሳይሆን የመቶ ሃያ ሚሊዮኑ ህዝባችን ዕድል ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ ከ50ና ከ100 ዐመት በኋላ ኢትዮጵያችን ምን ትመስላለች የሚለው? ነው የሚያሳስበን። የዚኸኛው ወይም የዚያኛው ፓርቲ ለስልጣን መውጣትና መራወጥ አይደለም አንጀታችንን የሚያቃጥለን። ባጭሩ የአገርና የህዝብ ደህንነት፣ ከሁሉም አቅጣጫ ዕድገት አለመኖር፣ ዕድገት እንዳይኖር ከውጭ የተሸረበብን ሴራና በጣም የደከመው ምሁራዊ እንቅስቃሴ ነው እንቅልፍና ዕረፍት የነሳን። በዚህ ላይ ደግሞ አገርን ለማስተዳደርና መመሪያ ለመስጠት የሚችል የሰለጠነ መንግስትና ተቋም አለመኖሩ ነው።

የዛሬው ሁኔታ በዚህ መልክ አፍጦ አግጦ ባለበት ወቅት አንዳንድ ምሁራን ስለተከታታይነት(Sustainable Economic Growth) ስላለው የኢኮኖሚ ዕድገት ይጽፋሉ። በየጊዜው ይህንን በማስመር የሚጽፉት ምሁራን፣ 1ኛ) ተከታታይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት ምን እንደሆነ ለተራው ሰው ሲያስረዱ አይታዩም። 2ኛ) ባለፉት 36 ዐመታት በአገራችን ምድር ተግባራዊ የሆነውን የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ትችታዊ በሆነ መልክ በመመርመርና በመጻፍ አላስተማሩንም። 3ኛ) ዛሬ አገራችን ምድር አፍጦ አግጦ ለሚታየው ድህነትና ረሃብ ዋናው ምክንያት ምን እንደሆነ አልነገሩንም። እንዲያው በደፈናው ብቻ ተከታታይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት ያስፈልጋል እያሉ ነው የሚነግሩን።  ይህንን ካላብራሩልን ደግሞ የዕውር ድንብራችን ነው የምንራመደው ማለት ነው። በሌላ ወገን ደግሞ ከዚህ ዐይነቱ አባባል የምንረዳው ኢኮኖሚው አድጓል፣ ይሁንና ግን ተከታታይነት የለውም የሚል ድምደማ ነው። በመሰረቱ  የተለያየ የኢኮኖሚ ዕድገት ሊኖር አይችልም።  በተለያዩ አገሮች የተለያዩ የህብረተሰብ አወቃቀሮችና አገዛዞች ቢኖሩም፣ የኢኮኖሚ ዕድገት ዋናው አንቀሳቃሽ ሃይል ፈጠራ፣ ከዚህ የሚፈልቁት ሳይንስና ቴክኖሎጂዎች ናቸው። ከዚህም ባሻገር ተከታታይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት ጉዳይ የቁጥር ብቻ ሳይሆን የዐይነትም ጭምር ነው። እነዚህ ጉዳዮች ደግሞ የግዴታ ከሰው ልጅ የኑሮ መሻሻል ጋር በቀጥታ የተያያዙ ናቸው። ስለተከታታይ የኢኮኖሚ ዕድገት በምናወራበት ጊዜ፣ ስለሪሶርስ አጠቃቀም ጉዳይ፣  ስለ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች መፈጠር ጉዳይ፣ ስለ አካባቢ ደህንነት ጉዳይ፣ ስለ ከተማዎችና መንደሮች በደንብ በዕቅድ መታቀድና መገንባት ጉዳይ፣ ስለ ፍሳሽና ስለቆሻሻ መጣያ ወይም ሪሳይክል ማድረጊያ ጉዳዮች… ወዘተ. ማተት ያስፈልጋል። በተለይም የተፈጥሮን ሀብትና ጫካንም በስነስርዓት መንከባከቡና መጠበቁ የተከታታይ ዕድገት ዋናው ዕምብርት ነው። ንጹህ አየር መተንፈስና ጤንነታችንም ሊጠበቅ የሚችለው የአካባቢያችን ሁኔታ ከሳይንስ አንፃር እየተጠና እንክብካቤ ሲደረግለት ብቻ ነው። በተጨማሪም የወንዞችንና የባህሮችን ህይወት መንከባከቡ እጅግ አስፈላጊ ነው። እንደሚባለው አብዛኛዎቹ የኢትዮጵያ ወንዞች የተመረዙና እየደረቁ የሄዱና ህይወትም የሌላቸው ናቸው። ለዚህ ሁሉ በብዙ የስልጣኔ ተመራማሪዎችና የኳንተም ሳይንስ ምሁራን የተደረሰበት ድምዳሜ ለተከታታይ ዕድገት ዋናው ወሳኝ ኃይል ንቃተ-ህሊና(Quantum Consciousness) ነው።  በሌላ አነጋገር ዝቅተኛ ንቃተ-ህሊና በሰፈነበት አገር ስለ ተራ ዕድገትም ሆነ ስለ ተከታታይ የኢኮኖሚ ዕድገት ማውራት  በፍጹም አይቻልም።

ስለሆነም ተከታታይነት ስላለው የኢኮኖሚ ዕድገት በምናውራበት ጊዜ፣ 1ኛ) የመንግስትን መኪናና የሚከተለውን ፖለቲካና የኢኮኖሚ ፖሊሲ መመርመር ያስፈልጋል። ይህ እንቅፋት ሆኖ ከታየ ደግሞ የግዴታ ይህንን መለወጥ ያስፈልጋል።  አንድ አገዛዝ እንደፈለገው በራሱ „ሎጂክ“ እየተመራ የአገርን ሀብት ሊመዘብርና ህዝብን ሊያደኸይ አይችልም። መብትም የለውም። 2ኛ) ተከታታይነት ስለሚኖረው የኢኮኖሚ ዕድገት ሲነሳ ወይም ሲጻፍ የግዴታ ስለነፃነትና ስለዲሞክራሲ አስፈላጊነት ማንሳትና መጻፍ ያስፈልጋል። 3ኛ) ተከታታይነት የሚኖረው የኢኮኖሚ ዕድገት የወጭ ኃይሎችን ግፊታዊ ጣልቃ-ገብነት ይቃወመል። በሌላ አነጋገር በዓለም አቀፍ ኮሙኒቲው ግፊት ተግባራዊ የሚሆን ፖሊሲ አንድን አገር የግዴታ መቀመቅ ውስጥ እንደሚከታት ማስተማር ያስፈልጋል።  ይህም ማለት በአገራችን ምድር ተከታታይነት የሚኖረው የኢኮኖሚ ዕድገት ተግባራዊ ሊሆን የሚችለውና ህዝባችንም የዕውነተኛ ስልጣኔ ባለቤት የሚሆነው ከዓለም አቀፍ ኮሚኒቲው መዳፍ ስር ሲላቀቅና በከፍተኛ ምሁራዊ ኃይል በግሎባል ካፒታሊዝም አማካይነት በሁሉም አቅጣጫ የሚመጣብንን ግፊት መቋቋም የቻልን እንደሆን ብቻ ነው። ለዚህ ደግሞ ስልጣን ላይ የሚወጡ ኃይሎች ከፍተኛ ዕውቀትና የአገር ወዳድ ስሜትነት እንዲኖራቸው ያስፈልጋል። በአገራችንም ምድር በምንም ዐይነት የውጭ ኃይሎች ተገዢና ታዛዥ የሆነ ኃይል ስልጣን ላይ መውጣት የለበትም። ይህ ሲሆን ብቻና በአሁኑ ወቅት በአቢይ አህመድ የሚመራው የኦሮሞ ኤሌት ነኝ ባይ የሆነው የወንበዴዎች ቡድን ከስልጣን ላይ ሲወገድ ብቻና፣ በአገር ወዳድና በሰለጠነ ኃይል ሲተካ ቀስ በቀስ ሰላም፣ ዲሞክራሲ፣ ነፃነትና ሁለ-ገብ የሆነ የኢኮኖሚ ዕድገት ተግባራዊ ሊሆኑ ይችላሉ የሚል የፀና ዕምነት አለኝ።  መልካም ንባብ !!

 

 

 

[email protected]

www.fekadubekele.com

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

ከነፃነት ዘገዬ የአራት ኪሎው ኦነግ ሸኔ ከቁጥር ጋር እንደተጣላ ዕድሜውን አገባደደ፡፡ ኦነግ/ኦህዲድ ዛሬም ሆነ ዱሮ፣ በቤተ መንግሥትም ይሁን በጫካ ቁጥር ላይ ያለው አቋም ምን ጊዜም ያስደንቀኛል፡፡ ደግሞም እየባሰባቸው እንጂ ሲቀንሱ አይታዩም፡፡ ጥቂት

80 ቢሊዮን ብር ስንት ብር ነው?

በላይነህ አባተ ([email protected]) መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ምዕራባውያን የኢትዮጵያን ልጆች እያታለሉና እየደለሉ ከእምነታቸው ለመንጠቅ ሲቃጡ በ1951 ዓ ም ባሳተሙት ‘መድሎተ አሚን ወይም የሃማኖት ሚዛን ጥልቅ መጽሐፍ ሽፋን ላይ ሕዝብ ልቡናውን፣ ዓይኑን፣ ጀሮውንና

ሰው ሆይ!

“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።”  መዝሙረ ዳዊት 39:1 ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 15 January 2025 መግቢያ የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን

ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

Go toTop