November 25, 2023
ታዲያ ለምንድነው? የሚል ጥያቄ ስለሚነሳና መነሳቱም ተገቢ ስለሆነ ይህንኑ ግልፅ ለማድረግ አስተያየቴን በጥያቄ መልክ በማቅረብ መልሱን ሃይማኖትን ጨምሮ መሠረታዊ ሰብአዊ መብት ፣ ነፃነት፣ ፍትህ (ዴሞክራሲ) ፣ ሰላም፣ ፍቅር ፣ የጋራ እድገት ፣ ወዘተ የሚረጋገጥበትና የሚከበርበት ሥርዓት እውን እንዲሆን ከምር ለሚሹ ወገኖች እተወዋለሁ።
ስለምንከተላቸው የሃይማኖት ተቋማት ነፃነትና ስኬታማነት ስንነጋገር ከምንኖርበት (ከምንገኝበት) የፖለቲካ ሥረዓት ለምንነት ፣ ለማንነት ፣ እንዴትነት እና ከየት ወደ የትነት አንፃር መሆኑን መዘንጋት የለብንም።
እናም ልቀጥል፦
1) ከማሰቢያ ረቂቅ አእምሮና ከማከናወኛ ብቁ አካል ጋር በክርስቶስ አምሳል የተፈጠረ ሰብአዊ ፍጡር ከፈጣሪው እርዳታ ጋር መሠረታዊ መብቱ ተጠብቆ፣ እርስ በርሱም ተከባብሮ፣ ተረደዳቶ ፣ ተፋቅሮ፣ ሰላምን ተንከባክቦ ፣ በጋራ በልፅጎ ፣ ወዘተ እንዲኖር እና እነዚሁ ወርቃማ እሴቶቹ ከሞት በኋላ ተስፋ ለሚያደርገው ህይወት ስንቅ እንዲሆኑት መርዳትና ማስቻል የሃይማኖት ዓላማና ግብ ካልሆነ ሌላ ምን?
3) እርግጥ ነው ይህንን እውን ለማድረግ መንገዱ አልጋ ባልጋ አይሆንም። ሃይማኖትን ጨምሮ መሠረታዊ መብቶች በተጠየቁ ቁጥር ሥልጣነ መንበራቸው ሥጋት ላይ የወደቀ እየመሰላቸው ነፃነትና ፍትህ በሚጠይቀው መከረኛ ህዝብ ላይ የጭካኔ ሰይፋቸውን የሚመዙ እኩያን ገዥዎችን አግባብነት ባለውና በማይታጠፍ መንፈሳዊ መሪነት መጋፈጥ የግድ መሆኑን ተረድቶና ተቀብሎ የእረኝነት ሃላፊነትንና ተልእኮን የመወጣት ጉዳይ የሃየማኖት መሪዎች ካልሆነ ሌላ የምንና የማን?
5) በዚህ ረገድ ከዘመን ዘመን ከመሻሻል ይልቅ በእጅጉ እየባሰበት የመጣው ውድቀታችን አይደለም ወይ ሃይማኖቶቻችን ከፍተኛ ፈተና ላይ እየጣላቸው የሚገኘው? ይህንን እጅግ አሳሳቢና አስፈሪ ሁኔታ በጥሞና እና አርአያነትን በተላበሰ የሃይማኖት አርበኝነት ማስተካከል የሚገባቸው የሃይማኖት መሪዎችና ሊቃውንት ራሳቸው ሆነው ሳለ በሥልጣነ መንበር ላይ እየተፈራረቁ የመከራውንና የውርደቱን ዘመን በአስከፊ ሁኔታ እያራዘሙ ካሉት ባለጌና ጨካኝ ገዥ ቡድኖች ጋር እየተሻሹ ዘመን ጠገብ የሆነውንና የማይደፈረውን ሃይማኖታዊ ዶግማና ቀኖና በአፍ ጢሙ ሲደፉትና ሲያስደፉት ማየትና መስማት የሃይማኖት ምንነትንና እንዴትነትን ከባድ ፈተና ላይ ቢጥል ለምን ይገርመናል?
6) በተለይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስና የእስልምና ሃይማኖቶች ከነችግራቸውም ቢሆን ለረጅም ዘመን ከመኖቸው ጋር ተያይዞ የጋራ የሆኑ ማህበራዊ፣ ትውፊታዊ፣ ባህላዊ፣ ሥነ ልቦናዊ፣ ሥነ ምግባራዊ ፣ ወዘተ እሴቶችን አጣምረው የያዙ ከመሆናቸው አንፃር የባለጌና ጫካኝ ገዥ ቡድኖች ርካሽ የፖለቲካ ጨዋታ ሰለባዎች ሲሆኑ ማየት ከምር የማያስበን ከሆነ ስለየትኛው ሃይማኖትና የሃይማኖት ነፃነት ነው የምናወራው?
7) የትኛውም ሃይማኖት ከማሰቢያ አእምሮና ከብቁ የማከናወኛ አካል ጋር በክርስቶስ አምሳል የተፈጠረው የሰው ልጅ (የአገሬ ሰው) የገዛ ምድሩ በባለጌ፣ ሸፍጠኛ፣ ሴረኛና ጨካኝ የጎሳና የቋንቋ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ገዥ ቡድኖች ምድረ ሲኦል ስትሆንበት በጋራ ቆሞ ቢያንስ ነውር ነው ካላለና ካልገሰፀ ምን አይነትና እንዴት አይነት ሰብአዊ ሃይማኖት እንደሆነ ለመረዳት አያስቸግርም እንዴ?
8) ሲኖዶስን እና መጅሊስን የባለጌና ጨካኝ የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ነጋዴዎች መፈንጫ ከማስደረግ የከፋ የሃይሃይማኖት መሪነት (አባትነት) ኪሳራ ይኖራል እንዴ? ሃይማኖታዊ ሃላፊነትና ተልእኮ ባፍ ጢሙ ሲደፋ ማየትና መስማት እውነተኛ ሃይማኖተኛ ነኝ ለሚል ወገን የሚያስከትለውን የህሊና ህመም የምንረዳው ስንቶቻችን ነን?
9) የሃይማኖት “መሪዎችና ሊቃውንት” በየራሳቸው ጊዜና ተጨባጭ ሁኔታ በታሪክ ሂደት ከተፈፀሙት ስህተቶች በአግባቡና ከምር ትምህርት በመውሰድ የዛሬውንና የነገውን ትውልድ የሚጠቅሙ ሥራዎችን ሠርቶ መገኘት ሲገባቸው የክስተቶችን ትኩሳት እየተከተሉ በግልብ ስሜት የመነዳት ሰለባዎች የመሆናቸው ግዙፍና መሪር እውነታ ህሊናውን የማይኮሰኩሰው እውነተኛ አማኝና አገር ወዳድ የሚል የአገሬ ሰው ይኖር ይሆን? “ክርስቶስ ነን የሚሉ ሃሳዊያን ይነሳሉና ተጠንቀቁ ተብሏልና አስተውሉ” እያሉ ሲሰብኩን የኖሩ የሃይማኖት መሪዎች ውድቀት ግልፅ የሆነው ለአሽከርነት ክድርና ፍፁም በሚመቹ ብአዴን ተብየ የአገር ጉዶች ተባባሪነት የህወሃትን የበላይነት አስወግዶ ቤተ መንግሥቱን የተረከበውንና የፖለቲካ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የሰብዕና ዝቅጠት የተጠናወተውን አብይ አህመድን ለመገምገም የሚያስችል ጊዜና ትእግሥት ሳይወስዱ የኢትዮጵያ “ትንሳኤ ብርሃን” አድርገው የነገሩን እለት አይደለም እንዴ?
10) ምንም እንኳን ይህንን ስህተት ለመከላከል የሚያስችል አሳማኝ ምክንያት ባይኖርም ሊያጋጥም እንደሚችል ቆጥረን እንዳናልፈው የሥልጣነ መንበሩን አራጊነቱንና ፈጣሪነቱን (ጠርናፊነቱን) የጠቀለለው ተረኛ የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቡድን (ኦህዴድ/ኦነግ/ብልፅግና) ይኸውና ለአምስት ዓመታት አገርን ምድረ ሲኦል እያደረገ ሲቀጥል እንኳንስ ስህተታቸውን አርመው ሃላፊነታቸውንና ተልእኳቸውን በአግባቡ ሊወጡ ይባስ ብለው የሃይማኖት አሿሿሙንና የሥራ ቦታ አመዳደቡን “ጥንብ ነው” እያሉ የሚሰብኩን የጎሳና የዘር አጥንት ስሌት ፖለቲካ ሥርዓት አካል የማድረጋቸው መሪር እውነት ልቡን የማያደማው እውነተኛ አማኝ ይኖር ይሆን?
12) ከዚህ የፀሎተ ምህላ አዋጅ ጋር ተያይዞ ፈፅሞ ለመግለፅ በሚያስቸግር ፖለቲካ ወለድ ወንጀል የበሰበሰውን (የከረፈውን) የፖለቲካ ሥርዓት በልፍስፍስ የአንተም ተው የአንተም ተው ሽምግልና ወደ የእርቅና የሰላም ጠረጴዛ ለማምጣት የሰላም ኮሜቲ ወይም ግብር ሃይል መሰል ቡድን የማቋቋም አስፈላጊነት ዜናን ሰምተናል።
“
በምሥራችነት በተነገረን ዜና እና ዜናውን የሚነግሩን የሃይማኖት መሪዎች በመጡበትና በሚገኙበት እጅግ ደካማ አቋምና ቁመና መካከል ያለውን ርቀት በምን ይሉኛል ደካማ አቀራረብ ሳይሆን እውነተኛና ዘላቂ መፍትሄንና አስተሳሰብን ግምት ውስጥ በሚያስገባ ሚዛናዊ ህሊና ለሚያስተውል ሰው የሃይማኖታዊ እምነት ነፃነት ከብልሹ ሥርዓት መወገድ ወይም አለመወገድ ጋር በጥብቅ የተያያዘ መሆኑን ለመገንዘብ ይሳነው ይሆን ?
13) ቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረትና ርብርብ የሚጠይቀውን የመከረኛ ወገን ህይወት ከመታደግ ይልቅ ባህርና ውቅያኖስ ማዶ ለሚሠራ ቤተክርስቲያንና ገዳም በብዙ ሚሊዮኖች የሚገመት ዶላር ብትሰጡ “ገነት ትገባላችሁ” በሚል ዘመቻ ላይ መጠመድ እውን የእውነተኛ ሃይማኖታዊ ምንነታችንንና እንዴትነታችንን ይመጥናል እንዴ? ለመሆኑ በየዋህነትም ሆነ በአንዳንድ የግልና የቡድን ጥቅም አሳዳጆች የሚካሄደውን ይህንን ዘመቻ “ልጆቻችንና ባልደረቦቻችን ሆይ፦ እስካሁን ከቆየንበት (ከኖርንበት) አይብስምና እባካችሁ መፅናኛ ላጣው ወገናችን የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረት ሰጥተን እንረባረብ ፤ ሌላው ቀጥሎ ይደርሳል/ይሆናል ” የሚል የሃይማኖት መሪና ሊቀ ሊቃውንት እንዴት ይታጣል?
14) አዎ! በእውነት ከተነጋገርን የክርስቶስ ማደሪያዎች ወይም ቤተ መቅደሶች የሆኑ በአያሌ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ንፁሃን ወገኖች ህይወት እየተደረመሰ (እየወደመ) ባለበት መሪር ሁኔታ ውስጥ የሚገነባው ቤተ ክርስቲያን ወይም ገዳም ለየትኛው እግዚአብሔር ነው ማረፊያና ማደሪያ የሚሆነው? ፈጣሪን ጨምሮ ለመከረኛ ፍጡሮቹ ቅድሚያ ከመስጠት ይልቅ በየባህርና በየውቅያኖስ ማዶ ድንቅ ህንፃዎችን (ቤተ ክርስቲያናትንና ገዳማትን) በማሠራት የሚደሰት ጨካኝ ለምን እናስመስለዋለን?
ከችግራችን ዘመን ጠገብነትና ውስብስብነት የተነሳ ልቀጥል ብል ጥያቄን ጥያቄ እየወለደው እቸገራለሁና ለማሳያነት ይሆናሉ ያልኳቸውን ካነሳሁ ይበቃኛል።
አያሌ የዋህ አማኝ ወገኖች እና የህዝብ መከራና ሰቆቃ እንደሌለ በሚያስመሰል አኳኋን በባህርና በውቅያኖስ ማዶ የእግዚአብሔርን ቤት ለመሥራት በሚል ዘመቻ የተጠመዱ ወገኖች ከላይ እንደ ዋነኛ ማሳያ ያነሰኋቸውን ግልፅና ቀጥተኛ ጥያቄዎች እንደ እግዚአብሔር አልባነት ወይም እንደ መርገምት በመቁጠር የውግዘትና የእርግማን ናዳ ቢሰነዝሩ ያሳዝነኝ እንደሆን እንጅ ከቶ አይገርመኝም። ለምን ቢባል ያፈጠጠውንና ያገጠጠውን የገዛ ራሳችንን የውድቀት አዙሪት በዓለማዊና በመንፈሳዊ የአርበኝነት አቋምና እና ቁመና በመጋፈጥ ለምድራዊውም ሆነ ለሰማያዊው ህይወት የሚበጀንን ሥርዓተ ማህበረሰብ አምጠን ከመውለድ ይልቅ የጥንካሬና የስኬታማነት እሴቶችን አጣምሮ የያዘውን ሃይማኖታዊ እምነት የድክመቶቻችን መሸፈኛ (መሸሸጊያ) የማድረግን እጅግ አስቀያሚ ድክመት በፍፁምነት ማስወገድ ባንችልም ከቁጥጥራችን እየወጣ ተገዥው እንዳያደርገን ለማድረግ ገና ብዙ እንደሚቀረን እረዳለሁና ።
የሃይማኖታዊ እምነቶቻችን ምንነት፣ ለምንነትና ለማንነት ፣ እንዴትነት እና ወዴትነት ሊያሳስበን የሚገባውም ከዚሁ መሠረታዊ እሳቤ አንፃር ነው የሚል ፅዕኑ እምነት አለኝ።
ከፈጣሪ እገዛ ጋር ከዘመን ጠገቡና ከአስከፊው ውድቀታችን ተምረን ለሁላችንምና ለሁሉም አይነት ነፃነትና እኩልነት የምትመች ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያንና አኩሪ የሆነ እኛነነትን እውን እንደምናደርግ እየተመኝሁ አበቃሁ!