የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በቅርቡ በተቆጣጠረው የራያ አካባቢ መስረታዊ የህዝብ አገልግሎቶችን ለማስጀመር ከፌደራል መንግስቱ ጋር ውይይት እያደረገ መሆኑንና በመግባባት እየሰራ እንደሆነ ለዋዜማ ተናግሯል።
በቅርቡ በሕወሓት ታጣቂዎች እና በአካባቢው ሚሊሻዎች መካከል የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ፣ የማንነትና የወሰን ጥያቄ በሚነሳባቸው የራያ አካባቢዎች ኹሉም የአገልግሎት መስጫ ተቋማት ዝግ መሆናቸውን፤ እንዲሁም መደበኛ እንቅስቃሴዎች በአብዛኛው መስተጓጎላቸውን ዋዜማ በሥፍራው ካሉ ነዋሪዎች አረጋግጣለች።
በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የደቡብ ትግራይ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ሃፍቱ ኪሮስ፣ በራያ አካባቢዎች መሰረታዊ የሚባሉ ግልጋሎቶችን ማለትም ትምህርት ቤቶችን፣ ባንኮችን፣ እንዲሁም የጤና ተቋማትን እና የመንግሥት መስሪያ ቤቶችን ወደ ሥራ ለማስገባት ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ውይይት ጀምረናል ሲሉ ለዋዜማ ተናግረዋል።
አገልግሎቶችን ለማስጀመር የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በተናጠል እንቅስቃሴ ጀምሯል ያሉት አስተዳዳሪው፣ ለአብነትም መድኀኒቶችን ወደተለያዩ አካባቢዎች ማሰራጨት እንደጀመረ ጠቅሰዋል።
አስተዳዳሪው፣ ከጦርነቱ ቀደም ብሎ የነበሩ የመንግሥት ሰራተኞች ወደ ሥራ እንዲመለሱ እያደረጉ መሆኑን ጠቅሰው፣ የአካባቢውን የህዝብ ስብጥር ለመቀየር እና ለፖለቲካ ዓላማ ከተለያዩ የአማራ ክልል አካባቢዎች በመንግሥት ሠራተኛነት ስም የተመደቡ ከ4 ሺሕ በላይ ሰዎች ሲቀሩ የቀድሞ ሠራተኛ አገልግሎት እንዲጀምር እያደረግን ነው ብለዋል።
አስተዳዳሪው ጦርነቱን ተጠቅመው “ሕገ-ወጥ አስተዳደር” መስርተው ነበር ያሏቸው እና አሁን ፈርሰዋል የተባሉት ኃይሎች፣ የአካባቢውን የመማሪያ መጽሐፍት እንዲሁም ካርታ ቀይረው ነበር ሲሉ ወቅሰዋል።
በፌደራሉ የትምህርት ሥርዓት መሰረት ትምህርት ቤቶችን ለማስጀመር ጥረት እየተደረገ እንደሆነ ሃፍቱ ኪሮስ ተናግረዋል።
በአካባቢው ሁኔታ ላይ ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ጥሩ ተስፋ የሚሰጥ መተጋገዝ መኖሩን የገለጹት አስተዳዳሪው፣ አሁን ላይ በአካባቢው ያሉት የመከላከያ እና የፌደራል ፖሊስ ኃይሎች ከእኛ ጋር በቅርበት ይሰራሉ፤ በቀጣይም እየተጋገዝን የምንሰራበትን ሁኔታ እየፈጠርን ነው ብለዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ(ኦቻ) ከቀናት በፊት ባወጣው መግለጫ ከኮረም፣ ዛታና ኦፍላ ወረዳዎች እንዲሁም ከራያ አላማጣ፣ ባላ እና አላማጣ ከተሞች በቅርቡ በሕወሓት ኃይሎችና በአካባቢው ሚሊሻዎች መካከል በተፈጠረው ግጭት ሳቢያ የተፈናቀሉ 36 ሺሕ የሚደርሱ ዜጎች በሰቆጣ እና ቆቦ ከተሞች እንደሚገኙ አስታውቆ ነበር። ሆኖም አስተዳዳሪው ኦቻ ያወጣው መግለጫ መሬት ላይ አይገኝም፤ “የተፈናቀለ ሰው የለም” በማለት መግለጫውን አጣጥለውታል።
ይልቁንም አሁን በፈረሰው መዋቅር ውስጥ የነበሩ አመራሮች እና ከሌሎች አካባቢዎች በመንግሥት ሰራተኛ ስም መጥተው የሰፈሩ ሰዎች ተንቀሳቅሰው ሊሆን እንደሚችል ግን ግምታቸውን አስቀምጠዋል።
በደቡብ ትግራይ ዞን ከእነዚህ አካባቢዎች ተፈናቅለው በመኾኒ እና በማይጨው መጠለያ ጣቢያዎች የነበሩ ከ41 ሺሕ በላይ ሰዎች ነበሩ ያሉት ሃፍቱ፣ ወቅቱ የዘር ወቅት በመሆኑ የፌደራል የጸጥታ ሃይሎች ይቆጣጠሩታል፣ በቅርበትም የእኛ ሚሊሻዎችና ፖሊሶች አሉበት ብለን በምናስባቸው ቦታዎች ሄደው የሚያርሱ ሰዎች መኖራቸውንም ጠቁመዋል።
ዋዜማ ያነጋገረቻቸው በአካባቢው በተለያዩ ቦታዎች የሚገኙ ነዋሪዎች፣ በአሁኑ ወቅት ኹሉም ትምህርት ቤቶች ዝግ መሆናቸውን ገልጸው፣ በአካባቢው ያሉ የትግራይ ታጣቂዎች ትምህርት ቤቶች ካሁን ቀደም ሲጠቀሙበት የነበረው በአማራ ክልል የተዘጋጀውን መጽሐፍ አንቀበልም እያሉ መሆኑን ገልጸዋል።
የመንግሥት ጤና ተቋማት በመድኀኒት እና በህክምና ቁሳቁስ ምክንያት ባብዛኛው አገልግሎት የማይሰጡ ሲሆን፣ የግል ጤና ተቋማት ከፍተኛ ገንዘብ በማስከፈል አገልግሎት ለመስጠት ሙከራ ያደርጋሉ።
የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ኹሉም ዝግ መሆናቸውን የገለጹት ነዋሪዎቹ፣ በአንዳንድ ቦታዎች የትግራይ ክልል ሰንደቅ አላማ ተሰቅሎ ማየታቸውን ነግረውናል። እንዲሁም ገጠር ውስጥ ባሉ መንደሮች እና በአንዳንድ ትንንሽ ከተሞች ከትግራይ ክልል የመጡ ናቸው ያሏቸው ሰዎች ማህበረሰቡን ሰብስበው እያወያዩ ነው ብለዋል።
ከገጠር ቀበሌዎች ወደ ወረዳ ከተሞች እንዲሁም ከአንድ ወረዳ ወደ ሌላ ወረዳ ለመጓጓዝ አስተማማኝ ሰላም ባለመኖሩ የትራንስፖርት አገልግሎት ባብዛኛው መቋረጡንም ጠቅሰዋል። ሆኖም ከአላማጣ ወደ መቀሌ እንዲሁም ከአላማጣ ወደ ቆቦ የሚደረጉ የመኪና ጉዞዎች ዋጋቸውን ከእጥፍ በላይ በመጨመር ጉዟቸውን መቀጠላቸውን ዋዜማ ተረድታለች።
ነዋሪዎቹ እንደተናገሩት፣ በአላማጣ እና ኮረም ከተሞች በይፋ የሚንቀሳቀሰው የመከላከያ ሠራዊት እና የፌደራል ፖሊስ ቢሆንም በአጃቢዎቻቸው የሚንቀሳቀሱ ከትግራይ ክልል የመጡ አመራሮች አሉ ብለውናል።
ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች እስከ 50 ሺሕ የሚገመቱ ከአካባቢው የተፈናቀሉ ዜጎች በሀሙሲት፣ ሰቆጣ፣ ቆቦ እና ወልዲያ ከተሞች ተጠልለው እንደሚገኙም ገልጸዋል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝዳንት ታደሰ ወረደ፣ ጦርነቱን ተክትሎ በአማራ ክልል ስር የተቋቋሙ አስተዳደሮች እስከ ሰኔ 30/2016 ዓ.ም. መፍትሄ ያገኛሉ ሲሉ በቅርቡ መናገራቸው ይታወሳል።
ዋዜማ