መስቀልን:- ከሺሕ ዘመን ታሪካችን እና ከኢትዮጵያ ቤ/ክ አንጻር በጨረፍታ. . . በዲ/ን ተረፈ ወርቁ

September 29, 2023
fd00eda212304a43b7bae4df4804f43e 640 426

 

የመስቀል የክርስትና ሃይማኖት ትልቅ ትእምርት/ሲምቦል ነው። መስቀል ከክርስትና ሃይማኖት ጋር ሺሕ ዘመናትን የዘለቀ፣ የጠበቀ ትስስር አለው። ወደ እኛው ታሪክ ስንመለስ ደግሞ ቅዱስ መስቀል በኢትዮጵያ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ትልቅ ክብር፤ ልዩ ስፍራ አለው።

 

ወደኋላ ተጉዘን ታሪክ መዛግብትን ስንፈትሽ፤ ክርስትና ሃይማኖት የሀገራችን ብሔራዊ ሃይማኖት በሆነበት በ4ኛው መቶ ክ/ዘመን የአክሱም/የኢትዮጵያ ነገሥታት የነበሩት ወንድማማቾቹ ኢዛና እና ሳይዛና በስመ ክርስትናቸው አብርሃ ወአጽብሃ በ፬ኛው መቶ ክ/ዘ የክርስትና ሃይማኖትን በይፋ ከተቀበሉና የመንግሥታቸው ሃይማኖት ባደረጉ ማግሥት በወርቅ ሳንቲሞቻቸው ላይ ቀድሞ ይጠቁሙበት የነበረውን የጨረቃ እና ሌሎች የግሪክ አማልክት ምስሎችን ወደ መስቀል ቀየራቸውን ያወሳሉ።

 

(በነገራችን ላይ የግሪክ ሥልጣኔ በዘመኑ እጅግ ገናና ከመሆኑ የተነሳ ሃይማኖታቸው/አማልክቶቻቸው፣ ቋንቋቸውና ባህላቸው መላውን ከዓለም ተቆጣጥሮት ነበር። ልክ እንደዛሬው እንግሊዝኛ የግሪክ ቋንቋም Linguafranka/ዓለም አቀፍ ቋንቋ ነበር። ኢትዮጵያውያን የግሪክ ቋንቋን ለዓለም አቀፍ ግንኙነት በሀገር ውስጥ ደግሞ ግእዝን እና የሳባውያንን ቋንቋዎችን ይጠቀሙ እንደነበርም ጥንታውያን የታሪክ መዛግብት በስፋት ይጠቁማሉ።)

 

በዘመኑ እጅግ ገናና የነበሩት ኢትዮጵያውያን/አክሱማውያን (በነገራችን ላይ በዘመኑ በዓለማችን ላይ ከነበሩ አራት የዓለማችን ታላላቅ ሥልጣኔዎች መካከል ከግሪክ፣ ከፐርሺያ/የአሁኗ ኢራንና ቻይና አገራት ጋር አክሱም/ኢትዮጵያ አንዷ የዓለማችን ታላቅ ሥልጣኔ እንደነበረች ልብ ይሏል፤) አክሱማውያን የአሁኗን የመንን ጭምር ሲገዙ የነበሩ ግዙፍ የባሕር ኃይል ባለቤቶች፣ ዓለም አቀፍ ንግድን ያሳልጡ የነበሩና በወርቅ ሳንቲም ይገበያዩ የነበሩ ታላቅና ሀብታም ሕዝቦች ነበሩ/ነበርን ልበል ይሆን… ከታሪካችን አንድ ሰበዝ እንምዘዝ እስቲ፤

 

ከክርስቶስ ልደት በፊት የነበረችው ኢትዮጵያዊቷ/አክሱማዊቷ ንግሥተ ሳባ/አዜብ እስራኤላዊውን ንጉሥ ሰለሞንን ለመጎብኘት ወደ ኢየሩሳሌም በሄደችበት ጊዜ ብዙ አጀብ አስከትላና በርካታ ውድ ገጸ-በረከት/ስጦታን ይዛ ነበር። ከእነዚህ ገጸ-በረከቶች መካከልም፤ ወርቅ፣ ዕንቁ፣ የከበሩ ድንጋዮች፣ ሽቱ፣ ልዩ ልዩ መዓዛ ያላቸው ለሽታና ለግንባታ የሚሆኑ ውብና ጠንካራ እንጨቶች… ይገኙበታል። (መጽሐፈ-ነገሥት ፲፤፲)።

 

መጽሐፍ ቅዱስ፤ ኢትዮጵያዊቷ ንግሥት ሳባ ለንጉሥ ሰለሞን ይዛ ስለሄደችው ስጦታ መጠንና ዓይነት ሲናገር፤ ከዛም በፊት ሆነ ከእርሷ በኋላ ለንጉሥ ሰለሞን እንዲህ ዓይነት ስጦታ ተመጥቶለት እንደማያውቅ በአድናቆት ተጽፎአል። እንግሊዛዊው የታሪክና፣ የፖለቲካ ምሁር/ጸሐፊ ዊሊያም ባጅ ደግሞ ከዛሬ 50 ዓመት በፊት፤ “Queen Sheba and Her Only Son Menilik” በሚል ርእስ በጻፈው የዳጎሰ መጽሐፉ፤

 

“… ንግሥተ ሳባ ለንጉሥ ሰለሞን ይዛ የሄደችውን የስጦታ መጠን በዘመኑ የዋጋ ስሌት መጠን 25 ሚሊዮን ፓውንድ እንደሚገመት፤” ጽፏል። ይሄ ስሌት ከዛሬ 50 ዓመት በፊት መሆኑን ልብ ይሏል። በዛሬው የዋጋ ጣሪያና የፓውንድ ምንዛሬ ስናሰላው የአገራችንን የዓመት በጀት በእጥፍ የሚያስከነዳ ይሆናል። እንግዲህ በዘመኑ ኢትዮጵያውያን/አክሱማውያን ምን ያህል ሀብታምና ታላቅ እንደነበሩና ዛሬ ግን የት እንዳለን ቆም ብለን ማሰብ ነው።

 

በሌላ በኩልም፤ እንደዛሬው ጠበን ጠበን በጎሳና በጎጥ ተከፋፍለን…የእናንተና የእኛ መሬት እያልን በመገዳደል የዓለም መሳለቂያ ከመሆናችን በፊት የቀደሙት ኢትዮጵያውያን/አክሱማውያን ሰውን በሰውነቱ ብቻ የሚያከብሩ ታላቅ ሕዝቦች ነበሩ። አሁንም ዳግመኛ ዓለም ካወቀው፤ ጸሐይ ከሞቀው ታሪካችን እንምዘዛ፤

 

በዘን ዘመን የነበሩትኢትዮጵያውያን/አክሱማውያን፤ የነቢዩ መሐመድን ተከታዮች/ሱሃባዎችን በምድራቸው በሰላም ተቀብለው ሲያስተናግዱ፤ ከግሪክና ከሮም ተሰደው የመጡ ተሰዓቱ/፱ኙን መነኮሳት/ቅዱሳንን በግዛታቸው በፍቅር ተቀብለው ሲያስጠልሉ፤ ግብፃውያኑን አባት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስን የሃይማኖታቸው ሐዋርያ ሲያደርጓቸው፤ የኦሮሞ ሕዝብም እኚህን ቅዱስ አባት አቡዬ/አባታችን በማለት በፍቅር ቃል ሲጠሯቸውና ሲያከብሯቸው መለኪያቸው ዘር/ጎሳ/ብሔር ሳይሆን ፍቅር፤ ሰውነት/ሰው መሆን ብቻ ነበር።

 

እንግዲህ መስቀሉ የፍቅር፣ የአንድነት፣ የሰላም ምልክትም አይደል… ታዲያ ጥንታውያኑ ኢትዮጵያውያን ቅዱስ መስቀሉን በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባር ጭምር የዘከረ እንዲህ ዓይነቱን አኩሪ ታሪክ ትተውልን አልፈዋል።

 

ወደቀደመው የመስቀል ጥንተ ታሪክ ጉዳይ ስንመለስም፤ አክሱማውያን ክርስትናንን ከተቀበሉ በኋላ ከግሪክ አማልክት ወደ ክርስትና ፊታቸውን በመመለስ መስቀልን ምልክታቸው ኢየሱስ ክርስቶስን ደግሞ አምላካቸው አደረጉ። ነገሥታቱ በዘመቱበት የጦር ግንባር ድል ባደረጉበት ጊዜ ሁሉ፤ “በመስቀል ምልክት፤ በአምላካቸውና በጌታቸው በኢየሱስ ክርስቶስ ኃይል ድል ማድረጋቸውን!!” የሚዘክር የድንጋይ ላይ ጽሑፍን አስቀርተውልናል። ከእነዚህም መካከል፤

 

ታዋቂዎቹን “የኢዛና ኢንስክሪፕሽን እና የአዶሊስ ኢንስክሪፕሽንን” የድል ዜናን የሚዘክሩት በግሪክ፣ በግዕዝና በሳባውያን ቋንቋዎች የተጻፉት የአክሱም ነገሥታት የድንጋይ ላይ ሐውልቶች ሺሕ ዘመናት የተሻገረውን ታሪካችንን ለዓለም እየተናገሩ ሕያው ምስክር ሆነው በታሪካዊቷና በጥንታዊቷ የአክሱም ከተማ ዛሬም ድረስ ቆመው ይታያሉ።

 

በዚህ ታሪካችን ላይ ተጨማሪ ለማወቅ/ለማንበብ ለምትሹ ማስረጃ ላጣቅስ፤

 

ከ120 ዓመታት በፊት የጀርመንን የታሪክና የአርኪዮሎጂ የጥናት ቡድንን በመምራት በዳግማዊ ዐጤ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ወደ ኢትዮጵያ የመጡትና የአክሱምን ታሪክ ለዓለም ያስተዋወቁት፤ የDeutsche Aksum Expidition የታሪክና የአርኪዮሎጂ ጥናት ቡድን ከሆኑት ውስጥ፤ the Leading Orientalist Eno Litmman, Architect Daniel Krencker, Photographer and Draughtsman Thedor von Lupke and Physician Erich Kaschke በአክሱም ከተማ ባደረጉት የአርኪዮሎጂ ጥናት በቁፋሮ የመስቀል ምልክት የተቀረጸባቸውን የወርቅ ሳንቲሞችን አግኝተዋል። እነዚህ የታሪካችን ሕያው ምስክሮች የሆኑ ሳንቲሞች በታላቅ ክብር- ልዩ ቅርስ ሆነው በብሔራዊ ሙዚየም እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ኢትኖግራፊክ ቤተመዘክር/ሙዚየም ይገኛሉ።

ከአክሱማውያን በኋላ የመጡ ኢትዮጵያውያን ነገሥታት መስቀልን ይጠቀሙ እንደነበርም በርካታ የታሪክ ማስረጃዎች አሉን። የቀደምት ነገሥታት ማኅተም በመስቀል ቅርጽ ሆኖ በአራቱ ማዕዘን ‹‹ኢየሱስ›› የሚል ስም ይጻፍበት ነበረ፡፡ ከዘመነ መሣፍንት ታላላቅ መሪዎች መካከል ሣህለሥላሴ መስቀልን ምልክት ያደርጉ ነበር፤ በመዓዝናቱ ኢየሱስ፣ አንዳንዴም ኢየሱስ ክርስቶስ እያሉ ጽፈውበታል፡፡ ከአክሱም ዘመነ መንግሥት የአንደኛው ንጉሣችን ስም ገብረ መስቀል ነበረ፡፡ የላሊበላ ሚስት ስም መስቀል ክብራ ነው፡፡ የዐፄ ይስሐቅ ስመ መንግሥትም ገብረ መስቀል ነው፡፡

 

ከላይ በመግቢያዬ እንደጠቀስኩት፤ መስቀል በኢትዮጵያ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ትልቅ ክብር፤ ልዩ ስፍራ አለው። ማንኛውም ሕንጻ ቤ/ክ ያለ ሞገሰ መስቀል አይሠራም። ስግደትና አስተብርኮም ይቀርብለታል። መስቀልን መሳለምና በመስቀል ማማትብ፤ መባረክም የቆየ የቤተክርስቲያን ሃይማኖታዊ ሥርዓት ነው።

 

መስቀልን በአንገት ማሰር፣ በግንባርና በክንድ ላይ መነቀስ፣ በአልባሳት፣ በአክሊል፣ በዘውድ፣ በገንዘብና በበትረ መንግሥት ላይ የሚደረገው የመስቀል ሃይማኖታዊ ምልክት እንጂ ጌጥ አይደለም።

 

እንደ ቤተክርስቲያን ሥርዓት ለቅዱስ መስቀል አብያተ ክርስቲያናት ታንጸዋል። ከመስከረም ፲፭ እስከ ፳፭ ያለው ጊዜም ዘመነ-መስቀል ይባላል። በዚህ ወቅት ነገረ መስቀል ይነገራል፤ መዝሙረ መስቀል ይዘመራል። በአጠቃላይ መስቀል በኢትዮጵያ ቤ/ክ የጸሎት ጥንትና ተፍጻሜት ነው።

 

በመጨረሻም፤ ንጉሠ ሣሕለሥላሴ ከ200 ዓመት በፊት በኢየሩሳሌም ስላለው የኢትዮጵያ ቤ/ክ ገዳም – ስለዴር ሱልጣን ጉዳይ ለእንግሊዛዊው ቆንሲል ሳሙኤል ጎባት የጻፉትን ደብዳቤ ስንመለከት የራስጌ ማሕተማቸው የመስቀል ምልክት እንደነበር ይታያል። ይህን ጥንታዊ ደብዳቤ ከዚህ ጽሑፍ ጋር አባሪ አድርጌያለሁ።

 

ታላቁ ቅዱስ መጽሐፍ፤

 

“እግዚአብሔርም በእርሱ፥ በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ጥልንም/ጥላቻንም በመስቀሉ ገድሎ፤ በመስቀሉ ደም ሰላም አድርጎ በምድር ወይም በሰማያት ያሉትን ሁሉ ለራሱ እንዲያስታርቅ ፈቅዶአልና፤” እንዲል የአባቶቻችን አምላክ በኢትዮጵያ ምድር ጥልና ጥላቻ/ጠላትነት ተወግዶ የሰላምን ዘመን ምናይበትን ጊዜ ያቅርብልን!! አሜን!!

 

መልካም የመስቀል በዓል!!

Leave a Reply

Your email address will not be published.

F7IDyi3X0AEtIWP
Previous Story

የአገዛዙ ሰራዊት ጭካኔ ቃላት የሚገልጹት አይደለም። እውን የኢትዮጵያ ማህጸን ያፈራችው ሰራዊት ነው? – መሳይ መኮንን

ethiopia keflethager Association 1
Next Story

በአዲስ አበባ ከተማ  የማንነት ጥያቄ ላይ የኢትዮጵያ ክፍላተሃገር ህብረት ያለው አቋም

Go toTop