April 22, 2024
45 mins read

የጋዛ ትምርት ላፍሪቃ፤ ያሜሪቃ የኑክሌር ስድነትና ያፍሪቃ ኑክሌር መታጠቅ አጣዳፊነት

የጋዛ ትምርት ላፍሪቃያሜሪቃ የኑክሌር ስድነትና ያፍሪቃ ኑክሌር መታጠቅ አጣዳፊነት

 

“We shouldn’t be spending a dime on humanitarian aid (in Gaza). It should be like Nagasaki and Hiroshima. Get it over quick. The same should be in Ukraine.  Defeat Putin quick. Instead of 80% of our funding being used for humanitarian purposes, it should be 80%, 100% to wipe out Russian forces.” (Tim Walberg, Republican Congressman from Michigan)

“የጋዛን ጉዳይ እንደ ሂሮሽማና ናጋሳኪ ባንዳፍታ መገላግል እንጅ ለሰብዓዊ እርዳታ ብለን ቀይ ሳንቲም ማውጣት የለብንም። የዩክሬንንም ጉዳይ እንደዚሁ።  የሩሲያን ጦር ባንዳፍታ ሙሉ በሙሉ ድምጥማጡን አጥፍተን ፑቲንን ማንበርከክ አለብን።” [ጢሞ (ጢሞቲወስ) ዋልበርግ፣ ያሜሪቃ ኮንግረሰኛ]

 

“If Canada someday ever attacked Buffalo, I’m sorry my friends, there would be no Canada the next day.” (Kathy Hochul, Democrat governor of New York)

“ካናዳ አንደ ቀን ተነስታ ቡፋሎን ብታጠቃ፣ ካናዳ የምትባል አገር በነገታው አትኖርም።” [ካቲ ሆኩ፣ የኒውዮርክ መንግስት ገዥ)

______________________________

ያሜሪቃ መንግስት የኑክሌር ጦር መሳርያ አጠቃቀም መስፈርት እጅግ የላላ (ስድ) ከመሆኑ የተነሳ፣ ዪክሬን በሩሲያ ላይ ከሁለታ ዓመታት በላይ በየቀኑ ከፈፀመችው እጅግ በጣም ያነሰ ሜክሲኮ ባሜሪቃ ላይ አንድ ቀን ብትፈፅም፣ የዚያኑ ቀን በኑክሌር ቦምብ ድምጥማጧ ጠፍቶ ከነመፈጠሯም በተረሳች ነበር።  ሜክሲኮ ይቅርና ያሜሪቃ ዋና አጋር ናት የምትባለው ካናዳም ብትሆን ያሜሪቃን ጫፍ እነካለሁ ብትል ተጨፍጨፋ እንደምታልቅ አዶ (Ms.) ካቲ ሆኩ (Kathy Hochul) በግልጽ ነግራታለች።  ካቲ ሆኩ በግልጽ የነገረቻት ደግሞ ጉራ ለመንፋት ሳይሆን፣ የካናዳ ድንበርተኛ ከሆኑት ያሜሪቃ ግዛቶች ውስጥ የትልቁ የኒውዮርክ ግዛት ገዥ (governor) በመሆኗ የምታውቀው ውስጠ ሚስጥር (classified information) ሳታስበው አምልጧት ነው።

በቬትናም ጦርነት ወቅት አሜሪቃ ኑክሌር ያልተጠቀመቸው፣ ለመጠቀም ስላልፈለገች ሳይሆን እጠቀማለሁ ብትል ሶቪየት ሕብረት (USSR) እና ቻይና (China) ባፀፋው ኑክሌር እንደሚጠቀሙባት አውቃ ስለፈራች ብቻ ነበር።  በኢራቅ ጦርነት ወቅት አሜሪቃ ኑክሌር ያልተጠቀመቸው፣ ለመጠቀም ስላልፈለገች ሳይሆን በኑክሌር ቦምብ ድምጥማጧ የጠፋ ኢራቅ ላሜሪቃ ታላላቅ የነዳጅ ዘይት ኩባንያወች፣ በተለይም ደግሞ በጊዜው ያሜሪቃ ምክትል ፕሬዚዳንት በነበረው፣ የኢራቅን ጦርነት በዋናነት ባቀናበረው በዲክ ቸኒ (Dick Cheney) ለሚመራው ለሃሊበርተን (Halliburton) የነዳጅ ዘይት ኩባንያ ምንም ስለማትጠቅም ብቻ ነበር።

ባፍጋኒስታን ጦርነት ደግሞ አሜሪቃ ኑክሌር ያልተጠቀመቸው፣ ለመጠቀም ስላልፈለገች ሳይሆን፣ ሰወች ተራርቀው በሚኖሩበት እንዳፍጋኒስታን ባለ ተራራማ አገር ላይ ኑክሌር ቦምቦችን እዚህም እዚያም መጣል እምብዛም የማይፈይድ ከመሆኑም በላይ፣ ከፍተኛ ውጭ ስለሚጠይቅ ብቻ ነበር።  እንዲህም ሆኖ ቁጥራቸው ካንድ መቶ (100) ያልበለጡ ያፍጋኒስታን ተዋጊወችን ለመግደል ስትል ብቻ፣ አሜሪቃ “የሁሉም ቦምቦች እናት” (“the mother of all bombs”) በማለት በቁልምጫ የምትጠራውን ከሁሉም አልኑክሌር ቦምቦች (non-nuclear bombs) ትልቁ የሆነውን ቦምብ ቶራቦራ (Tora Bora) ዋሻወች ላይ ጥላ ነበር።  የዚህ ቦምብ የፍንዳታ ሃይል (power of explosives) አስራ አንድ ሺ ኪሎግራም ደማሚት፣ የፍንዳታ አክዘንግ (radius) ደግሞ ከፍንዳታው እምብርት (center) በያቅጣጫው ሁለት ኪሎሜትር ነበር።

ባጭሩ ለመናገር፣ ያሜሪቃ የኑክሌር አጠቃቀም መስፈርት እጅግ ሲበዛ ልል (ስድ) ነው ማለት፣ አሜሪቃ ለማጥቃት ያሰኛትን አገር ባሰኛት ጊዜ ያሰኛትን ሰበብ (pretext) ፈብርካ (fabricate) በመደበኛ መሣርያ (conventional weapon) ልታጠቃና ልትወር ትችላለች፣ ተወራሪው አገር ለይስሙላም ቢሆን እከላከላለሁ ካለ ደግሞ በኑክሌር ቦምብ ድምጥማጡን ታጠፋዋለች ማለት ነው።  አሜሪቃ የኑክሌር አማራጭን የምትጠቀመው ግን ልታጠቃው የምትፈልገው አገር እንደ ፓኪስታን እና ሰሜን ኮርያ  የራሱ ኑክሌር ያለው ኑክሌረኛ ካልሆነ ወይም ደግሞ ሩሲያ (Russia) ለቤላሩስ (Belarus) እንደምታደረገው ለደህንነቱ ዋስትና የሚስጠው (security guarantee) ኑክሌረኛ አጋር ከሌለው ብቻ ነው።

አፍሪቃ ደግሞ እጅግ ግዙፍ በመሆኗ ሳቢያ ፀረቅኝገዥ (anticolonialist) የሆኑት ኑክሌረኛቹ ሩሲያ እና ቻይና ላፍሪቃ ደህንነት ዋስትና ሊሰጡ አይችሉም፣ መስጠትም አይጠበቅባቸውም።  ይህን የሚያውቁት  ባሜሪቃ አፄጌ (American Empire) ሥር የተሰባሰቡት ምዕራባውያን ቅኝገዝወች (western colonialists) ደግሞ አፍሪቃን ዳግም ቅኝ ለመግዛት አመቺውን ጊዜ እየተጠባበቁ እንደሆነ እነሱ ራሳቸው፣ በራሳቸው አንደበት በግልጽ ተናግረዋል።

 

“ላፍሪቃ የሚበጃት የቀድሞ ቅኝ ገዝወቿ እንደገና ወረዋት ምንም የጥፋተኝነት ስሜት ሳይሰማቸው እንደገና ቢቀራመቷት ነው።  አፍሪቃ አሳፋሪ ብትሆንም አሳፋሪነቷ እኛን አያስጨንቀንም።  ያፍሪቃ ችግር ቅኝ መገዛቷ ሳይሆን ነፃ መውጣቷ ነው።” (ቦሪስ ወልደዮሐንስ፣ የንግሊዝ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስቴር)

“The best fate for Africa would be if the old colonial powers, or their citizens, scrambled once again in her direction; on the understanding that this time they will not be asked to feel guilty. The continent may be a blot, but it is not a blot upon our conscience … The problem is not that we were once in charge, but that we are not in charge anymore.” (Boris Johnson, former prime minister of England).

አፍሪቃ የነጭ ላዕልተኛውን (white supremacist) የቦሪስ ጆንሰንን (Boris Johnson) ምኞት ባዶ ቅዥት ማድረግ የምትችለው በሌላ በማንም አገር ወይም ድርጅት ላይ በመተማመን ሳይሆነ በራሷ ጦር ኃይል ራሷን ሙሉ በሙሉ የመከላከል ብቃት ስታዳብር ብቻ ነው።  በኑክሌር ሃይላቸው የሚተማመኑት ምዕራባውያን ጋዛ (Gaza) ላይ በማናለብኝነት መንፈስ በገሃድ እየፈፀሙት ያለው መጠነሰፊ ዘርቀታይ (genocidal) ጭፍጨፋ በግልፅ የሚያመላክተው ደግሞ፣ አፍሪቃ ራሷን የመከላከል ሙሉ ብቃት ባጭር ጊዜ ውስጥ ካላዳበረች፣ በጋዛ ላይ እየተፈፀመ ያለው ባጭር ጊዜ ውስጥ ባፍሪቃም ላይ እንደሚፈፀም ነው።  የጋዛው ጭፍጨፋ ላፍሪቃ ነግ በኔ ነው።

የቀድሞወቹ የጀርመን ቅኝ ገዥወች መደበኛ መሣርያ (conventional) በመጠቀም ብቻ ሄሬሮ (Herero) የሚባለውን የናሚቢያ (Namibia) ትልቅ ጎሳ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ማጥፋት ከቻሉ፣ ያሜሪቃን ኑክሌር መሳርያ የታጠቁት ልጆቻቸው ናዚወች ባፍሪቃ ላይ ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉ ማሰቡ ብቻ ይሰቀጥጣል።  ኑክሌር ያልነበራት እንግሊዝ ባንዲት ያፍሪቃ አገር (ኬንያ) ውስጥ ባንድ የነፃነት አመፅ (የማው ማው አመፅ Mau Mau Rebellion) ላይ ብቻ አስር ሺወችን ያላንዳች ርህራሄ እንደ ቅጠል ካረገፈች፣ አሁን ኑክሌርኛ ሁና ቦሪስ ጆንሰን (Boris Johnson) እንዳለው ዜጎቿ ምንም የጥፋተኝነት ስሜት ሳይሰማቸው አፍሪቃን በድጋሚ ለመቀራመት ቢመጡ፣ በመላዋ አፍሪቃ ላይ ሊፈፀሙ የሚችሉትን መገመቱ ብቻ እጅግ ያስፈራል።

“ኢስልጡኖች በመርዝ ጋዝ መጨፍጨፋቸውን በፅኑ እደግፋለሁ …  ቀይ ሕንዶችና ጥቁር አውስትራሎች በደም በሚበልጣቸው ዘር ግዛታቸውን መነጠቃቸው ተገቢ ነው  …   ፍልስጤሞች የግመል ፋንድያ የሚበሉ መንጋወች ናቸው  … ሕንዶች ያስጸይፉኛል፣ እነሱ አረመኔ፣ ቋንቋቸው አረመኔ  …   ለጋንዲ የሚገባው እጅና እግሩን የፊጥኝ አስሮ ባማጋደም እንደራሴያችን በሚጋልበው ዝሆን ጨፈላልቆ ማሳረፍ ነው።” (ዊንስተን ቸርችል፣ የቀድሞ የንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስቴር)

 

“I am strongly in favour of using poisonous gas against uncivilized people …  I do not admit that a great wrong has been done to the Red Indians of America or the black people of Australia by the fact that a higher grade race has come in and taken its place …. Palestinians are hordes who eat camel dung… I hate Indians.  They are a beastly people with a beastly religion… Ghandhi ought to be lain bound hand and foot and then trampled  by an enormous elephant with the Viceroy on its back.” (Winston Churchill, former prime minister of England)

 

አሜሪቃ ሂሮሽማና ናጋሳኪ (Hiroshima and Nagasaki) ላይ የተጣሉትን ያለማችንን የመጀመርያወቹን አቶሚክ ቦምቦች የሰራቸው፣ የማንሐታን ፕሮጀክት (Manhattan Project) የሚል ስያሜ በሰጠቸው ልዩና አስቸኳይ ፕሮጀክት (crash project) ነበር።  ፕሮጀክቱ የተከናወነው ደግሞ ሎስ አላሞስ (Los Alamos) በሚባል (በልዩ ወታደሮች ልዩ ጥበቃ ይደረግበት በነበረ) ልዩ ቦታ ላይ ሳይንሰኛወችን (scientists) እና መሐንዲሶችን (engineers)  የማጎር ያህል (concentration camp) አስቀምጣ፣ የባርነት ያህል ቀን ከሌት በማሰራት ነበር።  ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ደግሞ ወታደራዊ እቅዷን በቀላሉ ማሳካት የማትችል መስሎ ሲታያት ወይም ደግሞ የበላይነቷን ለሚገዳደር (challenge) አገር ማስጠንቀቂያ ለመስጠት ስትሻ ኑክሌሮቿን ተጠቅማለች ወይም ለመጠቀም ትዝታለች።

ፕሬዚዳንት ትሩማን ሂሮሽማና ናጋሳኪ ላይ አቶሚክ ቦምቦችን ጥሎ ሩብ ሚሊዮን የሚጠቁ ሰላማዊ ጃፓኖችን ለመጨፍጨፉ ያቀረበው ምክኒያት፣ ሁሉንም ጃፓኖች በዚሁ መንገድ እጨርሳቸዋለሁ ብየ የጃፓንን መንግስት በማስፈራራት እጁን እንዲሰጥ አድርጌ ያሜሪቃን ወታደሮች መስዋእትነት ለመቀነስ ነው የሚል ነበር።  የጃፓን ንጉስ አጼ ሂሮሂቶ (Emperor Hirohito) የጃፓን መንግስት እጅ እንዲሰጥ ቀጭን ትእዛዝ ባይሰጡ ደግሞ ፕሬዚዳንት ትሩማን ልክ እንደዛተው ጃፓኖችን ሙሉ በሙሉ ጨፍጨፎ፣ ጃፓንን ያንግሎ ሳክሶን አገር ያደርጋት ነበር።  በጨካኔያቸው ወደር የሌላቸው አረመኔወቹ አንግሎ ሳክሶኖች ቀይ ሕንዶችን ከሞላ ጎደል ሙሉ በሙሉ ጨፍጭፈው ሰሜን አሜሪቃን (North America)፣ ጥቁሮችን ከሞላ ጎደል ጨፍጭፈው ደግሞ አውስትራልያን (Australia) ያንግሎ ሳክሶኖች የግል ርስት ማድረጋቸውን አፍሪቃውያን መቸም ቢሆን መርሳት የለባቸውም።

በኮርያ ጦርነት ወቅት ሰሜን ኮርያወች ባሜሪቃ ላይ በመጠኑ ስላየሉ ብቻ፣ ሰላማዊ ጃፓኖችን በኑክሌር የጨፈጨፈው ይሄው የኒክሌር ጨፍጫፊ ፕሬዚዳንት አቶ ሃሪ ትሩማን (Harry Truman) እንደለመደበት ሰላማዊ ኮርያወችን በኑክሌር ለመጨፍጨፍ ደጋግሞ ዝቶ የሶቭየት ሕብረትን (USSR) እና የቻይናን የኑክሌር አፀፋ ስለፈራ ብቻ ዛቻውን ውሃ በልቶታል።  ሰሜን ኮርያወችን እንደ ጃፓኖች ጨፍጭፎ አንግሎ ሳክሶናዊ የደም ጥማቱን ስላላረካ ደግሞ እንደቆጨው ሙቷል።

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ያውሮጳ ክፍል ዋና አዛዥ የነበረውና በጀርመኖች ላይ ኑክሌር መጠቀምን በጽኑ ተቃውሟል የሚባለው ፕሬዚዳንት ዳዊት አይዘንሃወር (Dwight Eisenhower) የታይዋን ሰርጥ ቀውስ (Taiwan Strait Crisis) በተከሰተበት ወቅት ነገሮች ካሜሪቃ ቁጥጥር በትንሹ የወጡ በመሰሉት ቅጽበት ላይ የኑክሌር ካርዱን (nuclear card) ወዲያውኑ ስቦ ቻይኖችን እንደ ጃፓኖች ለመጨፍጨፍ ዝቶ ነበር፣ የሶቭየት ሕብረትን (USSR) ሁኔታ አይቶ የሳበውን ካርድ ወዲያውኑ መለሰው እንጅ።

ፕሬዚዳንት ዮሐንስ ኬኔዲ (John Kennedy) ደግሞ የኩባ ሚሳየል ቀውስ (Cuban Missile Crisis) በተከሰተበት ወቅት ኑክሌር ካልተጠቀምኩ ብሎ ለያዥ ለገናዥ አስቸግሮ ነበር፣ የጊዜው የሶቭየት ሕብረት መሪ ኒኪታ ክሩስቸቭ (Nikita Khrushchev) ዋልህ ብሎ ሲያስጠነቅቀው ወዲያውኑ አደብ ገዛ እንጅ።

ፕሪዚዳንት ኬኔዲ ኑክሌር ለመጠቀም የተነሳሳው እሱ ቱርክ ላይ (ማለትም ሶቭየት ሕብረት ድንበር ላይ) ኑክሌር ሚሳየል ለመትከሉ አፀፋ ሶቭየት ሕብረት ኩባ ላይ (ማለትም ካሜሪቃ ድንበር 150 ኪሎሚትር ርቃ) ኑክሌር ሚሳየል በመትከሏ ነበር።  ይህ የሚያሳየው ደግሞ “እኔ ባሰኘኝ ጊዜ በኑክሌር ልምታችሁ፣ እናንተ ግን እኔን እመታለሁ ብላችሁ ጭራሽ እንዳታስቡ” የሚለውን ያሜሪቃን የማናለብኝነት እሳቤ ነው።

ያሜሪቃ ፕሪዚዳንት የሆነ ወይም ለመሆን የሚፈልግ ማናቸው ፖለቲከኛ ባሜሪቃ ነጮች (በተለይም ባንግሎ ሳክሶኖች) ዘንድ ያለውን ድጋፍ በከፍተኛ ደረጃ ለመጨመር የሚያስችለው ርግጠኛ ፍቱን ዘዴ፣ ያሜሪቃ ጠላት ወይም ተቀናቃኝ ነው በሚባል በማናቸውም አገር ላይ ኑክሌር ለመጠቀም ቅንጣት እንደማያቅማማ በግልጽ ቋንቋ በይፋ መዛት ብቻ ነው።

ዩክሬንን በተመለከተ ደግሞ አሜሪቃ በግልጽ እንደተናገረቸው ዋና ዓላማዋ ሩስያን ትልማዊ ሽንፈት (strategic defeat) መጋት ነው።  ይሄን ያሜሪቃን ዓላማ በመደበኛ ጦርነት (conventional) ማሳካት እንደማይቻል ግን ከቀን ወደ ቀን ይበልጥና ይበልጥ ግልጽ እየሆነ መጥቷል።  ዩክሬን ደግሞ አሜሪቃ ሩሲያን የምታሽንፍባት መሣርያ ከመሆን ይልቅ እሷ ራሷ ጠቅላላ ሽንፈት (comprehensive defeat) ተከናንባ፣ ወጣቶቿን ፈንጅ ረጋጭ በማድርግ አስጨርሳ፣ አብዛኛውን ሕዝቧን በስደተኝነት በመላው ዓለም ላይ በታትና፣ ፍርስርሷ የሚወጣበት ዕድል ከጊዜ ወደ ጊዜ ይበልጠና ይበልጥ እየሰፋ መጥቷል።  ባንፃሩ ደግሞ ሩሲያ ይበልጥና ይበልጥ በእሳት ተፈትና ይበልጥና ይበልጥ እየጠነከረች፣ ኢኮኖሚዋን ከምዕራባውያን ኢኮኖሚ ጥገኝነት ይበልጥና ይበልጥ በማላቀቅ ማናቸውንም የምዕራባውያን ማዕቀብ በስኬት የመቋቋም አቅሟን ይበልጠና ይበልጥ እየገነባች ፣ ከጦርነቱ በፊት ከነበራት ሁኔታ በተሻለ ሁኔታ ጦርነቱን የምትፈጽምበትን ዕድል ይበልጥና ይበልጥ እያሰፋች መጥታለች ።

ሩሲያ ዩክሬንን በመውጋት የዓለምን ሕግና ደንብ (rules-based international order) ጥሳለች እያሉ ሳያሰልሱ ይወቅሷትና ይከሷት የነበሩት ምዕራባውያን፣ የዓለምን ሕግና ደንብ በማናለብኝ ስሜት በግልጽ እየጣሰች ያለችውን እስራኤልን በዋናነት ሲደግፉና ሲያስታጥቁ መታየታቸው የለየላቸው ተመጻዳቂወች (hypocrites) መሆናቸው ገሃድ አውጥቶታል።  ይህ ደግሞ ሩሲያን በምዕራባውያን ላይ ከፍተኛ የሞራል ልዕልና አጎናጽፏታል።

በተጨማሪ ደግሞ (ምዕራባውያን በጫኑባት ታይቶም ተሰምቶም በማይታወቅ የማዕቀብ ብዛትና ክፋት ሳበያ) የተፈጥሮ ሐብቷ ዲካ የሌለው ሩሲያ የሰው ሐብቷ ዲካ ከሌለው ቻይና ጋር በሁሉም ዘርፎች ጠንካራ ትስስር (comprehensive partnership) ፈጥራለች። እነዚህ ሁሉ ሲዳመሩ የሚያመላክቱት ደግሞ አሜሪቃ ሩስያን ትልማዊ ሽንፈት (strategic defeat) አሸንፋለሁ ብላ እሷ ራሷ ጠቅላላ ሽንፈት (total defeat) የመሸነፏንና የዓለም አዛዥና ናዛዥነቷ የማብቃቱን ዕድል ከቀን ወደ ቀን ይበልጥና ይበልጥ እያሰፋች መሆኗን ነው።

“በእግዚአብሔር እንድ የሆንኩ የማልከፋፈል አገር ነኝ” (“one nation, indivisible under God”) እያለች የምትመጻደቀው አሜሪቃ፣ ዩጎዝላቪያን (Yougoslavia) በበታተነችው ዘዴ ሩሲያን እበታትናለሁ ብላ እሷ ራሷ የመበታተኗን ዕድል አስፍታለች።  ዩክሬንን ከሩሲያ ተፅዕኖ አድማስ (sphere of influence) አወጣለሁ ብላ የተነሳቸው አሜሪቃ፣ አላስካ (Alaska) በሩሲያ ተፅዕኖ አድማስ ውስጥ የምትገባበትን ዕድል ከፍ አድርጋለች።  ባጠቃላይ ደግሞ አሜሪቃ ወደ ሩሲያ የምትወረውራቸው እኩይ ነገሮች ሁሉ ወደራሷ ተመልሰው የሚምዘመዝሙ (boomerang) ምዝምዝሞች (ምሉስ ቅዝምዝሞች boomerang) ሁነውባታል፣ ተንጋለው ቢተፉ ተመልሶ ካፉ ነውና።

በነዚህ ሁሉ ተስፋ አስቆራጭ ምክኒያቶች ሳቢያ አሜሪቃ ጃፓን ላይ እንደለመደቸው ሩሲያ ላይ ኑክሌር ለመጠቀምና ፣ ኮንግረሰኛው ጢሞ ዋልበርግ (Tim Walberg) እንዳለው “የሩሲያን ጦር ባንዳፍታ ድምጥማጡን አጥፍታ ፑቲንን ለማንበርከክ” በጽኑ እያሰበችና እያሰላሰለች ባይሆን እንጅ ቢሆን አያስገርምም።  ሩሲያ ላይ ኑክሌር መጣል ደግሞ ዓለም የምትጠፋበትን የመጨረሻውን የኑክሌር አርማጌዶን (Nuclear Armageddon) በይፋ መጀመር መሆኑን አሜሪቃ አሳምራ ታውቃለች።

በዘር ጭፍጨፋ የተመሠረተችው፣ በባርነት የተገነባችው፣ በዘረኝነት የጨቀየችው የአሜሪቃ ግን መሰል የሌለኝ እጹብ ደንቅ ነኝ (American Exceptionality) እያለች ራሱን በራሷ የምታመጻድቅ፣  ለጨለማው ዓለም ብርሃን ነኝ (A shining light on a hill) እያለች በራሷ ውሸት ራሷን በራሷ የምታሞካሽ እጅግ ሲበዛ ራስ ወዳደ፣ እኔ ከሞትኩ ሠርዶ አይበቀል ባይ ስለሆነች፣ የዓለም የበላይነቷ ከሚቀርባት ይልቅ ዓለምን ይዛ ብትሞት ሺ አጥፍ ትመርጣለች።

ያሜሪቃ መንግስት የነጭ፣ በነጭ፣ ለነጭ (of whites by whites for whites) የሆነ፣ የሁሉም ነጮች (የጣልያኖች፣ ፈረንሳዮች፣ አይሪሾች፣ ፖሊሾች፣ ዩክሬኖች ወዘተ.) የበላይ ነን ብለው የሚያስቡት አንግሎ ሳክሶኖች (Anglo-Saxons) ከሞላ ጎደል ሙሉ በሙሉ የሚቆጣጠሩትና እንዳሻቸው የሚዘውሩት በሕግ (de jure) ባይሆንም በተግባር (de facto) የነጭ ዘረኝነትን የሚያራምድ ዘረኛ መንግስት ነው።  እነዚህ ያሜሪቃን መንግስት እንዳሻቸው የሚዘውሩት የዘመናቸን አንግሎ ሳክሶኖች ደግሞ የዊንስተን ቸርችል (Winston Churchill) አድናቂወች ስለሆኑ፣ እንደ ቸርችል በይፋ (overtly) ባይሆንም እንኳን በሕቡዕ (covertly) ነጭ ላዕልተኞች (white supremacists) ከመሆናቸው በላይ  የሕዝብ መጨፍጨፊያ መሳርያወችን (weapons of mass destruction, WMD) አድናቂወች መሆናቸው ምንም አያስገርምም።

በትክክል ለመናገር ያለማችን የመጀመርያው የሕዝብ መጨፍጨፊያ መሳርያ  (the first weapon of mass destruction) በፈረንጆች አቆጣጠር በ1884 እንግሊዝ አገር የተሠራው በደቂቃ 600 ጥይት የሚተፋው ማክሲም መትረየስ (Maxim machinegun) እንጅ፣ በፈረንጆች አቆጣጠር በ1945 አሜሪቃ ውስጥ የተሠራው አቶሚክ ቦምብ አይደለም።  እንግሊዝ ደግሞ አፍሪቃን ያሸነፈቸው ጀግና ሁና ወይም ስለጦርነት የምታውቅ የጦር ገበሬ ሁና ሳይሆን፣ ይህን የሕዝብ መጨፍጨፊያ መሳርያ ያለ ምንም ርህራሄ ስለተጠቀመች ብቻና ብቻ ነበር።  እንግሊዛዊው የታሪክ ምሁር ማርቲን ጊልበርት (Martin Gilbert) ማክሲም መትረየስን “የንግሊዝ አፄጌ ዋና የቅኝ ግዛት መሣርያ” (“the weapon most associated with imperial conquest”) ያለውም በዚሁ ምክኒያት ነበር።  ስለዚህም የሕዝብ መጨፍጨፊያ መሳርያ ለመጀመርያ ጊዜ የተጠቀሙት አሜሪቃኖች ሳይሆኑ እንግሊዞች ናቸው፣ የመጀመርያወቹ ሰለባወች ደግሞ ጃፓኖች ሳይሆኑ አፍሪቃውያን ናቸው ማለት ነው።

እንደ ምሳሌ ደግሞ ከታላቁ ያድዋ ጦርነት (Battle of Adwa) ስድስት ዓመታት ቀድሞ የተካሄደውን የኦምዱርማን ጦርነት (Battle of Omdurman) መጥቀስ ይቻላል፡፡  በዚህ ጦርነት ላይ፣ በጀነራል ሆራቲዮ ኪችነር (Horatio Kichener) የተመራው ቁጥሩ አስር ሺ ገደማ የነበረው የእንግሊዝ ወራሪ ጦር፣ በዳርፉራዊው አብዱላ ወልደሙሔ (Abdullah Ibn-Mohammed) በተመሩ፣ ጦርና ጋሻ ብቻ ባነገቱ ጥቁሮች ድባቅ ከመመታት የዳነው ማክሲም መትረየስ በመታጠቁ ብቻና ብቻ ነበር።

 

“Thus ended the Battle of Omdurman – the most signal triumph ever gained by the arms of science over barbarians. Within the space of five hours the strongest and best-armed savage army yet arrayed against a modern European Power had been destroyed and dispersed, with hardly any difficulty, comparatively small risk, and insignificant loss to the victors.” (Winston Churchill, The River War: An Historical Account of The Reconquest of the Soudan).

“ስልጡኑ የሳይንስ ጦር በኋላቀር አረመኔወች ላይ የመጀመርያውን አስደናቂ ድል የተጎናጸፈበት የኦምዱርማን ጦርነት እነሆ ተጠናቀቀ፡፡  ያውሮጳን ዘመናዊ ሠራዊት የገጠመው ያረመኔወች ጠንካራ ሠራዊት ይህ ነው የሚባል ጉዳት ሳያደርስ ባምስት ሰዓት ውጊያ ብቻ በመትረየስ እየተቆላ ተረፍርፎ፣ እንደ ጉም በኖ፣ እንደ ጤዛ ተኖ ድምጥማጡ ጠፋ፡።” (ዊንስተን ቸርችል፣ የቀድሞ የንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስቴር)

በርግጥም ዊንስተን ቸርችል የሰው ልጅ እንደ ዛፍ መጨፍጨፍ እንደ ቅጠል መረፍረፍ አለቅጥ የሚያስደስተው፣ ያውሬነት መንፈስ የተጠናወተው፣  በጥቁር ጥላቻ የሰከረ ነጭ ላዕልተኛ አረመኔ (white supremacist sadist) መሆኑንና በመሆኑም እንደሚታበይ፣ እሱ ራሱ በማያሻሙ ቃሎች ለመላው ዓለም ግልጽ አደርጓል።  ባንግሎ-ሳክሶኖች የሚዘወረው የምዕራባውያን ሚዲያ፣ ዓለማችንን ከሂትለር (Hitler) የታደገ ታላቁ የነጻነት፣ የዲሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ጋሻ  (bulwark of freedom, democracy, and human right) እያለ በመካብ ሰማይ የሚያደርሰውም እንዲህ ያለውን ነጭ ላዕልተኛ አረመኔ ነው።

ይህ የሚያሳየው ደግሞ ምዕራባውያን ነጻነት፣ ዲሞክራሲና ሰብዓዊ መብት እያሉ ሌላውን ዓለም የሚሰብኩት በነዚህ ባዶ ቃሎች ሰብረው ገብተው በሌላው ዓለም ላይ ለመስፋፋትና ለመንሰራፋት ሲሉ ብቻ መሆኑን ነው።   ሌላው ዓለም ማወቅ ያለበት ደግሞ በጭፍጨፋ፣ በቅኝ ግዛትና በባርነት ከሞላ ጎደል ሙሉ በሙሉ ከተገነቡት ከምዕራባውያን አገሮች (western countries built solely and exclusively on genocide, colonialism, and slavery) ነጻነት፣ ዲሞክራሲና ሰብዓዊ መብት መጠበቅ ከዕባብ እንቁላል እርግብ መጠበቅ መሆኑን ነው።

ዊንስተን ቸርችል እንዳለው እንግሊዝ አፍሪቃውያንን በማክሲም መትረየስ (Maxim machinegun) የጨፈጨፈቻቸው፣ እንግሊዞች መትረየሱን የሰሩ ላዕልሰቦች (superhuman) አፍሪቃውያን ደግሞ ታሕትሰቦች (subhuman) በመሆናቸው ስለሆነ መጨፍጨፋቸው ተገቢ ነው  (“ I do not admit that a great wrong has been done to the Red Indians of America or the black people of Australia by the fact that a higher grade race has come in and taken its place”)።  ይህን ባለበት አፉ ደግሞ ሂትለር ቪ-2 ጨሳፊ (V-2 rocket) የተሰኘውን ያለማችንን የመጀመርያ ፈናሪ ደርባጊ (ballistic missile) ሠርቶ ለንደንን (London) ሲደረብግ፣ አረመኔው ሂትለር ጨፍጨፎ ሊጨርሰን ነውና እባካሽ አድኝን ብሎ ሩሲያ እግር ሥር ወደቀ።

ስለዚህም በዚህ ሲቸግረው ሩሲያ እግር ስር በወደቀ ውዳቂ ግለሰብ የወደቀ አስተሳሰብ መሠረት ሮማውያን አንግሊዞችን ለምዕተ ዓመታት ቅኝ ገዝትው፣ ባርያ አድርገው እንደ ከብት ሲጠምዷቸው፣ እንግሊዞች ታሕትሰቦች (subhuman) የነበሩ ሲሆን፣ እንግሊዞች ወርተራ ደርሷቸው የሮማውያን የበላይ ሲሆኑ ደግሞ እኒሁ እንግሊዞች ከታሕትሰብነት በተዓምር ወደ ላዕልሰብነት (superhuman) ከፍ አሉና ሮማውያኑ ደግሞ በተቃራኒው ወደ ታሕትሰብነት (subhuman) ወረዱ ማለት ነው፡፡  የነ ዊንስተን ቸርችል ነጭ ላዕልተኝነት (white supremacism) ትርክት ጥልቀቱ እስከዚህ ድረስ ነው፡፡

እውነታው ግን አውሮጳውያን አፍሪቃውያንን አሸንፈው ቅኝ ለመግዛት ወደ አፍሪቃ የገሰገሱት እነሱ የታጠቁትን ዘመናዊ መሣርያ አፍሪቃውያን እንዳልታጠቁ ሙሉ በሙሉ እርግጠኞች ስለነበሩ ብቻና ብቻ ነበር፡፡  አውሮጳውያን ዘመናዊ የጦርና ሌሎች መሣርያወችን ሊሠሩ ባጠቃላይ ደግሞ በእደ ጥበብ ሊካኑ የቻሉት ደግሞ እኒህን የሚያሳልጥ የተደራጀ መንግሥት በመመሥረታቸው ብቻና ብቻ ነበር፡፡  እነሱ የሰሩትን አፍሪቃውያን ሊሰሩ ያልቻሉት ደግሞ በዚያን ወቅት አብዛኞቹ ያፍሪቃ መንግስታት ከዕድሜ ብዛት ፈራርሰው፣ የቀሩት ደግሞ ተዳክመው ስለነበረ ነበር ፣ መወለድ፣ ማደግ፣ ማርጀትና መሞት ያለ፣ የነበረና የሚኖር ዘላለማዊ የተፈጥሮ ሕግ ነውና።

ዕድሜ ጠገቦቹ ያፍሪቃና የእስያ መንግስታት በሞቱበት ወይም በተዳከሙበት ሰዓት ትናንት መጤወቹ ያውሮጳ መንግስታት ጎልማሶች ሆኑና መልካም አጋጣሚ ተፈጠረላቸው፣ ጊዜው የነሱ ሆነ።  ጊዜ የሰጠው ያውሮጳ ቅል ደግሞ ያፍሪቃንና የእስያን ዲንጋ ሰበረ።  አሁን ላይ ደግሞ ምዕራባውያን በተራቸው እየተዳከሙና እየሞቱ ፣ ሙተው የነበሩት አፍሪቃውያንና እስያውያን ደግሞ አፈር ልሰው እየተነሱ ነው።  ስለዚህም ምዕራባውያን ኑክሌር እንጠቀማለን እያሉ የሚዝቱት፣ እየሞቱ መሆናቸውን አውቀው ሌላውን ዓለም ይዘው ለመሞት  የተዘጋጁ ይዞ ማቾች በመሆናቸው ነው።  አፍሪቃን በተመለከተ ደግሞ ምዕራባውያን ባሁኑ ወቅት ጋዛ (Gaza) ላይ የሚፈጽሙት ጨፍጨፋ ላፍሪቃ መንግስታት ትልቅ ትምህርት ነው።

 

“Gaza’s waterfront property could be very valuable …. from Israel’s perspective I would do my best to move the people out and then clean it up” (Jared Kushner, son-in-law and senior advisor of President Trump)

“የጋዛ የባሕር ዳርቻ ትልቅ ገንዘብ የሚፈራበት ቦታ ነው  …  እስራኤል ማድረግ ያለባት ጋዛወችን ጠራርጋ ቦታውን ማጽዳት ብቻ ነው” (ያሬድ ኩሽነር፣ የፕሪዚዳንት ትራምፕ ልጅ ባልና ዋና አማካሪ)

ምዕራባውያን ለትንሿ ጋዛ የባሕር ዳርቻ ብለው ጋዛወችን ጨፍጭፈው ለማጽዳት በዚህ መጠን ተባብረው ከተነሳሱ፣ በተፈጥሮ ሐብት ለበለጸገቸው፣ በውበቷና ባየሯ ተስማሚነት ወደር ለሌላት ለግዙፏ አፍሪቃ ብለው ምን ሊያደርጉ እንዳሰቡ መገመት አያዳግትም።

ምዕራባውያን አንደኛውን ትኩረታቸውን ጋዛወችን በመጨፍጨፍ ላይ አድርገው፣ ሌላኛውን ትኩረታቸውን ያደረጉት ደግሞ ምዕራባዊ ያልሆነው ሌላው የዓለም ሕዝብ ለጋዛ ጭፍጨፋ እየሰጠው ባለው ግብረመልስ ላይ ነው።  የተለየ ትኩረታቸውን ያደረጉት ደግሞ ኑክሌረኞቹ ሩሲያ እና ቻይና በሚሰጡት ግብረመልስ ላይ ነው።

በኬስት ስርአት (caste system) የተቀረፀችው ሕንድ፣ በተለይም ደግሞ ናሬንድራ ሞዲን (Narendra Modi) በመሰለ የሂንዱ ብሔርተኛ (Hindu nationalist) የምትመራ ሕንድ፣ የነጭ አሸርጋጅ የመሆኗ እድል ከፍተኛ ስለሆነ፣ ነጭ ላዕልተኞ በሕንድ በኩል እምብዛም ስጋት የለባቸውም።  ለዚህ ደግሞ “አሜሪቃ ዘረኛ ሁና አታቅም” (America has never been racist) ያለችውን ሕንዳዊቷን ኒኪ ሄሊን (Nikky Haley)፣ “ባሜሪቃ ዘረኝነት የለም” (There is no racism in America) ያለውን ሕንዳዊውን ዲነሽ ዲሶዛን (Dinesh D’Souza)፣ “እንግሊዝ ዘረኛ ናት የሚሏችሁን አትስሟቸው” (Never let anyone tell you that this is a racist country) ያለውን ሕንዳዊውን ሪሺ ሱናክን (Rishi Sunak) መጥቀስ ብቻ ይበቃል።  ሕንድ በጦር መሣርያና በኢኮኖሚ ቻይናን በልጣ ቻይናን አፍና እድትይዝላቸው ምዕራባውያን እየተጣጣሩ ያሉትም በዚሁ ምክኒያት ነው።

ምዕራባውያን ጋዛ ላይ ለሚያካሂዱት ጭፍጨፋ የሌላው ዓለም (በተለይም ደግሞ የሩሲያና የቻይና) ግብረመልስ በማውገዝ ብቻ የተወሰነ ከሆነ ፣ በተለይም ደግሞ ኮንግረሰኛው ጢሞ ዋልበርግ (Tim Walberg) እንዳለው ጭፍጨፋውን ለማፋጠን አሜሪቃ ኑክሌር ከተጠቀመችና በውግዘት ብቻ ከታለፈች ፣ ተመሳሳይ ጭፍጨፋ አፍሪቃ ላይ እንድትፈጽም አረንጓዴ መብራት (green light) በራላት ማለት ስለሆነ፣ ቦሪስ ጆንሰን (Boris Johnson) እንደዛተው አመቺውን ጊዜ ጠበቃ ወደ አፍሪቃ በቀጥታ በመዝመት አፍሪቃን ዳግማዊ ጋዛ ታደርጋታለች።  ለዚህ ደግሞ ኦክቶበር ሰባት (October 7) የሚባለውን አይነት ሰበብ (pretext) ትጠቀማለች ይልቁንም ደግሞ ትፈበርካለች (fabricate)።

አፍሪቃ ዳግማዊ ጋዛ እንዳትሆን ሙሉ በሙሉ ርግጠኛ መሆን የምትችለው ፣ የራሷን የኑክሌር አቅም ገንብታ፣ ምዕራባውያን ደግማዊ ጋዛ ሊያደርጓት ቢነሱ በኑክሌር እንደምትመታቸው በግልጽ ስታሳውቃቸው ብቻ ነው።  አፍሪቃ ከፍተኛ የተፈጥሮና የሰው ሐብት ያላት መሆኑንና ዘመናቸን የመረጃ ዘመን (information age) መሆኑን ከግምት ውስጥ ስናስገባ ደግሞ አንደኛ ደረጃ (first-rate) የኑክሌር መሣርያወችና መወንጨፊያወች ባጭር ጊዜ ውስጥ ለመስራት ላፍሪቃ ቀላል ነው ባይባልም ከባድ ግን አይደለም።

ታናናሾቹ ፓኪስታንና ሰሜን ኮርያ ኑክሌር መሥራት ከቻሉ፣ ግዙፏ አፍሪቃ የማትችልበትም ምንም ምክኒያት አይኖርም፣ በተለይም ደግሞ የሰሃራ በታች አገሮች አቅማቸውን ባንድነት ካሰባሰቡ።  አሜሪቃ የመጀመርያወቹን አቶሚክ ቦምቦች የሠራችበትን ዮራኒየም (uranium) ሙሉ በሙሉ ያገኘቸው ኮንጎ (Congo) ውስጥ ካታንጋ (Katanga) ክፍለሀገር ከሚገኘው የሽንኮሎብዌ (Shinkolobwe) ማዕድን ነበር።  የዚህ ማዕድን የዩራኒየም ጥራት 63% ሲሆን፣ አሜሪቃና ካናዳ የሚገኙት የሁሉም ማዕድኖች የዩራኒያም ጥራት ደግሞ በዛ ቢባል 0.03% ነው (ማለትም ካፍሪቃው ማዕድን ጥራት ሁለት ሺ ጊዜ ያነሰ ነው)።  ስለዚህም በዩራኒየም ጥራቱ ባለማቸን ወደር የሌለው የሽንኮሎብዌ (Shinkolobwe) ማዕድን ያፍሪቃን የኑክሌር ቦምብ በቀላሉ ለመሥራት የማያስችልበት ምንም ምክኒያት የለም።

አፍሪቃ ኑክሌር ለመታጠቅ የሚያስፈልጋት ነጭን ከመጤፍ የማይቆጥር፣ ነጭ ጥቁር ሕዝብ ላይ የሠራውን ግፍ በዓይነት ለማስከፈል ቆርጦ የተነሳ፣ ባፍሪቃዊነቱ የሚተማመን፣ አፍሪቃን የሚያስቀድም አፍሪቃዊ አመራር ብቻ ነው።

ኢትዮጵያዊ በመሆኔ ደግሞ ያፍሪቃን ኑክሌር መሣርያወችና መወንጨፊያወች ባስቸካይ ለመሥራት በስፋት ከሚሳተፉትና መሣርያወቹ ከሚተከሉባቸው የሰሃራ በታች አገሮች ውስጥ ኢትዮጵያ ቀዳሚ ብትሆን ደስ ይለኝ ነበር።  ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪቃ ያላት ምዕራብ አውሮጳን በቀላሉ መምታት የሚያስችላት ስትራቲጅያዊ አቀማመጥ ብቻውን በቂ ምክኒያት ነው።  ባለመታደል ግን ኢትዮጵያ ባሁኑ ጊዜ እየተመራች ያለቸው ኢትዮጵያውያንን በጎሳ ከፋፍሎ እየጨፈጨፈና እያጨፋጨፈ ኢትዮጵያን ለመበታተን ቆርጦ በተነሳ፣ የነጭን ፀረጥቁር አጀንዳ ለማስፈፀም ቀን ከሌት በሚተጋና ለዚህ ተግባሩ የኖቤል ሽልማት በተሸለመ፣ ዐብይ አሕመድ በሚባል ባውሬነቱ ወደር በሌለው ጎጠኛ ነው።

እንዲህም ሆኖ ግን፣ ኢትዮጵያ ያውሮጳ ቅኝ ገዥወችን አድዋ ላይ ድባቅ በመምታት ላፍሪቃ ነጻነት ተምሳሌት መሆኗን ከግምት ውስጥ በማስገባትና፣ አፍሪቃን ዳግም ለመውረር እየቀሰቀሱ ላሉት ለነ ቦሪስ ጆንሰን (Boris Johnson) ማስጠንቀቂያ ለመስጠት፣ ያፍሪቃን ኑክሌር መሣርያ ባጣዳፊ ለመሥራት የሚከፈተው ፕሮጀክት የትም ይሁን የት (ደቡብ አፍሪቃ፣ ሩዋንዳ፣ ጋና ወዘተ.) የፕሮጀክቱ ስም ግን አድዋ ፕሮጀክት (Adwa Project) ተብሎ ቢጠራ አግባብ ይመስለኛል።  የመጀመርያው የነጭ ኑክሌር ቦምብ በማንሃታን ፕሮጀክት (Manhattan Project) እንደተሠራ፣ የመጀመርያው ያፍሪቃ ቦምብ ደግሞ ባድዋ ፕሮጀክት (Adwa Project) ይሠራ።  አፍሪቃ ከማንሃታን ፕሮጀክት መቅሰፍት ራሷን መታደግ የምትችለው ባድዋ ፕሮጅክት ብቻ ነው።

 

መስፍን አረጋ

mesfin.arega@gmail.com

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ¹⁵ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ ፥ ¹⁶ ተራራዎችንና   በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን ፤ ¹⁷ ታላቁ የቁጣው ቀን  መጥቶአልና ፥ ማንስ ሊቆም ይችላል ? አሉአቸው ። ራእይ 6 ፤  15_17 ይኽ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ። የኢየሱስን ልደት ሰናከብር የየሐንስ ራእይን ማንበብ ጠቃሚ ይመስለኛል ። ምክንያቱም በመጨረሻው ዘመን

ከኢየሱስ የፍርድ ቀን በፊት በህሊናችን ውስጥ ፍቅርን ለማንገስ እንጣር 

የምጣኔ ሀብታዊ ፍጥ፣ የፖለቲካ፣ የእውነትና የሰብአዊ መብት ታጋይ፣ የአመኑበትን ነገር ለመናገር እንደ ፖለቲከኛ በቃላት ሳያሽሞነሙኑ ቀጥታ የሚናገሩት የሀገሬ ኢትዮጵያ ታላቅ ሰው ነበሩ “ዘር ቆጠራውን ተዉት፤ የአባቶቻችሁን ሀገር ኢትዮጵያን አክብሩ!”  አቶ ቡልቻ ደመቅሳ

ሀገር ወዳዱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

January 6, 2025
ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ? ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። ) “ገብርዬ ነበረ

ግን ይህ ሁሉ ወጣት የት ገባ?

January 3, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ዛሬ እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ጥር 1ቀን 2025 ዓ/ም ነው ። አውሮፓውያኑ አዲስ ዓመትን “ሀ” ብለው ጀምረዋል ። አዲሱን ዓመት ሲጀምሩም ከልክ ባለፈ ፈንጠዚያ ነው ። ርቺቱ ፣ ምጉቡና መጠጡ

ዛሬ፣ 2025 ዓ/ም ላይ ብንገኝም በዝንጋታ ገመድ ወደ ሞት እየተጎተትን እንደሆነ አናውቅም። (ሁል ጊዜ የሚሞተው የገነዝነው ይመስለናል። )

Go toTop