ቅዳሜ የካቲት 23 ቀን 2016 ዓም (02-03-2024) አምስተርዳም
አዘጋጅና አቅራቢ አገሬ አዲስ
ዝክረ አጼ ሚኒሊክና እቴጌ ጣይቱ
እንኳን ለ128ኛው የድል በዓላችን አደረሳችሁ፤አደረሰን!
በዛሬው እለት የምናከብረው ይህ ትልቅ የድል ቀን መታሰቢያ ከ128 ዓመት በፊት የነጮችን (የጣሊያኖችን)የወረራና የቅኝ አገዛዝ ቀንበር የመጫን ሙከራ በንጉሠ ነገሥቱ በአጼ ሚኒሊክ ጥሪና የክተት አዋጅ ሃይማኖትና ጎሳ ሳይነጣጥላቸው በአንድ ኢትዮጵያዊነት ከያቅጣጫው ተሰባስበው፣የራሳቸውን ስንቅ ቋጥረውና ትጥቅ አንግበው በአድዋ ጦር ሜዳ ላይ ተሰልፈው የህይወት ዋጋ በመክፈል የወራሪውን ጠላት ቅስም የሰበሩበትና የቆዬ ነጻነታቸውን ያረጋገጡበት እለት ከመሆንም አልፎ በቅኝ አገዛዝ ቀንበር ለወደቁት ሁሉ የነጻነት ምሳሌና ፋና ወጊ የሆነ ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፍ አኩሪ በዓል ነው።ታዲያ በዚህ ቀን ለአኩሪው ድል ያበቁትን መሪዎች የዳግማዊ አጼ ሚኒሊክንና የእቴጌ ጣይቱ ብጡልን ስምና ተግባር አንስቶ መዘከር በዓሉን የተሟላ ገጽ እንዲኖረው ያደርገዋል።የአድዋ ድል ካለምንሊክና ጣይቱ አይደምቅምና!
ምንሊክ ተነስቶ ባያነሳ ጋሻ፣
ግብሩ እንቁላል ነበር ይህን ጊዜ አበሻ።
የሚለውን ዘመንና ትውልድ ተሻጋሪ መልእክት መነሻ በማድረግ ወደ መሪዎቻችን ታሪክ ስገባ እግረመንገዴን ኢትዮጵያ ከ150 ዓመት ወዲህ የተፈጠረች አገር ናት የሚለውንም የታሪክ ድኩማን ትርክት ስህተት መሆኑን የሚያሳዬውን የእረጅም ጊዜ ታሪኳን በአጭሩ ለማቅረብ እሞክራለሁ።
ኢትዮጵያ ከምንሊክ በፊት ከክርስቶስ ልደት በፊትና በዃላ ፣ከአክሱማዊ ስርወ መንግሥት የፈለቀው ከሳባውያን ጀምሮ ሰለሞናዊ የትውልድ ሃረግ ያላቸው ነገሥታት የመሯት የረጅም ዘመን ታሪክ ያላት አገር መሆኗን የውጭ ሃገር ታሪክ ጸሃፊዎች ሳይቀሩ የመሰከሩላት አገር ነች።የምንሊክም ዘውዳዊ ስርዓት ከዚያ ይመዘዛል።ዘርዘር አድርገን ስናዬው የሚከተለውን ይመስላል።
ከሰለሞናዊ የንግሥና ሃረግ ካላቸው የሸዋ ንጉስ ሣህለሥላሤ ልጅ ከሆኑት ከልዑል ሃይለመለኮትና ከወይዘሮ እጅግአዬሁ ለማ ሳህለማርያም ሃይለመለኮት የንግሥና ስማቸው ዳግማዊ ምኒሊክ በነሃሴ 12 ቀን 1836 ዓም ከደብረብርሃን ደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ 5 ኪሎሜትር ገደማ እርቃ በምትገኘው አንጎለላ ልዩ ስሟ እንቁላል ኮሶ በምትባለው መንደር ውስጥ ተወለዱ።እንደማንኛውም የመሳፍንት ልጅ ሳህለማርያም ሃይማኖታዊና አስተዳደራዊ እውቀትን እዬተከታተሉ አደጉ።
የፊተኛው ከሌለ የዃለኛው አይኖርምና ሳህለማርያም(ዳግማዊ ሚኒሊክ)የኖሩበት ዘመንና ስርዓት ካለፈው ሲያያዝ የመጣ እንጂ በአንድ ጀንበር የተከሰተ አይደለም።ኢትዮጵያ ሳህለማርያም (ዳግማዊ አጼ ምኒሊክ )ዘመነ መንግሥት ላይ ለመድረስ ብዙ ነገሥታትን አስተናግዳለች።ይህንንም ለማሳዬት ታሪኳን ቀንጨብ ቀንጨብ አድርገን ብናዬው በአገር ደረጃ ታውቃና ተከብራ መኖሯን ብቻም ሳይሆን የነበራትን የታላቅነት ደረጃ እንድናውቀው ይረዳናል።በተጨማሪም የመቶ ዓመት ታሪክ ያላት አገር ነች እያሉ ለሚጥላሏት ጠላቶቿ ትርክት አፍራሽ መልስ ይሆናል።ምናልባትም በዳግማዊ አጼ ምኒሊክ የተስፋፋውን የማዘመን ሂደት እንደ አገር ፈጠራ አድርገው ቆጥረውት ሊሆን ይችላል በሚለው እንዳንተረጉመው አሁንም ድረስ ያንኑ ተራ ትርክት እያላዘኑ የሚገኙት በትምህርት የገፉት ምሁር ተብዬ ጸረ ኢትዮጵያና ጸረ አንድነት የሆኑት አገር በቀል በመሆናቸው ሌላውን በተለይም ወጣቱን በማሳሳት ላይ ተጠምደዋል፤ያንን ዝም ብሎ ማዬት ተገቢ አይደለም። ስለሆነም የኢትዮጵያን አገራዊ የረጅም ዘመን ታሪክ መዳሰሱ ተገቢ ነው።
የኢትዮጵያ ታሪክና ሥልጣኔ ከ1300 ምዓተዓለም ከክርስቶስ ልደት በፊት ከነበረው ከአክሱማዊ/ሳባውያን ዘመን የጀመረ ሲሆን እስከመጨረሻው ንጉሠ ነገሥት እስከነበሩት አጼ ሃይለሥላሤ(ተፈሪ መኮነን)ዘመነ መንግሥት ድረስ የ3000 ዓመት ዕድሜ እንዳለው ታሪክ ይመሰክራል።እዚህ ላይ ከሰለሞናዊ ሃረግ ውጭ በዮዲት 40 ዓመት፣ በዛግዌ ነገሥታት 200 ዓመት፣በዘመነ መሳፍንት 80 ዓመት በካሣ ሃይሉ(አጼ ቴዎድሮስ) 15 ዓመት፣በበዝብዝ ካሣ(አጼ ዩሃንስ አራተኛ) 17 ዓመት ተዳድራለች። ዘመኑን በሂሳብ ብናሰላው
ከሳባውያን፣ሰለሞናዊ ስርወ መንግሥት እስከ ክርስቶስ ልደት ድረስ 1300 ዓመት
ከክርስቶስ ልደት በዃላ እስከመጨረሻው ሰለሞናዊ ሃረግ አጼ ሃይለሥላሤ ድረስ 1967 ዓመት
በጠቅላላው 3267 ዓመት
ከዚያ ውስጥ ከሰለሞናዊ ሃረግ ውጭ 40+ 200+80+15+17 352 ዓመት ተዳድራለች።ከመስከረም 2 ቀን 1967 ዓመት ወዲህ ያለውን የሃምሳ ዓመት አገዛዝ ስንደምርበት ኢትዮጵያ እንደ አገር የቆየችበት ዘመን 3317 ዓመት ይሆናል ማለት ነው።ይህም የ3000 ዓመት ታሪክ አላት የሚለውን የሚያረጋግጥ ይሆናል።
በዚህ ረጅም ዘመን የሥልጣን ቅብብሎሽ እያስተናገደች ፤መልካምና መጥፎ፣አኩሪና አሳፋሪ ክስተቶችን አልፋ አሁን እኛ ካለንበት ዘመን ላይ ደርሳለች።መሰረቱን በአክሱም ያደረገው የሣባውያን ስርወመንግሥት (ዳይናስቲ)ከፍተኛ የሥልጣኔ ደረጃ ላይ የደረሰው የንግሥት ሳባና የንጉስ ሰሎሞን ልጅ በሆነው ከቀዳማዊ ምኒሊክ እስከ መጨረሻው የአክሱማውያን ንጉሥ እስከ አጼ ገብረመስቀል ዘመነ መንግሥት ባለው ጊዜ ውስጥ እንደነበር በታሪክ መጽሃፍ ላይ ሰፍሯል።በዚህ ዘመን የአክሱም ነገሥታት እስከ አረብ መሬት(የመን)ድረስ ዘልቀው ያስተዳድሩ እንደነበር ከውድመት የተረፉት ሃውልቶችና ፍርስራሾች ይመሰክራሉ።በተለይም አጼ ገብረመስቀል ወደ የመን ሄዶ ይበጠብጡ የነበሩትን ፋርሶችን ወግቶ ድል በማድረግ ቦታውን (ግዛቱን)ማስከበሩ ከሚደነቅባቸው ሥራዎቹ አንዱ ነው።የመን ከ450-550 ለአንድ መቶ ዓመት የአክሱም መንግሥት አካል ነበረች።ሁሉም ነገር እንዳለ አይቆይም፤የነበረው ባልነበረና በአዲስ መተካቱ የተፈጥሮ ሕግ ነው። የመንም በተረኛው ሃይለኛ ስር በመውደቋ ከአከሱማውያን እጅ ወጣች።
ከሰሎሞናዊ የትውልድ ሃረግ ጋር የተቆላለፈው የአክሱም ስርወመንግሥት በአምበሳ ውድም ዘመነ መንግሥት በ880 ዓመተምህረት በተመሰረተ በ2680 ዓመቱ ዮዲት(በጭካኔዋ ጉዲት) በምትባል የነገደ እስራኤል (ፈላሻ)ተወላጅ ተቋረጠ።ዮዲት በኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ላይ ካደረባት ጥላቻ በመነሳት ሃይሏን ሰብስባ በጦርነት እያሸነፈች አብያተክርስቲያናትን እያቃጠለችና አማኞችንም እዬፈጀች ለ40 ዓመታት የአክሱምን የሥልጣን መንበር ተቆጣጠረች፤ከአክሱም የተባረረው ንጉስ አምበሳ ውድም ሸሽቶ ሸዋ ገብቶ ተቀመጠ።ዮዲት ከሞተች በዃላ ግን በ920 ዓም ወደ አክሱም ተመልሶ ለ20 ዓመት ያህል በዙፋኑ ላይ ተቀምጦ በተፈጥሮ ሞት ሲለይ ልጁ ድል ነአድ ተተክቶ ለ10 ዓመት ያህል በዙፋኑ ላይ ተቀምጦ ከያቅጣጫው በተነሳበት ተቃውሞ የተነሳ መንግሥቱ ተዳክሞ የሥልጣን ወንበሩን በተረኛው በዛግዌ ቤተሰብ ተነጥቆ ማእከሉ ከአክሱም ወደ ላስታ ዞረ።ድል ነአድ እንደአባቱ ወደ ሸዋ መጥቶ በተራ ሰውነት ሲኖር ቆይቶ ሞተ።እዚህ ላይ ልናጤነው የሚገባው ቁም ነገር የኢትዮጵያ ግዛት ከሰሜኑ ወደባዊ አልፎ ወደደቡቡ መዘርጋቱን ሲከፋቸው ወደሸዋ የሚመጡት ነገሥታት ታሪክ ያረጋግጣል።ግዛታቸው ባይሆንና የማያውቁት ቦታ ቢሆን ኖሮ ለመሸሽ ፊታቸውን ወደ ሸዋ ባላዞሩም ነበር። ሸዋ በአማካይ ቦታ በመኖሩ እንጂ የግዛታቸው የመጨረሻ ድንበር አልነበረም።የኢትዮጵያ ድንበር በደቡብ እስከነጭ አባይ መነሻ ድረስ የሚያካትት እንደነበር የታሪክ መጽሃፍት መዝግበውታል። በምስራቁም በምዕራቡም በኩል እንዲሁ የኢትዮጵያ ግዛት እንደአሁኑ የተሸበሸበና የጠበበ አልነበረም።በወራሪዎች ሴራ እዬተቆራረሰ አሁን ካለችበት ደረጃ ላይ ለመድረስ በቅታለች።ይህንን እዚህ ላይ አቁመን ስላነሳነው የዛግዌ ስርወመንግሥት እንቀጥል፤-
የዛግዌ ስርወመንግሥት ለ200 ዓመት በሥልጣን ላይ የቆዬ ሲሆን ብዙ ነገሥታትን አፍርቷል፤ከነዚያም ውስጥ በታሪክ ስሙ ገኖ የታወቀው ዘጠነኛው ንጉሥ ላሊበላ ነው።ከሚወደስባቸው ሥራዎቹም ውስጥ እስከአሁን ድረስ በዓለም ተደናቂ ሥራዎች ውስጥ በመመዝገብ የቱሪስት ስበት ያለው በላሊበላ ከአንድ ግዙፍ አለት(ቋጥኝ) ያስገነባቸው 11 ውቅረ ቤተክርስቲያናት ሲሆኑ ሌላው ደግሞ የአባይ ውሃ ወደ ግብጽ እንዳይፈስ አድርጎ የግብጽን ሕዝብና መንግሥት በማስጨነቅ ግብር እንዲከፍሉ በማስገደድ የአገሩን የበላይነትና ክብር ያሳዬበት ቆራጥነቱና ጀግንነቱ ነው።
የዛግዌ ስርወ መንግሥት እንዳለፉት ሥርዓቶች ሲዳከም በሸዋ ውስጥ በመኖር ተዋልዶ የነበረው የአክሱም ሰለሞናዊ ዝርያ ጋር በመስማማት ሥልጣኑን አሳልፎ ለመስጠት ተገደደ።ለዚህ ውሳኔ የደብረሊባኖሱ መነኩሴ በዃላም አቡነ ተክለሃይማኖት በመባል የሚታወቁት ትልቅ ሚና እንደተጫወቱ ታሪክ ይመሰክራል።ዳግም ያንሰራራው ሰለሞናዊው ዝርያ ኢትዮጵያን መልሶ በማጠናከር ተግባር ላይ ሲታክቱ በ700ኛው ዓመት ላይ በመካከለኛው ምሥራቅ በአረብያ የተነሳው እስላማዊ ንቅናቄ ከባቢውን እዬወረረ ክርስቲያኖችን በጉልበት እያሰለመ ሃይሉን ሲገነባ ምንም እንኳን ለእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ፍትሃዊ ከለላ በመስጠት ለሃይማኖቱ መስፋፋት ያገዘች የክርስቲያን መንግሥት አገር ብትሆንም ከጀሃዲያኑ ትንኮሳ አላመለጠችም።በዬወቅቱ ይተናኮሉዋት ስለነበር ነገሥታቱ ለአገር ግንባታ የሚያውሉትን ሃብት፣ጊዜና ጉልበት ወደ መከላከያ ግንባታ እንዲያውሉት አስገደዳቸው።በቱርክና በሰለሙት አገሮች የሚመራው እስላማዊው ጀሃዲስት ንቅናቄ በኢትዮጵያ ዙሪያ ያሉትን አገሮች እየዋጠ የኢትዮጵያንም ድንበር እያለፈ የክርስቲያኑን መንግሥት የማናጋቱን ሥራ በሰፊው ተያያዘው።የቀይ ባሕርን ተሻግሮ በሰሜኑና በምሥራቁ በኩል ግብጽንና ሶማሊያን በመቆጣጠር ከኢትዮጵያ ነገሥታት ጋር ዘመን የዘለቀ ጦርነት ውስጥ ገባ።
በተራዘመ ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ የጦርነት ጉዞ የተጓዘችው ኢትዮጵያ ከውጭና ከውስጥ በተከሰተው ችግር ተናጠች።የተጀመረው የእድገትና የሥልጣኔ አቅጣጫ መቀጠል አለመቻሉም ብቻ ሳይሆን አንድነቷም ፈተና ውስጥ ገባ፤የነበሩት ቅርሶች ከጥቂቶቹ በስተቀር አብዛኞቹ ወደሙ።የቱርክ ኦቶማንን የመስፋፋትና የማስለም ወረራን ተከትሎ ግብጾችም የኢትዮጵያን ክፍሎችና ወደቦች ለመቆጣጠር ድፍረት አገኙ።ከውስጥ የሚተባበራቸውም ባንዳ አልጠፋም።አሚር ማህፉዝ የተባለው እስልምናን የተቀበለ ኢትዮጵያዊ የአፋር ባላባት ከአጼ ናኦድ ጊዜ ጀምሮ ከግብጾችና ከቱርኮች እርዳታ በማግኘት ሰላም ይነሳ ነበር።በ1560 ዓም በሃምሌ ወር በይፋት አቅራቢያ በተደረገ ጦርነት ላይ ሲዋጋ በአንድ መነኩሴ የሰይፍ በትር ተመቶ ሲወድቅ የተከተለው ጅሃዳዊ ሠራዊቱ ተበታተነ።ከዚህም በዃላ ቢሆን የቱርኮችና የግብጾች የወረራ ሙከራ አልቆመም፤ይህም በቀጣይ ለግራኝ መሃመድ መነሳት ምክንያት ሆነ።የግራኝ ሙሃመድ ሙሉ መጠሪያ ስሙ አህመድ ኢብን ኢብራሂም አል ቃዚ ይባላል።በክርስትና እምነት ላይ ከነበረው ጥላቻና መንግሥት በጣለው የግብር ጭነት የተነሳ ባደረበት የበቀል ስሜት ላይ የቱርኮችና የግብጾች ድጋፍ ተጨምሮበት ግራኝ አህመድ ተግደርዳሪ ሃይል ሆኖ ለመውጣት ቻለ።የግራኝ አህመድ ወረራ ሰለባ የሆኑት አጼ ልብነ ድንግል ሲሆኑ አንድ ጊዜ ሲያሸንፉ ሌላ ጊዜ ሲሸነፉ ከቦታ ቦታ በመዘዋወር እንደባከኑ ቆይተው ሞቱ። ግራኝም ምንም እንኳን የተደላደለ የሥልጣን ዘመን ባይኖረውም በ15 ዓመት የበላይነት ዘመኑ ክርስቲያኑን እሺ ያለውን እያሰለመ እምቢ ያለውን እዬገደለ ፣ተጠልቶና ተፈርቶ ሲኖር ከአጼ ልብነድንግል ልጅ ከአጼ ገላውዲዎስ ጦር ጋር ሲዋጋ በጦር ሜዳ ላይ ተመቶ ሲሞት ጭፍራው ተበታተነ፤ኢትዮጵያም ከጅሃዳዊ ወረራ ለጊዜውም ቢሆን እፎይታ አገኘች።
እዚህ ላይ ልብ ልንላቸው የሚገባን ሁለት ነገሮች አሉ።አሚር ማህፉዝም ሆነ ግራኝ አህመድ ኢትዮጵያን እስላማዊ አገር ለማድረግ እንጂ ለመበታተን አለመነሳታቸውን ነው።ዮዲትም ብትሆን እንዲሁ ክርስትናን አጥፋታ የአይሁድን እምነት ለማስፈን እንጂ ኢትዮጵያን ለመገነጣጠል የተነሳች እንዳልነበረች ግልጽ ሊሆን ይገባል።ሌላው በማንኛውም ወቅት ጀግናና ፈሪ፣አድርባይና አገር ወዳድ እንደሚኖር ያሳለፍናቸው ታሪኮች ያሳያሉ። አሚር ማህፉዝን የገደለ መነኩሴ እንዳለ ሁሉ በስመ አብ ወወልደ መንፈስ ቅዱስ አሃዱ አምላክ ባለበት አፉ አላህ አኩበር ላኢላህ ሃይለላህ ሞሃመድ ረሱለላህ ብሎ በራሱ እምነትና በወገኖቹ ላይ ሰይፍ የመዘዘ መነኮሳትና ቀሳውስት እንደነበሩ ስናይ፣በዘመናችን በአድርባይነትና በፍርሃት ጸረ ሕዝብና ጸረ አገር ሚና የሚጫወቱ መኖራቸው እንግዳና አዲስ ክስተት አድርገን እንዳናይ ያደርገናል።አሁንም ሆነ ወደፊት ከሃዲና አድር ባይ ይኖራል።የውጭ ጠላትም የሚገባው በነሱ ትከሻ ላይ ነው።ያንን ለማድረቅ የሚያስችል ሥርዓት ከመፍጠር የተለዬ መፍትሔ አይኖርም።
ከብዙ ውጣ ውረድ በዃላ ለጥቂት ዓመታትም ቢሆን የሰለሞናዊ ትውልድ ሃረግ ሥልጣኑን እዬተቀባበለ ከኖረ በዃላ ወደ ሌላው ቀውስ ተገባና አገሪቱ በዬከባቢው በተነሱ ሽፍቶችና ባላባቶች መዳፍ ስር ወድቃ ለ80 ዓመታት በእርስ በርስ የስልጣን ሽኩቻ ታመሰች።በዚህ ዘመነ መሳፍንት ተብሎ በታወቀው የትርምስ ዘመን ዘውድና መንግሥት መጫወቻ ሆነ።ሁሉም የከባቢ ጉልበተኛ በዬፊናው ዘውድ እዬጫነ ሌላውን ለማስገበር አካኪ ዘራፍ ብሎ ጭፍራውን እያሰለፈ እርስ በርሱ ይጨፋጨፍ ጀመር። በወራራውም አንዱ የሠራውን ሌላው እያፈረሰና እያቃጠለው የጉልበት ማሳያ ጥበብ ሆነና ያገር ቅርስና ሃብት ወደመ።ይህ ዘመን ኢትዮጵያውያን አንድ ያልሆኑበትና ኢትዮጵያም የተዳከመችበት በመሆኑ በታሪክ አሳፋሪ ገጽ የያዘ ሆኗል።ይህ በኢትዮጵያ ብቻ የተከሰተ ሳይሆን በሌላውም የዓለም ክፍል በተለይም በአውሮፓ አገሮች የተከሰተ ችግር ነበር።ሆኖም ግን በአውሮፓ የምሑራኑ መፍለቅ፣የእውቀትና የእድገት በር መከፈት ከዃላ ቀር አስተሳሰብና ሥርዓት ለመላቀቅና ወደ ተሻለ ብሎም ወደ አሁኑ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመግባት የብዙ ዜጎች ትግልና መስዋእትነት ተከፍሎበታል።የፋብሪካዎች መስፋፋት፣የከበርቴ ሥርዓት ማቆጥቆጥ ፣የምሁራን መነቃቃትና (ኢንላትመንት)የሕዝቡም ንቃተ ህሊና መዳበር ለአሁኑ ደረጃ አብቅቷቸዋል።ከጎሳና ጎጥ ትንቅንቅ ወደ አገራዊ ብሎም ወደ መደብ ትግል እንዲገቡ አድርጓቸዋል።ይህም ሆኖ ግን ችግሩ ሁሉ በኖ ጠፋ ማለት አይደለም። እያንዳንዱ ሥርዓት የሚያመጣው የራሱ ድክመትና ችግር ስላለው የከበርቴውም ሥርዓት አገራትንና ሕዝብን በማተራመስ፣የቅኝ አገዛዝ ወረራ በማካሄድ፣በውስጡ በተነሳው ፉክክር ሁለት ታላላቅ የዓለም ጦርነቶችን ወልዷል።አሁንም እያተራመሰው መጥቷል።በስግብግብነትና በዘረፋ ላይ የተቃኘው የከበርቴዎች ሥርዓት ዓለምን አደገኛ የኑክሌር ጦርነት ስጋት ውስጥ ጨምሯታል።መፈናቀል፣ስደት፣በያገሩ ጦርነት የየእለቱ ክስተት ሆኗል፤በዚያ ላይ ለገንዘብ ሲባል የሚደረገው ዓይን ያወጣ ውድድርና ሽሚያ የተፈጥሮ ሚዛንን እያዛባ የፈጠረው የአዬር ብክለት በሰውና በእንስሳት ህይወት ላይ ብዙ ጉዳት አድርሷል።የልዩ ልዩ በሽታዎች ምንጭና ምክንያት ሆኗል።ይህም ለመድሃኒት አምራቾች የገቢ ምንጭ ሆኖ ገንዘብ የሌለው እንዲሞት ተፈርዶበታል።በጦርነትም የጦር መሳሪያ አምራቾች እንዲሁ ተጠቃሚዎች ሆነዋል።ጦርነትና በሽታ ከሌለ እነዚህ መስኮች ሊንቀሳቀሱ ስለማይችሉ ጦርነትና በሽታ መፍጠር እለታዊ ተግባራቸው ሆኗል።
ወደ እኛ አገር ስንመለስ የነበረው ባላባታዊ ስርዓት ለዘመናዊ አስተሳሰብ የማይመችና ጸርም ስለነበር (አሁንም ነው)ወደ እድገት የሚወስደው መንገድ ክርችም ብሎ ተዘግቶ ኖሯል።ይህንን የተዘጋ በር ለመክፈት በመሳፍንትና በባላባት እንዲሁም በጉልበተኞች የተከፋፈለችዋን ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ የደፈሩት የትንሹ እራስ አሊ ባለሟል የቋራው ተወላጅ ልጅ ካሣ ሃይሉ በንግሥና ስማቸው አጼ ቴዎድሮስ ናቸው።ደጃዝማች ካሣ ሃይሉ ሳይታሰቡና ሳይገመቱ ተነስተው ንጉሠ ነገሥትነትን ለመውሰድ በያለበት ያቆበቆቡትንና እርስ በርስ የሚዋጉትን ሁሉ በዬተራ አጥፍተው ወይም አንበርክከው የንጉሠነገሥትነትን ማዕረግ ለራሳቸው አድርገው ዘውድ ቢጭኑም ሰላምና ጸጥታ አስፍነው ሙሉ ኢትዮጵያን የመምራቱ ነገር ቢወጡ ቢወርዱ፣ ቢዋጉ ድል ቢያደርጉ፣ ቢራሩ ቢጨክኑ ሊሳካላቸው አልቻለም።ዛሬ ያሸነፉትና ገብሬአለሁ ያላቸው በማግስቱ እዬኮበለለ አስቸገራቸው።ከነዚህም የከባቢ መሳፍንትና ጉልበተኞች መካከል የትግሬው በዝብዝ ካሣ(የንግሥና ስማቸው አጼ ዩሃንስ አራተኛ)እና የሸዋው ሃይለመለኮት ነበሩ።የሸዋውን ለማስገበር ሠራዊታቸውን ክተት ብለው ሲዘምቱ በመካከሉ ንጉስ ሃይለመለኮት ታመው በመሞታቸው የሸዋ ጦር ተፈታ፤የጦር መሪዎቹም የደጃች ካሣን ንጉሠነገሥትነት ተቀብለው ለዋስትና የንጉሥ ሃይለመለኮትን ልጅ ሳህለማርያም ሃይለመለኮትን(ዳግማዊ ምኒሊክን)አሳልፈው ሰጧቸው። አጼ ቴዎድሮስ በግዞት የወሰዱትን የ12 ዓመቱን ልጅ ሳህለማርያምን እንደ ምርኮኛ ሳያዩ እንደራሳቸው ልጅ ከአጠገባቸው ሳይለዩ ተንከባክበው ያዙት።በመልካም ስነምግባር አንጸው አሳደጉት።ብልህና አስተዋይነቱንም አይተው ላቅመአዳም ሲደርስ ሴት ልጃቸውን ወይዘሮ አልጣሽ ቴዎድሮስን ዳሩለት።
አጼ ቴዎድሮስ ምንም እንኳን ውጣ ውረድ ቢበዛባቸውም አገራቸውን ለማዘመን ህልምና ምኞት ነበራቸው።በመጀመሪያ የወሰዱት የለውጥ እርምጃ በአርሶ አደሩ ጫንቃ ላይ እንደ ተባይ ተጣብቆ ላቡን የሚመጠምጠውን የጭፍራ ጦር በደመወዝ የሚተዳደር የጦር ሙያተኛ የመንግሥት ወታደር እንዲሆን ደንግገው ለጊዜውም ቢሆን አርሶ አደሩ እፎይታ እንዲያገኝ አደረጉት።ከውጭ አገር መንግሥታትም ጋር ግንኙነት እያደረጉ ለአገር ይበጃል ያሉትን ለማግኘት ይጥሩ ነበር።ያም ሆኖ ግን የአውሮፓ መንግሥታት በተለይም የእንግሊዝና የፈረንሳይ ለእቅዳቸው የቴዎድሮስን አይነት አገር ወዳድ ከቃላት መሸንገልና ማዘናጋት ያለፈ በጎ ነገር ለማድረግ ፈቃደኞች አልሆኑም።እንደውም የሚወድቁበትን ሴራ መጎንጎኑን አጠናክረው ቀጠሉበት።ከውጭ በኩል ከቱርክና ከግብጽ ጀርባ ከተሰለፈችው እንግሊዝ የሚሰነዘሩትን የወረራ ሙከራዎች ሲከላከሉ፣ከውስጥ በኩል ደግሞ ሥልጣኑን ለመቀማት ፣አልገብርም እያለ የሚሸፍተው ተቃዋሚ ከያቅጣጫው እዬተነሳ እረፍት ነሳቸው።በዚህ መሃል በሸዋ በዛብህ የሚባል ባላባት ተነስቶ የሸዋ ንጉሥ ነኝ ብሎ የሳህለማርያምን አባት የንጉስ ሃይለመለኮትን ወንበር ቀምቶ ተቀመጠበት።ይህንን የሰሙት ወጣቱ ሳህለማርያም አጼ ቴዎድሮስ ለዘመቻ በወጡበት ጊዜ አጋጣሚውን ተጠቅመው ከጎንደር በወሎ በኩል ሸዋ ገቡ።የሸዋ ሕዝብ የንጉሡን ልጅ መመለስ በደስታ ተቀብሎ በዛብህን አባሮ ሳህለማርያምን ንጉሥ አድርጎ ሾመ።
በዚህ የተናደዱት አጼ ቴዎድሮስ ሸዋን ለዳግመኛ ጊዜ ለመቅጣት ባሰቡበት ጊዜ በትግራዩ በበዝብዝ ካሣም በኩል እንዲሁ የመክዳት አዝማሚያ ይታይ ጀመር።ይህንን ሁኔታ ሲከታተሉና ሲመኙ የነበሩት እንግሊዞች በዝብዝ ካሣን እዬደገፉ አጼ ቴዎድሮስን ለመውጋት የወታደር ሃይላቸውን አዘጋጅተው ከንጉሠ ነገሥቱ ጦር ጋር በመቅደላ ሲዋጉ የቴዎድሮስ ጦር በጀግንነት ተዋግቶ በጠላት ዘመናዊ መሣሪያ በታገዘ ወታደር ወደ መሸነፉ ሲቃረብና በተለይም የሚተማመኑባቸውና የሚወዷቸው እንደ ገብርዬ ያሉ የጦር አበጋዞቻቸው የመሰዋት ዜና ለንጉሠ ነገሥቱ ሲደርስ ከባድ መርዶ ከመሆኑም ባለፈ ይበልጥ ብስጭት አሳደረባቸው።የሚቻላቸውን ካደረጉ በዃላ የመጣውን ጠላት እስከመጨረሻው ድረስ ተፋልመው በጠላት እጅ ላይ መውደቁን ተጠይፈው በገዛ ሽጉጣቸው እራሳቸውን በመግደል ጀግንነትና ድፍረታቸው ለራሳቸውም ህይወት የማይመለስና የማይሳሳ መሆኑን ፣እጅ መስጠት የኢትዮጵያውያን ባህል አለመሆኑን አሳይተው አለፉ።ኢትዮጵያን አንድ አድርጎና አሰልጥኖ የመምራት ዓላማቸው ከ14 ዓመት ድካም በዃላ በተወለዱ በ50 ዓመታቸው ሚያዝያ 6 ቀን 1860 ዓም የታሪካቸው መደምደሚያ ሆነ፤በድን አካላቸው በመቅደላ መድሃኔ ዓለም ቤተክርስቲያን ከርሰ መቃብር አረፈ።በአልቃሽም የሚከተለው እንጉርጉሮ ወረደላቸው
አባ ታጠቅ ካሣ ታባቱ ታባቱ፣
አልማሚት ሠራዊት ያስጉዛል ከፊቱ፣
እሱ እንደክርስቶስ አንድ ነው ለናቱ።
ዳር እስከዳር ይዞ የገዛው ንጉሥ፣
እንዲህም ስሱ ነው ጠመንጃ ሚጎርስ።
ጠላቶቹን ሁሉ አጭዶ እንደ ገብስ፣
መቅደላ ተጣለው እራሱን በራስ።
በመቅደላ በኩል ጩኸት በረከተ፣
የሴቱን አናውቅም ወንድ አንድ ሰው ሞተ።
አያችሁለት ወይ ያንበሳውን ሞት፣
በሰው እጅ መሞትን ነውር አድርጎት።
የትግሬንም ንጉሥ ሲንቁ ሲንቁ፣
የሸዋንም ንጉሥ ሲንቁ ሲንቁ፣
ወንድ አለራስዎ ገለውም አያውቁ።
አባትና እናቱ አላንድ አልወለዱ፣
አባ ታጠቅ ካሣ ያው አንዱ ያው አንዱ።
ገደልን እንዳይሉ ሞተው አገኟቸው፣n
ማረክን እንዳይሉ ሰው የለ በጃቸው፣
ምን አሉ እንግሊዞች ሲገቡ አገራቸው?
ከአጼ ቴዎድሮስ ቀጥለው የንጉሠ ነገሥትነቱን ሥልጣን የያዙት የቴምቤኑ ተወላጅ በዝብዝ ካሣ(አጼ ዩሃንስ አራተኛ)ናቸው።እሳቸውም አገራቸውን አንድ ለማድረግና ከውጭ ጠላት ሲከላከሉ እሽ ያለውን በፍቅር እምቢ ያለውን ደግሞ በጉልበት እያስገበሩ የኖሩ መሪ ናቸው።በጎጃም፣ በወሎ፣ በሸዋ የተነሳባቸውን ተቃዋሚና ተፎካካሪ በማለዘብ ተግባራቸው ይታወቃሉ።የተቀበላቸውን እዬሾሙና እዩሸለሙ አጋር ለማድረግ ሲሞክሩ እምቢ ያለን አይቀጡ ቅጣት እዬቀጡ በትረንግሥናቸውን አጽንተዋል።ከውጭ በኩል ከቱርክና ከግብጽ የሚሰነዘረውን ወረራ እንደቀድሞ መሪዎች በመከላከል ብቻም ሳይሆን በጦር ሜዳ በማሸነፍ ያገራቸውን ዳር ድንበር በተለይም የቀይ ባህር ወደብ በራቸውን በማስከበሩ ረገድ ለኢትዮጵያ ትልቅ ውለታ ከፍለዋል።በእንግሊዞች መሰሪ ቅስቀሳና ሴራ በሱዳን በኩል የማህዲስቶችን ወረራ በተደጋጋሚ ያከሸፉ ሲሆን በመጨረሻው ሙከራቸው ግን እንደ አንድ ወታደር መሃል ገብተው ሲዋጉና ሲያዋጉ ጦርነቱም በድል ለመጠናቀቅ ጫፍ ላይ ሲደርስ ከጠላት በኩል በተተኮሰ ጥይት ተመተው ሲወድቁ በሠራዊታቸው መካከል ድንጋጤ ተፈጥሮ ወደመበታተኑ አመራ።በዚህ መልኩ ለ17 ዓመት ኢትዮጵያን የመሩት መሪ አጼ ዩሃንስ አራተኛ መጋቢት 2 ቀን 1881 ዓም የታሪካቸው ፍጻሜ ሆነ።ደርቡሾቹም ከሸሹበት ተሰባስበው ቦታውን በመቆጣጠር የንጉሠ ነገሥቱን አንገት ቆርጠው የግዳይ ጥሎሽ አድርገው ለመሪያቸው አበረከቱለት።እስከ አሁን ድረስ የአጼ ዩሃንስ አራተኛ ጭንቅላት በካርቱም ሙዝዬም ውስጥ አንዱ የቱሪስት እይታ ሆኗል።አጼ ዩሃንስንና ከሳቸውም በፊት የነበሩት አገር ወዳዶች በበቀሉባት የትግራይ መሬት በእኛ ዘመን የተወለዱት አገር ጠልና ባንዳዎች የወያኔ ቡድን ስብስቦች ተግባር ከደርቡሾች ያልተለዬ የጠላትነት ታሪክ በመሆን ለዘለዓለሙ ሲወገዝ ይኖራል። የሌሎቹም እንዲሁ!
ከላይ እንዳዬነው የአገራችን መሪዎች የሥልጣን አያያዝ በጉልበትና በትውልድ ሃረግ ላይ የተመሰረተ መሆኑን የታሪኩ ስዕል ያስረዳናል።በመሆኑም ከአጼ ዩሃንስ ሞት በዃላም የመጣው ሥርዓት የተለዬ አይደለም።በጊዜው በጉልበትም በስልትም ብቁ ሆኖ የተገኘው በደጃዝማች ሳህለማርያም ሃይለመለኮት የሚመራው የሸዋ ንጉሣዊ አስተዳደር ሆነ።በአጼ ዩሃንስ መልካም ፈቃድ የሸዋ ንጉሥነታቸውን ያስከበሩት ሳህለማርያም ከቴዎድሮስና ከዩሃንስ የተረከቡትን አገር አንድ የማድረግና የማዘመን ተልእኮ በዘዴና በብልሃት እውን ለማድረግ ቆርጠው ተነሱ።በሃይል ብቻም ሳይሆን በጋብቻ ሰንሰለት እያስተሳሰሩ በቤተሰብ ግንኙነት በመጠቀም ሊነሱባቸው የሚችሉትን ሁሉ አለሳለሱት።ለራስ አርዓያ ዩሃንስ ሴት ልጃቸውን ዘውዲቱ ምኒሊክን በመዳር ከትግሬ በኩል የሚነሳባቸውን ተቃውሞ ሲያሶግዱ በወሎ በኩል የሚነሳውንም ቅራኔ ለወሎው ባላባት ለሙሃመድ አሊ በአጼ ዩሃንስ ክርስትና ተነስተው ራስ ሚካኤል ለተባሉት ሴት ልጃቸውን ወይዘሮ ሸዋረጋ ምኒሊክን በመዳር አለዘቡት።በዚሁ የትዳር ትስስር የልጅ ልጃቸው እያሱ ሚካኤል ተወለዱ።
አጼ ምኒሊክ ሰላምና አንድነትን ማጠናከር ብቻም ሳይሆን ኢትዮጵያ ወደተሻለ የእድገት ደረጃ እንድትደርስ ብዙ ለውጦችን ያመጡ መሪ ናቸው። ኢትዮጵያን ለማዘመን ያነሳሳቸው በወቅቱ የነበሩበት የዓለም የሥልጣኔ ደረጃ እንደሆነ አይካድም።የፈጠሩት ዓለም አቀፍ የግንኙነትና የዲፕሎማሲ ሰንሰለት ለሚያደርጉት ጥረት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል።በተለይም ብልህ አካሄዳቸው የውጩን ዓለም ለወዳጅነት ፉክክሩ በር የከፈተ ነበር።በተጨማሪ በቅርበት ከጎናቸው ሆነው በምክርና በሃሳብ የደገፏቸው ውድ ባለቤታቸው እመት ጣይቱ ብጡል እንደሆኑ አይካድም።
ለመሆኑ ከወይዘሮ ጣይቱ ብጡል ጋር እንዴት ሊተዋወቁና ሊጋቡ ቻሉ? ታሪኩ እንዲህ ነው።
ሳህለማርያም ከአጼ ቴዎድሮስ ጋር በጎንደር በነበሩበት ጊዜ ከወላጆቻቸው ጋር በደብረ ታቦር ይኖሩ ስለነበሩት ጣይቱ ብጡል ቁንጅናና ሙያ ይሰሙ ነበር።ምንም እንኳን ፍላጎት ቢኖራቸውም ሁኔታው ሳይፈቅድላቸው ቀርቶ ሳይገናኙ ወደ ሸዋ ይመለሳሉ። የጣይቱ ብጡል ወንድሞች ለምንሊክ አድረው ሸዋ መኖር ይጀምራሉ።በተደጋጋሚ ያደረጉት ትዳር ያልተዋጣላቸው ወይዘሮ ጣይቱ ወንድሞቻቸውን ለመጠዬቅ ወደ ሸዋ ይመጣሉ።ይህንን ዜና የሰሙት ንጉሥ ምንሊክና ባለሟሎቻቸው ሁኔታውን በመጠቀም ቤተሰባቸው ከጎጃም፣ከጎንደርና ከወሎ የተሳሰረውን ወይዘሮ በማግባት ሰላም እንዲፈጠር ከሚል ስልት በተጨማሪም ይመኟቸው የነበረውን ሴት ወይዘሮ በቅርበት በማግኘታቸው ተደስተው በጋብቻ ለመተሳሰር ወሰኑ።እንደ አገሩ ባሕል ታላቅ ወንድሞቻቸውን ልጅ ወሌ ብጡልንና ልጅ አሉላ ብጡልን በሽማግሌ አስጠይቀው ፈቃድ ስላገኙ በሚያዝያ 25 ቀን 1875 ዓም በአንኮበር መድሃኔ ዓለም ቤተክርስቲያን በአቡነ ማቴዎስ እጅ ሥጋዎ ደሙ ተቀብለው በቁርባን ተጋቡ።ከዚያ በዃላ 7 ዓመት አብረው ተቀምጠው በ1882 ዓም ንጉስ ሳህለማርያም ዳግማዊ አጼ ምኒሊክ ተብለው የንጉሠነገሥት ዘውድ በደፉ በሦስተኛው ቀን ወይዘሮ ጣይቱ ብጡልም ባቆረቧቸው ጳጳስ በአቡነ ማቴዎስ እጅ የሚገባቸውን ዘውድ ደፍተው እቴጌ ተባሉ።ከዚያን ቀን ጀምሮም እቴጌ ጣይቱ ብርሃነ ዘኢትዮጵያ እዬተባሉ ይጠሩ ጀመር። ሁለቱ ጥንዶች በመከባበርና በመመካከር ኢትዮጵያ አገራቸውን አስከብረው የኖሩ መሪዎች መሆናቸው የሠሩት ሥራዎች ይመሰክራሉ።
ያለፉት መሪዎች አገሪቱን አንድ የማድረግና የተበታተነውን ለመሰብሰብ የጀመሩትን የማዘመን ሥራ በደቡብ ፣በደቡብ ምዕራብና በምስራቅ በኩል የዘመነ መሳፍንት ቅሪት በሆኑት የከባቢ ባለሥልጣኖች ላይ እርምጃ በመውሰድ በውድና በግድ የኢትዮጵያን አንድነት አረጋገጡ።በባሪያ ንግድ የበለጸጉትን አባ ጅፋርን ከእኩይ ተግባራቸው እንዲታቀቡ በመጠዬቅና በማስጠንቀቅ የባርያ ንግድን በሕግ አገዱ።
የማንኛውም አገረ መንግሥት ምስረታ በሰላምና በፈቃደኝነት የተከናወነ አይደለም።በአውሮፓ በመሳፍንት አገዛዝ ተከፋፍለው ይኖሩ የነበሩ አካባቢዎችን በአንድ አገራዊ አስተዳደር ጥላ ስር ለማድረግ ብዙ ደም ፈሷል። ለአንድነት ፍላጎት ያለው ሲተባበር እምቢ ያለውም በሃይል ተደምስሶና በብዙሃኑ አንድነት ፈላጊው ሃይል አሸናፊነት የአንድ አገር አቀፋዊ ስርዓት የማስፈኑ ጥረት ሊሳካ ችሏል።በኢትዮጵያም የተከናወነው ከዚህ አይለይም። ከዳግማዊ አጼ ምኒሊክ በፊት የነበሩት መሪዎች ከአሁኑ የኢትዮጵያ ድንበር አልፈው ያስተዳድሩ እንደነበር የታሪክ ማስረጃዎች ይመሰክራሉ።ሌላው ቀርቶ አሁን የሕንድ ውቅያኖስ ተብሎ የሚጠራው በኢትዮጵያ ስም እንደነበረ የጥንት ካርታ ያሳያል።
የአገር ድንበር ጠንካራ መሪና መንግሥት ሲኖረው የሚሰፋ ለዚያ ያልታደለው ደግሞ ግዛትና ድንበሩ እዬተሸበሸበ በሌሎች ሲነጠቅ መኖሩ አይካድም።ኢትዮጵያም ከዚያ ውድቀት አላመለጠችም።በተለይም የምዕራባውያን ወረራ መካሄዱን ተከትሎ ብዙ አገሮች የነበራቸውን እያጡ በራሳቸው ስር የነበሩ እንደ አዲስ አገር እዬተፈለፈሉ መምጣታቸውን አሁን ያሉት አገራት ብዛት ማስረጃ ነው።ምንም እንኳን በውጭ ሃይሎች ሙሉ ለሙሉ ባትያዝም በእጅ አዙር ሴራ አገራችን የዳር ድንበሯ ተሸርሽሮ መሄዱ አይካድም።በምስራቁ ድንበሯ የእንግሊዝ የፈረንሳይና የጣሊያንን ወረራ ተከትሎ በርበራን ከዚያም ጅቡቲን ፣ከሰላሳ ዓመት ወዲህም የኤርትራን መገንጠል ተከትሎ ዘይላን፣ አዶሊስን፣ማሳዋና አሰብን የመሰሉ የወደብ በሮቿን ማጣቷ የዚያ ውጤቶች ናቸው።
በተለይም በዘመነ መሳፍንት ወቅት መካከለኛው መንግሥት ሲዳከም በዬቦታው ያሉ ባላባቶችና ጉልበተኞች ዕድሉን ተጠቅመው የራሳቸውን ግዛት ለመቆጣጠር ቻሉ።በዚህ ጊዜ ነበር ኢትዮጵያ አንድ አገራዊ ስርዓታዊ መንግሥትዋ የተዳከመው።በዚህ ውድቀት ውስጥ የገባችውን አገርና የተበታተነውን ሕዝብ ለመሰብሰብ ትግል ያደረጉት አጼ ቴዎድሮስ መሆናቸውን ከላይ በቀረበው ታሪካቸው የተገለጸ ሲሆን ያንን ህልማቸውን በተግባር ለመግለጽ የቻሉት ዳግማዊ አጼ ምኒሊክ ናቸው።አጼ ምኒሊክ የተበታተነውን ሰበሰቡ እንጂ አዲስ አገር አልፈጠሩም።ይህንንም የደቡብ ተወላጅ የሆኑት ፊታውራሪ መኮንን ዶሪ በሚከተለው መልኩ በእንግሊዝኛ “Benne The Land Of The Red Bull” በሚለው እርእስ በጻፉት መጽሃፍ በገጽ 80 ላይ እንዲህ ሲሉ መስክረዋል።”We all are Ethiopians,Menilik has united us.The Benne are the real and original Ethiopians.We intered into unity,but not to Ethiopianism.We were Ethiopians before,are Ethiopians now,and remain being Ethiopians in the future.”ይህ በአጭሩ ሲተረጎም ሁላችንም ኢትዮጵያውያን ነን፤ምኒሊክ ተነጥቀንና አጥተነው የነበረውን አንድነታችንን መልሶ አጎናጸፈን እንጂ ኢትዮጵያዊነትን አልሰጠንም።እኛ የቤኒ ተወላጆች የመጀመሪያዎቹና ቀዳሚዎቹ ኢትዮጵያውያን ነን፣ወደ አንድነት የመጣን እንጂ ወደ ኢትዮጵያዊነት የመጣን አዲሶች አይደለንም።ጥንትም ኢትዮጵያውያኖች ነበርን፣አሁንም ኢትዮጵያውያኖች ነን፣ወደፊትም ኢትዮጵያውያኖች ሆነን እንኖራለን።
የአጼ ምኒሊክንና የእቴጌ ጣይቱን መልካም ታሪክ ለማጉደፍ የማይሸረብ ሴራ፣የማይፈጠር ትርክት የለም።ኢትዮጵያን የመውረሩ ሙከራ ያልተሳካላቸው የውጭ ሃይሎች እንዲሁም የነሱ ደጋፊዎችና የከባቢ ባላባታዊ ስርዓት ተጠቃሚዎች በእልህና በቁጭት ተነሳስተው ያልሰሩትን በደልና ያልፈጸሙትን ጭካኔ ፈጸሙ በማለት በወንጀለኛ መሪነት የሚፈርጇቸው የዘመኑ ባንዳዎች የሚያሰሙት ጩኸት ቀላል አይደለም፤በዚህም ብዙ ወጣት ለማሳሳትና በጸረ ኢትዮጵያዊነትና በጸረ አንድነት ጎራ እንዲሰለፍ አድርገውታል። አሁን በሥልጣን ላይ ያለውም ቡድንና የሰፈነው አገዛዝ የዚያ ውጤት ነው።የጊዜ ጉዳይ ነው እዬጠራ ሲሄድና የአንድነት ጎራ ሲጠነክር ሁሉም የኢትዮጵያ ጠላት እንደ ጉም መብነኑ እንደ በረዶ መቅለጡ አይቀሬ ነው።ኢትዮጵያም ወደ ተሻለ የቀድሞ ክብሯ ትመለሳለች።
ዳግማዊ አጼ ምኒሊክ አገራቸውን አንድ ከማድረግም በላይ ለማዘመን ብዙ ደክመዋል።የነበሩበት ዘመን በዓለም ደረጃ በተለይም በአውሮፓ የለውጥና የሥልጣኔ ጮራ የፈነጠቀበት ጊዜ በመሆኑ ለሚያስቡት የእድገት ጉዞ መንደርደሪያ ሆኖላቸዋል።የከበርቴው ሥርዓት በውስጡ ይዟቸው የመጣው የኤኮኖሚና የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲሁም መንግሥታዊ አወቃቀር የምኒሊክን ቀልብና ልብ ለመሳብ ችሏል።ምንም እንኳን በዓይናቸው ባያዩትም በሚሰሙት በመመሰጽ በአገራቸው ውስጥ ተመሳሳይ የእድገት አቅጣጫ እንዲከሰት ፍላጎት ሊያሳድርባቸው ችሏል።ያንንም እውን ለማድረግ ከአውሮፓ መንግሥታት በተለይም ከእንግሊዝ፣ከፈረንሳይ፣ከጣሊያን፣ከጀርመንና ከሩስያ ጋር የወዳጅነት ግንኙነት መስርተው የንግድና የዲፕሎማሲ ስምምነት ይፈጽሙ ነበር።በዚያም ሳቢያ በኢትዮጵያ ውስጥ አዲስና የተለያዩ መስኮችና ተቋማትን ለመዘርጋት ቻሉ።
ከሁሉም መጀመሪያ ለወደፊቱ ሥራቸው አመቺ በሆነ ቦታ ላይ አስተዳደራቸውንና ቤተመንግሥታቸውን ማዋቀር እድሚያ ሰጥተው የአባታቸውን መንበር አንኮበርን ትተው ወደ ጥንቷ የንጉሥ ዳዊት ከተማ በነበረችው የበረራ ከፍተኛ ቦታ እንጦጦ ላይ ቤተመንግሥታቸውን አሠርተው ሥራቸውን ጀመሩ። ጥቂት እንደቆዩ በቀዝቃዛ ነፋሻነቱና ለመንቀሳቀስም አመቺ ስላልሆነ በተለይም የውጭ አገር መንግሥታት ተወካዮች እዬበዙ መምጣት፣የሕዝቡም ቁጥር መጨመር ቤተመንግሥታቸውን ወደ ሌላ ቦታ እንዲቀይሩ አስገደዳቸው። ከባቢውን በእይታቸው ሲቃኙ ከእንጦጦ ባሻገር ያለው ለጥ ያለ ሜዳማ ቦታ ስለማረካቸው ለባለቤታቸው ለእቴጌ ጣይቱ ብጡል ሲያማክሯቸው፣እቴጌም በከባቢው ውበት ተደንቀው አዲስ አበባ የሚለውን መጠሪያ ሰጡት።በአዘቦቱ በሽተኛ ከዬቦታው እዬመጣ የሚጠመቅበት ፊኒን እያለች የምትረጭ ፍልውሃ በህዝቡ አጠራር ፊኒኔ፣በአሁኑ ጊዜ በኦነጋውያኑ ፊንፊኔ በሚባለው ዙሪያ ከፍ ካለው ቦታ ላይ የአራት ኪሎውን ቤተመንግሥት በሚያምር ዘመናዊ መልክ አሠሩ። በዙሪያቸውም እንደማዕረጋቸው በቅደም ተከተል መኳንንቱንና መሳፍንቱን እንዲሁም ሠራተኛውና ጭፍራው ቤት እንዲሠራ ፈቀዱለት። ይህንን ተከትሎ የከተማዋ ግንባታ መልክና እቅድ እንዲይዝ ለመጀመሪያ ጊዜ በካርታና በካደስትራል የተደገፈ የቦታ ምዝገባ እንዲኖር አደረጉ።
በዚህ የእድገት ለውጥ ጉዞ ላይ የተቆረቆረችው የአዲስ አበባ ከተማ ከጊዜ በዃላ ሌላ ያልተጠበቀ ችግር ይዛ መጣች።ነዋሪው ሕዝብ ለማገዶ የከባቢውን ጫካ እዬጨፈጨፈ እርቃኗን አስቀራት።በዚህም የማገዶ ችግር ሊከሰት ቻለ።እንደ አሁኑ ዘመን ሌላ አማራጭ የለምና ችግሩን ለመቋቋም የታሰበው መፍትሔ ከተማዋን ወደ ሌላ ቦታ ለመቀዬር አንዱ አማራጭ ተደርጎ ቀረበ።ለዚያም ዓለም ገና ታጨች።ሆኖም ግን የውጭ አገር ተወካዮችና በንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩት ዳግም ለመንቀሳቀስ ስላልፈለጉ ለአጼ ምኒሊክ የተሻለ ምክር ይዘው ቀረቡ፤ያም የጫካ ልማት እንዲስፋፋ፣ከባሕር ማዶ ዛፍ በብዛት አስመጥተው እንዲተከል የሚል ነበር።ባሕር ዛፍ የሚለውም ስም ከዚያ በመነሳት ነው።በተደረገው እርብርቦሽ የዛፉ ፍሬ በአጭር ጊዜ መጥቶ በመተከሉ ሁለት ዓመት ሳይሞላው ባዶ የሆነው መሬት በቁጥቋጦ ተሸፈነ።ይህንን ፈተና ከተወጡት በዃላ ወደ ቀጣዩ የለውጥ ተግባር አመሩ።ያም እንደ አውሮፓያውያኑ መንግሥታቸውን በካቢኔ ደረጃ ማዋቀርና በሚኒስቴር የሥራ ክፍፍል ማድረግ ነው።በአገራችን ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜም የሚከተሉት ባለሥላጣናት የሚኒስቴርነት ሥልጣን ተሰጣቸው።
1 አፈንጉስ ነሲቡ የፍርድ ሚኒስቴር
2 ፊታውራሪ ሃብተጊዮርጊስ የጦር ሚኒስቴር
3 ሊቀመኳስ ተሰማ ያገር ግዛት ሚኒስቴር
4 ነጋድራስ ሃ/ጊዮርጊስ የውጭ ጉዳይና የንግድ ሚኒስቴር
5 በጅሮንድ ሙሉጌታ የገንዘብ ሚኒስቴር
6 ከንቲባ ወ/ጻድቅ የእርሻ ሚኒስቴር
7 አለቃ ገ/ ሥላሴ የጽሕፈት ሚኒስቴር
8 አዛዥ መታፈሪያ የግቢ ሚኒስቴር
9 ቀኛዝማች መኮንን ተወንድበላይ የሥራ ሚኒስቴር
10 ልጅ በዬነ ይመር የስልክና ፖስታ ሚኒስቴር
በተጨማሪ ለትምህርት ሚኒስቴር ቦታው ቢዘረጋም ሰው አልተመደበበትም ነበር።
ዳግማዊ አጼ ምኒሊክ በሥልጣን ዘመናቸው የተበታተነችዋን ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ ከሚያደርጉት ጥረት ጋር ጎን ለጎን ለማዘመንም የተለያዩ የለውጥና የእድገት ሥራዎችን አከናውነዋል፣አዳዲስ መስኮችንም ዘርግተዋል።ከጅቡቲ -አዲስ አበባ-አባይ-ከዚያም በደቡብ በኩል ወለጋና ከፋ የሚደርስ የባቡር መስመር ለመዘርጋት የጀመሩት ሥራ በአድዋ ጦርነት ምክንያት በግማሽ ማለትም ከጅቡቲ -አዲስ አበባ በተዘረጋው ሃዲድ መስመር ብቻ እንዲገደብ ሆኗል።ሌሎቹ ድንቅዬ ዘመናዊ ሥራዎቻቸውን ከዓመታቸው ጭምር የሚከተለው ዝርዝር ያመለክታል።
በ1835- ወፍጮ፣በ1882 ስልክ፣በ1886 ፖስታ፣ በ1886 ባሕር ዛፍ፣በ1886 ገንዘብ፣በ1886 የውሃ ቧንቧ፣በ1887 ጫማ፣በ1887 ድር፣በ1887 የሙዚቃ ት/ቤት፣በ1887 የጽህፈት መኪና፣በ1889 ኤሌክትሪክ፣በ1889 ዘመናዊ ሕክምና፣በ1889 ሲኒማ፣በ1889 የሙዚቃ ሸክላ፣በ1889 ቀይ መስቀል፣በ1890 ሆስፒታl፣በ1893 ባቡር፣በ1893 ብስክሌት፣በ1896 መንገድ፣በ1897 ፍልውሃ፣በ1898 ባንክ፣በ1898 ሆቴል፣በ1898 ማተሚያ፣በ1898 ላስቲክ፣በ1899 amራዊት ጥበቃ፣በ1899 ጥይት ፋብሪካ፣በ1900 ጋዜጣ፣ በ1900 አውቶሞቢል፣በ1900 የሚኒስትሮች ሹመት፣በ1901 ፖሊስ ሠራዊት፣በ1904 የመድሃኒት መሸጫ ሱቅ(ፋርማሲ)
እነዚህን ሥራዎቻቸውን የታዘቡ ከውጭ አገር የመጡ እንግዶች፣ታሪክ ጸሃፊዎችና ዬዬመንግሥታቱ ተወካዮች ስለ አጼ ምኒሊክ ችሎታና ደግነት፣ዬዬራሳቸውን ምስክርነት ሰጥተዋል። በተለይም የአገራቸውን አንድነት ለማስከበር፣የተበታተነውን ሕዝብ ለመሰብሰብና ከከባቢ ጨቋኞች ለማላቀቅ ያደረጉትን ተጋድሎ በሚገባ መዝግበውታል። ከነዚያም ውስጥ ቤኪንግ ሃምና ሃንቲንግ ፎርድ “Some records of Ethiopia,and Gallas of Ethiopia”በሚሉ እርእሶች በጻፏቸው መጽሃፎች ላይ እንዲህ ብለዋል።ምንሊክ መንግሥታቸውን ለማጠናከር ወደ ደቡብ ያገራቸው ክፍል ያደረጉት ጉዞ አውሮፓውያን ለአንድነት ካደረጉት የማይለይ ብሎም በተሻለ መልክ ብዙ ደም ሳይፈስ የተከናወነ ነው በማለት ገልጸዋል።የታሪክ ምሁሩ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስም መንግሥትና መሬት በኢትዮጵያ(Land and State in Ethiopia)በሚለው መጽሃፋቸው ሄነሪ ብላንክ የተባለ አገር ጎብኚ(አሳሽ)የጻፈውን እንዲህ አስቀምጠውታል። “ በተደረገው አገር የማቅናቱ ዘመቻ የጋላውን ንብረት ከማቃጠልና ከመዝረፍ ፈንታ በክብር ይዘው እንደ ሌላው የአማራ፣የትግሬ፣የአዳል፣የሶማሌ፣የጊሚራ፣የወላይታ ሕዝብ የሚጠበቅበትን ግብር እዬሰጠ እንዲኖር ከማድረጋቸውም በላይ የባላባቱን ሥልጣን አልተጋፉትም።በዚህም የጋላው ባላባቶችና ሕዝብ በደስታ የምኒሊክ አጋር በመሆን ወደ ሌላው ቦታ የሚደረገውን ዘመቻ ከመሳተፍም በላይ የመምራትም ሚና ተጫውተዋል።”በማለት መስክሯል።
የእንግሊዝ ወታደር ሻለቃ የነበረውም አውስቲን “የጋላ ወንድ ባላባቶች ብቻም ሳይሆኑ የጋላ ሴቶችም በቤተሰብ ደረጃ ይገባቸው የነበረው የመሬት ባለቤትነት መብትና የሥልጣን ቦታ የተከበረላቸው በምኒሊክ ጊዜ ነው ሲል የምስክር ቃሉን ሰጥቷል።
ይህ ሁሉ ማስረጃ የሚያረጋግጠው ምኒሊክ ምን ያህል ደግና እሩህሩህ ፍትሐዊም መሪ እንደነበሩ ነው።ያንንም ተከትሎ ሕዝባቸው እምዬ ምኒሊክ በሚለው አጠራር ሲያቆላምጣቸው መኖሩ ለአሁኑ ትውልድ ተርፎ የታሪክ ቅብብሎሽ ሆኗል።በሌላው በኩል አሁን ለጭቁን ሕዝብ ቆመናል የሚሉ በተለይም የኦሮሞ ጎሳ ተወላጆች የሆኑ ምሑራን ምኒሊክን ጡት ቆራጭ፣ጨካኝና አረመኔ አድርገው ከመሳላቸውም በላይ የናዚ ባህሪያትን ለመስጠት ደፍረዋል።ይህ ማለት ምኒሊክን የተቀበለ፣አድዋም ላይ ዘምቶ ለድል የበቃውን ጀግና የኦሮሞ ልጆች ጎበና ዳጨን፣ባልቻ አባ ሳፎን(ነፍሶን)፣ሌሎቹንም አርበኞች ሁሉ የጡት ቆራጭና የናዚ መሪ ተከታይ ናቸው ብሎ መክሰስና መወንጀል ይሆናል።በዚህ ልኩ ጣልያን እንኳን ምኒሊክን አልመደበም።አጼ ምንሊክ እንደ አገር ጠል የኦሮሞ ተገንጣዮች አባባል ቢሆኑ ኖሮ ከጎናቸው የተሰለፉትና የተዋጉት የአማራ፣የትግሬ፣የኦሮሞ፣የጉራጌ፣የወላይታ፣የሶማሌ፣የአፋር — ወዘተ ባላባቶች የድልና የሥልጣን ባለቤት ባልሆኑም ነበር።ሰው እንዴት አገሩንና ነጻነቱን ጠልቶ ባርነትን ይመርጣል?ሌላው ጭቁንና የቕኝ ግዛት ሰለባ የሆነው የተለያዩ አገሮች ሕዝብ ለምንሊክ ያለውን ክብርና ፍቅር እያዬ እንዴት ኢትዮጵያዊ የሆነ፣በኢትዮጵያ ተወልዶ አድጎ፣ተምሮ ለቁም ነገር የበቃ ዜጋ በአድዋ ድል መሪ በምኒሊክ ላይ ጥላቻ ያድርበታል?ጥላቻው ለምን የጣልያኖች ባሪያ አልሆንኩም በማለት ነው ወይስ የነጻነት አለርጅክ ከመሆን?ለኢትዮጵያ ለመዋጋት የሌላው አገር ተወላጅ በተሽቀዳደመባት አገራችን ከምን ቢወጡ ነው የራሷ ዜጎች በጠላትነት የተነሱባት?
ዳግማዊ አጼ ምኒሊክና እቴጌ ጣይቱ አገራቸውን ከወራሪ ጠላት አድነው ቀድሞ የጀመሩትን የማዘመን ሥራ በመቀጠል የሚችሉትን ሁሉ አድርገዋል።በተለይም ከአድዋ ድል በዃላ ዝናቸው ታውቆ ከኢትዮጵያ ጋር ወዳጅ ለመሆን ሁሉም ጥረት ያደርግ ነበር።
ዞሮ ዞሮ ከቤት ኖሮ ኖሮ ከመሬት ይባላልና ዳግማዊ አጼ ምኒሊክ ሥራ በቃኝ ብለው ሳያርፉ፣ባልጠበቁት ሕመም ተይዘው አልጋ ላይ ለመዋል ተገደዱ።በ1900 ዓም የጀመራቸው ህመም ክንዳቸውን አጠፈ፣አንደበታቸውንም ቆለፈ።ሃዘንና ጭንቀት በባለቤታቸውና የቅርብ ባለሟሎቻቸውን ብሎም በቤተመንግሥቱ ላይ ጥላውን ጣለ። ህይወታቸውን ለማትረፍ በዘመናዊ ሕክምና፣ በባህላዊ መንገድም፣በጠበልና በጸሎትም የሚቻለው ተደረገ፤ግን እዬባሰባቸው እንጂ እዬተሻላቸው አልመጣም።
ቀደም ሲል ከእሳቸው ቀጥሎ የዘውዳቸው ወራሽ እንዲሆን የመረጡት የሴት ልጃቸው የወይዘሮ ሸዋረጋ ምኒሊክ ልጅ የሆኑትን ልጅ እያሱ ሚካኤልን ነበር።እቴጌ ጣይቱ ባላቸውን እያስታመሙ የማስተዳደሩን ሥራ ደርበው በመሥራታቸው በብዙዎቹ መኳንንት በኩል ምቾት አልፈጠረም።ሙሉ ለሙሉ ሥልጣኑን ለመቆጣጠር ያላቸውን አዝማሚያ የተረዱትና የሥልጣናቸው ነገር ያሳሰባቸው መኳንንቱ ውስጥ ውስጡን አድማ ሲመቱ ቆይተው ይፋ በመውጣት መጋቢት 12 ቀን 1902 ዓም እቴጌ ጣይቱ ከመንግሥት ሥልጣን እንዲርቁ ተወሰነባቸው።በትረሥልጣኑም ለወጣቱ እያሱ ሚካኤል ተላልፎ ከሞግዚታቸው ከራስ ተሰማ ጋር ሆነው እንዲያከናውኑ ተወሰነ።ከጥቂት ጊዜ በዃላ ሞግዚቱ እራስ ተሰማ በድንገት ሲሞቱ ወጣቱ ንጉሥ የማንንም ሞግዚትነት አልፈልግም በማለት ቦታውን ለመያዝ ይራኮቱ የነበሩትን ሁሉ ኩም አደረጓቸው።ከዚያም ባለፈ እናንተ ሰውነታችሁ ከብዷል፣ሰብታችዃል፣ አርጅታችዃልም፤ እሩጣችሁ አታመልጡ ወይ አሳዳችሁ አትይዙ፣የተመደበላችሁን ብቻ ይዛችሁ ተቀመጡ፤ እንደወትሮው የንጉሥ ሞሰብ(ማድ) ከባችሁ መብላት አትችሉም ብለው ካጠገባቸው አባረሯቸው።በዚህም የተነሳ በወጣቱ ንጉስ ላይ ሴራ መጠንጠን ተጀመረ።
በዚህ ሁኔታ ውስጥ አጼ ምኒሊክ ለአምስት ዓመታት ከቆዩ በዃላ በተወለዱ በ69 ዓመት ከአራት ወር ዕድሜያቸው በ1907 ዓም ታህሳስ 3 ቀን አርፈው እራሳቸው ባሠሯት በባእታማርያም ቤተክርስቲያን ተቀበሩ።እቴጌ ጣይቱም በ1908 ዓም እንደ አያት ተንከባክበው ባሳደጉት በእንጀራ ልጃቸው ልጅ በአልጋወራሽ እያሱ ትእዛዝ ከቤተመንግሥት ወጥተው እንጦጦ ቤታቸው በግዞት እንዲቀመጡ ተወሰነባቸው።በ1910 ዓም መጀመሪያ ላይ እንደዋዛ የጀመራቸው ህመም ጠንቶባቸው የካቲት 4 ቀን 1910 ዓም በተወለዱ በ78 ዓመታቸው አረፉ።በቤተመንግሥቱ የደስታ ይሁን የሃዘን 25 ጊዜ መድፍ ተተኮሰ።
በልጅ እያሱ የአመራር ዘዴና አስተሳሰብ ያልተደሰቱት በተለይም ዙፋኑን ከበው ግብር መብላት የለመዱት መኳንንትና መሳፍንት በጠነሰሱት ሴራና ቅስቀሳ በመስከረም 17 ቀን 1909 ዓም ከሥልጣናቸው ተወግደው ቦታው ሚያዝያ 22 ቀን 1868 ዓም ከእናታቸው ከወይዘሮ አብችውና ከአባታቸው ከአጼ ምኒሊክ ለተወለዱት ለወ/ሮ ዘውዲቱ ምኒሊክ ተላልፎ ንግሥተ ነገሥት ተብለው ዘውድ ጫኑ።የምኒሊክ አክስት የልጅ ልጅ የሆኑትም ተፈሪ መኮንን ራስ ተብለው የአልጋወራሽነቱን ቦታ ያዙ።
ይህንን ሴራ ያልተቀበሉት የልጅ እያሱ አባት ንጉስ ሚካኤል ተከታዮቻቸውን አስከትለው በሰገሌ ሜዳ በጦር ሃይል ቢታገሉ ሊሳካላቸው አልቻለም።በመጨረሻው ተይዘው የተፈሪ መኮንን እስረኛ ሆኑ።ልጃቸውም እያሱ ሚካኤል በዬቦታው በግዞት ሲንከራተቱ ቆይተው በማይታወቅ መንገድ እስር ላይ እንዳሉ ሞታቸው ተሰማ።በ1909 ዓም የንግሥተ ነገሥትነት ዘውድ የጫኑት ዘዲቱ ምኒሊክም ለ13 ዓመት ከ6 ወራት ኢትዮጵያን በምልክትነት ሲመሩ ቆይተው ባደረባቸው ህመም መጋቢት 24 ቀን 1922 ዓም አርፈው ባባታቸው መቃብር ቤት ተቀበሩ።በሞቱ በ7ኛው ወር የንግሥናው ሥልጣን ለአልጋ ወራሹ ለራስ ተፈሪ መኮንን አልፎ በጥቅምት 23 ቀን 1923ዓም ሃይለሥላሴ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ተብለው ዘውድ ጫኑ።
ተረኛው አጼ ሃይለሥላሴ አጼ ምኒሊክና ሌሎቹ የጀመሩትን አገር የማዘመን ተግባር በስፋት ቀጥለውበት፣አቅም በፈቀደው ብዙ ለውጦችን በማድረግ የሙያ መስኮችንም ከፍተዋል። ትምህርት እንዲስፋፋ አድርገዋል።የእኛም ትውልድ የዚያ ትሩፋት ተካፋይ ነው።አሁን አገር ለመበታተን ግንባር ቀደም የሆኑትም ጸረ ኢትዮጵያ የሆኑት ቡድኖች በትምህርት ዓይናቸውን የከፈቱት በአጼ ሃይለሥላሴ ዘመን ነው።ለአፍሪካ አንድነት መመስረት ታላቁን ድርሻ የወሰዱ ፣በዓለም አቀፍ ደረጃም እውቅናና ክብር አትርፈው የኖሩ መሪ ናቸው። በአገራቸው በተንሰራፋው ድህነትና ዃላ ቀርነት ላይ የተፈጥሮ ዱላ ተጨምሮበት ለአገዛዛቸው አደጋ ይዞ መጣ።በተለይም ለዘመናት የሰፈነው ከባላባታዊ ስርዓት ያልተላቀቀው የመሬት ስሪት ጥያቄ መልስ ባለማግኘቱ ባመጣው ችግር ላይ ድርቅ ተጨምሮበት እርሃብ የብዙ ዜጎችን ህይወት ቀጠፈ፤ በዓለም ደረጃ የተከሰተው ቀውስና የዋጋ ግሽበት የመውደቂያቸውን መንገድ ጠራጊ ሆነ።ካቢኔ ቢቀያይሩ ለችግሩ መልስ ጠፋ፤ሕዝቡ በተለይም የተማረው ክፍል አሻፈረኝ አለ፤የመንግሥት ሠራተኛው ፣ወታደሩ ሳይቀር የተቃውሞ ጎራውን ተቀላቀለ፣በዚህ ላይ ለመገንጠል በሰሜኑ በኩል የሚካሄደው ጦርነት ችግሩን ያባባሰ ቤንዚን ሆነ።በአጠቃላይ የ44 ዓመት የንጉስነትና 13 ዓመት የአልጋወራሽነት በጠቅላላው የ57 ዓመት በላይ ለቆዬው ለአጼ ሃይለሥላሴ ሥርዓተ መንግሥቱ መፍረክረክና መውደቅ ምክንያት ሆነ።ያም ለወታደራዊ አምባ ገነን ቡድን ዕድል ሰጠና ንጉሡን ጨምሮ ብዙ የተማሩ ኢትዮጵያውያንን በግፍ ለጨፈጨፈ የ17 ዓመት ወታደራዊ አምባገነን መንግሥት አገሪቱም ሕዝቡም ተዳረጉ።17 ዓመት የጭቆና አገዛዝ ለአገሪቱ ምንም የተሻለ ነገር ሳያመጣ በታሪኳ ታይቶ ተሰምቶ በማይታወቅ መልኩ መንግስቱ ሃ/ማርያም የተባለ ወንጀለኛ ከውጭ ሃይሎች በተለይም ከአሜሪካኖች ጋር ተመሳጥሮ ያገሪቱን ካዝና መዝብሮ በጦር ሜዳ ላይ የተሰማራውን ወታደር በትኖ አገሪቱንና ሕዝቡን በቀጣይ ለባሰ ጸረ አንድነት ለሆነው የጎሰኞች ስብስብ አስረክቦ አውሮፕላን ጠልፎ ወደ ዚምባብዌ ፈረጠጠ።በወያኔ በሻብያና ኦነግ ጥምረት የሥልጣን ክፍተት ያገኘው ጸረ አንድነትና ጸረ ኢትዮጵያ የሆነው ቡድን እርስ በርሱ እዬተባላ ሕዝብም እያባላ ላለፉት 33 ዓመታት ባሰፈነው ጎሰኛ ሥርዓት መከራ ውስጥ ተዘፍቀን እንገኛለን።
ዘመን ሄዶ ዘመን ሲተካ በየዘመኑ አዲስ ትውልድና አዲስ አስተሳሰብ መከሰቱ የሕብረተሰብ ሳይንስ ያረጋግጣል።ከቶም ቢሆን የነበረውና ያለው ዘለዓለማዊ ሆኖ አይቀርም።ይለወጣል።ለውጡን የተሻለ ወይም የከፋ የሚያደርገው የትውልዱ ብስለትና ብቃቱ ነው።አሁን ባለንበት ዓለም የተዘበራረቁ አስተሳሰቦች ብሎም የጥቅም ሽኩቻዎች የሰፈኑበት ወቅት ላይ እንገኛለን።የመኖር ወይም ያለመኖር ፈተናዎች ተጋርጠውብናል።እነዚህን ፈተናዎች ለማለፍ የችግሩን ምንጭ አውቆ መፍትሔ መፍጠር ነው።ድህነትም ሆነ የሰላም መናጋት የሥርዓቶች ውጤቶች እንጂ የተፈጥሮ ክስተቶች አይደሉም።የተፈጥሮ ክስተቶችም ቢኖሩ የመቋቋም ብልሃትና ዘዴ እንዲኖር የሰፈነው ሥርዓት ሃላፊነት አለበት።
ስለሆነም በተለያዩ ጊዜያቶችም ሆነ አሁን አገራችንን ለተለያዩ ችግሮች ብሎም ያለመኖር አደጋ ላይ የጣላትን የጎሰኞች ሥርዓትና ዓለም አቀፍ አጋሮቹን መታገልና ማሶገድ ፣ዳግመኛም ጉልበተኛ እዬተቀያዬረ የሚፈነጭበትን ዕድል ለዘለቄታው የሚያሶግድ ሕዝባዊ አገር ወዳድ ሥርዓት እንዲሰፍን ከማድረግ ሌላ አማራጭ የለንም።ሕዝባዊ ሥርዓቱም ከሌላው የዓለም ሕዝብ በተለይም ከአፍሪካ ጎረቤቶቻችን ጋር በሰላምና በወዳጅነት መኖር የሚያስችለውን ግንኙነት የሚከተል እንጂ በባርነትና በተላላኪነት ለውጭ ሃይሎች የሚያጎበድድ ፣ብሔራዊ ክብሩን የሚሸጥ ወይም አሳልፎ የሚሰጥ መሆን አይገባውም።ያንን የኢትዮጵያን አንድነትና ነጻነት የሕዝቧንም መብትና እኩልነት፣ማስከበር የሚችለውን ሥርዓት ለመፍጠር ሁሉም አገር ወዳድ ጎጠኝነትንና ጎሰኝነትን ተጠይፎ በአንድነት ተሰልፎ መታገል አለበት።የተጀመረው የሕዝብ ትግል ፈሩን እንዳይለቅና ለድል እንዲበቃ መቆጣጠር ተገቢ ነው።
የአማራ ፋኖ ትግል ብሶት የወለደው ለህልውና የሚደረግ ትግል በመሆኑ ሁሉም ፍትህ አፍቃሪ ሊደግፈው ይገባል።ከዚያ ባለፈ ግን አማራውን የሥልጣን ባለቤት እናደርጋለን የሚለው አዝማሚያ ስርዓቱና የስርዓቱ ደጋፊዎች ለሚነዙት ፕሮፓጋንዳ ማጠናከሪያ ከመሆኑም በላይ ሌላው ኢትዮጵያዊ እንዲርቀው ስለሚያደርገው መጠንቀቅ ተገቢና አስፈላጊ ነው።ከእንግዲህ በዃላ ኢትዮጵያ የጎሳ ፖለቲካና የአምባገነኖች መጫወቻ መሆን የለባትም። ለሰላሟና ለእድገቷ ብሎም ለህዝቧ አንድነት በዘመናዊ ፖለቲካ ፍልስፍና የሚመራ ስርዓት የሰፈነባት አገር መሆን አለባት። ቀጣዩም የአድዋ ድላችንም በዚህ ዙሪያ የሚደረገው ትግል ውጤት ነው።
ለዳግማዊ አድዋ ድል እንሰለፍ! ኢትዮጵያ በአንድነትና በነጻነት ለዘለዓለም ትኑር!
አገሬ አዲስ
ታሪክ ይናገር!
በአገራችን በኢትዮጵያ ላለፉት 33 ዓመት ለሰፈነው የወያኔና ኦነግ መራሹ የጎሰኞች ስርዓትና የአገር መበታተኑ ስጋት ታሪካዊ መነሻው ምንድን ነው?ለሚለው ጥያቄ ከላይ ለማሳዬት እንደተሞከረው የውጭ ሃይሎች ለመውረር ሲያስቡ የሕዝቡን አንድነትና ጠንካራ ጎን መስበር ስለሚኖርባቸው አንዱን በሌላው ላይ እያስነሱ ፣አንዱን እዬደገፉ በክፍተቱ መግባት እንደሆነ ታዝበናል፤ያንንም ከራሳቸው አንደበት ከተነገሩት ውስጥ የሚከተሉትን እናገኛለን
ማስታወሻ
አሁን ኦሮሞ በመባል የሚታወቀው ጎሳ ቀድሞ ጋላ ይባል እንደነበረና ከ 1967 ዓም ወዲህ ግን በደርግ ኦሮሞ በሚለው መጠሪያ እንደተቀዬረ ማወቅ ተገቢ ነው።ከዚያ በፊት በዚሁ ጋላ በሚለው ስም እንደሚታወቅና ታሪኮቹም የተጻፉት በዚሁ ስያሜ እንደነበር ልብ ማለት ያስፈልጋል። ጋላ የሚለው ቃል በአክራሪያኑ እንደሚባለው በአማራው የተሰጠ መጥፎ ትርጉም ያለው ቃል ሳይሆን በራሱ በጋልኛ (ኦሮሞ) ቋንቋ “ግባ” ማለት እንደሆነ መታወቅ አለበት።
ከዛሬ 189 ዓመት በፊት የእንግሊዝ ምክር ቤት አባል የነበረው ሎርድ ማኩላይ ለእንግሊዝ ፓርላማና መንግሥት ከዚህ በታች ያለውን ምክር ሰጥቶ ነበር።
የምክሩ ይዘት በአጭሩ ሲተረጎም
“አፍሪካን ከላይ እስከታች ፣ከዳር እስከዳር ዞሬ አይቻለሁ።ሆኖም ግን እንደዚህ ለማኝና ሌባ ያላዬሁበት፣ የከፍተኛ ችሎታና ስብእና ባለቤት የሆነ ሕዝብ የሚኖርበት አገር አላዬሁም።እንዲህ ያለውን አገር አንበርክኮ ለመያዝ በቀላሉ ይቻላል ብዬ አላስብም።የግድ የአገሪቱ ጀርባ አጥንት የሆነውን መንፈሳዊና ባህላዊ ይዞታዎችን መስበር፣ የጥንታዊና ባህላዊ የትምህርት ተቋሟን በማጥፋት በእኛ ለውጠን የውጭ በተለይም የእንግሊዞች የሆነ ሁሉ መልካምና የተሻለ ነው ብሎ በማመን የራሱን ክብረሞገስ ዋጋ ቢስ ነው ብሎ አውልቆ እንዲጥልና እንደምንፈልገው የበታችነታቸውን ተቀብለው እንዲኖሩ ከማድረግ ሌላ መንገድ የለንም።
ይህ ምክር ከተሰጠ ከ137 ዓመት በዃላ የአሜሪካን መንግሥት የውጭ ጉዳይ ሚንስትር የነበረውና በቅርቡ በመቶ ዓመት ዕድሜው የሞተው ዶር ሄንሪ ኪሲንጀር የሚከተለውን የዕቅድ ምክር ለመንግሥቱ አቅርቧል።
ከላይ እንደተመለከትነው በአገራችን ላይ የመበታተኑ አደጋ የተጠነሰሰው በቅርቡ ሳይሆን ዘመን የተሻገረ መሆኑን ነው።ሁኔታውን አዲስ የሚያደርገው ግን ይህ የውጭ ሴራና እቅድ በራሷ ማህጸን የበቀሉ ያስተማረቻቸው ልጆቿ በተግባር ለመተርጎም ጥረት ማድረጋቸው ነው።
የራስን ቋንቋ፣ባሕልና እምነት ጠልቶ በነጮቹ ለውጦ እራስን የበታች አድርጎ የማዬቱና አገር የማፈራረሱ እቅድ አሁን ላይ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል።ይህንን ውድቀት ለመከላከል ሁሉም አገር ወዳድ ብቻም ሳይሆን ባርነትን የሚጠላና የሚጠዬፍ ሁሉ በአንድነት ቆሞ መታገል ብቻም ሳይሆን ማሸነፍ አለበት።
አሁን የአገራችንን ህልውና አደጋ ውስጥ የከተተው የኦሮሙማ ህሳቤ እንዴትና መቼ እንደመጣ የውጭና የአገር ውስጥ ምሁራን የታሪክ ጥናት ዋቢ በማድረግ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል
በቅርቡ ዶ/ር ዮናስ ብሩ በተባሉት ምሁር በእንግሊዝኛ ቋንቋ “Tribalism Primitizes and Zoombifies the Human mind and stifles the soul” በሚል እርእስ የጻፉት ትንተና በከፊል በአማርኛ ሲተረጎም የሚከተለውን ይመስላል።
በኦሮሙማ የፖለቲካ ፍልስፍና “ ከሌላው በሃይል ነጥቄ የወሰድኩት እስከወዲያኛው ድረስ ሕጋዊ ንብረቴ ነው፤ከእኔ ተነጥቆ የተወሰደው ግን ኢሰብአዊ ድርጊት ስለሆነ መወገዝ አለበት“በሚለው ፍትሕ አልባ ትርክት ላይ ይመሠረታል።በዚህም አይቆምም ሌላውን እዬወረሩ መስፋፋቱን በዚህ መልኩ ፈጽመውታል ይላሉ።”በሞጋሳ የመስፋፋት ወቅት የጋላ ጦረኞች ሌላውን መውረራቸው ሲሆን ከነዚያም ውስጥ ወሎ ብለው የሰዬሙት የአማራው መኖሪያ አንዱ ነው። በ1924 ዓም የዛሬ መቶ ዓመት መሆኑ ነው የታተመውይ የሮያል አፍሪካን ሶሳይቲ የሚባለው ጋዜጣ በቅጽ 23 በቁጥር 90 ላይ ሂደቱን እንዲህ አስፍሮታል። “የጋላ ጋዳ የጦር ስልት እንኳንስ አሁን ይቅርና በጊዜውም ቢሆን በጣም ጭካኔ የተመላበት፣ዘግንኛና ሰቅጣጭ ድርጊቶች የተፈጸሙበት የቆሰለና የተማረከም ብቻ ሳይሆን የሞተ ሳይቀር ሰውነቱ የተቆራረጠበት ነው” በማለት ድርጊቱን አጋልጦታል።ፔድሮ ፓዬዝ የተባለውም ጸሓፊ የጋዳን ወራሪዎች እንዲህ ሲል ገልጿቸዋል። “ ጋሎች ብዙ ሕዝብ አርደዋል፤በጣም ዘግናኝ ጭካኔም ፈጽመዋል፤ወንድ የሆኑትን ህጻናት ሳይቀሩ ቆራርጠዋል፤የረገዙ ሴቶችንም ሆድ ሰንጥቀው ጽንስ አውጥተው ጥለዋል፤ማህበረሰቡ በፍርሃትና በሽብር ተንበርክኮ እንዲገዛቸው አድርገዋል”በማለት በታሪክ የምስክርነት ቃሉን አስፍሯል።በዚህ ላይ ያለንበት ወቅት የኦሮሙማው ፍልስፍና ወኪልና ጠበቃ የሆነው ሙሃመድ ሃሰን የተባለው ምሁር?ሳይቀር እንደሚከተለው የኦሮሙማን ጭካኔ ገልጾታል።“የጋዳ ጦረኞች በሌሊት ስለሚወሩና ስለሚያጠፉ ሰይጣኖች ናቸው፤የተሸነፉትም ሆኑ ያጎበደዱት የበታች ሆነው ያድራሉ እንጂ ከዋጣቸው ወራሪ ጎሳ እኩል አይታዩም።ለሽያጭና ለስጦታ የሚቀርቡ ዕቃዎች እንጂ እንደ ሰው አይቆጠሩም።ያልተወረረው ሲወረር ወንዶች ይገደላሉ ፣እንስሳትም ይዘረፋሉ።የሞጋሳ ዓላማ ሶስት ናቸው፤እነሱም ቦታ መቀማት፣ህጻናትንና ሴቶችን ወስዶ ቋንቋቸውን ፣ባሕላቸውን፣እምነታቸውን እንዲጥሉ ስማቸው ሳይቀር ተለውጦ የወራሪውን ማንነት እንዲቀበሉ በማስገደድ ሙሉ ለሙሉ ማንነታቸውን መግፈፍ።ይህንንም በኦሮሙማ አባገዳ መሪነት በሚከናወን ስነስርዓት ላይ የምትዋጋውን እዋጋለሁ፤የምትጠላውን እጠላለሁ፤የምትወደውን እወዳለሁ፣በሄድክበት እሄዳለሁ፣የምታሳድደውን አሳድዳለሁ በሚል የመሃላ ቃል ይቋጫል።ሰውነታቸውንም መንፈሳቸውንም በኦሮሙማነት ያላጸኑ ተጠራርገው ይወገዳሉ” በማለት በኩራት ገልጾታል።
ሌንጮ ባቲ የተባለውም የኦነግ መስራችና የአገዛዙ ሹመኛ “የውሸት ትርክት በመፍጠርና በመንዛት ትግላችንን ለመገንባትና ለአሁኑ ደረጃ እንዲበቃ አድርገነዋል”በማለት ብዙዎቹን ወጣቶች በማሳሳት በኢትዮጵያና በኢትዮጵያውያን ላይ ያሳደሩትን የጥላቻ ዘመቻና ያስከተለውን ጥፋት ይፋ አድርጎታል።
ሌላው በፕሮፌሰር ግርማ ብርሃኑ የቀረበው የታሪክ ማስረጃ የሚከተለው ነው።
The Ethiopians: An introduction to country and people
By Edward Ullendorff
Page 76 “The gallas had nothing to contribute to the civilization of Ethiopia.They possessed no material or intellectual culture,and their social organization was at a far lower stage of development than that of the population among whome they setteled.They were not the only cause of the depresse state into which the country now sank,but they helped to perpetuate a situation from which even a physically and spiritually exhausted Ethiopia might otherwise have been able to recover far more quickly.”
ይህም ባጭሩ ሲተረጎም “ ጋላዎች ለኢትዮጵያ ሥልጣኔ ምንም ያበረከቱት የለም።ምንም አይነት ምሁራዊም ሆነ ቁሳዊ ባሕል የላቸውም።ያላቸው ማህበራዊ አደረጃጀትም ቢሆን ከሰፈሩበት ሕዝብ በጣም ባነሰ ደረጃ ላይ የሚገኝ ነው።አገሪቱን አሁን ከገባችበት ማጥ ውስጥ መክተታቸውም ብቻ ሳይሆን በአካልም ሆነ በመንፈስ በፍጥነት እንዳንታንሰራራ አድክመዋታል”
ከዚህ በላይ የቀረቡት ማስረጃዎች ነገሩን ለማጦዝና ግጭቱን ለማፋፋም ሳይሆን በተሳሳተ ትርክት ወጣቱ ትውልድ እንዳይጠመድ የተጠመደውም እውነቱን ተገንዝቦ ከስህተቱ ታርሞ እራሱንም ከጥፋት፣ አገሩንም ከመበታተን እንዲታደግ ለማሳሰብ ነው።