መስከረም አበራ በቅርቡ ከቃሊቲ ስለፃፈችዉ 94-ገፅ ፅሁፍ

April 7, 2024

meskeremሰሎሞን ገብረስላሴ

እስር ቤት ተወርዉረዉ ፅሁፎችን የፃፉ የታወቁ የፖለቲካ ሰዎች ጥቂት ናቸዉ፡፡ እስር ቤት ዉስጥ ሆኖ ፅሁፍ መፃፍ ማለት፤ እስር ቤት የወረወራቸዉን አምባገነናዊ አገዛዝ መፀየፋቸዉን ማረጋገጫና በአላማቸዉም ቢታሰሩ እንኳን በፅናት መቀጠላቸዉን ማሳያ ነዉ፡፡ ለተከታዮቻቸዉ የትግል ተስፋ ይሆናል፤ የትግሉን መንገድ ለማሳየትም ብርሃን ይፈነጥቃል፡፡

ከነዚህ ጉምቱ ፖለቲከኞች መካከል አንዱ የታወቀዉ ያንድ ወቅት የጣሊያን ኮሚኒስት ፓርቲ መሪ የነበረዉና በስነፅሁፎቹ የሚታወቀዉ አንቶንዮ ግራምቺ ነዉ፡፡ ግራምቺ ኢትዮጵያን በ1935 እኤአ የወረረዉ የጣሊያን የፋሽስት መንግስትን ፖሊሲ ተቃዋሚ ኮሚኒስት ሲሆን፤ ፋሽስቱ መንግስት በዚህ ተቃዉሞዉ በ1926 አም እስር ቤት ያጎረዉ ታጋይ ነበር፡፡ እስር ቤት እያለ “የእስር ቤት ማስታወሻዎች” በሚል ርእስ 33 ፅሁፎችን ኣቅርቧል፡፡ እነዚህ ፅሁፎች ባመዛኙ ባህል በፖለቲካና በኢኮኖሚ ላይ ያለዉን ተፅእኖ በንድፈ ሃሳብ ደረጃ ያብራሩ ፅሁፎች ሲሆኑ፤ እስካሁን ድረስ በአለም ታዋቂነት ያተረፉ ናቸዉ፡፡ ከ8 አመት እስር በሆዋላ ሲለቀቅ፤ ብዙም ሳይቆይ ከ3ኣመታት በሆዋላ ኣርፎኣል፡፡

ሁለተኛዉ ታዋቂ ፖለቲከኛ ጥቁር ኣሜሪካዊዉ ማርትን ሉተር ኪንግ ነዉ፡፡ በርሚንግሃም በተባለዉ በአላባማ ክፍለሀገር ከተማ በታሰረበት ወቅት ከእስር ቤት የፃፈዉ 6 ገፅ ደብዳቤ ዝነኝነትን ኣትርፎኣል፡፡ ደብዳቤዉ “ከበርሚንግሃም እስር ቤት ደብዳቤ” የተባለ ሲሆን፤ የተፃፈዉ April 16, 1963 ነበር፡፡ የደብዳቤዉ ይዘት፤ የመብት ታጋዮች ፍርድ ቤቶች ፍትህ ያመጣሉ ብለዉ መጠበቅና መለማመጥ ትተዉ ፍትህ አልቦ ህጎችን ዜጎች የመታገልና በህጎቹ ላይ የማመፅ መብት እንዳላቸዉ የሚያስረዳ ነበር፡፡ ይህ ደብዳቤ ለሰብኣዊ መብቶች (civil rights) ትግል መድመቅ ትልቅ ኣስተዋፆ ከማድረጉም በላይ civil disobedience ለሚባለዉ ጠንካራ ሰላማዊ ትግል አጋዥ ሆኖኣል፡፡

በኢትዮጵያ ከታወቁት የፖለቲካ እስረኞች መካከል ደጋግማ ፅሁፎችን ከእስር ቤት በማበርከት የምትታወቀዉ መስከረም አበራ ናት፡፡ እዚህ በምንመለከተዉ 94-ገፅ ፅሁፍ፤ መስከረም ብዙ ጉዳዮችን ትዳስሳለች፡፡ የፅሁፉ ርእስ “የኣማራ ህዝብ ጥያቄዎች” የሚል ሲሆን የተፃፈዉ መጋቢት 2016 ነዉ፡፡ የፅሁፉ ርእስ የአማራ ህዝብ ጥያቄዎች ይሁን እንጂ፤ መስከረም በዚህ ዘለግ ባለ ፅሁፍ ከጥያቄዎቹ ባሻገር የህዝቡን ታሪክ፤ ትግልና ስነልቦና በሰፊዉ ሂዳበታለች፡፡

በኣማራ ህዝብ ላይ የደረሱትን በደሎች በጣም በዝርዝር ከስር መሰረቱ አትታለች፡፡ እነዚህን በደሎች በተለያዩ ጊዜ የሰማናቸዉና ያየናቸዉ ቢሆኑም፤ ዝርዝር ጉዳዮችን ህይወት ለመስጠትና በደሎቹ ካሳ የሚያገኙበትንና በተለይም እንዳይደገሙ ለማድረግ የአማራ ምሁራን የሚባለዉ ድርጅትና (ተባባሪዎቹ ሌሎች ኢትዮጵያዉያን)  ከመስከረም በዱላ ቅብብሎሽ የስራ ክፍፍል አድርጎ ቅድመ ዝግጅት ሊያደርግበት ይገባል፡፡ ለምሳሌ ከወለጋና ቤኒሻንጉል የተፈናቀሉና ንብረታቸዉ የተዘረፈ፤ የተቃጠለ፤ ወዘተ ኢኮኖሚስቶች የንብረታቸዉን ግምት በማስቀመጥ በሽግግር ፍትህ ወቅት ካሳ ሊያገኙ የሚችሉበትን መንገድ ቅድመ ዝግጅት ሊያደርጉበት ይገባል፡፡ በተመሳሳይ መስከረም በዝርዝር የሄደችባቸዉን በኣማራዉ ላይ የተደረጉ ሃሰተኛ ትርክቶች እንዴት አይነት እንደሆኑና ከትምህርት ቤት መፅሃፍት ጀምሮ እስከ ህገመንግስቱ ድረስ መስተካከል የሚገባቸዉን የታሪክ ምሁራን ለይተዉ አዉጥተዉ ቅድመ ዝግጅት ሊያደርጉበት የሚገባ ነዉ፡፡ በቀጣይም በዚህ አገዛዝ የወደሙ ታሪካዊ ቅርሶችን ለይቶ በማዉጣት እንዴት ሊተኩ የሚችሉበትን፤ ካልተቻለ ደግሞ ተመጣጣኝነት ያለዉ ታሪካዊ ቅርስ የሚዘጋጅበትን ሊያስቡበት ይገባል፡፡ በተጭማሪም በወያኔ በተመሰረቱ ክልሎች ሆን ብሎ አማራዉን ለመጉዳት ግዛቶቹን ለአጎራባች ክልሎች ቆርሰዉ እንደሰጡበት ትናገራለች:: ይህንንም በሚመለከት እነዚህ ምሁራን በወደፊት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ የክፍለ ኣገር ክፍፍል እንዴት ሊሆን እንደሚገባ ማመላከት ይጠበቅባቸዋል፡፡

መስከረም በድፍረት የኣማራ ምሁራን ያለባቸዉን ስንፍናም ኣትደብቅም፡፡ ለፈረንጆች ኣማራዉ ያለበትን ሰቆቃ በተደጋጋሚ ማስረዳት ሲያቅተዉ የኣማራዉ ምሁር “ፈረንጆች ኣማራ ኣይወዱም” የሚል ተልካሻ ሃሳብ እንደሚያቀርብ ትናገራለች፡፡ (ገፅ 51)

አገዛዙ የኣማራ ጭቆናን ትኩረት እንዴት እንደነፈገዉ መስከረም ዝርዝር ዘዴዎችን ታሳያለች- ከጠቀሰቻቸዉ መካከልም ዝምታ፤ ማድበስበስ፤ መካድና መሳለቅን የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡ ከነዚህ አንዱ የሆነዉ በኣማራ ክልል ያሉ ልዩ ዞኖች መኖራቸዉ ተገቢና ዴሞክራሲያዊ መሆኑን አዉስታ፤ ነገር ግን ዞኖቹ ኣማራን ለማጥቃት መሸሸጊያና ዋሻ እንደሆኑ በማሳየት ነዉ- ለምሳሌ ከሚሴ፡፡ ባንፃሩ በኦሮምያ ክልል ዉስጥ ያሉ ኣማሮች ምንም አይነት የልዩ ዞን የመብት ጥበቃ እንደኤሌላቸዉ ታሳያለች፡፡ ይህ መብት የለሽነት ሌሎችም ኦሮሞ ያልሆኑ ኢትዮጵያዉያን ከኣማራዉ ጋር የተነፈጉት መብት መሆኑ የታወቀ ነዉ፡፡

ሌላዉ መስከረም የምታነሳዉ እንዴት ባእዴንና ኣገዛዙ ኣማራዉን በመንደርተኝነት ለመከፋፈል ተግተዉ እንደሚሰሩ ነዉ፡፡ ኣማራዉ ራሱም ለዚህ ተመቻችቶ መገኘት እንደሌለበት አፅንኦት ሊሰጠዉ የሚገባዉ ጉዳይ ነዉ፡፡ ለምሳሌ መስከረም ባታነሳዉም ዛሬ ላይ የምናየዉ የፋኖ መሪዎች በተከፋፈለና በተሰነጣጠቀ ሁኔታ ለየክፍለኣገሩ በተናጠል ከዲያስጶራዉ ገንዘብ ለመሰብሰብ የሚያደርጉት ሙከራ ከፋፋይ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡

መስከረም ኣዳዲስ ሃሳቦችንም በፅሁፉዋ ታስተዋዉቃለች፡፡ ለምሳሌ ኣማራ ጠል የሆነዉ ስርአት ከአማራዉ ጋር ያለዉ ልዩነት የፖለቲካ የሃሳብ ልዩነት ሳይሆን የሰብ አዊ ልዩነት ነዉ በሚል የኣፓርታይድ ስርኣትና የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋን በአስረጅነት ታቀርባለች፡፡ እንደመፍትሄም አማራዉ መብቱን ለማስከበር ስልጣን መያዝ አለበት ትላለች፡፡ መስከረም ኣማራዉ ስልጣን መያዝ አለበት ስትል ብቻዉን የስልጣን ባለቤት ይሁን አለማለቱዋ ከፅሁፍዋ መቸት በቀላሉ ይታያል፡፡ ኣማራዉ ከስልጣን ሆን ብሎ ስለታገደና ስለተገለለ ህልዉናዉ ራሱ አደጋ ላይ የወደቀበት ህዝብ ነዉ በማለት፤ ይህን ለመለወጥ ከወንድሞቹ ጋር በእኩልነት ስልጣን መጋራት አለበት ማለቱዋ ነዉ፡፡  ይህ ደግሞ ዘርን ማእከል ያላደረገ፤ የግለሰብና የቡድንን መብት ያረጋገጠ ዘመናዊ ህገመንግስት ሲዋቀር መልስ ያገኛል፡፡

የመስከረምን ብልህነት ያየሁበት፤ በኣማራ ጭቆና ላይ የሚፅፉም ሆነ የሚናገሩ ሰዎች ታሪካዊ ዳራዉን ሊያሳዩ ሲሞክሩ የ60ዎችን ትዉልድና የተማሪዉን እንቅስቃሴ በግልብነት በጅምላ በመኮነን ነዉ፡፡ መስከረም እንዲህ አይነት ቅሌትና ኢ-ምክንያታዊነት ኣይታይባትም፡፡ ገፅ 83 ላይ ብቻ አንድ ነገር ብላለች፡፡ ይሀዉም ስለ ጃዋር የኣቋም ለዉጥ ጉዳይ ስታጠቃልል ነዉ፡፡ እንዲህ ትላለች- “ስለ ጃዋር መብሰል አለመብሰል እንየዉ ከተባለ ሃገራችን ባልበሰሉ ፖለቲከኞች አንደበትና ብእር መዘዝ አሳር መከራ የመቁጠሩዋ ነገር በዋለልኝ መኮንን  ይብቃ ያልተባለ ክፉ እዳዋ እንደሆነ ተገንዝበን ማዘናችን አይቀርም፡፡”

ዋለልኝ በርግጥ አነጋጋሪ ፖለቲከኛ ነዉ፡፡ ሆኖም ብስለቱን በሚመለከት አጠያያቂ አልነበረም፡፡ በኢትዮጵያ ዉስጥ ታላላቅ ከሚባሉት አንዱን የብሄረሰቦች ጭቆናን በድፍረት ማንሳቱ ብስለቱን ያሳያል፡፡ ችግሩ በኔ እይታ ዋለልኝና ጓዶቹ ሙሉ ስእሉን ለማየት ኣለመቻላቸዉ፤ ሃገረ መንግስት ለመመስረት የጋራ ቋንቋና ስነልቡና ኣስፈላጊነትን ለማየት መቸገራቸዉ ነዉ፡፡ በማጠቃለል መስከረም በኢትዮጵያ ካሉ ወጣት ፖለቲከኞች መካከል ስትገኝ፤ በተለይ በትግሉ የንድፈ ሃሳብ ጥራትን ለማምጣት በምታደርገዉ ጥረት ግምባር ቀደም ነች፡፡ ይህንን ችሎታዋን በመፍራት ኣገዛዙ በእስር እንድትማቅቅ እያደረገ ነዉ፡፡ ከብእራቸዉ ሌላ ሃይል የሌላቸዉን መስከረምንና ጓዶችዋን (ለምሳሌ ታዴዎስ ታንቱ) ከራሱ እስከ ጥፍሩ የታጠቀዉ ሃይል ለምን እንደሚፈራቸዉ የኣምባገነኖችን ታሪክ ገለጥ ኣድርጎ በጨረፍታ በማየት ግንዛቤ ማግኘት ይቻላል፡፡

ሚያዝያ 2016

__

1 Comment

  1. Excellent piece with the exception of the section on Walelign.
    Walelign is not original in any shape or form. Typical of what happened in his generation, he was at best, someone who did a ‘copy-paste’ from Marxism-Leninism. The so called national question has been in circulation since before Walelign’s parents were born. Closer to the truth is that the Eritrean liberation movement, which had resolved to weaken the interior so as to facilitate Eritrean secession was the source of Walelign’s borrowed, uncharacteristic and inflated characterization of the national question in Ethiopia.
    The irony of the matter is that while Walelign was a Wolloye, the brunt of the consequences of the fire he ignited has consumed millions of Wollo people and, according to the threats of the Wallelignites, all of it appears to be only the beginning of the trials and tribulations for the people of Wollo as they are claimed by the various ethnic warlords.

Leave a Reply

Your email address will not be published.

189666
Previous Story

አርበኛ ዘመነ ካሤ አዲስ ፋኖ አስመረቀ | ቀጥታ ከስፍራው | የምሥራቅ አማራ ፋኖ የቪድዮ መልእክት |

189671
Next Story

ጄነራል አበባው ጦር ሜዳ ጉድ ሆነ | ኮረኔል ደመቀ ዘውዱ ኑና ግጠሙን አሉ | ጎንደር የአብይ ሰራዊት ጉድ ሆነ ተደመሰሰ ሸዋ ታላቅ ድል

Go toTop