April 27, 2024
11 mins read

በህልውና ትግላችን፤ ሁለት ጎራ ብቻ ነው ያለው! – አንዱ ዓለም ተፈራ

ቅዳሜ፤ ሚያዝያ ፲   ቀን፣ ፳  ፮  (4/27/2024)

Oromo 6 1 1 1

ሶስተኛ ጎራ የለም። አንደኛው ህልውናችንን ሊያጠፋ የዘመተብን የአክራሪው ኦሮሞ ገዢ ቡድን ጎራ ነው። ሌላው፤ አንጠፋም! ብለን ታጥቀን ህልውናችንን ለመጠበቅ የተነሳንበት የዐማሮች ጎራ ነው። ከዚህ ውጪ ሌላ ጎራ የለም። በህልውና ትግል፤ ከህልውና ውጪ ያለ ማንኛውን ነገር ቦታ የለውም፤ ወይንም በጣም ዝቅተኛ ቦታ ነው የሚኖረው። እስኪ በውጪ አገራት የምንኖር ዐማሮች ከዚህ ጎራ ስምሪት አንጻር፤ ምን እያደረግን እንደሆን ራሳችንን እንፈትሽ!

በውጪ አገር የምኖር ዐማራ ነኝ። አገሬን ጥዬ በሰው አገር ለመኖር የመረጥኩ ሳልሆን፤ በኢትዮጵያ የነበረው የፖለቲካ ሂደት አፈናቅሎኝ፤ እስከምችለው ድረስ የተሻለ ስርዓት እንዲመጣ ታግዬ፤ ሳይሳካልኝ ሲቀርና ተመልሶ መግባቱ የማይቻል ስለሆነብኝ፤ ውጪ አገር ለስደት የበቃሁ ነኝ። እኔን የመሰሉ ብዙዎች አሉ። ባለፉት ሃምሳ ዓመታት ወደ ውጪ አገራት የተሰደድን፤ ቁጥራችን በጣም ብዙ ነው። በያለንበት የግል ኑሯችንን ብንገፋም፤ ከአገራችን ጋር የሚያስተሳስሩን ብዙ ክሮች ስላሉ፤ ምን ጊዜም እረፍት አግኝተን አናውቅም። ጥሩ አጋጣሚዎች በየጊዜው ቢከሰቱም፤ ሥልጣን ወዳዶች፣ ቂመኞችና የግል ጥቅም አሳዳጆች፤ ካገራቸው ይልቅ የግል ኪሳቸው ማበጡ እየቀደመባቸው፣ በሁለት እጣት የመትገባ ዘውድ በራሳቸው ላይ መጫን እያጓጓቸው፤ መላውን ሕዝብ እየረገጡ ሲገዙ ቆይተዋል። ይህ በተለይ “የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር” ነኝ ባለው ጠባብ ቡድንና፤ አሁን ደግሞ “የኦሮሞ ብልፅግና!” ነኝ ባለው ገዢ ቡድን፤ እየተተገበረ ቆይቷል።

ከሁሉ በላይ እኔን የሚያንገበግበኝ ደግሞ፤ ዐማሮች በሁለቱም ጠባብ አምባገነን ገዢዎች፤ ለመግለጥ እንኳ በሚከብድ ደረጃ፤ ከፍተኛ ግፍና በደል የደረሰባቸው መሆኑ ነው። የስቃይ የመጨረሻው ጥግ ድረስ በመነዳታችን፤ አሁንስ በዛ! ብለን፤ ታጥቀን ተነስተናል። በዚህ በተነሳንበት የህልውና ትግል፤ ያለው ሁለት ጎራ ብቻ ነው። የኛው ጎራ፤ አልጠፋም! ኢትዮጵያ አገሬ ናት! በኢትዮጵያ የትም መኖር እችላለሁ! በኢትዮጵያ ሙሉ መብት ያለኝ ባላባት ነኝ! ኢትዮጵያን ከውጪ ወራሪ ጠብቄ ያኖርኩ ነፍጠኛ ነኝ! አገር ገንቢ ነኝ! ስርዓት አንጋሽ ነኝ! ሥልጣኑም ሆነ ሂደቱ ያገባኛል! ዐማራነት ክብር ነው!  ብለን ተነሳን ያለንበት ነው። ሌላው እኛን ሊያጠፋ የተነሳው ጠባቡ የኦሮሞ ገዢ ቡድን ሲሆን፤ ታሪክ አጥፍቶ አዲስ ትርክት የፈጠረ፣ አገር ገንቢ ሳይሆን አገር አፍራሽ፣ አንድነትን ሳይሆን መለያየትን ያስቀደመ፣ አጀንዳው ኢትዮጵያዊ ሳይሆን በጭንቅላቱ ያነገበው የሥልጣን መሰላሉ የሆነ፤ ያለበት ጎራ ነው። እንግዲህ በዚህ የህልውና ትግል፤ አንድም አጥፊ ሌላም አልጠፋም ባይ ብቻ ነው ያለው። ሶስተኛ ጎራ የለም። ታዲያ በውጪ የምንገኝ ዐማሮች ምን እያደረግን ነው!

በብዙዎች የረጅም ጊዜ ትግል የተገነባውን፤ ዓለም አቀፍ የዐማሮች ንቅናቄ ለማፍረስ፤ ወዲያ ወዲህ ባዮች አሉ! በየከተማው የተቋቋሙ የዐማራ ማኅበራትን መከፋፈልና መወነጃጀል ጦፏል! በተቋሞች ላይ ያለው ዘመቻ ጉድ ያስብላል። የመግለጫዎች ጋጋታ ፋታ የለውም! ለምን? በርግጥ ይሄ እንዳይሆንና የተከሰቱ ችግሮች በትክክል እንዲፈቱ ጥረት የሚያደርጉ እንዳሉ ይገባኛል። ጥያቄው፤ ይሄ ተግባር የትኛውን ጎራ ይጠቅማል? የሚለው ነው።

ጠቅላላ የህልውና ትግሉ አዲስ በመሆኑ፤ የተለያዩ የመፍትሔ ሃሳቦች ከተለያዩ ቦታዎች ይመጣሉ። ይሄ ተገቢና የሚጠበቅ ነው። እኒህ የሚቀርቡ ሃሳቦች፤ ሁሉም ትክክል ወይንም ሁሉም የተሳሳቱ አይደሉም። እያንዳንዳቸው ከበጎ ፍላጎትና፤ ቶሎ ሕዝባችን ሳያልቅ ወደ ትክክለኛ ግብ ለመድረስ ካለ ፍላጎት የመነጩ ናቸው። የግለ ሰቦች የፖለቲካ ብስለት እና የልምድ ማካበት የሚጫወተው ሚና ቀላል አይደለም። ከሞላ ጎደል ዛሬ ሁሉም አልቆ አዲስ አበባ ፋኖ ቢገባና፤ ይሄ የገዢ ቡድን ቢንኮታኮት የማይፈልግ የለም። ፍላጎት ግን ነጂው ኃይል አይደለም። ጊዜ የሚፈልጉና የዕድገት ሂደት ግድ የሚላቸው ክስተቶች አሉ። እኒህን ብን አድርጎ የሚያጠፋ ተዓምር የለም። በዚህ ማለፍና መላላጥ ግድ ነው። ግድ የማይሆነው ግን፤ ርስ በርስ መጠላለፉና እኔ ያልኩት ካልሆነ ሁሉም ገደል ይግባ! የሚል ግትርነት ነው።

ዐማሮች በሙሉ አንድ ዓይነት አስተሳሰብ የለንም። ይልቁንም አገር ወዳድ፣ አገር ገንቢ፣ ወገን አፍቃሪ፣ ለወገን ደራሽ፣ ረጅም ታሪክ ያለንና የአገር አስተዳደር ዕውቀቱ የተመላን ስለሆን፤ የተለያዬ ግንዛቤ የያዝን ነን። እናም ልዩ ልዩ የሆኑ መፍትሔዎችን እናቀርባለን። ይህ የጥበባችን የዲካ ጥልቀትን ያሳያል። አንድ ጠባብ አስተሳሰብ የለንም። ይሄን የመሰለ የአስተሳሰብ ስፋትና ጥልቀት ያለን ዐማሮች፤ አንድ ነገር ብቻ ይዘን የምንሄድ አይደለንም። ስለዚህ፤ እኔ ያልኩት ብቻ ነው ትክክል! የሚል ግትርነት፤ በዐማሮች ውስጥ ቦታ የለውም። በተለይም የህልውና ትግል ይዘን፤ የግል አስተሳሰባችን ሆነ ፍላጎታችን፤ ለብዙኀኑ ተገዢ መሆን አለበት። በርግጥ ሁልጊዜ ብዙሀኑ ነው የሚያውቅ! የሚል ችካል እምነት የለኝም። ነገር ግን፤ በባህላችን እንደምናውቀው፤ ሽማግሎች መክረው፤ አገር ዐውቆት የሚደረግ የስብስብ ውሳኔ፤ አብረን ወደፊት ወይንም ወደኋላ እንድንሄድ ያደርገናል። አሁን የያዝነው የህልውና ጉዳይ፤ ከማናችንም የግል ጉዳይ በላይ ነው። ይህ ሊገዛን ይገባል።

አገር ገንቢ የሆንነው ዐማሮች፤ በመካከላችን መግባባትን በቀላሉ ማስፈን ካልቻልን፤ እንዴት ብለን ነው በአንድ ራዕይና ተልዕኮ፤ ትግሉን ከግብ የምናደርሰው? እንዴት ብለን ነው ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር አገር ለማስተዳደር የምንችለው? መጀመሪያኮ ዐማሮች ሆነን ባንድ የተሰለፍነው፤ ሥልጣንና የግል ፍላጎታችን ገፍቶን ሳይሆን፤ በዐማሮች ህልውና ላይ አደጋ ስለመጣ ነው። በዐማራነታችን ተደራጅተን መታገል፤ የተፈጥሮ ግዴታ ስለሆነብን ነው። እናም በአንድነት ማሰብና መታገል መቻላችን ለህልውናችን ስንል የምናደርገው ግብግብ ነው። እዚህ ላይ የእኔ እበልጥ እኔ እበልጥ ውድድር የለም። ያለው ነገር፤ እኔ ልርዳ፣ እኔ በርዳታ በኩል ልቅደም፣ የትብብር ፍጥነት ብቻ ነው። በዚህ ስሌት፤ በውጪ አገራት የምንኖር ዐማሮች፤ በአንድነት ይሄን የህልውና ትግል መርዳት ዋናው ጉዳያችን ነው። በዚህ ተሳትፏችን ደግሞ፤ ማንም ወሳኝ ሳይሆን፤ የግል አስተዋፅዖዋችንን ከሌሎች ጋር ለመደረብ እንጂ፤ ለመፎካከር ወይንም የበላይ ሆነን ለመገኘት መሞከሩ፤ አፍራሽና የዐማሮችን ጎራ ሳይሆን የአጥፊውን ጎራ መጥቀም ነው።

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop