ዶ/ር በቀለ ገሠሠ (drbekeleg@gmail.com)
1ኛ/ መንደርደሪያ
የዘር ፖሊቲካ ከባድ ጉዳት እያደረሰ ይገኛል። በተለይ በአማራውና በኦርቶዶክስ ተከታዮች ላይ የሚካሄደው ጭፍጨፋና ማፈናቀል እጅግ በጣም አሳሳቢ ደረጃ ላይ ይገኛል።
የአገሪቷ ኢኮኖሚ ዚሮ ገብቷል። የአገሪቷ አንድነትና ሕልውና በከባድ አደጋ ላይ እየወደቀ ነው። ከጎረቤት አገሮች ጋር ሰላም የለንም። ከዚያም ከዚህ ጦርነቶች እየተጫሩ ይገኛሉ።
እነዚህን ከባድ ችግሮች ለመቅረፍ እያንዳንዱ ዜጋ ሊያስብበት ይገባል።
2ኛ/ የዘር ማጥፋት ወንጀል ቶሎ መቆም አለበት።
በተለይ በወለጋ፣ በቤኒሻንጉል፣ በሻሸመኔ፣ በሸዋ፣ ወዘተ በአማራ ህዝብ ላይ የተካሄደው ጭፍጨፋና ማፈናቀል ለጆሮ የሚቀፉ ከባድ ወንጀሎች ናቸው። አሁን ደግሞ በመላው አማራ ክልል ላይ ከባድ ጦርነት ታውጆ ምስኪኑ ህዝባችን በድሮንና በዲሽቃ እየረገፈ ይገኛል። ንብረቶችና ሰብሎች እየተቃጠሉ ናቸው።
ወጣቶች ትምህርት ቤቶችና ኮሌጆች ገብተው መማር አልቻሉም። በዚህ ከቀጠሉ የወደፊት ዕጣ ፈንታቸው ምን ሊሆን ነው?
እነዚህ ሁሉ አሳፋሪና አረመኔያዊ የዘር ማጥፋት ወንጀሎች ቶሎ መቆም ይገባቸዋል። ካለዚያ ተያይዞ መጥፋትን ሊያስከትል ይችላል።
3ኛ/ ኢኮኖሚያችን መሻሻል አለበት።
እግዚአብሔር ውድ አገራችንን ሀሉን አሟልቶ ፈጠራት። ከራሷ አልፋ ለሌሎችም የምትተርፍ የተቀደሰች አገር ናት።
ዳሩ ግን ወገን ወጥቶ ማረስና ዞሮ መነገድ ባለመቻሉ ኢኮኖሚያችን ደቀቀ፣ ህዝባችን ተራበ፣ ተሰደደ። ለወደፊቱ ለፍርድ መቅረባቸው ባይቀርም ለጊዜው ጥሩ ኑሮ የሚኖረው ዘራፊውና ነፍሰ ገዳዩ ብቻ ነው።
ዓለም ህዝቡን ለመመገብ በሚሯሯጥበት ወቅት የኛዎቹ ከመቶ ሃያ ሚሊዮን በላይ ህዝባችንም ይዘው በኢኮኖሚ እድገት ምትክ መጠፋፋትንና ውድመትን የመረጡበት ምክንያት ከባድ እንቆቅልሽ ሆኖብኛል። በዚህ መቀጠል አንችልምና ቶሎ መቆም አለበት።
4ኛ/ የውጪ ግንኙነታችን መሻሻል አለበት
4.1 ከጎረቤት አገሮች ጋር/ በተለይ ከኤርትራና ከሱማሊያ ጋር
አሁን ሥልጣን ላይ ያሉት ቡድኖች አለቃ የነበረው ኢህአዴግ ነበር ካለምንም ጠቃሚ ስምምነት የኤርትራን መገንጠል አፋጥኖ የሸኛቸው። ይባስ ብሎ ብዙም ሳይቆይ በሁለቱ መካከል በተቀሰቀሰው የባድመ ጦርነት ከመቶ ሺ በላይ ሠራዊቶች ህይወታቸውን አጡ። ብዙም ወገኖች ተፈናቀሉ።
ሁሉም ነገር በሰላም ቢጠናቀቅ ኖሮ በጥሩ ወዳጅነትና የኢኮኖሚ ትስስር ሁለታችንም በሰላምና በጥሩ የኢኮኖሚ እድገት መኖር በቻልን ነበር። ኢትዮጵያም ወደብ አልባ ሆና ባልቀረች ነበር። ከኤርትራ ጋራ ብዙ ታሪካዊ ትስስሮች ስላሉን አሁንም መፍትሄው መልካም ወዳጅነትና የኢኮኖሚ ትብብር መመሥረት ብቻ ነው።
አሁን ደግሞ በሱማሊያ በኩል ተመሳሳይ አደገኛ ስህተት እየተደገመ ነው። ሶማሊላንድ ገና ነፃ አገር አይደለችም። የዓለማቀፍ ሕግጋትን በመጣስ እውቅና መስጠቱ ከሶማሊያ ጋር ብቻ ሳይሆን ከብዙ ኃይሎች ጋር ሊያጋጨን ይችላል። መዘዙም ከባድ ስለሚሆን ቶሎ ቢታሰብበትና እርማቶች ቢደረጉ ይበጃል።
4.2 ከኢጋድ፣ ከአፍሪቃ አንድነትና ከዓለማቀፍ ድርጅቶች ጋር
ኢትዮጵያ በተከበረችባቸው ዘመናት ማመን የሚያቅቱ አያሌ ተግባራትን ፈጽማለች። ከአፍሪቃ እርሷ ብቻ ነበረች የሊግ ኦፍ ኔሽንስ አባል የነበረች። በመቀጠልም የዓለም መንግሥታት ድርጅት መሥራች አባል ነበረች። የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት መሥራች አባል ከመሆኗም በላይ ለምሥረታው ከፍተኛ ሚና ተጫውታለች። የአፍሪቃ ህብረትና የተለያዩ የዓለማቀፍ ቅርንጫፍ ድርጅቶች መቀመጫ ናት። የባርነትና የቅኝ አገዛዝ ሥርዓቶችን ለማስቀረት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጋለች።
ዛሬ ግን ተንቃ ትገኛለች። ወንጀል የተንሰራፋባት አገር ሆናለች። ከውስጥም ከውጪ ብዙ ጠላቶች እየተፈለፈሉ ናቸው። ይሄ ደግሞ በተለይ ለውጪ ታሪካዊ ጠላቶቻችን በር ሊከፍት ይችላል።
በዚህ ሁኔታ የቀድሞ ዝናዋንና ክብሯን ጠብቃ መቀጠል ሊከብዳት ይችላል። እነዚህም ብዙ ከባድ ችግሮች ሊፈጥሩብን ስለሚችሉ ቶሎ ብናስብባቸው ይሻላል።
5ኛ/ መደምደሚያ
ሰዎች መሆናችንን አንርሳ። የሰው ህይወት ውድ ነው። ማንም ተነስቶ የሰውን ህይወት ማጥፋትም ሆነ ከገዛ ቀዬው ማፈናቀል አይችልም፣ በምድርም በሰማይም ያስጠይቃልና።
ከጌታችን ቀዳሚ ትዕዛዛት መካከል ኢትቅተል/አትግደልና ኢትሥረቅ/አትስረቅ የሚሉ እጅግ ጠቃሚ ትምህርቶች ይገኛሉ።
የመከላከያ ኃይል ኃላፊነት ድንበር መጠበቅ ነው። የፓሊስ ሠራዊት ኃላፊነት የዜጎችን ሰላምና ደህንነት መጠበቅ ነው። ወንጀለኞች ለፍርድ መቅረብ አለባቸው።
ስለዚህ ንፁሐን ዜጎቻችን በዘርና በኃይማኖት ሆነ በጊዜያዊ ጥቅማጥቅሞች ሳይከፋፈሉ ባንድ ላይ ቆመው በመታገልና በመጸለይ እልቂቱን እንዲያቆሙ በጥሞና ደጋግሜ አሳስባለሁ።
ቸሩ አምላካችን በከንቱ የሚፈሰውን የእናቶች፣ የህፃናትና ጠቅላላ የጭቁን ህዥባችንን ደም ይመልከትና ይታደግልን።