AUGUST 27, 2023
ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን መግለጫ
ለኢትዮጵያ ሰላም፤ ዲሞክራሲ፤ አንድነትና ልማት ስለሚያስፈልጉ መሠረታዊ መፍትሔዎች
በሚመለከታቸው ድርጅቶች የቀረበ መግለጫ
መግቢያ፤ በኢትዮጵያ ተከስተው የሚገኙ እጅግ ከባድ ችግሮች፤
እንደሚታወቀው፤ በአሁኑ ጊዜ፤ በኢትዮጵያ እጅግ ብዙ የማሕበራዊ፣ የኢኮኖሚና የፓለቲካ ችግሮች የተከሰቱ ቢሆኑም፤ ዋነኞቹ በዘረኛነት የመከፋፈል ሥርዓቱ ያስከተለው መ ቆር፤ ከባድ ግጭት፤ እልቂት፤ መፈናቀል፤ መሰደድ፤ የንብረት ውድመት፤ የሕግ የበላይነት አለመኖር፤ እጅግ ከባድ ሙስና፤ የሴቶች መደፈር፤ የሰብዓዊ መብት አለመከበር፤ የመገንጠል ጠንቅ፤ ወዘተ፤ እንዲሁም የኢትዮጵያ ሕዝብ በአሰቃቂ ደረጃ በድህነት ጠንቅ ፍዳውን እያየ መሆኑ ነው፡፡
ከተጠቀሱት ችግሮች ለመገላገል በየጊዜው ከውስጥም፤ ከውጪም የሚያጋጥሙትን ጥቃቶችና ወንጀሎች ከመቋቋም (ከመተጋገል) በተጨማሪ፤ ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ራዕይ፤ እቅድና ዓላማዎች ያስፈልጋሉ፤
(ሀ) ለኢትዮጵያ ተገቢ የሆነ ሕገ መንግሥት በማዘጋጀትና ተግባራዊ በማድረግ፤ ውድ ሐገራችን ከጽንፈኛነት፤ ከዘረኛነትና ከጭቆና የተላቀቀ ኢትዮጵያዊነት፤ ሰላም፤ ጸጥታ፤ አንድነት፤ እውነተኛ ዲሞክራሲ፤ ሕብረት፤ መከባበር፤ የሕግ የበላይነት፤ ወዘተ. የሰፈነባት ሐገር እንድትሆን ማረጋገጥ፤
(ለ) የኢትዮጵያን ሕዝብ ከአሰቃቂ የድህነት አረንቋ ለማዳን፤ የተሟላና ሥልታዊ የሆነ የልማት እቅድ (የአጭር፤ የመካከለኛና የረጅም ዘመን) ማዘጋጀትና መተግበር፡፡
1ኛ/ አዲስ ሕገ መንግሥት ለኢትዮጵያ የሚያስፈልግ መሠረታዊ ጉዳይ ስለ መሆኑ፤ 1/1 የአሁኑ ሕገ መንግሥት ሰቆቃዎች፤
(ሀ) እንደሚታወቀው፤ በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ላይ ሰፍኖ የሚገኘው ሕገ መንግሥት ሕዝቡን በቋንቋና በጠባብ ዘረኛነት በተመሠረተ የክልል ሥርዓት ከፋፍሎ ባስከተለው የእርስ በርስ መናቆር፤ አለመተማመን፤ መከፋፈል፤ አለመተባበር እጅግ አሰቃቂ መጠነ ሰፊ ስቃይና እልቂት እያስከተለ ነው። በዘረኛነት በተከሰቱ ግጭቶች ምክንያት በብዙ መቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ተገድለዋል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ተፈናቅለዋል። እጅግ ብዙ ሰዎች በተለይ ሴቶችና ሕጻናት እየተሰቃዩ ነው። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ከሐገር ለመሰደድና በታሪክ ያስተናግዷቸው በነበሩ በዓረብ ሐገሮች ጭምር በዝቅተኛ ደረጃ ለመኖርና ለመደፈር ተገድደዋል። በጠባብ ጎሰኛነት መለያየት ምክንያት እጅግ ብዙ ንብረት ወድሟል። የዘረኛነቱ ጠንቅ፤ ፋሺሽት ኢጣልያ ኢትዮጵያን በወረረችበት ዘመን ከፈጸመችው አሰቃቂ የጦር ወንጀል ብሷል።
(ለ) ኤርትራ ከእናት ሐገሯ ከኢትዮጵያ ተገንጥላለች። በአሁኑ እኩይ የሕገ መንግሥት አወቃቀርና ሥርዓት፤ “ክልል” የተሰኙ አንዳንድ አካባቢዎችም ለመገንጠል እያኮበኮቡ ነው። ደቡብ ክልል ውስጥ ከሚገኙ አካባቢዎች ውስጥም ወደ ክልልነትና የመገንጠል አባዜ ለመዝቀጥ አቅጣጫ እያንጸባረቁ ነው።
(ሐ) ያሁኑን ሕገ መንግሥት ኢትዮጵያ ላይ የጫኑት ተጠያቂዎች አንደኛው ዓላማቸው፤ ሕዝቡ በዘረኛነት እርስ በርስ እንዲናቆርና እንዲጨፋጨፍ ስለ ነበር ያለሙት ሁሉ እየተሳካላቸው ነው።
(መ) ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ ልዩ የሚያደርጋት፤ ሕዝቧ በኢትዮጵያዊነት አንድነት የሚተባበርና የማይደፈር መሆኑን በነአፄ ካሌብ ዘመነ መንግሥት ከዚያም በአድዋ የጦርነት ድል ያስመሰከረች መሆኗ ነው። ያሁኑ ሕገ መንግሥት ግን ኢትዮጵያን በአሳፋሪና በውዳቂ ዘረኛነት ከፋፍሎ እያስደፈረን ነው። የባሰ ሊያጫርሰን ነው።
(ረ) በኢትዮጵያ ላይ ተከስቶ የሚገኘው ሕገ መንግሥት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እውቅና ያላገኘ ነው።
1/2 ለኢትዮጵይ የሚመጥንና የሚጠቅም ሕገ መንግሥት ስለማስፈለጉ
ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያን ሕዝብ ከተከሰተው አስከፊ ችግር ለማላቀቅ ከዚህ በታች በተዘረዘረው ሥልት አዲስ ሕገ መንግሥት መንደፍና መተግበር መሠረታዊ ጉ ዳይ ነው፡፡
1/3 አዲስ ሕገ መንግሥት ስለ ማርቀቅና ስለ ማጥናት፤
ብቁ በሆኑ ባለሞያዎች የተሟላ ረቂቅ ሕገ መንግሥት እንዲዘጋጅና በመጀመሪያ ደረጃ አንድ ዓለም አቀፍ ጉባኤ በጥልቀት እንዲመለከተው ማድረግ፤ ከዚያም፤ አስፈላጊው ማሻሻል ተከናውኖ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ለመላው ሕዝብና ለሚመለከታቸው ድርጅቶች ቀርቦ እንዲመረመር በመጨረሻም ተቀባይነት በሚኖረው ብሔራዊ ጉባኤ ሕገ መንግሥቱ እንዲጸድቅ ሆኖ በሚቀጥሉት ዓመታትም በሕገ መንግሥቱ መሠረት በሚመረጥ ምክር ቤት እንደ አስፈላጊነቱ ማሻሻል ማስቻል፤
2ኛ/ ለኢትዮጵያ ስለሚያስፈልጋት የተሟላ የልማት እቅድና ትግበራ፤
2/1 በኢትዮጵያ ላይ ተከስቶ ስለሚገኘው የድህነት ችግር፤
በዘረኛነት ሥርዓቱና የአመራር ከፍተኛ ድክመት ምክንያት ኢትዮጵያ በድህነትና በሙስና ታዋቂ ሆናለች። በተጨማሪም፤ በብዙ ዓለም አቀፋዊ መስፈርቶች ኢትዮጵያ የዓለም ጭራ ሆናለች። ተመጽዋች ሆናለች። ክነዚህ ውስጥ፤ በተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅት (UNDP) ኢትዮጵያ ከ191 ሐገሮች 175ኛ ሆና በአሳፋሪ ደረጃ ትገኛለች፡ ለዝርዝሩ ከዚህ በታች ባሉት መጠቆሚያዎች መመልከት ይቻላል፤
Http://Hdr.Undp.Org/Sites/All/Themes/Hdr_theme/Country-Notes/ETH.Pdf
Https://Ecadforum.Com/Amharic/Archives/19630/
Https://Www.Nytimes.Com/2019/01/03/Opinion/Ethiopia-Abiy-Ahmed-Reforms-Ethnic-Conflict-Ethnic-Federalism.Html
2/2 የተሟላ የልማት እቅድ ስለ ማርቀቅና ማጥናት የሚያስፈልግ ሥልት፤
(ሀ) ለኢትዮጵያ ተገቢ የሆነ የልማት እቅድ ለማርቀቅ የመጀመሪያ እርምጃ መሆን የሚገባው፤ ለተግባሩ ብቁ የሆኑ የሕግ፤ የኢኮኖሚ፤ የማሕበራዊ፤ የቴክኖሎጂ፤ ወዘተ. ባለሞያዎች በመምረጥ አንድ ግብረ ኃይል ማቋቋም ነው። ግብረ ኃይሉም በተቻለ ፍጥነት፤ ከተቻለ በ6 ወሮች ውስጥ፤ የአጭር ጊዜ (የ5 ዓመት)፤ የመካከለኛ ጊዜ (የ15 ዓመት) እና የሩቅ ዘመን (የ30 ዓመት) እቅድ የማርቀቅ ተግባሩን አከናውኖ በሚቀጥሉት 6 ወሮች ውስጥ በሚከናወን አንድ ዓለም አቀፍ ጉባኤ በጥልቀት እንዲመረመር ማድረግ ነው።
(ለ) የልማት እቅዱ የተሟላ እንዲሆን፤ ከዚህ በታች የሚገኙትንና ሌሎችም አስፈላጊ የሆኑ አርእስቶችን ሊያካትት ይገባል፤ አጠቃላይ(Macro) እና ዝርዝር (Micro) የልማት ዘርፎችን፤ አስፈላጊየሆኑ የልማት ተግባሮችን (የእርሻ፤ የውሀ አጠቃቀም፤ የኢንዱስትሪ፤ የቴክኖሎጂ፤ የኃይል፤ የአየር ንብረት፤ የመገናኛ፤ የአገልግሎት (የትምሕርት፤ የጤና፤ የአስተዳደር፤ የቱሪዝም፤ የንግድ፤ ወዘተ፤)፤ ሊሶቶ (Lesotho) ለደቡብ አፍሪካ ለምታጋራው ውሀዋ፤ በየዓመቱ ከ$40 ሚሊዮን በላይ እንደሚከፈላት፤ ኢትዮጵያም ከሱዳንና ከግብጽ ተመሳሳይ ክፍያ እንድታገኝ ማድረግ፤
ለበለጠ ዝርዝር፤ (Https://Zehabesha.Com/Prospects-Of-Collaboration-In-The-Horn-Of-Africa-And-The-Red-Sea-Region/) ወይም (Www.Semennaworq.Org) የበለጠ ዝርዝር ማስረጃ ማግኘት ይቻላል፡፡
እንደሌሎች የለሙ ሐገሮች የኢትዮጵያም የሕዝብ ሰፈራ 80% ከተሜ እንዲሆንና ገጠሬው ከ20% እንዳያልፍ በማድረግ የሚያስፈልገው መሠረታዊ የውሀ፤ የትምህርት፤ የጤና፤ የመገናኛ፤ የኃይል፤ ወዘተ አገልግሎት እንዲመቻችለት ማድረግ፡፡ በአሁኑ ጊዜ፤ 80% የኢትዮጵያ ሕዝብ ገጠሬ በመሆኑ በድህነት አረንቋ እየተሰቃየ ነው፡ በቀይባሕር አካባቢና በአፍሪካ ቀንድ የሚገኙት ሐገሮች ተባብረው እንዲጠቀሙ የሚያመቻች ሥልትና እቅድ ማዘጋጀት፤ (ለዝርዝር፡
PROSPECTS OF COLLABORATION IN THE HORN OF AFRICA AND THE RED SEA REGION መመልከት ይጠቅማል፡፡
3ኛ/ ስለ ረቂቆቹ አዲስ ሕገ መንግሥትና የልማት እቅድ ዝግጅት የኢትዮጵያን ሕዝብ ስለ ማሳተፍ፤ 3/1 የምክክር ሥልት፤ በተጨማሪም፤ ሌላ ተገቢ የሆነ ግብረ ኃይል በማቋቋም፤ በሚለጥቀው አንድ ዓመት ውስጥ፤ በኢትዮጵያ እስከ ወረዳ ድረስ በሚከናወን ምክክር፤ የሚመለከታቸውን ድርጅቶች በሙሉ በማሳተፍ ስለ ረቂቁ ሕገ መንግሥትና የልማት እቅድ የሚገኘውን ሀሳብ ማከማቸትና በሐገር ለሚከናወነው 2ኛ ጉባኤ በማቅረብ ጥልቀት ያለው ውይይት እንዲከናወንበትና እንዲወሰንበት ማድረግ ነው።
3/2 የአዲሱ ሕገ መንግሥትና የልማት እቅዱ ባለቤት፤
በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለራሱ የሚበጀውን ሕገ መንግሥትና የተሟላ የልማት እቅድ በጥልቀት መርምሮ የሚያጸድቀውና በሚያስፈልግበት ጊ ም እንደ አስፈላጊነቱ የሚሻሻልበትን ሥርዓት ይወስናል። ቸሩ የኢትዮጵያ አምላክ፤ ውድ ሐገራችንን በተገቢ ሕገ መንግሥት፤ የልማት እቅድና አመራር ከተጋረጡባት ከባድ ችግሮች ያድንልን፡፡
“ኢትዮጵያ ታበጽሕ እደዊሀ ሀበ እግዚአብሔር፡፡” ዳዊት (ም/ 68፡3
____________________________________
የጽሑፉ አቅራቢዎች፤
1ኛ/ ኢትዮጵያዊነት (Ethiopawinnet);
2ኛ/ Ethiopian American Civic Council (EACC);
3ኛ/ The American-Ethiopian Public Affairs Council (AEPAC);
4ኛ/ Ethiopian Survival Salvation Association (ESSA);
5ኛ/ Unity For Ethiopia;
6ኛ/ Ethiopian Advocacy Network;
7ኛ/ Horn Of Africa Peace And Development Center (HAPDC);