May 14, 2024
12 mins read

የአሜሪካው ልዩ መልዕክተኛ ከኦነግ እና ኦፌኮ ተወካዮች ጋር ምን ተወያዩ?

የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) እና ከኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) አመራሮች ጋር በትናንትናው ዕለት፣ ግንቦት 6 2016 ዓ.ም አዲስ አበባ በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ተወይተዋል።

በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ የሆኑት ማይክ ሐመር፣ የፕሪቶርያውን የሰላም ስምምነት አፈጻጸም ሂደት ግምገማ ላይ በመሳተፍ በዚያውም በኦሮሚያ እና በአማራ ክልል ባለው የጸጥታ ችግር ላይ ሊመክሩ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚጓዙ የአገሪቱ የውጪ ጉዳይ ጽህፈት ቤት ባለፈው ሳምነት ባወጣው መግለጫ ላይ ገልጾ ነበር።

በዚሁ መሰረት የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ተቀዳሚ ሊቀመንበር የሆኑት ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ከአምባሳደር ማይክ ሐመር ጋር አዲስ አበባ በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ውስጥ ለአንድ ሰዓት ተኩል ያህል መወያየታቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ውይይታቸው በአጠቃላይ ያተኮረው በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ስላለው ውስብስብ ችግር ሲሆን በተለይ ደግሞ በኦሮምያ ክልል በሚታየው ችግር ዙርያ ሰፊ ጊዜ ወስደው መወያየታቸውን ገልጸዋል።

ማይክ ሐመር ከኦፌኮ እና ኦነግ አመራሮች ጋር በነበራቸው ውይይት ከተነሱ ጉዳዮች መካከል የብሔራዊ ምክክር እና መንግሥት ሸኔ ብሎ የሚጠራው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ጦር ጉዳይ መነሳቱንም ፕሮፌሰር መረራ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ልዩ መልዕክተኛው ከእናንተ ጋር መምከር የፈለጉት ስለምንድን ነው? ተብለው የተጠየቁት ፕሮፌሰር መረራ “የዚህ አገር ሰላም፣ በተለይ ደግሞ በኦሮምያ ሠላም እንዴት ሊመጣ ይችላል? ምን ማድረግ አለብን? የእናንተ ሀሳብ ምንድን ነው ብለው ሊጠይቁን ነው” ብለዋል።

ፕሮፌሰር መረራ አክለውም በኦሮምያም ሆነ በኢትዮጵያ ያለው ችግር መንስኤው “የዲሞክራሲ ስርዓት አለመኖር” እንደሆነ በሰፊው ማስረዳታቸውን ገልጸዋል።

ልክ አንደ ፕሮፌሳር መረራ ሁሉ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳም በኤምባሲው ተገኝተው ከአምባሳደር ሐመር ጋር መነጋገራቸውን የግንባሩ ቃል አቀባይ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

አቶ ለሚ ገመቹ በማህበራዊ ሚዲያቸው ላይ ጉዳዩን አስመልክተው ባጋሩት ጽሑፍ፣ ውይይቱ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ምን ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ፣ በኢትዮጵያ ሠላም ዙርያ እንዲሁም በአፍሪካ ቀንድ ሠላም ላይ ሊጋርጥ የሚችለው አደጋ ላይ ያተኮረ ነበር ብለዋል።

የሚገኙበት የደህንነት ሁኔታ ምቹ ባለመሆኑ ለመገናኛ ብዙኀን ከመናገር ተቆጥበው የሚገኙት አቶ ዳውድ፣ ለማይክ ሐመር አቅርበውታል በተባለው የመፍትሔ ሀሳብ በእስር ላይ የሚገኙ የግንባሩ አባላት እንዲፈቱ፣ በኦሮምያ የተለያዩ አካባቢዎች ተዘግተው የሚገኙ ጽሕፈት ቤቶቻቸው እንዲከፈቱ እና በመላው አገሪቱ የሚገኙ የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ ጠይቀዋል።

ፕሮፌሰር መረራ በበኩላቸው የውይይቱ ዋና ጭብጥ “መፍትሔው ምንድን ነው የሚል ላይ ያተኮረ ነው። አንደኛ ችግሩ ምንድን ነው የሚል ነው። ሁለተኛ ደግሞ እንደ ኦሮምያም እንደ ኢትዮጵያም ከዚህ ችግር ላይ ለመውጣት ምን ማድረግ አለብን የሚል ነው” ብለዋል።

የአሜሪካ መንግሥት ከእነርሱ የፈለገው ባለው ችግር ዙርያ ያላቸው አቋም ምን አንደሆነ ማወቅ፣ በጉዳዩ ላይ ለአሜሪካ መንግሥት መግለጽ የሚፈልጉት ምን እንደሆነ መለየት፣ እንዲሁም የመፍትሄ ሀሳባቸውን ማወቅ እንደሆነም ጨምረው አስረድተዋል።

ማይክ ሐመር ከፖለቲካ ፓርቲ አመራሮቹ ጋር ውይይት ሲያደርጉ የኦሮምያን ጉዳይ በቅርበት የሚከታተሉ የኤምባሲው ሰዎች አብረዋቸው አንደነበሩ የሚናገሩት ፕሮፌሰር መረራ፣ “ጉዳዩ ችግሩን [በኦሮምያ ያለውን] አለመረዳት አይደለም” እላሉ።

“ጉዳዩ [በኦሮምያ ያለውን] ችግሩን አለመረዳት ሳይሆን ችግሩ የኦሮምያ ተቃዋሚዎች የሚያነሷቸው ጥያቄዎች እና መንግሥት ጥያቄዎቹን ለመመለስ ያለው ዝግጅት መካከል ያለው ርቀት እንዴት መጥበብ ይችላል የሚለው ነው” ብለዋል።

እንደ ፕሮፌሰር መረራ ገለጻ የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያም ሆነ በኦሮምያ እየሆነ ስላለው “በቂ መረዳት አላቸው፤ ትልቁ ነገር አሁንም አፈታቱ ነው። አፈጻጸም ነው፤ ስራ ላይ የሚያውሉበት መንገድ ነው፤ ምን ያህሉን ስራ ላይ ያውሉታል የሚለውን ለእነርሱ እንተወዋለን” ብለዋል።

አክለውም “የኢትዮጵያን ፖለቲካ ችግር አስመልክቶ ለአሜሪካ መንግሥት ፈተና የሆነው በመንግሥት እና ተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል ያለውን የተራራቀን ፍላጎት እንዴት ማቀራረብ እንደሚቻል እንደቸገራቸው ነግረውናል” ብለዋል።

የብሔራዊ ምክክር እና ኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት

ማይክ ሐመር እና ፕሮፌሰር መረራ በነበራቸው ውይይት ላይ ካነሷቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር እና የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ “ውጤት አያመጣም” ብለው ራሳቸውን ያገለሉበት የብሔራዊ ምክክር አንዱ ነው።

ፕሮፌሰሩ “ዋናው የተወያየንበት ጉዳይ ይህ ነበር። ይህ ሂደት መፍትሄ ያስገኛል ብላችሁ አትጠብቁ ብለን በግልጽ ነግረናቸዋል። ለመንግሥት ጊዜ ከመግዛት ባለፈ ግጭት አስቁሞ፣ የአገሪቱንም ችግር ፈትቶ የዲሞክራሲ ስርዓት ለመገንባት መፍትሄ አይሆንም” ብለው መግለጻቸውን ተናግረዋል።

የአሜሪካ መንግሥት የኢትዮጵያ ፖለቲካን ችግር ሁሉን አቀፍ እና ታማኝ በሆነ ብሔራዊ ምክክር መፍትሄ እንዲያገኝ ግፊት ሲያደርግ ቆይቷል።

በኦሮምያ ውስጥ በሚንቀሳቀሱት ሁለቱ ፓርቲዎች የአሜሪካ መንግሥት ሲገፋው ከነበረው አጀንዳ ራሳቸውን ማግለላቸው ላይ የልዩ መልዕክተኛው አቋም ምን እንደሆነ ፕሮፌሰር መረራ ተጠይቀዋል።

“ችግራችንን በደንብ ያውቃሉ። አመለካከታችን ለምን አንደዚህ እንደሆነ ኮሚሽኑም ይህንን ችግር መፍታት አይችልም ለምን እንደምንል ጠይቀውናል። እኛም በበኩላችን ያለፈውን አምስት ዓመት ልምዳችንን፣ ያለፉ ሰላሳ ዓመታት ልምዳችንን፣ እንዲሁም ያለፈውን ሀምሳ ዓመት ልምዳችንን ተጠቅሜ የኢትዮጵያ ፖለቲካ በገባኝ መጠን ነግሬያቸዋለሁ።”

በተጨማሪም ለምክክሩ ስኬት ፓርቲያቸው ወደ ምክክሩ ሂደት እንዲመለስ ተጽዕኖ አለማድረጋቸውን፣ ይልቁንስ መፍትሄው ምን ቢሆን ይሻላል የሚለው ላይ ማተኮራቸውን ተናግረዋል።

ማይክ ሐመር ከሁለቱ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር፣ ኦሮምያ ውስጥ ነፍጥ አንስቶ የሚታገለውን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትን አንስተው ተነጋግረዋል።

“እንዴት ብንሄድበት ይሻላል? ምን ይሻላል? ብለው ጠይቀውናል” ያሉት ፕሮፌሰር መረራ፤ የዚህ ችግር መንስዔ የዲሞክራሲ እጦት መሆኑን ጠቅሰው መፍትሄውም ዲሞክራሲን መተግበር እንደሆነ መግለጻቸውን ተናግረዋል።

በተጨማሪም “ከመንግሥትም ጋር ነፍጥ ካነገቡትም ጋር ተነጋግረው የደረሱበትን እነርሱ ያውቃሉ። ነገር ግን አሁንም ግንኙነታቸው [ከኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ጋር] እንዳልተቋረጠ ነግረውኛል” ብለዋል።

ፕሮፌሰር መረራ ኢትዮጵያ ውስጥ ዲሞክራሲ በሚገባው ያልተሞከረ ስርዓት ስለሆነ እርሱን መሞከር መፍትሄ አንደሚሆን በአጽንኦት መግለጻቸውን ተናግረዋል።

በስተመጨረሻም በምክክራቸው ወቅት፣ ልዩ መልክተኛው ማይክ ሐመር ወደፊት እንዴት ኢትዮጵያን መደገፍ እንደሚቻል እያሰቡ እንደሆነ መረዳታቸውንም ተናግረዋል።

BBC- Amhric

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

እነዶ/ር ደብረፅዮን እና በጠ/ሚ ዐብይ አህመድ በተሾሙት የትግራይ ጊዜያዊ መንግሥት መሪዎች እነጌታቸው ረዳ መካከል የነበረው አለመግባባት ተካርሮ ሰራዊቱን ወደውግንና አስገብቷል። የትግራይ ሐይል አዛዦች ትላንት ባወጡት መግለጫ ውግንናቸው ከእነዶ/ር ደብረፅዮን ጋር መኾኑን አስታውቀዋል።

በትግራይ የተፈጠረው ምንድነው?

January 23, 2025
የድሮ መሪዎች ያላደረጉትን ምሁር ጳጳሳቱ ያላስተዋሉትን ከፈረሰች ጎጆ ከባልቴት ቤት ገብቶ ክብሩን ዝቅ አድርጎ ውሀዋን ጠጥቶ ምግቧንም ተጋርቶ ያላለቀሰ ሰው ያንን ትይንት አይቶ ማን ይኖራል ከቶ? በዉሸት ፈገግታ ፊቱን አስመስሎ ፀሀይ የበራበት

ሰው በሰውነቱ – ከ ይቆየኝ ስሜ

የአማራ ፋኖ በጎጃም ምክትል የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ የነበረው እና አሁን ላይ በአማራ ፋኖ በጎጃም የሁለተኛ (ተፈራ ) ክፍለጦር ሰብሳቢ የነበረው ፋኖ ዮሐንስ አለማየሁ በክብር ተሰዋ። የአማራ ህዝብ የተጋረጠበትን የህሎና አደጋ ለመቀልበስ ያለ

ከአማራ ፋኖ በጎጃም የተሰጠ የሐዘን መግለጫ ታጋይ ይሰዋል ትግል ይቀጥላል !

January 22, 2025
Go toTop