ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝም “ዳኛው ይነሱልኝ” ብሎ በመጠየቁ አንድ ሺሕ ብር እንዲቀጣ ተፈረደበት

ጋዜጠኛ ተመስን ደሳለኝ የቀረበበትን ይግባኝ ከሚመለከቱት ዳኞች መሃል የግራ ዳኛው አቶ መሐመድ አሕመድ ከዚህ ቀደም በዚሁ መዝገብ በሰጡት የተሳሳተ ትዕዛዝ ምክንያት “በቀጣይ ትክክለኛ ፍትሕን ሊሰጡኝ ስለማይችሉ ይነሱልኝ” ሲል ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ያቀረበውን አቤቱታ ችሎቱ በዛሬው ቀን ትእዛዝ ሰጥቶበታል፡፡

ጋዜጠኛ ተመስገን ቅሬታውን ያቀረበው ጥር 7/2016 ዓ.ም ሲሆን፤ ውሳኔ ለመስጠት ለጥር 28/2016 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቶ ነበር፡፡ ይሁንና፣ በጥር 28ቱ ቀጠሮ እንዲነሱ “አቤቱታ የቀረበባቸው ዳኛ ስልጠና ላይ ስለሆኑ ውሳኔ አልሰጠንም” በሚል ለዛሬ የካቲት 21/2016 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቶ ነበር፡፡ ሆኖም፣ ከችሎት እንዲነሱ ቅሬታ የቀረበባቸው ዳኛ “አልነሳም” ብለዋል፡፡

በዛሬው ቀጠሮም፣ የችሎቱ ሰብሳቢ ዳኛ አቶ ሸምሱ ሲርጋጋ በንባብ ባሰሙት ትዕዛዝ “እንዲነሱ የተጠየቁት ዳኛ መልካም ስብዕና ያለቸው መሆኑን” በመጥቀስ ጥያቄውን ውድቅ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

ትእዛዝን በተመለከተ አስተያየቱን የገለጸው ጋዜጠኛ ተመስገን “የፍርድ ቤቱ ትእዛዝ እኔን ስጋት ላይ የጣለ ነው” ብሏል፡፡ ጋዜጠኛው ለዚህ ቅሬታው “መሰረታዊ ነው” ያለውንም ነጥብ አስቀምጧል፡፡ “ያቀረብኩት አቤቱታ፣ ዳኛው ከዚህ ቀደም በሰጡት ትዕዛዝ ዐቃቢ ሕግ ያልጠየቀውን ዳኝነት እንዲካተት አድርገው ከሳሽን ያለአግባብ በመጠቅማቸው፣ እኔን ጉዳት ላይ የሚጥል ትዕዛዝ መስጠታቸውን የተመለከተ ነው፡፡ ስለዚህም ፍርድ ቤቱ በቀረበለት ቅሬታ መሰረት ‹ዳኛው ስህተት ሠርተዋል ወይስ አልሠሩም?› ወይም ‹ከሳሽ ያለአግባብ ጠቅመዋል ወይስ አልጠቀሙም?› የሚለውን መመርመር ሲገባቸው፤ ይህን ዋንኛ ጉዳይ ወደጎን ብሎ የቀድሞ ስብእናቸውን መነሻ በማድረግ ቅሬታዬን ውድቅ መደረጉ እጅጉን አስደንግጦኛል፡፡” ብሏል።

ፍርድ ቤቱ ጋዜጠኛው ያቀረበውን ተጨባጭ ቅሬታ ወደጎን ትተው፤ “ዳኛው ይነሱልኝ” የሚል ቅሬታውን ስላቀረበ አንድ ሺሕ ብር መቀጮ እንዲከፍል ተፈርዶበት፣ የተባለውን ክፍያ ከፈጸመ በኋላ ከጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ግቢ ሊወጣ ችሏል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ድምጻችን ይሰማ መግለጫ አወጣ፦ "በህዝበ ሙስሊሙ ወኪሎች ላይ በማረሚያ ቤት እየተደረገ ያለው ወከባ በአስቸኳይ ይቁም!"

ጋዜጠኛው ላይ የቀረበውን የይግባኝ መልስ ለመስማት ለመጋቢት 16/2016 ዓ.ም ቀጠሮ ተስጥቷል፡፡

ጌታቸው ሽፈራው

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share