በአዲስ አበባ ከተማ  የማንነት ጥያቄ ላይ የኢትዮጵያ ክፍላተሃገር ህብረት ያለው አቋም

ነሓሴ 9 ቀን 2011 ዓም(15-08-2019)

አዲስ አበባ ኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያም አዲስ አበባ ነች!

ማንኛውም በመንግሥታዊ ስርዓት የሚመራ አገር ሥርዓተ መንግሥቱን በአንድ አካባቢ በቆረቆረው ከተማ  መዘርጋቱ እንግዳ አይደለም።መንግሥት ወይም  ስርዓት ያለመንበር ወይም ማእከል ወይም ያለከተማ ሊመሰረት አይችልም።የሁሉም አገር ስርዓትና የከተማ አመሰራረት ታሪክ ጊዜና ቦታው ቢለያይም ተመሳሳይ ነው።

ኢትዮጵያ መንግሥታዊ ስርዓት መስርታ እንደ አገር ከተዋቀረችበትና በተጓዘችበት ታሪኳ ሁኔታው ባስገደደውና በፈቀደው ምክንያት በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ ቦታዎች  የአስተዳደር  ወይም የመንግሥት ተቋማት መቀመጫ ማእከላትን መስርታ ፖለቲካዊ፣ታሪካዊ፣ባህላዊና ኤኮኖሚያዊ ግባቶችን አከናውናለች።ከነዚህም ቀደም ብለው በገናናነታቸው ከሚታወቁት የጥንት  ከተማዎች መካከል አሻራቸው ያልጠፋው፣የአሁኑ ትውልድ የሚኮራባቸውና የዓለም ሕዝብም በታሪክ ቅርስነታቸው ዕውቅና ሰጥቶ የቱሪዝም(የጉብኝት ስበት) ያገኙት የአክሱም፣ የጎንደር እንዲሁም የላሊበላ…ወዘተ ከተማዎች ምሳሌዎች ናቸው።እነዚህ ከተማዎች የከባቢ ነጠላ ጎሳ ብቻ የሚኮራባቸውና የግሌ ናቸው ብሎ ለመቆጣጠር የሚፈልጋቸው ሳይሆኑ የሁሉም ኢትዮጵያውያን የጋራ ይዞታዎች ነበሩ፣ናቸውም።

የከተማዎች ምስረታና ከቦታ ቦታ መቀያዬር በእድገትና በታሪክ አጋጣሚ የሚከሰት፣በተለይም በባላባታዊ ስርዓት የኖረ አገር በሚደረገው የሥልጣን ዝውውር አዲስ መጡ በተነሳበትና ሥልጣኑን በዘረጋበት አመቺ በሆነ ቦታ የመንግሥቱን መዋቅር መዘርጋቱ የተለመደ በመሆኑ ከዘመነ መሳፍንት በዃላ ኢትዮጵያን በአንድ ስርዎ መንግሥት ስር ለማስተዳደር ዕድልና ችሎታ የነበራቸው አጼ ሚኒሊክ አዲስ አበባን እንደገና ወደ ታሪካዊ ቦታዋ መልሰው፣የአገሪቱ ዋና ከተማ አድርገው ቆረቆሩ።

አዲስ አበባ ስትቆረቆርም ሆነ ከተቆረቆረች በዃላ የአንድ ነጠላ ጎሳ ንብረትና ይዞታ ሳትሆን የሁሉም ክፍላተሃገር ተወላጅ በህብረት የገነባት፣የኖረባት ከተማ ነች።አሁን ለደረሰችበት ለከተማዋ እድገት ደረጃ ሁሉም ዜጋ፣ሁሉም ክፍላተ ሃገር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እውቀቱን፣ጉልበቱን ሃብቱን፣እንዲያም ሲል ህይወቱን ገብሮላታል።ከየክፍላተ ሃገሩ ሕዝብ በግብር መልክ የሚሰበሰበው ገንዘብ ከፍተኛው ድርሻ ለዚሁ ተግባር ውሏል።ስለሆነም ሁሉም ክፍላተ ሃገር በአዲስ አበባ ላይ የባለቤትነት ድርሻ አላቸው።ጥያቄው የተወሰነ ስብስብ የሚያነሳው ብቻ ሳይሆን ሕዝባዊና አገራዊ ጥያቄ ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የኢህአዴግ መንግስት በሚቃወሙትና በሚተቹት ላይ እየወሰደ ያለውን አፈና እና እስር የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲታገለው ጥሪ እናቀርባለን!!!

አዲስ አበባ የሸዋ ክፍለሃገር ዋና ከተማ፣የኢትዮጵያ ክፍላተሃገር መናገሻ ከመሆኗም በላይ የአፍሪካ ህብረት መሰረቱን የጣለባት ያፍሪካውያን መዲና ናት። የብዙ ጎሳ ፣ቋንቋ፣እምነት፣ታሪክ፣ባህል የሚንጸባረቅባት ኢትዮጵያዊ ከዳር እስከዳር ወጥቶ የሚገባባት፣የሚኖርባት ፣የአገሪቱ ያስተዳደር መዋቅሮች የተተከሉባት፣የውጭ አገር ዜጎች ሳይቀሩ በነጻነት የሚስተናገዱባት የሁሉም ዓለም አቀፍ ከተማ ናት።አዲስ አበባ እንደስሟ ህብረቀለማዊ ውበቷ የተለያዩ ጎሳ ተወላጆች የሆኑ ኢትዮጵያውያን በሰላምና በአንድነት የሁላችንም ከተማ ብለው ስለሚኖሩባት ነው።

አዲስ አበባን ከኢትዮጵያ ኢትዮጵያንም ከአዲስ አበባ ነጥሎ ማዬት አይቻልም።የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጾች ናቸው። አንዱ ከሌላው ተነጥሎ ብቻውን አይኖርም።

የአንድን አገር ዋና ከተማ እንደግል መሬት መቁጠርና የእኔ ብቻ ነች ብሎ ሌላውን አሶግዶ ጠቅልሎ ለመያዝ መስገብገብ ከጅልነትም በላይ ጅብነት ነው። ስለከተማ ምንነትና ስብጥርነት ያለማወቅ ድንቁርና  ነው።ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተካሮ የመጣው  በኦነግ ግንባር ቀደምትነት የሚመራው የኦሮሞ ጎሳ አክራሪዎች ሁሉም የኛ በሚል  የይገባኛል ጥያቄና የሚፈጽሙት የማፈናቀል እርምጃ ከዚህ የተለዬ አይደለም። አገራት ድንበር ዘለል በሆነ ዓለም አቀፋዊ ፖለቲካ ላይ ሲረባረቡ እኛ ኢትዮጵያውያን መንደር ተኮር በሆነ የጎሳ ጭቅጭቅና ዃላ ቀር ፖለቲካ ላይ ተዘፍቀን ጊዜና ጉልበታችንን ስናባክን ለሚያዬን መሳቂያና መሳለቂያ ከዚያም በላይ በመዋእለ አራዊት(ዙ )ውስጥ ያለን አውሬዎች ሳንመስለው አንቀርም።በ21ኛው ክፍለ ዘመን ዓለም እየተቀራረበ ሲሄድ የእኛው ወገኖች ለመራራቅ ፣በጎሳ ተዋረድ በመሬት ቅርምት ግብግብ መግጠማቸው ያሳፍራል።በታሪክም አስነዋሪ ምዕራፍ ይይዛል።አዲስ አበባ የመካከለኛው ወይም የፌዴራሉ መንግሥት መቀመጫ እንጂ አንድ ጎሳ የሚያዝባት ክልል መሆን አይኖርባትም።ክልል በራሱ ሌላውን የሚያገልና  ከባለቤትነት የሚነጥል  እኩይ ዓላማ የወለደው ለአገራዊ አንድነት አደጋ የተሸከመ መሰሪ አደረጃጀት ነው።በአጠቃላይ  በተለይም ጎሳንና ቋንቋን መሠረት ያደረገ ክልል መወገዝና መወገድ ያለበት እንጂ ለሰላምና ለዕድገት የሚጠቅምና  ሊወዳደሩበት የሚገባ ገንቢ የእውቀት ምልክት  አይደለም።በአገራችንም ላይ የሚታዬውን ቀውስ ያመጣው የጎሳን ፖለቲካ ተከትሎ የሰፈነው የክልል አገራዊ አወቃቀር ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የኢትዮጵያ ከቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በጋምቤላ እና በምእራብ ወለጋ ለተከሰተው የንጹሐን ወገኖች ግድያ አስመልክቶ ያስተላለፈችው መልዕክት

የኢትዮጵያ ክፍላተ ሃገር ህብረት አዲስ አበባን እንደግል ወይም እንደ አንድ ጎሳ ንብረትና መኖሪያ አድርጎ ሌላውን ባይተዋር በማድረግ የሚከናወነውን የማፈናቀል እርምጃ ፣የከተማዋን ሕዝብ ስብጥርነት(ዴሞግራፊ)ለመለወጥ ሚዛኑ ወደ አንድ ጎሳ እንዲያጋድል የማድረጉን ሂደት፣ለዚያም ሲባል የከተማዋን አስተዳደር በአንድ ጎሳ (በኦሮሞው)ተወላጆች መዳፍ ስር እንዲወድቅ የማድረጉን ሴራ በቅጡ ያወግዛል።ይህ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን የማፈረስ ደባ እንደሆነ ይገነዘባል።ኦነግና ተባባሪዎቹ አገር የመመስረት እኩይ አላማና ነባሩን የማፈናቀል የቆዬ እቅድ ሥልጣን ላይ በወጡት አባሎቹ በስልት የማከናወኑ ሂደት በቀላሉ የሚታይ አይደለም።ነዋሪውን ኦሮሞ ያልሆነ ኢትዮጵያዊ ችሎ የማያሰራውን ሕንጻ እንዲያሰራ በማስገደድ ቦታውን በመንጠቅ፣በንግድ ላይ የተሰማራውን በማይችለው የግብርና የቤት ኪራይ ዕዳ ውስጥ አስገብቶ በማባረር አዲስ አበባን ፊንፊኔ ብሎ ለመሰዬምና ለመቆጣጠር የተቀመረውን ስልታዊ ዘመቻ የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድነት እንዲከላከለው ጥሪውን ያቀርባል።

የኢትዮጵያ ክፍላተሃገር ህብረት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአዲስ አበባ ነዋሪ መርጦና ፈቅዶ በሰየመው አካል መሆን እንዳለበት ያምናል።ስለሆነም አሁን በከተማዋ አስተዳደር ወንበር ላይ የተቀመጡትና ሕዝብ ያልመረጣቸው ባለሥልጣኖች ሳይውል ሳያድር ቦታውን የአዲስ አበባ  ሕዝብ ለሚመርጠው አካል እንዲያስረክቡ እስከዚያው ድረስ ከከተማው ሕዝብ የተውጣጣ ጊዜያዊ የከተማ አስተዳደር እንዲመሰረት ይጠይቃል።ይህ ካልሆነ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ሕዝብ አሁን ስልጣን ላይ ላለው ለማይወክለው አስተዳደር ትዕዛዝ ተገዢ እንዳይሆን፣በኢትዮጵያ አንድነት የሚያምነው የፖለቲካና የሲቪክ ድርጅት፣እጅ ለእጅ ተያይዞ ለዚህ አገራዊ ጥያቄ ቅድሚያ ሰጥቶ እንዲታገል  ጥሪ ያደርጋል።

አዲስ አበባን ከጎሰኞች ሴራ ማዳን ኢትዮጵያን ማዳን ነው፣፤ለዚያ ግብ ከሚታገሉት አገር ወዳዶች፣የፖለቲካ ድርጅቶችና ሕዝባዊ(የሲቪክ)ድርጅቶች ጋር የኢትዮጵያ ክፍላተሃገር ህብረት አብሮ እንደሚቆም ያረጋግጣል።

አንድነት ሃይል ነው!!

ተጨማሪ ያንብቡ:  የዘር ፍጅትን የማስቆም አስቸኳይ ጥሪ! በአዲስ አበባ የታፈኑ የአማራ ተወላጆችን በሚመለከት የተሰጠ መግለጫ !

የኢትዮጵያ ክፍላተሃገር ህብረት።

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share