April 30, 2024
23 mins read

የሁለቱ ስምምነቶች ወግ – ኤፍሬም ማዴቦ

ኤፍሬም ማዴቦ (emadebo@gmail.com )

አንደኛው ስምምነት ዉል ወይም በእንግሊዝኛ Treaty ይባላል። ዉሉን የተፈራረሙት የኢትዮጵያና የጣሊያን መንግስታት ሲሆኑ ዉሉን የተፈራረሙበት ቦታ ውጫሌ፣ ዉሉም የ”ውጫሌ ዉል” በመባል ይታወቃል። የውጫሌ ውል አወዛጋቢና ኢትዮጵያን የጣሊያን ጥገኛ የሚያደርግ ዉል መሆኑን የኢትዮጵያ መሪዎች በማወቃቸው፣ ዳግማዊ ምኒሊክ የውጫሌውን ዉል በተፈረመ በአንድ አመት ከአራት ወሩ ውድቅ አደረጉት። በዚያ ዘመናዊ ትምህርት ቤትና ዘመናዊ የመገናኛ ዘዴዎች ባልነበሩበት፣የድፕሎማሲ ስራዎች በእግር፣ በፈረስና በመርከብ በሚደረግ ጉዞ በሚሰሩበትና አዲስ አበባ ገና የ10 አመት ልጅ በነበረችበት ግዜ፣ዳግማዊ ምኒሊክ፣እቴጌ ጣይቱና ባለሟሎቻቸው ጣሊያን በአማርኛና በጣሊያንኛ የተለያየ ነገር ጽፎ ጉድ ሊሰራን መሆኑን አውቀው፣ የአገርን ሉዓላዊነት ያስከበረና የኢትዮጵያን ስም በታሪክ በወርቅ ቀለም እንዲጻፍ ያደረገ ቆራጥ እርምጃ ለመውሰድ ብዙ ግዜ አልፈጀባቸውም።

ሁለተኛው ስምምነት በኢትዮጵያ ፌዴራል መንግስትና በህወሓት መሪዎች መካከል ድርድር ተካሂዶ የተፈረመ ስምምነት ነው፣ ድርድሩ የተካሄደው ደቡብ አፍሪካ ፕሮቶሪያ ውስጥ ሲሆን፣ ስምምነቱም የ”ፕሪቶሪያ ስምምነት” በመባል ይታወቃል። የፕሪቶሪያው ድርድር የተካሄደው የኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ ወታደራዊ የበላይነት በነበረውና የህወሓት መሪዎች ከዛሬ ነገ “በላይነሽ አመዴ” ከዛሬ ነገ አመድ ታደርገናለች የሚል ከፍተኛ የህልውና ስጋት ውስጥ እያሉ ነው። የፕሪቶሪያው ስምምነት የተፈረመው እነዚህን ሁለት ሁኔታዎች ባገናዘበና የኢትዮጵያን ጥቅምና ፍላጎት ባስጠበቀ መልኩ ነው። ስምምነቱ ተግባራዊ የሆነው ግን የህወሓትን ጥቅም ባስጠበቀና የጦር ወንጀለኛውን ህወሓትን ባከበረ መልኩ ነው። ABCDን ያልቆጠሩና የዛሬ 135 አመት የነበሩ መሪዎች ጣሊያን በላቲን ፊደል የጻፈውን ሸፍጥ ፈልገው አውጥተው አገርን ከአደጋ ሲያድኑ፣ የዛሬዎቹ ዶክተር ተብዬዎች ግን በራሳቸው ቋንቋ የተጻፈን ስምምነት አፍረሰው አገርን ለአደጋ አጋልጠዋል። ግራ ገብቶት ግራ የሚያጋባን እውር ድንብሩ የኢትዮጵያ መንግስት የታጠቀውን መሳሪያ ሙሉ በሙሉ ማስፈታት የነበረበትን ህወሓትን ባደባባይ አቅፎ እየሸለመ፣ በመታጠቁ መንግስትንና አገርን ከአደጋ ያዳነውን የአማራን ህዝብ ትጥቅ ካልፈታህ ብሎ ውጊያ ገጥሞት የጦር ወንጀል እየፈጸመበት ነው።

እንደ ፈረንጆቹ ዘመን አቆጣጠር ግንቦት 2 1889 ዓም በኢትዮጵያና በጣሊያን መንግስታት መካከል ውጫሌ ውስጥ የተፈረመውና በታሪክ የ”ውጫሌ ውል” በመባል የሚታወቀው ስምምነት ጣሊያኖች ኤርትራን ከተቆጣጠሩ በኋላ ኢትዮጵያን ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣጠር የወሰዱት የመጀመሪያ ዕርምጃ ነው። ይህ ጣሊያኖች ከኢትዮጵያ ጋር ጦርነት ሳይገጥሙ በወረቀት ላይ በተደረገ ውል ብቻ አገራችን  ኢትዮጵያን ጥገኛቸው ለማድረግ የወጠኑት ሴራ ገና ከወዲሁ የከሸፈው በአገር ነጻነትና ሉዓላዊነት ላይ ከጠላት ጋር የማይደራደሩ አርቆ አስተዋይ መሪዎች ስለነበሩን ነው።

ጣሊያኖች የውጫሌውን ውል ሲጽፉ፣ በአማርኛ-የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት ከተለያዩ አገሮች ጋር ግኑኝነት ማድረግ በፈለጉበት ግዜ ሁሉ የመልካሙን የጣሊያን መንግስት ተቋሞች መጠቀም ይችላሉ ይላል። ይህ “መጠቀም ይችላሉ” የሚለው ሃረግ  በጣሊያንኛ የተጻፈው  “መጠቀም አለበት/Must use” በሚል አስገዳጅ ቃል ነው። የኢትዮጵያ መንግስት ይህንን የጣሊያኖች ሸፍጥ ለማወቅ ብዙ ግዜ አልፈጀበትም።

ዳግማዊ ምኒልክ ይህንን አገራቸውን የጣሊያን ጥገኛ የሚያደርግ ዜና ሲሰሙ ልባቸው አልተቀበለውም፣ ሆኖም ምን ማድረግ አለብኝ በሚለው ላይ መንፈሳቸው እንደተረበሸ አንዳንድ የታሪክ መረጃዎች ያሳያሉ። ሆኖም የጣሊያኖች ባጠቃላይ ነጮች ለጥቁር ህዝብ ያላቸው አስተሳሰብ የገባቸው እቴጌ ጣይቱ ጦርነት ገጥመን በክብር ለአገራችን እንሞታለን እንጂ የነጭ ጥገኛ የሚያደርገንን ውል አንቀበልም በማለታቸው አፄ ምኒልክ በመስከረም ወር 1890 ዓም የውጫሌውን ውል ውድቅ አደረጉት።

ዳግማዊ ምኒልክ ከጣሊያን መንግስት ጋር የውጫሌን ውል ሲፈራረሙ ዕድሜያቸው  44 አመት የኢትዮጵያ መሪ ከሆኑ ደሞ ገና 53ኛ ቀናቸው ነበር። ግዜው ኢትዮጵያ ውስጥ ዘመናዊ ት/ቤት፣ መኪና፣ስልክ፣ሬዲዮ የሌለበትና፣ ንጉሰነገስቱ እንኳን ከውጭ አገር መንግስታት ጋር ለመነጋገር፣ አንዳንዴ ከራሳቸው ባለስልጣኖች ጋር ቁጭ ብሎ ለመምከርም በወራት የሚቆጠር ግዜ የሚወስድ ከዘመናዊነት ጋር ያልተዋወቅንበት ግዜ ነበር። በጣም የሚገርመው ግን፣ በወቅቱ የነበሩ የኢትዮጵያ መሪዎች በዚያ በጨለማ ዘመን በቀላሉ የማይታዉን የጣሊያንን መንግስት ሴራ አይተው አገር ማዳን ችለዋል። ይህንን ያደረጉት ደሞ ጦርና ጎራዴ ይዞ ከመጣ ኃይል ጋር ሳይሆን እራሱ የሰራውን ታንክና መድፍ በመርከብ ጭኖ ከመጣ የአውሮፓ ኃይል ጋር ነው።

ዳግማዊ ምኒልክ፣ ባለቤታችው እቴጌ ጣይቱና አጠገባቸው የነበሩ ሰዎች ምን ያክል ቆራጥ፣ ብልህና አርቆ አስተዋይ እንደነበሩ የሚያሳየውንና 135ኛ አመቱን ሊያከብር 5 ቀን የቀረውን የውጫሌውን ውል ስናስብ፣ እነዚህ ሁለት ሰዎችና በወቅቱ አጠገባቸው የነበሩ ትልልቅ ሰዎች ገንብተው የሰጡን ትልቅ አገር ዛሬ የምትገኝበትን እጅግ በጣም አሳሳቢ ሁኔታ አብረን ማሰብ አለብን። ይህንን የምለው ያለምንም ምክንያት ከመሬት ተነስቼ አይደለም። አርቆ አሳቢ የሆኑ ትልልቅ ሰዎች ፈጥረው የሰጡን ትልቋ ኢትዮጵያ ዛሬ ማሰብ በተሳናቸው ትንንሽ ሰዎች እጅ ወድቃ ቁልቁል ወደ ታች እያደገች መሆኗን አይኔ አይቶ ልቤ አልቀበል ብሎኝ በቁጭትና በምሬት ነው።

ጥቅምት 24 2013, ማክሰኞ እኩለ ሌሊት በዘመናዊው የኢትዮጵያ ታሪክ የመርገም ቀን ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። “ቅኝ ግዛቴ አደርጋችኋለሁ”. . . . “እሱ በጭራሽ የማይታሰብ ነው” በሚል የካቲቲ 23 1888 ዓም አድዋ ላይ የተዋጉት የጥቁርና የነጭ ኃይሎች ወይም ጣሊያንና ኢትዮጵያ ናቸው። እኔ የማልመራት አገር ትፍረስ ብሎ በ2013 ጥቅምት ሃያ አራት ሌሊት የትግራይን ህዝብ ይጠብቅ በነበረው የአገር መከላከያ ሠራዊት አባላት ላይ ታሪክ ምን ግዜም በ”አገር ክህደት” የሚያስታውሰውን ግፍና ሰቆቃ የፈጸመውና ከራሱ ወገኖች ጋር ጦርነት የገጠመው ግን ዕብሪተኛውና ከጦርነት ውጭ ሌላ የችግር መፍቻ መንገድ የማያውቀው አገር በቀሉ ህወሓት ነው።

የህወሓት ኃይሎች ሰሜን ኢትዮጵያ ውስጥ የከፈቱት ጦርነት ከትግራይ እስከ ሰሜን ሸዋ ድረስ ያለውን በሚሊዮን የሚቆጠር ኢትዮጵያዊ ለሞት፣ለስደት፣ ለመፈናቀልና ለረሃብ ዳርጓል፣ ንብረትና መሰረተ ልማት እንዲወድም አድርጓል፣በህጻናት፣ አረጋዊያንና ወጣት ሴቶች ላይ ከፍተኛ የስነልቦና ጥፋት አድርሷል። የዚህ ጽሁፍ ጸሃፊ ሰሜን ሸዋ ደርሶ የነበረው የህወሓት ወራሪ ሰራዊት በኢትዮጵያ ጥምር ኃይሎች ተቀጥቅጦ ደሴና ኮምቦልቻ ነጻ ከሆኑ በኋላ ሳምንት በማይሞላ ግዜ ደብረሲናን፣ሸዋሮቢትን፣ከምሴን፣አጣዬን፣ኮምቦልቻን፣ ደሴን፣ ባቲን፣ የካሳጊታ ተራራማ አካባቢዎችን፣ ጭፍራን፣ ሚሌንና ሰመራን ጎብኝቶ፣ የህወሓት ወራሪዎች በሰው ህይወት፣በኤኮኖሚ፣በመሰረተ ልማትና በዜጎች ስነልቦና ላይ  ያደረሱትን ይህ ነው ተብሎ ሊነገር የማይችል ጉዳት በአይኑ ተመልክቷል። የህወሓት ወራሪ ኃይሎች በተለይ ደሴና ኮምቦልቻ ዉስጥ በትምህርትና በጤና ተቋሞች ላይ ያደረሱት ጥፋት የውጭ ጠላት ካደረሰብን ጥፋት የከፋ ነው።

ለትግራይ ህዝብ በተለይ እንደ ቅጠል ለሚረግፉት የትግራይ ወጣቶች ደንታ የሌለው ህወሓት ሁለተኛውን ዙር ጦርነት ከተሸነፈ በኋላ አርፎ አልተቀመጠም ወይም ከሽንፈቱ አልተማረም፣ እንዲያውም ነገረ-ስራዉ ሁሉ ተጨማሪ ወጣቶችን መመልመል፣ ማሰልጠንና ለሌላ ዙር ጦርነት መዘጋጀት ነበር። ምዕራባዊያን ወዳጆቹና ለህወሓት የሚራራ ልብ ያላችው የዛሬዎቹ የኢትዮጵያ መሪዎች አዳኑት እንጂ፣ ህወሓት የጀመረው 3ኛው ዙር ጦርነት በህወሓት መደመሰስ መቋጨት ነበረበት።

ህወሓትን በታሪኩ ለመጀመሪያ ግዜ ማሩኝ እንጂ “ትጥቄን ፈትቼ ወደ ሰላማዊ ኑሮ እመለሳለሁ” ያሰኘው የፕሪቶሪያው ድርድርም ቢሆን ስምምነት ላይ የደረሰው የኢትዮጵያን ህዝብ ጥቅምና ፍላጎት ባስከበረ መልኩ ነበር። ነገር ግን የዛሬ 135 አመት የውጫሌውን ውል ከፈረሙ በኋላ ሚስጥሩ ሲገባቸው ዉሉን አፍርሰው  የኢትዮጵያን ትልቅነት ለአለም ያበሰሩ አስተዋይ መሪዎች ከኖሩበት ግዜ አንጻር ሲታይ፣ ዛሬ የመረጃ ቴክኖሎጂ አለማችንን ትንሽ ባደረጋት ዘመን የሚኖሩ የኢትዮጵያ መሪዎች በአለም አቀፍ ደረጃ ድርድር ተካሂዶ በማያሻማ ቋንቋ የተጻፈን ስምምነት ጥሰው ህወሓት ከሙሉ ትጥቁና ሰራዊቱ ጋር መንግስት ሆኖ እንዲቀጥል ማድረጋቸው ብቻ ሳይሆን ህወሓት አራተና ዙር ጦርነት ከፍቶና አማራ ክልል ገብቶ የራያንና የወልቃት ጠገዴን ህዝብ እንዲያሸብር ፈቅደውለታል። የውጫሌው ውል የአገር ኩራት ምንጭ ነበር፣ዛሬም ነው፣ ለወደፊትም ተከታታይ ትውልድ በኩራት ያስታውስዋል፣የፕሪቶሪያው ስምምነት ግን አገራዊ ክህደት የተፈጸመበት የብሔራዊ ውርደት ምልክት ነው።

የውጫሌው ውል የተጻፈው በአማርኛና በጣሊያንኛ ነው፣አብዛኛው የውሉ ክፍል በሁለቱም ቋንቋዎች ተመሳሳይ ሆኖ አንድ አንቀጽ ላይ ጣሊያኖች ያስገቧት አንዲት ቃል ግን ኢትዮጵያን የጣሊያን ጥገኛ ስለምታደርግ የዘመናዊ ትምህርት ቤት ደጃፍ ያልረገጡት የወቅቱ መሪዎቻችን ያቺን ቃል ፈልገው አግኝተው ለጣሊያን መንግስት ቁርጡን ነገሩት። የፕሪቶሪያው ስምምነት የተጻፈው በአማርኛና በእንግሊዝኛ ነው፣ ደሞም በስምምነቱ ላይ ያለው እያንዳንዱ ቃል በሁለቱ ተደራዳሪ አካላት በሚገባ ታይቶ የጸደቀ ስምምነት ነው። ነገርግን ያልተጻፈ የሚያነቡ፣ የተጻፈን የሚደልዙ የዛሬዎቹ የኢትዮጵያ መሪዎች የፕሪቶሪያውን ስምምነት በሃላላ ኬላ ስምምነት ለውጠው በአንድ በኩል ህወሓት ከራሱ ጋር ተነጋግሮ ከነሙሉ ትጥቁ የሽግግር መንግስት እንዲመሰርት ፈቀዱ፣በሌላ በኩል ደሞ ህወሓት ሽብርተኛ አይደለም ብለው በፓርላማ አስወሰኑ። ይህ በአገር ላይ የተሰራ ከፍተኛ ክህደትና ወንጀል አልበቃ ብሏቸው፣ እፍረተ ቢሶቹ የኢትዮጵያ መሪዎች የሃላላ ኬላውን ስምምነት ወዳጅነት ፓርክ ውስጥ የህወሓትን መሪዎች በመሸለም አጸደቁት!

አለምን በብሔር መነጽር ብቻ የሚመለከተው የጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት የፕሪቶሪያውን ስምምነት ተግባራዊ አድርጎ ቢሆን ኖሮ፣ ዛሬ ህወሓት የጦርነት ስጋት ሳይሆን የተነፈሰ ጎማ ይሆን ነበር፣ የአማራ ክልል የህልውና ጦርነት ውስጥ አይገባም ነበር፣የራያና የወልቃይት ጠገዴ ህዝብ እንደገና የህልውና አደጋ ውስጥ አይገባም ነበር። ፕሮቶሪያ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ሆኖ ህወሓት ትጥቁን ፈትቶና ሰራዊቱ ሰላማዊ ኑሮ ጀምሮ ቢሆን ኖሮ፣ በየቦታው ያሰፈሰፉና ህወሓትን እንደ ነብስ አባታቸው የሚመለከቱ የብሔር ልህቃን አደብ ገዝተው፣ እንዴት ኢትዮጵያን በበላይነት እንምራ ከሚል የከሰረ የብሔር ፖለቲካ ቀመር ወጥተው፣ እንዴት ለሁላችንም እኩል የሆነች ኢትዮጵያን እንፍጠር ወደሚል ዘመናዊ የዜግነት ፖለቲካ ቀመር ውስጥ ይገቡ ነበር። ይህ ጤነኛና የሰለጠነ አካሄድ የጦርነት እሳት ለለበለባቸው የትግራይ፣ የአፋርና የአማራ ህዝብ ዘለቄታዊ ሰላምና መረጋጋት የሚፈጥርና ባጠቃላይ ሁላችንንም አሸናፊ የሚያደርግ አካሄድ ነበር። ነገር ግን አገራችን ኢትዮጵያ ትንንሾችና ካፍንጫቸው ስር ወጣ ብለው የማያሰቡ ሰዎች እጅ ስለወደቀች ዛሬ ሁላችንም ተሸናፊዎች ሆነናል።

ባለፉት ሁለት ወራት ጠሚ አቢይን ጨምሮ አንዳንድ ከፍተኛ የክልልና የፌዴራል መንግስት ባለሥልጣኖች ህወሓት ለጦርነት እየተዘጋጀ ነው ሲሉ ተደምጠዋል፣ ከሰሞኑ ደሞ ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ እንዲሉ፣ የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት የሚባለው ተቋም ህወሓት ትጥቁን መፍታት አለበት የሚል ሟርት አይሉት መግለጫ ነገር አውጥቷል። ህወሓት ትጥቁን መፍታት የነበረበት ከ2015 ግንቦት ወር በፊት ነበር፣ አሁን ያለነው 2016 ለግንቦት አጥቢያ ላይ ነው። ብልጥ ልጅ የያዘውን ይዞ ያለቅሳል እንዲሉ፣ ህወሓት ከሰሞኑ የፕሪቶሪያው ስምምነት ተግባራዊ አልሆነም በሚል የኢትዮጵያን መንግስት በመወንጀል የአፍሪካ ህብረት ተሰብስቦ በፕሪቶሪያው ስምምነት ላይ እንዲነጋገር ከማድረጉ ባሻገር፣ አማራ ክልል ገብቶ 4ኛ ዙር ጦርነት ከፍቷል። ከአሁን በኋላ ህወሓት ይዞት ለሚመጣው ጦርነትና ለሚፈጽመው ወንጀል ተጠያቂው ህወሓት ብቻ ሳይሆን፣ ህወሓት ከሙሉ ትጥቁና ሰራዊቱ ጋር መንግስት መስርቶ እንዲቀጥል የፈቀደው የጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት ነው። የጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት ወንጀልና ክህደት ህወሓት በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት ትጥቅ እንዲፈታ አለማድረጉ ብቻ ሳይሆን፣ የፌዴራሉ መንግስት ከህወሓት ጋር ጦርነት ውስጥ ሲገባ አብሮት ከጎኑ የተሰለፈውን የአማራ ህዝብ ትጥቅ ካልፈታህ ብሎ ጦርነት መክፈቱና በአማራ ህዝብ ላይ የጦር ወንጀል መፈጸሙ ጭምር ነው።

እነዚህ በአገር ላይ የተፈጸሙ ትልልቅ ወንጀሎች ፍትህ ይፈልጋሉ፣ ፍትህ እንዲኖርና እያንዳንዱ የፖለቲካ ተዋናይ ለፈጸመው ወንጀል ተጠያቂ እንዲሆን ደሞ እሱ እራሱ ተጠያቂ የሆነና ለህግ የሚገዛ መንግስት ያስፈልገናል  . . . . . .  የህግ የበላይነት የሰፈነበት የፖለቲካ ሥርዓትና ህግን አክብሮ የሚያስከብር መንግስት እንዲኖረን ማድረግ የሁላችንም ሃላፊነት ነውና ሃላፊነታችንን እንወጣ!!! 50 አመት ጮኸን፣ አልቅሰን፣ ተሰዳድበንና እርስ በርስ ተገዳድለን የትም አልደረስንም፣ አሁን እሱን ትተን ስራ እንስራ።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ¹⁵ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ ፥ ¹⁶ ተራራዎችንና   በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን ፤ ¹⁷ ታላቁ የቁጣው ቀን  መጥቶአልና ፥ ማንስ ሊቆም ይችላል ? አሉአቸው ። ራእይ 6 ፤  15_17 ይኽ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ። የኢየሱስን ልደት ሰናከብር የየሐንስ ራእይን ማንበብ ጠቃሚ ይመስለኛል ። ምክንያቱም በመጨረሻው ዘመን

ከኢየሱስ የፍርድ ቀን በፊት በህሊናችን ውስጥ ፍቅርን ለማንገስ እንጣር 

የምጣኔ ሀብታዊ ፍጥ፣ የፖለቲካ፣ የእውነትና የሰብአዊ መብት ታጋይ፣ የአመኑበትን ነገር ለመናገር እንደ ፖለቲከኛ በቃላት ሳያሽሞነሙኑ ቀጥታ የሚናገሩት የሀገሬ ኢትዮጵያ ታላቅ ሰው ነበሩ “ዘር ቆጠራውን ተዉት፤ የአባቶቻችሁን ሀገር ኢትዮጵያን አክብሩ!”  አቶ ቡልቻ ደመቅሳ

ሀገር ወዳዱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

January 6, 2025
ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። ) “ገብርዬ ነበረ

ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ?

January 3, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ዛሬ እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ጥር 1ቀን 2025 ዓ/ም ነው ። አውሮፓውያኑ አዲስ ዓመትን “ሀ” ብለው ጀምረዋል ። አዲሱን ዓመት ሲጀምሩም ከልክ ባለፈ ፈንጠዚያ ነው ። ርቺቱ ፣ ምጉቡና መጠጡ

ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። )

ትላንት አንድ ወዳጀ ደውሎ “አሳየ ደርቤን” ታውቀዋለህ ወይ” አለኝ፡፡ እኔም አላውቀውም አልኩት፡፡ ኢንጅኔር “ኡሉፍ” የተባለ ሰው የዛሬ ሰባት ዓመት ያሰራረውን ጥልቀትና ስፋት ያለውን ዘገብ አቅርቦታልና አዳምጠው አለኝ፡፡ እኔም “ጉድሺን ስሚ ኢትዮጵያ–ከባድ አደጋ

ተቆርቋሪ የሌላት ኢትዮጵያ – አክሎግ ቢራራ (ዶር)

ወገኖቸ፤ ለጊዜው ትችቱን እናቁምና ለወገኖቻችን እንድረስላቸው፡፡፡ በቤተ አማራ ወሎ ቡግና የተከሰተው ርሃብ ጉዳት ቀላል አይደለም፡፡ ለወገን ደራXኡ ወገን ስለሆነ እባካችሁ ህሻናትን እናድን፤ ለግሱ፡፡ ጦርነት ያመክናል፤ ተከታታይ ጦርነት አረመኒያዊነት ነው፡፡ ጦርነት ካልቆመ የረሃቡ

እግዚኣብሔር ግን ወዴት አለ?

Go toTop