በከንቱ የሚፈሰው የወገኖቻችን ደም ማቆሚያው መቼ ይሆን?! (እግዝእትነ ማርያም ስምዒ ኀዘና ወብካያ ለሀገሪትነ ኢትዮጵያ!!)

በዲ/ን ተረፈ ወርቁ

‹‹… እስከ ዛሬ ስጸልይ ነፍሳተ-ሙታንን ማርልን ነበር የምለው፤ አሁን ግን የካህኑ ዘካርያስን ደም የተበቀልክ አምላክ የካህናቶቻችንን፣ የንጹሀን ወገኖቻችንን ደም ተበቀል ነው የምለው!!››

(እማሆይ ፍቅርተ ማርያም ከደብረሊባኖስ ገዳም)

ይህን ከላይ በመግቢያነት የተጠቀምኩትን በኀዘን፣ በምሬትና በሰቀቀን የተሞላ መልእክት የላኩልኝ በደብረ ሊባኖስ የሚገኙ አንድ እማሆይ እናት ናቸው፡፡ የእኚህ እናት ሙሉ መልእክት እንዲህ ይነበባል፤

 

‹‹አንድ በቅርብ የማቃቸው ካህን አባት 3 ወንዶች ልጆቻቸው እዚህ ደብረሊባኖስ ገዳም ልከው ይማራሉ፡፡ ታዲያ ባለፈው ሰሞን ሁለት ልጆቻቸው አባታቸውን ጥየቃ ሲሄዱ መንገድ ላይ ይታፈናሉ፡፡ አምስት መቶ ሺሕ ካለመጣችሁ አትልቀቁም ይሏቸዋል፡፡ ጉዳዩን የሰሙት አባትም ከብታቸውን ሽጠው፣ ጎረቤቶቻቸውንና ዘመድ አዝማድ አስቸግረውና የሚያውቋቸው ሌሎች ሰዎችም ከውጪ ካሉ ኢትዮጵያውያን ገንዘብ አሰባስበው ልጆቻቸው ነጻ ወጡ፡፡

 

ይህ በሆነ በወሩ እኚህን ካህን አባት በአማርኛ ለምን ትሰብካለህ ያሉ አክራሪ፣ ፅንፈኛ ብሔርተኞች አረዷቸው፡፡ በደም የተነከረውን የአባታቸው ሬሳ ያዩ ልጆቻቸው አእምሮአቸው ተነክቶ ትምህርታቸውን ተዉት፡፡ ልቡ በኀዘን ተሰብሯል… እስከ ዛሬ ስጸልይ ነፍሳተ-ሙታንን ማርልን ነበር የምለው፤ አሁን ግን የካህኑ ዘካርያስን ደም የተበቀልክ አምላክ የካህናቶቻችንና የንጹሀን ወገኖቻችንን ደም ተበቀል ነው የምለው!!››

 

የካህኑ አባታችን ግድያ ይሰቀጥጣል፤ ግና አማራና ኦርቶዶክሳውያን ላይ ያነጣጠረው ማረዱ፣ ማሳደዱና ጭፍጨፋው አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡ የካህናቱ፣ የሕጻናቱና የንጹሐን ደም እንደ አቤል ደም ለፍርድ እየጮኸ ነው፡፡ እናት ኢትዮጵያም እንደ እስራኤላዊቷ ራሄል በግፍ ለታረዱባት ልጆቿ እንባዋን ወደ አርያም እየረጨች፤ እያነባች ነው፡፡

ታላቁ ቅዱስ መጽሐፍ፡- ‘‘የሰውን ደም የሚያፈስስ ሁሉ ደሙ ይፈስሳል፤ ሰውን በእግዚአብሔር መልክ ፈጥሮታልና፡፡’’ ደግሞም:- ‘‘… በሕዝብ ልጆች ላይ ቂምን አትያዝ፣ አትበቀልም፤ በባልንጀራህ ደም ላይም አትቁም፡፡ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፡፡’’ ይላል፡፡

 

ሰው ክቡር ፍጥረት ነው፡፡ በሃይማኖትም ሆነ በዘመናዊው ሳይንስ አስተምህሮ ሰው የፍጥረተ-ዓለሙ ሁሉ ቁንጮ፣ ዕፁብ፣ ድንቅና ውብ ፍጥረት እንደሆነ ነው አስረግጠው የሚናገሩት፡፡ በክርስትናም ሆነ በኢስላም ሃይማኖት አስተምህሮ መሠረት ደግሞ፣ ‘‘ሰው በፈጣሪ አምሳልና አርአያ የተፈጠረ፤ የአምላክ የሕይወት እስትንፋስ ያለበት እጅግ ክቡር ፍጥረት ነው፡፡’’

ተጨማሪ ያንብቡ:  ሰላም ጦርነትን ሲያሸንፍ፣ የደቡብ አፍሪካው ስምምነት፣ ይዘቱ፣ ተፈጻሚነቱና ተግዳሮቶቹ – ባይሳ ዋቅ-ወያ

 

ተጨማሪ ያንብቡ:  ሕዝባችን ንቁ ነው

በስድስቱ ቀናት ከተፈጠሩት ፍጥረታት መካከል ሰውን የሚተካከል ፍጥረት የለም፤ አልተገኘምም፡፡ ፈጣሪ ሰውን ከፈጠረ በኋላ ‘’ከፈጠራቸው ፍጥረታት ሁሉ መካከል ‘እጅግ መልካም’ እንደሆነ አየ፡፡’’ ይለናል የዘፍጥረት መጽሐፍ ጸሐፊ፣ ዕብራዊው ሊቀ-ነቢያት ሙሴ፡፡ የኢትዮጵያ ቤ/ክ ሊቃውንትም ሰው ምን ያህል በአምላኩና በፈጣሪው የተወደደና የከበረ ፍጥረት መሆኑን በተመለከተ እንዲህ አመስጥረዋል፤

ተጨማሪ ያንብቡ:  ትናንሽና ትላልቅ ጭንቅላቶች!! - ፈቃዱ በቀለ (ዶ/ር)

 

“ሰውን ቅዱሳት በሚሆኑ እጆቹ በርሱ አሳምሮ ፈጠረው፤ ሳመው፣ ወደደውም፡፡ የሕይወትንም መንፈስ በእርሱ ላይ እፍ አለ፡፡” እንዲሉ ሠለስቱ ምዕት/፫፻፲፰ቱ ሊቃውንት በቅዳሴያቸው፡፡

 

እንዲሁም በዓለማውያኑ ምሁራን ዘንድም መካከልም እንግሊዛዊው ባለቅኔውና ጸሐፊ ተውኔት ሼክስፒር በ‘ሐምሌት’ ድርሰቱ ውስጥ ሰውን እንዲህ ይገልጸዋል፡፡ “… ሰው እንዴት ዕፁብና ድንቅ ሥራ ነው! ሐሳቡስ እንዴት ክቡር ነው! ለአፈጣጠሩም ጥበብ ማብቂያ አይገኝለትም፤ በቅርጹ፣ በውበቱና በንግግሩስ እንዴት ያስደንቃል! በሥራውም መላእክትን ይመስላል! በመልኩም የፈጣሪውን! የዚህ ዓለም አስደናቂ ውበት፣ ከፍጥረታት ሁሉ የላቀ…!!’’

 

እንግዲህ እንዲህ ዓይነቱን የፈጣሪ ፍቅርና ጥበብ የታተመበትን ሰውን ያህል ክቡር ፍጥረት እንደ አልባሌ ፍጥረት ደሙን በየምክንያቱ በከንቱ እንዲፈስ ማድረግ የሚገባ ብቻ ሳይሆን በፈጣሪም ሆነ በሰው ፊት በፍርድ የሚያስጠይቅ እኩይ፣ የእኩይ እኩይ ምግባር መሆኑም በግልፅ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ለምን?! ሲባል ሰው በምንም ዋጋ ሊተመን የማይችል በፈጣሪ አምሳልና አርአያ የተፈጠረ ክቡር ፍጥረት ነውና!!

 

ይሁን እንጂ ከዚህ እውነት የተፋቱ ጨካኞች፣ ነፍሰ ገዳዮች በዚህ ክቡር ፍጥረት፣ በሰው ልጅ ላይ ሞትን አውጀዋል፡፡ ግፈኞቹ የጥፋት ሰይፋቸውን መዘው በግልፅ ወደ አደባባይ ወጥተዋል፡፡ በፅንፈኛ ብሔርተኝነትና በአክራሪ ሃይማኖተኝነት የተሰለፉ የጥፋት ልጆች በሕዝብ ላይ እልቂትን አውጀው፣ ምድሪቱን የኀዘን ከል እንድትለብስ አድረገዋታል፡፡ እነዚህ አክራሪዎችና ጽንፈኞች ሕጻን አረጋዊ፣ ወንድ ሴት ሳይሉ፣ ያለ ርኅራኄ በጭካኔ ሰይፋቸው- በሻሸመኔ፣ በዝዋይ፣ በአርሲ፣ በሐረሪ፣ በባሌ… ንጹሐን ዜጎችን ለአሰቃቂ ሞት ዳርገዋል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  “በ2007 ቅማንት ራሱን ያስተዳድራል ብለን እናምናለን”

 

ተጨማሪ ያንብቡ:  ኢትዮጵያዊያን ቅድሚያ ለሀገር ሉአላዊነት መስጠት ግዴታቸው ነው –  ሲና ዘ ሙሴ

ዛሬም እንኳን በዚህ የሕዝብ እልቂትና ሞት መካከል ሕዝብ ራሱን እንዳያይ የሚደልሉት ብዙ ወገኖች መበራከታቸውን እያስተዋልን ነው፡፡ ለሽልማት የሚያሞግሱ አዝማሪዎች፣ ለቁራሽ የሚያወድሱ ባለቅኔዎች፣ የአንተ ጎሣማ/ብሔርማ እያሉ ሥራን ሳይሆን ንቀትን የሚያስጠኑ ቤተ ዘመዶች፣ የተበደልህ ነህ፣ ደም መመለስ አለብህ የሚሉ ሽማግሌዎች ትውልድ ራሱን በማየት ካለበት ችግር እንዳይወጣ እንቅፋት ሆነዋል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ህይወት፤ ሰላምና ዕድገት - በቀለ ገሠሠ

 

የሌለንን እንዳለን አድርገው የሚናገሩ ነቢያት ነን ባዮች፣ ጥፋት እየመጣ ሰላም ነው! የሚሉ የአዎንታዊ/በጎ በጎውን ብቻ አስብ ስብከት አደራጆች፣ ዛሬ ላይ ትላንትን እንድንኖር የሚያደርጉ ጠብ አውራሾች፣ ያልጨረሱትን ክፋት በልጆቻቸው ላይ ለመፈጸም የሚጥሩ ዕድሜ ያላስተማራቸው ምንዱባኖች አገሪቷን እያተራመሷት፣ እረፍት እየነሷት እንደሆነ በግላጭ እያየን፣ እየታዘብን ነው፡፡

 

ዛሬም የወገኖቻችን እልቂት፣ ዛሬም የሰው ልጅ ሞት ቁጥር ሆኖብናል፤ ለመሆኑ አገር ተጎዳ ለማለት ያስቀምጥነው የሬሳ ኮታ ስንት ይሆን? የምንቆጨው በስንት አንገት ይሆን? ፍትሕን ለማስፈን የምንነሣው በስንት ሕፃናት መሰየፍ ይሆን? ኮታው ስላልታወቀ ጥፋት ዛሬም ነገም ቀጣይ እየሆነ ነው፡፡

 

የትናንትናው ግፍና ሰቆቃ ሳይሽር፣ በግፍ የፈሰሰው የወገኖቻችን ደም ሳይደርቅና የእናት ኢትዮጵያ እንባዋ ሳይታበስ ዛሬም ጨካኞቹ ምድሪቱን በደም አበላ እንድትዋኝ ፈርደውባታል፡፡ ክቡር የሰው ልጅ ሰውነት እየተቆራጠ በየጉድጓዱ እንደ ጉድፍ፣ እንደ ጥራጊ ቆሻሻ ተጥሏል፡፡ እናም ታላቅ የሆነ የለቅሶና የዋይታ ድምፅ ከኢትዮጵያ ምድር መስማቱን እንደቀጠለ ነው፡፡ የንፁሐን ደምና እንባ ምድሪቱን አጨቀይቷታል፡፡ ዛሬም የምስኪን ኢትዮጵያውያን እናቶች እንባ ወደ ሰማይ እየተረጨ፣ እንደ አቤል ደም ‘የፍርድ ያለህ! የፍትሕ ያለ እያለ!’ ወደ አርያም፣ ወደ ሰማይ አምላክ እየጮኸ፣ እየተጣራ ነው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የአሜሪካና ምዕራባውያን ጫናና መፈንቅለ መንግሥት በግርማዊነታቸው መንግሥት ላይ!! – መስፍን ማሞ ተሰማ

 

ተጨማሪ ያንብቡ:    ” በጎ ስጦታ ሁሉ ፍጹምም በረከት ሁሉ ከላይ ናቸው… ” መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ 

ገዳዮች ሆይ፤ ይህ በከንቱ የፈሰሰ ክቡር የሰው ልጅ ደም እንዲሁ አይቀርም፡፡ በፈጣሪ ፊት ይጮኻል፣ ይከሳል፣ ይፋረዳል፡፡ በግፍ የወደቁ ሰዎችን ደም እግዚአብሔር ከእጃችሁ ይፈልጋል፡፡ ገዳዮችን ብቻ ሳይሆን ይህ ክቡር የአምላክ ፍጥረት ደም በከንቱ ደሙ ሲፈስ ዝም ያልን፣ ለእውነትና ለፍትሕ ድምፃችንን ያላሰማን ሁላችንም ተጠያቂ ነን፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  አምናና ዘንድሮ - ነፃነት ዘለቀ

 

መንግሥት ሆይ፡- እንዲህ እንጠይቃለን… ገዳዮች እሽሩሩ ሲባሉ፣ ፍትሕ ሲሸጥ፣ እውነት አንገቷን ስትደፋ በዝምታ፣ በትዕግሥት የምትመለከተው እስከመቼ ይሆን…?!

 

በከንቱ የሚፈስ የንጹሐን ደም ለምድሪቱም መልካም አይሆንም፡፡ የሰው ልጅ ንጹሕ ደም አገርን ያፈርሳል፣ ያዋርዳል፣ ትውልድን/ሕዝብን ያፈልሳል፣ ከክብር ያሽራል፣ የግፍ ደም ጽዋ የሞላ ጊዜ ለወሬ የማይመች ነገር ይሆናል፡፡

መጽሐፍም የንጹሃን ደም በከንቱ መፍሰስ፤ ግፍና መከራ ለሀገር መቅሰፍት እንደሆነ እስራኤልን ምሳሌ አድርጎ እንዲህ ይናገራል፤

 

‹‹… ጽዮንን በደም፥ ኢየሩሳሌምንም በኃጢአት ይሠራሉ፡፡ አለቆችዋ በጉቦ ይፈርዳሉ፤ ካህናቶችዋም በዋጋ ያስተምራሉ፤ ነቢያቶችዋም በገንዘብ ያምዋርታሉ፤ ከዚህም ጋር እግዚአብሔር በመካከላችን አይደለምን?! ክፉ ነገር ምንም አይመጣብንም እያሉ በእግዚአብሔር ይታመናሉ፤ ስለዚህ በእናንተ ምክንያት ጽዮን እንደ እርሻ ትታረሳለች፥ ኢየሩሳሌምም የድንጋይ ክምር ትሆናለች፥ የቤቱም ተራራ እንደ ዱር ከፍታ ይሆናል፡፡

(ትንቢተ ሚኪያስ ፫፤፲-፲፪)

 

አበውም ሲተረቱ፤

ፈጣሪ ሲቆጣ በትርን አይቆርጥም፣

ያደርገዋል እንጂ ለወሬ እንዳይጥም፡፡ እንዲሉ፡፡

 

እግዝእትነ ስምዒ ኀዘና ወብካያ ለሀገሪትነ ኢትዮጵያ!!

ሰላም ለኢትዮጵያ!!

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share