ኤፍሬም ማዴቦ (emadebo@gmail.com)
ከ3ሺ አመታት በላይ ያስቆጠረ ተከታታይ የስርዓተ መንግስት ታሪክ ያለው የኢትዮጵያ ህዝብ በሚቀጥለው ወር የአንድን ትልቅ ታሪካዊ ክስተት ሃምሳኛ አመት ያከብራል። ጥር ወር አልቆ ወርሃ የካቲት ሲገባ፣የኢትዮጵያን የፖለቲካ ገፅታ ላንዴና ለመጨረሻ ግዜ የቀየረው የየካቲት 66ቱ አብዮት ሃምሳ አመቱን ይደፍናል። ከየካቲት 1966 እስከ ግንቦት 1983 ድረስ ባሉት 17 አመታት ውስጥ ኢትዮጵያ ሁለት ስር ነቀል አብዮቶችን አካሂዳለች። ባለፉት ሃምሳ አመታት የኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ልማትና መልካም አስተዳደር እናስፍናለን የሚሉ ሶስት መንግስታትን፣ለፍትህ፣ ለነጻነትና ለዲሞክራሲ እንታገላለን የሚሉ የትየለሌ ድርጅቶችን፣የብሔር ነጻ አውጪዎችንና በርዕዮተ አለም አሰላለፋቸው ሶሻሊስቶችን፣ ሊብራል ዲሞክራቶችን፣ሶሻል ዲሞክራቶችንና ምን አይነት ርዕዮተ አለም እንደሚከተሉ በውል የማያውቁ ግራ የተጋቡ የፖለቲካ ፓርቲዎችን አስተናግዷል። ይህ ሁሉ ከሆነና አገራችን ኢትዮጵያ በ17 አመት ልዩነት በሁለት ተከታታይ ስር ነቀል አብዮቶች ከታመሰች ከሃምሳ አመት በኋላ ዛሬም ኢትዮጵያ ውስጥ በፍጹም መልስ ያለገኘው ጥያቄ በ1950ዎቹና በ196ዎቹ የተጠየቀ የፍትህ፣ የነጻነትና የዲሞክራሲ ጥያቄ ነው።
አገራችን ኢትዮጵያ ብዙ ችግሮች ያሉባት አገር ናት። ችግሮቿ በአይነትም በመጠንም ብዙ ናቸው፣ ሆኖም ከችግሮቿ ሁሉ የከፋውና ዛሬ ላይ ለሚታዩት ብዙ ችግሮች ምንጭ የሆነው የፖለቲካ ሥርዓታችን የተዋቀረበት መንገድ ወይም ፖለቲካችን የገባበት ቀውስ ነው። ወታደራዊው ደርግ የፊውዳሉን ሥርዓት ሲያፈርስ የኢትዮጵያን ህዝብ ለረጂም ዘመን እንደሙጫ አጣብቀው እንደ አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ ያቆሙትን ማህበራዊ እሴቶች አብሮ ነው ያፈረሰው። ደርግ እሱ እራሱ የማያውቀውን ሶሻሊስት ሥርዓት እገነባለሁ በሚል ኢትዮጵያ ውስጥ ሁለቱን ትልልቅ ዘርፎች (ግብርናና እንዱስትሪ) እንዲሽመደመዱ አድርጓል። ህወሓት/ኢህአዴግ ደግሞ የኢትዮጵያን ፖለቲካ በብሔር ላይ በማዋቀር ኢትዮጵያዊያ ህዝብ በብሔር አጥር ታጥሮ እንደ አንድ አገር ህዝብ አንድ አንድ ላይ እንዳይቆም ከማድረጉ ባሻገር፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ከማህበራዊ እሴቶቹ ጋር ብቻ ሳይሆን ከቀድሞው ታሪኩና “ኢትዮጵያዊ” ከሚባል ማንነቱ ጋር እንዲጣላ አድርጓል።
ፖለቲካችን ቀውስ ውስጥ መግባቱ የኤኮኖሚ ቀውስ ፈጥሯል። የኤኮኖሚ ቀውሱ ደግሞ በፍጥነት እያደገ የሚሄድ ድህነትን፣ ስራ አጥነትን፣ ስደትን፣ ከገጠር ወደ ከተማ ፍልሰትን፣ የዋጋ ንረትን፣ የኑሮ ውድነትን፣ በዜጎች መካከል ከፍተኛ የገቢ ልዩነትን ወዘተ ፈጥሯል። ከዚህ በተጨማሪ ባለፉት ሃያ አምስት አመታት መንግስት ከውጭና ከአገር ውስጥ አበዳሪዎች የተበደረው ከፍተኛ ብድር የአገሪቱን ሎዓላዊነት መፈታተን በሚችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል። ይህ መጠኑ ከፍተኛ የሆነ ብድር በአንድ በኩል መጪውን ትውልድ ዕዳ ከፋይ አድርጎታል፣ በሌላ በኩል ደግሞ በአገራችን የወደፊት የዕድገት ዕቅድና ቅደም ተከተል ላይ ከፍተኛ ጫና ያደርጋል። የፖለቲካና የኤኮኖሚ ቀውስ አንድ ላይ ሆነው የሞራል መላሸቅን፣ በራስ አለመተማመንን፣ምን አገባኝን፣ ዋልጌነትን፣ ግድ የለሽነትን፣ስርአተ-አልበኝነትን፣ ወንጀልን፣ ሙሰኝነትን፣ ሱሰኝነትን ወዘተ የመሳሰሉ ማህበራዊ ችግሮችን ፈጥረዋል።
አገራችን ኢትዮጵያ መንግስታዊ የአስተዳደር ሥርዓት መስርታ በኖረችባቸው በሺዎች በሚቆጠሩ ረጂም አመታት ውስጥ የቅርብና የሩቅ ተስፋፊዎች፣ወራሪዎችና ቅኝ ገዢዎች አይናቸውን ያልጣሉባትና፣ አንድነቷና ሉዓላዊነቷ ፈተና ውስጥ ያልገባበት የታሪክ ምዕራፍ ኖሮ አያውቅም። ቱርኮች፣ማህዲስቶች፣የግብፅ ፓሻዎች፣እንግሊዞች፣ ጣሊያኖችና ሌሎችም በተለያየ ግዜ እየመጡ ሉዓላዊነታችንን ተጋፍተዋል። የኢትዮጵያ ህዝብ በታሪኩ መብቱ፣ነጻነቱና እኩልነቱ ተከብሮ ባያውቅም፣ አገሩ በጠላት ስትወረር ግን ቁጭ ብሎ የማየት ባህል የሌለው ህዝብ በመሆኑ በተለያየ የታሪክ ወቅት የመጣበትን የህልውና አደጋ ተጋፍጦ ኢትዮጵያን የአፍሪካ ብቸኛዋ በቅኝ ገዢዎች ያልተገዛች አገር ማድረግ ችሏል።
ባለፉት 30 አመታት ግን ይህ የአለም የጥቁር ህዝብ የነጻነት ተምሳሌት ያሰኘን አኩሪ ታሪክ የብሔር ፖለቲካ ባሰከራቸው ነጻ አውጪ ነን ባዮች እንዲደበዝዝ ተደርጎ ዛሬ ብዙ ኢትዮጵያዊያን “እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ” ብለን በኩራት መናገር የምንፈራበት አሳፋሪ የታሪክ ምዕራፍ ላይ ደርሰናል። ዛሬ ኢትዮጵያ የምትገኝበት ሁኔታ በታሪካችን ሰምተነውም አይተነውም የማናውቀው እጅግ በጣም የሚያስፈራ ግዜ ነው። እንደ አገር ያለንበት ግዜ የሚያስፈራው የዘር ፖለቲካ አገራችን ላይ የህልውና አደጋ ይዞ መምጣቱ ብቻ አይደለም፣ እንዳውም ትልቁ አደጋ እኛ ኢትዮጵያዊያን እንደ አባቶቻችን አንድ ላይ ቆመን አገራችን ላይ የተደቀነውን የህልውና አደጋ ማስቆም አለመቻላችን ነው፣ ወይም በሌላ አነጋገር ያ ጠላት አገርህን ሊወስድብህ ነው ሲባል “እኔ እያለሁ” ብሎ የራሱን ትጥቅና ስንቅ ይዞ ይዘምት የነበረ ህዝብ ዛሬ አገርን ያክል እጅግ በጣም ግዙፍ ክስተት የሚያፈርስ አደጋ ፊት ለፊቱ ላይ ተደቅኖ እያየ በዘር ግድግዳ ተለያይቶ ከአገሩ ይልቅ የራሱን ክልል ለማዳን ይሯሯጣል። በዘመናዊው የኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ግዜ አገራችንን በጋራ እናድን ከሚለው ኢትዮጵያዊ ድምፅ ይልቅ “በመጀመሪያ እራሳችንን እናድን” የሚል አካባቢያዊ ድምፅ በየቦታው መደመጥ ጀምሯል።
ለመሆኑ ዛሬ እንደ አገር የገጠመን አደጋ ምንድነው?
የዚህ ጽሁፍ ጸሃፊ ፖለቲካ ከኢትዮጵያ ኬንያ፣አሜሪካ፣ኤርትራ ከዚያ መልሶ ኢትዮጵያ የወሰደውና ከአፍላ የወጣትነት ዕድሜው ጀምሮ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ለረጂም አመታት የቆየ ሰው ነው። ኢትዮጵያ ዛሬ የምትገኝበት ሁኔታ በታሪካችን በየትኛውም ግዜ አይተነውም ሰምተነውም የማናውቀው ፍጹም እንግዳ የሆነ ሁኔታ ነው ለማለት የደፈረውም ከዚህ ልምዱ በመነሳት ነው።
የኢትዮጵያ ችግር ለአንዳንዶቻችን የህግ የበላይነት አለመከበር ነው፣ ለአንዳንዶቻችን ጠሚ አቢይ አህመድና ፓርቲያቸው ብልፅግና ናቸው፣ለአንዳንዶቻችን ከቀን ወደ ቀን እየከረረ የመጣው የኦሮሞ ብሔረተኝነት ነው፣ለአንዳንዶቻችን ኋላቀርነትና ድህነት ነው፣ ለአንዳንዶቻችን ጥላቻና የርስበርስ መገዳደል ነው፣ለአንዳንንዶቻችን ደሞ የሰላምና መረጋጋት አለመኖር ነው። እነዚህ የተጠቀሱት ችግሮች ሁሉም በቀጥታና በተዘዋዋሪ የአገራችን ችግሮች ናቸው። ለመሆኑ የአገራችን ኤኮኖሚ በፍጥነት ቢያድግ ዛሬ አላስቆም አላስቀምጥ ያሉን ፖለቲካዊና ማህበራዊ ችግሮች ይወገዳሉ? እውነቱን ለመናገር የኤኮኖሚ ዕድገት ብቻውን ዛሬ ለሚታዩት የአገራችን ችግሮች መፍትሄ አይሆንም፣ እንዲያውም የፓለቲካ ችግራችንን በተለይ በዘር የለያየንን የብሔር ፖለቲካ መስመር ሳናስይዝ በኤኮኖሚ ማደግ የምንችልም አይመስለኝም። ጠሚ አቢይ አህመድንና ፓርቲያቸው ብልፅግናን አስገድደን በሌላ ሰውና ፓርቲ ብንተካስ ችግሮቻችን ይወገዳሉ? በኔ እይታ ህወሓት በብልፅግና ሲተካ ችግሮቻችን እንዳልተወገዱ ሁሉ፣ ጠሚ አቢይ በሌላ ሰው ቢተኩም ችግሮቻችን ይወገዳሉ የሚል ዕምነት የለኝም። ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት የግለሰቦች ወይም የገዢ ፓርቲ ለውጥ ሳይሆን የሥርዓትና የአስተሳሰብ ለውጥ ነው። ስለዚህ አገራችን ኢትዮጵያን ከተደቀነባት የህልውና አደጋ ለማዳን የመጀመሪያው ዕርምጃ በሙሉ ኃይላችን ፊት ለፊት መጋፈጥ ያለብንን ዋናውን የአገራችን ችግር ለይቶ ማወቅ ወይም ማንን እና ምንን መታገል እንዳለብን ማወቅ ነው።
ባለፉት አምስት አመታት የክልልና የፌዴራል መንግስት ባለሥልጣናት፣ቤተሰቦቻቸውና የጥቅም ተካፋዮቻቸው፣ነጻ አውጭ ነኝ ባዩና የአገር ኃብት ዘርፎ የከበረው ሙሰኛው ሁሉ ወንጀለኛነቱ ሲነቃበት በየብሔሩ ጓዳ አየተደበቀ ጣቱን ሌላው ላይ ሲቀስር ነበር። ሁላችንም በየብሔራችን ጓዳ ተሸሽገን ለኢትዮጵያ ችግሮች ሁሉ መንግስትን ብቻ የምንከስ ከሆነና ችግሮቻችንን ለማስወገድ ህብረት ፈጥረን የማንታገል ከሆነ የኢትዮጵያ ችግር ጣታችንን የምንቀስርበት መንግስት ብቻ ሳይሆን እኛም ጭምር ነን። ዛሬ ላይ አገራችንን አላስቆም አላስቀምጥ ያሏት ውስብስብ ችግሮች ዛሬ በሥልጣን ላይ ያለው መንግስትና ከሱ በፊት የነበሩት ሦስት ተከታታይ መንግስታት፣ በእያንዳንዱ መንግስት ውስጥ በነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ምሁራን፣ልህቃን፣ ወጣቶች፣ሴቶች፣ የሲቪክ ማህበራት፣ የሙያ ማህበራት፣ የእምነት ተቋማትና ማህበራዊ ስብስቦች የየራሳቸውን አሉታዊ አስተዋጽኦ አድርገው የፈጠሩትና ከአንዱ ሥርዓት ወደ ሌላው እየተንከባለሉና እየተባባሱ የመጡ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኤኮኖሚያዊ ችግሮች ናቸው። ሆኖም ዛሬ ላይ ከችግሮቻችን ሁሉ የከፋውና ባስቸኳይ መፍትሄ ማግኘት ያለበት በዘር ላይይቶ የሚያጨራርሰን የብሔር ፖለቲካ ነው።
ባለፉት 30 አመታት፣በተለይ ባለፉት አምስት አመታት በዘር ግድግዳ ለያይቶ እርስ በርስ ያባላን፣አገራዊ ማንነትን አደብዝዞ የብሔር ማንነት ጎልቶ እንዲወጣ ያደረገው፣አንደ አንድ አገር ህዝብ አንድ ላይ እንዳንቆም የከፋፈለንና የአገራችንን ህልውና አደጋ ላይ የጣለው ህወሓቶች የመሰረት ድንጋይ ያኖሩለት የብሔር ፓለቲካ ነው። የብሔር ፖለቲከኞች፣ብሔር መደበቂያ ጓዳችሁ የሆነ የብሔር ደላላዎችና በብሔር ፖለቲካ ውስጥ አድጋችሁ ሌላ ለየት ያለ ፖለቲካ ለማይታይችሁ ሁሉ . . . . . እባካችሁ እኔ የኢትዮጵያ ትልቅ ችግር ነው ያልኩት የብሔር ፓለቲካን (Ethnic Politics) እንጂ ብሔር ብሔረሰቦችን አይደለም! በሁለቱ መካከል ትልቅና ሰፊ ልዩነት አለ። ብሔር ብሔረሰቦች የኢትዮጵያ ውበቶች ናቸው፣ የብሔር ፖለቲካ ግን ይህንን ውበት የሚያጠለሽ መድኃኒት የሚያስፈልገው ክፉ በሽታ ነው።
ብሔር (Ethnic Group) ሰዎች በሚኖሩበት ስጋት የሞላበት አለም ውስጥ ከተፈጥሮና ከሌሎችም የተለያዩ አካባቢያዊ ክስተቶች የሚመጣባቸውን ስጋት ለመቀነስ በረጂም ግዜ የአብሮ መኖር ሂደት ውስጥ የፈጠሩት ማህበራዊ ስሪት ነው። “ማንነት”/Identity የሚታዩና የማይታዩ መስተጋብሮች፣ ግኑኝነቶች፣ የተለያዩ ኩነቶችና ባህሪያት በሚገኙበት ውስብስብ ማህበራዊ አለም ውስጥ ግለሰቦች የራሳቸውን ቦታ አጠገባቸዉ ካሉ ሰዎች ጋር አንጻራዊ በሆነ መልኩ (Relative to others) ፈልገው ለማግኘት ማህበራዊውን አለም የሚቃኙበት ራዳር ወይም ምናባዊ መሳሪያ ነዉ።
የብሔር ፓለቲካ ግን ከዚህ በጣም የተለየ ነው። የብሔር ፖለቲካ የብሔር ልህቃን የራሳቸውን የሥልጣን ጥማትና የኤኮኖሚ ፍላጎት ለማርካት የተወለዱበትን ብሔር እንደ መረማመጃ የሚጠቀሙበት መሳሪያ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ በህወሓት ግዜም አሁንም ከህወሓት ካልተማሩ የኦሮሞ ብሔረተኞች የምንመለከተው ይህንኑ ሃቅ ነው። ለዚህ ነው የፍልስፍና ሰዎችና የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን ብሔርና የብሔር ፖለቲካ የቀንና የማታን ያክል የሚለያዩ ክስተቶች ናቸው እያሉ በተደጋጋሚ የሚነግሩን።
የብሔር ብሔረሰቦች መብት እንዲከበር የብሔር ፖለቲካ ያስፈልጋል የምትሉ የብሔር ፖለቲካ ነጋዴዎችም ብትሆኑ የብሔር ብሔረሰቦች መብት እንዲከበር ወይም እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ዜጋ በግለሰብ ደረጃም በቡድንም መብቱ እንዲከበር የብሔር ፖለቲካ አያስፈልግም። የብሔር ብሔረሰቦች መብት እንዲከበር የብሔር ፓለቲካ መኖር አስፈላጊ ቢሆንማ ኖሮ፣ ብሔር የፖለቲካችን መሰረት ከሆነ ከ30 አመት በኋላ ዛሬ ላይ የብሔር ብሔረሰቦች መብትና ነጻነት የፖለቲካ አጀንዳ ሆኖ መቅረብ አልነበረበትም። ኢትዮጵያ ውስጥ የብሔር ብሔረሰቦች መብትና ነጻነት እንዲከበር ብቸኛው መንገድ የግለሰብንና የቡድንን መብት ብቻ ሳይሆን መብትና ግዴታን ጭምር በግልጽ የሚያስቀምጥና፣ የኢትዮጵያን ህዝብ ሰብዓዊ፣ፖለቲካዊና ዲሞክራሲያዊ መብት የሚያጎናጽፍ ህገመንግስት እንዲኖረን ማድረግ ነው። የህግ የበላይነት የተረጋገጠበት ህገመንግስታዊ የፖለቲካ ሥርዓት ከገነባንና፣ በጋራ ጽፈን በጋራ ያጸደቅነውን ህገመንግስት የሚያከብር ህዝብና አክብሮ የሚያስከብር መንግስት ካለን የብሔር ብሔረሰቦችን መብት የሚደፍር ኃይል ሊኖር አይችልም።
አገራችን ኢትዮጵያ የብዙ ብሔር ብሔረሰቦች አገር ናት- ይህ ማንም ምንም ሊለውጠው የማይችል አብሮን የኖረ፣ አብሮን የሚኖርና የምንኮራበት እውነት ነው። ተጋብተናል? አዎ ተጋብተናል። ተዋልደናል? አዎ ተዋልደናል። ተጋብተናል ወይም ተዋልደናል ሲባል ግን ይህ መጋባታችንና መዋለዳችን የጋራ አድማሳችንን ያሰፋዋል እንጂ ማንነታችንን ጨፍልቆ አንድ ማንነት ውስጥ አይከተውም።ትግሬነት፣ኦሮሞነት፣አማራነት፣አፋርነት፣ከምባታነት፣ወላይታነት፣ሙርሲነት፣ ሶማሌነት፣ሲዳማነት፣ሃድያነት፣ጉራጌነት ወዘተ ሁሉም ክቡር ማንነቶች ናቸው። እነዚህ ክቡር ማንነቶች ግን የማይተዋወቁ፣የጋራ ታሪክ የሌላቸውና ለየብቻቸው የቆሙ ነጠላ ማንነቶች አይደሉም። ይተዋወቃሉ፣ የየራሳቸው የሆነ ልዩ ባህልና፣ እንደ አንድ አገር ህዝብ ለዘመናት አብሮ በመኖር የፈጠሩት የጋራ ባህል፣ ትርክት፣እሴትና እንዲሁም የሚጋሯት ኢትዮጵያ የምትባል አገርና በዚህች አገር ውስጥ በጋራ የሰሩት የጋራ ታሪክ አላቸው።
ለመሆኑ አንድ ሰው ብሔረተኛ (Ethno-nationalist) ነው ሲባል ምን ማለት ነው?
በዛሬዋ ኢትዮጵያ እንደ ነውር ቢታይም፣ አንድ ኢትዮጵያዊ በኢትዮጵያዊነቴ እንጂ በብሔሬ መጠራት አልፈልግም ቢል የግል ፍላጎቱ ነውና ይህ ፍላጎቱ መከበር አለበት፣ ነገር ግን ኢትዮጵያዊ ሆኖ ከአንድ ወይም ከአንድ በላይ ከሆኑ ብሔሮች የማይወለድ ሰው እንደሌለም ማወቅ አለብን። አንድን ሰው የዚህ ወይም የዚያ ብሔር አባል መሆኑ ብቻ በራሱ ብሔረተኛ አያሰኘውም። የኦሮሞ፣ የትግሬ፣የአማራ ወዘተ ብሔረተኛ መሆን ምርጫ ነው፣ ከኦሮሞ፣ከትግሬ፣ ከአማራ ወዘተ መወለድ ግን ምርጫ አይደለም።
አንድ ሰው ብሔረተኛ በተለይ አክራሪ ብሔረተኛ ሲሆን በሌላ ብሔር እህትና ወንድሞቹ ላይ የጥላቻና የበቀል ስሜት ያድርበታል፣እኔ ብቻ ተበዳይ ነኝ ብሎ ያስባል፣በድሎሃል ተብሎ የተነገረውን የሌላ ቋንቋ ተናጋሪ በጠላትነት ይፈርጃል፣የሱን ቋንቋ የማይናገረውን የአገሩን ዜጋ መጠጋት አይፈልግም፣ አብሮት ካደገውና አብሮት ከተማረው የሌላ ብሔር ተወላጅ ይልቅ አንድ ቀን ብቻ ያየውን የራሱን ብሔር ሰው ይቀርባል፣ይጠጋል ወይም ያምናል። እውነት ያለችው እኔጋ ብቻ ነው ብሎ ያስባል፣የሌላውን እውነት በፍጹም አይቀበልም፣ከአገር ፍቅር በላይ ብሔረተኝነቱ ይስበዋል፣የበታችነት ወይም የበላይነት ስሜት ሁሌም አብሮት ይኖራል።
ኢትዮጵያን “ኢትዮጵያ” ያሰኟት ከ80 በላይ የሚሆኑ ብሔር ብሔረሰቦቿ መብትና ነጻነታችው ሳይከበርና በእኩልነት ሳይታዩ ለብዙ አመታት አብረዉ ኖረዋል። የውጭ ወራሪ ሲመጣ በጋራ ተዋግተውና የኢትዮጵያን ዳር ድንበር አስከብረው የአኩሪ ታሪክ ባለቤት አድርገውናል። ዶጋሌ፣ጉንዲት፣ጎራዕ፣መተማ፣አድዋ፣ማይጮው፣ወልወልና ካራማራ ላይ አገሬ ብለዉ ተቃቅፈው ተዋግተው፣ ተቃቅፈዉ ወድቀዋል። ስለዚህ እነዚህ ቁጥራቸው ወደ ሰማኒያ የሚደርስ የተለያዩ ማንነቶች የጋራ መታወቂያችን ነው ብለው በአብሮነታቸው ያበቀሉት፣ በስራቸው ያጸደቁት፣በደማቸዉ የጻፉትና በአጥንታቸው ያጸኑት ኢትዮጵያዊ የሚባል ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የኖረ ክቡር ማንነት አለ። የብሔር ፖለቲካ ይህንን ክቡር ማንነት አስወግዶ ጎጠኝነት እንዲነግስ በማድረጉ ነው ዛሬ አገራችን የአለማችን የርስ በርስ ግጭት ምሳሌ የሆነቸውና በታሪኳ ለመጀመሪያ ግዜ እውን የሆነ የመበታተን አደጋ የተደቀነባት።
ያለምንም ማጋነን ባለፉት አምስት አመታት ኢትዮጵያ ውስጥ በግልጽ ያየነው ነገር ቢኖር ህወሓቶች የገነቡትን የአንድ ብሔር የበላይነት ከኛው ጋር ታግለው ያሰወገዱ የትናንትናዎቹ የህወሓት ተላላኪዎች ፊት ለፊት “ኢትዮጵያ” “ኢትዮጵያ” ብለው እየሰበኩን በጓሮ በር ግን የራሳቸው ብሔር የበላይነት የነገሰበትን የፖለቲካ ሥርዓት እየገነቡ መሆኑን ነው። አብረን በአገር አቀፍ ደረጃ መፍታት ያለብንን የቋንቋን ጉዳይ፣ የባንዲራንና የአዲስ አበባን ጉዳይ ስንመለከት፣ በሌላ በኩል ደግሞ የኦርቶዶክስ ቤ/ክርስቲያንን እና የሸገር ከተማ ግንባታን ጉዳይ ስንመለከት፣ ዛሬ አገራችን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ የሆነባት የኦሮሞ ብሔረተኞች አቅጣጫ የለሽ አካሄድና መልስ የሌለው የትየለሌ ጥያቄ ነው። በእርግጥም የሚሄድበትን አቅጣጫ የማያውቅና “ግዜው የኔ ነው” ባይ ብቻ ነው በብዙ መቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ህጻናትን፣ተማሪዎችን፣እናቶችን፣አባቶችንና አረጋዊያንን ቤት አልባ የጎዳና ላይ ነዋሪ አድርጎ “ህጋዊ ድሃ” አደርግናቸው ብሎ ደረቱን ነፍቶ የሚናገር!
ዛሬ አክራሪ የኦሮሞ ብሔረተኞች በሚሰሩት ትርጉም የለሽ ስራ ብዙ የኦሮሞ ተወላጆች ጭምር እያፈሩ ነው፣ አንዳንዶቹማ ጭራሽ የኦሮሞ ጥያቄ የሚቆመው መቼ ነው እስከማለት ደርሰዋል። የዛሬ አመት ትልቁ ችግር ወለጋ ውስጥ ያለምንም መከልከል የሚፈሰው የአማራ ተወላጆች ደም ነበር። ዛሬ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ በየቦታው አፈናው፣ እስሩ፣ግድያውና ግለሰቦችን እያፈኑ ገንዝብ መጠየቅ የቀን ከቀን ስራ ሆኗል። በ2011 ዓም ወያኔዎች አዲስ አበባ ውስጥ የገነቧቸውን የሰቆቃ መፈጸሚያ ቦታዎች አንድ በአንድ ያስጎበኙን ሰዎች ዛሬ እነሱ እራሳቸው በየቦታው ዜጎችን እያፈኑ ወስደው ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት የሚፈጽሙባቸውን ቦታዎች ገንብተው የኢትዮጵያን ህዝብ እያስለቀሱትና “ወያኔ ማረኝ” እያሰኙት ነው። እጅና ጓንት ሆነው አብረው ከሚሰሩትና ምንም አይነት ማዕከላዊነት ከሌለው “ኦነግ-ሸኔ” ከሚባለው ገዳይ ቡድን ጋር እየተደራደሩ፣ ትናንት የፌዴራል ኃይሎች ከህወሓት ጋር ሲዋጉ መንግስት ያቀረበለትን የአገርህን አድን ጥሪ ተቀብሎና ከመከላከያ ሠራዊታችን ጎን ተሰልፎ ኢትዮጵያን ከአደጋ ካዳነው ከፋኖና ከአማራ ልዩ ኃይል ባጠቃላይ ከአማራ ህዝብ ጋር ግን የማያዋጣና የኢትዮጵያን መጨረሻ የሚያፋጥን ፍጥጫ ውስጥ ገብተዋል።
ከ1983-2010 የኢትዮጵያ ችግር ህወሓቶች የገነቡት የትግራይ የበላይነት ነበር፣ እሱን ለ27 አመት ታግለን አሸንፈናል። ኢትዮጵያን መምራት ያለብን እኛ ብቻ ነን የሚሉት ዕብሪተኞቹ የህወሓት መሪዎች እንደገና ለመምጣት ቢሞክሩም ላንዴና ለመጨረሻ ግዜ አሸንፈናቸዋል። ዛሬ የአገራችን የኢትዮጵያ ትልቁ አደጋ ኢትዮጵያን እንደገና በራሳችን አምሳል መፍጠር አለበን የሚሉ አክራሪ የኦሮሞ ብሔረተኞች የማይጠረቃ የፖለቲካና የኤኮኖሚ ፍላጎት ነው። ኢትዮጵያ ሃያና ሠላሳ አመት እየቆጠረ የሚቀያየረውን የእያንዳንዱን ብሔር የበላይነት ማስተናገድ የሚችል አቅሙም ፍላጎቱም የላትም። የአቅማችንን ያክል ከሰራን ኢትዮጵያ የሁላችንንም ፍላጎት ማርካት ትችላለች፣የእያንዳንዳችንን ስስት ማርካት ግን አትችልምና ኢትዮጵያ ውስጥ የብሔር ፖለቲካ ተመልሶ ላይመጣ መቀበር አለበት።
ዛሬ በአስቸኳይ መወገድ ያለበት የአገራችን ትልቁ ችግር የብሔር ፓለቲካ ነው፣የብሔር ፖለቲካ መወገድ አለበት ስንል ዝም ብለን ከመሬት ተነስተን አይደለም፣ ለትክክልነታቸው ብዙም ያማያከራክሩን አያሌ ምክንያቶች አሉ። ሰሜን ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሊዮኖችን ህይወት የቀጠፈውና በብዙ ቢሊዮን ብር የሚገመት ንብረትና መሰረተ ልማት እንዲወድም ያደረገውን ጦርነት የወለደው የብሔር ፖለቲካ ነው፣ኦሮሚያ ውስጥ በነጋ በጠባ ለሚሞቱትና ለሚፈናቀሉት ዜጎች ምክንያቱ የብሔር ፖለቲካ ነው፣አማራ ክልል ውስጥ ከግማሽ አመት በላይ ላስቆጠረው ትርጉም የለሽ ጦርነት ምክንያቱ የብሔር ፖለቲካ ነው፣ኦሮሚያ ክልልን ክላስንኮቭ የያዘ ሁሉ መፈንጪያ ቦታ ያደረገው የብሔር ፖለቲካ ነው፣አንዱ ሆዱን አስሮ ያሰራውን ኮንዶሚኒየም ኮንዶሚኒየሙ መሰራቱንም የማያውቅ ሰው እንዲወስድ የተደረገው በብሔር ፖለቲካ ስለተለከፍን ነው፣ ጎን ለጎን ለዘመናት አብረን በኖርንበት አገር ውስጥ ‘አገርህ አይደለም” ውጣልኝ ውጪልኝ እንድንባባል ያደረገን የብሔር ፖለቲካ ነው፣አገራችንን የእርስ በርስ ግጭት መድረክ ያደረጋት የብሔር ፖለቲካ ነው፣አገራዊ አንድነታችን እንዲዳከም፣ኢትዮጵያዊ ማንነት እንዲደበዝዝና አገራችን ውስጥ ሰላምና መረጋጋት እንዲጠፋ ያደረገው የብሔር ፖለቲካ ነው፣መኖሪያ ቤታችን እላያችን ላይ ፈርሶ በብዙ መቶ ሺዎች የሚቆጠሩ እናቶች፣አባቶችና ህጻናት በየጎዳናው እንዲያድሩ ያደረገው የብሔር ፖለቲካ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ስርዓተ ትምህርት እንዲበላሽ፣ ዕውቀት ብርቅ እንዲሆንና ሙሰኝነት ህጋዊ አሰራር እንዲመስል ያደረገው የብሔር ፖለቲካ ነው።
ኢትዮጵያ ውስጥ መሰረቱ ፍትህ፣ነጻነት፣እኩልነትና ዲሞክራሲ የሆነ ሁሉን አቀፍ የፖለቲካ ሥርዓት እንዲመሰረት ከፈለግን ከብሔር ፖለቲካ መገላገል አለብን፣ ወይም ኢትዮጵያ ውስጥ ብሔርና ፖለቲካ ዳግም ላይጣመሩ ተፋተው ዜግነትና ፖለቲካ ላይፋቱ መጋባት አለባቸው። የብሔር ፓለቲካን ታግለን ካላሸነፍን የኦሮሞ ብሔረተኝነትን ወይም ሌላውንም ተራ ጠብቆ የሚመጣ ብሔረተኛ ማሸነፍ አንችልም፣ የኦሮሞ ብሔረተኝነትን ሳናሸንፍ የጠሚ አቢይ አህመድን መንግስት መስመር ማስያዝ አንችልም። ጠሚ አቢይ በህዝባዊ ቁጣ ወይም በሌላም በተለያዩ ምክንያቶች ከስሥልጣን ሊወገድ ይችላል፣ ቁምነገሩ የጠሚ አቢይ ከሥልጣን መወገድ አይደለም፣ዋናውና ቁልፉ ጥያቄ ጠሚ አቢይ ከተወገዱ በኋላ ኢትዮጵያን የሚያስተዳድረው የትኛው ፓርቲ ነው? ጠሚ ሆኖ አገር የሚመራውስ ማነው የሚለው ጥያቄ ነው። ይህንን ጥያቄ እንደዋዛ እንዳናየው! በ1966 ንጉሱን አስወግደን በትረ ሥልጣኑን ለደርግ ነው ያስረከብነው፣ ደርግን 17 አመት ታግለን ያመጣነውም ህወሓት የሚባለውን ጉድ ነው። ህወሓትን 27 አመት ሙሉ ስንታገል ትግላችን የብሔር ፖለቲካን ለማስወገድ ሳይሆን ህወሓትን ለማስወገድ በመሆኑ፣ ህወሓት ከተወገደ በኋላ የመጣው መንግስት የብሔር፣ ብሔረሰቦችንና ህዝቦችን መብት ያስከበረውን ህገመንግስት ሳይሸራረፍ አስቀጥላለሁ የሚል መንግስት ነው። አገራችን ኢትዮጵያን ከተደቀነባት የህልውና አደጋ ለማዳን የመጀመሪያው ዕርምጃ በሙሉ ኃይላችን ፊት ለፊት መጋፈጥ ያለብንን ዋናውን የአገራችን ችግር ለይቶ ማወቅ ነው። ስለዚህ ከላይ ለተነሳው ማንን ነው የምንታገለው ለሚለው ጥያቄ የማያወላዳው መልስ – መታገል ያለብን የብሔር ፖለቲካን ነው የሚል ነው። ይህ ማለት ግን የአጭር፣የመካከለኛና የረጂም ግዜ ግብና ስትራቴጂ አይኖረንም ማለት አይደለም።
ሌላው ትልቅ ጥያቄ እንዴት ነው የብሔር ፖለቲካን የምንታገለው የሚለው ጥያቄ ነው
የኦሮሞ ብሔረተኝነትን መታገልና የብሔር ፖለቲካን መታገል ልዩነት የሌለው ይመስለን ይሆናል፣ ነገር ግን የአንድን ቡድን ብሔረተኝነትና የብሔር ፓለቲካን ስንታገል የምናገኘው ውጤት ተመሳሳይ አይደለም። የትግራይን ብሔረተኝነት ታግለን በር የከፈትነው ለፍትህ፣ ለነጻነትና ለዲሞክራሲ ሳይሆን ለኦሮሞ ብሔረተኝነት ነው። 27 አመት ታግለን ኢትዮጵያን የገላገልናት ከብሔር ፖለቲካ ቢሆን ኖሮ ዛሬ ስለ ኦሮሞ ብሔረተኝነት አናወራም ነበር። ስለዚህ እኛ ኢትዮጵያዊያን ታግለን ማሸነፍ ያለብን የጠሚ አቢይ አህመድን መንግስት ወይም ብልፅግና ፓርቲን ብቻ አይደለም፣ የኦሮሞን ብሔረተኝነት ብቻም አይደለም። ኢትዮጵያ ውስጥ ፊትለፊት ገጥመን ማሸነፍ ያለብን ሁለቱንም (የኦሮሞ ብሔረተኝነትንና ጠሚ አቢይን መንግስት) አቅፎ የያዘውን የብሔር ፖለቲካን ነው፣ ወይም የሁሉም ብሔረተኞች መመኪያና መጠጊያ የሆነውን የብሔር ፖለቲካን ነው አሸንፈን ማስወገድ ያለብን።
የብሔር ፖለቲካ ባለበት አገር ውስጥ ሥልጣን ይዞ ሁሉም ነገር የኔ ነው ብሎ የሚያስብ ቡድንና ከሥልጣን ተገልዬ ተጎዳሁ ብሎ የሚያስብ ቡድን አብረው ጎን ለጎን ስለሚኖሩ፣ የብሔር ፖለቲካ ምን ግዜም ከጭቅጭቅ፣ከጥላቻና ከግጭት ጋር የተያያዘ ፖለቲካ ነው። ተደራጅተው ሥልጣን ለመያዝ የሚፎካከሩ ብሔሮች ባሉበት የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ የብሔር ግጭት፣ ዘር ማጥፋት፣የሰብአዊ መብት ጥሰት፣ በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች፣ የኢኮኖሚ ውድቀት፣ የመንግስት ውድቀት (State Falure) ፣ መፈናቀልና ስደት የሥርዓቱ ዋና ዋና መገለጫዎች ናቸው። እኛ ኢትዮጵያዊያን ይህንን ለማወቅ መረጃ ፍለጋ ሌላ ቦታ መሄድ የለብንም፣ ያለፉት 30 አመታት በተለይም ያለፉትን አምስት የለውጥ አመታት ወደኋላ ዞር ብሎ መመልከት ይበቃል።
ኢትዮጵያ ውስጥ የብሔር ፓለቲካ በአንድ ቀን እንዳልተገነባ ሁሉ በአንድ ቀን አይፈርስም፣ደሞም የብሔር ፖለቲካ ተቃዋሚዎች እንዳሉት ሁሉ ደጋፊዎችም አሉት። ይህ የሚነገረን በአንድ በኩል ከብሔር ፖለቲካ ጋር የምናደርገው ትግል ትዕግስት፣ አስተዋይነት፣አርቆ ማሰብና በጋራ አንድ ላይ መቆምን እንደሚጠይቅ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ የብሔር ፓለቲካን ከኢትዮጵያ ለማጥፋት ከብሔር ፖለቲካ ደጋፊዎች ጋር ተቀራርቦ መስራት እንደሚያስፈልግ ነው። የብሔር ፖለቲካን ለመታገል ጠንካራ ንህዝባዊ መሰረት ያለው አገራዊ እንቅስቃሴ መፍጠር ሊኖርብን ይችላል፣የአገራዊ ምክክሩን መድረክ መጠቀም ወይም አገራዊ ምክክሩንም አገራዊ እንቅስቃሴውንም አብረን መጠቀም ሊኖርብን ይችላል። የጠሚ አቢይ አህመድን መንግስት አስገድደን ምርጫ እንዲጠራ ማድረግ ወይም ተቃዋሚ ኃይሎችን አስተባበረን በሚቀጥለው ምርጫ የማዕከል ኃይሎች በአገር አቀፍ ደረጃም አዲስ አበባ ውስጥም ሥልጣን እንዲይዙ ማድረግም ሌላው የትግል እስትራቴጂያችን ሊሆን ይችላል። ከዚህ በተጨማሪ ሌሎች ብዙ የትግል አይነቶች ሊኖሩ ይችላሉ።በተናጠል ወይም አጣምረን መጠቀም ያለብንን የትግል ስትራቴጂ መምረጥና ይህንን ስትራቲጂ ሁሉም ባለድርሻዎች እንዲቀበሉት ማድረግ ትግሉን በአሸናፊነት ለመወጣት የመጀመሪያው ቁልፍ ኦርምጃ ነው።
አንዳንዶቻችሁ አብደሃል እንዴ እንዴት ነው ታንኩንም ባንኩንም የሚቆጣጠረውን አካል አስገድደህ ምርጫ እንዲጠራ የምታደርገው ትሉኝ ይሆናል። መልሴ አላበድኩም ነው። የምኖረው አልበሽርን የመሰለ አምባገንነ የዳቦ ዋጋ ጨመረ ብሎ ያስወገደ፣ቤን አሊን የመሰለ ሃይለኛ ሰው ሙሰኛ ነህ ብሎ ያባረረ፣ ሆስኒ ሙባረክን የመሰለ የ30 አመት ፈላጭ ቆራጭ እስከወዲያኛው የሸኘ ህዝብ ባለበት አህጉር ውስጥ ነው።ታግለን ነጻ ባወጣናት ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖረንን ቦታ ሳይሆን፣ ነጻ ባወጣናት ኢትዮጵያ ውስጥ መጪው ትውልድ የሚኖውን ብሩህ ዕድል እያየን ከታገልን የማናስገድደውና የማናሸንፈው ኃያል ኢትዮጵያ ውስጥ የለም!
ባለፉት 5 አመታት እርስበርስ ተዋግተል፣ተሰዳድበናል፣አንዳችን ሌላውን ተለጣፊ፣ ከሃዲ፣ባንዳ ተባብለናል። አንዳንዶቻችን በፍጹም ለአገር የማናስብ ሌሎቻችን ደሞ የኢትዮጵያ ብቸኛ ጠበቃ ሆነን እራሳችንን አይተናል። አንዳዶቻችን አገራችን አይናችን እያየ የመበታተን አደጋ ውስጥ ስትገባ ሌላ አማራጭ ስላልነበረን (በነገራችን ላይ አማራጭ አሁንም የለንም) ይህንን አደጋ ያድናል ብለን ካሰብነው አካል ጋር አብረን ሰርተናል። በእርግጥም ህወሓት የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነት ከጀመረ በኋላ አገር ውስጥም ውጭ አገርም ያለው ኢትዮጵያዊ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር አንድ ላይ ቆሟል።
እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት የደገፍናቸውና የተቃወምናቸው፣ ያደረግናቸውና ያላደረግናቸው ነገሮች ማናችንንም የተሻለ ቦታ ላይ አላስቀመጡንም፣ይልቁንም እኛ ስንኗቀርና ስንባላ አይናችን እያየ አገራችን የመበታተን አደጋ ውስጥ ገብታለች። የጠሚ አቢይን መንግስት ደግፈንም ተቃውመንም ታግለናል፣ግን ማናችንም አገራችንን ከገባችበት እጅግ በጣም አደገኛ ሁኔታ ማዳን አልቻልንም! ይህ ፍጹም አሌ ልንለው የማንችለው ሃቅ የሚነግረን አንድ ትልቅ ጉዳይ አለ፣ እሱም እኛ ኢትዮጵያዊያን እስካሁን በመጣንበት መንገድ መቀጠል እንደሌለብንና አካሄዳችንን፣የትግል ስልታችንን፣ ስትራቴጂያችንን እና በተለይ የኢትዮጵያን ችግሮች የምንመለከትበትን መንገድና ለችግሮቹ መፍትሄ ለማምጣት የምንሄድበትን መንገድ ፈትሸን መቀየር እንዳለብን ነው። ይህንን ማድረግ ካልቻልን የትናንቱን እየደገምን ትናንት በሄድንበት መንገድ ላይ ዛሬም፣ ነገም፣ ከነገወዲያም እንሄዳለን – ያለፈው ሃምሳ አመት ታሪካችንም የሚያሳየንም ይህንኑ ነው።
የብሔር ፖለቲካን በብሔር ተደራጅተን ማሸነፍ አንችልም፣ ምክንያቱም በዘር ስንደራጅ አንደኛ- እኛው እራሳችን ትግሉን ሳንጀምር ተለያይተናል፣ሁለተኛ- አንዳችን ሌላችንን እንደጠላት እንመለከታለን፣ሦስተኛ- ከምንታገለው ኃይል ጋር በአላማም በግብም ምንም ልዩነት አይኖረንም። ደሞስ የብሔር ፖለቲካን ማስወገድ አለብን ብለን ስንነሳ እንዴት ሆኖ ነው መሰባሰቢያችን እና የትግል ስትራቲጂያችን የብሔር ፖለቲካ የሚሆነው?
በምንታገላቸው የብሔር ኃይሎችና በኛ መካከል ከፍተኛ የአላማ፣ የመናበብ፣የመሰባሰብና አብሮ የመስራት ልዩነት አለ። በተለይ ዛሬ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሥልጣን እጃችን ላይ ነውና ኢትዮጵያን በኛ አምሳል እንደገና መፍጠር አለብን ብለው የተነሱት የኦሮሞ ብሔረተኞች አገር ቤት ያሉትም፣ ውጭ ያሉትም፣ ተቃዋሚውም፣ መንግስት ውስጥ ያለውም፣ ምሁሩና ልህቁ ሁሉም በኦሮሙማና በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ባላቸው የባለቤትነት ጥያቄ እጅና ጓንት ሆነው ይሰራሉ እንጂ በፍጹም እርስ በርስ አይጋጩም። በእርግጥ አንዳንድ ጫፍ የወጡ አክራሪ የኦሮሞ ኃይሎች አሉ፣ግን እነዚህ ጠሚ አቢይ የነፍጠኞች ተወካይ ነው ይሉ የነበሩ ኃይሎችም ቢሆኑ ባለፈው አመትጥር ወር የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ለመከፋፈል ጥረት ከተደረገ በኋላ አካሄዳቸውን ቀይረው ጠሚ አቢይ “መሪዬ ነው” ማለት ጀምረዋል። እኛስ?
የኦሮሞ ኃይሎች ከኢ-መደበኛ (Informal) መሪያቸው ከኦሮሚያ ክልል ጋር ይግባባሉ፣ይናበባሉ፣የአላማ አንድነት ስላላቸው አብረው ይሰራሉ እንጂ እርስ በርስ አይባሉም። “ኢትዮጵያ”፣ “ኢትዮጵያ” የሚለውና እራሱን የአንድነት ኃይል ብሎ የሚጠራው ኃይል ግን አገር ውስጥም በውጭ አገሮችም ቁጥሩ ከፍተኛ ቢሆንም፣ የቁጥሩን ያክል የተከፋፈለ፣ እርስ በርስ የሚባላ፣በሆነው ባልሆነው የሚጨቃጨቅና ፅንፈኛው፣ ግራ ዘመሙ፣ቀኝ ዘመሙና በሁለቱ መሃል ያሉ ኃይሎች የሚገኙበት ከራሱ ጋር የተጣላ ስብስብ ነው። የአንድነት ኃይል በሚባለው ቡድን ውስጥ የሚገኙ ኃይሎችን የሚያገናኛቸው “አንድነት” የሚለው ቃል ብቻ ነው። ለምንድነውሱ በዘር የተደራጁ ኃይሎች የምንፈልገው ካልሆነ “ኢትዮጵያ ትፍረስ” ብለው አንድ ላይ ሲቆሙ፣ እኛ “ኢትዮጵያ አትፈርስም” የምንልና የነሱ ኢላማ የሆንን ኢትዮጵያዊያን ሌላው ሁሉ ቢቀር በቁማችን ላለመዋጥ አንድ መሆን ያቃተን? ተለያይቶ ከመጥፋትና አንድ ላይ ሆኖ እራስንም አገርንም ከማዳን የቱ ይሻላል?
የዛሬዎቹ የአለማችን ኃያልና ኃብታም አገሮች ጠንካራ ማዕከላዊ መንግስትና አስተማማኝ ኤኮኖሚ መገንባት የቻሉትና ባጠቃላይ አሁን ያሉበት ከፍተኛ የዕድገት ደረጃ ላይ መድረስ የቻሉት አባቶቻቸው ጠንካራ አገር ለመገንባት ፈጥረው በሰጧቸው ትርክቶችና አፈ ታሪኮች ነው። እነዚህ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፉ የመጡ ትርክቶችና አፈ ታሪኮች ናቸው ጽናትና ብርታት ሆነው የየአገሮቹ ህዝብ ማንነቱን፣ባህሉን፣ታሪኩንና ዳር ድንበሩን አስከብሮ ጠንካራ የኤኮኖሚ ማህበረሰብ እንዲገነባ ያስቻሉት። እኛ ኢትዮጵያዊያን ግን ከትርክትና አፈ ታሪክ በተጨማሪ እንደማህበረሰብ በጋራ የሰራነውና የአገራችን የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የዓለም ጥቁር ህዝብ የነጻነትና የአልገዛም ባይነት ምልክት የሆነ አድዋን የመሰለ ታሪክ አለን። ታድያ ምን ነክቶን ነው ትናንት እኛ አክሱምን፣ላሊበላን፣ ፈሲለደስንና ሃላላ ኬላን ስንገነባ ያልነበሩ አገሮች ትርክትና አፈታሪክ ዛሬ ላሉበት ቦታ ሲያበቃቸው እኛ ግን አባቶቻችን ሰርተው በሰጡን ታሪክ ፊት ብትንትናችን ሊወጣ አንድ ሐሙስ የቀረው?
በተደጋጋሚ እንደተነገረው ዛሬ አገራችን ላይ የተደቀነው ትልቁ አደጋ፣ ኢትዮጵያን በኛ አምሳል እንደገና መገንባት አለባት በሚሉና ትላልቆቹን የአገራችንን ውሳኔዎች እኛ ብቻ ነን መወሰን ያለብን የሚሉ የኦሮሞ ብሔረተኞች የሚሄዱበት የዕብሪት መንገድ ነው። በውጭና በአገር ውስጥ የምንገኝ ኢትዮጵያዊያን ይህንን አደገኛ አካሄድ ገና ከጅምሩ ካላስቆምን ተወልደን ያደግንባትን አገር መጨረሻ የምናይበት ግዜ ሩቅ አይሆንም። በእርግጥም እኛ ኢትዮጵያዊያን የኦሮሞን ብሔረተኞች ሩጫ ባጭሩ ካላስቆምነው፣ አግላይ የሆነውን የብሔር ፖለቲካ ሁላችንንም እኩል በሚያቅፍ የዜግነት ፖለቲካ ካልተካነውና ያለፉት ሃምሳ አመታት ታሪካችንን ካልቀየርን ለመጪው ትውልድ “ኢትዮጵያ የምትባል አገር ነበረች” የሚል አዲስ ታሪክ እየጻፍንለት እንደሆነ መርሳት የለብንም!
እኛ ኢትዮጵያዊያን ባለፉት ሃያ ሰባት አመታት በተለይም ጠ/ሚ አቢይ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ እንደ አንድ ህዝብ ቆመን የነጻነትና የዲሞክራሲ ትግል ማድረግ ተስኖናል። ባለፈው አመት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ላይ የተቃጣው ጥቃት ግን ብሔር፣ ቋንቋና ሃይማኖት ሳንለይ አንድ ላይ መቆም እንደምንችልም በግልጽ አሳይቶናል፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ውጤቱ ያማረ ትግል ለማካሄድና ኢትዮጵያን የእኩሎች አገር ለማድረግ ከዘርና ከሃይማኖት በዘለለ መልኩ መደራጀት አማራጭ እንደሌለው በግልፅ አሳይቶናል።
የ1966ቱ አብዮት “ስዩመ እግዚአብሔር” ነኝ፣ የሥልጣን መሰረቴ መለኮታዊ ነው ብሎ የሚያምነውን ፍጹማዊ የንጉስ ሥርዓት ላንዴና ለመጨረሻ ግዜ የሸኘ ትልቅ ታሪካዊ ክስተት ነው። ሆኖም እኛ ኢትዮጵያዊያን ባለፉት ሃምሳ አመታት ጎራ ለይተን እርስ በርስ ከመገዳደል ውጭ የአገር ሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤት ማን መሆን አለበት የሚለውን ጥያቄ ቁጭ ብለን ተነጋግረን መመለስ ባለመቻላችን፣ በ1966 ዓ.ም. ከመለኮታዊያን እጅ የነጠቅነውን የፖለቲካ ሥልጣን በ1983 ዓ.ም. ለብሔር፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች በማስረከባችን ዛሬ የብዙ ኢትዮጵያዊያን ጥያቄ እንደ አገር እንቀጥላለን ወይ የሚል የ3ሺ አመት ታሪክ አለኝ ከሚል ህዝብ አፍ መውጣት የሌለበት ጥያቄ ነው።
የሰማዕታት መታሰቢያ ቀንን በምናስብበትና የአድዋን በአል በምናከብርበት በመጪው የከቲት ወር እያንዳንዷን ቀን ያለፉት ሃምሳ አመታት ጉዟችንን ወደኋላ ዞር ብለን መመልከትና ምን ተሳሳትን፣ ምን አጎደልን፣ምንድነው ማድረግ ሲገባን ያላደረግናው፣ አለማድረግ ሲገባንስ ያደርነው ምንድነው የሚሉ ጥያቄዎችን መመለስ አለበን። ከ1950ዎቹ መጀመሪያ ከነ ጄኔራል መንግስቱ ንዋይ ንቅናቂ ጅምሮ ላለፉት 65 አመታት ኢትዮጵያ ውስጥ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ገንብተን የስልጣን ባለቤትም መሰረትም ህዝብ መሆኑን ማረጋገጥ ያልቻለው ለምንድነው የሚልውን ጥያቄ በሚገባ መርምረን መመለስ ብቻ ሳይሆን በመልሱ ላይ ተመርኩዝን ለአሸናፊነት የሚያበቃ የትግል ስትራቴጂ በጋራ መንደፍ አለብን!
ያለን አንድ አገር ነው፣ ያለን ምርጫም አንድ ብቻ ነው . . . . . አባቶቻችን አንድ ላይ ታግለው ያወረሱንን አገር እኛም አንድ ላይ ታግለን ለልጆቻችን ማውረስ አለብን! ፊት ለፊታችን ላይ ሁለት ዕድሎች ይጠብቁናል. . . . . ቋንቋና ሃይማኖት ሳይለየን እንደ አንድ አገር ህዝብ አንድ ላይ በጋራ ታግለን እንደ አገር መቀጠል ወይም ተነጣጥለን መጥፋትና የአገራችንን መጨረሻ እጃችንን አጣጥፈን ቁጭ ብለን መመልከት። ምርጫው የኛ ነው! የቱን ትመርጪያለሽ? የቱን ትመርጣለህ?