የፋኖ እስረኛ አያያዝና አወዛጋቢ ውሳኔዎች፤ከተሞችን በመስዋዕት ይዞ በማግስቱ በነጻ መልቀቅ፤ ለምን???

እንስማው ሃረጉ

አንዳንድ ማብራርያ የሚያስፈልጋቸው ነገሮች አሉ፡፡ የሚድያ አካላት የፋኖ መሪዎችን ሲያገኙ መጠየቅ አለባቸው፡፡ እኒህ አንገብጋቢ ነገሮች ለህዝብ መብራራት አለባቸው ያለበለዝያ ዋጋ እያስከፈሉ ትግሉን ወደ ኋላ ሊያስቀሩት ይችላሉ፡፡ ህዝብ በፋኖ ላይ ጥርጣሬ እንዲያድርበት እያደረጉ ነው፡፡ የፋኖ ዓላማ ከተማ ይዞ በማግስቱ መልሶ ለብልጽግና አመራር መልቀቅ ሳይሆን ከተሞችን በቁጥጥሩ ስር አውሎ የብልጽግናን መዋቅር በሙሉ መደምሰስና በምትኩ በፋኖ የሚመራ የህዝብ አስተዳደር ማቋቋ፤ መሆን አለበት፡፡ ከተማ ይዞ፤ከተማ መልቀቅ እቃቃ ጨዋታ ሆኗል፡፡ ህዝብ ማብራርያ ይፈልጋል፡፡ ፋኖ ከተማ ለመያዝ የሚከፍለው መስዋዕትነት ከባድ ነው፤ታድያ በከባድ መስዋዕትነት የተያዘው ከተማ በማግስቱ ተመልሶ ለብልጽግና አመራር ይለቀቃል፤ለምን?

ባለፉት ስምንት ወራት በተደረገው የፋኖ ትግል ብዙ አያሌ ድሎችን አስመዝግቧል፡፡ አብዛኛው የአማራ ክልል በፋኖ እጅ ሆኗል ነገር ግን ከተሞችን ለረጅም ግዜ ፋኖ ይዞ መቆየት አልቻለም፡፡ ላሊበላን ጨምሮ አያሌ ከተሞች በፋኖ ተደጋግመው ቢያዙም ብዙ ሳይቆዩ ፋኖ ለቅቋቸው ወጥቷል፡፡ ከተሞች በፋኖ ተይዘው ያልቆዩበት ምክንያት አይታወቅም፡፡ የማንም አገር የፖለቲካ ሚዛን ከተሞች ውስጥ ነው፡፡ በከተሞች የአገልግሎት ተቋማትና የህዝብ ክምችት ስለሚገኝ ፖለቲካዊ ፋይዳው ከፍተኛ ነው፡፡ ፋኖ አብዛኛውን የገጠር አካባቢ ለረጅም ወራት መያዝ ቢችልም የዞን ከተሞችን ይዞ መቆየት አልቻለም፡፡ የፋኖ መሪዎች እንደሚናገሩት ከሆነ ከተሞችን ለረጅም ግዜ ይዘው ከቆዩ ብልጽግና በከባድ መሳርያና በድሮን ከተሞችን ስለሚያወድም እየለቀቅን ለመውጣት ተገዳናል ይላሉ፡፡ ይህ አባባል እውነት ከሆነ ታድያ ፋኖ ከተሞችን መያዝ አይችልም ማለት ነው? ፋኖ ከተሞችን ይዞ የሚያስተዳደረው መቼ ነው ታድያ?

ሌላው የፋኖ አወዛጋቢ ውሳኔ የምርኮኛ አያያዝን በተመለከተ ነው፡፡ የብልጽግና ጦር እስከ ደም ጠብታ ሲዋጋ ከርሞ መጨረሻ በፋኖ ሲሸነፍ ይማረካል፡፡ ይህ ምርኮኛ የብልጽግና ወታደር ቄስ ሲያርድ የነበረ፤ እናቶችን የደፈረ፤ ገዳማትን ያቃጠለ፤ ተቋማትን ያወደመ፤ንጹሃንን በጅምላ በአስፓልት የረሸነ፤የአርሶ አደሩን የእርሻ በሬ ቀምቶ አርዶ የበላ ቀማኛ ወንጀለኛ ነው፡፡ ይህ ምርኮኛ ለአገዛዙ ታማኝ ሆኖ ለወራት ሲዋጋ፤ ብዙ ፋኖዎችንም የገደለ ደመኛ ጠላት ነው፡፡ እንዲህ ያለውን ወንጀለኛ፤ደመኛ የአማራ ጠላት ምርኮኛ ሲሆን በዓለም ታይቶም ተሰምቶም የማይታወቅ እርህራሄ ይሰጠውና፤ መጫሚያው ተቀይሮለት፤ ልብስ ተሰጥቶት፤የላመ የጣመ ቀለብ ተሰጥቶት፤ መታወቂያ ወጥቶለት፤ የትራንስፖርት ገንዘብ ተሰጥቶት ምንም እንዳልተከሰተ፤የሰራው ወንጀል ሳይጣራና ፍትህ ሳይሰጥ በሰላም ወደ ቤቱ ይላካል፡፡ ፋኖ ሙሉ ወጪውን ሸፍኖ ይልከዋል፡፡ በዚህ መልኩ የተሸኑት ምርኮኞች ተመልሰው ለብልጽግና ሲዋጉ በድጋሚ ተማርከዋል፡፡ የሚላኩት ምርኮኞች አማራ የሆኑት ጭምር ነው፡፡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በነጻ የተላኩት አማራ ምርኮኞች ተመልሰው ለብልጽግና በመግባት የሚሊሻና አድማ ብተና ስልጠና እየሰጡ እንደሆነ ታውቋል፡፡ በነጻ የተላኩት የኦሮሞ ምርኮኞች ተመልሰው ለመከላከያ ሲዋጉ የተማረኩ አሉ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የሀገርና ወገን አድን ክተት ጥሪ ክፍል ፭ - ቅድመ ምርጫ የኢትዮጵያ መንግስት አዋላጅ ካውንስል ስለመመስረት- ከአባዊርቱ

ይህ የሚያሳየው የፋኖ የምርኮኛ አያያዝ በስህተት የተሞላ መሆኑን ነው፡፡ ብልጽግናን ማርኮ በነጻ የሚለቅ ብልጽግና እንጅ ፋኖ ሊሆን አይችልም፡፡ብልጽግናን ማርኮ በነጻ የሚሸኝ ፋኖ የህዝብ ትግል መሪ መሆን አይገባውም፡፡ እንዲህ አይነቱ ፋኖ የአማራ ትግልን ያዳክማልና ከአመራርነት መወገድ አለበት፡፡ በነጻነት ትግል ውስጥ ጽድቅና ኩነኔ የሉም፡፡ ባህታዊነት በፋኖ አርበኝነት ማዕረግ ቦታ የላቸውም፡፡ መጽደቅ የፈለገ ሱባኤ ይግባ እንጅ የህዝብ ትግል በመጥለፍ ሩህሩህ በመምሰል መንግስተ ሰማያትን መውረስ አይቻልም፡፡

ፋኖ እራሱን መገምገም አለበት፡፡ ፋኖ የአቅም ችግር ካለበት ሳይውል ሳያድር እራሱን ማነጽ አለበት፡፡ ፋኖ መዋቅሩን ማሳደግ አለበት፡፡ ፋኖ በውስጡ የደህንነትና የፍትህ ስርዓትን ገንብቶ የስለላና ዳኝነት ተግባር ስራ ላይ ቢያውል ኖሮ ተመልሰው ለብልጽግና የገቡት ምርኮኞች በማጣራት ሂደቱ ታውቀው በፋኖ እስር ቤት መቆየት ነበረባቸው፡፡ ፋኖ የብልጽግና ታማኞችን ተንከባክቦ ስለሚልክ ተመልሰው እየወጉት ነው፡፡ ይሄ አሳሳቢ ነገር ነው፡፡ ፋኖ ህዝብ እያስተዳደረ ስለሆነ የደህንነትና የፍትህ ስራንም አብሮ መዘርጋት አለበት፡፡ ፋኖ የተማረ ኃይል ችግር የለበትም፡፡ የፋኖ የስለላ መዋቅርም በሳይንሳዊ ዘዴ መደገፍ አለበት፡፡

ባጠቃላይ ፋኖ ከተሞችን መስዋዕት ከፍሎ ከያዘ በኋላ በነጻ መልቀቅ ትርጉም የለውም፡፡ ፋኖ የተማረኩትን ሳያጣራና ፍትህ ሳይሰጥ በጅምላ ስለሚለቅ፤መልቀቅ ብቻ ሳይሆን አሞላቅቆ ልብስና ገንዘብ እየሰጠ ስለሚልክ አላግባብ ከልክ ያለፈ እርህራኈ በማድረጉ የራሱን ትግል እየጎዳ ነው፡፡ ይሄ መታረም አለበት፡፡ የፋኖ ምርኮኛ የህዝብ ጠላት ነው፡፡ ይሄ ምርኮኛ ዘር ማጽዳት የፈጸመ የኢትዮጵያ ጠላት ነው፡፡ ይሄ ጠላት ተጣርቶ ፍርድ ሳይሰጠው በነጻ መለቀቅ የለበትም፡፡ ፋኖ ወንጀለኛን በነጻ የሚለቅ ከሆነ ከህዝብ ያጣላዋል፡፡ ምርኮኛ ይለቀቅ ከተባለ ቢያንስ በምትኩ የፋኖ መሪዎችን ማስለቀቅ ያስፈልጋል፡፡ በእስራኤልና በፍልስጤም ምርኮኞች መካከል የሆነው ይህው ነው፡፡ እስራኤል ባትፈልግም አፍጫዋን ተይዛ የሃማስ መሪዎችን ለቅቃለች፤ በምትኩ የአሜሪካ ዜግነት ያላቸውን ጨምሮ የተያዙ ሰላማዊ ዜጎችን ሃማስ ለቅቋል፡፡ በዪክሬይንና በሩስያ መካከልም እየሆነ ያለው ይህው ነው፡፡ ትናንትና ብቻ ከመቶ በላይ የሩስያ ወታደሮች ከዩክሬይን ተለቀዋል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ሀገራችን ወደ እርስ በርስ ጦርነት እንዳትገባ ምን ይደረግ? - ቴወድሮስ ኅይለማርያም (ዶ/ር)

የፋኖ የተለየ ሊሆን አይችልም፤ምርኮኛ ለምን በነጻ ይለቀቃል፤ለምን? ፋኖ ምርኮኞችን ለምን በነጻ ይለቃል? ለምን? እነ መስከረም፤ሲሳይ አውግቸው፤ወንደወሰን፤ክርስትያን ታደለ፤ዮሃንስ ቧያለውና የመሳሰሉት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የአማራ መሪዎችና ጋዜጠኞች በአዋሽ አርባ በኮንቴይነር እስር ቤት በበረሃ እሳት እየተሰቃዩ የብልጽግና ገዳይ አዋጊዎች፤ ካድሬዎችና አመራሮች በነጻ ይለቀቃሉ፡፡ ይሄ ትክክል አይደለም፤ መታረም አለበት፡፡ ፋኖ ብዙ የወረዳ እና የዞን አመራሮችን ማርኮ በነጻ ሲለቅ ቢያንስ የፋኖ መሪዎችን ማስለቀቅ ነበረበት፡፡ ሚሊሻና አድማ በተናም ከተማረከ በኋላ በነጻ መለቀቅ የለበትም፡፡ ቢያንስ ለፋኖ ቀለብ የሚሆን የእርሻ ስራ በመስራት ዋጋ መክፈል አለበት፡፡ ሂሳብ መወራረድ አለበት፡፡ ፋኖ በዳንግላ እስር ቤት የነበሩ 18 የትግሬ ተዋጊዎችን በነጻ ሲለቅ ህወሃት አያሌ የሚታወቁና የማይታወቁ አማራ እስረኞችን እስካሁን አስሮ እያሰቃየ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ከወልቃይት ታፍነው ተሰውረው ዳናቸው ጠፍቶ የቀረ ሺዎች አሉ፡፡ ፋኖ መስዋዕት ከፍሎ የትግራይ ተዋጊዎችን ነጻ ሲያወጣና ሲልካቸው በምትኩ ህወሃትን መጠየቅ ነበረበት፡፡ ምርኮኛን በነጻ መልቀቅ መልሶ እራስን ይጎዳልና ይታሰብበት!!

ለክርስትያን አንባቢዎቼና የዓለም መድኃኒት (በግዕዝ መድሃኒዓለም) ከድንግል ማርያም በማህጸን ተወስኖ መወለድ ለምታምኑ፤ መልካም የገና በዓል ይሁንላችሁ!!

ድል ለፋኖ፤ሞትና ስደት ለብልጽግና!!

 

4 Comments

  1. ፋኖ ምርኮኞችን ለምን በነጻ ይለቃል?
    Because the so-called government, TPLF or OLF do not give a damn about the prisoners captured by Fanno. If they were to be all killed, these criminal and terrorist institutions do not care at all. It is not like they care for the return of this prisoners and would in exchange free captured Fanno members or other victims of Amhara persecution.

    The one important point that I agree with the author is regarding the release of former Tigrayan members of Mekelakeya. These prisoners that had mechanized warfare experience should have been retained so they could train Fanno in the skills of mechanized warfare. So far, Fanno has been burning any tanks and heavy weapons for lack of the means or wherewithal to employ them in its operations. As the war progresses, the likelihood that Fanno is forced by circumstances to develop into a conventional force is high. Then such expertise would be in dire need.
    Four decades ago, TPLF used Derg POWs to train its combatants in several aspects of military science and mechanized warfare.

  2. ምድሪቱ ይልሱት ይቀምሱት ለሌላቸው የማታስብ በያዘው ጥለፈው ዘይቤ ለዘመናት በመገዳደል ፓለቲካ ተተብትባ የታሰረች ናት። ጦርነት የማጥቃትም ሆነ የመከላከል የራሱ የሆነ ወታደራዊ ስልትና ህግ አለው? የመሳሪያው አመራረጥና የጥቃት አጀማመርና አጨራረስም እንዲሁ በተሰላ መልኩ የሚከወን ነው። እርግጥ ነው ነገር እንደታሰበው አይሆንምና ያኔ ተራራ ያንቀጠቀጡት ሲንቀጠቀጡ፤ ያኔ አንድ ጥይትና አንድ ሰው እስኪቀር እያሉ ያፋከሩት እልፍ እረግጠው ነፍሴ አውጭኝ በማለት እንደፈረጠጡ ታሪክ ይናገራል። ይህ አሁን በፋኖና በመከላከያ መካከል የሚደረገው ስር ግብ የአማራን ህዝብ ሁለት አፍ ባለው መጋዝ እየከረከረ የሚቆርጥ፤ ከደርግ እልቂት፤ ከወያኔ የ 30 ዓመት ሰቆቃና የይፋ ጦርነት የተረፈውን ቅሬት እንዳይኖር ጨርሶ የሚያጠፋ ግጭት ነው። አውቃለሁ የሩቅ ሃገር አዋጊዎች ይህ ሃሳብ እንደማይዋጥላቸው። ጥሩ ነው አንቆ ይያዛቸው። ማወራረጃ ላጡበት ሃቅ ፈራጅ ጊዜ እንጂ የእኔም የእነርሱም ቃል አይደለም።
    እንዴት ባለ ሂሳብ ነው ፋኖ ጎንደር ላይ በገና ዋዜማና በገና እለት ጦርነት የሚከፍተው? ምን የሚሉት ወታደራዊ ስልት ነው? ሰው እንኳን ትንሽ ተንፈስ ብሎ ያለውን ቆርጥሞ ውሃ እንዳይጠጣና ፈጣሪውን ተመስገን እንዳይል እንዲህ ያለ መዓት ማዝነብ ለማን ታስቦ ነው? ግን ለህዝብ ለወገን ቆመናል ያሉን ያኔም አሁንም ገቢያ አውጥተው የሸጡንና የሚሸጡን ናቸው። ፓለቲካ አቅጣጫ እንደሌለው ንፋስ ነው። በኦሮሚያ ክልል፤ በአማራ ክልል እንዲሁም በሌሎቹ ሰላማቸው በደፈረሰው አካባቢ ህዝቡ መከራ የሚቀበለው ከሁለት ጎን ነው። ነጻ እናወጣሃለን በማለት በስሙ የሚፋለሙት ከሚያመጡበት ጦስና ከአራት ኪሎው መንግስት።
    እንዴት ያለ ወታደራዊ ኦፕሬሽን ነው ከተማ ገብቶ ሰውን አሸብሮና ተሸብሮ ነገርን አውድሞና አዋድሞ እግሬ አውጭኝ በማለት ዳግም ደግሞ ተመልሶ በመምጣት ያንኑ ያለምንም ማስተካከያ በመድገም ሰውን የሚያስጨርስ? ለህዝብ ነጻነት የሚታገል በህዝቡ ጉያ ውስጥ ተሸሽጎ ህዝብንና ያለውን መሰረታዊ የህብረተሰብ መገልገያ እንዲወድም አያደርግም። በመሰረቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ የብሄር ታጋዪችና በመንግስት መካከል ያለው ልዪነት ፋንታና ሚሪንዳ ካላቸው ጣዕም ጋር ይመሳሰላል። አንድን ከሌላው መለየት አይቻልም። ማሸጊያቸው ብቻ ነው ልዪነታቸውና! ሁለቱም ሃይሎች አጥፊ ሃይሎች ናቸው። ለዚህም ነው የህዝባችን ገመና ከዘመን ዘመን እየመረረ የሄደው። መንግስት በማሰር፤ በመግደል፤ በማስገደል፤ በመሰወር በጭራሽ እድሜውን ሊያራዝም አይችልም። ያ ቢሆን ኑሮ ደርግና ወያኔ ዛሬም ስልጣን ላይ በኖሩ ነበር። ግን የሃበሻው የፓለቲካ የአዙሪት ህግ ይህን አይፈቅድም። በላይ ዘለቀን ቆሞ ያስገደለው ጄ/ መንግስቱ ነዋይ እሱም በወረፋው ተንጠልጥሏል። በሰው እንባ በየጊዜው ይቀልድና ያስቀልድ የነበሩ የንጉሱ ባለስልጣኖች እንበለ ፍርድ ነው በጥይት ተደብድበው የሞቱት። ለዚህ ነው የሃበሻው ፓለቲካ የመገዳደል ፓለቲካ እንጂ ለምድሪቱ ወይም የዛሬዎቹ የቋንቋና የክልል ጣኦት አምላኪዎች እንደሚሉት ነጻ የሚያወጣም ነጻ የሚወጣም ህዝብ የለም የምንለው። ኢትዮጵያ የሁላችን የጋራ ሃገራችን ነበረች። ግን ያ ቀርቶ ሌላ ዘፈን መጣና ይኸው ጊዜ የሰጣቸው አካኪ ዘራፍ ይሉባታል። ይህም ያልፋል። ሌላ የተራበና የከፋ በቦታው ይተካል። ያለፈው ታሪካችን ይህን አስረግጦ ያስረዳል።
    ፋኖ ከተማ ያዘ አልያዘ ለአማራ ህዝብ የሚያመጣው አንድም ፋይዳ አይኖርም። 17 ዓመት ሙሉ ከደርግ ጋር የተፋለመው ወያኔ 30 ዓመት ሙሉ ከኢትዮጵያ ለመገንጠል የተዋደቀው ሻቢያ ለምድራቸው ያበረከቱት ያንኑ የተካኑበትን ጭካኔና መከራን ነው። ችግራችን የአስተሳሰብ ለውጥ የሚሻው ለዚህ ነው። ሁሌ ቃታ እየሳቡ ሰውን መግደልና ማስገደል እርባና የሌለው ጊዜ ያለፈበት የፓለቲካ ዘይቤ ነው። አሁን ማን ይሙት በኢትዮጵያ ውስጥ እውነተኛ ፍርድ ቢኖር ወያኔዎች ኑርንበርግ የሚያስቆም በደል አልፈጸሙም? ሻቢያ በሰው ደም እጅን አልታጠበም? ብልጽግና ግፍና መከራን አልሰራም? ግን ማን ሰምቶ ሁሉም በዘሩና በቋንቋው ተሰልፎ እንደ እንቁራሪት አንድ ሲጮህ አብሮ መጮህ ነው። የምድሪቱ መከራ ገና ቀጣይ ነው። የዛሬዎቹ የፓለቲካ ባላንጣዎች ነገ ይሻረካሉ፤ የዛሬዎቹ ሽርከኞች ነገ ተመልሰው ጠላት ይሆናሉ። በሃበሻ የፓለቲካ ታሪክ ገና ድሮ ድንጋይ ዳቦ እያለ ጀምሮ ያየነው ይህኑ ነው። የግፍ ምድር፤ ማባሪያ የሌለው ዶፍ። ሞትና ሰቆቃ የተለመደበት ምድር። መቼ ይሆን ማቆሚያው? በቃኝ!

  3. “ቢያምር ጠላሁ?” የሚል ብሂል አለ፡፡ ችግሩ ያለው ያንተ “ከተማ ያዙ/ተቆጣጠሩ” የሚለው አረዳድ ነው፡፡ 604ኛ ኮር በሻብያ እርዳታ ሽሬ ላይ ክተደመሰሰ በኋላ ደርግ መቀሌን ለቆ ሲወጣ እነ መለስ ዜናዊ ያልጠበቁት እና እጅግ ያስደነገጣቸው ዉሳኔ ነበር፡፡ ክሁለት አመት በኋላ ነው ኢህአዴግ የሚባል ስብስብ ፈጥረው ዉጊያውን ከትግራይ ያወጡት፡፡ ለደፈጣ ተዋጊ ያውም ወጥ እና ግልጽ ግብ በፕሮግራም ላላስቀመጠ ድርጅት [ትልቅ] ከተማ ተቆጣጥሮ ማስተዳደር ብዙ ዝባዝንኬ አለው፡፡ ቀላሉ ነገር “አትጠብቅ!”
    ስለምርኮኛ አያያዝ ያልከውም አዲስ አይደለም፡፡ ድሮ ሻዕቢያዎች በተለምዶ “የደርግ ጦር” የሚባለው ላይ የፈጸሙትን ነው ፋኖ እንዲፈጽም የምትገፋፋው፡፡ “ከታሪክ እየኮረጁ ታሪክ ራሱን ደገመ” ይሉናል ያለው ማን ነበር? እውነቱ ይነገር ክተባለ ደግሞ የመለስ ዜናዊ ህወሃት አሁን ፋኖ የሚያደርገውን አድርጓል፤ ተጠቅሞበታልም፤ ቢያንስ የታሪክ ጠባሳ ክመተው ተርፈዋል፡፡
    ስላማችን ይብዛ!

  4. Well, it is the right thing to ask what we need to know and have opinions how we do look things and make sure we are on the same page as far as the fight for existence and bringing about a fundamental democratic change in the country in which all citizens shall enjoy a real sense of life which has been terribly missing throughout our political history , and nowadays totally being destroyed by the very stupid and brutal ruling elites of ethno- Centrism .
    However, we need to be mindful what and how to ask and criticize this very though and sensitive issue of the ongoing fight of hit ( attack) and retreat tactic that is in line with the very strategy and goal of a successful counter and defeat !!!!
    We must be very careful and wise, not naive and simplistic !!!

    .

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share