March 10, 2024
ይህ ለርዕሰ ጉዳይነት የተጠቀምኩበት አጭር አባባል ከተራ ኮሜዲያንነት ወደ ታዋቂ የማህበራዊ ሚዲያ ቢዝነስ ባለቤትነት የተሸጋገረው እሸቱ መለሰ ከኢቢሱ (EBS) ሰይፉ ፋንታሁን ጋር ባካሄደው እና ያምርልናል ባሉት ግን አስቀያሚ በሆነ (ወደ ላይ በሚያስመልስ አይነት ተውኔተ ቀልድ ) በታጀበ አቀራረብ ባካሄዱት የተጠየቅና የእንጠያየቅ ፕሮግራም ላይ “በኢትዮጵያ እስከ ዛሬ ድረስ ያንተ ምርጥ መሪ ማን ነው” ለሚል ጥያቄ የሰጠው እጅግ አስተዛዛቢ ብቻ ሳይሆን በእጅጉ የሚረብሽ የአድርባይነት ምንነትና ማንነት የወለደው (the very result of an identity of deeply disturbing opportunism ) መልስ ነው።
እንኳንስ የአገር ሰው የትኛውም ሰው በተሰጠው ተሰጥኦ ወይም በሰለጠነበት ሙያ ወይም በተሰማራበት የሥራ መስክ እና እልህ አስጨራሽ በሆነ ጥረት የተዋጣለት የግል ህይወት ባለቤት ቢሆን ቅር የሚለው የጤናማ ህሊና ባለቤት የአገሬ ሰው የሚኖር አይመስለኝም።
የግለሰቦች ስኬታማ ህይወት የተወለዱበትን፣ ያደጉበትንና ፊደል ቆጥረው ለቁም ነገር የበቁበትን ህዝብ ወይም ማህበረሰብ እና ተጨባጭ እውነታ እያስረሳና በግልብ ስሜት እያስጋለበ ሲያስቸግራቸው ግን የግል ሰብእና፣ የግል አስተሳሰብ/አመለካከት ፣ የግል ሞት ወይም ሽረት ከመሆን ስለሚያልፍ ቆም እያላችሁ አደብ ግዙ ማለት የግድ ይሆናል።
እንደ እሸቱ አይነቶች የወጣት ወይም የጎልማሳ ትውልድ አባላትም ውጤታማነታችሁን አደብ እየገዛችሁ አስኪዱት ወይም ያዙት መባል ያለባቸው ከዚሁ መሠረታዊ እሳቤ አንፃር መሆኑ ግልፅና ግልፅ መሆን አለበት።
ምንም እንኳ የእሸቱን አስተሳሰብና አካሄድ ማሄስ (መተቸት) ከጭፍን ጥላቻ አልፎ ራሱን ፈጣሪን ማስቀየም እንደሆነ የሚቆጥሩ በአብዛኛው የዋህና በጥቂቱ ግን የራሳቸው ፍላጎት (ulterior motive) ያላቸው ወገኖች መኖራቸውን ባውቅም ከአሁን በፊት የሰነዘርኩትንና አሁንም የማምንበት ሂሳዊ ትችት ከዚህ በታች ደግሜ እለዋለሁ። ምክንያቱም ያንን የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረትን በእጅጉ የሚሻን መከረኛ ህዝብ (በፈጣሪ አምሳል የተፈጠረ ወገን) ትተን ጊዜ በሚሰጠን ጉዳይ ዘመቻ ላይ የመጠመዳችን ውድቀት ይኸውና ፖለቲካ ወለድ መከራውና ሰቆቃው እጥፍ ድርብ እየሆነ እንዲቀጥል እድል ሰጥተነዋልና ነው ።
እናም የእሸቱ የስኬታማነት መሠረትና ሂደት ጥያቄ ውስጥ የገባው የተወለደበት፣ ፊደል ቆጥሮ ያደገበትና ለቁም ነገር የበቃበት መከረኛ ህዝብ ከሩብ ምዕተ ዓመት በላይ በህወሃት የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኞች የበላይነት በተቃኘው (በተመራው) እና ከስድስት ዓመታት ወዲህ ደግሞ የዚያው ሥርዓት ውላጆች በሆኑ ተረኞች እየተመራ ባለው አገዛዝ የገዛ ምድሩ ምድረ ሲኦል በመሆኗ የወገን ያለህ የሚል የሰቆቃ (የመቃብር ውስጥና የቁም ሙትነት) ጩኸት እያሰማ ባለበት ወቅት ምንም እንዳልተፈጠረ በሚያስመስል ሁኔታ ባህር ማዶ ለሚገነባ “ታሪካዊ” ገዳምና ቤተ ክርስቲያን የቅድሚያ ቅድሚያ በመስጠት “በአያሌ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር መስጠት የፅድቅ መንገድ ነው” በሚል ዘመቻ ላይ የተጠመደ እለት እና ዶላሩን ከመሻማት ይልቅ “የወገንን ነፍስ መታደጉ ይቅደም” የሚል የሃይማኖት መሪ ፈልገን ማግኘት ያልቻልን እለት ነበር።
በተወሰነ ሙያ ወይም ተሰጥኦ ታዋቂነት (popularity) ማግኘት ሁሉን ነገር ማወቅ ማለት ከቶ እንዳልሆነ አውቀን በዚህ የተሳሳተ እሳቤ/ግንዛቤ ተሸንፈው “ሃይማኖታዊ እውቀትን ጨምሮ ሁሉን ማወቃችን እወቁልን” የሚሉ ደካማ ወገኖችን በወቅቱና በአግባቡ አደብ ግዙ ለማለት ባለመቻላችን ይኸውና ዛሬም ከእኛና ከአፍሪካ አልፎ በቅኝ ግዛት ቀንበር ሥር ለነበሩ የዓለም ህዝቦች ሁሉ ያለአንዳች ማቅማማት በአርአያነት የሚጠቅሷቸውን የአገራችን መሪ (ምኒልክን) በታላቅ መሪነት መጥቀስን ከሌሎች ጋር ያቀያይመናል ሲሉ ጨርሶ ሃፍረት ወይም ወራዳነት የማይሰማቸው እሸቱዎችን “አፍርተናል”። ሲሆን ያለምንም ገላጭ ቅጥያ ካልሆነ ደግሞ “እንከን የለሽ ነበሩ ባልልም አፄ ምኒልክን አደንቃለሁ” ለማለት የታሪክ ባለቤትነት ኩራትና የሞራል ልእልና በእጅጉ የሚገዳቸው የዚህ ትውልድ አባላት እሸቱዎችን አሁንም ቢሆን አደብ ይገዙ ዘንድ በግልፅና በቀጥታ መንገር የግድ ነው።
በመሠረቱ የትኛውም የፖለቲካ ሥርዓት በረጅሙ የአገርነት ታሪካችን ሂደት ከተፈፀሙ የአገር ውስጥ አስቀያሚ ስህተቶች ነፃ አልነበረም ፤ እንዲሆንም አይጠበቅም ። ይህ ደግሞ የጥፋቱ አይነትና መጠን ሊለያይ ቢችልም የሁሉም አገር የአገራዊነት የታሪክ አካል እንጅ የእኛ ብቻ አይደለም ፤ ሊሆንም አይችልም ። እናም በተለያየ የታሪክ ምዕራፍ (ኩነት) በአገር መሪነት ስለ ተነሱ የአገራችን መሪዎች ስንነጋገር፣ ስንመሰክር እና ብሎ አድናቆታችን ስንገልፅ አንዳቸው ከሌላው በተሻለ የተጫወቱትን ታሪካዊ ሚና ከሠሩት ስህተት አንፃር እያገናዘብንና እየተረዳን እንጅ ከፍፁማዊነት አንፃር ወይም ከእንከን አልባነት አንፃር አይደለም ፤ እናድርገው ብንልም ከቶ ሊሆን አይችልም። ተሳክቶልን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ብንመሠርትም እንኳ በመሪነት ላይ የሚሰየሙ ፖለቲከኞችም ሆኑ ሥርዓቱ እንደ ሥርዓት እንከን የለሽ ሊሆን አይችልም።
በዚያ በሁሉም ዘርፍ እጅግ ኋላ ቀር በሆነ ዘመንና ተጨባጭ ሁኔታ ውስጥ አስተባብረውና መርተው አገርን እንደ አገር ማቆየት ብቻ ሳይሆን ዘመናዊ ት/ቤት፣ ስልክ፣ የባቡር ሃዲድ እና መሰል ጠቃሚ ነገሮችን ያስተዋወቁ መሪን አደንቃለሁ ብሎ መናገር ከሰው ጋር ያቀያይመኛል ብሎ ከማሰብ አልፎ በግልፅና በቀጥታ መናገር እጅግ ወራዳና አዋራጅ አስተሳሰብ ካልሆነ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል? እንዲህ አይነቱ ጨካኝ አድርባይነት የሚነግረን ይህ ትውልድ የሶሻል ሚዲያ ወይም የሌላ አይነት ቢዝነሳቸው (ጥቅማቸው) በምኒልክ ጠሎች ከሚጎዳባቸው ዓለም በስፋትና በይዘት የሚያውቀውንና የሚያደንቀውን የምኒልክን ታላቅ መሪነት “ሁሉም መሪ የየራሱ ኳሊቲ ስላለው ምርጥ የምለው መሪ የለም” የሚል አደገኛ አድርባይነትን ነው።
በትናንትናው እለት ደግሞ “ዕፁብ ድንቅ ልጆች” በሚለው ፕሮግራሙ አንዲት ደስ የምትል እንቦቃቅላ አቅርቦ እርሱ ራሱ ደፍሮ ተናግሮት የማያውቀውንና የማይናገረውን የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማሩን እጅግ አስከፊ በሆነ ደረጃ እያስኬዱት ባሉት እኩያን ገዥዎች ምክንያት እንኳንስ የህፃናትን የአዋቂንም አእምሮ በእጅጉ የሚረብሸውን የጦር መሳሪያ ድምፅ (ፍንዳታ) በእርሷ አንበት እንድትናገረው ማድረጉን ታዝቤያለሁ።
ከአሁን በፊት እንዳልኩት ተገቢና ፈጥኖ ደራሽ የሆነና የህፃናትን ሥነ አእምሮና ሥነ ልቦና የሚንከባከብ ሥርዓት በሌለበት ሁኔታ ውስጥ ለጋ ህፃናትን በየአዳራሹና በየመድረኩ እያቀረቡና “በተኩስ ተሳቀቅሁኝ /ተሳቀቅን” የሚልና እንኳን ለህፃን ለአዋቂም የሚከብድ (ህሊናን የሚረብሽ) ነገርን እያናገሩ የሚዲያ ቢዝነስ ማሳለጫ ማድረግ ፈፅሞ ትክክለኛ ነገር አይደለም ፤ ከነውርም ነውር ነው።
እናም እንደ እሸቱ የመሰሉ ወጣት/ጎልማሳ የዚህ ትውልድ አባላት በጎ ህልማቸውና ጥረታቸው አስተማማኝና ዘላቂ መሆን ካለበት ደካማ ጎናቸውን በግልፅና በቀጥታ መንገር እና በጎ ጎናቸውን ደግሞ ማበረታት እንጅ “እሸን የነካ ወዮለት ወይም ፈጣሪን እንደ መንካት ነው ወይም ምቀኝነት ነው ወይም ጨለምተኝነት ነው ፣ ወዘተ” የሚልና ግልብ ከሆነ ጊዜያዊ ስሜት የማያልፍ ተከላካይነት ፈፅሞ አይጠቅምም።